Administrator

Administrator

በኦሮሚያ ክልል በሁሉም አካባቢዎች በፀረ ሰላም ሀይሎች ተጠርቶ የነበረው ሰልፍና አድማ በህዝቡና በፀጥታ አካላት ተሳትፎ መክሸፉን የክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።
የአሮሚያ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌታቸው ባልቻ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ፤ በውስጥና በውጭ ፀረ ሰላም ሀይሎች የሚደረገው የአድማ ጥሪና የኦሮሚያ ክልልን  የሁከትና የብጥብጥ ማዕከል የማድረግ ሙከራ የዛሬውን ጨምሮ ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን ጠቁመው፤ የአድማ ጥሪው፣ ሰላም ወዳድ በሆነው ህዝብና በጸጥታ አካላት የጋራ ቅንጅት ከሽፏል ብለዋል፡፡
ህዝቡ አሁን ያለውን የመልማት፣ የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ የሚፈታለትን እንጂ መንገድ የመዝጋት፣ የንግድ እንቅስቃሴን የማቋረጥና መሰል ፀረ ሰላም ድርጊቶችን እንደማይቀበል በዛሬው ዕለት በተግባር አሳይቷል ብሏል፤ ኃላፊው፡፡
ማንኛውንም የአድማ ጥሪ ተከተሎ የኦሮሚያ ክልልን የጥፋትና የሁከት ማዕከል ለማድረግ ከእንግዲህ በኋላ የሚካሄድ ሰልፍ እንደማይኖርም ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ማንኛውም ሰው ከህግ በታች መሆኑንና ላጠፋውም ጥፋት በህጉ መሰረት የሚጠየቅ መሆኑን በመግለፅ፤ ይህንን ለመቀልበስ የሚደረግ ማንኛውም ህገ ወጥ እንቅስቃሴ ተቀባይነት እንደሌለው አቶ ጌታቸው ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡን ሰልፍ ለማስወጣት፣ #በእስር ላይ የሚገኘው ጃዋር መሃመድ ሞቷል; የሚል ሃሰተኛ መረጃ ተሰራጭቶ እንደነበር ምንጮች ጠቁመዋል፡፡የፌደራል አቃቤ ህግ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፤ የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሆነው ተሾሙ፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት በዛሬው እለት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ ነው የምክትል ከንቲባነት ሹመቱን ያፀደቀው።

ቀደም ሲል በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ሃላፊነቶችና የአዳማ ከንቲባ በመሆን  ያገለገሉት ወ/ሮ አዳነች፤ የለውጡን መምጣት ተከትሎ የፌዴራል ገቢዎች  ሚኒስትር እንዲሁም  የመጀመሪያዋ ሴት የፌደራል አቃቤ ህግ ሆነው  ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

ወ/ሮ አዳነች በተለይ የገቢዎች ሚኒስትር ሳሉ በተሾሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በግብር አሰባሰብ ባስመዘገቡት አመርቂ ውጤት ከመንግስት አድናቆትን ማግኘታቸው አይዘነጋም፡፡

ላለፉት ሁለት ዓመታት አዲስ አበባን በምክትል ከንቲባነት ያገለገሉትን ኢንጂነር ታከለ ኡማን በመተካት ነው ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የተሾሙት፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ የኢንጂነር ታከለ ኡማን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ሚኒስትርነት ሹመት ጨምሮ በዛሬው ዕለት 10 አዳዲስ ሹመቶችን እንደሰጡ የጠ/ሚኒስቴር ጽ/ቤት  አስታውቋል፡፡

ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ዕለት 10 ሹመቶችን ሰጥተዋል።

 በዚሁ መሰረት፦

 1. ዶ/ር ቀንዓ ያደታ- የመከላከያ ሚኒስትር

2. ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቴዎስ- ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

3. ዶ/ር ሳሙኤል ሁርካቶ- የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር

4. ኢንጂነር ታከለ ኡማ- የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር

5. አቶ ተስፋዬ ዳባ- ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

6. አቶ ዮሐንስ ቧያለው – የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂክ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር

7. አቶ ንጉሡ ጥላሁን – የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን ኮሚሽነር

8. አቶ እንደአወቅ አብቴ – የብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ዳይሬክተር

9. አቶ ፍቃዱ ጸጋ – ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ

10. ፕሮፌሰር ሂሩት ወልደ ማርያም – በሚኒስትር ማዕረግ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ዘርፍ አማካሪ በመሆን መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስቴር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።

 

  --የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠር ሰዎች በአካባቢያቸው ካለው ዓለም ጋር ዘወትር በሚያደርጉት ግንኙነት ወቅት ይከሰታል፡፡ ዘወትር ከመገናኛ ብዙኃን፣ ኢንተርኔት፣ ሶሻል ሚዲያ፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ጓደኞችና የቤተሰብ አባላት አሳማኝ መልዕክቶች ይጐርፋሉ:: እንዲሁም የሕዝብ ጉዳዮችን በተመለከተ ከትምህርት ቤቶች፣ ከመንግሥትና የፖለቲካ ድርጅቶች ሰዎች መረጃዎችን ያገኛሉ፡፡ በተጨማሪም ከፖለቲካ የምርጫ ዘመቻም ስለ ተወዳዳሪዎቹና አቋማቸው እንዲሁም ስለ ወቅቱ ጉዳዮች ይማራሉ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ተከታታይ መረጃዎች ናቸው ሰዎች ስለተለያዩ የፖለቲካ ኩነቶች፣ ተዋናዮችና ፖሊሲዎች የሚኖራቸውን አስተያየት የሚቀርጹት፡፡
የአስተያየቶችና የጠባዮች መሠረት የሆኑት ልማዶችና (norms) የተወሰኑ ባሕርያት ወይም የማይለወጡ ሐሳቦች (stereotypes) በሕዝብ አስተያየት ምሥረታና ለውጥ ወይም አለመለወጥ ላይ ከባድ ተጽእኖ አላቸው፡፡ እነዚህም ፅንሰ ሐሳቦች ሰዎች ለመለወጥ፣ አንድ ድርጊት ለመፈፀም፣ እንዲሁም አስተያየታቸውን በምርጫ፣ በሰላማዊ ሰልፍ፣ በብጥብጥና አድማ ለማሳየት ለምን እንደሚገፋፉ ለማወቅ ጠቃሚ መሆናቸውን የሕዝብ አስተያየት ምሁራን ይረዳሉ፡፡ ለዚህም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ዎል ስትሪትን ተቆጣጠሩ “Occupy Wall Street” ብሎ ለተነሳው ንቅናቄ፣ በመነሻው ወቅት የአሜሪካን ሕዝብ ያሳየው የነበረው የጋለ ስሜትና ድጋፍ ቆይቶ ንቅናቄው ምንም የጠራ መልእክት እንደሌለውና ተቃዋሚዎቹም በደንብ ያልተደራጁና ችሎታ የሌላቸው መሆናቸው ግልጽ ሲሆን ማጣጣሉ ነው፡፡
