Administrator

Administrator

 በ23 ሚ ዶላር የህዝብ ገንዘብ ቤታቸውን አድሰዋል ተብሏል
    23 ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ገንዘብ ያለአግባብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ክስ የቀረበባቸውና ከሳምንታት በፊት ካባከኑት ገንዘብ የተወሰነውን ለመመለስ ቃል ገብተው የነበሩት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ በገቡት ቃል መሰረት ገንዘቡን ባለመመለሳቸው የአገሪቱን ህገ-መንግስት ጥሰዋል፣ ያባከኑትን ገንዘብ መመለስ ይገባቸዋል ሲል የደቡብ አፍሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳስተላለፈባቸው ተዘገበ፡፡
የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ባወጣው መግለጫ፣ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ እንደሚያከብሩና በቅርቡ በጉዳዩ ዙሪያ ያላቸውን አስተያየት በይፋ እንደሚሰጡ ማስታወቁም ተነግሯል፡፡
ቢቢሲ ከትናንት በስቲያ እንደዘገበው፣የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ ከመንግስት ካዝና ገንዘቡን ወጪ በማድረግ የግል መኖሪያ ቤታቸውን አሳድሰዋል በሚል ክስ የመሰረቱባቸው ሲሆን ጉዳዩን ሲከታተል የነበረው የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም፤ ፕሬዚዳንቱ ካባከኑት ገንዘብ የተወሰነውን ለመመለስ የገቡትን ቃል ባለመፈጸማቸው ጥፋተኛ መሆናቸውን ገልጾ፣ የሚመለከተው የመንግስት አካል መመመለስ የሚገባቸውን የገንዘብ መጠን አስልቶ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲያሳውቅ ትዕዛዝ አስተላልፏል፡፡
ፐብሊክ ፕሮቴክተር የተባለው የአገሪቱ የጸረ ሙስና ተቋም፣ ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ከመንግስት ካዝና 23 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በኩዋዙሉ አውራጃ የሚገኘውን የመኖሪያ ቤታቸውን፣ የቅንጦት እቃዎችን ባሟላና በዘመናዊ መልክ አሳድሰዋል በሚል ተጠያቂ እንዳደረጋቸው ያስታወሰው ዘገባው፣ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ እና ዲሞክራቲክ አሊያንስ የተባሉ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ መመስረታቸውን ገልጧል፡፡ የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ፍርድ ቤቱ በፕሬዚዳንቱ ላይ ያስተላለፈው የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዳስደሰታቸው የጠቆመው ዘገባው፣ አፍሪካን ክርስቲያን ዲሞክራቲክ ፓርቲም ፍርድ ቤቱ በገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ስር ሳይውል ነጻና ፍትሃዊ ውሳኔ ማስተላለፉ እንዳስደሰተው ገልጾ፣ የጃኮብ ዙማ ፓርቲ ስልጣን ላይ እስካለ ድረስ አገሪቱ ከአደጋ አትወጣም ሲል ማስጠንቀቁንም ዘገባው አስረድቷል፡፡

Monday, 04 April 2016 08:54

ተናዳፊ ግጥም

በዕውቀቱ የተቀኘው “የባይተዋር ገድል”
               ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ
                        [ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
-- ቁጥር 4 --
-------------------------------
የባይተዋር ገድል

