Administrator

Administrator

    ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት አሮጊት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ የማይታመን ነገር አዩ፡፡ ግቢያቸው በጎርፍ ተጥለቅልቋል፡፡ ውሃው የምድር ቤቱን አጥለቅልቆ ጨርሶ የመጀመሪያውን ፎቅ ሞልቶታል፡፡ አሰቃቂው ነገር ደግሞ ከደቂቃ ደቂቃ፣ ከሰዓት ሰዓት ገና ማጥለቅለቁን እየቀጠለ፣ እያደገ ነው፡፡
አሮጊቷ ከመኝታ ቤታቸው ወደ ውጪ ሲያስተውሉ፣ ጎርፉ ገና ካፋፍ ወደ ታች እየተንደረደረ ነው፡፡ ከፍታውም አፍታ በአፍታ እያደገ ነው፡፡ ሁለት ሰዎች በእጅ በምትቀዘፍ ጀልባ ሆነው በአሮጊቷ ቤት አጠገብ ሲያልፉ፤
“እማማ፣ እማማ፣ ኧረ እማማ!” ብለው ጮኸው ይጣራሉ!
“እመት፤ ምን ፈልጋችሁ ነው?”
“ይውረዱ፡፡ አብረን እንድናለን፡፡ እባክዎ ይምጡ!” አበክረው አሮጊቷን ለመኗቸው፡፡
“አመሰግናለሁ ሂዱ” አሉ አሮጊቷ፡፡ “ለእኔ እሱ የላይኛው ያውቅልኛል” ብለው ወደ ሰማይ አመለከቱ፡፡ አምላካቸው እንደሚያድናቸው በመተማመን መናገራቸው ነው፡፡
ባለ ጀልባዎቹ ትከሻቸውን ከፍ ዝቅ አድርገው፤ እኛ ምንቸገረን በሚል ስሜት በጀልባቸው እየቀዘፉ መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ ማታ ገደማ ውሃው አድጎ አድጎ የመኝታ ክፍላቸውን ወደ ማጥለቅለቅ እየመጣ በመሄዱ፤ አሮጊቷ ያላቸው አማራጭ ጣራው ላይ መውጣት ሆነ፡፡ አሮጊቷ ጣራው ላይ ወጡ፡፡ አንድ ባለሞተር ጀልባ እንዳጋጣሚ ብቅ አለና አያቸው፡፡ ከዚያም፤
“እማማ” ሲል ጮኾ ተጣራ፡፡
“አቤት የእኔ ልጅ” አሉ የሞት ሞታቸውን፡፡
“አይጨነቁ፤ መጥቼ አወርድዎትና በሞተር ጀልባ እንሄዳለን!”
አሮጊቷም፤
“ግዴለህም ልጄ በምንም አትቸገር! ለእኔ እሱ የላይኛው ያውቅልኛል፡፡ አንተ ሂድ በሰላም ግባ” ይሉታል፡፡ ጀርባቸውን ያዞሩበታል፡፡ ሞተሩን ቀስቅሶ እሱም መጭ ይላል!
አሮጊቷ ምንም ሳይቆዩ ጎርፍ ጣራውን ማጥለቅለቅ ስለጀመረ፤ ከጣራው በላይ ወዳለው ወደ ብቸኛው፣ እስካሁን ጎርፍ ወዳልነካው፣ ቦታ፤ ወደ ጭስ ማውጫው አናት ወጡ! እንደ ዕድል ሆኖ የቀይ መስቀል ጎርፍ መከላከያ ቡድን ወደ አሮጊቷ ቤት አጠገብ ይመጣል፡፡
“ወደ ትልቁ ጀልባ ይዝለሉ እማማ!” አለ ከመከላከያ ቡድን አባላት አንዱ፡፡
አሮጊቷ ራሳቸውን ነቀነቁና ኮስተር ብለው፤
“እሱ የላይኛው ያውቃል፡፡ እሱ የትም አይጥለኝም!” ይላሉ፡፡ ትልቁ ጀልባም፤ እየተምዘገዘገ የአሮጊቷን ቤት አልፎ ሄደ፡፡ ውሃው ማደጉን አላቋረጠም፡፡ እስከ ጭስ ማውጫው አናት ደረሰና አሮጊቷን ዋጣቸው፡፡ አሮጊቷ ውሃው እየዋጣቸው ሳሉ ፀሎታቸውን ለአምላካቸው አሰሙ፡፡
“ምነው አምላኬ! አንተን አምኜ ጉድ ታረገኝ?” ሲሉ አማረሩ፡፡
አምላክም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤
“አንቺ ሴት! ችግርሽን አይቼ ሶስት ጀልባ ላክሁልሽ፡፡ ያውም በመጀመሪያ በእጅ የሚዘቀፍ ትንሽ ጀልባ፡፡ ምናልባት ጥሩ ኑሮ ትኖሪ ስለነበር ትንሹን ጀልባ አልቀበልም ያልሺው ያንሰኛል ብለሽ ይሆናል ብዬ! ቀጥዬ በሞተር የሚነዳ መካከለኛ ጀልባ ላኩልሽ፡፡ እሱንም አሻፈረኝ አልሽ፡፡ በሶስተኛው ትልቁን ጀልባ፣ ከነትልቅ ሞተሩ፤ ሊያውም ከነሰራተኞቹ ላኩልሽ፡፡ በጭራሽ አልቀበልም አልሽ! ከዚህ በላይ ምን ላድርግሽ?! ከእንግዲህ የራስሽን መንገድ ፈልጊ!” አላቸው፡፡
*       *       *
ጎርፉንም ድርቅንም ካልተቆጣጠሩት ለከፍተኛ አደጋ እንደሚያጋልጥ እንገንዘብ፡፡ ሲረዷቸው የማይረዱ አያሌ ናቸው፡፡ በዓመታትና በወራት ጊዜ ውስጥ ሳይሆን በቀን ውስጥ ከተከሰተው የማይማሩ ብዙ ናቸው፡፡ ጎርፍ መምጣቱን፣ ክረምት መግባቱን እዩ፤ አጥራቸውን ማጠርን፣ እርከናቸውን መስራትን፣ ጣራቸውን ማጠንከርን የማይሹ በርካታ ናቸው፡፡ ኑሮ መቼም ሞልቶ አያውቅም፡፡ ውጣ ውረድ አለው፡፡ በሁሉም መልክ ጥረትና ትግልን ይጠይቃል፡፡ የአንዳንዱ ኑሮ ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ የአንዳንዱ የዘነጋ ተወጋ ነው፡፡ የአንዳንዱ ከድጡ ወደ ማጡ ነው፡፡ አንዳንዱ ወፍራም ውሻ፣ አለ ሲሉት ይሞታል ነው፡፡ ወረቀት ላይ ያስቀመጥነው ዕድገት የሰውየውን መሶብ እንዴት አድርጎት ይሆን ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ አለበለዚያ ድህነት ላይ የምናሰግረው መፈክር የወረቀት ላይ ነበር (Paper tiger እንዲሉ) ያደርገናል፡፡
ነጋ ጠባ የሚወራለት የመልካም አስተዳደር ችግር ዛሬ ቁስሉ ዳነ ሲባል፣ ነገ እያመረቀዘ የቆላ ቁስል ይሆንብናል፡፡ ጨርሶ ወደ ማይድን በሽታ፣ ወደ ጋንግሪንነት፤ እንዳይሄድ መጠንቀቅ ተገቢ ነው፡፡ የከፋው ችግር ደግሞ ለሙስናውም፣ ለዲሞክራሲዓዊና ለመብት ጥያቄውም፣ ለፍትሕ መጓደልም ወዘተ “ተጠያቂው መልካም አስተዳደር ነው” ማለቱ ሲሆን ዕውነቱን ከማደብዘዝም አልፎ ፈር ያስተዋል፡፡ የሀገራችን ሌላው ቁልፍ ችግር፣ ቤተ-ሰሪ ለፍቶ ለፍቶ “ደም - የለውም” እስኪባል ድረስ ቅርሱን ጨርሶ፣ ቤት ሰርቶ “ፊኒሺንጉ” ያስቸግራል እንደሚባለው፤ በጣም ያስቸግራል ይላሉ፡፡ ይሄንን በቀላሉ ለመረዳት የኳስ ቡድናችንን ማጤን ነው፡፡ ሁሌ እግብ ጋ ሲደርሱ አይሳካላቸውም እንደሚባለው ነው - “የአፈፃፀም ችግር” አለባቸው የተለመደች አባባል ናት፡፡ ስንት ዘመን የዚህ ችግር ቁራኛ እንሆናለን? ነው ወይስ እየደጋገምነው አዋቂው እንዳለው፤ “ትለምጂዋለሽ” ሆኖ አረፈው፡፡ የበጀት መዝጊያ ሲደርስ “ምንጣፍ መግዛት” የአፈፃፀም ችግርን መቅረፍ ነውን? ወይስ በዘመኑ ቋንቋ “የአፈፃፀም ችግር “ውስጤ ነው” በሚል “ቃና” የምናልፈው ጣጣ ይሆን? የችግሮቻችን ብዛትና የመፍትሔ አሰጣጣችን አቅም ሲታይ፣
“በነጠላ ጫማ፣ ባንቺ አረማመድ
እንዴት ያልቅልሻል ያ ሁሉ መንገድ!” የሚባለው ህዝባዊ ዘፈን ግጥም ዓይነት ነው፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ብዙ የወተወትነው በሥራ እንለወጥ ዘንድ እንጂ እንደው የማንጓጠጥ ወግ ለማምጠቅ አይደለም፤ በቀና መንፈስ ነው፡፡
“ለትምክህት አይደለም፣ ይህን መናገሬ
ለማስቀናት እንጂ ሰነፉን ገበሬ፡፡
ሃዋርያው ሲናገር ወደ ምዕመናኑ
ለምትበልጥ ፀጋ ይላል ቅኑ አስቀኑ!”
እንዳለው ነው፡፡
በህዝብ ተዓማኒነትን ለማፍራት የመሞከር ጉዳይ በመንግስት ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ በኦሮሚያ ግጭት ነበር፡፡ በአማራ ክልል ግጭት ነበር፡፡ በአዲስ አበባም ግጭት ነበር፡፡ በወለጋም ግጭት ነበር፡፡ ግጭትን በእልህ ሳይሆን በዘዴ፣ በብልህነት ለመፍታት መሞከር፣ ካለፈው ትምሀርት መውሰድ፣ ዋና መንገድ ነው፡፡ ሌላው ቁልፍ መንገድ ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ ነው፡፡ አንዱን በዱላ አንዱን በመላ፤ የሚለው አያያዝ መፈተሽ አለበት፡፡ ዲፕሎማሲያችን፤ “የሀፍረተ-ስጋህን ፀጉር የምታሳየው አለ፡፡ የብብትህን ፀጉር የምትከለክለው አለ፡፡” የሚለውን ልብ ይበል፡፡

