Administrator

Administrator


የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ፣ የአሜሪካውን አቻቸውን ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት ማጨታቸውንና ይህንን ያደረጉትም በትራምፕ አስተዳደር በተደረገባቸው ጫና እንጂ በራሳቸው ተነሳሽነት አለመሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ ከወራት በፊት ከዶናልድ
ትራምፕ አስተዳደር በተላከላቸው ደብዳቤ፣ ትራምፕን ለኖቤልየሰላም ሽልማት እንዲያጩ በተጠየቁት መሰረት፣ ያለ ፍላጎታቸው
ትራምፕን ማጨታቸወን አሻይ የተባለው የጃፓን ጋዜጣ ከሰሞኑ ያስነበበውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው አስታውቋል፡፡ ጋዜጣው መረጃውን ይፋ ያደረገው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ለኖቤል ሽልማት አጭተውኛል በሚል ባለፈው ሳምንት በዋይት ሃውስ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በኩራት መነገራቸውን ተከትሎ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ የትራምፕ አስተዳደር በሽንዞ አቤ ላይ ጫና ማድረጉን በተመለከተ የሰጠው ምላሽ አለመኖሩን አመልክቷል፡፡


ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው በነብሰ - ገዳይነት ተጠርጥሮ ተከሶ ፍርድ ቤት ይቀርባል፡፡
አንድ ሌላ ሰው ደግሞ በምስክርነት እዚያው ፍርድ ቤት መጥቷል፡፡
ዳኛ ለምስክሩ፤
“እሺ ያየኸውን ተናገር፡፡”
ምስክር፤
“ሰውየው በሞተ ጊዜ እዚያው አካባቢ ነበርኩኝ፡፡ የጥይት ድምፅ ስሰማ፤ ወደሰማሁበት አቅጣጫ ወዲያውኑ ሄድኩኝ፡፡ ሟቹ ጭንቅላቱን ነበር የተመታው፡፡ ትኩስ ደም እየፈሰሰው ነበር፡፡”
ዳኛ፤
“በትክክል በዐይንህ ገዳይ በጥይት ሲገለው አይተሃል?”
ምስክር፤
“አይ ከተተኮሰ በኋላ ነው የደረስኩት”
ዳኛ፤
“ገዳዩንስ አይተኸዋል?”
ምስክር፤
“አላየኹትም”
ዳኛ
“እንግዲያው ለምስክርነት አትበቃም፤ መሄድ ትችላለህ”
ምስክር ከፍርድ ቤት ሲወጣ ኮሪደሩ ላይ፤
“ወይ ዳኝነት! ወይ ዳኝነት! ወይ ዳኝነት!” እያለ ጮክ ብሎ እየሳቀ ሲሄድ፣ ዳኛው ሰምተው፣ የሥነስርዓት አስከባሪውን ልከው አስጠሩት፡፡
ዳኛ፡-
“ችሎቱን ደፍረሃል”
ምስክር፡-
“ምን አድርጌ ጌታዬ?”
ዳኛ፡-
“እየሳቅህ ተሳልቀሃል”
ምስክር፡-
“ስስቅ አይተዋል?”
ዳኛ፡-
“አላየሁም፡፡”
ምስክር
“እንግዲያው እርሶም ለምስክርነት አይበቁም!” አላቸው፡፡
***
ፍትህን የሚፈታተኑ አያሌ ጉዳዮች እንዳሉ መቼም አይረሱ! ዳኞችም ይፈተሹ፡፡ የአንድ ህዝብ ሥልጣኔ መለኪያ ናቸው ከሚባሉት ነገሮች አንዱ የትምህርት ሥልጣኔ ነው፡፡ ያ ህዝብ ምን ያህል የትምህርት ግብዓትና ጥቅም ገብቶታል እንደማለት ነው፡፡ ዱሮ፡- በመዝሙር ይገለፅ እንደነበረው፡-
“በጠቅል ጊዜ ያልተማረ
ማዘኑ አይቀርም እያደረ
ዐይናችን ታሞ ታውረን
ኃይለሥላሴ አዳኑን” ይባል ነበር፡፡
ለህዝቡ የትምህርትን ግንዛቤ ለማስጨበጥ ብርቱ ጥረት ተደርጓል፡፡ ብዙ ድካም ተደክሟል፡፡ ያ ባይሆን ዛሬ የደረስንበት ደረጃ ባልተደረሰም ነበር፡፡ ከዕቅዳችን ሁሉ ትልቁ ትምህርት ሊሆን ግድ ነው፡፡
“ዕቅድህ የአንድ ዓመት ከሆነ ጤፍ ዝራ፡፡ ዕቅድህ የአምስት ዓመት ከሆነ ባህር ዛፍ ትከል፡፡ ዕቅድህ የዘለዓለም ከሆነ ልጅህን አስተምር” የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡
አበው ፀሃፍትም፤
“ይህቺን ጨቅላ መጽሐፍ የምታነቡ ሁሉ
አደራ ስለእኔ ማርያም ማርያም በሉ
ከሆዴ ያለውን የትምህርት ሽል
ያለጭንቅ እንድወልድ እንድገላገል
ከሃያ ስድስቱ ወንዶች ፊደላት
አርግዣለሁና መዝገበ - ቃላት
ለትምክህት አይደለም ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ”
ስለዚህ ለተሻለ ዕውቀት እንቅና እናስቀና፡፡ በዚህ መልክ አገር ትሻሻላለች፡፡ ሙያዊ ክህሎትን ማሳደግ፣ ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ መመደቡን ማረጋገጥ፣ የሥራ ክትትልና ቁጥጥር (Monitoring and Evaluation) ላይ ማተኮር፣ ከአፍ አልፎ በተግባር ሲፈፀም እንይ፡፡ ለዕድገት እንጓጓ፡፡ ከልምድ ለመማር እንጓጓ፡፡ እርስ በርስ ለመማማር እንታትር፡፡
ይህን በሥራ ላይ ለማዋል ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ መላ ያስፈልጋል፡፡ ዋናው ሃሳብ እንዳያረጅብን መጣጣር ነው፡፡ “እንኳን ሞት እርጅና አለ አይደም ወይ?”
ያለው አንበሳ ወዶ አደለም፡፡ አዳዲስ ዘዴ እንፍጠር!