በቁም መስተዋት ፊት መቆምኽ ሲጨንቅህ
የቁም መስተዋቱ፥ “ሰውነትህ የታል?” ብሎ
ሲጠይቅህ
ግድግዳው ላይ ያለች፥ የገደል ማሚቶ፥ ዝም
ማለት ፈርታ
ሳሎንህን ስትሞላው ዝምህን አባዝታ
ሕልም የቀላቀለ፥ የዝናም ነጠብጣብ፥ ጣራኽን
ሲመታ
ከመስኮትኽ ማዶ፥ የሌሊት ወፍ ሞታ
የጊዜ ስውር ክንድ
የጓሮህን ዋርካ ያላጋር ሲያስቀረው
በሌሊት ወፍ ምትክ፥ የኑሮ ገባር ወንዝ፥ አልጋህን
ሲገምሰው
“መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?”
ሲያሰኝህ ዕድልህ
ያኔ ይጀምራል፥ የባይተዋር ገድልህ።
-------------------------------
©በዕውቀቱ ስዩም
 [ስብስብ ግጥሞች፥ ገፅ 72]
-------------------------------
ገድል፥ የፃድቃንና የሰማእታት ሣይሆን አንድ ግለሰብ ከማኅበረሰቡ ሲፋተግ፥ አለበለዚያ ሥነልቦናዊ ቁስሉ፥ ስጋቱ ሲመዘምዘው ገና የሚጠብቀውን ዕንግልት ይጦቅማል። የተወለድንበት ቀዬ ናፍቆት እና የመንደራችን ትዝታ አገርሽተው ከአዲስ አካባቢ መኖር ስንጀምር ባይተዋር ያደርጉናል። አዲሱን ስንላመድ ናፍቆት እየፈዘዘ፥ ትዝታም እያፈገፈገ መንፈሳችን ወከክ ተርከክ ይላል። ይህ የስፍራ ባዳነት ትንፋሽ ያጥረዋል፤ ከራስ ጋር መላተም ነው ጥልቅ ስሜት። በዕውቀቱ የተቀኘለት ግለሰብ ግን የስፍራ ለውጥ፥ የናፍቆት የትዝታ ሰለባ አይደለም። ውስጡ የደቀቀ ንቃተ-ህሊናው ለመርገብ ያልፈቀደለት ብቸኛ ይመስላል። በሁለቱም -በብቸኝነት እና በብቻነት- የሚማቅቅ ነው። ብቻነት ከሌላው ለመቀላቀል ጉጉት እያለው ተገፍትሮ ሌጣውን የቀረ ነው። ማኅበራዊ መተሳሰር፥ ፍቅረኛ ወዳጅ ቢያገኝ ሊተርፍ ይችላል። `ብቸኝነት` ግን ከሰዎች መካከል ሆኖ፥ ቤተሰብም ኖሮት ጣዕማቸው ሲሟጠጥ፥ ከነሱ ጋር መኖር የግድ ሆኖበት ሲጐመዝዘው ባይተዋር ነው። አንድ ግለሰብ ብቸኝነት ሲመዘምዘው፥ ሲገለል፥ ለራሱ ለሌላውም ባዳ ሲሆን ለአካላዊ ሆነ ሥነልቦናዊ እንግልት ይዳረጋል። ለዚህ ባይተዋር ነው በዕውቀቱ ገለልተኛ ተራኪ መልምሎ የተቀኘው። ዝነኛ አሜሪካዊቷ ገጣሚ Sylvia Plath ባለቤቷን ተከትላ ሁለት ህፃን ልጆቿን እያባበለች ለሥነጽሑፍ አድራ ማቀቀች። ለጥልቅና ውብ ግጥሞች ወይስ ለትዳሯና ለልጆቿ ትኑር? አቃስታለች። ስለ ኅላዌ ብሎም ዕጣ ፈንታዋ እየተብሰከሰከች ግራ ተጋብታ፣ ለራሷም ጭምር ባይተዋር ሆነች፤መሸሸጊያ የሆነ ጥግ ተነፈገች። በዕውቀቱ እንዲሚለው፤ “መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?” ሲልቪያ ጭንቅላቷን ከጋዝ ምድጃ ወትፋ ትሞታለች። ብርሃኑ ድንቄ ከኑሮ ልምድ ያጠነፈፈው ሀቅ አለ። “ብቻህን ለመቆም ተዘጋጅ፤ ልጅ፥ ወንድም፥ እህት፥ ዘመድ የሚባሉት ነገሮች የምቾት ጊዜ ጌጦችና አጫፋሪዎች ናቸው።” [አልቦ ዘመድ፥ ገፅ 1] ይህ አባባል ሰክነው የልጃቸውን ምስል እያዩ ለሚፈነድቁ ይጐመዝዛል፤ ለእንደነ ሲልቪያ ግን የርዕይ መነጠቅ ውጤት ነው። አበራ ለማ በአንድ ግጥሙ ተመስጦበታል። “ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ/ አንድ እራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ።” ይህ ነው የባይተዋር ዕንቆቅልሽ።
