Administrator

Administrator

Saturday, 21 March 2015 10:08

የፀሐፍት ጥግ

ፀሐፊ፤ የበለጠ ገንዘብ እንዴት አገኛለሁ ሳይሆን ብዙ አንባቢያን ጋ እንዴት እደርሳለሁ ነው ማለት ያለበት፡፡
ብሪያን አልዲስ
 ታሪክ ፀሐፊ ይመዘግባል፤ ልብ ወለድ ፀሐፊ ይፈጥራል፡፡
ኢ.ኤ.ፎርስተር
በአርታኢዎች ወይም በሃያሲያን አስተያየት አትዘን፡፡ እነሱ የጥበብ ትራፊክ ፖሊስ ናቸው፡፡
ጊኒ ፎውለር
ግንብን በመሬት ላይ ከመገንባት ይልቅ በአየር ላይ መገንባት የበለጠ እርካታ አለው፡፡
ኢድዋርድ ጊቦን
ስለምታውቀው ነገር ከመፃፍ ይልቅ  ስለሚሰማህ ነገር መፃፍ የተሻለ ነው፡፡
ኤል.ፒ.ሃርትሌይ
ፀሃፊ ጨርሶ እረፍት የለውም፡፡ የፀሐፊ ህይወት አንድም መፃፍ ነው አሊያም ስለሚፅፈው ማሰብ ነው፡፡
ኢዩጂኔ ሎኔስኮ
ጠዋት እነሳለሁ፤ መተየቢያ ማሽኑን እስኪያቃስት ድረስ እቀጠቅጠዋለሁ፤ ከዚያ አቆማለሁ፡፡
ክላረንስ ቡዲንግቶን ኬላንድ
የምንፅፈው ስለፈለግን አይደለም፤ የምንፅፈው መፃፍ ስላለብን ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
ፀሃፊውን ያላስለቀሰ፣ አንባቢውን አያስለቅስም፡
ጆርጅ ሙሬ
ሥራው መናገር ሲጀምር ደራሲው አፉን መጠርቀም አለበት፡፡
ፍሬድሪክ ኒቼ
 በትንሽ ድፍረት ማጣት ብቻ ዓለም ተሰጥኦዎችን ታጣለች፡፡
ሲድኒ ስሚዝ
የመጀመሪያው ምዕራፍ የአሁኑን መፅሃፍት ሲያሸጥ፣ የመጨረሻው ምዕራፍ ቀጣዩን መፅሃፍ ያሸጣል፡፡
ሚኪ ስፒላኔ
ሃያሲ መንገዱን የሚያውቅ ግን መኪና መንዳት የማይችል ሰው ነው፡፡
ኬኔዝ ቲናን
ለቃላት ድምፅ ትኩረት ስጥ፡፡
ዴቭ ዎልቨርተን
መፃፍ በወረቀት ላይ ማሰብ ነው፡፡
ዊሊያም ዚንሰር

ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት ለአቅመ -ሄዋን የደረሰች የደረሰች ሴት ልጅ የነበረቻቸው እናትና አባት
በአንዲት መንደር ይኖሩ ነበር፡፡
ልጅቱ ከቀን ቀን እየወፈረች ሆዷ እየሞላ ትሄዳለች፡፡ የመንደሩ ሰው ሊጠይቃቸው ሲመጣ ጥያቄው

አንድ ዓይነት ሆነ፡፡
አንዷ ትመጣና፤
“እንዴት ዋላችሁ?”
“ደህና እግዚሃር ይመስገን”
“ጤናዎትን እንዴት ከረሙ?”
“አልፎ አልፎ ይጫጫነኝና እተኛለሁ እንጂ ብዙውን ጊዜ ተመስገን ነው ጤናዬን ደህና ነኝ”
እንግዳዋ ትንሽ ታመነታና፤
“እንደው የዚች የልጅዎ ነገር እንዴት ነው?”
እናትየው እንዳላወቀ ሆነው፤
“ምኗ?”
“እንዲያው አወፋፈሯ የጤና ነው ይላሉ?”
“አይ እንዲሁ የልጅ ገላ ሆኖ ባንዴ ወፍራ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላማረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
“እንደዛስ ከሆነ ደህና” ትላለች እያመነታች፡፡
ሌላዋም ትመጣና የተለመደውን የጤናና የዝምድናዋን ያህል የእግዚሃር ሰላምታ ታቀርብና፤
“እንዲያው የዚችን ልጅ ነገር ዝም አላችሁ?”
“ምኑን” ይላሉ እናት ከመሰላቸት ጭምር፡፡
“ይሄ አወፋፈሯ አላመረኝም”
“አይ የልጅ ገላ ሆኖ ነው እንጂ ምንም የለም”
እንዲህ በተከታታይ ሲመልሱ፣ ለመጣው ሁሉ የልጅ ገላ ነው ሲሉ፤ እዳር ሆነው የሚያስተውሉት

