Administrator

Administrator


               “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በ1 ነጥብ 82 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ቀዳሚነቱን ይዟል

               በአለማችን የፊልም ኢንዱስትሪ ታሪክ በአገር ውስጥ ገበያ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” የተሰኘው ተወዳጅ ፊልም እጅግ ከፍተኛውን ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን መያዙ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ በ1939 ለእይታ የበቃው “ጎን ዊዝ ዘ ዊንድ” በወቅቱ በአገር ውስጥ ገበያ 200.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንና በቦክስ ኦፊስ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን የዘገበው ሲኤንቢሲ ኒውስ፣ ይህ ገቢ በዛሬው የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.82 ቢሊዮን ዶላር ያህል እንደሚደርስ አስታውቋል::
እ.ኤ.አ በ1977 ለእይታ የበቃውና በወቅቱ 461 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ያገኘው የመጀመሪያው “ስታር ዎርስ” ፊልም በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ፊልሙ ያገኘው ገቢ በአሁኑ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ዘገባው አመልክቷል፡፡
“ዘ ሳውንድ ኦፍ ሚዩዚክ” የተሰኘው ሙዚቃዊ ፊልም ለእይታ በበቃበት እ.ኤ.አ በ1965 ያገኘው አጠቃላይ ገቢ 159.3 ሚሊዮን ዶላር እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ በወቅቱ የአሜሪካ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.28 ቢሊዮን ዶላር የሚደርሰው ይህ ገቢ ፊልሙን በምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ የሶስተኛነት ደረጃ ላይ እንዳስቀመጠው አመልክቷል፡፡
የሳይንሳዊ ልቦለድ ዘውግ ያለውና እ.ኤ.አ በ1982 ለእይታ የበቃው ለእይታ የበቃው “ኢ.ቲ ዘ ኤክስትራ ቴሪስቴሪያል” በወቅቱ የዋጋ ግሽበት ሲተመን 1.27 ቢሊዮን ዶላር በማስገኘት የአራተኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን፣ ዘመን አይሽሬው ታይታኒክ በበኩሉ በ1.22 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በአምስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
“ዘ ቴን ኮማንድመንትስ” በ1.18 ቢሊዮን ዶላር፣ “ጃውስ” በ1.15 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዶክተር ዚያጎ” በ1.12 ቢሊዮን ዶላር፣ “ዘ ኤክሶርዚስት” በ996.5 ሚሊዮን ዶላር፣ “ስኖው ዋይት ኤንድ ዘ ሰቭን ድዋርፍስ” በ982.1 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከስድስተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የምንጊዜም ባለከፍተኛ ገቢ ፊልሞች መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በአለማችን የፊልም ታሪክ ከፍተኛ ገቢ ካስገቡ የምንጊዜም ምርጥ 26 ፊልሞች ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት ሌሎች ፊልሞች መካከልም “ቤንሁር”፣ “አቫታር”፣ “ዡራሲክ ፓርክ”፣ “አቬንጀርስ - ኢንድጌም”፣ “ዘ ላየን ኪንግ”፣ “ዘ ስቲንግ”፣ “ዘ ግራጁዌት”፣ “ፋንታሲያ” እና “ዘ ጋድ ፋዘር” እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


        የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር “በኪነ ጥበብ ፈጠራ ማበረታቻ ክፍያ አፈፃፀም መመሪያ” እና “በቴአትር ቤቱ የወደፊት ለውጥ ዙሪያ” ዛሬና ነገ በአዳማ ቶኩማ ሆቴል ውይይት ያካሂዳል፡፡ ውይይቱ በሁለት ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ በሚቀርቡ ጥናታዊ ፅሁፎች መነሻነት የሚካሄድ ሲሆን በጉዳዩ ላይ ለሚዲያ አካላት ግንዛቤ ለመፍጠር የተዘጋጀ መሆኑንም ቴአትር ቤቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በዕለቱ የሚመለከታቸው አካላትና የሚዲያ ባለሙያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

