Administrator

Administrator

 የፈረንጆች አመት 2019 የመጀመሪያዋ ቀን በሆነቺው ባለፈው ማክሰኞ ብቻ በመላው አለም ከ395 ሺህ በላይ ህጻናት ተወልደዋል ተብሎ እንደሚገመት የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ አስታውቋል፡፡
ከአለማችን አገራት መካከል ጃኑዋሪ 1 ቀን 2019 ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህጻናት የተወለዱባት ቀዳሚዋ አገር ህንድ ናት ያለው ድርጅቱ፣ በዕለቱ 69 ሺህ 944 ህንዳውያን ህጻናት ወደዚህች አለም መምጣታቸውን አመልክቷል፡፡ በዕለቱ 44 ሺህ 940 ህጻናት የተወለዱባት ቻይና በሁለተኛነት ስትከተል፣ ናይጀሪያ በ25 ሺህ 685 ህጻናት የሶስተኛነት ደረጃን መያዟንም ድርጅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
ፓኪስታን በ15 ሺህ 112፣ ኢንዶኔዢያ በ13 ሺህ 256፣ አሜሪካ በ11 ሺህ 86፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በ10 ሺህ 53፣ ባንግላዴሽ በ8 ሺህ 428 ህጻናት በቅደም ተከተላቸው መሰረት እስከ ስምንተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውን የገለጸው ድርጅቱ፣ በዕለቱ ከተወለዱት የአለማችን ህጻናት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በስምንቱ አገራት ውስጥ እንደተወለዱም አመልክቷል፡፡

የዚምባዌ መንግስት ከዩኒቨርሲቲ ቢመረቁም ስራ ሊያገኙ ያልቻሉ ከ16 ሺህ በላይ የአገሪቱ ዜጎችን በቅርቡ ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ ማቀዱን ሳውዝ ሱዳን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
የዚምባቡዌ የከፍተኛ ትምህርት፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ፕሮፌሰር አሞን ሙሪዋን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አገሪቱ በርካታ ቁጥር ያላቸው ምሩቃንን ወደ ደቡብ ሱዳን በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው፡፡
ዚምባቡዌ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2019 ብቻ በተለያዩ የሙያ መስኮች ከዩኒቨርስቲዎች የተመረቁና ስራ ያልያዙ ከ16 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ደቡብ ሱዳን ለመላክ ማቀዷን የጠቆመው ዘገባው፣ ታዋቂ የዚምባቡዌ ጋዜጠኞች ግን በርካታ ቁጥር ያላቸውን የራሷን የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ስራ ማስያዝ ያልቻለችው ደቡብ ሱዳን ከዚምባቡዌ ምሁራንን ማስገባቷ አስቂኝ ነው ሲሉ መተቸታቸውን አመልክቷል፡፡

