
Administrator
መልዕክቶቻችሁ
ከአዲስ አድማስ ጋር እንዴት ተዋወቅን?
አዲስ አድማስን ከ13 አመታት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ደብረ ማርቆስ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነው የተዋወቋት። ጋዜጣዋ ቅዳሜ ከሰዓት አንዳንዴ ደግሞ እሁድ ጠዋት ትደርስ ነበር፡፡ በወቅቱ እሸት አማተር የጋዜጠኞች ክበብ አባላት በተራ እየገዛን በፍቅር የምናነባት ተወዳጅ ጋዜጣ ነበረች። ለጋዜጣው አዘጋጆች ፣ አምደኞችና በትጋት ለምታነቡ የአዲስ አድማስ ወዳጆች በሙሉ እንኳን 25ኛ አመት የምስረታ በዓል አደረሳችሁ አደረሰን!
ጌትነት ተመስገን (ጌች ሐበሻ)
***
አዲስ አድማስን ማንበብ የጀመርኩት ገና ታትማ መውጣት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ነው። በወቅቱ Yellow journalism የተስፋፋበትና ጋዜጣ ከbroadsheet ወደ tabloid የተሸጋገረበት ጊዜ ነበር። ይልቁንም tabliod ጋዜጦች በነባር ጋዜጠኞች አሉታዊ አስተሳሰብ ሥር ነበሩ። አዲስ አድማስ ግን በ100 ከሚቆጠሩ ታብሎይድ ጋዜጦች ነጥራ ወጥታለች። ሆኖም የስፖንሰር አለመኖርና የወረቀት ዋጋ መጨመር እንዲሁም ወደፊት በሚመጣው የግብር ጫና ትቀጥል ይሆን? የሚል ስጋት አለኝ። እስካሁን ያቆዩዋትን በግሌ አመሰግናለሁ።
(ተሾመ ብርሃኑ ከድር)
***
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቅሁት አርሲ ነጌሌ ከተማ ሞኪያ የተባለ የመጻሕፍት መደብር ውስጥ ከብዙ መጽሔቶች ጋር ተጀቡና በተመለከትኩበት ወቅት ነው። መኮንን በተባለ በመጻሕፍት ቤቱ ባለቤት በኩል አዲስ አድማስ ጋዜጣ ለከተማችን አንባብያን የመጣችው ለአጭር ጊዜ ቢኾንም፣ በኤፍሬም እንዳለ ወጎች፣ በአሰፋ ጫቦ የትዝታ ፈለጎች፣ በነቢይ መኮንን ተረቶች የታጠኑ ርዕሰ አንቀጾች፣ በዓለማየሁ አንበሴ ወቅታዊ ዜናዎች፣ በእነ ሌሊሣ ግርማ መጣጥፎች ፍቅር ለመውደቅ ግን ከበቂ በላይ ጊዜ ነበር። ይህች የቅምሻ ተጽዕኖ፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በገባሁ ወቅት የማራኪ ካምፓስ ቤተ-መጻሕፍት ውስጥ ባለው የጋዜጣ ኮርነር ጋር የአዲስ አድማስ ጋዜጣ ቀበኛ እንድኾን አድርጎኛል።
እንኳን ለ25ኛ ዓመት አደረሳችሁ/ አደረሰን
(ቢንያም አቡራ)
**
ከድሮም ጀምሮ አነብ ነበር፣ ይሁንና ከዕለታት አንድ ቀን ለስራ ጉዳይ ጅማ ከተማ ሄድኩኝ፣ በከተማዋ ውስጥ ስዘዋወር ጋዜጣ የሚያዞር ልጅ አየሁኝና ጠራሁኝ፣ ከዚያ ሁለት ጋዜጣ ገዛሁኝ፣ ወደ መኖርያዬ ተመልሼ ሳነብ ግን የልበወለድ አፍቃሪ ስለነበርኩኝ በአዲስ አድማስ ተማረኩኝ፣ ከዚያ ትውውቅ ወዲህ የአዲስ አድማሰ አንባቢ ብቻ ሳይሆን ሰብሳቢ ሆንኩኝ። እዚያ ከተማ ስሄድ የሳምንቱን ብቻ ሳይሆን ያለፈውን ጭምር እየገዛሁ አስቀምጣለሁኝ።
በእርግጥ አሁን በከተማዋ ውስጥ ራስ የሚያዞር ጸሐይ እንጂ ጋዜጣ የሚያዞር የለም።
ያም ሆኖ ዕድሉ ሲገኝ በአካል ካልተገኘ በኦንላይን አነባለሁኝ። የምወደው ጥበብ የሚሰኘውን አምድ ነው፡፡ ጋዜጣውን በሙሉ ባነብም መጀመርያ ግን የኤፍሬም እንዳለን ሥራና አጭር ልበወለድ ነው የማነበው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አንብቤ የማስታውሰው አጭር ልበወለድ “ጭልፊቱ” የተሰኘው ትርጉም ልበወለድ ነው፣ አቤት አፍቃሪው ፌዴሪጎ እንዴት አሳዝኖኝ ነበር፣ እንዴት አስደስቶኝ ነበር፤ ለስንት ሰውስ ተረኩት።
ይህን አጭር ልበወለድ የያዘው ህዳር 3 ቀን 2009 ዓ.ም ዕትም አሁንም ድረስ አለኝ። እና አዲስ አድማስ አንጀት የምታርስ፣ እኔን ከመሻቴ የምታደርስ ስለመሰለኝ ከተዋወቅኋት ቀን ጀምሮ እስካሁን ድረስ አነባታለሁ፡፡ እውንም በአዲስ አድማስ ተምሬአለሁኝ፣
ተዝናንቻለሁኝ፤ ተሻሽያለሁ፡፡ አሁን ደግሞ እንደ ድሮ ጅማ እየተገኘች እንደልብ አነባት ዘንድ እናፍቃለሁኝ።
(ከድር ነብሶ)
***
አዲስ አድማስን በታላቁ ወንድሜ አማካይነት ነው ማንበብ የጀመርኩት፤ አሁንም እያነበብኩ አለሁ፡፡
(ሃኒቾ ከጦር ሃይሎች)
የኮካኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ በኢትዮጵያ “ከፍተኛው ቀጣሪ” ተባለ
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በኢትዮጵያ የ2025 ከፍተኛ ቀጣሪ ኩባንያ መሆኑን “ቶፕ ኢምፕሎዮ ኢንስቲትዩት” የተሰኘ ተቋም አስታወቀ።
ተቋሙ ባካሄደው ጥናት መሰረት፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ በ2025 የከፍተኛ ቀጣሪ ደረጃ እውቅና ካገኙ ስድስት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ተብሏል።
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ የገበያ ተደራሽነቱን እያሰፋ ኩባንያው፤ የሰራተኛ ቅጥርንም ገበያው በሚፈልገው ልክ እያሰፋ መሆኑ ተጠቁሟል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት በአገሪቱ የስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ማበረታታት አስፈላጊነት ሲገለፅ ቆይቷል።
ይሁንና የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፣ በኢትዮጵያ የፈጠረው ከፍተኛ የስራ እድልና የቅጥር አድማስ የ2025 ከፍተኛውን የዕውቅና ማእረግ ለመያዝ እንዳስቻለው ለማወቅ ተችሏል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሪል ዊልሰን ሲናገሩ፤ “ሽልማቱ ኩባንያው ከፍተኛ አቅምና አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች ለመሳብና ለማቆየት እንዲሁም፣ በሰው ሐብት አስተዳደር እድገት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን አቋም ያንፀባርቃል” ብለዋል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በአፍሪካ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከ720 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት “ቶፕ ኢምፕሎዮ ኢንስቲትዩት” ጠቁሟል።
ኩባንያው በ15 ሀገራት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን ስድስት ቁልፍ ገበያዎቹ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ናሚቢያ ናቸው። በተጨማሪም በታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ኮሞሮስ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶና ማላዊ ከፍተኛ ገበያ እንዳለው ተገልጿል።
ሁሌም ለመታረም ዝግጁ ነን!
