Administrator

Administrator

Sunday, 28 October 2018 00:00

“ወርደን እናየዋለን!”

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጎረቤታም ገበሬዎች ስለሚዘሩት እህል ይመካከራሉ፡፡
አንደኛው -
“ዘንድሮ ምን ብንዘራ ይሻላል?”
ሁለተኛው -
“በቆሎ ብንዘራስ?”
አንደኛው -
“አዬ በቆሎ አይሆንም፡፡ በቆሎ በቀላሉ በእንስሳቱ ስለሚጫር አያስተርፉልንም፡፡”
ሁለተኛው -
“እንግዲያው ባቄላ ይሁና?”
አንደኛው -
“አዬ እሱማ አልሸሹም ዞር አሉ ነው”
ሁለተኛው -
“ካልሆነ ማሽላ ይሁና?”
አንደኛው -
“ማሽላ ደግሞ ገና ከመሬት ብቅ ሳይል የወማይ ወፍ መጫወቻ መሆኑ ነው፡፡”
ሁለተኛው -
“አሁን እኛን በጣም የሚያስፈራን እህሉ ከመሬት ብቅ ሳይል ተጭሮ መበላቱ ነው እንጂ ከበቀለማ በኋላ ጠባቂ እናስቀምጥለታለን፡፡”
አንደኛው -
“ይልቅ አንድ ዘዴ ታየኝ”
ሁለተኛው -
“ምን ታየህ?”
አንደኛው
“ወጣም ወረደ የሚያስቸግሩን ዝንጀሮና ጦጣ ከሆኑ፣ መንገዳችን ላይ አንዳቸውን ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ያልዘራነውንና ለእነሱ የማይመቻቸውን እህል ጠቅሰን ለምን አናታልላቸውም?”
ሁለተኛው -
“በጣም ድንቅ መላ ነው”
በዚህ ተስማምተው በቆሎ ዘርተው ሲመለሱ፣ ጦጢት ዛፍ ላይ ሆና አገኙዋት፡፡
ጦጢት
“አያ ገበሬ?”
ገበሬ
“እንዴት ከርመሻል ጦጢት?”
ጦጢት
“ዘንድሮ ምን ዘርተህ መጣህ?”
ገበሬ -
“ተልባ፡፡ ተልባ ዘርቼ መጣሁ፡፡”
ገበሩው ይሄን ያለው ጦጣ ተልባ ጭራ ማውጣት እንደማትችል ስለሚያውቅ ነው፡፡
ጦጢትም፤
“ይሁን፡፡ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
***
እኛ ስለ ሌሎች ደካማ ጎን ስናስብ፣ እነሱስ ስለኛ ደካማ ጎን ምን ያስባሉ? ብሎ ማሰብ ከብዙ ስህተት ያድነናል፡፡ አስቀድሞ ነገር በሌሎች ደካማ ጎን በመጠቀም ዕድገትን ማሰብ ተላላነት ነው፡፡ “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚለውን ተረት ማጤን እጅግ ተገቢ የሆነበት ወቅት ላይ መሆናችንን እናስተውል፡፡ ክልልና ክልል፣ ፓርቲና ፓርቲ፣ ድርጅትና ድርጅት፣ ቡድንና ቡድን ቀና ውድድር ቢያደርጉ እንጂ በመሻኮትም ሆነ በመጠላለፍ ከቶም ትርፍ አያገኙም፡፡ ቀና ያልሆነውን መንገድ ለዘመናት እንደማያዋጣን አይተነዋል፡፡ በጠረጴዛ ውይይት ካልሆነ የማይፈቱ አያሌ ችግሮች እንዳሉብን እየታወቀ፤ መልሰን ግጭትና ሴራ ውስጥ መዘፈቅ ውሃ ወቀጣ ከመሆን አይዘልም፡፡
“እኛ ሳንስማማ
እኛ እየተባላን
መቼም ሳንቻቻል
እንኳን ሰማዩና መሬቱም ይርቃል!”
ስለ ሰላም እያወራን፣ ስለ ፍቅር እየሰበክን፣ ስለ እርቅ እያወሳን ወዘተ … መልሰን ከተጋጨን የተጫረው ብርሃን ይጨለመለማል፡፡ የለኮስነው ቀንዲል ይጠፋል፡፡ ያቀድነው ዲሞክራሲ፣ እናጠራዋለን ያልነው ፍትህ ሁሉ
“ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ይሆንብናል፡፡
ምንም እንኳ የተያያዝነው የለውጥ ሂደት ዕድሜው አጭር ቢሆን፣ ገና ዳዴ እያልን ነው ብለን ስህተት እያየን እንደ ፍጥርጥሩ ማለት አንችልም፡፡ ባወጣ ያውጣው ብለን ጥፋትን ሳንዳኝ፣ ችግርን በሰዓቱ ሳንፈታ መጓዝ “ሃማሊያን በሁለት ቆራጣ እግር” እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡ ገና ብዙ ዳገት እየጠበቀን ሜዳው ላይ ከደከምን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆናል፡፡ ከውጪው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ስምምነት መፈራረማችን በጎ ጎናችን የሆነውን ያህል፤ የውስጥ ችግራችንን በወቅቱ አለመፍታት አገርን ስጋት ላይ መጣል ነው፡፡ ችግራችን ከላይ ከላይ እንደሚወራውና የሚለባበስ ነገር አይደለም፡፡ ግልጥ ያለና አስጊ ነው፡፡ እንደ ጦጣዋ “ወርደን እናየዋለን” ማለት ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለእኛው ነውና፣ መሬት የረገጠ ነገር እንሥራ፡፡
ዛሬም፤
“… ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ” ብንል ይሻላል!
