Administrator

Administrator

በዛሬው ፈጣን አለም ባላሰለሰ ትምህርትና የክህሎት እድገት ውስጥ መሳተፍ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እጅግ አስፈላጊ ሆኗል።

በዕረፍት ላይ ላላችሁ ተማሪዎች፣ ለወጣት ባለሞያዎች፣ ራሳቸሁን በእውቀት በመገንባት በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ በጎ ተፅዕኖ ለመፍጠር ለምትጓጉ ሁሉ የአምስት ሚሊዮን ኮደርስ ፕሮጀክት ቀዳሚ ሊያደርጋችሁ ተሰናድቶላችኋል።

የትምህርትና የእውቀት መነሻችሁና ያላችሁበት ደረጃ ምንም ይሁን ያላችሁን ክሂሎት ለማሳደግም ሆነ አዲስ ነገር ለማወቅ ለምትሹ ሁሉ ሰፊ የእድል በር ተከፍቶላችኋል። በመላው ኢትዮጵያ ያላችሁ የክህሎት አበልፃጊዎች፣ አሣዳጊዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች ይኽንን ፕሮጀክትና እንቅስቃሴዎቹን እንዲደግፉ ጥሪ አቀርባለሁ።  

ውድ ባለተሰጥዖዎች፣ የኢትዮጵያችን ጥንካሬ በእናንተ እድገት ላይ የተመሠረተ ነው።

ለመመዝገብ: http://www.ethiocoders.et

Monday, 12 August 2024 20:25

ማህበራዊ ውል (social contract)

“በአንተ እንዲደርስ የማትፈልገውን በሌላው አታድርግ”


የአለም ስርአት በምን አይነት ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ውል መዋቀር አለበት የሚለው ሀሳብ በፍልስፍናው አለም ጎልተው ከወጡ ዋነኛ ጉዳዮች አንዱ ነው፡፡ በተለይም የመሀከለኛው ክፍለ ዘመን ፈላስፎች የሆኑት ሩሶው፤ ሎክ፤ ሆብስ እና አኩዊናሰ ቀዳሚዎቹ የዚህ ሀሳብ አውጠንጣኝ ናቸው፡፡ በዚህ ፅሁፍ state of nature እና natural law መርሆዎች ያላቸው ትስስር፤ የstate of nature እኩይ እና አስፈሪ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? የሰውን ልጅ ውል ለመዋዋል ምን ገፋፋው? ውሉ ለምንድን ነው ያስፈለገው? የማህበራዊ ውሉ ዋነኛ አላማስ ምንድን ነው? ፍትሃዊ የሆነውን የውል ሀሳብ በማዋለድ ሂደት የተዋዋዮቹ ሚና እስከ ምን ድረስ ነው? እና የመሳሰሉት ይዳሰሳሉ፡፡
State of nature
(ቅድመ ማህበራዊ ውል)
ስለ ሰው ልጅ ማህበራዊም ሆነ ፖለቲካዊ ህይወት ለመነጋገር ጥሩ መነሻ፣ ይህ ነባራዊ የህይወት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ የህይወት ምእራፍ የሰው ልጅ ተፈጥሮ እና አኗኗር ምን ይመስል ነበር? የህይወታቸው መልኮች ምን ይመስሉ ነበር? ሎክ እንደሚለው የ state of nature ዘመን የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ነፃነቱን ያለገደብ ያስመሰከረበት፤ ምንም አይነት ማህበራዊም ሆነ የህግ ጫናዎችን ሳይሸከም የኖረበት ዘመን ነው፡፡ መንግስት የለም፤ በአድርግ እና አታድርግ መሀከል ድንበር የሚያበጅ የህግ ድንጋጌ የለም፤ በሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ መብቶች ላይ ምንም አይነት ገደብ የለም፡፡ በstate of nature ዘመን የሰው ልጅ ነፃ፤ እኩል፤ ሁሉም የራሱ የተፈጥሮ መብቶች ጌታ ብሎም የነፃነቱ ዘብ ነው፡፡ ስሜቱን ስለሚከተል ራስ ወዳድና ገለልተኛ ነው፡፡ በሰው መሀል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶችን ሊፈቱ የሚችሉ የተደነገጉ ደንቦች ስለሌሉ እሾህን በእሾህ እንደሚባለው፣ ግጭትን በግጭት ለመፍታት ይሞክራሉ፡፡ የሰው ልጅ ድርጊት ኢ-ተገማች በመሆኑ ሌሎች በእኔ ላይ ምን ያደርሱብኝ ይሆን? የሚል የማያባራ ስጋት ተብትቦ ይይዛቸዋል፡፡
ሰው በተፈጥሮው ቅድሚያ የሚሰጠው ለራሱ ፍላጎት እስከሆነ ድረስ የራሱን ፍላጎት እና የስሜት ትእዛዞች ብቻ ይከተላል፡፡ እራሱ ለራሱ ወሳኝ ነው፡፡ የጋራ የሚባሉ ጉዳዮች የሉትም፡፡ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ገደብ የሌለበት ነፃነት ግጭትን ይጋብዛል፡፡ አንዱ ተፈጥሯቸው ፍርሃት ነውና ለህይወታቸውም ሆነ ለንብረታቸው ከለላ የሚሰጥ አካል ስለሌለ ሰዎች ያጠቁኛል የሚለው ስጋት ሁሌም አብሯቸው ይኖራል፡፡ እንዲህ ያለ ሰጋት ሰውን ሳይወድ በግድ የህይወቱ እና የንብረቱ ዘብ ያደርገዋል፡፡
“ሁሉም የሁሉም አቻ፡፡ እያንዳንዱ በራሱ ጉዳይ ንጉስ፡፡ ፍትህን እና እኩልነትን የማይረዱ፤ በንብረቱም ላይ ያለው የመጠቀም መብት አስጊ እና ደህንነቱ ያልተረጋገጠ ነው” ይለዋል ሎክ፡፡ በማያቋርጥ ስጋት ውስጥ መኖር ህይወትን አስፈሪ መልክ ይሰጠዋል፡: በአስፈሪነቱም የተነሳ ህይወት በግጭት የተሞላ አጭር እና እርባነቢስ ነው፡፡ የተጥሮአዊ ህግ (natural law) የሁሉንም ነፃነት ያንፀባርቃል፡፡ ሰዎች ሲፈጠሩ እኩል ናቸው፡፡ በተፈጥሮ ነፃ እና የመኖር መብትን የታደሉ ከሀዘን ይልቅ ደስታን የሚሹ ናቸው፡፡ እነዚህ ሶስት ወሳኝ የተፈጥሮ መብቶች የአሜሪካን ህገመንግስት የማእዘን ድንጋዮች ናቸው፡፡ የነፃነት አዋጃቸው በአብዛኛው በተጥሮአዊ ህግ መርሆዎች የተዋበ ነው፡፡ ግን ይህ የተፈጥሮ ህግ ምንድን ነው? ትእዛዛቱስ? የተፈጥሮ ህግ ከራሱ የሰው ልጅ ተፈጥሮ ውስጥ የሚወለድና ሁሉን አቀፍ የድርጊት ህግ ነው፡፡ ህጉም ፍፁምና እራሱን የቻለ በመሆኑ ማንም ማንንም በህይወቱ፤ በጤናው፤ በነፃነቱ እና በሃብቱ ሊያጠቃው አይገባም የሚል ነው፡፡ ይህ ልእለ ሃያል የሆነ ትእዛዝ በልቦናችን ተፅፎ ይገኛል፡፡
ማሰብ ለሚችል ሰው እነዚህ የተፈጥሮ ህግጋት የማያሻሙ መሆናቸውን ይረዳል፡፡ ሰው ብቻ ነው በተፈጥሮው አዕምሮን የታደለ ፍጡር፡፡ በዚህ ታላቅ የተፈጥሮ ችሮታ በበጎ እና መጥፎ፤ በፍትህ እና ኢ-ፍትህ መሀል ያለውን ልዩነት መለየት ይችላል፡፡ እንዲህ አይነት መረዳት በማሰብ ወዝ ላይ የቆመ ነው እንጂ በቀላሉ የሚደረስበት አይደለም፡፡ የተጥሮአዊ ህግ ከተፈጥሯችን ተነስቶ እኛኑ የሰው ልጆች የሚገዛ መርህ ነው፡፡ በቀላሉ ሲቀመጥ “በአንተ እንዲደርስ የማትፈልገውን በሌላው አታድርግ”፡፡ ማንም ማንንም በህይወቱም ሆነ በንብረቱ ጉዳት ሊያደርስበት አይገባም፡፡ እንዲህ አይነት ፍትህ ላይ መሰረቱን ያደረገ ሃሳብ ሊታወቅ የሚችለው ለማሰብ እራሳቸውን አሳልፈው በሰጡ ሰዎች ነው፡፡ ጊዜያቸውን መስዋእት ለማድረግ በተዘጋጁና ትኩረት ማድረግ በሚችሉ ሰዎች ሊታወቅ ይችላል፡፡
State of nature ነፃነት ቢኖረውም ብዙ የሚጎድለው ነገር አለ፡፡ እንደ አኩዊናስ ቅድመ ህግ የሚከተሉት ሶስት አበይት ጉድለቶች አሉበት፡-
ሰዎች በራሳቸው ፍርድ የታወሩ ስለሆኑ አብዛኛው የሰው ልጅ ለተፈጥሮ ህግ ትእዛዛት ትኩረት አይሰጥም፡፡ የሰው ልጆችን አስተሳስሮ ይገዛል የተባለው ህግ በብዙኃኑ የማይታወቅ ነው፡፡
ቅድመ ህግ በይፋ የተደነገገ ህግ ስለሌለው ልዩነትን በህግ አደብ ሊያሲዝ የሚችል ስርኣት የለውም፡፡ ልዩነትን በግጭት እንጂ በህግ መፍታት አይቻልም፡፡
ውሳኔ ሊያስፈፅም የሚችል አካል የለም- ማለትም ህግን በተላለፉ ላይ ቅጣትን ሊያስፈፀም የሚችል አካል የለም፡፡
ከዚህ በተጨማሪ ሆብስ እንደሚለው፤ “በአንድ መንግስት ስር ሆነው መኖር ባልቻሉበት ግዜ የሰው ልጆች ጦርነት በሚባለው ሁኔታ ውስጥ ናቸው፡፡ ሁሉም በሁሉም ላይ የተነሳበት ጦርነት፡፡ እንዲህ ሁሉም በሁሉም ላይ በተነሳበት ሁሉም ነገር ኢ-ፍትሃዊ መሆኑ የማይቀር ነው፡፡ ልክ እና ልክ አለመሆን፤ ፍትህ እና ኢ-ፍትህ ቦታ የላቸውም”፡፡ ስለዚህ ከተፈጥሮአዊ ህግ መርሆዎች አንፃር ሲታይ state of nature ህይወትን አዳጋች ያደርገዋል፡፡ state of nature የማይመች ይሆናል፡፡ ስለዚህ ይህን ለመሸሽ የሰው ልጅ በቂ ምክንያት አገኘ ማለት ነው፡፡ በምክንያት እገዛ state of nature የሚፈራ እና ሊወገድ የሚገባው መሆኑን መረዳት ይጀምራሉ፡፡ ይህን አይነት ህይወት በቃህ ማለት የሚቻለው እራስን ውል ውስጥ በማስገባት ብሎም እራስን ለአንድ በህዝብ ለተቋቋመ አካልና ህግ ማስገዛት ሲቻል ነው፡፡
Social contract
(ማህበራዊ ውል)
በተፈጥሮ የታደልነው አእምሮአችን ሁሉም በሁሉም ላይ የተነሳበት ጦርነት የማንም ፍላጎት እንዳልሆነ ያስገነዝበናል፡፡ በአእምሮ በመታገዝ ሰዎች ላቅ ወዳለው የህይወታቸው ግብ ያቀናሉ፡፡ ለህይወታቸውና ለንብረታቸው የጋራ ከለላ ለመስጠት ሲባል በአብሮ መኖር ስም ውል ውስጥ ይገባሉ፡፡ ማህበራዊ ውል ማለት በሰዎች መሀከል የማህበራዊ ተቋማትን፤ ህይወትን እና ነፃነትን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ደንቦችን ለማቋቋም የሚደረግ ስምምነት ነው፡፡ በዚህም እያንዳንዱ የተወሰኑ መብቶቹን ይተዋል፡፡ ሌሎች ላቅ ያሉትን ማለትም የጋራ ጥቅም፤ ሰላም፤ ደህንነትን ለመጠበቅ ሲባል የተወሰኑ ልዪ ጥቅሞችን ለህግ አሳልፎ ይሰጣል፡፡
ከመነሻው ጀምሮ ሰዎች እራሳቸውን ለእንዲህ አይነት ተቋማት ማስገዛታቸው ለራሳቸው ጥቅም መሆኑን ይረዳሉ፡፡ በዛውም ወሳኞቹን መብቶቻቸውን ያረጋግጣሉ፤ ከሰው ልጆች የሚጠበቀው ምክንያታዊነትን ግምት ውስጥ ማስገባት ብቻ ነው፡፡ የፍትህንና የነፃነትን ምንነት ካልተረዱ መዋዋል ፈይዳ ቢስ ነው፡፡ ውሉ ከመንስኤ ወደ ውጤት የሚመራ ሂደት ነው፡፡ ከሁሉ የላቀ አላማው ህይወትን፤ ነፃነትን እና ንብረት መጠበቅ ነው፡፡ እያንዳንዱ በፀደቀው ህግ ይመራል፤ የመንግስት መሰረቱም ይህ ነው፡፡ እነዚህ ህግጋት ተፈጥሮአዊ ናቸውና የሰውን የአብሮነት ኑሮ ያፀናሉ፡፡
በState of nature በእንቅፋት የተሞላው ህይወት በሚፀድቀው የማህበራዊ ውል መልክ ይይዛል፡፡ በውሉም መሰረት እያንዳንዱ የሚኖረው መብት እና ሀላፊነት ይለያል፡፡ ይህም ነው ሰዎችን በስርኣት እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው፡፡ መርሆዎቹ ከየትም የመጡ ሳይሆን ምክንያትን በማዳመጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ እራስን ማስገዛት የስልጡን ሰው መለያ ባህሪው ነው፡፡ ማህበረሰቡ ሊያብብ የሚችው እያንዳንዱ የሚናውን ማዋጣት ሲችል ነው፡፡ የጋራ ጎጇቸው የሚፈርሰው ከዚህ በተቃራኒ ሲሆኑ ማለትም ሁሉም ትኩረቱን በራሱ ጉዳይ ሲያደርግ ነው፡፡ በሌላ ቋንቋ ወደ ቀድሞው ሁኔታ (state of nature) ሲመለሱ፡፡ ከዚህ ሊገላገሉ የሚችሉት እራሳቸውን ለህጉ ማስገዛት ሲችሉ ብቻ ነው፡፡
የሰው ልጅ ከቅድመ ህግ ወጥቶ እራሱን በማህበራዊ ውል ውስጥ ያደረገው ለጋራ ጥቅም ሲባል እንደሆነ መረዳት አለበት፡፡ የጋራ ጥቅም ሊረጋገጥ የሚችለው በአንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ ውስጥ በመግባት ነው፡፡ ለህጋዊ መንግስት ጅማሮ የሚሰጠው ይህ እና ይህ ብቻ ነው፡፡ ሰዎች ተስማምተው ባወጡት ህግ ለመመራት ፍቃዳቸውን ያሳያሉ፡፡ ይህ ፍቃድ በተራው ለመንግስት ቅቡልነት ይሰጠዋል፡፡ በህዝብ ይሁንታ የተመሰረተው መንግስት የሚመራው እና ህዝቡም በተራው የሚተዳደረው በተደነገገው እና በፀደቀው ህግ ነው፡፡ ህጎቹ ከፍትህ መርህ ጋር ስሙም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሰብኣዊ መብት፤ ለሰው መብት ክብር መስጠት፤ የህግ የበላይነት እና የጋራ ጥቅም የፍትህ ነፀብራቆች ናቸው፡፡ በማህበራዊ ውሉ የተመሰረተው መንግስት የመጨረሻ ግብ ሰላምን፤ ደህንነትን እና ማህበራዊ አገልግሎትን ማረጋገጥ ነው፡፡ ህዝቡም የዚህ ተጠቃሚ መሆን አለበት፡፡ በstate of nature የታዩት ዋና ዋና ሀጥያቶች በመንግስት እና በተቋማቱ መወገድ አለባቸው፡፡

ተፈጥሯዊ ህግ
በአለም አቀፍ ህግ ውስጥ
የአለም ማህበረሰብ በሽብር እና በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰ ነው፡፡ ሰላሙም በዚህ ቋሚ በሚመስል የጦርነት ፍርሃት ነው የቆመው፡፡ ለየት ያለ እና ሰዋዊ እሴትን እንዲያብብ የሚያስችል አዲስ ትልም ያስፈለጋል፡፡አንድነት እና ህብረት፡፡ አለም ይህነ ማድረግ ከቻለ ይህ ያለንበት ዘመን ካለፉት ዘመናት የተሻለ ይሆናል፡፡ ሰላሙ እና ደህንነቱ በተጠበቀ አለም ውስጥ መኖር በእያንዳንዱ ፍላጎት ስር ነው፡፡ሰላሙን ከቤተሰባችን እና ካለንበት ማህበረሰብ እንጀምር፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ሀገራት ለጋራ ችግሮቻቸው መተባበር እና መተጋገዝ አለባቸው፡፡እራሳቸውን ለተፈጥሯዊ ህግ መርሆዎች ማስገዛት አለባቸው፡፡ የፈርንሳይ እና የአሜሪካ ህገመንግስቶች ለዚህ ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ለምሳሌ የአሜሪካ የነፃነት አዋጅ ከላይ እነደተመለከትነው የግለሰብ መብት፤ ማህበራዊ ውል እና የተፈጥሯዊ ህግ መርሆዎችን አቅፎ ይገኛል፡፡ “ሁሉም ሰው በእኩልነት እንደተፈጠረ እውነት መሆኑን እናምናለን፡፡የሰው ልጆችም በፈጣሪያቸውም የማይጣሱ መብቶች እንዳሏቸው ከነዚህ ውስጥ የመኖር፤ የነፃነት እና ደስታን የመሻት መብት ይገኙባቸዋል”፡፡እነዚህን መሰረታዊ መብቶች ለማረጋገጥ ነው በሰው ላይ መንግስት የፀናው፡፡ ስልጣኑንም ከተመሪው በፈቃድ እና በውክልና ይወስዳል፡፡ ስልጣኑ የውክልና እስከሆነ ድረስ መንግስት አጥፊ ሲሆን ህዝቡ የመቀየር እና የማስወገድ መብት አለው፡፡በዛውም አዲስ መንግሰት ይመሰርታሉ፡፡ደህንነታቸውን እና ሰላማቸውን ሊያፀኑላቸው የሚችሉትን መርሆዎች እና መንግስታቸውን በዛው ያዋቅሩታል፡፡ዜጎች ከሁሉም በላይ ለሰው ልጅ መሰረታዊ መብቶች ቅድሙያ መስጠት አለባቸው፡፡

የተፈጥሮአዊ ህግ ሚና እና አስፈላጊነቱ
የተፈጥሮ ህግ ሁሉን አቀፍ እና የማያሻማ ህግ ነው፡፡ ከላይ የተዘረዘሩትን በሙሉ መረዳት የምንችለው በማሰላሰል እገዛ ነው፡፡የሰው ህይወት ያለ ማህበራዊ ህይወት ሊቆም አይችልም፡፡ የሰውን ፍላጎቶች ያለማህበረሰብ ማሰብ አይቻልም፡፡ ሰዎች በማህበር ይኖራሉ ለደህንነታቸውም በዛ ይመረኮዛሉ፡፡ ይህ እውነት በሰው ብቻ ሣይሆን በሀገራት መሀከልም ይሰራል፡፡
በአለም አቀፍ ህግ ውስጥ የተፈጥሮ ህግ ተቀባይነት እንዲኖረው የሁሉም ሀገራት ይሁንታ ያስፈልገዋል፡፡ሰው ያለሌላው ሰው ድጋፍ እንደማይኖረው ሁሉ ሀገራትም እንደዛው ናቸው፡፡የተፈጥሮ ህግ ልምዶች በአለም አቀፍ ህግ መካተት አለባቸው፡፡የተካተቱም አሉ፡፡ ሀገራት እሱን ማክበር አለባቸው፡፡እኩልነት፤ ወንድማማችነት እና ነፃነት በተለይ ይህ ያለንበት ዘመን አብዝቶ ይፈልጋቸዋል፡፡አሁን ካሉት ተለምዷዊ መርሆዎች በተጨማሪ ሀገራት አንድ አዲስ አይነት ስምምነት ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማሻሻያ ይደረግብት የሚባልበት አንዱ ምክንያትም ይህ ነው፡፡የተፈትሮ ህግ ለአለም አቀፍ ህግ መሰረት ነው ፡፡ አዲስ አይነት ስምምነት ውስጥ መግባት ከቻሉ ሁሉም ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡ የአለም አቀፍ ህግ ግቡም የጋራ ጥቅምን እና ደህንነትን ማስጠበቅ ነው፡፡
አርስቶትል በአንድ ፅሁፉ “እያንዳንዱ ሀገር የአንድ ማህበረሰብ ውጤት ነው፡፡ ማህበረሰብ የተዋቀረው አንድን ግብ ለማሳካት ነው፡፡ ማህበረሰብ ያ ግብ ካለው የሃገር ግብ ደግም ከሁሉም የላቀ ነው” ይላል፡፡ የእያንዳንዱ ሰው በጎነት እና እርስ በራስ መደጋገፍ ነው የሁሉንም ህልውና የሚያረጋግጠው፡፡
አሁን ባለንበት ዘመን ይህ እውነት ነው፡፡ የጋራ ሰላም እና የጋራ ደህንነትን ማረጋገጥ የግሎባላይዜሽን ቀዳሚ አላማ ሆኗል፡፡ ሀገሮች በመተጋገዝ የተጋረጠባቸውን አደጋ መቀልበስ ይገባቸዋል፡፡ የአንዱ ህመም የሁሉም ነው፡፡ አንዱ ሲታመም ሌላውም ይታመማል፡፡ አለም አቀፍ ጉዳዮች፤ የጦር ወንጀል፤ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፤ ሽብርተኝነት በወንድማማችነት እንጂ የተናጥል ጉዞ እንደማይቀርፋቸው አለም መስክሯል፡፡ በዚህ መልኩ ሲታይ ነው አለምአቀፍ ህግ የተፈጥሮ ህግ ነፀብራቅ ነው የሚያስብለው፡፡ ሀገሮችም ለዚህ ሀሳብ ተገዢ መሆን ይገባቸዋል፡፡ የተወሰኑ መብቶቻቸውን በመተው ለልእልናው መገዛት አለባቸው፡፡
ወንድማማችነት ሌላው የተፈጥሮ ህግ መርህ ነው፡፡ በሀገሮች መሀከል ያለ ትስስርን ይገልፃል ፡፡ ሀገሮች ስለፈለጉት ብቻ ሳይሆን የእነሱ ህልውና ያለ ሌሎች ስለማይኖር ነው፡፡ የሚጋፈጧቸው ችግሮች በተሻለ የሚቀረፉት ሲተባባሩ ነው፡፡
ህልቆ መሳፍርት የሆኑት የአለም ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት ሀገሮች በወንድማማችነት ስሜት ሲተጋገዙ እና ሲደጋገፉ ነው፡፡ ለችግሩ ባለቤት እንደሆኑት ሁሉ በመቅረፉ ሂደትም የጎላውን ደርሻ ይወስዳሉ፡፡ ይህን የመሰለው የተፈጥሮ ህግ መርህ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አንቀፅ 1 ምእራፍ 2 ተቀምጧል፡-“የተመድ ዋነኛ አላማው አለም አቀፍ ትብብርን በማሳካት ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ ባህላዊ ወይም ሰብአዊ መልክ ያላቸውን አለም አቀፍ ችግሮች መቅረፍ ነው”፡፡ ሀገራት ትልቅ ትንሽ ሳይባባሉ በእንዲህ አይነት የትብብር መንፈስ አለምን ስጋት ላይ የሚጥሉ የሰላም እና ደህንነት ስጋቶችን ያስወግዳሉ፡፡ ወንድማማቻዊ ትብብር የአለም ሰላም ዘብ ነው፡፡ የተፈጥሮአዊ ህግ አንዱ አላማም ሰላምን ማስፈን ነው፡፡

ጸሐፊው ደራሲ ይልማ እሸቴ ፤የፊልም ዳይሬክተሯ ቅድስት ይልማ አባት ናቸው።
በሥራዎቿ ድንቅ የሆነችው ቅድስት ይልማ ወዳጆቿን፣ የሙያ አጋሮቿን እና ቤተሰቧን ይዛ ትጠብቀናለች።

በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተ መጻሕፍት (ወመዘክር) ቅዳሜ ነሐሴ 11፣ 2016 “ከበደች ትቀኛለች” በሚል ርዕስ ገጣሚ፣ ቀራጺ እና ሠዓሊ ከበደች ተክለአብ ስራዎቿን የምታቀርብበት የግጥም ሠርክ ዝግጀት ይካሄዳል፡፡
ሁላችሁም በአክብሮት ተጋብዛችኋል!
ሁላችሁም በአክብሮት ተጋብዛችኋል!

 

-  የህወሓት ሕጋዊነትን የመመለስ ሂደት ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ጎን ለጎን ሲካሄድ እንደቆየ ገልጸዋል

-  በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሁለቱ ፈራሚዎች እርስ በራሳቸው ዕውቅና እንደሚሰጣጡ “ይደነግጋል” ብለዋል


የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "ህወሓትን እንደአዲስ መመዝገብ ማለት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትን ማፍረስ ማለት ነው" ሲሉ ምርጫ ቦርድ ለፓርቲያቸው የሰጠውን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ነቅፈው ተናግረዋል። ሊቀ መንበሩ ይህንን የተናገሩት ትናንት ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ነው።

"ህወሓት ሃምሳ ዓመታትን ያስቆጠረ...እንደአዲስ መመዝገብ የሌለበት አንጋፋ የፖለቲካ ድርጅት ነው" ያሉት ደብረጽዮን (ዶ/ር)፣ "የህወሓት ሕጋዊነትን የመመለስ ጉዳይ ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት [ሂደት] ጎን ለጎን እንጂ አሁን የተጀመረ አይደለም " ብለዋል። አያይዘውም፣ "የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሁለቱ ፈራሚዎች እርስ በራሳቸው እውቅና እንደሚሰጣጡ ይደነግጋል" ሲሉ አመልክተዋል።

የህወሓት ህጋዊነትን ለመመለስ የተካሄዱ በርካታ ውይይቶችን ተከትሎ፣ ድርጅቱና ሌሎች ወገኖችን የሚያካትት፤ አዲስ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የሚመለከት የተሻሻለ ዓዋጅ እስከ መውጣት መደረሱን አብራርተዋል። "የተሻሻለው በአመፅ ድርጊት የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መልሶ ስለመመዝገብ የሚመለከተው ዓዋጅ፣ ህወሓት ወደ ቀደመው ዕውቅና ሊመልስ አይችልም " ብለዋል፣ ደብረፅዮን (ዶ/ር)።

አያይዘውም፣ ሊቀ መንበሩ "ህወሓት ወደ ነባር ዕውቅናው ይመለሳል እንጂ እንደ አዲስ አይመዘገብም " በማለት የተናገሩ ሲሆን፣ "ህወሓትን እንደአዲስ መመዝገብ ማለት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ማፍረስ ማለት ነው" ሲሉ ገልጸዋል። "የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢዎች በተገኙበት ነው ህወሓት ወደ ነባሩ ዕውቅና ለመመለስ ስምምነት ላይ የተደረሰው" በማለት ተናግረዋል።

ከቀናት በፊት፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ  ለህወሓት "በልዩ ሁኔታ" በማለት የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ መስጠቱ የሚታወቅ ነው።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በነገው ዕለት ነሐሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. በሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ እንደሚጀመር ተገልጿል። የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ለህወሓት ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ የኮሚሽኑ አባላት በጉባዔው ላይ እንዲሳተፉ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

ወይዘሮ ፈትለወርቅ "14ኛው የህወሓት ጉባኤ ነሃሴ 7 ቀን 2016 ዓ.ም. ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ጀምሮ በመቐለ የሰማዕታት ሐወልት አዳራሽ ይካሄዳል " በማለት በጻፉት ደብዳቤ አመልክተው፣ አዘጋጅ ኮሚቴው የጉባዔውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀ አስታውቀዋል።

ነገር ግን የደርጅቱ ማእከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽን ነገ ከሚጀመረው ጉባዔ ራሱን ማግለሉን ያስታወቀው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር። በሌላ በኩል፣ የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበርና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተካተቱበት፣ ሌሎች 14 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በጋራ "ማንአለበኝነት የተጠናወተው ጠባብ ቡድን " ሲሉ በጠሩት አካል በተዘጋጀው ጉባዔ እንደማይሳተፉ ትናንት በጻፉት ደብዳቤ አስታወቀዋል። በተመሳሳይ መልኩ፣ በትናንትናው ዕለት ሰባት የመቐለ ከተማና ሁለት የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ከፍተኛ የህወሓት ካድሬዎች "ጠባብ ቡድን" በማለት በጠሩት አካል “ተጠራ” ሲሉ በገለጹት የህወሓት ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔ እንደማይሳተፉ ገልጸዋል።

አመራሮቹ በጉባዔው ላለመሳተፍ የገፋቸውን ምክንያት "በአሁኑ ወቅት የሚካሄደው ጉባዔ ከጥቅሙ ጉዳቱ ስለሚያመዝን ላለመሳተፍ ወስነናል " በማለት ገልጸውታል። ይሁንና ጉዳቱ በዝርዝር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። አክለውም፣ "ጉባዔውን ተከትሎ ለሚመጣ ነገር እኛ የለንበትም " ብለዋል።

 የውጭ ምንዛሬ በመንግሥት ተመን ሳይሆን በገበያ ዋጋ?
•     እንዲህ ዐይነት የምንዛሬ አሠራር ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ያልታየ “ሥር-ነቀል ለውጥ” ነው።
•     ጥቅሙና ጉዳቱ ላይ ሰዎች ብዙ መነጋገርና መከራከር፣ ከዚያም ባሻገር መጨቃጨቅ ይችላሉ።
አስጨፋሪዎችም አስለቃሾችም ሞልተዋል


ለክፉም ለደጉም፣ አዲሱ የምንዛሬ ሥርዓት በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ያልታየ “ታሪካዊ ለውጥ” መሆኑ ግን አያከራክርም። ብዙዎች በዚህ አባባል የሚስማሙ ይመስላል። “ለውጡን ቢቃወሙም ቢደግፉም”። ይህም ብቻ አይደለም።
እውነት ለመነጋገር ከፈለጉ፣ ቢያንስ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን እንደሚያባብስም መመስከር ይችላሉ - ለውጡን ቢደግፉም ቢቃወሙም፣ እውነታውን ላለማየት እስካልሸሹ ድረስ።
ሌሎች የመስማሚያ ነጥቦችም አሉ።
ነባሩ የምንዛሬ ተመን እንደስካሁኑ ወደፊት ሊቀጥል የማችልበት ደረጃ ላይ እንደደረሰ ለመረዳት ከባድ አይደለም። በሆነ መንገድ ካልተስተካከለ በቀር፣ የመንግሥት የምንዛሬ ተመንና የጥቁር ገበያ ዋጋ በዕጥፍ ተለያይቶ እስከመቼ ይዘልቃል? በዚህ መንገድስ የኤክስፖርት ምርት እንዴት ሊያድግ ይችላል?
ከዐሥር ዓመት በፊት፣ አነስተኛ የወርቅ አምራቾች በዓመት ስምንት ኩንታል ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ የሸጡበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል።
የምንዛሬ ተመኑ አላዋጣ ሲላቸውስ? ለብሔራዊ ባንክ ከመሸጥ ይልቅ፣ በሰው በሰው፣ በነጋዴ በደላላ በየአካባቢያቸው በደህና ዋጋ ለመሸጥ ይሞክራሉ። ዞሮ ዞሮ በድንበር በኩል በኮንትሮባንድ በዶላር ወደ ውጭ አገር ይሄዳል። መንግሥት በቁጥጥር ብዛት ይህን ኮንትሮባንድ ማስተካከል አይችልም። ለነገሩ፣ አምራቾችም በቁፋሮ ያገኗትን ወርቅ በድብቅ ለመሸጥ እየተጨናነቁና በመንግሥት ቁጥጥር እየተሳቀቁ ምርታቸውን ማሳደግ አይችሉም። አገሪቱም ዶላር አታገኝም።
በዶላር ዕጥረት ሳቢያ ገደል አፋፍ ላይ የደረሰችው ለምን ሆነና! IMF ከሳምንት በፊት ባወጣው ሰነድ እንደገለጸው ከሆነ፣ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሬ ክምችት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቆተ፣ ለአንድ ሳምንት የማዘልቅ ሆኗል። ይሰውረን አትሉም? የምንዛሬ ተመን፣ ከዚህ አደጋ አላዳነንም። ለአደጋ ዳረገን እንጂ። IMF እንደዚያ ይላል።
በእርግጥ የዶላር ዕጥረቱና አደጋው በፍጥነት እየተባባሰ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ከክፉ ቀውስ የተጋለው፣ በጦርነት ሳቢያ ነው። ጦርነት መደበኛ ኑሮ ሊሆንብን ምን ቀረው? ከጦርነት ጋር አብረው የሚመጡ የሥነ ምግባር ብልሹነትና የሥርዓት አልበኝነት በሽታዎችን በየአካባቢያችሁ እየታዘባችሁ ነው? ሌላውን እርሱት። የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በመዘገብ የሚታወቀው ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ሰሞኑን ስለ ኢትዮጵያ ምን ብሎ እንደዘገበ አይታችኋል?
የምንዛሬ አሠራር ለውጥ፣ የአይኤምኤፍና የዓለም ባንክ ብድር… ምናምን አልዘገበም። ለእግረ መንገድ ያህል ጠቀስ ጠቀስ አድርጎ ጽፏል። የዘገባው ዋና ትኩረት ግን ሌላ ነው። የሰዎች እገታ በኢትዮጵያ እየተስፋፋ እንደመጣ በሰፊው ይተነትናል።
የምንዛሬ የማሻሻያ ለውጥ፣ ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን ለማሳደግ ሊጠቅም ይችላል። ሰላም ከሌለ፣ ጦርነት ካልቆመ፣ ሥርዓት አልበኝነት ከተስፋፋ፣ ሽፍትነትና እገታ “ሃይ ባይ” ካጣ… ለኢንቨስትመንት የሚጓጓ አይኖርም። ከኢንቨስትመንት የሚሸሽ እንጂ። ዘኢኮኖሚስት እንደዚያ ብሏል። እኛስ የጦርነትን ክፋት ጠፍቶን ነው?
ጦርነት የማዘውተው አባዜያችንን ካላራገፍን፣ ከዶላር ዕጦት አንገላገልም። ጦርነትን ዕርም ብለን ካልተውን፣ የትኛውም ዐይነት የምንዛሬ አሠራር የትም አያደርሰንም። ጦርነትን መግታትና ማስቀረትም ግን በቂ አይደለም።
በእስከዛሬው የምንዛሬ አሠራር የዶላር ዕጥረትን ማቃለል አይቻልም። በሌላ አነጋገር፣ የውጭ ኢንቨስትመንትንና ኤክስፖርትን የሚያዳክም እንጂ የሚያሳድግ አይደለም - ነባሩ የምንዛሬ አሠራር።
እንደታሰበው ቢሆን፣ ዘንድሮ ከኤክስፖርት ምርት 10 ቢሊዮን ዶላር ገደማ መገኘት ነበረበት። ግን ብዙም ፎቀቅ አላለም።


*

ሥር-ነቀል የምንዛሬ ለውጥ - ብዙ ጣጣ አለው!
በሌላ በኩልም ግን፣ ነባሩ የምንዛሬ አሠራር በአንዴ ከሥር ተነቃቅሎ ሲለወጥ ብዙ ነገሮችን ያናጋሉ። ለኢኮኖሚ አደጋዎችም ያጋልጣል። “ነባር የኢኮኖሚ ፖሊሲዎች” በሙሉ እንደገና ካልተከለሱና ካልተለወጡ፣ ከአዲሱ የምንዛሬ አሠራር ጋር አብረው ሊሄዱ አይችሉም። የፋብሪካዎች ሥራ በመለዋወጫ ዕቃ ዕጦት እንዳይደናቀፍ “ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ እንዲያገኙ በመንግሥት ተወስኗል” የሚል ዜና ካሁን በኋላ አይሠራም።
“የውጭ ምንዛሬ ለፍጆታ ሸቀጦች አናባክንም። የውጭ ምንዛሬ፣ ነዳጅና ማዳበሪያ ለመሳሰሉ መሠረታዊ ምርቶች፣ እንዲሁም ለኢንዱስትሪ ዕድገት የሚያስፈልጉ የፋብሪካ ማሽኖች መዋል አለበት”… እንዲህ ዐይነት አባባል ካሁን በኋላ ብዙ አያስኬድም። ለጊዜው ለሁለት ለሦስት ዓመት ያህል፣ ለነዳጅና ለማዳበሪያ የዶላር ኮታና ድጎማ መመደብ ይቻላል። ግን ለጊዜው ብቻ ነው ተብሏል። ወደ ፊት አይኖርም።
“ስንዴና ስኳር ከእንግዲህ ከውጭ አንገዛም። ብስኩትና ማስቲካ ከውጭ አናስገባም! የሸቀጥ ማራገፊያ አንሆንም”… የሚሉ አባባሎችም ከእንግዲህ ብዙ አያራምዱም። ይህም ብቻ አይደለም።
እንደምታውቁት፣ የኤሌክትሪክ ግድብ፣ የመንገድ ግንባታ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የማዳበሪያና የስኳር ፋብሪካ… የመንግሥት የፕሮጀክቶች ዐይነትና ቁጥር ብዙ ነው። ካሁን በኋላ ግን፣ እንደ ልብ መሆን አይቻልም። የምንዛሬ ገበያ ለመንግሥት አስቸጋሪ ነው። መንግሥት ከውጭ እየተበደረ የፕሮጀክቶችን የመጀመር ብዙ ዐቅም አይኖረውም። ዕዳ ከተከማቸበት በኋላ ብድሩን እንዴት መመለስ ይችላል?
የምንዛሬ ተመንና የምንዛሬ ገበያ - የሒሳብ ልዩነት።
የውጭ ብድር ከነወለዱ በየዓመቱ 2 ቢሊዮን ዶላር ሲከፍል እንደነበር ታስታውሳላችሁ። ያው መንግሥት ዶላር አይወልድም። ራሱ መንግሥት በሚመራው ተመን፣ በ60 ብር የምንዛሬ ሒሳብ ከባንኮች ዶላር ይወስዳል።
2 ቢሊዮን ዶላር ለመውሰድ 120 ቢሊዮን ብር ይከፍል ነበር ማለት ነው።
አሁንስ?
የምንዛሬ ዋጋው 100 ብር እያለፈ አይደል? በመቶ ብር ብናሰላው እንኳ፣ መንግሥት ከባንኮች 2 ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት 200 ቢሊዮን ብር መክፈል ይኖርበታል።
ልዩነቱ ቀላል አይደለም። የመንግሥት በጀት ላይ ተጨማሪ የ80 ቢሊዮን ብር ወጪ ያስከትልበታል - የምንዛሬ አሠራር ስለተለወጠ ብቻ።
በሌላ አነጋገር፣ ዶላር ለመንግሥትም እጅግ ውድ ይሆንበታል። መንግሥት ቅድሚያ በሚሰጣቸው የኢኮኖሚ ዘርፎች ላይ “አዳዲስ ግንባታዎችን እጀምራለሁ፤ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶችን እሠራለሁ” እያለ የውጭ ብድር የማምጣት ዐቅሙ ይዳከማል።
እንዲህ ሲባል ግን፣ ሙሉ ለሙሉ ከፕሮጀክቶችና ከውጭ ብድር ጋር ይቆራረጣል ማለት አይደለም።
የዓለም ባንክና የአፍሪካ ልማት ባንክ ከመሳሰሉ ተቋማት ጥቂት የፕሮጀክት ብድሮችን ማግኘቱ አይቀርም። ነገር ግን፣ አሁን አሁን የፕሮጀክቶቹ ባህርይም እየተቀየረ አይደል?
ድሮ ድሮ አብዛኛው ብድርና እርዳታ… የመንገድ ግንባታና የኤሌክትሪክ ግድብ ለመሳሰሉ ፕሮጀክቶች ነበር የሚውለው። ዛሬ ዛሬ ግን፣ ለምግብ ዋስትና… ማለትም ችግረኛ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎችን ለመርዳት ነው ብድር የሚመጣው። አስቸጋሪ ነው። በብድር በልቶ ማደር! ወዴት እንደሚያደርሰን እንጃ።
የሆነ ሆኖ፣ የዶላር ጨዋታው “ከነባር የምንዛሬ ተመን” ወደ “አዲስ የምንዛሬ ገበያ” ሲለወጥ፣ “ነባር የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችም” ጊዜ ያልፍባቸዋል።
“ጥራት ያለው የቡና ምርት በአገር ውስጥ ገበያ ለመሸጥ የሞከሩ ነጋዴዎች በፖሊስ ክትትል ተያዙ፣ ንብረታቸው ተወረሰ” የሚሉ ዜናዎችን ታስታውሱ ይሆናል።
የራሳቸውን ምርት ወደ ገበያ አውጥተው ለመሸጥ ስለሞከሩ እንደ ሌባ ይቆጠራሉ። ውንጀላውማ ከዚህም ይብሳል። በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሻጥር የሠሩ፣ የአገር ክህደት የፈጸሙ ያህል ነው የክስ መዓት የሚወራባቸው። ለምን እንደሆነ ይገባችኋል መቼም።
ያው፣ መንግሥት ዶላር ይፈልጋል። ማን የማይፈልግ አለ? ዶላር ተገኝቶ ነው! ሁሉም ይፈልጋል። መንግሥትም ዶላር ይፈልጋል። የመንግሥት ፍላጎት ግን ትንሽ ለየት ይላል። ጉልበት ይጨምርበታል። በምንዛሬ አሠራር ላይ አዲስ ሕግ ማወጅ፣ ደንብና መመሪያ አውጥቶ በጉልበት ማስፈጸም ይችላል። ራሱ ባወጣው የምንዛሬ ተመን የሰዎችን ዶላር ይወስዳል። ማን ከልካይ አለበት?
ጥራት ያለው የቡና ምርት እዚሁ መርካቶ ውስጥ ከተሸጠ መንግሥት ምንም ጥቅም አያገኝም። ቡናው ወደ ውጭ ከተላከ ግን ዶላር ይመጣል። ወደ ባንክ ይገባል። መንግሥት በገበያ ዋጋ ሳይሆን በራሱ የምንዛሬ ተመን ዶላሩን ይወስዳል - ለምሳሴ በ60 ብር ሒሳብ። ይህን እንዳያስቀሩበት ነው በኤክስፖርት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያካሂደው።
አሁን ግን፣ መንግሥት የሰዎችን ዶላር መውሰድ ከፈለገ… ያው በገበያ ዋጋ መግዛት ይኖርበታል ተብሏል። በመቶ ምናምን ብር ሒሳብ መሆኑ ነው። ቡና ነጋዴዎች ምን ቸገራቸው? በገበያ ዋጋ የዶላራቸውን ምንዛሬ የሚያገኙ ከሆነ፣ የራሳቸውን ንብረት በድብቅ በአገር ውስጥ ለመሸጥ የሚሞክሩበት ምክንያት ብዙም አይኖርም። ከሸጡም… ያው በገዛ ንብረታቸው ማን ይከለክላቸዋል? ወርቅ አምራቾችም እንዲሁ!
መንግሥትስ፣ እንደ ድሮው የኤክስፖርት ዶላሮችን በአነስተኛ የምንዛሬ ተመን መውሰድ ካልቻለ፣ ለቁጥጥር መስገበገብ ምን ያደርግለታል?
ምናለፋችሁ! የምንዛሬ አሠራር ላይ የተደረገው ለውጥ ሁሉንም ነገር ይነካካል። እንዲህ ሲባል ግን፣ “በምንዛሬ ተመን” ምትክ የመጣው “የምንዛሬ ገበያ” ምን ዐይነት መልክ እንደሚኖረው ሙሉ ለሙሉ ይታወቃል ማለት አይደለም።
የምንዛሬ ገበያው ምን ያህል ለገበያ እንደሚለቀቅ ከወዲሁ እርግጡን መናገር ያስቸግራል።
“ማስተካከያ ሕጎችን”፣ “ማሻሻያ ደንቦችን”፣ “ማሟያ መመሪያዎችን”… በየጊዜው በቁጥ ቁጥ እያዘጋጁ ማምጣት የተለመደ ነው። በሳምንታት ውስጥ፣ ወይም በጥቂት ወራት፣ አለያም ከመንፈቅና ከዓመት በኋላ፣ የምንዛሬ ገበያው መልክና አሠራር ቀስ በቀስ እየተቀየረ ሊሄድ ይችላል። ፊቱ ወደ ግራ ይሁን ወደ ቀኝ፣ ወዴት አቅጣጫ እንደሚዞር መገመት ቢያስቸግርም፣… ሲውል ሲያድር፣ ብዙም ሳይቆይ፣ አንድ ሁለት እያሉ፣ የማሻሻያ አንቀጾችና ልዩ መመሪያዎች እንደሚመጡ ግን አትጠራጠሩ።
እንደ ሁኔታው ነው። በአንድ በኩል መንግሥት አሁኑኑ ከIMFና ከዓለም ባንክ ጋር መጣላት አይፈልግም። የለየት ጥል ይቅርና ኩርፊያም ጉዳት ይኖረዋል። በዶላር ዕጥረት ሳቢያ ከገደል አፋፍ ላይ የደረሰች አገር ምን ዐቅም ይኖራታል? ግንባራቸውን ከቋጠሩባት ምን ይውጣታል?
ለብድር የዘረጉትን እጅ እንደገና መልሰው ካጠፉ፣ ነገሩ ሁሉ “ፉርሽ” ይሆናል። ብድር ቢያቋርጡባት አይደለም ቢያዘገዩባትም እንኳ ትቸገራለች።
የተመደበውን ብድር እየወሰደች ካጋመሰች በኋላ፣… ለጊዜው ከዶላር ዕጥረት ትንሽ ፋታ ካገኘች፣… ከዓመት ከሁለት ዓመት በኋላ መንግሥት ምን ለማድረግ እንደሚወስን ማን ያውቃል? አሁን በጀመረው መንገድ “የምንዛሬ ገበያን” አጥብቆ መያዝና መቀጠል ይችላል። ከባድ ነው። ግን ይቻላል።
በሌላ በኩል ግን…. አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መገንባት ሲያምረው፣ ዶላር ሲቸግረው፣ በጀት ሲያጥረው፣ በአነስተኛ የምንዛሬ ተመን ከባንኮች ዶላር መውሰድ ሊያሠኘው ይችላል።
ለይቶለት ወደ ምንዛሬ ተመን ባይመለስ እንኳ፣ “የገበያ ማሻሻያ ደንቦችን” ወይም “ጊዜያዊ አስቸኳይ መመሪያዎችን” ማወጅ አያቅተውም። ምክንያትና ሰበብ አይጠፋም። “አገራዊ ፕሮጀክቶች”፣ “ወሳኝ የኢኮኖሚ ዘርፎች”፣ “ድሀ ተኮር ምርቶች”፣ “ሕዝባዊ ጥያቄዎች”… በልዩ አሠራርና በልዩ ተመን የዶላር ኮታ የሚያገኙበት መመሪያ ቁጥር 1 ቁጥር 2 እያለ ማውጣት ይችላል።
መቼም IMFና የዓለም ባንክ… “የምንዛሬ ገበያ ተነካ፣ ተጣሰ” ብለው ወዲያውኑ እንደማይጣሉት ቢያስብ ቢገምት ብዙም አይገርምም። ትችትና ቅሬታ ይሰነዝሩ ይሆናል። ለማኩረፍ ግን ጊዜ ሊፈጅባቸው ይችላል።
መንግሥት በዚህ ግምት ተማምኖ፣ የምንዛሬ ገበያውን ቀስ በቀስ ወደ ቀድሞው የምንዛሬ ተመን እያንሸራተተ ለማስጠጋት ቢሞክር ማን ይመልሰዋል? እንዲያውም “ሚዛኑን የጠበቀ የምንዛሬ ሥርዓት” የሚል የሙገሳ አስተያየት ሊቀርብለት ይችላል።
ችግሩ ምንድነው? የተቀየጠ የተቃወሰ የምንዛሬ ሥርዓት ሆኖ ሊያርፈው ይችላል።
ከሆነ አይቀር፣ “የገበያ ምንዛሬ” ብለው ከጀመሩት አይቀር፣ ያንኑን እያጣሩና ቅጥ አያስያዙ ለመጓዝ መጣር ይሻላል። በእርግጥ ዋናው ትኩረት ለሥራ የተመቸ አገርና ሥርዓት የመፍጠር ጉዳይ ነው። ኢንቨስትመንት እየተስፋፋ ኤክስፖርት የሚያድግበት ጸዳ ሥርዓት ነው ዋናው ቁም ነገር። እንደ አያያዛችን ሆነ ግን፣ ሁለመናችንን በጦርነት የተጠመደ ነው የሚመስለው። ጸዳ ያለ ሥርዓት ይቅርና አገርን ማረጋጋትና ሰላምን በወጉ መፍጠር አቅቶናል።

አንድ ተረት አለ። የኢንዶኔዢያ ሳይሆን አይቀርም።
አንዲት የመንደሩ ሰው ንብረት የሆነች በግ አልፋፋ ብላ ህዝቡ ሲጨነቅ፤ ሹሙ አዩና፤ ወደ አደባባዩ መጥተው፤ በውይይት መልክ፤ በኃይለ-ቃል ጠየቁ።
"ምንድን ነው ለዚች በግ ያስጨነቃችሁ"
የህዝቡ ተወካይም፤
"ማሳደግ አቃተን። ግጦሹ ተወደደ። የአራዳው ዘበኛ ያገኘችውን  እንድትግጥ እድል አልሰጥ እያለ አለንጋ ያቀምሳታል። እንዳናርዳት አልሰባች፣ እንዲሁ እንዳንተዋት ጣጣዋ ተረፈን! እንዲያው ምን ይመክሩናል ሹም ሆይ?"
ሹሙም፤
"ለምን እኔ ግቢ መጥታ አትፋፋላችሁም?" ሲሉ፤ ጫን ብለው ጥያቄውን በጥያቄ መለሱ። መቼም ሹም ናቸውና የሹም ጥያቄ በአሉታ አይመለሰም። ከፊሉ ህዝብ ጭጭ አለ። ከፊሉ እሺም እምቢም ማለቱ በማይገባ ቋንቋ ራሱን ነቀነቀ። ጥቂቱ "ይሁን፤ እንደርሶ ግቢ የሚመች የት ይገኛል። ግቢዎስ ግቢያችን አይደለም ወይ?!" አላቸው።
በጊቱ ሹሙ ግቢ ገባች።
ጊዜ እየገፋ መጣ። በጊቱ ግን አልወፈረችም። ጭራሽ እየከሳች መጣች። ህዝቡ ወደ ሹሙ ግቢ አሻግሮ እያየ "ኧረ እቺን በግ አክስተው ሊገድሏት ነው፤ ጎበዝ?" እያለ በየመንደር መናኸሪያው ያጉተመትማል። ደፈር ያለም ሹሙን ወይም ባለሟሎቻቸውን ይጠይቃል። በተለያየ ጊዜ የተለያየ መልስ ያገኛል።
አንዴ፤ "የቤተ መንግሥት አጥር እየታከከች እየዋለች ስላስቸገረች ግጦሽ ተከልክላ ነው" ይባላል።
አንዴ ደግሞ፤ "የንጉሥ ማሳ ገብታ በአፈ-ላማ ተያዘች" ይባላል፤
"አሞሌ ሲሰጧት የቀላቢዋንም እጅ ልሼ ካልበላሁ እያለች አስቀየመችውና ተቀጣች" ይባላል። ደሞ ሌላ ቀን፤ እንዳጋጣሚ ደግሞ ባለሟል ይመጣና እውነቴን ያወጣል፤ "አፏን ሸብበው ሳር-ማሳ እየከተትዋት እንዴት ትወፍር። በዚያ ላይ ከወፈረች የጠገበች ትመስላለች፤ የህዝብ ሀብት ስለሆነች እንደከሳች ብትቆይ ምን አለበት?  ትባላለች" ይላል።
ሌላ ውስጥ አዋቂ ይቀጥላል። "በተጨማሪም ደግሞ ከሌሎች በጎች ጋር ሲያዩዋት ታረግዝብናለች፣ "ወንድ" የወለደች እንደሁ ኋላ ምን ሊባል ነው፤ ሲሉ ነበረ" ብሎ ያጋልጣል። ጨመር አድርጎም፤ "ጎረቤትና የሩቅ አገር ሰው ሲመጣ ዐይን ትገባለች ብለው ገመድ ሆዷ ላይ ያስሩባታል" ብሎ ሚስጥር ያወጣል።
እንዲህ እንዲህ ስትባል፤ ቀን ገፋ። በሹሙ በኩል ያልፍልሻል፤ አይዞሽ ትጠግቢያለሽ፣ ስትባል፤ ህዝቡ በበኩሉ፣ ዘንድሮስ እንጃላት ሲላት፣ ገናን አለፈች። ፋሲካ ደረሰ።
ህዝቡ ከእንግዲህ መበያዋ ደረሰ ሲላት፣ ገናን አለፈች። ፋሲካ ደረሰ።
ህዝቡ እንግዲህ መበያዋ ደረሰ በቃ አለና አንገቱን ደፋ።
ይሄኔ አንድ ሽማግሌ የመጣው ይምጣ በሚል ድፍረት፤ ወደ ሹሙ ባለሟሎች ሄደው፤
"ኧረ እቺን በግ ሹሙ አክስተው ሲገድሏት ነው። መቼ ሊበሏት ነው?" ሲሉ ጠየቁ።
የባለሟሎቹ ተወካይም፤
"ገና ንጉሥ ፊት ቀርባ፤ አክሷት ባሉበት አፋቸው፣ ብሏት ያሉ እንደሆነ ነዋ!" አላቸው።

እንደ ከሲታዋ በግ ማደግ ያቃተው ዲሞክራሲያችን ያልታደለ ነው። እንደልብ ግጦሽ ሳር ማጣት የምስኪንነት ጥግ ነው። ደህና ግቢ ይግባ ሲባል በአፈ-ላማ ተይዞ፣ በቅጣት ታጥሮ፣ ግጦሽ ተከልክሎ፤ አፉ ተሸብሽቦ፣ ከተራበ አደጋ ነው ተብሎ፣ በJamming ታፍኖ፣ ከውጪ ሰውም ተከልክሎ… ከቶውንም ሊዘልቅ አይችልም። የፕሬስ ነፃነት "የተከለከለ የበሰለ ፍሬ" በሆነበት ቦታ የዲሞክራሲ ህልውና ቀርቶ ሽውታውም አይታሰብም።
በሀገራችን እንደ ምስኪኗ በግ የሆኑ ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ከዛሬ ነገ ይመለሳሉ ሲባል ጭራሽ "እነዚህ ጥያቄዎች የእኛ አልነበሩም እንዴ?" እስከሚባል ድረስ ከኦርጅናሌ ባለቤታቸው እጅ ይወጣሉ። የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥያቄዎች፣ በተለይም ደግሞ የፕሬስ ነጸነት ጥያቄ፣ ከከሲታዋ በግ በበለጠ እሰው ግቢ ገብቶ ቀልጦ የቀረ ይመስላል። ሰሚ ጆሮ፣ አዛኝ አንጀት ያገኘ አይመስልም። ይልቁንም "ጎራዴን እጀታውን የያዘ ያሸንፋል" የተባለው አነጋገር ዛሬ ከምንም ጊዜ የበለጠ ሚዛን ያነሳው በሱው ሰበብ ነው። "ስለቱን የያዙ ቢንጠለጠሉበት እጃቸውን ማጣት ይሆናል ዕጣ-ፈንታቸው። "ከእጃችን በቀር የምናጣው ነገር የለም" ካላሉ በቀር። ( We have nothing to lose except our chains እንዲሉ)
የተሄደበት መንገድ ሁሉ ወደዚያው ወደተነሳበት የሚመልሰን ከሆነ "ነገር ቢኖራችሁ ነው እንጂ፣ የማለዳው መንገድ ጠፍቶባችሁ ነው ወይ?" ያሰኛል።
አንድ ዘመን የአዲስ አበባ ሰው የኮክቴል ድግስ ሲጠራ ጠብ የሚልለት ነገር ሳይኖር በባዶ ሆዱ ዘፈን ብቻ እየሰማ፣ ሠርግ አጅቦ መመለሱ ልማድ ሲሆንበት "የድጋፍ ሠልፍ" የሚል ስም አውጥቶለት ነበር አሉ።
ለአሳታፊ ዲሞክራሲ ቁልፉ ግትርነት የሌለበትና "ስሜት ያልተጫጫነው" ውይይት ለማካሄድ መቻል ነበር ቢያድለን፤ ሆኖም ነገራችን ሁሉ "ቤቴን ሠርቼ ጣራ ስመታ ሆነ እንጂ ምክራችሁስ የሚወድቅም ነገር አልነበረው" ያለው ጮሌ ቤተ-ሰሪ ዓይነት ሆነ።
"ለዲሞክራሲያዊ ውይይቱ" ሁሉ የጦር ስትራቴጂ አውጥተን፣ አንዘልቀውም ብሎ ማሰብ የአባት ነው። ረዥምና ዘላቂ በሚመስለን ዕድሜያችን ውስጥ ምን እንደሚያጋጥመን ሳናውቅ የተከለከለ መንገድ፣ የተዘጋ በር፣ የታጠረ አዕምሮ፣ የተሸበሸበ አፍ፣ በጓጉንቸር ሽቦ የተለጠፈ ብዕር ይዞ ለሰላም፣ ለዲሞክራሲ፣ ለነፃነትና ለፍትህ የቆመ ፕሬስ ማለም፣ የማለም "ነፃነት" እንጂ የፕሬስ ነፃነት አይሆንም። ማለምም ተበርትቶ- መተኛት ከተቻለ ነው። ከቶውንም በስርጥ  መንገድም መጣ በቀለበት መንገድ፣ በአውራ  ጎዳናም መጣ በመጋቢ መንገድ፣ እንደብራ መብረቅም መጣ እንደ ነጎድጓዳማ ዶፍ፤ "ዝናብና አዋቂ ሲመጡ ያስተውላሉ" ነውና ዓይኑን ለከፈተ ዜጋ የቀጭን ትዕዛዛት አመጣጥ ይታየዋል። "ገና ንጉሥ ፊት ቀርባ አክሷት ባሉበት አፋቸው፣ ብሏት ያሉ እንደሁ ነዋ" እንደተባለችው በግ የመሆን ሥጋት ለተጋረጠበት የሀሳብ ነፃነት፤
"አቤት በሰማይ ያለ ምፅአት
አቤት በምድር ያለ መዓት" ቢለው፤ "የት አየኸው?"፣ "አመጣጡን መች አጣሁ" የሚለው ተረት ወቅታዊ ሆኗል። ከሁሉም ይሰውረን።



በገበያ ላይ ተመስርተው የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መሸጥና መግዛት የሚፈልጉ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲቋቋሙ በተፈቀደው መሰረት፣. ከሰሞኑ ብሔራዊ ባንክ የሥራ  ፈቃድ መስጠት ጀምሯል፡፡
ፈቃዱን ለማውጣት ዝቅተኛ 15 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በዝግ በየትኛውም ባንክ የተቀመጠ 30 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋል ተብሏል።
ባንኩ፤ “የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መቋቋም የውጭ ምንዛሪ ገበያን መሠረት ለማስፋትና ለማጠናከር እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ ለመሸጥም ሆነ ለመግዛት የሚሹ ደንበኞችን ፍላጎት ለማርካት እንደሚረዳ እሙን ነው" ብሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ፣ “የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች እንዲከፈቱ የሥራ ፈቃድ መስጠታችን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለውጭ ኢንቨስትመንት ለመክፈትና ዘርፉን በቀጣይ ዓመታት ከዓለም ምርጥ ተሞክሮዎችና አሠራሮች ጋር የተመጣጣነና ተወዳዳሪ ለማድረግ የጀመርነውን አዲስ ምዕራፍ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የጀመረውን ስትራቴጂካዊ የሆነ ለውጥ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት መነሣሣቱን የሚያመለከት ነው” ብለውታል።
በአፍሪካና በሌሎች ዓለማት  የግል የውጭ ምንዛሬ ቢሮዎች  አገልግሎት እንደሚሰጡ የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚሁ ቢሮዎች የራሳቸው ጥቅሞች እንዳሏቸው ባለሞያዎች ይናገራሉ። እንደምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ገለጻ፣ የግል ምንዛሬ ቢሮዎች ብዙውን ጊዜ ከባንኮች የተሻለ የምንዛሬ ዋጋ መስጠታቸው፣ ምቹ ቦታዎችን በመምረጥ ያለ ቢሮክራሲያዊ መዘግየት  ምንዛሬ መለዋወጥን ማስቻላቸው ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡
የምንዛሬ ዋጋዎች በፍጥነት ሊለዋወጡ ስለሚችሉ፣ እነዚህ ቢሮዎች ትርፋማነትን ለማስጠበቅ አደጋዎችን በብቃት መቆጣጠር እንዳለባቸው የሚናገሩት  ባለሞያዎች፣ ከውድድር ባለፈ በደንበኞቻቸው ዘንድ ተዓማኒነትን የማትረፍ የቤት ስራ አለባቸው ይላሉ፡፡ ከፍተኛ የአገልግሎት ክፍያዎችን የመጠየቅ፣ የቁጥጥር ማጣት፣ ተለዋዋጭ የምንዛሬ ተመኖችን ማውጣታቸውና ለማጭበርበር ወንጀል ክፍት መሆናቸው ከእነዚሁ ቢሮዎች ጉዳቶች ጥቂቶቹ መሆናቸው በምጣኔ ሃብት ባለሞያዎች ይነገራል። ደንበኞች ላደረጉት የምንዛሬ ልውውጥ በቂ ደረሰኝ ስለማያገኙ ለመጨበርበር ሊዳረጉ እንደሚችሉም ነው የተነገረው።
ናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ግብጽና ጋናን  ጨምሮ በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የግል የምንዛሬ ቢሮዎች አገልግሎት እንደሚሰጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

“ይህን ህገ ወጥ እንቅስቃሴ እንታገለዋለን”


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ “ይካሄዳል” ከተባለው የህወሓት ድርጅታዊ ጉባዔ ራሳቸውን እንዳገለሉ አስታውቀዋል። አቶ ጌታቸው ይህን ያስታወቁት ለህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) እና የፓርቲው ማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ሊቀ መንበር አቶ ተክለብርሃን አርአያ ትናንት በጻፉት ደብዳቤ ነው።
አቶ ጌታቸው “ከወራት በፊት ጉባዔውን ለማካሄድ ያቋቋምነው ኮሚቴ ከድርጅታችን መርህ እና አሰራር ወጥቶ በጥቂት ሰዎች ስለተጠለፈ፣ የማዕከላዊ ቁጥጥር ኮሚሽን ራሱን ከኮሚቴው አግልሏል” በማለት የኮሚሽኑን ዕርምጃ አውስተው፣ በዞን እና በወረዳ ደረጃ በርካታ አመራሮችና አባላት ከጉባዔው ራሳቸውን ማግለላቸውን ጠቅሰዋል። በዚህም የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ ድርጅታዊ ጉባዔ መቼ እና እንዴት እንደሚካሄድ አንድ ዓይነት አተያይ አለመኖሩን ያነሱት አቶ ጌታቸው፣ “ቅጥ የጎደለው” ያሉት እንቅስቃሴ ሕዝብን እና ድርጅታቸውን ወደ አደጋ የሚከት መሆኑን አመልክተዋል።
ፕሬዝዳንቱ በደብዳቤያቸው “የድርጅታችንን አሰራር እና አወቃቀር በመጣስ፣ አንድ አካል የራሱን ጠባብ ጥቅም ለማስጠበቅ በማሰብ ድርጅታችንን ወደማይወጣበት አደጋ ለመክተት እየጣረ ነው።” በማለት ስሞታቸውን አቅርበዋል። ይሁንና ስለዚሁ አካል ግልጽ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ማዕከላዊ ኮሚቴው በአዲሱ የምርጫ ቦርድ ዓዋጅ መሰረት፣ የተጭበረበረ እና ያልተፈረ ሰነድ ለቦርዱ ማቅረቡ “ተራ ስሕተት አይደለም” የሚሉት አቶ ጌታቸው፤ “የትግራይን ሕዝብ ትግል እና ድርጅቱን ለማፍረስ ሆነ ተብሎ የሚሰራ ቡድናዊ ዕንቅስቃሴ ነው” ብለዋል።
“ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የቀረበው የዕውቅና ጥያቄና በህወሓት ስም የሚደረገው የጉባዔ ዝግጅት በአንድ ቡድን የሚደረጉ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች በመሆናቸው ራሴን ከጉባዔው አግልልያለሁ” ሲሉ በጻፉት ደብዳቤ አትተዋል፤ አቶ ጌታቸው። አክለውም “እየተደረገ ነው” ያሉትን ዕንቅስቃሴ ለመታገል ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጉባዔውን ባለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ እንደሚያደርግ በሊቀ መንበሩ በደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በኩል ቢገለጽም፣ እስካሁን ጉባዔው አልተካሄደም። ነገር ግን በዞን እና በወረዳ ደረጃ የካድሬዎች እና የከፍተኛ አመራሮች የድርጅታዊ ጉባዔ ዝግጅት ውይይቶች እየተደረጉ ነው። ለአቶ ጌታቸው ረዳ ደብዳቤ፣ ከህወሓት በይፋ የተሰጠ ምላሽ የለም።

Page 10 of 726