Administrator

Administrator

Saturday, 06 February 2021 14:33

ዛጎል

ከጠንካራው ልብሷ
ከውስጥ ከመንፈሷ
ውጪ ተስፈንጥሮ ከጉንጮቿ የኖረ
ጥቁር ምልክት ከፊቷ ነበረ
ከዛጎል ልቧ ላይ
ከሴትነቷ ላይ
የማጣትን ሸማ እየፈታተለ
ወጣትነት አልፎ እርጅና አየለ
ይኸው ምልክቷ
የትላንት ጉዞዋን፣ በግልጽ የሚናገር
ያለፈውን ሁሉ፣ በመዳፍ የሚሰፍር
ከአይኖቿ በታች፣ ጥቁር ጽህፈት አለ
መለያ ምልክት፣ ይኸው እየመሰለ
ማድያት አኑሮ፣ ውበቷን ሰውሮ
ከማጣት ሀሳቧ፣ ዛጎል ልቧን ትቶ
ካዘነው ልቧ ጋር፣ ፊቷ ላይ አምታቶ
ማዲያት አኖረ
ውበቷን ሰወረ
ማጣቷን ዘከረ።
(“የሱናማዊቷ ቃል” ከተሰኘው የገጣሚ ዋዜማ ኤልያስ የግጥም መድብል የተወሰደ)Saturday, 06 February 2021 14:32

የግጥም ጥግ

   ናፍቆት

ሰማዩ ቀልጦብርሀን አፍሮ ይሽኮረመማል፣
ጨለማ ሆኗል፤
ውኃ ተገርፎ እሳት ያነባል፣
የምድር ገላ ይገሸለጣል፤
ጽልመት ጎምርቶ፣
ፍሬ ያፈራል የመርገምት እጽ ያጎነቁላል፤
አንቺ ሳትኖሪ፣
ይህን ይመስላል፡፡
(ሳሙኤል በለጠ-ባማ)

 (የዩኒቨርሲቲ ትውስታ)

