Administrator

Administrator

“የፖሊሲ ለውጥ ከሌለ የግለሰቦች መቀያየር ለውጥ አያመጣም”

• ተቃዋሚዎችና ፖለቲከኞች በሹም ሽሩ ደስተኞች አይደሉም
• የህዝቡን ጥያቄዎች መለስ ብሎ ማየት ያስፈልጋል ተባለ
ኢህአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች በተቀሰቀሰው ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ አመፅና ተቃውሞ በአጠቃላይ ወደ አንድ ሺ የሚጠጉ ዜጎች ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን በብዙ ሺዎች የሚገመቱ በእስር ላይ እንደሚገኙ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሪፖርት ይጠቁማል፡፡ የሟቾች ቁጥር ተጋንኗል የሚለው መንግስት በበኩሉ፤የጸጥታ ሃይሎችን ጨምሮ ከ500 በላይ ሰዎች መሞታቸውን አልካደም፡፡  በተቃውሞው በርካታ የመንግስትና የግል ባለሃብቶች ንብረትም እንደተቃጠለና እንደወደመ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ይሄን የፖለቲካ ቀውስ ተከትሎ ነው በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት፤የከፍተኛ ባለስልጣናትን ሹም ሽር የሚያካትት “ጥልቅ ተሃድሶ” በማድረግ የህዝቡን ጥያቄዎች እንደሚመልስ በ2008 መጠናቀቂያ ላይ ቃል የገባው፡፡ በዚህ መሃል በኦሮሞ ባህላዊ የምስጋና ቀን “እሬቻ” በዓል ላይ በተከሰተው አስደንጋጭ የበርካታ ዜጎች ህልፈት ሳቢያ ህዝባዊ ቁጣ ተቀሰቀሰ፡፡ በቀጣዮቹ ቀናትም በተለይ የውጭ ባለሃብቶችን ክፉኛ ያስደነገጠ ውድመትና ዘረፋ በፋብሪካዎቻቸው፣በእርሻቸው፣በአጠቃላይ በንብረቶቻቸው ላይ ተፈጸመ፡፡ ይሄን ተከትሎም የዛሬ ሦስት ሳምንት መንግስት አገሪቱን ለማረጋጋትና የህዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚል ለ6 ወር የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁን አስታወቀ፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በግንቦት 200ገ ምርጫ ማግስት ራሳቸው ያቋቋሙትን የሚኒስትሮች ካቢኔት በመበተን፣ከወትሮው በተለየ መንገድ በምሁራን የተዋቀረ አዲስ ካቢኔ የመሰረቱ ሲሆን 9 ሚኒስትሮች ብቻ ባሉበት ሲቀሩ 16 አዳዲስ ሚኒስትሮችን ሾመዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 5 የሚሆኑት የፓርቲ አባል አይደሉም ተብሏል፡፡ ሹመቱ የተከናወነው በዋናነት የትምህርት ዝግጅትና ብቃትን መሰረት አድርጎ መሆኑን ለተወካዮች ም/ቤት የገለጹት ጠ/ሚኒስትሩ፤አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ አቅሙና ብቃቱ ያላቸው እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
 የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች ግን በአዲሱ ካቢኔ ደስተኛ አይደሉም፡፡ በምሁራን በተዋቀረው አዲስ ካቢኔም እምብዛም የተደመሙ አይመስሉም፡፡ ጠንከር ያለ ሂስ የሰነዘሩም አልጠፉም። ሁሉም በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ግን የፖሊሲ ለውጥ አስፈላጊነት ላይ ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ሳይደረግ ግለሰቦች መለዋወጥ ብቻውን ውጤት አያመጣም ባይ ናቸው፡፡ የህዝቡም ጥያቄዎች በዚህ መንገድ መልስ ያገኛሉ ብለው እንደማያምኑ አበክረው ይናገራሉ፡፡ አንጋፋዎቹን የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮችና ፖለቲከኞች በአዲሱ ሹም ሽር ዙሪያ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ አነጋግሯቸዋል፡፡      
                                                           ****

“ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ የፖሊሲ ለውጥ ነው”
ዶ/ር መረራ ጉዲና
(የፖለቲካ ሳይንስ ምሁርና የተቃዋሚ መሪ

