Administrator

Administrator

Saturday, 28 March 2020 11:42

ሰውየው ከውሻው ጋር

 ሰውየው ከውሳው ጋር እየተጓዘ ነው፤ የአካባቢውን ውበት በተመስጦ እያደነቀ:: ድንገት ግን አንድ ነገር ተከሰተለት-ለካንስ ሞቷል፡፡ አዎን…ለካንስ እሱም ሆነ ይሄ እግሩ ስር ኩስኩስ የሚለው ውሻ ከሞቱ ሰነባብተዋልና፡፡ መሞቱን መዘንጋቱ ደንቆታል፡፡ ምናልባትም ገና በቅርቡ በመሞቱ ይሆን? ይሆናል፡፡ ብቻ እሱና ውሻው ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ እናም ከአንድ ካማረ ቤተ መንግሰት ከሚመስል፣ የተሰራበት ዕምነ በረድ ከሚያንፀባርቅ ትልቅ ህንፃ አጠገብ ሲደርስ ቆመ፡፡ በትልቅ ኮረብታ አናት ላይ በታላቅ ግርማ ሞገስ ጉብ ያለው ህንፃ ከፊቱ በአንፀባራቂ ቅስት አሸብርቋል፡፡ በቅስቱ ስር የሚያምር መግቢያ ተመለከተ፡፡ ወደ መግቢያው የሚወስደው መተላለፊያ በወርቅ ተለብጧል፡፡ እንዴት ያለ ቅጥር ነው ሲል አሰበ፡፡ በመተላለፊያው ወደ በሩ ሲጠጋ፣ የቅጥሩ ጠባቂ የመሰለ ሰው ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ፤ ይህ ቦታ ምን የሚሉት ቦታ ይሆን?” ጠየቀ ሰውየው፡፡
“መንግስተ ሰማያት ነው ጌታው!” ሲል መለሰ ጠባቂው፡፡
“ግሩም ነው…” አለ ሰውያችን፤ “ጥቂት ውሃ ማግኘት እንችላለን? እኔና ውሻዬ በውሃ ጥም ጉሮሯችን እንዴት ተቃጥሏል መሰለህ…”
“ምን ችግር አለ…” አለ ጠባቂው፤ “አሁኑኑ ጥም ቆራጭ ቀዝቃዛ ውሃ ይቀርብላችኋል::”
ጠባቂው ይህን ብሎ በሩን እየከፈተ፤ “ግን ጌታው…አለ፤ “ወደዚህ ወደ መንግስተ ሰማያት ገብተህ ቀዝቃዛ ውሃ ብቻ ሳይሆን ሁሉንም በረከት መቋደስ ትችላለህ፤ ግን ወደዚህ መግባት የምትችለው ብቻህን ነው:: የቤት እንስሳም ሆነ ሌላ ተቀጥላ ጓደኛ ይዞ መግባት አይቻልም” አለ ሰውዬው እግር ስር ኩስኩስ እያለ የሚከተለውን ውሻ እየተመለከተ፡፡
ሰውዬው ዕጢው ዱብ አለ፡፡ ትንሽ አመነታ፡፡ ግን ወሰነ፡፡ ጓደኛዬን ውሻዬንማ ጥዬ አልገባም ብሎ በውሃ ጥም ጉሮሮው እየነደደ፣ ጀርባውን ለሚያምረው ህንፃ ሰጥቶ ጉዞውን ቀጠለ፡፡ ከረጅም አድካሚ ጉዞ በኋላ ደግሞ ሰውዬውና ውሻው ከአንድ ኮረብታ ቦታ ደረሱ፡፡ ከኮረብታው ስር ወደ አንዳች ቅጥር ግቢ የሚያመራ በጭቃ የላቆጠ የእግር መንገድ ይታያል፡፡ መንገዱ በእርሻ ውስጥ የሚያልፍ ሆኖ መላው ቅጥሩ አንዳችም አጥር የለውም፡፡ በሩ መቼም ተዘግቶ የሚያውቅ አይመስልም፡፡
መቼም ተዘግቶ ወደ ማያውቀው በር ሲጠጋ፤ ዛፍ ስር ደገፍ ብሎ መጽሐፍ የሚያነብ አንድ ሰው ተመለከተ፡፡
“ይቅርታ የኔ ወንድም፤ ጥቂት ውሃ ይኖርሃል…? በውሃ ጥም…” ከማለቱ፤ በቅጥር ግቢው ውስጥ ያለው ሰውዬ፤ “እንዴታ…” አለ፤ “እዛ ጋ ቧንቧ አለልህ፤ ሄደህ የፈለግከውን ያህል መጠጣት ትችላለህ፡፡”
ሰውዬው ቀጠለና ጠየቀ፤ “ይሄ ጓደኛዬ…” ብሎ ወደ ውሻው እየጠቆመ፤ “ውሃ ጥሙ ክፉኛ በርትቶበታል፤ እሱም ገብቶ መጠጣት ይችል ይሆን?”
“ይችላል” አለ ሰውዬው፤ “እንዲያውም ከቧንቧው አጠገብ መጠጫ አለልህ፡፡” ሰውዬውና ውሻው ተደስተው ወደ ቅጥሩ ገብተው ጥማቸው እስኪቆርጥ ከጠጡ በኋላ፣ ወደ ሰውዬው ተመልሰው መጡና፤ ሰውዬው እንዲህ ሲል ጠየቀ፤ “ለመሆኑ ይህ ቦታ ምን የሚሉት ቦታ ይሆን?”
“መንግስተ ሰማያት ነው” ሲል መለሰ ሰውዬው፤ አይኖቹን እንኳ ከሚያነበው መጽሐፍ ላይ ሳይነቅል፤ በታላቅ የዕረፍት ስሜት ዛፍ ስር ደገፍ ብሎ በተቀመጠበት፡፡
“ይሄማ እንዴት ሊሆን ይችላል” አለ ሰውዬው ግራ ተጋብቶ፤ “ቅድም ያጋጠመኝ ያማረ ህንጻም፤ መንግስተ ሰማያት ነው ብለውኛል፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል?”
“እህ…” አለ ዛፉ ስር የተቀመጠው ሰውዬ፤ መጽሐፉን እልባት አስይዞ እያጠፈ፡፡
“ያ ታላቅ ቅስት ያለው ባለ እምነበረዱ ሕንፃ…? መንገዱ በወርቅ የተለበጠው…? ከሱ ህንጻ በማምለጥህ ደስታ ሊሰማህ ይገባሃል፡፡ እሱ ህንጻ አላወቅከውም እንጂ፣ ንጽህናህ አዳነህ እንጂ ገሃነም ነው” አለ፡፡
“እንዴት” አለ ሰውዬው በጉዳዩ ይበልጥ ግራ ተጋብቶ፡፡ “እሺ ይሁን ይሄ መንግስተ ሰማያት ይሁን፤ ግን በስማችሁ ሲነግዱ እንዴት ዝም አላችሁ?”
“እንዴት ዝም አላችሁ ነው ያልከኝ…” አለ ሰውዬው፤ “ዝም ማለት ብቻ አይደለም፣ እንዲያውም በጉዳዩ ደስተኞች ነን፡፡ አየህ…”አለ ሰውዬው፤ “ያ ላዩን ያማረ ህንጻ፣ ያ ገሃነም፣ ጓደኞቻቸውን ጥለው የሚሄዱ፣ ወዳጆቻቸውን በቁርጥ ቀን ጥለው የሚሄዱ ሰዎችን አጣርቶ ስለሚወስድልን፣ ደስተኞች ነን፡፡”
(ምንጭ፡- “ግሩም  የዓለማችን ምርጥ ታሪኮች”)

