Administrator

Administrator

የጋዜጠኛና ገጣሚ ተስፋዬ ገብረማርያም “የማይሆን ዓለም” የተሰኘ ግጥሞች፣ አጫጭር ልቦለዶች እና ወግ የተካተቱበት መጽሐፍ ነገ በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ እንደሚመረቅ “ሀሳብ መልቲሚዲያ” አስታወቀ፡፡ በ62 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፣ በ20 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ጋዜጠኛና ገጣሚ ተስፋዬ በ“ኢትዮ ቻናል” ጋዜጣ ማህበራዊ ጉዳዮች አምድ ጸሐፊነቱና በዛሚ 90.7 ኤፍ ኤም ሬዲዮ በሚያቀርበው “ድርሻችን” የተሰኘ በአካል ጉዳተኞች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ይታወቃል፡፡

“ዜማ ቃል” የተሰኘ ወርሃዊ የጥበብ ምሽት ሐሙስ ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ  በሐገር ፍቅር ትያትር ቤት ትንሿ አዳራሽ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ ለአንድ ዓመት በሚዘልቀው ዝግጅት፣ የገጣሚያን፣ ጸሐፍትና ኮሜዲያን  ሥራዎች የሚቀርብበት ሲሆን የመግቢያ ዋጋው በነፍስ ወከፍ 50 ብር እንደሆነ ዝግጅቱን የሚያስተባብረው ፈለቀ ካሳ ጥንድ ፕሮሞሽን  ጠቁሟል፡፡ 

በዶ/ር ሱዛን ጄፈርስ የተፃፈው “Feel the Fear and Do it Anyway” የተሰኘ መፅሃፍ፤“ፍርሃትን ማሸነፍ” በሚል ርእስ በቢኒያም አለማየሁ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ አሉታዊ አመለካከትን ስለማስወገድ፣ ውሳኔዎችን በሥራ ስለ መተግበር፣ ፍርሃትን ስለ ማጥፋት እና ሌሎች ተያያዥ ቁም ነገሮችን የያዘ ነው፡፡ 192 ገፆች ያሉት መፅሃፉ፤ ዋጋው 40.50 ብር ነው፡፡
በሌላም በኩል “በአራጣ የተያዘ ጭን” የተሰኘ የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በዮፍታሔ ካሳ የተደረሰው መጽሐፍ፤ በ233 ገፆቹ አስራ ዘጠኝ አጫጭር ልቦለዶች ይዟል፡፡ በኤች ዋይ ኢንተርናሽናል ማተሚያ ቤት የታተመውን መጽሐፍ፤ ሊትማን ጀነራል ትሬዲንግ የሚያከፋፍለው ሲሆን ዋጋውም 46.99 ብር ነው፡፡
በተመሳሳይ “ከመለስ ሞት በስተጀርባ” የተሰኘ መጽሐፍ በዚህ ሳምንት ለንባብ በቃ፡፡ መፅሃፉ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ፣ በአባይ ግድብ፣ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙርያ ያጠነጥናል፡፡ በ70 ገጾች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ ለገበያ የቀረበው በ32 ብር ነው፡፡ በመፅሃፉ ውስጥ ከተካተቱት ፎቶግራፎች መካከልም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት የሃምሳ ብር ኖት ላይ የወጣው የአባይ ግድብን የሚያሳይ ምስል ይገኝበታል፡፡

ከሁለት ወር በፊት ራሷን ከጡት ካንሰር ለመታደግ ሁለት ጡቶቿን በቀዶ ጥገና ያስወገደችው አንጀሊና ጆሊ፤ለመላው ዓለም ስለ ጡት ካንሰር አስከፊነት ባስጨበጠችው ግንዛቤ ከፍተኛ አድናቆትን እንዳተረፈች ተገለፀ፡፡ ዝነኛዋ የሆሊውድ አርቲስት ህክምናውን ለማግኘት የወሰደችው ፈጣን እርምጃና ለመላው ዓለም ግልፅ መረጃ በማቀበል ባሳየችው ድፍረት የተመላበት ተግባር በህክምና ባለሙያዎች ዘንድ ተወድሶላታል። “ተግባሯ በሙያችን መነቃቃትና ግንዛቤ እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል” ብለዋል - ባለሙያዎቹ፡፡ የስድስት ልጆች እናት የሆነችው የ37 ዓመቷ አንጀሊና ጆሊ፤ሁለት ጡቶቿን የሚያስወግድ ቀዶ ህክምና ባታደርግ ኖሮ 87 በመቶ ለጡት ካንሰር፣ 50 በመቶ ለማህፀን ካንሰር ትጋለጥ እንደነበር ታውቋል፡፡ አንጀሊና በኒውዮርክ ታይምስ ላይ ባሰፈረችው ፅሁፍ፤ ህክምናውን ለመውሰድ የወሰደችው እናቷ በ56 ዓመታቸው በተመሳሳይ ችግር ለሞት በመዳረጋቸው እንደሆነ ገልፃለች። በመላው ዓለም በየዓመቱ ከ45ሺ በላይ ሴቶች በጡት ካንሰር እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

“ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” በተሰኘው የኔልሰን ማንዴላ ግለታሪክ መፅሃፍ ላይ ተመስርቶ የተሰራው አዲስ ፊልም ከወር በኋላ በመላው ዓለም መታየት እንደሚጀምር ተገለፀ፡፡ ፊልሙ የደቡብ አፍሪካውያንን የነፃነት ትግል ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ ታልሞ የተሰራ ነው ተብሏል፡፡
በጉበት ኢንፌክሽን በጠና ታመው በሆስፒታል ህክምና ሲደረግላቸው የቆዩት ኔልሰን ማንዴላ፤ ከሳምንት በፊት 95ኛ ዓመት የልደት በዓላቸው የተከበረላቸው ሲሆን አሁን ከህመማቸው ማገገማቸው ታውቋል፡፡
“ማንዴላ፡ ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” በሚል ርእስ በተሰራው ፊልም ላይ የማንዴላን ገፀባህርይ የሚተውነው እንግሊዛዊው ተዋናይ ኤድሪስ ኤልባ እንደሆነ ታውቋል፡፡ የ40 ዓመቱ ኤዲሪስ ኤልባ በፊልሙ ላይ ልዩ የትወና ብቃት እንደሚያሳይ ከወዲሁ የተነበየው ዘ ጋርድያን፤ ይሄም ለኦስካር ሽልማት ሊያሳጨው እንደሚችል ግምቱን አስፍሯል። “ማንዴላ፡ ኤ ሎንግ ዎክ ቱ ፍሪደም” የተሰኘው ፊልም በነፃነት ታጋዩ የልጅነት፤ የአስተዳደግና የትምህርት ሁኔታ እንዲሁም የ27 ዓመታት የእስር ቆይታ እና ደቡብ አፍሪካን በፕሬዝዳንትነት እስከመሩበት ጊዜ ድረስ ያለውን ሂደት የሚተርክ መሆኑን “ዘ ስዌታን” ጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 ዓ.ም በማንዴላ ተፅፎ ለንባብ የበቃው ግለ ታሪክ መፅሃፍ በመላው ዓለም ከ15 ሚሊዮን በላይ ቅጂዎች እንደተሸጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አጓጊው ዜና ምንድነው?
ዋርነር ብሮስ የተባለው የፊልም ኩባንያ እና ዲሲ ኮሚክስ እ.ኤ.አ በ2015 ባትማንና ሱፐርማንን በማጣመር ልዩ ፊልም እንሰራለን ማለታቸው ነው፡፡ ፊልሙ በሚቀጥለው ዓመት ቀረፃው የሚጀምር ሲሆን እውቆቹ የ“ሱፐርማን ሪተርንስ” ዳሬክተር ዛክ ስናይደር እና የ“ባትማን” ፊልም አካል የሆነው “ዘ ዳርክ ናይትስ” ዳሬክተር ክሪስቶፈር ኖላን በጥምረት ይሰሩበታል ተብሏል፡፡
ፊልሙን ለመሥራት እንዴት ታሰበ ?
የልዕለ ጀግና ጀብደኛ ገፀባህርያትን በመፅሃፍ እና በፊልም በመስራት ስኬታማ የሆነው ዲሲ ኮሚክስ፤ ባትማንና ሱፐርማንን በአንድነት በማጣመር ለመስራት የወሰነው አምና ማርቭል ኮሚክስ፤ የልዕለ ጀብደኛ ገፀባህርያትን ያሰባሰበውን “ዘ አቬንጀርስ” ለእይታ በማብቃት በመላው ዓለም 1.5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መሰብሰቡን በማየት ነው፡፡
እነማን ይተውኑበታል?
ዘንድሮ ለእይታ በበቃው በ“ሱፐርማን ሪተርንስ” ፊልም ላይ በመስራት ባሳየው ብቃቱ የተደነቀው ሄነሪ ካቪል ሱፐርማንን ሲተውን ፤ ባትማንን ለመተወን ደግሞ በ“ዘ ዳርክ ናይትስ” ላይ የተወነው ክርስቲያን ቤል ታጭቷል - ማረጋገጫ ባይገኝም፡፡


