Administrator

Administrator

Saturday, 14 November 2020 10:42

አሜሪካ ከምርጫው ማግስት….

  ባለፈው ቅዳሜ…
አለም ለሳምንታትና ወራት አይንና ጆሮውን ጥሎ ከቆየባት ልዕለ ሃያሏ አሜሪካ ያልተጠበቀ ነገር ሰማ - በ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸንፋሉ ተብለው እምብዛም ግምት ያልተሰጣቸው ዲሞክራቱ ጆ ባይደን፤ ከእልህ አስጨራሽና አጓጊ ትንቅንቅ በኋላ ድልን መቀዳጀታቸውና 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸው እርግጥ ሆነ፡፡
ባይደን 76.3 ሚሊዮን ድምጾችን በማግኘት ወይም 50.7 በመቶ ሲያሸንፉ፣ ትራምፕ በበኩላቸው 71.6 ሚሊዮን ድምጾችን ወይም 47.6 በመቶ አግኝተው መሸነፋቸውን መገናኛ ብዙሃን ይፋ አደረጉ።
ገና የምርጫው ውጤት ሙሉ ለሙሉ ሳይገለጽ ጀምሮ "ምርጫው ተጭበርብሯል፤ ክስ እመሰርታለሁ" ሲሉ የሰነበቱት ዶናልድ ትራምፕ፤ ባይደን በምርጫው ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎም፣ ሽንፈታቸውን በጸጋ ለመቀበል ሳይፈቅዱ ሳምንት አልፏል።
ባይደን አሸናፊነታቸው በታላላቅ መገናኛ ብዙሃን ይፋ መደረጉን ተከትሎ፣ ከተለያዩ የአለም አገራት መሪዎች የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት የተላለፈላቸው ቢሆንም፣ ተሸናፊው ትራምፕ ግን እንደ ወትሮው ልማድ ስልክ ደውለው የምስራች ሊሏቸው ይቅርና የምርጫ ውጤቱንና ሽንፈታቸውን በጸጋ ለመቀበል አለመፍቀዳቸውን “እጅግ አሳፋሪ” ሲሉ ነበር የገለጹት - ባይደን፡፡
በአሜሪካ የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሸናፊ የሆነው አዲሱ ተመራጭ፣ አዲሱ የፈረንጆች አመት በገባ በ20ኛው ቀን በደማቅ በዓለ ሲመት ቃለ መሃላ ፈጽሞ ስልጣኑን ከተሰናባቹ ፕሬዚዳንት እንደሚረከብ በህግ መደንገጉን ያስታወሰው ቢቢሲ፣ ተመራጩ ፕሬዚዳንት ስልጣን እስከሚረከቡበት ጊዜ ድረስ የሽግግር ቡድን እንደሚያቋቁሙም ጠቁሟል፡፡
ዘንድሮ ግን ነገሮች በተለመደው መንገድ የሚያመሩ አይመስልም፡፡ በአሜሪካ ታሪክ በምርጫ ተሸንፎ ስልጣን አልለቅም ያለ ፕሬዚዳንት አለመኖሩን ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ትራምፕ ግን አፍ አውጥተው “አልለቅም!” ባይሉም ሁኔታቸው ወደዚያ የሚያመራ ይመስላል ብሏል፡፡
ምርጫው መጭበርበሩንና አለመሸነፋቸውን በተደጋጋሚ በመናገር የድምጽ ቆጠራው እንዲደገም ሲጠይቁ የሰነበቱት ትራምፕ፣ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ወስደው እንደሚሟገቱ ኮስተር ብለው ማወጃቸውንና ከፍተኛ በጀት መድበው ለክርክር መዘጋጀታቸውን ቀጥለዋል፡፡
የመራጩ ህዝብ ድምጽ ቆጠራ አሁንም ገና ሙሉ በሙሉ ያልተጠናቀቀ ሲሆን፣ በአንዳንድ ግዛቶችም የድምጽ ቆጠራው ዳግም እንዲከናወን ተወስኗል፡፡ የምርጫው ውጤት በሚመለከተው የአገሪቱ አካል ማረጋገጫ የሚሰጠውና የመጨረሻው ውጤት ይፋ የሚደረገውም ከአንድ ወር ጊዜ በኋላ እንደሚሆን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ባይደን ምን አስበዋል?
በትራምፕ ቅጥ ያጣ የውጭ ግንኙነት ከተቀረው አለም በርካታ አገራት ያኳረፏትን አሜሪካ በአፋጣኝ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት እንደሚመልሷት ሲናገሩ የከረሙት ጆ ባይደን፣ ወደስልጣን ሲመጡ በቅድሚያ ያደርጓቸዋል ተብለው ከሚጠበቁ ነገሮች መካከል በትራምፕ እምቢተኝነት ከፓሪሱ የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት የወጣችውን አሜሪካ ወደ ስምምነቱ መመለስ እንደሚገኝበት ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በታላላቅና ሃብታም የአገሪቱ ኩባንያዎች ላይ ከበድ ያለ ግብር በመጫን የሚያገኙትን ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ስራዎችን ለማከናወን እንደሚጠቀሙበት የሚናገሩት ባይደን፣ አሜሪካውያን በሰዓት የሚያገኙትን ዝቅተኛውን ክፍያ ከ7.25 ዶላር ወደ 15 ዶላር ከፍ እንደሚያደርጉም በምርጫ ቅስቀሳቸው ደጋግመው ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
አሸናፊው መንበሩን ለመረከብ
ምን ቀራቸው?
ፎርብስ መጽሄት እንደዘገበው፣ ባይደን በይፋ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የተወሰኑ ነገሮች ይቀሯቸዋል፡፡ አንደኛው ነገር ሁሉም ግዛቶች የመጨረሻውን የድምጽ ቆጠራ ውጤት አጽድቀው ማስረከብና፣ እስከ ታህሳስ 8 ቀን ድረስም እያንዳንዱ ግዛት ለፕሬዚዳንቱ ድምጽ የሚሰጡ መራጮችን መምረጥ ይገባዋል፡፡
መራጮቹ ለፕሬዚዳንቱ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ተከትሎም የአገሪቱ ሴኔትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጋራ ድምጹን በመቁጠር የመጨረሻውን አሸናፊ ይፋ ያደርጉና ፕሬዚዳንቱና ምክትል ፕሬዝዳንቷ ቃለ መሃላ ፈጽመው በዓለ ሲመቱ ይከናወናል፡፡
80 በመቶ አሜሪካውያን የባይደንን
ድል ያምኑበታል
የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ነጻና ፍትሃዊነት በተለይ በትራምፕና በሪፐብሊካኑ ጥያቄ ውስጥ ቢገባም፣ 80 በመቶ አሜሪካውያን ግን የባይደንን ድል እንደሚያምኑበትና ምርጫው ነጻና ፍትሃዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ አንድ ጥናት ማመልከቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ሮይተርስ አይፒኤስኦኤስ ከተባለ ተቋም ጋር በመተባበር የሰራውን ጥናት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ 79 በመቶ ያህል አሜሪካውያን ባይደን አሸንፈዋል ብለው እንደሚያምኑ ሲናገሩ፣ 13 በመቶ ያህሉ አሸናፊው ገና አልተወሰነም ብለው እንደሚያስቡ፣ 3 በመቶው በአንጻሩ አሸናፊው ትራምፕ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በምርጫው ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት እንዲገልጹ ከተጠየቁት ሪፐብሊካን የጥናቱ ተሳታፊዎች መካከል 60 በመቶ ያህሉ ባይደን አሸንፈዋል ብለው የሚያምኑ ሲሆን፣ ሁሉም ዲሞክራቶች ማለት ይቻላል በባይደን አሸናፊነት ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ እንደሌላቸው መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ምርጫው መጭበርበሩን የጠቆመ
 1 ሚ. ዶላር ይሸለማል