*የሰሞኑን የሚኒስትሮች ሹመት እንዴት አገኙት? እንደጠበቁት ነው ወይስ ----?
“ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ” እንደሚባለው ነው የሆነው፡፡ ህዝብ እየጠየቀ ያለው መሰረታዊ ለውጥ ነው፡፡ ኢህአዴግ ደግሞ ቀባብቶ ለማለፍ እየሞከረ ነው፡፡ ከኋላ የነበሩትን ወደፊት በማምጣት “ይኸው እየተሻሻልኩ ነው፤እየተለወጥኩ ነው፤ እየታደስኩ ነው” እያለ ነው፡፡ ህዝብ ግን የጠየቀው፡- ነፃ ምርጫ ቦርድ፣ ነፃ ፍርድ ቤት፣ ነፃ ሚዲያ፣ ነፃ የሲቪክ ተቋማትና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን ነው። ራስን በራስ ማስተዳደር ሌላው የህዝብ ጥያቄ ነው፡፡ ኢህአዴግ ግን “እኔ ራሴ እየተለወጥኩ ነው እመኑኝ፤ ጥያቄያችሁን እየመለስኩላችሁ ነው” አይነት ነገር ነው እያለ ያለው፡፡
*ሹመቶቹ የትምህርት ዝግጅትንና ብቃትን መሰረት አድርገው የተሰጡ ናቸው ተብሏል፡፡ ከዚህ አንጻር ከቀድሞው የተሻለ ውጤት መጠበቅ አይቻልም?
ኢህአዴግ አሁን ከገባበት አጣብቂኝ ውስጥ ግለሰቦችን በመለዋወጥ የሚወጣ አይመስለኝም። ለህዝቡም ጥያቄ አጥጋቢ መልስ አይመስለኝም። ለምሳሌ ብዙ የእውቀት ሰርተፍኬት ያላቸው ሰዎች ገብተዋል ነው የተባለው፡፡ በኢህአዴግ ውስጥ ያለው ችግር ግን የእውቀት ብቻ አይደለም፤ መሰረታዊ የፖሊሲ ችግር አለ፡፡ የአሰራር ችግር አለ፡፡ ያንን የሚለውጥ ነገር መፈጠር ነው ያለበት። ግለሰቦች ብቻ መለዋወጡ፣ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም” ነው የሚሆነው፡፡ እነዚህ ተሾሙ የተባሉ ምሁራኖችም ቢሆኑ በኢህአዴግ አካባቢ የነበሩ ናቸው፡፡ አዳዲሶች አይደሉም፡፡ በተለያየ ደረጃ ኢህአዴግን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው፡፡ ምን ውጤት እንደሚያመጡ ለወደፊት የምናየው ይሆናል፡፡
*በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የሚሉትን ጨምሮ የጠ/ሚኒስትሩ አማካሪነት ሹመቶች እንዲቀሩ ተደርገዋል፡፡ በዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
እነዚህ የስልጣን እርከኖች ከህገ መንግስቱ ውጪ የነበሩ ናቸው፡፡ አንድ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ በርካታ ምክትል ጠ/ሚኒስትሮችና አማካሪዎች ይኖራሉ የሚል አንቀፅ ህገ መንግስቱ ላይ የለም። ስልጣንን ለማደላደል የተደረገ እንጂ ህጋዊ አልነበረም፡፡ ዞሮ ዞሮ ያመጡትም የወሰዱትም እነሱ ናቸው፡፡ ስለዚህ ይህን በማስቀረታቸው የሚመጣ ብዙ ለውጥ የለም፡፡ እንዳልኩት ዋናው መሰረታዊ ጉዳይ የፖሊሲ ለውጥ ነው፡፡ ፖሊሲው ከተለወጠ በኋላ የተሻለ ስራ መስራት ያስችላል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት ተሞክሮ አሁን ያለውን ቀውስ ያስከተለውን ፖሊሲ ሳይለውጡ፣ ባለስልጣናትን ወደ ፊትና ወደ ኋላ በማድረግ ምንም ውጤት ሊመጣ አይችልም፡፡ እንደ አንድ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር፣ በዚህ በኩል ምንም የሚታየኝ ነገር የለም፡፡
አዲሱ ካቢኔ በዚህ መልኩ በምሁራን ይዋቀራል ብለው ጠብቀው ነበር?
ምን መጠበቅ ያስፈልጋል! ተሃድሶ እናደርጋለን እያሉን አልነበር እንዴ፡፡ እኔ ግን ይሄን አልነበረም የጠበቅሁት፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ነበር የምጠብቀው። “እኔ ማስተዳደር አቅቶኛል፤ከሌሎች ኃይሎች ጋር መግባባት ፈጥሬ፣ከምሁራን ጭምር ተቀናጅቼ ለውጥ አመጣለሁ” ቢል ነበር መልካም የሚሆነው። የሠለጠነ ሃገር ቢሆን ኖሮ፣ ይሄ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ ጠይቆ ከስልጣን መውረድ ነበረበት፡፡ ብዙ ቃል የገባቸውን ነገሮች መፈፀም ስላቃተው፣ ”ስልጣን ወይም ሞት” ማለቱን ትቶ፣ ቢሆን ከስልጣን መውረድ ካልሆነ ደግሞ ከኢትዮጵያ ምሁራን ጋር ተቀናጅቶ፣የዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ለመጀመር ቁርጠኝነቱን ማሳየት ነበረበት፡፡
የፖሊሲ ለውጥ የሚሉትን ሊያብራሩልኝ ይችላሉ?
የፖሊሲ ለውጥ ሲባል ለምሳሌ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ አንዱ ነው፡፡ የዴሞክራሲ ተቋማት ነፃነት፣ ለምሳሌ የሚዲያ ነጻነት፣ የፍርድ ቤት ነጻነት፣ የፓርላማ ነፃነት ---- ሌላው ነው፡፡ ይሄ ሲሆን ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል፡፡ የስልጣን ክፍፍል ማድረግም አንድ የፖሊሲ ለውጥ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው ህዝቡ በመረጣቸው የአካባቢ አስተዳደሮች እንዲመራ ማድረግ ነው፡፡
መሬትን በተመለከተ “መድረክ” መሬት ይሸጥ የሚል አቋም የለውም፤ ነገር ግን ለምሳሌ መንግስት መሬቱን ሲሸጥ ከሚያገኘው ገንዘብ ላይ ለገበሬው በተገቢው መልኩ ማካፈል አለበት፡፡ እነሡ አሁን 50 ሺህ ብር ካሳ ከፍለው ወዲያው ያንን ቦታ 50 ሚሊዮን ብር ይሸጡታል፡፡ ነገር ግን ከ50 ሚሊዮኑ ለገበሬው 10 ሚሊዮኑን መስጠት ይቻል ነበር፡፡ በቦታው ላይ 50 መኖሪያ ቤቶች ከተሰሩ ደግሞ 10ሩን ለባለ መሬቱ ሰጥቶ፣ እያከራየ ህይወቱን እንዲለውጥ ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም ገበሬው የተሻለ ህይወት ሊመራ ይችላል፡፡ ዋናው ነገር ኢኮኖሚውንም የዲሞክራሲ ጨዋታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡  
የምርጫ ስርአቱ ይሻሻላል ተብሏል፡፡ ስርአቱ መሻሻሉ ምን የሚያመጣው ለውጥ ይኖራል?
በፊት ከነበረው ይሻላል እንጂ መሠረታዊ ለውጥ አያመጣም፡፡ ባለፉት 16 እና 17 አመታት የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንዲቀንስ ስንጠይቅ ነበር። አሁን ኦሮሚያ ውስጥ ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ቢደረግ ኢህአዴግ በዝረራ ይሸነፋል፡፡ የሆኖ ሆኖ የምርጫ ሥርዓቱ መሻሻሉ አይጠላም፡፡ እኛም ስንጠይቀው የነበረ ነው፡፡ ግን መሠረታዊ መፍትሄ አይደለም። አሁን ህዝብ እየጠየቀ ያለው ከዚያም የላቀ ነው፡፡ ራስን በራስ የማስተዳደር ጉዳይ አንዱ ጥያቄ ነው፡፡

==============================

“በምሁራን የተዋቀረ የመጀመሪያው ካቢኔ ነው”
አቶ ልደቱ አያሌው (ፖለቲከኛ)