   ጅማ ዩኒቨርሲቲ ከኤቢኤች ሰርቪስ ጋር በመተባበር በሁለት የድህረ ምረቃ ፕሮግራሞች ያስተማራቸውን 136 ተማሪዎች ነገ በሸራተን አዲስ ያስመርቃል፡፡
በማስተርስ ኦፍ ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽንና በማስተርስ ኦፍ ፐብሊክ ኸልዝ የሚመረቁት እነዚሁ የድህረ ምርቃ ተማሪዎች፤ ላለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ ኤቢኤች ካምፓስ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው፡፡
ዩኒቨርሲቲው የረጅም ዓመታት ሙያዊ እውቀትና ልምድ ያላቸውን መምህራን በመመደብ ተማሪዎቹን በማስተማር ላይ እንደሚገኝ የገለፁት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ለሜሳ፤ አሁንም አዳዲስ ፕሮግራሞችን በመክፈት የመንግስትና የግል ዘርፉን አጋርነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
 የኤቢኤች ሰርቪስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶ/ር ማርቆስ ፈለቀ በበኩላቸው፤ የጅማ ዩኒቨርሲቲን ወደ አዲስ አበባ መምጣት ተከትሎ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ፍላጎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ጠቁመው፤ በቀጣዩ በሁለት የድህረ ምርቃ ፕሮግራሞ በፐብሊክ ሪሌሽንና ኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን እንዲሁም በኸልዝ ሞኒተሪንግና ኢቫሉዬሽን አዳዲስ ተማሪዎን እንደሚቀበል ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በነገው ዕለት ከሚያስመርቃቸው የድህረ ምረቃ ተማሪዎች መካከል 42ቱ ሴቶች ሲሆኑ ባለፈው ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ 97 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ አስተምሮ ማስመረቁ አይዘነጋም፡፡ 

የከተማዋ ስራ አጦች ሁለት ወጣቶች ብቻ ናቸው

   ኬታንጋታ የተባለቺውና 800 ነዋሪዎች ብቻ ያሏት የኒውዚላንድ ከተማ “እጅግ ብዙ ክፍት የስራ ቦታና አነስተኛ ዋጋ ያላቸው የመኖሪያ ቤቶች ቢኖሩኝም፣ ይህን ዕድል የሚጠቀምበት ሰው አጥቼ ተቸግሬያለሁ፣ እባካችሁ ኑ ወደ እኔ” ማለቷን ቢቢሲ ዘገበ፡፡ የሰው ሃይል እጥረት ያጋጠመው የከተማዋ አስተዳደር ችግሩን ለመቅረፍ፣ የሌሎች የኒውዚላንድ ከተሞች ነዋሪዎችን እባካችሁ ኑልን ሲል ጥሪ ያሰተላለፈ ሲሆን፣ የከተማዋ የስራ አጦች ቁጥር 2 ብቻ ነው ሲሉ ከንቲባው ማስታወቃቸውንም ገልጧል፡፡ ከንቲባው ወደ ከተማዋ ለሚመጡ አዳዲስ ነዋሪዎች፣ የመኖሪያ ቤት በእጅግ አነስተኛ ዋጋ ከማቅረብ ባለፈ፣ሌሎች በርካታ ማበረታቻዎችን ለማድረግ ማቀዳቸውንም አስታውቀዋል፡፡ በከተማዋ ካሉ ክፍት የስራ ቦታዎች መካከል የመነሻ ደመወዛቸው እስከ 26ሺህ 500 ፓውንድ የሚደርሱ እንደሚገኙበት የጠቆመው ዘገባው፤ አስተዳደሩ በህክምና፣ በህንጻ ግንባታ፣ በወታደራዊ ሃይልና በሌሎች በርካታ ዘርፎች ያሉትን ክፍት የስራ ቦታዎች ዝርዝር ይፋ ማድረጉንም ገልጧል፡፡

