Administrator

Administrator


        በተመሳሳይ በበርካታ ፊልሞች ላይ በመተወን የሚታወቀው አርቲስት ጌታቸው እጅጉ (ባቡጂ)፤ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ሲሆን፤ የቀብር ስነ ስርዓቱ ሰኞ ዕለት በቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያ ንተፈጽሟል።
‘ሼፉ 2’፣ ‘ወደልጅነት’፣ ‘ጀማሪሌባ’፣ ‘ዕድሜለሴት’ የተሰኙና ሌሎች ከ60 በላይ ፊልሞች ላይ በመተወን በሙያው ለሀገሪቱ የራሱን አስተዋፅዖ አበርክቷል፡፡
በጥልቅ አንባቢነቱ ስሙ የሚነሳው ጌታቸው፤ መጽሐፍትን ስለመተርጎሙ፣ በብዕር ስም አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ስለመጻፉም በተለያዩ ጊዜያት መግለጹ አይዘነጋም፡፡


በተፈጥሮና በተለያዩ ምክንያቶች ለአካል ጉዳት ለተጋለጡ፣ የእግር መቆልመም፣ የወገብ መጉበጥና ልዩ ልዩ ችግሮች ላገጠሟቸው ልጆችና የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ለደረሰባቸው ልጆች ከቀላልና ውስብስብ ቀዶ ህክምናዎች ጀምሮ የተለያዩ ህክምናዎችን በነጻ በመስጠት የሚታወቀው ኪዩር ሆስፒታል፤ ሐምሌ 19 የሕዝብ መናፈሻ አጠገብ በሚገኘው የድርጅቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማውጣት የሚያካሂደውን የማስፋፊያ ግንባታ በይፋ አስጀመረ።
በዚሁ የማስፋፊያ ግንባታ የማስጀመሪያ ፕሮግራም ላይ የኪዩር ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ አደይ አባተ እንደተናገሩት፤ የማስፋፊያ ሕንፃ ግንባታው ተቋሙ ያለበትን የተደራሽነት ችግር በተወሰነ ደረጃ የሚያቃልልና የአገልግሎት አሰጣጡን አቅምና ጥራት ለማሳደግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
ሆስፒታሉ በአጠቃላይ ሕክምና ድጋፍ ሊስተካከል የሚችል ችግር ያለባቸውን ሕፃናት፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በመቀበል ነፃ የሕክምናና የመድሃኒት አገልግሎት በመስጠት ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ክራ አስፈጻሚዋ፤ የሕክምና ባለሙያዎችን ማሰልጠንና ማብቃት በሆስፒታሉ ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ይጠቀሳሉ ብለዋል።
የአገልግሎቱ ፈላጊዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱና፤ ሆስፒታሉ የሚሰጠው አገልግሎት ከታካሚዎች ቁጥር ጋር የማይጣጣም በመሆኑ ከፍተኛ ችግር አጋጥሞናል ያሉት ስራ አስኪያጇ፤ የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራት ለማሳደግና የስልጠና አቅሙን ለመጨመር ይረዳ ዘንድ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት የሚተገበር ግምቱ ከ10 ሚሊዮን ዶላር የሚልቅ የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ማስጀመሩን ገልጸዋል።
ሆስፒታሉ ባለፉት 15 የአገልግሎት ዓመታት፣ ከ118 ሺ 100 በላይ የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ልጆች፣ ሆስፒታሉ ከሚሠጠው አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ ከ33 ሺ 800 በላይ ነፃ የቀዶ ህክምና አገልግሎት ከመላ አገሪቱ ለመጡ ልጆች መሰጠቱን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡
በ2001 ዓ.ም የተከፈተውና አዲስ አበባን ማዕከሉን ያደረገው ኪዩር ኢትዮጵያ የልጆች ሆስፒታል፤ ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ባገኘው ህጋዊ ፍቃድና ከጤና ሚኒስቴር ጋር በገባው የፕሮጀክት ስምምነት መሠረት፣ ለአካል ጉዳተኛ ልጆች ነፃ የህክምና አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው፡፡

 

 

- "በጽናት እንታገላለን"

ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በትናንትናው ዕለት በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተደረገውን ሹምሽር ነቅፏል። ድርጅቱ ነቀፌታውን ያሰማው ዛሬ ማለዳ የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር በጻፉት ደብዳቤ ላይ ነው።

በደብዳቤው ላይ ህወሓትን ለማፍረስ ጥረት "ያደርጋሉ" ያላቸው ግለሰቦች በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ "ይሁንና በውጭም ሆነ በውስጥ ድርጅቱን ለማፍረስ ያደረጉት ጥረት ባለመሳካቱ፣ ድርጅቱ በጊዜያዊው አስተዳደር ውስጥ የተሰጡትን ስልጣኖች ከሕግ እና የተቋም አሰራር ውጪ የመንጠቅ ስራ አጠናክረው ቀጥለዋል" ብሏል። "የሕዝባችንን፣ የድርጅታችንን እና የፖለቲካችንን አንድነት ለመጠበቅ በትዕግስት እና በተቋማዊ አሰራር ስንታገል ቆይተናል" ያለው ህወሓት፤ "ዕለታዊ አዋኪ አጀንዳ በመፍጠር ሃላፊነት ላይ መቆየት የፈለጉ" ሲል የጠራቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች በዞን አመራርነት ደረጃ የሚገኙ የህወሓት አባላትን ከስልጣን ማውረዳቸው ገልጿል።

አያይዞም፣ "ይህ ድርጊት ህወሓትን ከስር መሰረቱ ነቅሎ የመጣል የተቀናጀ ዘመቻ ነው። በአንድ ወገን ብቻ የሚደረግ ሹምሽር ተቀባይነት የለውም" በማለት ነቀፋውን ያቀረበው ድርጅቱ፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ መዳቢነት የተሾሙ አመራሮች በስራ ቦታቸው ላይ ሆነው ስራቸውን መስራት እንደማይችሉ በአጽንዖት አመልክቷል። "በአንድ ወገን እየተደረገ ነው" ያለውን ድርጅቱን የማፍረስ እንቅስቃሴ "በጽናት እንታገላለን" ብሏል።

ህወሓት 14ኛ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔውን ማካሄዱ ተከትሎ፣ ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የድርጅቱ ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል "የራሳችንን አመራር በጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ መመደብ እንችላለን" ሲሉ "ኢትዮጵያ ኢንሳይደር" ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተው ነበር። ይሁንና በጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት መካከል የሚስተዋለው ፍትጊያ እያየለ ቢመጣ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እንደማያመሩ መግለጻቸው ይታወሳል።

ትናንት ከሃላፊነታቸው የተነሱት በጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔው በፖሊት ቢሮ አባልነት የተመረጡት ወይዘሮ ሊያ ካሳ ሲሆኑ፣ የደቡብ ምስራቅ አስተዳዳሪ ነበሩ። በእርሳቸው ምትክ የእንደርታ ወረዳ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ፀጋይ ገብረተኽለ መሾማቸውን ፕሬዝዳንት ጌታቸው ትናንት በጻፉት ደብዳቤ ጠቅሰዋል።