የካቢኔ ሹም ሽረቱን እንዴት ገመገሙት? ለውጥ የሚያመጣ ይመስልዎታል?
እኔ እንደጠበቅሁት አላገኘሁትም፡፡ ትንሽ ወጣ ብሎ ለህብረተሰቡ ጥሩ አስተዋፅኦ ሊያደርጉ የሚችሉ ግለሰቦችን ሊያካትት ይችላል የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ ግን ያ ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ አንደኛ የተቋቋመውን ካቢኔ “የምሁራን ካቢኔ” ልንለው እንችላለን፡፡ አሁንም በዋናነት የታየው አንደኛ የፓርቲ ታማኝነት ነው፤ ሁለተኛ የትምህርት ደረጃ ነው፡፡ እኔ ሁለቱም ብቻቸውን ውጤታማ የሆነ የህዝብ አስተዳደር ለማምጣት ያስችላሉ ብዬ አላምንም፡፡ የስራ ልምዳቸው ሲዘረዘር፣ ከአንድ ወይም ሁለት ሰው በስተቀር አብዛኞቹ በኢህአዴግ መዋቅር ውስጥ ባለፉት 15 ዓመታት የነበሩ ናቸው። አዲስ አመለካከት፤ አዲስ እይታ ያለው ሰው አልተቀላቀለም፡፡ ሁለተኛ፤ አንድ ሰው ሚኒስትር እንዲሆን የሚፈለገው ቴክኒካል የሆነ ምርምር እንዲሰራ አይደለም፡፡ ሚኒስትር ለመሆን በአንድ ነገር ላይ የረቀቀ እውቀት አይፈልግም። ሚኒስትርነት የበለጠ የፖለቲካ አመራር ብቃትን ይጠይቃል። ብዙ ጊዜ በኛ ሀገር ብቻ ሳይሆን በዓለም ሁኔታ የምናውቀው፣ የአካዳሚ ሰዎች የአመራርነት ሚናቸው በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ነው፡፡ በምሁርነት የቆዩ ሰዎች ወደ አመራርነት ሲመጡ፣ እውቀታቸውን በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ነው የሚሆኑት፡፡  
ምናልባት አሁን በሚሉት ጉዳይ ላይ አለማቀፍ ተሞክሮ ይኖር ይሆን?
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ በዚህ ደረጃ ከተዋቀረ በኋላ የተለያዩ የመረጃ አማራጮችን በመጠቀም አለማቀፍ ተሞክሮዎችን ለማየት ሞክሬያለሁ። የደረስኩበት መረጃ፣ አዲሱ ካቢኔ በዓለም ላይ በምሁራን የተዋቀረ የመጀመሪያው ካቢኔ መሆኑን ነው፡፡ ይህ የካቢኔ አደረጃጀት በዓለም ላይ የመጀመሪያዎቹ ሊያደርገን ይችላል፡፡ ሌሎች ሃገሮች ያልተደረገ ነው፡፡ ሚኒስትርነት ፖለቲካን የማስተዳደር፣ ውሳኔ የመስጠት ብቃትን የሚጠይቅ እንጂ ሙያን የሚጠይቅ አይደለም፡፡ ግለሰቡ በአንድ ጉዳይ ላይ ምርምርና ጥናት ማድረጉ አይደለም መታየት ያለበት፡፡
ዋናው የሚኒስትር መስሪያ ቤቱን የተለያዩ ዲፓርትመንቶች አስተባብሮ አቀናጅቶ መምራት መቻሉ ነው፡፡ ዶክተሮችና ምሁራንን መመደብ ብቻውን ለውጥ ያመጣል ብዬ አላምንም። አንድ ሁለት ሰዎችን ነው ወጣ ያለ የስራ ልምድ ያየሁባቸው፡፡ ሌሎቹ በአጠቃላይ በኢህአዴግ ውስጥ የኖሩ ናቸው፡፡ አዲስ አቀራረብና አሰራር ይዘው ለመጡ የሚችሉ አይመስለኝም፡፡ ከዚህ አንፃር ካቢኔው የሚፈለገውን ውጤት ያመጣል ብዬ አላምንም፡፡ ምናልባት አሁን ከተፈጠረው ቀውስ አንፃር ብሄረሰባዊ ተዋፅኦውን ጎላ አድርጎ በመሾም ሁኔታዎችን ለማርገብ የተፈለገ ይመስላል፡፡ ይሄ ግን አጉል ጨዋታ ነው የሚሆነው፡፡
ህብረተሰቡም እየጠየቀ ያለው ይሄን አይደለም። አቶ እገሌ ወርዶ፣ ዶ/ር እገሌ ይሾምልኝ አይደለም ያለው፡፡ የፖለቲካ ለውጥ ነው እየጠየቀ ያለው። ከዚህ አንፃር በቂ የሆነ ጥናትና ግምገማ ተካሂዶ፣ ለወቅቱ ችግር አስተዋፅኦ ሊያደርግ የሚችል ካቢኔ፣ በቅጡ ታስቦበት የተቋቋመ አልመሰለኝም። ቢቻል ከኢህአዴግ ወጣ ብሎ የሌላ ፖለቲካ ፓርቲ አባላትም ቢሆኑ፣ ህብረተሰቡን ለማገልገል ፍቃደኝነቱ እስካላቸው ድረስ ማካተት ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ ያ ባይሆን እንኳ ነፃና ገለልተኛ የሆኑ ሰዎችን ከንግዱ ማህበረሰብ፣ በሲቪል ተቋማት ከሚገኙ ምሁራን  ማካተት ይቻል ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነት ሰዎችን በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ አላየናቸውም። ከሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ጀምሮ በወረዳ መዋቅር ውስጥ የነበሩና የሚያውቋቸውን ሰዎች ነው ለሹመት  ያቀረቡት፡፡
አንዳንድ ፖለቲከኞች “የሚያስፈልገው የፖሊሲ ለውጥ ነው” ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
 አንዱ የስርአቱ ችግር የወቅቱን የህዝብ ተቃውሞና የብሶት እንቅስቃሴ ከአፈፃፀም ችግር ጋር አያይዞ ማየቱ ነው፡፡ ተቃውሞው በመልካም አስተዳደርና በኢኮኖሚ አፈፃፀም ጉድለት ሳቢያ ብቻ የመጣ አድርጎ ነው የሚመለከተው፡፡ የተቃውሞውን መሰረታዊ ምንጭ በደንብ ከመረመርነው ግን ችግሩ ፖለቲካዊም ነው፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ መፍትሄ ካልመጣ በስተቀር ይሄን ችግር መፍታት አይቻልም፡፡ ለጊዜው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ችግሩን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ ነገ ከነገ ወዲያ ግን በዘላቂነት ችግሩን መቆጣጠር ያዳግታል፡፡ ስለዚህ መለስ ብሎ የችግሩን ምንጭ በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። በዚህ ከተማመንን የችግሩን ምንጭ የማወቅ ጉዳይ ለኢህአዴግ ብቻ መተው የለበትም፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ህዝቡ መወያየት አለባቸው፡፡
ኢህአዴግ ብቻውን ለምንድን ነው የሚወስነው? የችግሩ ምንጭ ላይ መተማመን ካልተቻለ፣ በመፍትሄው ላይ መተማመን ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ኢህአዴግ የችግሩ ምንጭ ይህ ነው ብሎ በራሱ አይን አይቶ ከወሰነ በኋላ፣ ያንን ለማስፈፀም ነው ጥረት የሚያደርገው፡፡ ይሄ ግን ችግሩን አይፈታውም፡፡
የችግሩ ምንጭ ምንድን ነው? ብለን ከመረመርን፣ መሰረታዊ የሆኑ የፖለቲካ ችግሮች መኖራቸውን እንገነዘባለን፡፡ ያንን መፍታት የሚቻለው የአፈፃፀም አቅምን በማጎልበት ብቻ አይደለም፤ የፖሊሲ ለውጥ በማምጣት ነው፡፡ ከህገ መንግስቱ ጀምሮ የፌደራል አደረጃጀቱ የየራሳቸው ችግሮች አሉባቸው፤ እነሱ መሻሻል ይገባቸዋል፡፡ በሌላ በኩል በህገ መንግስቱም ሆነ በሌላ ህጎችም የተቀመጡ ጥሩ ጥሩ ህጎች መሬት ላይ መውረድ አለባቸው፡፡ ከወረቀት አልፈው ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል፡፡ የችግሮቹ መነሻ እነዚህ ነገሮች ናቸው፤ መፍትሄውም የሚገኘው ከእነዚህ ነው፡፡
ገዥው ፓርቲ ግን በጣም ቅንጭብጫቢ የሆኑ ከሙስና፣ ከመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ችግሮችን በመፍታት ብቻ ለውጥ አመጣለሁ እያለ ነው፡፡ ይሄ ግን ብቻውን መፍትሄ አይሆንም፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በተለያዩ የመዋቅር ማሻሻያዎች ለመፍታት ተሞክሮ የከሸፈ ነው፡፡ የችግሩ ምንጭ ያለው የፖለቲካ ሙስና ውስጥ ነው፤ የፖለቲካ ሙስና ሳይፈታ የኢኮኖሚ ሙስና ሊፈታ አይችልም፡፡ ኢህአዴግ የችግሩን መሰረታዊ ምንጭ አላወቀም ወይም ለማወቅ አልፈለገም፡፡
ተቃዋሚዎች በተደጋጋሚ፤ ”ኢህአዴግ ምሁራንን አያሳትፍም፤ ሙያን ለሙያተኛ አይለቅም” የሚል ትችት ሲሰነዝሩ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ይሄ ከእርስዎ አስተያየት ጋር እንዴት ይታረቃል?
ሚኒስትርነት የፖለቲካ ሹመት ነው፡፡ የሚፈለገው ውጤትም በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ያሉ የተለያዩ ዲፓርትመንቶችን አቀናጅቶ መምራት ነው። ከስራው ጋር ቀጥተኛ ሙያዊ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ምክትል ሆነው ሊሰሩ ወይም የዲፓርትመንት ኃላፊ ሆነው ሊመደቡ ይችላሉ፡፡ ትችቱ ከዚህ አንፃር ነው መታየት ያለበት፡፡ ለምሳሌ የማህፀን ሃኪም ናቸው ብሎ ማብራሪያ መስጠት ከሚኒስትርነት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ለመሆን በአንድ ውስን ሙያ ላይ ኤክስፐርት መሆን አይፈልግም፡፡ የሚኒስትርነት ቦታው ሙያዊ አይደለም፤ ፖለቲካዊ ነው፡፡ የሚፈለገው የአመራር ብቃት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር የግድ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር ወይም የህግ ምሁር መሆን አይጠበቅበትም፤ ዋናው የአመራር ክህሎቱ ነው፡፡ ሙያተኞች ምክትል ሆነው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡     


===============================

“ዋናው ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመመስረት ነው”
ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም (ዓለማቀፍ የህግ ባለሙያ)