 አንድ ፅሁፍ የሚከተለውን አስፍሯል፡፡
“አንድ ጉብል አንዲትን ጉብል ለማግባት መንገድ ላይ ነው፡፡
“እንደምወድሽ ታውቂያለሽ?” አላት፡፡
“አዎ በደምብ አውቃለሁ” ብላ መለሰች፡፡
“እንግዲህ የነገ ዕጣ ፈንታችንን ለመወሰን መወያየት መጀመር አለብን”
“ደስ ይለኛል”
“መቼ እንደምንጋባ መወሰን ይኖርብናል”
“ትንሽ አልፈጠነም”
“እንዲያውም! ለገና በዓል ማለቅ ያለበት ነገር ነው”
“ቢያንስ ለሳምንታት ማየት አለብን”
“እሱን አልቀበልሺም”
“እሺ በሶስት ቀን ጊዜ ውስጥ መልስ ልስጥህ?”
“እሱ ጥሩ”
በእነዚህ ሦስት ቀናት ውስጥ አንድ ነገር ተከሰተ፡፡
የሚኖርበት ሆቴል ክፍል አንዲት በጣም ቆንጆ፣ ቅርጿ የሚያማልል፣ ዐይነ - ግቧ የሚስብ ሴት፤ ስስ ቀሚስ ለብሳ፣ ፊቱ ሽንጥና ዳሌዋን እያማታች ትንጎራደድበት ጀመር፡፡
ሁሉ ነገሯ እንዳማረው ገብቶታል፡፡ እሷም ገብቷታል፤ ጓጉቶላታል፡፡ ግን ደግሞ ሊያገባ ጥቂት ቀናት የቀረው ሰው ነውና የቸገረው ይመስላል፡፡ ቆንጆዋ እጮኛው የላከችበት ፈተናም ልትሆን ትችላለች፡፡ ተነስቶ ወጣና ደጅ መኪናውን ወዳቆመበት ቦታ ሮጠ፡፡” ይልና፤ ከግርጌው “ከዚህ ታሪክ የምናገኘው ትምህርት ኮንዶም መኪና ውስጥ ማስቀመጥ እንደሚገባ ነው!!”
*   *   *
 በእቅድ መንቀሳቀስ የህይወታችን መመሪያ ሊሆን ይገባዋል፡፡ የአንድ መስሪያ ቤት መመሪያ ለመቅረፅ ምጥ ያህል አድካሚ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ የአንድ ሰው የህይወት መመሪያ ግን እጅግ ውስብስብና መጀመሪያውን እንጂ መጨረሻውን የማንተነብየው የጉዞ ሂደት ነው። ፍፃሜውን አወቅንም አላወቅንም ግን መኖር ይቀጥላል፡፡ የሀገር ጉዳይ ሲሆን ደግሞ የጨዋታው ህግ ይለወጣል፡፡ አንደኛ፤ መመሪያው ከመቀረፁ አስቀድሞ የአቃጁ ቡድን ያየዋል፡፡ ግራ ቀኙን ይመዝነዋል፡፡ ይሰርዛል፡፡ ይደልዛል፡፡ እመጫት ያስገባል፡፡ እዝባር እያደረገ አማራጭ ያስቀምጣል! እንዲህ ተጠንቶና ተጣርቶ የመጣ መመሪያ፤ የስህተት ዕድሉ እጅግ ውሱን ነው፡፡
በዚህ መንገድ ነጥረው ያልወጡ መመሪያዎች ግን የሀገር ዕዳ ናቸው፡፡ የአቅም ግንባታ ሳይሆን አቅመ - ጎዶሎነትን ጠቋሚ ናቸው! ነገር ዓለሙ አልሆን ካለንና የሄድነው መንገድ ሁሉ ወደ ጥፋት እያመራ ከመሰለን ወደ ኋላ ከመመለሳችን በፊት ቆም ብሎ ማውጠንጠን፣ የረገጥነውን ሁሉ መፈተሽ፣ ትርፍና ኪሳራውን ማስላት ያሻል፡፡ ከዚያ እንዳዲስ ሥራ ከመጀመር አንስቶ ችግሩን እየፈተሹ መላ መላውን እስከ ማበጀት መታገል ነው! ለዚህ ጠቃሚው ዘዴ ቀና ቀናውን ማትና ከብዙ መጥፎዎች መካከል እንኳ ተዛማጁ መልካም ነገርን በትዕግሥት መፈልፈልና ማግኘት ነው! መንገዳችን እንዳይምታታ ግን ሶስት ነገሮችን መገንዘብና ማስገንዘብ ይገባናል፡-
1ኛ/ የጊዜ ዕቅድ
2ኛ/ በመለስተኛ ፕሮግራም የመስማማት ዕቅድ
3ኛ/ ከራስና ከወዳጅ ዘመድ ጥቅም ባሻገር፣ አገርንና ህዝብን የማሰብ ዕቅድ
በጊዜ ውስጥ አገርን ማሰብ ይቻላል፡፡ ሁላችን ያለፅንፈኛ የፓርቲም ሆነ የድርጅት አጀንዳ እንደ ኑሮና እንደ ህይወት ህዝባዊ ጠቀሜታ ተግቶ ማገዝና መተጋገዝ ይቻላል፡፡ ከኢኮኖሚና ፖለቲካዊው ሰንሰለት የቱን ቀለበት ብናላላ፣ የቱን ቀለበት ብናጠብቅ ይሻላል? የሚል ዕቅድ ማቀድም ይቻላል፡፡ መነሻችንን እናቅድ፣ መድረሻችንን እንወቅ!
ይህን ለማድረግ ግን በወርቅ አልጋ፣ በእርግብ ላባ ላይ መተኛት የለብንም፡፡ አንችልምም! እንደ ጥንቱ ሶሻሊስታዊ መፈክር፤ “ትግላችን እረጅም ጉዟችን መራራ” ባንልም፣ ብዙ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አቀበት ገና መውጣት እንዳለብን አንስትም! የትኛውም ርዕዮታዊ መንገድ ቢታሰብ - (ሀ) የተቃርኖ ህግን (ለ) በአንድነት ውስጥ ልዩነትን እና (ሐ) የአዲሱን አሸናፊነት ማመን ግዴታችን መሆኑን ተግተን እናውቃለን!
“ጥንትም ወርቅ በእሳት፣ እኛም በትግላችን እየተፈተንን፣ እናቸንፋለን!” ብለን እንደነበር ለአፍታም ሳንጠራጠር ዛሬም እንናገራለን!
ኢትዮጵያ ብዙ ያልተዘጉ በሮች አሏት - ለሌቦች ክፍት የሆኑ፣ አያሌ የተከፈቱ በሮች! ሌቦቹ፣ ሌቦቹ ብቻ አይደሉም! ያቀበለ፣ ሀሳቡን የደገፈ፣ “ቢዝነስ ነው” እያለ የሰበከ፣ ሀሳቡን ያስተላለፈ፣ ሚስጥር አድርጎ ያቆላለፈ፣ ደብዛው እንዲጠፋ የደገፈና ያደጋገፈ … ሁሉም ሌቦች ናቸው!
ዛሬ የሌቦቹ ቋንቋ “በራቸውን ሳይዘጉ ሌባ ሌባ ይላሉ” አለች ውሻ፤ የሚለውን ተረት መተረት ሆኗል፡፡ ለማያውቅሽ ታጠኚ ማለት የኛ ፈንታ ነው! እውነቱን ለመናገር ግን በሩን ገርበብ ያደረገውም፣ ያለቁልፍ የተወውም፣ ቁልፍ እንዳይኖረው ያደረገውም፤ …. ሁሉም ሌቦች ናቸው! ወንጀሉ ሙሉው ሰንሰለቱ ላይ ተንጠልጥሎ ያለ መሆኑን አንርሳ! የተንጠለጠለው ወንጀል”  አንድ ቀን ሁሉንም ያንጠለጥላል፤ ብለን እንጠብቃለን!
ለክርስትና አማኞች
እንኳን ለብርሃነ ልደቱ አደረሳችሁ!

