Administrator

Administrator

Saturday, 20 February 2016 09:44

የዘላለም ጥግ

(ስለ ዲሲፕሊን)
- ዲሲፕሊን በግብና በስኬት መካከል ያለ
ድልድይ ነው፡፡
ጂም ሮህን
- አንድ ጊዜ ቁርጠኝነቱ ካለህ ያሰብክበት
ለመድረስ ዲሲፕሊንና ተግቶ መስራት
ይኖርብሃል፡፡
አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ
- ያለ ዲሲፕሊን ህይወት ጨርሶ የለም፡፡
ካታሪን ሄፕበርን
- ማህበራዊ ሚዲያ ጊዜህን እንዳይሰርቅብህ
ዲሲፕሊን ያስፈልግሃል፡፡
አሌክሲስ ኦሃንያን
- በራስ መተማመን የሚመነጨው
ከዲሲፕሊንና ከልምምድ ነው፡፡
ሮበርት ኪዮሳኪ
- ስኬት የሚለካው ባለህ ዲሲፕሊንና
በውስጣዊ ሰላምህ ነው፡፡
ማይክ ዲትካ
- ጥሩ ዲሲፕሊን ቢኖረኝ ኖሮ ወደ ሙዚቃ
ሙያ እገባ ነበር፡፡
ክሊንት ኢስትውድ
- ዲሲፕሊን ማለት የምትፈልገውን ነገር
ማስታወስ ነው፡፡
ዴቪድ ካምቤል
- አንዳንድ ሰዎች ዲሲፕሊንን እንደ ሥራ
ይቆጥሩታል፡፡ ለእኔ በነፃ እንድበር
የሚያደርገኝ የስርዓት ዓይነት ነው፡፡
ጁሊ አንድሪውስ
- የስኳር በሽታ ዲሲፕሊንን አስተምሮኛል፡፡
ሶንያ ሶቶማዮር
- ጥቂት ሰዎች ጀግና ሆነው ይወለዳሉ፡
፡ ብዙዎች የሚጀግኑት በልምምድና
በዲሲፕሊን ኃይል ነው፡፡
ፑብሊዩስ ፍላቪዩስ ቬጄቲዩስ ሬናቲዩስ
- ዲሲፕሊን? የቃሉን ትርጉም አላውቀውም፡፡
ሊያም ጋላግሄር
- አማፂ ለሆነ ሰው ዲሲፕሊን ከባድ ነው፡፡
ጆናታን ዊንተርስ

    ስሙ ያልታወቀ ፀሐፊን ጠቅሶ አንድ የኛ ፀሐፊ ያቀረበውን ለዛሬ ተረት እናርገው
ዐጼ ቴዎድሮስ አንድ ቀን አንድ የሚያምኑትን ዘበኛ ይዘው፣ አልባሌ መስለው ከጨለመ በኋላ በሠፈሩ ይዞሩ ጀመር፡፡ በየጐጆው እየተጠጉ ያደምጡ ነበር፡፡ እኩሉ ያልተኛ እኩሉም ተኝቶ፡፡ ከዝያ ወዲያ ካንድ ወታደር ጐጆ ተጠግተው ቢያደምጡ ባልና ምሽት በግብረ - ሥጋ ሲጣሉ ሰሙ፡፡ ወንዱ ይለምናል፡፡ ሴቲቱ አይሆንም ትላለች፡፡ ከዝያ ወዲያ ወንድየው፤
“በማርያም”፣ በሥላሴ፣ “በጻድቃን በቅዱሳን” እያለ ቢለምን፤ ሴትዮዋ፣
“እምቢ አይሆንም” ትላለች፡፡
ሰውየው፤
“ኧረ በሥላሴ ይሁንብሽ?”
“በጭራሽ ስልህ? አሻፈረኝ አልኩኮ!”
“በጻድቃን በቅዱሳን?”
“ሰውየው፤ እምቢ ማለት አይገባህም?”
ሰውየው የመጨረሻ ሙከራ አደረገ፡፡
“በይ በቴዎድሮስ ሞት…” አላት፡፡
“ቴዎድሮስማ ከሚሞት፣ ጐንደር አይታረስም” አለችና ፈቀደች፡፡
ንጉሡ ይሄንን ከሰሙ በኋላ እየሳቁ ወደ አዳራሻቸው ገቡና፣ ያን አብሮአቸው የነበረ ዘበኛ፤ ያችን ጐጆ እንዳታሳስትህ አስተውላት ብለውት ነበረና በነጋታው ያንን ዘበኛ፤
“ባልና ሚስቱን ጠርተህ አምጣቸው” ብለው ሰደዱት፡፡
ባልና ሚስቱም፤
“ምን ተገኘብን ይሆን?” ብለው እየተንዘፈዘፉ፣ እየተንቀጠቀጡ መጡና ከጃንሆይ ፊት ቆሙ፡፡
ንጉሡም፤
“እንዴት አደራችሁ?” አሉ፡፡
እነዚያም እየተብረጀረጁ ሳይሰሙ ቀርተው ኖሮ ባጠገባቸው የቆመ ቢነግራቸው በግንባራቸው ተደፍተው እጅ ነስተው ቆሙ፡፡
ቀጥለውም ንጉሡ፤
“ትላንት ማታ በምኝታ ጊዜ ከቤታችሁ ሆናችሁ ተናገራችሁ?” ብለው ጠየቋቸው፡፡
“ጃንሆይ የተናገርነው የለም፡፡ ጠላት ነገር ሠርቶብን እንደሆነም ያጋጥሙኝ፤ ድኻ ወታደር ባሪያዎ ነኝ፡፡”
“ከመኝታችሁ ላይ ጥቂት የተናገራችሁት ነገር እንዳለ አስበህ ንገረኝ አይዞህ” አሉት፡፡
እሱም ሰውነቱን አጠናከረና አስቦ፣ ያንን ምሽቱ ያደረገችውን ነገር ነገራቸው፡፡ ንጉሡም ሳቁ፡፡ ሴቲቱም አፈረች፡፡
***
“በኃይለስላሴ አምላክ ተወኝ!”፣ “በንጉሥ ይዤሃለሁ ተወኝ”፣ “በህግ አምላክ” ዱሮ ቀረ፡፡ የንጉሥ ስም ተጠርቶ አትንካኝ፣ አትምታኝ፣ መብቴን አትንካ፣ ማለት ጥንት የተለመደ ነበር፡፡ ዛሬ ያ ልማድ ቀርቷል፡፡ ማንም አይሰማም፡፡ ነገሥታቱ በህዝቡ የየዕለት ህይወት ውስጥ ይገቡ ነበር፡፡ የመፈራታቸውም መጠን ወሰን የለውም፡፡ ዛሬ ህጉ እየተለወጠ፣ ዘመኑ ጤና እያጣ መጥቷል፡፡
ዛሬ ከሽማግሌው ይልቅ ወጣቱ ጤና አጥቷል፡፡ በቀላሉ ይሸነፋል፡፡ የትምህርት አቅሙ ደካማ በመሆኑ ዕውቀቱ አገም ጠቀም ነው፡፡ ከመማር ማማረር የሚመርጠው እየበረከተ፤ የሚያመረው እየሳሳ መጥቷል፡፡ ቁርጠኝነት ጠፍቷል፡፡ ለሱስ ተገዥነት የማያጠያይቅ አደጋ ነው፡፡ የወሲብ ማጠናከሪያ ዕንክብል ካዋቂው ይልቅ የለጋው ወጣት ማዳበሪያ ሆኗል፡፡ ዛሬ በሪህ በሽታ የሚያዘው ወጣቱ ሆኗል፡፡ ንቅዘት (degeneration)  የወቅቱ ትዕዛዝ ይመስላል፡፡ ይቅር ይበለን እንጂ ምን ይባላል፡፡ እጅግ አሳሳቢ ነው!
“አረጋዊውን ባንቀልባ፣ ከምንሸከም እንኮኮ
ጐልማሳውን ከወኔ ጣር፣ ካልፈታን ከፍርሃት ምርኮ” የሚለን ነው ፀጋዬ ገ/መድህን፡፡
ሌላው ጣራችን ዲሞክራሲ ነው፡፡ ማንም መንግሥት፣ ገዢ ፓርቲ ወይም ተቃዋሚ ድርጅት ልብ ሊል የሚገባው ዲሞክራሲ የትግል ሂደት ውጤት እንጂ መና እንዳልሆነና አሸናፊ ከተሸናፊ ጋር የመቻቻል ግዴታ እንዳለበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ስለባለጋራዎቻችን ኡምቤርቶ ኢኮ የሚለንን ማዳመጥ እጅግ ተገቢ ነው፤
“መልካም ምግባር የሚከሰተው የባለጋራዎቻችንን መኖር በመካድ ሳይሆን፣ ባላጋሮቻችንን በቅንነት በመረዳት፣ በነሱ ቦታ ሆነን ነገሮችን በመመልከት ነው፡፡ ሌሎችን በቅንነት መረዳት ማለት ልዩነትን ሳንክድ ወይም ቸል ሳንል፣ የአድልኦ አስተያየቶችን ማስወገድ ማለት ነው”
አንድ የሀገራችን ፀሐፊም “መቻቻል መቻል ነው፡፡ መቻል ሳይኖር መቻቻልን ማሰብ ከባድ ነው” ይለናል፡፡ ትላንት ያሳደግነውን ቂም በቀል ነቅለን መጣል አለብን፡፡ ከዓመት ዓመት አንድ ዓይነት መላ ምት እየተለምን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በአቦ ሰጡኝ መጓዝ፣ ባለበት ሂድ እንጂ ወደፊት አያራምደን፡፡ One step forward two steps back እንደሚሉት እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ ጐታች ጉዞ ነው፡፡ የለማውን ግብ ለማድረስ ሙስና ማነቆ ከሆነ፣ የለማውን ፍሬ ሳንበላ ኢ - ፍትሐዊነት ካገደን፣ የለማውን ወደበለጠ ደረጃ እንዳናደርስ “የአብዬን እከክ ወደምዬ ልክክ” እንቅፋት የሚሆንብን ከሆነ አካሄዳችን ውሽልሽል ነው፡፡ ዕድገታችን ቁልቁል ነው፡፡ በወጉ ያልተንከባከብነው ዕድገት ለወሬ እንጂ ለተግባር አይመችም፡፡ ከጐረቤቶቻችን በዚህ በዚህ እንበልጣለን፤ በዚህ በዚህ እንሻላለን፤ በዚህ በዚህ በአብዛኛው አብረን እየተጓዝን ነው፣ ማለት በተጨባጭ ዕድገትና ማንነታችንን አያሳይም፡፡ ይልቁንም፤ “ተንከባክባ ያላሳደገችውን ልጅ፣ የእከሌ ልጅ እኩያ ነው ትላለች” የሚለውን ተረት ነው የሚያረጋግጥ!  


