Administrator

Administrator

“የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት የመደመር እሳቤ ውጤት ነው”

ሁለቱ በመንግሥት የሚተዳደሩት ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ ሰሞኑን  በይፋ  ተዋህደው  ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ ተመሥርቷል፡፡ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም  በግራንድ ኤሊያና ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ለተመሳሳይ ዓላማ የተቋቋሙት የሚዲያ ተቋማት ውህደት፣ አንድ ግዙፍና ተደራሽ ሚዲያ ለመመስረት ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ውህደቱ የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል፣ የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት አቅምን በማቀናጀት የሃብት ብክነትን ማስቀረት  እንደሚያስችል የተጠቆመ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር የተቋማቱ  ውህደት ትርፋማነትንና ውጤታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተገልጿል። የውህደቱ ሒደት አስፈላጊውን ሕግና ሥርዓት ተከትሎ መፈጸሙም   ተነግሯል፡፡  
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና  የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ መንግስት ከለውጡ ወዲህ የሚዲያን ጥቅም በመረዳት ሰፋፊ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት የመንግስት ግልጸኝነት እንዲታይ ሰፋፊ ሥራዎችን እንደሰሩ ጠቁመው፤ መንግሥትም ለሚዲያው ትኩረት በመስጠት ተቋማቱ የለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል። የመረጃ ተደራሽነት ከፍ እንዲል ማድረግ፣ ብሄራዊ ትርክት ላይ መስራትና ኢትዮጵያ በዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ እንድትሆን ማድረግ ከአዲሱ ተቋም እንደሚጠበቅም አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡   
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር  ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው፣ አዲስ የተመሰረተው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፤ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በገለልተኝነትና በብቁ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር፣ ትውልድን በብሔራዊ ማዕቀፍ የሚገነባ፣ የተለየ ተግባር ያለው ትልቅ ሚዲያ ነው ብለዋል።
የጠ/ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እና የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት  ባደረጉት ንግግር፤ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተዋህደው የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት የመደመር እሳቤ ውጤት ነው ብለዋል፡፡ “በኢትዮጵያ ልክ ኢትዮጵያን መግለጥ ለመቻል በማሰብ ተነጣጥለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሁለቱ ሚዲያዎች ተዋህደው አንድ ሆነዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞው የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ መሐመድ ሀሰን፣ በተቋሙ ቆይታቸው  ላበረከቱት አስተዋጽኦ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የሚዲያው አመራሮች፣ የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ተባባሪ አዘጋጆች፣ የሚዲያው አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡  
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ፤ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎችና ሦስት ሬዲዮ ጣቢያዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ የተነገረለት የፓስታ ፌስቲቫል፤ በዛሬው ዕለት ከረፋዱ 5፡30 ጀምሮ  በሚሊኒየም አዳራሽ ይከናወናል፡፡
በካልቸር ክለብ በተዘጋጀው የጣልያን ምግብ  ፌስቲቫል ላይ ከ5ሺ እስከ 7ሺ እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ ከ23 በላይ የፓስታ ምግብ ሻጮች የተለያዩ ዓይነት የፓስታ ምግቦች፣ ሱጎዎችና ጣፋጮችን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡
የመግቢያው ዋጋ 250 ብር ሲሆን፤ትኬቶችን በቴሌብር መግዛት ወይም  መግቢያው በር ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከግሩም የፓስታ ምግቦች ባሻገር፣ ሙዚቃና ከምግብ ማብሰል ጋር የተያያዙ አዝናኝ ትርኢቶች ይኖራሉ ተብሏል፡፡