 በአዲስ አበባ ከሚገኙ ክፍለ ከተሞች ውስጥ ጉለሌና ቦሌ የግዴታ ጋብቻ በብዛት እንደሚፈፀምባቸው ተገለጸ፡፡  ባለፈው ሐሙስ በኢንሽየቲቭ አፍሪካ አዘጋጅነት፣ “ለውጥን በመለወጥ መተግበር” በሚል መሪ ሃሳብ በሞዛይክ ሆቴል ለአንድ ቀን በተካሄደ ስብስባ ላይ 20 የሁለተኛ ደረጃና የልዩ ፍላጐት ትምህርት ቤቶች መምህራን፣ ርዕሰ መምህራንና ሴት ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
የኢንሽየቲቭ አፍሪካ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክቡር ገና በስብሰባው ላይ እንደገለጹት፤ድርጅታቸው ከኢትዮጵያ መምህራን ማኀበር ጋር በመተባበር ባካሄደው ጥናት፤40 በመቶ በሚሆኑት ተማሪዎች ላይ ልዩ ልዩ ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈጸም አረጋግጠዋል፡፡ ጥቃቱ በሁለቱም ፆታዎች ላይ የሚደርስ ቢሆንም ይበልጥ ተጐጂዎች  ልጃገረድ ተማሪዎች ናቸው ብለዋል፤ጥናቱን በመጥቀስ፡፡   
የስብሰባው ዋና አላማ በትምህርት ቤት አካባቢ በተማሪዎች ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት ለመቀነስ ምን ማድረግ እንደሚቻል ሃሳብ ለማመንጨት መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፤ችግሩን ፈጥኖ መከላከል ካልተቻለ የሚያስከትለው ጉዳት ቀላል እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡   
ለተሰብሳቢዎቹ የውይይት መነሻ መረጃዎችን ያቀረቡት፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ፆታ ኃላፊ፣ ወ/ሮ አበባ ዘውዴ፤የግዴታ ጋብቻ በአንዳንድ ክፍለ ከተሞች የሚታይ ቢሆንም በቦሌና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች በብዛት እንደሚፈጸም  አስረድተዋል፡፡
በ2010 የመጨረሻዎቹ ስድስት ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ 7 ሴት ተማሪዎች በግዳጅ እንዲያገቡ መደረጋቸውን የጠቆሙት ኃላፊዋ፤ በ35 ሴት ተማሪዎችና በ17 ወንዶች ላይ የፆታ ጥቃት መፈፀሙንና ከጥቃት አድራሾች ውስጥ አባትና አጐት እንደሚገኙበት አስምረውበታል፡፡  
“ለውጥን በመለወጥ መተግበር” በሚል መርህ የሚካሄደው የኢንሽየቲቭ አፍሪካ ፕሮግራም 20 ሚሊዮን ብር በጀት የተያዘለትና አዲስ አበባ በሚገኘው የስዊድን ኤምባሲ የሚደገፍ መሆኑ ታውቋል፡፡


