Administrator

Administrator

Sunday, 22 January 2017 00:00

የፖለቲካ ጥግ

- ሰላም መፍጠር የምትሻ ከሆነ፣ ከወዳጆችህ ጋር ሳይሆን ከጠላቶችህ ጋር ትወያያለህ፡፡
    ሞሼ ዳያን
- እኔ መናገር ስፈልግ ማንም አይሰማኝም፤ እነሱ እንድናገር ሲሹ እኔ የምለው የለኝም፡፡
   ዊንስተን ቸርቺል
- የፖለቲካ ልዩነት ሁልጊዜ ጤናማ ውይይት ይፈጥራል፡፡ ከጊዜ በኋላ ግን ውይይቱ ይበልጥ በጥላቻ የተሞላና አልፎ አልፎም ሁከት ፈጣሪ ይሆናል፡፡
    ማርክ ዩዳል
- ምንም የምትለው ነገር ከሌለህ፣ ዝም በል፡፡
   ማርክ ትዌይን
- እንደ ብልህ አስብ፤ነገር ግን በህዝብ ቋንቋ ተግባባ፡፡
   ዊሊያም በትለር ይትስ
- ዲሞክራሲ ማለት በውይይት የሚመራ መንግስት ነው፡፡ ውጤታማ የሚሆነው ግን ሰዎችን ከንግግር መግታት ከቻልክ ነው፡፡
   ክሌሜንት አትሊ
- ፖለቲካዊ ትክክለኛነት ውይይትን ይገድለዋል፡፡
   ላርስ ቮን ትሪዬር
- ውይይት የዕውቀት ልውውጥ ሲሆን ክርክር የድንቁርና ልውውጥ ነው፡፡
    ሮበርት ኪውይሌ
- በውይይት ላይ የሳይንቲስቱ ዓላማ ማግባባት አይደለም፤ ማብራራት እንጂ፡፡
    ሊዎ ስዚላርድ

ታዋቂዋ የሆሊውድ የፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጁሊ በ2007 ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ የወሰደቻት ዘሃራ ወላጅ እናት፤ ‹‹በህይወት አለሁ፤አንጀሊና ከልጄ ጋር እንድገናኝ  ትፍቀድልኝ›› በማለት መማፀኗ ተዘግቧል፡፡
አሁን የ12 ዓመት ታዳጊ የሆነችው ዘሃራ ወላጅ እናት፣ ወ/ት ምንትዋብ ዳዊት ሌቢሶ፤ ‹‹እባክሽን አንጀሊና፤ ልጄን እንዳነጋግራት ብቻ ፍቀጅልኝ›› ስትል በተማፅኖ መጠየቋን የእንግሊዙ “ዴይሊ ሜል ኦንላይን” ዘግቧል፡፡
በደቡብ ክልል ሾኔ ከተማ ከወላጅ እናቷ ጋር በዝቅተኛ ኑሮ ላይ የምትገኘው ወ/ት ምንትዋብ፤  ዘሃራን በ19 ዓመቷ በማታውቀው ሰው ተደፍራ መውለዷን፣ ጠቁማ፤ ከወሊድ በኋላ ለረዥም ጊዜ በመታመሟ በቤተሰቧ ግፊት ልጇን ለአሳዳጊ ድርጅት ለመስጠት መገደዷን ተናግራለች፡፡
‹‹ልጄን ላለፉት 12 አመታት በቀንም በሌት ሆነ ሳስባት የቀረሁበት ጊዜ የለም›› ያለችው ወላጅ እናቷ፤ ‹‹አሁን ግን የልጄን ናፍቆት መቋቋም አልቻልኩም፤ ልጄ ልክ እንደ አሳዳጊዋ  የምትወዳትና የምትሳሳለት ወላጅ እናት እንዳላት እንድታውቅ እፈልጋለሁ›› ብላለች ከዴይሊ ሜል ጋር ባደረገችው ቃለ ምልልስ፡፡
አንጀሊና ልጄን በማደጎነት ከወሰደቻት በኋላ ባሉት ጊዜያት ምንም ዓይነት ደብዳቤም ይሁን  መልዕክት አሊያም ገንዘብ ደርሶኝ አያውቅም›› ብላለች፤ የ31 ዓመቷ የዘሀራ ወላጅ እናት
‹‹እንዲያም ሆኖም ዘሃራ ወላጅ እናት እንዳላት እንድታውቅና እንድትጠይቀኝ ብቻ እንጂ ልጅቷን ከአንጀሊና ላይ የመውሰድ ፍላጎት የለኝም›› በማለት አስረድታለች፡፡
እውቋ የሆሊውድ ተዋናይት አንጀሊና ጁሊ፤ በ1997 ዓ.ም ዘሃራን ከኢትዮጵያ በጉዲፈቻ ለማሳደግ ስትወስዳት፣ ወላጆቿን በኤችአይቪ ያጣች ህፃን መሆኗ ተነግሯት እንደነበር ያስታወሰው ዴይሊ ሜል፤ ከ2 ዓመት በኋላ ግን ወላጅ እንዳላት መስማቷን ጠቁሟል፡፡