አባት በመጨረሻ ተነፈሱ፤
“እናንተ ይሄን ያህል ምን አስጨነቃችሁ?
የምግብም ከሆነ ሲቀንስ እናየዋለን፡፡
የልጅም ከሆነ ሲገፋ እናገኘዋለን!” አሉና ገላገሏቸው፡፡
*   *   *
“አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” እንደማለት ነው፡፡ ማንኛውንም ነገር መደበቅ፣ መሸፋፈኑ አይጠቅምም - ሁሉንም ጊዜ ይገልጠዋልና፡፡ ግልፅነት ዛሬ ወቅታዊ ወረት (fashion) የሆነ ይመስላል፡፡ ስንቶች በአደባባይ እየተናገሩ ጓዳ ጓዳውን ግን የልባቸውን እንደሚሰሩ ቤቱ ይቁጠራቸው፡፡ They shout at most against the vices they themselves are guality of ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ” እንደምንለው መሆኑ ነው በአማርኛ። ስለመልካም አስተዳደር ያወራሉ፡፡ ግን መልካም አያስተዳድሩም፡፡ ስለፍትህ ያወራሉ ግና የህግን መርህ አይከተሉም፡፡ ስለዲሞክራሲ ይናገራሉ፡፡ ግን ዲሞክራት አይደሉም፡፡ ስለእኩልነት ያወራሉ ግን ወግነው ሰው ይበድላሉ፡፡ በእኩል አያኖሩም፡፡ ስለ እጅ ንፅህና ያወራሉ፡፡ ነገር ግን እነሱ ከሙስና የፀዱ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ ግልፅነትን እንደሽፋን ነው የሚጠቀሙበት፡፡ ከእነሱ ጋር መከራከር ከንቱ ነው፡፡ አንድም “ዜጋና ሹም ተሟግቶ ደንጊያና ቅል ተላግቶ” ነው፡፡ አንድም ደግሞ ማርክ ትዌይን እንዲህ ይለኛልና፡- “ከደደብ ሰዎች ጋር አትከራከር፡፡ ወደ እነሱ ደረጃ ያወርዱህና በልምዳቸው ያሸንፉሃል” የሚለን ለዚህ ነው፡፡ (Don’t argue with stupid people, they will drag you down to their level and then beat you with experience) በትክክለኛው ሜዳ ተጫወት እንደማለት ነው፡፡ ልህነት የሌለበት ግጭት ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ “ተምረህ ተምረህ ደንቆሮ ሆነሃል” ይላሉ መንግሥቱ ለማ፡፡ በዚያው ጽሑፋቸው:-
“አንድ ዓለም ተሰጠ ለአዳም ለሄዋን
ለሁለቱ፤ ተረቱ እንደሚነግረን
…ምንስ ልጆቻቸው ቢረቡስ ቢራቡ
ጥቂቶቹ ጠግበው ብዙዎች ይራቡ
ጥቂቶች ሲያምራቸው ያንሱ ጦርነት
ብዙዎችም ይሂዱ ለመሞት ለዕልቂት!”
ይላሉ፡፡ ስለብዙሃኑ እናስብ ዘንድ ማስገንዘባቸው ነው፡፡ ጥቂቶች በሀብት የናጠጡበት ብዙሃን ይልሱት ይቀምሱት ያጡበት ሥርዓት መቼም በጅቶን አያውቅም፡፡ የናጠጡት የበደሉ የማይመስላቸው ሲሆን ደግሞ የባሰ መደናቆር ነው፡፡ ዳቦው ሳይኖር ለሰልፉ ሲሉ ብቻ ይሰለፉ ነበር እንደሚባሉት ምስኪን ሩሲያውያን እንዳንሆን መጠንቀቅም ብልህነት ነው፡፡ ለምርጫ ዝግጅት እየተደረገበት ባለበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ለአየር ሰዓትና ለበጀት በሚታገሉበት ባሁኑ ሰዓት፣ አሸናፊው ፓርቲ የለየለት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተቃዋሚዎች ጠንካራ ሆነዋል የሚል ይሆነኝ ተብሎ የተቀናጀ መንፈስ ያለበት በሚመስልበት ባሁኑ ሰዓት፣ ተሳትፈናል ማለት እንደ ድል በተቆጠረበት ባሁኑ ሰዓት፣ “ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ማለት በቀረበት ባሁኑ ሰዓት…ድል እንደ ዛፉ ብስል ፍሬ ስትርቅ፤ ቀበሮዋ ዘላ ዘላ ፍሬዋን መያዝና ማውረድ ሲያቅታት፤ “ለዛውም ሩቅ ናት፤ ደሞም መራራ ናት” አለች እንደተባለው እንዳይሆን ቆም
ብሎ ማሰብ ለሁላችንም ይበጀናል፡፡ ከዚህም ይሰውረን!!