ኢህአዴግ - አንድነት - ወህኒ ቤት

* ከ20 በላይ ሠላማዊ ሠልፍ ብመራም አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም
* ኢህአዴጎች ለልጅ ልጆቻቸው የማይቆጭ ነገር ትተው ቢያልፉ መልካም ነው
* ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁትና የተጠመቅሁት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው

 የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው፤በሽብር ወንጀል ተጠርጥሮ አንድ አመት ከ8 ወር ያህል በእስር ላይ የቆየ ሲሆን ባለፈው ማክሰኞ በዳኛ ትዕዛዝ ከማረሚያ ቤት ሊለቀቅ ችሏል፡፡ ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው የሚለው ሃብታሙ፤የመጀመሪያ ፓርቲውም ኢህአዴግ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከኢህአዴግ ጋር በምን ተቀያየመ? ተቃዋሚዎች እንዴት ተቀበሉት? ለእስር የዳረገው ምንድን ነው በአንድነት እጣፈንታ ምን ተሰማው? ወጣቱ ፖለቲከኛ ሃብታሙ አያሌው፤ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር ከእስር በተፈታ ማግስት በፖለቲካ ህይወቱ፣እምነቱና ፈተናዎቹ ዙሪያ አውግተዋል፡፡