1 ከርሞ (ዕድሜን ኖሮ) ማለፍ
የሰው ልጅ ዕድሜ ደረጃዎች አሉት ብሎ ማወጅ አዲስ ግኝት አይደለም፡፡ ዕድሜ በዓለም የኑሮ ቆይታ ውስጥ ሆነው የሚሸመግሉበት/የሚያረጁበት ወይንም የሚያልፉበት ዓመታት ቀመር ነው ብለን ብንወስደውስ? አያስኬድም? በዓለም ላይ የምናየው ሁሉ (ሰው፣ እንስሳት፣ ዛፍ፣ ደንጊያ፣ መሬት፣ ቤት፣ …) በቁጥር የሚተመን የዕድሜ/መክረሚያ ቀምር/ቁጥር አለው፡፡
በሰው ዕድሜ ላይ ለመጻፍ የሞከርኩት ካለ ምክንያት አይደለም፡፡ ወጣቶች በእያንዳንዱ የዕድሜ አጥራቸው ዙሪያ መሥራት ያሉባቸውን ተግባራት እየፈጸሙ እንዲቆዩ፤ ማስተካከል ያለባቸውንም ባሉበት ተጨባጭ ሁኔታ ዝግጁ ሆነው ቀድመው የሚያነጣጥሩበትን ዒላማ ለመጠቆም ነው፡፡ ባለ ዕድሜዎች (ጎልማሶች፣ አረጋውያንና ሽማግሌዎች) ደግሞ እያንዳንዷን የሕይወት ጉዟቸውን በሀሳብ መለስ ብለው እንዲቃኙበትና ለቀሪው መክረሚያቸው እንዲዘጋጁበት በማሰብ ነው፡፡   
ማንም ሰው ፍጹም መሆን አይችልም፡፡ በረጅም ዕድሜና በጥሩ ስኬት ተሟልተው የተገኙ ካሉ በጣም ዕድለኛ የሆኑቱ ናቸው፡፡ ምናልባትም፤ ዘመን፣ ዕድሜና ምኞታቸው የተገጣጠሙላቸውና ረጅም የኑሮ ድልና ስኬት ያገኙቱ ደግሞ የተባረኩቱ ናቸው፡፡ በረከት ስጦታ እንጂ በዕድሜ ቆይታ/መክረም እና የሥራ ልፋት የሚያገኙት አይደለም፡፡ በረከት ለሁሉም ዕድሜ የሚቸር ስጦታ ነው፡፡ ዕድሜ በበረከት ምስጢር ውስጥ ተታትቶ (ተሸምኖ) ያለ መክረሚያ (ሕይወት) ነው፡፡
ኖሮ ማለፍ የቢሊዮኖች ዕጣ ፈንታ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ኖራችሁ ብቻ ለማለፍ አትኑሩ፡፡ ላኖረቻችሁ መሬት ምንም ነገር ሳትተዉላት ኑሮን ብቻ ኖራችሁም አትለፉ፡፡ ዛፍ እንኳን ቅርፊትና ቅጠሉን ለመሬት ትቶላት ያልፋል - ሊያዳብራት፡፡ ሲነድም አመዱ ይተርፋታል፡፡ ከመሬት በላይ ስታለፉት የኖራችሁት በስባሽ ሥጋ የሚቀበረው መሬት ውስጥ በመሆኑ፣ ለመሬት ያ ብቻ ይበቃታል ካላችሁ፣ ንፉግ ትሆናላችሁ፡፡ ከላይዋ ስትኖሩ የረገጣችኋት አንሶ፣ ለሁለተኛ ጊዜ መኖሪያ እንድትሆናችሁ ከውስጧ ስትከፈኑባት/ስትቀበሩባት መሬት እንኳን የምታዝንባችሁ ለመሆኑ አልጠራጠርም፡፡ ሁለቱንም ጊዜ ኖራችሁባት እንጂ ምንም ነገር ለመሬት አልተዋችሁላትምና እስቲ እዘኑላት? በላይዋ ላይ አንዲት ትንሽ ነገር እንኳን ተዉላት፡፡ ዕድሜን መቁጠር ይህን ካላከለ ምን ፋይዳ አለው?   
የሰው ልጅ የኑሮ ዓይነቱና ሂደቱ ብዙ ነው፡፡ በኑሮ ዘመኑ ምኞቱ በስኬት የተሟላለት፣ ግን ደግሞ ዕድሜን ያልተቸረ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው “በአጭር ባይቀጭ ኖሮ የት በደረሰ” ተብሎ ይወራለታል፡፡ ይቆጩለታል፡፡ “ቢኖር ኖሮ…” ብለው መኖሩን ይመኙለታል፡፡ በአጭር መቀጨት በራሱ አወያይ ሃሳብ ነውና ልዝለለው፡፡
ዕድሜ የተቸረውና ምኞቱ በስኬት የተሟላለት ሰው ደግሞ አለ፡፡ ያንን ዓይነቱን ሰው “በዕድሜው ሙሉ ምኞቱን አሳክቶ የኖረ ሰው ነበር” በመባል ይታወሳል፡፡ እንደሱ በሆንኩኝ የሚል ምኞትን የሚጭርባቸው ሰዎችም ቀላል አይሆኑም፡፡ በዙሪያው ተኮልኩለው ሞቱን/ማለፉን ሳይሆን ኑሮውን ይመኙታል፡፡ ለራሳቸው ዕድሜንና ስኬትን መመኘታቸው መሆኑንም ልብ በሉላቸው፡፡ ሌላው ደግሞ፣ ዕድሜ ተችሮት፣ ምኞቱን ሳያሳካና ማንም እዚህ ግባ ሳይለው ኖሮ ሊያልፍ ይችላል፡፡ ያን ዓይነቱን ሰው ደግሞ “የዕድሜ ጠናዛ” (ዕድሜውን ብቻ በመቁጠር በዓለም ላይ የኖረ) በማለት እንዳልተሳካለትና ቢሠራም የማይሆንለት እንደነበረ በማንሳት ይታወሳል፡፡ እንዲታወስ ካላቸው ቁጭት ሳይሆን፣ አንስቶ ለመጣል (ለወሬ) ሲሉ ያነሱታል (አንስቶ መጣልም ባህል ነው)፡፡ “አይጣል ነው!” ሲባል አልሰማችሁም?
ከጠቀስኳቸው ከሦስቱ ዓይነት ሰዎች የትኛው ይሻላል ብዬ በመጠየቅ ምርጫን አላቀርብላችሁም፡፡ ይህን ዓይነት ጥያቄ “ስድብ” ነው፡፡ ሁሉም ሰው በኑሮ ዘመኑ መታወሻ ነገር ያለው መሆኑን ግን ያዙልኝ፡፡ ወይ በስንፍናው፣ ወይ በክፋቱ፣ ወይ በታታሪነቱ፣ ወይ በመልካም ሥራው፣ በሃብቱ ወይንም በድሕነቱ እንዲታወስ ይሆናል፡፡ ይበልጥ የሚታወሰው ግን የሚታወስ ሥራ የሠራው ነው በማለት፣ ኖሮ ብቻ ያለፈውን ሰው እንዴት ማስታወስ እንደሚቻል እያሰላሰላችሁ አብረን እንዝለቅ፡፡
2. ዕድሜና ስኬት  
የሰው ልጅ ዕድሜ ከብዙ ክንዋኔዎች ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች ይገናኛል፡፡ በዓለም ላይ የሚገኝ አብዛኛው ስኬት (የሃብት፣ የሥራ፣ …) እና ድል (የድርጊት/ውድድር ለምሳሌ፣ ስፖርት) የሚገኘው በወጣትነት ዕድሜ ነው፡፡ ስኬትና ድል ሲጨምር፣ እውቅና እያደገና የግል ዝና እየገነነ ይሄዳል፡፡ የግል ዝና ለአገርም/ለዜጎችም ይተርፋል፡፡ በአንፃሩ፣ ድል ከእድሜና ከተለያዩ አካላዊና ስነ-ልቡናዊ ሁኔታዎች ጋር በቅርብ የተዛመደ በመሆኑ እየቀነሰ መሄዱ አይቀሬ ነው፡፡ በስፖርት (ለምሳሌ፣ ሩጫ፣ እግር ኳስና ቅርጫት ኳስ በመሳሰሉ መስኮች) በግልና በቡድን የተገኙ ድሎችንና ዝናን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ዕድሜ ሲጨምር የውድድር ስፖርትን የመከወን ኃይል/ጉልበት በእጅጉ ይቀንሳል፡፡ በእግር ኳሱም ይሁን በሩጫው በወጣትነት ዕድሜ ተጀምሮ ወደ ጉልምስናው ሲቃረቡ የማቆም ሂደት የሚዘወተረው ተሳትፎው ስኬትን በነበረው ሁኔታ ሊያስቀጥል ስለማይችል ነው፡፡ ሆኖም፣ ዝና በአንድ ወቅት በተከናወነ ሁኔታ ላይ መመስረት በመቻሉ የሚቀጥል ሲሆን፣ ስኬት ግን የዕለት ጥረት ውጤት ነውና ዕድሜ ሲገፋ ይለግማል፡፡ ስኬትን ለማስቀጠል በድል የጨበጡትን ዝናና ወረት (ገንዘብ) በስስት/በዘዴ ሊጠብቁት የሚገባው ለዚያ ነው፡፡  
ድልን ዕድሜ የሚጫነው በመሆኑ፣ በዕድሜው መግፋት ምክንያት ድል ያልቀናው ሰው የቀድሞ ዝናውን አያጣውም፡፡ እሱ ያገኘው ድል የራሱ ቢሆንም ከእሱ በኋላ የሚመጣ ወጣት ድሉን ሊጋራውና እንደ አርአያው ሊመለከተውም ይችላል፡፡ ሁሉም በዘመኑ ባለዝናና ባለድል ሆኖ ሊወደስና ሊከበር ይችላል፡፡ ልዩነቱ እያንዳንዱ ባለድል ድሉንና ዝናውን የሚጠብቅበት መንገድ ነው፡፡
ዝና የሰው ልጅ ስስ ብልት ነው - እስከ መጨረሻው በስስት ተንከባክባችሁ ጠብቁኝ ይላል፡፡ አንዱ ከአንዱ በአንጻራዊ ሁኔታ የተሻለ ድል ሊያስመዘግብ ይችል እንደሆነ እንጂ፣ ድል አንዴ ከተመዘገበ ለባለድሉ ቋሚ ዝና ይፈጥረለታል፡፡  አጭርም ሆነ ረዥም ዕድሜ፣ ተከናውኖ የተመዘገበን ዝና አይሽርም፡፡
ድል ለዝና፣ ዝናም ለበለጠ ድል የሚያነሳሱ/የሚያበቁ ናቸውና፤ ድል ሲቀዘቅዝ ዝና በነበረበት ግለት ላይቀጥል ይችላል፡፡ እውቅናው የጨመረለት ሰው ባገኘው እውቅና መኩራራቱም የተለመደ የሰው ባሕርይ ነው፡፡ ባለድል የሆኑ ጥቂት ሰዎች፣ ድልን እያጠነከሩ ካልሄዱ ዝና ሊቀንስ እንደሚችልና እውቅናም እንደሚጋሽብ የማያሰላስሉ ይኖራሉ፡፡ የዕድሜ ባለጸጋ የሆነ ባለዝና የሚኖረው አማራጭ፣ የነበረውን ዝና በሌሎች መልካም ተግባራት ማስጠበቅ ነው፡፡ እንደቀድሞው ያለ ሌላ ተመሳሳይ ድል ማስመዝገብ ላይሆንለት ይችላል፡፡ የዕድሜ ባለጸጎች ላገኛችሁት ዝና መጠንቀቅ ያለባችሁ፣ ዝናችሁ በዕድሜአችሁ አማካኝነት እንዳይበላሽ ነው፡፡ ቅርሳችሁ ስለሆነ ልትጠብቁት ይገባል ለማለት ነው፡፡