ባትማንና ሱፐርማን በንፅፅር
*በካርቱን መፃህፍት ላይ ተመስርተው በመሰራት ትርፋማ ከሆኑት የሱፐርሂሮ ጀብደኛ ገፀባህርያት ባትማንና ሱፐርማን ግንባር ቀደም ናቸው፡፡
የባትማን ገፀባህርይ በመፅሃፍ፤ በፊልም፤ በዲቪዲ ሽያጭ እና ሌሎች ንግዶች በመላው ዓለም 12 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ሲያስገኝ የሱፐር ማን ገፀባህርይ ደግሞ በተመሳሳይ ዘርፍ 5 ቢሊዮን ዶላር አስገኝቷል፡፡
ዘንድሮ ለእይታ የበቃው እና በዳሬክተር ዛክ ስናይደር የተሰራው “ማን ኦፍ ስቲል ሱፕርማን ሪተርንስ” 700 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቶበታል፡፡
ባትማን ሰብዓዊ ፍጡር ያለው ገፀባህርይ ሲሆን ሱፐርማን ግን ከሰብዓዊ ፍጡር የላቀ ተሰጥኦ ያለው ልዩ ፍጥረት ነው፡፡
ባትማን ልዩ ሃይልና ተሰጥኦ ባይኖረውም በሳይንስና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም እና ጠቅላላ እውቀት የተገነባ የላቀ አዕምሮ ያለው ጀብደኛ የልዕለ ጀግና ገፀባህርይ ነው፡፡ ባትማን በምርመራ ችሎታው እና በሃብታምነቱም ይለያል፡፡ ሱፐር ማን ደግሞ መብረር የሚችል፤ከፍተኛ ጥንካሬ ያለውና በላቀ ተሰጥኦው የተለያዩ ጀብዶችን የሚያከናውን እንዲሁም ሰብዓዊ ፍጡር ሊያደርጋቸው የማይችላቸውን ተግባራት በቀላሉ የሚሰራ ገፀባህርይ ነው፡፡

  • ሚሊዮኖች በንፁህ ውሃ እጦት ሳቢያ ለህልፈት ይዳረጋሉ 
  • የተበከለ ውሃ - ለታይፎይድ፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ቁስለትና የጉበት ብግነት ያጋልጣል