ኩባንያው የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ተገልጿል

“ሚለርስ ፎር ኒውትሪሽን” የተሰኘው የውጪ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ ስራ መጀመሩን አስታወቀ። ኩባንያው ይህን ያስታወቀው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃን  በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና አጠቃላይ ዕቅድና ግቡን ለባለድርሻ አካላት ባስተዋወቀበት የግማሽ ቀን መርሃ ግብር ላይ ነው።
ሚለርስ ፎር ኒውስትሬሽን በተለይ “ሰርቭ” ከተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚታየውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ ስራ የጀመረ ሲሆን፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ለ140 ፋብሪካዎች የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም ለ40 ፋብሪካዎች ደግሞ ስልጠና መስጠት መቻሉን የኩባንያው ሀላፊ ተናግረዋል። የሚለርስ ፎር ኒውትሬሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሀላፊ አቶ እያቄም አምሳሉ ጨምረው እንደገለፁት፤ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚሁ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኙና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት 22 ከመቶዎቹ ከክብደት በታች እንደሚገኙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምር ልማት ማእከል በቅርቡ ያወጣውን መረጃ በዋናነት አቅርበዋል።
ከላይ የተቀመጠው አሀዝ በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ እጥረት በመቅረፍ፣ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር፣ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ከዚህ አኳያ ሚለር ፎር ኒውትሬሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀርፋል የተባለ ሲሆን፤ በተለይም የስንዴ ዱቄት አምራችና የምግብ ዘይት ፋብሪካዎችን በቫይታሚን በማበልፀግ እጥረቱን ለመቀነስ እንደሚሰረራ ተናግሯል።
ሚለርስ ፎር ኒውትሪሽን በአፍሪካና በእሲያ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆንበኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ ናጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዲሽን ጨምሮ በጥቅሉ በስምንት ሀገራት እየሰራ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት በተከናወነው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ታድመዋል።

ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል


በተለያዩ  የበጎ አድራጎትሥራዎች ላይ ገንዘቡንና ጊዜውን በመሥጠት በንቃት የሚሳተፈው  ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ፤ በዛሬው ዕለት አበበ በቂላ  ስቴዲየም አካባቢ ባለው  ባቡልኬይር በመገኘት  ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የ4ሺ ሰው የምሳ ወጪ ሸፍኗል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ ድርጅቱ እየሰራ ያለውን የበጎ  አድራጎት ለማገዝ የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ስጦታውን የተረከቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀናን ማህሙድ ምህረት አብ፣"ዛሬ ሰርፕራይዝ ነው ያደረግኸን፤ ይሄን ያህል መጠን ያለው  ድጋፍ ሲደረግልን የመጀመሪያው ነው።" ሲሉ ለባለሃብቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡



በሀገራችን በራስ ተነሳሽነት በደጋግ ኢትዮጵያውያኖች ከተመሠረቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ባቡል ኬይር የበጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ሲሆን፤ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አስታዋሽ ያጡ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል፡፡

"የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለሕዝብ ማስታወቂያ"

ከዚህ ቀድሞ በመስከረም 11 ቀን 1928 ዓ.ም በተነገረው አዋጅ እንደሰማችሁት የኢጣልያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ሥራ በመሥራቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከተነሣበት ጠላት እንዲከላከል ምንም ቢታዘዝ ጠላት የተባሉት ወሰን አልፈው መሣሪያ ይዘው የወገኖቻችንን የኢትዮጵያን ሰዎች ደም ለማፍሰስ የሚመጡ ኢጣልያኖች ናቸው እንጂ በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን ከከተማ ውጭም ቢሆን በኢትዮጵያ የሰላማዊነት ሥራ እየሠሩ ለመኖር የመጡት አይደሉምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱና በአክባሪነቱ ከውጭ አገር ሰዎች ጋራ ተስማምቶ በሳላም በመኖሩ በዓለም የተመሰገነ ስለሆነ ይህ መልካም ስማችን ሳይጠፋ ተከብሮ እንዲኖር ገፍቶ የመጣውን ጠላታችንን ወደድንበራችን ሒደን ለመመለስ ከማሰብ በቀር በመካከላችን እኛን ዘመድ አድርገው በሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎች ላይ ማናቸውንም የጠላትነት አሳብ የሚገልጥ ነገር እንዳታደርጉ እናስታውቃለን። አሁን ከኢጣልያን ጋራ በተነሣው ጠብ ምክንያት በማስፈራራት በመጋፋት ወይም የማይገባ ቃል በመናገር ይህን በመሰለ አደራረግ ሁሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩትን የውጭ አገር ሰዎች ያዋረደ፥ የማይገባም ቃል የተናገረ እንደ ሕጉ በብርቱ ቅጣት ይቀጣል።