ባለፈው ሳምንት ታህሳስ 3 ቀን 2017 ዓ.ም በወጣው የአዲስ አድማስ ዕትም “የአክሱም ሴት ሙስሊም ተማሪዎችን ጉዳይ ወደ ፍ/ቤት ወስጄዋለሁ” ከሚለው የፊት ገፅ ዜና ጋር የወጣው ኒቃም የለበሱ እንስቶች ምስል ስህተት መሆኑን ውድ አንባቢያን ደውለው ጠቁመውናል፡፡ ተማሪዎቹ የጠየቁት ሂጃብ እንጂ ኒቃም አይደለም ብለዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለተፈፀመው የምስል ስህተት ታላቅ ይቅርታ እየጠየቅን፣ በመቆርቆር ስሜት፣ ስህተታችንን ላረሙን ሁሉ ልባዊ ምስጋናችንን እናቀርባለን፡፡ ለ25ኛ ዓመታችን የደረስነው በናንተ ፍቅርና ድጋፍ ነው ስንል፣ ይህንን ማለታችን ነው፡፡ ሁሌም ለመታረም ዝግጁ ነን፡፡
የ25 ዓመት የሃሳብና የዕውቀት ጉዞ!!
የመጀመሪያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር - የዛሬ 25 ዓመት በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለ አንድ ቅዳሜ በስተቀር ጋዜጣው ያልታተመበት ጊዜ የለም፡፡ ያም ቢሆን የተከሰተው በ97 ምርጫ ማግስት በተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ነበር፡፡
የዛሬ 20 ዓመት፣ የአዲስ አድማስ ጠንሳሽ፣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ (አሴ) በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ባለፈበት ወቅት እንኳን ጋዜጣው ሳይታተም አልቀረም፡፡ ረቡዕ ከቀብር በኋላ ቢሮ ገብተን የቅዳሜውን ጋዜጣ ስናዘጋጅ ነበር፡፡ ከሃዘናችን ጋር እየታገልንም ቢሆን የቅዳሜውን ሳምንታዊ ጋዜጣ በጉጉት ለሚጠብቁን ውድ አንባቢያን አድርሰናል፡፡ በዚህም ኩራትና ክብር ይሰማናል፡፡ የጋዜጣው መሥራች አሰፋ ጎሳዬም ቢሆን፣ ከምንም በፊት ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለአንባቢያን ነበርና፡፡
እነሆ አዲስ አድማስ ከዚያም በኋላ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥራ፣ በብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች አልፍ፣ እነሆ ለ25ኛ ዓመቷ በቅታለች፡፡ ኮረኮንች በበዛበት የአገራችን የግል ፕሬስ፣ ሩብ ክፍለዘመን ቀላል ዕድሜ አይደለም፡፡ ረዥም ዕድሜ ነው፡፡ ትልቅ ስኬትም ነው ማለት ያስደፍራል፡፡
ለዚህ የደረስነው ግን በውድ አንባቢያን ገንቢ አስተያየትና ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ለአዲስ አድማስ ህልውናና በስኬት መቀጠል ከእኛ ከአዘጋጆቹ እኩል የሚጨነቁና የሚጠበቡት የረዥም ጊዜ ጽሁፍ አቅራቢዎችም ሌሎቹ ትልቅ ምስጋና የምንቸራቸው ባለውለታዎች ናቸው፡፡
ማስታወቂያቸውን በጋዜጣችን ላይ የሚያወጡ የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማትም ሁነኛ አጋሮቻችን ናቸውና ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡
መጪው ጊዜም ነጻ ሃሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት፣ ዕውቀትና ሥልጡንነት የሚያብብበት፣ የንባብ ባህል የሚዳብርበት እንዲሆን እንመኛለን፤ ለዚያም በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ በኢትዮጵያ "ከፍተኛው ቀጣሪ" ተባለ
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በኢትዮጵያ የ2025 ከፍተኛ ቀጣሪ ኩባንያ መሆኑን "ቶፕ ኢምፕሎዪ ኢንስቲትዩት" የተሰኘ ተቋም አስታወቀ። ተቋሙ ባካሄደው ጥናት መሰረት፤ ኩባንያው በኢትዮጵያ ውስጥ የ2025 የከፍተኛ ቀጣሪ ደረጃ እውቅና ካገኙ ስድስት ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ ሆኗል፡፡
በኢትዮጵያ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይ በማፍሰስ የገበያ ተደራሽነቱን እያሰፋ የሚገኘው ኩባንያው፤ የሰራተኛ ቅጥርንም ገበያው በሚፈልገው ልክ እያሳደገ መሆኑ ተጠቁሟል።
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት ሁለትና ሦስት አመታት በአገሪቱ የስራ አጥነት ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ሲሆን፤ ይሄንን ችግር ለመቅረፍም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን የማበረታታት አስፈላጊነት ሲገለፅ ቆይቷል።
ይሁንና የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፣ በኢትዮጵያ የፈጠረው ከፍተኛ የስራ እድልና የቅጥር አድማስ፣ የ2025 ከፍተኛውን የዕውቅና ማዕረግ ለመያዝ እንዳስቻለው ለማወቅ ተችሏል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ፣ የኢትዮጵያ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዳሪል ዊልሰን ሲናገሩ፤ "ሽልማቱ ኩባንያው ከፍተኛ አቅምና አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች ለመሳብና ለማቆየት እንዲሁም፣ በሰው ሐብት አስተዳደር እድገት ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ያለውን አቋም ያንፀባርቃል" ብለዋል።