ተራኪው አንባቢን ነው የሚያናግረው። አንተ/አንቺ ባይተዋሩን ብትሆኑ ኖሮ እያለ ከገፀባህሪዩ ተላቆ እኛን ያሳስበናል። ገላቸው እያለቀ፥ ክፍላቸው በዝምታ ተውጦ -የሌላ ሰውን አለመኖር የሚያጐላ- ብሎም በሌላው መረሳት ሰቆቃው መዘመዛቸው። የሳርተር ህልውናነት ተከታይ ይመስል፥ አንድ ውጫዊ ሃይል -እግዜር- አለ ይደርስልኛል ብሎ የሚያምን አይመስልም፤ መንፈሳዊ ምርኩዙን የተቀማ አይነት ነው። ስለት፥ ተማፅኖ፥ ፀሎት ... እንደ የተስፋ ስንቅ አይታወሱም። ገጣሚው በጥቅስ ያደመቀው መፍትሄ አሳሳቢ ነው። “`መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስመጥ ያቅተዋል ስው?`/ ሲያሰኝህ ዕድልህ/ ያኔ ይጀምራል የባይተዋር ገድልህ።”  እዚህ ላይ ተወሳሰበ። ራስን እስከማጥፋት እንደ የደነበረ በሬ ያሚያሯሩጥ፥ የሚፈገትር ብቸኝነት ሆነ። ገጣሚው ከደረደራቸው የሰቆቃ ምስሎች በኋላ “መስመጥ ያቅተዋል ሰው?” ብሎ ይጠይቃል። ከዕለታዊ ሥነልቦናዊ ማኅበራዊ ስቃይ -the pain of life- ለመገላገል ራስንም የማጥፋት ምርጫ እንዳለ ጠቋሚ ነው።
በግል ጉዳይ ሰው ተነጥቆ ከመንደሩ በብቸኝነት የተተበተበ ግለሰብ ሲማቅቅ ልብ አይል ይሆናል:: አለማየሁ ገላጋይ በ<ኩርቢቷ> አጭር ልቦለድ ሰዎች መካከል ሆና ብቸኝነት የቆረፈዳት ወጣት እናት ስሏል:: ድንገት የሞተው ባሏ ቤቱንና ንብረቱን በእናት አባቱ ስም ስላስመዘገበ ለልጇ ብላ ሁሉን ነገር ተነፍጋ፣ ተቸግራ ዝምታን ለምዳ አለማምዳም እንደ ጥላ ያለ ኮሽታ ትንቀሳቀሳለች:: ህፃን ልጇም ታዘበቻት። “እዚህ አያቶቼ ግቢ ዉስጥ የኖረችዉ በመንፈስ ህልውና ነው ማለት እችላለሁ:: ስትሄድ ኮቴዋ አይሰማም:: ለዚህ ዓለም ሙቀትና ቅዝቃዜ ምንም አይነት ምላሽ ስትሰጥ አይታይም:: አትስቅም፣  አታለቅስም:: ሆዷ ተከፍቶ ስትበላና ስትጠጣ አጋጥሞኝ አያውቅም::”[ ገፅ 53] ብቸኝነት የመጠጣት እናት አንድ ጠዋት ብድግ ብላ ጠፋች:: የባይተዋር ገድሏ የጀመረው፥ ትዳር እንደ ቀለሰች ነበር።
ስለ ባይተዋር እንግልት በወግ በትረካ ለመፃፍ አያዳግትም፤ የበዕውቀቱ ግጥም ልዩ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? በሥነግጥምና በዕውነታ መካከል መመሳሰልስ አለ ወይ? ግጥም የተለያዩ ገሃዶች (ማኅበራዊ፥ ሃይማኖታዊ፥ ፖለቲካዊ ...) ማንዘፍዘፍ ይችላል ወይ? የምናፈጥበት ሳይሆን የምናዋቅረው ቃላዊ-ዕውነታ -constructed verbal reality- ከምናብ ያንሰራራል፤ ጥበባዊ ነው። ሥነግጥም የሚዳሰስ አይደለም፤ ፈጠራ ነው። የስንኝ ትርታ፥ የተወለወለ አንጓ፥ ግጥማዊ ቅርፅ፥ ሙዚቃዊ ምት የግድ በውብ ምስላዊ ቃላት መወርዛት አለበት። ባለአንድ አንጓ ግጥም አስራ ሶስት ስንኞች ነዘሩበት። በስንኞች መካከል ክፍተት ወይም ቦግታ ሣይኖር መታፈጉ የባይተዋሩን የጭንቀት ድድርነት ይወክላል። ገፅ ላይ ተኮራምተው እንጂ ተበታትነው ስንኞቹ ለብርሃን -ለነጭ ባዶ መስመር- ስፍራ ነፍገውታል፤ የባይተዋር ገድሉ ጀመረ።