በግለሰብ ጠባይ ዙሪያ የሕዝብ አስተያየትን ካጠኑት መካከል የሶሲዮሎጂስቱ የደብሊው ፊልፕስ ዴቪሰን (W.Phillips Davison)  ሞዴል ለሕዝብ አስተያየት ምሥረታ ጉዳዮች (issues) ያላቸውን ሚና አጥብቆ ይናገራል:: እንደ ዴቪሰን አስተያየት፤ “…የምሥረታው ሂደት የሚጀምረው ጉዳዩ በቀረበ ወቅትና ሰዎች ሐሳቦችን በተለዋወጡ ጊዜ ነው፡፡ ጉዳዩ ወደ ሦስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛ ሰው በተላለፈ ጊዜ ሥር እየሰደደ ነው ይባላል፡፡ ብዙዎች ጉዳዮች ይህ የሰዎች ሰንሰለት ረጅም ርቀት እንኳን ሳይሄዱ ይጠፋሉ፤ ይሁንና የሚቀሩት ጥቂቶቹ የሕዝብ አስተያየት መነሻ ይሆናሉ:: የቅርብ ጊዜ ተምሳሌት የሚሆነን የዩቲዩብ ቪዲዮ መልዕክቱን በተጋሩት ሰዎች መጠን ወይ ገንኖ ይቆያል (“go viral”) አለበለዚያም ይደበዝዛል”::
እንደ ሶሲዮሎጂስቱ ኸርበርት ብሉመር፤ የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠር የሚከሰተው በውይይት ጊዜ ባለው መመላለስ ሲሆን፤ ቅርጽ የሚይዘው ግን በእሰጥ አገባው ወቅት ነው:: የሕዝብ አስተያየት ተፈጠረ ማለት ሰዎች የየራሳቸውን ልምድ በመጋራት ለአስታራቂ ሐሳብና ከእኔ ይቅር ለማለት ዝግጁ ናቸው ማለት ነው፡፡ እንደዚህም በማድረግ ነው የተከፋፈለው ሕዝብ አንድ ሆኖ ተግባር ላይ የሚሰማራው:: እንደዚሁም የቪንሰንት ፕራይስና ዶናልድ ኤፍ ሮበርትስ (Vincent Price and Donald F. Roberts) ሞዴል፤ የሕዝብ አስተያየትን የማኅበራዊ ሂደት መሆኑን ገልጾ ሲያብራራ፤ “የሕዝብ አስተያየት አፈጣጠርና አለዋወጥ ሂደት የተወሳሰበና የፖለቲካ ተዋንያኑን፤ ሚዲያንና ፍላጐት ያለውን ሕዝብ የሚያቅፍ ሆኖ፣ እነዚህ ሁሉ በማኅበራዊ ጉዳዮች አስተያየት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር ይጥራሉ፤ ስለሆነም የሕዝብ አስተያየት ሂደት የማኅበራዊ ስምምነት ውጤት ነው” ይላል፡፡
ሰዎች በህይወት ዘመናቸው ከአካባቢያቸው ካሉት ሰዎች የሚማሩት ማኅበራዊ ልማድ፣ እምነትና ጠባይ አስተያየታቸውን ይቀርጻል:: በዚህም ሂደት ውስጥ ቤተሰብ፣ የሃይማኖት ተቋሞች (ቤተ ክርስቲያንና መስጊድን የመሰሉ)፣ ትምህርት ቤቶች የሕዝብ አስተያየትን በመቅረፅ ሂደት ውስጥ ያላቸው ሚና ቀላል አይደለም፡፡ የእነዚህ ተቋሞች ተጽእኖ የሚጀምረው ማልዶ ቢሆንም፣ በሰው ልጅ የዕድሜ ዘመን ውስጥም ቆይቶ ይታያል:: “የፖለቲካ ባህሉ ተመሳሳይ በሆነበት አገር፣ ይህ የሆነበት ምክንያቱን ለማወቅ በመጀመሪያ መታየት ያለባቸው ቦታዎች የሕፃናት ማሳደጊያ፣ ትምህርት ቤት፣ ቤተ ክርስቲያን…” ናቸው ይላል ዋልተር ሊፕማን:: የፖለቲካ አስተሳሰብን በመቅረጽ ረገድ ቤተሰብ ዋነኛው ነው፡፡ ቤተሰብ ሕፃናትን በተለያዩ የማኅበራዊ ልማዶችና እሴቶች ይቀርጻቸዋል፤ ይህም ወደፊት ለሚኖረው የፖለቲካ ሥርዓት ባሕርይ አስፈላጊነት አለው፡፡ ቤተሰብ የፖለቲካ መሪዎችን፣ አክቲቪስቶችን፣ እንዲሁም ፖለቲከኞችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ የፖለቲካ ሥራዎች ያከናውናል፡፡ የኬኔዲና የቡሽ ቤተሰቦች በአሜሪካ፣ የኬንያታ ቤተሰብ በኬንያ፣ የኔህሩ ቤተሰብ በሕንድ ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡
ቤተሰብ በአባላቱ አስተሳሰብና አስተያየት ምሥረታና አፈጣጠር ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ ሀርውድ ኤል ቻይልድስ፣ “የሕዝብ አስተያየት ባሕርይ፣ አፈጣጠር እና ሚና” ብሎ በሰየመው በ1965 እ.ኤ.አ በወጣው መጽሐፉ እንዲህ ብሏል፡-
ብዙውን ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ ነው የሕፃናት የመጀመሪያው ቀረጻ የሚካሄደው፣ ልማዶች እንዲሁም ጥላቻዎች፣ የሚሰረፁት፣ የሚወደድና የሚጠላ፣ የሚፈቀድና፣ እንዲሁም ግቦች የሚዳብሩት:: በተጨማሪም ወላጆችና ቤተሰቦች በሕፃናቱ የመጀመሪያ ዓመታት ወቅት በሚገፋፏቸው ጉዳዮች ላይ ሙሉ ቁጥጥር አላቸው፡፡ በዚህን ወቅትም ነው የቤተሰባዊ ሕይወት የቅርብ ግንኙነት፣ የቅጂ፣ ድግግሞሽና ሐሳብ ማቅረብ የሚጧጧፈው፡፡ የአበላል፣ የመኝታ፣ የጨዋታ ልማዶች፣ ቀደም ብለው ይዳብሩና፣ ልምምዶቹም አድገውና ጐልብተው የአስተሳሰብ ቅርጽ ይይዛሉ፡፡ በእነዚህ የቀደሙ ዓመታትም ነው ሕፃናት የሥልጣንን ተፈጥሮ የሚያውቁት፣ ቢያንስ በቤታቸው ውስጥ የሚገኘውን የሥልጣን ዐይነት፡፡ እንዲሁም በቤት ውስጥ ነው ልምዶችና ተጽእኖዎች ስሜትን የሚነኩ አንዳንዶቹም እጅግ አሰቃቂ የሆኑ የተለያዩ መልኮች የሚኖራቸው፡፡ ምንም እንኳ ቤተሰብ ስለቀደሙ ዓመታት አስተማሪ ባይሆንም ቅሉ፣ ችሎታን፣ ስሜትን፣ ምኞትን ወይም ተስፋን በማሳደግ ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ ቤተሰብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በልጅነት ጓደኞች ምርጫ፣ በትምህርት ቤት አመራረጥና ሌሎች በዛ ያለ ጉዳዮች ላይ ተጽእኖ አለው፡፡ በርግጥም ለባህል መተላለፍ ተግባር፣ ለአጠቃላይና መካከለኛ አስተሳሰቦችና የተለዩ አስተያየቶች መዳበር ዋና ወኪል ነው፡፡
ትምህርት ቤቶችም እንዲሁ በሕዝብ አስተያየት አፈጣጠርና ምሥረታ ላይ ታላቅ ተጽእኖ ካላቸው ተቋማት መካከል የሚገኙ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ ባሁኑ ጊዜ በሥልጣን ላይ የሚገኙት ሰዎች መሠረታዊ አስተያየት ወይም ዕይታ በአብዛኛው የተቀረፀው ከሃያና ሠላሳ ዓመታት በፊት ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሕፃናትን ትናንሽ ኢትዮጵያዊያን፣ ኬንያዊያን፣ ናይጀሪያኖች፣ አሜሪካኖች፣ ጀርመኖች፣ ቻይናዊያን፣ የመኖች፣ ወዘተ አድርገው ይሠሯቸዋል፡፡ በሕፃናቱ አዕምሮ ውስጥ የሕዝቦችን ታሪክና ትውፊት፣ እምነትና ርዕዮተ ዓለም ይቀርፃሉ፡፡ ይህንንም ሲያደርጉ በሂደቱ የፖለቲካ ቅስቀሳን ተግባር ይደግፋሉ፡፡ የትምህርት ሥርዓቱም እሴቶችንና ርዕዮተ ዓለሞችን ከመቅረጽ ባለፈ ከትምህርት ቤት በተመረቀው ጐልማሳ የፖለቲካ ልምድና አስተያየት ላይ የሚንፀባረቅ ምሁራዊ ሙያዎችንና መሠረታዊ አስተሳሰብንም ያስፋፋል:: የትምህርት ሥርዓት በዜጐች ቀረጻ ላይ ተጽእኖ ከሚያሳርፉት መካከል አንደኛው ነው፡፡     
(ሰሞኑን ከወጣው የዶ/ር አድማሱ ጣሰው " የሕዝብ አስተያየት" እና ተዛማች ጽንሰ ሐሳቦች  መጽሐፍ የተቀነጨበ)


