Administrator

Administrator

የደራሲ በላይ ደስታ ስራዎች የሆኑት “የአበው አንደበት” እና “ያልተነበበው መፅሀፍ” የተሰኙ መፅሀፍቶች ከነገ በስቲያ በብሄራዊ ቴአትር አዳራሽ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ ይመረቃሉ፡፡ “የአበው አንደበት” የተሰኘው መፅሀፍ አንድ ሰው ለራሱ፣ ለቤተሰቦቹ፣ ለጓደኞቹና ለማህበረሰቡ በጎ ምክርን የሚለግስ እንደሆነና በሁሉም ጉዳይ ዙሪያ ጥልቅ ሀሳቦችን መሰብሰቡ የተለገፀ ሲሆን ከ90 በላይ በሆኑ ታላላቅ አባቶች የተነገሩ ከሶስት ሺህ በላይ ጥቅሶች፣ አባባሎችና ፍልስፍናዎች ተካትተውበታል ተብሏል፡፡ መፅሀፉ በ242 ገፆች ተመጥኖ፣ በ70 ብር ከ90 ሳንቲም ለገበያ የቀረበ ሲሆን ሁለተኛው ተመራቂ “ያልተነበበው መፅሀፍ” በ226 ገፆች ተመጥኖ በ69 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲው ከዚህ ቀደም ‹‹የስለላ ጥበብ››፣ ‹‹አሜሪካና 16ቱ የስለላ ተቋሞቿ›› እና ‹‹የአበው አንደበት›› የተሰኙ መፅሀፍትን ለንባብ ያበቁ ሲሆን በቀጣይም “ጓዜና ጉዞዬ”፣ “የምርመራ ጥበቦች” እና ‹‹ያልተነበበው መፅሀፍ›› 1 እና 2ን ለንባብ ለማብቃት መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል፡፡

ሞባይል ስልክ ለ3.8 ሚ. አፍሪካውያን የስራ ዕድል ፈጥሯል
     በአፍሪካ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥር 557 ሚሊዮን መድረሱንና  የአህጉሪቱ ኢኮኖሚ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2015 ከሞባይል ምርትና አገልግሎት 153 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን ፎርብስ መጽሄት ዘገበ፡፡
የአፍሪካ የሞባይል ኢኮኖሚ የ2016 ሪፖርትን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከአህጉሪቱ አጠቃላይ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የሚሸፍኑት የግብጽ፣ የናይጀሪያና የደቡብ አፍሪካ ተጠቃሚዎች ሲሆኑ፣ የሞባይል ስልክ ኢንዱስትሪው በ2015 ብቻ ለ3.8 ሚሊዮን አፍሪካውያን  የስራ ዕድል ፈጥሯል፡፡
በመጪዎቹ አምስት አመታት በአፍሪካ ተጨማሪ 168 ሚሊዮን ሰዎች የሞባይል አገልግሎት ተጠቃሚዎች እንደሚሆኑና ይህም የተጠቃሚዎችን ቁጥር 725 ሚሊዮን ያደርሰዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፤ በአህጉሪቱ አገልግሎት የሚሰጡ የስማርት ሞባይል ስልኮች ቁጥር በሶስት እጥፍ ያድጋል ተብሎ እንደሚገመትም ገልጧል፡፡ በእነዚህ አምስት አመታት የሞባይል ተጠቃሚዎች ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁ 168 ሚሊዮን አፍሪካውያን መካከልም ከ30 በመቶ በላይ  ኢትዮጵያውያን፣ ናይጀሪያውያንና ታንዛኒያውያን እንደሚሆኑም ተገልጧል፡፡
በሞባይል ስልክ አማካይነት የኢንተርኔት አገልግሎት የሚያገኙ አፍሪካውያን ቁጥርም፣ ባለፉት ሶስት አመታት በሶስት እጥፍ በማደግ፣ በ2015 የፈረንጆች አመት 300 ሚሊዮን መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፤ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ቁጥር በመጪዎቹ አምስት አመታት 550 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅም አስረድቷል፡፡