የኮካ ኮላ መጠጦች አፍሪካ (ሲሲቢኤ)፤ በአፍሪካ ከ18 ሺህ በላይ ሰራተኞች ያሉት ሲሆን፤ በአለማቀፍ ደረጃ ከ720 ሺህ በላይ ደንበኞች እንዳሉት "ቶፕ ኢምፕሎዪ ኢንስቲትዩት" ጠቁሟል። ኩባንያው በ15 ሀገራት ውስጥ የሚሰራ ሲሆን፤ ስድስት ቁልፍ ገበያዎቹ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ናሚቢያ ናቸው። በተጨማሪም በታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ጋና፣ ዛምቢያ፣ ኮሞሮስ፣ ኢስዋቲኒ፣ ሌሶቶና ማላዊ ከፍተኛ ገበያ እንዳለው ተገልጿል።
በተቋሙ መስፈርት መሰረት፣ ኩባንያዎች የከፍተኛ ቀጣሪነት (Top Employer) የዕውቅና ሽልማት የሚያገኙት የሥራ ከባቢያቸው፣የሠራተኞችን አቅምና ችሎታ ለማጎልበት የሚያደርጉት ጥረቶች፣ አካታችነት፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የሰው ሃብታቸውን ለማበልጸግ ያላቸው ቁርጠኝነት ከተገመገመ በኋላ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ዳሸን ባንክ፤ በባንክ ኢንዱስትሪው የመጀመሪያውን ሱፐር አፕ አስተዋወቀ
ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የእድሳት ሥራ ተጠናቆ ተመረቀ
እግር ኳስን ከባዶ እግሩ ከመጫወት እስከ አውሮፓ ክለቦች የተጓዘው ሴኔጋላዊው “ኔይማር”
ሀ’ሊዩ
ዓለምን እየገዛ ያለው
የደቡብ ኮርያ ሞገድ
ሀገራችንን ጨምሮ “በማደግ ላይ ያሉ” ተብለው የተፈረጁ ሀገራት (developing countries) ስለእድገታቸውና ስለወደፊት ውጥኖቻቸው ሲወያዩ፣ ደቡብ ኮርያን እንደ አብነት ሲጠቅሱ መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው። እውነት አላቸው! ደቡብ ኮርያ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በቅኝ ግዛት ስር የምትማቅቅና በእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚዋ የደቀቀ ሀገር ነበረች። ለማስታወስ ያህል እ.ኤ.አ. ከ1910 እስከ 1945 ድረስ በጠቅላላው በኮርያ ልሳነ ምድር (Korea peninsula) ይኖሩ የነበሩት ኮርያውያን በጃፓን ቅኝ ግዛት ሥር ይተዳደሩ ነበር። ከዛ አስከፊ የጭቆና ጊዜ ነጻ ከወጡ በቅጡ እንኳን አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ደግሞ በእርስበርስ ጦርነት መታመስ ጀመሩ። ዓለማችን ካስተናገደቻቸው አስከፊ ጦርነቶች መካከል አንዱ የሆነውና እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 1953 ድረስ የዘለቀው የኮርያ ጦርነት (Korean war) የኮርያን ምድር ሰሜንና ደቡብ በሚባሉ ሁለት ሀገራት ከፋፈለ።
እዚህ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያም 6,037 እግረኛ ጦር ሰራዊት (የቃኘው ሻለቃ ጦር) በመላክ በኮርያ ጦርነት ተሳትፋ እንደነበር ልብ ይሏል። እነዚህ ሁለት አበይት ክስተቶች የኮርያን ምድር ወደ ድህነት አረንቋ ከመክተት አልፈው የኮርያውያንን የመኖር ህልውና ጭምር የተፈታተኑም ነበሩ። ደቡብ ኮርያ ግን ትንግርታዊ በሆነ መልኩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ከዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ተርታ መመደብ ቻለች። ከምንም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራት፣ ለዚህ መብቃቷ የጽናትና የእድገት ምልክት እንድትሆን አስቻላት።
ዛሬ ዛሬ ደቡብ ኮርያ በኢኮኖሚዋ ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ባህሎቿም በዓለም መድረክ እየታወቀች መጥታለች፡፡ እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባህላዊ እሴቶች በሀገሬው ዘንድ “ሀ’ሊዩ (한류)” በመባል የሚጠሩ ሲሆን፤ የምዕራቡ ዓለም ደግሞ የኮርያ ሞገድ (K-wave) ሲል ይጠራቸዋል። ይህን አይነት ስያሜ ማግኘታቸው መቼም በጣም ባጭር ጊዜ (በፍጥነት) የዓለምን ቀልብ መሳብ መቻላቸውን ለማሳየት እንደሆነ መገመት ይቻላል። በዚህች አጭር ጽሑፍም ትኩረታችንን ዓለምን እየገዙ ባሉት የደቡብ ኮርያ ዋና ዋና ባህላዊ እሴቶች ላይ በማድረግ በወፍ በረር እንዳስሳቸዋለን። ቅኝታችንንም ሀገሪቱ በዓለም መድረክ በበጎ ጎኑ እንድትሳልና እንድትታወቅ ካደረጓት ባህላዊ እሴቶቿ መካከል ግንባር ቀደሙ በሆነው የደቡብ ኮርያ የፖፕ ሙዚቃ ስልት (K-pop) እንጀምራለን።
የK-ፖፕ ማዕበል ከሀገሬው አልፎ ዓለም አቀፋዊ ወደሆነ የሙዚቃ ዘውግ የተሸጋገረው በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ነው። በተለይ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2012 ፓርክ ጄይ ሳንግ በሚባለው ሙዚቀኛ (በመድረክ ስሙ PSY) የተቀነቀነውና “ጋንግናም ስታይል” በመባል የሚታወቀው ነጠላ ዜማ ለኮርያ ፖፕ ሙዚቃ የዓለም አቀፍ ስኬት መንገዱን የጠረገ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው ገናና የሆኑና ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፉ በርካታ የK-ፖፕ አርቲስቶች (ዘፋኞች) መምጣት ችለዋል። አንዳቸውም ግን በአሁኑ ወቅት እጅግ ተወዳጅ የሆኑትንና “BTS” በመባል የሚታወቁትን የሙዚቃ ቡድኖች የሚስተካከሉ አይመስሉም። BTS የሙዚቃ ቡድን ሰባት ወጣት ድምጻውያንን ያካተተ ሲሆን፤ ድምጻውያኑ በግልም በቡድንም በመሆን በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ማሸነፍ የቻሉ ናቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን ባላቸዉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተዉ ንግግር እስከማድረግ ድረስም ደርሰዋል። ባጠቃላይ BTSን ጨምሮ ሌሎች የK-ፖፕ አቀንቃኞች ቋንቋ ሳይገድባቸው የደቡብ ኮርያን ባህል የሚያንጸባርቁ ዜማዎችን በማቀንቀን ሚሊዮኖች በደቡብ ኮርያ ፍቅር ሀ’ሊዩ — ዓለምን እየገዛ ያለው የደቡብ ኮርያ ሞገድ እንዲወድቁ አድርገዋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኗቸውም በየደረሱበት ሁሉ የሀገሪቱ የባህል አምባሳደር መሆን ችለዋል።