    ጠቅላይ ሚ/ሩ ያዋቀሩትን አዲስ ካቢኔ እንዴት አዩት?
እኔ ብዙም ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም። ምክንያቱም የሰው ችሎታ ማነስ አይደለም የችግሩ ምንጭ፡፡ ዋናው ጥያቄ የፖሊሲ ጥያቄ ነው እንጂ በግለሰቦች ያለመርካት አይደለም። ዋናው መሰረቱ ፖሊሲ ነው፡፡ የፖሊሲ ለውጥ እስካልመጣ ድረስ በአዕምሮ ምጡቅ ነው የተባለ ሰው እንኳ ስልጣን ላይ ቢቀመጥ ለውጥ ላያመጣ ይችላል። ህዝቡ በተደጋጋሚ ሲጠይቃቸው ከነበሩት ጥያቄዎች መረዳት የሚቻለው፣ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስፈትሹ መሆናቸውን ነው።  ዋናው ሲጠየቅ የነበረው ዲሞክራሲን የማስፈን ጉዳይ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ስርአት ከተተገበረ ሌሎቹ ጥያቄዎች በዚያ አግባብ ምላሽ ያገኛሉ፡፡ የምርጫ ስርአቱ ስለሚሻሻል በህዝብ የተመረጠው ግለሰብ በሙስና ቢጨማለቅ፣ ህዝቡ በድምፁ መልሶ እንደሚያባርረው ያውቃል፡፡ ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ዲሞክራሲያዊ ስርአት የመመስረት ነው፡፡ የሚዲያዎች ነፃነት፣ የፍርድ ቤቶች ነፃነት፣ የሲቪክ ተቋማት ነፃነት ጥያቄ ነው፡፡ የግለሰቦች ለውጥ አይደለም ጥያቄው፡፡ የግለሰቦች መቀያየር ያን ያህል ለውጥ የሚያመጣ አይመስለኝም፡፡
የፖሊሲ ለውጥ ሲሉ ለምሳሌ--ይጥቀሱልኝ?
ነፃ ምርጫ፣ የፓርቲዎች ነፃነት፣ የጋዜጦችና የሚዲያ ነፃነት፣ የፍ/ቤቶች ነፃነት ---- በተለይ  ለህግና ለህሊናቸው እንዲገዙ ማድረግ የመሳሰሉ መሰረታዊ የፖሊሲ ማሻሻያዎች መደረግ አለባቸው። እነዚህ አሁን በሀገራችን እንደሌሉ ይታወቃል። እነዚህ መሰረታዊ ለውጦች እስካልተደረጉ ድረስ የሰዎች መለዋወጥ ትርጉም የለውም፡፡ ይህን ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ኢህአዴግ ዝግጁ አይመስለኝም፡፡
ምሁራን ወደ ሚኒስትርነት መምጣታቸው አስተዳደራዊ መዋቅሮችን በእውቀት ለመግራት አስተዋፅኦ አይኖራቸውም?
እርግጥ ነው ምሁራን የተሻሉ ናቸው፡፡ እውቀቱ ከሌላቸው ሰዎች እውቀቱ ያላቸው የተሻለ እንደሚሰሩ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ወሳኙ ግን የሚሰሩት ስራ ምንድን ነው የሚለው ነው?   አምባገነንነትን ለማጠናከርም ምሁራን ይሻላሉ፡፡ በዚያው ልክም ዲሞክራሲን ለማምጣት ምሁራን ይመረጣሉ፡፡
የፖለቲካ ምህዳሩ እስካልሰፋ ድረስ ግን የምሁራን መሾም ምንም ዋጋ የለውም፡፡ ምሁርነታቸውንና እውቀታቸውን በአግባቡ አውጥተውም ሊጠቀሙ አይችሉም፡፡

==============================

“ሹም ሽረቱን በበጎ አይን ነው የምመለከተው”

     ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (ፖለቲከኛ)

የህዝቡ ጥያቄ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ይፈቱልን የሚል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተሾሙት ምሁራን የበለጠ በእውቀት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት ሊሰጡ ስለሚችሉ ሹመታቸው መልካም ነው፡፡ በሌላ በኩል እነሱ ብቻ ሳይሆኑ ጠቅላላ ስርአቱ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ብቃቱና ዝግጁነቱ አለው ወይ? የሚለውን በደንብ ፈትሾ፣ የምሁራኑ እውቀት ተጨምሮበት ከተሰራ ጥሩ ነው፡፡ ያ ካልሆነ ግን ምሁራን በተለያዩ ዘርፎች መቀመጣቸው ብቻ የህዝብን ጥያቄ አይመልስም፡፡  
ከዚህ በፊት “የፖለቲካ ስልጣኑ እውቀትና ብቃት ባላቸው ሰዎች ሳይሆን በታማኝ ፖለቲከኞች ብቻ ነው የሚያዘው” የሚለውን ሲያነሱ የነበሩት ራሳቸው ምሁራኑና የፖለቲካ ድርጅቶች ነበሩ። ህዝቡ ይሄን ጥያቄ ያነሳ አይመስለኝም፡፡ ህዝቡ በዋናነት የሚፈልገው ያነሳቸው ጥያቄዎቹ መመለሳቸውን ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ኢህአዴግ ምሁራንን መሾሙ ምናልባት “ሰዎች በታማኝነት እንጂ በእውቀት አይመደቡም” ለሚለው መልስ ሊሰጥ ይችላል፡፡ እንደኔ ግን እነዚህ የተሾሙ ሰዎች፤ ዶክተሮች ፕሮፌሰሮችና ምሁራን ቢሆኑም ባይሆኑም ቴክኒካሊ የሚሰጣቸውን ስራ እውቀት ላይ ተመስርተው ይሰራሉ የሚል እምነት አለኝ። ግን እነዚህ ምሁራን የህዝቡን ፖለቲካዊ ችግሮች ይመልሳሉ ወይ ነው ጥያቄው፡፡
ይህን ለመመለስ መንግስትን የሚመራው ድርጅት የሚከተለው ርዕዮተ አለምና ከዚያም በመነሳት የሚያወጣው ፖሊሲ የህዝብን ጥያቄዎች ምን ያህል ይመልሳል የሚለውም መታየት አለበት፡፡ ትልቁ መሰረታዊ ጉዳይ ያለው ፖሊሲው ላይ ነው፡፡
የፓርቲ አባል ያልሆኑ ሰዎችንም የመሾም ሁኔታ እያየሁ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ የበላይነትና ልማታዊ ዲሞክራሲ የሚባለው ርዕዮተ ዓለም፣ የሀገሪቱን ህዝቦች ጥያቄ እየመለሰ ነው ወይ የሚለው ነው ዋናው ጥያቄ። ነባሮቹ እየለቀቁ አዳዲስ ሰዎች ማምጣቱ ጥሩ ነገር ነው፡፡ በአንድ በኩል ይህ ሲደረግ መንግስትና ፓርቲን የመለየት ነገር እየመጣ ነው ማለት ነው፡፡ ግን ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነው። መንግስትና ፓርቲ የተለያዩ መሆናቸውን የበለጠ ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ይሄ ማለት ካድሬ መሆን ብቻውን ለሚኒስትርነት እንደማያበቃ ማሳየት ማለት ነው፡፡ እኔ መልካም አካሄድ ነው ብዬ በበጎ አይን ነው የምመለከተው። በሌላ በኩል የብሄር ተዋፅኦን ከፍ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡ ይህ ለህዝቡ ጥያቄ ምን ያህል ምላሽ ሊሰጥ ይችላል የሚለውም በጥልቀት መታየትና መገምገም ይኖርበታል፡፡  