      በጁባ ባለፉት 3 ሳምንታት ብቻ ከ120 በላይ ጾታዊ ጥቃቶች ተፈጽመዋል
      የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ምክትላቸው የነበሩትን ተቀናቃኛቸውን ሬክ ማቻርን ከስልጣን አውርደው ጄኔራል ታባል ዴንግ ጋይን በቦታው መተካታቸውን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በአገሪቱ የሚደረጉ የስልጣን ሹም ሽሮች በሙሉ የሰላም ስምምነቱን ያከበሩ መሆን አለባቸው በሚል ፕሬዚደንት ሳልቫ ኬርን ማስጠንቀቁን ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር ሹም ሽሩን ማድረጋቸው በሁለቱ የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል ከስምንት ወራት በፊት የተደረገውን የሰላም ስምምነት የሚጥስና አገሪቱን ወደከፋ ጦርነት ሊያመራ የሚችል ነው መባሉን የጠቆመው ዘገባው፣ በሳልቫ ኬርና በማቻር መካከል በዚህ ወር ዳግም ግጭት መቀስቀሱን ጠቅሷል፡፡
ግጭቱ መቀስቀሱን ተከትሎ ማቻር ወታደሮቻቸውን ይዘው ከመዲናዋ መውጣታቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሳልቫ ኬርም ባለፈው ሳምንት ባወጡት መግለጫ ማቻር በአፋጣኝ ወደ ጁባ ካልተመለሱ ከስልጣናቸው እንደሚነሱ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡ በሁለቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች መካከል የተደረሰው የሰላም ስምምነት፣ የአገሪቱ ምክትል ፕሬዚዳንት በተቃዋሚው ሃይል ይመረጣል የሚል አንቀጽ ማካተቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኬር አዲሱን ምክትል ፕሬዚደንት መሾማቸው ከስምምነቱ ጋር የማይጣጣም እንደሆነም አስታውቋል፡፡
ሮይተርስ በበኩሉ፤ በአገሪቱ መዲና ጁባ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ ከ120 በላይ የጾታዊ ጥቃትና የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች ተፈጽመዋል ሲል ተመድ ባለፈው ረቡዕ ማስታወቁን ዘግቧል፡፡ የተመድ ቃል አቀባይ ፋራህ ሃቃን ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ወታደሮችና ሲቪል የለበሱ ግለሰቦች ግጭቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም፣ በሴቶችና በህጻናት ላይ አሰቃቂ የጾታ ጥቃቶችን ፈጽመዋል፡፡