ልዩ ልዩ ሹመቶች እየተሰጡና ተቋማት እየተጠናከሩ መሆኑ ደግ ነገር ነው፡፡ ሹመኞች ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ አይወጡም የሚለው መለኪያው ጊዜ ቢሆንም ቢያንስ ሙስና ውስጥ አይዘፈቁም የሚል ዕምነት አለን፡፡ ተስፋችን ትልቅ ነው፤ ጉዞው ጠመዝማዛ ነው - ጥናቱን ይስጣችሁ ማለት የአባት ነው!

• ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣል የተባለ መሪ ዕቅድ እንዲተገበር ተወስኗል
• ኅብረቱ በትግበራው ለመሳተፍና እስከ ግንቦት ለውጡ እንዲታይ ጠይቋል

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመዋቅርና የአሠራር ችግሮች ኹነኛ መፍትሔ በመስጠት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውና በአምባሳደር ካሳ ከበደ
የሚመራው የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ኅብረት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፊት ቀርቦ የአስተዳደር ለውጥ አቋሙን አስረዳ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ
ምላሽ እንደሚሰጥ ለኅብረቱ ተወካዮች አስታውቋል፡፡ የብዙ ሺሕ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ምእመናን ተወካዮች የኾኑና በአምባሳደር ካሳ ከበደ የሚመሩ 9 የኅብረቱ ልኡካን፣ ትናንት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ በመመራትና የምእመናንን ከፍተኛ ተሳትፎ በማረጋገጥ ማምጣት ስላለባት አስተዳደራዊ ለውጥ ያላቸውን አቋም በመካሔድ ላይ
በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ማስረዳታቸውን ምክትል ሰብሳቢው አርክቴክት ዮሐንስ መኰንን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ “ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ የካህናትንና የምእመናንን አቤቱታ ስለማቅረብ” በሚል ርእስ በንባብ በተሰማው ጽሑፍ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች በጥናት የተደገፈ አስቸኳይ እርምት አለመስጠት፣ ተግባራዊ እንዲኾኑ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጥናቶች አስፈጻሚ ማጣትና በስፋት አለመታወቅ ሁከትና ብጥብጥን እያስፋፋና ለህልውናዋ ቀጣይነትም አደጋ እያስከተሉ እንደኾነ ተጠቅሷል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአሁኑ ስብሰባው፣ ለቤተ ክርስቲኒቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ የኾነው የመሪ ዕቅድ ጥናት፣ የትግበራ ጽ/ቤት ተቋቁሞለት ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑና የ2.5 ሚሊዮን ብር መነሻ መመደቡን ኅብረቱ አድንቆ፣ በትግበራው ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ መመሪያ ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል ያላቸውን አምስት ዋና ዋና ጥያቄዎቹን ማቅረቡን አርክቴክት ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡
የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤቱ መቋቋሙን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አካል ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከባለሞያ ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ ስብሰባው እንዲሠይም፤ ጽ/ቤቱ  ከሚቀጠሩለት መደበኛ ባለሞያዎች ባሻገር አስፈላጊውን የሰው ኃይል ማሟላት እንዲችልና ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ ሙሉ ነፃነትና ሥልጣን እንዲሰጠው፤ አባላቱም እንደ ሞያቸው  በባለቤትነት መሳተፍ እንዲችሉ ኅብረቱ ጠይቋል፡፡ መሪ ዕቅዱ ቢያንስ፣ በግንቦት ወር እስከሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ድረስ ዋና መሥሪያ ቤት በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤትና የአህጉረ ስብከት ማዕከል  በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃ ተተግብሮ የለውጡ ተስፋና ምልክት መታየት እንዲጀምር ኅብረቱ አመልክቷል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ በየዓመቱ በሚካሔደው አጠቃላይ ጉባኤ  ላይ የምእመናን ውክልና በሕጉ መሠረት እንዲጠበቅና የምእመናን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የሚረጋገጥበት ሥርዐትና አሠራር በሚዘረጋበት ኹኔታ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ
እንዲመክር ኅብረቱ ጠይቋል፡፡