የግብጽ ፓርላማ አባላት የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን የሚያራዝመውንና የአገሪቱን መሪ አብዱል ፈታህ አልሲሲን ለተጨማሪ 12 አመታት በስልጣን ላይ ለማቆየት ሆን ተብሎ የታቀደ ነው የተባለውን የህገ-መንግስት ማሻሻያ ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ከትናንትና በስቲያ በከፍተኛ የድጋፍ ድምጽ ማሳለፋቸው ተዘግቧል፡፡
ከአገሪቱ 596 የፓርላማ አባላት መካከል 485ቱ ድጋፋቸውን የሰጡት የህገመንግስት ማሻሻያ፣ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ከሶስት አመታት በኋላ የሚያጠናቅቁት ፕሬዚዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ ለተጨማሪ ሁለት የስልጣን ዘመናት ወይም 12 አመታት በስልጣን ላይ እንዲቆዩ የሚያስችል መሆኑን ዋሽንግተን ፖስት ዘግቧል፡፡
በፕሬዚዳንት አልሲሲ ደጋፊዎች የተሞላው የግብጽ ፓርላማ በአብላጫ ድምጽ የደገፈው የውሳኔ ሃሳብ፣ እ.ኤ.አበ2014 በጸደቀው የአገሪቱ ህገመንግስት ላይ የተቀመጠውን የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ከአራት አመት ወደ ስድስት አመት የሚያራዝም ሲሆን፣ ለፕሬዚዳንት አልሲሲ የፍርድ ቤት ዳኞችንና ዋና አቃቤ ህግን መሾምን ጨምሮ የተለያዩ ተጨማሪ ቁልፍ ስልጣንና ሃላፊነቶችን የሚሰጥ ነው በሚል እየተተቸ መሆኑን ገልጧል፡፡
አልሲሲ ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን በአገሪቱ ፕሬዚዳንትነት የመቀጠል እቅድም ሆነ የህገመንግስት ማሻሻያ በማድረግ ስልጣን የማራዘም ዕቅድ የለኝም ሲሉ በ2017 ለቢቢሲ መናገራቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ ባለፈው አመት መጋቢት ወር ላይ በ97 በመቶ ድምጽ ተመርጠው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን መቀጠላቸውን ባረጋገጡ ማግስት ግን ደጋፊዎቻቸው የህገመንግስት ማሻሻያ ተደርጎ የፕሬዚዳንቱ የስልጣን ዘመን ይራዘም የሚል ሃሳብ ይዘው መነሳታቸውን አስታውሷል፡፡
የህገመንግስት ማሻሻያው በአገሪቱ ልዩ የህገመንግስታዊና የህግ ጉዳዮች ኮሚቴ ከተመከረበት በኋላ ለመጨረሻ ውሳኔ ዳግም ወደ ምክር ቤቱ እንደሚላክ የጠቆመው ዘገባው፣ በሁለት ወራት ጊዜ ውስጥ በአገር አቀፍ ደረጃ ህዝበ ውሳኔ ተደርጎበት የሚጸድቅ ይሆናል ብሏል፡፡