 የአለማችን ቢሊየነሮች ትርፍና ኪሳራ
የእንግሊዝን ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ዕቅድና በአሜሪካና በቻይና መካከል የተፈጠረውን የንግድ ጦርነት ጨምሮ የአለማችን የአክሲዮን ገበያ፣ ንግድና ኢንቨስትመንት በቀውስ ውስጥ ሆኖ የከረመበትና ስመጥር ኩባንያዎችና ቢሊየነሮች የከፋ ኪሳራን ያስተናገዱበት አመት ነበር - 2018፡፡
የአለማችን ቢሊየነሮች በአመቱ በድምሩ 511 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ገንዘብ እንደከሰሩ የዘገበው ፎርብስ፣ እጅግ ከፍተኛ ኪሳራ የደረሰበት በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 18.7 ቢሊዮን ዶላር ያጣው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግ ነው ብሏል፡፡ 16.2 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን የአመቱ ሁለተኛው ከፍተኛ ኪሳራ ያስተናገደው የአለማችን ባለጸጋ፣ ኢንዲቴክስ የተባለው የአልባሳት አምራች ኩባንያ ባለቤት የሆነው አማኒኮ ኦርቴጋ ነው፡፡
ለዙክበርግ ከፍተኛው የኪሳራ አመት ሆኖ ያለፈው 2018፣ የሃብት መጠኑን በ27.9 ቢሊዮን ዶላር ለጨመረው የአማዞኑ መስራች ጄፍ ቤዞስ በአንጻሩ፣ ከፍተኛ የትርፍ ዓመት ነበር ተብሏል፡፡ በፋሽን ኢንዱስትሪው መስክ የተሰማራው ዩኒሎ ኩባንያ መስራችና ባለቤት ጃፓናዊው ቢሊየነር ታዳሺ ያኒ በ7 ቢሊዮን ዶላር፣ ቫጊት አሌክፔሮቭ በ4.6 ቢሊዮን ዶላር የሃብት መጠናቸውን በመጨመር ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አመቱን በስኬት እያጠናቀቁ መሆኑ  ተነግሯል፡፡