- ቢል ጌትስ ለ16ኛ ጊዜ መሪነቱን ይዘዋል
- ቻይና በአንድ አመት 71 አዳዲስ ቢሊየነሮችን አፍርታለች
   በየአመቱ የዓለማችንን ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር የሚያወጣው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ባሳለፍነው ሳምንት የ2015ን ምርጥ 500 የዓለማችን ቢሊየነሮችን ይፋ አድርጓል፡፡
ፎርብስ ለ29ኛ ጊዜ ይፋ ያደረገውን የዘንድሮ የዓለማችን ቢሊየነሮች ዝርዝር በቀዳሚነት የመሩት አሜሪካዊው የማይክሮ ሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ ሲሆኑ፣ አጠቃላይ የሃብት መጠናቸውም 79.2 ቢሊዮን ዶላር ነው ተብሏል፡፡
ባለፈው አመት በነበራቸው ሃብት ላይ የ3 ቢሊዮን ዶላር ጭማሪ በማሳየት ለ16ኛ ጊዜ የዓለማችን ቁንጮ ባለጸጋ መሆናቸውን ያረጋገጡትን ቢል ጌትስ፣ በአመቱ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ለበጎ ምግባር በስጦታ መልክ ቢለግሱም፣ ልግስናቸው አተረፈላቸው እንጂ አልቀነሰባቸውም፡፡
እሳቸውን ተከትለው የሁለተኛነትን ደረጃ የያዙት ደግሞ፣ 77.1 ቢሊዮን ዶላር ሃብት ያላቸው ሜክሲኳዊው የቴሌኮም ዘርፍ ባለጸጋ ካርሎስ ስሊም ሄሉ ናቸው፡፡
ሌላኛው ስመጥር አሜሪካዊ ባለሃብት ዋረን ቡፌት በ72.7 ቢሊዮን ዶላር ሃብት የአመቱ የዓለማችን ሶስተኛ ባለጸጋ ተብለዋል፡፡
አመቱ በአለማችን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ቢሊየነሮች የታዩበት እንደሆነ በሚያሳየው የዘንድሮው የፎርብስ ዝርዝር ውስጥ፣ እስከ 500ኛ ደረጃ የያዙ በድምሩ 1826 ቢሊየነሮች የተካተቱ ሲሆን፣ አለማችን ባለፉት 12 ወራት ውስጥ ብቻ 181 ቢሊየነሮችን አግኝታለች፡፡

 በየዕለቱ የተወሰነ ስኒ ቡና አዘውትሮ መጠጣት ከደም ስር መዘጋት ችግር እንደሚታደግና በሰውነት ውስጥ ያለው የደም ዝውውር በአግባቡ እንዲከናወን በማድረግ ለልብ ህመም ከመጋለጥ እንደሚታደግ በጥናት መረጋገጡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች በ25 ሺህ ወንዶች እና ሴቶች ላይ የሰራውን ጥናት ዋቢ በማድረግ ዘገባው እንዳለው፣ በየዕለቱ ከሶስት እስከ አምስት ስኒ ቡና አዘውትረው የሚጠጡ ሰዎች ለልብ ህመም የመጋለጥ እድላቸው አነስተኛ እንደሆነ ተረጋግጧል፡
ቡና በልብ ጤንነት ላይ የሚያሳድረውን ተጽእኖ በተመለከተ ከዚህ በፊት የተሰሩ ጥናቶች የተለያዩ ድምዳሜዎች ላይ እንደደረሱ ያስታወሰው ዘገባው፣ አንዳንዶቹ ቡና ለልብ ህመም ያጋልጣል ሲሉ፣ ሌሎች ደግሞ በአንጻሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው ማለታቸውን ገልጧል፡፡
የኮርያ ተመራማሪዎች ያወጡት የጥናት ውጤት በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ትክክለኛ ግንኙነት በተመለከተ ግልጽ መረጃ እንዳልሰጠ የጠቆመው ዘገባው፣ ጉዳዩ አነጋጋሪ መሆን መጀመሩን አስረድቷል፡፡
የብሪቲሽ የልብ ፋውንዴሽን ባልደረባ የሆኑት ቪክቶሪያ ቴለርም፣ የተመራማሪዎቹን የጥናት ውጤት ለማረጋገጥና በቡና እና በልብ ጤንነት መካከል ያለውን ግንኙነት ለማጥራት ተጨማሪ ምርምር ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ 