ሰለሞን ፍቃዱ፤ በተደጋጋሚ እየተመላለሰ የሚያሰቃየው የሆድ ቁርጠት በሽታ፣ ቋሚ መፍትሔ ለማግኘት አለመቻሉ አሳስቦታል፡፡ በሽታው በተነሳበት ቁጥር የሚመላለስባቸው ክሊኒኮች ቁና ሙሉ መድሃኒት እያሸከሙት መመለሱን ለምዶታል፡፡ ታይፎይድ፣ ታይፈስ፣ የአንጀት ቁስለት፣ ጃርዲያና ባክቴሪያ ለበሽታው ከሚሰጡት ስሞች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የእነዚህ በሽታዎች መነሻ ምክንያቱ ደግሞ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሃና የተበከለ ምግብ እንደሆነ ሐኪሞቹ ደጋግመው ነግረውታል፡፡ በዚህ ምክንያትም በየሆቴሉና በየሬስቶራንቱ መመገቡን እርግፍ አድርጐ ከተወው ሰነባብቷል፡፡
ሆኖም በየጊዜው እያገረሸ አቅል የሚያሳጣው ህመሙ አልተወውም፡፡ ግራ ቢገባው ስለሚጠጣው ውሃ ማሰብ ያዘ፡፡ ከቧንቧ እየቀዳ የሚጠጣው ውሃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተለየ ጣዕምና ሽታ ማምጣቱን ሲያስታውስ፣ ችግሩ ምናልባትም ከውሃው ሊሆን ይችላል ሲል አሰበ፡፡ ግን ደግሞ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የተጣራና ንጽህናው የተረጋገጠ እንደሆነ ሲነገር በተደጋጋሚ ሰምቷል፡፡ ታዲያ ውሃው እንዴት ሆኖ እሱ ለገጠመው ችግር መነሻ ይሆናል? ማሰብ ጀመረ፡፡ የአራትና የአምስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቹም የተሟላ ጤና ካጡ ሰነባብተዋል፡፡ የህፃናቱ ችግር ንጽህናውን ያልጠበቀ ምግብና ውሃ ሊሆን እንደሚችል ሃኪማቸው ሲናገር ሰምቷል፡፡ ጥርጣሬው ከፍ ሲል ውሃውን በብርጭቆ እየቀዳ ማስተዋል ጀመረ፡፡ በብርጭቆ ውስጥ እየዘቀጡ የሚቀሩት ቆሻሻዎች ጥርጣሬውን አባባሱት፡፡ ስለጉዳዩ ለሃኪሙ መንገር እንዳለበት ወሰነና ነገረው፡፡ ሃኪሙም ውሃ በቧንቧ ስለመጣ ብቻ ንፁህ ነው ብሎ መጠቀሙ አደጋ እንዳለውና የቧንቧ ውሃም በተለያዩ ምክንያቶች ሊበከልና ለጤና እጅግ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስረዳው፡፡
ይህንን ችግር ለማስወገድም የመጠጥ ውሃን በሚገባ አፍልቶና አቀዝቅዞ መጠቀም እንደሚገባ፣ አለበለዚያም በተለያዩ የማከሚያ መድሃኒቶች በማከም መጠቀም ተገቢ እንደሆነ አብራራለት፡፡ በየጊዜው እየተከሰተ ለሚያሰቃየው የጤና ችግር መነሻው፣ የሚጠጣው ውሃ መሆኑን ማወቁ እፎይታ ቢሰጠውም የችግሩ ቋሚ መፍትሔ አለመገኘት አሳስቦታል፡፡ ለማን አቤት ይባላል? በከተማዋ እንዲህ አይነት ችግር ሲከሰት የሚቆጣጠረውና መፍትሔ የሚሰጠው አካል ማነው? ሰለሞን ይጠይቃል፡፡
ችግሩ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለከተማ፣ አለም ባንክ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነዋሪ የሆነው የሰለሞን ፍቃዱ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ያሉ በርካታ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ደንበኞች የሚያነሱት ችግር ነው፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በአብዛኛው የሚጠቀሙበትን ውሃ የሚያገኙት ከቧንቧ ነው፡፡ የከተማው ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን 368ሺ ቆጣሪ ያላቸው ደንበኞች ያሉት ሲሆን ከገፈርሳ፣ ለገዳዲና ድሬ ግድቦችና የማጣሪያ ሥፍራዎች እንዲሁም 110 ከሚደርሱ ጉድጓዶች በቀን 374ሺ ሜትር ኪዩብ ውሃ እያመረተ ለነዋሪው እንዲሰራጭ ያደርጋል፡፡ ውሃው ለህብረተሰቡ ከመድረሱ በፊት በተለያዩ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ መንገዶች ተጣርቶና በአስተማማኝ ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዲሁም በርካታ የማጣራት ሂደቶችን አልፎ እንደሚሰራጭ ቢነገርም አንዳንድ ጊዜ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የደፈረሰና ለጤና አደገኛ የሆነ ውሃ እንደሆነ ይነገራል፡፡ ውሃውን ሳያፈሉ መጠቀም ለበርካታ የጤና ችግሮች እንደዳረጋቸው መሆኑንም የከተማ ነዋሪዎች ይገልፃሉ፡፡ በቧንቧ የሚመጣው ውሃ የተጣራና ለጤና ጎጂ የሆኑ ባክቴሪያዎች እንዳይኖሩበት በቂ ማጣራትና ህክምና እንደሚደረግለት የሚናገሩ የባለስልጣን መ/ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች፣ አንዳንድ ጊዜ የውሃ ቧንቧዎች ሲሰበሩና ጉዳት ሲደርስባቸው የቆሸሸና የደፈረሰ ውሃ በቧንቧ ሊመጣ እንደሚችል ይገልፃሉ፡፡
በተለይ አሁን ከመንገድ ሥራ ግንባታው ጋር በተያያዘ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የውሃ ቧንቧዎች በመሰበራቸው ምክንያት በውሃው ንጽህና ላይ ችግር እያስከተሉ መምጣታቸውንም እነዚሁ ኃላፊዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ ችግር በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በግልጽ ተነግሮ፣ ሕብረተሰቡ ለመጠጥነት የሚጠቀመውን ውሃ በማፍላትና በማቀዝቀዝ ወይንም በተለያዩ የማከሚያ መድሃኒቶች አክሞ እንዲጠቀም ማድረጉ ተገቢ መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት ዶ/ር ታደሰ ተስፋዓለም ስለዚሁ ጉዳይ ሲናገሩ፣ የተበከለ ውሃ ለታይፎይድ፣ ኮሌራ፣ የአንጀት ቁስለትና የጉበት ብግነት በሽታዎች እንደሚዳርግ ጠቁመው፣ እነዚህ በሽታዎች በቀላሉና በፍጥነት ከአንዱ ሰው ወደ ሌላው ለመተላለፍ የሚችሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ ህክምና ካልተገኘም ታማሚውን ለሞት የሚያበቁ ገዳይ በሽታዎች ናቸው ብለዋል፡፡
ንጽህናው ያልተጠበቀና በሚገባ ተጣርቶ ያልታከመ ውሃን መጠቀም ለትንሹ አንጀታችን መቁሰልና ለተቅማጥ በሽታ እንደሚዳርገን የሚናገሩት የህክምና ባለሙያው፣ በንፁህ የመጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ የሚከሰተው የተቅማጥ በሽታ በህፃናት ላይ ጐልቶ የሚታይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ የተቅማጥ በሽታ በወቅቱ ህክምና ካላገኘና በተቅማጥ መልክ የሚወጣውን የሰውነታችንን ፈሳሽ ሊተካ የሚችል ንጥረ ነገር ካላገኘ፣ታማሚውን ለህልፈት የሚዳርግ በሽታ መሆኑን የሚናገሩት ዶ/ር ታደሰ፣ እንዲህ እንደአሁኑ የክረምት ወቅት በሚሆንበት ጊዜ ውሃ በተለያየ መንገድ ሊበከል ስለሚችል፣ በተቻለ መጠን በቤት ውስጥ በማጣራት፣ በማፍላትና በማቀዝቀዝ እንዲሁም የውሃ ማከሚያ መድሃኒቶችን በመጨመር መጠቀሙ አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡
በክረምት ወራት የሚከሰቱ የጤና ችግሮች በአብዛኛው ከውሃ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ ናቸው ያሉት ዶ/ር ታደሰ፣ በአገራችን በየአመቱ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ በንፁህ መጠጥ ውሃ እጦት ሳቢያ በሚከሰቱ የጤና ችግሮች ለህልፈት እንደሚዳረግም ጠቁመዋል፡፡ ለመጠጥነት የሚውለውን ውሃ በማጣራት፣ በማፍላትና፣ በማከም በዚህ ሳቢያ የሚከሰተውን የጤና ችግርና ሞት ማስቀረት እንደሚቻልም ገልፀዋል፡፡ በቀላሉ ልንከላከለውና ልናስወግደው በምንችለው ችግር ሳቢያ፣ ለህመምና ለሞት ከመዳረግ መጠንቀቁ ከሁላችንም የሚጠበቅ ተግባር ነው ሲሉ የጤና ባለሙያው ያሳስባሉ፡፡

Saturday, 27 July 2013 13:57

‘አባባ ገፋ፣ ገፋ…’