“ጥበብ ለእኔ እንደ ሱስ ነው፤ ከጥበብ ተለይቼ መኖር አልችልም”
                        ዓለምፀሐይ ወዳጆ

              ሕይወቴን በሙሉ ያሳለፍኩት በኪነ ጥበብ ውስጥ በተዋናይነትና  በገጣሚነት ሙያ ነው:: ወደ አሜሪካ ከመጣሁ በኋላ ኑሮን ለማሸነፍና ቤተሰቤን ለማስተዳደር ያልሰራሁት ሥራ የለም፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ከምወደው ሙያ አልተለየሁም፡፡ ጥበብ ለእኔ እንደ ሱስ ነው፤ ከጥበብ ተለይቼ መኖር አልችልም፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ዳግም የመኖር ዕድል ቢሰጠኝ፣ የምመርጠው የአሁኑን ሙያዬን፣ መሆን የምፈልገውም የአሁኗን ዓለምፀሐይን ነው፡፡
እኔ በተወለድኩ ጊዜ፣ እናቴ 16 ዓመቷ ነበር፡፡ ወዲያው አባቴ በግሪክ አገር ሥነ መለኮት የመማር ዕድል አግኝቶ ስለሄደ ያደግሁት፣ ፍቅር በተሞላበት የአያቶቼ ቤት፣ የጠየቅሁት ሁሉ እየተሟላልኝ ነበር:: የልጅነት አርአያዬ የሆነችው ማራኪዋና ከሰው ተግባቢዋ ሴት አያቴ፤ ተግቶ መስራትንና ለጋስነትን አስተምራኛለች፡፡ ሁሌም “መኖር ብቻውን ትርጉም የለውም፤ ሌሎችንም መርዳት አለብሽ” ትለኝ ነበር፡፡ ጥበብን እንደ ነፍሷ ነበር የምትወደው፡፡ ታንጎራጉራለች፡፡ በአሮጌ ቴፕዋም ሙዚቃ ታዳምጥ ነበር፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ወስዳ ተውኔት ያሳየችኝ እሷ ናት፡፡ የግጥምና የድራማ ፍቅር የተጋባብኝም ከእርሷ ነው ማለት እችላለሁ፡፡
አስተማሪዎቼ ለኪነ ጥበብ ያለኝን ፍላጎትና ተሰጥኦ የተረዱት ገና ታዳጊ ሳለሁ ነበር፡፡ በ13 ዓመቴ እኔን ለሌሎች ምሳሌ በማድረግ የአማርኛ አስተማሪዬ፣ ግጥሜን ለተማሪዎች ድምጹን ከፍ አድርጎ አንብቦልኛል፡፡ በዚያው ዓመት በየክፍለ ሀገሩ እየዞረ ለሚያሳየው ቲያትር፣ ተማሪዎችን ይመለምል የነበረው የሙዚቃ አስተማሪዬ መላኩ አሻግሬ፤ በሀገር ፍቅር ቴያትር መድረክ ላይ እንድተውን ዕድል ሰጠኝ፡፡ እዚያው ቲያትር ቤት በነበረ የአማተር ክበብ ውስጥም አባል ሆንኩኝ፡፡ ይህ የቲያትር ፍላጎቴ ግን ቤተሰቤ ውስጥ አከራካሪ ጉዳይ ነበር፡፡ አባቴ ከግሪክ እንደተመለሰ በትምህርቴ አንደኛ እንድወጣ ብቻ ሳይሆን ሐኪም ወይም ጠበቃ መሆን እንዳለብኝ ቁርጤን ነገረኝ፡፡ መድረክ ላይ ቢያየኝ እግሬን መስበር ብቻ ሳይሆን እንደሚገድለኝም ጭምር አስጠነቀቀኝ:: አያቴ ግን እንድተውን ፈቀደችልኝ፡፡ በእርግጥ እሷም ብትሆን ቅድመ ሁኔታ አስቀምጣልኝ ነበር:: ትምህርቴን ማጠናቀቅ እንዳለብኝና ምስሌ በፖስተር ወይም በበራሪ ወረቀት ላይ እንደማይወጣ ቃል አስገባችኝ፡፡ ትያትር የምሰራው ሕዝብ ፊት እንደመሆኑ ትወናዬን ከአባቴ መደበቁ አስቸጋሪ ነበር:: ሁልጊዜ መድረክ ላይ ስተውን ድንገት አባቴ ከተፍ ቢልብኝ በማለት፣ ሁሌም ተክቶኝ የሚሰራ ተዋናይ አዘጋጅ ነበር፡፡
በ18 ዓመቴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ፣ በብሔራዊ ቴአትር ለሁለት ዓመት ይሰጥ በነበረው አዲስ የሥልጠና ፕሮግራም ውስጥ ከተካተቱት 12 እጩዎች መካከል አንዷ ሆኜ ለመመረጥ በቃሁ፡፡ ይህንንም የስልጠና ፕሮግራም በበላይነት ይመራ የነበረው፣ አስደማሚው ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድኅን እንደነበር አስታውሳለሁ:: ሥልጠናውን እንዳጠናቀቅሁ ነበር፣ በብሔራዊ ቲያትር፣ በከፍተኛ ተዋናይነት ተቀጥሬ፣ የረዥም ጊዜ ሕልሜን እውን ማድረግ የጀመርኩት፡፡ ከሥልጠናው በተጨማሪ ከአገሪቱ ድንቅና ምርጥ ተዋናዮች፣ ጸሐፌ-ተውኔቶችና አዘጋጆች ጋር በመሥራት ያገኘሁት ልምድ፣ የትያትር ተሰጥኦዬንና ችሎታዬን በማጎልበት ረገድ በእጅጉ አግዞኛል፡፡ ለቀጣዮቹ 17 ዓመታትም በተዋናይነትና በጸሐፊነት መሥራቱን ገፋሁበት፡፡ በኢትዮጵያ ትያትሮች ብቻ ሳይሆን ዘመን አይሽሬ በሆኑ የጥንት የውጪ ደራሲያን ተጽፈው በሀገራችን ሰዎች በተተረጎሙ ትያትሮችም ላይ ድንቅ ገጸ ባሕርያትን በመወከል ተጫውቼአለሁ፡፡ በ“የቬኑሱ ነጋዴ” ፖርትያን፣ በ “ሐምሌት” ኦፌሊያን እንዲሁም በኒኮላይ ጎጎል “ዋናው ተቆጣጣሪ” ማርያን ሆኜ ለመተወን በመቻሌ፣ ነፍሴ በሐሴት ጮቤ እረግጣለች፡፡ “መድረክ ላይ ባይሽ እግርሽን እሰብረዋለሁ” ሲል ያስጠነቀቀኝ አባቴ፤ ለ14 ዓመት ከተወንኩ በኋላ ነበር በ “ሐምሌት” ትያትር ላይ አፌሊያን ሆኜ ስተውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየኝ፡፡ ይሄን ጊዜ ግን እሱም ሐሳቡን ቀይሮ ነበር፡፡ በሙያዬ በእጅጉ ኮራብኝ፡፡ ለእኔ የጥበብ ጣኦቴ፣ በአስገራሚ የትወና ብቃቷ የማመልካት አንጋፋዋ ተዋናይት አስናቀች ወርቁ ነበረች፡፡
የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው፣ የንጉሡን አገዛዝ በመቃወም በተጀመረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ተሳታፊ የሆንኩት፡፡ 11ኛ ክፍል ሳለሁ ለአዲስ አበባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተዘጋጀ የጽሑፍ ውድድር፣ ትምህርት ቤቴን መድኃኔ ዓለምን ወክዬ ተወዳድሬ ነበር፡፡ ሌሎች ተወዳዳሪዎች፤ በንጉሳውያን ቤተሰብ አባላት ስም ከተሰየሙ ት/ቤቶች የመጡ መሆናቸውን ካስተዋወቁ በኋላ፣ ተራዬ ሲደርስ “እኔ ግን የመጣሁት ሰዎች ከየት መጡ ወይም ከማን ተወለዱ ሳይል ሁሉንም በእኩል ከሚያይ፣ ያሻውን ሁሉ የማድረግ ኃይል ካለው፣ ነገር ግን በኃይሉ ከማይመካውና ከማይታበየው ኃያሉ ፈጣሪ፣ መድኃኔ ዓለም ስም ከተሰየመ ትምህርት ቤት ነው” ብዬ ራሴን ሳስተዋውቅ፣ አስተማሪዎቼ በድንጋጤ የሚገቡበት ቢጠፋቸውም፣ ታዳሚው ግን በሚያስገመግም ድምጽ አድናቆቱን ገለጸልኝ:: የተወዳደርኩበት ግጥም የንጉሰ ነገሥቱን አገዛዝ የሚተች ነበር፤ እንዲያም ሆኖ ግን በውድድሩ አሸናፊ ሆንኩኝ፡፡ ይህንንም ተከትሎ፣ የትምህርት ቤቴ የተማሪዎች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኜ በመመረጤ፣ ከሁለተኛ ደረጃና ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መሪዎች ጋር ትስስር የመፍጠር ዕድል አገኘሁ፡፡ ለዲሞክራሲና ለሴቶች መብት የመሟገት የዕድሜ ልክ ትግሌ የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር:: ለአጭር ጊዜ፣ በንጉሡ አገዛዝ ታስሬም ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜ ለአያቴ ጎረቤት! ወህኒ ቤት ከመክረም አትርፈውኛል፡፡ አባቴም የአገዛዙ ተቃዋሚ ስለነበረ በዚህ ረገድ እኔና አባቴ ልዩነት አልነበረንም፡፡