ከአንድነት ፓርቲ ብንጀምርስ? እንዴት ነበር ፓርቲውን የተቀላቀልከው?
በኢትዮጵያ ውስጥ በወቅቱ ከነበሩ ፓርቲዎች የተሻለ ነው ብዬ ነበር የተቀላቀልኩት፡፡ በወቅቱ በሠላማዊ ትግሉ ላይ የተሻለ ነገር ማምጣት ይችላል የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ አንደኛ የሊበራል አስተሳሰብ ይዞ ወደ ግራ ሆነ ወደ ቀኝ ጠርዙ ሳይሄድ መካከለኛውን የያዘ ነበር፡፡ ይሄ አስተሳሰብ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚጠየቁ የፖለቲካ መብቶችን፣ የቡድን ጥያቄዎችን ይመልሣል፡፡ ማዕከሉን ሊብራሊዝም አድርጓል፡፡ መካከለኛ ፓርቲ ሆኖ መሄዱ ለምርጫዬ አንዱ መሠረት ነበር፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ሉአላዊነትና አንድነት ላይ ያለው አቋም ጥሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም በፓርቲው ውስጥ ተስፋ የሚጣልባቸው ወጣት አመራሮች ነበሩ፡፡ ከነሱ ሥር በመሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የሆነ የዲሞክራሲ ሥርዓት ለመገንባት እድል ይኖራል፡፡ ስለዚህ ከነዚህ ሰዎች ጋር መታገል አለብኝ ብዬ፣ ጥያቄው ሲቀርብልኝ ቀጥታ በብሔራዊ ም/ቤት ደረጃ ነበር አባል የሆንኩት፡፡  
ከዚያ በፊት ግን በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚመራው ኢህአዴግ አባል ነበርክ፡፡ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ወደ ሊበራል ያደረግኸው ሽግግር አላስቸገረህም?
የኢህአዴግን አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከማወቄ በፊት የፖለቲካ እውቀቱም እምብዛም አልነበረኝም፡፡ ከፖለቲካ ጋር የተዋወቅሁበት ጊዜ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በ1997 በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከሚከተሉና ከሚፈልጉ ወጣቶች አንዱ ነበርኩ፡፡ በእርግጥ ከ3 ዓመታት በላይ በውጭ ሀገር በትምህርትም በስራም ቆይቼ የተመለስኩት በ1997 አጋማሽ ላይ ነበር፡፡ ስመጣ የለውጡን እንቅስቃሴ በሚገባ ተከታትያለሁ፡፡ በወቅቱ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማድረግም ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ከምርጫው በኋላ ቅንጅት ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ወደ ሌላ ምዕራፍ አሸጋገረኝ፡፡ እንደ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የራሴን ስራ እየሠራሁ ኑሮዬን ቀጠልኩኝ፡፡
በ1999 ዓ.ም መጨረሻ ላይ የአዲስ አበባ ወጣቶች ፎረም ሲመሠረት፣ በወቅቱ የሚያውቁኝ አመራሮች ጥሪ አድርገውልኝ፣ ምስረታው ላይ እንድገኝ አደረጉኝ፡፡ የፎረሙ ምስረታ በጣም ሳቢ ነበር፡፡ በኋላ የሚከተለው አካሄድ የተሳሳተ መሆኑን አውቀን፣ መታገል እስከጀመርንበት ድረስ መነሻው ላይ ባይቀለበስ ጥሩ ነበር፡፡ ከመንግስት ጋር መቀራረብ፣ መመካከር፣ በሀገር ጉዳይ ላይ ወጣቱ ተሣታፊ እንዲሆን ማድረግ ነበር ዓላማው፡፡
 የመንግስት አመራሮች ተጠያቂ መሆን በሚገባቸው መጠን ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚከታተል፣ የሚቆጣጠር የህብረተሰቡ በተለይም የወጣቱ ተወካይ እንዲሆን ነበር የታሰበው፡፡ ጥቅሙንም ተሣትፎውንም ማስከበር የሚችል፣ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት የፀዳ በሚል ነበር የተመሠረተው፡፡
እየቆየን ስንሄድ በፎረሙ አመራር ላይ ለነበርን ወጣቶች የፓርቲ አባልነት ጥያቄ እየቀረበልን መጣ፡፡ ፖለቲካን ለመካን ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ምንድን ነው እየተባለ እንድንሰለጥን ተደረግን፡፡ ያኔ የኢህአዴግን ፖሊሲዎች በዝርዝር ለማንበብ ሞከርኩኝ፡፡ ከእኔ ውስጣዊ አቋም ጋር ይሄዳል አይሄድም የሚለውን ስገመግም ቆየሁ፡፡
የሶሻሊዝሙ ጐራ ምንድን ነው? የሊበራሊዝሙስ? አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከእነዚህ ጋር ያለውን አንድነትና ልዩነት ሠፊ ጊዜ ወስጄ አጠናሁ፡፡ በ2001 ዓ.ም ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮችን አላጌ ወስዶ ባሰለጠነ ጊዜ ተሣታፊ በመሆን በአጠቃላይ በድርጅቱ አስተሳሰብ ላይ በቂ ግንዛቤ ያዝኩኝ፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ የነበረህ ተሳትፎ ምን ያህል ነበር?
በአብዮታዊ ዲሞክራሲ ላይ ሠፊ ክርክሮች ሲደረጉ በንቃት ከሚሳተፉት አንዱ ነበርኩ፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ የማይነኩ የሚባሉ እንደ የመሬት ፖሊሲው፣ በቋንቋ ላይ የተመሠረተው ፌደራሊዝም --- የመሳሰሉ ጉዳዮችን አንስቼ እከራከራቸው ነበር፡፡ በተለይ የቋንቋ ፌደራሊዝም እነ ራሺያን ከመበታተን እንዳላዳናቸው በመረዳቴ፣የኢህአዴግ ፌደራሊዝም እንደማይጠቅመን ፊት ለፊት እነግራቸው ነበር፡፡ ሌላው “ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት” የሚባል ነገር አለ፤ ግለሰቦችን ፈላጭ ቆራጭ የሚያደርግ ነው፡፡ አንድ መሪ የተናገረውን ከመቀበል ውጪ ሌላ ሃሳብ ማራመድ የማይቻልበት አካሄድ ነው፡፡ በኢህአዴግ ቤት ውስጥ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ እንደማይፈቀድና ከነውር እንደሚቆጠር ተረዳሁኝ፡፡ እነዚህንና መሠል ጉዳዮችን በየትኛውም መድረክ ላይ በድፍረት እቃወማቸው ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በነበሩበት ስብሰባ ላይም በግልጽ “ተሳስተሃል” ብዬ አውቃለሁ፡፡ አቶ መለስ “ይሄን አስተያየት እንቀበለዋለን” ያሉበት ጊዜ አለ፡፡ “ለምን እንዲህ ያለ ጥያቄ ይጠይቀኛል” ብለው የተቃወሙበት ጊዜም አለ፡፡
በኢህአዴግ ውስጥ ምን ያህል ቆየህ?
