Administrator

Administrator

 ከተማዋ በአመቱ በ21.5 ሚ. ሰዎች ተጎብኝታለች
      የታይላንድ ርዕሰ መዲና ባንኮክ፣ በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት 2016፣ በርካታ ቁጥር ባላቸው ሰዎች በመጎብኘት ከአለማችን ከተሞች የአንደኛነት ደረጃ መያዟን ፎርብስ መጽሄት ዘግቧል፡፡
በአመቱ ባንኮክን የጎበኙ ሰዎች ቁጥር 21.5 ሚሊዮን እንደደረሰ ማስተርካርድ የተባለው ተቋም ያወጣው አመታዊ ዓለማቀፍ የመዳረሻ ከተሞች ሪፖርት ማስታወቁን የጠቆመው ዘገባው፤ በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠቺው ደግሞ በ19.9 ሚሊዮን ሰዎች የተጎበኘቺው ለንደን መሆኗን አስታውቋል። የፈረንሳዩዋ መዲና ፓሪስ በአመቱ በ18 ሚሊዮን ሰዎች በመጎብኘት ከአለማችን ከተሞች የሶስተኛነት ደረጃን የያዘች ሲሆን ዱባይ በ15.27 ሚሊዮን፣ ኒውዮርክ በ12.75 ሚሊዮን፣ ሲንጋፖር በ12.11 ሚሊዮን፣ ኳላላምፑር በ12.02 ሚሊዮን፣ ኢስታምቡል በ11.95 ሚሊዮን፣ ቶክዮ በ11.70 ሚሊዮን፣ ሴኡል በ10.2 ሚሊዮን እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በአመቱ በ3.6 ሚሊዮን ሰዎች የተጎበኘቺው የደቡብ አፍሪካዋ ጁሃንስበርግ፣ ከአፍሪካ ከተሞች በአመቱ በበርካታ ሰዎች በመጎብኘት ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ ካይሮ በ1.55 ሚሊዮን፣ ኬፕታውን በ1.37 ሚሊዮን ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ መያዛቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ባለፈው ሃምሌ የተቃጣውን የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከትሎ ተግባራዊ ያደረገውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከአንድ ወር በፊት (በጥቅምት) ለ3 ወራት ያራዘመው የቱርክ ፓርላማ፤ባለፈው ማክሰኞ ባሳለፈው ውሳኔ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንደገና ለ3 ወራት ማራዘሙን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፓርላማው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ደጋግሞ ማራዘሙ፣ የአገሪቱ መንግስት ያለ ከልካይ የዜጎችን መብቶች የሚገድቡ ወይም ሙሉ ለሙሉ የሚያሳጡ አዳዲስ ህጎችን ለማውጣትና ተግባራዊ ለማድረግ አስችሎታል ያለው ዘገባው፣ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ግን፣ አዋጁን ዳግም ማራዘም ያስፈለገው የሽብርተኞች እንቅስቃሴ መቀጠሉን በማጤን ነው ብለዋል፡፡
 ከቀናት በፊት በተከበረው የፈረንጆች አዲስ ዓመት ዕለት የተከሰተው የሽብር ጥቃት 39 ያህል ቱርካውያንን ለሞት መዳረጉን ተከትሎ በአገሪቱ ከፍተኛ ውጥረትና ስጋት የተፈጠረ ሲሆን ፓርላማው በጠራው ስብሰባ፣ አዋጁን እንደገና ለማራዘም መወሰኑን ዘገባው ገልጧል፡፡
የቱርክ መንግስት በሃምሌ ወር ከተቃጣበት መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ከ40 ሺህ በላይ ሰዎችን ማሰሩንና 100 ሺህ ያህል የመንግስት ሰራተኞችን ከስራ ገበታቸው ማባረሩን ያስታወሰው ዘገባው፤ የአውሮፓ ህብረት የቱርክ መንግስት ያወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተደጋጋሚ ሲተቸው እንደነበርም አክሎ ገልጧል፡፡