የንጉሡ አገዛዝ በደርግ ወታደራዊ ኃይል ተገርስሶ እንደወደቀ፣ የኢትዮጵያ ሴቶች አደራጅ ኮሚቴ (በኋላ የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር የተባለው) የብሔራዊ ቴአትር ተወካይ በመሆን ተሾምኩ:: የማኅበሩም ሥልጣንና ኃላፊነት፣ የአዲሲቱን ሶሻሊስት አገር ሴቶች ማደራጀት እንዲሁም በመብታቸውና ነጻነታቸው ዙሪያ ንቃተ ኅሊናቸውን ማሳደግ ነበር፡፡ የማኅበሩ ተወካይ ብሆንም ቅሉ፣ በምሥጢር ኢሕአፓ የተባለውን ተቃዋሚ ቡድን እደግፍ ነበር፡፡ በዚያን ሰሞን የብሔራዊ ቴአትር ከያኒያን፣ የጡረታ ጥቅማጥቅሞች ጥያቄያቸው ምላሽ እንዲያገኝና የሙያ ማኅበር የመመስረት መብታቸው እንዲከበር ሰላማዊ ሰልፍ ባደረጉበት ጊዜ፣ ይህንን አጋጣሚ በመጠቀምም፣ የኢሕአፓ አባላት መንግስትን የሚቃወም ወረቀት በማሰራጨታቸው፣ ፖሊስ ተኩስ ከፍቶ 11 ከያኒያን ተይዘው ታሰሩ፡፡ በዕለቱ አያቴ ሞታ ስለነበር እኔ በሰልፉ ላይ ለመሳተፍ ባልችልም፣ “ምን ያለበት ዝላይ አይችልም--” እንዲሉ፣ የሥራ ባልደረቦቼ ከተቃዋሚ ቡድን ጋር ግንኙነት አንዳለኝ ይጠረጥሩኝ ስለነበር፣ ወደ ሥራ ለመመለስ  ክፉኛ ፈራሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ከቤት ወጥቼ ዘመዶቼ ጋ ለስድስት ወር ያህል ተሸሸግሁ፡፡ የማታ ማታም ከተሸሸግሁበት ወጣሁና የታሰሩትን 11 ከያኒያን ይቅርታ ጠይቄ ሥራችንን ቀጠልን፡፡
ከዚያ በኋላ ነው ለመንግሥት የሶሻሊስት መርሐ ግብሮች የሰራሁት፡፡ በተለይም ሴቶችና ሕጻናትን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ በማተኮር፡፡ ወላጆቻቸው የጦርነት ሰለባ የሆኑባቸው ሕጻናት በነበሩበት የዝዋይ ሕጻናት አምባ ውስጥ የኪነ ጥበብ ፕሮግራምን ለሕጻናት እየቀረጽኩ አቀርብ ነበር:: ይሄንንም ፕሮግራም በየ15 ቀኑ በበጎ ፈቃደኝነት እያካሄድኩ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ ዘልቄአለሁ:: በባህል ሚኒስቴር የሕጻናት የቲያትር ክፍልን አቋቁሜም በኃላፊነት መርቻለሁ፡፡ የትያትር ክፍሉን የመሰረትኩት ምሥራቅ ጀርመንን በጎበኘሁበት ወቅት ያየሁትን ምሳሌ በማድረግ ሲሆን ክፍሉን በባህል ሚ/ር ሥር ለሰባት ዓመት አስተዳድሬያለሁ:: ከሙያ ባልደረቦቼ ጋር በመተባበር ደግሞ የኢትዮጵያ ተዋናዮች ማኅበርን መሥርቼአለሁ:: ማኅበሩን በሊቀ መንበርነት ባገለገልኩባቸው 14 ዓመታት ውስጥ የተዋንያን ደሞዝ እንዲሻሻል ስኬታማ ቅስቀሳ አድርገናል፡፡ ሌላው ስኬታማ እንቅስቃሴያችን፣ ስለ ወሲብና በግብረ ሥጋ ግንኙነት ስለሚተላለፉ በሽታዎች ማውራት ነውር በነበረበት ዘመን፣ በአዲስ አበባ ያዘጋጀነው ለሳምንት የዘለቀ የጸረ - ኤድስ ፌስቲቫል ሲሆን  በፌስቲቫሉ ላይ በርካታ ዕውቅ ከያኒያን ስራቸውን አቅርበዋል፡፡ ፌስቲቫሉ በተካሄደበት ስታዲየም ውስጥ “በጥንቃቄ ተጠቀሙ” የሚል ጽሑፍ በሰፈረበት የክብሪት ቤት ውስጥ ኮንዶም ጨምረን ለታዳሚው አሰራጭተናል:: ከዚህም ባሻገር፣ በኅብረተሰቡ ዘንድ ስለ ኮንዶም የነበረውን የኃፍረት ስሜት ለመስበር፣ ኮንዶሙን እንደ ፊኛ በመንፋት ለማዝናናት ሞክረናል፡፡
በብሔራዊ ቴአትር ተውኔቶችንና ግጥሞችን ከመተወንና ከመጻፍ ጎን ለጎን፣ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎችን እንዲሁም ፕሮግራሞችንና ዝግጅቶችን መምራቴን ገፋሁበት፡፡ ምንም እንኳን ወታደራዊው መንግሥት የከያኒያንን ሥራ በሳንሱር መቀስ ይጎማምድ የነበረ ቢሆንም፣ ጥበባዊ ፈጠራዎች እንዲስፋፉ የተገኘችውን ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመናል:: “ደማችን” ከተሰኘው የመጀመርያ የሙሉ ሰዓት ትያትሬ (የመጀመርያው ባለቤቴ ታደሰ ወርቁ፣ ስብሐት ተሰማና እኔ በጋራ የጻፍነው ነበር) በኋላ መንግስትን ክፉኛ የሚተች “በሩ” የሚል ተውኔት የጻፍኩ ሲሆን በራስ ትያትር ለአምስት ጊዜ ያህል ከታየ በኋላ፣ የባህል ሚኒስትሩ ጠርተውኝ በትያትሩ ላይ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እንዳደርግ ጠየቁኝ፡፡ እኔ ግን አሻፈረኝ አልኳቸው፡፡ በዚህም ሳቢያ ትያትሬ እንዳይታይ እገዳ ተጣለበት፡፡