የቴክሳሱ ገዢ ሪፐብሊካኑ ዳን ፓትሪክ በዘንድሮው የአገሪቱ ምርጫ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸሙን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ላቀረበ ወይም ጥቆማ ለሰጠ የ1 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት እንደሚሰጡ ማስታወቃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደ ትራምፕ ሁሉ በተደጋጋሚ የዘንድሮው ምርጫ ተጭበርብሯል ሲሉ የተደመጡት ፓትሪክ፣ በቴክሳስ ግዛት ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአገሪቱ ግዛቶች ጭምር የምርጫ ማጭበርበር መፈጸሙን ለጠቆሙ ሰዎች ወይም ተቋማት ሁሉ ሽልማቱን ማዘጋጀታቸውን እንደተናገሩ ዘገባው አመልክቷል፡፡
ትራምፕ ለመጽሐፍና ለቲቪ 100 ሚሊዮን ዶላር ቀርቦላቸዋል
ዶናልድ ትራምፕ ምንም እንኳን በምርጫው ቢሸነፉም፣ ቢዝነሱ ግን እንደ ፖለቲካው አክሳሪ እንዳልሆነባቸው ነው ዴይሊ ሜይል ባለፈው ረቡዕ የዘገበው። ዘገባው እንዳለው ከሆነ ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበራቸው የአራት አመታት የፕሬዚዳንትነት ቆይታ ዙሪያ የሚያጠነጥን መጽሐፍ እና የቴሌቪዥን ፕሮግራም ለማዘጋጀት ከኩባንያዎች የ100 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ቀርቦላቸዋል፡፡
“እንኳን ደስ ያለዎት!”
ዲሞክራቱ ባይደን በምርጫ ማሸነፋቸው ይፋ መደረጉን ተከትሎ የተለያዩ አገራት መሪዎች ለተመራጩ የ“እንኳን ደስ ያለዎት!” መልዕክታቸውን በአፋጣኝ መላካቸው ቢነገርም፣ ባልተለመደ ሁኔታ አንዳንድ አገራት ግን በነገርዬው ያላመኑበት ይመስል ዝምታን መርጠው መቀጠላቸው ነው የተነገረው፡፡
ለባይደን የምስራች መልዕክት ካልላኩ የአለማችን አገራት መካከል የሩስያ፣ ሜክሲኮና ብራዚል መሪዎች እንደሚገኙበት የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤መሪዎቹ ለምን ዝምታን መረጡ ለሚለው ጥያቄ ሁነኛ መልስ ለመስጠት ቢያዳግትም አንዳንዶች ግን ከፖለቲካዊ ሽኩቻ ጋር እያያዙት እንደሚገኙ ጠቁሟል፡፡
  “አንድ ሃሳብ ላይ መድረስ አለብንና የመጨረሻ ሃሳብ ስጡበት”
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉስ  ልጆች ሶስት ልጆቻቸውን ጠርተው “እንግዲህ ልጆቼ፤ ዕድሜዬ እየገፋ፣መቃብሬ እየተቆፈረ፤ የመናዘዣዬ ክሬ እየተራሰ ያለሁበት የመጨረሻዬ ሰዓት ላይ ደርሻለሁ፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳቸሁ ውርስ ትወስዱ ዘንድ ለሃገራችሁ ልትሰሩላት የምትችሉትን ነገር ትነግሩኛላችሁ፡፡ በሃሳቡ የላቀና የበቃ ልጅ መንግስቴን ያስተዳደርል” አሉ፡፡
ስለዚህ ልጆቹ ተራ በተራ ተናገሩ፡-
አንደኛው እኔ የመንስግት የማስተዳር እድል ባገኝ፤
ሀ/ መልካም አስተዳደርን አነግሳለሁ
ለ/ ስልጣኔን አስፋፋለሁ
ሐ/ ደሃው እንዲማር የተጀመረው የትምህርት ሥርዓት በተሸሻለ ደረጃ የተለየ  መልክ እንዲይዝ አደርጋለሁ፡
ሁለተኛው
ሀ/ሌላ ዝርዝር ሳያስፈልገኝ ፣ሀገሬን የነካ ማንም ይሁን ማን ቢቻል በሰላም             አሊያም  በኃይል አቋሙን እንዲያሻሽል አደርገዋለሁ፡፡
ለ/ ያ አይሆንም ካለ ለአንዴም ለሁሌም አስቦበት ለሀገርና ለህዝብ እንዲቆም  እደራደረዋለሁ
ሐ/ ሁሉም ካላዋጣ የማያዳግም እርምጃ እንዲወሰድበት አደርጋለሁ፡፡
ሶስተኛው ልጅ፡-  የእኔ ሃሳብ ፤ከማንኛውም ይለያል ፤በምንም ዓይነት ህዝቡን            ሳላማክር  ማናቸውንም፣ እርምጃ አልወስድም!
 ንጉስ አማካሪዎቻቸውን ሰብስበው፤ “እንግዲህ የአማካሪዎቻችሁን ሃሳብ ሰማችሁ፡፡ አንዳንድ ሃሳብ ስጡበት፡፡”
የመጀመሪያው --  ለዲሞክራሲ ቅድሚያ እንስጥ
ሁለተኛው------  አገር እየተወረረ ወዲያና ወዲህ የለም፤ እንዝመት
ሶስተኛው----የአፍሪካን መንግስታት ሃሳብ እንወቅ - ከተባበሩት  መንግስታት ህግና መመሪያ አንጻር እየሄድን  መሆናችንን  እንወያይበት የጎረቤቶቻችንን ሁኔታ ያገናዘበ ውሳኔ እንወስን…. አሉ
ንጉሱም፤ “የሁላችሁንም አስተሳሰብ አድምጫለሁ፡፡ ሁላችሁም፣ የበኩላችሁን ልባዊ አስተያየት ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ፤ የለውጥ አየር የነፈሰባት አገር መቼም ቢሆን ጉዞው አልጋ በአልጋ ሆኖ አያውቅም፡፡ ስለሆነም ሂደቱን ከነችግሩ መርምሬና መክሬበት አስተውዬዋለሁ፡፡ ውጤቱ እሩቅ ቢሆንም ለእርምጃ መቻኮሉ አያዋጣንም፡፡ ትዕግስት ዛሬም መራራ ናት፤ ፍሬዋም ግን ጣፋጭ  ነው!ስለዚህ አሁንም ታገሱ፡፡ ጊዜ ራሱ መልሶ ይሰጣል”   አሏቸው፡፡
በየትም አገር፣ ህይወት ከዳገትና ከቁልቁለት ተለያይታ አታውቅም። ጥጋ ጥጓን  ውስጧን፣ ጓዳ ጎድጓዳዎቿን ሳናስብ ሜዳ ሜዳውን ብቻ መሸምጠጥ አንችልም። ይህን ደግሞ ሲደርስና ስንደርስበት ብቻ ሳይሆን አስቀድመን ከባለሙያዎች ከሀገር ወዳዶች፣ ከምሁራን፣ ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ከአመራሮቻችን ጋር ተመካክረን አደብ እንድንገዛበት ማድረግ ይኖርብናል። በእርግጥ አንድ የስነጥበብ ፈላስፋ እንዳለው “ በጦርነት መካከል ጎራዴ ምዘዝ እንጂ ግጥም ላንብብ አትበል።” ትክክለኛውን መሳሪያ ለትክክኛው ቦታ ምረጥ ማለቱ ነው! ዕውነት ነው፤ ግድም ነው።
ለውጥ እንዲኖር ከተፈለገ ለዋጩም ተለዋጩም እውቀትም፣ ንቃተ-ህሊናም ሊኖራቸው ያስፈልጋለ፤። ጂኒየስ (የላቀ -ሊቅ) እንጂ ጂኒ እና አልጂኒ በመባባል ለውጥ አናመጣም። የፕሮፓጋንዳ ቅስቀሳ ብቻውን መንጋጋጋሪያ መሆን እዲ ህዝብን አስተማሪም አጋዢም ሊሆኑ አይችሉም። በሁሉም ወገን ስንት የደም መስዋዕትነት የተከፈለባቸውን ትግሎች ዛሬ ለወግና እኛ ማለፊያና መስተዋት መወልወያ ብናደርጋቸው፣ ያለጥርጥር በደም የቀላ ቲቪና ሬዲዮ ብቻ ነው- ምርታችን፡፡በሬዲዮና በቴሌቪዥን ሆኖም ለሁሉም ሰዓት አለው። ኢትዮጵያ ዛሬም “ምነው የጦርነቱንስ  ነገር ዝም አላችሁ?” ብላ እንደምትዘብትብን ቢያንስ ለህሊናችንና ለአሁን ህልውናችን ሊገባን ይገባል። ከዘመነ-መሳፍንት እስከ ዛሬ የፈሰሰውን ደም አይታለች! ወራሪ ሲመጣ ደም ፈሷል! በመሳፍንትና ሹማምንት ሽኩቻ ደም ፈሷል! በድርጅቶችና ፓርቲዎች ሽኩቻ ደም ፈሷል። በጎሳዎች ሽኩቻ ደም ፈሷል! በእርስ በርስ (ሲቪል) ጦርነት ደም ፈሷል! በሰላም መንገድ ላይ ናት በተባለ ማግስት ደም ፈሷል… ነገም እዚያው መንገድ ላይ መሆኗን  አልቀበልም የሚል ካለ የኢትዮጵያ ነገረ- ስራ ያልገባው ሰው ነው!
ዛሬ ስለ ሀገሩ የሚቆረቆር አሳቢ - አንጎልና ሩህሩህ አንጀት ያለው ዜጋ ይህን አይስተውም!
ለብዙ ዘመናት “እናቴን ያገባ ሁሉም አባቴ ነው!” አልን
“ከክፉ ተወልጄ ስፈጭ አደርኩ” አልን!
“ላግዝሽ ቢሏት መጇን ደበቀች” አልን!
“አገባሽ ያለሽ ላያገባሽ፤ ከባልሽ ሆድ አትባባሽ!” አልን።
“እናውቃለን ብንናገር እናልቃለን” አልን።
ብዙ አልን… አልን… አልን…
አሁን የቀረን አንድ አውራ ተረት፡-
“ከሞት ከህይወት የቱ ይሻልሃል? ቢባል፣ ሲያስብ ዘገየ!” የሚለው ነው።

