Administrator
"ነጻነት" የተሰኘ የሥዕል ኤግዚቢሽንና ጨረታ የፊታችን ሐሙስ ይካሄዳል
https://t.me/AdissAdmas
የዱር አበባ
የአፍሪካ የሥነ-ጥበብ ሴቶች ሽልማት የ2024 የመጨረሻ እጩዎች ይፋ ሆኑ
24 ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው በቻይና ይወዳደራሉ
“AI ENJOY” ውድድር ላይ ያሸነፉ የወርቅ ሜዳልያ ተሸለሙ
የኢትዮ-ሮቦቲክስ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሰናይ መኮንን፤ በቅርቡ በቻይና በሚካሄደው ዓለማቀፍ የ”ኮዲንግ ስኪል ቻሌንጅ” ላይ 24 ተማሪዎች ኢትዮጵያን ወክለው እንደሚሳተፉ ተናገሩ።
ውድድሩ በየዓመቱ በቻይና እንደሚካሄድ ለአዲስ አድማስ የገለጹት አቶ ሰናይ፤ ዘንድሮም በሻንጋይ ከተማ ከዲሴምበር 14-16 ቀን 2024 ዓ.ም ለሦስት ቀናት እንደሚደረግ አመልክተዋል።
ለዚህም ኢትዮ ሮቦቲክስ ባለፈው ቅዳሜ የኢንጆይ ኤአይ አገር አቀፍ የመጨረሻ ውድድር አካሂዷል። በውድድሩ ላይም ቲም ናይል፣ ቲም አልፋ፣ ቲም ዊነርስ፣ ቲም ላየንስ፣ ቲም ኤግል፣ ቲም አቢሲኒያና ሌሎች ስያሳች የተሰጣቸው የታዳጊ ቡድኖች ተሳትፈዋል፡፡
አሸናፊዎችን ለመለየት በታዳጊ ቡድኖቹ መካከል እልህ አስጨራሽ ፍልሚያ የተካሄደ ሲሆን፤ የማታ ማታ የላቀ ብቃት ያሳዩ ተማሪዎች አሸንፈዋል። ታዳጊዎቹ ስፔስ ትራቭሊንግ፣ ጋላክቲክ ዲፌንስ ባትል እና ክሎዚንግ ሰረሞኒ ኦቭ ስፖርትስ በተሰኙ ዘርፎች ለሦስት ዙር ተወዳድረዋል፡፡
በመጨረሻም፣ ከየዘርፉ ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡ አሸናፊዎች የወርቅ፣ የብርና የነሐስ ሜዳልያ እንዲሁም የምስክር ወረቀት ተሸልመዋል፡፡ የወርቅ ተሸላሚ የሆኑት ሦስት ቡድኖች የሚከተሉት ናቸው።
ቲም ኤግል -በ120 ነጥብ በክሎዚንግ ሰረሞኒ ኦቭ ስፖርትስ
ቲም ስፓርታ - በ630 ነጥብ በስፔስ ትራቭሊንግ ዘርፍ
ቲም ናይል - በ100 ነጥብ በጋላክቲክ ዲፌንስ ዘርፍ
ለአሸናፊዎቹ የወርቅ ሜዳልያ የሸለሙት የቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ሚኒስትሩ ተወካይ አቶ ሰላምይሁን አደፍርስ ባደረጉት ንግግር፤ ኢትዮ ሮቦቲክስ ከወትሮው ውድድር በተለየ የኤአይ እና ዲጂታል ስኪል አቀላቅሎ መምጣቱን አድንቀው፤ የድርጅቱ መሥራች አቶ ሰናይ ዘርፉን ለማሳደግ በየጊዜው እያደረገ ስላለው ጥረት አመስግነዋል፡፡
አክለውም፤ ውድድሩ ሰፋ ብሎ እንዲካሄድና ተደራሽ ይሆን ዘንድ የሚኒስቴር መ/ቤታቸው ለኢትዮ ሮቦቲክስ የሚያደርገውን እገዛና ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል፡፡
የኢትዮ ሮቦቲክስ መሥራች አቶ ሰናይ፤ በቅርቡ በቻይና የሚደረገውን የኮዲንግ ስኬል ቻሌንጅ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፤ በእስካሁኑ ተሞክሮአችን ቻይናውያኑ ታዳጊዎች የተሻለ ልምድ ያላቸው በመሆኑ፤ በየዓመቱ ውድድሩን በአንደኝነት ነው የሚያጠናቅቁት ብለዋል፡፡
እንዲያም ሆኖ ታዳጊ ኢትዮያውያን ከዓመት ዓመት ቁጥራቸውን በመጨመርና ደረጃቸውን በማሻሻል በዓለማቀፍ ውድድሮች ላይ ኢትዮጵያን እያስጠሩ ነው- ብለዋል። የዲጂታል ኢትዮጵያ ተስፋዎችም እንደዚህ ዓይነቶቹ ታዳጊዎች መሆናቸውን ጨምረው ገልፀዋል።
የሪል እስቴትና የቤት ኤክስፖ ይከፈታል
7ኛው ዓመታዊ የሪል እስቴትና የቤት ኤክስፖ ታህሳስ 18 ቀን 2017 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ይከፈታል፡፡ ለሦስት ቀናት የሚቆየው ኤክስፖው ከፍተኛ አልሚዎችን፣ ባለሀብቶችን፣ የፋይናንስ ተቋማትን፣ የቤት ገንቢዎችንና የቤተ ውበት ባለሙያዎችን ጨምሮ፣ የሪል እስቴትና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን ከፍተኛ ባለድርሻ አካላት በአንድ ላይ እንደሚያሰባስብ ተነግሯል፡፡