ከ2001 እስከ 2002 አጋማሽ ድረስ በኢህአዴግ ውስጥ ቆይቻለሁ፡፡ በወቅቱ ፖሊሲውን በዝርዝር ለመረዳት ችያለሁ፡፡ እነዚህን በሂደት የተረዳኋቸውንና ያላመንኩባቸውን ጉዳዮች ይዤ ዲሞክራሲያዊ ትግል ማድረግ ነበረብኝ፡፡ ኢህአዴግ ጭፍንና አምባገነናዊ አካሄድ ነው የሚከተለው፡፡ በኢህአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች ጐራ የተሠለፉ ጫፍ የረገጡ የ60ዎቹ ፖለቲካ አራማጆች አሉ፡፡ ይሄን ጭፍንነት ይዘው ትግሉን እየጐተቱ ያሉ ሰዎች ስፍራውን ለአዲሱ ትውልድ እንዲለቁ መሠራት አለበት የሚል ጽኑ እምነት ነበረኝ፡፡
አንድነት ውስጥ ዘመናዊ የሚባሉ፤ ለዚህች ሀገር የሚጠቅሙ ወጣቶች ወደፊት እንዲመጡ ከገባሁበት ጊዜ ጀምሮ ታግያለሁ፡፡ አማራጮች እንዲፈልቁ፣ ፓርቲው ከህዝብ ጋር የበለጠ እንዲተዋወቅ ጥረት አደርግ ነበር፡፡ ለኔ ትልቅ ስልጣን ከተባለ ከተቃዋሚ ፓርቲ ይልቅ ኢህአዴግ ቤት ውስጥ የነበረኝ ነው፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ባለስልጣን ሆነህ የፈለከውን በኩርኩም እየመታህ ትሄዳለህ፡፡ አንድነት ጋ ባለስልጣን ስትሆን ግን እንደዚህ እስር ቤት ነው የምትወረወረው፡፡ ይሄን ጠንቅቄ አውቅ ነበር፡፡
እኔ ውስጣቸው አባል ሆኜ ብዙ ነገር ለማስተካከል፣ በሃሳብ ለመሞገት ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ፈጽሞ ሃሳብ የሚስተናገድበት ሁኔታ ኢህአዴግ ቤት ውስጥ የለም፡፡ የምችለውን ሁሉ ከጣርኩ በኋላ በተአምር የሚቀየር ነገር ባለመኖሩና በሮች በሙሉ በመዘጋታቸው ከፓርቲው ወጥቼ የጥሞና ጊዜ ወሰድኩ፡፡ ከዚያ ደግሞ የባለራዕይ ወጣቶች ማህበርን መሠረትን፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያዊነት ስሜት እየተሸረሸረ መሆኑ ያሳስበኝ ስለነበር ማህበሩ በዚህ ረገድ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ነበር የመሠረትነው፡፡ የፌደራሊዝም ስርአት ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ፤ ነገር ግን አሁን ቋንቋን፣ ዘርን --- መሠረት ያደረገው ስርአት ሃገሪቱ ወደማትወጣው ችግር ውስጥ የምትገባበት እንዳይሆን እፈልጋለሁ፡፡ በኢህአዴግ አካሄድ ሀገሪቱ አደጋ ላይ ትወድቃለች የሚል እምነት ነበረኝ፡፡ ደግሞም የያዝኩት እምነት ትክክል እንደነበር አሁን እያየነው ያለው ውጤት ምስክር ነው፡፡ የልዩነቱ ድንበር መድመቅ አልነበረበትም፡፡
በ1983 ኢህአዴግ ሲገባ ይዞት የመጣው አስተሳሰብ ጊዜው በሚጠይቀው ልክ የነበረ ነው፡፡ በወቅቱ በብሔር ጥያቄ ነፍጥ ያነገቡ ከ18 ድርጅቶች በላይ ነበሩ፡፡ እነዚህን “አንዲት ኢትዮጵያ” ቢሏቸው ኖሮ አስቸጋሪ ነበር፡፡ እንደገና ጦርነቱ ይቀጥላል፡፡ ነገር ግን በየጊዜው የማህበረሰቡን እድገትና ስነልቦናዊ አንድነት እየተመለከተ፤ የነበሩትን ስጋቶችና አለመተማመኖችን እየሰበረ፣  ብሔራዊ አስተሳሰብን መገንባት ነበረበት፡፡ ቆይተው ተቃውሞው ሲበረታ ነው “የሰንደቅ አላማ ቀን” የመሳሰሉትን የጀመሩት፡፡ ኢህአዴጐች፤ “ልዩነታችን አንድነታችን፣ አንድነታችን ውበታችን” የሚሉት ነገር አላቸው፤ ግን ከልዩነታችን አንድነታችን ይበልጣል ብለን ብንይዘው፣ ሰው ውስጥ የአንድነት ሃሳብን ማሳደግ ይቻላል፡፡ በባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ውስጥ በዚህ መልኩ ብዙ ጥረት አደረግን፤ግን ኢህአዴግ አንድ የተሰባሰበ አካል ሲያይ ይፈራል፡፡ እናም ማህበሩን እንዳይንቀሳቀስ አደረገው፣ እኛም ስንታሰር ስንፈታ ቆየንና --- በመጨረሻም ማህበሩ ተዳክሞ ተበተነ፡፡ ከዚያ በኋላ የያዝኩት አላማና አስተሳሰብ ለሀገሬ ይጠቅማል፤ ግን እንዴት ልታገል ብዬ ሳስብ አንድነት ፓርቲን አማራጭ አድርጌ መታገል ጀመርኩ፡፡ በዚህች ሀገር ከጦርነት በመለስ ያለው ትግል መኖር አለበት፡፡ አንዱ ሌላውን በሃይል የሚጥልበት አካሄድ መቆም አለበት፡፡ በሃይል የሚመጣ አካል፣ በሃይል ብቻ ነው የሚወድቀው፡፡ “ሰይፍ የሚያነሳ በሠይፍ ይሞታል” ነው የሚለው መጽሐፍ ቅዱስም፡፡ ስለዚህ ሰይፍ ማንሳት ሳያስፈልግ፣ በሠላማዊ ትግል መንግስት መቀየር አለበት የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡
የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ከሆንክ በኋላስ ችግሮች ቀነሱልህ?
በተቃውሞው ጐራና በኢህአዴግ መካከል ያለው ልዩነት በራሱ ለወጣቱ እጅግ በጣም ፈተና ነው፡፡ በሁለቱም ውስጥ ጫፍና ጫፍ የረገጡ ሃይሎች አሉ፡፡ ያንን መስበር እጅግ ከባድ ነው፡፡ እነዚህን አመራሮች የሠለጠነ አስተሳሰብ ባላቸው ሰዎች መቀየር አንዱ አማራጭ ነው፡፡ እኔ ኢህአዴግ ውስጥ ሃሳብ እንደልብ ማንሸራሸር አይቻልም ብዬ ወደዚኛው ስመጣ፣ “ወያኔ” በደንብ አሠልጥኖ ልኮብናል” የሚል አቋም ይዘው አላሠራም ያሉበት ሁኔታ ነበር፡፡ ይሄን ሁሉ ታግለን ፓርቲው እየተጠናከረና ለስርአቱ አደጋ እየሆነ ሲመጣ፣ኢህአዴግ “እነዚህን ከጀርባ ሆኖ የሚገፋ አለ” ብሎ ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ገባ፡፡
እኔ ወደ ተቃውሞ ጐራ ከገባሁ በኋላ ከ20 በላይ ሠላማዊ ሠልፍ መርቻለሁ፡፡ አንዲት ጠጠር አልተወረወረችም፡፡ በሆስፒታሎች አካባቢ ስናልፍ በፍፁም ጨዋነትና ፀጥታ ነበር፡፡ ግን በመጨረሻ አሸባሪ ነው የተባልነው፡፡ በተቃውሞው ጐራ ደግሞ “ወያኔ ነው የላከብን” እየተባልኩ በመሃል ላይ በሁለት እሣት እየተጠበስኩ ነው ትግል ሳደርግ የነበረው፡፡ ሌላው በተቃውሞ ጐራ ያለው ችግር አንዳንዱ ዝም ብሎ የጡረታ ጊዜውን የሚያሣልፍበት ነው የሚመስለው፡፡ ምንም ለውጥ አያመጣም ግን ዝም ብሎ እየተቃወመ መኖርን የመረጠ ነው፡፡ ይሄ መለወጥ አለበት፤ አካሄዱ ትክክል አይደለም፡፡ ዘመናዊ ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንገንባ ባልን ነው መከራ የምናየው፡፡ እኔም ሆንኩ አብረውኝ የታሠሩ ጓዶቼ ይሄ ነው አመለካከታችን፤ ግን ያልተገባ ዋጋ እንድንከፍል ነው እየተደረግን ያለነው፡፡ ነገ ይህቺን ሀገር ሁሉም ትቷት ይሄዳል፤ ግን ለልጅ ልጆቻቸው የማይቆጭ ነገር ትተው ቢያልፉ መልካም ነው፡፡
ወደ እስር የተወሰድክበት ሁኔታ እንዴት ነበር?
እኔና ጓደኞቼ የተያዝነው ለምርጫ 2007 ዝግጅት በሚደረግበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ኢህአዴግ እኛን ደጅ ትቶ ምርጫ ማካሄድ አልፈለገም፡፡ ወደፊትም የሚፈልግ አይመስለኝም፡፡ በወቅቱ ኢህአዴግን በሃሳብ ማሸነፍ እንደሚቻል እኛ በተግባር ማሳየት እንችል እንደነበር ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ሃሳብ በማንፀባረቅ ብቻ ኢህአዴግን እንበልጠዋለን፡፡ ስለዚህ ከአነሣሣችን ከኢህአዴግ በተሻለ የህዝቡን ቀልብ እንደምንገዛ፣ ሌላ አማራጭ ይዘን እንደምንቀርብ ጥርጥር አልነበረኝም፡፡