Saturday, 07 November 2020 13:58

የጃሉድ አስገራሚ ንግግሮች

   (በተለየ የአዘፋፈን ስልቱ ከፍተኛ አድናቆትን ያተረፈው ድምፃዊ ጃሉድ፤ በቃለ-መጠይቆች ላይ በሚሰጣቸው አስቂኝና አስገራሚ ምላሾችም  ይታወቃል፡፡ "የጃሉድ 10 አስቂኝ ንግግሮች" በሚል በዩቲዩብ ላይ ካገኘናቸው ከተለያዩ ሚዲያዎች የተሰባሰቡ ቃለ ምልልሶች መካከል ለጋዜጣ
አቀራረብ ምቹ የሆኑትን መርጠን እነሆ ብለናል - ዘና እንድትሉበት፡፡)             ጋዜጠኛ፡- ስለ ስራዎችህ እንጂ ስለ ህይወትህ ብዙም እውቀት የለንም። ስለ ትውልድህና እድገትህ ትንሽ ብታጫውተን…….?
ጃሉድ፡- ትውልድ… የተወለድኩት መንገድ ላይ ነው። እዚህ ጎተራ የሚባል ቦታ…። ያው እንግዲህ ምጥ መጣ ተባለና ወደ ሆስፒታል እናትህን ስንወስዳት… ጎተራ ጋ ተወለድክ ነው ያሉኝ።
ጋዜጠኛ፡- አዲስ አበባ ማለት ነው?
ጃሉድ፡- አሁን ቀለበት መንገዱ ማለት ነው፡፡ ፈርጡ እኔ ነኝ መሰለኝ… አላውቅም (እየሳቀ)
አስፋው (ኢቢኤስ)፡- አሜሪካን ሃገር ኮንሰርት ላይ ባገኘሁህ ሰዓት፣ ትንሽ ችግር ላይ ነበርክ መሰለኝ....  ምን ነበር የተፈጠረው በዚያን ወቅት?
ጃሉድ፡- እ….እኔ አልገባኝም…
አስፋው፡- አልጫወትም እስከ ማለት ሁሉ ደርሰህ ነበር?
ጃሉድ፡- እንትን ነው… ልክ ዋንጫው የተወሰደ ቀን…..
አስፋው፡-  የዋንጫው ዕለት!
ጃሉድ፡- እንግዲህ እኔ የማውቀው …..ለሃገሪቱ ኪነ ጥበብ ብዙ መድከሜን ነው… እንጂ ሌላ ነገር አላውቅም። እነሱ ታዳጊ ልጆች ናቸው… መድረክ ላይ መጥተው የሆነ የሆነ ነገር ተናገሩኝ። የብሔር ብሔረሰቦች ሰንደቅ በሙሉ የእኔ ነው…. ከዚህ በፊትም የነበረው የእኔ ነው… የኃይለስላሴም ባንዲራ የእኔ ነው፡፡ ዛሬ ባንዲራ በዝቷል……ባንዲራው በሙሉ የእኔ ነው።
ግን የፈለኩትን ብይዝ ባልይዝ ችግር የለብኝም….. ብዕር ይበቃኛል ለእኔ፡፡ “ለምን ይሄንን  አደረክ… ባንዲራ እንደዚህ ነው… እኛ እንደዚህ እንባላለን” ምናምን ብለውኛል። እኔ ምን አገባኝ… እዚያ ውስጥ! በዚያ የተነሳ ነው ረብሻው የመጣው። እኔ አገሬን እወዳለሁ፡፡ እዚያም ያሉት አገራቸውን አይጠሉም። በመጨረሻ ተያይዘን… ጓዛችንን ይዘን፣ ወደ አገራችን እንግባ አልኩኝ። በቃ ቢቸግረኝ -- እንደዚህ ነው ያልኩት። ሌላ ነገር አልተናገርኩም።
ነፃነት (የቤተሰብ ጨዋታ)፡- ጃሉድ… በጣም የሚያሳስብህ ነገር ምንድን ነው?
ጃሉድ፡- አረ ምንም! (ቆፍጠንና ኮስተር ብሎ)
ነፃነት (በረዥሙ ከሳቀ በኋላ)፡- ምንም አያሳስብህም?
ጃሉድ፡- አይ ምናልባት… አፈር ውስጥ ገብቼ፣ ከላይ አፈር ሲጭኑብኝ… እሱ ብቻ ያሳስበኛል።
እንደው  እንዳላውቀው……እዚያ ጋ ሆኜ እያወቅሁት ከጫኑብኝ…..
ነፃነት፡- ማንም አውቆ አያውቅም።
ጃሉድ፡- አንተ… ገብተህ ታውቃለህ?
ነፃነት፡- ማንም አውቆ አያውቅም፡፡
ጃሉድ፡- አረ? እርግጠኛ ነህ?
ነፃነት፡- አዎ!
ጃሉድ፡- እስቲ (እጁን ይዘረጋና ይመታዋል) በቃ እሱ ብቻ  ነው የሚያሳስበኝ…
ጋዜጠኛ፡- እስቲ ስለ ግል ህይወትህ ንገረን …ትዳር አለህ? ትዳር ላይ ያለህ ስሜት እንዴት ነው?
ጃሉድ፡- አዎ እሷ ነገር ትቀረኛለች መሰለኝ። እሷ ነገር ከተሟላች… ዓለም ለእናንተ ዘጠኝ ናት አይደል… ለእኔ አስር ትሆናለች… አስር ትሞላለች፡፡ እሷ ነገር እስክትስተካከል… ያው ላገባ ነው፡፡ (ይቅርታ አግብቻለሁ ብያችሁ ነበር።) አሁንም እሷም ከሰማችኝ አላውቅም…. አልገረመችኝም፡፡ ሌላ የምትገርም አይቻለሁ…. ከእንደገና ሌላ ላገባ ነው።
ጆሲ፡- አሁን በእኔ በኩል ጥያቄዎቼን ጨርሻለሁ። ጃሉድ… ቀረ የምትለው ነገር ካለ ወይም ማስተላለፍ የምትፈልገው መልዕክት ካለ..…ወይም ምስጋና ማቅረብ የምትፈልግ ከሆነ …. ዕድሉን ልስጥህ…..
ጃሉድ፡- ጆዬ … አንተ ለብዙ ሰው ቤት አሰጥተሃል… መኪና አሰጥተሃል…ህመምተኞች ጤነኛ አስደርገሃል። አሁን ለእኔም እንግዲህ ሁለት የአንበሳ ግልገል አሰጠኝ። በቃ በመጨረሻ የማስተላልፈው መልዕክት ይሄ ነው ጆዬ….
ጆሲ (በሳቅና በድንጋጤ መሃል ሆኖ)፡- ሁለት የአንበሳ ግልገል?
ጃሉድ፡- አዎ ግልገሎች አሰጠኝ…
ጆሲ (አሁንም እየሳቀ)፡- ምን ታደርጋቸዋለህ?
ጃሉድ (ኮስተር ብሎ)፡- በቃ አብሬያቸው እኖራለሁ ...የቤት እንስሳት ማድረግ እፈልጋለሁ።
ፍላጎቴ ነው ጆዬ - ምን ችግር አለው?! ምን ችግር አለው?!  

  የሪፐብሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ እና ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ከፍተኛ ፉክክር ያደረጉበትና ለ59ኛ ጊዜ የተካሄደው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የመጨረሻ ውጤት፣ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ፣ በፖስታ ድምጻቸውን የሚሰጡ ዜጎችን ድምጽ ለመቁጠር ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ፣ ለቀናት ይፋ ሳይደረግ ሊቆይ እንደሚችል ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ እጅግ የተካረረ ፉክክር የታየበት ምርጫ እንደሆነ በተነገረለት የ2020 ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፤ መደበኛው ድምጽ በተሰጠበት ባለፈው ረቡዕ፣ ገና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ድምጾች ተቆጥረው ባላለቁበት ሁኔታ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከነጩ ቤተ መንግስት ምርጫውን ስለማሸነፋቸው ፍንጭ የሚሰጥና ማጭበርበር ስለመፈጸሙ ያደረጉት ንግግር፣ ሪፐብሊካኖችን ክፉኛ ማስቆጣቱና ግጭት ሊቀሰቅስ እንደሚችል መሰጋቱ ተዘግቧል፡፡
45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለተጨማሪ አራት አመታት በስልጣን ላይ የሚቆዩበት ወይም ጆ ባይደን 46ኛው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሚሆኑበት የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ከመደበኛው የድምጽ መስጫ ጊዜ በፊት 100 ሚሊየን የሚሆኑ ዜጎች ቀድመው ድምጻቸውን የሰጡበትና በአገሪቱ ታሪክ ይህን ያህል ሰው ድምፁን የሰጠበት የመጀመሪያው ምርጫ ነው ተብሏል፡፡
በአሜሪካ የምርጫ ስርዓት መሰረት፣ አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ፕሬዚዳንት ለመሆን፣ የአገሪቱ ግዛቶች እንደ ሕዝብ ብዛታቸው ተከፋፍለው ከያዙት 538 አጠቃላይ ድምፅ ውስጥ 270 ድምፅ ማግኘት ይጠበቅበታል፡፡
እጅግ ውዱ ምርጫ
የ2020 የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊና የኮንግረስ ምርጫ፣ በአገሪቱ ታሪክ ከፍተኛ ወጪ የወጣበት እጅግ ውዱ ምርጫ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው፤ የዘንድሮው ምርጫ በድምሩ 14 ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ሲሆን፣ ገንዘቡ ባለፉት የ2016 እና የ2012 ምርጫዎች ከወጣው ድምር ወጪ የሚበልጥ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው…
ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው የሚሸነፉ ከሆነ፣ በቀድሞ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በምርጫ የተሸነፉ የመጀመሪያው አሜሪካዊ ፕሬዚዳንት እንደሚሆኑ ተነግሯል፡፡ ትራምፕ ቀንቷቸው በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ ደግሞ፣ የዘንድሮው ምርጫ በአሜሪካ ታሪክ አራት ፕሬዚዳንቶች ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ዳግም የተመረጡበት የመጀመሪያው ምርጫ ይሆናል፡፡
ባይደን በምርጫው የሚያሸንፉ ከሆነ፣ የትራምፕን መንበረ ስልጣን ብቻ ሳይሆን በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ዕድሜያቸው ከገፋ ወደ ስልጣን በመምጣት ይዘውት የነበረውን ክብረ ወሰን ጭምር የሚነጥቁ ይሆናል ተብሏል፡፡
ትራምፕም ያሸንፉ ጆ ባይደን አሜሪካ በታሪኳ የዕድሜ ባለጸጋውን ፕሬዚዳንት የምታገኝ ሲሆን ትራምፕ ካሸነፉ በ74 አመታቸው፣ ባይደን ካሸነፉ ደግሞ በ78 አመታቸው በዓለ ሲመታቸውን እንደሚያከብሩ ተነግሯል፡፡
“ትራምፕ ካሸነፈ አገር ጥዬ
እጠፋለሁ” ባዮች
“አነጋጋሪው ዶናልድ ትራምፕ በምርጫው አሸንፈው ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን አገሪቱን የሚመሩ ከሆነ፣ ማቄን ጨርቄን ሳልል አገር ጥዬ እጠፋለሁ” የሚሉ አሜሪካውያን ዝነኞች መበራከታቸውን ሚረር ዘግቧል፡፡
ትራምፕን ደጋግሞ በመተቸት የሚታወቀው ጆን ሌጀንድ፣ ከእነዚህ ዝነኞች አንዱ ሲሆን ትራምፕ ካሸነፉ ከእነ ቤተሰቡ አሜሪካን ጥሎ እንደሚሄድ መናገሩ ተዘግቧል፡፡  
የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኙ ቶሚ ሊ በበኩሉ፤ ትራምፕ ካሸነፉ አገሩን ተሰናብቶ ወደ እንግሊዝ አልያም ግሪክ በማቅናት ቀሪ ህይወቱን በስደት እንደሚገፋ በፈጣሪ ስም መማሉ ተነግሯል፡፡
ሌላኛው የሮክ ሙዚቃ አቀንቃኝ ብሩስ ስፕሪንግስተን፣ በቅርቡ ከዴይሊ ቴሌግራፍ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ፣ ትራምፕ ካሸነፉ አገሩን ጥሎ እንደሚሰደድ ተናግሯል ተብሏል፡፡
በ2016 ትራምፕ ካሸነፈ አሜሪካን ጥለን እንጠፋለን ሲሉ በይፋ ተናግረው የነበሩት ሳሙኤል ጃክሰንና ሁፒ ጎልድበርግን የመሳሰሉ በርካታ ታዋቂ አሜሪካውያን፣ ትራምፕ ቢያሸንፉም፣ ቃላቸውን አክብረው ከአገር እንዳልወጡ የሚረር ዘገባ አስታውሷል፡፡          በአለማችን የከተማ ነዋሪዎች ብዛት በፍጥነት እየጨመረ እንደሚገኝና በአሁኑ ወቅት ከአጠቃላዩ የአለማችን ህዝብ 56.2 በመቶ ያህሉ በከተሞች እንደሚኖር የአለም የኢኮኖሚ ፎረም ከሰሞኑ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ባለፉት 70 አመታት በአለማቀፍ ደረጃ ያለውን የከተማ ነዋሪዎች ሁኔታ በገመገመበት ጥናት ያወጣውን ሪፖርት ጠቅሶ ፎረሙ በድረገጹ እንዳስነበበው፣ በእነዚህ አመታት በአፍሪካና በእስያ የከተማ ነዋሪዎች ቁጥር ከእጥፍ በላይ ማደጉን ለማየት ተችሏል፡፡
እ.ኤ.አ እስከ 2050 ድረስ ባሉት አመታት ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ ከ68 በመቶ በላይ የሚሆነው የከተማ ነዋሪ ይሆናል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው መረጃው፣ በ2035 በህዝብ ብዛት ቀዳሚዋ የአለማችን ከተማ ጃካርታ ትሆናለች ተብሎ እንደሚገመትም አመልክቷል፡፡
በመጪዎቹ 50 አመታት ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ከተሞች የሚኖረው ህዝብ ቁጥር አሁን ካለበት 40 ሚሊዮን ወደ 150 ሚሊዮን ከፍ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክሎ ገልጧል፡፡