ኢትዮጵያ ከ178 የዓለም አገራት ባለመረጋጋት 24ኛ ደረጃን ይዛለች

የዓለማችንን አገራት ያለመረጋጋት አደጋ ደረጃ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገውና ፈንድ ፎር ፒስ የተባለው ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነው የምርምር ተቋም ባለፈው ረቡዕ ባወጣው የ2016 አመታዊ ሪፖርት፤ ሶማሊያ ከፍተኛ ያለመረጋጋት ችግር የታየባት ቀዳሚዋ የአለማችን አገር መሆኗን አስታውቋል፡፡
የአገራትን አጠቃላይ ሁኔታ የሚያመለክቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሪፖርቶችንና ጽሁፎችን በመተንተን እንዲሁም ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን የሚያመላክቱ 10 ቁልፍ መስፈርቶችን መሰረት በማድረግ ደረጃ የሚሰጠው ተቋሙ፤ ለ12ኛ ጊዜ ባወጣውና 178 የአለማችን አገራትን ባካተተው ሪፖርቱ፣ ሶማሊያን በቀዳሚነት አስቀምጧታል፡፡ከሶማሊያ በመቀጠል ከፍተኛ ያለመረጋጋት ችግር ያለባት አገር ደቡብ ሱዳን እንደሆነች የጠቆመው ሪፖርቱ፤ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ሱዳን፣ የመን፣ ሶርያ፣ ቻድ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታንና ሃይቲ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ እንደያዙ ገልጧል፡፡ኢትዮጵያን በ24ኛ ደረጃ ላይ ያስቀመጠው የዘንድሮው ፈንድ ፎር ፒስ ሪፖርት፤ አገሪቱ ባለፉት አራት አመታት የመረጋጋት ሁኔታዋ እየተሻሻለ  ቢመጣም፣ በአገሪቱ የቡድን ግጭቶችና የተማረ የሰው ሃይል ፍልሰት ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ አሳይቷል ብሏል፡፡
ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ ዘላቂ የሆነ መረጋጋት ያለባት አገር ፊንላንድ ናት ብሏል የተቋሙ ሪፖርት፡፡

የአየር ሃይል አዛዡና ሌሎች ባለስልጣናትም በ74 ሚ. ዶላር ሙስና ተከስሰዋል

   የናይጀሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃመድ ቡሃሪ ልዩ ጠባቂ የሆነው ሃሰን አሚኑ የተባለ የአገሪቱ የደህንነት አባልና ሌሎች ለፕሬዚዳንቱ ቅርበት ያላቸው የደህንነትና የጦር ሃይል አባላት አገሪቱን በሽብር ከሚያምሰው ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሃራም ጋር ንክኪ አላቸው በሚል ተጠርጥረው ባለፈው ረቡዕ አቡጃ ውስጥ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ፡፡
የአገሪቱ መንግስት የደህንነት ልዩ ግብረ ሃይል ለፕሬዚዳንቱ ቅርበት ያላቸውን ግለሰቦች የጀርባ ማንነትና ድብቅ አጀንዳ በመመርመር ላይ እንደሚገኝ የዘገበው ናሽናል አኮርድ ኒውስ ድረገጽ፤ይሄው የፕሬዚዳንቱ ጠባቂና የደህንነት አባላትም ከአሸባሪው ቡድን ጋር የድብቅ ግንኙነት እንዳላቸው በመረጋገጡ መታሰራቸውን ገልጧል፡፡ግለሰቡና ግብረ አበሮቹ ከቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጋገጡንና በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ፣ ሽብርተኞች በፕሬዚዳንቱ ጠባቂዎችና ለቤተመንግስቱ ቅርበት ባላቸው ግለሰቦችና ሰራተኞች አማካይነት ጥቃት እንዳይፈጽሙ ለመከላከል የተጠናከረ ክትትል እየተደረገ መሆኑም ተነግሯል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጠባቂና የደህንነት አባላቱ ከቦኮ ሃራም ጋር ግንኙነት እንዳላቸው መረጋገጡ፣ አሸባሪ ቡድኑ ከሽምቅ ውጊያ ባለፈ ምን ያህል እስከ ቤተ መንግስቱ የሚደርስ የጥቃት ሰንሰለት እንደዘረጋ ያመላክታል ተብሏል፡፡በተያያዘ ዜናም፣ የቀድሞው የናይጀሪያ አየር ሃይል አዛዥና ሌሎች ሁለት የጦር ሃይል ባለስልጣናት በሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር  የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል ተከስሰው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የቀድሞው የአገሪቱ የአየር ሃይል ላይ አዛዥ ማርሻል ጃኮብ ቦላ አዲጉን እና ሌሎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ባለስልጣናት በድምሩ 74 ሚሊዮን ዶላር የህዝብ ገንዘብ መዝብረዋል በሚል ነው የተከሰሱት፡፡

   ለታሪክና ለባህላዊ ጥናቶች ትልቅ ዋጋ ያለው ሥራ፤ የተባለለት ‹‹እጨጌ ዕንባቆም - ከየመን እስከ ደብረ ሊባኖስ›› በሚል ርእስ በዲያቆን ዳንኤል ክብረት የተዘጋጀው አዲስ መጽሐፍ ታትሞ በያዝነው ሳምንት ለንባብ በቅቷል፡፡ ብዙ ምስቅልቅል፣ ጦርነቶች፣ ከፍተኛ የሕዝቦች እንቅስቃሴና መፈናቀል የተከሠተበትን የኢትዮጵያን የ16 ኛውን ክፍለ ዘመን ታሪክና አስተዳደራዊ መልክዓ ምድር (ጂኦግራፊ) ለመረዳት ያስችላል የተባለው ይኸው መጽሐፍ፤
ዋጋው ብር 60.00 ሲሆን፤ በመጪው ሳምንት ቅዳሜ (ሐምሌ 9) ከሰዓት በኋላ ከ 8፡30 እስከ 12፡00 ሰዓት፤ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል አዳራሽ የታሪክ ምሁራንና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት እንደሚመረቅ ተገልጿል፡፡ አዲሱ ጽሐፍ የዲያቆን ዳንኤል ክብረት 23ኛ ሥራ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል የአዲስ አድማስ ቋሚ አምደኛ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

Saturday, 02 July 2016 12:37

‘Fikru’….‘ፍቅሩ’

