Administrator

Administrator

 ከዕለታት አንድ ቀን ጅቦች በጠፍ ጨረቃ ተርበው የሚበላ ፍለጋ ሲዘዋወሩ አንድ ግዙፍ ዝሆን ገደል ገብቶ ሞቶ አዩ፡፡
አንደኛው ጅብ - በረሀብ ከምንሞት እንግባና እንብላው
ሁለተኛው ጅብ - ገደሉ በጣም ሩቅ ነው፡፡ እንኳን ገብተን ሆዳችን ሞልቶ እንዲሁም ለመውጣት አዳጋች ነው፡፡ ስለዚህ መዘዋወራችንን እንቀጥልና የረፈደበት አህያ እንፈልግ፡፡
ሦስተኛው ጅብ - እንግባና ከበላን በኋላ እንደጋገፍና አንዳችን አንዳችን ትከሻ ላይ እየወጣን ከገደሉ እንወጣለን፡፡
አራተኛው ጅብ - ከገባን በኋላ እናስብበታለን
አንደኛው ጅብ - በድምፅ ብልጫ እንለየው
ሁሉም በድምፅ ብልጫ ይሁን በሚለው ሀሳብ ተስማሙ፡፡
አንደኛው ጅብ - እሺ፤ እንግባና በልተን እናስብበታለን የምትሉ?
ሁሉም እጃቸውን አወጡ፡፡
በሙሉ ድምፅ እንብላው አሉና ተግተልትለው ገቡ፡፡
ለአንድ ሁለት ሦስት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡ ዋለ አደረና የዝሆን መቀራመቱ ጥጋብ አበቃና፣ ረሀብ በተራው ይሞረሙራቸው ጀመር፡፡
እንደተገመተውም ከገደሉ መውጫው ዘዴ ሊገኝ አልተቻለም፡፡
እየተራቡ መተኛትም ሆነ ዕጣ-ፈንታቸው፡፡ አንድ ሌሊት አንደኛው ጅብ ጐኑ ላለው ጅብ፤ “በጣም የተኛውንና ዳር ያለውን ጅብ ለምን አንበላውም?” ሲል ሀሳብ አቀረበ፡፡ አንዱ ለአንዱ እያማከረ፣ ዳር ላይ ለጥ ያለው ላይ ሰፈሩበት፡፡ ለአንድ ሁለት ቀን ፈንጠዝያ ሆነ፡፡
እንደገና ረሀብ ሆነ፡፡ በዚያው ተዘናግቶ በተኛው ተረኛ ጅብ ላይ እየፈረዱ፣ በመጨረሻው ሁለት ቀሩ፡፡ ብዙ ለሊት እየተፋጠጡ አደሩ፡፡ ሆኖም መድከም አይቀርምና አንዱ ደክሞት ተኛ። የነቃው በላው፡፡ ጥቂት ሰነበተና እራሱም በረሀብ ሞተ!