Saturday, 30 July 2016 11:54

ዕዳ ከሜዳ

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ ጠዋት ማለዳ ተነስቶ ለሚስቱ፡-
“ዛሬ ከቤት ውጣ ውጣ ብሎኛል” ይላታል፡፡
ሚስቲቱም፤
“ወዴት ነው ውጣ ውጣ ያለህ?” ስትል ትጠይቀዋለች፡፡
“ወደ ሆነ ጫካ ሄጄ መዝፈን ፈልጌያለሁ”
ሚስቲቱም፤
“እኔ አልታየኝም፡፡ ደግሞስ ከመቼ ወዲያ ያመጣኸው ፀባይ ነው? እኔ ቀፎኛል፡፡ መዝፈንም ከሆነ ያማረህ እዚሁ ቁጭ ብለህ እንደልብህ እየጮህክ ዝፈን ምን ጫካ ለጫካ ያንከራትትሃል?” አዝማሪውም፤
“በገዛ አገሬ ጫካ ብሄድ፣ ሜዳውን ብጋልብ፣ ያሰኘኝን ባረግ ምን እንዳልሆን ብለሽ? እባክሽ ፍቀጂልኝና ዱር ሄጄ ዘፍኜ ይውጣልኝ” ሲል ለመናት፡፡
“እንግዲህ ይሄን ያህል ተንገብግቤለታለሁ ብለህ ልብህ ከተነሳ እዚህ ቁጭ ብለህም ምንም አትፈይድልኝ፤ ይሁን ሂድና ያሰብከው ይሙላልህ” አለችው፡፡
አዝማሪው ደስ ብሎት ወደ ዱር ሄዶ አንድ ትልቅ የዋርካ ዛፍ ስር ተቀምጦ ክራሩን ቃኝቶ፤ በሚያምር ድምፅ፤ ጮክ ብሎ፣ መዝፈን ይጀምራል፡፡
“ኧረ ፋኖ ፋኖ፣ አንት አሞተ መረራ የልብህ ሳይሞላ፣ ተኝተህ አትደር፡፡
ሜዳላይ አይድከም፣ ለዳገት የጫንከው የልቡን አርጎ ነው፤ ጀግና እፎይ የሚለው፡፡”
ይህን እየዘፈነ ፍንድቅድቅ እያለ አርፍዶ በድንገት ወደሱ የሚመጣ የእግር ኮቴ ሰማ፡፡ በርካታ ሰዎች መጥተው ከበቡት፡፡
እነዚህ ሰዎች በሬያቸው ተሰርቆባቸው ፍለጋ ላይ ናቸው፡፡
“የበሬያችን ሌባ ተገኘ፡፡ ያዙት! ያዙት!” እያሉ ይቀጠቅጡት ጀመር፡፡
አዝማሪው
“እረ ጌቶች፤ እኔ በሬ እሚባል አላየሁም፡፡”
“አንተ ነህ እንጂ የሰረቅኸው! ይሄው ከጀርባህ ያለውን አታይም፡፡ ሥጋውን በልተህ በልተህ ስትጠግብ የተረፈህን ሰቅለህ፤ በጥጋብ ትዘፍናለህ፡፡ ቆዳውም ያው የኛ በሬ መልክ ነው ያለው፡፡ መስረቅህ አንሶ ልታታልለን ትፈልጋለህ?” እያሉ እንዳይሞት እንዳይድን አድርገው ቀጥቅጠው፣ እጅ እግሩን አስረው፤ ጥለውት ሄዱ፡፡ የተረፈውን ስጋ ይዘው ሄዱ፡፡ ሚስቱ ወደ አመሻሹ ላይ ቤት ሳይመለስ በመቅረቱ ሰው ይዛ በጫካው ስታስፈልገው ዋርካው ስር ተኮራምቶ ተኝቶ ተገኘ፡፡
“ምነው ምን ሆንክ?” ብትለው፤
“እረ ተይኝ፡፡ ዕዳ ከሜዳ ነው የገጠመኝ!”
*   *   *
በል በል አለኝ፣ እንዲህ አርግ አሰኘኝ ብለን በዘፈቀደ የምናደርገው ነገር ዕዳ ከሜዳ ያመጣል፡፡ አካባቢን፣ ግራ ቀኙን በቅጡ አለማየትና አለመመርር ዕዳ ከሜዳ ያመጣል። የሌሎች ግንዛቤና የእኛ ግንዛቤ ላይጣጣም ይችላልና የሀሳብ ርቀትን ልብ እንበል። ደምቦች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች የድንገቴ ሲሆኑ ህዝብ ላይ ዕዳ ከሜዳ ይሆናሉ፡፡ ዕዳ ከሜዳ መሆናቸው ሳያንስ የአፈፃፀም ችግር ካለ ደግሞ ይብሱን ከድጡ ወደማጡ ይሆናል፡፡
ስለአፈፃፀም ችግር ሌት-ተቀን ቢወተወትም ‹‹ወይ›› ያለ የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹እሺ እናርማን› የሚል፣ ጉዳዩ የሚመለከተው ባለሥልጣን ወይም አለቃ አልተገኘም፡፡ ችግሮች የማያባራ ዝናብ የሆኑ አንድም በምንግዴ ነው፤ አንድም ሠንሠለታዊ ባህሪ ስላላቸው ማን ማንን ይነካል ነው፤ አሊያም እከክልኝ ልከክልህ ነው፤ ወይም ደግሞ የአቅም ማነስ ነው፡፡ የችግሮች ባለቤት ማጣትም ሌላው ችግር ነው፡፡ የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታም ዓይነተኛ አባዜችን ነው፡፡ አንድ ነገር የተሸከመው ችግር ሳያንስ፤ ቆሻሻ ማንሳት ችግር ሆኖ ሲያነጋግር ማየትና መስማት እጅግ አሳፋሪ ነው፡፡ ዛሬ እንደ ዘበት ‹‹ቆሻሻ ውስጤ ነው!›› እየተባለ ሲቀለድ መስማት ይዘገንናል፡፡ ስለለውጥ ማውራት ከጀመርን ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ዛሬም ውሃ የለም፡፡ ሆኖም ስለአተት እናትታለን። ዛሬም መብራት የለም፡፡ አገር እየተሰጠነች ስትሄድ መብራት የኃይል ምንጭነቱ የህልውና ጉዳይ ይሆናል እንጂ ዛራና ቻንድራን ለመመልከቻ አሊያም ስፖርት መከታተያ አይደለም ዋናው ጭንቅ ስለምጣድና የእለት እንጀራ ማሰብ ግዴታ ነው። ስለኢንዱስትሪ መፈጠር ነጋ-ጠባ የምንወተውተው ካለኤሌትሪክ ግባት ከሆነ የታሪክ ምፀት ይሆናል! የትራንስፖት እጥረት፣ ያውም በክረምት፣ እሰቃቂ ሆኗል፡፡ ከጫፍ እስከጫፍ አንዳንዴም ሰልፍ ዞሮ የት ገባ እስከሚባል ድረስ እየተምዘገዘገ የሚሄደው ሰልፍ ከዕለት ዕለት እየረዘመ መምጣቱን ለማንም አለቃ መነገር ያለበት ጉዳይ አልሆነም፡፡ ፀሀይ የሞቀው ጉዳዳ ነውና፡፡ ይልቁንም ህዝብ ትዕግሥቱንና ልቦናውን ሰጥቶት በሥነ-ስርዓት ሰልፍ ገብቶ ራሱን ማስተናገዱና ቅጥ ስለ መፍጠሩ ሊመሰገን ይገባል ያም ሆኖ በየተቋማቱ ዘንድ አሁንም የአፈፃፀም ችግር የማይዘለል ችግር ነውና። የዘፈቀደ አሰራር ሥር ከሰደደ አድሮ ዕዳ ከሜዳ መሆኑ አይቀሬ ነው! ግምገማ ውሃ ወቀጣ እንዳይሆን እናስብበት!