ልክ እንደ K-ፖፕ ሁሉ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉትና የኮርያ ሞገድ አካል የሆኑት ደግሞ የኮርያ የቴሌቪዥን ድራማዎች (K-drama) እና ፊልሞች (K-movie) ናቸው። በቅርቡ እንኳን እጅግ ገናና ከሆኑትና የተለያዩ ሽልማቶችን ማሸነፍ ከቻሉት መካከል “Parasite” የተሰኘውን ፊልምና “Squid Game” የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ጥልቅ በሆኑ ስሜቶችና ትእይንቶች የሚታወቁት የደቡብ ኮርያ የቴሌቪዥን ድራማዎችና ፊልሞች የሀገሪቱን ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ልማድ በዓለም ዙሪያ ላሉ ማህበረሰቦች (ተመልካቾች) ማስተዋወቅ ችለዋል። በዚህም ከመዝናኛነት አልፈው የደቡብ ኮርያን የቱሪዝም ፍሰት እጅግ እንዲያድግ በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው። ይህንንም ለመረዳት በደቡብ ኮርያ ድራማዎችና ፊልሞች ፍቅር ተነድፈው ወደ ሀገሪቱ የሚጎርፉትንና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን አሜሪካውያን፣ አውሮፓውያንና እስያውያን መመልከት በቂ ነው።
በእኛም ሀገር ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደቡብ ኮርያ ድራማዎችና ፊልሞች ተወዳጅነትን እያተረፉ መጥተዋል፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ በነበርኩበት ወቅትም የK-ፖፕ ሙዚቃዎችን ማድመጥ ብቻ ሳይሆን የኮርያ ድራማዎችንና ፊልሞችን በፍቅር የሚመለከቱና ቋንቋውን ጭምር መማር የቻሉ በርካታ ወጣቶችን ማግኘት ችዬ ነበር። አንዳንዶቹም ወደ ደቡብ ኮርያ መዝለቅና ስለሀገሪቱ ይበልጥ ማወቅ ትልቁ ጉጉታቸው እንደነበር አጫውተውኛል። በቅርቡም KBS በሚባል የሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ አንድ ዶክመንተሪ ላይ አንዲት ኢትዮጵያዊት ቤተሰቦቿ ለደቡብ ኮርያ ድራማዎች ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ስትገልጽ ሰምቻለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች “እውነትም ሞገዱ ዓለም አቀፍ ነው!” እንድንል ያስገድዱናል። ከዚህ ባለፈም “ዓለም እንደ አንድ መንደር እየጠበበች መጥታለች” ለሚለው ዲስኩር እንደ አንድ ማሳያ መንገድ ይሆኑናል።
የደቡብ ኮርያ ሞገድና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን እያተረፈ ያለው የኮርያ ምግብ (K-food) ነው። ከባህላዊ ምግቦች ጀምሮ በፋብሪካ እስከሚቀነባበሩት ድረስ ያሉትን የኮርያ ምግቦች ለማጣጣም የማይፈልግ የማህበረሰብ ክፍል ያለ አይመስልም። በተለይ ደግሞ በምዕራቡ ዓለምና በሌሎች የእስያ ሀገራት ተፈላጊነታቸዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ ስፍር ቁጥር ከሌላቸዉ የደቡብ ኮርያ የባህል ምግቦች መካከልም “ኪምቺ” ተብሎ የሚጠራውና በዋናነት ከጎመን (የቻይና ጎመን) የሚሰራው የምግብ ዓይነት ከእስያ አህጉር አልፎ የምዕራቡን ዓለም ማዳረስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በመብላላት ሂደት (fermentation) የሚሰራውን ኪምቺ ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ባህላዊ ምግቦች በርካታ የጤና በረከቶች እንዳሏቸው መታወቁ የብዙዎች ምርጫ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በነገራችን ላይ የኪምቺ ባህላዊ አሰራር ሂደት (ኪምጃንግ) እ.ኤ.አ. በ2013 በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መካተትም ችሏል። ባጠቃላይ ልክ እንደ K-ፖፕና K-ሲኒማ ሁሉ የደቡብ ኮርያ ባህላዊ ምግቦችም የዓለምን ትኩረት እየሳቡና ለሀገሪቱ እድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ የሞገዱ አካል ናቸው።
ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች በተጨማሪ ደቡብ ኮርያ በመዋቢያ እቃዎች (K-beauty) እና በፋሽን (K-fashion) ማዕበሎችም ዓለምን ማጥለቅለቅ ከጀመረች ሰነባብታለች። የደቡብ ኮርያ የባህል ሞገድ እያሳደረ ያለው ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በጥናት እየተደገፈ መሆኑ ደግሞ ቀጣይ ተመሳሳይ ዘርፎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሳያ ነው። እነዚህ የደቡብ ኮርያ ሞገዶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ ያስቻሏቸው ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ባህልን ከዘመናዊነት ጋር በተዋጣለት መልኩ አዋህደው ማንጸባረቃቸው ዋናው እንደሆነ ይነገራል። እናም ደቡብ ኮርያ ባህሏን፣ ታሪኳንና ወጎቿን በK-ፖፕ ዘፈን ምት፣ በK-ድራማና ፊልም፣ K-ምግብና ሌሎች ሞገዶች እያዋዛች ለዓለሙ ማህበረሰብ እንካችሁ እያለችና ተምሳሌትነቷን እያገዘፈች ትገኛለች። ህዝቦቿም ከባዶነት፣ ከድህነትና ከአስከፊ ጦርነት ተነስቶ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚቻልበት መንገድ ገብቷቸዋል። “የነብርን ጭራ ከያዙ አይለቁ” ነዉና ነገሩ፣ ለዚህም ዕለት ተዕለት በጽናት የሚታትሩ ሆነዋል።