የኅብረቱን ጥያቄዎች ምልዓተ ጉባኤው እንደሰማ የገለጹት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ ውሳኔውን እንደሚያስታውቅ
መናገራቸውን የኅብረቱ ልኡካን ገልጸዋል፡፡
ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም፤ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ የሚገዳቸው ከፍተኛ ኤክስፐርቶች በሦስት ጥራዝ
አጥንተው ያቀረቡት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማዘመኛ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እንዳይተገበር ለውጡን በማይፈልጉ አካላት ታግዶ መቆየቱን የኅብረቱ
ም/ሰብሳቢ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

   (“ዘ ያንግ ክሩሴደር”)
 የመጽሐፉ ርዕስ- “ዘ ያንግ ክሩሴደር”
 ደራሲ- ሰለሞን ኃይለ ማሪያም
 የገጽ ብዛት - 220
 ሒሳዊ አስተያየት - በተሾመ ብርሃኑ ከማልበደራሲ ሰለሞን ኃይለማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› (ማህበራዊ ንቅዘትን በወኔ የተፋለመው ወጣት) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ተደርሶ፣ በ2003 ዓ.ም በኮድ ኢትዮጵያ ለህትመት የበቃው መጽሐፍ፤ በ2010 ዓ.ም ወደ ጀርመንኛ ለመተርጎም በቅቷል፡፡ መጽሐፉ ወደ አማርኛ ከመተርጎሙ በፊት ወደ ጀርመንኛ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ የሚገርም ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ደራሲ የተጻፈና ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ትምህርታዊ ከመሆኑ አንጻር፣ ይህን የሥነ ጽሁፍ ሥራ በመገምገም እግረ መንገድም ማስተዋወቅ  ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

የመጽሐፉ መጠንሰስ
በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ላይ ኮድ ኢትዮጵያ እና ኮድ ካናዳ የተባሉ አጋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ዕድሜያቸው ከ12-18 ለሆኑ ወጣት አንባቢያን የሚመጥን የልቦለድ ታሪክ (የስነጽሑፍ) ውድድር አዋጅ ያስነግራሉ፡፡ ተወዳዳሪዎች  የሚያቀርቡት የልቦለድ ሥራ፤ ከዘመኑ ማኅበራዊ  ሕይወት ጋር የተዛመደ፣ ወጣቶች የማህበረሰቡ አባላት በመሆናቸው፣ በአፍላ ዕድሜያቸው ፊት ለፊት የሚጋፈጡት የማህበራዊ ሕይወት ቀውስ ፈተና ምን እንደሚመስል  የሚያንጸባርቅ  ወይም በሀገሪቱ ማህበራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ታስቦ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያሳስብ ነበር- የውድድር መመሪያው፡፡
ደራሲ ሰለሞን ኃይለ ማሪያም፤ ይህንን የውድድር መመሪያ ከመረመረ በኋላ ተልእኮው የማህበረሰቡን ቁስል ማወቅና የማህበራዊ ጠንቁን ዓይነት፣ ምንነት፣ ስፋትና ጥልቀት መጠቆም ብቻ ሳይሆን መፍትሔው ምን እንደሆነ ለመጠቆምም ውድድሩ መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት ይመስላል፡፡ በዚያ ወርቃማ አጋጣሚም፣ በደራሲው ውስጥ ሲብሰለሰል የኖረው ማህበራዊ ንቅዘት፣ አድማሱ ስዩም ብሎ በቀረጸው ዋነኛ ገጸ ባህርይው አማካኝነት መፍሰስ ጀመረ፡፡

ታሪኩ
አድማሱ የተባለው ዋነኛ ገጸ ባህርይ፣ ገና ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ወደ ሥራ ዓለም እስከ ተሰማራበት ጊዜ ድረስ ሙሰኝነትን የተዋጋ ቅን ዜጋ ነው፡፡ ተማሪ ሳለ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ፣ ሰዎች የተፈጨ በርበሬን ከደቀቀ ጡብ ጋር እየቀላቀሉ ለሽያጭ ሲያዘጋጁ ይመለከትና፣ ለፖሊስ ይጠቁማል። ይህም በጓደኞቹ ዘንድ እንዲታወቅና መልካም አርአያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ጉቦ እየተቀበሉ፣ መጠኗ አነስተኛ በሆነች ክፍል ተጨናንቀው ምን እንደሚያደርጉ  ይገነዘብና፣ ያንን አሳፋሪ ተግባር ያጋልጣል፡፡ የርዕሰ መምህሩም ጉዳይ በአድማሱ ጥቆማና ክትትል  ወደ ወላጅ ኮሚቴ ቀርቦ ከሥራቸው  ይባረራሉ፡፡ አድማሱ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ በአንድ ዕቃ መለዋወጫ መሸጫ መደብር ሲቀጠርም፣ አጭበርባሪዎች ይገጥሙትና፣ ፊት ለፊት ተጋፍጦ፣ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል፡፡
ይሁንና በሕይወት የሚገጥምን ፈተና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማለፍና በአሸናፊነት የመወጣት ጉዞ  አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲል  በጀግንነት በመታገሉ ሊያሸልመው፣ ሊያስመሰግነውና ሊያስከብረው ሲገባ በሐሰት መረጃ ይወነጀላል። በዚህም ብዙ  እንግልት ይደርስበታል፡፡ ሆኖም  የሚገጥመውን ፈተና በጽናት  ይወጣዋል፡፡
