Administrator

Administrator

ተልዕኮው በአልሻባብ ላይ ጥቃት መሰንዘር ነው ተብሏል

ከባድ መሳሪያ የታጠቁ 3ሺህ ያህል ወታደሮችን የያዘ የኢትዮጵያ ጦር፣ በአልሻባብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር ባለፈው ሰኞ ወደ ሶማሊያ መግባቱን ዘ ኔሽን ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡ከሶማሊያ መዲና ሞቃዲሾ በ450 ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምትገኘዋ ዶሎ ከተማ የሚኖሩ የአይን እማኞችን በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ከባድ መሳሪያ የታጠቁና በታንክ የታገዙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደ ሉኩ ከተማ ሲጓዙ የታዩ ሲሆን የአካባቢው ነዋሪዎችም ወታደሮቹ የሚያመሩት በአልሻባብ ቁጥጥር ስር ወደምትገኘው ባርዴሬ ከተማ ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ባርዴሬ በሶማሊያ ጌዶ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ከተሞች በአልሻባብ ቁጥጥር ስር የምትገኝ ብቸኛዋ ከተማ ናት ያለው ዘገባው፤ አልሻባብ በተለይም በተያዘው የረመዳን ጾም ወቅት በሶማሊያ መንግስትና በአሚሶም ጦር ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ገልጿል፡፡የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ በበኩሉ፤ የኢትዮጵያ ጦር እ.ኤ.አ በ2006 አሸባሪውን አልሻባብ ለመደምሰስ ወደ ሶማሊያ መግባቱን አስታውሶ፣ ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያትም የኢትዮጵያ ጦር በተደጋጋሚ የሶማሊያን ድንበር አልፎ መግባቱን ገልጧል፡፡አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ ይዟቸው ከነበሩ አብዛኞቹ አካባቢዎች ቢለቅም መጠነ ሰፊ ጥቃት መሰንዘሩን ገፍቶበታል ያለው ዘገባው፤ ባለፈው ማክሰኞ በሰሜን ምስራቅ ኬንያ በፈጸመው ጥቃት 14 ሰዎችን መግደሉንም አክሎ አስታውሷል፡፡

    መኖሪያ ቤቶችንና ንብረቶችን በኢንተርኔት መሸጥና መግዛት የሚያስችል ዘመናዊ የግብይት ሥራ
የሚያከናውን “ላሙዲ” የተባለ አለምአቀፍ የኦንላይን ሪልስቴት ኩባንያ ሥራ ጀመረ፡፡ደንበኞች ንብረታቸውን በቀላሉ ለመሸጥና ለመግዛትያስችላቸዋል የተባለው ዘመናዊው የኢንተርኔት መገበያያበኢትዮጵያ ሥራ መጀመሩን አስመልክቶ ከትናንት በስቲያበኩባንያው ቢሮ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይእንደተጠቆመው፤ በአገሪቱ ሪልእስቴቶች ከጊዜ ወደ ጊዜእያደጉና እየሰፉ የመጡ ሲሆን በዚህም የተነሳ ደንበኞችስለ መኖሪያ ቤቶች በቂና ጥልቀት ያለው መረጃ ለማግኘትየሚችሉበት መንገድ በስፋት ሊኖር ይገባል፡፡ ኩባንያውገዢና ሻጭ በኦንላይን ተገናኝተው መኖሪያ ቤታቸውንናሌሎች ንብረቶች እንዲገበያዩ ያስችላል ተብሏል፡፡ኩባንያው ኢንተርኔት ለማይጠቀሙ ደንበኞቹዳያል 4 ሆም የተሰኘ የስልክ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆንደንበኞች ስልክ በመደወል የሚፈልጉትን መኖሪያ ቤትበተመለከተ ዝርዝር መረጃና አገልግሎት እንደሚያገኙተገልጿል፡፡ እስካሁን ከተለያዩ ሪል እስቴቶችና ወኪሎችያገኛቸውን 20ሺ ገደማ መኖርያ ቤቶችና ንብረቶችበድረገፁ ላይ እንዳቀረበም ለማወቅ ተችሏል፡፡ላሙዲ በተለያዩ ዘርፎች የኦንላይን አገልግሎትየሚሰጥ ሲሆን በኬንያ፣ ታንዛኒያ፣ ናይጀሪያ፣ ጋና፣ኡጋንዳና ሩዋንዳ ቢሮዎቹን ከፍቶ ተመሳሳይአገልግሎቶችን በመስጠት ላይ የሚገኝ ኩባንያ እንደሆነታውቋል፡፡