 “ቤቢ ሻርክ” የተሰኘውና በ10 አመቱ ኮርያ አሜሪካዊ ታዳጊ ሆፕ ሴጎይን የተቀነቀነው ተወዳጅ የህጻናት መዝሙር በዩቲዩብ 7.04 ቢሊዮን ጊዜ ያህል መታየቱንና በድረገጹ ታሪክ በብዛት የታየ የመጀመሪያው ቪዲዮ በመሆን አዲስ ክብረ ወሰን መያዙን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በደቡብ ኮርያዊው ኩባንያ ፒንክፎንግ የተቀረጸው “ቤቢ ሻርክ” በዩቲዩብ ላይ ከተጫነበት 2015 አንስቶ የታየበት አጠቃላይ ጊዜ ቢደመር 30 ሺህ 187 አመታት ያህል እርዝማኔ እንደሚኖረው የጠቆመው ዘገባው፣ ኩባንያው በዚህ መዝሙር አማካይነት ከዩቲዩብ ብቻ 5.2 ሚሊዮን ዶላር ያህል ገቢ ማግኘቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ከዚህ ቀደም በዩቲዮብ በብዛት በመታየት ክብረወሰኑን ይዞ የነበረው “ዲስፓሲቶ” የተሰኘው የድምጻዊ ሉዊስ ፎንሲ የሙዚቃ ቪዲዮ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፣ ቪዲዮው 7.038 ቢሊዮን ጊዜ ያህል መታየቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
የኤድ ሼራን “ሼፕ ኦፍ ዩ” በ5.05 ቢሊዮን፣ የዊዝ ካሊፋ “ሲዩ አጌን” በ4.79 ቢሊዮን፣ የጌት ሙቪስ “ማሻ ኤንድ ዘ ቢር” በ4.36 ቢሊዮን፣ የሎሎ ኪድስ “ጆኒ ጆኒ የስ ፓፓ” በ4.14 ቢሊዮን፣ የማርክ ሮንሰን “አፕ ታውን ፋንክ” በ3.99 ቢሊዮን፣ የፒኤስዋይ “ጋንጋም ስታይል” በ3.84 ቢሊዮን፣ የሚሮሻካ ቲቪው “ለርኒንግ ከለርስ” በ3.65 ቢሊዮን እንዲሁም የጀስቲን ቢበር “ሶሪ” በ3.36 ቢሊዮን እይታዎች እንደ ቅደም ተከተላቸው ከ3ኛ እስከ 10ኛ ደረጃ የያዙ፣ በዩቲዩብ በብዛት የታዩ ቪዲዮዎች መሆናቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

  የቀድሞው የአለማችን የእግር ኳስ ኮከብ አርጀንቲናዊው ዲያጎ አረማንዶ ማራዶና፣ ባለፈው ሳምንት የተሳካ የአንጎል ቀዶ ህክምና እንደተደረገለት መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በደም ማነስ ሲሰቃይ የቆየው የ60 አመቱ ማራዶና ባለፈው ሰኞ ቦነስ አይረስ ውስጥ ወደሚገኝ አንድ ክሊኒክ መወሰዱን ያስታወሰው ዘገባው፤ በአንጎሉ ውስጥ የደም መርጋት ችግር በመገኘቱ 80 ደቂቃ የፈጀ የተሳካ ቀዶ ህክምና እንደተደረገለት የግል ሃኪሙ መናገራቸውን አመልክቷል፡፡
ማራዶና ከቀዶ ህክምናው በኋላ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝና እንዳገገመ የጠቆመው ዘገባው፤ በርካታ አድናቂዎቹና ደጋፊዎቹ ከሆስፒታል ሲወጣ ጠብቀው ስሙን እየጠሩ ደስታቸውን እንደገለጹለትም አስረድቷል፡፡