    ከዕለታት አንድ ቀን እመት ጦጢት አንድ ዋርካ ላይ ጥፍር ተደርጋ ታሥራ፣ አላፊ አግዳሚውን “እባካችሁ ፍቱኝ ወይም አስፈቱኝ” እያለች ትለምናለች፡፡
በመጀመሪያ የመጣው አንበሳ ነው፡፡
አንበሳ - “እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ነው የታሠርሽው?” ሲል ጠየቃት፡፡
ጦጢትም - “አልበላም ብዬ ነው የታሠርኩት” አለች፡፡
አንበሳም - “አንቺ እንኳን ብልጥ ነበርሽ፡፡ ምን ሆነሽ ነው ያልበላሽው? በይ ሥራሽ ያውጣሽ” አላትና ሄደ፡፡
ቀጥሎ የመጣው ነብር ነው፡፡
“እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ታሠርሽ፡፡
ጦጢት - “ብይ ብባል አልበላም ብዬ ነው”
ነብር - “አንቺ ብልጥ አልነበርሺም እንዴ? አብረሽ ሌላ ጥፋት አጥፍተሽ ነው እንጂ አልበላም ስላልሽ ብቻ አትታሰሪም፡፡ በይ ሥራሽ ያውጣሽ” ብሏት አለፈ፡፡
ቀጥሎ ጦጢት አጠገብ የደረሰው ቀበሮ ነበር፡፡
ቀበሮም - “አመት ጦጢት፣ ምን አጥፍተሽ ነው የታሠርሽው?”
ጦጢት - “ከሰው ማሣ የተሰረቀ አተር ካልበላሽ ብለውኝ እምቢ ስላልኳቸው እነ ዝሆን ናቸው ያሠሩኝ!”
ቀበሮም - “አይ እመት ጦጢት፣ አንቺን እናውቅሻለን’ኮ እንዲያውም ሳትጠሪ ሰው ማሣ ገብተሽ የምትሠርፊ አይደለሽ እንዴ? ሌላ ያጠፋሽው ጥፋት ቢኖር ነው” ብሏት አለፈ፡፡
ቀጠለና ዝንጀሮ መጣ፡፡
ዝንጀሮ - “እመት ጦጢት ምን አርገሽ ነው የታሠርሺው?”
ጦጢት - “አልበላም ብዬ!”
ዝንጀሮም - “አንቺ አጭበርባሪ ነሽ፡፡ እናውቅሻለን ካገኘሽ የማንንም ሰብል አትምሪም! አንድ የሆነ ያጠፋሽው ሌላ ጥፋት ቢኖር ነው!”
ዝሆን በተራው ከጫካ ሲመለስ ጦጢት ታሥራ አየ፡፡
“እመት ጦጢት ምን ሆነሽ ታሠርሽ?”
“አልበላም ብዬ”
“ምን አልበላም ብለሽ?”
“ባቄላ”
“አሄሄሄሄ! አንቺ ባቄላ አይተሽ ዝም ብለሽ ልታልፊ? አታጭበርብሪ!” አላትና እየሳቀባት ሄደ፡፡
ቀጠለና ድኩላ መጣ፡፡
ድኩላም፤
“እመት ጦጢት ምን አጥፍተሽ ታሠርሽ?”
“ከሰው አዝመራ ገብቼ እሸት ስበላ አግኝተው፤ አሰሩኝ”
“ባለቤቱ ሲመጣ አጣርተን ነው የምናስፈታሽ!” ብሏት ሄደ፡፡
በመጨረሻ አያ ጅቦ ይመጣል፡፡
አያ ጅቦም ሌሎቹ እንደጠየቋት ጠየቃት፡፡
አያ ጅቦ- “እንዴ እመት ጦጢት! ምን ሆነሽ ነው የታሠርሺው?”
ጦጢትም - “ብዙ መንገድ መጥቼ እዚህ ስደርስ ራበኝ! “እባካችሁ መንገደኛ ነኝ፡፡ ርቦኛል” ብላቸው፤ “ዞር በይ ከዚህ አሉኝ፡፡ እነሱ ሲዘናጉልኝ ጠብቄ ልሰርቅ ስገባ ያዙኝና እንደምታየው አሠሩኝ፡፡ አሁን ግን አሳዘንኳቸውና “አስኮናኝ ነሽ! በይ ብይ አሉኝ!” እኔም ተራዬን አልበላም! አልኳቸው”
አያ ጅቦም፤
“እንደሱ ከሆነማ እኔ ስለራበኝ ባንቺ ቦታ ልታሠርና ልብላ” አላት፡፡
“በጣም ጥሩ” አለችው፡፡
አያ ጅቦም ጦጢትን ፈታትና፤ በሷ ገመድ ገባ! ጦጢትን ያሠሯት ሰዎች መጡ፡፡ በእሷ ቦታ አያ ጅቦን አገኙት፡፡ እስኪበቃው ድረስ ቅጥቅጥ አደረጉት፡፡
“እባካችሁ አይለምደኝም ልቀቁኝ!” ብሎ ለመናቸውና ለቀቁት፡፡
አያ ጅቦ እስከዛሬ ድረስ እመት ጦጢትን አያምናትም፡፡ እንዲያውም እይዛታለሁ ብሎ ብዙ ጥሯል፤ ግን አልተሳካለትም!
***
የሠራነውን ደግ እንጂ ክፉውን አንርሳ፡፡ ደግ የተሠራለት ቢረሳ፤ ክፉ የተሠራበት ምን ጊዜም በደሉን አይረሳም! የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም ይባላል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን፤ የዚህን ግልባጭ በጥበቡ ተቀኝቶበታል፡፡ እንዲህ ሲል፡-
ትቸዋለሁ ይተዉኝ
አልነካቸውም አይንኩኝ
ብለህ ተገልለህ ርቀህ
ዕውነት ይተዉኛል ብለህ
እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?!
የተወጋ በቅቶት ሲተኛ፣ የወጋ መች እንቅልፍ አለው
የጅምሩን ካልጨረሰው፡፡
እና በእኔ ይሁንብህ
እንቅልፍ ነው ‘ሚያስወስድህ!
“እንቅልፍ ነው ሚያስወስድህ”
(እሳት ወይ አበባ)
የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የምንወደውን ሰላምታና መጨባበጥ እንሰዋ ዘንድ ሆነ፡፡ ኮሮና ቫይረስ ቀሳፊ ነው! ሲሆን ሲሆን ለኮሮና ብቻ ብለን ሳይሆን ስለ ንፅህናችን መቆርቆርን ባህል እናድርግ! እንዳጋጣሚ ሆኖ ኮሮና መምጣቱ “ሳይደግስ አይጣላም” እንደሚባለው ነው - A Blessing in disguise እንደማለት ሆነ ማለት ነው፡፡ እነሆ ለራስም ለሌላውም ማሰብ ያለብን አሳሳቢ ሰዓት ነው፤ ለመዘጋት ጊዜ የለም! ለእንዝህላልነት ቅጽበት የለም! የሁላችንም ሥጋት፣ የሁላችንም ፍርሃት የተከሰተበት ሰዓት ነው! ዛሬን የአሥራ አንደኛው ሰዓት ክፍልፋይ ሰኮንዶቹ ብቻ የቀሩበት አድርገን እንጨነቅ! የግል ብቻ አይደለም፤ የቡድንም ብቻ አይደለም! የህብረተሰብ ጉዳይ ነው! “የአንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት” ብለን ነበር ዱሮ፡፡
ዛሬ ግን የሁላችንንም ቤት በአንድ ጊዜ የሚያንኳኳ፣ ሁላችንም ላይ ያነጣጠረ ቀሳፊ ጊዜ መጥቷል፡፡ ራስን ብቻ ሳይሆን ዓለምን የሚያባብስ የጭንቅ ሰዓት ነው! በዚህ ሰዓት የሁላችንንም ሰቆቃ ሥራዬ ብለን የምንደማመጥበት፣ ህብረታችንን የሚያናጋ፣ ነጋችንን የሚያጨልም እጅግ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ነን፤ እንተሳሰብ እንመካከር!
ምንም እንኳ የበሽታ ምርጫ ውስጥ የምንገባ ባይሆንም፣ የክፉም ክፉ እንዳለ ማስተዋል ሊሳነን አይገባም፡፡ ከጽንሱ አንስቶ እስከ የክፉ ገጽታ ስትጭቱ፣ የቅድመ ምርመራውና የመጣራቱ ሂደት ድረስ እጅግ አንገብጋቢ የንክኪ አደጋ መኖሩን በጥሞና እናሰላስል፡፡ ነፃ መሆን ወይም ኔጋቲቭ መሆን ምንጊዜም ከጥንቃቄ ሊገታን በጭራሽ አይገባም፡፡ አሁንም ያለን የዕለቱ መልዕክት፡-
“ጥንቃቄ!
ጥንቃቄ!!
ጥንቃቄ!!!
እናድርግ!” የሚለው ነው! የሁላችንም ያልተቆጠበ ጥረት ያስፈልጋል፡፡ ከቶውንም በእርዳታ ያገኘነውን ናሙና መውሰጃና መመርመሪያ፣ እንዲሁም መከላከያ ቁስን፤ በአግባቡ ሥራ ላይ እናውል!!
ትላንትና መነካካትን እንደፆምን፣ ዛሬ መቀራረብንም እንፁም!!!
የሠራውን የረሳ ዋጋውን ያገኛል! ሥራውን ያስታወሰ መዋያውን ያውቃል የሚባለውን ለአፍታም ቢሆን አንዘንጋ! አንዘናጋ! አንዘናጋ! ከአደጋው ይሰውረን!!!