Monday, 16 March 2015 09:59

የአዲስ አድማስ ምስጋና

ባለፈው ሰኞ በብሔራዊ ቴአትር በተከበረው የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የ15ኛ ዓመት በዓል ዝግጅት ላይ ግጥምና ሙዚቃ በማቅረብ፣ እንዲሁም ፕሮግራሙን ስፖንሰር በማድረግ ድጋፋችሁን ለሰጣችሁን ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን ልናቀርብ እንወዳለን፡፡
በዝግጅቱ ላይ በመታደም በዓላችንን ላደመቃችሁልን የአዲስ አድማስ ወዳጆችም ምስጋናችን የላቀ ነው፡፡
ዝግጅት ክፍሉና ማኔጅመንቱ

Monday, 16 March 2015 09:44

የፀሐፍት ጥግ

አዲስ ሃሳብ እንደ ህፃን ነው፡፡ ከመውለዱ ይልቅ መፀነሱ ይቀላል፡፡
ቴድ ኮይሲስ
አንዴ በአዲስ ሃሳብ የሰፋ አዕምሮ ወደቀድሞ ቦታው ፈፅሞ አይመለስም፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ሁሉም ስኬቶችና በልፋት የተገኙ ሃብቶች መነሻቸው ሃሳብ ነው፡፡
ናፖሊዮን ሂል
ሁሉም ነገር የሚጀምረው ከሃሳብ ነው፡፡
ኧርል ናይቲንጌል
ሃሳብ ማግኘት ስፒል ላይ እንደመቀመጥ መሆን አለበት፡፡ አዘልሎ የሆነ ነገር ሊያሰራህ ይገባል፡፡
ኢ.ኤል ሲምፕሶን
ሁሉም ታላላቅ ሃሳቦች አወዛጋቢ ናቸው፤ ወይም የሆነ ጊዜ ላይ አወዛጋቢ ነበሩ፡፡
ጊልበርት ሴልዴስ
ሃሳቦች በእርግጥም በዓለም ላይ እጅግ አደገኛ መሣሪያዎች ናቸው፡፡
ዊልያም አርቪሌ ዳግላስ
ብዙ ሃሳቦች ከበቀሉበት አዕምሮ ይልቅ ወደ ሌላ አዕምሮ ሲዛወሩ የተሻለ ያድጋሉ፡፡
ኦሊቨር ዌንዴል ሆልሜስ
ሃሳብ ሳይለወጥ ከአንድ ቋንቋ ወደ ሌላ  አይተላለፍም፡፡
ሚጉልዲ ኡናሙኖ ይጁጉ
ሃሳቦች አሻፈረን ሲሉ ሰዎች ቃላትን ይፈጥራሉ፡፡
ማርቲን ኤች ፊሸር
ሁሉም ነገር ተብሏል፡፡ ግን ሁሉም ሰው አላለውም፡፡
ስታኒስሎው ሌስ