   ግጥምን ሁሉም ሰው አንብቦ ለየራሱ የሚሰጠው ትኩስ ስሜት አለ፤ ወይ ይጠላል፤ ወይ ይወድዳል - ይላሉ የስነ ግጥም ሂስ ምሁር የሆኑት ኤስ ኤች በርተን፡፡ ይህ ግን ገና ድስቱ ምድጃ ሲነካ ነው፡፡ ደጋግመው ሲያጣጥሙትና፣ የቅመማውን ስልትና ይዘት ሲያጤኑ የሰውም ልዩነት፣ የጥበብም ቃና በጣም ይለያል፡፡
ግጥምን Good and bad በማለት አሊያም “Great, Good and bad” በማለት ሒሊየርና ፔረኔ ይለዩታል፡፡ የመጀመሪያው ግን እንዲህ ብለን ባንከፍለው በተሻለ ነበር ይሉናል፡፡ እንደገና “Major” “Minor” ስለሚባሉ ገጣሚያን ያወራሉ። እኛ ሀገር ገጣሚ አይደለሁም የሚል ሰው ስለሌለ፣ አንገታቸው ቀና ያለ፣ ዓይኖቻቸው ሕይወት መዝነው ስንኝ ጠርበው፣ የዜማ ቀለም የቀቡትን መለየት ከባድ ነው፡፡ የመጽሐፉ ብዛት የትየለሌ ነው (መጽሐፍ ካልነው) አንዳንዴም ነፍስ ያላቸው፣ የተወለዱና አበባቸው ውስጥ ፍሬ ያዘሉ ቀንበጦች ሳይታዩና ሣይጤኑ እንደ ሕልም ያልፋሉ፡፡
እናም በግልቦች ተርታ ሲወድቁ ስሜታቸው ይጐዳል፡፡ ውስጣቸው ይቀዘቅዛል፡፡ ከዚህ ለማዳን ብጥርጥር ያለ ሂስ ለመሥራት ጊዜውና ሁኔታው ባይፈቅድ እንኳ ፍካታቸውን ለአደባባዩ፤ ቁመናቸውን ለተደራሲ መሸሸግ አግባብ አይመስለኝም፡፡
ስለዚህም መፃሕፍት ቤት በገባሁ ቁጥር ስለ ግጥም ልቤ ተስፋ አይቆርጥም፡፡
አንዳንዶቹን በጨረፍታ አይቼ ቤት ሰልፍ ላይ ያስቀመጥኳቸውም ጥቂት አይደሉም። ይሁንና ግን ደግሞ ተስፋ ያነቦጡ አሉ። ለምሣሌ የትዕግስት ዓለምነህን የግጥም መጽሐፍ ሳየው፤ ሽፋኑ እጅግ ዘግንኖኝ ነበር፤ በዚያ ላይ ደግሞ በተገኘው መጽሐፍ ላይ (ሳይመርጡ) አስተያየት ለሚሰጡ ሰዎች ያለኝ እምነት ዝቅተኛ ስለሆነ ጀርባውን አይቼ እንደዋዛ አልፌው ነበር፡፡
የትዕግስት ጥራዝ ግን፣ ነፍስ የሚኮረኩሩ ማማሰያዎች አሉት፡፡
ለምሣሌ ገፅ 25 “ጥሪ” የሚለውን ግጥም እነሆ፡-
የተሳሰሩበትማገርናፍልጡ፣
የተቀጣጠለውላልቷልናምጡ፤
በጭድ ያልተቦካ፣ የመረሬ ልጥፍ ምርጉ
እየወደቀ፤
ሰንበሌጥ ክዳኑ፣ በድንገቴ ነፋስ ተመዞ
እያለቀ፣
አዝምማለችና ያረጀች ጐጇችን፣
በቁር በሐሩሩ ከመበተናችን፣
ጭቃውን ረግጠን፣ ቋሚና ወጋግራ በልኳ
ተጠርቦ፣
ምሰሶዋ ሳይወድቅ፣ ትጠገን ቤታችን፣
እንውጣ በደቦ፡፡
ግጥሟን ሙሉዋን የወሰድኳት፣ እንዴት ተሽሞንሙና የተጠረበች እንደሆነች አይተን - እንድናጣጥማት ነው፡፡
ዜማና ምት ብቻ አይደለም - የሀሳብ አወራረዱና ቅርፁ ሁሉ ሸጋ ነው፡፡ ቁምነገሩን ጭብጡን ስታዩት ሁለንታዊ (Universal) ነው፤ ለሀበሻ ብቻ አይደለም፤ ለሌላውም የሰው ዘር ይሆናል፡፡ ጐጆ ያልሠራ፣ ወይም የማይሠራ የለም፡፡ እንደተምሣሌት - ስታዩት ደግሞ ጀርባው ላይ ያለው ሥዕል፣ ውስጡ የደበቀችው ጥላ፣ ምናባዊ አቅምዋን የሚያሳይ ነው። ሼክስፒርን የማይበርድ የጥበብ እሣት ያደረገው የጭብጡ ትልቅነት እንደሆነ ግጥምን የተነተኑ ሁሉ መሥክረውለታል፡፡
 “ስቆርጠው” የሚለው የትዕግስት ግጥምም እጅግ የሚመስጥና የሚመነዘር ነው፡፡
አንድ ሁለት ስንኞችን ብቻ ልውሰድ፡-
የልብህ መሬቱ ጭንጫ ነበር ለካ፣
ሥር አልይዝ ብሎኛል የተከልኩት ዋርካ።
የልቡን ሚዛን ተመልከቱ፤ አስቸጋሪነቱን። ደግሞ የተራኪዋን ገርነት መዝኑት!
በጭንጫ ልቡ ላይ፣ የተከለችውን ዛፍ ግዝፈት፡፡ ምናልባት ይህ ዛፍ የእምነት ስራ ነው ዘር እንደመበተን፡፡
ይህ የተከለችውን የፍቅር ዋርካ ስር እንዳይሰድድ ያጠጠረውን ሰው መልሳ እንዲህ ትለዋለች፡- አሁንም ፍቅር እንደ ጐርፍ ውስጧ እየፈሰሰ፡፡
አልሻውምካልከኝ፤
አላስቸግርህም በፍሬ አልባ ሙግት፤
ባይሆንአትንቀለው፣
ይሆንሃልና ለርስትህ ምልክት፤
ግን አደራምልህ፣
ቅርንጫፉንሁሉ በሆዴ ከምረው፣
መልምልና ግንዱን
ለ’ሳቴ እየማገድኩ እንዳልፍበት ብርዱን፡፡
ግርምርም የሚል ነገር ነው፡፡ አሁንም ዛፉ ርስትህ ነው! ማለት፣ እንግዲህ ለሌላ ሰው አይሰጥም ዓይነት ነው፡፡ ያ ብቻ አይደለም፤ የመጨረሻዎቹ መዝጊያ ስንኞች እንዴት ያለ ዜማ ነው ያላቸው!! ብዙዎቹ የትዕግስት ግጥሞች በሙዚቃና ምት ችሎታቸው ከፍ ያለ ነው፡፡  የብዙ አማርኛ ግጥሞች ሠባራነትና ሽባነት ያለበትን ቦታ እርሷ ተወርውራ አልፋዋለች። ግጥሞቻችንን መርምሩ! ዋናው በሽታ ይህ ነው፡፡
“ጦም አዳሪ” የሚለው ግጥም የሀበሻን ይሉኝታ ቁልጭ አድርጐ የሚያሳይ ነው፡፡
ከልብህ በራፍ
ላይ ለወራት ቆሜአለሁ፣   
 ስትከፍት ስትዘጋ፣ ስትዘጋ ስትከፍት፣
ተወው አንዳከም ሐበሻነት ክፉ፣
 ነይ ግቢ እስካላልከኝ፣
አላልፍም ከደፉ፡፡
ተራኪዋ ግብዣ ትጠብቃለች፣ ተፈቃሪው ራስዋ ትምጣ ይላል፡፡ ይተያያሉ፣ ግን ውሣኔ እንደውሻ በባህል ሰንሰለት ተጠፍሯል። በ“ባቢሎን በሳሎን” ኮሜዲ ቴአትር ላይ ባልና ሚስቱ ልባቸው እየተፈላለገ፣ በይሉኝታ ሳሎናቸውን አጥረው፣ በስቃይ ነፍሳቸው ተንጠልጥላ እንደምትቃትት አይነት ነው ነገሩ! እነዚህ ግን ገና አልጀመሩም፡፡ ይህንን ነው ገጣሚዋ የምትሸነቁጠው፡፡ በዚህ መሃል ደግሞ ነጣቂ ቢመጣ፣ ስሜት ቢላላ፣ የዕድሜ ልክ ፀፀት ነው፡፡
የመጽሐፉን ርዕስ የያዘው “እልልታና ሙሾ”ም የሚመረጥ ግጥም ነው፡፡
እዚህ ግጥም ላይ መሠሪነትና ብቀላ አይን ላይን ተፋጥጠዋል፡፡ ተበቃዩ ወገን ግን ዳኛ ነው የሚፈልገው። ይኸ ዳኛ ከየት ይሆን…የሚመጣ!መዘግየቱ ሩቅነትን የሚጠቁም ይመስላል፡፡ ትዕግስት ብዙ በሽታዎችንና ግሣንግሥ ችግሮቻችንን ከነጥቀርሻቸው ታውቃቸዋለች፡፡ ከላይ የሚለብሱትን የበግ ለምድም ከቀበሮዎቹ ገፍፋ የማየት አቅም አላት። ግጥሞችዋ ማህበራዊ ሒሶች ይበዟቸዋል፡፡ “ገመና” የምንላቸው ሽንቁሮቻችንም ከአይኗ አልተሰወሩም፡፡ ፈልፋይና ቅንዐት (Zeal) ያላት ናት፡፡ ለብቻቸው ሞቀን ብለው፣ እሾህ ያንገበገበውን የሚረሣ ነፍስ የላትም። “ምናልባት “ሀገርህን ጥላት ልጄ” የሚል መጽሐፍ የፃፈውን ወጣት ደራሲ አይነት ነገር አይቼባታለሁ፡፡
ጆሮዎችዋ ወደ ውስጥም ወደ ውጭም የሚያዳምጡ ይመስላል፡፡ ግጥሞችዋ ከአንድ ሰሞን ወረት ያፈሠቻቸው አይደሉም። በሰው ልጅ ፍቅር የነደዱ ልቦች ላይ የከሰሉ ማዲያቶች ምስል ናቸው፡፡ ሳቆችዋ ይጣፍጣሉ፣ እንባዎችዎ አንገት ይነቀንቃሉ፡፡
ግጥሞቿ፤ እንደ ባህር ዛፍ ቅጠል ላይ ላዩን አይነድዱም፤ ሥር ገብተው የልብን እምብርት ይቆነጥጣሉ፡፡ እንደ ጉንዳን ደም ውስጥ ይሄዳሉ፤ እየቆነጠጡ፡፡
ገጣሚዋ ትልልቅ ጭብጦች እጅዋን ሞልተውታል፣ ብዕርዋን ውጠውታል፡፡ ጥቅል ሰው፤ ሀገር፣ እና ያገር ሰው ጭብጦችዋ ናቸው፡፡ ብዙዎቹ ጉዳዮችዋ መሣጭና ቆንጣጭ ናቸው፡፡ “አዬ ኢትዮጵያዬ!” ብላ ሀገርዋን በቁልምጫ እየጠራች፣ ችግሯን የተጋራቻትን ግጥም ቀዳዳችሁ አንብቡት፤ ደጋግማችሁ፡-
“ሐዘንሽ ቅጥ
አጣ
ከቤትሽ አልወጣ፣
የገደለው ባልሽ፣
የሞተው ወንድምሽ”
እንዲል ባለቅኔው ዕጣ ክፍልሽ ሆኖ፣ ይዘሽ እንደ ሲቃ፣ እንባሽ ወደ ውስጥሽ፣ መፍሰስ መንቆርቆሩ ዛሬም አላበቃ፡፡
  ከልጅሽ ገዳይ ጋር፣ ድንኳን
ተጋርታችሁ ደረት እያደቃሽ፣
  ማን ያባብልሻል አንቺም
እሱም አልቃሽ፡፡
(ከሃያሲ ደረጀ በላይነህ ለህትመት የተዘጋጀ ረቂቅ መጽሐፍ የተወሰደ)

   (የዛሬ 3 ሳምንት ምን ተጽፎ ነበር?)