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የረጅም ጊዜ አምደኛ የሆነዉ ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ ባሳለፍነዉ ሳምንት ባስነበበን “የአዲስ አድማስ ትዝታዬ አጽቆች!” ጽሑፍ ዉስጥ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ጉዞ ሲገልጽ እንዲህ አለ፤ “…በተለያዩ የዕድገት አንጓዎች፣ በተዥጎረጎሩ የሀገር ጉዞ ምዕራፎች፣ በምጣኔ ሀብታዊ መንገዳገዶች ስታልፍ ያንን ሁሉ አስልታ፣ መክራና ዘክራ ኀላፊነቷን ተወጥታለች። በዚያ ሂደት እነሆ አሁን የብር ኢዩቤልዩ ደጅ ላይ መድረሷ የሚያሳየን፣ ብስለትና ዕድሜ በንባብ ከታጀቡ፣ ከኪሳራ ነፃ መሆናቸውን ነው።” እኔም የደቡብ ኮርያን አጠቃላይ የእድገት ጉዞ ለመግለጽ ጸሐፊዉ የተጠቀማቸዉን ቃላት መዋስ ፈለግሁ። ማጠቃለያ ይሆነኝ ዘንድ! ደቡብ ኮርያ በኢኮኖሚ ኃያል ሀገር ለመሆን ባደረገችው ጉዞ በተለያዩ የዕድገት አንጓዎች ውስጥ አልፋለች። በእነዚህ የእድገት ምዕራፎች ዉስጥ ያጋጠሟትን የትየለሌ ፈተናዎች ተቋቁማ ዛሬ ላለችበት ደረጃ መብቃቷ ደግሞ ሀገሪቱ የእድገት ብቻ ሳይሆን የጽናት ተምሳሌት መሆኗንም ያሳያል። የደቡብ ኮርያ የእድገት ጉዞ የሚያሳየን ሌላዉ ነገር ብስለት፣ ጥበብና ማስተዋል የተሞላበት አካሂያድ መከተል ከጦርነት ኪሳራ ነፃ መዉጫ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ነው። በተጨማሪም እንዲህ አይነት አካሂያድ መከተል ባህልና እሴት ብለው የያዟቸው ነገሮች ተጽዕኖ ማምጣት የሚያስችሉ ሞገዶችን መፍጠሪያ ግብዓቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላክታል። አልታየን ብሎ እንጂ እንደኛ የባህል ጎተራ የሆነ ሀገር ማግኘት መቼም ቀላል አይደለም። ለዚያውም ከዉጭ ሲታይ የሚያስቀና! እናም የአዲስ አድማስ ጋዜጣን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል ስናከብር ትልቁ ምኞቴ፣ ዓለምን የምናንበረክክበት የሀ’ሊዩ ውሽንፍር ይመታን ዘንድ ነው። ኢ-ፖፕና ኢ-ድራማ ብለን ብለን ቢያቅተን ኢ-እስክስታ፣ ኢ-ጩምቦ፣ ኢ-ጥዕሎ፣ ኢ-ቡና፣ ኢ-ጠላ፣ ኢ-ቡሄ፣ ኢ-ቡርሳሜ… ማለት መቼም አያቅተን!? ቸር ያቆየን!
መልከ ብዙ ከያኒ ነቢይ መኮንን!
በሀገራችን የሥነጽሑፍ ጉዞ ውስጥ አሻራቸው የማይደበዝዝ፣ አበርክቷቸው የጎላ፣ በዚህም ስማቸው በደማቁ የሚጠቀሱ ጸሐፍት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ብዙ የጻፉ፣ ደጋግመው ያሳተሙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ሁለት እና ሦስት ሥራዎችን ብቻ ያሳተሙ (የጻፉ ከማለት መቆጠቤ፣ አለማሳተም ላለመጻፍ ምስክር አይቆምም በሚል ነው) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከሁለት ዓይነቶቹ ወጣ ብለን ስንማትር ደግሞ፣ በሌላ ጎራ ልናስቀምጣቸው የሚቻለን ጸሐፍት አሉ - መልከ ብዙ ልንላቸው የሚቻለን ጸሐፊያን፡፡
እነዚህኞቹ በበርካታ ዘውጎች ራሳቸውን የገለጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ መቻላቸውንም ያስመሰከሩ፣ ገበታቸው የደረጀ፣ ማዕዳቸው የሰፋ፣ በዚህም ያቀብሉት የሞላቸው ዓይነት ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሥነጽሑፋችን ብዙም ደረታችንን ነፍተን፣ ድምጻችንን አሰምተን የምንጠቅሳቸው ጸሐፍት ያሉት አይመስልም፡፡ ወይም ሥራቸውን አደባባይ አውለው፣ እኛም ዳብሰን፣ አንብበን እንመሰክርላቸው ዘንድ አላገኘናቸውም፡፡
በእኔ ዕይታ መልከ ብዙ ብለን እንጠራቸው ዘንድ የእጃቸው ፍሬዎች ከሚፈቅድላቸው፣ ደግሞም ካሳመኑን ጸሐፍት አንዱ ነቢይ መኮንን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ነቢይ “ከሁሉም በላይ ገጣሚ” ነኝ ሲል ቢደመጥም ቅሉ፣ እኛም መረጃ ጠቅሰን፣ ምስክር አቁመን ሌሎች አቻ መልኮችም አሉህ የማለት መብታችንን ተጠቅመን፣ የከያኒውን መልከ ብዙነት መመስከር ማንም የማይነጥቀን የራሳችን ፈቃድ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነቢይ የተገለጠባቸውን በልዩ ልዩ ዘውጎች ሥር የሚመደቡ ሥራዎቹን የጋዜጣ አምድ በሚፈቅድልን መጠን በማነሳሳት፣ የከያኒውን መልከ ብዙነት መግለጽ ነው፡፡
፩. ተርጓሚው ነቢይ
ትርጉም፣ እጅግ ጥልቅ ቢሉ ውስብስብ፣ በርካታ ብቃቶችን በአንድ ጊዜ በዛው ቅጽበት መጠቀምን ወይም አገልግሎት ላይ ማዋልን የሚጠይቅ መጠበብ ነው፡፡ ተርጓሚውም በዚህ መጠበብ ውስጥ በምልዐት ማለፍ ይችል ዘንድ በርካታ ብቃቶችን ሊካን ይገባዋል፡፡ ተተርጓሚውንና የሚተረጎምበትን ቋንቋ ማወቅ ብቻ (ቋንቋውን መናገር፣ በቋንቋው መጻፍ) ተርጓሚ አያደርግም፤ በፍጹም፡፡ ይልቁንም የሚተረጉሙትን ድርሰት ባህል፣ እሴቶች፣ እምነቶች፣ ተተርጓሚው ድርሰት የተጻፈበትን ዘመንና የዘመኑን መንፈስ የመሳሰሉትን ጠንቅቆ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊትም ተተርጓሚውን ቋንቋ ከእነጓዙ በጥልቀት ማወቅን ግድ ይላል፡፡ ይሄ እንግዲህ ከተተርጓሚው ቋንቋ አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በበለጠ ደግሞ ድርሰቱ የሚቀዳበትን/ የሚተረጎምበትን ቋንቋ መጠንቀቅ (በምልዐት ማወቅ) ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ብቃቶች በትርጉም ሥራዎቹ ላይ ፍንትው ብለው የሚታዩ ጸሐፊ ለብቁ ተርጓሚነቱ አሌ የለውም፡፡