Monday, 16 March 2015 09:40

የውሃ ህክምና ፈውስ

የውሃ ህክምና (ሃይድሮቴራፒ) ጥንታውያን ግሪኮች፣ ግብፆችና ሮማውያን ከበሽታ ለመፈወስ  ሲጠቀሙበት የኖሩት ህክምና ሲሆን በቀላሉ ሊገኝ የሚችልም ነው፡፡ ውሃ በፈሳሽ፣ በበበረዶና በጋዝ መልኩ የተለያዩ ጠቀሜታዎችን ይሰጣል፡፡ ቀዝቃዛ፣ ሙቅና ፍል ውሃም አገልግሎቱ ለየቅል ነው፡፡
ውሃን በመጠጣት የሚገኝ ፈውስ
 ንፁህ ውሃን በመጠጣት ለህመም ፈውስ ማግኘት ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሲተገበር የቆየ ህክምና ነው። ውሃን መጠጣት የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅምን                                                                                ያዳብራል፡፡ ውሃን በመጠጣት የኩላሊት፣ የጨጓራ፣ የፊኛ፣ የመገጣጠሚያ አካላት፣ አንጀትና ጣፊያ በሽታዎችን፣ ኪንታሮት፣ የሳንባ ምች፣ የተለያዩ ተላላፊ በሽታዎችን፣ የጡንቻና አጥንት ጤና ችግሮችን ማስወገድ ይቻላል፡፡
ሁልጊዜ ጠዋት ቁርስ ከመመገባችን በፊት ከአምስት ብርጭቆ ያላነሰ ውሃ ብንጠጣ ለተለያዩ ውስጣዊ የጤና ችግሮቻችን መፍትሄ እናገኛለን፡፡ ውሃ በተፈጥሮው የአሲድነት ፀባይ የሌለው በመሆኑ ለሰውነታችን ውስጣዊ ኡደት መቀላጠፍ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው። በአግባቡ ሳይሰለቀጡ ወደ አንጀታችን የሚገቡ ምግቦች በቀላሉ እንዲብላሉና በጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ረገድ ውሃ የሚሰጠው ጠቀሜታ ከፍተኛ ነው፡፡
ውሃን በመነከር የሚገኝ ፈውስ
በጣም የቀዘቀዘ ውሃ ማይግሪን ለተባለው ራስ ምታት ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ህመሙ በሚነሳበት ወቅት በጣም የቀዘቀዘ ውሃን ለአምስት ደቂቃዎች ያህል አናት ላይ በመያዝ ህመሙን ማስታገስ ይቻላል፡፡
ቀዝቃዛ ውሃ ለአለርጂ፣ ለጡንቻ መዛል፣ ለአዕምሮ መረበሽ (ለድብርት)፣ ለውጥረት፣ ለትኩሳትና ለሌሎችም በሽታዎች ፍቱን መድኀኒት ነው፡፡ ውሃ በሞቃትና በፍል መልኩ ጥቅም ላይ ሲውል ደግሞ ለመገጣጠሚያ ችግሮች፣ ለጉንፋን፣ ለብርድ፣ ለኢንፍሉዌንዛ ፍቱን መድኀኒት ነው። የሙቀት መጠኑ 750c የሆነ ውሃ ህመም በሚሰማን ቦታ ላይ ማፍሰስ (መነከር) ከህመም እፎይታን ሊያስገኝ ይችላል፡፡
ውሃን በበረዶ መልክ መጠቀም  
በመገጣጠሚያ አካላት ላይ በአደጋ (መውደቅ፣ መጋጨት) ለሚደርስ ጉዳትና በዚህ ሳቢያ በሰውነታችን ላይ ለሚከሰት እብጠት፣ የጡንቻ መሸማቀቅ ወይም ውልቃት በረዶ ፈጣን ፈውስን ያስገኛል፡፡ በረዶ በተጎዳው ሰውነታችን ላይ ሲደረግ ከህመም እፎይታን ከማግኘታችንም በሻገር እብጠቱን ለመቀነስ ያስችላል፡፡
ውሃን በመታጠን መፈወስ
ውሃን አፍልቶ መታጠን (በጋዝ መልኩ) ለጉንፋን፣ ለሳል፣ ለኢንፍሉዌንዛና ለጉሮሮ ህመሞች ፈጣን ፈውስ ይሰጣል፡፡  
የውሃ ህክምና ጥንቃቄዎች
በውሃ ህክምና በመታገዝ ፈውስ ለማግኘት በምንሞክር ወቅት ያሉብንን የጤና ችግሮች በሚያባብስ መልኩ እንዳይሆንብን ልንጠነቀቅ ይገባል፡፡ ቁስለት ባለባቸው የሰውነት አካላት ላይ ሙቅም ሆነ ቀዝቃዛ ውሃ መጠቀም የለብንም፡፡
እርጉዝ ሴቶች በውሃ ህክምና ከመጠቀማቸው በፊት ከሃኪማቸው ጋር መማከር ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ ህክምናውን በብልት (በማህፀን አካባቢ) ላሉ ችግሮች መጠቀም የሚፈልጉ እርጉዝ ሴቶች ህክምናውን ከመጀመራቸው በፊት ሃኪማቸውን ማማከር ይገባቸዋል፡፡