በምን አይነት ሁኔታ ነበር በቁጥጥር ስር የዋልከው?
እኔ በወቅቱ ባንክ ቤት ነበርኩኝ፡፡ የፓርቲያችንን ፕሬዚዳንት ጨምሮ 6 አመራሮች ወደ አሜሪካን ሀገር ሄደን፣ በስድስት ስቴቶች ላይ ከዳያስፖራው ጋር ለመወያየት መድረክ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ለዚህም የመጨረሻውን የቪዛ ክፍያ ጨርሼ፣ የሁሉንም አመራሮች ፎርም አንድ ላይ ይዤ ለአሜሪካን ኤምባሲ 4 ሰአት ላይ ለማቅረብ ልሄድ ባልኩበት ቅጽበት ነው ከእነ ፓስፖርቱ መጥተው የያዙኝ፡፡ አያያዛቸው በጣም የሚገርም ነበር፡፡ አንድ ተራ ሰው የሚይዙ አይመስሉም፡፡ ኦሣማ ቢላደን ያለ ነበር የሚመስለው፡፡ በወቅቱ የተሰማኝ፤ “ወይኔ ታሰርኩ በቃ” የሚል አይደለም፡፡ እኛ በገዛ ሀገራችን መታሰር ችግር የለውም፤ ስንቱ እየተሰደደ የበረሃ ሲሳይ ሆኖ የለም እንዴ፡፡ ልጄ 1 አመት ከ4 ወሯ ነበር፤ ከሷና ከባለቤቴ ነጥለው ወሰዱኝ፡፡ ቤቴን ፈተሹ፤ ምንም የተገኘ ነገር አልነበረም፡፡ ማዕከላዊ ለ4 ወር ቆየሁ፡፡ እኔ ፊት ለፊት የግንባር ስጋ ሆኜ የምታገል ሰው ነኝ፡፡ ከጀርባ ሆኖ የሚታገል ሰው እኮ አደባባይ አይወጣም፡፡ ሲይዙኝ እንፈጥረዋለን ብለን ያሰብነው የመድብለ ፓርቲ ስርአት ወደ ኋላ መመለሱ አሳዝኖኝ ነበር፡፡ የማታ ማታም ያው እንደሚታወቀው ፓርቲያችን እንዲፈርስ ተደረገ፡፡
በምርጫ ቦርድ ውሣኔ የአንድነት ፓርቲ አመራር ሲለወጥ ምን ተሰማህ?
እኔ በመሠረቱ ከድርጅት (ፓርቲ) ጋር የተለየ ፍቅር የለኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የመጠፋፋትና የጥላቻ ፖለቲካ እንዲቆም፣ በተቻለ መጠን ለሌላው አለም ምሣሌ የሚሆን ዲሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባ ነው ፍላጎቴ፡፡ ይሄን ማምጣት የሚችል ድርጅት ለመገንባት ነበር ስንጥር የነበረው፡፡ ግን አንድነት በዚህ ሁኔታ እንዲበተን ሲደረግ የፖለቲካ ስርአቱ አንዳች መደምደሚያ እየተሠራለት መሆኑ ገባኝ፡፡ አንድነት ስለተበተነና እኔ ስለታሠርኩ የኢትዮጵያ መድብለ ፓርቲ ስርአት ግንባታ አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ በሠላማዊ ትግሉና በህዝብ ላይ ተስፋ እንደመቁረጥ አድርጌ ስለምወስደው፣ የበለጠ መስራትና ዋጋ እየከፈልን መቀጠል አለብን የሚል እምነት አለኝ፡፡
ኢህአዴግ እግር ያወጣውን ፓርቲ እግሩን ሲቆርጥ የተቃዋሚ አመራሩ ደግሞ በቀላሉ የሚወድቅ የተልፈሰፈሰ መሆኑ፤ ቁርጠኛ የሆነ ታጋይና አመራር አለመፈጠር የመሳሰሉት ክፍተቶች ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ኩርኩም በሰደደ ቁጥር የምንፈርስ ሆነን ነው የተገኘነው፡፡ የኢህአዴግን ኩርኩም መቋቋም የሚችል ድርጅት ለመገንባት ባለመቻላችን በራሳችን በጣም አዝኛለሁ፡፡ እውነት አብሬያቸው ስታገል የነበረው ከነማን ጋር ነው? የሚለውን ሳስብ ነበር፡፡
 የማረሚያ ቤት ቆይታህን በምን ነበር የምታሳልፈው?
መፃህፍት አነብ ነበር፡፡ አብዛኛውን ጊዜዬን ያሳለፍኩት በማንበብ ነው፡፡ ወዳጆቼ የማረሚያ ቤቱን ሳንሱር ያለፉ መፃህፍትን ያስገቡልኝ ነበር፡፡ መፃህፍቶች በአስገራሚ ሁኔታ ሳንሱር ይደረጋሉ፤በማረሚያ ቤቱ፡፡ በሀገሪቷ ታትመው የተሠራጩ መፃህፍት ሁሉ ማረሚያ ቤት ለመግባት ለምን እንደሚከለከሉ አይገባኝም፡፡
 ከዚያ ውጪ እንግዲህ ቴሌቪዥን ያለ አማራጭ እንከታተላለን፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ተነስቶ ጠ/ሚኒስትሩ ጭምር እንዲያ ሲናገሩ የተስፋ ጭላንጭ ታይቶኝ ነበር፤ነገር ግን ወዲያው በማረሚያ ቤቱ የሚፈፀመው ተግባር እንኳን እየተጠናከረ ሄደ፡፡ መጽሐፍቶች ላይ የሚደረገው ክልከላም ተጠናከረ፡፡ ሽብርተኛ ተብለን እንደተከሰስነው ሁሉ፣ልክ እንደ አሸባሪ ከሰው እንድንገለል ተደረግን፡፡ ይሄ ይገርመኛል፡፡ እዚያ ያለው አካል ለለውጥ ዝግጁ እንዳልሆነ ነው የተረዳሁት፡፡ ከማንበብ ውጪ የሚተርፈኝን ጊዜ እዚያ ለሚገኙ ታራሚዎች የህግ ድጋፍ አገልግሎት በነፃ እሰጥ ነበር፡፡ የክስ ማቆሚያ ንግግራቸውን ማዘጋጀት፣ መሪና መስቀለኛ ጥያቄያቸውን ማደራጀት የመሳሰሉ የህግ አገልግሎት በነፃ እሰጥ ነበር፡፡
በማረሚያ ቤት ቆይታህ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በEBC ስትከታተል እንደነበር ነግረኸኛል፡፡  ምን ታዘብክ ታዲያ?
አንዱ እንግዲህ የወቅቱ የኢህአዴግ አጀንዳ የሆነው የመልካም አስተዳደር ጉዳይ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደር ውስጥ ችግሩን የፈጠረው ሰው ችግሩን አይፈታም፡፡ እኔ እንደዚህ አይነት እምነት አለኝ፡፡ ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግር ፈጥሯል፡፡ መልካም አስተዳደር ግን ማምጣት አልቻለም፡፡ ችግሩን ራሱ መፍታት ይችላል ወይ ስንል? ኢህአዴግ ራሱን መፈተሽ አለበት፡፡ ሙስና አለ ከተባለ ሙሰኞች አይደሉም ችግሩን የሚፈቱት፡፡ ስለዚህ መጀመሪያ ማድረግ ያለበት የችግሩን ፈጣሪዎች ለይቶ ማውጣት ነው፡፡ ከዚህ በኋላ ነው ስለ መልካም አስተዳደር ማውራት ያለበት፡፡ ጠ/ሚኒስትሩም ተስፋ ቆርጠው፤ “ከዚህ ስትወጡ ወደ የኔት ዎርኮቻችሁ ነው የምትሄዱት” ብለ
ዋል፡፡ እንግዲህ ሁሉንም ወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
ከአሁን በኋላ ምን አሰብክ? በፖለቲከኝነቱ ትቀጥላለህ … ?
እውነቱን ለመናገር ገና አላወቅሁም፡፡ አሁን ምንም ማለት አልችልም፡፡ ዝም ብዬ ተራ የፖለቲካ ታጋይ ሆኜ ነው የምቀጥለው? ወይስ  የሚለውን አልወሰንኩም፡፡ ገና ብዙ ማየትና ማገናዘብ አለብኝ፡፡
በመጨረሻ…ምን ትላለህ ?
 እናንተ ከእስር መልስ ሃሳቤን ሰው እንዲሠማው ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ፡፡
እየታሠርን ሁሌም ስንፈታ ስራችን መደሰት ቢሆንም ጓደኞቼ አብረውኝ ባለመውጣታቸው ደስታዬ ሙሉ እንዳይሆን አድርጐታል፡፡ ከዚያ በተረፈ ግን ባለቤቴ ቤተልሄም አዛናውና ልጄ ኤማንዳ ሃብታሙ፣ እህቴ ገነት አያሌውና ወንድሞቿ ከባድ ዋጋ ከፍለዋል፡፡
ጠበቃ ተማም አባቡልጉና አመሃ መኮንን ላደረጉልኝ ድጋፍና ትብብር በሙሉ አመሰግናለሁ፡፡ ከእግዚአብሔር ቀጥሎ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ በሀገርም በውጪም ላሉት ምስጋናዬ ይድረስ፡፡