ከካበተ የሕይወት ልምዳቸውና ዕውቀታቸው የሚያካፍሉት የገነተ ልዑሉ የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሽማግሌው አቶ ንጋቱ፤ በአድማሱ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ያለ ማቋረጥ በመለወጥ ላይ በምትገኘው ዓለም ውስጥ እራስን ከለውጡ ጋር አስማምቶ መጓዝ፣ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ  መሆኑን ከምሁሩ አንደበት እንገነዘባለን፡፡ ስለ ቤተሰብ ምጣኔ፣ ራዕይ ስላላቸው ወጣቶችና ፊት ለፊት የሚጠብቃቸውን የሕይወት ፈተና እንደምን ተጋፍጠው ድል እንደሚያደርጉት መጽሐፉ አቅጣጫ ያመላክታል፡፡

የልቦለዱ ጭብጥ
ታሪኩ የሚፈጸመው በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ሲሆን ዘመኑም ያለንበት ነው፡፡ የታሪኩ ምንጭም በማህበራዊ ንቅዘት የተዘፈቀው ህብረተሰብ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋነኛ ጭብጥ፤ ማህበራዊ ንቅዘት ለእድገታችን ጸር ነውና እንዋጋው፣ ወደዚህም የውጊያ መስክ ነገ ኃላፊነትን የሚረከበውን ወጣት ትውልድን አስገብተን፣ በለጋ ዕድሜው በማሰልጠን፣ በደመ ነፍስ ሳይሆን በስልት እንዲዋጋው እናስችለው በሚል መሠረታዊ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጋናዊው ደራሲ አርማህ፤ ‹‹ዘ ቢዩቲፉልስ አር ኖት የት ቦርን›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) በሚል ርእስ እ.ኤ.አ በ1968 ለንባብ ባበቃው መጽሐፉ፣በወቅቱ የነበረውን ማህበራዊ ንቅዘት እንዳሳየውና ካሜሩናዊው ደራሲ ፈርዲናንድ ኦዮኖ፤ «ቦይ» ወይም «ዘ ሐውስ ቦይ» በተሰኘው መጽሐፉ፤ የነጮችን ደካማ አስተሳሰብ እያዋዛ እንደሚተቸው ሁሉ፣ ሰለሞንም እያዋዛ ማህበራዊ ሕጸጻችንን ሊነግረን ይሞክራል፡፡ «ዘ መኒይ ኦርደር» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፈው ሴኔጋላዊው ደራሲ ዑስማኔ ሰንባኔ «ኒው ዮርክ ታይምስ» እና «ታይምስ» ከመሳሰሉ መጽሔቶች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገር፤ «ያደረግሁት ነገር ቢኖር አፍሪካውያን ያልተገሰሰ ድንግል የኪነ ጥበብ ሐብት በውስጣቸው እንዳላቸው ማሳየት ነው፤ መቸም አንድ ሰው ሲፈጥር አገሩን እንጂ ዓለምን እያስተነተነ አይፈጥርም። በመሠረቱም በአፍሪካ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት አፍሪካውያን እንጂ አሜሪካዊያን ወይም ፈረንሳውያን ወይም ሩሲያውያን ወይም ቻይናውያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡» ብሏል፡፡ ሰለሞን ኃይለማሪያም በመጽሐፉ ያሳየን ይህንኑ ነው፡፡  
የመገምገሚያ አውድ
በመሠረቱ፣ በሀገራችን ያለው ማህበራዊ ንቅዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። አንድ ህጻን ልጅ ለመላክ መደለያ በመስጠት ይጀመራል። በትምህርት ቤት ‹‹ካስኮረጅከኝ ይህን አደርግልሃለሁ›› በሚል ይቀጥላል፡፡ “የሚያስፈራራኝን ከመታህልኝ ገንዘብ ከየትም አምጥቼ እሰጥሃለሁ” ወደሚል የሚታለፈውም በልጅነት ዘመን ነው። በቤት ብቻ ሳይሆን በጎረቤት፣ በቀበሌ፣ በመንደር፣ በትምህርት ቤት በመደለያ፣ በጉቦ፣ በሸፍጥ፣ አስመስሎ በመንገርና በማስመሰል የሚታዩ፣ የሚሰሙና የሚደረጉ ብዙ ማህበራዊ ህጸጾች አሉ፡፡  እድሜ ከፍ እያለ በሄደ መጠን የማህበራዊ ቀውሱ ዓይነትና መጠን እያደገ እንደሚሄድም አያጠያይቅም፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባቀረበው አንድ የታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደጠቆመው፤ «ጉቦ» ለሚለው ቃል አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ «ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን ዕውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚበረከት መማለጃ ነው፡፡ ስለሆነም ጉቦ በስጦታም ሆነ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁአን ሁሉ ብፅእ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ፣ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ፣  ዞሮ ዞሮ ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈንና ፍርድን ለመገምደል የሚያገለግል ማህበራዊ ንቅዘት ከመሆን አያልፍም» ሲል ፍቺውን ከእነ ማብራሪያው ይሰጣል፡፡  