 ባማኮን ኢንጂነሪንግ ከእህት ኩባንያዎቹ ጋር በመተባበር ለኮቪድ 19 ህሙማን ከፍተኛ አገልግሎት የሚሰጡ ኦክስጂን ኮንስትሬተሮችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ረቡዕ ነሐሴ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ለገሰ፡፡ ኩባንያው ያበረከታቸው እነዚህ 100 ኮንሰንትሬተሮች እያንዳንዳቸው ለሁለት ታማሚ በበቂ ሁኔታ ኦክስጂን መሰብሰብ የሚችሉ ሲሆን፤ ለዚሁ ተግባር ታቅደው በልዩ ሁኔታ መታሰራቸውን የባማኮን ኢንጂነሪንግ ኩባንያ ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ግርማ ገላ አስታውቀዋል፡፡
የኦክስጅን መሰብሰቢያ ማሽኖቹ በሶኬት የሚሰሩና ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ሲሆን፤ ከ10 ሚ ብር በላይ ወጪ እንደወጣባቸውም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው አገራችን አሁን ያለችበትን ተጨባጭ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባትና ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ ጋር የተገጠመውን ትንቅንቅ ታሳቢ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት እነዚህን መሳሪያዎች መለገሱንም ኢ/ር ግርማ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩም ለተደረገለት ልገሳ ለኩባንያው ኃላፊዎች ምስጋና አቅርቧል፡፡ ባማኮን ኢንጂነሪንግ በሀገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የረጅም ዓመታት ልምድ ያለው የደረጃ 1 ተቋራጭ ሲሆን፤ በስራቸውና እየሰራቸው ባሉ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የህንፃ ግንባታዎች ይበልጥ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የሃይል ንዑስ ጣቢያዎችንና ሃይል ማስተላለፊያ አውታሮችንም የሚሰራ ኩባንያ መሆኑም ታውቋል፡፡