   የኮሮና ቫይረስን በሳይንሳዊ ምርምር በተደገፈ የሀገር በቀል እውቀት ከዘመናዊ ሳይንስ ጋር በማቀናጀት፣ ቫይረሱን ለማከም የተሰራው መድሃኒት መሰረታዊ የምርምር ሂደት በማለፍ ተደጋጋሚ የቤተ ሙከራ ሞዴሊንግ ሂደቶችን በስኬት ማለፉ ተገልጿል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር እንዳስታወቀው፤ ምርምሩ የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ መከሰቱ ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ በሃገር ውስጥና ከሃገር ውጪ ከሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ጋር በመሆን ሲካሄድ የቆየ ሲሆን ተደጋጋሚ የምርመር ሂደት አልፎ ወደ ምርትና ቀጣይ የእንስሳት ፍተሻና ክሊኒካል ፍተሻ ስራዎች እንዲሸጋገር ተደርጓል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር ኢንጂ.)፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ፣ ከኢትዮጵያዊያን የባህል ሃኪሞችና የህክምና ተመራማሪዎች ጋር በመሆን የሀገር በቀል እውቀቶችን በሳይንሳዊ ሂደቶች በማሳለፍ፣ ለዘመን አመጣሹ ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ - 19) ወረርሽኝ ህክምና የተዘጋጀውን መድሃኒት ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችላቸውን ስራ በመስራት ላይ ይገኛሉ።
መድሃኒቱ የመከላከል አቅም የሚጨምር፣ መርዛማነት የሌለውና አዋጭነቱ የተረጋገጠ እንደሆነም ተገልጿል፡፡


      የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በጥሬ ገንዘብ ብር 3,500,000 (ሦስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ ብር ለገሰ

            በአለም ላይ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ በቂ ክትትልና ትኩረት ተሰጥቶት አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የሚያመጣው ጥፋት እጅግ አሰቃቂ መሆኑን ተቋማችን ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ ግንዛቤ ወስዷል፡፡ ይህንኑ ሁኔታ ለመቋቋም መጀመሪያ ራስንና አካባቢን የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት መንቀሳቀስ እንደሚኖርብን በማመን፣ የስራ መርሀ ግብር በመንደፍና በየፋብሪካዎቻችን አንድ አንድ ግብረ ሃይል በማቋቋም፣ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመርን ውሎ አድሯል፡፡
በዚሁ መሰረት ፋብሪካዎቻችን በሚገኙበት በአዲስ አበባ፣ በኮምቦልቻ፣ በሃዋሳ፣ በማይጨው፣ በጉብሬ ወልቂጤና ዝዋይ የራሳችንን ሰራተኞችና የአካባቢውን ህብረተሰብ በመጨመር ፤ ችግሩን በጥልቀት እንዲረዱና ግንዛቤ እንዲኖራቸው ተደርጓል፤በየፋብሪካዎቻችን በሁሉም መግቢያ በሮች ላይ ሰራተኞቻችንም ሆነ እንግዶች በሙቀት መቆጣጠሪያ እየተለኩና በስነ-ስርዐት እንዲታጠቡ በማድረግ እንዲገቡ እየተደረገ ይገኛል፤በቂ ርቀት በአቀማመጥ ወቅት እንዲኖር ለማስቻል የሰራተኞች ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል፤በየፋብሪካው እንግዳውና ሰራተኞች የሚስተናገዱበት የሰራተኞች ክበብ ለጥንቃቄ ሲባል ተዘግቷል፤
ፋብሪካዎቻችን በሚገኙበት አካባቢ፣ ከህብረተሰቡና ከአካባቢው የስራ ሀላፊዎች ጋር በመሆን፣ የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታዎች አድርገናል፤
በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚከናወኑ ስራዎች ደግሞ ለጤና ሚኒስቴር
በጥሬ ገንዘብ ብር 3,500,000 (ሦስት ሚሊዮን አምስት መቶ ሺ) ከመለገስም አልፎ በየከተሞች የሚገኙትን የማስታወቂያ ግዙፍ ሰሌዳዎቻችንን፣ የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መልእክቶች እንዲያስተላልፍበት  ፈቅደናል፡፡
እንዲሁም በስራ አጋሮቻችን ለስራ የምንጠቀምባቸው ከፍተኛና መለስተኛ የጭነት መኪናዎች በተፈለጉበት ጊዜ ሁሉ ለማቅረብ ዝግጁ ነን፡፡
ምንግዜም ቢሆን ችግርን አሸንፈን የመወጣት ባህላችንን ዛሬም እንደምንደግመው ቢ.ጂ.ኣይ ኢትዮጵያ ፍጹም እምነቱ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለኢትዮጵያ ህዝብ ሙሉ ጤንነትን
እየተመኘ፣ ይሄንን ችግር በጋራ በአጭር ጊዜ እንደምንወጣው ተስፋ በማድረግ ጭምር ነው፡፡
ቢ.ጂ.ኣይ ኢትዮጵያ

    ሁኔታዎችን እያየን ድጋፉን እንቀጥላለን›› - አቶ አቤ ሳኖ የባንኩ ስራ አስኪያጅ

            የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለውንና የአለም ስጋት የሆነውን ኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19)ን ቀድሞ ለመከላከል የሚረዳ የ10.ሚ ብር ድጋፍ ለጤና ሚኒስቴር ሰጠ፡፡ ባንኩ ትላንት በዋና መሥሪያ ቤቱ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች፣ የጤና ሚኒስትር ዴኤታዋና የባንኩ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት ነው ድጋፉን ያስረከበው፡፡
የባንኩ ስራ አስኪያጅ አቶ አቤ ሳኖ ድጋፉን ለጤና ሚኒስትር ዴኤታ ካስረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር ባንኩ ኮሮና ቫይረስ መከሰቱን ተከትሎ ስርጭቱን ለመቆጣጠር ያደረገው የመጀመሪያ ድጋፍ መሆኑን ገልፀው ሁኔታው እየታየ ድጋፉ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ በበኩላቸው ችግሩን ለመቆጣጠር በሚደረገው ርብርብ ፈጣን ምላሽ የሰጠውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን አመስግነው ይህን ውሳኔ በፍጥነት የወሰኑትን የባንኩን አመራሮች አመስግነዋል፡፡ የባንኩን አርአያ በመከተል ሌሎችም የመንግሥትና የግል ተቋማት ለዚህ አገራዊ ጥሪ ምላሽ እንዲሰጡና ችግሩን ለመቅረፍ የሚደረገውን ትግል እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

     ገርጂ መብራት ሀይልና ጀሞ የሚገኘው ኦልማርት ሱፐር ማርኬት፤ በአገራችን የኮሮና ቫይረስን  መከሰት ተከትሎ፣ ለአቅመ ደካሞች ከመቶ ሺህ በላይ ብር የሚያወጡ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን ለገሰ፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ይህንን በጎ አድራጎት ያደረገው በተለይም ቫይረሱ በብዛት ያጠቃቸዋል ለተባሉት አረጋዊያን ሲሆን በዚህም ምክንያት ለመቄዶኒያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን ማዕከል፣ ለሜሪ ጆይና ገርጂ መብራት ሀይልና ጀሞ ቅርንጫፎቹ ለሚገኙበት ሁለት ወረዳዎች አረጋውያን ለግሷል፡፡
ድርጅቱ በረኪና፣ ዲቶል፣ ላይፍ ቦይ ሳሙና፣ የልብስ ሳሙናና ላርጎ ፈሳሽ ሳሙናዎችን የለገሰ ሲሆን ዓለም አቀፍ ስጋት የሆነው ኮሮና ቫይረስ በአገራችን ሲቀሰቀስ እጅን አጣጥፎ ከመቀመጥ ሁሉም እንደ ዜጋ የሚጠበቅበትን በማድረግና በመረዳዳት ይህን ክፉ ቀን ማለፍ ይገባል ብለዋል የኦልማርት ሱፐር ማርኬት ቃል አቀባይ ወ/ሪት ዘኢማ አህመድ፡፡
ሱፐር ማርኬቱ ያደረገውን በጎ አርአያ ተከትለው፣ ሌሎችም የአቅማቸውን በማድረግ የቫይረሱንና ስርጭት በመቆጣጠር በጋራ ታሪክ መስራት አለብን ብለዋል፡፡
የሜሪ ጆይ የተራድኦና የልማት ማህበር፣ የመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማን መርጃ ማዕከል፣ እንዲሁም ሱፐር ማርኬቶቹ የሚገኙባቸው ሁለት ወረዳዎች ተወካዮች ገርጂ መብራት ሀይል በሚገኘው የሱፐር ማርኬቱ ዋና መስሪያ ቤት ተገኝተው ቁሳቁሶቹን ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፣ ሱፐር ማርኬቱ በተለይ ቫይረሱ በቀላሉ የሚያጠቃቸውን አረጋዊያን ታሳቢ በማድረግ ለቅድመ ጥንቃቄ የሚረዳቸውን የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁስ በመለገሱና በቀድሞ ደራሽነቱ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው ሌላውም በዚሁ አርአያነት ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
አረጋውያንን የመታደግ ሥራ ኮሮና ቫይረስ በዕድሜ ገፋ ያሉና ሌላ የጤና ችግር ያለባቸውን እንደሚያጠቃ መነገሩን ተከትሎ መቄዶንያ የሚደግፋቸውን ከ2 ሺህ በላይ አረጋዊያንና የአዕምሮ ሕሙማን ከቫይረሱ ለመጠበቅ ምን አይነት ሥራ እየተሰራ ነው በሚል ላቀረብነው ጥያቄ፣ በመቄዶኒያ የማዕከሉ ነርስ ዮናስ ሙሉጌታ ሲመልሱ፤ በአሁኑ ወቅት የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አዳዲስ አረጋዊያን ወደ ማዕከሉ ማስገባት ማቆማቸውን፣ ድንገተኛና ከባድ የጤና ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ሕሙማንን ወደ ተለያዩ ሆስፒታሎች እንደማይወስዱ፣ ጎብኚዎች ሲመጡ በአስተናጋጆች በኩል የሚለግሱትን ለግሰውና ቃል ገብተው ከመሄድ ውጭ አረጋዊያኑን መጎብኘት መከልከሉንና የማዕከሉ ሰራተኞች ለሥራ ወጥተው ሲገቡ፣ የእጅ ማስታጠብና የአልኮል አቅርቦት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ፤ የአረጋውያኑን ክፍሎች በአልኮልና በበረኪና በማፅዳትና በማናፈስ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነርስ ዮናስ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለቅድመ መከላከል ሥራ የሚረዱ ቁሳቁሶችን በማቅረብ በኩል በተቋምም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ድጋፎች እየመጡ መሆኑን የገለፁት ባለሙያው፤ ከተቋማቱ መካከል ሐሙስ ከሰዓት በኋላ ልገሳ ያደረገው ኦልማርት ሱፐር ማርኬት ይገኝበታል ብለዋል፡፡   


