Administrator

Administrator

 ከዕለታት አንድ ቀን አያ አንበሶ የዱር አራዊትን አቤቱታ ለማዳመጥ በትህትና ተቀመጠ፡፡
ጦጢት ተነስታ “አያ አንበሶ ያስፈራሩናል፡፡ የልባችንን መናገር አልቻልንም” አለች፡፡
አያ ዝንጀሮ፡- “ምንም እንኳን የጦጢትን ያህል ፍርሃት ባይገባንም መፍራታችንማ መቼም አልቀረም!”
አያ ነብሮ፡- “አያ አንበሶን መፍራት አለብን ብዬ አላምንም! ምክንያቱም እኛ በሺዎች የምንቆጠር ነን፡፡ አያ አንበሶ ግን አንድና አንድ እንስሳ ነው፡፡
አያ ዝሆን፡-
“የአያ ነብሮ ንግግር ማርኮኛል፡፡ እኛ ስንት መንገድ ተጉዘናል ኢትዮጵያን ለማሸነፍ፡፡ አውቀን ይሁን ሳናውቅ ሁሌ እኛ እናሸንፋለን ብለን ብዙ ፈግተናል፡፡ ከተሳሰብን ግን ብዙ መንገድ የመሄድ ዕድል አለን፡፡ ብዙ ችግር እንፈታለን፡፡ ብዙ ተስፋ እንሰንቃለን፡፡
አያ አንበሶ፡-
“ይሄንን እንደ ዱለታ ነው የማየው፡፡ እኔ አንበሶ ጥፋትን ከልማት የማልለይ ይመስላችኋል? በጉልበት ልሠራው የማልችልስ ይመስላችኋል? እችላለሁ!!
ሁሉም፤ በህብረት፡-
“አያ አንበሶ፤ አሁንም ቢሆን በፍቅር፣ በስምምነት፣ በአንድነት በህብረት እንቁም፡፡ ጠላትና ወዳጅን በአግባቡ እንለይ ጥያቄዎቻችንን ለይተን እናሳይዎ! አግባብ ያለው መልስ ባናገኝ እንኳ፤ ሀሳባችን ከመልሳችን በታች እንደማይሆን እናውቃለን፡፡ ስለዚህ አያ አንበሶ፤ የህብረት መልስ እንዳለን እናስብና እንተማመን!!
***
ብዙ ሰው ይለናል፣ ይህ ያ ነው፣ ያ ያ ነው
ግን ከተሳሰብን፣ ቋንቋችን አንድ ነው!
***
ዕውነትን ፍለጋ በቆፈርነው ምድር
እህል ዘራንበት በልተን እንድናድር!
ይህ ግጥም የጥንት የጠዋት ነው፡፡ በሙሉ ዐይኑና በሙሉ ብሌኑ ለሚያየው ግን ከሙሉ በላይ ነው! ምክንያቱም አንድ ሙሉ ትውልድ በዚህ ግጥም ውስጥ ተሰድሯል - ስለአለፈ ትውልድ ሊመሰክር አለሁ ይላል፡፡
የወትሮዎቹን ገጣሚያን ደራሲ ከበደ ሚካኤልንና ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማን በዚህ ወቅት መጥቀስ የግድ ይመስለናል!
“ለሁሉም ጊዜ አለው” ብሏል ሰለሞን
እጠይቀው ነበር በተገናኘን
ሞት እራሱ እሚሞት ምን ጊዜ እንደሆን?
(ከበደ ሚካኤል)
በሌላኛው ወገን ፀሐፌ ተውኔት መንግሥቱ ለማ፡-
“ቀማኛን መቀማት ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ የድሆችን ጭንቅ
በኔ ቤት ጽድቅ ነው አንድ ሰው ይሙት
አንድ መቶ ሺ ሰው ኪኖር በምጽሞት፡፡
(ባለካባና ባለዳባ)
በሌላ ወገን የወሬ ሱስ፣ የነገር ሱስና የሀሜት ሱስ የት እንደሚያደርሰን አይታወቅም፡፡ አቤ ጉበኛ ጠዋት ነው ነገሩ የገባው፡፡ ለዚህ ነው ገና በማለዳ፤
“ሰማይን በአንካሴ ቆፍሬ ቆፍሬ
ለወሬ ሱሰኞች አገኘሁኝ ወሬ” ብሎ የፃፈው፡፡
 (መስኮት)
ፀጋዬ ገ/መድህንም በበኩሉ፤
“ያለፈ ጥረታችንን ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይልቅ ያልሞከርነው ነው ሚቆጨኝ
ዛሬ ለወግ ያደረግሺው ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው፣ ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞም የሠለጠነ እንደሁ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል”
ሐምሌት (ሼክስፒር - ፀጋዬ ገ/መድህን እንደተረጐመው)
ከላይ እንዳየነው ሁሉ ሰው ለትግል ተነሳ፡፡ ያን የትግል ሜዳ ግን የእህል መዝሪያ አደረገው::
ንጉሥ ሰለሞን፤ በምንም ስሜት ይበለው፣ የተለመደውን አካሄድ መጠየቅ ጤናማ አካሄድ ነው::  ይሄ መንፈስ ያለጥርጥር መልካም ሰፈር ያደርሰናል፡፡
የድሆችን ጭንቅ ማቃለል ድካም አለበት
ለወሬ ሱሰኞች ሰማይ ተቆፍሮም ወሬ እንደሚገኝ ማወቅ ፀጋ ነው፡፡
እንግዲህ ሰው ቢገባውም ባይገባውም፤ ከላይ የተጠቀሱት ነጥቦች ዋጋ አላቸው ብለን እናስባለን፡፡
ግጭቶች በየቦታው መንፈሳቸው አይቀርም፡፡
ህይወትም በየትም አቅጣጫ መፍሰሷ ግድ ነው
ዕድሜውን ይሰጠን እንጂ ሁሉንም ያሳየናል፡፡ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡፡ ከለውጥ ህግ በስተቀር የማይለወጥ ነገር የለም (Everything changes except the law of change)
እስከዛሬ ያለፈው ሁሉ ለዛሬው ቀን ምክንያት ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ለነገ ምክንያት ነው፡፡
ዞሮ ዞሮ፤
“ዕድሜ ጥሩ ነው አያራርቅም
ዕድሜም በማዳን ሰው አይጣላም”
የሚባለው ለዚህ ነው፡፡