ነቢይ እንደጸሐፊ በኖረበት የሥነጽሑፍ ዓለም በርካታ ዘውግ ያላቸውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን (አጭርና ረጅም ልቦለዶችን፣ ተውኔቶችን እና ግጥሞችን) ተርጉሟል፤ አሳትሟልም፡፡ እነዚህም የትርጉም ሥራዎቹ ሙሉ ለሙሉ መነበብንም መደነቅንም የተቸሩ ናቸው፡፡
ስሙ በጉልህ ከሚነሳበት በከባዱና በአሰቃቂው የማዕከላዊ እስር ቤት ሆኖ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ የተረጎመውን የእውቋ አሜሪካዊት ደራሲ Margaret Mitchell “Gone with the Wind” ረጅም ልቦለድን ጨምሮ፣ የDan Brown ረጅም ልቦለድ “The Da Vinci Code” “ዘ ዳ ቬንቺ ኮድ” በሚል ርዕስ፣ የNawal El-Saadawiን “Woman at Point Zero”፣ የMitchell David Albomን “Tuesdays with Morrie” “ፕሮፌሰሩ” ብሎ፣ የMarina Lewycka “A Short History of Tractors in Ukrainian” የRandy Pauschን “The Last Lecture” “የመጨረሻው ንግግር” ብሎ ድንቅ በሚባል የቋንቋ ብቃት፣ በውብ ስልት ተርጉሟል፡፡
አስቀድሜ እንዳልኩት ድንቅ ተርጓሚነቱን ያሳየው በልቦለድ ዘውግ ብቻ አይደለም፡፡ የዓለማችንን ስመ ጥር ጸሐፌ ተውኔቶችን ተውኔቶች፣ ገጣሚያንንም ግጥሞች ዕጹብ ድንቅ በሚባል ብቃት ተርጉሟል፡፡ የእውቁን ጀርመናዊ ፈላስፋና ጸሐፊ የEphraim Lessing ተውኔት የሆነውን “Natahn the Wise” “ናትናኤል ጠቢቡ” ብሎ የBernard Shawን ተውኔት፣ እንዲሁም የShakespeare ተወዳጅ ሥራ የሆነውን “Julius Caesar” ተርጉሞ ለመድረክ አብቅቷል፡፡ ሌሎች የነቢይን የተርጓሚነት ብቃት የሚመሰክሩት ደግሞ፣ የበርካታ ባለቅኔዎች ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ግጥሞች ሲሆኑ፣ እነዚህ ትርጉም ግጥሞቹ ለዓመታት በአዘጋጅነት በመራው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አለፍ አለፍ እያሉም ባሳተማቸው የግጥም መድበሎቹ ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡
፪. ጋዜጠኛው ነቢይ
የነቢይን ብርቱ ጋዜጠኝነት ለመመስከር ብዙ መድከም፣ አስረጂ ፍለጋ መባዘን ያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ የዚህችው (የአዲስ አድማስ) ጋዜጣ አንባቢያን አጋዥ ተባባሪ ሆነው እንደሚሞግቱልኝ ጥርጥር የለውም፡፡ ነቢይ የዛሬ 25 ዓመት በምስጉኑ የኪነጥበብ ተቆርቋሪ እና የቢዝነስ ሰው በአሰፋ ጎሳዬ የተመሠረተችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ፣ ተናፋቂና ተነባቢ፣ በብዙ ሺዎች የምትወደድ ሆና ከዓመት ዓመት እንድትዘልቅ ማድረግ ችሏል፡፡ በአንድ ጋዜጣ ወይም መጽሔት ላይ የዋና አዘጋጁ ተግባር ምን ያህል አድካሚና በጥንቃቄ የተሞላ የሠርክ ተግባር መሆኑን እዚህ ለመዘርዘር መሞከር ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ምናልባት “architect of the building” ወይም “captain of the ship” የሚሉትን አነጋር ጠቅሶ ማለፉ ይሻል ይሆናል፡፡
ነቢይን እና በዋና አዘጋጅነት ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የመራትን አዲስ አድማስን አንስቶ የነቢይን ርዕሰ አንቀጾች እና የጉዞ ማስታወሻዎች አለማንሳት ማጉደል ነው የሚሆነው፡፡ ወዲህም ብርቱ ጋዜጠኛ ነው ብዬ ለምሞግትለት መልከ ብዙ ከያኒ ነቢይ አስረጂዎቼ ናቸውና ትንሽ ልሂድባቸው፡፡
ነቢይ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅነት ዘመኑ ቢያንስ ከ900 በላይ ርዕሰ አንቀጾችን ጽፏል፡፡ በእኔ ግምገማ እነዚህ ርዕሰ አንቀጾች ከዚህ በፊት በሀገራችን የሕትመት ሚዲያ ውስጥ ከስልት አንጻር ፍጹም ያልታዩ (በዓለምም ያላጋጠሙኝ) የተለየ ቅርጽና ስልት ያላቸው ናቸው፡፡ የነቢይ ርዕሰ አንቀጾች መንገር ወይም ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት የሚገልጹት በተረት ውስጥ ነው፡፡ እጅግ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ነቢይ ተረቱን ሲቋጭ የሚላት ነገር ጥቂት ናት፡፡ እነዚህ ተረቶች በተረት ያደገውን ቢሉ የኖረውን፣ ለሁሉ ስለሁሉ ተረትን እማኝ የሚያደርገውን ኢትዮጵያዊ አንባቢ ፍላጎት በመግዛት ተነባቢነትን በማትረፍ፣ አዘጋጁ ነቢይ የጋዜጣዋ አቋም የሆነውን ሃሳብ በዚሁ ውስጥ እያዋዛ ማድረስ እንዲችል አድርጎታል፡፡ ይህንን መንገድ ከነቢይ በፊት ማንም አልሞከረውም፡፡
ነቢይ በዚህ ስልት ተነባቢ ርዕሰ አንቀጽን ከመፍጠር ባለፈ (በአጋጣሚም ይሁን ይሁነኝ ብሎ) ሌላም ያሳካው አቢይ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ጋዜጣዋን ከጥቃትና ከመዘጋት ከልሎ በዘመናት ውስጥ ህልውናዋን ጠብቃ እንድትዘል ማስቻሉ ነው፡፡ ምንም እንኳን አዲስ አድማስ በአብዛኛው ማህበራዊና ኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር ብትሆንም፣ ሁሌም እንደማንኛውም የሕትመት ሚዲያ ሁሉ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የራሷ አቋም አላት፡፡ ይህንንም በዋና አዘጋጁ በሚጻፈው ርዕሰ አንቀጽ ላይ ታሰፍራለች፡፡ ሆኖም ጥንቁቁና በሳሉ ነቢይ የተከተለው ስልት በማዋዛት መግለጽ መሆኑ፣ በጋዜጣዋ ሚዛናዊነት ላይ ተደምሮ ጋዜጣዋ በየወቅቱ በገጠሙ ከባድ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥም ከሕትመት ሳትጎድል ለአንባቢዎቿ እንድትደርስ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል፡፡