   ባለፈው ማክሰኞ ማለዳ…
አለም ከወደ ሩስያ በሰማው በጎ ዜና ተደሰተ፣ ተስፋ አደረገ፡፡
“ምስጋና ይግባ ለታላቋ ሩስያ ተመራማሪዎች፤ ለወራት ነጋ ጠባ ባደረጉት ምርምር እነሆ ለኮሮና ቫይረስ ሁነኛ ክትባት አግኝተናል፤ ስፑትኒክ - 5 የሚል ስያሜ የሰጠነው የአለማችን የመጀመሪያው የኮሮና ክትባት፣ የሩስያ የቀዳሚነት ተምሳሌት ነው!...” አሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፡፡
ፑቲን ባለፉት ሁለት ወራት በሰዎች ላይ ሙከራ ሲደረግበት ነበር ያሉት በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በገፍ ተመርቶ ጥቅም ላይ እንዲውል መፈቀዱን ማስታወቃቸውን ተከትሎ ግን፣ ነገሩ ከመላው የአለም ዙሪያ በጥርጣሬ አይን መታየቱና ጥያቄ ማስነሳቱ አልቀረም፡፡ ክትባቱ መደበኛውን የምርምር ሂደት ሳያጠናቅቅ በችኮላ በገፍ ወደማምረት የተገባበት ነው በሚል አገራትና ተቋማት የሩስያን አስደሳች ዜና ጥርጣሬና ትዝብት ውስጥ ሲጥሉት ጊዜ አልፈጀባቸውም፡፡
የህክምናው ዘርፍ ባለሙያዎች የሩስያ ክትባት ያሰጋናል ሲሉ ስጋታቸውን በስፋት እየገለጹ ሲሆን፣ የኮሮና ክትባት ምርምር ሚስጥሮቻችንን ልትመነትፈን መሞከሯን ደርሰንበታል ሲሉ ሩስያን ሲወነጅሉ የሰነበቱት እንግሊዝ፣ አሜሪካና ካናዳም የፑቲንን መግለጫ ተከትሎ በሰውዬው ላይ የፌዝና የስላቅ ቃላትን መወርወራቸውን ቀጥለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ፑቲን ግን ክትባቱ አስፈላጊውን የምርመራ ሂደት ማለፉንና ፍቱን መሆኑን በመግለጽ እንዲሁም የገዛ ልጃቸውም መከተቧን በዋቢነት በመጥቀስ፣ ከያቅጣጫው የሚሰነዘርባቸውን ትችት መሰረተ ቢስ ብለው አጣጥለውታል፡፡
ባለፈው ሳምንት ሩስያ ክትባት በማምረት ሂደት አለማቀፍ አካሄዶችን እንድትከተል ያሳሰበውና በሶስተኛ ደረጃ ላይ ካስቀመጣቸው ክትባቶች ተርታ ያላሰለፈው የሩስያ ክትባት ጉዳይ ያሳሰበው የአለም የጤና ድርጅት፤ በመዲናዋ ሞስኮ የሚገኘው ጋማሊያ ኢንስቲቲዩት የተባለው ተቋም ከተለመደው አሰራር ውጭ የምርምር ሂደቱን ለማንም ትንፍሽ ሳይልና በተጣደፈ ሁኔታ አግኝቻለሁ ብሎ ባወጀው በዚህ በክትባት ዙሪያ ከሩስያ መንግስት ጋር ውይይት መጀመሩ ተነግሯል፡፡
የሆነው ሆኖ ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በስፋት መሰራጨቱን የቀጠለ ሲሆን፣ ቫይረሱ እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ድረስ በመላው አለም 20.9 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ማጥቃቱንና የሟቾች ቁጥር ከ749 ሺህ ማለፉን የገለጸው ዎርልዶ ሜትር ድረገጽ፤ ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም 13.7 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቋል፡፡ እስከተጠቀሰው ጊዜ ድረስ በአሜሪካ ከ5.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውና የሟቾች ቁጥርም ከ169 ሺህ ማለፉን የጠቆመው ድረገጹ፣ በብራዚል 3.17 ሚሊዮን ሰዎች ተጠቅተው ከ104 ሺህ በላይ ሰዎች መሞታቸውን፣ በህንድ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መጠቃታቸውንና በሜክሲኮ ወደ 55 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡
ኮሮና ቫይረስ በአፍሪካ አህጉር እስካለፈው ሃሙስ አመሻሽ ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን አጥቅቶ ወደ 25 ሺህ የሚደርሱትን ለሞት መዳረጉን የገለጸው የአፍሪካ የበሽታ ቁጥጥርና መከላከል ማዕከል፤ ያገገሙት ሰዎች ቁጥርም 769 ሺህ ያህል መድረሱን ባወጣው መረጃ አስታውቋል:: ወደ 569 ሺህ ሰዎች የተጠቁባትና ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች የሞቱባት ደቡብ አፍሪካ በአህጉሪቱ ከፍተኛውን ጉዳት ያደረሰባት ቀዳሚዋ አገር ስትሆን፣ ግብጽ በ96 ሺህ፣ ናይጀሪያ በ48 ሺህ፣ ጋና በ42 ሺህ፣ አልጀሪያ በ37 ሺህ የቫይረሱ ተጠቂዎች ቁጥር ይከተላሉ፡፡
በሌሎች ተያያዥ ዜናዎች፣ ለ102 ቀናት ያህል በቫይረሱ የተያዘ ሰው ሳትመዘግብ የቆየችው ኒውዚላንድ ከሰሞኑ አራት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ማግኘቷን የዘገበው ቢቢሲ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከአጠቃላዩ የእንግሊዝ ህዝብ 6 በመቶ ያህሉ ወይም 3.4 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እስካለፈው ሃምሌ ወር አጋማሽ ድረስ በኮሮና ቫይረስ ተይዘዋል ተብሎ እንደሚገመት ኢምፔሪያል ኮሌጅ ኦፍ ለንደን ከ100 ሺ በላይ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ላይ እንዲሁም በቤት ለቤት ምርመራ ባደረገው ጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት የቅርብ አማካሪ የሆኑትና የአገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ጆርጅ ሮድሪጌዝ በኮሮና መጠቃታቸው መነገሩን የዘገበው ቢቢሲ፤በኬንያም አንድ ከፍተኛ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባለስልጣን በቫይረሱ ሳቢያ ለሞት መዳረጋቸውን አመልክቷል፡፡