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…መቼም ጉዳችን አያልቅ! ብሎ፣ ብሎ የኬት መውለድና አለመውለድ ‘ጉዳያችን’ ሆኖ ይረፍ! እንደው አሰሳቸውንም፣ ገሰሳቸውንም ስንሰበስብ እያዩ… “እናንተ ብሎ ባለድሪምላይነር…” ቢሉን ምን ይገርማል! ለሶፍትዌር ባለሙያዎቻችን ሀሳብ አለን…ከመከረኛው ኢንተርኔት ላይ ለእኛ የሚሆነውና የማይሆነውን እየለየ ‘ፊልተር’ የሚያደርግ ሶፍትዌር ይሥሩልንማ!
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይሄኔ እኮ ጎረቤታችን ስትሰቃይ ከርማ የወለደችን ሴት አይደለም “እንኳን ማርያም ማረችሽ!” ልንላት…አለ አይደል… “አንድ ለራስ እንኳን በቀን ሁለቴ መመገብ አስቸጋሪ በሆነበት ጊዜ የምትወልደው… ሙጃ ልታበላው ነው!” ምናምን የምንል እንኖራለን። እናላችሁ… “ገንፎ ብሉ…” ባልተባልንበት… “እልል በሉ፣ ኬት ወንድ ልጅ ከእነቃጭሉ ዱብ አደረገች…” አይነት ነገር አሪፍ አይደለም፡፡
ስሙኝማ…የድሪምላይነሩን ነገር ተከትሎ ኢንተርኔት ላይ እየተሰጡ ያሉ አስተያያቶች…አለ አይደል…ዓለም አሁንም እንዴት ‘እንደሚተረጉመን’ አሪፍ ማሳያዎች ናቸው፡፡ “አንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች…” የሚሉት አዲስ አበባ ብቻ እንደሚቀር ልብ ይባልማ! በየስፖርቱም፣ በየምናምኑም “ዓለም በጉጉት የሚጠብቀው…” ምናምን የምንለው ሁሉ ‘ሳይንስ ፊክሺን’ እንደሆነ ልብ ይባልልንማ! ቂ…ቂ…ቂ… (በተለይ…ግርም የምትለኝ ነገር ምን መሰላችሁ…የሆነ እኛን የሚመለከት ነገር በሆነ የኤፍ.ኤም. ፕሮግራም ላይ ይጠቀስና ምን ይከተላል መሰላችሁ…“ዓለምን እያነጋገረ ያለ ጉዳይ…” ይባላል። ዓለምማ አይደለም ‘ራዲዮናችን’… የኢትዮዽያ ድሪምላይነር አውሮፕላን… ምናምን ሲባል ምን ይል መሰላችሁ… አንዱ ‘ፈረንጅ’ በመከረኛው ፌስቡክ ላይ እንደለጠፈው… “Dreamliner! Ethiopia! You must be kidding me!” ይላል፡፡ የእኛ ነገር እንዲሁ ነው፡፡
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ዘንድሮ የ‘መሳም’ና የ‘ማቀፍ’ ትርጉሞች እየተለዩላችሁ ነው፡፡ እናማ…በአደባባይ ‘መሳም’… ‘መታቀፍ’…ፍቅር ላይሆን ይችላል፡፡
የምር…ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ይቺን አገር የሚያሾሯት ነገሮች “አላዩንም፣ አልሰሙንም…” ተብለው የሚሠሩ ነገሮች መአት ናቸው፡፡ እናማ…በአደባባይ “ተሳምኩ” ተብሎ ከመጋረጃ ጀርባ ‘መነከስ’ አለላችሁ!
አንድ የንግድ ሽርክና ተቋቁሞ ተቃቅፈው ከተለያዩ፣ ሻምፓኝ ከተቃመሱ በኋላ… በአምስተኛ ወሩ ከአምስቱ ሸሪኮች ሦስቱ የ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የመጋረጃ ጀርባ ‘ግዝገዛ’ ይጀምራሉ። እናማ… ደበቅ ይሉላችሁና ሁለቱን ፈንግለው እንዴት ድርጅቱን እንደሚጠቀልሉ ይመክራሉ፡፡ ግን ምን መሰላችሁ…ቆይቶም ቢሆን ‘ነቄ’ መባሉ አይቀርም፡፡
እናማ ምን መሰላችሁ…ዘንድሮ ብዙ ነገራችን በአደባባይ ‘ጉንጭ ላይ’…ከመጋረጃ በስተኋላ ‘ጀርባ ላይ’ ሆኗል፡፡ የምር ቀሺም ነው…አሀ ልክ ነዋ! በኤድዋርድ ስኖውደን ዘመን “አላዩንም፣ አልሰሙንም…” ብሎ ነገር ቀሺም ነው፡፡
እናላችሁ…ሙሉ ኮሚቴው፣ ሙሉ ሥራ አስፈጻሚ…ምናምን ሳያውቃቸው በ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የሚተላለፉ ውሳኔዎች መአት ናቸው፡፡ ማለት…በ“አላዩንም፣ አልሰሙንም…” የ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ’…‘ታክቲክና ስትራቴጂዎች’ የሚተላለፉ፡፡
እኔ የምለው…የ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ’ ነገር ካነሳን አይቀር… እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ይቺን በከተማችን የሆነ ቦታ የተደረገች እውነተኛ ነገር ስሙኝማ፡፡ እናላችሁ…ባልና ሚስቱ የአራት ዓመት ልጅ አላቸው፡፡ ባል ደግሞ ሥራ ነው የሚውለው። ለካስ ሰውየው ሥራ ሲሄድ አንድ መንደር ውስጥ የሚታወቁና ራሳቸውን ‘ሪቻርጅ’ በማድረግ ተወዳዳሪ የሌላቸው ሰው ቤቱ ብቅ ይላሉ፡፡ እናማ… ልጁ “ህጻን ነው፣ አያየንም፣ አይሰማንም…” ብለው እሳቸውና እሜቲት ሚስት ‘እነሆ በረከት’ ምናምን ይባባሉላችኋል፡፡
አንድ ቀን ታዲያ “አያየንም፣ አይሰማንም…” የተባለው ልጅ እየተኮላተፈ ለአባቱ የሰውየውን ስም እየጠቀሰ “አባዬ፣ አንተ ሥራ ስትሄድ አባባ…..ቤታችን ይመጣሉ” ይላል፡፡ አባትየውም ሰውየው መጥተው ምን እንደሚሠሩ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁ ምን አለ መሰላችሁ…“ከእማዬ ጋር ገፋ…ገፋ…ገፋ….ያደርጋሉ፣” ሲል ይመልሳል፡፡ የእንቅስቃሴውንም አይነት ለአባቱ በሚችለው መልኩ ያሳያል፡፡
እናላችሁ… ወሬው መንደር ውስጥ ተዛመተና ሠፈርተኛው መካካል የሰውየው መጠሪያ ማን ሆነ መሰላችሁ…“አባባ ገፋ፣ ገፋ…” አሪፍ አይደል!
እናማ… “እነሱ አያዩም፣ አይሰሙም…” እየተባለ የሚደረገው ‘ገፋ፣ ገፋ’ ሁሉ አንዳችን ባናይ ሌላችን እንደምናይ ይታወቅልንማ!
የባልና ሚስት ነገር ካነሳን ይቺን ስሙኝማ…ባል ሆዬ ሚስቱ በሆነ ባልሆነው እየጨቀጨቀችው ለካስ ነገረ ሥራዋ ‘አፍንጫው ጫፍ’ ደርሶበታል፡፡ ታዲያላችሁ…አንድ ቀን እሷ ለቁርስ እንቁላል እየጠበሰች እያለ ማብሰያ ቤት ዘው ብሎ ይገባና ጮክ ብሎ ትዕዛዞች መስጠት ይጀምራል፡፡ “ተጠንቀቂ… ተጠንቀቂ! ትንሽ ቅቤ ጨምሪበት! ኧረ በእግዜሐር! ይሄን ያህል እንቁላል ለምን ጨመርሽ! ያንን ያህል ቅቤ ከየት እናመጣለን! ይጣበቅብሻል ነው እኮ የምልሽ! ተጠንቀቂ… ተጠንቀቂ! ተጠንቀቂ እያልኩሽ እኮ ነው! ምግብ ስታበስይ እኔን አታዳምጪኝም! ሁልጊዜም አታዳምጪኝም! እንቁላሉን ገልበጥ፣ ገልበጥ አድርጊው እንጂ! አንቺ ሴትዮ ነካ ያደርግሻል እንዴ! ያምሻል! ደግሞ ጨው አታብዢ፡፡ ሁልጊዜ ነው እንቁላል ስትጠብሺ ጨው የምትሞጅሪው! ጨው ጨምሪ! ጨው!”
ይሄን ጊዜ ሚስት ብው ትላለች፡፡ “አንተ ሰውዬ ያምሀል እንዴ! እኔ እንቁላል መጥበስ ያቅተኛል!” ብላ ትጮህበታለች፡፡
ባል ሆዬ ምን አለ መሰላችሁ…“መኪና ስነዳ አጠገቤ ሆነሽ ስትጨቀጭቂኝ የሚሰማኝን ስሜት እንድታውቂው ነው!” አለና አረፈው፡፡
እናማ…በየመሥሪያ ቤቱ እነኚህ የፈረደባቸው ‘ዓላማና’…. ‘ግብ’ ምናምን የሚሉ ነገሮች ግድግዳ ሙሉ ተጽፈው ታያላችሁ፡፡ ታዲያላችሁ…ሁሉም ላይ ደግሞ ‘ግልጽነት’ የምትለዋ ነገር አትጠፋም፡፡ ያው እኛም እያየን “ድንቄም ግልጽነት!” እንላለን፡፡ የ“አባባ ገፋ፣ ገፋ…” ዘመን ነዋ!
እዚህ አገር “አያዩንም፣ አይሰሙንም…” ሳይባል የሚሠራ ነገር ምን መሰላችሁ…መንገድ ላይ ፊኛ ማቃለል! የምር…አሳፋሪ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ አሀ…ጥግ መፈለግ፣ ከግንብ ጀርባ መዞር ምናምን ቀረ እኮ! (አንዳንዴም እነኚህ ነገሮች ከመረሳታቸው የተነሳ… “ጎጂ ባህል…” ምናምን የተባሉ አይመስላችሁም!) በአደባባይ መጸዳዳት ትክክል አለመሆኑን ለልጆቹ ማስተማር የሚገባው ‘ሱፍ በከረባት ግጥም’ ያደረገው ሰው በጠራራ ጸሀይ ትራፊክ መብራት ላይ ዚፕ ሲፈታ ታገኙታላችሁ፡፡ እናላችሁ… አስቸጋሪ ሁኔታዎች እያየን ነው፡፡ አንዳንዴ ምን ይመስለኛል መሰላችሁ…ከተማዋ በሙሉ ሳንቲም ሳይከፈልባት እንትን መባያ የሆነች ይመስለኛል፡፡
እናላችሁ…በፊት ለፊት ግጥም አድርገን ከሳምን በኋላ ዘወር ሲልሉን ምላሳችንን የምናወጣ አይነት ሰዎች እየበዛን ስንሄድ አሪፍ አይደለም፡፡ እናማ…እንዲህ፣ እንዲህ ሆነን እንዴት መግባባት እንደምንችል…አስቸጋሪ ነው፡፡
ስሙኝማ…የመስማት ነገር ካነሳን አይቀር…ይቺን ስሙኝማ… ሰውየው ምን አለ መሰላችሁ…“ሽማግሌዎቹ ምን ጊዜም ሰርግ ላይ ሲያገኙኝ አጠገቤ ሆነው ጎኔን ነካ ያደርጉና ‘ቀጥለህ አንተ ነህ’ እያሉ ይጨቀጭቁኛል፣” ይላል፡፡
እሱ ምን እንደሚያደርግ ሲጠየቅ ምን አለ መሰላችሁ…“እኔ ደግሞ ቀብር ላይ አጠገባቸው እሆንና ጎናቸውን ነካ እያደረግሁ ‘ቀጥሎ እርሶ ነዎት’ እላቸዋለሁ፡፡”
እናማ…“አያዩንም፣ አይሰሙንም” እየተባለ የሚደረጉ ‘አባባ ገፋ፣ ገፋ…’ ነገሮችን የሚያስቀር ተአምር አንድዬ ይላክልንማ!
ደህና ሰንብቱልኝማ!