*   *   *
የሀገራችን የሙስና ደረጃ ገና ያልተጠረገ በረት ነው፡፡ “አህያም የለኝ ከጅብም አልጣላ” ብለን የምንዘልቀው እንዳልሆነ ካወቅነው ውለን አድረናል፡፡ “ሙስናው በአዲስ መልክ ሥራ ቀጥሏል፡፡” እንዳንል፣ መረር ከረር ብሎ መገታት እንዳለበት መገንዘብ ያሻል፡፡ ብርቱ ጥንቃቄና ብርቱ እርምጃ ግድ ነው፡፡ “ግርግር ለሌባ ያመቻልና” የህዝቡን ፀጥታ የሚያደፈርስን ሁኔታ በችኮላም ሳንደናገር፣ በመኝታም ሳንዘናጋ በአስተውሎት መጓዝና ፍሬ ያለው ሥራ መስራት ያሻል፡፡ በየትኛውም አገር ለውጥን ተከትሎ የሚመጣ አደናጋሪ ሁኔታ ይከሰታል፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ መንጣጣቱም” ሆነ፤ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች” መባሉ የነበረ፣ ያለና ወደፊትም የሚኖር በመሆኑ፤ ነፃ አስተሳሰቡን እጅግ ልቅ ሳናደርግ፣ ግትርነቱንም (die-hardism) እጅጉን ሳናከርረው፣ በሥነ ሥርዓትና በዲሲፕሊን መራመድ ብቻ ነው የሚጠበቅብን። የረፈደ ነገር ያለ ቢመስለን አይገርምም! የአጭር ጊዜ ለውጥ ነውና! አመለካከታችን እስኪጠራ፣ በሀገራችን ህዝብ ዘንድ ብትሰራም ትኮነናለህ - ባትሰራም ትኮነናለህ (Do, damned! Don’t damned) ነውና፣ የያዝነውን መንገድ አለመልቀቅ ረብ ያለው እርምጃ ነው፡፡ ሰላምን ማደፍረስም ለሙስና ማራመጃም መከላከያም ሊሆን የሚችል አደገኛ መሣሪያ ነው! ዞሮ ዞሮ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ልብላው - ልብላው ነው” ከሚለው ተረት አይዘልም! ወንጀሎችን እንቆጣጠር! የመሣሪያ ዝውውርን በሕግ የበላይነት ሥር እናድርግ! “ጦር ሜዳ ማህል ግጥም አታነብም” እንደሚባል አንዘንጋ! ዘረፋን እንቋቋም! ያለ መስዋዕትነት ድል የለም! ከመጠምጠም መማር ይቅደም! የዕውቀትንና የባለሙያን ግብዓት በየፕሮግራሞቻችን ውስጥ ቀዳሚ እናድርግ፣ ከዘርና ከጐሣ ግጭት ወጥተን፣ በዲሞክራሲና በሕግ የበላይነት ራሳችንን እንገንባ! የዴሞክራሲያዊነት እንጂ የገዥነትና የተረኝነት ስሜት የትም አያደርሰንም!

 የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሀኪሞች ማህበር በአሜሪካ ከሚገኘው የአሜሪካን የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ኮሌጅ ጋር በመተባበር የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ቀርጾ ደጋፍ በሚያደርጉ ድርጅቶች አጋዥነት ስራ ከጀመረ እነሆ ሁለት አመታት ተቆጥረዋል፡፡ በእነዚህ ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ የተሰሩ ስራዎችን በሚመለከት አንዳንዶቹን እንደሚከተለው ለንባብ ብለናል፡፡
RESIDENCY: -
ከጠቅላላ ሐኪምነት ወደ ጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትነት የሚሰለጥኑ ባለሙያዎች በአገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ የትምርት መመሪያ እንዲሰለጥኑና ብቃት እና ጥራት ባለው መንገድ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል ስራ ከጤና ጥበቃ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጋራ ስራ ተሰርቶአል፡፡ ለሚማሩ ሰዎች ጥሩ ትምህርት መስጠት፤ ጥሩ ጥናትና ምርምር ማድረግ ፤የተሻለና ጥሩ የሆነ ሕክምና መስጠት የሚሉትን ነጥቦች ተግባራዊ ማድረግ የሚያስፈልግበት ምክንያትም የድህረ ምረቃ ትምህርቶቹ ከበሽተኛ ጋር የተገናኙ በመሆናቸውና ሐኪሙ ብዙ እናቶችን በሕክምናው አገልግሎት የመርዳት ኃላፊነት ስለአለበት በጥሩ ሁኔታ መሰራት እንዳለበት ስለታመነ ነው፡፡
ETHICS: -  
