Administrator

Administrator

      ሰው በሀገር ይወለዳል ይባላል። ግን ደግሞ ሀገርን የሚወልዱ ሰዎች አሉ።  
አብደላ እዝራ ጥበብና ፍቅር የተቃቀፉበት ሀገር በውስጡ ተሸክሟል።አብሮም ኖሯል።  የምናውቀው በተባ ብዕሩ፣በሰላ ሂሱ፣ስለ ጥበብ ሲል ሁሉንም በሚተው ኪናዊ ፍቅሩ ነው።  የአንጋፋ ደራስያንን ሥራ ፈትኗል፤የረገበውን የሀገር ጥበብ ቆንጠጥ አድርጎ በከፍታ አጉልቶ ለማሳየት።  ጠቢባን የሚያደንቁ ውብ ዓረፍተ ነገሮችን ዘክሯል። እምቡጥ አበቦቹን ወጣት ደራሲያንን በሚሳሳ እጁ ኮትኩቷል።  ቸርነቱ በጥበብም በቁስም ነው።   አብደላ እዝራ ጭው ባለ በረሃ ውስጥ ዕድሜውን ሙሉ ለጥበብ ንጽህና እንደ ምንጭ
የፈሰሰ ጅረት ነበር!   በፈረሰው  ቅጥር -----     የቆመ የጥበብ ዘብ!!
                                   *********   
        አንጋፋው የጥበብ ሃያሲና የአዲስ አድማስ ጸሐፊ እዝራ አብደላ፣ ቅዳሜ ግንቦት 28  ቀን 2008  ከዚህ ዓለም በሞት  ተለይቶናል። የቀብር ሥርዓቱ እሁድ ተፈጽሟል።  ለቤተሰቡ፣ለወዳጆቹ፣ለአድናቂዎቹና ለጥበብ አፍቃሪያን መጽናናትን እንመኛለን።


ከጥር ወዲህ ከ2 ሺህ 500 በላይ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል

አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም በዚህ ሳምንት በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስደተኞችን አሳፍረው
ሲጓዙ በነበሩ ጀልባዎች ላይ በደረሱ አደጋዎች  አለማቀፉ የስደተኞች ተቋም በዚህ ሳምንት በሜዲትራኒያን ባህር ላይ ስደተኞችን አሳፍረው ሲጓዙ በነበሩ ጀልባዎች ላይ በደረሱ አደጋዎች ለሞት የተዳረጉ የተለያዩ አገራት ዜጎች ቁጥር 1 ሺህ ያህል እንደደረሰ ማስታወቁን ዘ ጋርዲያን ዘገበ፡፡ካለፈው ጥር አንስቶ በሜዲትራኒያን ባህር በደረሱ የጀልባ አደጋዎች ከ2 ሺህ 500 በላይ ስደተኞች ህይወታቸው እንዳለፈ የገለጸው ተቋሙ፤ በአካባቢው በሚከሰቱ አደጋዎች ለህልፈት የሚዳረጉ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መሆኑን ጠቁሞ፣ በ2014 ተመሳሳይ ወቅት የሞቱት ሰዎች ቁጥር 57 ብቻ እንደነበር አስታውሷል፡፡ በተለይም ከሊቢያ ወደ ጣሊያን የሚዘልቀው የባህር ላይ የጉዞ መስመር እጅግ አስቸጋሪና አደገኛ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ አንድ ጀልባ ከመያዝ አቅሙ በላይ እስከ 600 ስደተኞችን በማሳፈር ረጅሙን የባህር ላይ ጉዞ ለማድረግ እንደሚሞክር ገልጾ፣ በተያዘው የፈረንጆች አመት 2016 ብቻ በአካባቢው 2 ሺህ 119 ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን አስረድቷል፡፡ወደ አውሮፓ የሚደረገው ስደት እየተባባባሰ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ ካለፈው ጥር ወዲህ 204 ሺህ ስደተኞች ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው በሰላም ወደ አውሮፓ መግባታቸውን በመግለጽ፣ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 92 ሺህ ብቻ እንደነበር አስታውሷል፡፡

የሪዮ ኦሎምፒክ በዚካ ቫይረስ ሳቢያ መራዘሙን አልተቀበለውም
     የዓለም የጤና ድርጅት የምዕራብ አፍሪካ አገራት ከፍተኛ የጤና ቀውስ ሆኖ የቆየው የኢቦላ ቫይረስ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰባት ጊኒ፣ ከቫይረሱ ነጻ መሆኗን ባለፈው ሰኞ በይፋ ማስታወቁንና በቅርቡ በብራዚል የሚጀመረው የሪዮ ኦሎምፒክ በዚካ ቫይረስ ሳቢያ ለሌላ ጊዜ ይተላለፍ መባሉን እንዳልተቀበለው ተዘገበ፡፡