             ቴአትር ስንማር ነው፤ የኢትዮጵያ የቴአትር ታሪክ የሚባል ኮርስ ስንወስድ፤ በምን ምክንያት እንደሆነ እስካሁን በማይገባኝ ሁኔታ ሌሎች የትምህርት አይነቶች ላይ ባልተለመደ መልኩ የቃል ፈተና ወስደን ነበር። መምህራችን በቢሯቸው ተቀምጠው በየተራ እየገባን፣ የባለጉዳይ ወንበር ላይ ተቀምጠን፣ ለሚቀርብልን የቃል ጥያቄ የቃል መልስ መስጠት። የትምህርት ክፍሉን ስንቀላቀል ቁጥራችን በርከት ያለ ቢሆንም፣ ቀስ ቀስ በተለያዩ ምክንያቶች ያቋረጡ ተማሪዎች ስለነበሩ፣ ይህንን ኮርስ ስንወስድ ምን ያህል ተማሪዎች በክፍል ውስጥ እንደቀረን የማስታውሰው፣ በዚያን እለት ለፈተና የተዘጋጁት ጥያቄዎች 22 እንደነበሩ ትዝ ሲለኝ ነው።
እናም ተራዬ ደርሶ ገባሁ፣ ገና ወንበሩ ላይ ተደላድዬ ሳልቀመጥ፣ ከጊዜ ጋር ቀጠሮ ያላቸው የሚመስሉት መምህራችን፣ ስለ ፈተናው አሰጣጥ፣ ዘለግ ባለ ድምፃቸው መመሪያ ቢጤ መስጠት ጀመሩ፡-
 “ሃያ ሁለት ጥያቄዎች አሉ፤ ከነዚህ መካከል አንድ ቁጥር ትጠሪያለሽ። የሚደርስሽ ጥያቄ ዘለግ ያለ መልስ የሚያስፈልገው ከሆነ አብራርተሽ ትመልሺያለሽ፤ 7 ደቂቃ ይሰጥሻል። መልሱ አጭር ከሆነ ደግሞ ተጨማሪ ጥያቄ ትጠየቂያለሽ”
“እሺ” አልኩ።
የትኛው እንደሚሻለኝ እርግጠኛ ባልሆንም፣ ገና “ፈተና” ሲባል በደቂቃ 140 ጊዜ የሚመታውን ልቤን አደብ ለማስያዝ እየሞከርኩ። ቀላሉ እንዲገጥመኝ ለራሴ ተመኝቼ ሳልጨርስ፤
“የጥያቄ ቁጥር ምረጪ!” አሉ መምህሬ
“እእእእእ... ጥያቄ ቁጥር...” ብዬ ሳሰላስል፣ ለጥያቄው መልስ ከምሰጥበት ጊዜ የበለጠ ቁጥር ለመምረጥ የማጠፋው ጊዜ የቆጫቸው ይመስል፣ “ከአንድ እስከ ሃያ ሁለት ካሉት ቁጥሮች ውስጥ አንዱን ምረጪ” ብለው አጣደፉኝ። በድንጋጤ፤ “ማርያም አውጪኝ” ብዬ አፌ ላይ እንደመጣልኝ “21” አልኩኝ።
“21... 21....” አሉና ጥያቄ የፃፉበትን ወረቀት በእስክሪብቶአቸው ጫፍ እየጠነቆሉ፣ከአንድ ጀምረው ቁልቁል ወደ ጠራሁት ጥያቄ በአይናቸው ተንደረደሩና፤
“21!... ተይዟል” ብለው ቀና አሉ። ቀደም ሲል በመመሪያቸው ላይ እንዲህ ያለ ነገር ስላልገለፁልኝ ግር እየተሰኘሁ ሌላ ቁጥር በማሰብ ላይ ሳለሁ “ተይዟል፤ ብርቱካን ተጠይቃ መልሳዋለች፤ ሌላ ምረጪ” ብለው አከሉበት። ቀጥሎ የጠራሁትን ቁጥር አላስታውሰውም፤ ብቻ አንዱን ጠራሁ። መምህሬ ፈገግ ብለው፤ “ዘርዘር ያለ መልስ የሚያስፈልገው ጥያቄ ነው የመረጥሽው” አሉ። ፈገግ አባባላቸው “የታ’ባሽ፣ አገኘሁሽ” የሚል ይመስል ነበር። (አብዛኛው የሃገራችን መምህር ለተማሪ ፈተና በማክበድ የሚዝናና ይመስለኛል)
“ወይ ጉዴ አለቀልኝ; አልኩ
“ሰባት ደቂቃ ነው ያለሽ” ጊዜ ለመቆጠብ እኔን ሲያጣድፉ እሳቸው አንዱን መመሪያ እየደጋገሙ የሚያጠፉት ሰአት አይታወቃቸውም፤ ወይም ነገር በመደጋገም የፈተናውን ድባብ አስጨናቂ ሊያደርጉት ይሞክራሉ፤ ያም ተጨማሪ ደስታ ሳይሰጣቸው አይቀርም።
“ልብ ብለሽ አዳምጪ...ጥያቄ ቁጥር...” ይሉና ፋታ ይወስዳሉ። የኔ ልብ ምቷ ይጨምራል። የቴአትር አፃፃፍ መምህሬ ቢሆኑ ኖሮ፣ አንድ ተውኔት እንዴት ልብ አንጠልጣይ መሆን እንደሚገባው፣ በተግባር ሊያስተምሩኝ ይመስለኝ ነበር። ለነገሩ ተመርቄ ከወጣሁ ከጥቂት ጊዜአት በኋላ የኢቲቪ ጥያቄና መልስ አቅራቢ ሆኜ ስሰራ ይቺን “ጥያቄ ቁጥር...” እያሉ ተወዳዳሪዎች ላይ ጭንቀት መፍጠርን ሳልጠቀምባት አልቀረሁም። (እንዲህ ነው የተማሩትን በተግባር ላይ ማዋል)