የበዕውቀቱ ስዩም ስብስብ ግጥሞች ለአማርኛ ሥነጽሑፍ ፈርጥ ናቸው። “ግድግዳው ላይ ያለች፥ የገደል ማሚቶ፥ ዝም ማለት ፈርታ/ ሳሎንህን ስትሞላው ዝምህን አባዝታ” በዓሉ ግርማ የዛሬ አርባ አመት “ከአድማስ ባሻገር” ልቦለዱን በዝምታ ነው የበረገደው። “ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል” በማለት ከዝምታ ሙዚቃ  ሲመነጭም ይሰመዋል። ደበበ ሰይፉ “ባለአደራ” በሚለው ግጥሙ በዘመን ጭራ ታስራ ስለተጐተተች የገደል ማሚቶ ተቀኝቷል። በየግጥሙ የሚያባባው ምስል ነው። “የገደል ማሚቶ ትንቃ፥ ከእንቅልፍ ትራሷ ትከንበል/ ከቦዘን ህልሟ ትፈንገል/ አንደበታችንኮ ዝጓል እማምዬ፥ አእምሯችን በክሎ/.../ የጆሮን ታሪክ በዝምታ አብጠልጥሎ” የበዕውቀቱ ገደል ማሚቶ እንደ ግዙፍ ተናዳፊ ሸረሪት ድሯን ስትተበትብ ቤቱን በዝምታ ታፍነዋለች። ይህ ተንቀሳቃሽ ዝምታ፥ የገደል ማሚቶ ምስል ብዙ ሊያወያይ ይችላል። መስተዋት ግዑዝ ሳይሆን በጥያቄ ሲያፋጥጥህ፥ የገደል ማሚቶ ግድግዳው ላይ በመንፏቀቅ ድምፅ ተነፍጋ ስታፍንህ፥ የሌሊት ወፍ ከበራፍህ ሲሞት (አስፈሪነቱ)፥ ጊዜ እንደብል እድሜን ሲያደቀው፥ እንቅልፍ ሲሸሽህ፥ በሌሎች መረሳት ሲመዘምዝህ ባይተዋር ነህ።
“መንሳፈፍ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?” መንሳፈፍ እንደ ነገሩ መኖር ከሆነና ይህ ከሰቀቀህ፥ ይህ ሥነልቦናህን ቀጥቅጦ ካንገላታህ መፍትሄው -የማያቅትህ- መስጠም ነው፤ ራስን አጥፍቶ የመገላገል ምርጫም አለ ባይ ነው። ግለሰብ እንዲህ ለማሰብ ሲነሳሳ “ያኔ ይጀምራል፥ የባይተዋር ገድልህ” ሲል ገድል ደግሞ የስቃይ ታሪክ ከሆነ የገድል መጀመር፥ የእንግልት ቅፍለት ያስደነግጣል። የዘመነኛ ንቁ ሰው እጣ ፈንታው በህይወት መፍካት ሣይሆን ለኅላዌ ጭንቀት ይገጣጠባል። በሌሎች መገለል መረሳት ነባር የቃል ግጥም ያስታውሰናል። “እህል ዱር አደረ፥ ብቻውንም ዋለ/ ጠላት እንደሌለው፥ ሰው እንዳልገደለ” ለባይተዋሩ ከእህል በበለጠ የሰው -የብጤው- ረሃብ ያንገላተዋል። በዕውቀቱ ግለሰብ ከራሱ ሲላተም ነው በበለጠ የሚያሰጋው። “መሽቷል አትበል” በተሰኘ ግጥሙ የባይተዋርን ገድል ከግለሰብ ውስጠት አፍርጦታል። “በውስጥህ ላለው ብርሃን/ ግርዶሽ የኾንህ ለ`ታ/ ያን ጊዜ ኾኗል ጽልመት/ ያን ጊዜ ኾኗል ማታ።”  ከግጥሞቹ ፈቀቅ ብለን “ከአሜን ባሻገር”ን ብናነብ በዕውቀቱ አሁንም ባለቅኔና ጥልቅ እንጂ ግልብ አይደልም።