  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰውዬ ሠፈር ውስጥ ሲዘዋወር አንድ መንገደኛ ያገኝና አብረን እንሂድ ይባባላሉ፡፡
“ወዴት ነው የምትሄደው ወዳጄ?” አለ የሠፈሩ ሰውዬ፡፡
“ዘመድ ለመጠየቅ ወደ ሩቅ አገር እየሄድኩ ነው” አለ መንገደኛው፡፡
“እኔም የምሄደው ቅርብ አይደለም”
“የተወሰነ ርቀት አብረን እንጓዛ?”
“ደስ ይለኛል”
አብረው መሄድ ጀመሩ፡፡
ሠፈር ውስጥ የሚዘዋወረው ሰው ጨዋታ ቀጠለ፡-
“ልጆች አሉህ ወዳጄ?”
“አዎን፤ ብዙ ልጆች አሉኝ”
“ታዲያ አንዳቸው እንኳን ለምን አብረውህ አልመጡም?”
“ምን እባክህ፤ የዛሬ ልጆች እነሱ የሚሄዱበትን እንጂ አንተ የምትሄድበትን አያደንቁም፡፡ እነሱ ወደሚሄዱበትም አንተ የመሄድ ፍላጐት ብታሳይ በቀላሉ አያበረታቱህም፡፡”
“ይሁን፡፡ መታገሥና ዕድገታቸውን መከታተሉ ይሻላል፡፡”
“አዎን ምርጫ የለንም፡፡”
ጥቂት እንደ ተጓዙ አጥር ላይ ያለ አንድ አውራ ዶሮ ይጫሃል፡፡
ይሄኔ አንደኛው መንገደኛ፤
“ወዳጄ፤ አሁን ይህ አውራ ዶሮ እዚህ አጥር ላይ ሆኖ ሲጮህኮ መንግሥተ ሰማይም ውስጥ ልክ ይሄንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ ይጮሃል” አለ፡፡
ሁለተኛው መንገደኛም፤
“ወዳጄ ትቀልዳለህ እንዴ? እንደ ዶሮ አይነት ልክስክስ ቆሻሻ ነገር እንዴት ብሎ ነው መንግሥተ ሰማይን የመሰለ ንጹህ ቦታ የሚገባው?”
አንደኛው፤
“አይደለም ወዳጄ ይህ አውራ ዶሮ መንግሥተ ሰማይ ውስጥ ሲገባ ጭራውን ወደ ሲዖል አፉን ወደ መንግሥተ ሰማይ አድርጎ ነው! የሚጮኸው” አለው፡፡
ሁለተኛው መንገደኛም፤
“አዬ፤ ነገሩን እንዲህ በቀላሉ አትየው፡፡ የሲዖል እሳት የወዛ አይምሰልህ፡፡ እንኳን እሳቱ ወላፈኑም እንኳ ዶሮ ላባ አግኝቶ ደረቅ እንጨት ቢያገኝ ዝም አይልም››
አንደኛው ትዕግሥቱ አለቀና፤
“ዎዎ! እኔ ምን ቸገረኝ - የአባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንበገብገው!” ብሎት ሄደ፡፡
*     *    *
ከማይሆን ተሟጋች ጋር ትክከለኛም ሙግት ቢሆን የምንሟገተው ከንቱ ድካም ነው:: ወደ ራሱ ስሜት እንጂ ወዴ ትክክለኛው አመክንዮ ስለማይወስደን በከንቱ ጊዜያችንን፣ መልካም አስተሳሰባችንና ስብዕናችንን ያባክንብናል፡፡ ከቶውንም በትግዕስት በጥሞናና በበሰለ አካሄድ ያልተቃና የአገር ነገር ታጥቦ ጭቃ የሚሆን ነው፡፡
ነገርን እንደ በቀቀን ስለደጋግምነው ብቻ ወደ ዕውነቱ መቀረቢያውን ቀንዲል ለኮስን ማለት አይደለም፡፡ ሞቅ ደመቅ እያደረግን የምናሰማምራቸው ጉዳዮች አንድም በሙያዊ ብቃት፣ አንድም በልባዊ ፅናት ካልታገዙ ደጋግመው ለእንቅፋት እንደሚዳረጉን ግልጽና ግልጽ ነው፡፡
“ትላንትና ማታ ወደ ቤትህ ስትገባ በርህ ላይ የመታህ እንቅፋት ዛሬም ከመታህ ድንጋዩ አንተ ነህ”  ይላሉ ቻይናዎች፡፡ በአገራችን እንቅፋት የሆኑ አያሌ ሳንካዎች አሉ፡፡ እንኳንስ ተነጣጥለን አንድና ህብር ሆነንም በቀላሉ ነቅለን የማንጥላቸው ያመረቀዙና አዲስ ያቆጠቆጡ ብዙ ችግሮች አሉብን፡፡ ዛሬም ደግመን ልንለው የምንሻው እንደ ተጠቃሽ አነጋገር አለ፡-
If Your plan is for a year, plant Teff.
If Your plan is for fire years plant  eucalyptus tree.
If Your plan is forever, educate your child.
ስንተረጉመው፤
“እቅድህ ለአንድ ዓመት ከሆነ ጤፍ ዝራ፡፡
እቅድህ ለአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡
እቅድህ ለዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር!!”
ማለት ነው፡፡
ምንጊዜም ሕይወት አዳጊ እንቅስቃሴ፣ አዳጊ ሂደት መሆኑን አትዘንጋ፡፡ Life is an incremental Process  እንዲሉ፡፡ እኛ ብንቆምም አይቆም፡፡ እንሽሽህ ብንለውም አይሸሽም ሰልጠንና ጨከን ብሎ መጓዝ ብቻ ነው መድሀኒቱ፡፡ ኮስተር መረር ማለት ነው መፍትሔው፡-
“እረ ምረር ምረር፣ ምረር እንደቅል
አልመርም ብሎ ነው፣ ዱባ እሚቀቀል”
የሚለው የአገራችን ሰው ወዶ አይደለም፡፡ ያም ሆኖ ጊዜውን ጠብቆ ሊፈነዳ ያላጠነጠነ እንቡጥ በግድ ለቅቄ አፈካዋለሁ ብንል ውጤቱ ማፍካት ይለዋል መጽሐፉ፡፡
በዚህም አልን በዚያ የምንሄድበትን አቅጣጫ ለመወሰን ዋንኛው ዘዴ ሶስት መንገዶች ማስተዋል ነው!! መሞከር ነው፡፡ ሁለተኛውም መላ መሞከር ነው! ሦስተኛውም መላ መሞከር ነው!
“እጅህን ባህሩ ውስጥ ክተት፡፡
ካገኘህ አሳ ትይዛለህ፡፡
ካጣህ እጅህን ታጥበህ ትወጣለህ!!” የሚባለው ታላቅ ቁም ነገር በሙከራችን ተስፋ እንዳንቆርጥ የሚመክረን ይሄንኑ ነው!! አለም በቅርብ ዘመናት ታሪኳ ገጥሟት በማያውቀው “ኮሮና” የተሰኘ አስከፊ የጥፋት ማዕበል መመታቷን፣ ነጋ ጠባ ከዳር እስከ ዳር በሚያጥለቀልቃትና ልትገታው አቅም ባጣችለት ገዳይ ወረርሽኝ ክፉኛ መፈተኗን ቀጥላለች፡፡
ከቻይና የተነሳውና ቀስ በቀስ መላውን አለም ማዳረሱን የቀጠለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፤ ቀናት አልፈው ቀናት ቢተኩም፣ ሳምንታት ቢፈራረቁም ይህ ነው የሚባል ልጓም ሳይገኝለት በፍጥነት መስፋፋቱንና በርካቶችን መቅሰፉን ተያይዞታል፡፡
አሁን ኮሮና የጤና ጉዳይ ከመሆን አልፎ የሰውን ልጅ በህልውና ስጋት ውስጥ የከተተ፣ መንግስታት፣ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጡት አንገብጋቢ ጥያቄ ሆኖ እረፍት የነሳ፣ መላውን አለም ክፉኛ እየፈተነ የሚገኝ የጤናም፣ የኢኮኖሚም፣ የፖለቲካም፣ የሁሉም ነገር ጉዳይ ሆኗል፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 176 አገራትና ግዛቶች ውስጥ ከ230 ሺህ 715 በላይ ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከ9 ሺህ 390 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት ደርጓል፡፡
ቫይረሱ የተቀሰቀሰባት ቻይና እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ 80 ሺህ 928 ያህል ዜጎቿ በኮሮና የተጠቁባት ሲሆን ከ3 ሺህ 245 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ለሞት ተዳርገውባታል፡፡
በአውሮፓ ኮሮና እጅግ ከፍተኛውን ጥፋት ባደረሰባት ጣሊያን፣ 35 ሺህ 713 ሰዎች ተጠቅተው፣ 2 ሺህ 978 ሰዎች ሲሞቱ፣ በኢራን 18 ሺህ 407 ሰዎች ተጠቅተው፣ 1 ሺህ 284 ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

