Administrator

Administrator

  በመላው አለም የሚገኙ መንግስታት፣ ኩባንያዎችና ግለሰቦች ባለፈው የፈረንጆች አመት 24 ትሪሊዮን ዶላር መበደራቸውንና አለማቀፉ አጠቃላይ ብድር በአመቱ መጨረሻ 281 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱን ብሉምበርግ ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
ኢንስቲቲዩት ኦፍ ኢንተርናሽናል ፋይናንስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ 281 ትሪሊዮን ዶላር የደረሰው አለማቀፉ አጠቃላይ ብድር፣ በታሪክ ከፍተኛው ሲሆን ገንዘቡ ከአለማቀፉ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ከ355 በመቶ በላይ እንደሚሆንም ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከፍተኛ የበጀት ጉድለት የገጠማቸው የአለማችን አገራት፣ በአዲሱ የፈረንጆች አመት 2021፣ ተጨማሪ 10 ትሪሊዮን ዶላር ያህል ይበደራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ሰሜን ኮርያ 9 የኮሮና ክትባቶችን መረጃ ለመዝረፍ መሞከሯ ተነገረ


          የአሜሪካ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ፣ በተለያዩ የአለማችን ባንኮችና የንግድ ኩባንያዎች ላይ ላይ የኢንተርኔት ጥቃት በመፈጸም በድምሩ ከ1.3 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለማጭበርበር የሞከሩ #የ21ኛው ክፍለ ዘመን ስመጥር የባንክ ዘራፊዎች; ናቸው ባላቸው ሦስት ሰሜን ኮርያውያን ላይ ክስ መመስረቱን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የሰሜን ኮርያ መንግስት የደህንነት መስሪያ ቤት ባልደረቦች እንደሆኑ የተነገረላቸው ጆን ቻንግ ሆክ፣ ኪም ኢል እና ፓርክ ጂን ሆክ የተባሉት ሶስት ሰሜን ኮርያውያን፣ በተለያዩ ጊዜያት፣ የኤቲኤም ማሽኖችን በቫይረስ በመበከል እንደፈለጉ እንዲከፍሉ ማድረግን ጨምሮ በተለያዩ ባንኮች ላይ የሳይበር ጥቃት ወንጀሎችን በመፈጸም፣ 1.2 ቢሊዮን ዶላር ያህል ለማጭበርበር መሞከራቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡
የክፍለ ዘመኑ ቀንደኛ የባንክ ዘራፊዎች የተባሉት ሰሜን ኮርያውያኑ፣ ጠመንጃ ሳያነግቡ በኮምፒውተር ኪቦርድ ብቻ በመጠቀም ከፍተኛ የዝርፊያ ወንጀል ሲፈጽሙ መቆየታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ግለሰቦቹና ግብረአበሮቻቸው ከ2015 እስከ 2019 በነበሩት አመታት በቬትናም፣ ባንግላዴሽ፣ ታይዋን፣ ሜክሲኮ፣ ማልታና ሌሎች አገራት ባንኮች ላይ የማጭበርበር ድርጊት መፈጸማቸውንና በባንግላዴሽ ባንክ በፈጸሙት ጥቃት ብቻ 81 ሚሊዮን ዶላር ማጭበርበር መቻላቸውን አስታውሷል፡፡
በፈረንጆች አመት 2017 በተፈጸመውና “ዋናክራይ” በሚሰኘው ግዙፍ የኢንተርኔት ጥቃት ተሳታፊ ነበሩ ከተባሉትና በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኮርያ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀሩም ከተባሉት ተከሳሾች አንዱ የሆነው ፓርክ፣ በ2014 በሶኒ ፒክቸርስ ኩባንያ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ተሳታፊ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ተከስሶ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ፣ ሰሜን ኮርያ የአሜሪካ መድሃኒት አምራች ተቋም ከሆነው ፋይዘር፣ የኮሮና ክትባት መረጃዎችን በኢንተርኔት ጥቃት ዘርፋ ለመውሰድ መሞከሯን፣ የደቡብ ኮሪያ ደህንነት ኤጀንሲ ባወጣው መረጃ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡
ኮሮና ቫይረስ ወደ ግዛቴ አልገባም በማለት ደጋግሞ ሲናገር የከረመው የሰሜን ኮርያ መንግስት ያሰማራቸው የኢንተርኔት መንታፊዎች፤ ከፋይዘር በተጨማሪ ኖቫክስ እና አስትራዚኔካን ጨምሮ ቢያንስ በዘጠኝ የኮሮና ክትባት አምራች ኩባንያዎች ላይ የመረጃ ዘረፋ ሙከራ ማድረጉንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
           የሚከተለው ትርክት የአረቦች ተረት ነው።
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ንጉስ፣ ሶስት በእስር ላይ ያሉ ፈላስፎቻቸውን አስጠርተው፤  “መልካም ሃሳብ ያለው ፈላስፋ ሽልማቱ መፈታት ነው፤ እስኪ ተአምር ነው የምትሉትን ሃሳብ ንገሩኝ፤ ታላቅ ተዓምር የነገረኝን ሰው እሸልመዋለሁ” አሉ።
አንደኛው ፈላስፋ፡- “ይሄን ፈረስዎን ሌጣውን እጋልበዋለሁ” አለ።  
ሁለተኛው ፈላስፋ፡- “ይሄን ፈረስዎን ሳር እያበላሁ እያማለልኩ፣ እየጋለብኩ፣ ከየትኛውም ፈረስ ቀዳሚ አደርገዋለሁ” አለ።
ሶስተኛው ግን፡- “እኔ ደግሞ ቋንቋ አስተምረዋለሁ” አለ።
ሁለቱ እስረኞች በመገረም፤ “አብደሃል እንዴ? እንዴት አድርገህ ነው ፈረሱን ቋንቋ አስተምረዋለሁ ብለህ ለማለት የደፈርከው?” ሲሉ ይጠይቁታል፡፡  
ሶስተኛው ሰውዬ፡- “ሶስት መንገዶችን አስቤ ነው። አንደኛ ወይ ፈረሱ አማርኛ አይገባውም ብዬ እከራከራለሁ፤ ሁለተኛ ወይ አማርኛ ገብቶት አንድ ቀን ይናገራል፤ በመጨረሻም  ወይ ንጉሱ ይሞታሉ። በመካከል እኔ ለራሴ ጊዜ እገዛለሁ አለ” ይባላል።
*   *   *
ጊዜ መግዛትን የመሰለ ነገር የለም። ማምሻም እድሜ ነውና። ዋናው ነገር ደግሞ ያንን ዕድሜ ምን እንሰራበታለን የሚለው ነው። የሚባክነው እድሜ ከበዛ በሕይወታችን ላይ መሳለቅ ነው። የዛሬውን ህይወት ማባከን አይደለም፣ ከነገ ላይም መስረቅ ነው የሚጠበቅብን። (Plagiarize the future እንዲሉ) ለእድገት አንዱ መሰረቱ ለነገ መሰረት መጣል ነው። ከመነሻው ያላማረ አብዛኛውን ጊዜ መድረሻው ያማረ አይሆንም። የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል እንዲሉ አይነት ነው። (The end justifies the means) የሚባለውን አይዘነጉም።
የሀገራችን ፖለቲካ ቶሎ ተናኝ (Volatile) ነው፤ በቶሎ ይግላል፤ በአንድ አፍታ ይቀዘቅዛል። ፖለቲከኞቻችንም እንደዚያው ተናኝ ናቸው። በሰላሙ ጊዜ አይዘጋጁም። ሁኔታዎች ከተወሳሰቡ በኋላ መደነጋገር ስራቸው ነው። ይህ ደግሞ ዳፍንተኝነትን ያስከትላል።
የሀገራችን ኢኮኖሚ ለያዥ ለገራዥ ማስቸገሩ ፀሀይ የሞቀው ሀቅ ነው። መላ እመታበታለሁ፣ ዘዴ እዘይድበታለሁ ያለ ምሁር ነጋዴው፣ አዋቂው፣ አላዋቂው፣ ብልጡም የዋሁም እኩል ይደነጋገራል።
ስለዚህም የወል ማሀይምነት ጽናትም ያስፈልገዋል። ጽናቱ ለእቅድ፣ ጽናቱ ለዘላቂነት ይበጃል። ወጣም ወረደም ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንኡ የሚለውን በኃይለ ስላሴ ጊዜ ይሰጥ በነበረው ዲግሪ ላይ እንደ መፈክራዊ ምክር የሚቀመጠው ሃምሳ ዓለቃዊ አነጋገር፣ ለዛሬም አግባብነት ያለው መሆኑን እንረዳ። “ሁሉንም ሞክሩ፤ የተሻለውን አጽኑ” የምንለው ዛሬም፣ እንደሚሠራ ስለምንረዳ ነው!  