Tuesday, 01 January 2019 00:00

የአገራት የጤናማነት ደረጃ

 በአለማችን 149 አገራት ላይ የተደረገን ጥናት ጠቅሶ ዴይሊ ሜይል እንደዘገበው፣ ሲንጋፖር ከአለማችን አገራት መካከል ደረጃውን የጠበቀ የጤና እንክብካቤ በመስጠት አቻ ያልተገኘላት፣ እጅግ ጤናማዋ አገር በመሆን የ2018 የፈረንጆች አመትን በቀዳሚነት አጠናቅቃለች፡፡
የአገራትን የጤና አገልግሎት መሰረተ ልማት፣ የበሽታዎች ክስተት መጠንና ሌሎች መስፈርቶችን መሰረት አድርጎ በወጣው የአመቱ የአለማችን አገራት የጤናማነት ደረጃ ዝርዝር፣ በሁለተኛነት የተቀመጠችው ሉግዘምበርግ ስትሆን፣ ጃፓን፣ ስዊዘርላንድና ኳታር እስከ አምስተና ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2018 እጅግ ዝቅተኛ የሆነ የጤናማነት ደረጃን ይዘዋል ተብለው ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ ያለውን ደረጃ የያዙት አገራት ደግሞ፣ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ቻድ እና ጊኒ ናቸው፡፡

አለማችን ከፖለቲካ እስከ ሳይንስ፣ ከንግድና ኢንቨስትመንት እስከ መዝናኛው ኢንዱስትሪ በተለያዩ መስኮች ደማቅ ታሪክ የሰሩና እውቅናን ያተረፉ በርካታ ታላላቅ ሰዎችን በሞት ያጣችበት አመት ነበር - 2018፡፡
በአመቱ ከዚህ አለም በሞት ከተለዩ የኪነጥበቡ ዘርፍ ከዋክብት መካከል ለስድስት አስርት አመታት በሙዚቃው መስክ ደምቃ የዘለቀችው የአለማችን የሶል ሙዚቃ ንግስት አሪታ ፍራንክሊን አንዷ ናት፡፡ የበርካታ ታላላቅ ሽልማቶች ባለቤት የሆነችው አሪታ ፍራንክሊን፣ ባለፈው ነሃሴ ወር ላይ ነበር በተወለደች በ76 አመቷ ከዚህ አለም በሞት የተለየችው፡፡
በሳይንስና ቴክኖሎጂው መስክ በአመቱ ካጣናቸው ዝነኞች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ደግሞ፣ በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ በ76 አመቱ በሞት መለየቱ የተሰማው እንግሊዛዊው የፊዚክስ ሊቅ ስቴፈን ሃውኪንግ ነው፡፡
ወደ ፖለቲካው መስክ ጎራ ስንል ደግሞ በህዳር ወር ላይ በተወለዱ በ94 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩትን የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆርጅ ኤች ደብሊው ቡሽን እናገኛለን፡፡ በፖለቲካው መስክ በአመቱ በሞት ከተለዩት ታላላቅ ሰዎች መካከል የሚጠቀሱት ሁለት አፍሪካውያን ደግሞ፣ የኖቤል የሰላም ተሸላሚው የቀድሞው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ጋናዊው ኮፊ አናን እና ደቡብ አፍሪካዊቷ የጸረ አፓርታይድ ታጋይ ዊኒ ማንዴላ ናቸው፡፡

Tuesday, 01 January 2019 00:00

የተፈጥሮ አደጋዎች


    በአለማችን የተለያዩ አገራት በፈረንጆች አመት 2018 የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ከ5 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት የዳረጉ ሲሆን 28.9 ሚሊዮን ያህል ሰዎችንም በአደገኛ የአየር ንብረት ለውጦች ሳቢያ ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ መዳረጋቸው ተዘግቧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ እንዳለው፣ በአመቱ የተከሰቱ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ ሰደድ እሳት፣ ጎርፍና ሌሎች አደገኛ የተፈጥሮ አደጋዎች በርካቶችን ለሞትና ለመፈናቀል የዳረጉ ሲሆን ፍሎሪዳን የመታው ሃሪኬን ሚካኤል፣ የካሊፎርኒያ የሰደድ እሳት፣ የስፔንና የፈረንሳይ ሃይለኛ ሙቀት፣ የኢንዶኔዢያ የመሬት መንቀጥቀጥና ጎርፍ በአመቱ ከተከሰቱና የከፋ ጥፋት ካደረሱት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