አንድ ጊዜ/ወቅት ድልን ከተጎናጸፉ በኋላ፣ ምንጊዜም በዚያ ዝና ብቻ እንዲሞገሱ “ሌላውን መተላለፌን ተውት” በማለት ለሰውም ሆነ ለራሳቸው ክብር የማይጠነቀቁ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ድሉ ያስገኘላቸው ዝና ቶሎ የሚያሰክራቸውና በፍጥነት ታይተው እንደጤዛ የሚረግፉም በርካታ ናቸው፡፡ አንዴ ባስመዘገቡት ድል እስከ ዕለተ-ሞታቸው ተከብረውና ተወድደው የሚኖሩ ዕድለኞችም አሉ፡፡ እኒህኞቹን በዘላቂነት ሊያስከብራቸው የቻለው ከድል በኋላ ያስመዘገቧቸው መልካም ባህሪያት ጭምር ናቸው፡፡ ድል ከመልካም ተግባርና ባህሪይ ጋር ሲጣመር የዝናን ዘላለማዊ የመሆን ዕድሉን ከፍ ያደርገዋል፡፡ ዕድሜም ክብር ተችሮት ከዝና ጋር አብሮ ይዘልቃል፡፡
ሰው በዕድሜው ምክንያት የበለጠ ድል የመሥራት/የማስመዝገብ አቅሙ እየደከመ ቢመጣም፣ ቀደም ተጎናጽፎት የነበረው ድል ዝናውን ጠብቆ የሚያቆይለት እየመሰለው መኩራራቱን ይቀጥላል፡፡ ድሉ ፈጥሮለት የነበረውን የዝና ሞቅታ ባለበት እንዲቆይ የሚችለውን ከማድረግም አይቆጠብም፡፡ በርካቶች ማበረታቻ እጽ እስከመጠቀም የሚደርሱት ለዚያ ነው፡፡ ያን ጊዜ የውድቀትን ቁልቁለት ይያያዙታል፡፡ ዕድሜ፣ ድልና ዝናም ከንቱ ይሆናሉ፡፡ በዚህ ረገድ ታሪክ ያሳየን ነገር አለ፡፡
የዓለም ምርጥ እግር ኳስ ተጫዋች የነበረውን ማራዶናን የማስታውሰው በቁጭት ነው፡፡ ማራዶና በድንገት ተከስቶ ብርሀኑን ለዓለም ያበራና በቶሎ የጠፋ ኮከብ ይመስለኛል፡፡ ዝናውና (የስፖርት ቤተሰቦች ፍቅርና ሀዘን) በእጽ ሱስ ተለክፎ በኑሮው የተንገዳገደባቸው ዓመታት ከሕሊና የሚጠፉ አይደሉም፡፡ ሮናልዲኒዮን የትኛው ላይ ልመድበው ይሆን? ድንቁ የኳስ ከያኒ ሮናልዲኒዮ (ስሙን በትክክል ጽፌው ይሆን?) ዕድሜ ብቻውን አልተሟገተውም፡፡ ያገኘው ዝና ከቁጥጥር ውጪ አውጥቶት የሚሠራውን አሳጣው ልበል? አሱንም ሳስብ ሀዘን ይሰማኛል፡፡  
ከፍተኛ ዝና ላይ የነበረውና፣ “የኳስ ንጉሥ” ተብሎ ተወዳጅነቱን እንደያዘ ተከብሮ በመኖር ለህልፈተ ሥጋ የበቃው፣ የዕድሜ ባለጸጋው የብራዚሉ ፔሌን ማየት ደግሞ በሌላው ጠርዝ የሚገኝ ትልቅ ትምህርት/አርአያነት ነው፡፡  
እግር ኳስን እንደ ምሳሌ ወሰድኩኝ እንጂ፣ በሁሉም ድልና ዝና በሚያስገኙ ስፖርቶች (ለምሳሌ፣ አትሌቲክስ፣ የቅርጫት ኳስ) ውስጥ የሚገኙ አያሌ ባለ ድልና ዝናዎች አሁንም አሉ፡፡ ለአብነት ያህል ግን የኳሱ ይበቃል፡፡ በአትሌቲክሱ ዘርፍ ከገባሁኝ፣ በአገራችን ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ዝናን ከዕድሜ ጋር ይዘው በጉዞ ላይ የሚገኙ ወጣቶች፣ ጎልማሶችና አረጋውያን አትሌቶች አሉን፡፡ የኋለኞች/የአሁኖቹ ከፊተኞች መልካም ቢማሩ፣ መልካምን ይሠራሉ፡፡  
በጥቅሉ፣ ባለ ድልና ባለዝናው ሁሉ በዕድሜው ምክንያት የለመደውን ሲያጣ የቀድሞውን ድልና ዝና በሃሳብ መመኘቱ የሰው ባሕሪ ነውና ቀድሞ ማሰብ ዋጋ አለው፡፡ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርስ ይበቃኛል ማለት እንደሚገባው ቀድሞ ካላሰበ፣ ወይም በእጁ ላለው ድልና ዝና ካልተጠነቀቀ፣ እንደ ቁማርተኛ ሰው መሆኑም እሙን ነው፡፡ ዕድሜ፣ አንድ ሥፍራ ላይ ሲደርሱ ያገኘሁት በቃኝ ማለትን የግድ ይላል፡፡ ጉልበትን፣ ወቅትን፣ ዕድሜንና ተጽዕኖውን ቀድሞ ማጤን ብልህነት ይመስለኛል፡፡
3. የቁማርተኛ ሰው ባህሪ
የቁማርተኛ ሰው ባህሪ ይገርመኛል፡፡ ድልን/ስኬትን ከቁማርተኛ ሰው ባህሪ ጋር ሳነጻጽር፣ ዕድሜም በውስጡ እንዳለበት እያሰባችሁ ተከተሉኝ፡፡
ቁማርተኛ ሰው ሲቀናው ብዙ ለማግኘት፣ ሳይቀናው ደግሞ እያደር ሊቀናው እንደሚችል እልህ ተያይዞ ቁማር “መጫወቱን” ይቀጥላል፡፡ ሊቀናውም ላይቀናውም ይችላል፡፡ የት ላይ ማቆም እንዳለበት መወሰን ይከብደዋልና ይቀጥላል፡፡ የሚታየው ያጣው (“የተበላው”) ገንዘቡ ነው፡፡
ከእልሁ የሚነቃው ደግሞ በእጁ የነበረው ገንዘብ በሙሉ ሲያልቅና ምንም ማድረግ እንደማይችል ሲረዳ ብቻ ነው፡፡ በጥቅሉ፣ ቀሪ ገንዘብ በእጁ ቢኖር ኖሮ የቀድሞ ገንዘቡን ሁሉ መልሶ ሊያገኝ እንደሚችል ይመኛል እንጂ፣ አልቻልኩም ብሎ ምኞቱንና እልሁን አይገታም፡፡ ምኞት፣ እልህን በውስጡ ቀላቅሎ የያዘ የሰዎች ሁሉ ጉልበት ነው፡፡ እልህ ደግሞ ለጥሩም ሆነ ለመጥፎ ነገር የማድረግ ኃይልን የሚቸር የሰው ድክመት ወይንም ብርታት ነው፡፡ እልህ ብርታት ሲሆን ሰውን ይገነባል፡፡ ድክመት ሲሆን ደግሞ ሰውን ያሳንሳል፡፡ ብርታትና ድክመት በሰው ልጆች የዕድሜ ሂደት ውስጥ የሚከሰቱ ጠባያት ናቸው፡፡
ብልህ ቁማርተኛ ሲበላና (በ ይላላ) ሲበላ (በ ይጥበቅ) ጠባዩና በዚያም ሳቢያ የሚወስናቸው ኤኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ይለያያሉ፡፡ ብልህ ቁማርተኛ የሚበላው (በ ይጥበቅ) ቀድሞ የበላውን የተቀናቃኙን ገንዘብ ነው፡፡ ከራሱ የሚሰጠው ጥቂት ነው፡፡ ሊያጣ የሚችለውን ሊያገኝ ከሚችለው አንጻር አስቀድሞ ያሰላል፡፡
ብዙው ቁማርተኛ ከእልሁ የሚነቃው ሁሉንም ገንዘቡን ካጣ በኋላ ሊሆን ይችላል፡፡ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ንብረታቸውን በመያዣነት አሲዘው የሚጫወቱ ቁማርተኞች አሉ ይባላል፡፡ ያጡትን ለመመለስ ካላቸው እልህና ምኞት በስተቀር፣ ያሲያዙትን ንብረት በተጨማሪ ሊያጡት እንደሚችሉ በዚያን የጫዎታ ወቅት የደረሱበት የባህሪ ለውጥ አይፈቅድላቸውም፡፡ የሚታያቸው በፊት ያጡት ገንዘብ ሊሆን ይችላል፡፡ ያጡትን መልሰው ማግኘት ሲመኙ፣ የያዙትን ማጣት ሊከተል መቻሉ ግን ሊያልፉት የማይችሉት እውነት ነው፡፡
በርካቶች ከዝና ማማ ላይ ወርደው ተንኮታኩተዋል፡፡ ተጎናጽፎት በነበረው ድል ሳቢያ የተቸረው ዝና እንደነበረ እንዲቆይ የሚመኝ እንዳለ ሁሉ፣ የተበላውን ቁማር ለመመለስ ንብረቱን ሁሉ አስይዞ በእልህ ወደ ኪሳራ የሚንደረደርም አለ፡፡ በእጅ ላይ ባለ ነገር መርካት ትልቅ ችሎታ ነው፡፡ እያንዳንዱ ዕድሜ፣ ድልና ዝና በእጅ ውስጥ የሚገኝ እንቁ ነው፡፡ የዕድሜን፣ የድልንና የዝናን ውኃ ልክ በማወቅ መኖር መልካም ነው፡፡
ይበቃኛል ማለት ከተቻለ፣ በእጅ ያለው ካጡት ይልቅ ይበልጣል፡፡ በቃኝ ማለት መቻል ትልቅ ዕውቀት፣ ሙሉ ሃብት ነው፡፡ ሁሉም ግን አይታደለውም፡፡ ቁማርተኛ ሰው በቃኝ ብሎ ቢያስብ እንኳን የመወሰን ችሎታውና የቁማሩ ባህሪ አይፈቅዱለትም፡፡ ዕድሜም የራሱ ባህሪያት አሉት፡፡ የዕድሜን ቁጥሩን እንጂ ሂደቱንና መጨረሻውን መገመትና መቆጣጠር ከባድ ነው - ጥሩው መጥፎ፣ መጥፎው ደግሞ መልካም ሆኖ ሊደመደም ይችላል፡፡ ዕድሜ አንዳንዴ ምስጢር ነው፡፡
ሰላም ለሁላችን፡፡