          የተደራጁ የኢንተርኔት ዘራፊዎች በህገወጥ መንገድ የሰረቋቸውን 620 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ ድረገጾች  አካውንቶች ለሽያጭ ማቅረባቸውን ፎርብስ ዘግቧል፡፡
የኢንተርኔት ዘራፊዎቹ የ16 ድረገጾችን ማለፊያ ቃል ሰብረው በመግባት 620 ሚሊዮን ያህል የተጠቃሚዎችን አካውንቶች በመዝረፍ የኢሜይል አድራሻዎችን የይለፍ ቃልና ሌሎች የግል መረጃዎች በእጃቸው ማስገባታቸውንና ለሽያጭ ማቅረባቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ አካውንቶቹን የሚገዙ ወንጀለኞች ላልተገባ ድርጊት ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ስጋት መኖሩን አመልክቷል፡፡
ባለፈው ጥር ወር ላይ 1 ቢሊዮን ያህል የኢሜይል አድራሻዎችና የይለፍ ቃሎች በኢንተርኔት መንታፊዎች መዘረፋቸውን ያስታወሰው ዘገባው፣ በቀናት ጊዜ ውስጥ ደግሞ በ2.2 ቢሊዮን አካውንቶች ላይ ተመሳሳይ ዝርፊያ መፈጸሙንም አስታውሷል፡፡


           የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ከ3 በላይ ልጆችን የሚወልዱ የአገሪቱ እናቶች ዕድሜ ዘመናቸውን ሙሉ የገቢ ግብር እንዳይከፍሉ እንደሚደረጉ ከሰሞኑ ማስታወቃቸው ተዘግቧል፡፡
በሃንጋሪ የወሊድ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱና በቀጣይ አገሪቱን የሚረከብ በቂ የሰው ሃይል ላይገኝ ይችላል የሚል ስጋት የተፈጠረበት የአገሪቱ መንግስት፤ እናቶች ልጆችን እንዲወልዱ ለማበረታታት ከገቢ ግብር ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው እሁድ ባደረጉት ንግግር ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
መንግስት ለአዲስ ተጋቢዎች የመቋቋሚያ ብድር ለመስጠትና ጥንዶቹ ሁለት ወይም ሶስት ልጆችን ከወለዱ ዕዳቸውን በከፊል ወይም ሙሉ ለሙሉ ለመሰረዝ ማቀዱን ያስታወቁት ቪክቶር ኦርባን፤ ከዚህ በተጨማሪም ቢያንስ ሁለት ልጆች ላሏቸው ቤተሰቦች የቤት መግዣ የብድር አቅርቦት ለማሟላት ማቀዱንም አክለው ገልጸዋል፡፡
በአገሪቱ አብዛኛው የተማረ የሰው ሃይል የተሻለ ስራና ገቢ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገራት መሰደዱን የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ እናቶች መውለድ ማቆማቸውንና በዚህም የአገሪቱ የህዝብ ብዛትም እ.ኤ.አ እስከ 2050 ድረስ በ15 በመቶ ሊቀንስ ይችላል መባሉን አመልክቷል፡፡
የወሊድ መጠን መቀነሱ ያሰጋቸው ፖላንድና ሰርቢያ፣ ወሊድን ለማበረታታትና አገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በማሰብ በቅርቡ ለእናቶች ተመሳሳይ ማበረታቻዎችን ማድረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡


         ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ አንዲት ክፉ ሚስት ነበረችው፡፡ በእርሻ ሲደክም ውሎ ሲመጣ፤
“ና ወጥ ስራና ራቴን አብላኝ”
“ና እግሬን እጠበኝ” ትለዋለች፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ፤
“ወገቤን አሞኛል ና እሸኝ” ትለዋለች፡፡
ደሞ ሌላ ጊዜ፤
“ና፤ እግሬን እጠበኝ”
“ና በቅባት እሸኝና አስተኛኝ!” ትለዋለች፡፡
እንዲህ ቁም ስቅሉን ስታሳየው ከርማ፣ የአምላክ ፈቃዱ ሆኖ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች፡፡
ከሞተች በኋላ ብዙ ጊዜ በብቸኝነት መኖሩን ያስተዋሉ ሰፈርተኞች መክረው ዘክረው፤ ሌላ ሚስት እንዲያገባ አደረጉት፡፡