የከፋው ጥፋት የሚጠብቃት አፍሪካ
የአለም የጤና ድርጅት በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው መግለጫ፤ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተቀረው አለም በባሰ መልኩ በአፍሪካ አገራት ላይ የከፋ ጥፋት ያስከትላል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመጠቆም፣ አገራቱ በከፍተኛ ቁርጠኝነት ቫይረሱን ለመዋጋት እንዲነሱ አስጠንቅቋል፡፡
ከእስያና ከአውሮፓ ጋር ሲነጻጸር በአፍሪካ ቀሰስተኛ ስርጭት እንዳለው የተነገረለት ኮሮና፤ እስከ ትናንት በስቲያ በ34 የአፍሪካ አገራት ከ600 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና 17 ሰዎችን መግደሉን የዘገበው ሮይተርስ፣ በሲዲሲ የአፍሪካ ሃላፊ ጆን ኬንጋሶን ግን የኮሮና ምርመራን ለማምለጥ የሚደበቁና የሚሸሹ አፍሪካውያን ቁጥር እየተበራከተ ከመምጣቱ ጋር ተያይዞ፣ አህጉሪቱ የከፋውን ጥፋት ታስተናግዳለች ብለው እንደሚሰጉ መናገራቸውን ገልጧል::
በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁባቸው አገራት መካከል በግብጽ 196፣ በደቡብ አፍሪካ 116፣ በአልጀሪያ 72 መጠቃታቸውን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል::

ሃኪሞች እና ኮሮና
በጣሊያን ወረርሽኙን ለመከላከልና ዜጎችን ከሞት ለመታደግ ደፋ ቀና ሲሉ በቫይረሱ የሚያዙ ሃኪሞች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት በእጅጉ እየጨመረ መሆኑንና እስካሁንም ከ2 ሺህ 629 በላይ የአገሪቱ ሃኪሞች በቫይረሱ መያዛቸውን አልጀዚራ ዘግቧል:: የአሜሪካ ሜዲካል አሶሴሽን በበኩሉ በቻይና በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁት ሰዎች መካከል 3.8 በመቶ የሚሆኑት የህክምና ባለሙያዎች መሆናቸውን ሰሞኑን ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በቡልጋሪያ የኮሮና ቫይረስ መከላከያ ቁሳቁስና የህክምና መሳሪያዎች ሳይሟሉልን የኮሮና ህክምና እንድንሰጥ ተገድደናል ያሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው የህክምና ዶክተሮችና የጤና ባለሙያዎች በገዛ ፈቃዳቸው ስራቸውን መልቀቃቸው ተዘግቧል፡፡

መንግስታት በገፍ በጀት እየመደቡ ነው
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ኢኮኖሚውን ለመደገፍ 1 ትሪሊዮን ዶላር መመደባቸው የተነገረ ሲሆን፣ የካናዳ መንግስት በኮሮና ለተጎዱ ቤተሰቦችና የንግድ ተቋማት የ18.6 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መወሰኑን ባለፈው ረቡዕ ይፋ አድርጓል፡፡
እንግሊዝ በኮሮና ሳቢያ ለኪሳራ የመዳረግ አደጋ ያንዣበበባቸውን የንግድ ኩባንያዎች ለመታደግ 400 ቢሊዮን ዶላር የመደበች ሲሆን፣ ጀርመን በበኩሏ፤ አነስተኛ ነጋዴዎችን ለመደገፍና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚውል 40 ቢሊዮን ዩሮ መመደቧን አስታውቀዋለች፡፡
ኢኮኖሚያቸውን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ሊከሰት ከሚችል ቀውስ ለመታደግ ከፍተኛ ድጎማና በጀት ከመደቡ የአለማችን አገራት መካከል 56 ቢሊዮን ዶላር የመደበቺው አውስትራሊያ አንዷ ስትሆን የደቡብ ኮርያው ፕሬዚደንት ሙን ጄ ኢን በበኩላቸው፤ ለተመሳሳይ ተግባር 39 ቢሊዮን ዶላር መመደባቸውን ከትናንት በስቲያ አስታውቀዋል፡፡

ጭር ያሉ ከተሞች
ባለፈው ረቡዕ ብቻ በአንድ ቀን 475 ሰዎች በኮሮና የተጠቁባትና አስከሬን በወጉ ለመቅበር የማይቻልበት ሁኔታ ላይ የደረሰችው ጣሊያን፤ ለአንድ ሳምንት የቆየውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላልተወሰነ ጊዜ ለማራዘም ማሰቧን የዘገበው ቢቢሲ፣ በየቤታቸው ተዘግተው የሰነበቱ ዜጎች በቤታቸው መቆየታቸው የአገሪቱ ከተሞችም ጭው ጭር ብለው መቀጠላቸው እንደማይቀር አመልክቷል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በመላ አገሪቱ መደበኛ እንቅስቃሴዎች ለ15 ቀናት ያህል እንዲቋረጡ ያደረገው የፈረንሳይ መንግስት፣ ቀነ ገደቡን ሊያራዝም እንደሚችል መግለጹ ተነግሯል፡፡
የመሬት ውስጥ ባቡር አገልግሎትን ያቋረጠችው የእንግሊዟ መዲና ለንደን ከትናንት ጀምሮ ትምህርት ቤቶችን የዘጋች ሲሆን፣ ከሞላ ጎደል የዘጋችው ጀርመንም፤ ሆቴሎችን እና የህዝብ መሰብሰቢያ አዳራሾችን የኮሮና ታማሚዎችን ማከሚያ ሆስፒታል አድርጋ ለመጠቀም ማሰቧ ተነግሯል፡፡

የከፋ ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ
የኮሮና ቫይረስ በአለማቀፍ ደረጃ ሊያስከትለው የሚችለው ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆንና አጠቃላዩ አለማቀፍ ምርት በ30 በመቶ ያህል ሊቀንስ እንደሚችል መነገሩን የዘገበው ብሉምበርግ፣ አለም 26 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ የኢኮኖሚ ማነቃቂያ በጀት እንደሚያስፈልጋት ገልጧል፡፡
ጄ ፒ ሞርጋን የተባለው ተቋም ኢኮኖሚስቶች ያወጡትን ጥናት ጠቅሶ ሮይተርስ እንደዘገበው፤ ኮሮና ቫይረስ የቻይናን የሩብ አመት ኢኮኖሚ በ40 በመቶ፣ የአሜሪካን የቀጣዩ አመት ኢኮኖሚ ደግሞ በ14 በመቶ ይቀንሰዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ባንኮች በከፋ የፋይናንስ እጥረት ውስጥ እንደገቡ የተነገረ ሲሆን፣ የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪውም የከፋ ቀውስ ያጋጥማቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ዘርፎች አንዱ መሆኑን ከሰሞኑ የወጡ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ስራቸውን ያቋረጡት ታዋቂዎቹ የመኪና አምራቾች ቶዮታ፣ ኒሳን ሞተርስና ሆንዳ ሞተርስ በተናጠል በሳምንቱ መጀመሪያ በሰጡት መግለጫ፤ በሰሜን አሜሪካ ፋብሪካዎቻቸውን ለተወሰነ ጊዜ እንደሚዘጉ ያስታወቁ ሲሆን፣ ፎርድ፣ ጄኔራል ሞተርስና ፊያት በበኩላቸው፤ በአሜሪካ የሚገኙ መገጣጠሚያዎቻቸውን እንዲሁም በካናዳና በሜክሲኮ ያሏቸውን ፋብሪካዎች እንደሚዘጉ አስታውቀዋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው የአክሲዮን ገበያ ቀውስ ሳቢያ ባለፈው የካቲት ወር ብቻ የአለማችን 20 እጅግ ባለጸጋ ቢሊየነሮች ሃብት በድምሩ በ293 ቢሊዮን ዶላር መቀነሱን ፎርብስ መጽሄት ሰሞኑን ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
በአውሮፓና አሜሪካ ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ወዲህ ከፍተኛ በተባለ መጠን ፋብሪካዎች መዘጋታቸውን የዘገበው ብሉምበርግ፣ ኩባንያዎች በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ምርታቸውን ማቋረጣቸውንና ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡

ኮሮና ወደ ቻይና ዞሮ እየገባ ነው
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቀሰቀሰባትና የዚህ ሁሉ መነሻ በሆነችው የቻይናዋ ዉሃን ግዛት፣ ኮሮና ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ አንድም ሰው በቫይረሱ አለመያዙ ይፋ ቢደረግም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከወራት እልህ አስጨራሽ ትግልና ርብርብ በኋላ የወረርሽኙን ስርጭት በመግታት ረገድ ተጨባጭ ስኬት ማስመዝገቧ በሚነገርላት ቻይና ርዕሰ መዲና ቤጂንግ፤ ባለፈው ረቡዕ ከሌላ አገራት ቫይረሱን ይዘው የመጡ 21 ሰዎች መገኘታቸውንና አገሪቱ ሌላ ፈተና እንደተደቀነባት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
 