  የአልበሙ ሽያጭ ሙሉ ለሙሉ ለፌስቱላ ህሙማን ይውላል
    በሰርከስ ትግራይ ውስጥ ያደገው የወጣቱ ኢሳቅ ኪ/ማሪያም “ፍናን” የትግርኛ አልበም የፊታችን ሐሙስ ድምፃዊው ላለፉት ሰባት አመታት እየሰራበት ባለው ‹‹ክለብ ፍሪደም›› ይመረቃል፡፡ በቅርቡ ለገበያ የቀረበው አልበሙ 400 ሺህ ብር እንደወጣበት የገለፀው ድምፃዊ ኢሳቅ፤ የአልበሙ ሽያጭ ሙሉ ለሙሉ ለፌስቱላ ህሙማን እንደሚውል ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ 12 የትግርኛ ዘፈኖችን ያካተተው ‹‹ፍናን›› 16 የሙዚቃ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ሲሆን አልበሙን ሰርቶ ለማጠናቀቅ በርካታ አመታት ፈጅቷል ተብሏል፡፡ በቀጣይ በመቀሌና በአውሮፓ እንደሚመረቅ አስተባባሪው አቶ ተስፋዬ ገ/ዮሀንስ ገልጸዋል፡፡ የአልበሙ ስያሜ “ፍናን” የግዕዝ ቃል ሲሆን ሞራል (ወኔ) የሚል ፍቺ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡

 ደራሲና ጋዜጠኛ ዩሱፍ ያሲን የፃፈውና በማንነት ጥያቄዎች ዙሪያ ያሉትን ውስብስብ ክርክሮች አሰባስቦ በመያዝ፣ መፍትሄዎችን ያመላክታል የተባለው ‹‹ኢትዮጵያዊነት፣ አሰባሳቢ ማንነት በአንድ አገር ልጅነት›› የተሰኘ መፅሃፍ ለንባብ በቃ፡፡ መፅሀፉ በተለይም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት ውስብስብ የማንነት ጥያቄ አንፃር የሚያስጨንቁና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች በጥልቀት የተተነተኑበት ነው ተብሏል፡፡ የመጽሀፉ የመጀመሪያ ዕትም በውጭ አገር ለገበያ የቀረበ አንደነበር የተገለፀ ሲሆን የያዘው ቁም ነገር በውጭ አገር ተገድቦ እንዳይቀርና ኢትዮጵያዊያን በስፋት እንዲያወያዩበት ታስቦ፣ ሁለተኛው እትም አገር ቤት መሰራጨቱም ታውቋል፡፡ በበርካታ ምዕራፎችና ንዑስ ምዕራፎች ተከፋፍሎ በ437 ገፆች የተቀነበበው፤ መፅሁፉ በ131 ብር ከ60 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

 በክንፈ ባንቡ ተፅፎ የተዘጋጀውና የፍቅር ዘውግ ያለው ‹‹ፍሬ›› ፊልም ለዘንድሮው የታላቁ አፍሪካ ፊልም ፌስቲቫል (ፌስፓኮ) መታጨቱ ተገለፀ፡፡ አንጋፋዎቹ አርቲስት ፈለቀ የማር ውሃ አበበ፣ ራሄል ግርማና ኤማ ብዙነህ በመሪ ተዋናይነት የተሳተፉበት ይህ ፊልም፤ በፊስቲቫሉ እጩ በመሆኑ መደሰቱን ደራሲና ዳይሬክተሩ ገልጿል፡፡ በዘንድሮው የፌስፓኮ ፊልም ፌስቲቫል ላይ ከአንድ ሺህ በላይ ፊልሞች ለውድድር የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያዊው ‹‹ፍሬ›› ፊልም ለፍጻሜ ከቀረቡት 20 ፊልሞች አንድ መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ ፌስቲቫል ላይ የፕሮፌሰር ሃይሌ ገሪማ ‹‹ጤዛ›› ፊልም ከዚህ ቀደም እጩ እንደነበር የገለፀው ክንፈ ባንቡ፤ ‹‹ፍሬ›› ሁለተኛው ኢትዮጵያዊ የዘርፉ እጩ ፊልም መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ከፌቡራሪ 25 እስከ ማርች 4, 2017 በሚካሄደው በዚህ ፌስቲቫል ላይ ለመሳተፍ የፊልሙ አዘጋጆችና ተዋንያን ወደ ቡኪናፋሶ እንደሚጓዙ ታውቋል፡፡

 የደራሲ አክሊሉ ዘለቀ ስራ የሆነው ‹‹ሰው ስንት ያወጣል›› የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ። ደራሲው ስለ ልጅነት ትዝታቸው፣ ስለ ውትድርና አጀማመራቸውና የወትድርና ሕይወታቸው ከፍታና ዝቅታ ከከርቸሌ እስከ ዴዴሳ ስላሳለፉት እስር፣የተረኩበት ነው ተብሏል፡፡ መፅሀፉ በ208 ገፆች የተመጠነ ሲሆን በ91 ብር እና በ20 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

  የሰዓሊ ትዝታ ብርሃኑ የተመረጡ ስራዎች ለዕይታ የሚቀርቡበት "Features of Emotion"   የተሰኘ የስዕል አውደ ርዕይ ዛሬ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ጀምሮ ከጋና ኤምባሲ አለፍ ብሎ በሚገኘው "ሌላ ኢትዮጵያ ኮንቴምፖራሪ አርት ጋለሪ" ይከፈታል፡፡  አውደ ርዕዩ ለ20 ቀናት ገደማ ለተመልካች ክፍት ሆኖ የሚቆይ ሲሆን ከረቡዕ እስከ እሁድ ከጠዋቱ 4 ሰዓት እስከ ምሽት 12 ሰዓት መጎብኘት እንደሚቻል ታውቋል፡፡
 ሰዓሊዋ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበብ ት/ቤት ተመርቃ ከወጣች ወዲህ በሸራተን አዲስ የሚካሄደውን ዓመታዊ የስዕል ኤግዚቢሽን  ጨምሮ በተለያዩ የጋራ አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቿን ስታቀርብ የቆየች ሲሆን ለብቻዋ አውደ ርዕይ ስታቀርብ የአሁኑ የመጀመሪያዋ ነው ተብሏል፡፡ 

  የገጣሚ ታዲዮስ ተክሉ “የማያውቁት መልዓክ” የግጥም መድበል ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ በሰበታ ከተማ ጂም ሲኒማ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መድበሉ በህይወትና በተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ40 በላይ ግጥሞችን እንዳካተተ ታውቋል፡፡ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ አንጋፋና ወጣት ገጣሚያን ከመፅሐፉ የተመረጡ ግጥሞችንና የራሳቸውን ስራዎች ለታዳሚው ያቀርባሉ ተብሏል፡፡ የግጥም መድበሉ ለገጣሚው የመጀመሪያ ስራው ሲሆን በቀጣይም “የነፍስ ዕዳ” የአጫጭር ልቦለዶች ስብስብና “መልካም መንገድ” የተሰኘ ወጥ ልቦለድ ለማሳተም በዝግጅት ላይ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

  በገጣሚ ተስፋ በላይነህ የተጻፉ ግጥሞችን የያዘ “አርዑት” የተሰኘ የግጥም መድበል ሰሞኑን ለገበያ ቀርቧል፡፡ መድበሉ ስለ ሰው ሰራሽና ስለ ተፈጥሮ ነጻነት የሚያወሱ ከ80 በላይ ፍልስፍናዊ ግጥሞችን ያካተተ ነው ተብሏል፡፡ ገጣሚው ለመድበሉ ርዕስነት የተጠቀመው “አርዑት” ፍቺው፤"መጥመጃ፣ መጠመጃ፣ ቀንበር፣ ህግ (ስርዓት)" የሚል መሆኑን በመግቢያው ላይ አስፍሯል፡፡ የመፅሐፉ መታሰቢያነት ለአንጋፋው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያምና ለመላው “ዞን ዘጠኝ” ነው ተብሏል፡፡  በ150 ገጾች የተቀነበበው የግጥም መድበሉ፤በኢንተርኔትም ጭምር እንደሚሸጥ የታወቀ ሲሆን  ለአገር ውስጥ በ49 ብር፣ለውጭ አገራት በ15 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 “የ92 አመቱ የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ በመጪው ጥቅምት ወር አጋማሽ እንደሚሞቱ ፈጣሪ አምላክ ነግሮኛል፣ ከዚያች ቀን አያልፉም” በማለት በአደባባይ ትንቢት የተናገረ አንድ የአገሪቱ ፓስተር፤ “በታላቁ መሪ ላይ አሟርተሃል” በሚል መታሰሩን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ፓትሪክ ሙጋድዛ የተባለው ፓስተሩ ባለፈው ሳምንት በተናገረው ትንቢት፣” ሙጋቤ ጥቅምት 17 ቀን ከዚህ አለም በሞት እንደሚለዩ ፈጣሪ ነግሮኛል” ማለቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የፓስተሩ ጠበቃም፣ “ጉዳዩን የያዙት መርማሪ ፖሊሶች፣ ፈጣሪ ለፓስተሩ ይህንን ነገር አለመናገሩን የሚያረጋግጡበት መንገድ ስለሌለ ደንበኛዬን ተጠያቂ ማድረግ አይችሉም” ሲሉ መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ፓስተሩ ከትንቢቱ በተጨማሪ “የአገሪቱን ሰንደቅ ዓላማ ለብሰሃል” በሚል ተከሶ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንደነበር ዘገባው አስታውሷል፡፡ ሮበርት ሙጋቤ በተደጋጋሚ ለህልፈተ ህይወት ተዳርገዋል የሚሉ ሀሜቶች ሲነዙባቸው እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ እሳቸው ግን “ከእየሱስ ክርስቶስ ይልቅ እኔ በተደጋጋሚ ሞቼ ተነስቻለሁ” በማለት፣ መሰል ሀሜቶችን በማሾፍ ሲያጣጥሏቸው መደመጣቸውን ገልጧል፡፡