 በወርቅ በተለበጠ የሰርግ ካርድ፣ 50 ሺህ ሰዎች ተጠርተዋል
      በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ህንዳውያን በገንዘብ እጥረት ቀውስ በሚሰቃዩበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት፣ የቀድሞው የህንድ ሚኒስትር ዲኤታ ጋሊ ጃናርዳና ሬዲ፤ 74 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ድል ባለ ድግስ ልጃቸውን መዳራቸው፣በአገሪቱ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደገጠመው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የቀድሞው የቱሪዝም ሚኒስትር ዲኤታ ሴት ልጃቸውን የዳሩበት ይህ ሰርግ፣ በአገረ ህንድ ታሪክ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ከተደረገባቸው የቅንጦት ሰርጎች አንዱ እንደሆነ የጠቆመው ዘገባው፤ የሰርጉ መጥሪያ ካርድ በወርቅ የተለበጠ፣ ለሰርጉ የተጋበዙ እንግዶች ቁጥርም 50 ሺህ መሆኑን አመልክቷል፡፡
የቅንጦት ሰርጉ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞ መቀስቀሱን ተከትሎ፣ የአካባቢው የግብርና መስሪያ ቤት ባለስልጣናት የግለሰቡን የንግድ ድርጅቶች መዝጋታቸውንና ስለ ሰርጉ ወጪ ማብራሪያ እንዲሰጡ ማድረጉ ተነግሯል፡፡ ሰውዬው ለባለስልጣናቱ በሰጡት ምላሽ፣ በሲንጋፖርና በሌሎች አካባቢዎች ከሚያከናውኑት የቢዝነስ ስራ ባገኙት ገንዘብ፣ የሰርጉን ወጪ መሸፈናቸውንና ለመንግስትም ተገቢውን ግብር በወቅቱ መክፈላቸውን እንደገለጹ ዘገባው አስረድቷል፡፡
ሚኒስትሩ በሙስና ክስ ተመስርቶባቸው ለሶስት አመታት በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ፣ ባለፈው አመት በዋስ መፈታታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ከእስር ከወጡ በኋላም”ክዛር” የተባለውን የማዕድን አውጭ ኩባንያ ማስተዳደር መቀጠላቸውን ጠቁሞ፣ በርካታ ህንጻዎችና ሌሎች የንግድ ኩባንያዎችመም እንዳሏቸው አስታውቋል፡፡

 የአገር መሪዎች ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ምን ይሰሩ እንደነበር ወይም በምን ሙያ ላይ ተሰማርተው እንደቆዩ አስባችሁት ታውቃላችሁ? እኔ ትዝ ብሎኝም አያውቅም፡፡ ግን እኒህ ሰዎች ሲወለዱ ፕሬዚዳንት ወይም ጠ/ሚኒስትር ሆነው አለመወለዳቸውን ያለ ጥርጥር እናውቃለን፡፡ (የንጉሳውያን ቤተሰብ ካልሆኑ በቀር) ይሄ ማለት ደግሞ ወደ ሥልጣን እስኪመጡ ድረስ ባለው ዕድሜያቸው ሲተዳደሩ የቆዩበት ሙያ እንደሚኖራቸው ይጠቁማል፡፡ አንዳንዴ ታዲያ ተሰማርተው የነበሩበት ሙያ ወይም የሥራ ዘርፍ ከፖለቲካና ከአገር መሪነት ጋር ባለው ከፍተኛ ርቀት የተነሳ መገረምና መደነቅ ሊፈጥርብን ይችላል፡፡ የሚከተሉት መሪዎች ማለፊያ ምሳሌዎች ይመስሉኛል፡፡
                                  