ፕሬዝዳንት የሚሆነው ግለሰብ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ብቻ ስለመሆኑ ወይም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕጩ ሆኖ መቅረብ የሚችል ስለመሆኑ ግልጽ ባለ ሁኔታ የተደነገገ አንቀጽ በሕገ መንግስቱ ውስጥ አይገኝም፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲህ ይላል “የምክር ቤት አባል ፕሬዝዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል” ይላል፡፡ ይህ ጥቅል አገላለጽ በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ይመስለኛል፡፡

 ሰሞኑን በመዲናችን እየተናፈሱ ካሉት የወሬ ቱማታዎች አንዱ፣ በመጪው መስከረም ወር 2006 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ሆኖ የሚመረጠው ሰው ማን እንደሆነ የመተንበይ ጉዳይ ነበር፡፡ በወሬው ሂደት በፕሬዝዳንትነት ዕጩ ሆነው ይቀርባሉ ከተባሉት ግለሰቦች አንዱ እውቁ አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ እንደሆነም ተደጋግሞ ሲጠቀስ ሰምተናል፡፡ 

ታዋቂው አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴም ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሐምሌ 13 ቀን 2005 ዓ.ም እትም ላይ ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ አትሌት ኃይሌ “በመጪው ምርጫ ፓርላማ እገባለሁ፤ ግን ወዲያው ፕሬዝዳንት አልሆንም” በሚል የሰጠውን ቃለ ምልልስ ካነበብኩ በኋላ እነሆ ይህቺን ጽሁፍ ለማዘጋጀት ተነሳሁ፡፡
በዚህ መጣጥፍ በሦስት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ማድረግን መረጥኩ፡፡ አንደኛ፤ ከሀገሪቱ ሕገ-መንግስት እና ከሁለቱ ምክር ቤቶች (ከሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና ከፌዴሬሽን ም/ቤት) የጋራ ስብሰባ መተዳደሪያ ደንብ አኳያ የፕሬዝዳንት አመራረጥን በተመለከተ የፈጻጸም ሂደቱን መቃኘት፣ ሁለተኛ፤ አትሌት ኃይሌ በቃለ ምልልሱ ባነሳቸው አንዳንድ ሃሳቦች ዙሪያ አስተያየት መስጠት እና ሦስተኛ፤ የሀገሪቱ 3ኛ ፕሬዝዳንት ማን ቢሆኑ ይሻላል? በሚለው ላይ የግል እይታዬን ማቅረብ ይሆናል፡፡
የፕሬዝዳንት አመራረጥ፣
ብዙ ሰዎች የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሚሆነው ሰው በግሉ ተወዳድሮ በማሸነፍ የፓርላማ አባል የሆነ ግለሰብ ብቻ እንደሆነ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ በዚህ ረገድ ያለውን ብዥታ ለማጥራትና ትክክለኛውን ግንዛቤ ለመያዝ የህገ መንግስቱን ድንጋጌ መመልከቱ ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 1 መሰረት ፕሬዝዳንት የሚሆንን ሰው ዕጩ አድርጎ የማቅረብ ስልጣን የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ ይህ ዕጩ ፕሬዝዳንት የሚሾመው በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና በፌዴሬሽን ም/ቤት የጋራ ስብሰባ በተገኙ አባላት በሁለት ሦስተኛ (2/3ኛ) ድምፅ ድጋፍ ያገኘ እንደሆነም፣ በአንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 2 ላይ ተደንግጓል፡፡ ፕሬዝዳንት የሚሆነው ግለሰብ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ብቻ ስለመሆኑ ወይም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዕጩ ሆኖ መቅረብ የሚችል ስለመሆኑ ግልጽ ባለ ሁኔታ የተደነገገ አንቀጽ በሕገ መንግስቱ ውስጥ አይገኝም፡፡ ይሁን እንጂ፣ አንቀጽ 70 ንዑስ አንቀጽ 3 እንዲህ ይላል “የምክር ቤት አባል ፕሬዝዳንት ሆኖ ከተመረጠ የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል” ይላል፡፡ ይህ ጥቅል አገላለጽ በውስጡ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ይመስለኛል። እኔ እንደገባኝ ከሆነ፣ የዚህ አንቀጽ መንፈስ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆኖ መቅረብ የሚችል መሆኑን፤ ይሁን እንጂ እጩው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባል ከሆነ (የምክር ቤት አባልም ፕሬዝዳንትም መሆን ስለማይኖርበት) መቀመጫውን እንደሚለቅ ያስገነዝባል፡፡
የዚህን አንቀጽ ትርጉም ሰፋ አድርገው የሚያዩ አንዳንድ ሰዎች “የተወከለበትን ምክር ቤት ወንበር ይለቃል” ማለት የፓርቲ አባል ከሆነ ‘የፓርቲ መታወቂያውን ይመልሳል’ ማለት እንደሆነ አድርገው ሲናገሩም የሰማሁበት አጋጣሚ አለ፡፡ በኔ እምነት ይህ አተረጓጎም ግን ትክክል አይመስለኝም፡፡ ያ ቢሆን ኖሮ የመጀመሪያው የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ነጋሦ ጊዳዳ፤ እስከ ስልጣን ዘመናቸው ማብቂያ ድረስ የኦህዴድ አባል ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ አመራርም ሆነው አይዘልቁም ነበር የሚል መከራከሪያ ማቅረብ የሚቻል መስለኛል፡፡ ከላይ የጠቀስኩት የሕገ መንግስቱ ድጋጌ እንተጠበቀ ሆኖ፤ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እና በፌዴሬሽን ም/ቤት የጋራ የአሰራርና የስብሰባ ሥነ-ስርዓት ደንብ ቁጥር 1/2000 ላይ፤ ስለ እጩ ፕሬዝዳንት አቀራረብ፣ አንድ እጩ ፕሬዝዳንት ማሟላት ስለሚገባው መስፈርት፣ ስለ ሌሎችም ጉዳዮችና ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደቶች የተብራራበት ሁኔታ አለ፡፡በዚሁ ደንብ አንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት፤በዕጩ ፕሬዝዳንትነት የሚቀርብ ሰው አራት መስፈርቶችን ማሟላት እንዳለበት ተደንግጓል። ይኸውም፤ (1) ለሕገ መንግስቱ ታማኝ የሆነ፣ (2) ሀገሪቱን በርዕሰ ብሔርነት ለመምራት የሚያስችል ብቃትና ሥነ-ምግባር ያለው፣ (3) ዕድሜው 21 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆነ እና (4) ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሆነ፣ የሚሉ ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ “ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆኖ የሚቀርብ ማንኛውም ሰው ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ወገንተኛነት ነፃ ሆኖ ለማገልገል ፈቃደኛ መሆን አለበት” የሚል ድንጋጌ በዚሁ ደንብ በአንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 4 ላይ ተደንግጓል፡፡
አንድ ሰው ለሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ እጩ ፕሬዝዳንት ሆኖ ለመቅረብ ደግሞ በቅድሚያ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ በአብላጫ ድምፅ እጩነቱ ተቀባይነት ማግኘትና መጽደቅ እንደሚኖርበትና የዚህ አፈጻጸም ሂደትም በጋራ ደንቡ በአንቀጽ 5 ንዑስ አንቀጽ 1 እና 2 ላይ በዝርዝር ተብራርቷል፡፡