ከወደቀው አገዛዝ ጋር በቅርበት ሥሰራ በመቆየቴ ደርግ ሊወድቅ አንድ ዓመት ሲቀረው፣ ሁለት ልጆቼን (ተወለድ ታደሰና አይናለም ደጀኔን) ይዤ ወደ አሜሪካ ተጓዝኩ፡፡ ባለቤቴ ደጀኔ ገረመው ከስድስት ወር በኋላ እኔን ተከትሎ አሜሪካ ገባ:: በአሜሪካ ኑሮን ለማሸነፍ የተለያዩ ሥራዎችን ለመስራት ብገደድም፣ ልቤ ግን መቼም ቢሆን ከጥበብ ተለይቶ አያውቅም፡፡ ከልቤ የምወደውን የኪነ ጥበብ ስራ በስፋት የመስራት ዕድል ያገኘሁት ግን  በ1992 ዓ.ም በዋሺንግተን ዲሲ፣ ጣይቱ የባህል ማዕከልን በማቋቋም፣ በዋና አስተዳዳሪነት መምራት ስጀምር ነበር፡፡ ማዕከሉ ላለፉት 13 ዓመታት ያለ ብዙ የውጭ ድጋፍ፣ በርካታ የኢትዮጵያ ባህላዊ ዝግጅቶችን ሲያስተናግድ ቆይቷል፡፡ እስካሁን ከ35 በላይ ተውኔቶችን ሰርተን ያቀረብን ሲሆን ከ150 የሚበልጡ የዓርብ የግጥም ምሽቶችን አዘጋጅተናል:: ከዚህም በተጨማሪ በየዓመቱ በአሜሪካ 17 ግዛቶችና በአውሮፓ እየተጓዝን፣ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ የኪነጥበባዊ ዝግጅቶችን እናቀርባለን፡፡ ወጣት የኪነጥበብ ባለሙያዎችን ለማሰልጠን በየጊዜው ዐውደ ጥናቶችን እናዘጋጃለን:: ግጥም በኢትዮጵያ ባህላዊና መንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ጉልህ ድርሻ በመያዝ ለዘመናት የዘለቀ ጥበባዊ ኃይል ነው፡፡ ፕሮግራማችን በስደት ላይ ያለን ኢትዮጵያውያን ሁሉ ባህላችን ህያው ሆኖ እንዲቀጥል ብቻ ሳይሆን ከአገራችን ጋር ያለን መንፈሳዊ ቁርኝት እንዲጠናከር፣ የመጪው ዘመን ተስፋችንም እንዲለመልም አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም፡፡ በቅርቡ በአሜሪካ የመጀመርያውን የአማርኛ ቤተ መጻሕፍት በዋሺንግተን ዲሲ ከፍተናል፡፡ የአገሪቱን መዲና በመቆርቆር ጉልህ ድርሻ የነበራቸው የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ሐውልት በአዲስ አበባ ከተማ ቆሞ ማየት ትልቁ ህልሜ ነው፡፡
ኢትዮጵያ የበርካታ ሴት መሪዎችና ንግስቶች አገር ብትሆንም፣ ለብዙኃኑ ሴቶች ግን ተመችታ አታውቅም፡፡ ሴቶች በሥራቸው ላይ ለመቆየት፣ ደሞዝና ዕድገት ለማግኘት እንዲሁም ሐሳባቸው እንዲከበርና ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ከወንዶች እጥፍ ተግተው መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወንዶች ፊት ስለ ሴቶች እኩልነትም ሆነ በሥራ፣ በቤትና በአጠቃላይ በኅብረተሰቡ ውስጥ ስለሚደርስባቸው በደልና ኢ-ፍትሃዊነት ማውራት አይሞከርም፡፡ ወንዶች እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለመስማት አይፈልጉም፡፡ እኔን የገጠሙኝ ፈተናዎች፣ ለራዕዬ ወይም ለሙያዬ ያለኝን ፍቅር ለማደናቀፍ አቅም ያላቸው አልነበሩም፡፡ ሰዎች “ብረቷ እመቤት” እያሉ ይጠሩኛል፤ እኔም እራሴን መንፈሰ ጠንካራና የምወደውን ሥራ ለመስራት ፈጽሞ የማይታከተኝ ሰው አድርጌ ስለምመለከት፣ ይህን መጠሪያዬን እወደዋለሁ፡፡
ለወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች የማስተላልፈው ምክር ግልጽና ቀላል ነው፡- “በራሳችሁ እምነት ይኑራችሁ፣ ትልቅ ነገር አልሙ፣ መንፈሳችሁን አጠንክሩት፣ በምንም ሁኔታ ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ” የሚል ነው፡፡
                   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ መምህር ሲያስተምሩ፣ አንድ ተማሪ አስተዋይና ረቂቅ ነበራቸው፡፡ ተማሪው፤ ሊቃውንት በተሰበሰቡበት ጥያቄ እያቀረበ አስቸገራቸው፡፡ በዚህ ተናደዋል፡፡ ስለዚህ ቆይ እሰራለታለሁ ብለዋል፡፡ የተማሪው ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው፡። የመምህሩ አፋፉ ላይ ነው፡፡ ስለዚህ ምን እየሰሩ እንደሆን ለእሱ ቁልጭ ብሎ ይታየዋል፡፡
በዚህ ጠዋት መምሩ የወይራ አለንጋ ግቢያቸው ካለው የወይራ ዛፍ ሊመለምሉ ዛፍ ላይ ወጡ፡፡
 ተሜ ከታች ሽቅብ ያስተውላቸዋል፡፡
ከዚያ መምህሩ ተማሪዎቻቸውን ማስተማር ጀመሩ፡፡
በመካከል ግን ያንን ትላንት ሊቃውንቱ ፊት ያስቸገራቸውን ለማግኘት አስበው “ታምሪሃ ወ-እግዚሃር” አሉ … ታምሪሃ ተ ጠብቆ የማይነበበውን አጥብቀው ነው ያነበቡት፡፡
 ያ ተማሪ ግን ሳይመልስላቸው ፀጥ ብሎ ኑሯል፡፡
“ታምሪሃ ወ-እግዚሃር” አሉ፡፡
ተሜ ጭጭ፡፡ በመካያው መምህሩ ተናደዱና፤
“ምን ሆነህ ነው አንተ፤ አትመልሰኝም እንዴ?”
ተሜም፤
“አዬ የኔታ፤ እቺማ ውስጠ ወይራ ናት” አላቸው፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ውስጠ ወይራ የሚለው ሐረግ፣ በህብረተሰቡ ዘንድ፣ ፋይዳ ያለው ትርጉም አገኘ!
***
ብልህና በሳል ተማሪ ሊኖር ይችላል ብሎ፣ ብልህ መምህር ራሱን ለማየት  መቻል አለበት፡፡
“አዬ ያ አስተማሪ
ያለበት አባዜ
አስተዋይ ተማሪ
    የጠየቀው ጊዜ”  
የሚባለው ለዚህ ነው፡፡
እርግጥ ነው ተማሪው ሙሉ ክህሎት ያገኝ ዘንድ አስቀድሞ መምህሩ መቃኘት ይኖርበታል፡፡ አልፎ ተርፎም የተማረውን በሥነ ስርዓት ማደስና ማሻሻል ተገቢ ነው፡፡ ማንም ሰው ለማደግ፣ ካለማደግ ነው የሚጀምረው፡፡
ጥንት ትምህርት ከድል በኋላ መፈክር ነበረ፡፡ ያለ ትምህርት አገር የትም እንደማይደርስ ለሚያውቅ ገዢ ኃይለኛ መፈክር ነው፡፡ ትውልድ ወይ ቤተሰብ ውስጥ፣ ወይ ት/ቤት ውስጥ  ወይ Co-curricular activity ውስጥ ነው የሚወለደው፡፡ ስለዚህ እነዚህን ሶስት ዘርፎች አግዝፈን እንያቸው፡፡ ያለ ትውልድ አገር አትገነባም፡፡ እሱም የአንድ ጀምበር ሩጫ እንዳልሆነ አበክረን እናስተውል፡፡
እዚህች ምስኪን አገራችን ላይ አያሌ መሪዎች ነግሰዋል፡፡ ችግሩ አዲሱ ካለፈው ሳይማር፣ በአሮጌው መንገድ መውደቃቸው ነው፡፡ እንደ አለመታደል ሆኖ ሒስ የሚሰጥ ትጉ ሰው አልተፈጠረልንም፡፡ መንገዳችን ገና ጣጣው ብዙ ነው፡፡ ተቃዋሚና ደጋፊ በሌለበት ሁኔታ እንኳን ተግባብተን የመስራት ባህል አለመኖር እንዳገተን አለ፡፡ ሆኖም እንንቃና እንነሳሳ፤ ጥንት ደጋግመን እንደጠቀስነው፡-
“ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ፣
 ከንግግር በፊት የአርምሞ ፀጥታ፣
 ዛሬም ሀገራችን የአንድ አፍታ ዝምታ፤
 ነገ ግን ይተጋል፤ መነሳቱ አይቀርም፤
ተነስቶም ያሸንፋል፤ አንጠራጠርም”
በሀገራችን ብዙ ቃል የተገቡልን ጉዳዮች አሉ፡፡ ብዙ ጠብቀን ጠብቀን ግን ሳይከሰቱ ሲቀሩ የሀገራችን ተረት ፊታችን ድቅን ይላል፡፡ የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ!