ይህንኑ ቃል ዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርብር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥልጣን ኃላፊነቱን እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት ስጦታ ውለታ፣ ወዘተ በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነገር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በሌላ መዝገበ ቃላት ትንታኔ፤ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ» ማለት ሲሆን በቀጥታ እኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን «ይሆናል»፣ የሚሆነውን «አይሆንም» በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወስድ፣ ጉቦ የራስ ሀቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታን በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበርና ማታለል መሆኑን ያብራራል፡፡
በርግጥም መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ዘንግቶ ሥልጣኑን ለሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል ሲገባው የራሱን ጥቅም የሚያሳደድ ከሆነ፣ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጡ በስተቀር ጫካ ከገባ ወንበዴ፣ ጨለማን ተገን አድርጐ ቤት ከሚሰረስር ሌባ፣ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር አድርጐ ከሚዘርፍ ነጣቂ፣ የሰው ኪስ ከሚገባ ሞሽላቃ ሌባ ሊለይ አይችልም፡፡ ጉቦ በጉልተኛው ሥርዓት መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ፣ ጉርሻ፣ ወዘተ የወግ ስሞቹ ሲሆኑ መደለያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ ወዘተ የሐሜት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡ የማዕረግ ስሞቹ ደግሞ አመኃ፣ ገፀ በረከት፣ ሙገሳ፣ ውደሳ፣ ቅደሳ፣ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ማስታወሻ፣ መታሰቢያ፣ ስጦታ--- የሚሉት ደግሞ ከቁልምጫ ስሞቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ «የመንግሥት ገቢን የሚሰበስብ ባለሥልጣን ማር የፈሰሰበት ምላስ» የሚል የህንዶች ተረት ይጨመርበታል፤ «ተሹሞ የማይበላ ተጥዶ የማይፈላ የለም» የሚል የአገራችንን አባባልም ይጠቀሳል፡፡ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» ተብሎም እንደ ትልቅ ነገር አዋቂ ተብዬዎች በምክር ስም የሚሰጡት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡
ሥነ ጽሁፋዊ ውበት
ምንም እንኳን ድርሰቱ ያነሳው ጭብጥ  ጠንካራና መረር ያለ ቢሆንም በውብ ቋንቋና ተጀምሮ እስኪያልቅ ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ የአተራረክ ሥልት በመቅረቡ ተነባቢና ተወዳጅ ሊሆን በቅቷል፡፡ ለሽልማት የበቃውም ሆነ በሌላ ቋንቋ ለመተርጎም የታደለው አንድም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥም የተደራሲውን  ስሜት ጨምድዶ ካልያዘ፣ የታሰበለትን ግብ ከቶ ሊመታ አይችልም፡፡
ደራሲው ማነው?
ደራሲው ሰለሞን ኃይለማሪያም በ220 ገጾችና በ29 ምዕራፎች ከፋፍሎ፣ ድርሰቱን  ውድድሩን ላዘጋጀው ለኮድ ኢትዮጵያ  ያቀርባል፡፡ ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› የሚል ርዕስ የሰጠው የልቦለድ ሥራውም አንደኛ ይወጣና የበርት ሽልማት ድርጅት በአፍሪካ የአሸናፊነት የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ያገኛል፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ጀርመንኛ የተተረጎመ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ አታሚዎች ታትሞ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያና እና በሱዳን የመጻህፍት መደብሮች ለሽያጭ ቀርቧል። አማዞን የተባለው የኢንተርኔት ገበያም በዲጂታልና  በሕትመት ለአንባቢያን አቅርቦታል፡፡ በሀገራችን ብዙም ባይታወቅም  በሜጋ አሳታሚና አከፋፋይ እንዲሁም በዩኒቨርሳል መጻሕፍት መደብር ይገኛል፡፡
ሰለሞን ኃይለማሪያም የተወለደውና ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡ በተጨማሪም ለቪኦኤና ቢቢሲ ኮረስፖንደንት ሆኖ ሰርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተቋቁሞ የነበረው ፔን ኢንተርናሽናል የተባለ የስነጽሑፍ ክበብ ፕሬዚደንት በመሆንም አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር በካናዳ ይኖራል፡፡ ደራሲው “ላቭ ኤንድ አንዛይቲ” የተሰኘ መጽሐፍም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ የበርት አዋርድ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል። እ.ኤ.አ በ2016 እና 2017 የጻፋቸው የአጫጭር ልቦለድ መድበሎችም የተደነቁለት ሲሆን የተወሰኑት ሥራዎቹም  ወደ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ስዊድንኛ ተተርጉመውለታል፡፡
እንዴት ወደ ጀርመንኛ ተተረጎመ?