መስከረም 14 ቀን 1928 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከንቲባ

ምንጭ:- ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

•  የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ተጠይቆ ነበር

ለወራት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የሚማስኑት የህወሓት አመራሮች ትላንት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በትግራይ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
 
በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው ውዝግብና አለመግባባት መፍትሄ ሳይበጅለት የቀጠለ ሲሆን፤  ሁለቱም ወገኖች ቡድን ለይተው  መካሰሳቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ትላንት ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በጠ/ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በክልሉ የፀጥታና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ  ሲሆን፤ በዚህ ስብሰባ ላይም ሁለቱ ቡድኖች መካሰሳቸው ተነግሯል፡፡  

ቢቢሲ ስማቸውን መጥቀስ ያለፈለጉ ውይይቱን በቅርበት የተከታተሉ ታማኝ ምንጩን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በትግራይ ክልል  የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ቢሆንም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ጥያቄ ቀርቧል ብሏል፡፡

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በትግራይ እየተከሰተ ላለው ችግር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ደካማነት በምክንያትነት  በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ  ጌታቸው ረዳ ከሥልጣን እንዲነሱ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡

 "ጌታቸው ተነስቶ ምክትሉ ጄኔራል ታደሰ ወረደ" ቦታውን እንዲይዙ ሃሳብ ማቅረባቸውን ጉዳዩን በቅርብት የተከታተሉት አንድ  ተሳታፊ ለቢቢሲ ትግርኛ መናገራቸው ታውቋል፡፡

በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን በበኩሉ፤ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን" በማድረግ ዶ/ር ደብረጽዮንንና ቡድናቸውን ከሷል።

"ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራዎች እንቅፋት የሆናችሁት እናንተ ናችሁ" በማለት ምላሽ የሰጡት ጌታቸው ረዳ፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋል።

በድርጅቱ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናን ያላገኘው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አቶ ጌታቸውና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ከተባረሩ በኋላ ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪዎች ሥልጣን ላይ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።

አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንትነትን ቦታ የያዙት በህወሓት ውክልናቸው ነው በሚልም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የፌደራል መንግሥቱን ሲጠይቁ ነበር ተብሏል። አሁን ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት ጊዜም፣ ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ይህንኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ተነግሯል፡፡
 
ዶ/ር ደብረጽዮን፣ አቶ ጌታቸው ከጊዜያዊ አስተዳደር መሪነታቸው ተነስተው በቦታው ጄኔራል ታደሰ እንዲተኩ ያቀረቡትን  ሃሳብን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ታማኝ ምንጩ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

"ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን እንዳያከናውን 'የትግራይ ሠራዊት' ከጎናችን ነው' በማለት ሕዝቡን ግራ እያጋባችሁት ነው" በማለት የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድንን የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በስመ ምክር ቤት በሚል ሕዝቡን እየረበሻችሁት ነው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ጨምረውም፣ መንግሥታቸው የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ አድርጌለታለሁ እንደማይል በማንሳት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሚጠበቅበትን እያከናወነ እንደሚቆይ ማሳወቃቸውን የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ግጭቶችና ልዩነቶችን ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለብን ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ያላትን አቋም ለአረብ ሀገራት በአረብኛ ቋንቋ በስፋት በማድረስ የሚታወቁት ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ እንደ ሕዝብ ብሔራዊ የሆኑ አጀንዳዎቻችን ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ግብጻውያን በመሀከላቸው መከፋፈል ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው አንድነት ጠንካራ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