የሥዕል ትርዒት ዳሰሳ (Exhibition Review)
የትርዒቱ ርዕስ፡ ፍቅሩ
ሠዓሊ፡ ፍቅሩ ገ/ማርያም
የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ስራዎች
ብዛት፡ 25 የቀለም ቅብ፤ ስራዎች
የቀረበበት ቦታ፡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ጊዜያዊ የስዕል ማሳያ አዳራሽ አዲስ አበባ
ጊዜ፡ ሰኔ 06 - ሐምሌ 7: 2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ(የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ)

“ፍቅሩ”
ለግል የሥዕል ትርዒት ስያሜነት ከሚውሉ አሰያየሞች መካከል መጠሪያ ስምን ለትርዒት ስያሜ ማድረግ ከተለመዱት መሃል አንደኛው ነው፡፡
ይህን ማድረግ ራሱን የቻለ መደንግግ ነው፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገብረማርያም ለዚህኛው ብቻ ሳይሆን በላጮቹንና አብዛኛዎቹን የግል የሥዕል ትርዒቶቹን መጠሪያ በስሙ ‘ፍቅሩ’ በሚል ነው ለህዝብ እይታ የሚያበቃው፡፡ ይህ ደግሞ መደንግግነቱን እንድናስተነትንና ‘ፍቅሩ’ የሚለውን ስያሜ በድግምግሞሽ እንዲጠቀም ያስቻለውን አመክንዮ ለመረዳት ቆፈር ቆፈር እያደረግን እንድንፈትሽው በር ከፋች ነው ባይ ነኝ፡፡ አሃዱ፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ‘ፍቅሩ’ ነቱ ላይ ችክ ያለ ሠዓሊ መሆኑን መረዳት እንድንችል እየነገረን ሊሆን ይችላል፡፡ ክልኤቱ፡ ሠዓሊው ገና የ’ፍቅሩ’ነቱን ፍቅር አጣጥሞ አለመጨረሱን እንድንጠረጥር በገቢርም ሆነ በነቢብ የማርያም መንገድ እየሰጠን ይሆናል፡፡ ሰልስቱ፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ራሱ ፍቅሩን ወይም የፍቅሩንነቱን ጥግ፣ልክ፣ጥልቀትና ርቅቀት ገና ዳሰሶ ወይም ፈልጎ አለመጨረሱንና አለማግኘቱን ለመጠቆም፤ ይልቅስ በፍለጋው ሂደት ያገኘውን ወይም የደረሰበትን ፍቅሩን እንካችሁ ማለቱ ሊሆን ይችላል፡፡ አርባዒቱ፡ ሠዓሊው በደረሰበት ወይም ባገኘው ፍቅሩነት እርግጠኛ ሆኖ፣ እነሆ ፍቅሩ መጥቷልና ከበረከቱ ትካፈሉ ዘንድ ትርዒቱን እንካችሁ እያለም ይሆናል፡፡ ሐምስቱ፡ መ ሁሉም መልስ ነው፣ አልተሰጠም ወይም መ መልስ የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ልንደርስ እንችላለን፡፡ ወደ ትርዒቱ፡-
በትርዒቱ ከቀረቡት ስራዎች ሰባ በመቶ የሚሆኑት በአውታረ መጠናቸው ብቻ የሚናገሩት ሃቅ አለ፡፡ የሥራዎቹ የጎን ስፋትና ቁመት ተቀራራቢነት ያላቸው፤ ወደ ስኩዌር ካሬነት የሚያዘነብሉና መሃከለኛና በብዛት ትልቅ መጠን ያላቸው የሥዕል ሰሌዳዎችን ነው የሚጠቀመው፡፡ እንዲህ አይነቱ አውታረ መጠን በተለምዶ ግዘፍ የሚነሳ፤ ዓይን የሚሞላና ደርፈጭ ያለ ወይም (bald) እንደሆነ ይነገራል፡፡ አንድ ሠዓሊ ይህን አይነት አውታረ መጠን ሲጠቀም ግዘፍ የሚነሱና ስለ ራሳቸው በልበ ሙሉነት የሚናገሩ ሀሳቦችን በማንሸራሸር እንዲያግዘው ሆን ብሎ የሚመርጠው እንደሆነ ይታመናል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡ አብላጫዎቹ ስራዎች በዚህ አቀራረብ የተቃኙ እንደሆኑ ይስተዋላል፡፡ ሆኖም እንዲህ አይነት ዝንባሌ ያላቸው ስራዎች በአንድ ላይ ለዕይታ ሲቀርቡ፣ ሲደረደሩና ሲሰቀሉ ሰዓሊውም ሆነ የትርዒቱ አጋፋሪ (curator) በጥንቃቄ ማሰብና መከወን የሚገባውን ወሳኝ ነጥብ የሳተ አቀራረብ በዚህ ትርዒት ይስተዋላል፡፡ ይኸውም ትርዒቱ ከሚታይበት ህንፃ ውስጥ ፎቅ ላይ ባለው የመጨረሻውና ሰፊው የሥዕል ማሳያ አዳራሽ ውስጥ የተሰቀሉት ሳይሆን የተገጠገጡት ሊባል በሚያስችል ደረጃ እንደ ሱቅ በደረቴ በአንድነት ተቸምችመው ያሉት አምስት ስድስት ሰራዎች የግዙፍነታቸውን ብቻ ሳይሆን ያመቁትን የሃሳብና የስሜት  ጥቅጥቅነት (density) ከግምት ያላስገቡ ናቸው፡፡ ሠዓሊው ፍቅሩ ገ/ማርያም፤ በፍቅር የወደቀላቸውን ስራዎች ለማሳየት በጉጉት ሲጣደፍ አሰቃቀሉ ለዕይታ እንደሚጎረብጥ እንኳ ማስተዋል እንደነሳው ማየት እንችላለን፡፡ ለአንድ ነገር ፍቅር ብቻ ሲቸረው የሚያስከትለው ችግር ይኖራል፡፡ ምናልባትም በ’ፍቅሩ’ነቱ ጥግና ልክ እርግጠኛ የሆነ ቢሆን ኖሮ እንዲህ ከመገጥገጥ ይልቅ አንድ ወይ ሁለት ስራዎቹን ብቻ “ገጭ” አድርጎ ሰቅሎ ሙሉ “ፍቅሩ”ነቱን በልበ-ሙሉነት መንፈስ ጀባ ሊለን ይቻለው ነበር የሚል ሙግት አመክንዮ እንዳነሳ የሚጋብዝ ፍንጭ በተለይ ከተጠቀሰው የሥራዎቹ አውታረ መጠናቸውን መሰረት በማድረግ፣ሥራዎቹ ከተሸከሙት የሀሳብና የስሜት ጥቅጥቅነት በመነሳት ለተመልካች እይታ ብሎም መረዳት ትግዳሮት (problem) የሚፈጥረውን የትርዒቱን ባህሪ ማየት ይቻላል፡፡ በመሰረቱ እንዲህ አይነት ጥቃቅን የሚመስሉ ነገር ግን ለአንድ የሥዕል ትርዒት