ሰለሞን ኃይለ ማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› በሚል ርእስ የጻፈው ልብወለድ መጽሐፍ  በአንድ አውስትሪያዊ ደራሲ እጅ ይገባና የመነበብ ዕድል ያጋጥመዋል፡፡ በአጻጻፍ ውበቱና በታሪኩ የተሳበው ሔልሙት ኤ ናይደር፤ ወዲያው ወደ ጀርመንኛ ተረጎመውና ለህትመት በቃ፡፡ ወደ አማርኛ ግን እስካሁን አልተተረጎመም፡፡  
በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት፣ መጀመርያውኑ ድርሰቱ በአገር ውስጥ  ቋንቋዎች ቢጻፍ፣ ያም ባይሆን ደግሞ ወዲያው በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ቢተረጎም መልካም ነበር፡፡ አሁንም የመጽሐፉ ትምህርታዊ ፋይዳው ከግምት ውስጥ ገብቶ፣ በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ቢካተት ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢንተርኔት ቁልፍ ሰባሪዎች የ29 ሚሊዮን ያህል የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንቶች ሰብረው በመግባት መረጃዎቻቸውን መመንተፋቸውን ዴችዌሌ ዘግቧል፡፡
መረጃ መንታፊዎቹ፣ የፌስቡክ ተጠቃሚዎቹን ስም፣ የኢሜይል አድራሻና የስልክ ቁጥሮች ጨምሮ ሌሎች ድብቅ መረጃዎች ፈልፍለው ማግኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ፌስቡክ ኩባንያ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ደንበኞቹ የማስጠንቀቂ መልዕክቶችን እንደሚልክ ማስታወቁንም አመልክቷል፡፡
በቅርቡ በተደረጉ ተመሳሳይ የመረጃ ምንተፋዎች ሰለባ ከሆኑት የፌስቡክ አካውንቶች መካከል፣ የኩባንያው መስራች የማርክ ዙክበርግ አካውንት አንዱ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 የላይቤሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ጸጉራቸውን ቀለም የሚቀቡና ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጸጉር ለማስረዘም ሲሉ ሰው ሰራሽ ጸጉር ወይም ዊግ የሚቀጥሉ ሴት ሰራተኞቹን እንደሚቀጣ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ሴቶች ጸጉራቸውን እንዳያቀልሙና ዊግ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ህግ ከወጣ አራት አመታት ያህል ቢሆነውም፣ የመንግስት ተቋማት ህጉን ተግባራዊ ሳያደርጉት እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ግን ከሰሞኑ ድርጊቱን በሚፈጽሙ ሰራተኞቹ ላይ ቅጣት እንደሚጥል ማሳሰቡን አመልክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ሰራተኞቹን ማስጠንቀቁን ተከትሎ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በማህበራዊ ድረገጾችና በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ህጉን ከአባታዊ ባህል የመነጨ አግባብነት የሌለው ጾታዊ መድልዖ ሲሉ መተቸታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ ሴቶች  ቀለም መቀባታቸውም ሆነ ዊግ ማድረጋቸው በስራ ገበታቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የለውም፣ ምንም አይነት መሰረት የሌለው ያልተገባ ክልከላ ነው ሲሉም ተቃውሟቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ላይቤሪያውያን ሴቶችን የጸጉር ቀለምና ዊግ አጠቃቀም የሚከለክለው ህጉ የወጣው በቀድሞዋ የአገሪቱ መሪ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የስልጣን ዘመን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፈው አመትም በጸጉር ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉን አስታውሷል፡፡


የኢንተርኔት አቅርቦትን በእኩልነት መጠቀም ለደቡብ አፍሪካውያን ዜጎች እንደ አንድ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መቆጠር እንዳለበት ሚዲያ ሞኒተሪንግ አፍሪካ የተባለ ተቋም ጠይቋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዊሊያም በርድ ለአገሪቱ መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ለደቡብ አፍሪካውያን ሰብዓዊ መብት መሆን እንደሚገባው መናገራቸውን ሜይል ኤንድ ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት በተለይ ለድሃ ዜጎቹ መረጃዎችን የሚያገኙበትና የሚለዋወጡበት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ያለምንም ገደብና መቋረጥ ካላቀረበ፣ አገሪቱ ወደ አፓርታይድ ዘመን መመለሷ አይቀሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ እጅግ ውድ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ሃብታሞች ገንዘብ ከፍለው ቢጠቀሙም ከአገሪቱ የህዝብ ቁጥር አብላጫውን የሚይዙት ድሃ ዜጎች ግን አገልግሎቱን ለመጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ከ4.4 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶባቸዋል


    በአለማችን የተለያዩ አገራት ባለፉት 20 አመታት የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት 1.3 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 56 በመቶው በርዕደ መሬትና በሱናሚ ሳቢያ የሞቱ መሆናቸውን ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሞት ከዳረጓቸው ሰዎች በተጨማሪ በ4.4 ቢሊዮን ሰዎች ላይ የመቁሰልና ከመኖሪያ መፈናቀልን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውንም አመልክቷል፡፡