የአትሌት ኃይሌ ቃለ ምልልስ፣
አትሌት ኃይሌ ገ/ስላሴ ከላይ በዝርዝር የጠቀስኳቸውን የሕገ መንግስት እና የሁለቱ ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ መተዳደሪያ ደንብ የፕሬዝዳንት አመራረጥ ድንጋጌዎች ይወቃቸውም አይወቃቸው በመጪው ሀገራዊ ምርጫ ተወዳድሮ በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ለመሆን እና ከዚያም የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ለመሆን መነሳቱ መልካም ነገር ይመስለኛል፡፡ ባደጉትና በሰለጠኑት ሀገሮች የጎላ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉት ምሁራንና ባለሀብቶች እንደሆኑ ይነገራል፡፡ የሀገራችን ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ባለሀብቶች በስልጣን ላይ ያለውን ገዢ ፓርቲ ፖሊሲዎችና አፈጻጸም በሩቁ ሆነው ከመተቸትና ከማማረር አልፈው ወደ ፖለቲካው መድረክ ብቅ ሲሉ ብዙም አይታይም፡፡ እናም በዚህ ረገድ አትሌት ኃይሌ ያሳየው ተነሳሽነት የሚያስመሰግነው እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡
ይሁን እንጂ፣ አትሌት ኃይሌ ወደ ፖለቲካው መድረክ “ዘው” ብሎ ከመግባቱ በፊት በጥልቀት ሊያያቸውና ሊመረምራቸው የሚገቡ ጉዳዮች ያሉ መሆኑን በዚህ ጽሁፍ መግቢያ ላይ በጠቀስኩት አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ከሰጠው ቃለ ምልልስ ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ለምሣሌ፤ “ፕሬዝዳንት ብትሆን ምን ምን ሥራዎችን እንደምታከናውን ግለጽልኝ” ተብሎ ለቀረበለት ጥያቄ “በስራ አጥነት፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኤክስፖርት ላይ ብዙ መስራት ይቻላል…” የሚል መልስ ሰጥቷል፡፡
ይህንን የኃይሌን መልስ ሳነብ፣ አትሌት ኃይሌ ከተራ ሀገር ወዳድነት እና ከሥራ ተነሳሽነት ውጪ “ፖለቲከኛ” የሚያደርገው አቅም የገነባ አለመሆኑን ነው የተረዳሁት፡፡ የፕሬዝዳንቱ የስራ ድርሻ ምን ምን እንደሆነ እንኳ ሕገ መንግስቱን አንብቦ በቅጡ የተገነዘበ አልመሰለኝም፡፡ እንኳን የጠለቀ ግንዛቤ ሳይዙ የመጠቀ ግንዛቤ ተይዞም የኢትዮጵያ ፖለቲካ ዳር ላይ ሆነው እንደሚያዩት ቀላል አደለም፡፡ ሁላችንም እንደምናውቀው በእኛ ሀገር የፕሬዝዳንቱ ስልጣን ውሱን (በእንግሊዝኛው አገላለጽ Ceremonial) ነው፡፡ በሕገ መንግስቱ በተደነገገው መሰረት የፕሬዝዳንቱ የስራ ድርሻ በአጭሩ “በየዓመቱ የሁለቱን ም/ቤቶች የጋራ ስብሰባ በንግግር መክፈት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያቀርቡ አምባሳደሮችን መሾም፣ ፓርላማ ያጸደቃቸውን ሕጎች መፈረምና በነጋሪት ጋዜጣ ማወጅ፣ ኒሻንና ሽልማት መስጠት፣ ይቅርታ ማድረግ፣…ወዘተ.” የሚሉ ናቸው፡፡ በሕገ መንግስቱ ከተሰጠው ስልጣን ውጪ መስራት እንደማይቻልም ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ፣ አትሌት ኃይሌ ይህንን ባለመገንዘብ ይመስለኛል “ሥራ አጥነትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ ጠቃሚ ያልሆኑ ባህሎችን፣ ሰርግን፣… ወዘተ.” የመሳሰሉትን በተመለከተ እሰራለሁ የሚል መልስ በቃለ ምልልሱ ያነሳው፡፡ ልክ በአትሌቲክሱ በማራቶን ለመወዳደር የተመዘገበ፣ በመቶ ሜትር ርቀት መወዳደር እንደማይችለው ሁሉ፣ፕሬዝዳንቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የሥራ ድርሻ ሊሰራ እንደማይችል ወንድሜ ኃይሌ ልብ አላለውም፡፡
እዚህ ላይ አንድ ነገር ለማለት ወደድሁ፡፡ አትሌት ኃይሌ፣ በአትሌቲክሱ መስክ የተዋጣለት ሥራ በመስራት ስኬታማ ሊሆን የቻለው በመስኩ የጠለቀ እውቀትና ግንዛቤ ያለው አሰልጣኝና ማናጀር በሚሰጠው ምክርና አቅጣጫ በመጓዙ ይመስለኛል። ስለሆነም፤ በፖለቲካውም መስክ የተሳካ ውጤት ላይ ለመድረስ በቂ ግንዛቤና ልምድ ያለው አማካሪ ቢኖረው መልካም ነው፡፡ በዚህ ረገድ እኔን ጨምሮ የቀድሞ የተቃዋሚ ወይም የኢህአዴግ አባል የነበርን “የፖለቲካ ጡረተኞች” ስላለን የአማካሪ ችግር የሚኖር አይመስለኝም፡፡ ባይሆን ከእጅህ ፈታ ማለት ነው - ወዳጄ ኃይሌ! (አጋጣሚውን በመጠቀም አዲስ አድማስ ያላወቀው ማስታወቂያ መስራቴ ነው)
ማን ፕሬዝዳንት ይሁን?
ባለፉት አስራ ስምንት ዓመታት ሁለት ፕሬዝዳንቶች በርዕሰ ብሔርነት ተሹመዋል። አሁን በስራ ላይ ያሉት ፕሬዝዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ የስልጣን ዘመን በመጪው መስከረም ወር 2006 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅና አዲስ ፕሬዝዳንት እንደሚመረጥ ይጠበቃል፡፡ እጩ ፕሬዝዳንቱን መርጦ በማቅረብ ረገድ ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው መሪው ፓርቲ ኢህአዴግ ትልቁን ሚና እንደሚጫወትም ይታመናል፡፡ በመስፈርቱ መሰረት ኢህአዴግ ይህንን “እድል” ለማን እንደሚሰጥ ምንም ዓይነት ፍንጭ አልሰማሁም፡፡ ግን ለማን ቢሰጥ ይሻላል? ከፆታ አኳያ ለወንዶች ወይስ ለሴቶች? ከዕድሜ አኳያ ለወጣት፣ ለጎልማሳ ወይስ ለአረጋዊ? ከሃይማኖት አኳያ ለኦርቶዶክስ እምነት ተከታይ፣ ለሙስሊም፣ ለካቶሊክ፣ ለፕሮቴስታንት ወይስ ለሌላ? ከብሔር ብሔረሰቦች አኳያ ለሶማሌ፣ ለአፋር፣ ለመዠንገር፣ ለሀዲያ፣ ለከንባታ፣ ለኩናማ፣ ለኤሮጵ፣ ለኛጋቶም፣ ለሙርሲ፣ ለሐመር፣…ወይስ? ኢህአዴግ ካለፉት ሁለት የእጩ ፕሬዝዳንት አቀራረቦች ሂደት የተገኙ ተሞክሮዎችን በማየትና ከላይ የጠቃቀስኳቸውን የፆታ፣ የዕድሜ፣ የሃይማኖትና የብሔር ብሔረሰቦች ስብጥር ከግንዘቤ በማስገባት፣ በአንፃራዊነት የኢትዮጵያን ሕዝቦች ሊወክል የሚችል እጩ ቢያቀርብ የተሻለ እንደሚሆን አስባለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ከሀገሪቱ ዜጎች ከግማሽ በላይ ለሚሆኑት ለሴቶች እድሉ ቢሰጥ የተሻለና አስፈላጊም ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ በዚህ ረገድ ይህንን ኃላፊነት ሊሸከሙ የሚችሉ እውቀትም፣ ልምድም ሆነ ችሎታ ያላቸው በርካታ ሴቶች እንዳሉ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ከታሪክም አኳያ እንኳን አሁንና በጥንታዊት ኢትዮጵያ እነ ንግስት ሳባ፣ ንግስት እሌኒ፣ ንግስት ሀዲያ፣ ዮዲት ጉዲት (ባኑኤል ሃይሙያ?)፣ ዘውዲቱ እና ጣይቱ የነበራቸውን ሚና ማስታወስ መልካም ነው፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የሻቃ ሀይሌ ገ/ስላሴን ፕሬዚዳንት የመሆን ፍላጐትና ያገኘውን ትኩረት በሚመለከት ከአትሌቱ ጋር ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ በተፈጠረ ስህተት ቃለ-ምልልሱ ሙሉ ለሙሉ አልቀረበም፡፡ ለተፈጠረው ስህተት አንባቢያንን ይቅርታ እየጠየቅን ሳምንት የቀረውን ቀጣይ ክፍል እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