ምሉዕነት ጉልህ ሚና ያላቸውን የአቀራረብ ባህሪያት ከግምት ውስጥ አስገብቶ የሚሰራ የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ ከሌላው ትርዒት የሚጠበቅ ህፀፅ ቢሆንም እንደ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በዓለም አቀፍ መድረኮች፣ በታላላቅ ሙዚየሞችና ጋለሪዎች ዓለማችን ካፈራቻቸው ምርጥ ሠዓሊያን ጎንና በአንድነት ስራውን ካቀረበ ሠዓሊ የማይጠበቅ በመሆኑም ነው ይህን ያህል ትኩረት ሰጥቼው የነካካሁት፡፡ በአንፃሩም የትርዒት ማሳያው አዳራሽ አስተዳደርም ቢሆን ለአዳራሹ ኪራይ አይሉት አበል ለፅዳትና ጥበቃ አንዳንዴም የአዳራሹን በርና መስኮት ከፍቶ ለሚዘጋው ሰው አበል በሚል ሰበብ ለሚሰበሰበው ገንዘብ ትኩረት ከመስጠት ውጪ ለእንዲህ አይነት ሙያዊ እገዛዎችም ሆነ የአዳራሹን ግድግዳዎች ለማደስ፣ የሥዕል አስቃቀልንና ዕይታን ለሚረብሹት እንዲያው እንደዘበት አቡጂዲ ጨርቅ በመስኮቶቹ ላይ ጣል ከማድረግ ውጪና አንድ የሥዕል የተሳካ ለሚያደርጉት የብርሃን አምፑሎች “በዕድላቸው” እንዲበሩ ከመተው የዘለለ መፍትሔ ከማቅረብ ሌላ ዳተኝነቱን በተከታታይ እየተዘጋጁ ካሉ ትርዒቶች ለመረዳት ችለናል፡፡ እናም ከዚህ ዓይነት የአዳራሹ አስተዳደር የሥነ-ጥበብ አጋፋሪ (curator) መጠበቅ “እዬዬም ሲደላ ነው” ሊሆንብን ይችላል፡፡ ሆኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ … የሚል ሁለት ከባባድ መጠሪያዎችን ከተሸከመ የሥዕል ማሳያ አዳራሽ እንዴት “እዬዬም ሲዳላ” ይሆናል የሚል ሀሳብ ዘወትር ወደ አዳራሹ ጎራ ባልኩ ቁጥር የሚነዘንዘኝ ሃሳብ በመሆኑና መተቸት የሚገባው እንደሆነ ስለማምንበት ነው ያነሳሁት፡፡ አስተዳደሩ አዳራሹን ለተከታታይ ትርዒት ክፍት ከማድረጉ ባሻገር በዚህ በ “ፍቅሩ” ትርዒት ሙዚየሙና የአዳራሹ አስተዳደር ካሳየው አበረታች ጅምሮች መሃከል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አቶ ዮናስ ደስታ በትርዒቱ መክፈቻ ተገኝተው ስለ ትርዒቱና ስለ ሥነ-ጥበብ እንዲሁም ባለስልጣን መ/ቤቱ ለሥነ-ጥበብ ስለሚያደርገው ድጋፍ የሰጡት ጠንካራ የመክፈቻ ንግግር ነው፡፡ በተለይ ባለስልጣን መ/ቤቱና የአዳራሽ አስተዳደር ከላይ የተጠቀሱት አይነት ችግሮችን በጊዜ ሂደት እየቀረፈ ቢሄድ ይበል የሚያስብል ማለፊያ ማበረታቻ ነው፡፡ ወደ “ፍቅሩ” እንመለስ፡-
ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በ1987 ዓ.ም ነው ከአሁኑ የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ  አለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት  በቀለም ቅብ በዲፕሎማ የተመረቀው፡፡ ለዲፕሎማው አራት ዓመታትን፣ ከዚያ በፊት ት/ቤቱ ይሰጥ በነበረው የማታ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ለሁለት ዓመታት፣ እንደገና ከእነዚህ ሁለት ዓመታት በፊት ለአራት ዓመታት በተከታታይ የክረምት ትምህርት ክፍለ ጊዜ በት/ቤቱ ተከታትሏል- አስር ዓመታትን በድምሩ የሥዕል ትምህርት ሲማር ቆይቷል ማለት ነው፡፡ ተመርቆ ከወጣ በኋላ እስካሁን ባሉት ሀያ አንድ ዓመታት ውስጥ ደግሞ  በስቱዲዮ ሠዓሊነት ቆይቷል፡፡ ሥዕል የተማረበትና የሰራበት ዓመታት ሲደመሩ የአንድ ትውልድ እድሜ ይተካከላሉ ማለት ነው፡፡ የሥዕል ትምህርት መማር ሠዓሊ አያደርግም፤ምናልባት ሥዕል ለመስራት ያግዝ ይሆናል እንጂ፡፡ የሥዕል ትምህርት አለመማምርም ከሠዓሊነት አያግድም፡፡ በሀገራችን ብቸኛው የሥነ-ጥበብ ተቋም ሆኖ ከግማሽ ምዕተ ዓመታት በላይ የዘለቀው የአለ የሥነ-ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት፣ ሲያስተምርበት የቆየውንና አሁንም ከሞላ ጎደል እያስተማረበት የሚገኘውን የትምህርት አሰጣጥ ዘዬና ፍልስፍና እጅጉን ክሊሎት (skill) ላይ መሰረት ያደረገና ቆይታው ያዳበረው ልምድ ብቻቸውን ወደ አንድ ከዚህ ቀደም ሲሰራ ከቆየበት ወደ ተለየ የአሰራር አቅጣጫ እያመጡት እንደሆነ በዚህ ትርዒት ላይ መመልከት እንችላለን፡፡
 ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም አበድ፣ሰከር፣ቆፍጠንና ፈጠን ያለ ድፍረት በዚህ ትርዒት አሳይቶናል፡፡ እብደቱ ስካሩ ነፃነቱን፤ፍጥነቱና ቆፍጣናነቱ ደግሞ ሩቅ አላሚነቱን ያመለክታሉ፡፡ ጭልጥ አድርጎ ከመጠጣት ሳይሆን ቀስ በቀስ፣ ያውም የአስር ዓመታት ትምህርትንና ሃያ የሚሆኑ የሠዓሊነት ዓመታት ልምዶችን በዝግታ በማጣጣምና በማሰላሰል ከሚመነጭ ድፍረት ነው እብደቱና ስካሩ የተወለዱት፡፡ ቀጥ ብሎ ለመቆም፣አሻራውን ለመተው፣ምናልባትም ለመዝናናት፣ ፈታ ብሎ በስራዎቹ ሙከራ ለማድረግና እንደውም (ቀጣዩን ዓረፍተ ነገር ቡፍ ብሎ ከሚያመልጥ ሳቅ ጋር ነው ያሰብኩት)… እንደውም “ሥዕል ምናባቱ-የታባቱ አፈር ድሜ ማብላት ነው እንጂ” እያለ መስራ ከሚያስችል ድፍረት ውሰጥ የሚገኝ ሩቅ አላሚነት የከሰቱት ፍጥነትና ቆፍጣናነትም በስራው ማየት ይቻላል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡት ሥራዎች በሥነ-ጥበብና በሚሰራው ሥዕል ለመፈላሰፍና ለመዝናናት የሸሚዞቹን እጀታ ከክንዱ ከፍ አድርጎ የሰበሰበ ሰው የሚሰራቸው አይነት ስራዎቸ ይታዮኛል፡፡ ሥራዎቹ ቆፍጣናነትና ፍጥነት ካልተሞላባቸውም ለዘዝ ብለው ለዘመናት ሲመላለስበት ወደ ኖረበት ድግምግሞሽ ለመመለስ የፈራ የሚደፍረው ዓይነት ድፍረት ይስተዋላል፡፡ ይልቅስ ቆፍጠን ብሎ ፍጥነት በመጨመር ቢነጉድ አንድ ከፍታ ላይ ለመድረስ የሚያልም፣ነፍሱን የሳተ እብድና ሰካራም ጋላቢ ከሚደፍረው ድፍረት የመነጩ ስራዎች በትርዒቱ ይታያሉ፡፡
በትርዒቱ የቀረቡ አብዛኛዎቹ ሥራዎች ሙከራዊ (experimental) ቢሆኑም የአካዳሚክ (የሥዕል ትምህርት) ህግጋትን ለመጣስ የሚፍጨረጨሩ ናቸው፡፡ ከመማርም አልፎ በሥራ ያዳበረውን የአሳሳል መንገዶች ካላፈረስኩ ብሎ መታገል፣ እብደትና ስካር ካልታከለበት በቀር መድፈር አስቸጋሪ ነው፡፡ ብዙ ሠዓሊያን ይህን ድፍረት አጥተው ለተማሩት ትምህርት ብቻ እስረኛ ሆነው ቀርተዋል፡፡ በሥነ-ጥበቡም ሆነ በፍልስፍናው እመርታ ለማሳየት ሙከራ ወሳኝ ነው፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩ ይህንኑ ነው እያደረገ ያለው፡፡ እየሞከረ፡፡ ሙከራውም አያሌ የዓለማችን ሠዓሊያን ከሞከሩት የተለየ አይደለም፡፡ አሜሪካዊው ሠዓሊ ዊሊያም ደኩኒንግን ማንሳት እንችላለን፡፡
የፍቅሩ ሙከራ ማፍረስ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ የሚሰራቸውን ምስሎች እያጠፋ አንዳች ሥነ-ጥበባዊ ፋይዳ ለማግኘት ነው እየተጋ ያለ የሚመስለው፡፡ በዚህ ከቀጠለም ያለፈባቸውንና በስራዎቹ ይስተዋሉ ከነበሩ ተፅዕኖዎች ከመላቀቅና ነፃ ከማውጣትም ባሻገር እንደ ድግምት ከሚደጋግመው “ፍቅሩ”ነቱ ሲጎነጩት እሚያረካ ጣዕም ሊቸረን ይችላል፡፡ ይህን ትጋት ወደ አንድ ጥበባዊና ሰብዓዊ አላማ የማዞር ኃላፊነት እንዳለበትም የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ጥበብ ሃቀኝነትን ትሻለች፡፡ በሃቀኝነት የሚከወን ጥበብ፣ከሠዓሊው ባሻገር ሃገርን፣ዓለምንና ሰብዓዊነትን ያገለግላል፡፡ በዚህ ትርዒት የቀረቡ ሥራዎች ይህን ታላቅ ኃላፊነትና ዓላማ ለማሳኪያ በር ከፋች አድርጌ ብወስዳቸው እመርጣለሁ፡፡ ሠዓሊው ጊዜውን፣አትኩሮቱንና እድሜውን ሙሉ ሲለፋለት በኖረለት ሥነ-ጥበብ ውስጥም አንዳች ፋይዳ ከመፈለጉና … ይህን ፍላጎት ክብር መስጠት አስፈላጊ ሆኑ በማግኘቴ ይበል ከማለት ውጪ መጨረሻውን ለመተንበይ እንኳንስ እኔ ሠዓሊውም የሚያውቀው አይመስለኝም፡፡
 ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ተማሪ በነበረበት ጊዜና ተመርቆ ከወጣም በኋላ የት/ቤቱ አስተማሪዎችም ሆኑ የሀገራችን ግንባር ቀደም ሠዓልያን ክሂሎት ላይ የተመረኮዘ የአሳሳል መንገድን ሲያቀነቅኑ ነው የኖሩት፡፡ ሠዓሊ ፍቅሩና በዚህ ትውልድ ውስጥ ያለፉ አብዛኞቹ ሠዓልያኖቻችን፣ይህን ዘፈን ሲያዜሙም ነው የኖሩት፡፡ በእርግጥ የዜማው ጥዑምነት ያማልላል ነፍስንም ይገዛል፡፡ ብዙ አቅም ያላቸው ነገር ግን የዜማውን ጥዑምነት ብቻ እያጣጣሙና እየነሆለሉ በዚያውም የዓለምና የዘመኑ የሥነ-ጥበብ ኮቴ እያሰማና እየፈጠረ ያለውን ንቅናቄ ማዳመጥ ተስኖአቸው በዚያው የጠፉና የቀሰሙ እንዲሁም በዚሁ አዘቅጥ ውስጥ ያሉ ሠዓሊያኖቻችንም አያሌ ናቸው፡፡ አዲሱን፣ዘመንኛውን፣ የዘመኑንና የአለምን የቅርብ ጊዜ ወይም ለእኛ አውድ “መጤ” የሆነውን የሥነ-ጥበብ ኮቴ ለመስማት ብለውም ለቀደመው ጥዑሙ ዜማ ጆሮና ሁለመናቸውን ደፍነው ያሉበት እስኪጠፋቸው እየተደናበሩ ያሉትንም  የስዕል ስቱዲዮ  ይቁጠራቸው፡፡ የወቅቱ የሀገራችን ሥነ-ጥበብ መመለስ ከሚገባው ጥያቄዎች አንዱም ይሄኛው ይመስለኛል፡፡ ሚዛን መጠበቅ አልያም ሚዛን መድፋት የሚችለውንም በጊዜ ሂደት የምናየው ይሆናል፡፡
ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም በሥነ-ጥበብ ት/ቤት ቆይታው ክሂሎቱን ሲያዳብር ለመቆየቱና በስቱዲዮ ሠዓሊነት ባሳለፋቸው ዓመታት የተማረውን ክሂሎት ሥዕል ለመስራት ሲጠቀምበት ለመቆየቱም አንዳች ጥርጣሬ የለኝም፡፡ የዳበረ ክሂሎቱን ብቻም ሳይሆን በት/ቤት ቆይታው በእሳት የተጠመቀባቸው እስኪመስል የተጣቡት የእነ ፒካሶና ጉጌይን ተፅዕኖዎች፤ በፍቅር ያንበረከከውና እንደ ድርሳን ለዓመታት ሲደጋግመው የኖረው የመምህሩና የሃገራችን ታላቁ ሠዓሊ የታደሰ መስፍን ተፅዕኖ በስራዎቹ ለዓመታት መታየታቸው የእርግጠኝነቴ መሰረቶች ናቸው፡፡ ተፅዕኖቹ በአካዳሚክ ህይወቱና በመስራት ልምዱ የተፈጠሩ ናቸው፡፡ ከመስራትም ደጋግሞ በመስራት፡፡ እነዚህ ሁለት ተፅዕኖዎች መልካም ጎኖች እንዳሏቸውም ልብ ማለት ይኖርብናል፡፡ የመጀመሪያው ገንዘብና እውቅና፡፡ የሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም የሥነ-ጥበብ ልምምድ (practice) በትጋት የተሞላ ነው፡፡ ያለማቋረጥ ይሰራል፤ከዚህም ባሻገር ልፋቱ ተገቢው ቦታ ክብርና ዋጋ እንዲያገኝም ይለፋል፡፡ መሳል ብቻ ሳይሆን ሥራውን ለማስተዋወቅ ይጥራል፡፡ በዚህም የሀገራችን የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ “ሙት” እንደሆነ ገና ድሮ ገብቶት የሚያገኛቸውን እድሎች ሁሉ እንደ መሰላል እየተጠቀመ፣ ሥራዎቹን ሞቅ ያለ የሥነ-ጥበብ እንቅስቃሴ ባላቸው የዓለማችን ሀገራት ጋለሪዎች ሙዚየሞችና አጋፋሪዎች ዘንድ ለማድረስ ቀና ደፋ ሲል ብዙ ተንከራቶ ተሳክቶለትማል፡፡  ገንዘብንና እውቅናንም በዓለም አቀፍ ደረጃ አግኝቷል፡፡ ተፅዕኖዎቹ ጠንካራ መሰረት ባይኖራቸው ማንኛውም ጋለሪ ሙዚየምና ኪዩሬተር ፊት እንደነሱት ነበር የሚኖረው፡፡ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃም ላይበቃ ይችል ነበር፡፡ እነ ፒካሶና ጎጌይን የሰሩት ለዓለምና ለሃገራቸው አሁንም ድረስ ቤዛ እየሆነ ነው፡፡ ታደሰ መስፍንም ለሠዓሊ ፍቅሩ በቀጥተኛ መልኩ፣ ከሰላሳ ሶስት ዓመታት በላይ ለአስተማረበት ት/ቤትና ተማሪዎቹ በተለያየ መልኩ፣ለሀገራችን ሥነ-ጥበብ ደግሞ በጥቅሉ ቤዛ ነው፡፡
ሠዓሊ ታደሰ መስፍን እንደ “እድር አህያ” አንዴ በማስተማር፣ በሌላ ጊዜያት የስብሰባዎች ናዳ ሀገሪቱን ያሻሽሏት ይመስል እዚህም እዚያም በሚካሄዱት ስብሰባዎች ሲዶል በስቱዲዮው ጊዜ ለማሳለፍና ለመስራት መላ መምታት ተስኖት፣ በዘመናት ያዳበረውን ሥነ-ጥበባዊ እርምጃ አንድ ቦታ ማድረስ ቢሳነውም፤ ተማሪው የነበረው ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም ተፅዕኖው አርፎበት የተጀመረውን ለማስቀጠል እንኳን ባይሆን እንደ መሻገሪያ ተጠቅሞት ሊያተርፍበት ችሏል፡፡  ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም የተጠመቀባቸውና የተንበረከከባቸው እነዚህ ሁለት ተፅዕኖዎች፣ገንዘብና እውቅናን እንዲሸምትባቸው ከማስቻላቸውም በላይ አብዛኛው ሠዓሊ ስራውን ለመቀጠል ተግዳሮት ከሚሆንበት የገንዘብ  ጥያቄ ነፃነት አግኝቶ ስራውን በረጋና በነፃነት መንፈስ እንዲሰራ አስችሎታል ወይም ሊሰራ እንዲችል ምቹ ሁኔታ እየፈጠረለት ነው ባይ ነኝ፡፡
የተፅዕኖዎቹ ዳና በድግግሞሽ፤ አሊያም በመስልቸት፤ “አዲስ” ነገር ለመፈለግ እንዲነሳሳ፣ የተፅዕኖዎቹን ዳና ለማጥፋት የራሱ ብቻ ወደሆነ ዳና እንዲመጣ በማድረግ አቀጣጣይ፣ አነሳሽ ወይም ደግሞ አናዳጅ ሀይል መሆን ሁለተኛው ተፅዕኖቹ የተፈጠሩለት መልካም ጎን ይመስለኛል፡፡ ከላይ ስለዘረዘርኩት የአንደኛው ተፅዕኖ ምክንያታዊነት ሰዓሊው ፍቅሩ ገ/ማርያም ራሱ፣ሌሎች ሠዓሊያንና የሥነ-ጥበብ ባለሙያዎች እንዲሁም አንባቢ ሊስማማበትም ሆነ ላይስማማበትም ይችላል፡፡ እንደው የቀደሙ ሥራዎቹ ከማንኛውም ተፅዕኖ የፀዱ ናቸው ተብሎ ቢካድ እንኳን ለዓመታት የተማረው ትምህርት በሠዓሊነቱ ላይ ተጽዕኖ ከማሳደሩም በላይ አሁንም ከተጽዕኖው ለመላቀቅ የሚያደርገው ጥረት ላይ ማነቆ እየሆነበት እንደሆነ ማየት ይቻላል፡፡
ትርዒቱን ታድሜ ከገጠሙኝና ልጠቅሳቸው ከምፈልጋቸው ሁነቶች መሃል እንካችሁ፡-
“እንትን ያለው ልጅ”፤ ትርዒቱን ታድመው የነበሩ አንድ ትልቅ ሰው ናቸው አሉ “ከእስክንድር በኋላ እንትን ያለው ሰዓሊ ተገኘ” ሲሉ የተደመጡት፡፡
አባባሉ “እንትን” ያላቸው ሠዓሊያንና እንትናቸው የሚያዝና ዘር የሚዘራ፤ እየዘራም ያለ ሠዓሊያን በሞሉባት ሀገር፣ ሠዓሊ ፍቅሩ ገ/ማርያም እኔ ብቻ ነኝ “እንትናም” ብሎ እንዲያስብ በር ከፋች ሊሆን ይችላል፡፡ ይሁን ሠዓሊው ፍቅሩ፤እኔ ብቻ ነኝ “እንትናም” ብሎ ያስብ… ግን እሳቸው የሌሎችን ሠዓሊያኖቻችንን እንትን ማየት አልቻሉምና ባለ እንትናም እሱ ብቻ ነው?
የተመልካች አስተያየቶች፡- የብሔራዊ ሙዝየም ታዳሚያን ብዙዎቹ ትርዒቱን ዘልፈውታል፣ ሰድበውታል፣ አነፃፅረውም ዋጋ ቢስ አድርገውታል፡፡ ሥዕል መመልከት፣ ልምምድ ዕውቀት ቢጠይቅም ከሚታየው ሥራ ጋር ስሜታዊና ሃሳባዊ ቁርኝት ይፈልጋል፡፡ የዕይታ ባህሉ ያልዳበረ የማህበረሰብ ክፍል ትርዒቱን ሲመለከት ምንም ስሜት ባይሰጠው፣ ሃሳብ ባይገለጥለትና የሆነ ዘባተሎ ነገር ቢሆንበት ሊገረም ወይም በሰዓሊው ሊናደድ አይገባም፡፡
ጎበዝ የሆነ ተመልካች ራሱን ይጠይቃል-፤ካልሆነም እርዳታ ይጠይቃል- ይህም ካልተሳካ አይተወውም? ምን አስጨነቀው? በእርግጥ አጥብቆ ጠያቂ፣ የእናቱን ሞት ሊረዳ ቢችልም መዳኗንም ሊበሰር ይችላል፡፡