     ኢትዮጵያና ኬንያ በሶማሊያ የተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ጦር (አሚሶም) ከአልሻባብ ጋር የሚያደርገውን ውጊያ ለማገዝ፣ የጦር ሂሊኮፕተሮችን ሊሰጡ ነው ሲል የኬንያው ዘ ስታር ትናንት ዘገበ፡፡አሚሶም የአልሻባብ ታጣቂዎችን ለመደምሰስ በሚያደርገው ውጊያ፣ ተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች አስፈላጊ ሆነው በመገኘታቸው፣ አገራቱ  ሄሊኮፕተሮችን ለማቅረብ መፍቀዳቸውን ዘገባው አስታውቋል፡፡ የሄሊኮፕተሮችና ብዛት ባይገለጽም፣ የሰላም አስከባሪው ወታደሮች በአየር ላይ ድጋፍ እጦት ሳቢያ የገጠሟቸውን እንቅፋቶች ለማስወገድ ያገለግላሉ መባሉን ዘገባው ገልጿል፡፡
ኡጋንዳ ለሰላም አስከባሪው አራት ሄሊኮፕተሮችን ለመስጠት ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም፣ ሶስቱ ሄሊኮፕተሮች በ2012 ወደ ሶማሊያ በመብረር ላይ ሳሉ ከተራራ ጋር ተጋጭተው መከስከሳቸውን ተከትሎ ሃሳቧን መቀየሯንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የሰላም አስከባሪ ወታደሮችን በማሰማራት እንዲሁም የጦር መሣሪያና ቁሳቁስ በማቅረብ፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያና ሩዋንዳ እንደሆኑ ዘኢኮኖሚስት መዘገቡ ይታወሳል፡፡