“ቴአትር በዘመነ ኢህአዴግ ያሳየው እመርታ?” ጥያቄውን ዱብ አደረጉት። (አልጨመርኩም አልቀነስኩም፤ ጥያቄው ቃል በቃል ነው)።
“እደግመዋለሁ... ቴአትር...” ሊቀጥሉ ሲሉ “እመርታ ምንድነው?” አልኩኝ ጣልቃ ገብቼ። የእመርታ ትርጉሙ ጠፍቶኝ አልነበረም፤ ይልቁንም ለጥያቄው ማብራሪያ እስከሚሰጡኝ የማሰቢያ ጊዜ ለመግዛት ነበር።
መምህሬ ሃሳቤ ገብቷቸው ይሁን የእመርታን ትርጉም አለማወቄ አበሳጭቷቸው፤ “ይሄ እኮ ፈተና ነው ፤መልሰሽ እኔን ተጠይቂኛለሽ?” ብለው ተቆጡ። ሰአታቸውን እየተመለከቱ፣ የተሰጠኝ ደቂቃ መቁጠር መጀመሩን አክለው ነገሩኝ።
በታሪክ ትምህርታችን፣ ቴአትር በኢትዮጵያ የዘመናዊ ትምህርት መስፋፋትን ተከትሎ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ በበጅሮንድ ተ/ሐዋርያት ተ/ማርያም ፋቡላ/የአውሬዎች መሳለቂያ መጀመሩን ይነግረናል። ይህንንም ማወቅ መሰረታዊ በመሆኑ በጥያቄ መልክ አለመቅረቡ የሚጠበቅ ነው። የትምህርቱ የመጨረሻ ምዕራፍ ግን ምን ነበር? ጠፋብኝ፣ በእርግጠኛነት ግን ዘመነ ኢህአዴግ ላይ አላደረሰንም። የማንም ድክመት ይሁን በምንም ምክንያት ግን በትምህርታችን ውስጥ የሚጠቀሱ የቴአትር ስራዎች ብዙዎቹ ቀደምት ናቸው (ከ"ውበትን ፍለጋ" እና ከ"ፍቅር የተራበ" ውጪ ለምሳሌነት የሚነሳ ከነበረ፣ አብራችሁኝ የተማራችሁ አስታውሳችሁ አርሙኝ)፡፡
እናም መምህራችን ሲያስተምሩን ምናልባትም ዘመኑን እየኖርንበት ስለነበረ ገና በታሪክነት አልደመሩት ይሆናል። ግን ለፈተና ሲሆን “ዘመነ ኢህአዴግን ያውም እመርታዋን ምን ሲሉ አሰቧት?” እያልኩ ሳሰላስል፤
“የመጀመሪያው ደቂቃ አልቋል” አሉኝ፤ በስል ድምፃቸው።
ዞሮ ዞሮ ያጠናሁትን ሳይሆን ያየሁትንና እየኖርኩ ያለሁትን እንድገልፅ ስለተጠይቅኩ በአንድ በኩል ዘና አልኩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ (በወቅቱ ቴአትር እሰራ ስለነበር) በቴአትር ቤቶች አካባቢ የሚነሱ ችግሮችን እንጂ እመርታ ለማየት እድል አልነበረኝምና፣ ምን እንደምመልስ ግራ እንደገባኝ ትንፋሼን ሳብ አድርጌ ፈተናው በቀጥታ የሚገናኘው ከውጤቴ ጋር በመሆኑም ስጋቴ የወለደልኝን ማብራራት ጀመርኩ።
“አንደኛ የቴአትርና የቴአትር ቤቶች መስፋፋት” አልኩ።
“ማለትም ተጨማሪ ቴአትር ቤቶች መከፈታቸው፤ እነዚህም የህፃናትና ወጣቶች ቴአትር፣ ሜጋ አምፊ ቴአትር፣ የፑሽኪን የባህልና ቴአትር አዳራሽ እና ባህርዳር ሙሉዓለም የቴአትር አዳራሽ። ሁለተኛ በርካታ የቴአትር ክበባት ተመስርተዋል፤ በተጨማሪም በሆቴል አዳራሾችና በግል ሲኒማ ቤቶች ቴአትሮች መታየት ጀምረዋል።” አልኩኝ፤ የተብራራ እንዲመስል ረጋ ብዬ ቃላቶቼን ለጠጥ እያደረግኩ።
“የት ሲኒማ ቤት እና ሆቴል ነው ቴአትር የሚታየው? ምን የሚባል ቴአትር?” መምህሬ ስለጠቀስኳቸው እንቅስቃሴዎች መረጃ ያላቸው አይመስሉም። አጠያየቃቸውም የማፋጠጥ ሳይሆን “እንዲህም ተጀምሯል?” የሚል አይነት ነበር። እኔም ያልጠበቁት አዲስ መረጃ መስጠቴ እንደ ተጨማሪ ነጥብ ተቆጥሮ ማርክ ያስጨምርልኝ ይሆን? ብዬ እያሰብኩ፣ አብራርቼ መለስኩ። "ለእረፍት የመጣ ፍቅር" በኢምፔሪያል ሆቴል፣ "የአዛውንቶች ክበብ" ዋቢ ሸበሌ ሆቴል፣ "የዳዊት እንዚራ" (መሰለኝ አሁን ተዘንግቶኛል) ለመጀመሪያ ጊዜ በአለም ሲኒማ ይታዩ ነበር።
“ሌላ...." ብዬ አንድ ሙሉ ደቂቃ በዝምታ ካጠፋሁ በኋላ፣ የፊልም መበራከትና የሲኒማ ቤቶች መስፋፋትም ተመልካቹ ኪነጥበብን ለመዝናኛነት እንዲመርጥ ስለሚያደርግ፣ በተዘዋዋሪ ወደ ቴአትር ቤቶች እንዲመጣ ያደርገዋል። ለባለሙያዎችም ተጨማሪ የስራ ዕድል ስለሚፈጥር..." ብዬ አበቃሁ።