  ዛሬ በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ ይጀመራል
   የክረምቱን መግባት ተከትሎ በመዲናዋ ታላቅ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ዘመቻ አርሴማ በሚል የተዘጋጀ ሲሆን ዛሬ በአቡነ ጴጥሮስ አደባባይ አካባቢ ተከላው ይጀመራል፡፡  
 ወደ 150 ሰው ገደማ ይሳተፍበታል ተብሎ በሚጠበቀው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም፤ከአቡነ ጴጥሮስ እስከ ፖሊስ ክበብ ባለው የዋናው መንገድ አካፋይ ላይ ወደ 280 የተለያዩ የዛፍ ዝርያዎች እንደሚተከሉ ፕሮጀክቱን የሚመራው ኤልፍሬዝ ፕሬስ ስራዎች ኃላ.የተ.የግ. ማህበር አስታውቋል፡፡
የችግኝ ተከላ አስተባባሪዋ አርሴማ በቀለ፤ከዛሬው ፕሮግራም በተጨማሪ ከሐምሌ 4-9  ለ 5 ቀናት የሚዘልቅ ታላቅ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመዲናይቱ መዘጋጀቱን ለአዲስ አድማስ ገልጻለች፡፡  የችግኝ ተከላው ሐምሌ 4 በሚኪላንድ አካባቢ የሚጀመር ሲሆን በሌሎች በተመረጡ አካባቢዎችም ይከናወናል ተብሏል፡፡
የችግኝ ተከላው የሚካሄደው በበጐ ፍቃደኛ ወጣቶችና የህብረተሰቡ ክፍሎች መሆኑን የጠቆመችው አስተባባሪዋ፤የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ችግኞችን በጉዲፈቻ (በአደራ) እንደሚሠጥና ተካዩ አመቱን ሙሉ የመንከባከብ ግዴታ እንደሚጣልበት ተናግራለች፡፡  
የአካባቢ መራቆት በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ የገለጸችው አስተባባሪዋ፤ድርጅቷ እየጠፋ ያለውን የደን ሃብት የመታደግ አላማ አንግቦ መርሃግብሩን ለማከናወን እንዳቀደ ገልፃለች፡፡ በየአመቱም የችግኝ ተከላና እንክብካቤ በመዲናዋና ከመዲናዋ ውጪም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ገልፃለች፡፡
ኤልፋሬዝ ፕሬስ ስራዎች “አርሴማ” የተሰኘች ጋዜጣ የሚያሣትም ሲሆን ላለፉት 7 አመታት በማህበራዊና በሴቶች ጉዳይ ላይ አተኩራ ስትታተም ቆይታለች፡፡

ድምፃቸው ጠፍቶ የከረሙት ወጣቶቹ የጃኖ ባንድ የሙዚቃ አባላት ከሚቀጥለው ሳምንትጀምሮ በክለብ H20 ማቀንቀን የሚጀምሩ ሲሆን ለመዲናዋ የመጀመሪያ ነው የተባለውን የሮክሙዚቃ ለታዳሚዎች ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ባንዱ ከተቋቋመ ወዲህ በምሽት ክለብ የሙዚቃ ሥራውን ሲያቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያውእንደሚሆን ታውቋል፡፡የባንዱ አባላት ሁለተኛ የሙዚቃ አልበማቸውን በሦስት ወራት ጊዜ ወስጥ እንደሚለቁምለአዲስ አድማስ አስታውቀዋል፡፡ከዚህም በተጨማሪ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች ለ1 ወር የሙዚቃ ኮንሰርት ያቀርባሉ
ተብሏል፡፡ የጃኖ ባንድ አባላት ተለያይተዋል በሚል ሲናፈስ የቆየውን ወሬ መሰረተቢስ ነው
በሚል ባንዱ አስተባብሏል፡፡