ሠኞ እለት አንድ ሰው በባቡር አደጋ ህይወቱ አልፏል የኢትዮ - ጅቡቲ መስመርን ሁለቱ ሃገራት በጋራ ያስተዳድራሉ  

    በአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ እያጋጠመ ያለውን የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ለመቋቋም ጀነሬተር ሊገዛ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ባቡሩ ባለፈው ሠኞ ሥራ ከጀመረ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በደረሰ አደጋ የአንድ ሠው ህይወት ጠፍቷል፡፡
የጀነሬተር ግዢውን ለማከናወን የምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በጋራ አጥተነው ወደ ሂደት እየተገባ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የኮሚኒኬሽን ኃላፊ ገልፀዋል፡፡
የትራንስፖርት አገልግሎቱ ዋነኛ ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ የሚገዙት ጀነሬተሮች መብራት እንደጠፋ ወዲያው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ ትራንስፖርቱ ሳይቋረጥ ያለ እንከን አገልግሎቱን ለመስጠት ያስችላል ብለዋል፡፡
የከተማዋ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ከጀመረ ወዲህ አንድም አደጋ ደርሶ እንደማያውቅ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ባለፈው ሠኞ ከምሽቱ 4 ሰዓት ላይ በኡራኤልና መገናኛ መሃል ባለው መስመር አጥሩን በመዝለል ቀጥታ የባቡሩ መስመር ላይ የገባ ግለሰብ ህይወቱ ማለፉን  ገልፀዋል፡፡ ግለሰቡ የአዕምሮ ህመምተኛ ሳይሆን እንደማይቀር መጠርጠሩንና በህክምና ለማረጋገት እየተሞከረ እንደሆነ የጠቀሱት ኃላፊው፤ ባቡሩን ማቆም በማይቻልበት ቅርብ ርቀት ላይ የነበረ በመሆኑ ህይወቱን ማትረፍ ሳይቻል መቅረቱን ኃላፊው ጠቅሰዋል፡፡ ባቡሮቹ ጠዋት 12 ሰዓት ስራ ከመጀመራቸው በፊት በየቀኑ ከሌሊቱ 10 ሰዓት ጀምሮ ተሳፋሪ ሳይጭኑ ሙከራ እንደሚያደርጉና አጠቃላይ የቴክኒክ ፍተሻ ተደርጎላቸው የሚጀምሩ በመሆኑና ህብረተሰቡ ለአደጋ ያለው ግንዛቤ እያደገ በመምጣቱ፣ የተፈራውን ያህል አደጋ አለመከሰቱን ተናግረዋል ኃላፊው፡፡
በአሁን ሰዓት ለከተማዋ ትራንስፖርት በሁለቱ መስመሮች 28 ባቡሮች የተመደቡ ሲሆን 10 ባቡሮች በቅርቡ ይጨመራሉ ተብሏል፡፡ አሁን ያሉት በቀን እስከ 120 ሺህ ሰው በማጓጓዝ በቀን እስከ 4 መቶ ሺህ ብር ገቢ እያስገቡ መሆኑንም ኃላፊው ጠቁመዋል፡፡ ለአካል ጉዳተኞችና ለአቅመ ደካሞች ታስበው በተወሰኑ ባቡር ጣቢያዎች የተዘጋጁ ሊፍቶችና ስካሌተሮች ቀደም ብሎ አገልግሎት እንዲሰጡ በተደረገበት ወቅት በጥንቃቄና በአጠቃቀም ችግር ጉዳት አጋጥሟቸው እንደነበር ያወሱት አቶ ደረጃ፤ ጥገና ከተደረገላቸው በኋላ በዚህ ወር መጨረሻ አገልግሎት መስጠት ይጀምራሉ ብለዋል፡፡ የወረቀት ቲኬቶች ለመጭበርበር ምቹ መሆናቸውን የጠቀሱት ሃላፊው፤ የኤሌክትሮኒክስ ቲኬት አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ ቲኬቶቹ በውጭ ሃገር እንዲዘጋጁ መታዘዙንና የሂሳብ መሙያ ማሽኖች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በቅርቡ አገልግሎቱ ይጀምራል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት ሲጀምር 58 በመቶ ያህሉ የባቡር ሠራተኞች ቻይናውያን፣ 42 በመቶ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን ያስታወሱት ኃላፊው፤ በአሁን ወቅት ኢትዮጵያውያኑ በረዳትነት በስፋት ባቡሩን እየዘወሩ መሆኑንና ከ3 ዓት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ከቻይናውያኑ እንደሚረከቡ ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
የድርጅቱ ባለሙያዎች ተቋሙ ያለውን አቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ ደሞዝ እንደሚከፈላቸውና ጥቅማ ጥቅም እንደሚያገኙ የጠቀሱት አቶ ደረጀ፤ በቃሊቲና በሃያት የባቡር ማሳደሪያዎች አካባቢ የመኖሪያ ቤት እንደተሰጣቸውና የምግብ አገልግሎት እንዲያገኙም ተደርጓል ብለዋል፡፡   
የአዲስ አበባ - ጅቡቲ የባቡር መስመርን የስራ ክንውን በተመለከተ የተጠየቁት ኃላፊው፤ አጠቃላይ ስራው ከ90 በመቶ በላይ መጠናቀቁን፣ በአሁን ሰዓት የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታና ከባቡር ጣቢያዎች ወደ ዋና አውራ ጎዳናዎች የሚያደርሱ መንገዶች እየተገነቡ መሆኑን በመጥቀስ ባቡሩ በቅርቡ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል ከተባለው ጊዜ የዘገየ ቢሆንም በዚህ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ ሰራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ አንገብጋቢ ለሆነው የድርቁ ችግር ሲባል ይፋዊ የሙከራ ስራ አለመጀመሩን ያወሱት አቶ ደረጀ፤ ከህዳር 11 ቀን 2008 ዓ.ም ጀምሮ ለ14 ጊዜ ያህል በዲዝል በሚሰሩ ባቡሮች የእርዳታ ስንዴ እስከ አዳማ ድረስ መጓጓዙን አስታውቀዋል፡፡
ባቡሩን ሥራ ለማስጀመር የጅቡቲና የኢትዮጵያ መንግስታት ስምምነት እንደሚያስፈልግ ያወሱት አቶ ደረጀ፤ የባቡር አገልግሎቱን የሚያስተዳድር ኩባንያ ለማቋቋምና የማናጅመንት ኮንትራት ለመስጠት በሁለቱ ሃገራት መካከል ውይይት እየተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር መስመር የሁለቱ ሃገራት የጋራ ንብረት መሆኑንና የትርፍ ክፍፍልንና የእዳ አከፋፈልን በተመለከተም ሀገራቱ እየተወያዩ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ለወደፊት በመስመሩ ላይ የሚሰሩ ባለሙያዎችም ከሁለቱ ሃገሮች የተውጣጡ ይሆናሉ ተብሏል፡፡

ባለፈው ጥቅምት 1 ሚ. ቶን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ አውጥቶ ነበር

   በአንዳንድ አካባቢዎች ድርቅ መከሰቱን ተከትሎ የምግብ እህል ክምችቱን ለማሳደግ እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት፣ 70 ሺህ ቶን ስንዴ ለመግዛት ሰሞኑን አለማቀፍ ጨረታ ማውጣቱን ኤዢያዋን የተባለው ድረገጽ የአውሮፓ የንግድ ኩባንያዎችን ጠቅሶ ትናንት ዘገበ፡፡መንግስት ግዢውን የሚፈጽመው ከአለም ባንክ አለማቀፍ የልማት ማህበርና ከሌሎች ለጋሾች ባገኘው ገንዘብ እንደሆነ ኩባንያዎቹ መግለጻቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጨረታው የሚዘጋውም በመጪው ማክሰኞ እንደሆነ መጠቆማቸውን ገልጧል፡፡የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ወራት ተደጋጋሚ ጨረታዎችን ማውጣቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው በጥቅምት ወር 1 ሚሊዮን ቶን ስንዴ ለመግዛት ጨረታ አውጥቶ እንደነበርና የመጨረሻው ጨረታም በጥር ወር መጀመሪያ ላይ 70 ሺህ ቶን ለመግዛት ያወጣው አለማቀፍ ጨረታ እንደሆነ ገልጧል፡፡የዝናብ እጥረት መከሰቱን ተከትሎ በአገሪቱ የምግብና የውሃ እጥረት መከሰቱንና መንግስት የከፋ የምግብ እጥረት ችግር ተጠቂ የሆኑ 10.2 ሚሊዮን ዜጎችን ለመታደግ እየተደረገ ያለውን ጥረት እንዲደግፉ ባለፈው ወር ለአለማቀፍ ለጋሾች ጥሪ ማቅረቡንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