ባለጸጎች እጃቸውን እየዘረጉ ነው
የኮሮና ወረርሽኝ ተስፋፍቶ መቀጠሉን ተከትሎ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት ወረርሽኙን ለመግታትና ለተለያዩ የምርምርና የህክምና ስራዎች የገንዘብና የሌሎች ድጋፎችን የሚያደርጉ  ባለጸጎች ቁጥር መጨመሩን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
የቅንጦት ዕቃዎች አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆኑት በርናርድ አርኖልት፣ 3 የሽቶ አምራች ፋብሪካዎቻቸው መደበኛ ስራቸውን አቋርጠው የቫይረስ መከላከያ ኬሜካል በማምረት በነጻ እንዲያከፋፍሉ ያደረጉ ሲሆን፣ የሚዲያው ዘርፍ ቢሊየነር ማይክል ብሉምበርግ በበኩላቸው፤ ወረርሽኙን ለመግታት የሚውል የ40 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡
የማይክሮሶፍቱ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ በፋውንዴሽናቸው በኩል 100 ሚሊዮን ዶላር ያበረከቱ ሲሆን፣ ሌላው የቴክኖሎጂው ዘርፍ ባለጸጋ ማይክል ዴል ደግሞ ለኮሮና ህክምና ቁሳቁስ መግዣ የ284 ሺህ ዶላር ልገሳ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ፣. በገንዘብና በአይነት እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ ካደረጉ ሌሎች የአለማችን ቢሊየነሮች መካከልም 14 ሚሊዮን ዶላር የለገሱትና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቁሳቁሶችን ለመስጠት ቃል የገቡት የቻይናው አሊባባ ኩባንያ መስራች ጃክ ማ፣ 100 ሚሊዮን ዶላር የለገሰው የፌስቡኩ ማርክ ዙክበርግ ይገኙበታል፡፡

25 ሚሊዮን ሰዎች ከስራ ሊፈናቀሉ ይችላሉ
አለማቀፉ የሰራተኞች ድርጅት አይኤልኦ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገው መረጃ እንደሚለው፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አንዳች መላ ካልተገኘለት በቀር በመላው አለም 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከስራ ገበታቸው ሊያፈናቅል ይችላል ተብሎ ይሰጋል፡፡
የአለማችን ሰራተኞች በኮሮና ሳቢያ ገቢያቸው በድምሩ 3.4 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ሊቀንስ እንደሚችል የጠቆመው የተቋሙ መረጃ፣ መንግስታትና ተቋማት ቫይረሱ በሰራተኞች ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቀነስ መስራት እንዳለባቸው አመልክቷል፡፡

በቻይና ፍቺ ጨምሯል
በቻይና ከኮሮና ስጋት ጋር በተያያዘ ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን ገትተው በቤታቸው ለረጅም ቀናት እንዲቆዩ የሚያስገድድ መመሪያ መውጣቱን ተከትሎ፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የፍቺ ጥያቄ የሚያቀርቡ ባለትዳሮች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ የተነገረ ሲሆን፣ ይህም የመጣው ባለትዳሮች ለተራዘመ ጊዜ አብረው ሲቆዩ በመሰለቻቸታቸው ወይም ግጭቶች በመፈጠራቸው ሳቢያ ሊሆን እንደሚችል ተዘግቧል፡፡
በደቡብ ምዕራባዊቷ የቻይና ዳዙ ግዛት ባለፉት ሶስት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ300 በላይ ጥንዶች ትዳራቸውን በፍቺ ለማፍረስ ለሚመለከተው የመንግስት አካል ጥያቄ ማቅረባቸውንና ይህም ከኮሮና በፊት ከነበረው በእጅጉ እንደሚበልጥ የዘገበው ዘ ቴሌግራም፣ የግዛቲቷ ባለስልጣናትም በተለይ ወጣት ባለትዳሮች ከትዳር አጋራቸው ጋር ለረጅም ጊዜ በአንድ ላይ ሲቆዩ የመሰላቸትና ጸብ የመቀስቀስ ዕድላቸው ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር የተያያዘ ሊሆን መቻሉን እንደተናገሩ አመልክቷል፡፡
ሻንዚ በተባለችው ሌላ የአገሪቱ ግዛት በሚገኝ ከተማ ውስጥም በአንድ ቀን ብቻ 14 ባለትዳሮች የፍቺ ጥያቄ ይዘው መምጣታቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

በኮሮና የተጠቁ ፖለቲከኞችና ዝነኞች
ከሰሞኑ በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ የአለማችን ታዋቂ ፖለቲከኞችና ዝነኞች መካከል በአውሮፓ ህብረት ዋና የብሬግዚት አደራዳሪ የሆኑት ሚሼል ባርኒየር አንዱ መሆናቸው ተዘግቧል:: የብራዚል የማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስትር ቤኔቶ አልቢኩሪ፣ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ኦግስቶ ሄሌኖ፣ በጀርመን የእስራኤል አምባሳደር ጄርሚ ኢሳካሮፍ፣ የአውስትራሊያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፒተር ዱቶን፣ የፈረንሳይ የባህል ሚኒስትር ፍራንክ ሬስተር እና የፖላንድ የአካባቢ ሚኒስትር ሚካል ዎስ በሳምንቱ በኮሮና ከተያዙ ፖለቲከኞች መካከል ይገኙበታል፡፡
ታዋቂው የአፍሮ ጃዝ ድምጻዊና የሳክስፎን ተጫዋች ማኑ ዲባንጎ በኮሮና ተይዞ ባለፈው ረቡዕ ፈረንሳይ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል መግባቱ የተነገረ ሲሆን፣ በተለያዩ አገራት በስፖርቱ ዘርፍ የሚታወቁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዝነኞችም በኮሮና መጠቃታቸው ተዘግቧል፡፡
ከዚህ ቀደም በቫይረሱ ከተያዙ ዝነኞች መካከል የሆሊውዱ የፊልም አክተር ቶም ሃንክስና ባለቤቱ፣ የፊልም ተዋናይትና ድምጻዊት ሪታ ዊልሰን፣ እንግሊዛዊው የፊልም ተዋናይና ድምጻዊ ኢድሪስ ኢባ እና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዱ ባለቤት ሶፊ ግሪጎሪ ትሩዱ ይገኙበታል፡፡

     ኮሮና ቫይረስ ከቻይና ተነስቶ መላውን አለም እያዳረሰ በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ካጠቃና ከ4 ሺህ በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለህልፈተ ህይወት ከዳረገ፣ በኩባንያዎችን እንቅስቃሴና በአገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ካደረሰ፣ በየአቅጣጫው ብዙ ጥፋትን ካስከተለ በኋላ፣ መስፈርቴን አላሟላምና “ወረርሽኝ” ብዬ አልጠራውም በሚል ለወራት ሲያመነታ የቆየው የአለም የጤና ድርጅት በስተመጨረሻም “ኮሮና አለማቀፍ ስጋት የሆነ ወረርሽኝ ሆኗል!” ሲል ባለፈው ረቡዕ በይፋ አወጀ፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በአለም ዙሪያ በሚገኙ 125 አገራትና ግዛቶች ውስጥ 129 ሺህ 854 ሰዎችን ያጠቃ ሲሆን፣ ከ4 ሺህ 751 በላይ የሚሆኑትንም ለህልፈተ ህይወት ዳርጓል፡፡
ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተባት ቻይና ምንም እንኳን በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎችን ቁጥር በሳምንቱ በእጅጉ መቀነሱን ይፋ ብታደርግም፣ እስከ ትናንት በስቲያ በአገሪቱ 80 ሺህ 796 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውንና 3 ሺህ 169 ሰዎች ደግሞ ለሞት መዳረጋቸውን ዘገባዎች ያመለክታሉ፡፡
አንድ በሽታ ወረርሽኝ ተብሎ የሚጠራው በዓለም ዙሪያ በተመሳሳይ ጊዜ በተለያዩ አገራት ሲሰራጭ መሆኑን የተናገሩት የአለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ኮሮናም በመላው አለም በስፋት እየተሰራጨ በመሆኑ ወረርሽኝ መሆኑ መታወጁንና አገራትም ከመቼውም በበለጠ የወረርሽኙን ፍጥነት ለመግታት መረባረብ እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከቻይና ውጭ ባሉት የአለም አገራት ባለፉት ሁለት ሳምንታት በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በ13 እጥፍ ያህል ማደጉን የተናገሩት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ አለም ወረርሽኙን ለመግታት እጅ ለእጅ ተያይዞ መስራት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