“--የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡--”

             በልጅነቴ ሬዲዮ ላይ እሰራለሁ የሚል ሀሳብ ሽው ብሎብኝም አያውቅም ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ ከኋላ እንጂ ከፊት መሆንን የማልደፍር፤ በፅሑፍም ሆነ በትወና ችሎታዬ እርግጠኛ ያልሆንኩ ተማሪ ነበርኩ፡፡ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ አንዴ የመስራት ዕድል አገኘሁና የምወደውን ሙያ እንዳገኘሁ አወቅሁ፡፡ ለመስራት ወደምሻው ሙያ የሚያቀርበኝን ስራ ሳፈላልግ ግን ከአስር ዓመት በላይ ፈጀብኝ፡፡ በ1987 ዓ.ም በኢትዮጵያ ሬዲዮ 97.1 ኤፍኤም ላይ ጨዋታ ፕሮግራምን በጋራ የማዘጋጀት እድል አገኘሁ፡፡ በ1999 ዓ.ም ደግሞ ከባለቤቱ አበበ ባልቻ እና ከረዥም ጊዜ ጓደኛዬና የሥራ ባልደረባዬ ተፈሪ አለሙ ጋር ሸገር ኤፍኤምን አቋቋምን፡፡ የምወደውን ሙያ የመስራት እድል የከፈቱልኝ እነዚህ አጋጣሚዎች ነበሩ፡፡
የተወለድኩት በ1950 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ወላጆቼ የሐረር ሰዎች ሲሆኑ፤ እስከ 9 ዓመቴ ድረስ በምዕራብ ሐረርጌ በምትገኘው ትንሿ የሂርና ከተማ ነበር ያደግሁት፡፡ ሂርና በሚገርም ሁኔታ የተለያዩ ህዝቦችን በአንድ ላይ ያስተሳሰረች ከተማ ነበረች፡፡ ጎረቤቶቼ የመናውያን፣ ኦሮሞዎች፣ ሐረሪዎችና ሶማሌዎች ነበሩ፡፡ የእነዚህን ሁሉ ህዝቦች የበለፀገ የባህል መስተጋብር እያጣጣምኩ አደግሁ፡፡
ወላጆቹ ነጋዴዎች ነበሩ፡፡ አባቴ ቡናና ሌሎች ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ የተዋጣለት ነጋዴ ሲሆን እናቴ ደግሞ የአነስተኛ ግሮሰሪ ባለቤት ነበረች:: ባለፀጋ ቤተሰብ ነበርን፡፡ አንብቦ የማይጠግበው አባቴ፤ ብዙ መጻሕፍትና ጋዜጦችን ወደ ቤት ይዞ ይመጣ ነበር፡፡ ጋዜጦችን እንዳነብ ከማበረታታትም ባሻገር የእጅ ጽሑፌ እንዲሻሻል ከጋዜጣው ላይ በእጄ እንድገለብጥ ያደርግ ነበር፡፡ ሁሌም በእኔ ላይ ትልቅ ተስፋ እንዳለው ይነግረኝና ያበረታታኝ ነበር፡፡ አባቴ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ቢሞትም፣ በራሴ ላይ እምነት ሳጣ እንኳን፣ እሱ በእኔ ላይ የነበረው እምነት ብርታት ይሰጠኛል፡፡
የ9 ዓመት ልጅ ሳለሁ ወላጆቼ አዲስ አበባ ባለው የቅድስት ማርያም አዳሪ ት/ቤት አስገቡኝ፡፡ ሴቶች ብቻ በሚማሩበት በዚህ የካቶሊክ አዳሪ ት/ቤት፤ መነኮሳቱ የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች ወለም ዘለም አያውቁም ነበር፡፡ በሥነ ሥርዓት ጉዳይ ላይ ፈፅሞ የሚደራደሩም አልነበሩም፡፡ ለመጀመሪያዎቹ ሁለት ሳምንታት ማታ ማታ ስራዬ ማልቀስ ብቻ ነበር:: ቀስ በቀስ ግን የአዲስ አበባ ኑሮን ተላመድኩት፤ የሳምንቱን የእረፍት ቀናት አክስቴ ቤት ማሳለፌም አረጋጋኝ፡፡ ንባብ ብቸኝነቴን የማመልጥበት መደበኛ ባልንጀራዬም ሆነ፡፡ ያኔ ልጃገረዶች ወጣ ወጣ ማለት አይፈቀድላቸውም ነበርና በየሳምንቱ መጨረሻ አክስቴ ቤት ስሄድ፣ ሁለትና ሶስት መጻሕፍትን እየያዝኩ ነበር፡፡ ለዚያን ዘመን ልጃገረዶች ያልተለመደ ቢሆንም፣ “አዲስ ዘመን” እና “የዛሬይቱ ኢትዮጵያ” ጋዜጦችንም ማንበብ እወድ ነበር፡፡
የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ በደርግ ወታደራዊ መንግስት የእድገት በሕብረት ዘመቻ፣ በሰሜን ትግራይ ወደምትገኘው ውቅሮ የተባለች የገጠር መንደር ተላኩ፡፡ ለእኔ ነፃ የወጣሁበት ጊዜ ይሄ ነበር ማለት እችላለሁ፡፡ ትክክለኛ ኃላፊነት ምን እንደሚመስል የተገነዘብኩበት የመጀመሪያ አጋጣሚዬም ነበር፡፡ ገበሬዎችን የሕብረት ሥራ ማህበራት እንዲመሰርቱ ለማገዝ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር እልም ወዳለ ገጠር ነበር የተላኩት:: ከስድስት ወራት አገልግሎት በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተመለስኩ፡፡ ከዚያም ቅድስት ማሪያም ት/ቤት ተመልሼ በመግባት ያቋረጥኩትን ትምህርት የቀጠልኩ ሲሆን በ1970 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀቅሁ፡፡ ይህ ጊዜ የደርግ መንግስት አስከፊውን የቀይ ሽብር ዘመቻ ያጧጧፈበት ወቅት ስለነበር፤ በተለይ ለተማሪዎች አስፈሪ ነበር:: አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ብገባም የእለት የእለቷን ከመኖር ውጭ ለወደፊት ህይወቴ ምንም ዓይነት ህልም አልነበረኝም፡፡ የተመደብኩበትን የሥነ ልሳን ትምህርት ባልወደውም፣ አብረው ለሚሰጡት የሥነ ጽሑፍ ትምህርቶች ስል ገፋሁበት፡፡
የመጨረሻ ዓመት ተማሪ ሳለሁ በአጋጣሚ በሬዲዮ ድራማ ላይ የመተወን እድል አገኘሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- አንድ ቀን የትያትር ጥበባት የትምህርት ክፍል ተማሪዎች የነበሩት አስታጥቃቸው ይሁን እና ተፈሪ አለሙ፤ የተማሪዎች መኖሪያ ደባል ጓደኛዬን መንበረ ታደሰን ፍለጋ ወደ ክፍላችን ይመጣሉ፤ መንበረን የፈለጓት አስታጥቄ በፃፈው የሬዲዮ ድራማ ላይ ለመቀረፅ አብራቸው እንድትሄድ ነበር:: እሷ እንደሌለች ስነግራቸው በእሷ ምትክ ካልሰራሽ ብለው ወጥረው ያዙኝ፡፡ መጀመርያ ላይ አሻፈረኝ ብያቸው ነበር፡፡ በኋላ ግን ተስማምቼ፣ በያኔው የታደሰ ሙሉነህ ‹እሁድ ፕሮግራም› የተሰኘ ተወዳጅ የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ድራማ ለመቅረፅ አብሬያቸው ሄድኩ፡፡ ያኔ ‹የእሁድ ፕሮግራም› በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከወታደራዊው አገዛዝ አብዮታዊ ፕሮፓጋንዳ የተለየ መዝናኛ የሚያቀርብ ብቸኛ ዝግጅት ነበር:: በቀረፃው ወቅት ታደሰ ሙሉነህ አገር ውስጥ አልነበረም:: እንደተመለሰ ግን “ለሬዲዮ ጥሩ ድምፅ አላችሁ” በሚል እንድናነጋግረው ጠየቀን፡፡ በሬዲዮ ላይ መስራት የጀመርኩት በዚህ መልኩ ነበር፡፡ ታደሰ ሙሉነህ ለሁላችንም የሙያ አባታችን ነበር፡፡ ምንም ልምድ ባልነበረን ጊዜ ተቀብሎ በማሰልጠንና በሬዲዮ እንድንሰራ እድሉን በመስጠት አግዞናል፡፡
ከዩኒቨርሲቲ ከተመረቅሁኝ በኋላ መንግሥት፤ ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መደበኝ፡፡ ያኔ የሚዲያ ዋና ስራው የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት ስለነበረ፣ ሚዲያ ውስጥ የመስራት ጉጉት አልነበረኝም:: መጀመርያ ላይ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የፕሬስ መምሪያ ኃላፊ፣ አብሬው እንድሰራ አልፈለገም ነበር:: ለነገሩ በእሱም አይፈረድም፤ ቀድሞ የነበረችው ሰራተኛ የወሊድ ፈቃድ እየወሰደች በቅጡ ስለማትሰራ እኔም እንደሷ እንዳልሆን ሰግቶ ነው:: ከስድስት ወራት የሥራ ጊዜ በኋላ ግን አቅሜንና ችሎታዬን በማረጋገጡ፣ የመርሃ ስፖርት ጋዜጣ፣ የስፖርት ዘጋቢ እንድሆን ተመደብኩ፡፡ እውነቱን ለመናገር የስፖርት ፍላጎት አልነበረኝም፤ ነገር ግን የክልል ውድድሮችን ለመዘገብ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ስለምጓዝ፣ በአጋጣሚው ያገኘሁትን ኢትዮጵያን ተዘዋውሮ የማየት እድል ወድጄው ነበር፡፡ በኋላ ላይ ወደ ባህል ሚኒስቴር ዓለም አቀፍ ግንኙነት ክፍል ተዛወርኩ፡፡ ጎን ለጎን