በጊኒ የኢቦላ ቫይረስን ስርጭት ለመግታትና በቁጥጥር ስር ለማዋል ባለፉት አመታት ሰፊ ርብርብ ሲደረግ መቆየቱን ያስታወሰው የኤቢሲ ኒውስ ዘገባ፤በአገሪቱ ባለፉት 3 ወራት በቫይረሱ ስርጭት ላይ የተቀናጀ ክትትል ሲደረግ እንደቆየና አንድም ሰው በቫይረሱ እንዳልተያዘ መረጋገጡን አስታውቋል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ ምንም እንኳን በቫይረሱ የተያዘ አዲስ ታማሚ በአገሪቱ ባይገኝም፣ ቫይረሱ በተለያዩ የሰውነት ክፍሎች ውስጥ በሚገኙ ፈሳሾች ውስጥ ለወራት ተደብቆ የመቆየት ባህሪ ያለው እንደመሆኑ ስርጭቱ ሙሉ ለሙሉ ተገትቷል ማለት እንደማይቻልና ዳግም ሊከሰት እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በ2013 በጊኒ የተቀሰቀሰውና ሴራሊዮንና ሊይቤሪያን ወደመሳሰሉ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በስፋት የተሰራጨው ኢቦላ ቫይረስ፣ ከ11 ሺህ በላይ ሰዎችን ለህልፈት መዳረጉንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜናም የዓለም የጤና ድርጅት፣ በብራዚል የተቀሰቀሰውና ነፍሰ-ጡሮችን በማጥቃት የተዛባ ጤንነት ያላቸው ህጻናት እንዲወለዱ የሚያደርገው የዚካ ቫይረስ፣ የከፋ የጤና ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል የሪዮ ኦሎምፒክ እንዲሰረዝ ወይም ለሌላ ጊዜ እንዲራዘም ከ150 የተለያዩ የአለማችን አገራት የጤና ኤክስፐርቶች ለተመድ ያቀረቡትን ሀሳብ ውድቅ እንዳደረገው አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሪዮን ኦሎምፒክ ለማራዘም የሚያስገድድና የጤና ቀውስ ሊከተል እንደሚችል የሚያሳይ ተጨባጭ ምክንያት የለም፤ ውድድሩን ማራዘምም ሆነ በሌላ አገር እንዲካሄድ ማድረግ፣ ቫይረሱ በአለማቀፍ ደረጃ ያለውን ስርጭት ለመግታት ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ አያበረክትም ብሏል፤ የዓለም የጤና ድርጅት፡፡

ፕሮጀክቱ የአፍሪካን 40 በመቶ የሃይል ፍላጎት ያሟላል ተብሏል

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዓለማችን በትልቅነቱ ቀዳሚውን ስፍራ ይይዛል የተባለውን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ በ14 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በጥቂት ወራት ውስጥ መገንባት እንደምትጀምር ተዘገበ፡፡
የአገሪቱ ግዙፍ ፕሮጀክት የመጀመሪያ ክፍል የሆነውና በኮንጎ ወንዝ ላይ የሚገነባው ኢንጋ 3 የተባለው ይህ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድብ፣ በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ተጠናቅቆ ሃይል ያመነጫል ተብሎ እንደሚጠበቅ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤4 ሺህ 800 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለውም ጠቁሟል፡፡
ይህ ግዙፍ ግድብ የሚያመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል፣ 20 ትላልቅ የኒውክሌር ሃይል ማመንጫዎች ሊያመነጩት ከሚችሉት ሃይል ጋር የሚመጣጠን ነው መባሉን የጠቀሰው ዘገባው፤የፕሮጀክቱ ቀጣይ አካል የሆነና 40 ሺህ ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው ሌላ ግድብ በ100 ቢሊየን ዶላር ለመገንባት መታቀዱንም ገልጧል፡፡
የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ 40 በመቶ ያህሉን የአፍሪካ የሃይል ፍላጎት ማሟላት ይችላል መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤አለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችና የአካባቢ ተቆርቋሪዎች ግን ፕሮጀክቱ በሁለቱም ክፍሎቹ በድምሩ 60 ሺህ ያህል ዜጎችን ያፈናቅላል በሚል እንደተቹት ገልጧል፡፡

400 ሺህ ፓውንድ ከመንግስት በጀት ወጪ አድርገው ነው የገዙት
    የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ፣ 400 ሺህ ፓውንድ የህዝብ ገንዘብ ወጪ በማድረግ ለአራት ሚስቶቻቸው 11 ዘመናዊ መኪኖችን ገዝተዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ የአገሪቱ ፍርድ ቤት ማጣራት መጀመሩ ተዘገበ፡፡ የህዝብ ገንዘብ ለግል ጥቅማቸው አውለዋል በሚል በተደጋጋሚ ሲከሰሱና ውሳኔ ሲተላለፍባቸው የከረሙት ዙማ፣ አሁን ደግሞ ይህን ያህል ገንዘብ አውጥተው ለሚስቶቻቸው የቅንጦት መኪና ገዝተዋል በሚል እንደተወነጀሉ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤መኪኖቹ ከአገሪቱ ፖሊስ በጀት ወጪ በተደረገ ገንዘብ መገዛታቸውን ጠቁሟል፡፡
የአገሪቱ የፖሊስ ሚኒስትር ንኮሲያንቲ ኔሊኮ ሰሞኑን መኪኖቹ መገዛታቸውን አምነው፣ ለፕሬዚዳንቱ ሚስቶች ደህንነት ሲባል ግዢው መፈጸሙ አግባብነት አለው ማለታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ፍርድ ቤት ጉዳዩን እየተከታተለው እንደሚገኝም ተዘግቧል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሚስቶቻቸው ገዟቸው ከተባሏቸው የቅንጦት መኪኖች ውስጥ አራት ሬንጅሮቨር ኤስዩቪ እና ሁለት ላንድሮቨር ዲስከቨሪ ኤስዩቪ የተባሉ እጅግ ዘመናዊ መኪኖች እንደሚገኙበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የትርዒቱ ርዕስ፡ W@tch me…
ሠዓሊ፡ ቴዎድሮስ ሐጎስ
የትርዒቱ አይነት፡ የግል፤ የቀለም ቅብ ሥራዎች
ብዛት፡ ሃያ አራት
የቀረበበት ቦታ፡ አሊያንስ ኢትዮ-ፍራንሴስ፡ አዲስ አበባ
ጊዜ፡ ሚያዚያ 03-22፡2008 ዓ.ም
ዳሰሳ አቅራቢ፡ ሚፍታ ዘለቀ (የሥነ - ጥበብ አጋፋሪ)


እንደ መሻገሪያ
ልክ እንደ ወቅታዊ የሀገራችን እውነታ ሁሉ ሥነ - ጥበባችንም በበሰለና በተብላላ የግል የሥዕል ትርዒት አቅርቦት ድርቅ የተመታ እስኪመስል ነባራዊ መሰረት ይዞ፣ ዘመንን የሚተርክና ዘመን የሚሻገር ሃሳብና ክህሎት የሚታይበት ትርዒት በናፈቀኝ (ን) ወቅት ነበር ሠዓሊ ቴዎድሮስ ሐጎስ ‹W@tch me…›ን ይዞ ከተፍ ያለው፡፡  
ለነገሩ፤ የማሳያ ቦታዎች እጥረት፤ በወኔ የመነሳሳት፣ የሞራል፣ የመስሪያ ቦታ፣ የቁሳቁስና ባጠቃላይ የመኖር ዘዴ እጥረት፤ ብሎም በሚሰሩት የሥነ - ጥበብ ስራ የዕምነትና የፍልስፍና እጥረትና የመሳሰሉት ተግዳሮቶች የኢትዮጵያ ሥነ - ጥበብን ጋሬጣ የተሞላበት እንዲሆን ባደረጉበትና አብዛኛዎቹ ዘመነኛ ሠዓልያኖቻችን “የጥበብ መጀመሪያው ኤግዚቢሽን (በተለይ solo exhibition) መፍራት ነው!” የሚለውን ስላቅ እውነታ አድርገው የተቀበሉ በሚመስልበት በዚህ ወቅት ነው ሠዓሊ ቴዎድሮስ ‹የደረስኩበትን እንካችሁ!› ለማለት የደፈረው!
ይህ ዳሰሳ ግላዊ፣ ሃሳባዊና ሂሳዊ አተያዬን ለማንፀባረቅ፤ የትርዒት ዳሰሳ አናስራትን (elements) በጨረፍታም ቢሆን ለማስተዋወቅ የተጻፈ መሆኑንና ምንም ዓይነት ተቋማዊ መሰረትና ዝንባሌ እንደማይከተል ልገልጽ እወዳለሁ!!
