
Administrator
በ800 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አትሌት ፅጌ ድጉማ ድል ቀናት
በፈረንሳይ ሜዝ በተካሄደ የ800 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር እትሌት ፅጌ ድጉማ አሸንፋለች፡፡ ፅጌ የ800 ሜትሩን 1 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ97 ማይክሮ ሴኮንድ በመጨረስ በቀዳሚነት ማጠናቀቋን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ ረግጠህ አትሻገር
በፐርሺያ ስለፐርሺያ የጥንት ንጉሥ የሚነገር አንድ አፈ - ታሪክ አለ፡፡
እንዲህ ይላል፡፡
አንድ ጊዜ የንጉሡ ሁለት ባለሟሎች ባጠፉት ጥፋት ዙፋን ችሎት እንዲቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ከዚያም ያጠፉት ጥፋት ፍርዱ እንደሚከተለው ተነገራቸው፡፡
ንጉሱ፤ ተደላድለው ዙፋናቸው ላይ ከተቀመጡ በኋላ፡-
“ያጠፋችሁት ጥፋት ፍፁም ምህረት የማይደረግለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለታችሁም በሞት እንድትቀጡ ተወስኗል፡፡ ይግባኝ ማለት ወይም የመሰላችሁን አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ” አለ፡፡
ከሁለቱ ፍርደኞች አንደኛው ንጉሱ ከልብ የሚወድዱት ፈረስ እንዳላቸው ስለሚያውቅ፤
“ንጉስ ሆይ! አንድ ዓመት ይሰጠኝና የሚወድዱት ፈረስዎን በአየር ላይ እንደ ወፍ መብረር ላስተምረው፡፡ ይህንን ካደረግሁኝ ነብሴን ይምሩልኝ ከሆነ ማስተማሬን ልቀጥል” አለና ተማጠነ፡፡
ንጉሱ፤ በአንድ ወገን የሚወድዱት ፈረሳቸው መብረር መቻል፣ በሌላ በኩል የጥፋተኛውን ፍርድ መሻር፣ በጣም ካማለላቸው በኋላ፣ በአለም ላይ የሚበር ፈረስ ያለው ንጉስ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አሰቡና ልባቸውን ሞቅ አላቸው፡፡ በመጨረሻም፤
“ይሁን፤ ፈረሴን በአየር ላይ መብረር አስተምርልኝ! አንድ ዓመት ሰጥቼሀለሁ” አሉት፡፡
ይህን ወስነው እንደሄዱ ሁለቱ ሰዎች መወያየት ጀመሩ፡፡
ሁለተኛው ፍርደኛ - “ስማ፤ አብደሃል እንዴ? ፈረስ በአየር ላይ በምንም አይነት እንደማይበር ታውቃለህ፡፡ በምን ተአምር ፈረሱን በአየር መብረር ልታስተምረው ነው? አንድ አመት እሩቅ መሰለህ? የማይቀረውን ነገር ቀኑን ማስተላለፍስ ለምን ይጠቅምሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አንደኛው ፍርደኛም፤
“ይህንን ያደረግሁት በአራት መንገድ ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ታይቶኝ ነው” አለና መለሰ፡፡
“አራት መንገድ? ለመሆኑ ንጉሱን የሚያሳምን አንድስ መንገድ ይገኛል? ስማ፤ ንጉሱ የሚለቅቁህ ፈረሳቸውን ለማብረር ከቻልክ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ምን መንገድ ታይቶህ ነው?”
አንደኛው ፍርደኛም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“አንደኛ፤
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ንጉሱ እራሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
ሁለተኛ፤
እኔ እራሴ ልሞት እችላለሁ፡፡
ሦስተኛ፤
ፈረሱ ሊሞት ይችላል፡፡
አራተኛ፤
ማን ያውቃል፤ ምናልባት ፈረሱን በአየር ላይ መብረር ላስተምረው እችል ይሆናል” አለ፡፡
* * *
ከእንዲህ ያለ አጣብቂኝና ውጥረት ሀገራችንን ይሰውራት፣ ማለት ደግ ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አማራጮች ሌላ አማራጭ ቢፈልጉም እንኳ የሚቻለውን ጥረት አድርጎ መፈለጉን መቀጠሉን ሁኔታዎች ግድ ይላሉ፡፡ ከአማራጮች መካከል መደራደር አንዱ መንገድ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች እጅግ በተወጣጠሩ ሰአት ረጋ እና ሰከን ብሎ የሚያስብና መውጫ መንገዶችን የሚያሰላ ግለሰብ ወይም ቡድን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በጣም አስፈላጊም ነው፡፡
የመጨረሻ ውጥረት ቢኖርም እንኳ ማረጋጋትና ማርገብ ሁሌም ከአማራጮች መካከል የማይቀር ነው፡፡
ዛሬ ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ሀገርና ህዝብን የማረጋጋት ሂደት ተቀዳሚ ነው፡፡ ሰላም የሁሉ ማሰሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ግጭትና ፍጭት የሰፈነበት የአሁኑ ሁኔታ፣ የህዝቡን ብሶትና ምሬት የፈጠሩት ሁኔታዎች የነባራዊና ህሊናዊ መንስኤዎች ጥምርና ድምር ቢሆንም፣ ህዝብ የሚለውን ሳይታክቱ መስማትና የልብ - ትርታውን ማዳመጥ፣ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን መግለፅ የህዝብ መብት ነው፤ የሚለውን ቋሚ መርህ ከልብ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ መቼም ቢሆን መች “ላይ ላዩን ይነጋገራሉ፣ ልብ ለልብ ይተዛዘባሉ” እያለ ጀምሮ፣ ከሮና መርሮ የብስጭትና ምሬቱ ጫፍ ላይ እስኪደርስ መጠበቅ ኋላ ማጣፊያው እንዲያጥር ያደርጋል፡፡
የህብረተሰብ ድርና ማግ በረዥም ሂደት ውስጥ የተሸመነ እንደመሆኑ፤ የተጠራቀሙ ብሶቶች ያልተፈቱ ችግሮች፣ መናቅና መግፋት፣ እንዲሁም ሁኔታዎችን እንደማያድጉ አድርጎ ማሰብ፤ ውሎ ሲያድር ውሉ ከማይታወቅ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል ከዛሬው ሁኔታ ሌላ አስተማሪ አይኖርም፡፡ ዴቪድ ፖል ቴሩ የህዝብ አልታዘዝ ባይነት በሚለው ታዋቂ ፅሁፉ፤ “የህዝብ አልታዘዝ - ባይነት ማለት የሲቪል ህግጋት ወይም ድንጋጌዎች አልቀበል ወይም አልታዘዝም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተቃውሞ የሰላማዊ ተቃውሞን ወይም የሀይል - አልባ ተቃውሞን ቅርፅ የያዘ ነው፡፡ ይህ አይነት ተቃውሞ የሚያካሂዱ ዜጎች ህግን የማያከብሩት ኢ-ፍትሀዊነት አለ ብለው ከልብ ሲያምኑና እንለውጠዋለንም ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ነው” ይላል፡፡
እስከዛሬ በነበረችው ኢትዮጵያ “ባለቤቶች ሲሸሹ፣ ባለቆዳዎቹ ይዋጋሉ” የሚባለው አይነት ሁኔታ ውስጥ የቆየው ህዝብ ወደፊት አምርቶ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ራሱ ወደ ማወቅ ሲጓዝ መታየቱ ታሪካዊ ነው፡፡ ልዩ እመርታም ነው፡፡ ይህ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቀና ብሎ መብቴን ነፃነቴን ስጠኝ የሚልበት ብቻ ሳይሆን መብቱም ነፃነቱም የእኔ ነው፡፡ የሚልበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል እያንዳንዱ ፓርቲ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በተደጋጋሚ በዓለም ያየነው የፖለቲካ ታሪክ “ሰው እስኪጠላህ እድሜ አይስጥህ” በሚለው ተረት የሚጠቃለል እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ በዚህ እረገድ ሁሉም እራሱን ቢፈትሽ መልካም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እርጋታ ያስፈልጋል፡፡ በጥሞና የሄዱበትንና የሚሄዱበትን ሁሉ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ካጠፉ ለመታረም፣ ከተቃረኑ ለመደራደር የፀና ልቦና የሰለጠነ አእምሮ ያስፈልጋል፡፡
ህዝብ የታሪክ ወንዝ ነው፡፡ መንግሥታት ይለወጣሉ፡፡ መሪዎች ይቀየራሉ፡፡ የሀገሪቱ ነገ በህዝቡ ዛሬ የሚወሰን ነው፡፡
የህዝቡ ዛሬ ደግሞ በሁላችንም እጅ ላይ ነው፡፡ ህዝቡን ማዳመጥ ፣ ጎንበስ ብሎ የልብ-ትርታውን ማወቅ እና መረዳት ግዴታችን ነው፡፡ “ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ እረግጠህ አትሻገር” መባሉ ለዚህ ነው፡፡ ሰላም የዚህ ሁሉ ቁልፍ ይሁን፡፡
የሌሊሳ ግርማ “በታችም በምድር” ነገ በገበያ ላይ ይውላል
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የደራሲ ሌሊሳ ግርማ “በታችም በምድር” የተሰኘው ወጥ የልቦለድ መፅሐፍ በነገው ዕለት በገበያ ላይ ይውላል፡፡
በተለያዩ መጣጥፎችና አጭር ልብ ወለድ ጽሁፎች በአንባቢያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ሌሊሳ ግርማ፤ አሁን ደግሞ በመጀመሪያ የወጥ ልቦለድ ድርሰት መጥቻለሁ እያለ ነው፡፡
ደራሲ ሌሊሳ ግርማ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚያቀርባቸው ጥበባዊ መጣጥፎቹም ይታወቃል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም “የንፋስ ህልም እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች”፣ “አፍሮ ጋዳ”፣ “መሬት - አየር - ሰማይ”፣ “የሰከረ እውነታ”፣ “እስቲ ሙዚቃ”፣ “ነፀብራቅ”፣ “ይመስላል ዘላለም”፣ የሚሰኙ የመጣጥፍና የአጭር ልብ ወለድ ስብስብ መድበሎችን ለአንባቢያን ማበርከቱ ይታወሳል፡፡
የመጽሐፉ አሳታሚ ዋሊያ መፅሐፍት ድርጅት ሲሆን፤ መጽሐፉ ከነገው ዕለት ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ መጻሕፍት ቤቶች ሁሉ ለገበያ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ከአድማስ ትውስታ ፤ 1992
“ሴቶች ይሄን ያህል ወሬኛ የሆኑት ለምንድነ ነው?”