አንድ የሞንጎላውያን ተረት እንዲህ ይለናል፡፡
ከእለታት አንድ ቀን ጥንት፣ ግመል የዛሬው አጋዘን አይነት የሚያምሩ ቅርንጫፋማ ቀንዶች ነበሩት ይባል፡፡ ባለ አስራ ሁለት ቅርንጫፍ ቀንዶች ነበሩ፡፡ ቀንድ ብቻ አይደለም፤ እንዴት ያለ የሚያብለጨልጭ ሀር የመሰለ ጆፌ ረዥም ጭራም ነበረው፡፡
በዚያን ዘመን አጋዘን ደግሞ ቀንድ-አልባ ነበር፡፡ ሙልጭ ያለ ሌጣ ራስና አስቀያሚ መልክ ነበረው፡፡ ፈረስ ደግሞ ምንም ጭራ የሌለው ጉንድሽ ነበር፡፡
አንድ ቀን ግመሉ ውሃ ሊጠጣ ወደ ኃይቅ ወረደ አሉ፡፡ ውሃው ውስጥ ባየው የራሱ ውብ ምስል ተማረከ፡፡ “እንዴት  አምራለሁ!” አለ ለራሱ ራሱን በማድነቅ፡፡ “ምን አይነት ቆንጆ እንስሳ ነኝ እኔ!”
ይሄኔ አጋዘን ድንገት ከጫካ ብቅ ብሎ እያለከለከ መጣ፡፡
“ምን ሆነህ እንዲህ ትንፋሽ እስኪያጥርህ ታለከልካለህ ወዳጄ አጋዘን?” ሲል ጠየቀው ግመሉ፡፡
“አንተ ታድለሃል! እርጥብ ፀሐይ የመሰለ ቆንጆ መልክ ያለህ እንስሳ ነህ! እኔ ግን ምስኪን ነኝ፡፡ ዛሬ ማታ እንስሳት በሙሉ ወደሚሳተፉበት ፌስቲቫል የክብር እንግዳ ሆኜ ተጋብዤ ነበር፡፡ ግን ምን ያደርጋል…”
“መቼም እንዲህ ያለ በነፃና በክብር የተጋበዝክበት ፀጋ በዋዛ አይገኝም” አለ ግመሉ፡፡
“እሱስ ነበር፡፡ ግን እንዲህ ያለ የተገጠበ ግንባር ይዤ ከነአስቀያሚ መልኬ እንዴት ብዬ እንስሳቱ ፊት እቀርባለሁ? እንደምታውቀው ነብር ዥጉርጉር ውብ ቆዳውን ይዞ የሚቀርብበት ድግስ ነው፡፡ ንሥርም ማራኪ ላባዋን የምታሳይበት መድረክ ነው፡፡ እኔ ምንም ቦታ አይኖረኝም፡፡ እባክህ ግመል ሆይ፤ ለአንድ ሁለት-ሦስት ሰዓት ቀንዶችህን አውሰኝ፡፡ መልሼ ልሰጥህ ቃል እገባልሃለሁ፡፡ ነገ በጠዋት የመጀመሪያ ሥራዬ፣ ያንተን ቀንድ መመለስ ነው ሲል” ተማፀነው፡፡
“ይሁን እሺ” አለ ግመል በለጋስ ኩራት፡፡ “እርግጥ አሁን ባለህበት ሁኔታ በጣም አስቀያሚ ነህ፡፡ ይህም ያሳዝነኛል፡፡ ስለዚህ ለዛሬ ማታ ተጊያጊያጥበትና አምረህ ቅረብ” አለና ባለቅርንጫፍ ቀንዶቹን አውልቆ ያውሰዋል፡፡ አጋዘኑ ጮቤ እየረገጠ ፈረጠጠ፡፡ ከዚያ ግመሉ አስጠነቀቀው፡፡ “ግን ልብ አድርግ፡፡ አንዲት ቅባት ወይም የፍሬ ጭማቂ ምናምን ይፈስስበትና ዋ!”
የፈረጠጠውን አጋዘን መንገድ ላይ ፈረስ አገኘውና፤
“እኔ አላምንም፤ እንዴት የሚያምር ቀንድ ነው ያለህ?” አለው፡፡
አጋዘን - “ቀንዴ በጣም ያምራል አይደል?! ግመል ነው የሰጠኝ” አለ፡፡
ፈረሱ - “እ….. እንዲህ ከሆነማ እኔም በጨዋ ወግ ከጠየቅሁኝ ግመል ለኔም የምፈልገውን ይሰጠኝ የሆናል!” አለ፡፡
ይሄ ሁሉ ሲሆን ግመሉ ኃይቁ ጋ ውሃ እየጠጣ፣ የበረሃዋን ጨረቃ ማድነቁን ቀጥሏል፡፡
በመጨረሻ ፈረስ ወደ ግመሉ ይመጣል፡፡
“ወዳጄ ግመል እንደምን አለህልኝ? ይገርምሃል ስፈልግህ ነው የተገናኘነው፡፡ እባክህ ለዛሬ ምሽት ውብ ጭራህን አበድረኝ ውለታህን እከፍላለሁ፡፡ ያቺን ያንተ አድናቂ የሆነችውን ፍቅረኛዬን በቅሎን ዛሬ ማታ አገኛለሁ፡፡ መቼም ያንተን ጭራ አድርጌ ፊቷ ብኩነሰነስ ልቧ ቅልጥ ነው የሚለው!”
ግመል በሚያምር ጭራው ኮራና የቀረበለት ጥያቄ አነሆስለው፡፡
“እውነትክን ነው? የእኔው አድናቂ ናት ማለት ነው? በል እሺ ለጊዜው ጭራ እንለዋወጥ፡፡ ግን ልባርግ ነገ በጠዋት አንዲት ፀጉር ሳትበላሽ እንድትመልስ፡፡ እንደምታውቀው በዓለም ላይ ያለው ምርጥና ቆንጆ ጭራ ይሄ ብቻ ነው!” አለና አስጠነቀቀው፡፡
ከዚህ ቀን በኋላ ብዙ ወራትና ብዙ አመታት አለፈ፡፡ ያም ሆኖ አጋዘኑ የግመሉን ቀንዶች አልመለሰለትም፡፡ ፈረስም ይሄው ዛሬ በየኮረብታው ላይ በግርማ ሞገስ ሶምሶማ የሚረግጠው፣ የግመሉን የተውሶ ጭራ እየነሰነሰ እንዳማረ እንደኮራ አለ፡፡ አንዳንድ ስዎች አንደሚሉት፤ ዛሬ ዛሬ ግመል ውሃ ሊጠጣ ወደ ኃይቅ በወረደ ቁጥር ሌጣና አስቀያሚ መልኩን ባየ ጊዜ ሁሉ ወደ ኋላው አፈግፍጎ እንደማስጎስበት ይላል፡፡ በዚያው የውሃ ጥሙን ይረሳዋል፡፡ በተጨማሪም ግመል አንገቱን ሰገግ አድርጎ ማዶ ማዶ እያየ የተከመረ አሸዋ ወይም ራቅ ያለ የተራራ ጫፍ ሲያይ በልቡ እንዲህ እያሰበ ነው ይላሉ፡-
“ለመሆኑ ያ ፈረስ ጭራዬን የሚመልስልኝ መቼ ነው?” ግመል ሆሌ ሀዘንተኛ የሚመስለን በዚሁ ምክንያት ነው ይባላል፡፡
*           *          *
በሀገራችን የአንዱ መሰረታዊ ንብረት የሌላው ማጌጫና መጠሪያ የሆነበት፣ ያንዱ ደግነትና ለጋስነት ሌላው በብልጥነት ግብር የሚጠራበት ካርድ የሆነበት ሁኔታ በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ያንዱ ልባዊ መስዋዕትነት የሌላው መኳያና መዳሪያ፣ የሌላው ዓለም ማያ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ ያንድ ጊዜ ግፍ ቁስሉ ሳይጠና ሌላ ግፍ በመጨማመር ያለፈውን ጥፋት ህጋዊ ለማድረግ መጣር በጣም የተዘወተረ ባህላዊ ተግባር ሆኗል፡፡ “የዝንጀሮ ልጅ ከተራራ አይወድቅም፡፡ አመለኛም አመሉን አይተውም” እንዲሉ ማለት ነው፡፡
ስንቱ መፈክሩን፣ ጥንስስ ሀሳቡን፣ እውቀቱን ተነጥቆ ሌላው በየአደባባዩ እንቁልልጬ ሲሉት እንደግመሉ “ለመሆኑ ያ ፈረስ ጭራዬን የሚመልስልኝ መቼ ነው?” ከሚል ልመናዊ ምኞት ባሻገር አማራጭ አጥቶ ቁጭ ብሏል፡፡
“የራስህ ዲሞክራሲ ነው፤ ሰጪም ነሺም የለብህም” ተብሎ ባዶ እጁን የተቀመጠ ስንቱ ነው? ትላንት ራሱ ባጠረው አጥር ከጨዋታው ውጪ ሆኖ እንቁልልጭ ሲባል የሚውል ስንቱ ነው? አባብሎ ለምኖ፣ ቅበረኝ ብሎ ጎጆ - ወጥቶ አላውቅህም ሲባል አፉን የዘጋ ስንቱ ነው? ውሃ ጠምቶት እንደ ግመሉ ጥሙን የረሳ ስንቱ ነው? ብዙ ጊዜ ተነስተው፣ ብዙ ጊዜ ተድበስብሰው፣ እንደገና ብዙ ጊዜ የሚያዳክሩን ስንት ጉዳዮች ይሆኑ?
ልመናዎች፣ ማቆሻበሎች፣ ያላንተ ማን አለኝ መባባሎች ለህዝብ ብዙ ፋይዳ እንዳልሰጠው ብዙ የቅርብና የሩቅ ትውስታዎች ይነግሩናል፡፡ ሁሌም ልብ የማይባለው ግን “አገጭህን ይዞ የሚለምንህ በጥፊ ሊልህ” የሚለው ተረት ነውና፣ ዛሬም በአፅንኦት ግንዛቤ ውስጥ ሊቀመጥ ይገባል!