           ከሕወሓት አመራር መካከል የትግራይ ሕዝብ፣ ከገዛ አገሩና ከወገኑ መለየት አለበት የሚል እምነት የያዘ ቢኖር፣ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መጠየቅ ይችላል። ይህን ለማድረግ ጸብ አያስፈልግም፤ ጦርነት አያስፈልግም። ከሕግ ውጭ ሕዝቡን በውሸት ሰበካ ወደ ግጭት ለማስገባት መሞከር፣ በኢትዮጵያና በትግራይ ላይ የሚፈጸም ወንጀልና ክህደት ነው።
ዲፋክቶ (de facto) የሚባል እንደ ዋዛ፥ ቀስ በቀስ ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰብ አገረ መንግስትነት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ በፈረሰበት አገር ውስጥ ተኩኖ ሊታሰብ የሚችል መሆኑ ይታወቃል። የሕወሓት አመራር ስልጣን ከእጁ ከወጣ በኋላ "ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፥ መንግሥት አልባ ትሆናለች" የሚል ድምዳሜ ላይ ሳይደርስ አልቀረም። እግዚአብሔር ይመስገን፤ አልፈረሰችም፤ መንግሥት አልባም አልሆነችም። ዛሬም የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለ። ያለ ሕግ በዋዛ ዋዛ [በተጨባጭ ላለማለት] ወይም ዲፋክቶ (de facto) ሳይሆን በሕግ ወይም ዲጁሬ (de jure) የሚታወቅ መንግሥት ነው። የትግራይ ክልል፤ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፑብሊክ አባል መሆኑ በሕግ የታወቀ ነው። መንግሥትና ሕገ መንግሥት ባለበት አገር፤ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ሕጋዊ እውቅና ያለውን የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግሥት ወደ ዲፋክቶ መንግሥትነት ለመለወጥ አይቻልም። ስለሆነም በፌዴሬሽኑ ጥላ ሥር ሆኖ፣ ከሌሎች አገሮችና ድርጅቶች ጋር በተናጠል ለመገናኘትና ቀስ በቀስ፥ እያዋዙ ዕውቅና ለማግኘት መሞከር ወንጀል መሆኑ ታውቆ በሩ መዘጋት አለበት።
ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመለየት የሚፈልጉ የሕወሓት አመራር አባላት፣ ፍላጎታቸው ከሕዝቡ ጥቅም ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አሳምረው ያውቁታል። ዛሬ “ታግለን ነጻ ባወጣን፣ አሃዳዊው ኃይል ሊወጋን ነው” በማለት በፍርሃት የሸበቡት ሕዝብ፤ የግድ እንዲመርጣቸው ማድረግ ቢችሉም፥ ከኢትዮጵያ እንገንጠል ቢሉት እንደማይሰማቸው ያውቁታል። ሕዝቡ ይሰማናል የሚሉ ከሆነ፣ ሕጉን በተከተለ መልኩ፣ ሕዝቡ ምርጫውን እንዲገልጽ ዕድል መስጠት ይቻላል፤ ሳይቸኩሉ፤ ሳያዋክቡት።
የሕወሓት አመራር፤ ነጻ አገር የመመስረት ነሻጣውን ለማሳካት ቢፈልግ፣ ቅድሚያ በቀጣዩ ምርጫ ተወዳድሮ የክልሉን ምክር ቤት በቂ ወንበሮች መያዙን ያረጋግጥ። ከዚያ በኋላ ጥያቄውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቅርብ። የፌዴሬሽን ምከር ቤትም፣ በሦስት ዓመት ውስጥ ሪፈረንደም ያዘጋጅለታል። ከዚያ የሚሆነው ይሆናል።
መቼም ለቸኮለ ሰው ሦስት ዓመት ረዥም ጊዜ ነው። ታዲያ አገር መገንጠልን የሚያክል ትልቅ ነገር ፈልጎም ተቸኩሎም አይሆንም። ከዚያ ውጭ ሕዝቡን በሐሰት ወደ ግጭትና ደም መፋሰስ በማስገባት፣ በከንቱ ከሚፈሰው ደም፣ ለመገንጠል የሚሆን ምክንያት ለማግኘት መሻት፣ ደንታ ቢስነትና የለየለት ፀረ ሕዝብነት ነው።
የሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ ፍላጎቶች ተቃርኖ
የሕወሓት አመራር አባል የሆኑት አቶ አስመላሽ፤ ከላይ በጠቀስነው መስከረም አጋማሽ ላይ በተለቀቀው ቪዲዮ፤ የቀድሞ ኦህዴድና ብአዴን አመራር፣ በለውጡ ዋዜማ የፈጠሩትን “ኦሮማራ” ተብሎ ስለሚታወቀው “ጥምረት” ተጠይቀው የተናገሩት፣ ባንድ በኩል በፓርቲ መሪዎችና በሕዝቦች ጥቅም መካከል ያለውን ልዩነት፥ በሌላ በኩል፤ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት፣ ጥቅምና አንድነትን በሚመለከት ምንም ብዥታ እንደሌለባቸው የሚያረጋግጥ ነው ለማለት ይቻላል። ልጥቀስ፤
“ጥምረቱ፤ የኦሮሞና አማራን ሕዝብ ጥቅም የሚወክል አይደለም። ምክንያቱም የአማራና የኦሮሞ ህዝቦች ጥቅም፤ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ አይደለም። ጥቅማቸው አንድ ነው። ሕዝብና ሕዝብ የሚያጣላ ነገር የለም። ይሄ ጥምረት ግን ልሂቃን ተሰብስበው የፈጠሩት ጥምረት ነው። ጥምረቱ ለመሸዋወድ የተመሠረተ ነው።” ብለዋል።
የአቶ አስመላሽን ትንታኔ ወስደን፣ በሕወሓት አመራርና በትግራይ ሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት እንመለክት።
በመሠረቱ የትግራይ ሕዝብ ችግርም ሆነ ጥቅም ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ የማይለይ መሆኑ የታወቀ ቢሆንም፣ በአቶ አስመላሽ አንደበት፤ በዚህ ጊዜ መነገሩ ግን በሕወሓትና ኦሮማራ-ነበር-ብልጽግና አመራር መካከል ያለው ጸብና ፍጥጫ፣ የትግራይን ሕዝብ የማይወክል መሆኑን ብቻ ሳይሆን፣ ይህን አሳምረው በሚያውቁት በአቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የተያዘው ጠብ አጫሪ አቋም፣ በስሙ የሚምሉለትን የትግራይን ሕዝብ ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳናል።
ዘርዘር ለማድረግ ያክል ከአቶ አስመላሽ ትንታኔ የሚከተሉትን እንገነዘባለን፦
1) በሕወሓትና “የኦሮማራ ጥምረት” በመሰረቱት ልሂቃን መካከል የተፈጠረው ጸብ ወይም “መሸዋወድ” በልሂቃን መካከል የተፈጠረ መሆኑን፤ 2)“ኦሮማራ ጥምረት” አይወክላቸውም የሚሏቸው፣ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች ጥቅም፣ ከትግራይ ሕዝብ ጥቅም ጋር አንድ መሆኑን፤ 3) እንደ አማራውና ኦሮሞው ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ጥቅም፣ “ከሌሎች ኢትዮጵያውያን የተለየ” አለመሆኑን፤ 4) ሕወሓት ሸወዱኝ ከሚላቸው የቀድሞ ኦሮማራ፥ ያሁኑ ብልጽግና አመራር ጋር ያለው ጸብና ቁጭት፣ የትግራይን ሕዝብ የሚወክል አለመሆኑን በግልጽ እንደሚገነዘቡ፤ 5) የሕወሓት አመራር፣ የትግራይን ሕዝብ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት በመጥቀስ ያካሄዱት ሕገወጥ ምርጫም ሆነ በፌዴራል መንግሥት ላይ የሚሰነዝሩት ትንኮሳና በእብሪት የገቡበት አደገኛ ፍጥጫ፣ የትግራይን ሕዝብ እንደማይወክል ከማረጋገጡም ባሻገር አቶ አስመላሽና ጓዶቻቸው የሚያራምዱት ሕገወጥ አካሄድና ጠባጫሪነት፣ ከሕዝቡ ጥቅም ጋር የሚጋጭ፤ የአውቆ አጥፊ ሥራ መሆኑን ያስረዳል።
ሕወሓት፤ ከትግራይ ልጆች ጉዳት ሲያተርፍ የኖረ ድርጅት ስለመሆኑ፤
የሕወሓት አመራር፤ የክልሉ ሕዝብ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ እንደሚጠላ፥ እንደሚገለልና እንደሚፈናቀል፥ በሌሎች ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጥርጣሬ ዓይን እንደሚታይ በመግለጽ፥ መጣብህ፥ አለቀልህ እያሉ ራሱን ከገዛ ወገኖቹ ለይቶ እንዲመለከት ሲኮረኩሩት መኖራቸው ይታወቃል። ሆኖም የትግራይ ሰው፣ በሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ፣ በጥርጣሬ ዓይን መታየት የጀመረበት ጊዜና መነሻው ለብዙዎች ግልጽ ላይሆን ይችላል።
ጊዜው 1970 ዓ.ም ነበር። መነሻውም የሕወሓት አመራር ከልቡ አፍልቆ የተገበረው የተንኮል ሥራ ነበር።
እነሆ ማስረጃ። ከአቶ ገብሩ አስራት መጽሐፍ በረዥሙ ልጥቀስ፦
“...በ1970 ዓ.ም ደርግ ካካሄደው የማጋለጥና የመመንጠር ዘመቻ በኋላ ቁጥራቸው የማይናቅ የትግራይ ተወላጆች ደርግን ማገልገል ጀምረው ነበር። እነዚህም በሁሉም የአውራጃና የወረዳ ከተሞች ህዝቡን ያውኩ ስለነበር፣ ሕወሓት እነሱን ለማጥፋት አንድ ዘዴ ቀየሰ። የሐሳቡ አመንጪ እውቁ የከተማ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኛ ተክሉ ሐዋዝ ሲሆን ዕቅዱን ለማስፈጸም ሦስት ታጋዮች እንዲመደቡለት ጠየቀ። ሦስቱ ታጋዮች ከተማ ገብተው ህዝቡን የሚያውኩትን ግለሰቦች ደርግ ራሱ እንዲያጠፋቸው የተቀየሰውን የረቀቀ ዕቅድ እንዲያፈጽሙ ተልዕኮ ተሰጣቸው። ተክሉ አንድ ረዥም የሐሰት ደብዳቤ አዘጋጀ። ከተክሉ ሐዋዝ በወቅቱ የፖለቲካ ኃላፊ ለነበረው ዓባይ ፀሐዬ የተላከ የሚል ነው።  ‘ጥብቅ ምስጢር’ የሚል ተጽፎበት በሙጫና ስቴፕልስ ታሸገ። ደብዳቤው ውስጥ በኮድ የተጻፈ የብዙ ሰዎች የስም ዝርዝር ሰፍሯል። ከስም በተጨማሪ ማን ከማን ጋር በሕዋስ እንደተደራጀና የአመራር ኮሚቴ አባላቱ ማንነት በማመልከት ሐሰተኛውን ‘የከተማ መዋቅር’ ቁልጭ አድርጎ ያሳይ ነበር። ስሞቹ በኮድ፣ ኮዱ የደርግ ባለሙያዎች በቀላሉ እንዲፈቱት ተደርጎ የተዘጋጀ ነበር። በደብዳቤው ሕወሓትን ሲያውኩ የነበሩት አብዛኞቹ የደርግ ጋሻ ጃግሬዎች ስም ሰፍሮ የሕወሓት እጅግ ታማኝ አባላት እንደሆኑ ተጠቁሟል። እንዲያውም ከአንዳንዶቹ ስም ጎን ሆን ተብሎ አስተያየት ጭምር ታክሎበታል፤ ‘ይህ ሰው ቁልፍ ሚን የሚጫወትና ከበላዮቹ ጋር እየተገናኘ ጠቃሚ ምስጢር የሚያቀብለን ነው’ የሚለው ተሰምሮበት ነበር። በኮዱ መሠረት አ=12 ብ=16 ር=70 ሃ=20 በ=08 ላ=63 ቸ=74 ው=32 ሆኖ እንዲወከል ተደርጎ በደብዳቤው ’12 16 70 20 08 63 74 32 ጥሩ እየሠራ ነው’ የሚል ብቻ ተጽፏል። ኮድ ሰባሪ ባለሙያዎች ቁጥሩን በቀላሉ ሰብረው አብርሃ በላቸው ይሉና፣ ከሚቀጥለው ሃረግ ጋር በማዛመድ፣ ‘አብርሃ በላቸው ጥሩ እየሰራ ነው’ ብለው ያነቡታል። ሌሎቹንም እንዲሁ።