በጠቅላላው አምስት ደቂቃዎችን ተጠቅሜአለሁ። የቀሩኝን ሁለት ደቂቃዎች ደግሞ ደጋግሜ እንዳስብና እንድጠቀምባቸው በመወትወት ራሳቸው መምህሬ ጨረሷት። ሌላ መልስ አልነበረኝም።
“መልካም! ፈተናው አልቋል። ትክክለኛ መልሶቹን እንመለከትና ከሰጠሽው መልስ በመነሳት ውጤትሽን እነግርሻለሁ” አሉኝ፤ እንደ አዲስ ተናጋሪ ድምፃቸውን እየሞረዱ፤ “አንደኛ ምላሽሽ መጀመር የነበረበት ለዘመነ ኢህአዴግ ትርጉም (definition) በመስጠት ነበር። ማለትም ‘ዘመነ ኢህአዴግ ማለት ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ማለት ነው’ ካልሽ በኋላ እመርታዎቹን ትቀጥያለሽ። በዚህም አንዱንና ዋነኛውን በትክክል አብራርተሻል፤ በጣም ጥሩ ነው!” እያሉ በመልስኩበት ወቅት ሲፅፏቸው የነበሩ ነጥቦችን ከማስታወሻ ደብተራቸው ላይ እየተመለከቱና በሚያጉተመትም ድምፅ እያነበቡ፤ “ትክክል፣ ራይት፤ ትክክል፣ እእእ ህፃናትና ወጣቶች ብለሻል ራይት፣ ትክክል..” እያሉ ማረማቸውን ሲቀጥሉ፣ የኔም ልብ ሞቅ ማለት ጀምራ ነበር “ኤክስ” አሉ በመሃል ጮክ ብለው፤ “‘ፑሽኪን አዳራሽ’ ነው ያልሽው፣ ሩሲያ የሳይንስና የባህል ማዕከል ነው የሚባለው፣ ይሄ ፈተና ነው! ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የቴአትር ቤቶቹም የተመሰረቱበትን ጊዜ አልጠቀስሽም።” ቀና ብለው ሲመለከቱኝ አሳዘንኳቸው መሰለኝ፣ መለስ ብለው “ይሁን ብቻ ግማሽ እሰጥሻለሁ። ሌላው ግን አልተመለሰም”።
ሌላው ምንድነው? አልኳቸው በጉጉት
"ሌላውና ሁለተኛው ‘ሴቶችን ወደ ስልጣን ማምጣት ነው’" አሉኝ ።
ሴቶችን ወደ ስልጣን ማምጣት ከቴአትር ጋር ያለው ግንኙነት አልተከሰተልኝም። ግራ መጋባቴን አይተው ቀጠሉ፤ "ሴቶችን በቴአትር ቤቶች አስተዳዳሪነት መሾም! ጀማነሽ ሰለሞን የአ.አ ቴአትርና ባህል አዳራሽን፤ መንበረ ታደሰ እንዲሁም ማርታ ስለሺ የሀገር ፍቅር ቴአትር ቤትን እንዲመሩ መደረጉ ነው።
"ሶስተኛው እመርታ ደግሞ ቴአትሮች በብሄር ብሄረሰቦች ቋንቋ መሰራት መጀመራቸው ነው፤ ለዚህም ቅድም የጠቀስሽው የሜጋ አምፊ ቴአትር የኦሮምኛ ቴአትር ማሳየቱን ለምሳሌነት ማንሳት ይቻላል። እናም የዛሬው ፈተና ይህንን ይመስላል” ብለው ወደ ማስታወሻ ደብተራቸው ተመልሰው ያገኘኋቸውን “ኤክስ” እና “ራይት” እየቆጠሩ ሲያሰሉ ከቆዩ በኋላ “እንግዲህ የዛሬው ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩት የፅሁፍ ፈተናዎችና የክፍል ውስጥ ተሳትፎ ጋር ተደማምሮ (የአ.አ.ዩ የቴአትር ትምህርት ክፍል ከተጀመረ ጀምሮ "ለ30 አመታት በተማሪዎች የተሰሩ የመመረቂያ ፅሁፎች ዳሰሳ" በሚል ርዕስ የኮርስ ማሟያ ፅሁፍ ታዝዤ ማቅረቤን ልብ ይሏል)
በጠቅላላው ያመጣሽው ውጤት ሲ (C) ነው! በይ አሁን ፈጠን ብለሽ ቀጣዩን ተፈታኝ ጥሪልኝ” ብለው ወረቀቶች ማገላበጣቸውን ቀጠሉ። በሩን ከኋላዬ እየዘጋሁ “ተረኛ!” አልኩ።
እናም ዛሬ ከ10 አመታት በኋላ ቴአትር በዘመነ “ለውጥ” ላይ ሆና መቶ አመቷ ሲዘከር፣ ተረኛ ተፈታኞች ምን እየመለሱ ይሆን? እላለሁ። ቴአትርስ መቶ አመት ተጉዛ ያሳየችው እመርታ ምንድነው? እያልኩ የመምህሬን ጥያቄ እጠይቃለሁ። መልስ ያላችሁ ...
(ሜሮን ጌትነት፤ ከፌስቡክ ገጽ)