የተፈጥሮ አደጋዎች በአለማችን ህዝቦች ላይ የሚያስከትሉት ሁለንተናዊ ጉዳት ባለፉት 20 አመታት በ151 በመቶ ያህል መጨመሩን የገለጸው ሪፖርቱ፤ በአለማችን የተለያዩ አገራት ርዕደ መሬት፣ እሳተ ገሞራ፣ ጎርፍና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ያስከተሉት ውድመት 2.9 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚገመትም አብራርቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተፈጥሮ አደጋዎች 944 ቢሊዮን ዶላር ያህል ያወደሙባት አሜሪካ፣ ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆነ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የገጠማት የአለማችን ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድና ፖርተሪኮ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡


    “አዲስ አበባ በልጆቿ መመራት አለባት” በሚል በአሁኑ የከተማዋ አመራር ላይ አሲረዋል ተብለው የታሰሩት የህግ ጠበቃና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው አቶ ሄኖክ አክሊሉ፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ፡፡
ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሌላው ታሳሪ አቶ ሚካኤል መላኩ መታሰር፤ አሁንም በሀገሪቱ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ተሟልተው እየተከበሩ እንዳልሆነ ጉልህ ማሳያ ነው ብሏል የሰብአዊ መብት ተቋሙ፡፡
“እስሩ መንግስት የጀመረውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት እንቅስቃሴን በእጅጉ የሚጎዳ ነው” ያለው አምነስቲ፤ “ፖሊስ የመብት ተሟጋቾችን ከማሰር ይልቅ መብታቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀሙበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል” ብሏል፡፡
በሀገሪቱ ሃሳብን የመግለፅና የመደራጀት መብት ተሟልቶ እንዲከበር መንግስት ያለውን ቀናኢነት ሁለቱን ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር በመፍታት ማሳየት አለበት ብሏል - አምነስቲ ኢንተርናሽናል፡፡
ለበርካታ የሽብር ተከሳሾች በነፃ ጭምር ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ፤ “አዲስ አበባ በልጆቿ ብቻ ነው መመራት ያለባት” ሲሉ አሲረዋል በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤት አስታውቋል፡፡
ረቡዕ እለት በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ተጠርጣሪው፤ ሐሙስ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን “የክፍለ ሃገር ልጅ አዲስ አበባን ሊመራ አይገባም” በሚል ወጣቶችን በመቀስቀስና በማደራጀት፣ እንዲሁም ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና ስልጠና ወስደዋል በሚል መታሰራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡
ከህግ ባለሙያውና ጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ጋር የታሰሩት አቶ ሚካኤል መላኩም፤ በተመሳሳይ ድርጊት መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አስረድቷል። በተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ፖሊስ ተጨማሪ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)፤ የታሰሩበትን ክፍል መስኮት በመስበርና ከጥበቃ ጋር በመተናነቅ የማምለጥ ሙከራ አድርገው ነበር ሲል ፖሊስ ትናንት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተናገረ ሲሆን ግለሰቡ ግን ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ለችሎቱ መግለጻቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
አብዲ ሞሃመድ ኡመር፤ በምርመራ ወቅት ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንደነበረባቸውና የአእምሮ ጤና ችግር ካለበት አንድ ታሳሪ ጋር በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረው እንደነበር ለችሎቱ አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ፣ ግለሰቡ የጤና ችግር እንዳለባቸው በመግለጻቸው ለቢሮ በሚያገለግል ክፍል ውስጥ ታስረው እንደነበርና የማምለጥ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ግን፣ ወደ መደበኛ የእስረኞች ክፍል ተዛውረው ለብቻቸው እንዲታሰሩ ተደርጓል ማለቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ሰውዬው ከሰፈሩ ሁሉ በምስኪንነቱ የታወቀ ነው፡፡ ዓመት በዓል በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ አንዱ ይመጣና፤
“ጋሽ ሰመረ፤ በዚህ በዓል ምን ልታርድ ነው ያሰብከው?”
ጋሽ ሰመረም፤
“ካገኘሁ በሬ፣ ካላገኘሁ አንዲት ጫጩት አላጣም!”
ሁለተኛው መንደርተኛ በቀጣዩ በዓል ይጠይቀዋል፤
“ጋሽ ሰመረ፤ በቀጣዩ በዓልስ ምን ልታርድ አስሃበል?”
ጋሽ ሰመረ፤
“በሬ፣ ፍየል፣ በግ … ከጠፋ አንዲት ጫጩት!”
በዓሉ ይመጣል፡፡ አንድ ጫጩት ያርዳል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ብዙ ጫጩት እያረደ ከበላ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን ሞላለትና አንዲት ኮስማና በግ ገዛ፡፡
በመንደሩ እየተዘዋወረ፤ የየቤቱን በር እያንኳኳም፤
“በግ ያየህ ና ወዲህ በለኝ!
በግ ያየህ ና ወዲህ በለኝ!...” ይል ጀመር፡፡
“አላየንም!” ይሉታል፡፡
ለካስ ጋሽ ሰመረ፤ በጓ ጠፍታበት ሳይሆን አንደኛው ግቢ ውስጥ በአጥር ወርውሯት ኖሯል፡፡
መዘዋወሩን የቀጠለው ግን በሌሎቹ ግቢዎች አቅጣጫ ነው፡፡ ጋሽ ሰመረ በግ እንደገዛ ሰፈሩ ሁሉ ማወቅ አለበታ!
በመጨረሻ በጓን የወረወረበት ግቢ ዘንድ ሲደርስ ሰውነቱ ዛል ብሏል፡፡
በር አንኳኳና ተከፈተለት፡፡
“ማነው?” አሉ፤ አንድ አሮጊት ሴትዮ፡፡
“እኔ ነኝ፡፡ እዚህ ግቢ በግ ገብታብኝ ነበር፡፡ ባለበጉ ነኝ!”
“ውይ ይቺ አቃስታ አቃስታ ክልትው ብላ የሞተችው በግ ያንተ ኖራለች እንዴ?”
ጋሽ ሰመረም፤
“ገደላችኋት? በምን መታችኋት ነው?”
"ደሞ በምን ትመታለች? ለራሷ ኮሳሳ? … እንደመሰለኝ በአጥር የወረወርካት ጊዜ አጥሩ ወግቷት ነው ደሟ አልቆ የሞተችው! … በል ጓሮ ዙርና ሬሳህን ተሸክመህ ሂድ!”
ጋሽ ሰመረም፤
“አይ እማማ! እጄን በጄ ነው በሉኛ!”
አሮጊቷም፤
“አይ ልጄ፤ አሁን ንዴቱም፣ ፀፀቱም አይጠቅምህም! ሚስጥሩ በእኔና ባንተ ማህል ይቆይና፤ አልሞተችም በጌ ብለህ አስበህ በሥነ ስርዓት ይዘሃት ሩጥ!” አሉት፡፡
***
የሞተውን አለ፣ ያለውን ሞቷል ከማለት ያውጣን!
ማስተዋል ያነሰው አድናቆትም፣ ማስተዋል ያነሰው ተቃውሞም ሁለቱም መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ታላቁ ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ”
ይለናል፡፡ በትኩስ ስሜት ውስጥ የሚሰራ ስራ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄ ፋታ ሊሰጠን ይችል ይሆናል እንጂ ዘላቂ ድል አያስገኝም፡፡ መሰረታዊ ድህነትን አስወግዶ መሰረታዊ የህይወት ለውጥን አያመጣም! እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን ተሸክማ የኖረች አገር፤ አብዛኛው ሰቆቃዋ የሚመነጨው ከኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማጣት ነው፡፡
“ድህነት በአፍ አይገባም” የሚለን ሎሬት ፀጋዬ “ማጣት፤ በነብስህ ጫፍ ተንጠራርተህ ሩቅ አልመህ ሁሉን መሳት” ይለናል፡፡ ነጋ ጠባና ለዘመናት ስለ ኢኮኖሚ ውድነት ማውራት የህዝብ መዝሙር እስኪመስል ድረስ ለምደነዋል፡፡ መፍትሄ ሳያገኝ የቆየ ችግር ደግሞ፣ ምንም ያህል ቢድበሰበስ፣ ቀን ቆጥሮ አመርቅዞ እጥፍ ድርብ ሆኖ ብቅ ይልብናል፡፡ ለአንድ ሰሞን የሥጋ ዋጋ ቀንሰናል ብለን ስናበቃ፣ ዛሬ የት እንደደረሰ ማስተዋል ነው፡፡ በቀን ሶስቴ እንመገባለን ብለን፣ ዛሬ ስንቴ እንደምንመገብ ልብ ማለት ነው፡፡ “ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ” የምንልባት አገር መሆን የለባትም፡፡ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል፤ ሽሮ አበድሪኝ" ማለትም የአፍ አመል ሆኖ ቀሪ ነው!
የኢኮኖሚ ሙያ ምሁራኖቻችን ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው፤ “ከእንግዲህ አንራብም!” ብለው ሀሞታቸውን መረር አድርገው፣ እንደ ጥንቶቹ አውሮፓውያን ቆርጠው አገር የሚገነቡ ህዝቦች ማየት አለብን ብለው፤ ምርምር ላይ ማትኮር አለባቸው፡፡ “አፍአዊ ሳይሆን ልባዊ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተግተው፣ ለህዝብ መጠቆም፣ ፈር መቅደድ አለባቸው፡፡
ራስን መደለልም ሆነ ሌላውን ማታለል ወንዝ አያሻግርም፡፡ የፖለቲካ ስብከት መሬት አያስረግጥም፡፡ ዲሞክራሲም፣ ፍትህና እኩልነትም የአንድ ሰሞን ሰበካ እንጂ ባዶ ሆድ የሚሞሉ እህል ውሃዎች አይሆኑም፡፡ በየዓመት በዓሉ ባልነበረ በግ፤ “በግ ያያችሁ ና ወዲህ በለኝ” ከሚለው ግብዝ ባለበግ መማር አለብን፡፡ ለሰው ይምሰል ብለን የምናደርገው ነገር፣ የማታ ማታ ዋጋ ያስከፍለናልና እናስብበት!
 


Page 3 of 406