“ሦስቱ ታጋዮች ደብዳቤውን እንደያዙ አክሱም ለሚገኘው አስተዳደር እጃቸውን ሰጡ። ከተኽሉ ሐዋዝ ለዓባይ ፀሐዬ የተጻፈ ደብዳቤ ይዘው መምጣታቸውን ገለጹ። የአክሱም ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች ተክሉ ሐዋዝና አባይ ፀሐዬ በድርጅቱ ውስጥ ያላቸውን ሚና ያውቃሉ። ምስጢራዊ የተባለውን ደብዳቤ ይዘት በመገመት ባስቸኳይ መቀሌ ለነበሩት የበላያቸው አስታወቁ። የበላይ ኃላፊውም እጅግ ተደስቶ፣ ወዶ ገቦቹ ባስቸኳይ ወደ መቀሌ እንዲላኩ አዘዘ። ታጋዮቹ ከነደብዳቤው በሄሊኮፕተር መቀሌ ተላኩ። ደብዳቤው ተከፍቶ የኮድ ባለሙያዎች በቀላሉ ፈቱት። ደብዳቤው ሲነበብ በርካታ በታማኝነታቸው የታወቁ የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና አስተዳዳሪዎች፣ የሕወሓት አባላት መሆናቸው ተረጋገጠ። ለደርግ እጅግ ታማኝ የነበሩት እነ አብርሃ በላቸውና አፈወርቅ አለም ሰገድ ሳይቀሩ ስማቸው ዝርዝሩ ውስጥ ተገኘ። በሁኔታው እጅግ የተደናገጠው ደርግ፤ ወዲያውኑ ሁሉንም ለቃቅሞ አስሮ በግርፋት ፍዳቸው አሳያቸው።
“•••ከመቀሌ ማዕከላዊ ምርመራ ለደኅንነት ሚኒስትሩ ኮ/ል ተስፋዬ ወልደ ሥላሴ በተጻፈ ደብዳቤ፤ ‘ራሱን ህወሓት ብሎ የሚጠራው ጸረ አንድነት የወንበዴዎች ድርጅት በረሓ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ ሌላ፣ በከተማ በቂና ወቅታዊ መረጃ፥ የማቴርያልና ሞራል ድጋፍ ለማግኘት በየክፍላተ ሃገራት የወንበዴ ሕዋስ [ሴል] በመዘርጋት፣ የትግራይ ክፍለ ሃገር ተወላጆችን በአባልነት በማሰባሰብ ፀረ አንድነት ድርጊቱን በማካሄድ ላይ ይገኛል. . . የማዕከላዊ ምርመራ ቅርንጫፍ የሆነው የትግራይ ክፍለ ሃገር ማዕከላዊ ምርመራ ዋና ክፍልም፣  የአብዮቱ ወገኖች መስለው ስዉር ጸረ ሕዝብ ደባ በመፈጸም ላይ የሚገኙትን የውስጥ ቦርቧሪዎችን ለማጋለጥና የወንበዴውን ሴል ለመበጣጠስ በወሰደው እርምጃ፣ 209 የሕወሓት ወንበዴ አባላት በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራውን በሰፊው ቀጥሏል’ ይላል።
“ሕወሓት በዚህ ዘዴ ቀንደኛ የደርግ ካድሬዎችና ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ አደረገ። የኢሠፓአኮ ማ/ኮ አባልና የፖለቲካ ት/ት ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን የነበረው ታደሰ ገ/እግዚአብሔር ሳይቀር በቁጥጥር ሥር ውሎ መጨረሻ ላይ ከወኅኒ ቤት ተወስዶ በደርግ አፋኞች ተገደለ። የክፍለ ሃገሩ ተቀዳሚ ምክትል ሊ/መ የነበረው ኅሩይ አስገዶም፣ የሕወሓት የውስጥ አርበኛ ነው ተብሎ እጁን ለመያዝ ሲሞከር በተከፈተው ተኩስ ሞተ። ሕወሓት ውስጥ በደኅንነት ሥራ ተመድቦ ሲሠራ ቆይቶ እጁን ለደርግ ፣ በጸጥታ ሥራ ተመድቦ የነበረው አለማየሁ በቀለም እንዲሁ በሰርጎ ገብነት ተጠርጥሮ እጁን እንዲሰጥ ሲጠየቅ፣ እምቢ ብሎ በጥይት ተመትቶ ሞተ።
“በተደረገው የምንጠራ ዘመቻ ከአንድ ሺ በላይ የማኅበራት መሪዎች፥ የመንግሥት ሹመኞች የኢሠፓአኮ ካድሬዎችና ታጣቂ ሚሊሻዎች ታስረዋል። (“ሉዓላዊነትና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ”፥ ገጽ 127 እስከ 129]
ይህን ተግባር የሕወሓት አመራር ለትግሉ ሲል የወሰደው ብልህ እርምጃ ነው በማለት የሚያሞካሽ አይጠፋ ይሆናል። ያኔ የተነዛውና ጥርጣሬ ያጫረው መርዝ ግን ዛሬ ድረስ መዝለቁን መካድ አይቻልም።
ከላይ የተጠቀሰው በወቅቱ የነበሩትን የትግራይ ተወላጅ የደርግ አባላት ለጥቃት ያጋለጠ ሲሆን ከዚያ ባሻገር ደርግ በሕዝቡ ላይ የነበረውን እምነት ያስለወጠ ነው ለማለት ይቻላል። የደርግ ጥርጣሬና እርምጃዎችም ለሕዝቡ የስጋት ምንጭ እየሆነ፣ በሁለቱም ወገን አለመተማመን በመስፈኑ፣ ሕወሓት የዘራው ጥርጣሬ ደርግ በስተመጨረሻ ሲያራምደው ለነበረው በሕዝቡ ላይ ያነጣጠረ የሚመስል አቋም ሳይዳርገው አልቀረም። ሕወኃትም ያን የጥርጣሬ መርዝ ከረጨ በኋላ ደርግ የሚሰነዝረውን ጥቃት ሸሽቶ ለሚመጣው መጠጊያና አለኝታ ሆኖ በመቅረብ አትርፏል።
ሕወሓት በራሱ ላይ የተነጣጠረውን የደርግ መንግሥት ጥቃት፣ በሕዝቡ ላይ እንደመጣ የፀረ ሕዝብና ጨፍጫፊ መንግሥት ሥራ በማቅረብ፣ በሕዝቡና በድርጅቱ መካከል ልዩነት የሌለ አስመስሎ ሲያቀርብ ኖሯል። ዛሬም አያሌ የዋህ ተንታኝ፤#ሕወሓትና የትግራይ ሕዝብ አንድ ነው አይደለም; የሚል አሳዛኝ ጥያቄ ማንሳቱም ከዚያ ድሮ ከተዘራው ጥርጣሬ መቀዳቱ አይቀርም።
የሕወሓት አመራር መንግሥት ከሆነ በኋላም፣ የትግራይን ሕዝብ ማሸበሩን አልተወም። ችግር ባጋጠመው ጊዜ ሁሉ የትግራይን ሕዝብ ለጥቃት ሲያጋልጥ መኖሩ አልያም “ና ሙትልኝ” ሲል መኖሩ ይታወቃል።
ለምሳሌ በምርጫ 97 የቅንጅት ሰፊ ተቀባይነት አስደንግጦት፣ "ኢንተርሃምዌ መጣብህ" በማለት ሕዝቡን አሸብሮ ከጎኑ እንዲሰለፍ ማድረጉ ይታወቃል። ልክ በረሃ እያለ የውሸት ሰነድ አዘጋጅቶ ንጹሐን አገር ወዳድ የትግራይ ልጆችን እንዳስመታ ሁሉ፣ ዛሬም በመላው ኢትዮጵያ ያሉት የትግራይ ልጆች ቢመቱለት ደስታውን አይችለውም። የሕወሓት አመራር፤ የፌዴራል መንግሥትን ስልጣን ለቆ ከሄደ በኋላም የራሱን ሽሽትና ፍርሃት ወደ ሕዝቡ በማጋባት፥ በራሱ ላይ የሚሰነዘረውን ክስና ስድብ፣ በህዝቡ ላይ የተሰነዘረ በማስመሰል፥ ያልተባለውን ተባለ፥ ያልተደረገውን ተደረገ በማለት፥ ስብከቱን አልቀበል ያለውንም “ባንዳ” የሚል ስም ሰጥቶ ከሥራ በማፈናቀል፣ በትግራይ ተወላጁ ደምና መስዋዕትነት፣ የራሱን ሕይወት ለማቆየትና የክልል ስልጣኑን ዕድሜ ለማራዘም ይዳክራል። በመላው ኢትዮጵያ፣ ለአስርት ዓመታት ተጭኖ የነበረው የጭቆና ቀንበር ከነዝርፊያው፥ መሬት ወረራው፥ ከነጭንቀቱ ዛሬ ትግራይ ላይ ብቻ ተንሰራፍቶ ይገኛል።
 የሕወሓት አመራር፤ የዛሬ 30 እና 40 ዓመት በርካታ ታጋዮች ፈንጂ ረግጠው እንዲሞቱላቸው አድርገው ሲያበቁ፥ ያ ሁሉ መስዋዕትነት የተከፈለለትን የሟች ጓዶቻቸውን ፍትሕና እኩልነትን የማረጋገጥ አደራ በመብላታቸውም ሳያዝኑ፥ ጭራሽ አሁን ደግሞ የነዚያን ጀግኖች ልጆች፥ ብሎም የልጅ ልጆች በሐሰተኛ ሰበካ “ኑ ሙቱልን” በማለት ለጦርነት ይቀሰቅሳሉ። የሕወሓት አመራር ነገር ሁሌም #እናንተ ሙቱልኝ፤ እኔ ልሰንብት; ነው።
ዛሬ ደግሞ የያዙት ዕቅድ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወገኑ በምንም የማይለየውን የትግራይ ሰው፣ እንዲሁ በከንቱ ከገዛ ያገሩ ልጆች ጋር ደም ማቃባት ሳይሆን አይቀርም። ሆኖም ደም በማቃባት እንለየዋለን ካሉ፣ የተለየ ጥቅም ሳይኖረው ከገዛ ወገኑ ለመለያየት ካጩት፣ ጠላቶቹ እነሱና እነሱ ብቻ ናችው።
እስቲ ዛሬ እንኳን የኛ ለምትሉት ሕዝብ እዘኑለት!
የትግራይ ሕዝብ ወዶም፥ ተገዶም ለሕወሓት አመራር በትግል ጊዜ ስንቅ፥ ትጥቅና ወጣት አቅራቢ ሆኖላችሁ፥ ወደ ስልጣን ስትወጡ መወጣጫ መሰላል፥ ወንበራችሁ ሲነቃነቅ የግዱን ድጋፍ ሆኗችሁ ኖሯል። እነሆ ከስልጣን ስትወርዱ ደግሞ መደበቂያ ሆኗችኋል። እንደገና ጦርነት? አያሳዝናችሁም? ከዚያ በላይ ምን ይኁንላችሁ? ዛሬስ ሙትልን የምትሉት ለምን ዓላማ ነው? ለመገንጠል? ለምን? ምነው አሁን እንኳን ብትተዉት? ምነው ለኢትዮጵያውያን ከመጣው ነጻነትና ተስፋ ቢቋደስበት?
ዛሬ በኢትዮጵያ የሕዝቦችን እኩልነት ለማረጋገጥ ቆርጦ የተነሳ፥ ጠመንጃን ከፖለቲካ ቋንቋነት ውጭ ለማድረግ ግማሽ መንገድ ሳይሆን ሙሉውን መንገድ ተጉዞ፣ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ካሉበት ድረስ ሄዶ እጃቸውን ስሞ አገር ቤት ያስገባ፤ እናንተንም የይቅርታ እጁን ዘርግቶ በትዕግስት የሚጠብቅ መንግሥት
መኖሩን ታውቃላችሁ። ተጠቀሙበት። ካላመናችሁት በሽማግሌ ፊት በር ዘግታችሁ አስምሉት። ካልተጣላኸን ግን አትበሉት። የጠየቃችሁትን ሁሉ ሲሰጣችሁ የኖረውን፥ የኛ የምትሉትን ሕዝብ ታይቶ በማይታወቅ ትእግስት ከሚጠብቃችሁ የኢትዮጵያ መንግሥትና ከገዛ ወገኑ ጋር ደም አታቃቡት። ፍጥጫውን አርግቡት። ዛሬ ከናንተ የሚጠበቅ የጀግንነት ሥራም ይኸው መሆኑን እወቁት።