Monday, 15 February 2021 17:39

ADDIS Admass


           ቻይና በአለማችን በግዙፍነቱ ወደር አይገኝለትም የተባለውን እጅግ ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በቲቤት ግዛት ከሂማሊያ ተራሮች ግርጌ በሚገኘው የርሉንግ ሳንፖ ወንዝ ላይ ልትገነባ ማቀዷን አልጀዚራ አስነብቧል፡፡
60 ጊጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የተነገረለት ይህ ግዙፍ ግድብ፣ በአለማችን ትልቁ ግድብ የሆነውና ስሪ ጎርጅስ የተሰኘው የቻይና ታዋቂ ግድብ ከሚያመነጨው ሃይል በሶስት እጥፍ የሚበልጥ ሃይል እንደሚያመነጭም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ቻይና እ.ኤ.አ እስከ 2060 ከካርቦን ነጻ ኢኮኖሚ ለመገንባት የያዘችው ዕቅድ አካል እንደሆነ ከተነገረለት ከዚህ ግዙፍ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ከ14 ሺህ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው ይፈናቀላሉ መባሉንና ይህም ከቲቤታውያን ዘንድ ተቃውሞ እንደገጠመው ዘገባው ገልጧል፡፡


   ከኮሮና ቫይረስ ስርጭት ጋር በተያያዘ ሽያጩ በከፍተኛ ሁኔታ የቀነሰበት የአለማችን 2ኛው ግዙፍ የቢራ አምራች ኩባንያ ሄኒከን ወጪውን ለመቀነስ ሲል በተለያዩ የአለም አገራት ውስጥ ከሚገኙ ሰራተኞቹ 10 በመቶ ያህሉን ወይም 8 ሺ የሚደርሱ ሰራተኞቹን ከስራ ሊያሰናብት ማቀዱን አስታውቋል፡፡ በፈረንጆች አመት 2019፣ 2.2 ቢሊዮን ፓውንድ ትርፍ ያስመዘገበው  ሄኒከን፣ በ2020 ግን ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ አጠቃላይ ሽያጩ በ17 በመቶ በመቀነስ ትርፉ ከአምናው በ204 ሚሊዮን ፓውንድ መቀነሱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ኩባንያው ሰራተኞቹን መቀነስን ጨምሮ የተለያዩ የወጪ ቀነሳ እርምጃዎችን በመውሰድ በ3 አመታት ጊዜ ውስጥ 2 ቢሊዮን ፓውንድ ለማዳን ማቀዱን አመልክቷል፡፡

  በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በሲጋራ ሳቢያ ለሞት ይዳረጋሉ

            በአለም ዙሪያ የሚገኙ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር ከ1.8 ቢሊዮን ማለፉንና በየአመቱ ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በማጨስ ሳቢያ ለሞት እንደሚዳረጉ አናዶሉ ኤጀንሲና ታዋቂው የሳይንስ መጽሔት ባወጡት ዘገባ ገልጸዋል፡፡ የአለም የጤና ድርጅት ያወጣውን መረጃ ጠቅሶ አናዶሉ ኤጀንሲ እንደዘገበው፣ በአለማችን ከሚገኙት 1.8 ቢሊዮን ያህል አጫሾች መካከል ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ባላደጉ ወይም በማደግ ላይ ባሉ ድሃ አገራት ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ሲሆኑ፣ አብዛኞቹ ከማጨስ ጋር የተያያዙ የሞት አደጋዎችም አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የሚከሰቱ ናቸው፡፡
እድሜቸው ከ15 አመት በላይ ከሆናቸው የአለማችን ወጣቶች መካከል 21.9 በመቶው አዘውትረው የሚያጨሱ መሆናቸውንና ከአጫሾች ዙሪያ በመገኘታቸው ለሞት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥርም 1.2 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ በመላው አለም ከሚገኙት ህጻናት መካከል 40 በመቶ ያህሉ ከአጫሾች አጠገብ በመሆናቸው ብቻ ለጤና ችግር እንደሚጋለጡና፣ በየአመቱ ለሞት ከሚዳረጉት ህጻናት መካከል 28 በመቶ የሚሆኑት ከአጫሾች አጠገብ በመሆናቸው ለሞት የሚዳረጉ ስለመሆናቸውም አክሎ ገልጧል፡፡
47.4 በመቶ የሚሆኑ ዜጎቿ ሲጋራ የሚያጨሱባት ኪሪባቲ ከአለማችን አገራት ከህዝብ ብዛቷ አንጻር ብዙ አጫሾች የሚገኙባት ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ዘገባው፣ በሞንቴኔግሮ 46 በመቶ፣ በግሪክ 43.7 በመቶ ዜጎች እንደሚያጨሱም አክሎ ገልጧል፡፡