   የዚምባቡዌ መንግስት፣በቂ ደመወዝ አይሰጠንም በሚል የአገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች በጀመሩት የስራ ማቆም አድማ ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን 77 የህክምና ዶክተሮች ከስራ ያባረረ ሲሆን ይህን ተከትሎም በርካታ የመንግስት ሰራተኞች ባለፈው ረቡዕ አደባባይ ወጥተው በፕሬዚዳንቱ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ማሰማታቸውን  ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የመንግስት ሰራተኞች “የሚከፈለን ደመወዝ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የማይመጣጠን በመሆኑ የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግልን ይገባል” በሚል የስራ ማቆም አድማውን ማድረግ የጀመሩት ባለፈው መስከረም ወር እንደነበር ያስታወሰው ቢቢሲ፤ ፍርድ ቤት “የስራ ማቆም አድማው ህገ ወጥ በመሆኑ በ48 ሰዓታት ውስጥ ወደ ስራ ገበታችሁ እንድትመለሱ” የሚል ትዕዛዝ ቢያስተላልፍም፣ ከስራ የተባረሩት 77 ሃኪሞች ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል ብሏል፡፡
በዚምባቡዌ የስራ ማቆም አድማውን ያላቋረጡ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የህክምና ዶክተሮች እንዳሉ የጠቆመው ዘገባው፤ መንግስት በእነሱም ላይ ተመሳሳይ እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል ቢነገርም፣ይህን ማድረግ ክፉኛ የተጎዳውን የአገሪቱን የህክምና ዘርፍ የባሰ ቀውስ ውስጥ ያስገባዋል የሚል ስጋት መፈጠሩን አመልክቷል፡፡
በኢኮኖሚ ቀውስና በዋጋ ግሽበት በተመታችው ዚምባቡዌ፣ የዜጎች ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እየቀነሰ መምጣቱንና የመንግስት ሰራተኞችን ጨምሮ ብዙዎች ኑሯቸውን መምራት የማይችሉበት ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ መግባታቸውን ያስታወቀው ዘገባው፤ የአንድ የህክምና ዶክተር ወርሃዊ ደመወዝም ከ100 ዶላር በታች መውረዱንና በዚህም ሳቢያ በርካታ ሃኪሞች ስራቸውን በመልቀቃቸው የጤና ተቋማት፣ ስራ እስከማቆም ደረጃ መድረሳቸውን ጠቁሟል፡፡