Monday, 16 March 2015 09:42

ካፌይን እና መዘዞቹ

ካፌይን አዕምሮን ለማነቃቃት የሚረዳና በተለይ በቡና፣ በሻይና በተለያዩ የለስላሣ መጠጦች ውስጥ በስፋት የሚገኝ ኬሚካል ነው፡፡ ካፌይን ከእነዚህ መጠጦች በተጨማሪ በቸኮሌቶች፣ በብስኩቶችና በተለያዩ የህመም ማስታገሻና የራስ ምታት መድሃኒቶች ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህ ኬሚካል ሱስ የማስያዝ ባህርይው ከፍተኛ ነው፡፡ የተጠቀሱት መጠጦችና ምግቦች እንዲሁም መድሃኒቶች ካፌይን የመያዝ አቅማቸው እንደየሁኔታው የተለያየ ሲሆን በቡና ውስጥ የሚገኘው የካፌይን መጠን ከፍ ያለ ነው፡፡ አንድ ስኒ ቡና ከ100-150 ሚሊ ግራም ካፌይን በውስጡ ይይዛል፡፡ አንድ ሰው በቀን በአማካይ 80 ሚሊ ግራም ካፌይን ይወስዳል ተብሎ ይገመታል፡፡ ከመጠን ያለፈ ካፌይንን መጠቀም ለከፋ የጤና ችግር ይዳርጋል፡፡ በካፌይን ሳቢያ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)፣ ሱሰኝነት፣ የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት ይጠቀሳሉ፡፡  
የካፌይን ስካር (ኢንቶክሲኬሽን)
ከ250 ሚሊ ግራም በላይ የሆነ ካፌይን ከተወሰደ የካፌይን ስካር ይጀምራል፡፡ የዚህ ችግር ምልክቶች ጭንቀት፣ መቅበጥበጥ፣ የህሊና መረበሽ፣ ማቅለሽለሽ፣ ማላብ፣ የሽንት መብዛት፣ እንቅልፍ ማጣት፣ እጅና እግርን የመውረር ስሜት መኖርና መነጫነጭ ናቸው፡፡ የካፌይን መጠኑ እየጨመረ ከሄደ እና 1000 ሚሊ ግራም ከደረሰ የአፍ መኮላተፍ፣ የሃሳብ መደነጋገርና የልብ ትርታ መዛባት ሊከተል ይችላል፡፡ መጠኑ ከዚህ እየጨመረ ከሄደም ድንገተኛ የልብ ምት መቆም (ሞትን) ሊያስከትል ይችላል፡፡
የካፌይን ሱሰኝነት
ራስ ምታት፣ ድብርት፣ ጭንቀት፣ ድካም፣ ማቅለሽለሽና ማስመለስ፣ እንቅልፍ እንቅልፍ የማለት ስሜት--- በካፌይን ሱሰኝነት ምክንያት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች ናቸው፡፡
ይህ ችግር ካፌይኑ ከቀረ ከ10-12 ሰዓታት ውስጥ የሚጀምር ሲሆን ከጥቂት ቀናት ተደጋጋሚ ስሜት በኋላ ሊጠፋ የሚችል ነው፡፡
የእንቅልፍ ማጣትና ጭንቀት
መረበሽ፣ መነጫነጭ፣ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ አለመቀመጥ፣ መርበትበትና መጨነቅ በካፌይን ሰበብ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ካፌይን ለእንቅልፍ ማጣት ሰበብ ከመሆኑም በተጨማሪ  ለድብርት፣ ለጭንቀትና ለውጥረት ዋንኛ ምክንያትም ነው፡፡
የመፍትሔ እርምጃዎች
የሚወሰደውን የካፌይን መጠን በአንድ ጊዜ ለመቀነስ መሞከር አይመከርም፡፡ ይልቁንም ዕለት በዕለት ቀስ እያሉ የሚወስዱትን የካፌይን መጠን በመቀነስ በሂደትም ማቆም በካፌይን ሰበብ ከሚደርሱ የጤና ችግሮች ሊታደገን ይችላል። ካፌይን የሌለባቸውን ምግቦችና መጠጦች ለይቶ በማወቅ እነሱ ላይ ትኩረት በማድረግ መጠቀም፣ ራስን በሌሎች ነገሮች ለማዝናናት መሞከርና ውሃን አብዝቶ መጠጣት በካፌይን ሳቢያ የሚከሰቱትን የጤና ችግሮች ለማስወገድ ይረዳል፡፡