*  * * *  *
ይመልከቱኝ …. (1)
የትርዒቱ ርዕስ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የተሰየመ፣ የተጻፈ ወይም የተነገረ ሲሆን W@tch me … የተሰኘ ነው፡፡ ይህ ስያሜ አማካይ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታ ላለው ማንኛውም ሰው ውስብስብ አይደለም፡፡
ይመልከቱኝ … (2)
በትርዒቱ የቀረቡ ሁሉም ስራዎች “ይመልከቱኝ … ፤ እኔን ይመልከቱኝ …. እኔን ይመልከቱኝ እንጂ …” ማለት የሚፈልጉ ብቻ ሳይሆኑ እንድንመለከታቸው የሚያስገድዱ ጭምር ናቸው፡፡ እንዴት? ቢባል ዋነኛው ድርሰታዊ አወቃቀራቸው (Composition) ሲሆን የድርሰቱን ገዢ ቦታ በበላይነት ተቆጣጥረውት ነው የሚታዩትና የሚያዩን፡፡ በተጨማሪም ፊት ተደግነው (frontal ሆነው) የተደራሲን እይታዊ ንፍቅ (Visual inter-surface of the viewer’ን) እንዳይፈናፈን ወጥረው በመያዝ፣ ትኩረቱ ሁሉ እነሱ ላይ እንዲሆን ያስገድዱታል፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ አቅም ተጠቅመው ግዘፍ ከነሱ በኋላ ምን እንድናይና ምን አድርጉ ነው የሚሉን?
ብዙ ይላሉ፡፡ ለምሳሌ፡ ‹ይመልከቱን… እኛ አራታችንን …!!!› ይላሉ፡፡
ከትርዒቱ አዳራሽ መግቢያ በስተግራ ያለው ግድግዳ፣ የሁለት አንጋፋ ሰዓልያን የፊት ገጽ (portrait) የተሳለባቸውና እያንዳንዳቸው መቶ ሰማንያ በመቶ ሃያ ሴንቲ ሜትር አውታር ያላቸው ሁለት ስራዎች ተንጠልጥለውበታል፡፡
(ግድግዳው ከዘመናት በፊት ከብርቱ ደንጊያ የታነጸ በመሆኑ እንጂ ሁለቱ ስራዎች እንደተሸከሙት የሀሳብ ክብደት ቢሆን ግን ገና አንደኛው ስራ ሊሰቀልበት ሲሞክር ተብረክርኮና ተፈረካክሶ የእንቧይ ካብ ሆኖ ይቀር ነበር)፡፡ ቴዎድሮስ ለነዚህ ስራዎቹ ዓይነ - ግብ (Subject - matter) ያደረጋቸው ሁለቱ አንጋፋ ሠዓልያን፣ ሠዓሊ ታደሰ መስፍንና ሠዓሊ መዝገቡ ተሰማ ናቸው፡፡
እኒህ ሁለት ልሂቀ ጠበብት፤ ዘመናዊው የኢትዮጵያ ሥነ - ጥበብ ገና በሁለት እግሩ ለመቆም ደፋ ቀና በሚልበት ዘመን፣ አብዮት ፈንድታ ቋንጃውን መበጠስ ከጀመረችበት ከ1960ዎቹ አንስቶ እስከ አሁኑ ገና አቅጣጫውን መወሰን ካቃተው ዘመነኛዊው የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ ትንታግ ድረስ ተመስጦአቸውን ሳያደፈርሱ፣ ጥናታቸውን ሳያቋርጡ፣ ባሕር ሃሳባቸውንና ጥልቅ እውቀታቸውን ሳይሰስቱ ለተማሪዎቻቸው ሲለግሱ፣ ትውልድ ሲገነቡና ራሳቸውን ሲወልዱ የኖሩ ብርቅዬና የቁርጥ ቀን የሀገር ልጆች ናቸው፡፡
 ድንብርብሩ እየወጣ አንዱን ሲይዝ ሌላውን እየለቀቀ በመጓዝ ላይ ባለው የስነ ጥበባችን ታሪክ ውስጥም አንዳችም ሳይረበሹ ይልቁንስ አቅጣጫቸውን እያጠሩ የሚጓዙት እኒህ አንጋፋ ሰዓልያን፤ የደረሱበትን ከፍታ አጥንቶ ተገቢው ቦታ ሊሰጣቸው ባልተቻለበት ሁኔታ በምስላዊ (figurative art) የሄዱበትን ርቀት ለመዘከር እንኳ ልብ በጠፋበት ዘመን ነው ቴዎድሮስ ከሃያ ስምንት ሳንቲ ሜትር የማትበልጥ ረቂቅ የፊት ገጻቸውን በዚያ ግዙፍ ሸራ ላይ ያለ ስስት እንዲናኙ፣ እንዲገዝፉና እንዲንፏለሉ ያደረገው፡፡ ከዚህ የላቀ አክብሮትና ዋጋ ለሁለቱ አንጋፋ ሠዓልያን የትም ተችሮ  አያውቅም! ታዲያ “ይመልከቱ … ይመልከቱ እንጂ … ማለት ይህ ነው ‘ንጂ! ደግ ያደረግህ ቴዎድሮስ!