    አስገራሚ ክስተቶች፣ ያልተጠበቁ ሁነቶች፣ አስቂኝ ምልልሶች፣ አስደንጋጭ መረጃዎች፣ ኃይለኛ ፉክክሮች፣ ብዙ ብዙ ትኩረት የሚስቡ ያልተለመዱ ነገሮች የተስተናገዱበት የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ  የፍጻሜው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ የፊታችን ማክሰኞ ይለይለታል፡፡
ማን ይጠበቃል?
በዘንድሮው 45ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ ላይ የከረሙት ሁለቱ እጩዎች፣ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻቸው አንዳቸው ሌላኛቸውን እያብጠለጠሉና እያንኳሰሱ ጎልተው ለመውጣትና የመራጩን ቀልብ ለመግዛት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፡፡  በቅድመ ምርጫ ትንበያ ተጠምደው የሰነበቱት ታላላቅ አለማቀፍ መገናኛ ብዙሃንና ተቋማት በምርጫው ማን ያሸንፋል የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የየራሳቸውን ጥናት በመስራት ውጤት ይፋ ሲያደርጉ ሰንበተዋል፡፡ አንዳንዶች የዲሞክራቷን ዕጩ ሄላሪ ክሊንተንን ለአሸናፊነት ሲያጩ፣ ሌሎች አነጋጋሪውን የሪፐብሊን ዕጩ ዶናልድ ትራምፕን ለድል አጭተዋቸዋል፡፡
ዲሞክራቷ ሄላሪ፣ በአንዳንድ የቅድመ ምርጫ ትንበያዎች ለሳምንታት በሰፊ ልዩነት ሲመሩ ቢቆዩም፣ ልዩነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጠበበ መምጣቱና በተለይም ኤፍቢአይ በሄላሪ ላይ የኢሜይል ቅሌት ምርመራ መጀመሩን ማስታወቁን ተከትሎ በአንዳንድ ትንበያዎች ትራምፕ መምራት መጀመራቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡
ኒውዮርክ ታይምስ ከትናንት በስቲያ ባወጣው አገር አቀፍ የቅድመ ምርጫ ትንበያ፣ሄላሪ ቢሊዬነሩን ትራምፕ በሶስት ነጥብ በመምራት ላይ እንደሚገኙ ያስታወቀ ሲሆን፣ ኤቢሲ ኒውስና ዋሽንግተን ፖስት በበኩላቸው፤ ልዩነቱን ወደ ሁለት ዝቅ ያደርጉታል - ለሄላሪ 47፣ ለትራምፕ 45 ነጥብ በመስጠት፡፡
ኦባማም በቅስቀሳ ተጠምደዋል
ሄላሪና ትራምፕ የፖሊሲ አማራጮቻቸውን በማስተዋወቅ፣የተሻለ ያደርገኛል የሚሉትን ነጥብ በማስተጋባት፣ አንዳቸው የአንደኛቸውን ጉድ በመዘክዘክና በማሳጣት የህዝቡን ቀልብ ለመግዛትና የበለጠ ድምጽ አግኝተው ለፕሬዚዳንትነት ለመብቃት በየፊናቸው በምርጫ ቅስቀሳ ቢጠመዱም፣ ኦባማ የትራምፕን ምላስ ለመቋቋም ተስኗቸው አስሬ “ሴት ትንቃለህ” የሚል ነገር የሚደጋግሙትን ሄላሪን ለመደገፍ ባለቀ ሰዓት አደባባይ ወጥተዋል፡፡
የፓርቲ አጋራቸውን ሄላሪን በምርጫ ቅስቀሳ ለመደገፍ ከእነ ሚስታቸው ታጥቀው የተነሱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ አዮዋን ጨምሮ በተለያዩ ስቴቶች በመዘዋወር “ትራምፕ አይበጃችሁም፤ ሄላሪን ምረጡ” በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲቀሰቅሱ ሰንብተዋል፡፡ ኦባማ ባለፈው ረቡዕ በኖርዝ ካሮሊና ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ፣ የዘንድሮውን የአሜሪካ ምርጫ፣ የአሜሪካ ብቻ ሳይሆን የመላው አለም ጉዳይ ጭምር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“ዲሞክራቶች ሆይ!... ይሄ ምርጫ ለአገራችን ብቻ ሳይሆን ለአለም ጭምር ወሳኝ ነው፡፡ ዶናልድ በሚሉት ሰው ሳቢያ፣ የዓለማችን ዕጣ ፈንታሽ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ ይህ ሰው ወደ ስልጣን እንዲመጣ አትፍቀዱለት፡፡ በነቂስ ውጡና ለሄላሪ ድምጻችሁን ስጡ!...” ብለዋል ኦባማ፡፡
መልስ የማያጡት አሽሙረኛው ትራምፕ፤ፍሎሪዳ ውስጥ ሆነው ይሄን ሰሙ፡፡ ሰምተውም እንዲህ አሉ፣ ይላል ቢቢሲ...
“ይሄ ኦባማ የሚሉት ሰው፣ ለሄላሪ  ማሽቃበጡን ትቶ፣ አገሪቱን በመምራቱ ላይ ማተኮር አለበት!...”
ቀድመው የመረጡ
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ አሰራር መራጮች ከመደበኛው የድምጽ መስጫ ዕለት በፊት ለሚደግፉት ዕጩ ድምጻቸውን መስጠት ይችላሉ፡፡ በዚህም መሰረት ከ22 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን፣ ማክሰኞን መጠበቅ ሳያስፈልጋቸው ለመረጡት ዕጩ ድምጻቸውን መስጠታቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ኮሚ ምን ነካቸው?
የምርጫ ቅስቀሳው በተጧጧፈበት፣ አንደኛው የሌላኛውን ዕጩ ድብቅ ገበና በሚያነፈነፉበት፣ የቆየ ወንጀላቸውን ነቅሰው በማውጣት አደባባይ ለማስጣትና ተፎካካሪያቸውን ትዝብት ላይ ለመጣል ደፋ ቀና በሚሉበት፣ ትራምፕ እና ሄላሪ አይጥና ድመት በሆኑበት ወሳኝ ወቅት ላይ፣ያልተጠበቀ ዱብ ዕዳ ተሰማ፡፡
አሜሪካውያን ለሚደግፉት ዕጩ ድምጻቸውን የሚሰጡባት ወሳኝ ዕለት የምትደርስበትን ቀን ሲቆጥሩ ከርመው፣ 11 ቀናት ብቻ ሲቀራቸው፣ ዲሞክራቷን ሄላሪን ክው ያደረገ፣ ሪፐብሊካኑን ትራምፕ በደስታ ያስፈነጠዘ ሰበር ዜና ተሰማ፡፡ የሄላሪን የኢሜይል ቅሌት ክስ መርምሬ፣ አንዳች እንኳን የሚያስከስሳት ወንጀል ባለማግኘቴ ክሱን ወደ መዝገብ ቤት ልኬያለሁ ብሎ የነበረው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሚ፣ ድንገት በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ አሉና፣ ሌላ የኢሜይል ቅሌት አግኝተንባታልና ልንመረምራት ነው አሉ፡፡
ሄላሪ ደነገጡ፤ ትራምፕ በደስታ ፈነጠዙ፡፡
“ምን!?...” አሉ ሄላሪ፣ የሰሙትን ባለማመን፡፡
“አላልኳችሁም!?... ይህቺ ወንጀለኛ፣ ገና ወህኒ ትወርዳለች!...” አሉ ትራምፕ፣ ሲሉት የከረሙትን ነገር የሚያረጋግጥ ጮማ ማስረጃ እጃቸው ላይ ሲወድቅ፡፡
“ጄምስ ኮሚ ምን ነካቸው?...” አሉ ብዙዎች በሰሙት ነገር ተገርመው፡፡
ኤፍቢአይ በምርጫ ውጤቱ ላይ ተጽዕኖ የሚፈጥር መሆኑን እያወቀ፣ በወሳኝ ወቅት ይህን አደገኛ ውሳኔ ማሳለፉ ብዙዎች በጥርጣሬ ሲያዩት፣ አንዳንድ የህግ ተንታኞችም የተቋሙን ውሳኔ ህግን ያልተከተለ ብለውታል፡፡ ዳይሬክተሩ ይቅር የማይባል ጥፋት ሰርተዋልና፣ ዛሬ ነገ ሳይሉ ስልጣናቸውን ይልቀቁ ያሉም አልታጡም፡፡ የኤፍቢአይ ውሳኔ የምርጫ ሂደቱን የሚያስተጓጉልና የዲሞክራቷን ዕጩ አሸናፊነት ጥያቄ ውስጥ የሚጥል አደገኛ ነገር ነው ያሉ ተንታኞች የመኖራቸውን ያህል፣ ተጽዕኖው እምብዛም ነው ብለው ያጣጣሉትም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን፣ የጄምስ ኮሚን መርዶ ተከትሎ፣ የሄላሪና የትራምፕ የቅድመ ምርጫ የአሸናፊነት ትንበያ ልዩነት እየጠበበ ሲመጣ፣ አንዳንዴም ትራምፕ ሲመሩ ታይቷል፡፡
ጠመንጃ ተወዷል!...
የአሜሪካ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ፣በአገሪቱ የጦር መሳሪያ ገበያው መድራቱ ተነግሯል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ በአገሪቱ ባለፉት ሶስት ወራት የጦር መሳሪያዎች ሽያጭ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ሽያጩ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ጊዜ ከነበረው ጋር ሲነጻጸር ከ30 በመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቷል ያለው ዘገባው፣ ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ የ161. 4 ሚሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ መሸጡን ገልጧል፡፡
የዚህ ሰበብ ደግሞ፣ ዲሞክራቷ ሄላሪ ናት ይላል ዘገባው፡፡
በአገረ አሜሪካ ምርጫው መቃረቡን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ግብይቱ የተጧጧፈው፣ አገሬው ዲሞክራቷ ሄላሪ ታሸንፍ ይሆናል ብሎ በመስጋቱ ነው ተብሏል። እሷ ካሸነፈች ደግሞ የጦር መሳሪያ ቁጥጥሩን የበለጠ ታጠብቀዋለች፣ ስለዚህ አበክሮ መሸመት  ያወጣል በሚል ነው ምድረ አሜሪካዊ ጠመንጃ ገበያ የወረደው ብሏል - ዘገባው፡፡
እሷም እንደ ኮንጎ?...
ከሳምንታት በፊት...
የዲሞክራሲ ባህል ያበበባት፣ ህገ መንግስታዊ ስርዓት የሰፈነባት፣ በስርዓት የሚገዛ ፖለቲካ ስር የሰደደባት ልዕለ ሃያል አሜሪካ፣ ለሺህ ዘመናት ወደ ኋላ ተንሸራትታ እነ ኮንጎ የተዘፈቁበት አዘቅት ውስጥ ልትነከር ማቆብቆብ ጀመረች እንዴ? የሚያሰኝ አጉል ነገር ሆነ፡፡ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ስልጣን የሚያዝባት፣ የምርጫ  ስርዓቷ ነጻና ፍትሃዊነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባባትን አሜሪካን ለመምራት ታጥቀው የተነሱት፣ የእነ አብርሃም ሊንከንን ወንበር ለመቆናጠጥ የቋመጡት አነጋጋሪው ትራምፕ፣ በመጨረሻው ዙር የምርጫ ክርክራቸው ሌላ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን፣ የአሜሪካን ዲሞክራሲ ቁልቁል የሚጎትት ነገር ተናገሩ፡፡
“እሷ ካሸነፈች፣ ውጤቱን በጸጋ ለመቀበል ያዳግተኛል!...” አሉ ትራምፕ፡፡
ትራምፕ እንዲህ ማለታቸውን ተከትሎ፣ አሜሪካም እንደእነ ኮንጎ በምርጫ ሳቢያ ብጥብጥ ውስጥ ትገባ ይሆናል የሚል ስጋት መፈጠሩን የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘግቧል፡፡
ዩኤስኤ ቱዴይ እና ሱፎልክ ዩኒቨርሲቲ በቅርቡ በጋራ በሰሩት ጥናት፣ ድምጻቸውን ይሰጣሉ ተብለው ከሚጠበቁት አሜሪካውያን 51 በመቶው፣ ከምርጫው ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ብጥብጥ ይነሳል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ ጆ ዋልሽ የተባሉት የቀድሞ የአሜሪካ ኮንግረስ አባል ስጋት ግን ከዚህም ያልፋል ይላል - ዘገባው፡፡
“ማክሰኞ ድምጼን ለትራምፕ እሰጣለሁ፡፡ ረቡዕ ማለዳ ትራምፕ ተሸንፏል የሚል ነገር ከሰማሁ ግን፣ጠመንጃዬን መወልወሌ አይቀርም!... እናንተስ?...” ብለዋል ዋልሽ ሰሞኑን በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ስጋት አቀጣጣይ ወጋቸው፡፡
የአሜሪካ ዕድሜ ጠገብ የዲሞክራሲ ሥርዓትና ባህል፣እንደ ዘንድሮም ተፈትኖ አያውቅም፡፡ ከዓይን ያውጣው!!

*በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የክላስተር ሹመት ቀርቷል
*9 ሚኒስትሮች ባሉበት ይቀጥላሉ
የህዝብ ጥያቄን ለመመለስ በኢህአዴግ የሚመራው መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ አደርጋለሁ ባለው መሰረት
ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በዛሬው ዕለት የአዳዲስ ሚኒስትሮችን ሹመት ለህዝብ ተወካዮች
ም/ቤት ይፋ አድርገዋልCC ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ 9 ሚኒስትሮች ባሉበት ሃላፊነት የቀጠሉ ሲሆን
የጠ/ሚኒስትር አማካሪነት ማዕረግ መቅረቱ ታውቋልCC ጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተሾሙ ማግስት
የተጀመረው በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የክላስተር አስተባባሪነት ሹመትም አስፈላጊ አይደለም ተብሎ
ስለታመነበት ቀርቷል ተብሏልCC አዳዲሶቹ ሚኒስትሮች የተሾሙት የትምህርት ዝግጅታቸውንና የመምራት
ብቃታቸውን መሰረት አድርጎ በመሆኑ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በተሻለ መልኩ ይወጣሉ ብለው እንደሚያምኑ
ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋልCC በግንቦት 2007 ምርጫ ሁሉም መቀመጫዎቹ በኢህአዴግ አባላት የተሞላው
የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፣በጠ/ሚኒስትሩ የቀረቡትን አዳዲስ ተሹዋሚዎች በሙሉ ድምጽ አጽድቆታልCC
የአዳዲሶቹ ሚኒስትሮች ስም ዝርዝርC-
1. የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር - ዶ/ ር ወርቅነህ ገበየሁ
2. የፐብሊክ ሠርቪስና የሰው ሃብት ሚኒስትር - አቶ ታገሠ ጫፎ
3. የንግድ ሚኒስትር - ዶ/ ር በቀለ ሙላቱ
4. የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትር - ዶ/ ር አብርሃም ተከስተ
5. የእንስሳትና አሳ ሃብት ሚኒስትር - ፕ/ ር ፍቃዱ በየነ
6. የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስትር - ዶ/ ር እያሱ አብርሃም
7. የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር - ዶ/ ር ኢ/ ር ጊታሁን መኩሪያ
8. የትራንስፖርት ሚኒስትር - አቶ አህመድ ሺዴ
9. የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር - ዶ/ ር አምባቸው መኮንን
10- የኮንስትራክሽን ሚኒስትር - ኢ/ ር አይሻ መሃመድ
11- የውሃ መስኖ ኤሌክትሪክ ሚኒስትር - ዶ/ ር ኢ/ ር ስለሺ በቀለ
12- የማዕድን ነዳጅና ተፈጥሮ ሚኒስትር - አቶ ሞቱማ መቃሣ
13- የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ሚኒስትር - ዶ/ ር ገመዶ ዳሌ
14- የትምህርት ሚኒስትር - ዶ/ ር ሽፈራው ተ/ ማርያም
15- የጤና ጥበቃ ሚኒስትር - ፕ/ ር ይፍሩ ብርሃኔ
16- የመንግስት ልማት ድርጅት ሚኒስትር - ዶ/ ር ግርማ አመንቴ
17- የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር - ዶ/ ር ሂሩት ወ/ ማርያም
18- የሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች ሚኒስትር - ወ/ ሮ ደሚቱ ሃምቢሣ
19- የወጣቶች ስፖርት ሚኒስትር - አቶ ርስቱ ይርዳው
20- ለገቢዎችና ጉምሩክ መስሪያ ቤት ኃላፊ ሚኒስትር - አቶ ከበደ ጫኔ
21- ለመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት ኃላፊ ሚኒስትር - ዶ/ ር ነገሪ ሌንጮ
በነበሩበት የቀጠሉ ሚኒስትሮች
•    1- ም/ ጠቅላይ ሚኒስትር - አቶ ደመቀ መኮንን
2- የመከላከያ ሚኒስትር - ሲራጅ ፈርጌሣ
3- የፌደራልና አርብቶ አደር ጉዳዮች ሚኒስትር - አቶ ካሣ ተ/ብርሃን
4- የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ - አቶ ጌታቸው አምባዬ
5- የመገናኛ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር - ዶ/ ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል
6- የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር - አቶ አህመድ አብተው
7- የሰራተኛ ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር - አቶ አብዱልፈታህ አብዱላሂ
8- የብሔራዊ ኘላን ኮሚሽን ኃላፊ ሚኒስትር - ዶ/ ር ይናገር ደሴ
9- የመንግስት ተጠሪ ዋና ሚኒስትር - አቶ አስመላሽ ወ/ ስላሴ