Saturday, 02 November 2019 13:46

የዘላለም ጥግ

• በዓለም ላይ ግጭት ወደ መረጋጋት አይወስድም፡፡
    ሞሃመድ ሙርሲ
• ሰላም የግጭት አለመኖር አይደለም፤ ግጭትን በሰላማዊ መንገዶች የመያዝ አቅም ነው፡፡
   ሮናልድ ሬገን
• ሥልጣን ባለበት ተቃውሞ መኖሩ አይቀርም፡፡
   ሚሼል ፎውካልት
• ግጭት አይቀሬ ነው፤ ጦርነት ግን የግድ አይደለም፡፡
  ማክስ ሉኬድ
• ግጭትና መፍትሄ፤ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው፡፡
   ሃርሽ ሊፒ
• ግጭቶች ወደ ጦርነት ከማደጋቸው በፊት መፍትሄ ለማበጀት ፈጣን ሁን:: ሃይለኛው አዞ በአንድ ወቅት ተሰባሪ እንቁላል ነበር!
   እስራኤልሞር አዩቨር
• አንዳንዶች ግጭት በመፍጠር ታሪክ ሲሰሩ፣ ሌሎች ግጭት በመፍታት ታሪክ ይሰራሉ፡፡
   አንቶኒ ሂጊንሰን
• ሁልጊዜም ንትርክን ማስቆም ትችላለህ:: እንዴት ቢሉ …አፍህን መዝጋት ነው፤ ዝም ማለት፡፡
   ጃና ካቾላ
• ግጭት ያለ አንተ ተሳትፎ መኖር አይችልም፡፡
   ዋይኔ ዳዬር
• በዓለም ላይ የምናየው ግጭት ሁሉ፣ በራሳችን ውስጥ ያለ ግጭት ነው፡፡
   ብሬንዳ ሾሻና
• የሰው ልጆች አብረው ሲኖሩ ግጭት አይቀሬ ነው፤ ጦርነት ግን አይቀሬ አይደለም፡፡
    ዳይሳኩ አይኬዳ
• ግጭት ከድንቁርናና ከጥርጣሬ ውስጥ ይወለዳል፡፡
   ጎርዶን ቢ.ሂንክሌይ- “…በእርግጥ ኢትዮጵያዊ ትስስሩ ጠንካራ ስለሆነ የአንድነታችን ገመድ አልበጠስ ብሎ ነው እንጂ፣ ክስተቱ አንድነታችንን ለመበጠስ የተሰራ ነው…”
    አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ሊቀ መንበር)
- “…ይሄኔ ሌላ አገር ቢሆን ግልብጥብጥ የሚልበት ሁኔታ ይፈጠር ነበር፡፡ መከራን ተሸክሞ ነገን በተስፋ ማየት ባህላችን ነው፡፡…”
    አቶ ይልቃል ጌትነት (የኢህን ሊቀ መንበር)
• “…ከዚህ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ ትርፍ አገኛለሁ የሚል አካል ካለ እርካሽ ነው:: አገር እየፈረሰ ፖለቲካዊ ትርፍ አገኛለሁ ማለት ሞኝነት ነው፡፡…”
   አቶ ሙሉጌታ አበበ (የመኢአድ ም/ሊቀመንበር)
• “…እኛ እንደ ድርጅት ከኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት በላይ ምንም የሚመለከተን ነገር የለም፡፡ ይህ ነገር የሥልጣን ወይም ማን የበላይነት ይያዝ የሚል ጉዳይ አይደለም:: ይህ ጉዳይ አገርን የማዳንና በሰላም ወደሚቀጥለው ምዕራፍ ማሸጋገር ነው:: በዚህ ጉዳይ ላይ ከመንግስት ጋር በምንም መልኩ እንተባበራለን፡፡…”
   ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነገ (የኢዜማ መሪ)
• “…የአገር መሪ በመሪነት ተግባሩ ላይ፣ ፖሊስ በፖሊስ ሥራው፣ ደህንነቱ በተመደበበት ሥራ፣ ጦር ሠራዊቱ በአገር ጥበቃ ሥራ፣ ሁሉም በተሰማራበት
ተግባር ላይ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ሥራው ምንድን ነው?...”
     ሙፍቲ ሐጂ ዑመር እድሪስ (የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠ/ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና የጉባኤው የበላይ ጠባቂ)