Saturday, 06 February 2021 14:13

...I put a spell on you...

  ...’cause you’re mine... “ ትላለች Nina Simone...
እኔ አይኔን ጨፍኜ በሷ ድምፅ እሰማዋለው ዘፈኑን...
የኔ ቆንጆ ፍፁም ነች!
Nina በድምፅ እንኳን አጠገቧ አትደርስም... በኔ perfect አለም “I put a spell on you... ‘cause you’re mine...” የምትለኝ እሷ ነች...ጆሮዬ ስር...
አንገቴን የሶፋዬ መደገፊያ ጠርዝ ላይ እየወጠርኩ ተንጠራርቼ ሰፊውን የሳሎኔን ጣሪያ እቃኛለው... ሙሉ ቤቴን እሷው ነች... ፈገግ ስትል እንደ ጂኒ ከጥርሷ ተፈልቅቆ የሚወጣ ግዙፍ ውበት አላት... ቤት... ሰፈር... ሀገር የሚያክል...
ብትኖር... አቅፌያት ቢሆን ኖሮ ምን አባቴ ይውጠኝ ነበር? አንድዬ ሲያስብልኝ የሌላ ናት!
እኔ አስቃታለው... ትን እስኪላት ሆዷን በእጆቿ ደግፋ ፍርፍር እስክትል አስቃታለው... እኔ ስቀልጥ... እሷ ሲደክማት “ፍቅር ደወለ...” ብላ እብስ ትላለች...
እሱን ብሎ ፍቅር...
እኔ እኩያዋ፣ አጫዋቿ፣ ጓደኛዋ ነኝ...
እሱ አስተዋይዋ፣ አፍቃሪዋ፣ ፍቅረኛዋ ነው...
እንደሷ አይነት መልዓክ ከእንደሱ አይነት ጭራቅ እንዴት እንደሚገጥም አይገባኝም። ቁጣውን ስትታገስ ቱግ እል፣ እቆጣና ደግሞ ተናግሬ እንዳላጣት ንዴቴን ዋጥ አድርጌ እፈግጋለው።
ጭንቅላቴ ውስጥ ስንት ጠርሙስ አናቱ ላይ እንዳፈረስኩ መድሐኒዓለም ነው የሚያውቅ...
ትወደዋለች...
ብዙ ትወደዋለች...
ሱቋን 10:30 ዘግታ 11:00 እስኪል ስልኳ ላይ አፍጣ ነው ምትጠብቀው... ተንደርድራ ልትለጠፍበት...
እቤቱ ይዟት እንዲሄድ ስትለማመጥ ሳይ ጥውልውል ያደርገኛል...
አንድ ጊዜ ጨብ ብላ አንሶላው ላይ የሌላ ሴት ጠረን እንዳለ አጫውታኛለች... ጓደኛዋ ነኛ...
እሷ ግዷ አይደለም... ዋናዋ የሱ ጠረን ነው... የሆነ Intimately Beckham የሚባል ሲጃራ ሲጃራ የሚል ሽቶ ይቀባል... ስለምናባቱ ጠረን እንደምታወራ አይገባኝም... ባይገባኝም አያገባኝም... እወዳታለው!
አንድ የከፋት ቆንጆ ቀን አንገቴ ስር ተወትፋ ቀና ብላ እያየችኝ ትንፋሿ ቅርብ ብሎ ሲያጓጓኝ ድክም ብዬ አፍንጫዋን በአፍንጫዬ ነካሁት... ዐይኗን ጭፍፍን አድርጋ መሀል ከንፈሬ ላይ ሳም አደረገችኝ... እኔ ከከፍታዬ ወርጄ ለመንቃት ስታገል እሷ ቀና ብላ ምንም እንዳልተፈጠረ እሮሮዋን ቀጠለች...
ብዙ ቀን “ይኼ ነገር ሆኗል ወይስ ጭንቅላቴ ውስጥ ነው?” እያልኩ ተወዛግቤያለው...
እሷ እቴ...
ምን አለባት...
“የባለፈዋን ቸከስ ምን አረካት?” ትለኛለች ፈገግ ብላ...
ምን አደርጋታለው ሌላ?
ስለ ሌላ ሴት ስታወራ እናደዳለው...
ምን ይሉት ጥያቄ ነው? ምን አዲስ ነገር አደርጋለው...?
“የታባቷ... ክብር ካልወደደላት” እልና አኮርፋታለው... ልቤ “when hell freezes over...” ምናምን እያለ ይደክምብኛል...
“የምታፈቅራት ታፍቅርክ!” ይሉት ምርቃት የሞኝ ፀሎት እየመሰለ ያስቀኝ ነበር... ምርቃቱን እጁ ላይ ያቀለልኩበት መድሐኒዓለም ቁልቁል እያየ እምባው ጠብ እስኪል ይስቅብኛል...
አምርሬ እንዳልጠላው በዛች የአንገቴ ስር ተዓምር አጉል ጫፍ አስይዞኛል...
አይኔን ጨፍኜ ብቻዬን እሰማታለው...
“ ...I put a spell on you...
...’cause you’re mine... “
ትለኛለች ጆሮዬ ስር...
የአንገቴን ስር ቅፅበት እያሱን በሚያስንቅ እምነት በየቀኑ እለጥጣታለው... እኖራታለው... እወዳታለው...  በጉዞ ሚዲያና ማስታወቂያ የሚዘጋጀው “ብራና” የኪነ ጥበብ ምሽት፣ ከነገ በስቲያ  ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ጀምሮ “እስከ መቼ” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ሆቴል ይካሄዳል፡፡ በዕለቱ ዲስኩር፣ ወግ፣ ግጥምና ሙዚቃ  የሚቀርብ ሲሆን ፕ/ር ብርሀኑ ነጋ፣ አቶ ኦባንግ፣ አርቲስት አስቴር በዳኔ፣ አርቲስት ደሳለኝ ሀይሉ ዲስኩር፣ ገጣሚያኑ ኤፍሬም ስዩምና አንዷለም አባተ (የአፀደ ልጅ) ግጥም፣ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም ወግ እንደሚያቀርቡና ድምጻዊ ካሳሁን እሸቱ ከሻሎም አቢሲኒያ የባህል ቡድን ጋር እንደሚያቀነቅን  ተጠቁሟል፡፡ መድረኩ በጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ የሚመራ ሲሆን የመግቢያ ዋጋ 100 ብር ነው ተብሏል፡፡ ትኬቶቹ በጃፋር፣አይናለምና ዮናስ መጽሀፍት መደብሮችና በኢትዮጵያ ሆቴል እንደሚገኙም ታውቋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና፤ በሰምና ወርቅ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት በየወሩ የሚዘጋጀው ጥበባዊ ምሽት የፊታችን ሰኞ ከ11፡00 ጀምሮ “ከአገሬ ሰማይ ስር” በሚል ርዕስ በብሔራዊ ቴአትር ይካሄዳል። በዕለቱም ዲስኩር፣ ወግና ሙዚቃ የሚቀርቡ ሲሆን ወዳጄነህ ማህረነ (ዶ/ር)፣ ሲሳይ መንግስቴ (ዶ/ር)፣ ደራሲ ሕይወት እምሻው፣ ሮዳስ ታደሰ (ዶ/ር)፣ ጋዜጠኛ ጌጡ ሰምሀር ተክኢ (ዶ/ር)፣ ገጣሚ ሰይፉ ወርቁ፣ ባንቻየሁ አሰፋና መአዛ ፋንታዬ የጥበብ ስራዎቻቸውን ያቀርባሉ ተብሏል። አድዋ ሙሉ ባንድ የኪነጥበብ ምሽቱን  በሙዚቃ ያደምቀዋል ተብሏል፡፡ የመግቢያ ዋጋው 100 ብር ሲሆን ትኬቶቹ በጃዕፋር፣ በዮናስ፣ በዘውዱ እና በዕውቀት በር መፃሕፍት መደብሮች እንደሚገኙም ታውቋል፡፡