   በዶ/ር ዓለማየሁ አረዳ የተፃፈውና “የሰጐን ፖለቲካ - የኢትዮጵያ ምሁራን ሚና” የተሰኘ መፅሃፍ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ፡፡ “ምሁር ሲባል ምን ማለት ነው? ሚናውስ ምንድን ነው? አፈጣጠሩስ ምን ይመስላል? የኢትዮጵያን ምሁራን ሚና በሌሎች ምሁራን ሚና ተመን ማየት ይቻላል ወይ?” በሚሉ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥነው መፅሃፉ፤ ብሄርተኝነትና የኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ግንባታ ፈተናዎችንም ይዳስሳል፡፡ በሰባት ምዕራፎች የተከፋፈለውና 154 ገፆች ያሉት መፅሃፉ፤ በ45 ብር ለገበያ ቀርቧል፡

Saturday, 02 July 2016 12:30

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ሥነ ፅሁፍ)

ግጥም የሥነ - ፅሁፍ ዘውድ ነው
ደብሊው. ሶመርሴት ሙዋም
ሥነ - ፅሁፍ መልሱ የተቀነሰለት ጥያቄ ነው፡፡
ሮላንድ ባርቴስ
ሥነ - ፅሁፍ እጅጉን አባባይ፣ እጅጉን አታላይ፣
እጅጉን አደገኛ ሙያ ነው፡፡
ጆን ሞርሌይ
መፅሃፍ ቅዱስ ሥነ-ፅሁፍ እንጂ ቀኖና አይደለም፡፡
ጆርጅ ሳንታያና
የሥነ-ፅሁፍ ኃይል ከጨቋኝ ኃይል የጠነከረ ነው
ብዬ አምናለሁ፡፡
ማ ጅያን
ሥነ-ፅሁፍ የአንድ ህዝብ ህያው ትዝታ ሆኗል፡፡
አሌክላንዶር ሶልዝሄኒትሲን
የእያንዳንዱ ሰው ትዝታ የየራሱ የግል ሥነ ፅሁፍ
ነው፡፡
አልዶውስ ሂክስሌይ
ታላላቅ የሥነ - ፅሁፍ ስራዎች በሙሉ አንድም
የሆነ ዘውግን ያጠፋሉ አሊያም ሌላ ዘውግ
ይፈጥራሉ፡፡
ቻርለስ ጄ. ሺልድስ
የሥነ-ፅሁፍ ዓላማ ማስተማር፣ ማነቃቃት ወይም
ማዝናናት ነው፡፡
ጆርጅ ሔነሪ ልዊስ
የሁሉም ሥነ-ፅሁፍ መሰረቱ ግለሰባዊ የህይወት
ተመክሮ ነው፡፡
ጆርጅ ሔነሪ ልዊስ
ማንኛውም የረዥም ልብ ወለድ ፀሐፊ፤ የሥነ-
ፅሁፍ ጉዳይ ሊያሳስበው ይገባል ብዬ አላስብም፡፡
ጃኩሊን ሱሳን
ፀሐፊ የሚያጠናው ሥነፅሁፍን እንጂ ዓለምን
አይደለም፡፡
አኒ ዲላርድ
እኔ ሥነ-ፅሁፋዊ እንስሳ ነኝ፡፡ ለእኔ ሁሉ ነገር
የሚቋጨው በሥነ-ፅሁፍ ነው፡፡
ካርሎስ ፉንቴስ
ለእኔ ሥነ-ፅሁፍ፣ እኔን ስለማይመስሉ ሰዎች
በማወቅ፣ ራሴን የማሳደጊያ መንገድ ነው፡፡
አኔ ፋዲማን
በእኔ ሥነ ፅሁፍ ውስጥ ዕድል የሚጫወተው ሚና
አለ ብዬ አላምንም፡፡
ኢታሊ ካልቪኖ
ያለ ሥነ ፅሁፍ ህይወቴ አሰቃቂ ነው፡፡
ናጀብ ማህፉዝ




ፈጠራውን ያገኘሁት ከ24 አመታት በፊት ነው ብሏል
     ቶማስ ኤስ ሮዝ የተባለው አሜሪካዊ አይፎን እ.ኤ.አ በ1992 ያገኘሁት የግሌ የፈጠራ ውጤት ነው፣ አፕል ኩባንያ የፈጠራ ውጤቴን ዘርፎኛልና 10 ቢሊዮን ዶላር ካሳ  ሊሰጠኝ ይገባል ሲል በኩባንያው ላይ ክስ መመስረቱን ዘ ቴሌግራፍ ዘገበ፡፡
አሜሪካዊው እ.ኤ.አ በ1992 ኤሌክትሮኒክ ሪዲንግ ዲቫይስ ለተባለ ባለ አራት ማዕዘንና ስክሪን ያለው በእጅ የሚያዝ የፈጠራ ውጤቱ የባለቤትነት ማረጋገጫ እንዲሰጠው ለሚመለከተው አካል አመልክቶ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤አፕል ኩባንያ ከዚህ የፈጠራ ውጤቴ የወሰዳቸውን ቴክኖሎጂዎች በመጠቀም አይፎን፣ አይፓድና ሌሎች የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎችን አምርቷል በሚል ክስ መመስረቱን ጠቁሟል፡፡
ግለሰቡ የእሱን ፈጠራና የአይፎንን ተመሳሳይነት ያረጋግጣሉ ያላቸውን የፈጠራ ውጤት ንድፎች ከክሱ ጋር አያይዞ ያቀረበ ቢሆንም፣ በወቅቱ ያቀረበውን የፈጠራ ባለቤትነት ማረጋገጫ ማመልከቻ ተከታትሎ ዳር ሳያደርሰው በመቅረቱ የባለቤት እውቅና ሳይሰጠው መቅረቱን በመጥቀስ፣በአፕል ላይ የመሰረተውን ክስ በአሸናፊነት ላይወጣው ይችላል መባሉን አስረድቷል፡፡ቶማስ ኤስ ሮዝ አቤቱታውን ለፍሎሪዳ ደቡባዊ አውራጃ ፍርድ ቤት ማቅረቡን የጠቆመው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን አፕል በግለሰቡ የቀረበበትን የፈጠራ መብት ዝርፊያና የተመሰረተበትን ክስ በተመለከተ የሰጠው ምላሽ አለመኖሩን ገልጧል፡፡