Saturday, 02 November 2019 13:43

የህይወት ጥግ

- የተለመደ ተራ ህይወት አሰልቺ ነው፡፡
    ኤሚነም
- ፍቅር ሲይዝህ ሁሉም ነገር ጥርት ይልልሃል፡፡
   ጆን ሌኖን
- አንዳንዶች ዝናቡን ያጣጥሙታል፡፡ ሌሎች ይበሰብሱበታል፡፡
   ቦብ ማርሊ
- ፍቅር የእብደት ደረጃ ላይ ካልደረሰ፣ ፍቅር አይደለም፡፡
   ፔድሮ ካልዴሮን
- ለማቃለል፣ አንተም የቀለልክ ልትሆን ይገባል፡፡
    ካሊል ጂብራን
- ፀሐይ ስትወጣ ማናቸውንም ነገሮች ማድረግ እችላለሁ፤ ያን ጊዜ መውጣት የማይቻል አ ንድም ረ ዥም ተ ራራ አይኖርም፤ ሊፈታ መፍታት የማይቻል
አንድም ከባድ ችግርም የለም፡፡
   ዊልማ ሩዶልፍ
- እውን የማይደረግ ምንም ነገር መዝፈን አልሻም፡፡
     ክላውድያ አኩና
- ይገባናል ብለን የምናስበውን ፍቅር ነው የምንቀበለው፡፡
    ስቲፈን ችቦስኪ
- በበጋ የሚዘፍኑ ሰዎች፤ በክረምት መደነስ አለባቸው፡፡
    የጣሊያን ምሳሌያዊ አባባል
- ሰዎችን ከወደድክ ልትቀይራቸው አትጥርም፡፡
    ዋይኔ ዳየር
- ሰላምን ለማምጣት ጠብመንጃና ቦንብ አያስፈልገንም፡፡ ፍቅርና ርህራሄ ነው የሚያስፈልገን፡፡
    ማዘር ቴሬዛ
- አንዱ በር ሲዘጋ፣ ሌሎች በርካታ ክፍት በሮች መኖራቸው አታውቅምን?
    ቦብ ማርሊ
- ሁሉም የራሱን ዕጣ ፈንታ የመወሰን መብት አለው፡፡
   ቦብ ማርሊ
- ሙዚቃ የልብ ሥነጽሑፍ ነው፤ ንግግር ሲያልቅ ነው እሱ ይጀምራል፡፡
   አልፎንሴ ዲ ላማርቲኔ
- ብቸኝነት እንዳይሰማህ፤ መላው ዩኒቨርስ ያለው አንተ ውስጥ ነው፡፡
     ሩሚ