ላሰንት መጽሄት በበኩሉ፤ አገራት የአጫሾችን ቁጥር ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስዱም ከአለማችን አገራት መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ምንም አይነት ለውጥ ለማስመዝገብ አለመቻላቸውን ዘግቧል፡፡
ትንባሆ በውስጡ 7 ሺህ ያህል ጎጂ ንጥረ ነገሮች እንዳሉትና 250 ያህሉ ሰውነትን ክፉኛ የሚመርዙ፣ 50 የሚሆኑት ደግሞ ለካንሰር የሚያጋልጡ መሆናቸውንም ዘገባው ሃኪሞችን ዋቢ በማድረግ ባወጣው መረጃ አስታውቋል፡፡

      የአሜሪካ የበሽታ መከላከልና ቁጥጥር ማዕከል አንድ ማስክ ከማድረግ ይልቅ 2 ማስኮችን ደራርቦ መጠቀም የኮሮና ቫይረስን በመከላከል ረገድ በእጥፍ ውጤታማ እንደሆነ በምርምር ማረጋገጡን ይፋ እንዳደረገ አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ማዕከሉ በላቦራቶሪ ባደረገው ምርምር አንድ ከጨርቅ የተሰራ ወይም ሰርጂካል ማስክ ብቻ በማድረግ 40 በመቶ ያህሉን ቫይረስ መከላከል ሲቻል፣ ሁለቱንም አይነት ማስኮች ደራርቦ ማድረግ ደግሞ 80 በመቶ ያህሉን ቫይረስ ለመከላከል እንደሚያስችል የሚያሳይ ውጤት ማግኘቱን ባለፈው ረቡዕ ባወጣው መግለጫ ማስታወቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ሁለት ሰዎች በቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ሁለቱም ማስኮችን ደራርበው ሲያደርጉ 95 በመቶ ያህሉን ቫይረስ መከላከል እንደሚችሉ በጥናቱ ማረጋገጡን የጠቆመው ማዕከሉ፤ ያም ሆኖ የማስክ እጥረት ስለሚያስከትል ከተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች በስተቀር ሁሉም ሰዎች ማስኮችን ደራርበው ማድረግ እንደማይጠበቅባቸውም ምክሩን ለግሷል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፤ በኮሮና ቫይረስ መነሻ ዙሪያ ምርመራ ለማድረግ በቻይና የነበረውን ቆይታ ያጠናቀቀው የአለም የጤና ድርጅት የባለሙያዎች ቡድን፣ ቫይረሱ በቻይና ከሚገኝ ላቦራቶሪ አምልጦ በመውጣት ወደ ሰዎች ተሰራጭቷል የሚለውን ጥርጣሬ አጣጥሎታል፡፡
ቫይረሱ በተገኘባት የቻይናዋ ውሃን ግዛት ምርመራውን ያደረገው ቡድኑ ባለፈው ማክሰኞ በሰጠው መግለጫ እንዳለው፣ ቫይረሱ ከላቦራቶሪ የወጣ ነው የሚለው ጥርጣሬ መሰረተ ቢስ እንደሆነ የሚያመለክቱ መረጃዎችን ለማግኘት ተችሏል፤ ያም ሆኖ ግን ሌሎች ሶስት መላ ምቶችን ግን አሁንም ድረስ ትክክለኛ መሆናቸውን ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡
የቫይረሱን መነሻ በተመለከተ አራት መላምቶች ሲሰጡ መቆየታቸውን የዘገበው ሮይተርስ፤ እነሱም ከእንስሳት በቀጥታ ወደ ሰዎች የተላለፈ ነው፤ ከእንስሳት በሌላ አስተላላፊዎች አማካይነት ወደ ሰዎች የተሰራጨ ነው፤ ከሌላ አካባቢ ወደ ቻይና የገባ ነው እንዲሁም ከላቦራቶሪ አምልጦ የወጣ ነው የሚሉ መሆናቸውን አስታውሷል፡፡
ቫይረሱ ወደ ሰዎች የተሰራጨው ከእንስሳት መሆኑን የጠቆሙት የቡድኑ መሪ ፒተር ቤን ኢምበረክ፤ያም ሆኖ ግን ትክክለኛውን የቫይረሱን መነሻ ለማወቅ በቀጣይ ተጨማሪ ጥናትና ምርመራዎች መደረግ እንዳለባቸውም ተናግረዋል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ በጋና ፓርላማ የህዝብ ተወካዮችንና ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ168 በላይ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው መረጋገጡን ተከትሎ ፓርላማው ለሶስት ሳምንታት ያህል እንዲዘጋ መወሰኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በቫይረሱ ከተጠቁት መካከል 17 ያህሉ የፓርላማ አባላት ሲሆኑ 151 የሚሆኑት ደግሞ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች መሆናቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ፓርላማው ባለፈው ማክሰኞ እንዲዘጋ መወሰኑንና የጽዳት ስራዎች ሊሰሩ መታቀዱንም አክሎ ገልጧል።
ከወደ ፈረንሳይ በተሰማው ሌላ በጎ ዜና ደግሞ፣ በአሁኑ ወቅት በአለማችን የረጅም እድሜ ባለጸጋ እንደሆኑ የተነገረላቸውና በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት የ117 አመቷ መነኩሲት ሉሲሊ ራንደን ከበሽታው ማገገም መቻላቸው ተነግሯል፡፡