- 172 ሴቶች ተጠልፈዋል፣ 79 ሴቶችና ልጃገረዶች ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባቸዋል
- መንግስት ወታደሮቼ ፈጸሙት የተባለውን ድርጊት ለማመን ይከብደኛል ብሏል

     የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወታደሮች በአገሪቱ ሴቶችና ልጃገረዶች ላይ ጠለፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ግርፋት፣ በቁማቸው በእሳት ማቃጠል፣ ግድያና የመሳሰሉ አሰቃቂ ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶችን ፈጽመዋል ማለቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ቃል አቀባይ በበኩላቸው፤ ወታደሮቻችን በገዛ ህዝባቸው ላይ ይህን አይነት አሰቃቂ ተግባር ይፈጽማሉ ብለን ለማመን ይቸግረናል፣ ይሄም ሆኖ በሪፖርቱ የቀረቡትን ውንጀላዎች ችላ አንላቸውም፣ ጉዳዩን በጥልቀት መርምረን ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የደቡብ ሱዳን ሴቶችና ልጃገረዶች በአገሪቱ ወታደሮች የሚፈጸምባቸው ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እጅግ አሰቃቂ ነው ያለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አንዳንዶቹም ተጠልፈው በግዳጅ ከመደፈራቸው ባሻገር፣ በቁማቸው በእሳት እንዲቃጠሉ መደረጋቸውን ደርሼበታለሁ ብሏል- ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው ሪፖርት፡፡
በመንግስት ጦርና በአማጽያን መካከል ላለፉት 18 ወራት የዘለቀው የደቡብ ሱዳን ግጭት፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመባባስ ወደ ደም አፋሳሽ ጦርነት ማምራቱንና አገሪቱን የከፋ ቀውስ ውስጥ እየከተታት መሆኑን ዘገባው ጠቁሟል፡፡ ግጭቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ በመንግስት ወታደሮች ከ172 በላይ የአገሪቱ ሴቶች መጠለፋቸውንና 79 የሚሆኑ ሴቶችና ልጃገረዶችም ወሲባዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው የተመድ ሪፖርት፣ ዘጠኝ ያህል ሴቶችና ልጃገረዶች ተገደው ከተደፈሩ በኋላ በእሳት መቃጠላቸውን ይፋ አድርጓል፡፡
115 የአይን እማኞችንና የጥቃት ሰለባዎችን እማኝነት በመጥቀስ በደቡብ ሱዳን የተመድ ልኡክ ያወጣው ሪፖርት እንዳለው፣ በአገሪቱ መንግስት ወታደሮች እየተፈጸመ የሚገኘው ጥቃት እየተባባሰ ወደ አሰቃቂ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ ሱዳን ትሪቢዩን በበኩሉ፤ የመንግስት ጦርና የአማጽያኑ ወታደሮች የአገሪቱን ዜጎች ብሄርን መሰረት አድርገው እንደሚገድሉና መንደሮችን በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚያቃጥሉ በሪፖርቱ መገለጹን ዘግቧል፡፡

አወዛጋቢው የብሩንዲ ምርጫ ባለፈው ሰኞ መካሄዱን ተከትሎ ባለፈው ረቡዕ በመዲናዋ ቡጁምቡራ በተቀሰቀሰ ግጭት አንድ የፖሊስ መኮንንን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን ቻናል አፍሪካ ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ህገ መንግስቱ ከሚፈቅድላቸው ውጪ ለሶስተኛ ዙር በምርጫ ለመወዳደር መወሰናቸውን የተቃወሙ ዜጎች ለወራት የዘለቀ ግጭት ሲፈጥሩ የቆዩ ሲሆን፣ የምርጫ ውጤቱ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅበት ባለፈው ረቡዕም ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
17 ያህል የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ባገለሉበት የሰኞው ምርጫ ድምጽ ለመስጠት የተመዘገበው ህዝብ ብዛት 3.8 ሚሊዮን እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ሆኖ በመዲናዋ ቡጁምቡራና በአካባቢዋ ድምጹን የሰጠው ህዝብ ቁጥር አነስተኛ ነበር ብሏል፡፡ የምርጫው ድምጽ ቆጠራ ባለፈው ማክሰኞ መጠናቀቁን የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ለወራት በዘለቀው ግጭት ከ70 በላይ የአገሪቱ ዜጎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 ባለፉት ስድስት ወራት 137
ሺህ ስደተኞች አውሮፓ ገብተዋል
- በባህር ጉዞ የሞቱ ስደተኞች
ቁጥር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል

   ባለፉት ስድስት ወራት አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ የአለማችን አገራት በመነሳት የሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ የተጓዙ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ታይቶ በማይታወቅበት ደረጃ ላይ መድረሱንና በስደት ጉዞ ላይ ሳሉ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥርም ከሶስት እጥፍ በላይ መጨመሩን ሲኤንኤን ዘገበ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ባለፉት ስድስት ወራት የሚዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ ግሪክ፣ ጣሊያን፣ ማልታ እና ስፔን የገቡ ስደተኞች ቁጥር 137 ሺህ የደረሰ ሲሆን ይህም ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅና አዲስ ክብረወሰን ያስመዘገበ ነው፡፡
አብዛኞቹ ስደተኞች ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት ያለባቸው አገራት ዜጎች መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ በተጠቀሰው ጊዜ ባህር አቋርጠው ወደ ጣሊያንና ግሪክ ከገቡት ስደተኞች መካከል አንድ ሶስተኛ የሚሆኑት በጦርነት የምትታመሰዋ ሶርያ ዜጎች እንደሆኑ ገልጧል፡፡ ከሶርያ በመቀጠል የበርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት አገራት፣ በግጭት ውስጥ ያለችው አፍጋኒስታንና ጨቋኝ ስርዓት የገነነባት ኤርትራ ናቸው ያለው ሪፖርቱ፣ ወደ አውሮፓ የሚሰደዱ በርካታ ስደተኞች መነሻ የሆኑት ሌሎች አገራትም ሶማሊያ፣ ናይጀሪያ፣ ኢራቅና ሱዳን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
የተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ሃላፊ አንቶኒዮ ጉቴሬስም እንደገለጹት፣ አብዛኞቹ ስደተኞች ወደ አውሮፓ የሚጓዙት የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ሳይሆን በአገራቸው ያለውን ግጭት፣ ጦርነትና ስቃይ ለመሸሽና ህይወታቸውን ለማዳን በማሰብ ነው ብለዋል፡፡ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ወደ አውሮፓ የገቡ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ቁጥር 75 ሺህ እንደነበር ያስታወሰው የተመድ ሪፖርት፣ ይህ ቁጥር ባለፉት ስድስት ወራት የ83 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 137 ሺህ ደርሷል ብሏል፡፡
ባለፉት ስድስት ወራት የሜዲትራንያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር፣ ካለፈው አመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከሶስት እጥፍ በላይ ጨምሯል ያለው የተመድ ሪፖርት፣ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ 1ሺህ 867 ስደተኞች መሞታቸውን አስታውቋል፡፡
ባለፉት ሁለት ወራት ጣሊያን 67 ሺህ 500፣ ግሪክ 68 ሺህ ስደተኞችን እንደተቀበሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የስደተኞቹ ቁጥር  በቀጣዮቹ ስድስት ወራትም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡


- የተናዘዙት ኃጢያት ለሸክም አይከብድም፡፡
የህንዶች አባባል
- ሃዘንህ ከጉልበትህ ከፍ እንዲል አትፍቀድለት፡፡
የስዊዲሽ አባባል
- ወጣትነት በየቀኑ የሚሻሻል ጥፋት ነው፡፡
የስዊዲሽ አባባል
- የተረታ ሰው የተሰጠውን አሜን ብሎ ይቀበላል፡