ሀይሌ አለም አቀፍ ሰው ነው ከፍተኛ እውቅናም አለው ነገር ግን አሁን ሩጫ የሚያቆምበት ዘመን ስለሆነ ላለመረሳት ነው ወደ ፖለቲካው ለመግባት የሰበው ይባላል እውነት ነው?
አቤት አቤት! (በግርምት ጭንቀላቱን እያወዛወዘ) አንድ ነገር ልንገርሽ እኔ እንዳልረሳና ዘላለም እየታወስኩ እንድኖር ከፈለግኩኝ ኢንተርናሽናል ኦሎምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ተወዳድሬ መግባት እችላለሁ፡፡ ጓደኛዬ ፖልቴርጋት አሁን እዚያ ሊገባ ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከዚህ በላይ ማብራሪያ መስጠት አልፈልግም በቂ ነው፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃ እየተከፈለኝ እዚያ መስራት እችል ነበር በቃ ይሄው ነው፡፡
ቀደም ሲል ልጆቼ ሲቪክ ስለሚማሩ ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት እንደሚመረጥ ያውቃሉ ብለሀል ይሁን እንጂ ሃይሌ ልጆቹ አማርኛ መናገር በማይችሉበት ሁኔታ እንዴት አገር ልምራ ይላል የሚሉ አሉ ምላሽህ ምንድነው?
እንዴት ያለ ነገር ነው በናትሽ እንደው በአሉ አሉ ወሬ ስንቱ ገደል ገባ መሰለሽ፡፡