ከአንጋፋውያኑ ሰዓልያን ትይዩ ደግሞ በተመሳሳይ ጥልቀትና አውታር እንዲሁ በሀገራችን የዘመናችን የሥነ - ጥበብ ፎቶግራፍ ፋና ወጊና ቀድሞ ሰዓሊ የነበረው ሚካኤል ጸጋዬ፤ እንዲሁም በዓለም-ዓቀፉ የሥነ-ጥበብ መድረክ ዘመንኛዊውን የኢትዮጵያ ሥነ-ጥበብ እያስጠራ ያለውን ሠዓሊ ዳዊት አበበ በግዝፈት አስቀምጧቸዋል፡፡ በገለልተኛው የሥነ-ጥበብ ታሪካችን ቅብብሎሹን በማስቀጠል ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ካሉ ጥቂት ወጣት ሠዓልያን መሃል ሁለቱን መርጦ መሳሉ፣ ቦታ መስጠቱና የሚጠብቃቸውንም ኃላፊነት ማመላከቱ ሌላኛው የቴዎድሮስ ሐጎስ ‹ይመልከቱ› …. ነው ባይ ነኝ፡፡
ይመልከቱኝ … (3)
የፊት ገጽ እንደ አንድ የሥነ - ጥበብ ዘዬ ስንመለከተው፤ ጥንታዊ መሰረት ያለውና እስከ አሁኑ ጊዜም በስፋት የሚሰራበት ዘዬ ነው፡፡ ለምሳሌ ከጥንታዊት ግብጽ ሥነ - ጥበብ፣ ከጣሊያን ሬኔይሳንስ፣ ከመካከለኛው የአውሮፓ ሥነ - ጥበብ ከፍታ እስከ ዘመንኛ ፎቶግራፍ በሰፊው ጥቅም ላይ ውሏል፡፡ በዓይነትም ቢሆን ከሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ የታዋቂ ሰዎች፣ የእርቃን፣ የተራና ተርታ ሰዎችን የፊት ገጽ የመስራት ዘዬ በሥነ - ጥበብ ታሪክ ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በዓለም ታሪክም እንደነ ሊዎናርዶ ዳቬንቺ፣ ሬምብራንት፣ቪንሴን ቫን ጎ፣ ፓብሎ ፒካሶን የመሳሰሉ ስመ ጥር የዓለም ሠዓልያንም የፊት ገጽ በመስራት ይታወቃሉ፡፡
ቴዎድሮስ ሐጎስ፤ በዚህ ዘዬ ከአስር ዓመት በላይ ከመስራቱም ባሻገር ምናልባትም የራሱን ዘዬ በማዳበር፣ ስራዎቹ ጥልቀት እንዲኖራቸው በመመራመርና ሃሳቡን በማጠናከር ረገድ ግንባር ቀደም ዘመንኛ ሠዓሊያችን ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ቴዎድሮስ የራሱን ዘዬ አዳብሯል? አዎ! ይህን ደግሞ ማየት የምንችለው የሚሰራቸውን ሰዎች የፊት ገጽ ከእውነታ አግዝፎ (larger than life size) ነው የሚሰራቸው፡፡ ከእውነታ አግዝፎ መስራት አዲስ ነገር ባይሆንም በእያንዳንዱ ስራዎቹ ይህንን የሙጥኝ ብሎ መስራቱ ዘዬውን ለማዳበር ረድቶታል፡፡
 በዚህ ትርዒት ከቀረቡ ስራዎች ሶስት አራተኛዎቹ ሞዴሎቹ የቀን ሰራተኞች ናቸው፡፡
የቀን ሰራተኞች እንደ ዓይነ - ግብ (Subject matter) መጠቀሙ ራሱን የቻለ ውሳኔና ድንጋጌ ነው፡፡ የቀን ሰራተኞች በአሁኗና በግንባታዎች አማካኝነት ዘመንኛ ለመሆን በምትጣጣረው ኢትዮጵያችን ያላቸውን ሚና ማንም አይዘነጋውም፡፡ ቴዎድሮስ ይህንን ሃቅ ከፊታቸው ይመልከቱ … እያለን ይመስለኛል፡፡
አለም አላለም ግን ሠዓሊው እንካችሁ ያለውን ተመልካቹ የመጠየቅ፣የመመርመርና የማዛመድ መነሳሳት ቢኖረው፣ ሠዓሊውን ከመረዳት አልፎ ለግል አስተሳሰቡና ለግንዛቤው የሚጠቅሙ አያሌ መንገዶችን መፍጠር ይችላል ባይ ነኝ፡፡ ደግሞ ምንስ ቢሆን የእነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎችን አኗኗርና አመለካከትን መመልከት የለብንም? ከ“ይመልከቱ” … ብዙ ነገር ማየት ይቻላል፡፡ ሌላው እንደ ዓይነ - ግብ (Subject matter) የተጠቀማቸው የቀን ሰራተኞች የለበሱት ልብስና በልብሶቹ ላይ የታተሙት ጽሁፎች ነው፡፡
ቴዎድሮስ እንደነገረኝ ከሆነ፣ በልብሶቹ ላይ የታተሙት ጽሁፎችን ትርጓሜ ለባሾቹ አያውቁትም፣ አያስጨንቃቸውምም፡፡ ይህ ደግሞ በሰፊው ህዝብም የሚስተዋል ነው፡፡