ነቢይ በርካታ ተወዳጅ የጉዞ ማስታወሻዎችን ከትቦ አስነብቦናል፡፡ የነቢይ የጉዞ ማስታወሻዎች ተራ ዘገባዎች አይደሉም፡፡ በጉጉት የሚጠበቁ፣ ተስገብግበው የሚነበቡ ዓይነት እንጂ፡፡ በሀገረ አሜሪካን በእንግድነት በነበረው ቆይታ ያስነበበን “የእኛ ሰው በአሜሪካ” እና እንደ ኢራን በመሳሰሉት የውጪ ሀገሮች ባደረጋቸው ጉዞዎች የከተባቸው የጉዞ ማስታወሻዎች በጠንካራ ሥነጽሑፍነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ማስታወሻዎች በወቅቱ ለአንባቢ ይደርሱባት የነበረችውን ጋዜጣ (አዲስ አድማስ) ተናፋቂነትና ተነባቢነት በመጨመር ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም፡፡
፫. የድራማ እና የዘፈን ግጥም ጸሐፊ
ነቢይ በቴሌቪዥን ድራማ እና በዘፈን ግጥም ጸሐፊነትም ራሱን መግለጥ የቻለ መልከ ብዙ ከያኒ ነው፡፡ ትኩረቱን የወቅቱ የሀገሪቱ (በእርግጥ ዛሬ ብሷል) አንገብጋቢ ሰንኮፍ በነበረው ሙስና ላይ ያደረገ “ባለጉዳይ” የተሰኘ ሳትሪካል ድራማ ጽፎ ለዕይታ አብቅቷል፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ሳምንታት ይታይ የነበረው ይህ ድራማ፣ ከፍተኛ ትኩረትን የሳበና በርካታ ተመልካቾችን ከቴሌቪዥን ፊት ያስቀመጠ ድንቅ ኪነጥበባዊ ሥራ ነበር፡፡
መልከ ብዙው ከያኒ ነቢይ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በዘፈን ግጥሞችም ተራቋል፡፡ በ1990ዎቹ ኤችአይቪ ኤድስ የብዙዎችን ቤት የሐዘን ማቅ ባለበሰበት፣ በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ ባደረገበት፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደ አውሬ ይፈሩበት፣ እንደ ጸያፍ ይገለሉበት በነበረበት በዛ ጨለማ ውስጥ፣ እጅግ አስተማሪ የሆነ መልዕክት በውብ አቀራረብና የሙዚቃ ስልት ለአድማጭ ተመልካች ያቀረበው “ማፍቀር ነው መሰልጠን” የተሰኘው የወቅቱ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራ ግጥም ጸሐፊ ነቢይ ነው፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ተጠቃሽ ድምጻዊ አስቴር አወቀ ያቀነቀነችው “መጠንቀቅ ነው ደጉ፤ ላንተም ለኔም ጤና” የሙዚቃ ሥራ ግጥም ደራሲ መልከ ብዙው ከያኒ ነቢይ መኮንን ነው፡፡
፬. ከሁሉም በላይ ገጣሚ
ምንም እንኳን ነቢይ ራሱን ከሁሉም በላይ እንደገጣሚ ቢቀበልም፣ የጠቆምኳቸውን ራሳቸውን የገለጸባቸውን ዘውጎች አስረጂ አድርገን ገፍተን ብንመረምር “ገጣሚ ብቻ አይደለህም፤ መልከ ብዙ ከያኒ እንጂ” ብለን አፋችንን ሞልተን እንሞግተው ዘንድ ይቻለናል፡፡ እንዴት ቢሉ፣ ከያኒው ራሱን የገለጠባቸው ዘውጎችም ሊያስጠሩት የሚያንሱ ስላይደሉ፡፡ የነቢይን ግጥሞች ተተኳሪ ጭብጦች እና ግጥሞቹ የተበጀባቸውን ቋንቋ ብቻ በጥቂቱ ላንሳ፡፡ ነቢይ ሦስት የግጥም መድበሎችን አሳትሞ ለአንባቢያን እነሆኝ ብሏል፡፡ እነዚህ መድበሎች “ጥቁር ነጭ ግራጫ”፣ “ሥውር ስፌት ቅጽ 1” እና “ሥውር ስፌት ቅጽ 2” ናቸው፡፡ የነቢይን ግጥሞች በመቃኘት የግጥሞቹ ተመላላሽ ጭብጦች ሀገር፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ሞትና (ተቃራኒው) ህይወት፣ ፍቅር፣ ጊዜ እና ባይተዋርነት ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ ሀገር፣ ነቢይ በርካታ ግጥሞቹን የጻፈበት ዋነኛው ማተኮሪያው ነው፡፡ ከእነዚህ ሀገር ከሚገዳቸው ግጥሞቹ መካከል “ሀገርህ ናት በቃ” ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ ድረስ ዘልቀው የሚሰሙ ሀገር ሙሉ ስሜትን ያቋቱ ደማቅ ግጥሞቹ ናቸው፡፡ ሞትና ተቃራኒው የሚመስለው ሕይወት፣ ሌሎቹ የነቢይ ተመላላሽ ጭብጦች ናቸው፡፡ ነቢይ ሞትን ጭብጡ አድርጎ በርካታ ግጥሞችን ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ሞትን ጭብጣቸው ካደረጉ ግጥሞቹ አብዛኞቹ ሞትን የጠመዱ (የጠሉ)፣ በግብሩ የሚብሰለሰሉ ዓይነት ናቸው፡፡ እዚህ ላይ “ከሞት ጋር ተቃጥረን”፣ “ለካስ ሞት ግጥም አይችልም”፣ “የእድሜ እቁብ ቢኖር”… የመሳሰሉትን ተወዳጅ ግጥሞቹን ልብ ይሏል፡፡ ነቢይ ተብሰልሳይ ገጣሚ ነው፡፡ በተለይም የደጋግ (የታላላቅ) ሰዎች እጦት በእጅጉ ያብሰለስለዋል፡፡ ሞታቸው የሚፈጥረውን ሽንቁር የሕይወቱ ሽንቁር አድርጎ ነው የሚወስደው፤ የእግር እሳት ሆኖ ያትከነክነዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሀገር ዋርካዎቹ ህልፈት የነቢይ ግጥሞች ጭብጥ የሆኑት፡፡ ነቢይ በመድበሉ ውስጥ የዚህ ዓይነት ጭብጥን ያዘሉትን ግጥሞቹን ክቡር ስም ብሎ ነው በወል የሚጠራቸው፡፡
በዚህ ረገድ ለሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ህልፈት የተቀኘው “ገብሬ”፣ ለታላቁ ባለቅኔ ለጸጋዬ ገብረ መድኅን ህልፈት የከተበውን “አይሉት ነገር አባባል/ የጥበብ ሰው ቅስም ያማል”ን ማንሳት እንችላለን፡፡ ለታላቁ ደራሲያችን ለበዓሉ ግርማ የጻፈው ግጥምም እንዲሁ ቀጣዮቹን ተብሰልሳይም ጠያቂም ስንኞች አዝሏል፡፡
ይሄ ምን አማርኛ ነዉ፣ ፌዙ ለጆሮ የከፋ
ምን ያለስ ልብስ ሰፊ ነዉ፣ ሞትን በልኬ እሚሰፋ?