     ሙዚቃ ቀማሪው ፕሬዚዳንት
 -   የክሮኤሽያው ፕሬዚዳንት ኢቮ ጆሲፖቪክ፤ወደ ፖለቲካ  ከመግባታቸው በፊት የክላሲካል ሙዚቃ ቀማሪ ነበሩ፡፡ በደርዘን የሚቆጠሩ ክላሲካል ሙዚቃዎችን የደረሱ ሲሆን የክሮኤሽያን ዋነኛ የሙዚቃ ፌስቲቫል መርተዋል፡፡  
•   ጆሲፖቪክ በፕሬዚዳንትነት የተመረጡት እ.ኤ.አ በ2010 ሲሆን በወቅቱ የሙዚቃ ሙያቸውን እንደማያቆሙ ቃል ገብተው ነበር። በኋላ ላይ ግን የፕሬዚዳንትነት ስራቸው ፋታ የማይሰጥ በመሆኑ ቃላቸውን መፈፀም እንዳልቻሉ አምነዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አንድ ፒያኖ  ወደ ፕሬዚዳንታዊ ቢሮአቸው ለማስገባት አልሰነፉም፡፡ ኢቮ ጆሲፖቪክ፤ በቅድመ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ኪ-ቦርድ መጫወታቸው ተዘግቧል፡፡
    ሰዓሊው ጠ/ሚኒስትር
 -   የአልባኒያው ጠ/ሚኒስትር ኢዲ ራማ ወደ አገር መሪነት ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ሰዓሊ ነበሩ፡፡ በፓሪስ የሥነ  ጥበብ ት/ቤት ስዕል ያጠኑት ራማ፤ እ.ኤ.አ በ1998 ወደ አልባኒያ ሲመለሱ የባህል ሚኒስትር ሆነው ተመደቡ። ከዚያም የአልባኒያ ከተማ- ቲራና፣ ከንቲባ ሆነው ተሾሙ፡፡ ይሄም ለሥነ ጥበባዊ ውበት ያላቸውን ስሜት ለመወጣት ዕድል የሰጣቸው ሲሆን በሲሚንቶ የተገነቡ የኮሙኒስት ዘመን ግራጫ ህንፃዎች፤ በሮዝ፣ በብጫ፣ በአረንጓዴና ሀምራዊ ቀለማት እንዲዋቡ አስደርገዋል፡፡
•   የቀድሞ የቅርጫት ኳስ ተጫዋችም የነበሩት ራማ፤ እ.ኤ.አ በ2004 ለቢቢሲ በሰጡት  ቃለ መጠይቅ፤ “በእርግጠኝነት ፖለቲከኛ ነኝ ለማለት አልችልም፡፡ እኔ አሁንም ሰዓሊ ነኝ ነው የምለው፤ ፖለቲካን ለለውጥ በመሳሪያነት ለመጠቀም እየሞከርኩ ነው” ብለው ነበር፡፡
•   በ2012 የTED ቶክ ላይ ለመሪዎች ባስተላለፉት ጥሪ፡- “ከተማችሁን በቀለም መልሳችሁ ፍጠሩ” ብለዋል፡፡  
   ገጣሚው ፕሬዚዳንት
 -   የአየርላንድ ፕሬዚዳንት ማይክል ዲ.ሂጌንስ፣ የሥልጣን መንበር ከመቆናጠጣቸው በፊት ገጣሚ ነበሩ፡፡ አራት የግጥም ጥራዞችን (volumes) ለህትመት ያበቁ ሲሆን የአየርላንድ የመጀመሪያው የሥነ ጥበብ ሚኒስትርም ነበሩ። ማይክል ዲ. በሚል ቁልምጫ የሚታወቁት ታጋይ-ገጣሚ ፕሬዚዳንቱ፤ አየርላንድ “የፈጠራ ሪፑብሊክ” እንድትሆን ጠይቀዋል፡፡  
•    የራሳቸው የግጥም ስራዎች ግን ከሃያስያን የሰላ ትችት አላመለጡም፡፡ አንዱ ሃያሲ እንደውም፤ “ፕሬዚዳንቱ በሥነ ፅሁፍ ላይ ለፈፀሙት ወንጀል ክስ ሊመሰረትባቸው ይችላል” ማለቱ ተዘግቧል፡፡

Friday, 06 January 2017 12:32

የቢዝነስ ጥግ

- ባለፀጋ ለመሆን ከፈለግህ፣ ተኝተህም ገንዘብ መስራት አለብህ፡፡
      ዴቪድ ቤይሊ
- አበዳሪም ተበዳሪም አትሁን፡፡
     ዊሊያም ሼክስፒር
- ገንዘብ ማስቀመጥ ስህተት ከሆነ፣ ትክክል መሆን አልፈልግም፡፡
    ዊሊያም ሻትነር
- ከባለፀጎች የምወድላቸው ገንዘባቸውን ብቻ ነው፡፡
    ናንሲ አስቶር
- ሀብታም ብዙ አዱኛ ያለው ሳይሆን ብዙ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡
    ኤሪክ ፍሮም
- ሀብታም የሚያደርግህ ደሞዝህ ሳይሆን የአወጣጥ ልማድህ ነው፡፡
   ቻርልስ ኤ. ጃፌ
- ህይወት በዶላር ኖት ላይ መታተም የለበትም፡፡
   ክሊፎድ ኦዴትስ
- የምንኖረው በወርቃማው ህግ ነው፡፡ ወርቁ ያላቸው ህጉን ያወጡታል፡፡
   ቡዚ ባቫሲ
- ሴቶች ባይኖሩ ኖሮ በዓለም ላይ ያለው ገንዘብ በሙሉ ትርጉም አይኖረውም ነበር፡፡
   አሪስቶትል ኦናሲስ