    ስምንት የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ባለፉት አራት አመታት ብቻ ከ1 ቢሊዮን ፓውንድ በላይ የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለመካከለኛው ምስራቅ አገራት መሸጣቸው በምርመራ መረጋገጡን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡
ባልካን ኢንቬስቲጌቲቭ ሪፖርቲንግ ኔትዎርክና ኦርጋናይዝድ ክራይም ኤንድ ኮራፕሽን ሪፖርቲንግ ፕሮጀክት የተባሉ ተቋማት ያወጡትን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፤ ከ8 የምስራቃዊ አውሮፓ አገራት ወደ መካከለኛው ምስራቅ አገራት ከገቡት በሺህዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ ከባድና ቀላል የጦር መሳሪያዎች መካከል አብዛኞቹ በእርስ በርስ ጦርነት ወደምትታመሰው ሶርያ ደርሰው ጥቅም ላይ እየዋሉ ይገኛሉ፡፡  የጦር መሳሪያዎቹን የሸጡት አገራት ቦስኒያ፣ ቡልጋሪያ፣ ክሮሺያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ሞንቴኔግሮ፣ ስሎቫኪያ፣ ሰርቢያና ሮማኒያ እንደሆኑ ለአንድ አመት በዘለቀ የተደራጀ ምርመራ መረጋገጡን የጠቆመው ዘገባው፤ አገራቱ እ.ኤ.አ ከ2012 አንስቶ ባሉት አመታት በድምሩ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ለሳኡዲ አረቢያ፣ ለዮርዳኖስ፣ ለተባበሩት አረብ ኢሜሬትስና ለቱርክ ሸጠዋል ብሏል፡፡ የጦር መሳሪያዎቹ በመካከለኛው ምስራቅ አገራት በሚገኙ አክራሪ ቡድኖች በጥቅም ላይ እየዋሉ እንደሚገኙ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የአውሮፓ ህብረት ከሽያጩ ጋር በተያያዘ ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውንና የህብረቱ ፓርላማ ከፍተኛ ባለስልጣንም አንዳንዶቹ ሽያጮች የአውሮፓ ህብረትን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ብሄራዊና አለማቀፍ ህጎች የሚጥሱ ናቸው ማለታቸውን አመልክቷል፡፡ 

“በወረዳ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለው ነው”