Saturday, 02 November 2019 13:25

ከመሪዎች አንደበት

• ማንም ሰው በቆሻሻ እግሩ በአዕምሮዬ ላይ እንዲራመድብኝ አልፈቅድም፡፡
    ማሃትማ ጋንዲ (ህንዳዊ የነፃነት ሰላማዊ ታጋይ)
• ያንተ ፈቃድ ሳይታከልበት፣ ሰዎች ሊጎዱህ አይችሉም፡፡
    ማሃትማ ጋንዲ
• ደካሞች ፈጽሞ ይቅርታ አያደርጉም፡፡ ይቅር ባይነት የጠንካሮች መገለጫ ነው፡፡
    ማሃትማ ጋንዲ
• ጨለማ፤ ጨለማን ሊያጠፋ አይችልም፤ ብርሃን ብቻ ነው ጨለማን የሚያጠፋው:: ጥላቻ፤ ጥላቻን ሊያጠፋው አይችልም፤ ፍቅር ብቻ ነውጥላቻን የሚያጠፋው፡፡
   ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄ.አር  (ጥቁር አሜሪካዊ የሲቪል መብት ታጋይ)
• እንደ ወንድማማቾች አብረን መኖርን መማር አለብን ወይም እንደ ጅሎች አብረን እንጠፋለን፡፡
    ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄ.አር
• ብዙ ጊዜ ሰዎች እርስ በርስ ይጠላላሉ፤ ምክንያቱም እርስ በርስ ይፈራራሉና፤ እርስ በርስ የሚፈራሩት ደግሞ እርስ በርስ ስለማይተዋወቁ ነው፤ እርስ በርስ
የማይተዋወቁት መነጋገር ስለማይችሉ ነው፤ መነጋገር የማይችሉት ደግሞ ስለተነጣጠሉ ነው፡፡
   ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄ.አር
• የሚባክን ትርፍ ጊዜ የለም፡፡ አሁኑኑ አንድ መሆን አሊያም መጥፋት ነው ያለብን፡፡
   ጁሊየስ ኔሬሬ (የቀድሞ የታንዛንያ መሪ)
• አንዳንድ ሰዎች በመንግስት ሥልጣን ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቆየት መጥፎ ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ነገር ግን ብዙ በቆየህ ቁጥር ብዙ ትማራለህ፡፡ እኔ አሁን
በመንግስት አስተዳደር ኤክስፐርት ነኝ፡፡
   ዩዌሪ ሙሴቪኒ (የኡጋንዳ መሪ)
• መሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መርህን በተመለከተ ማናቸውንም እርምጃዎች ለመውሰድ ፈቃደኛ ነኝ፡፡
    ባን ኪ-ሙን (የተባበሩት መንግስታት ዋና ፀሐፊ)
• ሚስቴን በአደባባይ ብስም፤ ቀጣዩን ምርጫ አላሸንፍም፡፡
     ዮዌሪ ሙሴቪኒ