(የኢዜማ የቀድሞ ዋና ጸሐፊ)

ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣
የቀድሞ ኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ
ከሃላፊነታቸው በገዛ ፈቃዳቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።  
የለቀቁበትን ምክንያት ለፓርቲው ባስገቡት የመልቀቂያ ደብዳቤ ላይ ሲገልጹ፣
ከፓርቲው አቋምና አካሄድ ጋር “ባለመስማማታቸው”  መሆኑን ጠቅሰዋል።
አቶ አበበ ከአዲስ
አድማስ ጋር ባደረጉት ቆይታ ከኢዜማ የለቀቁበትን  ምክንያትና
ስለፓርቲያቸው በዝርዝር ያብራራሉ፤
ቀጣይ የፖለቲካ መዳረሻቸውንም
ያመላክታሉ እነሆ፡-


ከኢዜማ ለመልቀቅ ያስገደድዎ ዋና ዋና ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
እንግዲህ ላለፉት አምስት ዓመት ከሶስት ወራት አካባቢ የኢዜማ ዋና ጸሃፊ በመሆን፣ ፓርቲውን ሳገለግል ነበር። መጀመሪያ የነበረውን የፓርቲውን ቁመና ስናይ፣ በጣም ጠንካራ የሆነ መዋቅር በመላ አገሪቱ ያለው፤ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከፍተኛ የሆነ መገዳደርን ያሳየ፣ ብዙ ዕጩዎችን በማቅረብ ከገዢው ፓርቲ ሁለተኛ ሆኖ ቀጥሎ የነበረ ፓርቲ ነው። በዚያ ውስጥ መዋቅራችንን ዘርግተን በደንብ በጥንካሬ ነው የተንቀሳቀስነው። ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ግን ፓርቲው ቀስ እያለ ለሕዝብ ያለውን ወገንተኝነት ወይም የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ መጣ። መዋቅሩም ከምርጫ ማግስት ጀምሮ ፓርቲው በሚይዛቸው የተለያዩ አቋሞች ምክንያት ከፓርቲው እየተነጠለ ሲመጣ፣ እጃችን ላይ ቀስ እያለ እየሟሟ መምጣት ጀመረ። አንድ የሚገዳደር ፓርቲ መሆን አልቻለም። የመለሳለስ ባሕርይው ተከታዮችንም፣ አባላትንም እያሳጣው መጣ። ይህን ጉዳይ በብዙ መልኩ ብንሞክርም፣ ማስታረቅ አልተቻለም። ከመንግስት ጋርም አብሮ በመስራት ሂደት ውስጥ “ምንድን ነው ፓርቲው ያገኘው? አገር ምን ተጠቀመች? ፓርቲውስ ምን ተጠቀመ?” የሚለው መገምገም ነበረበት። መጀመሪያ እኛ ማድረግ የነበረብን ፓርቲውን ማቆም ነው። ፓርቲው ቆሞ፣ እንደ አገር ተገዳዳሪ፣ ተፎካካሪ ሆኖ በደንብ መውጣት የሚችል ፓርቲ መሆን አለበት። በአንድ በኩል ገዢው ፓርቲ ብቻ በየአምስት ዓመቱ እየተመረጠ አይደለም የሚገዛው። ሕዝቡ ሲከፋው፣ ‘’ይኼኛውን ፓርቲ ስልጣን ላይ አውጥተን እንሞክረው” የሚል መሆን አለበት። ይህን መሆን አልቻለም። ከዚህ ይልቅ እያደር እንደበረዶ እጃችን ላይ መሟሟት ሲጀምር፣ ጉዳዩን ቆም ብለን ማጥናት አልቻልንም። ከዚህ መታደግ ስላልተቻለ፣ በዚህ ዓይነት መቀጠሉ የትም እንደማያደርስ ሳይ፣ በቃ -- እዚያ ውስጥ ጊዜዬን ማባከን አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ፓርቲውን ትቼ ወጥቼያለሁ።
ቅድም የጠቃቀሷቸው ነገሮች አሉ። ፓርቲው በጊዜ ሂደት የሕዝብ ድምጽ የመሆን አቅሙ እየቀነሰ “መጥቷል” ብለዋል።  ይህን አቅሙን በትክክል መቼ ላይ ነው  እያጣ የመጣው?
ከምርጫው ማግስት በኋላ፣ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ስምምነት ከተደረገ በኋላ፣ ቀስ እያለ ይህን አቅሙን እያጣ መጣ። ከመንግስት ጋር መስራት ሌላ፣ የሕዝብ ድምጽ መሆን ሌላ። ይህን ብለን ነው አብሮ መስራት የሚለውን ያኔ የተቀበልነው። “አብሮ መስራት” የሚለው ቋንቋ በደንብ መገምገም አለበት። ቅድም እንዳልኩህ ምንድን ነው ለፓርቲው የጠቀመው? አንደኛ ፓርቲው ማደግ መቻል አለበት። አስራ አራት ሚሊዮን አባል “አለኝ” ከሚል ፓርቲ ጋር ነው የምንገዳደረው። አስራ አራት ሚሊዮን ማለት አንድ ሶስተኛ ወይም አንድ አራተኛ መራጭ ሕዝብ ማለት ነው። ስለዚህ ከዚህ ጋር የሚገዳደር ፓርቲ የራሱን መዋቅር እየዘረጋ፣ 547 መቀመጫዎችን ጭምር ሸፍኖ፣ ስራ መስራት ሲገባው፣ በዚህ ደረጃ እጁ ላይ ያለውን መዋቅር ጭምር እስከ ማጣት ድረስ ቁልቁል መውረድ “ምንድን ነው ተስፋው?” የሚለው ነገር በጣም ነው ጥያቄ የሚፈጥርብኝ። ታግለህ ለውጥ የማታመጣ ከሆነ፣ ታግለህ ልዩነት ፈጥረህ ለሕዝብ ድምጽ መሆን የማትችል ከሆነ፣ ነገ ወደ ስልጣን የመምጫው መንገድ በየቀኑ እየጠበበ የሚመጣ ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ …ተቃዋሚ ብቻ መሆኑ? ይሄ ደግሞ ሞልቷል በጣም! በዚህ መልኩ የሚቃወሙ  ፓርቲዎች ናቸው ያሉት። አማራጭ ይዘን የምንቀርብ አለመሆናችን በጣም ነው የሚያሳዝነው።
ወደ እርስዎ ስንመጣ፣ ኢዜማ በሚከተለው የፖለቲካ አካሄድ መቼ ነው አመኔታዎን የቀነሱት? በምን ምክንያት?
ይህን ነገር ማሰብ ከጀመርኩ ወደ አንድ ዓመት ገደማ ይሆነኛል። ከአምና ጀምሮ ጥሩ አመለካከት አልነበረኝም። ይሄ ነገር በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ የእኔ ከዚህ ፓርቲ ጋር መቀጠሌ “እስከ ምን ድረስ ነው?” የሚል ጥያቄ በውስጤ አነሳለሁ፤ ብዙ ጊዜ። ብዙ የምቀርባቸው ሰዎች ትንሽ እንድቆይ ይገፋፉኝ ነበር። ነገር ግን በየጊዜው የማያቸው ነገሮች -- አንደኛ ፓርቲው ቀድሞ ከነበረው ወደ 4 መቶ የምርጫ ክልሎች አካባቢ መዋቅር ዘርግተን እንንቀሳቀስ ነበር። ዛሬ ግን ያ የለም። ጭራሽ ቁልቁል ነው የሄደው። የቀሩትን አይደለም ለመድረስ፣ ያሉትንም ከእጃችን እያጣን ነው። የሸፈንናቸው አካባቢዎችን ጭምር … በጣም ነው የሚያሳዝነው … በየጊዜው አባላት እየቀነሱ እና እየጫጩ ነው የመጡት። መዋቅሩ ችግር ውስጥ ሲገባ እየተመለከትኩ ነው። ይህንን ቆም ብለን ገምግመን፣ “ምንድን ነው ችግሩ?” ብለን፣ ችግሩን ለይተን መስራት ነበረብን። ይህን ማሰራት የሚችል ነገር የለም። “ከመንግስት ጋር አብሮ መስራት” የሚለውን ነገር መገምገም አለብን። “በመስራት የተገኘው ጥቅም ምንድን ነው?” ማየት መቻል አለብን። የጎዳን ነገር ካለ፣ ቆም ብለን ማሰብ ያስፈልገናል። “እንዴት ነው ከመንግስት ጋር እየሰራን ያለነው? በምን ያህል ፍጥነት እየሄደ ነው? ስንት ቦታ ነው የምንሰራንው? ምን ያህል ሰው ነው ሃላፊነት ላይ ያለው? ስንት ክልሎች ላይ ነው የምንሰራው?” -- ይህን በደንብ ተገምግሞ ቆም ብለን በዚህ ሶስት ዓመት ውስጥ ማሰብ ነበረብን። ይሄን ማድረግ አልቻልንም። እንዴት አንድ ፓርቲ በየዓመቱ ያለውን ውድቀት እና ከፍታ አይፈትሽም? መቼም ኢዜማ በሰነድ አይታማም። የያዘው አቋም፣ ያለው ፕሮግራም በጣም አመርቂ ነው። ማኒፌስቶዎቹ በጣም አጓጊ ናቸው። የዜግነት ፖለቲካን በመስበክ እንደኢዜማ ዓይነት ፓርቲ የለም። በጣም ጥሩ ነገር ነው ያለው። ነገር ግን ተግባራዊ የማይደረግ ከሆነ፣ ማኒፌስቶውን እና ፕሮግራሙን ብቻ እያደነቅን መኖር አያስኬድም። መተግበር አለበት። ሁለተኛ በአንድ ወቅት የነበረህን ድጋፍ እያጣህ ትመጣለህ። የአንድ ፓርቲ ትልቁ ሃላፊነት ለምርጫ ከመወዳደር ባሻገር፣ ገዢው ፓርቲ የሚያደርሰውን ተጽዕኖ ዕለት በዕለት፣ እግር በእግር ተከትለህ እየነቀስክ ማጋለጥ ነው፤ ትልቁ ነገር። ኢትዮጵያ በብዙ ችግሮች የተወሳሰበች አገር ነች። ችግሮቿ ፖለቲካዊ ናቸው። የመንግስትን አካሄድ እየነቀስክ አውጥተህ መንቀፍና እንዲያስተካክል መታገል አስፈላጊ ነው የሚሆነው። ዝም. . .ዝም የምትል ከሆነ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ሕዝቡ. . .በየጊዜው እየጠላን. . .እየራቀን. . .ድጋፉን የሚሰጠን እያጣን ሲመጣ፣ የራሱ አባላት እና አመራሮች ለቅቀው ሲሄዱ፣ ምንድን ነው ትርጉሙ? ይሄን ማስተካከል  አልተቻለም።
እንግዲህ እርስዎ በፓርቲ አመራር ላይ እያሉ፣  ሌሎች ቀድመው ፓርቲውን ለቀዋል። የእርስዎና የእነሱ የመልቀቅ ሰበብ ይለያያል?
የሁለታችን አለቃቀቅ ይለያያል እኮ! እነርሱ የለቀቁት ፓርቲው የመጀመሪያውን ጉባዔ አድርጎ፣ ሁለተኛ ዙር ምርጫ ሲያደርግ ነው። ምርጫው ላይ ተወዳድረዋል። መሪም፣ ሊቀ መንበርም ለመሆን። በዚያ ሂደት ውስጥ አልፈውበት ሄደዋል። ከዚያም በኋላ፣ ለወራት ያህል ከፓርቲው ጋር ቆይተዋል። እኔ ግን በዚያ ሰዓት ላይ በምርጫው ተሳትፌ፣ የያዝኩትን ቦታ እንደያዝኩ በከፍተኛ ድምጽ ተመርጬ አልፌ ነው የመጣሁት። የእነርሱ አለቃቀቅ እና የእኔ አለቃቀቅ አይገናኝም። “ለምን አንድ ላይ አልሆነም?” ለሚለው፣ ምንም የሚያገናኘን ነገር የለም። ስለዚህ ያንን ማነጻጸር አይቻልም። በመሰረቱ፣ እኔ ሰውን ተከትዬ አልወጣም። በራሴ ጊዜ ነው። “ዘግይተሃል” የሚለውን አልቀበልም። “ከአሁን አሁን ይሻሻላል” የሚል ዕምነት ነበረኝ። በተለይ፣ ሁለተኛው ዙር ምርጫ ከተደረገ በኋላ፣  የነበረው መገፋፋት ይቆምና ፓርቲው በደንብ ተጠናክሮ ይወጣል የሚል የጸና አቋም ነበረኝ። ይህንን ደግሞ መጠበቅ ግድ ነው የሚለው። እርሱን ጠብቄያለሁ። እኔ ያሰብኩት ሃሳብ ባለመሳካቱ፣ “ዘግይቼያለሁ” ብዬም አልቆጭም። የወጣሁበት ተገቢ ሰዓት ነው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ የእኔ አወጣጥ ከእነርሱ ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። አሁንም ማንም “ውጣ” ብሎ ያስገደደኝ የለም። በዚህ ዓይነት መቀጠል እንደማልችል ሳውቅ፣ በፈቃዴ ነው ሃላፊነቴን የለቀቅኩት።