ይህንን ከአያሌ ጥያቄዎች ጋር ማገናኘት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ግሎባላይዜሽን የሀገርና የግለሰብ ማንነት ላይ ሊያደርሰው የሚችለው ተጽዕኖ፤ ተጽዕኖዎቹን ለመቋቋምም ሆነ በተጽዕኖዎቹ ስር ለመውደቅ እንደ ሀገርና ግለሰብ የገነባነው ማንነት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ለማሰላሰል ያስችሉናል፡፡
ምናልባት የመጨረሻ “ይመልከቱ”… የአንዳንድ ሞዴሎቹ አቋቋም፡
አቋቋማቸው ከትከሻቸው ዞር ያሉ፣ እይታቸውን ወደ ተመልካችና ወደ ሩቅ ያደረጉ ሰዎችን እንደ ሞዴል ተጠቅሟል፡፡
እንዲህ አይነት አቋቋሞች በአብዛኛው ልበ ሙሉነትን፣ ሩቅ አላሚነትን፣ ተስፈኝነትንና ታላቅነትን አመላካች ናቸው፡፡
ከነዚህም መሃል አንደኛውን የሥዕል መስሪያ ቀለም፣ ሌላኛውን ደግሞ በአንድ እጁ ደብተር በሌላኛው እጁ ሹራብ አንጠልጥሎ ሰርቷቸዋል፡፡ … ቀለምና ደብተር ምንን ይወክላሉ? ለምን ሌላ ነገር አልያስያዛቸውም?
እንደው ሳስበው  W@tch me…. ን መዳሰስ ብቀጥል ይመልከቱኝ … እያልኩ ላተክናችሁ ነው፡፡ ስለዚህ ይብቃኝ፡፡ እስቲ እናንተም የበኩላችሁን … በሉኝ! ቸር እንሰንብት፡፡

3.5 ሚሊዮን ፓውንድ እንደሚያወጡ ይገመታል

    ብራዚላዊው የእግር ኳስ ንጉስ ፔሌ፤ በተጫዋችነት ዘመኑ የተሸለማቸውና ይጠቀምባቸው የነበሩ የተለያዩ ውድ ንብረቶች በመጪው ወር ለንደን ውስጥ በሚካሄድ ጨረታ ለሽያጭ እንደሚቀርቡና 3.5 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣሉ ተብሎ እንደሚገመት ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ጁሊየንስ ኦክሽን በተባለው አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለጨረታ ከሚቀርቡት የፔሌ ውድ ንብረቶች መካከል ዋንጫዎች፣ ውድ የእጅ ሰዓቶች፣ ሜዳሊያዎች፣ ኳሶችና ሌሎች የስፖርት ቁሳቁስ ይገኙበታል ያለው ዘገባው፣ ተጫዋቹ ከሽያጩ ከሚገኘው ገቢ የተወሰነውን በብራዚል ለሚገኝ አንድ የልብ ህክምና ሆስፒታል በስጦታ ለማበርከት ማቀዱን ገልጿል፡፡
ለጨረታው ከቀረቡት እቃዎች መካከል በዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ቅርጽ የተሰራው የፔሌ ውድ ዋንጫ፣ እስከ 420 ሺህ ፓውንድ ያወጣል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ዘገባው፣ ሜዳሊያዎቹ 141 ሺህ ፓውንድ፣ 1ሺኛዋን ጎሉን ያስቆጠረባት ታሪካዊት ኳስም 42 ሺህ ፓውንድ ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡
የ75 አመቱ ብራዚላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ፔሌ፤ በአለማችን እግር ኳስ ታሪክ ደማቅ ተግባር የፈጸመ፣ ዘመን የማይሽረው ተጫዋች እንደሆነ የገለጸው ዘገባው፣ “የክፍለ ዘመኑ የዓለማችን ምርጥ የእግር ኳስ ተጫዋች” በሚል በፊፋ መሸለሙንም አስታውሷል፡፡

    ሰሞኑን ኢትዮጵያን የጎበኙት የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፊሊፕ ሃሞንድ፣ በሽብር ወንጀል ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸውና በእስር ላይ የሚገኙት አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ፤ የህግ ድጋፍ የሚያደርግላቸው ጠበቃ ማቆም ይችላሉ የሚል ማረጋገጫ ከኢትዮጵያ መንግስት እንዳገኙ ተገለጸ፡፡
ሪፕራይቭ የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም በበኩሉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ አንዳርጋቸው ከእስር ተፈትተው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የኢትዮጵያን መንግስት አልጠየቁም በሚል ትችት ሰንዝሮባቸዋል፡፡