የሰርቢያኖች አባባል
- ምሳሌያዊ አባባሎች የታሪክ ቤተ መፃህፍት
ናቸው፡፡
የቤልጂየሞች አባባል
- ማንንም እንዲያገባ ወይም ወደ ጦርነት እንዲሄድ
አትምከር፡፡
የዳኒሽ አባባል
- እንቁላልና መሃላ በቀላሉ ይሰበራሉ፡፡
የዴኒሽ አባባል
- በባህር ላይ ሃብታም ከመሆን ይልቅ በመሬት
ላይ ድሃ መሆን ይሻላል፡፡
የዴኒሽ አባባል
- አንደኛው እጅ ሲገነባ፣ ሌላኛው ያወድማል፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- የበሰበሰ ዝናብ አይፈራም፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- እናት ስትሞት፣ ጎጆውም ይሞታል፡፡
የኢራቃውያን አባባል
- ውበት የሴቶች ጥበብ ነው፡፡ ጥበብ የወንዶች
ውበት ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል
- የቅፅበት ንዴትን ከታገስክ የ100 ቀናት ሃዘንን
ታመልጣለህ፡፡
የቻይናውያን አባባል
- አይጦችን ለማጥፋት ቤትህን አታቃጥል፡፡
የአረቦች አባባል
- መሸለም ቢያቅትህ ማመስገን አትርሳ፡፡
የአረቦች አባባል
- ፀሐይ ምንጊዜም ቢሆን መጥለቋ አይቀርም፡፡
የአረቦች አባባል
- ልጆች የሌሉበት ቤት መቃብር ነው፡፡
የህንዶች አባባል
- ከአዲስ ሃኪም የቆየ በሽተኛ ይሻላል፡፡
የህንዶች አባባል



በወጣቷ ገጣሚ ፅጌረዳ ጌታቸው የተፃፉ የእንግሊዝኛ ግጥሞች የየዘ “The Unspoken Outlook” የተሰኘ የግጥም መድበል በዛሬው ዕለት ከ10፡30 ጀምሮ ቦሌ ኤርፖርት መዳረሻ ጋ በሚገኘው ቲኬ ህንፃ፣ 8ኛ ፎቅ ላይ ይመረቃል፡፡ በምረቃው ሥነ -ሥርዓት ላይ የስነ ፅሁፍ ባለሙያ ሂሳዊ ዳሰሳ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በ84 ገፆች የተቀነበበው የግጥም መድበሉ፤ በ38 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ገጣሚዋ ዘንድሮ በሲቪል ኢንጂነሪንግ ከአምስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እንደምትመረቅ ታውቋል፡፡

በደራሲ ገነት አዲሱ የተፃፈው “የማንነት አደራ” የተሰኘ የረዥም ልብወለድ መጽሐፍ ባለፈው እሁድ በራስ አምባ ሆቴል የተመረቀ ሲሆን ከሳምንቱ መጀመሪያ አንስቶ በመሸጥ ላይ እንደሆነ ታውቋል፡፡
“ከዓመታት ጀምሮ በርካታ ሃሳቦች በውስጤ ከወዲያ ወዲህ ሲሉ ኖረዋል፤ እነሆ ዘመናቸው መጥቶ በአምላክ እርዳታ ቃሎች ከጥበብ ጋር እንደመዋደድ ያሉልኝ ሲመስለኝ ዛሬ ሃሳቦቼ ጽሑፍ ሆነው ሊወለዱ ደፈሩ” ብላለች፤ ደራሲዋ በመፅሀፉ መግቢያ ላይ ባሳፈረችው ሃሳብ፡፡
በ376 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ94 ብር፣ ለውጭ በ25 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲዋ በኢንተርናሽናል ቴኳንዶ በአፍሪካ የመጀመሪያውን 4ኛ ዲግሪ ያገኘች የማርሻል አርት አስተማሪ ስትሆን “አላዳንኩሽም” እና “ምርቅዝ በቀል” የተሰኙ ፊልሞች ላይ በመተወንም ትታወቃለች፡፡