አንዳንድ ወገኖች “ኢዜማ የገዢው ፓርቲ ተላላኪ እንጂ ራሱን የቻለ እንቅስቃሴ የሚያደርግ ፓርቲ አይደለም” የሚል ፍረጃ ያቀርባሉ። እንደ አንድ የቀድሞ አመራር ይሄን ፍረጃ  እንዴት ይመለከቱታል?
በዚህ ደረጃ ፓርቲውን ማውረድ ጥሩ አይደለም። ብዙዎች ‘ተለጣፊ’ የሚል ስያሜ  ይሰጣሉ። ከዚህ አንጻር ይህን ያስባለን አብሮ መስራት የሚለውን በግልጽ ለይተን መጠቀም ስላልቻልን ነው። የቱ ጋ ነው አብረን የምንሰራው? አገርን ከማልማት እና ሰላምን ከመጠበቅ አንጻር? የቱ ጋ ነው የምንቃወመው? የሚለውን ለይተን ባለመንቀሳቀሳችን የተፈጠረ ነው፤ ይህ ስያሜ። አንዳንዴ ሕዝቡ እንደዚህ ቢለን አትፈርድበትም። ስለዚህ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው የሚሆነው።
ያኔ ከመንግስት ጋር አብሮ የመስራት ጉዳይ እንደአጀንዳ ሲቀርብ፣ እርስዎ እንደደገፉት ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የድጋፍ ድምጽ በመስጠትዎ የመጸጸት ስሜት ይሰማዎታል?
ምንም አልጸጸትም። እኔ ብቻ አይደለሁም። ለቅቀው የወጡት፣ እነ አንዱዓለምም -- እነ የሺዋስም -- በስራ አስፈጻሚም፣ በጉባዔው ላይም ደግፈነዋል እኮ፤ “አብሮ መስራት” የሚለውን ሃሳብ። ይህ ምንም ሊዋሽ አይገባውም። አብሮ መስራት ማለት እኮ ለዘላለም መጣበቅ አይደለም። ቆም ብሎ አስቦ የማያሰራ ጉዳይ ካለ፣ ገምግሞ ለቅቆ መውጣት ይቻላል። በወቅቱ ያንን ውሳኔ መወሰናችን ስሕተት አልነበረም። ስሕተቱ እኛ ጋ ነው። እኛ ያንን ገምግመን “ምን ላይ ደርሷል?” ብለን፣ የምንወጣ ከሆነ ገምግመንና ጉዳቱ ካመዘነ በጉባዔ አስወስነን ለቅቆ መውጣት ይቻላል፤ “አብሮ መስራት አያስኬደንም” ብለን። የእኔ ጥያቄ “ለምን መገምገም ተሳነን?” የሚል እንጂ የተወሰነውን ውሳኔ ሁላችንም ተስማምተን የወሰንነው ነው። በዚህ ቅር አይሰኝም። ያኔም ትክክል ነበርኩ፤ አሁንም ትክክል ነኝ። የተቃውሞ ሃሳባችን ለመግለጽ አያግደንም። ምክንያቱም በርካታ ፓርቲዎች ከመንግስት ጋር አብረው እየሰሩ፣ የሕዝብ ድምጽ ሲሆኑ እንሰማቸዋለን።
መጀመሪያ አንድነት ለዴሞክራሲ እና ለፍትሕ (አንድነት)፣ በኋላም ሰማያዊ ፓርቲ ውስጥ ነበሩ። አንድነት ሲፈርስ፣ እርስዎና ጓዶችዎ ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ገብታችሁ ነበር። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ያለው የእርስዎን የፖለቲካ ተሳትፎ ላይ “ንግግራቸውና ተግባራቸው አይገጥምም የሚሉ ወገኖች አሉ። የእርስዎ ምላሽ ምንድን ነው? ራስዎን እንደ አንድ ፖለቲከኛ እንዴት ይገልጡታል?
እኔ የኢዜማ መዋቅሮችን ድምጽ የምሰማ፣ አባላቱ እና አመራሮቹ በሚገባ የሚወዱኝ፣ ድምጽ መሆን የሚገባኝ ቦታ ላይ ለእነርሱ ድምጽ የምሆን፣ በግሌ ማድረግ የሚገባኝን ነገር ሃላፊነትን ሳላይ የማገለግል፣ አንዳንዴም አስቸጋሪ ነገር ሲመጣ፣ በዚህ ዕድሜዬ ቢሮ አድሬ የማገለግል ነበርኩ። ለነፍሴ ሳልሳሳ በስድስተኛው ዙር አገራዊ ምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከአዲስ አበባ እስከ አርሲ -- ሲሬ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ይርጋጨፌ ድረስ፣ ትልቅ ስራ ስሰራ የቆየሁ ሰው ነኝ። ከዚህ ባሻገር የፖለቲካ ነገር ሆኖ፣ ምናልባት ቃል ገብተንላቸው ያልተሳካ ነገር ካለ፣ እኔ ብቻ ሳልሆን በጋራ ነው የምንጠየቀው። በግሌ የማደርገው ነገር ስለሌለ ማለት ነው። የጋራ አመራር ነው ያለው። አንድነት ፓርቲ ውስጥ በቆየሁበት አጭር ጊዜ በጣም በርካታ ስራዎችን ሰርቼ፣ ፓርቲው ሲፈርስ ዕንባ አውጥቼ አልቅሼ፤ በወቅቱ የታሰሩ የትግል ጓዶች ስለነበሩ፣ እነርሱን ጥለን ቤት አንቀመጥም ብለን ነው ሰማያዊን የተቀላቀልነው። የነበረው አማራጭ ሰማያዊ ፓርቲ ብቻ ነው። እዚያም የራሴን የትግል አስተዋጽዖ አድርጌያለሁ። መክፈል የሚገባኝን … ትብዛም፣ ትነስም …መስዋዕትነት ከፍያለሁ። ከዚህ አንጻር እኔ ቃል ገብቼ ያልተሰሩ ስራዎች ካሉ፣ እንዲህ ነው ተብሎ ቢነገረኝ፣ ደስ ይለኛል፤ በደፈናው ከሚሆን።
አሁን ላይ -- ከኢዜማ ለቅቆ እንደወጣ አንድ ፖለቲከኛ … ፓርቲውን በሩቁ ሲመለከቱት፣ ምንድን ነው የሚሰማዎ? ለራስዎ ስለፓርቲው ምን ይነግሩታል?
ገና አስረኛ ቀኔ ነው ትቼ ከወጣሁ። እየሰራኋቸው ያሉ ስራዎች አሉ። በደንብ አድርጌ የማነብባቸው ነገሮች አሉ። የምፈትሻቸው ነገሮች አሉ። በቅርብ ጊዜ ውስጥ አንድ የራሴን አስተያየት ስለኢዜማ እሰጣለሁ። ፓርቲው ተጠናክሮ ቢወጣ ደስ ይለኛል። ምንም ጥርጥር የለውም። የሚቀጥለው ትውልድ ተክቶት ቢሰራ፣ ጥሩ ፕሮግራም አለው፤ ጥሩ ማኒፌስቶ አለው። ራስን አጠንክሮ፣ ድክመትን ፈትሾ መውጣት ነው።
ቅድም ያነሷቸው የፓርቲው ሳንካዎች አሉ። እነዚያን ፓርቲው አርማለሁ ቢል፣ እርስዎ ወደ ኢዜማ ይመለሳሉ?
እኔ ከዚህ በኋላ፣ ወደ ኢዜማ አልመለስም። ጓዜን ጠቅልዬ ነው የወጣሁት። ከአባልነትም፣ ከአመራርነትም ነው ራሴን ያገለልኩት። ነገር ግን እኔ ካልበላሁ፣ ጭሬ ላጥፋው አልልም። የሚቀጥለው ትውልድ እኔ የምነግርህን ድክመቶች. . .አሁን አልተናገርኋቸውም፣ ወደፊት የምናገራቸውን አርሞ የሚወጣ ከሆነ፣ በጥንካሬው በጣም ደስ ይለኛል። ቅር አይለኝም። ትልቅ አማራጭ ፓርቲ አድርጎ ማውጣት ተገቢ ነው። “ለምን እኔ አልኖርኩበትም?” ብዬ አልቆጭም።
ከዚህ በፊት የጠቀሱልኝን ድክመቶች በሚመለከት፣ እርስዎ ያደረጓቸው የውስጠ ፓርቲ ትግሎች ነበሩ?
የጎንዮሽ ፍትጊያውን ሳልፋተግ፣ ዝም ብዬ አልወጣም። ስላልቻልኩ ወጥቼአለሁ። ሃይሌን መጨረስ የለብኝም ብዬ ነው የወጣሁት። ወደፊት እርሱን እገልጸዋለሁ።
በእርስዎ የቀድሞ የትግል አጋሮች “የንጋት ኮከብ” የተሰኘ አዲስ ፓርቲ እየተቋቋመ ነው። ስለዚህ ፓርቲ  መረጃ ነበረዎ? ወይስ እንደማንኛውም ሰው ነው የሰሙት?
እኔ እንደማንም ሰው ነው የሰማሁት። የእኔ ጉዳይ ከእነርሱ ጋር የሚነካካ አይደለም። አማራጭ ፓርቲ መመስረት ካስፈለገ፣ መመስረት ነው። እኔ ግን በግል ዕይታዬ ተፈልፍሎ ያለ ፓርቲ ብዙ ነው። አዲስ ፓርቲ አቋቁሞ እንደገና ከዜሮ መጀመር ከባድ ነው። ያሉትም በዝተዋል። እንመሰርታለን ካሉ ደግሞ መብታቸው ነው። እኔ ምንም መረጃው የለኝም። በቀለ ይኑርበት ከበደ፣ አንዱዓለም ይኑርበት የሺዋስ ምንም የማውቀው ነገር የለም።
ለመቀላቀል ሃሳብ የለዎትም?
አዲስ ፓርቲ በተመሰረተ ቁጥር እያንኳኳሁ አልሄድም። እንዲህ ዓይነት ሱሰኛም አይደለሁም።
ስለዚህ አቶ አበበን በምን እንጠብቃቸው? ከዚህ በፊት መምሕር እንደነበሩ ሰምቼአለሁ። በእንጨት ስራ ላይ ሞያ እንዳለዎ ይታወቃል። በፖለቲካ ውስጥም እንቅስቃሴ አድርገዋል። እና፣ እርስዎን በምን እንጠብቅዎ?
እኔ በፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ውስጥ እቀጥላለሁ፤ በሚቀጥለው የሕይወት ዘመኔ። በኢትዮጵያ እኔ የማስበው ዓይነት ዴሞክራሲ እስኪሰፍን ትግሉን አላቆምም። ሰላማዊ ትግል ነው የሚያዋጣው። በአንድ የፖለቲካ ዕንቅስቃሴ ላይ መገለጥ እችላለሁ ብዬ አስባለሁ። እርሱም ሩቅ ላይሆን ይችላል። ከዚያ ውጭ ግን ደራሲ ነኝ። ራሴን ማሞገስ ስለማልፈልግ ነው። ሁለት ለሕትመት በቅተው እስከ ሶስተኛ ዕትም የደረሱ መጽሐፎች ነበሩኝ። “የሲዖል ፍርደኞች 1 እና 2” መጽሐፍት አሉኝ። እግዚአብሔር ቢረዳኝ፣ በሚቀጥለው ዓመት በተከታታይ ሶስት መጽሐፍትን አወጣለሁ፡ አንድ ያልታተመ፣ የአርትዖት ስራ የማከናውንበት ቀድሞ የተሰራ መጽሐፍ አለ። የስዕል እና የቅርጻ ቅርጽ ሞያዬ ከፍተኛ ነው። አሁን ወደዚያ አልመለስም። ሰው በስተርጅናው የሚሰራው አንድም ጽሁፍ ነው። ወደ ጽሁፍ ስራዎቼ እመለሳለሁ። አሁንም እየሰራሁ ነው ያለሁት። ከሰላማዊ ትግሉ አልሸሽም። ሚዲያ ላይ ሄጄ አንዳንድ አስተያየቶችን እየሰጠሁ ነው። የአገሬን የፖለቲካ ሁኔታ መተንተን፣ በእኔ የዕውቀት ደረጃ ያለውን ሁኔታ መግለጽ፣ መንግስት ሊያስተካክላቸው የሚገባቸውን ነገሮች መተቸት፣ ሰላማዊ ትግል እንዴት እንደሚያስፈልግ፤ በተለይ አሁን አገሪቱ ካለችበት ውጥንቅጥ ለመውጣት፣ አሁን የተያዘው የዕርቅ ጉዳይ ጠንክሮ እንዲወጣ ምክረ ሃሳብ አቀርባለሁ፤ እንደአቅሜ።