Monday, 04 April 2016 09:00

የኪነት ጥግ

(ስለ ፒያኖ)
ለእኔ ፒያኖ እንደ ሙሉ ኦርኬስትራ ነው፡፡
ዴቭ ብሩቤክ
ምንም ነገር ባልነበረኝ ጊዜ እናቴና ፒያኖ ነበሩኝ፡፡ አይገርማችሁም? ያኔ የሚያስፈልጉኝ እነሱ ብቻ ነበሩ፡፡
አሊሺያኪስ
ህይወት እንደ ፒያኖ ነው፤ ነጫጮቹ ቁልፎች ደስታን ይወክላሉ፤ ጥቁሮቹ ደግሞ ሃዘንን፡፡ ነገር ግን አስታውስ! በህይወት ጉዞ ውስጥ ስትነጉድ ጥቁሮቹ ቁልፎችም ሙዚቃ ይፈጥራሉ፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
ስትጫወት ስለሚያደምጥህ ሰው ፈፅሞ ደንታ አይስጥህ፡፡
ሮበርት ሹማን
መንግስት ብቃት ለሌላቸው ሰዎች፣ በፒያኖ ላይ ግብር እንዲጥል እመኛለሁ፡፡
ኢዲዝ ሲትዌል
ፒያኖ ስጠኝና ሙዚቃ እሰጥሃለሁ፡፡
ዮሃን ዳፌዮ
አባቴ ግንበኛ እንዲሁም ተሰጥኦ ያለው አማተር ፒያኖ ተጫዋችና ድምፃዊ ነበር፡፡
ጆን ኢ.ዎከር
ህይወት እንደ ፒያኖ ነው፤ ከውስጡ የምታገኘው በአጨዋወትህ የሚወሰን ነው፡፡
ቶም ሎህረር
እኒህ የእኔ ጣቶች በውስጣቸው አዕምሮ አላቸው፡፡ ምን መስራት እንዳለባቸው መንገር የለባችሁም - ራሳቸው አውቀው ይሰሩታል፡፡
ጄሪ ሊ ሌዊስ
አብዛኞቹን ቀናት ጠዋት ፒያኖ እለማመዳለሁ፤ ቀሪውን ጊዜ ስዕል በመስራት አሳልፋለሁ፡፡
ቻዮ ፎኔስካ
ፒያኖን በጣቶቻችን አይደለም የምንጫወተው፤ በአዕምሮአችን እንጂ፡፡
ግሌን ጉልድ