ለመሆኑ ለምን ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበለጠ እንደሚያወሩ በመገረም ራሳችሁን ሳትጠይቁ ትቀራላችሁ? ሴቶች ደክሟቸው ተዝለፍልፈው እስከሚወድቁ ድረስ ገበያ ሲገበዩ ቆይተው፣ ቤት የተቀመጠውን አባወራ “የአልጋ ላይ አንበሳ ነህ አንተ” እያሉ እየዘለፉት ለምን ለማሳመን እንደሚችሉስ ታውቃላችሁ? በአንፃሩ ወንዶች ሚስቶቻቸውን ለማታለል ለምን እንደሚፈልጉ፤ በምንም ዓይነት ጥፋተኛ ተደርገው ለመታየት ለምን እንደማይሹና ምክር አልቀበልም ማለታቸውስ ከምን እደሚመጣ ታውቃላችሁ?
ይህ ፅሁፍ በወንዶችና በሴቶች መሀከል ያለውን ልዩነት የፈጠሩት የሰው ልጅ ስነ - ተፈጥሮአዊና ዝግመተ - ለውጣዊ (Evolutionary) ሳይንሳዊ ሂደቶች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አለንና ባርባራ ፒስ የተባሉ ፀሃፊዎች “ወንዶች ለምን ምክር ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ሴቶችስ ለምን ካርታ ማንበብ አይችሉም?” ከሚለው መፅሀፋቸው የሚጠቅሱልን ነው፡፡
ሴቶች ይሄን ያህል ወሬኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
ለመናገር የሚያስችለንን ችሎታ የሚሰጠን የአንጎል ክፍል የሴቶች ሁለት ሲሆን፤ የወንዶች ግን አንድ ብቻ ነው፡፡
ወንዶች ዕቃ ፈልጎ ማግኘት የማይሆንላቸው ለምንድን ነው?
ወንዶች “ተነል ቪዥን” የሚባል ተፈጥሮአዊ የሆነ “የርዝመት - እይታ ማነጣጠሪያ አሸንዳ” አላቸው፡፡ ይሄ የዕይታ አሸንዳ የዕይታ ዳርቻን የሚወስን ሲሆን፤ ከሴቶች ይልቅ የወንዶቹ ሰፊ የርቀት አድማስ ይዳስሳል፡፡ ይሄ ጉዳይ በቅድመ - ታሪክ ወንዶች ለአደን በሚወጡበት ሰዓት ረዥም እርቀት ላይ ያለ ታዳኝ አውሬ ለማየት ከመፈለጋቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ነው፡፡ ባንፃሩ የዚያን ዘመን ሴቶች በቅርብ ዕይታ ስር ያሉትን ጎጆዎቻቸውን በመጠበቅ ላይ ብቻ ይሰማሩ እደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ወንዶች የሩቅ የሩቁን ለማነጣጠር ብቻ ዐይናቸውን ገርተውታል፡፡
ወንዶች ብዙ ሴት ወዳጆች እዲኖሯቸው የሚፈልጉትስ ለምንድን ነው?
የዝግመተ - ለውጥ ጥያቄ ነው፡፡ የኢቮሊዩሽን፡፡ ብዙ ሴቶች የማግኘት ፍላጎት ከወንዱ አንጎል ጋር ድርና ማግ ሆኖ የተሰራ ነገር ነው፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው በጦርነት ሳቢያ በብዛት የሚያልቀው ወንዱ በመሆኑ የሴቶች መትረፍረፍና የወንዱ ቁጥር ማነስ በግልፅ የሚታይ ችግር ሆኗል፡፡ ማንኛውም ጎሳ ደግሞ የዘሮቹን ቁጥር መጠበቅና ማብዛት ይሻል፡፡ ስለዚህ ወንዱ ዘሩን በብዛት መዝራት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
በሰው አንጎል ውስጥ የወሲብ ግፊትና ፍላጎት የሚመለከተው ክፍል ከሴቶች ይልቅ የወንዶቹ ትልቅ ነው፡፡
ወንዶች ጥፋተኛ ሆኖ ለመቆጠር ለምን አይሹም? ምክር ለመቀበልስ ስለምን ፈቃደኛ አይሆኑም?
አንድ ወንድ ወደ አንድ ቦታ መኪና ሲነዳ ድንገት የሚሄድበት ቦታ ቢጠፋው አቁሞ መንገድ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ከጎኑ ሴት ካለች ግን በጭራሽ አይጠይቅም፡፡
ምክንያቱ አሁንም ያው እዋሻ - ውስጥ ጥንት የነበረው ወንድ ደመ - ነብስ እውስጠ በመኖሩ ነው፡፡ አንዳች የደካማነት ስሜት ካሳየ ቤተሰቡን ያስጨንቃልና፣ በጭራሽ ያ እንዲሆን አይፈቅድም፡፡ ጀግናውና ከቤቱ ወጥቶ አድኖ ቤተሰቡን መጋቢው የዋሻ ሰው፤ በቤተሰቡ ፊት ደካማ መስሎ መታየት አይፈልግም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወንዶች ተሸናፊ ሆነው መታየት የማይሹት፡፡
ሴቶች ለምን ሱቅ ሄዶ መገብየት ይወዳሉ?
ለሴቶች ገበያ መውጣት እንደማውራት ነው፡፡ ያዝናናቸዋል፡፡ ወንዶች ከ20 ደቂቃ በኋላ ገበያ ውስጥ አይቆዩም፡፡ ይሰለቻቸዋል፡፡ ወንድ አስቀድሞ ምን ምን ለመግዛት ወደ ገበያ እንደሚሄድ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ የትና ምን ያህል ጊዜም እንደሚፈጅ ሊያውቅ ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ቢባል፣ እንደማንኛውም አዳኝ - ወንድ ቶሎ ግዳይ - ጥሎ ወደ ቤቱ ይዞ መምጣት ስለሚፈልግ ነው፡፡
ትናንሽ ወጠጤ ወንዶ ልጆች ወደ ጉርምስና እየተጠጉ ሲመጡ ለምንድን ነው ሰው የሚላቸው የማይሰሙት?