   በየውብዳር አንበሴ ተጽፎ የተዘጋጀውና የገዳ ስርዓት ከዘመናዊ ዲሞክራሲ ጋር ያለውን አንድነት የሚያስቃኘው “Gada System፡ A blue Print for Democracy” የተሰኘው ዘጋቢ ፊልም፤  ከትላንት በስቲያ ምሽት በኦሮሞ ባህል ማዕከል ተመረቀ፡፡ የ38 ደቂቃ ርዝመት ያለውና በተስፋዬ  ፊልም ፕሮዳክሽንና ፕሮሞሽን የተሰራው ዘጋቢ ፊልም ቀረፃው በጉጂ ዞን የተካሄደ ሲሆን በገዳ ስርዓት ስር ያሉ ህዝቦች ዲሞክራሲን እንዴት እንደሚተገብሩ በስፋት ያስቃኛል ተብሏል፡፡ በምርቃቱ ላይ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የአካባቢው ህዝብ ተወካዮችና የባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎች  እንደተገኙ አርቲስት ተስፋዬ ማሞ ተናግሯል፡፡

  በቲያትር መልክ ተዘጋጅቶ ለእይታ ይበቃል
    ደራሲ ጄ ኬ ሮውሊንግ፤ ሃሪ ፖተር በሚል ርዕስ በተከታታይ ስታሳትመው የቆየችው ተወዳጅ መጽሃፍ 8ኛው ክፍል ሃሪ ፖተር ኤንድ ዘ ከርስድ ቻይልድ በሚል ርዕስ በመጪው ሃምሌ ወር ለንባብ እንደሚበቃ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደራሲዋ ስምንተኛ መጽሃፍ ለገበያ እንደሚበቃ ባለፈው ረቡዕ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በመጽሃፍ ሽያጭ ሰንጠረዥ በቀዳሚነት መቀመጧ ተነግሯል፡፡ የታተመው መጽሃፍ በ29.99 ዶላር፣ በሶፍት ኮፒ የተዘጋጀው ደግሞ በ14.99 ዶላር በገበያ ላይ እንደሚውል በተነገረለት የመጽሃፉ የምረቃ ስነስርዓት ላይ የመጽሃፉ ታሪክ በቲያትር መልክ ተዘጋጅቶ በለንደኑ ፓላስ ቲያትር ለእይታ ይበቃል ተብሏል፡፡
የሃሪ ፖተር የመጨረሻው ክፍል እ.ኤ.አ በ2007 ለንባብ መብቃቱ ይታወሳል፡፡

  - በሙስና ተጠርጥረዋል ቢባልም፣ በስነ-ምግባራቸው እንደሚታወቁ ተነግሯል
           - ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ የመከላከያ ሚኒስትሩን በሞርታር አስገድለዋል
    የሰሜን ኮርያ የጦር ሃይል አዛዥ ጄኔራል ሪ ያንግ ጊል፤ በሙስናና የግል ጥቅምን በማካበት ህገወጥ ተግባር ተሰማርተው ተገኝተዋል በሚል ባለፈው ሳምንት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ትዕዛዝ መገደላቸውን ውስጥ አዋቂ ምንጮች እንደገለጹ ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡
ላለፉት ሶስት አመታት የአገሪቱ የጦር ሃይል አዛዥ ሆነው ያገለገሉት ጄኔራል ሪ ያንግ ጊል ለስነ-ምግባር መርሆዎች ተገዢ መሆናቸው የተመሰከረላቸው ግለሰብ ናቸው ያለው ዘገባው፣ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ጄኔራሉን ያለአግባብ የወነጀሉት ለግድያው ሰበብ ለመፈለግ ነው መባሉን ፀቁሟል፡፡ ግድያውን በተመለከተ ተጨባጭ ማረጋገጫ ባይገኝም፣ ፕሬዚዳንት ኪም ጆንግ ኡን ከወራት በፊት የቀድሞውን የአገሪቱ  የመከላከያ ሚኒስትር በሞርታር ማስገደላቸው ይህንን ግድያም ሊያስፈጽሙት እንደሚችሉ ያመላክታል መባሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በቅርቡ የፓርቲ መሪዎችን በቁልፍ የአገሪቱ ጦር ሃይል የስልጣን ቦታዎች ላይ መሾማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ይህም በጄኔራሉ ላይ ተፈጸመ ከተባለው ግድያ ጋር ሊያያዝ እንደሚችልና አዲሶቹ ባለስልጣናትም በጄኔራሉ ግድያ ውስጥ እጃቸው ሊኖርበት ይችላል መባሉንም አብራርቷል፡፡

 የቀድሞዋ  እጣ እንዳይደርስባት፣ የአደጋ መቆጣጠሪያዋ ተሻሽሏል
   ከ104 አመታት በፊት በሰሜን አትላንቲክ ውቅያኖስ በደረሰባት አደጋ በሰጠመችው ታዋቂዋ ታይታኒክ መርከብ ዲዛይን የተሰራችውና ታይታኒክ ሁለተኛ የሚል ስያሜ የተሰጣት አዲስ መርከብ፣ ከሁለት አመት በኋላ መቅዘፍ እንደምትጀምር ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
ብሉ ስታር ላይን የተባለው ታዋቂ ኩባንያ ባለቤት የሆኑት አውስትራሊያዊው ቢሊየነር ክሊቭ ፓልመር ያሰሯት ዳግማዊት ታይታኒክ፣ ከቀድሞዋ ታይታኒክ ጋር ዲዛይኗ ተመሳሳይ ቢሆንም፣ ከዘመኑ የባህር ሃይል ደህንነት መመሪያ ጋር በሚስማማ መልኩ የተወሰነ ማሻሻያ እንደተደረገባት ተነግሯል፡፡
270 ሜትር እርዝማኔ ያላት ዳግማዊት ታይታኒክ፣ ቁመቷ 53 ሜትር ሲሆን ክብደቷም 40 ሺህ ቶን ይደርሳል ተብሏል፡፡ ዘጠኝ ወለሎች ያሏት ሲሆን 2ሺህ መንገደኞችንና 900 የቀዘፋ ሰራተኞችን የመያዝ አቅም እንዳላትም ተነግሯል፡፡ ይህቺኛዋ ታይታኒክ አያድርግባትና የቀድሞዋ ታይታኒክ ክፉ ዕጣ ቢደርስባት፣ የከፋ ጥፋት እንዳይከሰት በሚል በቂ የአደጋ ጊዜ ማምለጫ ጀልባዎች እንድትይዝ ተደርጋለች፡፡ ሌሎች የባህር ላይ አደጋ መቆጣጠሪያና የህይወት አድን መሳሪያዎች በበቂ መጠን የተገጠሙላት ዳግማዊት ታይታኒክ፣ በ2008 መጀመሪያ ጂያንዙ ከተባለችው የምስራቃዊት ቻይና ከተማ ወደ ዱባይ የመጀመሪያዋን ጉዞ ታደርጋለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