በእድሜ ከአለም ሁለተኛ ከአውሮፓ አንደኛ የሆኑትና በጥር ወር አጋማሽ ላይ በቫይረሱ መጠቃታቸው የተነገረው አይነስውሯ ሉሲሊ ራንደን በአሁኑ ወቅት ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ማገገማቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ መነኩሴቷ በሚኖሩበትና በደቡብ ፈረንሳይ በሚገኘው የአረጋውያን መጦሪያ ማዕከል ውስጥ ልደታቸውን ለማክበር እየተዘጋጁ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡

 ከእለታት አንድ ቀን የዱር አራዊት ተሰብስበው ድግስ ለመደገስ ያስቡና የድግሱን እቃ ግዥ የሚያሳኩ እጩዎችን ለመምረጥ ይወያያሉ። በመጀመሪያ በአያ አንበሶ ጥያቄ ሰጎን ስሟ ተጠቀሰ። እመት ጦጢት ሃሳብ ሰጠች፡-
“ሰጎን ለሩጫና ለሽቅድምድም ትመቻለች፤ ነገር ግን የእቃ ግዥነት ልምድ የላትም፤ ስለዚህ ሌላ ተመራጭ እንጠቁም” አለች።
ቀጥሎ ዝሆን ሀሳብ  ሰጠ፡-
“እንደ እኔ እንደ እኔ ጦጢት የምትሻል ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ገበያውን ስለምታውቅ የተሻለ እቃ ግዥ ትሆነናለች”
ቀጥሎ ዝንጀሮ ተነሳና:-
“ጦጢት ብልጥ ናት እንጂ የምግብ ዓይነት ምርጫዋ ውስን ነው፤ ስለዚህ ነብርን ብንልከው ያዋጣናል”
አያ ጅቦ ቀጥሎ ሃሳቡን ገለጠ:-
“አያ ነብሮ ጥሩ ምርጫ አይመስለኝም፤ እሱ ስጋ በል ስለሆነ ስጋ ያሳሳዋል። ስለዚህ ስጋ በሎቹንና ቅጠል በሎቹን ያምታታቸዋል። በእኔ እምነት ዔሊ ሄዳ ገዝታ ብትመጣ ያዋጣናል እላለሁ”
በአያ ጅቦ ሃሳብ አብዛኛዎቹ እንስሳት ተስማሙና ዔሊ ወደ ገበያ ተላከች። ጥቂት ሰዓታት እንዳለፈ አውሬዎቹ ማጉረምረም ጀመሩ። ረሃቡ ጠንቶባቸዋል።
“ድሮም ዔሊን መላካችንና ይቺን ቀርፋፋ መልዕክተኛ ማድረጋችን ትልቅ ስህተት ነው። ገና እየተንቀረፈፈች ደርሳ እስክትመለስ ድረስ ሁሉም በርሃብ ሊሞት ይችላል; አሉ።
ለካ ዔሊ ገና አልተንቀሳቀሰችም ኖሯል። አንገቷን በበሩ ብቅ አድርጋ፡-
“እንደዚህ የማታምኑኝ ከሆነ እንደውም ከነጭራሹ አልሄድም” አለች፡፡
*   *   *
የሀገራችን የሰው ሃይል ምጣኔና ምርታማነት መለኪያ ከሆኑት መስፈርቶች አንዱ ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ ማስቀመጥ  ነው። (The right man at the right place) የሚባለው ነው። የተማረ የሰው ሃይልን በወጉ አለመጠቀም ትልቅ በደል ነው። በአንጻሩም የተማረው የኢትዮጵያ ህብረተሰብ እውን በአግባቡ ተምሯል ወይ ብሎ መጠየቅም ያባት ነው።
የተማረው ክፍል አገሬን እወዳለሁ እንዲልና ምን ጎድሎባታል? ምንስ ሞልቶላታል? እኔ ምን አስተዋጽኦ ላድርግ? ብሎ እንዲጠይቅ ማድረግ ተገቢ ነው። የቀድሞው ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፡- “ሀገሬ ምን ታደርግልኛለች ከምትል እኔ ለሀገሬ ምን ላድርግላት በል” ብለው ነበር። የህዝቡን የትምህርት ስርዓቱን መመርመር፣ ከተቻለም በየጊዜው መፈተሽ ዋና ነገር ነው። ምንግዴነትን ማስወገድ ያሻል። አንድ የሀገራችን ገጣሚ እንዳለው፡-
“እኔ ምን አገባኝ የምትሉት ሐረግ
 እሱ ነው ያረዳት ሀገሬን እንደ በግ
ብዬ ግጥም ልጽፍ ተነሳሁኝና
ምናገባኝ ብዬ ቁጭ አልኩ እንደገና”
እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። አንድም የምርጫ ዘመን እየመጣ ነውና ትክክለኛውን ተመራጭ አንጥሮ በአግባቡ መምረጥ፣ ለሀገርና ለህዝብ ሁነኛ እርምጃ እንደሚሆን ከወዲሁ እንገንዘብ።
አይሰግሩም ተብሎ ፈረስና በቅሎ
አይሮጡም ተብሎ ፈረስና በቅሎ
እንደው በጥላቻ
ትመረጥ ይሆናል ዔሊ ለኮርቻ
የሚለውንም ሀገርኛ አባባል አለመዘንጋት ነው። ትክክለኛና አግባብነት ያለውን ምርጫ ማካሄድ አስፈላጊነቱን በተለይ ከዲሞክራሲ መጎልበት አንፃር ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ለዓመታት ስንናገር ቆይተናል። ሆኖም ነቢብ ወገቢር እንዲሉ፣ እስከዛሬም ለግብሩ አልበቃንም። ገና ብዙ መንገድ መጓዝ ይጠበቅብናል። ይህም በፈንታው ትክክለኛውን አቅጣጫ ማወቅንና መምረጥን ግድ ይለናል። ከሯጭ ፈረስ ይልቅ መንገድ የምታውቅ አይጥ ትሻላለች የምንለው ለዚህ ነው።

“ተቃዋሚዎቹን በትግራይ ጉዳይ ማን ፈቃጅና ከልካይ አደረጋቸው?!”