ወደ መጎርመስ ሲጠጉ የጆሮዋቸው የማዳመጫ አሸንዳ በድንገት የመወፈር ፀባይ ይፈጥራል፡፡ ይህም ጊዜያዊ ነው፡፡ ግን ጊዜያዊ የመደንቆር ችግር ያስከትላል፡፡
ወንዶች አንድ ነገር አንድ ጊዜ መስራት ነው የሚሆንላቸው፡፡ ሴቶች ደግሞ ግራና ቀኙን አይለዩም፡፡ ይህስ ለምን ይሆናል?
በወንዱ አንጎል ውስጥ ግራና ቀኙን ክፍል የሚያዝዙት የነርቭ ድሮች ቁጥራቸውን ትንሽ ነው ከሞላ ጎደል የአንጎላቸው ግራና ቀኙ እራሱን የቻለ ክፍል ነው፡፡ የሴቶች ግን ግራና ቀኙ በብዙ ድሮች የተገናኘ ነው፡፡ በዚህ ምክንያ ግራና ቀኙን ወገን አይለዩም፡፡ በዙ ነገር በአንዴ ማሰብ ይችላሉ፡፡
ወንዶች “አፈቅርሻለሁ” ብለው በአፋቸው ለመናገር የማይችሉትስ ለምንድን ነው?
ወንድ በተፈቀርኩኝ ስሜት በመገበዝ እና ከፍተኛ የፍቅር ፍላጎት /ጉጉት/ በማሳየት መካከል ያለው ልዩነት ይምታታበታል፡፡ በተጨማሪም በወሲብ ፍላጎቱ ሳቢያ አሊያም ዘር ለማፍራት በመሻቱ ምክንያት ብቻ ራሱን በቃል-ኪዳን ማሰር ያስፈራዋል፡፡ ስለዚህም አፍ አውጥቶ ማፍቀሩን አይናገርም፡፡
ለምንድ ነው? ከወዶች ይልቅ ሴቶች ብዙ ልብስ እንዲኖራቸው የሚፈልጉት?
ሴቶች ብዙ ስሜቶችና የፀባይ መለዋወጥ አመል አላቸው፡፡ ከእዚህ ጋር የሚጣጣም ቀለም ያላቸውና ፋሽን የተከተሉ ልብሶች ይፈልጋሉ፡፡ በሴት ልጅ አንጎል ውስጥ ዙሪያ - ገባውን ስሜቶቿን የሚቆጣጠሩና የሚቃኙ ክፍሎች አሉ፡፡ የወንድ ልጅ አንጎል ግን በስተቀኙ ወገን ብቻ ሁለት የቁጥጥር ማዕከሎች ናቸው ያሉት፡፡ ለዚህ ነው የወንዱን ማንነቱን በቀላሉ ለመገመት የሚቻለው፡፡ ግትርም የሚሆነው በዚህ ምክንያ ነው፡፡ በተጨማሪም ከስምንት ወንዶች መሀከል አንዱ የቀለም ዳፍንት /Color Blindness/ እንዳለበት ታውቋል፡፡
የትራፊክ አደጋን ለመከላከል በጋራ እንስራ
የሰው ልጅ የፈጠራ ውጤት የሆነው ተሽከርካሪ፤ የሰዎችን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ምቹና ቀላል በማድረግ ረገድ አይተኬ ሚና እንዳለው የማይታበል ሃቅ ነው፡፡ ሰዎች ያሹት ቦታ በፍጥነት እንዲደርሱ በማገዝ፣ ከጊዜና ጉልበት ብክነት ታድጓቸዋል፡፡ ንብረቶቻቸው ደህንነቱ ተጠብቆ ከቦታ ቦታ በቀለጠፈ መልኩ እንዲጓጓዝ አስችሏቸዋል፡፡ ተሽከርካሪ በአጠቃላይ የሰው ልጆች እንቅስቃሴን የተሳለጠ አድርጎታል ማለት ይቀላል፡፡
ተሽከርካሪ የሰው ልጆችን ህይወት ለማቅለልና ለማቀላጠፍ ታልሞ የተፈጠረ የአዕምሮ ውጤት ቢሆንም ታዲያ፣ አሁን ላይ በራሱ በሰው ልጅ ግዴለሽነትና ጥፋት ለሞትና ለአካል ጉዳት የሚዳረገው ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
እንደ ተባበሩት መንግስታት መረጃ በአለም አቀፍ ደረጅ በየዓመቱ ሁለት ሚሊየን ገደማ ሰዎች ሂወታቸውን በትራፊክ አደጋ ያጣሉ ከዚህ በተጨማሪም ከ30 እስከ 50 ሚሊየን የሚደርሱ ሰዎች ለከባድና አደጋ ሲጋለጡ በተለይም እድሜያቸው ከ 5 እስከ 29 የሚደርሱ ዜጎች ይበልጥ ተጋላጭ ናቸው ተብሏል፡፡ የአለም ጤና ድርጅት በገዳይነቱ ከቀዳሚዎች ተርታ የመደበው ይኸው ችግር እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ አገራት የከፋ ነው የተባለ ሲሆን በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ በአመት የ400 ሰዎችን ሂወት እንደሚያሳጣ የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት መረጃ ይጠቁማል፡፡
የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለስልጣን ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ የመንገድ ደህንነት አቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል በዚህም የትራንስፖርት ስረአቱን በማሻሻልና የትራፊክ አስተዳደሩ ላይ በተሰሩ ስራዎች አሁን ላይ አደጋው እየቀነሰ መጥቷል፡፡
የትራፊክ አደጋ የዜጎችን ህይወት መቅጠፍ ሳያንሰው፣ ሃብትና ንብረት በማውደም፣ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡ የትራፊክ አደጋ ሰብዓዊም ቁሳዊም ኪሳራም ነው የሚያደርሰው፡፡
የዜጎችን ህይወት እየቀጠፈና ለአካል ጉድለት እየዳረገ የሚገኘው የትራፊክ አደጋ ዋና መንስኤዎች በጥናት ከተለዩ መካከል ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር፣ ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ ሳያደርጉ ማሽከርከር፣ ስልክ እያናገሩ ማሽከርከር ፣ ለሞተር ሳይክል ሄልሜት አለማድረግ ፣ የአሽከርካሪዎች ግዴለሽ አነዳድ እንዲሁም ቸልተኝነት፣ የሥነምግባር ጉድለት እና የችሎታ ብቃት ማነስ በሌላ በኩል በመንስኤነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በተጨማሪም የእግረኞች ያልተገባ የመንገድ አጠቃቀም፣ የተሽከርካሪዎች የቴክኒክ ብቃት መጓደልና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የመንገድ መሰረተ ልማቶች በተጨምሪ በመንስኤነት ይጠቀሳሉ፡፡ በቅርቡ የወጣ ጥናት ደግሞ ከፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር የትራፊክ አደጋ ቁጥር አንድ ችግር መሆኑን አመልክቷል፡፡
ሰሞኑን የአዲስ አበባ ከተማ ትራፊክ ማኔጅመንት ከጆን ሆፕኪንስ ዓለም አቀፍ የጉዳት ምርምር ክፍልና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህብረተሰብ ጤና ትምህርት ክፍል እንዲሁም ከብሉምበርግ ፊላንትሮፒስ ዓለም አቀፍ የመንገድ ደህንነት ኢኒሼቲቭ ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ መንገድ አደጋና ሞት ቅነሳ የዳሰሳ ምልከታ ሪፖርት ይፋ ተደርጓል፡፡
በዳሰሳ ጥናቱ ከተካተቱ አሽከርካሪዎች መካከል 44 በመቶ የሚሆኑት በከተማ ውስጥ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ (57 ኪሎ ሜትር በሰዓት) እንደሚያሽከረክሩ በሪፖርቱ ተጠቁሟል፡፡ የዳሰሳ ምልከታ ከተደረገባቸው የሞተር ሳይክል አሽከርካሪዎች ውስጥ ደግሞ 46 በመቶ የሚሆኑት ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ እንደሚያሽከረክሩ የተመላከተ ሲሆን፤ የሞተር ሳይክሎች ከፍጥነት በላይ ማሽከርከር በብዛት የሚስተዋለው በዕረፍት ቀናት ወይም (በሰንበት) እንደሆነ ጥናቱ ይጠቅሳል፡፡
በተደረገው የዳሰሳ ጥናት እንደተመለከተው፤ በአብዛኛው አደጋ የሚደርሰው ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 8 ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን፤ በተለይም ሰንበት ወይም የዕረፍት ቀናት ከመንገድ መጨናነቅ ነፃ ስለሚሆኑ፣ በፍጥነት ማሽከርከር ሳቢያ የሞት ምጣኔው ከፍተኛ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡
በመዲናዋ ለሚደርሱ የትራፊክ አደጋዎች ዋነኛ መንስኤ ናቸው ተብለው ከተለዩት ውስጥ ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ ማሽከርከር አንዱ ነው የሚሉት የአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ባለሥልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አማረ ታረቀኝ፤ በተጨማሪም ጠጥቶ ማሽከርከር፣ የደህንነት ቀበቶ አለማሰርና የአሽከርካሪዎች ለእግረኞች ቅድሚያ አለመስጠት ለትራፊክ አደጋ መንስኤ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ቢሮው በአሁኑ ወቅት ለትራፊክ አደጋ መንስኤ ይሆናሉ ተብለው በተለዩ ጉዳዮች ዙሪያ ለህብረተሰቡ ስልጠናና ግንዛቤ እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ የገፅ ለገፅ ስራዎችንም በ11ዱም ቅርንጫፎች በስፋት እያከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡ ከሚዲያዎችም ጋር በመተባበርም የግንዛቤ መፍጠር ሥራዎችን ያከናውናል ብለዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ዋና ዋና መንገዶች ለፓርኪንግ አገልግሎት ሲሰጡ እንደነበርና ይህም የትራፊክ መጨናነቅ በመፍጠር ለአደጋ ሲያጋልጥ መቆየቱን ያነሱት አቶ አማረ፤ አሁን ላይ ከተማ አስተዳድሩ በኮሪደር የለሙ ቦታዎች ላይ ሰፊ ፓርኪንግ በማዘጋጀት ዋና ዋና መንገዶች ከተሽከርካሪ ክፍት እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡
በሌላ በኩል የህንፃ ስር ፓርኪንጎች ሙሉ ለሙሉ ለታለመላቸው አላማ እንዲውሉ ደንብ አፀድቆ ወደ ስራ በመግባቱ፣ አደጋዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የትራፊክ አደጋ ከ2010 ዓ.ም በፊት ለተከታታይ ዓመታት 6 በመቶ እየጨመረ እንደነበር የጠቆሙት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፤ ከ6 ዓመት ወዲህ የትራፊክ አደጋ ምጣኔ ባለበት ማቆም ብቻ ሳይሆን፣ ከ5 በመቶ በላይ መቀነሱን ነው የጠቆሙት፡፡ ይሁን እንጂ አሁንም በአዲስ አበባ ከተማ በየዓመቱ ከ400 ባላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን እያጡ ነው ተብሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናዋ እየተስተዋለ የመጣው የትራፊክ አደጋ የመቀነስ አዝማሚያ ቀጣይነት እንዲኖረው፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶችን ያሳተፈ የመፍትሄ እርምጃዎችን በቅንጅት መውሰድ ይጠይቃል፡፡
ይህንን ታሳቢ በማድረግ በከተማ አስተዳድሩ ስር የሚገኙ 13 ተቋማትን ያካተተና በከንቲባ የሚመራ የመንገድ ደህንነት ምክር ቤት ተቋቁሞ የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡ በተጨማሪም የከተማ አስተዳደሩ በቅርቡ የ5 ዓመት የመንገድ ደህንነት ስትራቴጂ (2017-2023) ይፋ ያደረገ ሲሆን፤ ስትራቴጂው እስከ 2023 ዓ.ም በትራፊክ አደጋ የሚደርስ ሞትንና የአካል ጉዳትን በ25 በመቶ የመቀነስ ግብ አስቀምጧል፡፡
የትራፊክ አደጋን የመከላከል ተግባር በተወሰኑ አካላት ላይ ብቻ የሚጣል ሃላፊነት ባለመሆኑ ከመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ነቅሶ ማረምና እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል፡፡ የትራፊክ ተቆጣጣሪ አካላት ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ተከታትሎ ማረምና ማነጽ ይጠይቃል፡፡ ከተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር ጋር የሚታየውን ጉድለትም በወጉ ፈትሾ ችግሩን ከምንጩ ማድረቅ የግድ ይላል፡፡ ከመንገድ መሰረተ ልማት ጋር የተያያዙ ጉድለቶችንም አጢኖ ማረም እንዲሁም የግንዛቤ ክፍተቶችንም መሙላት እንደሚያስፈልግ አቶ አማረ ታረቀኝ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ይሄን ማድረግ በእርግጥም ዜጎችን ከሞትና ከአካል ጉድለት መታደግ ነው፡፡ የአገር ሃብትና ንብረትን ከውድመት መጠበቅ ነው። የአገሪቷንና የመዲናዋን መልካም ገጽታም መገንባት ነው፡፡ ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም የድርሻውን በባለቤትነት ስሜት መወጣት ይኖርበታል፡፡ አሽከርካሪዎች፣ የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች፣ መንገድ ገንቢዎች፣ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ብቃት አረጋጋጮች፣ እግረኞች፣ ወዘተ… በትብብርና በቅንጅት ስሟ በትራፊክ አደጋ የማይጠቀስ ከተማ ለመፍጠር በትጋት መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ያኔ ከምርም ለሌሎች ጭምር አርአያ የምትሆን የአፍሪካ መዲና ይኖረናል፡፡
ራስ መስፍን
አባት-ቢስ ገላ ነው፡፡ አንድ ልጅ በዚህ ቤተሰብ ይወሰዳል፡፡ ሰፈር ጎረቤት ለገንፎ ይጠራና ይበላል፡፡ ይጠጣል፡፡ እንደ አገሩ ደንብ ስም የማውጣት ልማድ የሚቀጥለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ በየራሱ ስም እያወጣ ሰጠ፡፡ በመጨረሻ ከስሞቹ መካከል የሚወደደውን ማጽደቅ ያለበት የቤቱ አባወራ ነውና፣ የመረጥከውን ስም ንገረን ተባለ፡፡ አባትዬው፤
“የወጣው ስም በጠቅላላ አልተስማማኝም፡፡ ስለዚህ የራሴን ባወጣ ይሻላል” አለ፡፡
የተሰበሰቡት ሰዎችም፤
“ጥሩ የአንተን እንስማ” አሉት፡፡
አባትዬውም፤
“መልካም፡፡ ብዙዎቻችሁ ያወጣችኋቸው ስሞች በተስፋ፣ በአክብሮት፣ በመልካም ምኞት እና በጀግንነት የተሞሉ ናቸው፡፡ ለቤተሰባችንና ለልጃችን ያላችሁን ልባዊ ፍቅር መግለጻችሁ ነውና ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
በበኩሌ ግን ላወጣ የፈለግሁት ስም በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ታሪክን የሚመለከትና የቤተሰባችንን የትውልድ ሀረግ የሚያጣቅስ ነውና፣ እንደምትቀበሉኝ እተማመናለሁ፡፡”
“እኔ ያወጣሁት ስም” ሲል!
የተሰበሰበው ሁሉ ማጉተምተሙንና ማንሾካሾኩን ትቶ ፀጥ፣ እረጭ አለ፡፡ ይሄኔ አባትዬው፡- ”ጣጣህ ገና ብየዋለሁ” አለ፡፡ የቢስ-ገላነት ችግር በዘር ይተላለፋል ይባላልና፣ ሰው ሁሉ ነገሩ ባንዴ ገብቶት በጭብጨባ ያወጣውን ስም አፀደቀለት፡፡
* * *
በኢትዮጵያ ያለውን ሥርዓት በማውገዝ፣ ዛሬ ፊት ለፊት የሚወሳው ችግር ሁሉ የዚያ ቅሪት ነው ብሎ መፈረጅ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል ዘዴ ይሁን እንጅ ቀስ በቀስ የዚህኛው ሥርዓትም የራሱ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች እንደ እስከዛሬው ሁሉ አፍጥጠው ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ጣጣው ያለቀ እንጂ ጣጣው ገና የሆነ ህዝብ፣ የነገ ህይወቱ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ የነገ ተረካቢ ትውልዱ ተስፋና ራዕይም በአሉታዊነት (Negativist outlook) ተፅዕኖ ስር ይወድቃል፡፡ ተጠራጣሪ ይሆናል፡፡ ሽሽግ ይሆናል፡፡ ተመራማሪና ጠያቂ ሳይሆን በደፈናው ሁሉን ተቀባይ ወይም የሆዱን ደብቆ የተቀበለ የሚመስል ህዝብ ይሆናል፡፡
እንኳንስ መሪዎቹን በሙሉ ልብ ሊቀበል፣ እርስ በእርሱም ሙሉ በሙሉ ለመተማመን እጅግ ረዥም ጊዜ የሚፈጅበት ይሆናል፡፡ ወይ ግፍና መከራ አንገቱን ያስደፋው፣ አሊያም የኑሮ ጫና ለዝምታ የዳረገው ዓይነት ህዝብ ይሆናል፡፡ መሪዎቹም ቢሆኑ ቡድናዊ አስተሳሰብ የሚያጠቃቸው እንጂ በየግላቸው ነጻ የሆነ በራስ መተማመን ያዳበሩ ስላልሆኑ ቅራኔዎች ይደበቃሉ እንጂ ወደ ስብሰባው ጠረጴዛ ጎልተው አይመጡም፡፡ አንድ የሀገራችን እውቅ ፀሐፌ-ተውኔት እንደገለጸው፡-
“በተቀራረብን ቁጥር የበለጠ እንጠፋፋለን!”