  አሜሪካ 33.7 ሚሊዮን ክትባቶችን ስትሰጥ፤ አልጀሪያ 30 ክትባቶችን ብቻ ሰጥታለች

          በአለም ዙሪያ በሚገኙ 66 አገራት እስካለፈው ረቡዕ ድረስ በድምሩ ከ104 ሚሊዮን በላይ የኮሮና ክትባቶች ለዜጎች መሰጠታቸውንና ብዛት ያላቸው ክትባቶችን በመስጠት አሜሪካ፣ ከህዝብ ብዛት አንጻር ከፍ ያለ የክትባት ሽፋን በማስመዝገብ ደግሞ እስራኤል ከአለማችን አገራት ቀዳሚዎቹ መሆናቸውን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በአሜሪካ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ 33.7 ሚሊዮን ያህል የኮሮና ክትባቶች መሰጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በቻይና 24 ሚሊዮን፣ በእንግሊዝ 10 ሚሊዮን፣ በእስራኤል 5.9 ሚሊዮን፣ በህንድ ደግሞ 4.14 ሚሊዮን ያህል ክትባቶች መሰጠታቸውንም ገልጧል፡፡
ከ100 ሰዎች 58 ያህሉ የኮሮና ክትባት ያገኙባት እስራኤል ከህዝብ ብዛት አንጻር ከፍተኛ መጠን ያለው ክትባት በመስጠት ከአለማችን አገራት በአንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ 35፣ እንግሊዝ 15፣ ባህሬን 10 እንዲሁም አሜሪካ 9.8 በመቶ የሚሆነውን ነዋሪ ህዝብ በመከተብ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም የብሉምበርግ ዘገባ ያሳያል፡፡  
ባሳለፍነው ሳምንት በአለም ዙሪያ በየዕለቱ በአማካይ 4.25 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አይነት ውጤታማነታቸው የተረጋገጠ የኮሮና ክትባቶች ለተጠቃሚዎች መሰጠታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ክትባት መስጠት ከጀመሩት 66 የአለማችን አገራት መካከል አልጀሪያ 30 ክትባቶችን ብቻ በመስጠት በመጨረሻ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አመልክቷል፡፡
ያደጉ አገራት የኮሮና ክትባት ሽሚያቸውን አጠናክረው እንደገፉበት የጠቆመው ዘገባው፣ እስካለፈው ወር አጋማሽ ድረስ ከክትባት አምራቾች ጋር ግዢ ከፈጸሙት የአለማችን አገራት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ያደጉ አገራት መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
በሌላ የኮሮና ክትባት መረጃ ደግሞ የአለም ባንክ ለአፍሪካ አገራት የኮሮና ክትባት መግዣ የሚውል የ12 ቢሊዮን ዶላር በብድርና በድጋፍ መልክ ለመስጠት መወሰኑን የዘገበው አሶሼትድ ፕሬስ፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራትም ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መነገሩን አመልክቷል፡፡
የታንዛኒያ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን አስገብቶ ለዜጎቹ የማዳረስ እቅድ እንደሌለው ማስታወቁን የዘገበው ቢቢሲ በበኩሉ፤ የአገሪቱ መሪም፣ ነጮች የሚያመርቱት የኮሮና ክትባት እጅግ አደገኛና ጎጂ በመሆኑ ክትባት እንዳትወስዱ ሲሉ ከሰሞኑ ማስጠንቀቃቸውን አስታውሷል፡፡