ጠንካራ የጉዞ እገዳዎች
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኮሮና ቫይረስን ስርጭት ለመግታት በማሰብ በአውሮፓ ህብረት አገራት ላይ የጉዞ እገዳዎችን መጣላቸውን ባለፈው ረቡዕ ይፋ ማድረጋቸውን ተከትሎ ጉዳዩ በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ለኮሮና ጉዳይ ተገቢውን ትኩረት አልሰጡም በሚል ሲተቹ የሰነበቱት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከእንግሊዝ በስተቀር ከ26 የአውሮፓ አገራት ወደ አገሪቱ የሚደረጉ ጉዞዎች በሙሉ ከትናንት ጀምሮ ለ30 ቀናት ያህል መታገዳቸውን ማስታወቃቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ የጉዞ እገዳው አሜሪካውያን ዜጎችን አይመለከትም መባሉንና ኮሮና በአሜሪካ ከ1 ሺህ 135 በላይ ሰዎችን ማጥቃቱንና 38 ሰዎችን መግደሉንም አመልክቷል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የትራምፕን የጉዞ እገዳ በማስመልከት ባወጣው መግለጫ፣ “ኮሮና አለማቀፍ ቀውስ እንጂ የአንድ አህጉር ጉዳይ ብቻ አይደለም፤ ከአንድ ወገን እርምጃ ይልቅ ትብብርን የሚሻ የጋራ ችግር ነው” ሲል የትራምፕን እርምጃ ማውገዙን የዘገበው ቢቢሲ በርካታ የአውሮፓ አገራት መሪዎችም ሌላ ቀውስ የሚያመጣ አደገኛ እርምጃ በሚል ትችታቸውን መሰንዘራቸውንም ዘግቧል፡፡
በተመሳሳይ መልኩም፣ በኮሮና ቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቶ 45 ያህል መድረሱ ያሰጋት ሳዑዲ አረቢያ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አውሮፓ ህብረትና ሌሎች 12 የአለማችን አገራት የሚደረጉ ጉዞዎችን ከትናንት በስቲያ ያገደች ሲሆን በተጠቀሱት አገራት የሚገኙ ዜጎች በ72 ሰዓታት ውስጥ ወደአገራቸው እንዲገቡም ጥሪ አቅርባለች፡፡
የአገሪቱ መንግስት ባወጣው መግለጫ የጉዞ እገዳው ከተጣለባቸው የአውሮፓ፣ የእስያና የአፍሪካ አገራት ወደ ሳዑዲ የሚደረጉና ከሳዑዲ ወደ አገራቱ የሚደረጉ የጉዞ በረራዎች ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆሙ መወሰኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ክፉኛ የተጎዳ ንግድና ኢኮኖሚ
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአውሮፓ አገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣላቸውን ተከትሎ አሜሪካ፣ አውሮፓና እስያን ጨምሮ በአለማቀፍ የፋይናንስ ገበያዎች ላይ ያልተለመደና ከፍተኛ የአክሲዮን ዋጋ ማሽቆልቆል እንደታየ ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ከአውሮፓ አገራት ወደ አሜሪካ የሚገቡ የጭነት አውሮፕላን በረራዎች ጭምር የሚያግደው አነጋጋሪው የትራምፕ ውሳኔ የሁለቱን አገራት ብቻ ሳይሆን የተቀረውን አለም የንግድና ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በእጅጉ ይጎዳዋል ተብሎ መሰጋቱን የጠቆመው ዘገባው፣
የቻይና አምራች ኩባንያዎች ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ስራቸው በከፍተኛ ሁኔታ መስተጓጎሉን ያስታወቁ ሲሆን፣ በተለይ በመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች ላይ የተከሰተው የሰው ሃይልና የግብዓት እጥረት በአለማቀፉ የመድሃኒት ገበያ ላይ ከፍተኛ እጥረት ሊያስክትል እንደሚችል ተሰግቷል፡፡
አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ አገራት ውስጥ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎች ሰራተኞቻቸውን የመቀነስ ወይም በቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ የማድረግ አማራጭን እየተጠቀሙ ሲሆን፣ ይህ ግን በአንዳንድ አገራት እጅግ አስቸጋሪ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የጎግል እህት ኩባንያ የሆነው አልፋቤት በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ አፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰራተኞቹ በሙሉ እስከ ሚያዝያ ወር መጀመሪያ ድረስ ቤታቸው ውስጥ ሆነው ስራቸውን እንዲሰሩ መምከሩን የዘገበው ሲኤንቢሲ፣ ትዊተር በበኩሉ 5 ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞቹን በተመሳሳይ ሁኔታ ቤታቸው ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ቀጭን ትዕዛዝ ማስተላለፉን ገልጧል፡፡
ኢኮኖሚው በቫይረሱ ሳቢያ ክፉኛ የተጎዳበት የጣሊያን መንግስት 28.3 ቢሊዮን ዶላር ድጎማ ለማድረግ ማሰቡ የተነገረ ሲሆን፣ የጀርመኖቹ የስፖርት ትጥቅ አምራች ኩባንያዎች አዲዳስና ፑማ ሽያጫቸው በከፍተኛ ሁኔታ ሊቀንስ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ስርጭት መስፋፋቱን ተከትሎ በአለም ዙሪያ የሚገኙ አየር መንገዶች በሺህዎች የሚቆጠሩ በረራዎችን መሰረዛቸውን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ሪያንኤር፣ ኢዚጄት፣ ኖርዌጂያን ኤር፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስና አሜሪካን ኤርላይንስ በረራቸውን በብዛት የሰረዙና ለከፍተኛ የገቢ መቀነስ የተዳረጉ አየር መንገዶች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የተዘጋች ጣሊያን
ከአውሮፓ አገራት መካከል ኮሮና ክፉኛ እንዳጠቃት በሚነገርላትና የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ከ12 ሺህ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 827 በደረሰባት ጣሊያን የዕለት ከዕለት የስራና የንግድ እንቅስቃሴ እየተገደበ ሲሆን፣ የአገሪቱ መንግስትም ከምግብ መደብሮችና ፋርማሲዎች በስተቀር ሁሉንም ሱቆችና የንግድ ተቋማት በመዝጋት ላይ ይገኛል፡፡
የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ የሰጡትን መግለጫ ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ ጂምናዚየሞች፣ ሙዚየሞችና የምሽት ክለቦች ቀደም ብለው በተዘጉባት ጣሊያን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሲባል መጠጥ ቤቶች፣ ሬስቶራንቶችና ጸጉር ቤቶችን ጨምሮ እምብዛም አንገብጋቢ ያልሆኑና መሰረታዊ ግልጋሎቶችን የማይሰጡ የንግድ ተቋማት በሙሉ ለሁለት ሳምንታት ያህል የሚዘጉ ይሆናል፡፡
በጣሊያን በኮሮና ቫይረስ ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ረቡዕ በ30 በመቶ ያህል መጨመሩን ተከትሎ፣ የአገሪቱ መንግስት ዜጎች እንቅስቃሴያቸውን ገትተው በቤት ውስጥ እንዲቀመጡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ማስተላለፉ ተነግሯል፡፡

አፍሪካ
ከሌሎች አህጉራት ጋር ሲነጻጸር ኮሮና ቫይረስ እምብዛም ጉዳት ያላደረሰው በአፍሪካ ቢሆንም፣ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ ቫይረሱ የተገኘባቸው 12 የአፍሪካ አገራት ግብጽ፣ አልጀሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቱኒዝያ፣ ሞሮኮ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሩን፣ ቡርኪና ፋሶ፣ ናይጀሪያ፣ ቶጎ፣ ዶሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኮትዲቯር መሆናቸው ተዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ እስከ ትናንት በስቲያ ድረስ በተጠቀሱት አስራ ሁለት የአፍሪካ አገራት ውስጥ በድምሩ 119 ሰዎችን ማጥቃቱ የተነገረ ሲሆን፣ 60 ሰዎች በቫይረሱ የተጠቁባት ግብጽ በአህጉሩ በከፋ ሁኔታ ተጠቂ የሆነች ቀዳሚዋ አገር ናት፡፡
አልጀሪያ 20፣ ደቡብ አፍሪካ 13፣ ቱኒዚያ 7፣ ሞሮኮ 6፣ ሴኔጋል 4፣ ካሜሩን ቡርኪናፋሶና ናይጀሪያ እያንዳንዳቸው 2፣ ቶጎ ዲሚክራቲክ ኮንጎና ኮትዲቯር እያንዳንዳቸው 1 ሰው በኮሮና ቫይረስ እንደተጠቃባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመርኬል “ግምት”
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ በሳምንቱ ከተሰሙትና መላውን አለም ሲያነጋግሩ ከሰነበቱት ጉዳዮች መካከል፣ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ መርኬል “ኮሮና ቫይረስ 70 በመቶ ያህል የጀርመንን ህዝብ ሊያጠቃ ይችላል” ሲሉ ባለፈው ረቡዕ በይፋ ያሰሙት ማስጠንቀቂያ አንዱ ነው፡፡
ከጀርመን ህዝብ 70 በመቶ ያህሉ ወይም 58 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ሊያዙ ይችላሉ የሚለው የአንጌላ መርኬል ማስጠንቀቂያ ብዙዎችን ሲያስደነግጥ፣ አንዳንዶችን ደግሞ “ሴትዮዋ ወይ ቁጥር ወይ ግምት አይችሉም!” ብለው እንዲሳለቁ ማድረጉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

በ22 አገራት ትምህርት ሙሉ
ለሙሉ ተቋርጧል
በመላው አለም በሚገኙ 22 አገራት ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የመደበኛና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሙሉ ለሙሉ መቋረጡን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ከተቋረጠባቸው የአለማችን አገራት መካከል ጣሊያን፣ ዴንማርክ፣ ካዛኪስታን እና ጃፓን እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፣ አገራቱ ትምህርት ቤቶችንና ዩኒቨርሲቲዎችን እንዲዘጉ የወሰኑት ለተለያየ የጊዜ እርዝማኔ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ሌሎች 13 የአለማችን አገራት ደግሞ ቫይረሱ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የተወሰኑ ትምህርት ቤቶችን ብቻ መርጠው መዝጋታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህ አገራት መካከል ስፔን፣ ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመንና ዩክሬን እንደሚጠቀሱም አክሎ ገልጧል፡፡