   ፌስቡክ በ3 ወራት 22.5 ሚሊዮን የጥላቻ መረጃዎችን አስወግጃለሁ አለ

            በመላው አለም በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ800 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በተሳሳቱና ሃሰተኛ በሆኑ የኮሮና ቫይረስ መረጃዎች ሳቢያ ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን፣ አሜሪካን ጆርናል ኦፍ ትሮፒካል ሜዲስን ኤንድ ሃይጂን በተባለው የህትመት ውጤት ላይ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃን አንድ ጥናት ጠቅሶ ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከጥር እስከ መጋቢት ባሉት ሶስት ወራት ብቻ በተሳሳተ መረጃ ሳቢያ ለሞት ከተዳረጉት መካከል አብዛኞቹ ከኮሮና ያድናሉ በሚል ሜታኖል ወይም ሌሎች ከአልኮል የተሰሩ የጽዳት ፈሳሾችን በመጠጣት ምክንያት መሞታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 5 ሺህ 800 ያህል የተለያዩ አገራት ዜጎችም በማህበራዊ ድረገጾች በኩል በተሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች ሳቢያ ወደ ሆስፒታል እንዲገቡ መደረጋቸውን አስታውሷል፡፡ በርካታ ሰዎች በማህበራዊ ድረገጾች የሚሰራጩ ሳይንሳዊ ያልሆኑና በጥናት ያልተረጋገጡ መረጃዎችን በመከተል ከፍተኛ መጠን ያለው ነጭ ሽንኩርት ከመብላት የላም ሽንት እስከ መጠጣት የተለያዩ ለጤና አደገኛ ድርጊቶችን እንደፈጸሙም በጥናቱ ተገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ታዋቂው ማህበራዊ ድረገጽ ፌስቡክ እስካለፈው ሰኔ በነበሩት ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ ከ22.5 ሚሊዮን በላይ የጥላቻ ንግግር የጽሁፍና የምስል መረጃዎችን ከገጹ ማስወገዱን አስታውቋል፡፡
ኩባንያው እስከ ሚያዝያ በነበሩት ሶስት ወራት መሰል እርምጃ የወሰደባቸው ከዘር፣ ብሄር፣ ሃይማኖትና ሌሎች ጉዳዮች ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግር መረጃዎች 9.6 ሚሊዮን ያህል ብቻ እንደነበሩ ያስታወሰው ሮይተርስ፣ ቁጥሩ ሊጨምር የቻለው መሰል መረጃዎችን የሚያሰራጩ ተጠቃሚዎች ከመበራከታቸውና ኩባንያው ለጉዳዩ የሰጠው ትኩረት ከመጨመሩ ጋር በተያያዘ መሆኑንም አመልክቷል፡፡

 ሂላሪ ሃምፍሬ ካዌሳ የተባለው ኡጋንዳዊ የ19 አመት ታዳጊ በመጪው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደርና አገሪቱን ከ35 አመታት በላይ ያስተዳደሩትን ሙሴቬኒን ለመተካት ዝግጅት ማድረግ መጀመሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
አገር አልምራ እንጂ ወትሮም የመሪነት ብቃት አለኝ፤ አገሬን ለመምራት ብቁ ነኝ የሚለው ካዌሳ፣ ለዕጩ ተወዳዳሪነት ምዝገባ ክፍያ የሚያስፈልገውን 5ሺህ 400 ዶላር ከለጋሾች ለማሰባሰብ መዘጋጀቱን ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፣ ከ100 በላይ የአገሪቱ ግዛቶች ከእያንዳንዳቸው 100 የድጋፍ ፊርማ ለማሰባሰብ ማቀዱንም አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ህገ መንግስት መሰረት ዕድሜው ከ18 አመት በላይ የሆነው ዜጋ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ታዳጊው ኡጋንዳን ከሶስት አስርት አመታት በላይ በብቸኝነት ያስተዳደሩትንና አሁንም ስልጣናቸውን ለማራዘም ቆርጠው የተነሱትን ፕሬዚዳንት ዩሪ ሙሴቬኒን ተክቶ አገሪቱን በአዲስና በትኩስ ሃይል ወደ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ቆርጦ መነሳቱን እንደገለጸም አክሎ ገልጧል፡፡