አብሮ ማደግ፣ አብሮ መማር፣ አብሮ መታገል፣ አብሮ ማሸነፍ፣ አብሮ መምራት እጅግ ጠቃሚ ነው እንዳላልን ሁሉ፣ “ከአብሮ አደግህ አትሰደድ” ዓይነት አስተሳሰብ እየገነነ ይመጣል፡፡ አብሮ አደግ እንደ ውስጥ አዋቂ፣ እንደ ገበና አጋላጭ ይቆጠራል፡፡ ያም ሆኖ ሁሉም በህዝብ ይምላሉ፡፡
“… በአዕምሮው ወይ በገንዘቡ፣ ወይ በሥልጣኑ ሊያውቁበት
ጠላታቸውን ጠላቱ፣ አርገው ጠላት ሊገዙለት፣
ወዳጃቸውን ወዳጁ፣ አርገው ወዳጅ ሊሸጡለት
እምነቱን ሊታመኑበት
እድገቱን ሊታደጉበት
ውስጡን ሆድ ለሆድ ሊስቁ
ለሆዳቸው ስላወቁ…”
እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ መተሳሰብ ወደ መተናነቅ ይለወጣል፡፡ “ሀ ራስህን አድን” የመመሪያዎች ሁሉ ቀዳሚ ይሆናል፡፡ አገር ወደ ፓርቲ፣ ፓርቲ ወደ ቡድን፣ ቡድን ወደ ግለሰብ ይጠብብ ይለወጥና፣ የአገር ጉዳይ ሲባል የአንድ የራስ ጉዳይ ወደ መሆን ይዘቅጣል፡፡ ይሄኔ ሪፖርቶች የራስ ቅኝት ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ፖሊሲዎች ራስን በማይጎዱበት መልክ ይቀረጻሉ፡፡ አጀንዳዎች ወደተፈለገበት አቅጣጫ ይመቻቻሉ፡፡ ዓላማ ቋሚ ፍኖት መሆኑ ይቀርና የወቅቱን ችግር ለማለፍ የተቀመረ የእሳት አደጋ መኪና ነው ይባላል፡፡ ቅዱሱን እርኩስ፣ አባዩን ሀቀኛ ማድረግ ቀላል ጉዳይ ይሆናል፡፡ አንድ እውቅ ገጣሚ እንደተቀኘው፡-
“ሕሊናቸውን ባይሹት፣ ሀዘን የሚሸሹ እነሱ
ለሰባት እምነት ሲምሉ፣ ለሰባት ምላስ ሲያወሱ
ባንደኛው ሲነካከሱ
በሌላው ሲሞጋገሱ
በሦስተኛው ሲካሰሱ
ሌት ዐይኑን ላፈር ያሉትን፣ ሳይነጋ የሚያወድሱ” ይሆናሉ፡፡
በሀገራን የታዩ ነጋሲዎች፣ ገዥዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ማህበሮች ታሪክ አካሄድ ውስጡ ሲታይ፣ ከላይ ወደተጠቀሰው አጠቃላይ እውነታ ሲያመራ ነው የተገኘው፡፡ ማኪያቬሊያዊ የአስተዳደር ዘይቤ (ወይ ሴሜቲክ አካሄድ እንበለው ይሆን?) ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በደም ክትባት የተገኘ እስኪመስል ድረስ ተጠናውቶን መታየቱ ታሪካችንን፣ ባህላችንንና ፖለቲካችንን ወደ ኋላ ዘልቆና ጠልቆ መመርመር ግድ መሆኑን ሳይጠቁመን አይቀርም፡፡
የአመራሩ ሂደት ድግግሞሽ፣ የአለቃና የምንዝሩ መልክ፣ የሐዋርያውና የደቀ-መዝሙሩ ባህሪ፣ የአላማጁና የመታያ አቅራቢው መመሳሰል፣ የአሮጌው ዲታ አቆራቆዝና የአዲሱ ቱጃር አመጣጠቅ የፈጠረው የኢኮኖሚ መሪና ተመሪነት፣ አሰላለፍ ወዘተ… ህዝቡን “ያው በገሌ” ሲያሰኘው ቆይቷል፡፡ ምንም ይሁን ምን ህዝብ ከጠዲቁም ከጠበሉም አይደርሰኝም ብሎ የማሰቡን ያህል፤ መንግስት ፈረሰ፣ ፓርቲ ተከላከለ፣ ምናልባትም አገርህ ውሃ በላው ቢሉትም፤
“ካልተነካችብኝ የደሀ ጎጆዬ
ህንፃዎች ቢናዱ እኔ ምን ተዳዬ”
እንዳለው መምህር ገጣሚ፣ አያገባኝም ማለቱን ይያያዘዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለማንም ደግ አይደለም፡፡ አሮጌው ተሽዋሚ ጣጣህ ገና ነው፡፡ አዲሱ ተሽዋሚ ጣጣህ ገና ነው፡፡ አሮጌው ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡፡ አዲሱ ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡ መከራ ሲፈራረቅበት “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው” እያለ ያሳልፋል፡፡ ጊዜም ለውጥ ይዞ ቢመጣ “ፊት የበቀለን ወፍ ይበላዋል…” ብሎ ሲያፈገፍግ ብልጣ-ብልጡ ይቀድመዋል፡፡ ቀድሞ መስዋዕትነት ለመክፈል የሚቆርጠው ቁጥር እየመነመነ፣ ይመራል የተባለው ጀሌ እየሆነ፣ መልካም ተናጋሪ እንደ አስተማማኝ አዋቂና መሪ እየተቆጠረ ወዘተ-- ሰው ሰራሽ ማህበረሰብ (Fictious society) ወደ መፍጠር እንዳንጓዝ ያሰጋል፡፡ ብልጣ- ብልጦች ብቻ እየኖሩ፣ የዋሀን ከቀን ቀን እያሽቆለቆሉ የሚታዩበት ሁኔታ አሰቃቂ ነው፡፡
“ኑሮ መስዋት ነው” ሲባል የነዋሪዎቹን ምስል ያሳያልም ማለት ነው፡፡ ይህ መስተዋት የዛሬን የአገሪቱን ጉስቁልና ብቻ ሳይሆን፣ የነገን አባዜም ያሳያል፡፡ ሀቀኛ ሠራተኛና ባለሙያው እንደላቡ አይኖርም፡፡ ይልቁንም አፈ-ጮማው፣ አንደበተ-ቀናው እያወለወለ የሚታይባት ሀገር እንዳትሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰራር ጣጣው ገና ነውና፡፡ “የብልጥ ውሻ ቡችላ ሆዷ ውስጥ ይጮሀል” የሚለውን ተረት አለመርሳት ነው! እየወረድን ላለንበት ቁልቁለት በጊዜ ታኮ ካልተደረገ፣ “ለጥቂቶች ገነት ለብዙዎች ሲዖል” እንደመመኘት ይሆናል፡፡
የብልጥ ውሻ ቡችላ ሆዷ ውስጥ ይጮሀል
አባት-ቢስ ገላ ነው፡፡ አንድ ልጅ በዚህ ቤተሰብ ይወሰዳል፡፡ ሰፈር ጎረቤት ለገንፎ ይጠራና ይበላል፡፡ ይጠጣል፡፡ እንደ አገሩ ደንብ ስም የማውጣት ልማድ የሚቀጥለው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ የተሰበሰበው ሰው ሁሉ በየራሱ ስም እያወጣ ሰጠ፡፡ በመጨረሻ ከስሞቹ መካከል የሚወደደውን ማጽደቅ ያለበት የቤቱ አባወራ ነውና፣ የመረጥከውን ስም ንገረን ተባለ፡፡ አባትዬው፤
“የወጣው ስም በጠቅላላ አልተስማማኝም፡፡ ስለዚህ የራሴን ባወጣ ይሻላል” አለ፡፡
የተሰበሰቡት ሰዎችም፤
“ጥሩ የአንተን እንስማ” አሉት፡፡
አባትዬውም፤
“መልካም፡፡ ብዙዎቻችሁ ያወጣችኋቸው ስሞች በተስፋ፣ በአክብሮት፣ በመልካም ምኞት እና በጀግንነት የተሞሉ ናቸው፡፡ ለቤተሰባችንና ለልጃችን ያላችሁን ልባዊ ፍቅር መግለጻችሁ ነውና ከልብ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ፡፡
በበኩሌ ግን ላወጣ የፈለግሁት ስም በእውነት ላይ የተመሰረተ፣ ታሪክን የሚመለከትና የቤተሰባችንን የትውልድ ሀረግ የሚያጣቅስ ነውና፣ እንደምትቀበሉኝ እተማመናለሁ፡፡”
“እኔ ያወጣሁት ስም” ሲል!