ባለፈው ረቡዕ ኢትዮጵያን የጎበኙት ፊሊፕ ሃሞንድ፤ የአቶ አንዳርጋቸውን ጉዳይ በጉብኝታቸው ዋና አጀንዳ እንዳደረጉት የጠቆመው የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ጋር በአቶ አንዳርጋቸው ጉዳይ ዙሪያ መምከራቸውንና አቶ አንዳርጋቸው ጠበቃ ማቆም እንደሚችሉ ማረጋገጫ እንደተሰጣቸውም ገልጧል፡፡
ፊሊፕ ሃሞንድ ምንም እንኳን አቶ አንዳርጋቸውን የእንግሊዝ ቆንስላ እንዲጎበኛቸው መፈቀዱና ወደ ፌደራል እስር ቤት እንዲዛወሩ መደረጋቸው አንድ እርምጃ ቢሆንም፣ ሌሎች ቀጣይ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ሲሉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለ ማርያም መግለጻቸውንና፣ የህግ አማካሪ እንዲኖራቸው መፈቀዱን ተናግረዋል፡፡
እንግሊዝ በሌሎች አገራት የፍትህ ስርዓት ጣልቃ እንደማትገባ የገለጹት ፍሊፕ ሃሞንድ፤ የአገሪቱ ቆንስላ የአቶ አንዳርጋቸውን  ደህንነትና የህግ ምክር አገልግሎት ማግኘት የማረጋገጥ ሚናውን እንደሚጫወት ጠቁመው መንግስታቸው ግለሰቡንና ቤተሰቦቻቸውን መርዳቱን  እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡
የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ባለስልጣን ባለፈው ረቡዕ አቶ አንዳርጋቸውን እስር ቤት ሄደው መጎብኘታቸውንም መግለጫው አክሎ ገልጧል፡፡
ሪፕራይቭ የተባለው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ተቋም ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፤ “ፊሊፕ ሃሞንድ ጉብኝታቸው የፈጠረላቸውን መልካም አጋጣሚ አልተጠቀሙበትም፤ አቶ አንዳርጋቸው የህግ ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ፈጥሪያለሁ ማለቱም ትርጉም የለውም” በማለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን መግለጫ አጣጥሎታል፡፡

የግብጽ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሳሜን ሹክሪ፤ “የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እውን ሆኗል፣ ህልውናውን ለመካድ መሞከር ራስን መሸንገል ነው፤ በተጨባጭ የምናየውን ግድብ ህልውና ለመካድ መሞከር አያዋጣንም” ማለታቸውን አሃራም የተባለው የአገሪቱ ድረገጽ ዘገበ፡፡
ሚኒስትሩ ባለፈው ማክሰኞ አል-ሃያት በተባለው የአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ባደረጉት ንግግር፣ አገሪቱ የግድቡን ጉዳይ በተመለከተ የምታደርገው እንቅስቃሴ በጥርጣሬ፣ ባለመተማመንና በተጋነኑ አደጋዎች ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ጠቁመው፣ ይሄም ሆኖ ግን ከግድቡ ጋር በተያያዘ ለአገሪቱ አስጊ የሆኑ አደጋዎች መኖራቸውን አስታውቀዋል፡፡
መንግስታቸው እነዚህ አደጋዎች በአገሪቱ ላይ ምንም አይነት ጉዳት የማያደርሱበትን መላ ለመፍጠር የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ውይይት እያደረገ እንደሚገኝ ሚኒስትሩ ቢናገሩም፣ የአደጋዎቹን ባህሪና ምንነት በተመለከተ ግን ግልጽ ማብራሪያ አለመስጠታቸውን ዘገባው ጠቁሟል፡፡

    ለ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተና መቋረጥ ምክንያት የሆነውን የፈተና መሰረቅ ጉዳይ ፖሊስ እየመረመረ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን ለድጋሚ ፈተና የህትመትና የመጠረዝ ስራ እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡
በስርቆቱ ጉዳይ የሚደረገው ምርመራ በተጠናከረ መልኩ ሙሉ ለሙሉ በፀጥታ ኃይሎች መያዙን ያስታወቁት በትምህርት ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አህመድ ሲራጅ፤ ጉዳዩን ተከታትሎ ለህግ የማቅረብ ስራ የፖሊስ መሆኑን ጠቁመው ጉዳዩ የፀጥታ አካላት የሚፈትኑበት ነው ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው የህግ ባለሙያ፤ በመንግስት ከፍተኛ መስሪያ ቤት እንዲህ ያለው ወንጀል ሲያጋጥም ፖሊስ በሁለት መንገድ ምርጫ ሊያደርግ እንደሚችል ጠቅሰው አንደኛ ቀጥታ ጥቆማ ከመስሪያ ቤቱ ሲደርሰው፣ ጥቆማ ካልደረሰው ያገኘውን ፍንጭ መነሻ አድርጎ ምርመራ እንደሚያደርግ አብራርተው፤ ማህበራዊ ድረ ገፅ ላይ “ፈተናው ተሰርቋል” ተብሎ ይፋ በተደረገ ጊዜ ፖሊስ ምን ህል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ምርመራ ለማድረግ እንደሞከረ መጠየቅ አለበት ብለዋል፡፡ ትምሀርት ሚኒስቴር በበኩሉ፤ በአሁን ወቅት በዋናነት ትኩረት የሰጠው ፈተናው በድጋሚ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ በጥንቃቄ ማካሄድ በሚቻልበት ጉዳይ ላይ መሆኑን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል ፈተናው ተጠርዞ፣ ታሽጎ፣ በሀገሪቱ በሚገኙ 802 የፈተና ጣቢያዎችና በውጭ ሀገር በሚገኙ 3 ጣቢያዎች ለማድረስ እስከ 3 ወር ይፈጅ እንደነበርና የተዘጋጀው መጠባበቂያ ፈተና በልዩ ግብረ ኃይል እየተመራ፣ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ በ23 ቀን ውስጥ ሁሉንም ጉዳዮች ለማጠናቀቅ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
ፈተናውን ለመስጠት የታቀደው ከሰኔ 22 እስከ 30 ባለው ጊዜ ውስጥ ሲሆን የረመዳን የፆም ወቅት መሆኑንና የኢድአል ፈጥር በአልም ከተያዙት ቀናት መካከል በአንዱ ሊሆን እንደሚችል በመግለፅ የተያዘው ፕሮግራም እንዲቀየር እየተጠየቀ ቢሆንም ትምህርት ሚኒስቴር ፕሮግራሙን እንደማይቀይር አስታውቋል፡፡
ፈተናው ተሰርቆ መውጣቱ ተረጋግጦ ቀደም ያለው መርሃ ግብር ከተሰረዘ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ፈተናውን እንዴት መስጠት ይቻላል በሚለው ላይ አመራሮችና ባለሙያዎች ውይይት ማድረጋቸውን ሃላፊው ጠቁመው፤ በ23 ቀናት ውስጥ ማከናወን እንደሚቻል ታምኖበት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል ይሄም የተማሪዎችን የጭንቀትና የመቆዘሚያ ጊዜ ለመቀነስ ታስቦ ነው” ገልፀዋል - ይሄም፡፡
የረመዳን ወር መሆኑ እንደሚታወቅና ካለው ችግር አንፃር በአሉ የሚውልበትን ቀን መዝለሉ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን ያብራሩት ኃላፊው የረመዳንን ወር “ፆም ከስራ ጋር የታረቀ  ህብረተሰብ በስራ የሚያሳልፈው መሆኑን ሙስሊሙ ህብረተሰብም መንግስት ያለበትን ጫና በአግባቡ ይረዳል የሚል እምነት እንዳለ ተናግረዋል፡፡ አሁን በድጋሚ ከተያዘው ቀን ወደፊት ይራዘም ቢባል የፈተና ማረሚያ፣ ውጤት ማሳወቂያና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፕሮግራሞችን የሚያፋልስ መሆኑን ያስረዱት ኃላፊው አስቀድሞ የተያዘውን የጊዜ ሰሌዳ ለማሳካት ሲባል ርብርብ ማድረጉ አስፈላጊ ሆኗል ብለዋል፡፡