ኢህአፓም “አሲምባ”ን ማስጎብኘት ይችላል----

  ልጅ ያሬድ የተባለው ታዋቂ ኮሜዲያን ሰሞኑን በዋሽንግተን ሆቴል (የአዲስ አበባው ነው!) ባቀረበው የኮሜዲ ምሽት ላይ የታደመችው የሥራ ባልደረባዬ ሰምታ ካጣጣመቻቸው ቀልዶች ውስጥ  ጥቂቶቹን ስለነገረችኝ እኔም ለናንተ ላጋራችሁ፡፡ (“sharing is caring” አሉ!)
ወደ ልጅ ያሬድ ቀልድ፡- አንድ የሆነ ሰፈር ነው አለ፡፡  ሌላው ጋ 3 ብር የሚሸጠውን አንድ እንጀራ 4 ብር ነው የሚሸጡት ---- ለምንድን ነው እዚህ ሰፈር  4 ብር የሚሸጠው ሲል ይጠይቃቸዋል፡፡ ምን ቢሉት ጥሩ ነው --- እኛ ሰፈር ውሃ ስለሌለች ሊጡን በሃይላንድ ውሃ ነው የምናቦካው፡፡ (የጨረሰች  ቀልድ!)  
ባለፈው ሳምንት ትዝ ይላችሁ እንደሆነ ስለ ህወሃት 40ኛ ዓመት በዓል ሳወጋችሁ አንዳንድ ተቃዋሚዎች፤ ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳነት እየተጠቀመበት ነው የሚል ክስ መሰንዘራቸውን ጠቅሼ ነበር (ነገርዬው ባይሆን ለወቀሳ እንጂ ለክስ እንኳን አይበቃም!) የሆኖ ሆኖ ---- ተቃዋሚዎች ለምን እንዲህ ያለ ወቀሳ ሰነዘሩ ብዬ ሳሰላስል ሁለት መላ ምቶች ብልጭ አሉልኝ፡፡ አንደኛው፤ ህወሃት ለምን ለበዓሉ አልጠራንም የሚል የአበሻ ቅያሜ ቢጤ ይመስለኛል፡፡ ለነገሩ አይፈረድባቸውም፡፡ ለምን መሰላችሁ ----- ሱዳኖችንና የቻይና ኮሙኒስት ፓርቲን በሰበብ አስባቡ እየጋበዙ ለአገር ቤት ተቃዋሚ ጀርባ መስጠት ያናድዳላ፡፡ (ቀላል ያጨሳል!)  
በነገራችሁ ላይ በእንዲህ ያሉ መልካም አጋጣሚዎች (የህወሃት 40ኛ ዓመትን ማለቴ ነው!) ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የዘለቀውን የፖለቲካ ኩርፍያ (የኩርፍያ ፖለቲካም ያስኬዳል!) ለመስበር መትጋት እኮ ብልህነት ነው፡፡ (አረ ብልጥነትም ጭምር!) ፖለቲከኞቻችን ሌላው ቢቀር … ለአዲሱ  ትውልድ የሚያስረክቡትን አገር ማሰብ አለባቸው፡፡ (ኩርፍያ የሞላት አገር ማን ይረከባል!)
እናላችሁ----በተለይ የመንግስትን ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ ተነሳሽነቱን መውሰድ አለበት ባይ ነኝ፡፡    (ከተቃዋሚም ቢገኝ አንጠላም!) አያችሁ ቢገባን እኮ---ለሰላምና ለፍቅር መሸነፍ ከማሸነፍ እኩል ነው፡፡ (ኧረ ኩርፊያው ይሰበር!) አሁንስ እኔ ለእነሱ ደከመኝ… (ስፖንሰር ከተገኘ “ኩርፊያው ይሰበር” የሚል የ6 ወር አገራዊ ንቅናቄ ለመጀመር አስቤያለሁ!)
ሁለተኛውን መላ ምት እንኳ ሳምንትም ጠቀስ አድርጌዋለሁ (የአርቲስቶች ደደቢትን መጎብኘት ማለቴ ነው!) ዛሬ ግን ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሄውንም ይዤአለሁ፡፡ ባለፈው ጠቀስ እንዳደረግሁላችሁ ተቃዋሚዎች በዚህ ነገር ደስ የተሰኙ አይመስሉም፡፡ ለዚህ ነው ኢህአዴግ በዓሉን ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀመበት የሚል ወቀሳ የመጣው፡፡ (ሁሉ ነገር በአስተማማኝ ግምት ላይ የተመሰረተ ነው!)
ለነገሩ እስቲ ራሳችሁን በተቃዋሚዎች ቦታ አድርጋችሁ አስቡት፡፡ (ለአፍታ የእነሱን ጭንቅላት ልዋስ!) እናላችሁ--ለምሳሌ አርቲስቶችን ደደቢት ድረስ ወስዶ ማስጎብኘት ለምን አስፈለገ? (ያውም በምርጫው 11ኛ ሰዓት ላይ!) ግን እኮ ጥያቄው መቅረብ የነበረበት ለራሱ ለህወሃት ነው! የጉብኝቱ ዓላማ እንደተባለው ታሪክን ለትውልድ ማስተላለፍ ነው? (እንዴት አሁን ትዝ አላቸው?) ወይስ በምስኪንነት ሆድ አባብቶ አሊያም በጀግንነት ቀልብ ማርኮ የአርቲስቶችን ድምፅ ለመግዛት ነው? እኒህ ሁሉ ጥያቄዎችና መላምቶች  የእኔ አይደሉም … እኔ ለእነሱ የመታሁት መላ እንጂ!! (ራሴን በተቃዋሚዎች ጫማ ውስጥ አስገብቼ ማለት ነው!)
እናም ማንም ተቃዋሚ የሆነ (ያውም ደግሞ ያኮረፈ!) ከላይ ከቀረቡት ውስጥ ልቡ ወደ ሁለተኛው ጥያቄና መላ ምት እንደሚያደላ ሳይታለም የተፈታ ነው!! እናም ለዚህ ይሆናል የህወሃትን 40ኛ ዓመት  ለምርጫ ቅስቀሳ ተጠቀሙበት የሚለው ክስ (ይቅርታ ወቀሳ!) የመጣው፡፡ አሁን ወደ መፍትሄው እንግባ፡፡ የእኔ ሃሳብ ምን መሰላችሁ? ተቃዋሚዎችም ልክ እንደ ህወሃት የየራሳቸውን “ደደቢት” ለአርቲስቶች እንዲያስጎበኙ ዕድል መስጠት! (ከከተማ ሳይወጡ ደደቢት!) ግን ምን መሰላችሁ? ምንም እንኳን ተቃዋሚዎች እንደ ህወሃት በረሃ ገብተው ባይዋጉም አልታገሉም ማለት ግን አይደለም፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ዕውቅና ማግኘት፣ ህዝባዊ ስብሰባ ለማካሄድ አዳራሽ ወይም ሆቴል መከራየት፣ በየክልሉ ካሉ ትናንሽ የወረዳ ንጉሶች ጋር መወዛገብ፣ ሰላማዊ ፈቃዱ ህገወጥ ነው ከሚል የጸጥታ ኃይል ጋር መጋፈጥ (ዱላና ድብደባን ያካትታል!) ------ እኒህ ሁሉ የትግሉ አካል ናቸው፡፡
 ሌሎችም የትግል ቦታዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ---ተቃዋሚዎች ፓርቲያቸውን ለመመስረት ሃሳብ የጠነሰሱበት ሥፍራ፣ በኢህአዴግ ካድሬ ተዋከብን የሚሉበት ቦታ፣በየጊዜው እነሱ ወይም ጓዶቻቸው የታሰሩበት፣(ቃሊቲ፣ዝዋይ፣ማዕከላዊ--ወዘተ) እነዚህ ሁሉ የእነሱ የትግል ቦታዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጋሩት አንድ የድል ቦታም አላቸው -የህዝብ ማዕበልን የሚያስታውሳቸው፡፡ መስቀል አደባባይ!! (የ97 ምርጫን ልብ ይሏል!) አያችሁ----ተቃዋሚዎችም ለአርቲስቶች ሊያስጎበኙት የሚችሉት ከበቂ በላይ የትግል ቦታና ታሪክ  አሏቸው፡፡ (የየራሳቸው ደደቢት እንደማለት!) በነገራችሁ ላይ የትጥቅ ትግሉን ያሸነፈው ኢህአፓ ቢሆን ኖሮ---- አርቲስቶቹ የሚጎበኙት ደደቢትን ሳይሆን አሲምባን ይሆን ነበር፡፡
 እናላችሁ … ተቃዋሚዎች አርቲስቶችን ሰብስበው የየራሳቸውን “ደደቢት” ቢያስጎበኙ ኩርፊያውን ለማርገብ የሚያግዝ ይመስለኛል፡፡ (አርቲስቶች የህዝብ ሃብት ናቸው ብዬ እኮ ነው!) በነገራችሁ … ላይ የህዝብ ሃብት ያልሆነ ነገር እኮ ፈልጋችሁ አታገኙም! ለምሳሌ መሬት የህዝብ ሃብት ነው (ይቅርታ እና የመንግስት!)፣ ቲቪና ሬዲዮ ጣቢያም የህዝብ ሃብት ነው፡፡ የኢህአዴግ ኢዶውመንቶች ራሳቸው - የህዝብ ሃብት ናቸው፡፡ የሥልጣን ባለቤት ማነው? ህዝብ ነው!! የመንግስት ሹማምንት የማን አገልጋይ ናቸው? የህዝብ!! ግን እኮ አርቲስቶች ሃብታቸውን ሲጠየቁ----ሃብታችን ህዝብ ነው ይላሉ፡፡ (ከምራቸው እንዳይሆን!)