“የትግራይ ህዝብ ህውኃት በፈጠረው ችግር መከራ ላይ መውደቅ የለበትም”
መንግስት በአገሪቱ የተከሰተውን ችግር ለመቅረፍ ህግ የማስከበር ስራ በሚሰራበት ወቅት በተለይም በትግራይና በመተከል በርካታ ዜጎች ለማህበራዊ ቀውስና ለችግር ተጋልጠዋል። የአስቸኳይ ጊዜ ምግብና ቁሳቁስ የሚያስፈልጋቸውም በርካቶች ናቸው። በዚህ ምክንያት እንደለመደው አርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ በሰብሳቢነት የሚመራቸው ማህበራትና በጎ ፈቃደኞች ማለትም ግሎባል አሊያንስ፣ ሰብአዊ ድጋፍ ጥምረት፣ የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኛና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ማህበር፣ ኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር፣ የትግራይና የመተከል እርዳታ አሰባሳቢ በጎ ፈቃደኞች በጋራ ከማክሰኞ ከሰዓት በኋላ ጀምሮ እርዳታ ማሰባሰብ ጀምረዋል። የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ በእርዳታ አሰባሰቡ ጀምሮ፣ እርዳታ ማሰባሰቡን ተከትሎ ስለገጠመው ተቃውሞ፣ በአገሩ ስለላው ተስፋና ተያያዥ ጉዳዮች ከአርቲስትና የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ታማኝ በየነ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች እነሆ።
የእርዳታ አሰባሰብ ጅማሮው ምን ይመስላል…አበረታች ነው?
አጀማመሩ ጥሩ ነው ግን፣ እኛ የምናስበው ምንድን ነው። የዚህ እርዳታ ዋና ዓላማ አራት አምስት ድንኳን ሙሉ እህል መሰብሰብ ወይም የተከፈተውን አካውንት የሚያጨናንቅ ገንዘብ ሳይሆን እያንዳንዱ ዜጋ በዚህ ጉዳይ ሃላፊነት አለብኝ፤ የኔ ጉዳይ ነው እንዲል የማድረግ ስራ ነው የምንሰራው። ምክንያቱም እኛ እርዳታ አሰባሳቢ፤ የተወሰነ የተመቸው ሰው ብቻ እርዳታ የሚሰጥበት ፕሮግራም አይደለም። ፕሮግራሙ "ትግራይም መተከልም ውስጥ በከፍተኛ ችግር ውስጥ የወደቁ ወገኖችህ አሉና ምን አድርገሃል ስትባል ምንድን ነው የምትመልሰው?" ወይስ አሁንም የካናዳና አሜሪካ መንግስት አለያም የካናዳ ስንዴና የአሜሪካ ዱቄት ነው የምትጠብቀው? አንተ እንደ ዜጋ ምንድን ነው ያደረግከው? የሚል መልዕክት ነው ማስተላለፍ የምንፈልገው። እና በዚህ ልክ ስንለካው ገና ነው። የምልሽ አገሪቱ ከመቶ ሚሊዮን በላይ ዜጋ ነው ያላት። ገጠር ያለውና አቅም የሌለው ይህን ማድረግ ባይችል እንኳን በቴሌቪዥንና በተለያየ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ዜና የሚከታተለው ህዝብ በበቂ ደረጃ ምላሽ ሰጥቷል ብዬ አላስብም።
በዚህ በኩል ሚዲያውም ሊተባበረን ይገባል ብዬ አስባለሁ። በመግለጫው ላይ  ለተገኙ ጋዜጠኞች "ጉዳዩ የራሳችን ነውና እንደ ራሳችሁ አድርጋችሁ ሌሎች እንዲሳተፉበት አድርጉ" ብለን ነግረናቸዋል። ነገር ግን ከአንድ ቀን የዘለለ ሽፋን የሰጠን የለም። በእኛ በኩል የምናስበውን ለማድረግ እየሞከርን ነው። ከተሳካልን ደስ ይለናል፤ ካልተሳካልንም የአቅማችንን አድርገናል ነው የምንለው።
ይህን እርዳታ ለመሰብሰብ ስትነሳ አክቲቪስቶች "አንተን ለትግራይ ህዝብ ምን አገባህ እኛ እንበቃለን" የሚል ተቃውሞ አስነስተውብሃል። አንተስ በዚህ ጉዳይ ምን ትላለህ?