 የጋዜጠኛና ደራሲ ተሾመ ገብረሥላሴ “ባልታሰሩ ክንፎች” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡  መጽሐፉ፤ ወጐችን ተረኮችን፣ የታሪክ ማስታወሻዎችን፣ ዝርው ግጥሞችንና አጭር ልብወለዶችን ያካተተ ሆኖ በ184 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
“ጋዜጠኝነትን ሙያዬ ብዬ የጀመርኩት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው” ያለው ተሾመ፤ ከዚያም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በሸገር ሬዲዮና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞችና አምዶችን ከአዘጋጅነት እስከ አርታኢነት እንደሰራ ይናገራል፡፡  ደራሲው “የባህር ጠብታ” የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፉን ከ10 ዓመት በፊት ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡  

   በዶ/ር መስከረም ለቺሳ የተደረሰውና ከሁለት ዓመት በፊት ለንባብ የበቃው “(ኢ) ዮቶፕያ” የተሰኘው መጽሐፍ ዛሬ ከቀኑ 10 ሰአት፣አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሔራዊ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ በባህል፣ በፍልስፍናና በሃይማኖት ዙሪያ የካበተ ልምድ ባላቸው አንጋፋ ሃያሲያን ተገምግሞም ለውይይት እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡  
መጽሃፉ፤ለእንግሊዝ መንግስታዊና ሃይማኖታዊ ተሃድሶ ምክንያት የሆነው የመካከለኛው ዘመን የኢትዮጵያ ስርአተ መንግስትንና የህዝቧን አኗኗር የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ የትርጉም ስራና የምርምር ማስታወሻዎችን ያካተተው መጽሐፉ፤በ348 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን ዋጋው 85 ብር ነው፡፡

 ደራሲ ፦ ኦስካር ዋይልድ
                ተርጓሚ ፦ አሸናፊ አሰፋ

      አንድ ምሽት ነፍሱ ‘ለቅጽበት የሚኖር ደስታ’ ሀውልት መቅረጽ ሻተች። ለዚህ ሀውልት የሚሆን ነሀስ ፍለጋ ወደ አለም ተሰማራ። ማሰብ የሚችለው በነሀስ ብቻ ነው።  መጠበብ የሚችለው በነሀስ ብቻ ነው።
በአለም ላይ ያለው ነሀስ ሁሉ ተሰውሯል። በየትኛውም ስፍራ ነሀስ ብሎ ነገር አልነበረም። የነበረው፦ ‘ለዘለአለም የሚፀና ሀዘን’ ሀውልት የተቀረፀበት ነሀስ ብቻ ነው ።
የዚህም ሀውልት ባለቤት ይኸው አርቲስት ነው። ሀውልቱን የቀረፀውም እራሱ ነበር። ይህንኑ ሀውልት በህይወት ይወደው የነበረው ብቸኛ ነገር መቃብር ላይ አኑሮታል። የሰው ልጅን የማይሞት ፍቅር ምልክት ይሆንለት ዘንድና የሰው ልጅን ለዘለአለም የሚፀና ሀዘን ይወክልለት ዘንድ፣ በራሱ እጅ የቀረፀውን ይህን ሀውልት እጅግ ይወደው የነበረው  ነገር መቃብር ላይ አኑሮታል። በአለም ላይም ይህ ሀውልት ከተሰራበት ነሀስ ሌላ ነሀስ አልነበረም።እራሱ ያበጀውን ይህን ሀውልትም ወደ ታላቅ ምድጃ ወስዶ ለእሳት ሰጠው።
‘ለዘለአለም ከሚፀናው ሀዘን’ ሀውልት ነሀስም፦ ‘ለቅጽበት የሚኖር ደስታ’ን ሀውልት ቀረፀ፡፡
 (የእንግሊዝኛው ርዕስ ፦ The Artist)

 በቶፓዚዩን ፊልም ፕሮዳክሽን ተዘጋጅቶ፣ በደራሲና ዳይሬክተር አንተነህ አስረስ የተሰራው “በዝምታ” የተሰኘው ፊልም ዛሬና ነገ አዲስ አበባ በሚገኙ በሁሉም ሲኒማ ቤቶች በ8፣ በ10 እና በ12 ሰዓት ይመረቃል፡፡ 850 ሺህ ብር እንደፈጀ የተነገረለት ፊልሙ፤የ1፡35 ርዝመት ያለው ልብ አንጠልጣይ የቤተሰብ ድራማ ነው ተብሏል፡፡
በፊልሙ ላይ እንግዳሰው ሀብቴ፣ አንተነህ አስረስ፣ ናሆም ጌታቸው፣ ፀደንያ ኤፍሬም፣ መራዊት ዮሐንስና ሌሎችም ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡

 የእውቁ ቱርካዊ ደራሲ አዚዝ ኔሲን የአጫጭር ልብ ወለዶች መድብል “ራሴን አጠፋሁ” በሚል ርዕስ በአዲስ አድማሱ አምደኛ በኤፍሬም እንዳለ ወደ አማርኛ ተመልሶ ለገበያ ቀረበ፡፡ አዚዝ ኔሲን ቱርክ ካፈራቻቸው ደራስያን ከግንባር ቀደሞቹ አንዱ ሲሆን በስራዎቹ በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን አግኝቷል፡፡ ስራዎቹም በተለያዩ ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፡፡
አዚዝ ኔሲን ልዩ ከሚያደርጉት ባህርያት ዋናው የሚያነሳቸው ማህበራዊና ፖለቲካዊ ርዕሶች ጥንካሬ ነው፡፡ “ራሴን አጠፋሁ” ውስጥ የተካተቱት አጫጭር ልብ ወለዶችም ይህንኑ ያንጸባርቃሉ፡፡ በዚህም አቋሙ ደራሲው በተደጋጋሚ ለእስርና ለእንግልት ተዳርጓል፡፡ ከረዣዥም ልብ ወለዶቹና ሌሎች የስነ ጽሁፍ ስራዎች በተጨማሪ ወደ ሁለት ሺ ገደማ አጫጭር ልብ ወለዶች እንደፃፈ ይነገርለታል፡፡
መድበሉ በ157 ገፆች 21፣ አጫጭር ልብ ወለዶችን ያካተተ ሲሆን በጃፋር መጽሐፍት መደብር አከፋፋይነት በ49 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በኮሎኔል በፈቃደ ገብረየስ የተዘጋጀው “ድርጅታዊ የጤና ምርመራ” የተሰኘው መጽሐፍ በትላንትናው እለት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ተመርቋል። ማንኛውም ድርጅት አመታዊ የጤና ምርመራ ማድረግ እንደሚገባው የሚገልፀው መጽሐፉ፤ የጤና ምርመራ ማድረግ ጠንካራ የሆነ ድርጅትን ለመፍጠር እንደሚረዳ ያስረዳል፡፡
በ153 ገፆች የተቀነበበው መፅሃፉ፤ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ባለፉት ሰላሳ አመታት በተለያዩ የውትድርና ዘርፎች ያገለገሉት ኮሎኔል ፈቃደ፤ በውትድርና ሳይንስና በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን ሁለት የማስተርስ ዲግሪ እንዳላቸው ታውቋል፡፡ ደራሲው ከሁለት ወራት በፊት “ስትራቴጂ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ ማብቃታቸው ይታወሳል፡፡

የጋዜጠኛና ደራሲ ተሾመ ገብረሥላሴ “ባልታሰሩ ክንፎች” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡
መጽሐፉ፤ ወጐችን ተረኮችን፣ የታሪክ ማስታወሻዎችን፣ ዝርው ግጥሞችንና አጭር ልብወለዶችን ያካተተ ሆኖ በ184 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ60 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
“ጋዜጠኝነትን ሙያዬ ብዬ የጀመርኩት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነው” ያለው ተሾመ፤ ከዚያም በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት፣ በሸገር ሬዲዮና በሌሎች መገናኛ ብዙሃን ፕሮግራሞችና አምዶችን ከአዘጋጅነት እስከ አርታኢነት እንደሰራ ይናገራል፡፡
ደራሲው “የባህር ጠብታ” የተሰኘውን የመጀመሪያ መጽሐፉን ከ10 ዓመት በፊት ለንባብ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