የፈረንሳዩ  ሎቨር ግሩፕ፤  ከ480 ሚ.ብር በላይ በሆነ ወጪ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያለውን  “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር፣ ”በገዝ ቢዝነስ ግሩፕ” ከተሰኘ የኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር ተስማማ፡፡ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሆቴሉ፤ 88 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ታውቋል። ሆቴሉ የሬስቶራንት፣ የስፓ፣ የስብሰባ አዳራሽ (ለቢዝነስና ተጓዦች) አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የላቁ መስተንግዶዎችንም ያቀርባል ተብሏል፡፡
ሎቨር ሆቴልስ ግሩፕ፤ ሁለተኛውን ባለ 5 ኮከብ “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ሆቴል በኢትዮጵያ መክፈቱ፤ ሎቨር በአፍሪካ ያቀደውን ሆቴሎቹን የማስፋፋት ስትራቴጂ ያጠናክርለታል ተብሏል፡፡ በኬንያ፣ ሩዋንዳ እንዲሁም በታንዛንያ የሆቴሎቹን ቁጥር እያሳደገና አገልግሎቱን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በ2017 እ.ኤ.አ ሎቨርስ ሆቴልስ፤ ወደ 15 ተጨማሪ ሆቴሎችን በክልሉ ለመክፈት አቅዷል፡፡  
ሉቨር ሆቴል ግሩፕ ከሚያስተዳድራቸው ሶስት የሆቴል ብራንዶች አንዱ የሆነውን “ጎልደን ቱሊፕ” ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦሌ ከፍቶ እያስተዳደረ ሲሆን “ሮያል ቱሊፕ” የተሰኘው ብራንድ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ድርድር መካሄዱ በስምምነት ፊርማው ላይ ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ድርድሩን ያካሄደው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ቢዝነስ ላይ የተሰማራው “አዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ” መሆኑን የ”ኦዚ ቢዝነስ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጅምነት” ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡
የሆቴሉ በአዲስ አበባ መከፈት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአገሪቱን የጎብኚ ፍሰት ለማስተናገድና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለመስጠት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሚገነባው የልብ ህሙማን ማዕከል የ2.6 ሚ. ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ፡፡ ባንኩ በገና ዕለት የሚተላለፍ የበዓል የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን የበዓሉ ቅድመ ቀረፃም ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በልብ ህሙማን ማዕከል አዳራሽ መከናወኑን የቀረፃውም ምክንያት የገንዘቡ ልገሳ እንደሆነ ባንኩ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባንኩ በልብ ህመም የሚሰቃዩ ጨቅላ ህፃናትን ለመታደግ ከማዕከሉ ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ከዚህ ቀደም ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት የባንኩ ተቀዳሚ ስራ አስኪያጅና ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ በልሁ ታከለ ይህኛው ድጋፍ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገ የልገሳ ልዩ ስነ ስርዓት እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ባንኩ በቀጣይም ለማዕከሉ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

 በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የጉራጌ ተወላጆችን የሚያሳስብና የሚያወያይ የጉራጌ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መድረክ ባለፈው ሳምንት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተመሰረተ፡፡ በምስረታ ስነ-ስርዓቱ ላይ ድምፃዊያን፣ ተወዛዋዦች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ደራሲያን፣ ሰዓሊያን፣ ተዋንያንና ሌሎችም ከመቶ በላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የጉራጌ ተወላጅ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች፤ አካባቢያቸውን ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለቀሪው ኢትዮጵያዊና ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ፣ በሙያቸው ዙሪያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የሚያስችል መድረክ እንዳልነበራቸው በምስረታው የተገለፀ ሲሆን የመድረኩ መመስረት ዋና አላማ፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትና የጉራጌን እምቅ ባህልና አብሮነት በጋራ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተርና ደራሲ ተስፋዬ ጉይቴ ተናግረዋል፡፡
የተመሰረተው መድረክ እስኪጠናከርና በራሱ እስከሚቆም የጽ/ቤት፣ የፋይናንስና መሰል ድጋፎችን የጉራጌ ልማትና የባህል ማህበር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የማህበሩ የባህል ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡
በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ መድረኩን የሚመሩ ሀላፊዎች ምርጫ፣ ስለ መድረኩ የወደፊት ጉዞ ውይይትና የመዝናኛ ፕሮግራሞች የተካሄዱ ሲሆን ድምፃዊያንና ተወዛዋዦች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡

‹‹አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም›› በሚል መሪ ቃል የፋሽን ትርኢት ተካሄደ፡፡ በአካል ጉዳተኛዋ ሳባ ከድር (ሳቤላ) የተዘጋጀውና አካል ጉዳተኞች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ ግንዛቤን ያስጨብጣል የተባለው የአካል ጉዳተኞች የፋሽን ትርኢት፤ ባለፈው ሳምንት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተካሂዷል። የፋሽን ትርኢቱ ማየት በተሳናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪዎች፤ በአካል ጉዳተኛ ሰዓሊዎች፣ በድምፃዊያንና በሌላ ሙያ ላይ ባሉ አካል ጉዳተኞች የቀረበ ሲሆን የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ዲዛይነሮችም ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በትርኢቱ ላይ በአካል ጉዳተኝነት ላይ አተኩረው የሚሰሩ እውቅ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች ማርታ ደጀኔና ተስፋዬ ገ/ማሪያም በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን፡፡ አካል ጉዳተኛዋ ወ/ሪት ሳባ ከድር ለታዳሚው ተሞክሮዋን ከማቅረቧም በተጨማሪ ራሷ ፅፋ ያዘጋጀችውን ‹‹ማስተዋል›› የተሰኘ የ8 ደቂቃ ፊልም ለእይታ አቅርባለች፡፡ በቀጣይም በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያለውን አመለካከት ለመለወጥ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልፃ ለዚህ ህልሟ እውን መሆን ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች፡፡

Friday, 06 January 2017 12:11

የህይወት ጥግ

· ህይወት በጣም ቀላል ነው፤ እኛ ግን ልናወሳስበው እንታገላለን፡፡
      ኮንፉሺየስ
· ሞትን መፍራት ህይወትን ከመፍራት ይመነጫል፡፡ ህይወትን በቅጡ የኖረ ሰው በማንኛውም ጊዜ ለመሞት ዝግጁ  ነው፡፡
     ማርክ ትዌይን
· በራስህ የማትተማመን ከሆነ በህይወት ሩጫ ሁለቴ ትሸነፋለህ፡፡
     ማርከስ ጋርቬይ
· የህይወታችን ግብ ደስተኛ መሆን ነው፡፡
     ዳላይ ላማ
· ማንም ሰው ህይወትን የኋሊት አ ይኖርም። ወደፊት ተመልከት፣ መጪው ህይወትህ ያለው እዚያ ነው፡፡
     አን ላንደርስ
· ህይወት ቢስክሊሌት እንደ መጋለብ ነው፡፡ ሚዛንህን ለመጠበቅ እንቅስቃሴህን መቀጠል አለብህ፡፡
     አልበርት አንስታይን
· ህይወት ከባድ ነው፤ ደደብ ከሆንክ ግን የበለጠ ይከብዳል፡፡
     ጆን ዋይኔ
· ዓይንህን ግለጥ፤ ወደ ውስጥህ ተመልከት፡፡ በምትመራው ህይወት ደስተኛ ነህ?
     ቦብ ማርሌይ
· በህይወት ብቸኛው አቅመ-ቢስነት አሉታዊ አመለካከት ነው፡፡
    ስኮት ሃሚልተን
· ህይወት ጉዞ ነው፡፡ ስንቆም ነገሮች ትክክል አይመጡም፡፡
    ፖፕ ፍራንሲስ
· ህይወት የተሰራው ከእምነበረድ እና ከጭቃ ነው፡፡
    ናታኔል ሃውቶርን
· እድገት የህይወት ብቸኛ ማስረጃ ነው፡፡
    ጆን ሄንሪ ኒውማን