የተሰበሰበው ሁሉ ማጉተምተሙንና ማንሾካሾኩን ትቶ ፀጥ፣ እረጭ አለ፡፡ ይሄኔ አባትዬው፡- ”ጣጣህ ገና ብየዋለሁ” አለ፡፡ የቢስ-ገላነት ችግር በዘር ይተላለፋል ይባላልና፣ ሰው ሁሉ ነገሩ ባንዴ ገብቶት በጭብጨባ ያወጣውን ስም አፀደቀለት፡፡
* * *
በኢትዮጵያ ያለውን ሥርዓት በማውገዝ፣ ዛሬ ፊት ለፊት የሚወሳው ችግር ሁሉ የዚያ ቅሪት ነው ብሎ መፈረጅ ለተወሰነ ጊዜ የሚያገለግል ዘዴ ይሁን እንጅ ቀስ በቀስ የዚህኛው ሥርዓትም የራሱ የሆኑ መሠረታዊ ችግሮች እንደ እስከዛሬው ሁሉ አፍጥጠው ብቅ ማለታቸው አይቀርም፡፡ ጣጣው ያለቀ እንጂ ጣጣው ገና የሆነ ህዝብ፣ የነገ ህይወቱ አጠያያቂ ይሆናል፡፡ የነገ ተረካቢ ትውልዱ ተስፋና ራዕይም በአሉታዊነት (Negativist outlook) ተፅዕኖ ስር ይወድቃል፡፡ ተጠራጣሪ ይሆናል፡፡ ሽሽግ ይሆናል፡፡ ተመራማሪና ጠያቂ ሳይሆን በደፈናው ሁሉን ተቀባይ ወይም የሆዱን ደብቆ የተቀበለ የሚመስል ህዝብ ይሆናል፡፡
እንኳንስ መሪዎቹን በሙሉ ልብ ሊቀበል፣ እርስ በእርሱም ሙሉ በሙሉ ለመተማመን እጅግ ረዥም ጊዜ የሚፈጅበት ይሆናል፡፡ ወይ ግፍና መከራ አንገቱን ያስደፋው፣ አሊያም የኑሮ ጫና ለዝምታ የዳረገው ዓይነት ህዝብ ይሆናል፡፡ መሪዎቹም ቢሆኑ ቡድናዊ አስተሳሰብ የሚያጠቃቸው እንጂ በየግላቸው ነጻ የሆነ በራስ መተማመን ያዳበሩ ስላልሆኑ ቅራኔዎች ይደበቃሉ እንጂ ወደ ስብሰባው ጠረጴዛ ጎልተው አይመጡም፡፡ አንድ የሀገራችን እውቅ ፀሐፌ-ተውኔት እንደገለጸው፡-
“በተቀራረብን ቁጥር የበለጠ እንጠፋፋለን!”
አብሮ ማደግ፣ አብሮ መማር፣ አብሮ መታገል፣ አብሮ ማሸነፍ፣ አብሮ መምራት እጅግ ጠቃሚ ነው እንዳላልን ሁሉ፣ “ከአብሮ አደግህ አትሰደድ” ዓይነት አስተሳሰብ እየገነነ ይመጣል፡፡ አብሮ አደግ እንደ ውስጥ አዋቂ፣ እንደ ገበና አጋላጭ ይቆጠራል፡፡ ያም ሆኖ ሁሉም በህዝብ ይምላሉ፡፡
“… በአዕምሮው ወይ በገንዘቡ፣ ወይ በሥልጣኑ ሊያውቁበት
ጠላታቸውን ጠላቱ፣ አርገው ጠላት ሊገዙለት፣
ወዳጃቸውን ወዳጁ፣ አርገው ወዳጅ ሊሸጡለት
እምነቱን ሊታመኑበት
እድገቱን ሊታደጉበት
ውስጡን ሆድ ለሆድ ሊስቁ
ለሆዳቸው ስላወቁ…”
እንደተባለው መሆኑ ነው፡፡ መተሳሰብ ወደ መተናነቅ ይለወጣል፡፡ “ሀ ራስህን አድን” የመመሪያዎች ሁሉ ቀዳሚ ይሆናል፡፡ አገር ወደ ፓርቲ፣ ፓርቲ ወደ ቡድን፣ ቡድን ወደ ግለሰብ ይጠብብ ይለወጥና፣ የአገር ጉዳይ ሲባል የአንድ የራስ ጉዳይ ወደ መሆን ይዘቅጣል፡፡ ይሄኔ ሪፖርቶች የራስ ቅኝት ይዘው ይቀርባሉ፡፡ ፖሊሲዎች ራስን በማይጎዱበት መልክ ይቀረጻሉ፡፡ አጀንዳዎች ወደተፈለገበት አቅጣጫ ይመቻቻሉ፡፡ ዓላማ ቋሚ ፍኖት መሆኑ ይቀርና የወቅቱን ችግር ለማለፍ የተቀመረ የእሳት አደጋ መኪና ነው ይባላል፡፡ ቅዱሱን እርኩስ፣ አባዩን ሀቀኛ ማድረግ ቀላል ጉዳይ ይሆናል፡፡ አንድ እውቅ ገጣሚ እንደተቀኘው፡-
“ሕሊናቸውን ባይሹት፣ ሀዘን የሚሸሹ እነሱ
ለሰባት እምነት ሲምሉ፣ ለሰባት ምላስ ሲያወሱ
ባንደኛው ሲነካከሱ
በሌላው ሲሞጋገሱ
በሦስተኛው ሲካሰሱ
ሌት ዐይኑን ላፈር ያሉትን፣ ሳይነጋ የሚያወድሱ” ይሆናሉ፡፡
በሀገራን የታዩ ነጋሲዎች፣ ገዥዎች፣ የፖለቲካ መሪዎች፣ ፓርቲዎች፣ ድርጅቶች፣ ማህበሮች ታሪክ አካሄድ ውስጡ ሲታይ፣ ከላይ ወደተጠቀሰው አጠቃላይ እውነታ ሲያመራ ነው የተገኘው፡፡ ማኪያቬሊያዊ የአስተዳደር ዘይቤ (ወይ ሴሜቲክ አካሄድ እንበለው ይሆን?) ከልሂቅ እስከ ደቂቅ በደም ክትባት የተገኘ እስኪመስል ድረስ ተጠናውቶን መታየቱ ታሪካችንን፣ ባህላችንንና ፖለቲካችንን ወደ ኋላ ዘልቆና ጠልቆ መመርመር ግድ መሆኑን ሳይጠቁመን አይቀርም፡፡
የአመራሩ ሂደት ድግግሞሽ፣ የአለቃና የምንዝሩ መልክ፣ የሐዋርያውና የደቀ-መዝሙሩ ባህሪ፣ የአላማጁና የመታያ አቅራቢው መመሳሰል፣ የአሮጌው ዲታ አቆራቆዝና የአዲሱ ቱጃር አመጣጠቅ የፈጠረው የኢኮኖሚ መሪና ተመሪነት፣ አሰላለፍ ወዘተ… ህዝቡን “ያው በገሌ” ሲያሰኘው ቆይቷል፡፡ ምንም ይሁን ምን ህዝብ ከጠዲቁም ከጠበሉም አይደርሰኝም ብሎ የማሰቡን ያህል፤ መንግስት ፈረሰ፣ ፓርቲ ተከላከለ፣ ምናልባትም አገርህ ውሃ በላው ቢሉትም፤
“ካልተነካችብኝ የደሀ ጎጆዬ
ህንፃዎች ቢናዱ እኔ ምን ተዳዬ”
እንዳለው መምህር ገጣሚ፣ አያገባኝም ማለቱን ይያያዘዋል፡፡ ይሄ ደግሞ ለማንም ደግ አይደለም፡፡ አሮጌው ተሽዋሚ ጣጣህ ገና ነው፡፡ አዲሱ ተሽዋሚ ጣጣህ ገና ነው፡፡ አሮጌው ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡፡ አዲሱ ምዕመን ጣጣህ ገና ነው፡፡ መከራ ሲፈራረቅበት “ጊዜ ያመጣውን ጊዜ እስኪመልሰው” እያለ ያሳልፋል፡፡ ጊዜም ለውጥ ይዞ ቢመጣ “ፊት የበቀለን ወፍ ይበላዋል…” ብሎ ሲያፈገፍግ ብልጣ-ብልጡ ይቀድመዋል፡፡ ቀድሞ መስዋዕትነት ለመክፈል የሚቆርጠው ቁጥር እየመነመነ፣ ይመራል የተባለው ጀሌ እየሆነ፣ መልካም ተናጋሪ እንደ አስተማማኝ አዋቂና መሪ እየተቆጠረ ወዘተ-- ሰው ሰራሽ ማህበረሰብ (Fictious society) ወደ መፍጠር እንዳንጓዝ ያሰጋል፡፡ ብልጣ- ብልጦች ብቻ እየኖሩ፣ የዋሀን ከቀን ቀን እያሽቆለቆሉ የሚታዩበት ሁኔታ አሰቃቂ ነው፡፡
“ኑሮ መስዋት ነው” ሲባል የነዋሪዎቹን ምስል ያሳያልም ማለት ነው፡፡ ይህ መስተዋት የዛሬን የአገሪቱን ጉስቁልና ብቻ ሳይሆን፣ የነገን አባዜም ያሳያል፡፡ ሀቀኛ ሠራተኛና ባለሙያው እንደላቡ አይኖርም፡፡ ይልቁንም አፈ-ጮማው፣ አንደበተ-ቀናው እያወለወለ የሚታይባት ሀገር እንዳትሆን መጠንቀቅ ይገባል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰራር ጣጣው ገና ነውና፡፡ “የብልጥ ውሻ ቡችላ ሆዷ ውስጥ ይጮሀል” የሚለውን ተረት አለመርሳት ነው! እየወረድን ላለንበት ቁልቁለት በጊዜ ታኮ ካልተደረገ፣ “ለጥቂቶች ገነት ለብዙዎች ሲዖል” እንደመመኘት ይሆናል፡፡
መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚወስደው እርምጃ መባባሱ ተገለጸ
የኢትዮጵያ መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ የሚወስደው እርምጃ እየተባባሰ መምጣቱን ሂውማን ራይትስ ዎች አስታወቀ። ዓለምአቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ባወጣው መግለጫ፤ የኢትዮጵያ መንግስት በሲቪል ድርጅቶች ላይ በጣለው ዕግድ ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ፍላጎት አለማሳየቱን አስታውቋል።
ሂውማን ራይትስ ዎች ባለፈው ረቡዕ ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ ከሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ መንግስት በሁለት የሲቪል ድርጅቶች ላይ የወሰደውን የዕግድ እርምጃ አውግዟል። መንግስት በሲቪል ድርጅቶቹ ላይ የወሰደው ዕርምጃ ከሲቪል ድርጅቶች ዓዋጁ ጋር እንደማይጣጣም ገልጿል።
ድርጅቱ ይህ ዕርምጃ መንግስት የዘፈቀድ እስሮችን ጨምሮ ትችትን ለማፈን ሲያደርጋቸው የቆዩ ጥረቶች “አንድ አካል ነው” ብሏል። የሂውማን ራይትስ ዎች መግለጫ ሲቀጥል፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የኢትዮጵያ መንግስት የመብት ተሟጋቾችን ዒላማ አድርጎ ጥቃት መሰንዘሩን በጥብቅ እንዲቃወሙት ጠይቋል።
የኢትዮጵያ ዓለምአቀፍ አጋሮች፣ በተለይም አሜሪካና ፈረንሳይ ሲቪል ድርጅቶች በአገሪቱ ላላቸው ሚና ድጋፋቸውን እንዲገልጡ፣ ብሎም ዕገዳዎቹን እንዲያወግዙም ጥሪ አስተላልፏል፣ ድርጅቱ።