 የታዋቂው ሰዓሊ ሰይፉ አበበ ከ50 በላይ ስዕሎች ለእይታ የሚቀርብበት “Think Out Side  the Box” የተሰኘ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ ዛሬ ከቀኑ 10፡00 ላፍቶ ሞል በሚገኘው ላፍቶ አርት ጋለሪ ይከፈታል፡፡
ለቀጣዩ አንድ ወር ለተመልካች ክፍት ሆኖ በሚቆየው በዚህ አውደ ርዕይ ለእይታ የሚቀርቡት ስዕሎች፡- የመልክአ ምድርን፣ መልክአ ሰማይንና አጠቃላይ የተፈጥሮን ውበትና ቀለም የሚያሳዩ በ3D እና 2D የተዘጋጁ ስራዎች እንደሆኑ ሰዓሊው ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም ከሌሎች ሰዓሊዎች ጋር በውጭና በአገር ውስጥ ለበርካታ ጊዜያት ሥራዎቹን በቡድን ለዕይታ ያቀረበው ሰዓሊው፤ ለብቻው ደግሞ በጣይቱ ሆቴል፣. በብሔራዊ ሙዚየም፣ በብሔራዊ ቴአትር አርት ጋለሪና በዓለም ጋለሪ ሥዕሎቹን ለተመልካች አቅርቧል፡፡ ሰዓሊ ሰይፉ በ1987 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አለ ፈለገ ሰላም የስነ ጥበብና ዲዛይን ት/ቤት የተመረቀ ሲሆን በአሁን ሰዓት ከስዕል ስራው በተጨማሪ በካክተስ የሚዘጋጀው የ“what’s out” መፅሄት ግራፊክስ ዲዛይነርና የኢትዮጵያ ሰዓሊያንና ቀራፂያን ማህበር ዋና ፀሐፊ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡

 አዶት ሲኒማና ቲያትር፤ አዳዲስ የሆሊውድ ፊልሞችን ከዛሬ ጀምሮ ለተመልካች እንደሚያሳይ ተገለጸ፡፡ ከሁለት ዓመታት በፊት በ30 ሚሊዮን ብር ወጪ ተገንብቶ ቲያትሮችንና የአማርኛ ፊልሞችን ለተመልካቾች ሲያቀርብ የቆየው ሲኒማ ቤቱ፤ አዳዲስ የሆሊውድ ፊልሞችን በማምጣት ማሳየት እንደሚጀምር የአዶት ሲኒማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘለዓለም ብርሃኑ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ በሆሊውድ የተሰሩና የተመረጡ አዳዲስ ፊልሞችን ከሆሊውድ እኩል ለማሳየት ዝግጅቱን አጠናቋል ብለዋል - ሥራ አስኪያጁ፡፡  

   - የምርጫ ውጤትን እቅጩን የሚገምቱት ፕሮፌሰር፣ ትራምፕ ያሸንፋል ብለዋል
                   - ሪፐብሊካኑ ኮሊን ፖል ድምጻቸውን የሚሰጡት ለዲሞክራቷ ሄላሪ እንደሆነ አስታውቀዋል

        የሳምንታት ጊዜ በቀረው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሪፐብሊካኑን ወክለው የሚወዳደሩት አነጋጋሪው ዕጩ ዶናልድ ትራምፕ፣ 3ኛው የዓለም ጦርነት የሚጀመረው ተፎካካሪያቸው ሄላሪ ክሊንተን ይዛው በተነሳቺው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳቢያ ነው ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሄላሪ ክሊንተን በሶርያ ጉዳይ ላይ የያዘቺው እቅድ በአሜሪካና በሩስያ መካከል የከፋ ግጭት የሚያስከትልና ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት መነሻ ሊሆን አንደሚችል ትራምፕ ባለፈው ማክሰኞ ባደረጉት ቃለ ምልልስ ማስጠንቀቃቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
የሄላሪን ዕቅድ በመደገፍ በምርጫው ድምጻችንን የምንሰጣት ከሆነ፣ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩ አይቀሬ ነው ያሉት ትራምፕ፤ ሄላሪ ስታብጠለጥለው ከከረመቺው ከሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመደራደር ያላት ብቃት እንደሚያጠራጥራቸው በመግለጽ፣ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ታበላሸዋለች ብለዋል፡፡
ያልተለመዱ ክስተቶች የተስተናገዱበት የዘንድሮው የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳ እየተጧጧፈ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት፣ ሪፐብሊካኑ የቀድሞው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኮሊን ፖል ዲሞክራቷን ሄላሪን እንደሚመርጡ ማስታወቃቸውን የዘገበው ደግሞ ስካይ ኒውስ ነው፡፡ ሊዲሞክራቷ ዕጩ ድምጻቸውን እንደሚሰጡ በይፋ የሚናገሩ ስመጥር ሪፐብሊካኖች እየተበራከቱ መምጣታቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ኮሊን ፖልም ሄላሪ እንደ አገር መሪ ያላትን የካበተ ልምድና ክህሎት በማድነቅ ድምጻቸውን ለእሷ እንደሚሰጡ ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቃቸውን ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና ምንም እንኳን በርካታ ቅድመ ትንበያዎች በቀጣዩ ምርጫ ዲሞክራቷ ሄላሪ በለስ እንደሚቀናት እያመላከቱ ቢሆንም፣ የአሜሪካን ምርጫ ውጤት በመተንበይ የሚታወቁት የፖለቲካ ተንታኙ ፕሮፌሰር ሄልሙት ኖርፖዝ ግን፣ በስተመጨረሻ ድል የትራምፕ ትሆናለች ሲሉ መተንበያቸውን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
ላለፉት 100 ያህል አመታት በአሜሪካ ከተከናወኑ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች ከአንዱ በቀር የሁሉንም ውጤት በትክክል የገመቱት የኒውዮርኩ ሰኒ ስቶኒ ብሩክ ዩኒቨርሲቲ መምህር ፕሮፌሰር ሄልሙት ኖርፖዝ፣ በቀጣዩ ምርጫ ትራምፕ እንደሚያሸንፉ በይፋ ተንብየዋል፡፡
ፕሮፌሰር ኖርፖዝ የፈጠሩትና ያለፈውንና የወደፊቱን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት የሚያመላክተው የትንበያ ቀመር፣ እ.ኤ.አ ከ1912 አንስቶ በተደረጉት የአገሪቱ ምርጫዎች ላይ ያቀረበው ትንበያ ከአንዱ በስተቀር በሁሉም ስኬታማ እንደነበር የጠቆመው ዘገባው፣ ቀመራቸውን ተጠቅመው የሰጡት ትንበያ ያልያዘላቸው እ.ኤ.አ በ2000 በተካሄደው ምርጫ ብቻ እንደነበርም አስታውሷል፡፡

                - ባለፉት 10 ወራት ብቻ 3 ሺህ 740 ስደተኞች ባህር ሲያቋርጡ ሞተዋል

      ሊጠናቀቅ የሁለት ወራት ጊዜ የቀሩት የፈረንጆች አመት 2016፣ የሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለህልፈተ ህይወት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በታሪክ ከፍተኛው ደረጃ ላይ የደረሰበት መሆኑን አለማቀፉ የስደተኞች ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን ባለፈው ማክሰኞ ጄኔቫ ውስጥ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለፉት አስር ወራት ብቻ 3 ሺህ 740 የተለያዩ አገራት ስደተኞች ሜዲትራንያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸውንና ይህም ቁጥር በታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ባለፉት አስር ወራት ብቻ 327 ሺህ 800 ያህል የተለያዩ አገራት ስደተኞች በአስቸጋሪ የባህር ጉዞ አልፈው ወደ አውሮፓ መግባታቸውን የጠቆሙት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ ዊሊያም ስፒንድለር፤ሜዲትራኒያን ባህርን አቋርጠው ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚሞክሩ ስደተኞች ለሞት የመዳረግ እድላቸው በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንም ገልጸዋል፡፡
ስደተኞች ባህር የሚያቋርጡባቸው ጀልባዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ መሆናቸውና ከመጫን አቅማቸው በላይ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች አሳፍረው መጓዛቸው እንዲሁም አስቸጋሪ የአየር ጸባይ የስደተኞቹን ለሞት የመዳረግ እድል ከፍ እንዳደረገው ተነግሯል፡፡ ቀሪዎቹ ወራት ለባህር ላይ ጉዞ ፈታኝ ወቅቶች ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በአመቱ ለሞት የተዳረጉ ስደተኞች ቁጥር በቀጣይም በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽኑ አክሎ ገልጧል፡፡