Tuesday, 01 January 2019 00:00

የስደተኞች ቁጥር

በ2018 የስደተኞች ቁጥር በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ሲሆን 6.3 ሚሊዮን ያህል ዜጎቿ የተሰደዱባት ሶርያ በአለማችን እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች አገራቸውን ጥለው የተሰደዱባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን ዩኤስኤ ቱዴይ ዘግቧል፡፡
ከአለማችን አገራት በርካታ ዜጎችን በማሰደድ የሁለተኛ ደረጃን የያዘቺው 2.6 ሚሊዮን ያህል ዜጎች የተሰደዱባት አፍጋኒስታን ናት ያለው ዘገባው፣  እ.ኤ.አ በ2011 ነጻነቷን ያወጀቺውና እንደ አገር መቆም ተስኗት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትታመስ የኖረቺዋ ደቡብ ሱዳን በ2.4 ሚሊዮን ስደተኞች የሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡
ሌላዋ አፍሪካዊት አገር ሶማሊያ በ806 ሺህ ያህል ስደተኞች የአራተኛ ደረጃን ይዛለች ያለው ዘገባው፣ 723 ሺህ ያህል የሮሂንጋ ሙስሊሞች ወደ ጎረቤት አገር ባንግላዴሽ የተሰደዱባት ማይንማር በአምስተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አመልክቷል፡፡

 በአመቱ በአለማችን ከተከሰቱ አነጋጋሪና የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው ከከረሙ ጉልህ አለማቀፋዊ ጉዳዮች መካከል በቱርክ የሳዑዲ አረቢያ ኢምባሲ የተፈጸመው የጋዜጠኛ ጀማል ካሾጊ ግድያ ይጠቀሳል፡፡
ቻይናና አሜሪካ የገቡበትና ዳፋው ለበርካታ የአለም አገራት ይተርፋል ተብሎ የተሰጋው የንግድ ጦርነት፣ አሜሪካ ከኢራን ጋር የገባቺውን የኒውክሌር ስምምነት በማፍረስ ተጨማሪ ማዕቀብ መጣሏና ለኢየሩሳሌም የእስራኤል መዲናነት በይፋ እውቅና መስጠቷ፣ በውዝግብ የታጀበው የእንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት የመውጣት ዕቅድም በአመቱ አለማቀፋዊ ትኩረትን ስበው የከረሙ ጉዳዮች ናቸው፡፡
ተካርረው የከረሙትና ከዛሬ ነገ ወደ ኒውክሌር ጦርነት ይገባሉ ተብሎ አለም በስጋት ይመለከታቸው የነበሩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕና የሰሜን ኮርያው አቻቸው ኪም ጆንግ ኡን ባልተጠበቀ መልኩ አቋማቸውን ቀይረው በወርሃ ሰኔ ሲንጋፖር ውስጥ ታሪካዊውን ሰላማዊ ውይይት ማድረጋቸውና ኪም ኒውክሌራቸውን ሊያወድሙ መስማማታቸው የአለምን ትኩረት የሳበ ሌላው ጉዳይ ነበር፡፡
የኮንጎ የኢቦላ ወረርሽኝ፣ የሩስያው የአለም የእግር ኳስ ዋንጫ፣ የደቡብ ሱዳን የሰላም ስምምነት፣ የሳኡዲ አረቢያው ልኡል ሞሀመድ ቢን ሳልማን ሚኒስትሮችንና ባለሃብቶችን በሙስና ሰበብ ድንገት ማሰራቸው፣ የፈረንሳይ ተቃውሞና የዚምባቡዌው ሙጋቤና የደቡብ አፍሪካው ጃኮብ ዙማ ከመንበረ ስልጣን መወገድም በ2018 የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ስበው ከከረሙ አለማቀፋዊ ጉዳዮች ተርታ ይሰለፋሉ፡፡


---------------

Page 6 of 417