  ባለፈው ሰኞ ማለዳ በተደረገ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው ወርደው ለእስር የተዳረጉት የኖቤል የሠላም ተሸላሚዋ የማይንማር ብሔራዊ መሪ አን ሳን ሱ ኪ፤  የአገሪቱን የገቢ ንግድ ህግ በመጣስ ከውጭ አገር ያስገቡትን “ህገወጥ የሬዲዮ መገናኛ” ያለፈቃድ ይጠቀሙ ነበር ተብለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ተነግሯል፡፡
ለዲሞክራሲ መስፈን ባደረገት ትግል ምክንያት 15 አመታትን በቁም እስር ያሳለፉትና በአገሬው ዘንድ “የዲሞክራሲ እናት” እየተባሉ ሲንቆለጳጰሱ የኖሩት አን ሳን ሱ ኪ፤ ከወራት በፊት በምርጫ አሸንፈው ከያዙት ስልጣን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት መውረዳቸውን ተከትሎ ለእስር መዳረጋቸውን ያስታወሰው አሶሼትድ ፕሬስ፣ ባለፈው ረቡዕ ደግሞ በመኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ በህገወጥ መንገድ ከውጭ አገር ያስገቡትና ያለፈቃድ የሚጠቀሙበት የሬዲዮ መገናኛ ተገኝቶባቸዋል በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው አመልክቷል፡፡
ፖሊስ በ ሱ ኪ ላይ የጀመረውን ምርመራ እስኪያጠናቀቅ ድረስ ግለሰቧ ለ15 ቀናት ያህል በእስር ላይ ይቆያሉ መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ ሁለት አመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ እንደሚችሉም አክሎ ገልጧል፡፡
በወታደሮች በቁጥጥር ስር ከዋሉበት ጊዜ አንስቶ ደብዛቸው የጠፋው አን ሳን ሱ ኪ  በአሁኑ ወቅት ታስረው ያሉበት ቦታም በግልጽ እንደማይታወቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ፖሊስ ከእሳቸው በበተጨማሪ በወታደራዊ ሃይሉ ተይዘው ለእስር በተዳረጉት የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ዊን ማይንት ላይ የተለያዩ የወንጀል ክሶችን መመስረቱንም ገልጧል፡፡
በማይንማር የሮሂንጋ ሙስሊሞች ላይ ከተፈጸመው አስከፊ ግፍና ስደት ጋር በተያያዘ በብዙዎቸ የሚተቹት የ75 አመቷ አን ሳን ሱ ኪ፣  ባለፈው ህዳር በተደረገ አገራዊ ምርጫ ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ የተባለውን ፓርቲያቸውን ወክለው በማሸነፍ ወደ ስልጣን ቢመጡም፣ የአገሪቱ የጦር ሃይል ግን ከተቃዋሚዎች ጋር በመወገን ምርጫው ተጭበርብሯል ሲል ቆይቶ በስተመጨረሻ፣ ባለፈው ሰኞ በጦር አዛዡ ሚን ኡንግ ሃይንግ መሪነት በተቀነባበረ መፈንቅለ መንግስት ከስልጣናቸው አውርዶ መንበሩን በመረከብ የአንድ አመት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አጽንቷል፤ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎች የቀድሞ ባለስልጣናትንም አስሯል፡፡
ፓርቲያቸው ናሽናል ሊግ ፎር ዲሞክራሲ አን ሳን ሱ ኪ በአስቸኳይ እንዲፈቱ መጠየቁንና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ የሴትዮዋ ደጋፊዎችም በማህበራዊ ድረገጾች እና በአደባባይ የተቃውሞ ሰልፍ በጀመሩት ዘመቻ ህዝቡ ለወታደራዊው ሃይል እንዳይገዛና በእንቢተኝነት ታጥቆ እንዲወጣ ጥሪ በማቅረብ ላይ እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፣ የወታደሩ ደጋፊ የሆኑ አንዳንድ ታዋቂ የአገሪቱ አክቲቪስቶች በአንጻሩ ህዝቡ እንዲረጋጋ ጥሪ ማስተላለፋቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
አሜሪካና ሌሎች ምዕራባውያን አገራት መፈንቅለ መንግስቱን እንዳወገዙት የዘገበው ሮይተርስ በበኩሉ፣ የቡድን ሰባት አገራትም የማይንማር ጉዳይ በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ በመፈንቅለ መንግስት ስልጣን የያዘው ወታደራዊ ሃይል በአፋጣኝ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲሽር፤ ስልጣኑን በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለተመረጠው መንግስት እንዲያስረክብ፣ ያላግባብ ያሰራቸውን ባለስልጣናት እንዲፈታና የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብር ጥሪ ማቅረባቸውን  ዘግቧል፡፡

      - ቶዮታ ባለፈው አመት 9.53 ሚሊዮን መኪኖችን ሽጧል
        - አፕል የአመቱ የአለማችን እጅግ ስመጥር ኩባንያ ሆኗል

          የጃፓኑ ቶዮታ መኪና አምራች ኩባንያ በ2020 የፈረንጆች አመት ብዛት ያላቸው መኪኖችን በመሸጥ በአለማችን ቀዳሚው ኩባንያ መሆኑን የዘገበው ብሉምበርግ፣ ኩባንያው በአመቱ 9.53 ሚሊዮን የተለያዩ ምርቶቹን ለመሸጥ መቻሉን አመልክቷል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ አለማቀፉ የአመቱ የመኪኖች ሽያጭ በ2019 ከነበረው በ14 በመቶ ያህል ቅናሽ ማሳየቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የቶዮታ ሽያጭም በ11 በመቶ ቢቀንስም በሽያጭ ቀዳሚውን ደረጃ ከመያዝ የሚያግደው ኩባንያ አለመገኘቱን ገልጧል፡፡
ላለፉት አምስት አመታት በሽያጭ ሲመራ የነበረው የጀርመኑ የመኪና አምራች ኩባንያ ቮልስዋገን በአመቱ 9.31 ሚሊዮን መኪኖችን ብቻ በመሸጡ ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ሊል መገደዱንም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የቢዝነስ ዘገባ ደግሞ፣ በአለም ዙሪያ የሚገኙ ታላላቅ ኩባንያዎችን የእውቅናና የተደናቂነት ደረጃ እየገመገመ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርቹን መጽሔት ከሰሞኑም የ2020 የፈረንጆች አመት ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን፣ ላለፉት 13 ተከታታይ አመታት በ1ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ የዘለቀው የአሜሪካው የቴክኖሎጂ ኩባንያ አፕል ዘንድሮም የአለማችን እጅግ ስመጥር ኩባንያ ሆኗል፡፡
ፎርቹን የሃብት መጠን፣ የስራ አመራር ብቃት፣ ማህበራዊ ሃላፊነትን የመወጣት አቅምና ዝና ጨምሮ 9 መስፈርቶችን ተጠቅሞ የኩባንያዎችን ሁኔታ በመገምገም ባወጣው አመታዊ ሪፖርቱ፤ ሌላኛው የአሜሪካ ኩባንያ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ማይክሮሶፍት በበኩሉ የአመቱ ሶስተኛው ስመጥር ኩባንያ ለመሆን መብቃቱን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡
ዋልት ዲዝኒ፣ ስታርባክስ፣ ቤክሻየር ሃታዌ፣ አልፋቤት፣ ጂፒሞርጋን ቼዝ፣ ኔትፍሊክስ እና ኮስቶኮ ሆልሴል እንደቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአለማችን ኩባንያዎች መሆናቸውም ተነግሯል፡፡
ፎርቹን መጽሔት በአመቱ ሪፖርቱ ውስጥ ያካተታቸው ኩባንያዎች ገቢያቸው ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሆኑትን እንደሆነ የጠቆመ ሲሆን፣ ኩባንያዎቹ ቴክኖሎጂን ጨምሮ በ52 የተለያዩ የንግድ መስኮች የተሰማሩ እንደሆኑም አመልክቷል፡፡