 - የፕሬዚዳንቱ ልጅ የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር ናት

       የአንጎላው ፕሬዚዳንት ጆሴ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስ ህግን ጥሰው ሴት ልጃቸውን ኤሳቤል ዶስ ሳንቶስን የአገሪቱ የነዳጅ ኩባንያ ዋና ስራ አስፈጻሚ አድርገው መሾማቸው አግባብነት የሌለው አድሏዊ ተግባር ነው በሚል ክስ እንደተመሰረተባቸው ሮይተርስ ዘገበ፡፡
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ሴት ቢሊየነር የሆነቺው ኤሳቤል፣ በአንጎላ መንግስት ስር የሚተዳደረውን ሶናንጎል የተባለ ግዙፍ የነዳጅ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት እንድትመራ ባለፈው ሰኔ በአባቷ መሾሟን ያስታወሰው ዘገባው፣ 14 የአገሪቱ ጠበቆች ሹመቱ የአገሪቱን ህግ የጣሰ ነው በማለት በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ መመስረታቸውን ገልጧል፡፡
ክሱን በመከታተል ላይ የሚገኘው የአንጎላ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም፣ ኤሳቤል በምን መንገድ የኩባንያው ሃላፊ ተደርጋ ልትሾም እንደቻለች ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጡ ባለፈው ረቡዕ ለፕሬዚዳንት ዶስ ሳንቶስና ለልጃቸው ጥሪ በማስተላለፍ የስምንት ቀን ጊዜ መስጠቱን ዘገባው አብራርቷል፡፡
በአገሪቱ ህግ መሰረት አንድ የመንግስት ባለስልጣን የቤተሰብ አባሉን በሃላፊነት ቦታ ላይ እንዲቀመጥ በዕጩነት ማቅረብ ወይም እንዲቀርብ መፍቀድ አይችልም ያለው ዘገባው፤ አንዳንድ የአገሪቱ የፖለቲካ ተንታኞችም ፕሬዚዳንቱ ልጃቸውን የግዙፉ የነዳጅ ኩባንያ መሪ አድርገው መሾማቸው በአገሪቱ ቤተሰባዊ አስተዳደርን በዘላቂነት ለመመስረት የያዙት የስልጣን አፍቃሪነት ማሳያ ነው ሲሉ መናገራቸውንም ገልጧል፡፡
ኤሳቤል ዶስ ሳንቶስ የአገሪቱን የነዳጅ ምርትና ኤክስፖርት በበላይነት የሚመራውን ሶናንጎልን እንድትመራ በአባቷ መሾሟን ተከትሎ ለጋዜጠኞች ባደረገቺው ንግግር፣ ኩባንያውን ከገባበት ችግር ለማውጣትና በአለማቀፍ ደረጃ ስኬታማ ለማድረግ የአደረጃጀትና ሌሎች ለውጦችን ለማድረግ ማቀዷን አስታውቃ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡
የአፍሪካ ቁጥር አንድ ነዳጅ አምራች በሆነቺው ናይጀሪያ ከሽብርተኝነትና ከኢኮኖሚ ቀውስ ጋር በተያያዘ የተከሰተው ችግር የአገሪቱን የነዳጅ ምርት መጠን ማሳነሱን ተከትሎ፣ የአለማቀፉ የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ድርጅት አባል የሆነቺው አንጎላ በአህጉሩ ቀዳሚዋ የነዳጅ አምራች አገር ለመሆን መብቃቷንን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

 - አምና ለ300 ክፍት የስራ ቦታዎች፣ 2 ሚ. ህንዳውያን ቀርበው ነበር

       በቻይና በቅርቡ አመልካቾችን አወዳድሮ አንድ የእንግዳ ተቀባይ ለመቅጠር ይፋ በተደረገ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ 10 ሺህ ያህል ቻይናውያን ስራ ፈላጊዎች ማመልከታቸውን ቢቢሲ ባለፈው ረቡዕ ዘግቧል፡፡
እምብዛም እውቅና የሌለውና የቻይና ዲሞክራቲክ ሊግ የተሰኘው የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ ያወጣው ይህ የእንግዳ ተቀባይነት ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ፣ በአገሪቱ የስራ ቅጥር ታሪክ ከፍተኛ ቁጥር ያለው አመልካች የቀረበበት ነው ያለው ዘገባው፤ በዚህ አመት ብቻ 1.4 ሚሊዮን ቻይናውያን የስራ አመልካቾች ለተለያዩ የስራ መደቦች የሲቪል ሰርቪስ ፈተና መውሰዳቸውን ጠቁሟል፡፡ በቻይና በዘንድሮው የፈረንጆች አመት ለወጡ የተለያዩ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያዎች በርካታ ቁጥር ያላቸው አመልካቾች መቅረባቸውንና፣ ለአንዱ የስራ ቦታ በአማካይ 49 አመልካቾች በተወዳዳሪነት ቀርበው ማመልከታቸውንም ዘገባው አስታውቋል፡፡
የወቅቱ የአገሪቱ የስራ አጥነት ምጣኔ 4 በመቶ ነው ያለው ዘገባው፤ ተመሳሳይ የስራ አጥነት መጠን ባለባት ህንድ ባለፈው አመት ለወጡ 300 ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያዎች 2 ሚሊዮን አመልካቾች ቀርበው እንደነበርም አስታውሷል፡፡

 ባትሪው እየጋለ እሳት በሚፈጥረው አዲሱ ምርቱ ጋላክሲ ኖት 7 ሳቢያ ከገባበት ቀውስ ለመውጣት ደፋ ቀና የሚለው ሳምሰንግ ኩባንያ፤ በመጪው አመት ለገበያ ያቀርበዋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውን አዲሱን ጋላክሲ ኤስ8 ስማርት ፎኑን መስራት የሚጀምርበትን ጊዜ በሁለት ሳምንታት ማራዘሙ ተዘግቧል፡፡
ሳምሰንግ ኤስ8ን ማምረት የሚጀምርበትን ጊዜ ያራዘመው፣ የኩባንያው የቴሌኮም ኢንጂነሮች በጋላክሲ ኖት 7 ላይ የተፈጠረውን ችግር ትክክለኛ መንስኤ በማጣራት ስራ በመጠመዳቸው ነው መባሉን የዘገበው ኤክስፕረስ ጋዜጣ፤ ሳምሰንግ አዲሱን ምርቱን ተጣድፎ ወደገበያ በማስገባት የጋላክሲ ኖት 7 የቀመሰውን መከራ ዳግም እንዳያስተናግድ ሰግቷል ብሏል፡፡
የደቡብ ኮርያው ሳምሰንግ በዚሁ ጦሰኛ ምርቱ በጋላክሲ ኖት 7 ሳቢያ የገባበት ቀውስ ህልውናውን አደጋ ላይ እንደጣለው የዘገበው አፍሪዶትኮም በበኩሉ፣ ከሰሞኑ ደግሞ ኖት 7 ገዝተው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ የአገሩ ደንበኞች “አጉላልቶናል ካሳ ሊሰጠን ይገባል” ሲሉ ክስ እንደመሰረቱበት ገልጧል፡፡
527 ደቡብ ኮርያውያን የሳምሰንግ ደምበኞች ለእያንዳንዳችን 440 ዶላር ካሳ ሊሰጠን ይገባል በሚል በኩባንያው ላይ ሰኞ ዕለት ክስ መመስረታቸውን ተከትሎ፣እኛም እንከሳለን የሚሉ አመልካቾች ቁጥር እየተበራከተ መምጣቱንና የከሳሾቹ ቁጥር በሺህዎች ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ዘገባው ገልጧል፡፡