አዎ እውነት ነው።  በደንብ በተጠናከረ መልክ "አንተ ምን አገባህና ለትግራይ ህዝብ እርዳታ ትሰበስባለህ" ብለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ የጀመሩ አሉ። ይህን ማለት እንደ መብት ይችላሉ። እንደ እውነት ግን ማነው እነሱንስ ፈቃጅ ከልካይ ያደረጋቸው!?
በሁለተኛ ደረጃ ይሄ የ30 ዓመት የህገ-መንግስት አስተሳሰብ ነው። በዚች ምድር ላይ የሚደርስ ችግር፤ የሁሉም ዜጎች ችግር ነው ብዬ ነው የማምነው። በ1966 እና 67 ዓ.ም በወሎና በትግራይ በተከሰተው ረሃብ ላይ ሁሉም ዜጋ የሚችለውን ነው ያደረገው። ማይጨው ሲዘመት ሁሉም ዜጋ ያለው ቋጥሮ ነው የዘመተው፣ ሶማሊያ ስትወርረን ሁሉም ዜጋ ነው  የተሳተፈው። አንተ ምን አገባህ ፣ ይሄ የሀረር ችግር ነው፣ ያኛው የኦጋዴን ችግር ነው ተብሏል? አልተባለም። በዚህ አይት አስተሳሰብ የታሰሩ፣ የዚህ ስርዓትና የዚህ ህገ-ምንግስት ጠባብ አእምሮ ባለቤቶች ናቸው ለመከልከልና ለመቃወም የሚሞክሩት።
እኔ እውነት ነው ያንን ክልል ያአስተዳድር የነበረውን ድርጅት ስቃወምና ሳጋልጥ ኖሬያለሁ። አላፍርበትም አምኜበት ነው ያደረግሁት። ህውሐት እና የትግራይ ህዝብም ፍፁም አይገናኙም። የህወሃት ቡድን ከትግራይ ህዝብ የበቀለ ቡድን መሆኑን አምናለሁ። ነገር ግን የትግራይ ህዝብ የጥፋት ተካፋይ ሊሆን አይገባውም። ህወሃት በፈጠረው ችግር መከራ ላይ መውደቅ የለበትም። እንደ ማንኛውም ዜጋ፣ የትግራይ ህዝብ ጉዳይ ያሳስበኛል፤ ያገባኛል ብዬ ነው የማደርገው። በዚህ ሂደት ከዚህ መስመር ጀምሮ እዚህ ክልል ይሄ አጭር እስከታጠረበት እንዳትመጣ እንዳታስብ የሚለው ለእኔ አይሰራም።
ወደ ትግራይ ብቅ ብለሃል እንዴ?
ገና ነኝ አልሄድኩም።
የመሄድ ሀሳብ አለህ?
እንዴ! አገሬ አይደል እንዴት አልሄድም። እርግጥ የመጣሁት በግል ጉዳይ ነው። ነገር ግን ያየሁት ነገር ስላሳሰበኝና ስላስጨነቀኝ አመጣጤን ፈረንጆች ቫኬሽን (ቤተሰብ ጥየቃ) ቢሉትም፣ ከዚህ አይበልጥም በሚል ነው የገበዘሁበት። እንደው የሆነች ትንሽ አስተዋፅኦ ማድረግ ብችልና ምናልባት አፉ የደረቀ አንድ ህጻን ልጅ ትንሽ ውሃ አግኝቶ ቢጠጣና ትንሽዬ አልሚ ምግብ አግኝቶ ቢበላ፣ ለኔ ትልቅ ቁም ነገር ነው በሚል ነው እንጂ የመጣሁት በግል ጉዳይ ነው። ወደፊት ግን ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደ ማንኛውም ዜጋ ሄጄ ማድረግ የሚገባኝን ማድረግ እፈልጋለሁ።
የእርዳታ አሰባሰብ ሂደቱ ለምን ያህል ጊዜ ይቆያል? በገንዘብ ደረጃስ ምን ያህል ገንዘብ ለማሰባሰብ ነው ያቀዳችሁት?