  ባል ሆዬ፤ ሪፐብሊካን ነው፡፡ (ኢህአዴግ ነው እንደሚባለው) የለየለት የትራምፕ ደጋፊ ነበር፡፡ ሚስት ደግሞ የትራምፕ ቀንደኛ ጠላት ናት፡፡ ትራምፕ ጎጆአቸውን በፖለቲካ ልዩነት ቢያምሰውም፤ ጥንዶቹ በአንድነት በሚያስተሳስራቸው  ተልዕኮ ላይ ተሰማርተዋል፡፡
ጆን ላውራ ሃንተር ለዓመታት የውሃ ጣቢያዎች በማቋቋም፣ በአሜሪካ-ሜክሲኮ ድንበር፣ በህገ ወጥ መንገድ አቋርጠው የሚሻገሩ ስደተኞችን ከሞት ሲታደጉ ነው የኖሩት፤ በካሊፎርኒያ፣ የአንዙ በሬጐ  በረሃ ላይ ከሚከሰተው አደገኛ ሙቀት፡፡
 የ65 ዓመቱ አዛውንት ጆን፤ የዛሬ 21 ዓመት አትራፊ ያልሆነውን የውሃ ጣቢያ ቡድን የመሠረቱት፣   ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች፣በውህ እጦት በሚከሰት ድርቀትና በከፋ ሙቀት አቅላቸውን እየሣቱ መሞታቸው ተከትሎ ነው፡፡  
“እኔ እዚህ ነው የተወለድኩት። ታላቅ ነፃነትና ብዙ እድሎች ባሉበት አገር በመወለዴ ዕድለኛ ነኝ; የሚሉት የህክምና ባለሙያው፤ “ከደቡብ የሚመጡ ሰዎች የሚከተሉት የመንግስት ስርዓት፤የተለየ በመሆኑ የኛ ዓይነት እድሎች አይኖሯቸውም፡፡ በዚህ የተነሳ እኔም እንደ እነሱ ብሆን፤ ወደ ሰሜን መምጣቴ አይቀርም ነበር” ብለዋል።
በሜክሲኮ የተወለደችው ባለቤታቸው ላወራ፤ የውሃ ጣቢያውን በበጎ ፍቃደኝነት የተቀላቀለች ሲሆን ከዓመታት በኋላም ከጆን ጋር በትዳር ቀለበት ተሳስረዋል።
“ሳገባት ዲሞክራት መሆኗን አልነገረችኝም ነበር። በድጋሚ ተታልያለሁ” ሲሉ ጆን ቀልደዋል፤ “ያኔ ስለ ፖለቲካ አናወራም ነበር፤ እዚህ እየመጣን ውሃ ብቻ ነበር የምንቀዳው”  
ከመቼውም የበለጠ ትዳራቸው የተፈተነው ዶናልድ ትራምፕ በ2016 የአሜሪካ ምርጫ፤ ህገ ወጥ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እርምጃ እንደሚወስድ ቀስቅሶ ካሸነፈ ወዲህ ነው። ይሄ በመካከላችን ጥቂት ቅራኔ ፈጥሮ ነበር፤ምክንያቱም ትራምፕን ስጠላው ለጉድ ነው፤ የሚሉት የ73 ዓመቷ ላውራ፤ሰዎችን የሚያወርድበት መንገድ ያስጠላኛል፤በተለይም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ  ድሆችን ” ይላሉ፡፡
 በ2016 ምርጫ ጆን፤ ለትራምፕ ድምጽ አልሰጡም ነበር፤ለምን ቢሉ? ባለቤታቸውን አክብረው፤ለትዳራቸው ቅድምያ ሰጥተው፡፡ የቀድሞ የሪያሊቲ ቲቪ ኮከብ፤ የተለመደው ዓይነት ፖለቲከኛ አለመሆናቸውን ግን አስደስቷቸው እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
“ራሱን የሆነ ሰው ማግኘት አነቃቂ ነው፤ ምንም እንኳን እንደልቡ ቢናገርም” ብለዋል ጆን፡፡
የውሃ ጣቢያዎቹ የሚደግፉት ፖለቲካውን ወደ ጎን በመተው፣ የነፍሳቸውን ጥሪ በሚከተሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ በጎ ፍቃደኞችና ለጋሾች ነው ተብሏል።
“ሁሉም ሰው የራሱ ሃሳብ የማንጸባረቅ መብት አለው” ይላሉ፤ላውራ። “ሁላችንም ግን አንድ ዓላማ፣ አንድ ግብ ነው ያለን፤ ይኸውም በዚህ አካባቢ ከከፋ ሙቀት ጋር የተያያዙ ሞቶችን ቁጥር ለመቀነስ መትጋት ነው፡፡” የሚቀድመውም እሱ ነው፡፡


Page 4 of 504