ሰሞኑን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ለመንግስት መ/ቤቶች የፃፉት ደብዳቤ፤ ህገ-መንግስታዊ መብቶችን የሚጥስ ነው ሲሉ በትግራይ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ነቅፈዋል። ደብዳቤው ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጭ ሰልፍና ስብሰባ ማካሄድ እንደማይፈቅድ ይገልፃል።
ከአዲስ አድማስ ጋር ቆይታ ያደረጉት የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፓርቲ ከፍተኛ አመራር አባል አቶ ኪሩቤል ገብረእግዚአብሔር በሰጡት አስተያየት፤ አቶ ጌታቸው ረዳ “ለክልሉ መንግስታዊ መስሪያ ቤቶች የጻፉት ደብዳቤ፤ የመንግስት ሰራተኛን የሚመለከትና ስምንት ሰዓት የመስራት ግዴታ እንዳለበት የሚያስረዳ እንዲሁም  የሕግ ጉዳዮችን የጠቃቀሰ ነው”፤ ሲሉ አስረድተዋል። አንድ ፓርቲ የመንግስት አዳራሽን በልዩ ሁኔታ መጠቀም እንደማይኖርበትም ይኸው ደብዳቤ እንደሚያብራራ ነው የተናገሩት።
የአቶ ጌታቸው ደብዳቤው የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሃሳብን የመግለጽ መብቶች ላይ  ጉዳት ማድረሱ እንደማይቀርና በሕግ ሰበብ የሚፈጠር ችግር ሊኖር እንደሚችል አቶ ኪሩቤል ገልጸዋል። “በደፈናው ስብሰባ እና ሰልፍ ‘አይቻልም’ ማለት አግባብነት የለውም። ፈቃድ የሚጠየቀው ሰላማዊ ሰልፉ ላይ የጸጥታ እንከን እንዳይፈጠር ቅድመ ጥንቃቄ ለማድረግ ነው” ብለዋል።
የፕሪቶሪያ ስምምነት ላይ ጊዜያዊ አስተዳደር ከሕዝቡ እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ተውጣጥቶ እንደሚቋቋም ቢገለጽም፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ምስረታ ላይ ፓርቲያቸው አለመሳተፉን አቶ ኪሩቤል አስታውሰዋል። የጊዜያዊ አስተዳደሩን ምስረታ “የአንድ ፈረስ ግልቢያ ይመስላል” ሲሉ የነቀፉት አመራሩ፣ “ባንክ እና ታንክ የሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች የጸጥታ አካሉ ገለልተኛ እስከሆነ ድረስ መንግስት ለማቋቋም አቅም አያንሳቸውም፤ በዚህ ስጋት ምክንያት ነው ፓርቲዎቹን የሚደፈጥጧቸው።” ብለዋል።
“አሁን በፈጠሩት ሽኩቻ እንጂ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና ህወሓት አንድ ናቸው። ህወሓት ብቻውን መንግስት ሊሆን አይገባውም። ሕዝቡን ከሚወክሉ ተቋማት  ተውጣጥቶ ነው መንግስት መቋቋም ያለበት።” ብለዋል-አቶ ኪሩቤል።
በትግራይ ክልል የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በህወሓት ውስጥ ከተፈጠረው ክፍፍል ጋር በተያያዘ ሁሉንም የትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች ያሳተፈ ክልላዊ መንግሥት እንዲመሰረት ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ፓርቲዎቹ ጥሪውን ያቀረቡት፣  በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ ያለው ዋነኛ አደጋ “ሥርዓት የወለደው ስንፍና ነው” በማለት ነው። “አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሲታመም የማይታመም መንግሥት ያስፈልገናል። ይህም የሚሆነው ሁሉንም ድርጅቶች ያካተተ እና ሕዝብን ማሰለፍ የሚችል መንግሥት ሲቋቋም ነው” ብለዋል፤ ተቃዋሚዎቹ።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፈቀደው ውጪ ሌላ ስብሰባ ማካሄድ እንደማይቻል የሚያትተው የፕሬዚዳንቱ ደብዳቤ፣ “የኮሌራ በሽታ መከላከል፣ ተፈናቃዮችን ወደ ቀዬአቸው መመለስና የክልሉን ግዛታዊ አንድነት ማስከበር፤ እንዲሁም በጀት መዝጋትና በጀት ማዘጋጀት የመሳሰሉ ሌሎች ሕዝባዊና መንግስታዊ ዕቅዶች” የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሆናቸውን ይገልጻል። “ከዚህ ውጭ የሚደረጉ ሰብሰባዎች የተያዘውን ዕቅድ ስለሚጎዱ አይፈቀዱም” ይላል-ደብዳቤው።