አዲሲቱ ሚስት ደግሞ የመጨረሻ ደግ፣ አስተዋይ ሆነችለት፡፡
ጠዋት ከአልጋው ሳይነሳ ቆንጆ ቁርስ ሰርታ እዛው ባፍ-ባፉ አጉርሳው፤ ማታም ከእርሻ ሲመለስ እግሩን አጥባ ወገቡን በቅባት አሽታ፣ ራቱን አጉርሳው አቅፋው ትተኛለች፡፡
ይሄኔ ይህ ባል፤ እንዲህ ብሎ ፀለየ ይባላል፡-
“አምላኬ ሆይ፤ ስላደረክልኝ ሁሉ ምስጋና ይግባህ! አንድ ውለታ እንድትውልልኝ እጠይቅሃለሁ፡፡ ይኸውም ከዚች የተሻለች የምትመጣ ከሆነ እባክህ እቺንም ግደልልኝ!”
***
ዱሮ፤ ዱሮ ዱሮ፤
“ጉዟችን ረዥም
ትግላችን መራራ” ይባል ነበር፡፡
አንድ የደርግ ካድሬ አገሩን ሲያምስ ሲያተራምስ ከርሞ ተረኛ ታካሚ ሆኖ ራሱ ታሰረ፡፡ ከዚያ ሲደጋግመው የኖረውን ያንን መፈክር መጠየቅና መቃወም ጀመረ፡-
“ትግላችን መራራ፣ ጉዟችን ረዥም” ብሎ ነገር ምንድን ነው? መራራ ከሆነ አጠር ይበል፣ ረዥም ከሆነ ጣፈጥ ይበል፡፡ ለምንድን ነው ለህዝባችን ደግ የማንመኘው” አለ። ካልተቀጡ የማይማሩ አያሌ ካድሬዎች ስናፈራ ኖረናል፡፡ ዞሮ ዞሮ ቤት ያፈራቸው ናቸው!
ዛሬም ሊቀጥል እንደሚችል ጭንቅላትን ይዞ ማሰብ አይጠይቅም፡፡ ዋናው ከሆነውና ከሚሆነው መማር ነው!
“ምንኛ ታድሏል የሰነፍ አዕምሮ
እንኳን መማር ቀርቶ ፊደል ሳያጠና
ሁሉንም ያወቀ ይመስለዋልና
አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ብለዋል ከበደ ሚካኤል፡፡ መስማት ካቃተን ለውጥ አናመጣም፤ ዕውነት ለመናገር ለውጥን ከልብ ካላሰብነው አገር አንለውጥም፡፡ መቼም! መቼም! መቼም!
የመከላከያን መዋቅርና አስተሳሰብ፣ መለወጥ፣ ስለደ ህንነት ያለንን ግንዛቤ ማሻሻል፣ አገርን ከማዳን አኳያ መታደጊያችን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የንቃተ ህሊናችን መበልፀግ እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ እነዚህን የአገር ህልውናዎች በጤናማ መንገድ አለመንከባከብ ቆይቶ ያስከፍለናል፡፡ ወታደራዊና ደህንነታዊውን ኃይል በጤናማ ዐይን ካላየን፣ እንዲሁም የምንመኛትን ኢትዮጵያ ለመገንባት ካልተዘጋጀን፣ እንደ ልማዳችን ይረፍድብናል፡፡ “ባለበት ሃይ!” የምንባለው ለዚህ ነው!
አንዳንድ ዕድሎች አይደገሙም፡፡ አጋጣሚዎችን ቀልጠፍና መጠቅ ብለን ካልተጠቀምንባቸው ያመልጡናል፡፡ አንዴ ከጠፉ የማይመለሱ ብዙ ናቸውና ይሄንን ቀን አንጣው!
Girl, if you want to
Prove that you are a virgin
Don’t forget, that
 you’ll never prove it again!
ድንግልናሽን ማረጋገጥ ከፈለግሽ ደግመሽ እንደማታረጋግጪው እወቂ፤ እንደማለት ነው፡፡ “ጓሳና ድንግል ያለአንድ ቀን አይበቅል” ማለት ይሄ ነው!!