በቁሳቁስ ደረጃ ይሄው አሁንም እየተቀበልን ነው። አሁን የምታናግሪኝ ራሱ እዚሁ ጣይቱ ሆቴል ድንኳን ዘርግተን፣ ህዝቡ እየመጣ እየሰጠን እየተቀበልን ነው። መልዕክቱ በአግባቡ ደርሷል አልደረሰም አላውቅም። ምክንያቱም በምናስበው ደረጃ ብዙ ነው አልልም። አሁንም ግን በመኪናቸው ጭነው፣ በትከሻቸው ተሸክመው መኮሮኒና ፓስታ የመሳሰሉትን እያቀረቡልን ነው። በገንዘብ ደረጃ በውጭ አገር “ያን ያህል የአትርዱ” ዘመቻ እየተካሄደ፣ “እንዳትረዱ ለመሳሪያ መግዣ ነው” እየተባለ፣ “የታማኝ ቡድን ነው አትርዱ” እየተባለ እንኳን እግዚአብሔር ይመስገን በሁለት ቀን ውስጥ ወደ 117 ሺህ ዶላር ተሰብስቧል።  በአገር ቤት ባንክ ውስጥ ወደ 400 ሺህ ብር ገብቷል። ገና የሚቀጥል ነው፤ ገደብ የለውም። ገደቡ እንደነገርኩሽ ይሄን መልዕክት የሚያገኘው እያንዳንዱ ዜጋ ምን አድርገሃል? ምን እያደረግክ ነው ሲባል፤ ምላሽ የሚሰጥበት ተሳትፎ እንዲያደርህ ነው የምንፈልገው እንጂ የብሩ ማነስና መብዛት አይደለም ዋናው አላማ፡፡  የሚመጣው ቁሳቁስ መብዛት ማነስ አይደለም ጉዳዩ። ነገር ግን እንደ ዜጋ እነዚህ ዜጎች ተጎድተው ስታይ ምን አድርገሃል ሲባል ዜጋ ምላሽ እንዲሰጥ ነው እንጂ በጊዜ ገደብ፣ በገንዘብ መጠንና በቁሳቁስ ልክ የሚለካ አይደለም።
የቀደመውን እንተወውና በቅርብ ጊዜ እንኳን ካሰባሰብካቸው እርዳታዎች ብንነሳ፣ የቡራዩው ቀውስ፣ የጉጂ ተፈናቃች፣ የአማራ ተፈናቃዮች፣ የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ ቀውስ በሻሸመኔ ለተፈጠረው ቀውስ ያደረግከው በጥቂቱ ይጠቀሳሉ። አንተ ይህን ሁሉ ስታደርግ መቼም አንድ ቀን ይህቺ አገር ላይ ፍትህና ርትዕ መግሶ አያለሁ በሚል ተስፋ ይመስለኛል፡፡ ተሳስቼአለሁ?
(በግርምት እየሳቀ…) እንደው ለዚህ ጥያቄሽ እግዚአብሔር ይስጥሽ። በእውነቱ በጣም ልብ የሚያደማ ነገር ነው። ይሄ በየቀኑ የሚከሰተውና የሚታይው ችግር፣ ይህንን ድጋፍ ለማድረግ ስትነሺ እንቅፋቱ ብዙ ነው። በዚሁ ሁሉ እንቅፋት፣ የሰው ፊት እንደ እሳት የሚገርፍበት ለማኝ እየተባልኩ በምሰደብበት ደጋግሜ ለድጋፍ ልመና ስወጣ፤ በጣም ያምማል ግን  በዚህ ምድር ላይ እንደ ሰው ቆይቼ የምሄድበት ጊዜ ይደርሳል። ሌላው አገር ደግ አያለሁ። እና በጣም ይከፋኛል። እንዴት ይህቺ አገር በገዛ ልጆቿ እኛው እራሳችን እናውድማት እያልኩ እቆጫለሁ አስባለሁ። ብቻ አንድ ቀን ማንም ዜጋ እኩል ሆኖ፣ በሰላም ገብተን እንወጣለን የሚለው ምኞቴ ነው። ያ ጊዜ እስኪመጣ ችግር እያየን ዝም ስለማባል በሌላውም መስክ ይሄንን ማረጋጋጥ የሚፈጥር ነገር ለመስራት እንደማንኛውም ዜጋ ያቅሜን አደርጋለሁ። በሌላ አቅጣጫ ማለቴ ነው፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የተፈጠረው ችግር ተጎጂ የሆኑትን ዝም ብሎ ማለፍ ስለማይችል ድጋፍ ማሰባሰቡን በተቻለኝ መጠን አደርጋለሁ።

Page 7 of 521