   መንግስት ‹‹ህገ ወጥ›› ያላቸውን ቤቶች ያፈረሠበት መንገድ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብቶች ድንጋጌና በህግ ተቀባይነት እንደሌለው የገለጹ የህግ ባለሙያዎች፤ድርጊቱ የህግ ተጠያቂነትን ሊያስከትል እንደሚችል ተናገሩ፡፡ ቤታቸው ለፈረሰባቸው ዜጎች፣መንግስት ተለዋጭ ቤት መስጠት አለበትም ብለዋል - የህግ ባለሙያዎቹ፡፡  
ዓለማቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት፤ማንኛውም ሰው ደህንነቱ እንዲጠበቅና መኖሪያ ቤቱ እንዲከበር በፅኑ ይደነግጋል ያሉት አለማቀፍ የህግ ባለሙያው ዶ/ር ያዕቆብ ወ/ማርያም፤በተለያዩ የሠብዓዊ መብት ስምምነቶች፣ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ በዋናነት ጥበቃ የሚደረግለት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡   
‹‹ሠዎች ህገ-ወጥ ቤት ቢሠሩ እንኳን ቤቶቹ ሲሠሩ በዝምታ የታለፉ እንደመሆናቸው በድጋሚ አይፈርሱም›› ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤ ‹‹በተለያዩ ሃገራት በህገ ወጥ መንገድ ቤት የሠሩ ሰዎች ካሳ ከፍለው ቤቱ ህጋዊ ይሆንላቸዋል” ሲሉ የሌሎች አገራትን ተመክሮ ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ የአዲስ አበባ አስተዳደር ያፈረሳቸው ቤቶች አፈራረስም የኢትዮጵያንም ሆነ ዓለማቀፍ የሠብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የጣሰና ዜጎችን ያለ አግባብ ለእንግልት የዳረገ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ ‹‹የከተማ አስተዳደሩ የግድ ማፍረስ አለብኝ ካለም በቅድሚያ ቤት ሊያዘጋጅላቸው ወይም ቤት ሊያሰራቸው የሚችል ተመጣጣኝ ካሣ መክፈል ነበረበት፤ይህን አለማድረጉ በሠብአዊ መብት ጥሰት ሊያስጠይቀው ይችላል›› ብለዋል፡፡
“አስተዳደሩ ቤቶቹ ሲሠሩ እያየ ዝም ካለ፣የቤቶቹን መሰራት እንደፈቀደ ይቆጠራል” ያሉት የህግ ባለሙያው፤ነዋሪዎች መብራትና ውሃ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶችን ሲያሟሉ በዝምታ ማለፉ ብቻውን ቤቶቹን ህጋዊ ያደርጋቸዋል ሲሉም ይሞግታሉ፡፡ ቤቶቹ መፍረስ አይገባቸውም ነበር፤ ስለዚህ አስተዳደሩ የፈፀመው ህገ-ወጥ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡
ይህን የአስተዳደሩን ድርጊት ማረም የሚቻለው መንግስት ለተጎጂዎቹ በቂ ካሳ ሲከፍልና ቤት ሰርቶ ሲሰጣቸው ብቻ ነው ያሉት ዶ/ር ያዕቆብ፤‹‹ወቅቱን ባላገናዘበ መልኩ ቤቶችን በጅምላ አፍርሶ ዜጎችን ሜዳ ላይ መጣል አለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ፈፅሞ የተቃረነ ኢ-ሠብአዊ ድርጊት ነው” ብለዋል፡፡ ቤቶቹን በማፍረስ ተግባር ላይ የተሣተፉ ግለሰቦችም ሆኑ ባለስልጣናትም በግላቸው በህግ መጠየቅ እንዳለባቸው ዶ/ር ያዕቆብ ይናገራሉ፡፡
የህግ መምህርና ባለሙያ አቶ ቁምላቸው ዳኜ በበኩላቸው፤የመጠለያ ጉዳይ በአለማቀፍ የሠብአዊ መብት ድንጋጌዎች ውስጥ በህይወት ከመኖር መብት ጋር ተያይዞ የሚታይ መሆኑን ጠቅሰው፣መጠለያን በዚህ መልኩ ማሳጣት የሠብዓዊ መብት ክብርን የመግፈፍ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ አለማቀፉ የሠብአዊ መብት ድንጋጌ፣ የመንግስት በሲቪል መብቶች ላይ ጣልቃ መግባትን እንደሚከለክል የጠቀሱት ባለሙያው፤መንግስት ቤቶቹን ያፈረሠበት መንገድም በዚህ የህግ ጥሰት የሚታይ ነው ሲሉ አሰረድተዋል፡፡
መንግስት ለዜጎች መጠለያ ማቅረብ ካልቻለ ለራሳቸው እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንዳለበት የጠቀሱት የህግ ባለሙያው፤ለዚህ አንደኛው መፍትሄ ቤቶቹን ከማፍረስ ይልቅ ወደ ህጋዊ መስመር የሚገቡበትን መንገድ ማመቻቸት ነበር ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ሲገነቡ መጀመሪያ ማስቆም ይገባ ነበር ያሉት የህግ ባለሙያው፤ቤቶቹ ከተገነቡ በኋላና ዜጎች በተለያየ መንገድ ህጋዊነት እንዲሰማቸው ከተደረገ በኋላ ማፍረሱ የሠብአዊ መብት ጥሰት ነው ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ መብራት ያስገቡበት፣ ሌሎች የልማት መዋጮዎችን ያወራረዱበት ሰነድ ካላቸውና ወረዳው እያወቀ መሰረተ ልማቶችን ያሟሉ ከሆነ፣ በከፊል ህጋዊ እንደሆኑ ይቆጠራል ያሉት ሌላው ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የህግ ባለሙያ፤ መንግስት ከዚህ አንፃር መሰረታዊ ስህተቶች መሰራታቸውን አምኖ፣ለተጎጂዎች ተገቢውን ካሳና መጠለያ ሊያቀርብ ይገባል ብለዋል፡፡
ግለሰቦቹ ህገወጥ ናቸው ከተባሉም ግልፅ አማራጮች ተቀምጠው፣በቀጥታ የሚያርፉበት ምትክ መጠለያ ተዘጋጅቶላቸው፣ፍትሃዊ በሆነ ሂደት ተዳኝተው፣ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ሲገኝ ብቻ ነው ቤቶች ሊፈርሱ የሚገባው ሲሉ ባለሙያው አስረድተዋል፡፡ “በቂ ማስጠንቀቂያ ሳይሰጠን ነው ቤታችን እንዲፈርስ የተደረገው” የሚለው የዜጎች አቤቱታም ከህግ አንፃር መንግስትን ሊያስጠይቀው ይችላል ብለዋል፤የህግ ባለሙያው፡፡
 የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ በርሄ በበኩላቸው፤መንግስት ቤቶቹን ከማፍረሱ በፊት ደጋግሞ ማሰብና የተለያዩ አማራጮችን ማስቀመጥ ይገባው ነበር ይላሉ፡፡ ህዝቡ መኖሪያ ቤት የሚያገኝበትን መንገድ መንግስት በሚገባ ማሰብ አለበት የሚሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤ “ሰዎቹ ከገበሬ ላይ ቦታ ገዝተው ቤት ሰርተው የሚኖሩ ከሆነ፣መጠነኛም ቢሆን ገንዘብ ያላቸው መሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ፣መንግስት ራሱ ዲዛይን አውጥቶላቸው በህጋዊ መንገድ በማህበር ተደራጅተው ኮንዶሚኒየም እንዲሰሩ ቢያደርግ ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል” ብለዋል፡፡  
“ፈረሱ የተባሉት ቤቶች መሰረተ ልማት እስኪሟላላቸው ድረስ ወረዳና ክ/ከተማ ያሉ የመንግስት አካላት የት ነበሩ?” ሲሉ የሚጠይቁት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤“በወረዳና ክፍለ ከተማ አመራሮች የሚሰሩ ስህተቶች መንግስትን በከፍተኛ መጠን ዋጋ እያስከፈለው ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት በወረዳ ደረጃ በአመራርነት መመደብ ያለበት ብቃት ያላቸውን ሰዎች ሊሆን ይገባል የሚሉት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፤እነዚህ የፈረሱ ቤቶች ይሄን ያህል አመት የቆዩት በተለያየ መንገድ የወረዳ አመራሮች ቢፈቅዱላቸው ነው፤በቤቶቹ ግንባታ ላይ የወረዳ አመራሮች እጅ አለበት ብለዋል፡፡ ቤቶቹ ከመፍረሳቸው በፊት ሌሎች አማራጮች በስፋት ሊታዩ ይገባ ነበር ያሉት ዶ/ር ቆስጠንጢኖስ፤በቀጣይም ቤታቸው የፈረሰባቸው ዜጎች ቤት ማግኘት መቻል አለባቸው፤መንግስትም መፍትሄ ያገኝለታል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡



     የደንበኞች ቀንን ለ3ኛ ጊዜ ያከበረው መሰቦ ሲሚንቶ ፋብሪካ፤የገበያ ድርሻዬን አሳድገውልኛል ፣አጋርም ሆነውኛል ያላቸውን ደንበኞቹን ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 16 ቀን፣ በባህር ዳር ከተማ ሸለመ፡፡
የሲሚንቶ ምርቶቹን በማጓጓዝና ምርቶቹን በመጠቀም ሁነኛ ደንበኞቼ ናቸው ያላቸውን በርካታ ድርጅቶች ፋብሪካው በተለያዩ ደረጃዎች የሸለመ ሲሆን በትራንስፖርት ዘርፍ የላቀ ተሸላሚ በመሆን ትራንስ ኢትዮጵያ ተጠቃሽ ነው፡፡ ምርቶቹን በማስፋፋት ደግሞ ጉና ትሬዲንግ ተሸልሟል፡፡ ምርቶቹን በመጠቀም የላቀ ሽልማት ከተሰጣቸው መካከል የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፅ/ቤትና የህዳሴውን ግድብ የሚገነባው ሳሊኒ ኮንስትራክሽን በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ፡፡  
የፋብሪካው ስራ አስኪያጅ አቶ ክብረአብ ተወልደ፤ፋብሪካው ዋነኛ ችግሩ ምርቶቹን በራሱ ትራንስፖርት ማጓጓዝ አለመቻሉ መሆኑን ጠቅሰው፣ በቀጣይ በራሱ ትራንስፖርት ለማጓጓዝ  200 ተሽከርካሪዎችን በ877 ሚሊዬን ብር መግዛቱን ተናግረዋል፡፡ እስካሁን ፋብሪካው ምርቶቹን የሚያሰራጨው ከግል ትራንስፖርት ሰጪዎች ጋር ውለታ በመግባት እንደነበርም ሥራ አስኪያጁ አውስተዋል፡፡  
መሰቦ ሲሚንቶ፤ ግልገል ጊቤ 1, 2 እና 3 እንዲሁም ታላቁ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለመንግስት የተለያዩ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክቶች ምርቶቹን እያቀረበ ሲሆን በሀገሪቱ የገበያ ድርሻውም ወደ 24 በመቶ ከፍ ማለቱን ስራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው በዓመት 2.3 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ የማምረት አቅም ያለው ሲሆን በየጊዜው አቅሙን የሚያሳድጉ የማስፋፊያ ስራዎችንም እየሰራ ነው ተብሏል፡፡