ግን በኢትዮጵያ ሬዲዮ እሁድ ፕሮግራም ላይ በግል መስራቴን ቀጠልኩ፡፡ በባህል ሚኒስቴር ሥራዬ እርካታ ባይኖረኝም፣ አስደሳች ተመክሮ መቅሰምና ለጋዜጠኝነት የሚቀርብ ሥራ ማፈላለጌን ገፋሁበት:: ከዚያም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተቀጥሬ የባንኩ ወርሃዊ መፅሄት ብሪቱ ዋና አዘጋጅ በመሆን፣ የፋይናንስ ዜናዎችንና አጭር ልብወለዶችን መፃፍ ጀመርኩ፡፡ በመቀጠልም አዲሱ የኢትዮጵያ የሽግግር መንግስት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሬስና መረጃ ዋና ዳይሬክተር እንድሆን ጠየቀኝ፡፡ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት፣ በዚህ መ/ቤት ውስጥ ያገለገልኩ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ለስራው እንደማልሆን ተገነዘብኩ:: በሬዲዮ ሥራዬ የሚያውቁኝ አንዳንድ ሰዎች ለቢሮክራሲያዊ ስራ እንደማልሆን ይነግሩኝ ነበር፤ እኔም ትክክል እንደሆኑ አውቅ ነበር፡፡ ለስምንት ዓመታት በግሌ በሬዲዮ ላይ ሰርቻለሁ፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም በሬዲዮ ድራማዎቼ፣ ጭውውቶቼና ጥናታዊ ስራዎቼ ታዋቂነትን አትርፌአለሁ፡፡  
ሦስተኛ ልጄን እርጉዝ ሳለሁ ነበር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የለቀቅሁት፡፡ ለጥቂት ጊዜያት ምን መስራት እንዳለብኝ እያሰላሰልኩ ቆየሁ፡፡ ለትንሽ ጊዜ በፕሬስ አደራጅነት የሰራሁ ሲሆን የሕዝብ ግንኙነት ስራዎችን የሚያከናውን ድርጅትም ከፍቼ ነበር፡፡ በዚህ መሃል ግን የኢትዮጵያ ሬዲዮ ሥራ አስኪያጅ የነበረው ፈቃዱ የምሩ፣ ባለቤቴን በኤፍ ኤም 97.1 የአየር ሰዓት ወስዶ፣ የራሱን ፕሮግራም እንዲያዘጋጅ ጠየቀው፡፡ ባለቤቴ አዘጋጅ ሆኖ፣ እኔና ተፈሪ አለሙ ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የሚቀርበውን “ጨዋታ” የተሰኘ ፕሮግራም ማዘጋጀት ጀመርን፡፡ በኋላም ጌታቸው ማንጉዳይ፣ ብርሃኑ ድጋፌ፣ ግሩም ዘነበና ደረጀ ኃይሌ ተቀላቀሉን፡፡ “ጨዋታ” ለስምንት ዓመት ገደማ በአየር ላይ ውሏል፡፡ ፕሮግራሙ የመፅሄት ይዞታ የነበረው ሲሆን የታሪክ ትረካዎች፣ ድራማዎች፣ ቃለ ምልልሶችና ሌሎችንም ያካተተ ነበር፡፡
ከዚያም መንግስት ለሁለት የግል ሬዲዮ ጣቢያዎች ፈቃድ እንደሚሰጥ ይፋ ሲያደርግ ባለቤቴ ማመልከት አለብን አለ፡፡ መጀመርያ ላይ ወደ ኋላ ብዬ ነበር፡፡ ሳልፈልግ ቀርቼ ሳይሆን ገንዘቡም ዝግጅቱም ሳይኖረን፣ ምኑን ከምኑ እናደርገዋለን የሚል ፍራቻ ይዞኝ ነው፡፡ ባለቤቴ ግን ይህን እድል በድጋሚ ላናገኘው እንችላለን ብሎ ተሟገተኝ፡፡ በመጨረሻም የእሱ ሃሳብ አሸነፈና ከተፈሪ አለሙ ጋር አመለከትን:: ረዥም ጊዜ ከፈጀ ሂደት በኋላም የሸገር ኤፍኤምን ፈቃድ በእጃችን አስገባን፡፡ ይኼኔ በፍርሃት ራድኩኝ:: “አሁን ምንድነው የምናደርገው?” ብዬ ግራ ገባኝ:: የምንመዘነው የ90 ዓመት እድሜ ካስቆጠረው ግዙፉ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ድርጅት ጋር ነው፡፡ ሸገር ከዜሮ መጀመር ነበረበት፡፡ ነገሩ በከፍታና በዝቅታ የተሞላ አጓጊ፣ አነቃቂና እልህ አስጨራሽ ነበር:: አንዳንዴ “ለምንድነው እዚህ ውስጥ የገባሁት?” እያልኩ ራሴን እጠይቅ ነበር፡፡ የእኔ ጥንካሬ በሬዲዮ ፕሮግራሞችና ይዘቶች ዝግጅት ላይ እንጂ በቴክኒክ፣ በአስተዳደራዊ ወይም በንግድ ጉዳዮች ላይ አልነበረም፡፡ እንደመታደል ሆኖ ግን ከአሜሪካዊው አማካሪዬ ከዴኒስ እስራኤል ጋር ዕድል አገናኘኝ:: እሱ የሬዲዮ ጣቢያ ለማቋቋም አስፈላጊ የሆኑ ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ሁሉ ቁጭ አድርጎ አማከረኝ፡፡ በንግዱ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከደጓሚዎች ጋር የመስራት መጠነኛ ልምድ ነበረን፡፡ ባለቤቴም በማስተዋወቅና የንግድ ትልሙን በመንደፍ አገዘን:: በመጨረሻም የግል ሬዲዮ ሥርጭት መስፋፋትን በሚደግፉ በርካታ ባለሙያዎች እገዛ፣ ሸገር 102.1 መስከረም 25 ቀን 1997 ዓ.ም አየር ላይ ዋለ፡፡
ሸገር በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሌሎች የሬዲዮ ጣቢያዎች ለየት የሚያደርገው የራሱ ልዩ ድምፅና ድባብ እንዲኖረው እንፈልግ ነበር፡፡ ከኢትዮጵያ ሬዲዮ ውጭ ከነበሩ ሁለት አማራጮች አንደኛው ስለነበርን፣ መጀመርያ ላይ ይሄን ማድረግ ከባድ አልነበረም፡፡ ዛሬ ግን ሌሎች ሬዲዮ ጣቢያዎች የአቀራረብ ስልታችንን ያለ ፈቃድ ስለሚወስዱብን፣ ሁልጊዜም አዲስ ነገር መፍጠር ይጠበቅብናል:: በእርግጥ ይሄ ያኮራናል እንጂ አያስቆጨንም:: በየሳምንቱ ቅዳሜ የሚተላለፈውን ‹የጨዋታ እንግዳ› እና የእሁድ ጠዋቱን ‹ሸገር ካፌ› ፕሮግራሞች በመቅረፅ የማሳልፋቸው አራት ሰዓታት ለእኔ ተወዳጅና ተናፋቂዎች ናቸው፡፡
ወደፊት ሸገር ኤፍ.ኤም ወደ ሸገር ሬዲዮና ቴሌቪዥን፣ ቀስ በቀስም ወደ ሸገር ሲኒማ አድጎና ሰፍቶ ማየት እፈልጋለሁ፡፡ ሸገር ኤፍኤም ህብረተሰቡ ሰምቶት የማያውቀውንና የሚማርበትን፣ የሚያዝናናውንና የሚያስቀውን ነገር እንዲያቀርብ እንሻለን፡፡ ሸገር አድማጮቹ ሃሳባቸውን የሚያንሸራሽሩበት ትክክለኛ መድረክና ድምፅ አልባ ለሆኑትም ድምፃቸው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ ሴት ሆኖ መኖር ተጨማሪ ፈተና አለው፡፡ በስፖርት ኮሚሽን ሳለሁ ሥራዬን የማከናወን ብቃት እንዳለኝ ለአለቃዬ ለማሳየት የበለጠ መትጋት ነበረብኝ፡፡ አሁንም ሳይቀር በሥራዬ ላይ አንዲትም ክፍተት እንዳይገኝብኝ በከፍተኛ ጥንቃቄ እዘጋጃለሁ፡፡ በቀላሉ ደግሞ ተስፋ አልቆርጥም፡፡ በመንገዴ ላይ መሰናክል ከገጠመኝ መውጪያ መንገድ የምፈልገው በመሰናክሉ ዙሪያ ነው፡፡ በምሰራው ሁሉ መቶ በመቶ እርግጠኝነት ተሰምቶኝ አያውቅም፡፡ አሁንም ወደ ቃለ መጠይቅ ስሄድ፣ ሁሉን ነገር እንደማላውቅ ስለማውቅ መረበሼ አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ ሁሉን ነገር አለማወቃችን ነው ህይወትን የሚያጣፍጣት፡፡ ያልተገመቱ ነገሮች እንዲከሰቱም እድል ይሰጣል፡፡
የኢትዮጵያ ሴቶች የሚገባቸውን ያህል ዋጋ አልተሰጣቸውም ብዬ አምናለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ሴቶች አካላዊ ውበት ላይ የማተኮር አዝማሚያ ይታያል፤ የኢትዮጵያ ሴቶች መለያ ግን አካላዊ  ውበታቸው ብቻ ነው ብዬ አላምንም፡፡ አስደናቂ ጥንካሬና ብርታታቸውም መለያቸው ነው፡፡ ራሳቸው የኢትዮጵያ ሴቶችም ሆኑ ቀሪው ዓለም ይሄን ጥንካሬያቸውን የሚገነዘቡላቸው ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
በትምህርት ቤት ወይም በራሳቸው ንባብ አሊያም ደግሞ እርስ በእርስ በመማማር ሴቶች ራሳቸውን እንዲያስተምሩ እመክራለሁ፡፡ በባል፣ በልማድ፣ በሃይማኖት ወይም በአጠቃላይ በህብረተሰቡ የተቀመጡ መለኪያዎችን ወይም ገደቦችን መቀበል የለባቸውም፡፡ ራሳቸውም ቢሆኑ በራሳቸው ላይ ገደብ ከማስቀመጥ መታቀብ አለባቸው፡፡ ሁሉ ነገር ወዲያውኑ አይሳካምና የሚፈልጉት ነገር ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል መረዳት፤ እንዲሁም ውስጣቸውን ማድመጥ አለባቸው፡፡  
ምንጭ፡- (ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች፤2007)   