“ግብጻውያን በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ፤ ረጅም ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙ ዜጎቻቸው ጭምር በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸው አቋም አንድ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤት ብትሆንም በዜጎች ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት ሊሠራበት የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ተተኪ ለሆኑ ትውልዶች ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብትና የዓባይን ውሃ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ በመሥራት ረገድ ያለን ተሞክሮ ደካማ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህ ጉዳይ ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ሀገርን ወክለው በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማሳወቅ፣ በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብና የራሳቸውንም ሚዲያ በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ በመሞገት ይታወቃሉ፡፡

• በመቀሌ የህወሓት ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ጠየቀ

 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች በአዲስ አበባ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት፣ ከፌደራል መንግሥት አመራሮች ጋር በትግራይ ክልል ባለው አጠቃላይ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

በውይይቱም ላይ በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን እንዴት በጋራ መፍታት እንደሚገባ ምክክር የተደረገ ሲሆን፤ በተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ የጋራ አቅጣጫዎች መሠረት በጋራ ለመስራትና የክልሉ ህዝብ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ፍላጎት ለማሟላት አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል።

በተለይም ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ፣ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሂደትን በትኩረት በሚሰራበትና በሚሳለጥበት ሁኔታ ላይ መግባባት ተደርሷል።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም ህጋዊ በሆነ አግባብ የህዝብንና የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሆን፣ ለህዝብ የሚቀርቡ የመንግስት አገልግሎቶች የሚሻሻሉበትና የህዝብን ፍላጎት የሚመጥኑ እንዲሆኑ፣ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ስራ እንዲሰራ ተገቢው አቅጣጫ በውይይቱ መለየቱ ተነግሯል፡፡

በመጨረሻም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ያለበትን ሃላፊነት ለመወጣት በሚያስችለው አግባብ ላይም አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ መቋጨቱ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን፣ የፊታችን እሁድ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

ቡድኑ ለመቀሌ ከተማ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፤ “ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በትጥቅ የተደገፈ የአስተዳደር ፈረሳ በመከናወኑ፣ ይህን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን” ብሏል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ እንዲሰጠው ቡድኑ ጠይቋል፤ በደብዳቤው፡፡

“ለዘመናት መስዋዕት ከፍለን የመሰረትናቸው ምክር ቤቶች በግለሰቦች ሲፈርሱ አንታገስም በሚል ምክንያት፤ ከህዝባችንና አባላቶቻችን በተደጋጋሚ ጥሪ እየቀረበልን በመሆኑ ህዳር 29 በመቀሌ ከተማ ሰልፍ ለማድረግ አቅደናል” ብሏል፤ ቡድኑ።

እሁድ ህዳር 29 ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 6:30 ሰልፉን ለማድረግ ተዘጋጅተናል ያለው የህወሓት ቡድን፤ የጸጥታ ኃይል ጥምር ኮሚቴ ሰልፉን እንዲፈቅድለትና ከለላ እንዲያደርግለት ጠይቋል፤ በመቀሌ የህወሓት ጽ/ቤት፡፡

• ሁለት ታዋቂ ሴት አርቲስቶች በአመራሩ ተካትተዋል


የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በጊዮን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፤ ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩትን ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚዎችን መርጧል። አርቲስት ማስተዋል ወንደሰንና አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ በአመራሩ ውስጥ ተካትተዋል፡፡


ፌዴሬሽኑ የቀድሞውን አልቢትር ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃን በፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን፤ አርቲስት ማስተዋል ወንደሰን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል፡፡

አንጋፋዋ ተዋናይት ሀረገወይን አሰፋን ጨምሮ አቶ ሲሳይ ዳኜ፣ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ፣ አቶ ኢሳያስ ታፈሰ፣ አቶ ሸሀመለ በቀለ፣ አቶ በለጠ ወልዴና ወ/ሮ አሰፋሽን በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ተካተዋል።


ፌዴሬሽኑ አለብኝ የሚለውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ አርቲስቶችን ወደ ሥራ አስፈፃሚ በማምጣት የማርኬቲንግ ስራዎችን ለመስራት እንዳሰበ ተነግሯል፡፡

ጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለአራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ኢንጂነር ሀይለእየሱስ ፍስሀን መምረጡን ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Page 10 of 749