የ251 ኮሙዩኒኬሽንና ማርኬቲንግ መሥራች አቶ አዲስ አለማየሁ እንደተናገሩት፤ የዘንድሮው ኤክስፖ በኢትዮጵያ ሪል እስቴት ዘርፍ ትልቅ ፋይዳ ያለው ክስተት ሲሆን፤ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ተደማጭነት ያላቸውን ተዋናዮች ያሰባስባል። አቶ አዲስ አክለውም፤ “ዘላቂ ልማትን፣ ፈጠራንና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ መስተጋብራዊ መድረክ በመፍጠር የዘርፉን እድገት ለመደገፍ ቁርጠኛ ነን።” ብለዋል፡፡
ኤክስፖው በሪል እስቴት ዘርፍ ውስጥ ያሉ አዳዲስ እድገቶችን፣ ፈጠራዎችንና የኢንቨስትመንት እድሎችን ለማሳየት ያለመ ሲሆን፤ በኢንዱስትሪ መሪዎች መካከል ትስስርና ትብብርን ይፈጥራል ተብሏል።
በ7ኛው አመታዊ ሪል እስቴትና የቤት ኤክስፖ ላይ ከኤግዚቢሽኑ በተጨማሪ በኢንዱስትሪው ላይ ከሚገኙ ዋና ባለድርሻ አካላትና ከመንግስት ተወካዮች ጋር የመገናኘት እድል የሚፈጠር ሲሆን፤ የፓናል ውይይትም እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡
የመጀመሪያው የቡና ፌስቲቫል ዛሬ በሸራተን ተከፈተ
10 ታዋቂ የቡና አምራች ኩባንያዎች ይሳተፋሉ
ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው የተባለለት የቡና ፌስቲቫል (ኮፊ ፌስት) ዛሬና ነገ እሁድ በሸራተን አዲስ ሆቴል ፋውንቴይኑ አካባቢ እንደሚካሄድ ተገለጸ፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ አሥር የሚደርሱ ታዋቂ የቡና አምራችና ላኪ ኩባንያዎች ይሳተፉሉ፡፡
የቡና አምራች ኩባንያዎቹ የተለያዩ ዓይነት የቡና ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ለኤክስፖርት የተዘጋጁ የቡና ምርቶችን ጨምሮ ለሸያጭ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ የቡና ቀመሳ ሥነስርዓትም ይካሄዳል፡፡
ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የቡና ፌስቲቫል አስመልክቶ የኹነቱ ጠንሳሾችና አዘጋጆች ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሸራተን አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከፌስቲቫሉ ግንባር ቀደም ስፖንሰሮች አንዱ የሖነው የሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ - በመግለጫው ላይ የተገኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቡና ፌስቲቫል በሆቴሉ መዘጋጀቱ ልዩ ደስታና ጉጉት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ቡና ፌስቲቫል አስፈላጊነትን ያብራሩት አዘጋጆቹ፤የኢትዮጵያን ቡና በሚገባው ልክ ለማክበርና ለማጉላት ነው ብለዋል፡፡ ”እኛ ኮፊ ፌስትን እንደ በዓል ነው የምንቆጥረው፤ቡናችንን የምናከብርበትና የምናጎላበት ታላቅ በዓል ነው፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡
እንደ ጀርመን ያሉ አገራት በኦክቶበር ፌስት (ዓመታዊ የቢራ ፌስቲቫል) እንደሚታወቁ የጠቀሱት አዘጋጆቹ፤ ኢትዮጵያም በቡና ፌስቲቫል (ኮፊ ፌስት) መታወቅ አለባት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡
የወቅቱ ጥቅስ
ያሸነፍን ሲመስለን መሸነፍን እንረሳለን
የተሸነፍን እንደሆነ
ማሸነፍ የኛም አይመስለንም
ሁለቱ መካከል ግን
አንድ አዲስ ልጅ እንወልዳለን፡፡› (የአገሬ ገጣሚ)
በሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣሉ ዕገዳዎች አሳሳቢ እንደሆኑ ተገለጸ
“እገዳው ከባድ ጫና እየመጣ መሆኑን ጠቋሚ ነው”