ሞት ከአረጋዊ ቢያረጅም፣ ከሰዉ የባሰ ክፉ ነዉ
በተለይ ደራሲ ሲያገኝ፣ ሲስገበገብ ለብቻዉ ነው
የነቢይ ቋንቋ ጸናን ያይደለ ገር ነው፡፡ ደግሞም ቀላል፤ እንደጨዋታ ያለ፡፡ ደግሞም ለወግ የሚቀርብ፡፡ ነቢይ የደረጀ ቃላዊ ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ግን ደግሞ እነሱን እንደወረዱ ሲጠቀማቸው አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ደቂቁ ቢሉ ለጋ አንባቢው ሳይቀር እንዲረዳቸው አድርጎ አቅልሎ ነው የሚሸምናቸው፡፡ የነቢይ ቋንቋ ቀላል ነው፤ ተራና ተርታ ያልሆነ፡፡ ደግሞም አዘቦታዊ፤ ያልጨረተ ኦርጅናሌ ነው፡፡ ነቢይ የትኛውን ቃል የት፣ ከምን ጋር እንዴት ባለ መልኩ ማቀናጀት እንዳለበት የሚያውቅ ጥንቁቅና በሳል ገጣሚ ነው፡፡ በእኔ መረዳት ነቢይ በቀላል የቋንቋ አጠቃቀም ግጥምን ለወግ ያቀረበ ገጣሚ ይመስለኛል፡፡
፭. ሌሎች የነቢይ መልኮች
ነቢይ መኮንን ጽፎና አሳትሞ ከማለፍ ባለፈ በአማርኛ ሥነግጥም ውስጥ የሚወሳባቸውን መልኮች ነድፎ ያለፈ ከያኒ ይመስለኛል፡፡ እነዚህም መልኮች ከቀላል አሰነኛኘት እና በአዘቦታዊ ቃላት ረቂቅና ውስብስብ ሃሳቦችን መግለጽ ከመቻል አንጻር ሊወሱ ይችላሉ፡፡
ነቢይ ከግጥማዊ የአሰነኛኘት ድንጋጌዎች ይልቅ ሃሳቡ የሚገደው ዓይነት ገጣሚ ነው፡፡ ይህንን ስል ግን ነቢይ ለተለመዱት የአማርኛ ግጥም አሰነኛኘቶች አይገዛም እያልኩ አይደለም፤ ፍጹም ተገዢያቸው ሆኖ ሲያገለግላቸው አይታይም እያልኩ እንጂ፡፡ የነቢይ ግጥሞች ከአሰነኛኘታቸው ግላዊነት በመነጨ፣ አንዳንዶቹም በተለመደው የግጥም አነባበብ ስልት ከመነበብ ይልቅ ሌላ መንገድን የሚጎተጉቱ ዓይነት ናቸው፡፡ ነቢይ ማቅለል ላይ አብዝቶ ይተጋል፡፡ “If you can’t explain it simply, you don’t understand it well enough” እንዲል Albert Einstein፡፡
ሌላው የነቢይ መልክ እጅግ አዘቦታዊና ተርታ በሚመስሉ ቃላት ታላላቅና ውስብስብ ሃሳቦችን በቀላሉ ማቅረብ/መጻፍ መቻሉ ነው፡፡ ረቂቁ ቢሉ፣ ቀድሞ ያልተሰማ/ያልታወቀ፣ ጸናን ሃሳብ በነቢይ ብዕር የሚቀርበው በቀላል ቃላት ነው፡፡ በሚያጫውቱ፣ በሚያግባቡ፣ አሁን እየገባህ ነው አይደል እያሉ ሃሳባቸውን በሚያሰርጹ ቃላት፡፡
ነቢይ በንባብ፣ በልምድ እና በበርካታ ተጋልጦዎች የበለጸገ ታላቅ ገጣሚ ነው፡፡ እውቁ የሥነጽሑፍ መምህርና በተለይም የግጥም ተመራማሪ ብርሃኑ ገበየሁ የነቢይን ምልዑ ገጣሚነት ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡፡
“የራሱን የነቢይ ግጥሞች ኪናዊ ውበትና አማላይነት ከሦስት የገጣሚው ታላላቅ ችሎታዎች የሚነቃ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው፣ የተራችነት ችሎታውና የገጣሚው ሰፊ የባህል እውቀት፣ ሁለተኛው ታላቅና የማይመጠን የቋንቋ ችሎታው፣ ሦስተኛው ደግሞ የአገላለጹ ወርጅናሌነት፣ ትኩስነትና ትባት ነው::”
ሌሎችም መልከ ብዙ ሊያሰኙት የሚችሉ በርካታ ጸጋዎች የከያኒው ነቢይ ሀብቶች ናቸው፡፡ ነቢይ ማንም ሊያደምጠው የሚናፍቀው፣ እድሉን አግኝቶ ማዳመጥ ከጀመረም ሁለመናውን ጆሮ አድርጎ የሚያደምጠው ድንቅ ታሪክ ነጋሪ (storyteller) ነው፡፡ ይህንን አሌ የሚለኝ ቢኖር፣ በየመድረኮቹ ያወጋቸውን፣ እንዲሁም ቃለመጠይቆቹን እንዲያደምጥ እጋብዘዋለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ከእኔ ጋር እንደሚስማማ ጥርጥር የለኝም፡፡
በዚህ ሁሉ ላይ መልከ ብዙ ከያኒው ነቢይ ቀደምቶቹን ጸሐፍት የሚያከብር፣ ሥራቸውን ደጋግሞ የሚያወሳና የሚያከብር ትሁት ሰው ነው፡፡ ትሁትነት የነቢይ ብርቱ መገለጫ ይመስለኛል፡፡ የትኞቹንም ሃሳቦቹን በፍጹም እርጋታ ሲገልጽ ነው የምታገኙት፡፡ እሱ ቀድሞ የደረሰበትን ጉዳይ እንኳን ነቢይ የሚነግራችሁ በአዋቂነት መመካትና ኩራት ሳይሆን፣ በዛችው አፋራም ፈገግታ በከበባት የሠርክ ትህትናው ውስጥ ሆኖ ነው፡፡
እነሆ ነቢይም እንደቀደምቶቹ ሁሉ፣ የዚህችን ምድር ቆይታውን አጠናቆ ሥፍራውን ወደሌላኛው ዓለም ቢቀይርም ቅሉ፣ ራሱን በደማቁ የገለጠባቸው ታላላቅ ሥራዎቹ ሞትን አሸንፎ በትውልድ ውስጥ እንዲወሳ፣ ሃሳቦቹ እንዲጠቀሱ በዚህም ሕያው ሆኖ እንዲኖር ያስቻሉት ከያኒ ነው፡፡ ማንስ በቀጣዩ ትውልድ ውስጥ ሕያው ሆኖ ከመኖር በላይ ምንን ይመኛል?
ቸር እንሰንብት!