      የአለማችን ቱሪዝም ዘርፍ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 በታሪክ የከፋውን ቀውስ ማስተናገዱንና የአለማቀፍ ቱሪስቶች ቁጥር አምና ከነበረበት ከ74 በመቶ ወይም በአንድ ቢሊዮን መቀነሱን የአለም የቱሪዝም ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች ከተጣሉ በርካታ የጉዞ እና የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲሁም ከቱሪዝም ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ጋር በተያያዘ የቱሪዝም መስኩ ያጣው ገቢ 1.3 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚደርስም ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
ከአለማች በአመቱ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የቱሪስቶች ቁጥር ክፉኛ የቀነሰባቸው የእስያና ፓሲፊክ አገራት መሆናቸውን የሚያሳየው የድርጅቱ ሪፖርት፣ በአገራቱ የቱሪስቶች ቁጥር ከአምናው በ84 በመቶ ወይም በ300 ሚሊዮን መቀነሱን እንዲሁም በመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ አገራት በ75 በመቶ መቀነሱንም ያብራራል፡፡
በቱሪዝሙ መስክ የተፈጠረው ቀውስ እስከ 120 ሚሊዮን የሚደርሱ በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎችን የስራ ዕድል አደጋ ውስጥ መጣሉን የጠቆመው ድርጅቱ፣ በቅርቡ ባደረገው ጥናት ከተሳተፉ የመስኩ ባለሙያዎች መካከል ግማሽ ያህሉ ቱሪዝሙ በመጪው አመት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘግባል ብለው እንደሚጠብቁ መግለጻቸውንም አስረድቷል፡፡
አለማቀፉ የንግድ ጉዞ ማህበር በበኩሉ በፈረንጆች አመት 2020 ለንግድ ጉዞ ወጪ የተደረገው ገንዘብ ካለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ52 በመቶ ወይም የ694 ቢሊዮን ዶላር ቅናሽ ማሳየቱን ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የንግድ ጉዞ ወጪ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2021 ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በ21 በመቶ ያህል እድገት ያሳያል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ የዘርፉ ወጪ ከኮሮና ወረርሽኝ በፊት ወደነበረው 1.43 ትሪሊዮን ዶላር ለመመለስ ግን ሶስት አመታት ያህል ሊወስድበት አንደሚችል መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡


  ድረገጹ በየወሩ በአማካይ 92.5 ቢሊዮን ጊዜ ተጎብኝቷል

           ታዋቂው የመረጃ ፍለጋ አውታር ጎግል በአመቱ በብዛት በመጎብኘት ቀዳሚው የአለማችን ድረገጽ ለመሆን መብቃቱና ባለፈው የፈረንጆች አመት 2020 ድረገጹ በየወሩ በአማካይ 92.5 ቢሊዮን ጊዜ መጎብኘቱ ተዘግቧል፡፡
በየአመቱ ከ2 ትሪለዮን በላይ የመረጃ ፍለጋ ጥያቄዎችን የሚያስተናግደውንና የጎብኝዎቹ ቁጥር ካለፈው አመት የ52.9 በመቶ እድገት ያሳየውን ጎግል በመከተል ዩቲዩብ 34.6 ቢሊዮን ጊዜ በመጎብኘት፣ ፌስቡክ ደግሞ 25.5 ቢሊዮን ጊዜ በመጎብኘት የሁለተኛና የሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውን ቪዡዋል ካፒታሊስት ድረገጽ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ባየወሩ በአማካይ ትዊተር 6.6 ቢሊዮን፣ ዊኪፔዲያ 6.1 ቢሊዮን፣ ኢንስታግራም 6 ቢሊዮን፣ ባይዱ 5.6 ቢሊዮን፣ ያሁ 3.8 ቢሊዮን፣ ኤክስቪዲዮስ 3.4 ቢሊዮን፣ ፖርንሃብ 3.3 ቢሊዮን ጊዜ ያህል በመጎብኘት ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንና በብዛት ከሚጎበኙ 50 ታዋቂ የአለማችን ድረገጾች መካከል 27ቱ መቀመጫቸው በአሜሪካ መሆኑንም መረጃው አክሎ ገልጧል፡፡

https://youtu.be/vEiQh2ZMBbU?t=81

Page 3 of 516