 በእስራኤል የሚገኝ አንድ ታዋቂ የጌጣጌጥ አምራች ኩባንያ በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የተተመነለትን እጅግ ውድ የፊት ጭምብል ባለፈው እሁድ ለእይታ ያበቃ ሲሆን፣ የጭምብሉ የመሸጫ ዋጋ 1.5 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ያቬል የተባለው ኩባንያ እያመረተው የሚገኘው ይህ የፊት ጭምብል ከ18 ካራት ነጭ ወርቅ የተሰራና በ3 ሺህ 600 ደቃቅ የአልማዝ ፈርጦች የተንቆጠቆጠ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ ጭምብሉ በቀጣዩ አመት ተጠናቅቆ ለሽያጭ እንደሚበቃም አመልክቷል፡፡ ኩባንያው ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያመርተውን ይህንን እጅግ ውድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር መዥረጥ አድርጎ ለመግዛት የፈቀደ ገዢ መገኘቱን የጠቆመው ዘገባው፣ በአሜሪካ የሚኖር ቻይናዊ ነጋዴ ከመሆኑ ውጭ ስለ ግለሰቡ ተጨማሪ መረጃ አልሰጠም፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአለም ህዝቦች በኮሮና ቫይረስ ሳቢያ በከፋ የኢኮኖሚ ቀውስ እየተመቱና ለስራ አጥነት እየተዳረጉ በሚገኙበት አስቸጋሪ ወቅት ላይ ለአንድ ጭምብል 1.5 ሚሊዮን ዶላር ግፍ ነው የሚሉ አስተያየቶች መደመጣቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ጭምብሉ 270 ያህል ግራም ክብደት ያለው ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ ኮሮናን ለመከላከል በፊት ላይ አጥልቆ ለመንቀሳቀስ አመቺ ላይሆን እንደሚችል መነገሩንም አክሎ ገልጧል፡፡

  ፎርብስ መጽሄት የ2020 የፈረንጆች አመት የአለማችን ከፍተኛ ተከፋይ ወይም ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ወንድ የፊልም ተዋንያንን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ይፋ ያደረገ ሲሆን ባለፈው አመት በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ዋይኔ ጆንሰን ዘንድሮም በ87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በቀዳሚነት ተቀምጧል፡፡
የቀድሞው የሪስሊንግ ተጫዋችና ሬድ ኖቲስ በሚለው ፊልም የሚታወቀው ተዋናዩ በኔትፍሊክስ ድረገጽ ከሚታዩት ፊልሞቹና ፕሮጀክት ሮክ ከተሰኘው የአካል ብቃትና የአልባሳት ኩባንያው ያገኘውን ገቢ ጨምሮ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ በድምሩ 87.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙት ቀዳሚዎቹ 10 የፊልም ተዋንያን በድምሩ 545.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርበስ፣ ሩብ ያህሉን ገቢ ያገኙትም ኔትፍሊክስ ከሚባለውና ፊልሞችን በአንተርኔት አማካይነት በስፋት ከሚያሳየው ኩባንያ መሆኑን ገልጧል:: በአመቱ ሁለተኛውን ከፍተኛ ገቢ ያገኘው የአለማችን ታዋቂ የፊልም ተዋናይ ሬድ ኖቲስና ሲክስ አንደርግራውንድ በተባሉት ፊልሞች ላይ ድንቅ ብቃቱን ያሳየው ሪያን ሬኖልድስ መሆኑን የጠቆመው መጽሄቱ፣ ተዋናዩ በአመቱ 71.5 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን አመልክቷል፡፡
ታዋቂው የፊልም ተዋናይና ፕሮዲዩሰር ማርክ ዋልበርግ በ58 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ፣ ቤን አፍሊክ በ55 ሚሊዮን ዶላር አራተኛ፣ ቪን ዲዝል በ54 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ አምስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
እስከ 10ኛ ያለውን ደረጃ በያዙት ባለ ከፍተኛ ገቢ የአለማችን ተዋንያን መካከል የተካተተው ብቸኛው የቦሊውድ ተዋናይ ህንዳዊው አክሻይ ኩማር ሲሆን በ48.5 ሚሊዮን ዶላር የስድስተኛ ደረጃን ይዟል፡፡
ሊል ማኑኤል ሚሪንዳ እና ዊል ስሚዝ (በተመሳሳይ 45.5 ሚ. ዶላር)፣ አዳም ሳንድለር (41 ሚ. ዶላር) እና ጃኪ ቻን (40 ሚ. ዶላር) እንደ ቅደም ተከተላቸው ከሰባተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙ የአመቱ የአለማችን ባለ ከፍተኛ ገቢ ወንድ የፊልም ተዋንያን መሆናቸውንም ፎርብስ መጽሄት ያወጣው ዝርዝር ያሳያል፡፡