  በአለማችን በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ህጻናት ወታደሮች እንደሚገኙ ተነግሯል
                       በየአመቱ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በተበከለ ምግብ ለሞት ይዳረጋሉ

          በአለማችን በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ውትድርና የሚገቡ ህጻናት ወታደሮች ቁጥር ባለፉት አምስት አመታት ከእጥፍ በላይ መጨመሩንና በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ በ17 አገራት ብቻ ከ29 ሺህ በላይ ህጻናት ወደ ውትድርና መግባታቸውን አንድ ጥናት አስታውቋል፡፡
በአለማችን የተለያዩ አገራት በጦር መሳሪያ የታገዙ ግጭቶች መስፋፋታቸውን ተከትሎ ወደ ውትድርና የሚገቡ ህጻናት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ እንደሚገኝ ያስታወቀው ቻይልድ ሶልጀርስ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም፣ በመላው አለም በውትድርና ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ቁጥር በመቶ ሺህዎች  ሊቆጠር እንደሚችል መግለጹን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተቀማጭነቱን በለንደን ያደረገው ተቋሙ ባለፈው ማክሰኞ ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፤ በ2017 የፈረንጆች አመት በአለማችን 15 አገራት ውስጥ ብቻ 8 ሺህ ያህል ህጻናት ወደ ውትድርና እንዲገቡ የተደረጉ ሲሆን፣ በታጣቂ ቡድኖች ውስጥ እንዲገቡ የተደረጉ ልጃገረዶች ቁጥርም ባለፈው አመት ከነበረበት በአራት እጥፍ ያህል ጨምሯል፡፡
በተለያዩ አገራት የሚገኙ ታጣቂ ቡድኖችና አማጽያን፣ ህጻናትን በመመልመል በተዋጊነት፣ በመረጃ አስተላላፊነት፣ በስለላ፣ በጉልበት ስራና በወሲብ ባርነት እንደሚያሰማሩ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በከፍተኛ ደረጃ የችግሩ ሰለባ የሆኑትም የመካከለኛው ምስራቅ አገራት፣ የደቡብ ሱዳን፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ህጻናት መሆናቸውንና በደቡብ ሱዳን ከ19 ሺህ በላይ ህጻናት በታጣቂ ቡድኖች ተመልምለው እያገለገሉ እንደሚገኙም አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ በአለማችን በየአመቱ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በተበከለ ምግብ ምክንያት ለሞት እንደሚዳረጉና ተጨማሪ 600 ሺህ ያህል ሰዎችም ለህመም እንደሚጋለጡ ተመድ አስታውቋል፡፡
በባክቴሪያ፣ በቫይረስ፣ በጥገኛ ህዋሳትና በኬሚካሎች የተበከሉ ምግቦች በአለማችን የተለያዩ አገራት በርካታ ሰዎችን ለሞትና ለከፋ የጤና ችግር እየዳረጉ እንደሚገኙ የአለም የምግብና የእርሻ ድርጅትና የጤና ድርጅት በጋራ ባዘጋጁት መድረክ ላይ ተጠቁሟል፡፡