Saturday, 02 November 2019 13:42

የዕውቀት ጥግ


• ዕውቀት፤ ፍቅር፣ ብርሃንና ርዕይ ነው፡፡
    ሄለን ከለር
• ዕውቀትን የመሰለ ሀብት የለም፤
ድንቁርናን የመሰለ ድህነትም የለም፡፡
   ቡድሃ
• ማንንም ም ንም ነ ገር ማ ስተማር አልችልም፤ እኔ እንዲያስቡ ብቻ ነው ማድረግ የምችለው፡፡
   ሶቅራጠስ
• ዕውቀት መጀመሪያ አለው፤ መጨረሻ ግን የለውም፡፡
    ጌታ ኤስ. ሊንገር
• ዕውቀት የሚጨምረው በማካፈል እንጂ በመቆጠብ አይደለም፡፡
     ካማሪ አካ ሊሪካል
• ሃሳባቸውን መለወጥ የማይችሉ ሰዎች፣ ምንም ነገር ሊለውጡ አይችሉም፡፡
    ጆርጅ በርናርድ ሾው
• በዕውቀት ላይ የሚደረግ ኢንቨስትመንት የላቀ ትርፍ ያስገኛል፡፡
    ቤንጃሚን ፍራንክሊን
• መማር ፈጽሞ አታቁም፤ ዕውቀት በየአስራ አራት ወሩ በእጥፍ ያድጋል፡፡
   አንቶኒ ጄዲ’ አንጄሎ
• ዕውቀት ይናገራል፤ ጥበብ ግን ያደምጣል፡፡
   ጂሚ ሄንድሪክስ
• ሳይንስ ዕወቀት ይሰጠናል፤ ጥበብ የሚያጐናጽፈን ግን ፍልስፍና ብቻ ነው::
   ዊል ዱራንት
• ዕውቀት ያላቸው አይተነብዩም፡፡ የሚተነብዩ ደግሞ ዕውቀት የላቸውም፡፡
    ላኦ ትዙ

   ከዚህ አለም በሞት ቢለዩም በስራዎቻቸው እጅግ ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ የአለማችን ዝነኞችን ዝርዝር በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ፎርብስ መጽሄት፣ የ2019 ባለ ከፍተኛ ገቢ በህይወት የሌሉ ዝነኞችን ዝርዝር ባለፈው ረቡዕ ያወጣ ሲሆን ላለፉት ስድስት ተከታታይ አመታት በመሪነት የዘለቀው ማይክል ጃክሰን ዘንድሮም በ60 ሚሊዮን ዶላር ቀዳሚነቱን ይዟል::
በወርሃ ሰኔ 2009 ከዚህ አለም በሞት የተለየው እውቁ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ማይክል ጃክሰን፣ የሙዚቃ ስራዎች በአመቱ በአሜሪካ ውስጥ ብቻ በድረገጾች 2.1 ቢሊዮን ጊዜ መታየታቸውንና በዚህም ከፍተኛ ገቢ ማግኘቱን የጠቆመው የፎርብስ መረጃ፣ ምንም አንኳን ገቢው ካለፈው አመት በእጅጉ ቢቀንስም ዘንድሮም ከአንደኛ ደረጃ አለመውረዱን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ1977 በልብ ድካም ህመም ይህቺን አለም የተሰናበተው ሌላኛው እውቅ ሙዚቀኛ ኤልቪስ ፕሪስሊ   በ39 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ከ19 አመታት በፊት በካንሰር ለሞት የተዳረገው ቻርለስ ሹልዝ በ38 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ሆኗል፡፡
ታዋቂው የጎልፍ ተጫዋች አርኖልድ ፓርመር በ30 ሚሊዮን ዶላር፣ የሬጌው ንጉስ ቦብ ማርሌይ በ20 ሚሊዮን ዶላር፣ ዶክተር ሲዩስ በ19 ሚሊዮን ዶላር፣ ድምጸ መራው ጆን ሌነን በ14 ሚሊዮን ዶላር፣ ዘመን አይሽሬዋ ማርሊን ሞንሮ በ13 ሚሊዮን ዶላር፣ ፕሪንስ በ12 ሚሊዮን ዶላር፣ በቅርቡ በወሮበሎች የተኩስ እሩምታ ድንገት ህይወቱ ያለፈው ኤርትራዊው ድምጻዊ ኒፕሲ ሃስል በ11 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ በዘንድሮው የፎርብስ መጽሄት ባለከፍተኛ ገቢ የአለማችን ሟች ዝነኞች ዝርዝር ውስጥ እንደ ቅደም ተከተላቸው፣ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ታውቋል፡፡