            ሚዩዚክ ሜይዴይ ከኢትዮጵስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ “Born a crime” በተሰኘውና በጥላሁን ግርማ “የአመፃ ልጅ” በሚል ወደ አማርኛ በተመለሰው መፅሀፍ ላይ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መፃህፍት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ይካሄዳል፡፡
በዕለቱ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የገቨርናንስና ዴቨሎፕመንት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት መኮንን መንገሻ ሲሆኑ የመፅሀፉ ተርጓሚ ጥላሁን ግርማ በዕለቱ ተገኝተው በውይይቱ ላይ እንደሚካፈሉና የውይይቱ መድረክ በሰለሞን ተሰማ ጂ. እንደሚመራ የገለፀው ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ጋብዟል፡፡

 ደራሲ ገጣሚ ተርጓሚና ፀሐፌ ተውኔት ጋዜጠኛ ነቢይ መኮንን ለማህበረሰቡ ላበረከተው አስተዋጽኦ፣ ለመራው መንገድና ላጋራው እውቀት፤ ምስጋናና አክብሮት ለመስጠት የተዘጋጀው “ነብይ ባገሩ እንዲህ ይከበራል” የምስጋናና የኪነጥበብ ምሽት ትላንት በአዲስ አበባ ቲያትርና ባህል አዳራሽ በድምቀት ተካሄደ፡፡ ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱና የመሶብ ባህላዊ ባንድ መስራችና ዋሽንት ተጫዋች ጣሰው ወንድም ሃሳብ አፍላቂነት በተዘጋጀው በዚህ የምስጋና ምሽት፤ ገጣሚያን ሰዓሊያንና ሙዚቀኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ ገጣሚና ጋዜጠኛ ተፈሪ አለሙ፣ አርቲስት አበባ ባልቻና አዋቂው በሃይሉ ገ/መድህን ስለታላቁ የጥበብ ሰው ነቢይ መኮንን የሚያውቁትን ለታዳሚ ገልፀዋል፡፡
ሰዓሊያን በበኩላቸው ነቢይን እንደ ገጣሚ፣ እንደ ተርጓሚ፣ እንደ ጋዜጠኛና ፀሐፌ ተውኔት ምን ሊመስል ይችላል በሚል በገባቸው መጠን በመድረኩ ላይ በስዕል ገልፀውታል፡፡ በተጨማሪም ገጣሚያኑ ጌትነት እንየው፣ ኤፍሬም ስዩም፣ ተስፋሁን ፀጋዬ፣ አበባው መላኩ ደምሰው መርሻ፣ ሰለሞን ሳህለ፣ ፍሬዘር አድማሱ፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ምስራቅ ተረፈና ረድኤት ተረፈ የግጥም ስራዎቻቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ተፈሪ አለሙና በሃይሉ ገ/መድህን ወግ አቅርበዋል፡፡
“አንድ ሰው በርካታ ስራዎችን ሰርቶ ምንም እንዳልሰራ ሊቆጠር ይችላል፤ ነገር ግን የሰራውን ያበረከተውን መስዋዕትነቱንና አስተማሪነቱን በተዘዋዋሪ መንገድ ለራሱ ለመንገርና ከፍታውን ለማሳየት፣ ከዛም ራሱን መቃኘት እንዲችል እንዲህ አይነት መድረኮች ወሳኝ ናቸው” ያለው ገጣሚ ፍሬዘር አድማሱ፣ ነቢይ መኮንንም በዚህ መድረክ ሲመሰገንና አክብሮት ሲቸረው ራሱንም ይቃኝበታል በሚል የምስጋና መድረኩ መዘጋጀቱን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ገጣሚ ነቢይ መኮንን፤ የአዲስ አድማስ መስራችና ዋና አዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል፡፡

 ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የተፈጸመውን ግድያ አውግዟል

             የሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞ  ተባብሶ መቀጠሉንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች በወሰዱት የሃይል እርምጃ ባለፉት ጥቂት ቀናት አንድ መቶ ያህል ተቃዋሚዎች መገደላቸውን ተከትሎ፣ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፣ ሱዳንን ከህብረቱ አባልነት ማገዱን ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤቱ በሱዳን ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በአዲስ አበባ ያካሄደውን አስቸኳይ ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ሱዳንን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ስልጣኑን በሲቪል ለሚመራ የሽግግር መንግስት እስከሚያስረክብ ድረስ ሱዳን በየትኛውም የህብረቱ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል፡፡
በተቃውሞ እየተናጠችና ወደ እርስ በእርስ ግጭት እያመራች የምትገኘዋን ሱዳን ከቀውስ ለመታገድ የሚቻለው በሲቪል አስተዳደር የሚመራ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሲቻል ነው ያለው የህብረቱ የሰላምና የጸጥታ ምክር ቤት፤ ወታደራዊው ምክር ቤት ይህን አማራጭ በመጠቀም አገሪቱን ከጥፋት እንዲታደግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
ኡመር አልበሽር ከስልጣን ከወረዱ በኋላ እጅግ አስከፊው የተባለው የተቃውሞ ሰልፍ ባለፈው ሰኞ በካርቱም መካሄዱንና የወታደራዊ የሽግግር ምክር ቤት ወታደሮች ባለፉት ቀናት በድምሩ 100 ያህል ተቃዋሚዎችን መግደላቸውን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፤ ይህን ተከትሎም ተቃውሞው ወደ ሌሎች የሱዳን ከተሞች መስፋፋቱንና ውጥረቱ መባባሱን አመልክቷል፡፡
ከትናንት በስቲያ የተወሰኑ ሰራተኞቹን ከሱዳን ያስወጣውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጨምሮ የተለያዩ የአለማችን አገራት መንግስታት ወታደሩ በሱዳን ተቃዋሚዎች ላይ የሚወስደውን የሃይል እርምጃ እያወገዙት እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ ሩስያ በበኩሏ በሱዳን ላይ የሚደረግን የውጭ ሃይሎች ጣልቃ ገብነት እንደምታወግዝና ችግሩ በብሄራዊ መግባባት መፈታት እንዳለበት ያላትን አቋም አስታውቃለች፡፡ አለማቀፉ ተቋም አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፤ ወታደራዊው መንግስት ከሃይል እርምጃዎች እንዲታቀብ አለማቀፍ ጫና ሊደረግ ይገባል ሲል መግለጫ አውጥቷል፡፡
የሱዳን ዶክተሮች ማዕከላዊ ኮሚቴ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ በሳምንቱ በወታደሮች በተፈጸመባቸው ጥቃት ከ108 በላይ ተቃዋሚዎች መገደላቸውንና ከ500 በላይ የሚሆኑትም መቁሰላቸውን ቢያስታውቅም፣ የሱዳን የጤና ሚኒስቴር ግን “ቁጥሩ ተጋኗል፤ የሞቱት 61 ብቻ ናቸው” ሲል ማስተባበሉን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
በሱዳን ህዝባዊ ተቃውሞው ተባብሶ መቀጠሉን ተከትሎ፣ የቱርክ አየርመንገድን (ተርኪሽ ኤርላይንስን) ጨምሮ ወደ አገሪቱ ይጓዙ የነበሩት የግብጽና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አየር መንገዶች በጸጥታ ስጋት ሳቢያ በረራቸውን መሰረዛቸውን አናዶሉ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡

 የህንዷ ከተማ ሙምባይ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ከአለማችን አገራት ከተሞች መካከል እጅግ አስከፊው የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የነበረባት ቀዳሚዋ ከተማ መሆኗን አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
ቶምቶም የተባለው የሆላንድ የጥናት ተቋም በ56 የአለማችን አገራት ውስጥ በሚገኙ 403 ከተሞች ላይ የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በሙምባይ ጎዳናዎች ላይ የሚያሽከረክር አንድ ሾፌር በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ ጉዞው ከሚፈጅበት ጊዜ 65 በመቶ ያህል ተጨማሪ ጊዜ ለማባከን ተገድዷል፡፡
የኮሎምቢያዋ መዲና ቦጎታ በትራፊክ መጨናነቅ ከአለማችን ከተሞች በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በከተማዋ ጎዳናዎች የሚመላለሱ መኪኖች ካሰቡበት ለመድረስ 57 በመቶ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚፈጅባቸውም አመልክቷል:: በትራፊክ መጨናነቅ የፔሩዋ ሊማ በሶስተኛ፣ የህንዷ ርዕሰ መዲና ኒው ደልሂ በአራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጣቸውን የጠቀሰው ተቋሙ፤ ባለፉት አስር አመታት 75 በመቶ በሚሆኑት የአለማችን ከተሞች የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል ብሏል፡፡

  ሳኒ አባቻ በእንግሊዝ ባንክ ያስቀመጡት 267 ሚሊዮን ዶላር ተወረሰ

              በአፍሪካ በነዳጅ ሃብቷ ቀዳሚውን ስፍራ በምትይዘው ናይጀሪያ፣ በየቀኑ በአማካይ 100 ሺህ በርሜል ያህል ድፍድፍ ነዳጅ በህገ ወጦች እንደሚዘረፍ ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በመላው ናይጀሪያ የነዳጅ መተላለፊያ ቱቦዎችን እየሰረሰሩ ከፍተኛ መጠን ያለው ነዳጅ የሚዘርፉ ሰዎች ቁጥር ግማሽ ሚሊዮን ያህል እንደሚደርስ የጠቆመው ዘገባው፤ ይህም አገሪቱ ከነዳጅ ኤክስፖርት የምታገኘው ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ ማድረጉንም አመልክቷል፡፡
በናይጀሪያ ነጋ ጠባ የሚዘረፈውና በመቶዎች በሚቆጠሩ ትናንሽ የነዳጅ ማጣሪያዎች እየተጣራ በህገ ወጥ መንገድ ለሽያጭ የሚቀርበው ነዳጅ በገንዘብ ሲተመን የአገሪቱን የበጀት ጉድለት ሙሉ ለሙሉ የመሸፈን አቅም እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፤ በአገሪቱ የሚገኙ የነዳጅ ኩባንያዎችም የዝርፊያው ሰለባ መሆናቸውን ገልጧል፡፡
ታዋቂው ሼል ኩባንያ በናይጀሪያ ባለፈው የፈረንጆች አመት (2018)፣ በየቀኑ 11 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በወንጀለኞች መዘረፉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜና ደግሞ፣ የቀድሞው የናይጀሪያ ፕሬዚዳንት ሳኒ ኣባቻ፣ በስልጣን ዘመናቸው በሙስና ያፈሩትና በእንግሊዝ ውስጥ በሚገኝ ባንክ ከዝነውት የነበረ 267 ሚሊዮን ዶላር እንዲወረስ መወሰኑ ተዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1993 አንስቶ በሞት እስከተለዩበት 1998 ድረስ አገሪቱን የመሩትና በአምባገነንነታቸው የሚታወቁት ሳኒ ኣባቻ፤ በህገ ወጥ መንገድ ከአገር አስወጥተውታል የተባለውና ላለፉት 5 አመታት እንዳይንቀሳቀስ ታግዶ የነበረው ይህ ገንዘብ፣ ለናይጀሪያ ለአሜሪካና ለእንግሊዝ እንደሚከፋፈል ተነግሯል፡፡


Page 11 of 440