አቶ ደስታ አስፋው
(በኢህአዴግ ፅ/ቤት የህዝብና ውጭ
ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ)
         አዲስ አድማስ ጋዜጣ በቆየባቸው 15 ዓመታት ውስጥ ጠንካራም ደካማም ጎኖች እንዳሉት ታዝቤያለሁ፡፡ ከጠንካራ ጎኖቹ መካከል የተለያዩ ጉዳዮችን በተከታታይ በመረጃ መልክ ለህዝብ ማድረሱ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ አልፎ አልፎ የሚዛናዊነት ችግሮች ይታዩበታል፡፡ አዲስ አድማስ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አይቶ፣ ጥንካሬዎቹን አጠንክሮ ጉድለቶቹን አርሞ ከቀጠለ፣ለሃገራችን የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ በግሌ ቢያንስ በመሰረታዊ የሙያው መርሆች ይሰራሉ ከምላቸው ጋዜጦች ውስጥ አስገባዋለሁ፡፡ አዲስ አድማስ የሚዲያ ሥራ በባህሪው የሚያጋጥመውን ተግዳሮት ተወጥቶ በየጊዜው ራሱን እያሳደገ፣ እዚህ መድረሱ ጥሩ ነው፤ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ ትልቁ ነገር ግን፣ ለህዝቡ መረጃ ለማድረስ በሚደረገው ጥረት የጋዜጠኝነትን መርህ መለኪያ ማድረግ ነው፡፡ የተሰሩ ጥሩ ነገሮችንም መዘገብ አለባችሁ፡፡ ለወደፊትም ጋዜጣው ደካማ ጎኑን አርሞ ጠንካራ ጎኑን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡ እንኳን ለ15ኛ አመታችሁ አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ፡፡