የብሩንዲው ፕሬዚዳንት ፔሪ ንኩሩንዚዛ ባለቤት ቀዳማዊት እመቤት ዴንሴ ንኩሩንዚዛ፣ በሴቶች መብቶች መከበርና በጾታዊ ጥቃቶች ዙሪያ የሚያተኩርና ዜጎችን ለእኩልነት የሚቀሰቅስ አዲስ ነጠላ ዜማ መልቀቃቸው ተዘግቧል፡፡
“ኡሞኬንዚ አሬንግዬ ኩቭየራ ጉሳ” ወይም ሴት ልጅ ከመውለድ በላይ ዋጋ አላት የሚል ትርጉም ያዘለ ርዕስ ያለውና የአገሪቱ ወንዶች ሴቶችን ዝቅ አድርገው መመልከታቸውን እንዲያቆሙ ጥሪ የሚያስተላልፈው የቀዳማዊት እመቤቷ ነጠላ ዜማ፤ የቪዲዮ ክሊፕ ተሰርቶለት በሳምንቱ መጀመሪያ በዩቲዩብ የተለቀቀ ሲሆን በርካታ ተመልካቾችን ማግኘቱንና በማህበራዊ ድረገጾች መነጋገሪያ መሆኑን ኦል አፍሪካን ኒውስ ዘግቧል፡፡
ከፕሬዚዳንት ኑኩሩንዚዛ ጋር ባሳለፉት የ23 አመታት የትዳር ህይወታቸው አምስት ልጆችን ያፈሩት የ49 አመቷ ቀዳማዊት አመቤት ዴንሴ፤ አራት ደቂቃ እርዝማኔ ባለው የቪዲዮ ክሊፕ ላይ አንድ አባወራ ሚስቱን ሊደበድብ ሲሞክር ጣልቃ ገብተው ሲያስታርቋቸው ይታያሉ፡፡

  አፍሮባሮሜትር የተባለው የጥናት ተቋም፣ ከ28 በመቶ በላይ የሚሆኑት አፍሪካውያን፣ አንድ ባል አልፎ አልፎ ወይም በየዕለቱ ሚስቱን ቢደበድብ ጥሩ ነው ብለው እንደሚያምኑ በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ በተለያዩ 34 የአፍሪካ አገራት የሰራውን ጥናት መሰረት አድርጎ ሰሞኑን ይፋ ባደረገው ሪፖርት እንዳለው፣ ምንም እንኳን በጥናቱ ከተካተቱት አፍሪካውያን መካከል 71 በመቶ የሚሆኑት ባሎች፣ በምንም አይነት ሁኔታ ሚስቶቻቸውን ሊደበድቡ አይገባም የሚል አቋም ቢይዙም፣ 28 በመቶ ያህሉ ግን ድብደባው ተገቢ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በጥናቱ ከተካተቱት 46 ሺህ ያህል የተለያዩ የአፍሪካ አገራት ዜጎች መካከል ድብደባው ተገቢ ነው የሚል ምላሽ የሰጡት 24 በመቶ ሴቶች እና 31 በመቶ ወንዶች መሆናቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ በአንዳንድ የአፍሪካ አገራት በጥናቱ ከተካተቱት ሰዎች መካከል እስከ 70 በመቶ የሚደርሱት ድብደባን ጨምሮ በባለትዳር ሴቶች ላይ በቤት ውስጥ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ተገቢ ናቸው ብለው እንደሚያምኑ መናገራቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ መሰል አመለካከቶች ስር የሰደዱት ጋቦንና ላይቤሪያን በመሳሰሉ የመካከለኛውና ምዕራባዊ አፍሪካ አገራት ዜጎች ዘንድ መሆኑንም አመልክቷል፡፡
ተቋሙ ከቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር በሰራው በዚህ ጥናት ከተካተቱትና ባሎች ሚስቶቻቸውን መደብደብ አለባቸው ብለው እንደሚያስቡ ከገለጹት ሰዎች መካከል 41 በመቶ ያህሉ ምንም አይነት መደበኛ ትምህርት ያልወሰዱ መሆናቸውም ተነግሯል፡፡