      ላቀረብነው የጥገኝነት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ አልተሰጠንም በሚል በግብጽ ከሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ቢሮ ፊት ለፊት ባለፈው ማክሰኞ ተቃውሞ ካሰሙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች መካከል ሁለቱ ራሳቸውን በእሳት ማቃጠላቸውን ‹‹ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት›› ዘገበ፡፡
የጥገኝነት ጥያቄ አቅርበው ምላሹን ሲጠባበቁ የቆዩ የኦሮሞ ተወላጆች እንደሆኑ የተነገረላቸው ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች፤ 6ኛው ኦክቶበር ሲቲ በሚባለው አካባቢ ከሚገኘው የኮሚሽኑ ቢሮ ፊት ለፊት ራሳቸውን በእሳት አቃጥለዋል ያለው ዘገባው፣ ኢትዮጵያውያኑ ድርጊቱን የፈጸሙት በግብጽ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች የጥገኝነት መብታቸው እንዲከበር ካደረጉት ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ነው መባሉን ገልጧል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ፤ በተቃውሞው ወቅት ለህልፈተ ህይወት በተዳረገቺው አንዲት የኦሮሞ ተወላጅ  ሞት የተሰማውን ሃዘን እንደገለጸ የጠቆመው ዘገባው፤ ይሄም ሆኖ ግን ኮሚሽኑ ሟቿ የሁለት ልጆች እናት መሆኗን ከመጥቀስ ውጭ ለህልፈተ ህይወት የተዳረገቺው ራሷን አቃጥላ ስለመሆኑ በግልጽ ያለው ነገር እንደሌለ ገልጧል፡፡
“በግብጽ የሚገኙ ጥገኝነት ጠያቂዎች ቁጥር ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ፣ የአቀባበል ስርዓቱ ረጅም ጊዜን የሚወስድ መሆኑ፤ በጥገኝነት ጠያቂ ስደተኞች ላይ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥን እንደሚፈጥር እንገነዘባለን፡፡ ለሁሉም አገር ጥገኝነት ጠያቂዎችና ስደተኞች ፍትሃዊ፣ ወጥና ግልጽነት ያለው አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት የሚሰራው ኮሚሽኑ፣ ሁሉም የስደተኛ ማህበረሰብ ይህንን በመገንዘብ በሰላማዊ መንገድ ትብብር እንዲያደርግ ይጠይቃል” ብሏል ኮሚሽኑ ባወጣው መግለጫ፡፡
በግብጽ መዲና ካይሮ የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች በድረገጾች አማካይነት ያሰራጩት አንድ ቪዲዮ፤ በካይሮ በተደረገው ተቃውሞ ተሳታፊ የነበሩ ሁለት የኦሮሞ ተወላጆች ራሳቸውን በእሳት ማቃጠላቸውን እንደሚያሳይ የጠቆመው ዘገባው፣ ከሁለቱ አንደኛዋም ኮሚሽኑ ባወጣው የሃዘን መግለጫ ላይ ስሟ የተጠቀሰው ሟች እንደሆነች ገልጿል፡፡
የግብጽ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴርና ካይሮ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡኝ ጠይቄ ነበር ያለው ‹‹ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት››፣ ሁለቱም አካላት ተፈጸመ ስለተባለው ድርጊት ምንም መረጃ እንደሌላቸው ጠቁመውኛል ሲል ዘግቧል፡፡
 

• ከ60 ሚ.ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን 4 ህንጻዎች ተረክቧል
• የአዲስ አበባን ጨምሮ በ4 ከተሞች ተጨማሪ ህንፃዎች እያስገነባ ነው

  የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎችን ደረጃ ለማሳደግ ባስቀመጠው መርሐ ግብር መሰረት፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህንፃዎችን በማስገንባት ላይ ሲሆን በአራት ከተሞች ከ60 ሚ. ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን ህንፃዎች መረከቡን አስታውቋል፡፡ በአርባ ምንጭ ባለ ሁለት ወለል፤ በወልቂጤ፣ በነቀምትና በወሊሶ ከተሞች ባለ ሦስት ወለል ህንፃዎች ነው፤የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ያስገነባው፡፡
በተጨማሪም በአዲስ አበባ በቱሪስት ሆቴል አካባቢ ባለ አራት ወለል፤ በሽሬ ባለ ሦስት ወለል፣ በደብረ ታቦር ባለ  ሦስት ወለል፣ በወልዲያ ባለ ሦስት ወለል ህንፃ በአጠቃላይ በ45 ሚ. ብር የ4 ሕንፃዎች ግንባታ በማካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን ግንባታዎቹ በመጪው ዓመት ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተመሳሳይ፤በአዳማ ባለ ሰባት ወለል፣ በአሰላ ባለ አምስት ወለል፣ በጂግጂጋ ባለ አራት ወለል ህንጻዎችን ለማስገንባትም በዝግጅት ላይ መሆኑን ያስታወቀው ድርጅቱ፤በቀጣይም በአዲግራት፣ በዝዋይ፣ በአላማጣና በአሰበ ተፈሪ ከተማዎች የሕንፃ ግንባታ ለማካሄድ ማቀዱን ጠቁሟል፡፡  
ርክክብ የተፈጸመባቸውም ሆነ በግንባታ ላይ ያሉ ህንጻዎች፤ድርጅቱ ለህብረተሰቡ በሚሰጠው ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ተደራሽነቱን ለማስፋት ያስችለዋል ተብሏል፡፡

      በማረሚያ ቤት አያያዝ ተበድለናል ያሉት የሽብር ተካሳሾቹ የአሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረንስ አመራሮችና የሠማያዊ ፓርቲ አባላት ላለፉት 9 ቀናት የረሃብ አድማ ያደረጉ ሲሆን ከማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ትናንት መመገብ መጀመራቸውን የረሃብ አድማ ካደረጉት አንዱ የሆኑት የሰማያዊ ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ለፍ/ቤት አስረድተዋል፡፡
መንግስት በኦሮሚያ ከተቀሠቀሰው ግጭትና ተቃውሞ ጋር በተያያዘ በሽብር ወንጀል ጠርጥሬያቸዋለሁ ሲል ክስ ያቀረበባቸውና በቂሊንቶ ማረሚያ ቤት የሚገኙት የአፌኮ ተ/ም/ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ የፓርቲ አመራሮች፡- አቶ ገርሣ አያኖ፣ አቶ ደጀኔ ጠፋ እና አቶ አዲሱ ቡላላ እንዲሁም የሰማያዊ ፓርቲ አመራርና አባላት አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ በሌላ ጉዳይ በሽብር የታሰሩት አቶ ብርሃኑ ተ/ያሬድ፣ አቶ ፍቅረ ማርያም አስማማውና ማስረሻ ሰጠኝ በረሃብ አድማ ላይ መሠንበታቸው ታውቋል፡፡
ተከሳሶቹ “በማረሚያ ቤቱ ከሌሎች እስረኞች ተለይተን በጨለማ ክፍል ውስጥ መታሠር የለብንም፤ በቤተሰብም እንዳንጠየቅ ተደርገናል” በሚል የረሀቡን አድማ ላለፉት ማድረጋቸውን የአቶ ዮናታን ተስፋዬ ጠበቃ አቶ ሽብሩ በለጠ ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡
የረሃብ አድማውን ካደረጉት መካከል ትናንት ፍ/ቤት ቀጠሮ መሰረት የነበረው አቶ ዮናታን ተስፋዬ፤ ቆሞ ችሎት መከታተል አለመቻሉን ለፍ/ቤቱ በማስረዳቱ፣ ተቀምጦ ጉዳዩን እንዲከታተል የተደረገ ሲሆን ማክሰኞ እለትም ጉሉኮስ ተሰጥቶት እንደነበር ጠበቃው አስረድተዋል፡፡
በተመሳሳይ እነ አቶ በቀለ ገርባም፤ በረሀቡ መንቀሳቀስ እስኪያቅታቸው ሰውነታቸው መጎዳቱንና ጉሉኮስ እንዲያገኙ መደረጉን ቤተሰቦቻቸው አስረድተዋል፡፡
የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ከትናንት በስቲያ እስረኞቹን በተፈጠረው ችግር ዙሪያ ማነጋገራቸውንና ያላቸውን ጥያቄ ተቀብለው ጉዳዩን “እናየዋለን” ማለታቸውን ተከትሎ፣ ታሳሪዎቹ መመገብ መጀመራቸውን አቶ ዮናታን ለፍ/ቤት ተናግረዋል፡፡