ተቆጣጣሪው የመንግስት አካል ለዕገዳው “ማሕበራቱ ነጻነት የጎደላቸው እና ከተፈቀደላቸው ስልጣን ባሻገር እየሰሩ ነው” የሚል ክስ ማቅረቡን ሂውማን ራይትስ ዎች በመግለጫው አመልክቷል። እንዲሁም ሂውማን ራይትስ ዎች መንግስት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤን ጨምሮ በመብት ተሟጋች ሲቪል ድርጅቶች ላይ በቅርቡ የጣለውን ዕገዳ እንዲያነሳና ድርጅቶቹን ዒላማ ከማድረግ እንዲቆጠብ ጠይቋል።
በሂውማን ራይትስ ዎች የአፍሪካ ዳይሬክተር ማውሲ ሴጉን፤ “የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል” ብለዋል። ዳይሬክተሯ አያይዘውም፣ “መንግስት ወሳኝ የሰብዓዊ መብት ጉዳዮችን በመመርመርና በመሰነድ ላይ የተሰማሩ ድርጅቶችን በማገድ በጉዳዩ ላይ ገለልተኛ ምርመራ የማድረግ ፍላጎት አላሳየም” ሲሉ ገልጸዋል።
መንግስት በእነዚሁ ማሕበራት ላይ ከወሰደው እርምጃ አስቀድሞ የመብቶች እና የዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣ በሰብዓዊ መብቶች ጠበቆች ማሕበር እና የሰብዓዊ መብቶች ማሕበር ላይ ተመሳሳይ ዕገዳ መጣሉ የሚታወስ ነው። በኋላ ላይ ግን በሰብዓዊ መብቶች ማሕበር ላይ የተጣለው ዕገዳ ተነስቷል።
የሲቪክ ድርጅቶችን የሚቆጣጠረው የመንግስት አካል ባለፈው ታሕሳስ ወር አንጋፋው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) እና የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል ከስራ ማገዱ ይታወሳል።
የኤፈርት ባለአደራ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ ጠየቁ
የትካል እግሪ ምትካል ትግራይ (ትእምት/ኤፈርት) ባለአደራ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ ለምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጥያቄ አቅርበዋል። ትእምት በበኩሉ፤ የተጠራ ስብሰባ የለም ሲል ጥያቄውን አስተባብሏል።
የትግራይ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የታጋዮች ማሕበራትን ጨምሮ ሌሎች ሶስት የትእምት ምክር ቤት አባል የሆኑ ማሕበራት በጻፉት ደብዳቤ፣ ተቋሙን በበላይነት እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት መሆኑን አውስተዋል። ምክር ቤቱ የቁጥጥር ስርዓት የመዘርጋት፣ በጀት እና ዕቅዶችን የማጽደቅ፣ የስራ አፈጻጸም የመገምገም፣ የትእምት ሃብት እና ንብረት ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ የመቆጣጠር ስልጣን እንዳለውም ጠቅሰዋል።
“ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት ዓመታት ስለተሰሩ ስራዎች እና አጠቃላይ የተቋሙ ሁኔታዎች የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ያመለከቱት እነዚሁ ማሕበራት፣ ከዚህ በመነሳት የባለአደራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ስብሰባ እንዲጠሩ ጥያቄ አቅርበዋል። ይሁንና ስብሰባው መቼ መጠራት እንደሚኖርበት በጻፉት ደብዳቤ ላይ አልጠቀሱም።
ይህንኑ ጥሪ ተከትሎ ትእምት (ኤፈርት) ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ “የተጠራ ስብሰባ የለም” ሲል በማሕበራቱ የቀረበውን ጥሪ አጣጥሏል። “የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት ለጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. የስብሰባ ጥሪ እንዳቀረበ የሚገልጽ እና የስድስት ማሕበራት ማሕተም ያረፈበት ደብዳቤ ተመልክተናል” በማለት የገለጸው ትእምት (ኤፈርት)፣ ደብዳቤው እና “ተጠርቷል” የተባለውን ስብሰባ በተመለከተ የትእምት ባለአደራ ቦርድ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ጠቅሷል።
የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት እና ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ በተፈረመ እና ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው ደብዳቤ እንደተገለጸው፣ የባለአደራ ምክር ቤቱ ለጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. የጠራው ስብሰባ የለም። የትእምት የሕግ መምሪያ በበኩሉ፣ የማሕበራቱ ስብሰባ “ይጠራልን” ጥያቄ የትእምት መመስረቻ ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንብን “ያልተከተለና ሕጋዊነት የሌለው ነው” ብሏል።
መምሪያው አክሎም፣ የምክር ቤቱን መደበኛ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ መጥራት የሚችሉት የትእምት ቦርድ አባላት፣ የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት እና ቦርድ ሊቀ መንበር እና የትእምት ምክር ቤት አባላት መሆናቸውን አመልክቷል። “ከእነዚህ ውጪ በተቋማት ወይም በማሕበራት አማካይነት ስብሰባ አይጠራም” ሲል፣ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፉት ማብራሪያ፣ በትእምት (ኤፈርት) ስር የሚገኙ ተቋማትን በመጀመሪያ በኮሜርሻል ኖሚኒስ ድርጅት አማካይነት እንዲተዳደሩ ተደርጎ መቆየቱን በማውሳት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ የትእምት ባለአደራ ቦርድ እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ከፌደራል መንግስት ጋር ባደረጉት ድርድር ወደ ቀድሞ ስራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም፣ የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት ከተከሰቱ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ጋር ተጣጥሞ እንዴት መስራት እንደሚችል በጥናት እየተመለሰ ያለ ጉዳይ መሆኑን እና ይኸው ጥናት ሲጠናቀቅ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና የትእምት አመራር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል።
“ከዚህ አሰራር ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተቋማቱን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ መቆጠብ ያስፈልጋል ሲሉ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል የተከሰተውን የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ፣ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል በሚመራው የህወሓት ቡድን እና በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ፍትጊያዎች እንደሚስተዋሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ በትእምት ውስጥ የተከሰተው ጉዳይም ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የክልሉን ፖለቲካ የሚታዘቡ አካላት አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