ለሰሞኑ በ3 የሲቪል ማህበረሰብድርጅቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ከሲቪል ማሕበረሰብ ዓዋጅ ያፈነገጠ መሆኑ እንደሚያሳስብ “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” የተሰኘው ተቋም ገልጿል። ተቋሙ እንደገለጸው፤ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ብቻ መርምሮ ለታገዱት የሲቪል ድርጅቶች ተገቢ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ባለፈው ሐሙስ ሕዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ በመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሞያዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና በስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተባሉት ድርጅቶች ላይ የተጣሉ ዕገዳዎች የሲቪል ማሕበረሰብ እንቅስቃሴ “የሚያቀጭጩ ናቸው” ሲል ስጋቱን ገልጿል። በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሰረት፤ ዓዋጁን እና ሌሎች ሕጎችን ለሚጠቀሱ ድርጅቶች ባለስልጣኑ በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ፣ እንዲህም ባለስልጣኑ በሲቪል ድርጅቶች ላይ ምርመራ በሚያካሂድበት ወቅት ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ፣ ጊዜያዊ ዕግድ ሊጥል እንደሚችል መደንገጉን አብራርቷል።
ይሁን እንጂ በታገዱ ድርጅቶች ላይ በዓዋጁ መሰረት ቢሮ ድረስ በመምጣት ባለስልጣኑ ክትትል አለማድረጉን ማስጠንቀቂያ አለመስጠቱን፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ምርመራ አለመጀመሩንና “አስተካክሉ” የተባሉበት መነሻ ሳይኖር፣ ቀጥታ እግድ መጣሉን “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” ለመረዳት መቻሉን አትቷል። “መንግስት ዓዋጁን ሳይከተሉ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለሲቪል ማሕበረሰብ እንቅስቃሴ እጅግ የሚጎዳና የሚያቀጭጭ መሆኑን ተረድቶ፣ ጉዳዩን ሕጉ በሚያዘው መሰረት ብቻ መርምሮ ተገቢ መፍትሔ እንዲሰጣቸውና ወደፊትም ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የ”ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” ዋና ሃላፊ አቶ ተስፋዓለም በርሄ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፣ “በእነርሱ ላይ የተጣለው ዕገዳ ለእኛም የማይመጣበት ምክንያት የለም” ብለዋል። አያይዘውም፣ ተቋማቸው መርህን መሰረት በማድረግ በሦስቱ የሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣሉትን ዕገዳዎች መቃወሙን አስታውቀዋል።
“የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሻሻልን ተከትሎ፣ በሲቪል ድርጅቶች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲደረግና ዕንቅስቃሴያቸውም ሲስፋፋ ነበር” ያሉት አቶ ተስፋዓለም፣ “አሁን ግን ፖለቲካዊ ጫናዎች እየመጡ፣ ብዙ የሲቪል ድርጅት መሪዎች ከአገር ወጥተዋል” ሲሉ ተናግረዋል። በሶስቱም ሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ከባድ የሆነ ጫና እየመጣ መሆኑንና የመንቀሳቀሻ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ሲሉም ስጋታቸውን አጋርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሰሞኑ ዕገዳ በተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታወቋል። ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ አንዳንድ ክስተቶች ምክንያት የሲቪል ምህዳሩ “ጠብቧል” ብሎ መደምደም ተገቢ አለመሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በዕገዳው ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ተፋላሚ ወገኖችን ለማደራደር ዝግጁነቱን ገለፀ
የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ውስጥ ሚና ያላቸውን ተፋላሚ ወገኖች ለማደራደር ዝግጁ መሆኑን ገልጿል። የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን በማሰብ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶችና የስራ አስፈጻሚ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሆቴል በጋራ ባቀረቡት የሰላም ጥሪ ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በንፁሃን ላይ ያነጣጠሩ የግድያ፣ የጥቃት፣ የእገታ፣ የመፈናቀል እና የዘረፋ ተግባራት መፈጸማቸውን አውስተዋል። መግለጫቸውም፤ “የተፈፀሙት ተግባራት በየትኛውም የሃይማኖት አስተምህሮ የሚወገዙ ፍፁም ወንጀል ድርጊቶች ሲሆኑ የአንዳንዶቹ ተግባራት አፈፃፀምም በጭካኔና በአረመኔነት የተሞሉ እንደሆኑ ተመልክተናል፡፡” ብለዋል።
በቅርቡ በሰሜን ሸዋ ዞን፣ ደራ ወረዳ፣ ሰላሌ አካባቢ የተፈፀመው አሰቃቂና ጭካኔ የተሞላበት የግድያ ድርጊት ችግሩ የደረሰበትን ደረጃ በተጨባጭ ማስረጃ እንደሚያሳይ የገለጹት የጉባዔው የበላይ ጠባቂዎች፣ በአጠቃላይ ይህንን እና ከአሁን ቀደም የተፈፀሙ መሰል ድርጊቶችን ሁሉ በጽኑ እንደሚያወግዙ አስታውቀዋል። በማያያዝም፣ የመንግስት ቀዳሚ አጀንዳ የአገር ሰላምና የዜጎች ደህንነት የመጠበቅ ጉዳይ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል።
እንደ አገር የምንገኝበት ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ያነሱት የበላይ ጠባቂ አባቶች፣ ዜጎች ከቦታ ወደ ቦታ ተንቀሳቅሰው ለመስራት አዳጋች እንደሆነባቸውና የአገር አቋራጭና ድንበር ተሻጋሪ አሽከርካሪዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ሁነው እየሰሩ እንደሚገኙ በተለያየ ጊዜ ከሚወጡ መግለጫዎች ለመረዳት መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡
የጉባዔው የበላይ ጠባቂ አባቶች በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ካለው የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በክልሎቹ አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚኖሩ ሕዝቦች ከባድ ፈተና መፍጠሩን በማንሳት፣ ሁሉም ተፋላሚ ወገኖች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግርና ድርድር እንዲመጡ የሰላም ጥሪ አቅርበዋል። በትክክል ቀኑን ይፋ ባያደርጉም፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ግን በግጭቶች ውስጥ ያሉ ተፋላሚ ወግኖችን ለማቀራረብ፣ ለማደራደርና ለማስታረቅ ቁርጠኛና ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተያያዘ በነገው ዕለት ዕሁድ ሕዳር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ አገራዊ የሰላም እና የጸሎት መርሃ ግብር በመቄዶንያ የአረጋውያን እና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል እንደሚከናወን የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደለ አስታውቀዋል። አያይዘውም፣ ከዚህ ቀደም የሐይማኖት አባቶች በተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ማቅረባቸውን በማስታወስ፣ አሁንም ይህንኑ ጥሪ እያቀረቡ መሆናቸውን ቀሲስ ታጋይ ተናግረዋል።
በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለው ግጭት ዙሪያ በቤተ ዕምነቶች እና የሃይማኖት አባቶች ላይ የደረሱ ጉዳቶችን ጉባዔው “እንዴት ይመለከታቸዋል?” የሚል ጥያቄ አዲስ አድማስ ለቀሲስ ታጋይ አቅርቦ ነበር። ቀሲስ ታጋይ በምላሻቸው፣
“የመግለጫው አንድ አካል ነው። በአገሪቱ የትም ክልል ለተገደሉ ወገኖች ውግዘት አድርገናል። ማንም ይሁን ምን ተግባሩ የሚወገዝ ነው፤ ለሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ወደ ጠረጴዛ ዙሪያ ንግግር እንዲመጡ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል መምህራን የጥቅምት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተናገሩ
የብልፅግና አባል ያልሆኑ መምህራን ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ተጠይቀዋል
በሲዳማ ክልል፣ ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን፣ ደራራ ወረዳ የሚገኙ መምህራን የጥቅምት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል። መምህራኑ አክለውም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ያነሱ መምህራን ለእስር መዳረጋቸውን አመልክተዋል።
ደራራ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚያስተምሩ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ መምህር ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፣ በመጀመሪያ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ ሌሎችም የወረዳው ካቢኔ አባላት መምህራኑን ሰብስበው አነጋግረዋቸዋል። በዚህ መድረክ ላይ ለወረዳው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከደመወዛቸው ላይ ተቆራጭ እንዲሆን ለመጠየቅ እንደመጡ ለመምህራኑ መናገራቸውን አውስተዋል።
ይሁንና መምህራኑ ኑሮ እንደከበዳቸውና የሚከፈላቸው ደመወዝ እንደማይበቃቸውና የፓርቲ አባል እንዳልሆኑ፣ በዚህም ግዴታ እንደሌለባቸው ለአወያዮች መናገራቸውን የሚያስረዱት እኚሁ መምህር፣ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ ከሰዓት 9፡00 ስብሰባው ቢከናወንም፣ በመጨረሻም መምህራኑ ከአወያዮቹ ጋር ለመግባባት ባለመቻላቸው መድረክ ረግጠው እንደወጡ ጠቅሰዋል። “ስብሰባው የተደረገው በስራ ቀን ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ተደርጓል” ብለዋል።
በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ መምህራን፣ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመካክረው ፊርማ በማሰባሰብ፤ ለወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ ከደመወዛቸው ተቆራጭ ማድረግ እንደማይችሉና ለስብሰባ ተብሎ የወረዳው የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ ጥያቄ ማቅረባቸውን መምህሩ ያብራራሉ። ያሰባሰቡትን ፊርማ ለወረዳው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ ለወረዳው ፐብሊክ ሰርቪስ ጽሕፈት ቤትና ለሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ማስገባታቸውንም አስታውቀዋል።