በትግራይ ክልል፣ ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ በስፋት የሚከናወነው ባሕላዊ የወርቅ ማውጣት ስራ የኮሌራ በሽታን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ተግዳሮት መፍጠሩን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ። የኮሌራ በሽታ ስርጭት ከዕለት ተዕለት እየተባባሰ መምጣቱንም አክሎ አመልክቷል።
የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ በሪሁ ኪሮስ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ የኮሌራ በሽታ ስርጭት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰተዋለው ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ላይ ሲሆን፣ ቦታውም ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ እንደሆነ አስረድተዋል። አያይዘውም፤ በሽታው እስከ አሁን ድረስ 24 ወረዳዎች ላይ ተስፋፍቷል ብለዋል።
“በጥቅሉ 221 በሽተኞች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ 151 ያህሉ አገግመዋል። 5 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።” ያሉት አቶ በሪሁ፣ በሽታው መቐለ አንድ ቦታ ላይ መታየቱን ገልጸዋል። ይሁንና የሕሙማኑን ብዛት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አብዛኛዎቹ በሽተኞች በሰሜን ምዕራብ ዞን 11 ወረዳዎች ውስጥ ነዋሪ የሆኑ 204 ሰዎች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ 146 ያህሉ በሽተኞች አስገደ ወረዳ እንዳሉ ነው አቶ በሪሁ ያስረዱት።
“በአጎራባች ክልሎች በሽታው ይታይ ስለነበር፣ የቅድመ መከላከል ስራ ለመስራት ተሞክሯል።” የሚሉት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው፣ ይሁንና የበሽታውን ስርጭት ለመከላከል በአስገደ ወረዳ የሚከናወነው ባሕላዊ የወርቅ ማውጣት ስራ ፈተና መጋረጡን አልሸሸጉም። በወረዳው በባሕላዊ መንገድ የወርቅ ማውጣት ስራ በግላቸውም ሆነ በማሕበር የተሰማሩ ከ10 ሺህ በላይ ወርቅ አውጪዎች መኖራቸውን ሃላፊው አረጋግጠው፣ በወርቅ ማውጣት ስራ ላይ ምክንያት፣ እንዲሁም የወቅቱ ክረምት መሆን የኮሌራ በሽታን ለመከላከል ተደራራቢ ፈተና መጋረጣቸውን ጠቁመዋል።
“የጤና ባለሞያዎች ወደ ስፍራው ሄደው፣ የውሃ ማከም እና ጄሪካን ማቅረብ እንዲሁም ትምሕርት የመስጠት ስራዎችን እየሰሩ ነው። ቢሆንም፣ ቦታው አስቸጋሪ ነው።” ያሉት አቶ በሪሁ፣ በጤና ጣቢያና በሆስፒታል ደረጃ ጊዜያዊ የማከሚያ ማዕከላት መቋቋማቸውን አመልክተዋል። ራቅ ባሉ ቦታዎችም ጊዜያዊ የሕክምና ቦታዎችን የማደራጀት ስራ፣ በተጓዳኝም የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
“ከዕለት ወደ ዕለት በወረዳ ሽፋን እና በበሽተኛ ቁጥር ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል። ሱር የሚባል ወንዝ፣ የበሽታው ስርጭት መነሻ ነው። በሌላ በኩል፣ ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤት ለመስራት ለሕብረተሰቡ ትምሕርት ተሰጥቶ ቢሰራም፣ በከባድ ዝናብ የተነሳ ይፈርሳል። ቢሆንም፣ እንደገና እየተሰራ ነው” በማለት ሃላፊው ተናግረዋል።
የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው የጸጥታ ችግር ያለባቸውና በኤርትራ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ቦታዎች መኖራቸውን አውስተው፣ ገልፀዋል በዚህም ለሕዝቡ በአፋጣኝ ለመድረስ አዳጋች የሆነበት ሁኔታ መፈጠሩን ገልፀዋል።

በማገዶ እንጨትና ተቀጣጣይ ነገሮች አማካይነት የሚመጣ የሳንባ ካንሰር መጨመሩን የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ባወጣው ጥናት  አመልክቷል፡፡ “የሳንባ ካንሰር የተጋላጭነት መጠን  በሴቶችና በወንዶች መካከል ተመጣጣኝ ነው" ብሏል - ጥናቱ፡፡

ብዙዎቹ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ተቋማት የሚመጡት ዘግይተው መሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፤ የሳንባ ካንሰር አራት ደረጃዎች እንዳሉትም ይጠቁማል፡፡ በመጀመሪያው  የሳንባ ካንሰር ደረጃ  ላይ የሚገኝ ታማሚ ወደ  ሕክምና ተቋም ከመጣ፣ የመዳን ዕድሉ ሰፊ መሆኑን የሚጠቅሰው ጥናቱ፤ በሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ላይ ሆኖ ከመጣ ግን የመፈወስ ዕድሉ ጠባብ ነው ይላል።

በአገራችን ከ90 በመቶ በላይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች ወደ ሕክምና ቦታ የሚመጡት የመጨረሻዎቹ ሁለት ደረጃዎች ላይ ከደረሱ በኋላ መሆኑን የገለጸ ጥናቱ፤ በኢትዮጵያ የሳንባ ካንሰር ሕሙማን አማካይ ዕድሜ፣ ከሌሎች አገራት አማካይ የሳንባ ካንሰር ታማሚዎች አንጻር ወጣት መሆናቸው ተጠቁሟል። በዚህም 55 ወይም 56 ዓመት ዕድሜያቸው ላይ ታማሚ እንደሚሆኑ ነው ጥናቱ ያረጋገጠው፡፡

ጥናቱ በማገዶ እንጨቶች፣ በከሰል፣ በኩበት ጭስና ሌሎች ተቀጣጣይ ነገሮች የሚመጣው የሳንባ ካንሰር አይነት እየጨመረ መምጣቱን አመልክቷል፡፡ ይሁንና የትኛው የማገዶ ዓይነት የሚለው ተጨማሪ ጥናት ይፈልጋል ተብሏል።

“የሳንባ ካንሰር በሲጋራ ጭስ አማካኝነት የሚመጣ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ሲጋራ የሚያጨሱ ሴቶች ቁጥር ከ1 በመቶ በታች ሆኖ እያለ ለሳንባ ካንሰር ያላቸው ተጋላጭነት ግን ከወንዶች እኩል ነው" ሲል የኢትዮጵያ ቶራሲክ ማሕበር በጥናቱ አመልክቷል።

”የኢትዮጵያ ልጆች” ቴሌቪዥን ላይ በምትሰራው ደራሲ ገሊላ ተስፋልደት የተዘጋጀው “ባለጋሪው አንበሳ” የተሰኘ የልጆች መጽሐፍ ከሰሞኑ ለገበያ ቀርቧል፡፡

መጽሐፉ፤  ክፉ አለመሥራትን፣ መዋደድን፣ ተባብሮ መኖርንና ፍቅርን ለልጆች ያስተምራል ተብሏል፡፡  

“ባለጋሪው አንበሳ”፣ ለደራሲዋ አራተኛ ሥራዋ ሲሆን፤ የበኩር ሥራዋ “አመለኛ ልጅሽ” የተሰኘ የግጥም መድበል ነው፡፡ ሁለተኛ ሥራዋ “አንበሳ እና ነብር” የተሰኘ የልጆች  መጽሐፍ ነው፡፡


ሦስተኛው መጽሐፏ “እሽኮኮ አድራጊዋ ቀጭኔ” የሚሰኝ ሲሆን፤ ለልጆች መልካምነትና ደግነት መልሶ እንደሚከፍል ያስተምራል - ብላለች ደራሲዋ፡፡

Page 3 of 721