ትእምት በ1987 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በስሩ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 17 ድርጅቶችን አቅፎ ይዟል። ተቋሙ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አጠቃላይ ንብረቱ ታግዶ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በኋላ ላይ በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካይነት እንዲተዳደር መደረጉ የማይዘነጋ ነው።
የግብርና ምርምር ማዕከላት የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ ነው ተባለ
የማዕከላቱ ሕልውና ለአደጋ መጋለጡ ተገልጿል
የግብርና ምርምር ማዕከላት እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት በከተማ አስተዳደሮች የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ መሆኑ የተገለፁ ሲሆን የኖራ አቅርቦት ችግር መከሰቱም ተመልክቷል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባለፈው ሰኞ ጥር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባካሄደው 4ኛ ዓመት፣ አንደኛ ልዩ ስብሰባ፣ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ የሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውን የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል። በዚህ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ለ2017/ 18 የምርት ዘመን የሚያገለግል ማዳበሪያ በ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ለመግዛት እየተሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
በተጨማሪም በ156 ቢሊዮን ብር በጀት ለመስኖ፣ ለመኸርና ለበልግ ልማት የሚውል 24 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት “እየተሰራ ነው” ያሉት ሚኒስትሩ፣ “ከዚህ ውስጥ 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ጂቡቲ ደርሷል” ብለዋል። አያይዘውም፣ በተያዘው የበጀት ዓመት የምርት ዘመን፣ ማዳበሪያ ገዝቶ ለማቅረብ 84 ቢሊዮን ብር ድጎማ መደረጉንም አንስተዋል።
በአማራ ክልል ስለቀረበው የማዳበሪያ መጠን ሲናገሩ፤ ከ7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለክልሉ ተላልፏል ብለዋል። “ይህም ክልሉ ሰላም በነበረበት ወቅት አግኝቶት የማያውቀው መጠን ነው” ብለዋል፡፡
ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ወደ አገር ውስጥ እየገባ መሆኑን በመግለፅም፤ በድጎማ እንዲተላለፍ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አሲዳማ አፈር እንዲያገግም ለማድረግ በሚሰሩ ስራዎች ላይ የኖራ አስፈላጊነት የጎላ መሆኑን ያወሱት ዶክተር ግርማ አመንቴ፣ ለዚሁ ስራ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ተመድቦ እየተሰራ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት። ሆኖም ግን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የኖራ አቅርቦት ችግር “ገጥሞታል” ብለዋል፣ ሚኒስትሩ። የአቅርቦት ችግሩን ለመቅረፍ ግብርና ሚኒስቴር ከገንዘብ ሚኒስቴር በመተባበር እየሰራ መሆኑንም ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።
የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለሚኒስትሩ ባቀረበው ጥያቄ፣ የግብርና ምርምር እና የእንስሳት ብዜት ተቋማት በከተማ አስተዳደሮች የመሬት ይዞታቸውን እየተነጠቁ እንደሚገኙ አንስተዋል። በዚህም ማዕከላቱ እና ተቋማቱ ሕልውናቸው ለአደጋ መጋለጡ ተጠቁሟል።
የሆለታ፣ ጂማ፣ ቁልምሳ እና ቢሾፍቱ ማዕከላትን ለአብነት የጠቀሰው ኮሚቴው፣ 312 ሄክታር የምርምር ስራ የሚሰሩባቸውን መሬቶች በየከተማ አስተዳደሮቹ እንደተነጠቁ አብራርቷል። ይህንንም በየጊዜው ባደረገው ምልከታ እና ተቋማቱ በሰጡት መረጃ ማረጋገጡን ገልጿል።
በተጨማሪም፣ በአማራ ክልል የወረዒሉ የግብርና ምርምር ተቋምን ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታው አለመጀመሩን፣ ብሎም የደብረ ማርቆስ የግብርና ማዕከል በቂ የመሰረተ ልማት ግንባታ እንዳልተደረገለት ቋሚ ኮሚቴው አመልክቷል። በየማዕከላቱ የሚደረገው የግንባታ ሂደት ለምን እንደዘገየ አያያዞ ጥያቄውን ለሚኒስትሩ አቅርቧል።
ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በምላሻቸው፣ “አብዛኛዎቹ የግብርና ምርምር ተቋማት የይዞታ ማረጋገጫ ሳይኖራቸው ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል” ብለዋል። እነዚሁ ማዕከላት የሚገኙባቸው ከተሞች የማስተር ፕላን ለውጥ በማድረጋቸው፣ የመሬት አጠቃቀም ለውጥ መደረጉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ዶክተር ግርማ የምርምር ተቋማቱ ስራዎቻቸውን ማዘመን እና ማሳደግ እንደሚገባቸው ያመለከቱ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ የይዞታ ንጥቂያውን ”ለጊዜያዊ ችግር መወጣጫነት” በማሰብ የሚከናወኑ ድርጊቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል። ሚኒስትሩ ይህንን ድርጊት የሚፈጽሙ አካላት እነማን እንደሆኑ በግልጽ አላብራሩም።
የምርምር ተቋማት የሚጠቀሙበትን መሬት የፌደራል መንግስት የመስጠትና የመቀማት ሃላፊነት እንደሌለው ያመለከቱት ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ ለየማዕከላቱ መሬት መስጠት የክልሎች ሃላፊነት በመሆኑ፣ ፓርላማው “ያግዘን” ሲሉ ተማጽነዋል፡፡
የወረዒሉ እና ደብረ ማርቆስ የግብርና ማዕከላትን በተመለከት የግንባታ አፈጻጸማቸውን ማሻሻል ያልተቻለው ከመንግስት ተጨማሪ የካፒታል በጀት ባለመገኘቱ “ምክንያት ነው” ብለዋል፣ ሚኒስትሩ። የግብርና ዘርፉን ለማሻሻል ከተፈለገ በማዕከላቱ ላይ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው፣ የካፒታል በጀቱ ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚሰጥ በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ መቆየቱን አስታውቀዋል። የካፒታል በጀቱ እንዲፈቀድ ምክር ቤቱ የግብርና ሚኒስቴርን እንዲያግዝ ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ ጠይቀዋል።