ከቶም ሃንክስ እስከ ፓብሎ ኤግሊሲያስ
ለስራ ጉዳይ ወደ አውስትራሊያ ጎራ ብለው የነበሩት የኦስካር ተሸላሚው የፊልም ተዋናይ ቶም ሐንክስና ባለቤቱ ሪታ ዊልሰን በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው በምርመራ መረጋገጡን ባለፈው ረቡዕ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃን በስፋት ዘግበዋል፡፡
ፎረስት ጋምፕና ሴቪንግ ፕራይቨተር ራያንን ጨምሮ በበርካታ ፊልሞቹ የሚታወቀው ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ወደ አውስትራሊያ የተጓዙት የኤልቪስ ፕሪስሊን የሕይወት ታሪክ በፊልም ለማዘጋጀት እንደነበር የዘገበው ሆሊውድ ኒውስ፣ ሁለቱም የህመም ስሜት ሲሰማቸው ወደ አንድ ሆስፒታል መሄዳቸውና በተደረገላቸው ምርመራ በቫይረሱ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ ከሌሎች ሰዎች ተነጥለው እንዲቀመጡ መደረጋቸውን አመልክቷል፡፡
የስፔን የእኩልነት ሚኒስትር አይሪን ሞንቴሮ ባለፈው ረቡዕ በኮሮና መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ የትዳር አጋራቸው የሆኑት የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ፓብሎ ኤግሊሲያስም  ራሳቸውን ነጥለው እንዲቀመጡ መደረጋቸውና ሁሉም የአገሪቱ የፓርላማ አባላትና ባለስልጣናት ምርመራ እንዲያደርጉ መወሰኑን የአገሪቱ መንግስት አስታውቋል፡፡
በቫይረሱ እንደተያዙ ከተነገረላቸው ሌሎች የአለማችን ታዋቂ ሰዎች መካከል ለጣሊያኑ የእግር ኳስ ክለብ ጁቬንቱስ የሚጫወተውና በተገገለ ቦታ እንዲቀመጥ የተደረገው ዳኔል ሩጋኒ እና የእንግሊዝ የጤና ሚኒስትር ናዳኔ ዶሪስ ይጠቀሳሉ፡፡
በስፔን የአንድ ቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋች በኮሮና መያዙ መረጋገጡን ተከትሎ የሪል ማድሪድ የቅርጫት ኳስና የእግር ኳስ ቡድኖች ተጫዋቾች በሙሉ ወደ ጊዚያዊ የማረፊያ ቦታ እንዲገቡ መደረጋቸውም ተነግሯል፡፡


____________________________________________

የአገሩ ስም የተጠቂዎች
ቁጥር
የሟቾች
ቁጥር
ቻይና 80,796 3,169
ጣሊያን 12,462 827
ኢራን 10,075 429
ደቡብ ኮርያ 7,869 66
ስፔን 3,003 84
ጀርመን 2,355 4
ፈረንሳይ 2,281 48
አሜሪካ 1,377 38
ስዊዘርላንድ 867 6
ኖርዌይ 713
ዲያምንድ
ፕሪንስ መርከብ
696 7
ጃፓን 643 16
ስዊድን 635 1
ዴንማርክ 615
ኒዘርላንድ 614 5
እንግሊዝ 590 10
ቤልጂየም 399 3
ኦስትሪያ 302 1
ኳታር 262
ባህሬን 195
ሲንጋፖር 178
ማሌዢያ 158
አውስትራሊያ 156 3
ሆንግ ኮንግ 130 3
ካናዳ 118 1
ፊላንድ 109
አይስላንድ 103
እስራኤል 100
ግሪክ 99 1
ቼቺያ 96
ስሎቫኒያ 89
የተባበሩት አረብ
ኤሜሬትስ
85
ኩዌት 80
ፖርቹጋል 78
ህንድ 74
ኢራቅ 71 8
ታይላንድ 70 1
ሳንማሪኖ 69 3
ብራዚል 69
ሊባኖስ 68 3
ግብጽ 67 1
ፊሊፒንስ 52 2
ፖላንድ 51 1
ታይዋን 49 1
ሮማኒያ 49
ሳዑዲ አረቢያ 45
አየርላንድ 43 1
ቬትናም 39
ኢንዶኔዢያ 34 1
ፍልስጤም 31
ሩስያ 28
ጆርጂያ 25
ብሩኒ 25
አልጀሪያ 24 1
አልባኒያ 23 1
ቺሊ 23
ኮስታ ሪካ 22
አርጀንቲና 21 1
ፓኪስታን 21
ክሮሺያ 19
ሉግዘምበርግ 19
ሰርቢያ 19
ኦማን 18
ኢኳዶር 17
ኢስቶኒያ 17
ፔሩ 17
ደቡብ አፍሪካ 17
ቡልጋሪያ 16 1
ላቲቪያ 16
ሃንጋሪ 16
ስሎቫኪያ 16
ፓናማ 14 1
ቤላሩስ 12
ሜክሲኮ 12
አዘርባጃን 11
ቦስኒያ
ሄርዘጎቪኒያ
11
ማካኦ 10
ሰሜን ሜቄዶኒያ 9
ኮሎምቢያ 9
ማልታ 9
ማልዴቪስ 8
አፍጋኒስታን 7
ቱኒዚያ 7
ቆጵሮስ 7
ሞሮኮ 6 1
ጊኒ 6
ካምቦዲያ 5
ዶሚኒካን
ሪፐብሊክ
5
ኒውዚላንድ 5
ሴኔጋል 5
ፓራጓይ 5
አርሜኒያ 4
ሊችተንስቲን 4
ሞልዶቫ 4
ሊዪቲያና 3
ባንግላዴሽ 3
ቻነል ደሴቶች 3
ኩባ 3
ማርቲሚኒክ 3
ናይጀሪያ 2
ሲሪ ላንካ 2
ቦሊቪያ 2
ቡርኪና ፋሶ 2
ካሜሮን 2
ፋኦሬ ደሴቶች 2
ሆንዱራስ 2
ጃማይካ 2
ሴንት ማርቲን 2
ጊኒ 1 1
አንዶራ 1
ዮርዳኖስ 1
ሞናኮ 1

  “ያገባናል” የበጐ አድራጐት ድርጅት ከ“ሻዴም ሚዲያና ኮሙኒኬሽን” ጋር በመተባበር በ46ቱም የመንግስት ዩኒቨርስቲዎች የሚተገበር “ጤናማነት ለራስ” የተሰኘ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የማንቂያ ንቅናቄ ሀሙስ መጋቢት 3 ቀን 2012 ከምሽቱ 12፡00 ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል፡፡
በይፋ በተጀመረበት ሰዓት የ ያገባኛል በጐ አድራጐት ማህበር መስራችና ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ መስታወት ስሜ እና የሻዴም ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛ ሄኖክ ይርጋ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ “ወጣት ለምክንያት እንጂ ለስሜት አይሞትም” በሚል መርህ በየዩኒቨርስቲው በመንቀሳቀስ ወጣቶች በትምህርት ላይ እያሉ ማድረግ ስለሚገባቸው የጤና የትምህርትና የተግባቦት ሁኔታ እንዲሁም ተመርቀው ሲወጡ ስለሚገጥሟቸው ፈርጀ ብዙ የህይወት መስመሮች በማስተማርና በማንቃት በአካልም ሆነ በስነ ልቦና ጤናማ የትምህርት ቆይታ እንዲኖራቸው ድጋፍ ያደርጋል፡፡
የተለያዩ አነቃቂ ንግግር አድራጊዎችን አርቲስቶችን በሱስ ውስጥ ኖረው ነፃ የወጡ ባለተሞክሮዎችን በየዩኒቨርስቲው ይዘው በመጓዝ ተሞክሮና ልምድ እንደሚያካፍሉም ዋና ሥራ አስኪያጆቹ ተናግረዋል፡፡
“ያገባናል የበጐ አድራጐት ማህበር በ2004 የተቋቋመ ሲሆን ማህበረሰብ ተኮር የሆኑ በተለይ ወጣቱን ማዕከል በማድረግ በርካታ ስራዎችን የሰራ ሲሆን ባለፈው ዓመት በወላይታ ሶዶ፣ ጅግጅጋ፣ ጋምቤላ፣ ኮተቤ ሜትሮፖሊታንና በአርሲ ዩኒቨርስቲዎች በመጓዝ ተማሪዎች ከግጭትና ከብጥብጥ ራሳቸውን አቅበው የመጡበትን ዓላማ አሳክተው እንዲወጡ በማስተማር በኩል ያስመዘገቡትን አመርቂ ውጤት የሚያሳይ ዘጋቢ ፊልም ለታዳሚ አቅርበዋል፡፡
 “ጤናማነት ለራስ” የተሰኘውና ትላንት በይፋ የተጀመረው ይህ እንቅስቃሴ ከከፍተኛ ትምህርትና ሳይንስ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንደሚተገበርና በሶስት ዓመት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡  

Page 10 of 476