በነገራችን ላይ የኔ ልጆች ይህንን ነገር አለ የተባለው ሰው ጋር ልካተገናኘን ሞተን እንገናኛለን አሉ፡፡ “እሱ እና እኛ ቁጭ ብለን የትኛችን አማርኛ እንደምንችል እንተያይ” ብለው ነበር፡፡ አንድ መጽሔት ላይ ነው ይህ የተፃፈው፡፡ እና እኔ እንዴት እንዳስቆምኳቸው ታውቂያለሽ ይሄ እኮ የቀልድ መጽሔት ነው በቃ ጆክ ነው ብዬ ነው ያሳመንኳቸው፡፡ በነገራችን ላይ በእኔ እምነት አማርኛ ማወቅና አለማወቅ የኢትዮጵያዊነት መገለጫው አይደለም፡፡ እንግሊዝኛ ማወቅም ምሁርነት አይደለም፡፡ እኔ በልጆቼ ከምረካባቸው ነገር አንዱ አገራቸውን መውደዳቸው ነው፡፡ ሁለቱ ትልልቆቹ የ15 እና የ13 ዓመት ናቸው፡፡ (ቢሮው ግድግዳ ላይ ወደተሰቀለው የልጆቹ ፎቶ እያመለከተ) አሁን አንድ ትምህርት ስላላቸው አሜሪካ ነው ያሉት፡፡ አሁን ደውዬ ባሰማሽ “ወደ ኢትዮትያ የምንመለስበት ጊዜ አይደርስም እንዴ” ነው የሚሉት ትላንትና ማታ ለ30 ደቂቃ ነው ያዋራኋቸው ከሄዱ ገና ሁለት ሳምንታቸው ነው፡፡ ይታይሽ እና አንዳንድ ጊዜ መፃፍ ቻልን መድረክ አገኘን ብለው ሃላፊነት የጐደለው ስራ ባይሰሩ ደስ ይለኛል፡፡ የግል አስተያየት በቃ የግል ነው፡፡ ወደ አድማጭና አንባቢ ሲደርስ የሚያመጣውን ችግር መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡
ነገሩ የገጠመበት ደግሞ ምን መሰለሽ ሃዋሳ ላይ አንድ ኢንተርቪው ነበረን፡፡ እኔ እየተጠየቅኩ ሳለ በመሃል ሁለቱ ልጆቼ መጡ፡፡ ደንግጠው የሚሉት ሲጠፋባቸው እንግሊዝኛ እየቀላቀሉ ሲያወሩ በቴሌቪዢን ስለታዬ ነው እንዲህ የሚባለው፡፡ ግን ልጆቼ ጥሩ ኢትዮጵያዊያን ናቸው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሁሉንም እየዞሩ ማስረዳት አይቻልም የቢግ ብራዘሯ ቤቲ ገና ሁሉንም ዞራ ማስረዳት ስላልቻለች እንደውም ነገሩ ወደ ክስ እየሄደባት ነው ከአዲስ አድማስ ከጋዜጣሽ እንዳነበብኩት በነገራችን ላይ አንድም ዕትም ሳያመልጠኝ እገዛለሁ የማነበው ጋዜጣ ነው አዲስ አድማስ፡፡
ሰው ወደ ሃላፊነት ሲመጣ ነገሮች አልጋ በአልጋ አይሆኑም ፕሬዚዳንት ብትሆን ምን ውጣውረዶች የሚገጥሙህ ይመስልሃል?
እሱማ ቻሌንጅ እንደሚገጥመኝ አውቄ እየተዘጋጀሁ ነው፡፡ አሁንም ወደ ቻሌንጁ እየባሁ ነው፡፡ ለምን እንዴት፣ ገብተህ ምን ትፈጥራለህ፣ እያሉ ቤተሰቦቼና ጓደኞቼ በጥያቄ ሲያጣድፉኝ እኮ ይሄ የቻሌንጅ መጀመሪያ ነው፡፡ ወደ ውድድር ውስጥ ስትገቢ ደግሞ በርካታ ቻሌንጆች አሉ፡፡ እንዲህ ታግሰሽና ተዘጋጅተሽም አለመመረጥ ይመጣል፡፡ ከተመረጥሽ በኋላ ሌላ ከፍተኛ ቻሌንጅ አለ፡፡ እኔ ወደ ፓርላማ ልግባ ወይም ፕሬዚዳንት ልሁን ስል ላገልግል እንጂ ልገለገል አይደለም፡፡ ምንድነው የምታገለግለው ካልሽኝ በርካታ ነገሮች አሉኝ ልሠራቸው የማስባቸው፡፡
ወደዚያ እንድትገባ የሚፋፋህና አንገብጋቢ የምትላቸው ጉዳዮች ወይም ፓርላማ ብገባ እቀርፋቸዋለሁ ፕሬዚዳንት ብሆን እልባት እሰጥባቸዋለሁ የምትላቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
በጣም በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ በኢኮኖሚው ላይ ማድረግ ያለብን ነገሮች አሉ፡፡ በስራ አጥነት ላይ ከፍተኛ ሥራ መሠራት አለበት፣ አሁንም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ የኤክስፖርት ከሶስትና ከአራት ቢሊዮን ዶላር ያልዘለለ ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ላይ ሁሌ እናወራለን፡፡ ግን መልካም አስተዳደር በአንድ ምሽት የሚመጣ አይደለም፡፡ ሂደት ነው በዚያ ላይ ትኩረት ሰጥቼ እሰራለሁ፡፡ እኛ ኢትዮጵያ ነን እያሰብን ያለነው መካከለኛ ገቢ ያለን ዜጐች ስለመሆን ነው ይሄ እንዴት ይመጣል እነማን ናቸው መካከለኛ ገቢ ያላቸው አገራት እከሌ እከሌ፣ እኔ ብዙ አገሮችን በመጐብኘት ባገኘሁት ልምድ የእነዛን አገሮች የማደግ ምስጢር በአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ላይ ተመስርተን ተግባራዊ በማድረግ ለውጥ ማምጣት ላይ መስራት ይቻላል፡፡ በአጭሩ ለመናገር ወደ ፓርላማ የምገባው ተሞክሮዬን ለማካፈል ነው፡፡ ልምዴን ሳካፍል ግን በፖለቲካም በይው በማህበራዊም በይው በኢኮኖሚው በሁሉም ረገድ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ለምሳሌ ማህበራዊ ነገሮችን እናውራ ቢባል ጠቃሚ ባህል እንዳለን ሁሉ ጐጂም ባህል ሞልቶናል፡፡
ምሳሌ እየጠቀስክ ብትነግረኝ …
ለምሳሌ ኢትዮጵያ ውስጥ እንነጋገር ከተባለ የኢትዮጵያ የሠርግና የሀዘን ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሰርጋችንም ሀዘናችንም ከአንድ ሳምንት በላይ ይወስዳል ሰርግም ሀዘንም አያስፈልግም እያልኩ አይደለም በዓላት አከባበር ላይ ብታይ ጊዜ የሚድል ነገር ነው የምታይው ይህ ሁሉ ካልተስተካከለና ጊዜ አጠቃቀማችን ላይ ( ) ካለመድን ለውጥ ማምጣት አይቻልም በዚህ ላይ እሠራለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለዚህ ደግሞ ራሴ ምሳሌ ሆኜ መገኘት አለብኝ፡፡ ሠርቼ ነው ማሳየት ያለብኝ
ሰርግን በተመለከተ ላነሳኸው አንተ በሠርግ ነው ያባኸው መልስም እንደነበረህ አልጠራጠርም በዚህ እንዴት ሌላውን ማስተማር ትችላለህ?
እኔ ሰርጌ የዛሬ 16 ዓመት ነበር፡፡ ሠርግ ነበር ግን ይህን ያህል ቀን የፈጀ አይደለም አላደረግኩትም፡፡ ከሰርጌ በኋላ በማግስቱ ልምምድ ላይ ነበርኩ፡፡ መልስ ሄደሃል ወይ አዎ ሄጃለሁ፡፡ ነገር ግን ልምምድ ሰርቼ ስጨርስ ነው መልስ የሄድኩት፡፡ ይሄው ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ መስራት አለብን፡፡ ይሄ ያሳስበኛል እሠራበታለሁ፡፡
አንተ በግልህ ይህቺን አገር ፕሬዚዳንት ሆኖ ለመምራት አንድ ሰው ምን ምን ነገሮችን ሊያሟላ ይገባል ትላለህ?
ከበርካታ ነገሮች ውስጥ አንቺ ጣል ጣል ያደረግሽው እውቅና ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ካለኝ እውቅና እና እንደ ኢትዮጵያዊ አትሌቲክስ በውጭው ያሉ የአለም መሪዎችን የማግኘት እድል ገጥሞኛል መሪ ስትሆኚ ደግሞ የዛን ሁለትና ሶስት እጥፍ ነው ስለዚህ እውቅና አንዱ ሊሆን ይችላል ማለቴ እውቅና ካለ ያግዛል ግን ግድ አይደለም በተረፈ ዋናው ግን ልምድ “Experience” የሚባለው ወሳኝ ነው፡፡ ለምሳሌ የአሁኑን ፕሬዚዳንት አቶ ግርማን እያቸው ልምዳቸው የትናየት እንደሆነ፡፡ በተለያየ ዘርፍ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ እንዲህ አይነት ሰው ያስፈልጋል በተረፈ አገሪቱን እና ህዝቧን በደንብ ማወቅ ወሳኝ ነው፡፡ አዲስ አበባ ብቻ አይደለችም ኢትዮጵያ የህዝቡን ስነ - ልቦና የዝቅተኛውን ህብረተሰብ ኑሮ ማወቅ መረዳት ለአንድ መሪ ወሳኝ ነው እነዚህን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በዋናነነት የምትመሪውን ህዝብ ማወቅ አለብሽ ማወቅ ያለብሽ በከፊል ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ ነው፡፡ ለሁሉም አባት ሆኖ ነው መሪ የሚመረጠው አንዱ ሀብታም ነው ሌላው ደሀ ነው ያልተማረነው የተማረነው የሚል የለም፡፡ ሁሉንም እኩል ማየት ይጠበቅበታል፡፡ ይህን ሁሉ የምነግርሽ የእኔ የራሴ የግሌን አስተያየት ነው፡፡
ካነሳሀቸው ሀሳት አንፃር አንተ እነዚህን ጉዳዮች አሟላለሁ ብለህ ታስባለህ በእውቅናስ ብቻ አገር ይመራል የሚል እምነት አለህ?
እሱማ እግር ነቃ ማለት ጭንቅላት ነቃ ማለት አይደለም ነገር ግን የተሻለ የብዙ አገር ልምድ አለኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ እውቅና ብቻ ሳይሆን በተዘዋወርኩባቸው በርካታ አገራት የተለያዩ ለአገር የሚበጁ ልምዶችን አካብቻለሁ መስፈርቶቹን ከሞላ ጐደል አሟላለሁ የሚል እምነት አለኝ፡፡
አሁን ስንት አመትህ ነው
አርባ አመት ሞላኝ
እድሜም ለመሪነት ወሳኝ ነው አይደለም እንዴ?
በትክክል ወሳኝ ነው አሁን ስለፕሬዚዳንት “ስላወራን ነገ ዘልዬ ፕሬዚዳንት ልሆን አልችልም፡፡ አሁን ፕሬዚዳንት የተዘጋጀ ይመስለኛል ከመስከረም ጀምሮ በአዲስ ፕሬዚዳንት እንመራለን የሚል እምነት አለኝ፡፡ እኔ ፓርላማ እገባለሁ፡፡ አዲሱ ፕሬዚዳንት ስድስት አመት ይመራሉ እስከዛ እኔ ፓርላማ እቆያለሁ እድሜዬም ያን ጊዜ ይታያል፡፡