 ጦቢያ ግጥም በጃዝ መንደር በአገሪቱ በሚገኙ 45ቱም ዩኒቨርሲቲዎች በመዘዋወር “ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማድመቅ” በሚል መርህ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና መምህራን ጋር ለመወያየትና የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶችን ለማቅረብ ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ውል ፈፅሟል፡፡
በዚህ መሰረትም በአዲስ አበባና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙ የተካሄደ ሲሆን በቀጣይም እስከመጪው የክረምት ወራት መግቢያ ድረስ በ20 ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮግራሙን ለማካሄድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን የፕሮግራሙ አስተባባሪ ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ ለአዲስ አድማስ ተናግራለች፡፡ በአዲስ አበባና በወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች በተካሄደው ስነ ስርዓት ላይ የዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎችና መምህራን “አጥራችን ኢትዮጵያ ናት፤ ሌላ አጥር የለንም” የሚል ቃል ኪዳን ስነ ስርዓት አካሂደዋል፡፡

 ፊሊፒንሳውያን በቀን ከ10 ሰዓት በላይ ኢንተርኔት ላይ ያጠፋሉ


    በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2019 በተለያዩ የአለማችን አገራት ውስጥ የሚገኙ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች በድምሩ 1.2 ቢሊዮን አመት ያህል ጊዜ ኢንተርኔትን በመጠቀም ያጠፋሉ ተብሎ እንደሚገመት ሁትሲዩት የተባለው የጥናት ተቋም ያወጣው አለማቀፍ ሪፖርት አመለከተ፡፡
ዘ ዲጂታል 2019 የሚል ርዕስ ያለውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በአለማቀፍ ደረጃ በኢንተርኔት የሚጠፋው ጊዜ በእጅጉ እየጨመረ ሲሆን ባለፈው የፈረንጆች አመት ዜጎቿ ረጅም ጊዜን በኢንተርኔት ላይ ያጠፉባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር ፊሊፒንስ ናት ተብሏል፡፡
ፊሊፒንሳውያን ባለፈው አመት በየቀኑ በአማካይ 10 ሰዓት ከ2 ደቂቃ የሚሆን ጊዜ ኢንተርኔት በመጠቀም እንዳጠፉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በየቀኑ በአማካይ ዘጠኝ ሰዓት ከ29 ደቂቃ ኢንተርኔት ላይ ያጠፉት ብራዚላውያን የሁለተኛነት ደረጃን ይዘዋል ብሏል፡፡
በየቀኑ በአማካይ ለዘጠኝ ሰዓት ከ11 ደቂቃ ኢንተርኔት ላይ ተጥደው የሚውሉ ዜጎችን ያፈራቺዋ ታይላንድ በሶስተኛነት ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፣ ኮሎምቢያውያን ለዘጠኝ ሰዓታት፣ ኢንዶኔዢያውያን ደግሞ ለስምንት ሰዓታት ከ36 ደቂቃዎች እንደቅደም ተከተላቸው እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
ሪፖርቱ ካካተታቸው የአለማችን አገራት መካከል በ2018 ያለፈው የፈረንጆች አመት ዜጎቿ አነስተኛ ጊዜን በኢንተርኔት ላይ ያጠፉባት ቀዳሚዋ አገር ጃፓን ስትሆን፣ ጃፓናውያን በአመቱ በአንድ ቀን ውስጥ ኢንተርኔት ላይ ያጠፉት አማካይ ጊዜ ሶስት ሰዓት ከ45 ደቂቃ ብቻ ነው ተብሏል፡፡
በአለማቀፍ ደረጃ በየቀኑ በኢንተርኔት የሚጠፋው አማካይ ጊዜ ስድስት ሰዓት ከ42 ደቂቃ ያህል እንደሆነ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን የሚያጠፉት ፌስቡክን በመሳሰሉ ማህበራዊ ድረገጾች እንደሆነም አመልክቷል። ጃፓናውያን በማህበራዊ ድረገጾች ላይ የሚያጠፉት ጊዜም በአለማችን አነስተኛው ነው ተብሏል፡፡

  በወር አንድ ቀን ሙሉ ሌሊት ለመንግስታቸው እንዲጸልዩም ተነግሯቸዋል


     የቀድሞው የአለማችን ኮከብ እግር ኳስ ተጫዋችና የወቅቱ የላይቤሪያ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ አገሪቱ ከገባችበት አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ቀውስ እንድታገግም በቀን ለ2 ሰዓታት ያህል ተግታችሁ ጸልዩ ሲሉ ለዜጎቻቸው ጥሪ ማቅረባቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ላይቤሪያውያን ምዕመናን ለኢኮኖሚው ቀውስ በየቀኑ ከሚያደርጉት የሁለት ሰዓታት ጸሎት በተጨማሪ በየወሩ የመጨረሻው አርብ ለአገራቸው መንግስትና ህዝብ ሙሉ ለሌት ተግተው እንዲጸልዩ በፕሬዚዳንት ዊሃ በአማካሪያቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክት ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡
ጉዳዩን በተመለከተ በጎ አስተያየታቸውን የሚሰጡ በርካታ ላይቤሪያውያን የመኖራቸውን ያህል ብዛት ያላቸው ሌሎች ግን፣ ገዢዎቻችን እርኩሳን ስለሆኑ ጸሎታችን ሰሚ አያገኝም በማለት የመሪያቸውን የጸሎት አማራጭ እንደተቹት ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ታዋቂ የሬዲዮ ጣቢያ ላይ ስልክ በመደወል አስተያየቱን የሰጠ አንድ ላይቤሪያዊ በበኩሉ በየቤተክርስቲያኑና መስጊዱ ደጃፍ ተደፍተን ለመጪዎቹ 100 አመታት ብንጸልይ እንኳን፣ ጠብ የሚልልን ነገር አይኖርም ማለቱም ተነግሯል፡፡
የጆርጅ ዊሃን የጸሎት ጥሪ ያልተቀበሉት ሄንሪ ፒ ኮስታ የተባሉት ታዋቂ የአገሪቱ የሬዲዮ ጋዜጠኛም፣ አሜሪካ፣ ቻይናና ጃፓንን የመሳሰሉ በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገራት ወደ እድገት ማማ የወጡት በጸሎት ሳይሆን ጠንክረው በመስራትና ብዙ መስዋዕትነት በመክፈል ነው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡

Page 7 of 424