የወረዳው መምህራን ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ዘውዴ አዲስ አድማስ ከ5 ት/ቤቶች የተውጣጡ 160 መምህራን ፊርማ ማሰባሰባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከ5 ትምሕርት ቤቶች የተውጣጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ፊርማ ለሚመለከታቸው ተቋማት ገቢ በተደረገ በሳምንቱ፣ (ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም.) “መምህራኑ ሳያውቁ ነበር የወረዳው የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ለብቻቸው የመጡት። የመጡትም ከረፋዱ 4፡00 ላይ ሲሆን፣ በዚያ ሰዓት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዲወጡ ተደረገ።” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ። አያይዘውም፣ ምክትል ሃላፊው “መጀመሪያ ለክልሉና ለዞኑ ቃል የገባነው እናንተን ተማምነን ነው። ከወረዳው ሰራተኞች ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ቃል ገብተናል። ያንን ቃል እኛ ምን እናድርገው?” ብለው መናገራቸውን ገልጸዋል።
መምህራኑ ግን እነርሱ በይፋ ቃል እንዳልገቡ፣ ቃል የገቡት አመራሮቹ እንደሆኑና ራሳቸው አመራሮቹ እንዲወጡት በማስታወቅ፣ ኑሮ እንደከበዳቸው መግለጻቸውን የሚናገሩት መምህሩ ይናገራሉ። “ደመወዜ በወር 4 ሺሕ 700 ብር ነው። አብዛኛው መምሕር ከእኔ የደመወዝ መጠን በላይ አያገኝም። የተወሰኑት ከፍ ያለ ደመወዝ ካገኙ ደግሞ፣ 5 ሺሕ 300 ብር ነው።” በማለት ተናግረዋል።
ከደመወዛቸው ላይ ለሕንጻው ግንባታ 100 ፐርሰንት እንዲቆረጥ በወረዳው አመራሮች እንደተጠየቁ ገልጸው፣ በ10 ወር ጊዜ ውስጥ አብዛኛው ደመወዛቸው ለግንባታ ስራው ገቢ እንደሚደረግም ለማወቅ መቻሉን መምሕሩ ጠቅሰዋል።
በግልጽ ከደመወዛቸው ተቆራጭ ገንዘብ መወሰዱን የተቃወሙ ሦስት መምህራን በፖሊሶች ታስረው ሐዋሳ እንደሚገኙ ያመለከቱት እኚሁ መምህር፣ “ከደመወዛቸው የተወሰነው ገንዘብ ለፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ እንዲውል በፍራቻ የፈረሙት መምህራን ቁጥር 17 ነው።” ብለዋል። ይህን ተከትሎ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለፈረሙ መምህራን ብቻ ደመወዝ ገቢ ሲደረግ፣ ደመወዝ ያልተከፈላቸው መምህራን ለምን እንዳልተከፈላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ መጀመሪያ ወረቀቱን እንዲፈርሙ ቅድመ ሁኔታ እንደቀረበላቸው ለማወቅ ተችሏል።
የወረዳው መምህራን ማሕበር ለምን ለተወሰኑ መምህራን ደመወዝ እንዳልተከፈለ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ተመሳሳይ ምላሽ እንደተሰጠው መምህሩ አስታውቀዋል። የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ስለተሰጣቸው ምላሽ ሲናገሩ፣ “ችግሩ እንዲቀረፍ ጥረት ብናደርግም፣ የመንግስት አመራሮች ግን ለመተባበር ፈቃደኞች አይደሉም” ብለዋል። ደመወዝ በወቅቱ ስላልተከፈለው በተፈጠረበት አዕምሯዊ ጫና ምክንያት ተሾመ ታደሰ የተባለ መምህር ራሱን ማጥፋቱን የሚናገሩት አቶ ዘላለም፣ የወረዳው አመራሮች ከመምህራኑ የህዳር ወር ደመወዝ ተቆራጭ ለማድረግ ማሰባቸውን አስታውቀዋል። ይህንን ጉዳይ እስከ ፌደራል ተቋማት ድረስ ለመውሰድ እርሳቸው የሚመሩት ማሕበር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካልንም።