Administrator

Administrator

 ከአንድ አመት በፊት በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ፤ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለትና በቅርቡ ግንባታው የተጠናቀቀው ‹‹ግሪን ላይት አውቶሜካኒክ” የስልጠና ማዕከል ረቡዕ ረፋድ ላይ በይፋ ተመረቀ፡፡ በኪያ ሞተርስና በኮሪያን ኢንተርናሽናል ኮኦፕሬቲቭ ኤጀንሲ (KOICA) ወጪው ተሸፍኖ፣ በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ የተገነባው ይሄው ማዕከል፤ ባለ 4 ወለል ህንፃ ሲሆን ኢትዮጵያዊያንን ወጣቶች በአውቶሜካኒክ ስልጠና ወስደው ባለሙያ የሚሆኑበት ነው ተብሏል፡፡
ህንፃው ለአውቶ ሜካኔክና ለእጅ ስራ ሙያ ስልጠና የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ያሟላ ሲሆን በቀጣይም በተጨማሪ ቁሳቁሶች ተደራጅቶ በአጠቃላይ ለ615 ወጣት ወንዶችና ሴቶች ስልጠና ይዘጋጃል ተብሏል፡፡ በቀጣዩ ግንቦት ስልጠና መስጠት ይጀምራል የተባለው ማዕከሉ፤ የህንፃውን ግንባታ ጨምሮ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ፕሮጀክት ሲሆን 220 ወጣቶችን በአውቶ ሜካኒክ፣ 395ቱን ደግሞ በእጅ ስራ ሙያ አሰልጥኖ፣ ራሳቸውን እንዲችሉ የማድረግ እቅድ ይዟል፡፡ ማዕከሉ የራሱ የአስተዳደር ቁመናና ስርዓተ ትምህርት እየተቀረፀለት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ስድስት የመማሪያ ክፍሎች፣ ሶስት ወርክሾፖች፣ አምስት ቢሮዎች፣ አምስት የእቃ ማከማቻ ክፍሎች፣ ሁለት የመምህራን ቢሮዎች፣ አንድ የICT ክፍል፣ አንድ ቤተ መፅሀፍት፣ አንድ ጋራዥና አንድ ላውንጅ አሟልቶ የያዘም ነው ተብሏል ህንፃው፡፡ በዚህ ማዕከል በአውቶ ሞቲቭ ኢንጂን በሌቭል 1 እና በሌቭል 2 በፓወር ትሬይንም እንዲሁ በሌቭል 1እና ሁለት ስልጠና የሚሰጠው ማዕከሉ በቀጣዩ ግንቦት በሁለት ዙር ስልጠና ለመስጠት ሰልጣኞችን መመዝገቡን አስታውቋል፡፡
በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የወርልድ ቪዥን ካንትሪ ዳይሬክተር ኤድዋርድ ብራውን ባደረጉት ንግግር፤ “ካንትሪ ዳይሬክተር ሆኜ ከተሾምኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የጎበኘሁት ትልቅ ፕሮጀክት በመሆኑ ለእኔ ትልቅ በዓል ነው” ብለዋል። ሌላው በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ በእንግድነት የተገኙት የአዲስ አበባ ቴክኒክ፣ ሙያና ትምህርት ስልጠና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ዘሩ ስሙር፤ ኮሪያና ኢትዮጵያ ባላቸው ታሪካዊ ግንኙነት በእጅጉ ኢትዮጵያን እየደገፉ መሆኑን ጠቁመው መንግስት በቴክኒክና ስልጠና በርካቶችን ተጠቃሚ እያደረገ ቢሆንም ሁሉንም ስለማያዳርስ እንዲህ አይነት ድርጅቶች የሚያደርጉት ድጋፍ ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡ የኮሪያ አምባሳደር በኢትዮጵያ ሚስተር ሙን ሁዋን ኪም ኢትዮጵያ ለኮሪያ ባለውለታ በመሆኗ ይህን ውለታ ለመመለስ ብዙ ምክንያቶችን እንፈልጋለን፤ ይሄም ፕሮጀክት ውለታ ለመመለስ አንዱ መንገድ ነው ብለዋል፡፡ ማዕከሉ ለሚያከናውነው የ5 ዓመት ፕሮጀክት፤ የ2.5 ሚ ዶላር (57.8) በጀት ተይዞለታል ተብሏል፡፡

 አዲስ አልበሙን አስተዋወቀ

     በኢትዮጵያ ሙዚቃ ወርቃማ ዘመን ለ25 ዓመታት በልዩ ብቃት ዘመን ተሻጋሪ የሙዚቃ ስራዎችን ለአድማጮች ያቀረበው ከያኒ ግርማ በየነ ባለፈው ማክሰኞ በብሔራዊ ቴአትር ከ ‹‹አካሌ ውቤ›› ባንድ ጋር ያቀረበው ኮንሰርት አስደሳችና አዝናኝ እንደነበር ታዳሚያን ገለፁ፡፡ ድምፃዊ፣ የሙዚቃ ቀማሪና አቀናባሪ እንዲሁም የፒያኖ ተጫዋች የሆነውና ለረጅም አመታት በአሜሪካ በስደት የቆየው አንጋፋው ከያኒ፤ ከሙዚቃው ተራርቆ የከረመ ሲሆን ወደ ሙዚቃው የተመለሰው ከሁለት ዓመት ወዲህ መሆኑ ተገልጿል፡፡
በታዋቂው የሙዚቃ ሰው ፍራንሲስ ፋልሴቶ አነሳሽነት በግንቦት 2016 ፓሪስ በሚገኘው ‹‹ላ ኤሪ ቴጅ›› የተባለ ስቱዲዮ ግርማ በየነ ‹‹አካሌ ውቤ›› ከተሰኘው የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ቡድን ጋር ‹‹ኢትዮፒክስ 30 ሚስቴክስ ኦን ፐርፐዝ›› የተሰኘውንና 14 ዘፈኖችን ያካተተው አልበሙን ያሳተመ ሲሆን፣ ባለፈው ማክሰኞ ያቀረበው ኮንሰርትም ይህንኑ አልበም ለማስተዋወቅ ያለመ እንደነበር ታውቋል፡፡ ለአርቲስቱ የመጀመሪያው ሙሉ አልበሙ ነው ተብሏል፡፡ ግርማ አልበሙን ለማስተዋወቅ ባዘጋጀው ኮንሰርት፤ ከ‹‹አካሌ ውቤ›› ባንድ ጋር አስደናቂ ትርኢት ያሳዩ ሲሆን በተለይ ግርማ በድምፅ ብቻ ሳይሆን በፒያኖ ችሎታውም ብዙዎችን አስደንቋል፡፡ አርቲስቱ በ1960ዎቹ፣ ከ60 በላይ የሙዚቃ ቅንብሮችን የሰራ ሲሆን ግሩም የግጥምና ዜማ ደራሲም ጭምር እንደነበር ይነገርለታል፡፡ በብሔራዊ ትያትር ቤት ባቀረበው ኮንሰርት ‹‹እንከን የሌለሽ››፣ ‹‹ካንቺ ወዲያ ሴት አላምንም››፣ ‹‹ፍቅር እንደክራር››፣ ‹‹ፅጌረዳ››፣ ‹‹መስሎን ነበር››፣ ‹‹ሙዚቃዊ ስልት›› የተሰኙትን ጨምሮ በርካታ ስራዎቹን በመጫወት አድናቆት የተቸረው ሲሆን ‹‹የድምፁ አለማርጀት›› ለብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ አምሽቷል፡፡ በኮንሰርቱ ላይ ስለፍቅር አብዝቶ የሰበከው ድምፃዊው፤ ከኢትዮጵያ ሴት ድምፃዊያን ሄለን በርኼ በተለይ ‹‹አታስፈራራኝ›› ለሚለው ዘፈኗ ያለውን አድናቆት በአደባባይ ገልጿል፡፡
ግርማ በየነ ከዚህ ቀደም ‹‹ዘራፍ››፣ ‹‹ጋይድ ቱ ሚዩዚክ ኦፍ ኢትዮጵያ››፣ እ.ኤ.አ በ2004 ‹‹በወርልድ ሚዩዚክ ጌት ወርክ›› አሳታሚነት ‹‹ኢትዮፒክስ ቁጥር 8››፣ ‹‹ስዊን ጊንግ አዲስ››፣ በቡዳ ሚዩዚክ አሳታሚነት ደግሞ ‹‹ኢትዮፒክስ 22›› በተሰኙ አልበሞች ላይ ተሳትፏል፡፡ አርቲስት ግርማን ያጀበው ‹‹አካሌ ውቤ›› የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ቡድን፤ በፈረንሳይ ሙዚቀኞች የተደራጀ ሲሆን ከ74 በላይ የሙዚቃ ኮንሰርቶችን በዓለም ዙሪያ ማቅረቡ ታውቋል፡፡ ከወራት በፊትም በፈረንሣይ ከታዋቂው የፒያኖ ተጫዋች ሀይሉ መርጊያ ጋር በ ‹‹ስቱዲዩ ዴላ ኤል ሚቴጅ›› ታላቅ የሙዚቃ ዝግጅት ማቅረባቸው ተጠቁሟል፡፡

 እኻ ቲያፈኳን ኧኳዳር አት ኧደንግር ባነ ባረም) የቤተ ጉራጌ ተረት
ከኤዞፕ ተረቶች አንዱ እንዲህ ይለናል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን፣ አንድ ሰው ክፉኛ ይታመምና ቤቱ ይተኛል፡፡ የመንደሩ ሰው ሁሉ የሚበላም የሚጠጣም እያመጣ በየተራ ይጠይቀዋል፡፡
“አቶ እገሌ” ይላል ጠያቂ
“አቤት” ይላል ተጠያቂ
“ዛሬስ እንዴት ነህ?”
“ከትላንቱ ይሻለኛል”
“ሐኪም ዘንድ ሄደህ ነበር?”
“አልሄድኩም”
“ታዲያ ከትላንቱ እንደተሻለህ በምን አወቅህ?”
“የታመምኩት እኔ አይደለሁ፡፡ ሰውነቴ ይነገርኛልኮ”
“ደህና እንኳን ለዚህ አበቃህ!”
ጠያቂዎቹ ተሽሎታል ብለው ሰውየውን ለመጠየቅ መምጣታቸውን ያቆማሉ፡፡ ሰውዬው ግን ካልጋው አልተነሳም፡፡ “እስቲ እንሂድና እንየው፡፡ ይሄ ሰው ለምን አልተነሳም” ብለው ቤቱ ቢሄዱ እዚያው እንደተኛ አገኙት፡፡
“አያ እገሌ” ይላል ጠያቂ
“አቤት” ይላል ተጠያቂ
“ዛሬስ እንዴት ነህ፡፡ እኛ’ኮ ተሽሎኛል ስትል፣ ትነሳለህ ብለን ነው የቀረነው፡፡ ዛሬ እንዴት ነህ?”
“ከትላንቱ ይሻለኛል”
“ባለፈውም ዛሬ እንዴት ነህ ስንልህ ከትላንቱ ይሻለኛል ብለኸን ነበር፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?”
“እዚህ አገር ከትላንቱ ይሻለኛል የማይል ማን አለ?”
“እንደዚህ ከሆነ ሐኪም ቢያይህ ነው የሚሻለው” ብለው ሐኪም ይጠሩለታል፡፡ መድኃኒት አዞለት ይሄዳል፡፡ መድኃኒቱን ይወስዳል፡፡
በነጋታው ሐኪሙ ይመጣል፡፡
ሐኪሙ - “እንዴት ነህ?” ይለዋል፡፡
በሽተኛው - “ደህና ነኝ ዶክተር፡፡ ግን በጣም ያልበኛል”
ሐኪሙ - “ይሄ በጣም ጥሩ ምልክት ነው” ይለውና ይሄዳል፡፡
በሚቀጥለው ሐኪሙ ይመጣል፡፡
“እህስ አሁንስ እንዴት ነህ?” ይለዋል፡፡
በሽተኛው - “ተሽሎኛል፡፡ ግን እዚህ መገጣጠሚያዬ ላይ ይቆረጥመኛል፡፡ ያንቀጠቅጠኛል፡፡ ከዚያ ሰውነቴ በሙሉ በረዶ ይሆናል፡፡”
ሐኪሙ - “ይሄም በጣም ጥሩ ምልክት ነው” ብሎት ይሄዳል፡፡
ሐኪሙ ሌላ ቀን ይመጣል፡፡
“እህ ዛሬስ እንዴት ነህ?” ይለዋል በሽተኛውን
በሽተኛው - “ደህና ነኝ ግን አሁን ደግሞ ኃይለኛ ትኩሳት ለቆብኛል” ብሎ ይመልሳል፡፡
ሐኪሙም - “ኦ ይሄም በጣም ጥሩ ምልክት ነው፡፡ በጣም እየተሻለህ ነው ማለት ነው” ብሎት ይሄዳል፡፡
ከሠፈሩ ሰው አንዱና ወዳጁ የሆነው ሰው ከህክምናው በኋላ ምን ለውጥ እንዳመጣ ሊጠይቀው ይመጣል፡፡
ጠያቂ - “እሺ አያ እገሌ፡፡ ሐኪሙ ካየህ በኋላ እንዴት ሆንክ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
በሽተኛውም - “ወዳጄ አያድርስብህ፡፡ “በጣም ጥሩ ምልክት” ሊገለኝ ነው!”
***
እየተሻለኝ ነው እያለ ከሚሞት፣ “በጣም ጥሩ ምልክት ነው” እያለ ከሚገድል ይሰውረን፡፡ ‹‹ደግ ደጉን ማውራት የተሻለ ዓለም ለማየት ይጠቅማል›› የሚለው ብሂል እንደተጠበቀ ሆኖ፤ እየከፋ ያለን ጉዳይ እየተሻሻለ ነው ማለት ግን እያወቁ ማለቅ ዓይነት ነው፡፡ ‹‹ዕውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር ››ለአገርና ህዝብ ይበጃል እንጂ ጐጂ አይደም፡፡ “የማይሰጋ ተስፋ የሌለው ሰው ነው” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ “አይመጣምን ትተሽ ይመጣልን ጨምሪበት” የሚሉት ነው አበሾች፡፡ በየኑሮ መስኩ ያለውን ህመም፣ በየሙያ መስኩ ያለውን ተወሳክ፣ በየፖለቲካ መስኩ ያለውን ወረርሽኝ በጊዜ መመርመር ዋና ነገር ነው፡፡ እኛ የወደድነውን እያጐላን በየሚዲያው ብንለፍፍ ለሀገርና ለህዝብ ፋይዳ ያለው ላይሆን ይችላል፡፡
አንድ ፀሐፊ ስለጋዜጠኝነት ሲጽፍ “ዋናው የሙያው ቁልፍ - ነገር…
አስፈላጊውን ነገር ተወዳጅ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ እኛ ግን የወደድነውን፤ አስፈላጊ ፋይዳ እንዲኖረው የማድረግ አደገኛ ተግባር ላይ ነን (Make the important interesting but we are in a danger of making the interesting important) ያለውን በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፣ በማህበራዊ ዘርፍም መንዝረን ብናየው ይጠቅመናል፡፡
ዕውነትን መናገር በሽታን ከመደበቅ ያድናል፡፡ ሳይሻለን ተሻለን፣ ሳንድን ድነናል ከማለት ያድነናል፡፡ ከትላንት የተማርን ከማስመሰል ያወጣናል፡፡ ሰፈር - ሙሉ ሰው ከማሳሳት ያተርፈናል፡፡
በየዘመኑ ነባራዊ ዕውነታን ለራስ በሚያመች መልኩ በመቅረጽ ‹ዕውነቱ ይሄ ነው› እያሉ ለማሳመን መጣር የተለመደ ዘዴ ነው፡፡ ላንዳንዶች የአገዛዝ መላ ነው፡፡ ላንዳንዶች ከጣር ማምለጫ ነው፡፡ ኒክ ዴቪስ የተባለው ፀሐፊ ዕውነት እንዳንናገር የሚያደርጉን ሦስቱ ገዳይ ድክመቶች (1) የምንመርጣቸው ርዕሰ ጉዳዮች ዕውነታውን በመሠረታዊ መንገድ የሚያፋልሱት እንዲሆኑ በማድረግ ዋናውን ጭብጥ ማሳት፤
2) በተደጋጋሚ የምንጠቀምባቸውን ኢተአማኒ፣ አንዳንዴም ፈጽሞ ውሸት፣ የሆኑ ጭብጦች ደጋግመን በመጠቀም ዕውነተኛ ማስረጃዎች እንዲመስሉ ማድረግ፤
3) ከአካባቢው ህብረተሰብ መካከል ኃይለኛ ጉልበት ያላቸውን ወገኖች የሚያደምቁ ዕሴቶችን የማያቋርጥ አሻራ እንዲኖራቸው ፖለቲካዊና ሞራላዊ ውትወታን ማብዛት፤
ናቸው፤ ይለናል፡፡
ስለ ዛሬ ጤንነታችን ስንጠየቅ፣ ስለትናንት በሽታ ብናወራ የምናገኘው ጠቀሜታ ራስ ተኮር እርካታ ካልሆነ በቀር፣ ደርዝ ያለው ነገር አገር አንጀት ላይ ጠብ አያደርግም፡፡
ራሳችንን ከዛሬ ሥራችን፣ ከዛሬ ትልማችን፣ ከዛሬ ዕውቀታችን፣ ከዛሬ ውጤታችን ጋር እናመዛዝን፡፡ ህዝብ እየወደደኝ ነው እየሸሸኝ፣ እየሰለቸኝ ነው እየረካብኝ፣ የተናገርኩት እንደ ‹‹ቡመራንግ›› ተመልሶ እኔኑ እየወጋኝ ነውን? ዕውነተኛ ደጋፊ እያፈራሁ ነውን? ዕውነተኛ ተቃዋሚ አለኝ?
ኢንፎርሜሽን የሥልጣኔ መሠረት የሆነበት ዘመን ላይ ነን፡፡ ኢንፎርሜሽን የሚደብቅ በሽታውን ከደበቀው ሰው አይለይም፡፡
ሌላው ዓለም ዛሬ፤ የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች የዜና ምንጭ ሊሆኑ እንደማይችሉ፣ የመረጃ ፍሰትን እንደሚያደናቅፉ እየተሟገተ መሆኑን አንርሳ፡፡
“የህዝብ ግንኙነት ዲሞክራሲ” (ኤሮን ዴቪስ) በተባለው መጽሐፍ ከጥናት የተገኙ ድምዳሜዎችን እንዲህ ያስቀምጣቸዋል:- “ለሚዲያ ከሚሰጡ መረጃዎች ተለይቶ የሚደበቅ አንድ መረጃ ሁሌ ይኖራል፡፡ በብዙ ድርጅቶች ውስጥ ያሉት የህዝብ ግንኙነት ሠራተኞች ግማሹ ወይም አብዛኛው ሥራቸው፤ ጋዜጠኞች መረጃ እንዳያገኙ ማድረግ ነው፡፡ አንዳንዴም ያለውን እንደሌለ ማድረግ፣ ስለ ድርጅቱ ክፉ ክፉ ወሬ ካለ ጨርሶ መደምሰስ (መሸምጠጥ) ነው ሥራቸው፡፡” ቢሮዎች፣ የቢሮ መሪዎችና ሠራተኞች፤ የፖለቲካ ሰዎች፤ ለኢንፎርሜሽን፣ ኢንፎርሜሽን ቢሉም ለዕውነተኛ ኢንፎርሚሽን፤ በራቸው ክፍት ሊሆን ይገባል፡፡ ልባቸውም እንደዚያው፡፡
ቼስተርተን የተባለው ፀሐፊ ያለውን ነገር ከልባችን ባናወጣው መልካም ነው፡፡
“እራት ላይ የሚቀርብ ሙዚቃ፤ ምግብ አብሳዩንም፣ ሙዚቀኛውንም እንደመስደብ ነው፡፡”
ባንድ ጊዜ ሁለት ተበዳይ ከሚኖርበት ሥርዓት ይሰውረን፡፡ ያም ምግቡ ሳይጣጣምለት፣ ያም ሙዚቃው ሳይሰማለት፣ መቅረቱ የሙያ ብክነት ነው፡፡ ከሁሉም በላይ ግን፤ ከምግቡም ከጥበቡም ያልሆነው የግብር ታዳሚ ህዝብ ያሳዝናል፡፡ ይህንን ልብ ያላለ ታዳሚ ሁለተዜ ጥፋት ላይ ወደቀ ማለት ነው፡፡ ሙዚቀኛ ሳይሰማ እየተሰማሁ ነው ካለ፣ ምግብ አብሳዩ ህዝቡ እየበላ ነው ካለ፣ ታዳሚው ሙዚቃ እየሰማሁ፣ ምግብ እየበላሁ ካለ ተያይዘው ጠፍተዋል፡፡ እየታመመ ተሻለኝ፣ እየተቸገረ ኖርኩኝ የሚል “ሸማኔ ውሃ ሙላት ሲወስደው እስካሁን አንድ እወረውር ነበር አለ” እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ ከ20ኛ ፎቅ ላይ እየወደቀ ሳለ 8ኛ ፎቅ ያሉ ሰዎች እንዴት ነህ? ቢሉት፤ “እስካሁን ደህና ነኝ” አለ እንደተባለው ሩሲያዊ ብናስበውም ያስኬደናል፡፡ “እንዳካሄድ” አደል መንገዱ ሁሉ!

 “ህጋዊዎቹ ባልተለዩበት የሚደረግ ድርድር የህገ መንግስት ጥሠት ያስከትላል”

      የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ መሰፈርት አሟልተው እየተንቀሣቀሱ ነው ያላቸውን 5 ሃገር አቀፍ ፓርቲዎች ማንነት በዝርዝር እንዲያሣውቅ መኢአድ እና ሠማያዊ በደብዳቤ ጠይቀዋል፡፡
ቦርዱ ግንቦት 17 ቀን 2009 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ፤ በሃገር አቀፍ ደረጃ ከሚንቀሳቀሱ 22 ፓርቲዎችና በክልል ከሚንቀሳቀሱ 40 ፓርቲዎች መካከል በተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ መሠረት፤ ህጋዊ መስፈርት ያሟሉት 5 ሃገር አቀፍና 5 ክልላዊ ፓርቲዎች ብቻ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
ሆኖም ቦርዱ የትኞቹ ፓርቲዎች ህጋዊነቱን እንዳሟሉና እንዳላሟሉ በዝርዝር የገለፀው ነገር የለም፡፡
ይሄን ተከትሎ ሠማያዊ እና መኢአድ፤ የትኞቹ ፓርቲዎች ህጋዊ እንደሆኑ አለማሣወቁ በወደፊት እንቅስቃሴያችን ላይ አሣሣቢ ችግር ይፈጥርብናል” በሚል ቦርዱ ማብራሪያ እንዲሠጣቸው የጠየቀ ሲሆን፤ ህጋዊዎቹ ህጋዊ ካልሆኑት ሣይለዩ ከገዥ ፓርቲ ጋር የሚደረገው ድርድርም ትርጉም እንደሌለው መኢአድ ለአደራዳሪ ቦርድ ፅ/ቤትና ለምርጫ ቦርድ በላከው ደብዳቤ አስታውቋል፡፡
“ህጋዊ መስፈርት አሟልተው ካልተገኙ ፓርቲዎች ጋር ለድርድር መቀመጥ የህገ መንግስት ጥሠት የሚያስከትልና የህዝብን ጥያቄ የሚያዳፍን በመሆኑ በአፋጣኝ ምርጫ ቦርድ ማብሪያ እንዲሠጥበት መኢአድ በደብዳቤው ጠይቋል፡፡
ማብራሪያው ባልተሠጠበትና ህጋዊች ተለይተው ባልተገለፁበት ሁኔታ ድርድሩን ማካሄድ እንደማይቻልም መኢአድ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሠጥ ላለፉት ሁለት ሣምንታት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሊሳካልን አልቻለም፡፡

 1700 ስደተኞች በ20 ዩኒቨርሲቲዎች በነፃ እየተማሩ ነው

     ከ850 ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞችን ማስተናገዷ ያስመሰገናት ኢትዮጵያ፤ የዘንድሮውን የዓለም የስደተኞች ቀን በዓል የተመድ የስደተኞች ኮሚሽነር በተገኙበት የፊታችን ማክሰኞ በጋምቤላ ታስተናግዳለች ተብሏል፡፡ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ስደተኛ በማስተናገድ ከአፍሪካ ቀዳሚ የሆነችው ኢትዮጵያ፤ በስድስት የሀገሪቱ ክልሎች 27 የስደተኛ መጠለያዎችን አቋቁማ ማስተናገዷ እውቅና ተሰቶት “we
stand together with refugees” በሚል መሪ ቃል የሚከበረውን በዓል እንድታስተናግድ እድል ማግኘቷን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
“ስደተኞች እንደሀገሬው ዜጎች የሚኖሩባት ሀገር ነች ኢትዮጵያ” ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ በ20 ዩኒቨርሲቲዎች ለ1700 ስደተኞች ነፃ የትምህርት እድል ተሰጥቷቸው በመማር ላይ መሆናቸውንም አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ በአሉን እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በአለም አቀፍ ደረጃ ከስደት ጋር ተያይዘው እየተከሰቱ ባሉ ችግሮች መፍትሄ ዙሪያ ኃላፊነት በመሸከም ችግሩን ለማጋራት ባሳየችው ቁርጠኝነት ነው ተብሏል፡፡

     5G የቴሌኮም አገልግሎት አቀርባለሁ ብሏል

      የቻይናው የቴሌኮም ኩባንያ ዜድቲኢ በኢትዮጵያ፤ የቴሌኮም ምርምርና ፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም የሚያስችለውን ስምምነት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር መፈራረሙን አስታወቀ። በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ የመጀመሪያው ነው የተባለው የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከሉ፤ አዳዲስ የቴሌኮሚኒኬሽንና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አማራጮችን እዚሁ ሀገር ቤት በመፍጠር ለተጠቃሚዎች ያቀርባል ተብሏል፡፡
የምርምርና ፈጠራ ተግባር ከሚያከናውንባቸው ዘርፎች መካከልም በገመድ አልባ ኢንተርኔትና የስልክ ግንኙነቶች፣ የኔትዎርክ ሽፋንና ጥራትን የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ምርምርና ፈጠራ እንዲሁም በሀገሪቱ የተዘረጋውን የቴሌኮም መዋቅር የሚያሻሽሉ ቴክኖሎጂዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ከሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከሎች ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል የተባለውና በ3 ሺህ ስኩየር ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፈው የፈጠራ ማዕከሉ፤ ከኢትዮጵያ አልፎ ለአፍሪካ የሚተርፍ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ያፈልቃል ተብሏል፡፡ በተመሳሳይ ኩባንያው የ5ኛው ትውልድ (5G) የቴሌኮም አገልግሎትን በኢትዮጵያ ለማቅረብና ለማስፋፋት እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከተመሰረተ 25 አመት ሞልቶታል። በዚህ 25 አመት ጊዜ ውስጥ ምን ሰርቶአል? ሲባል ብዙ ክንውኖችን ማሳካቱ 25ኛ አመቱን ሲያከብር ተወስቶአል።
ለማስታወስ ያህልም ፡-
በስነተዋልዶ ጤና የሚያገለግሉ ሙያዊ ትንተናዎችን ለማቅረብ በአገር ደረጃ በሚዋቀሩ የተለያዩ ኮሚዎች ውስጥ በመሳተፍ ሁነኛ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጎአል።
ባለፉት 25 አመታት ከ20 በላይ የሆኑ እጅግ ተጠቃሽ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር አከናውኖአል።
ኤችአይቪ ከእናት ወደልጅ እንዳይተላለፍ ለመግታት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምና እንዲሰጥ ከማድረግ አኩዋያ ወደ 70 የሚሆኑ የህክምና ድርጅቶች ውስጥ የሚገኙ ባለሙያዎችን ማሰልጠንና በተጨማሪም ክትትል በማድረግ የበኩሉን ሚና ተጫውቶአል።
በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችን በማዋለድ ተግባር ላይ የተሸለ ክህሎት ኖሮአቸው በተለይም በኦፕራሲዮን መውለድ የሚያስፈልጋቸውን እናቶች ከመደገፍ አኩዋያ ቁጥራቸው ወደ 47 ለሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቶአል። ይህ ስልጠና እስከ 6 ወር የደረሰ ተከታታይ ስልጠና ሲሆን በተለይም እስፔሻሊስት ሐኪሞች በማይገኙበት ቦታ ለወላድ እናቶች ባለሙያው አስፈላጊውን እገዛ ሊያደርግ የሚችልበት ስራ ተሰርቶአል። በዚህም ፕሮጀክት እስከ መቶ ሺህ እናቶች ተጠቃሚ ሆነዋል።
በወሲባዊ ጥቃት እና ትንኮሳ ዙሪያ በተለይም ሴቶች ጥቃቱ ከደረሰባቸው በሁዋላ ተገቢውን ሕክምና እንዲያገኙ እና ክትትል እንዲደረግላቸው የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን በአዲስ አበባና በተለያዩ መስተዳድሮች ዋና ዋና ከተሞች ውስጥ 6 ሞዴል ክሊኒኮችን በመመስረት ደረጃውን የጠበቀ ሕክምናና እንክብካቤ እንዲያገኙ አድርጎአል።
በማደግ ላይ ባሉ ክልሎችና በአርብቶ አደሮች አካባቢ የማህረሰቡን የስነተዋልዶ እውቀ ትና ግንዛቤ ከማሳደግ አኩዋያ የሚሰሩ ስራዎች ያሉ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ሙያተ ኞች እርህራሔንና ተገቢ የሆነን የህክምና እርዳታ ለተገልጋዩ ለማዳረስ የሚችሉበትን ስልጠና ማህበሩ በመስጠት ላይ ነው።
ማህበሩ ከ20 በላይ የሚሆኑ ሙያነክ መመሪያዎችን በማዘጋጀት ደረጃውን የጠበቀ ግልጋሎት ለማህበረሰቡ እንዲሰጥ ሲያደርግ ቆይቶአል።
ከላይ ያነበባችሁት እውነታ በማህበሩ ፕሬዝዳንት ዶ/ርደረጀ ንጉሴ የተገለጸ ነው። የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር በ25 አመታት ውስጥ እንዳካበተው ልምድ አሁንም የእናቶች ንና ጨቅላዎቻቸውን ጤንነትና ሕይወት ለመጠበቅ የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ነድፎ ከተለያዩ ድጋፍ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በመስራት ላይ ይገኛል።በኢትዮጵያ እናቶች በሰለጠነ የሰው ኃይልና በተገቢው ደረጃ በጤና ተቋም አገልግሎት እንዲያገኙ ያስፈል ጋል ሲባል አንዳንድ እንደችግር የሚታዩ ነገሮችን መንቀስ ወይንም እንዲወገዱ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህንንም በሚመለከት ከታቀዱ ስራዎች መካከል ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር የሚሰራው ይገኝበታል።
 በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ አዳዲስና ነባር ዩኒቨርሲቲዎች በጠቅላላ ሐኪምነት ሙያ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በልዩ ሙያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምናን በማሰልጠን ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን እነዚህ የተለያዩ ተቋማት በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ስለማይገኙ አገሪቱ የምታፈራቸው ባለሙያዎች የተለያየ ደረጃ እንዲኖራቸው ስለሚያደርግ ጥራት ያለው እና በተመሳሳይ ደረጃ ብቃት ያለው ሕክምና ከመስጠት አኩዋያ ክፍተት እንዲመጣ ያደርጋል። ስለዚህም ይህንን ክፍተት በዋነኛነት በተሻለ ደረጃ መሙላት አስፈላጊ ሲሆን ይህንንንም የትም ህርት እና ሙያ ጥራትና ብቃት ለማምጣት እንዲያስችል የፌደራል ጤና ጥበቃ ሚኒስ ር በአምስት አመቱ የጤናው እቅድ ውስጥ እንዲካተት አድርጎታል። ከዚህም በመነሳት የማህ ጸንና ጽንስ ሕክምና ተማሪዎች በተሻለ ዝግጅት ሰልጥነው እንዲወጡ ማድረግና ስራ ላይ ያሉ ደግሞ የተሻለ ተከታታይ ትምህርት እንዲያገኙና ከዚህ በሁዋላ በእነዚህ ዝግጅቶች አማካ ኝነት ለተገል ጋዩ ሕዝብ ጥራቱን የጠበቀ ግልጋሎት መስጠት እንዲያስችላቸው ማድረግ አንዱ ግብ ነው።
የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ጋር በመተባበር ለመስራት እቅድ ከያዘባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ ሐኪሞችን በብቃት እና በተመሳሳይ ደረጃ ማስተማር በመሆኑ በፈረንጆቹ አቆጣጠር ጁን 5-6 ማለትም ግንቦት 28 -29 በአዲስ አበባ በተለያዩ መስተዳድር የሚገኙ ከ12 ድህረ ምረቃ ተቋማት ለተወከሉ የድህረ ምረቃ ዳይሬክ ተሮች ለሆኑ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ስልጠናውን ሰጥቶአል። እንደ ዶ/ርባልካ ቸው ንጋቱ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ኮሌጅ መምህርና ተባባሪ ፕሮፌሰር የጽን ስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት የድህረ ምረቃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ገለጻ የድህረ ምረቃው ትምህርት በየተቋማቱ በተለያየ መንገድ ይሰጥ የነበረ ሲሆን መመራት ያለበት ግን በራሳችን ሀገራዊ ሁኔታ በመመስረት የፕሮግራሙን ባህል ሳይለቅ ነገር ግን መሰረታዊ የሆኑ ሳይንሳዊ ነገሮችን ሁሉም ጋ አንድ አይነት ለማድረግ ነው የስልጠናው ዋና አላማ።
በተለይም ስልጠናው ያስፈለገበት ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ በሚካሄዱ የማህጸንና ጽንስ ድህረ ምረቃ ትምህርቶች ላይ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎች መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጡ እና ትምህ ርቱ አግባብ ባለው መንገድ በመላ ሀገሪቱ ባሉ የትምህርት ተቋማት ወጥ የሆነ የትምህርት ሂደት እንዲኖራቸው ለማገዝ ነው። በዚህ ረገድም ለስልጠናው የተጋበዙት የየፕሮግራሙ ዳይሬክተሮች ሲሆኑ ለስልጠናውም ከአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ትምህርት ኮሌጅ ጋር በመተባበር ባለሙያዎች ተጋብዘው አስፈላጊውን ሳይንሳዊ እውቀት አስጨብጠዋል። ይህ ስልጠና በድህረ ምረቃ ትምህርት ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ነገሮችን በምን አይነት መንገድ ሁሉም ቦታ ያሉ የድህረ ምረቃ አስተባባሪዎች መያዝ አለባቸው የሚለውን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በማሳየት ከድህረ ምረቃ ተማሪዎች አቀባበል እስከ ተመርቆ መውጣት ድረስ ያለው ሂደት በምን መንገድ መመራት አለበት? ምን አይነት ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ? ችግሮች ሲያጋጥሙስ እንዴት ነው መፍታት የሚቻለው? ከየትምህርት ተቋማቱስ ሊደረግ የሚገባው ድጋፍ ምንድነው? ተማሪዎቹስ በየአመቱ ማወቅ ያለባቸው የትኞቹን ነገሮች ነው? እነዚህን ነገሮች እያገኙ መሆናቸውን እንዴት መከታተል ይቻላል? የሚሉትና የመሳሰሉት ነገሮች ትኩረት ተሰጥቶአቸው ስልጠና ተሰጥቶአል።
እንደ ዶ/ርባልካቸው ማብራሪያ ከአሁን ቀደም ፕሮግራሞቹ ይመሩ የነበሩት በባህላዊ መንገድ ነበር ማለት ይቻላል። ነገር ግን ተማሪዎቹ የአራት አመት ቆይታቸውን በምን መንገድ ስርአት ባለው መልክ በሁሉም ተቋማት በተመሳሳይ ሁኔታ መምራት ይገባል የሚለው የዚህ ፕሮጀክት ዋናው ማጠንጠኛ ነው። በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች ብዛት በጣም ውስን በመሆኑ ተገልጋዩን ለመድረስ በማይችልበት ሁኔታ ይገኛል።
በኢትዮጵያ ካሉት የጽንስና ማህጸን ሕክምና ባለሙያዎች 65ኀየሚሆኑት በአዲስ አበባ የሚሰሩ ናቸው።
ቀሪዎቹ 35 ኀየሚሆኑትም የሚገኙት በየመስተዳድሩ ትልልቅ ከተሞች እንደ መቀሌ ፣አዋሳ ፣አዳማ በመሳሰሉት ነው።
ከላይ በተመለከተው መረጃ መሰረት የህክምና ባለሙያዎችን ብቃት እና ብዛት ማግኘት ወሳኝ ሁነት ነው። ይህ የድህረ ምረቃ ትምህርት ደግሞ የባለሙያዎችን ቁጥር ለማሳደግ እና አገል ግሎቱንም በመላ አገሪቱ በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዳረስ ለማድረግ እንደሚያስችል እሙን ነው። የአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሕክምና ኮሌጅ ከኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር ለጀመረው ፕሮጀክት በአሜሪካ ዳይሬክተር በመሆን የሚሰሩት ዶ/ርብርሀኑ ታደሰ ሀሳባቸውን እንደሚከተለው ገልጸዋል።
“...የአሜሪካው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከኢትዮጵያው የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ጋር በመተባበር ከሚሰራው ስራ አንዱ የማህጸን ሐኪሞች ስልጠናን ማገዝ ነው። በዚህም ፕሮግራሙ የድህረ ምረቃው ትምህርት በሚሰጥባቸው በሁሉም ተቋማት ያሉ ዳይሬክተሮችን እውቀት ከፍ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ስልጠና ነው። ተማሪዎቹ መሰልጠ ናቸው በትምህርት እና በስራ ጥራታቸው ብቁ መሆናቸው በኢትዮጵያ ለሚሰጡት አገልግሎት ብቻም ሳይሆን በመላው አለም ተገኝተው ብቃት ባለው መንገድ መስራት እንዲችሉ ያደርጋቸ ዋል። ስለዚህም ለስልጠናው የተጋበዙት በትምህርት ቤቶቹ ውስጥ ፕሮግራሙን የሚመሩ ዳይሬክተሮች በመሆናቸው የተሻለ አመራር መስጠት እንዲችሉ የሙያ ብቃታቸውን የሚያዳብር ስልጠና ነው። ስልጠናው የማህጸን ሐኪሞች ለመሆን የድህረ ምረቃ ትምህርታቸውን ለሚከታ ተሉ ሁለገብ የሆነ ድጋፍ በመስጠት በመርሐ ግብሩ ውስጥ በጥራት የሚወጡበትን መንገድ የሚያመቻች የአመራር ክህሎት ስልጠና ነው። ይህንን ስልጠና ለመስጠት የመጡት ሶስቱም ባለሙያዎች በአሜሪካ ከፍተኛ ሙያ ያላቸው ፕሮፌሰሮች ሲሆኑ ለአሜሪካ ሐኪሞች የሚሰጠ ውን ስልጠና በተመሳሳይ ደረጃ ኢትዮጵያ ላሉት ባለሙያዎችም እየሰጡ ነው። ስለዚህም ከትምህርቱ ጋር በተያያዘ ልምዳቸውንም ያካፍላሉ።”

  በፌስቡክ በተሰራጨ አንድ ጽሁፍ ላይ የተሰጡና ያለአግባብ የአንድን ግለሰብ ስም የሚያጠፉ ናቸው የተባሉ ስድስት  አስተያየቶችን ላይክ ያደረገው ስዊዘርላንዳዊ፣ ዙሪክ ውስጥ በሚገኝ ፍርድ ቤት ውሳኔ የ4 ሺህ 100 ዶላር ቅጣት እንደተጣለበት አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የ45 አመቱ ስዊዘርላንዳዊ በአገሪቱ የሚሰራ አንድ የእንስሳት ተንከባካቢ ቡድን ሃላፊ የሆኑትን ኤርዊን ኬስለር የተባሉ ግለሰብ በተመለከተ በፌስቡክ በተሰራጨ ጽሁፍ ላይ የተሰጡ ስም አጥፊና ሃሰተኛ አስተያየቶችን ላይክ በማድረግ ብዙ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች እንዲመለከቷቸውና እውነት አድርገው እንዲቀበሏቸው በማድረጉ ጥፋተኛ ነው በሚል ፍርድ ቤቱ ቅጣቱን እንደጣለበት ዘገባው ገልጧል፡፡
ኤርዊን ኬስለር፤ “መሰረተ ቢስ በሆኑ ሃሰተኛ መረጃዎች ላይ የተመሰረቱና ያለ አግባብ ስሜን የሚያጠፉ የፌስቡክ ጽሁፎችንና አስተያየቶችን ላይክ በማድረግ ህገወጥ ወንጀል ፈጽመውብኛል” በሚል አስራ አምስት ያህል የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን መክሰሳቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡

    ከሳምንታት በፊት በ2 ራሰ-በራዎች ላይ አሰቃቂ ግድያ ተፈጽሟል
     ራሰ-በራ የሆኑ ሞዛምቢካውያን የባዕድ አምልኮ ተከታዮች በሆኑ ግለሰቦችና ቡድኖች ጥቃት ሊሰነዘርባቸው እንደሚችል ያስጠነቀቀው የአገሪቱ መንግስት፤ ራሰ-በራዎች ራሳቸውን ከጥቃት ለማዳን ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጥሪ ማስተላለፉን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በሞዛምቢክ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ በርካታ ዜጎች መኖራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ እነዚህ የባዕድ አምልኮ ተከታዮች ራሰ-በራ በሆኑ ሰዎች የራስ ቅል ውስጥ ወርቅ ይገኛል ብለው በማመን ግድያ እንደሚፈጽሙባቸው የአገሪቱ ፖሊስ ማስታወቁን አስረድቷል፡፡
የባዕድ አምልኮ ተከታዮች የሆኑ ግለሰቦች ዛምቤዚያ በተባለቺው የአገሪቱ ግዛት ከሳምንታት በፊት በሁለት ራሰ-በራ ሞዛምቢካውያን ላይ አሰቃቂ የግድያ ጥቃት መፈጸማቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ መሰል ጥቃቶች በቀጣይም ሊፈጸሙ እንደሚችሉ የአገሪቱ ፖሊስ ሰሞኑን ማስጠንቀቁን ገልጧል፡፡
ከሳምንታት በፊት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት ሰለባ የሆነው አንደኛው ራሰ-በራ፣ በባዕድ አምልኮ ተከታዮች አንገቱ ተቀልቶና ሌሎች የሰውነት ክፍሎቹም ተቆራርጠው መገኘታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ድርጊቱን የፈጸሙት ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው በእስር ቤት እንደሚገኙም አስረድቷል፡፡
ግድያውን በመፈጸማቸው በእስር ላይ የሚገኙት ሁለት ሞዛምቢካውያን ወጣቶች ለፖሊስ በሰጡት ቃል፣ የገደሏቸውን ራሰ-በራዎች የሰውነት ክፍሎች ለጠንቋዮች ለመሸጥ አቅደው እንደነበር መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ጠንቋዮቹም የሰውነት ክፍሎቹን በመቀመም ለደምበኞቻቸው ሃብት የሚያትረፈርፍ መድሃኒት እንደሚሰሩበት መግለጻቸውን አክሎ አብራርቷል፡፡

 በኢራቅ የአይሲስ ታጣቂዎች ባለፈው ሳምንት ብቻ ከምዕራባዊ ሞሱል ለማምለጥ የሞከሩ ከ231 በላይ ሰዎችን መግደሉ የተነገረ ሲሆን፣ አልሻባብ በበኩሉ፤ ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸመው ጥቃት 70 ያህል ሰዎችን መግደሉ ተዘግቧል፡፡
ታጣቂዎቹ ባለፈው አንድ ሳምንት ብቻ ከአይሲስ ይዞታ በማምለጥ በኢራቅ ወታደሮች ቁጥጥር ስር ወደሚገኙ አካባቢዎች ለማምለጥ ሞክረዋል የተባሉትን ከ231 በላይ ኢራቃውያንን መግደሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከትናንት በስቲያ አስታውቋል፡፡
ዛንጂሊ በተባለቺው የምዕራባዊ ሞሱል አካባቢ ሰሞኑን በተከፈተ የአየር ጥቃት እስከ 80 ያህል ኢራቃውያን መገደላቸውን የሚጠቁም መረጃ ማግኘቱን የገለጸው ተመድ፤ ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝም አስታውቋል፡፡ በአሮጌዋ የሞሱል ከተማ ከ200 ሺህ በላይ ኢራቃውያን የስቃይ ኑሮ እየገፉ እንደሚገኙም ተመድ አመልክቷል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ በበኩሉ፤ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የአልሻባብ ወታደሮች ከትናንት በስቲያ በፑንትላንድ በሚገኝ የጦር ሰፈር ላይ በፈጸሙት ጥቃት ከ70 በላይ ሰዎችን መግደላቸውንና በርካቶችን ማቁሰላቸውን የዘገበ ሲሆን በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በቅርብ አመታት ታሪክ የተፈጸመው የከፋ ጥቃት ነው በተባለው በዚህ የአልሻባብ ጥቃት ሴቶችንና ህጻናትን ጨምሮ አንገታቸው ተቀልቶ የተገደሉ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ተገልጧል፡፡  
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ በዘገባው፤ ቦኮሃራም በናይጀሪያዋ ሜዱጉሪ ከተማ ከትናንት በስቲያ በፈጸመው የተኩስና የአጥፍቶ መጥፋት ጥቃት 11 ያህል ሰዎች መገደላቸውን ጠቁሟል፡፡