ሌላው የፕሮጀክቱ ዘርፍ የጽንስና ማህጸን ህክምና ባለሙያዎች የስነምግባር መመሪያን መቅረጽ ነው፡፡ የማህጸን እና ጽንስ ሐኪሞች ለሕመምተኛው መደረግ ያለበት የትኛው ነው ?የሚለውን ለመወሰን የሕመም ተኛው ፈቃድ፤ የሚኖረው አቅም የመሳሰሉት ሁሉ የሚያስፈልጉ ሲሆን ይህንን በትክክ ለኛው መን ገድ ለመምራት የሚያስችል የስነ ምግባር መመሪያ  በመዘጋጀት ላይ ነው ፡፡
CME: -
የህክምና ባለሙያዎች በስራ ላይ ባሉባቸው ጊዜያት እውቀታቸውን ከተለያዩ ሳይንሳዊ ግኝቶች እና አሰራሮች አንጻር የሚፈትሹባቸው ቀጣይነት ያለው ስልጠና እንዲያገኙ ማገዝ አንዱ  የESOG_ACOG ፕሮጀክት አቅጣጫ ነው፡፡ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች በዚህ ዘርፍ ጊዜው በሚፈቅደው የአገልግሎት አሰጣጥ ውስጥ እንዲያልፉ የሚያስችል አሰራር ነው፡፡
LEADERSHIP: -
የአመራር ብቃትን ማጎልበት ለጽንስና ማህጸን ሐኪሙ እጅግ ጠቃሚ በመሆኑና በስራ ላይ ያሉ ጉድለቶችን ለማስተካከል የሚረዳ በመሆኑ ባለሙያዎቹ በተወሰኑ ጊዜያት ስልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡ Transformational leadership በሚል የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለ ሙያዎች መሰልጠናቸው በተለይም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ሙያን በማስተማር ላይ ለሚገኙት እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡
ከተጠቀሱት በተጨማሪ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ቀደም ብሎ የጀመራ ቸውን ሳይንሳዊ ምርም ሮችን የሚያሳትምበት ጆርናልና ፤በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን ለህብረ ተሰቡ ስለጤንነቱ እንዲያ ውቅና አስቀድሞ እራሱን እንዲከላከል የሚያስችል ስራ የሚሰራባ ቸውን የመገናኛ ብዙሀን ስራዎች ማሳደግና የተሻለ ጥራት እንዲኖራቸው እገዛ ከማድረግ ባሻገር ሐኪሞች ባሉበት ቦታ ሆነው በኢንተርኔት አማካኝነት ትምህርትና መረጃዎችን እንዲያገኙ የማድረግ እና ሌሎችንም ተያያዥነት ያላቸውን ስራዎችን በመተግበር ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ከሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ (CIRHT) The Central For International Reproductive Health Training Of The University of Michigan ) በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ ለአምስት አመት ሊተገብረው የታሰበው ፕሮጀክት በሁለት አመቱ ወደ ኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያው ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንዲዛወር የመደረጉን ምክንያት ፕሮጀክቱ ስራውን ሲጀምር የኢሶግ ቦርድ ፕሬዝዳንት የነበሩት የማህጸንና ጽንስ ሕክምና እስፔሻሊስት  የሆኑት ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ ለዚህ እትም አብራርተዋል፡፡
ዶ/ር ደረጀ እንደገለጹት ‹‹… ከአሜሪካ የማህጸንና ጽንስ ሐኪሞች ማህበር  ጋር የተጀመረው ፕሮጀክት ጽንሰ ሐሳብ ኢሶግ  ከነበሩት ስትራቴጂክ ዶክመንቶች ውስጥ አንዱ በተለይም እንደውጭው አቆጣጠር ከ2012-2016/ የነበረውን የአምስት አመት ተግባራት በሚያመላክተው ውስጥ ማህበሩ በዚህ ፕሮጀክት ስንፈጽማቸው የነበሩትን ተግባራት እና ሌሎችንም ማህበሩ ከነበረው ራእይና ተልእኮ ጋር የተያያዘ ስለሆነ ይህንን ተግባር ዋነኛ ማድረግ ይገባል የሚል እቅድ ነበረ፡፡ስለዚህም እኔ የቦርድ ፕሬዝዳንት ሆኜ ስመረጥ ከ2014/እንደውጭው አቆጣጠር ጀምሮ ዶክመንቱን በመፈተሸ ከላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት ለመምራት የሚያስችለን የኢትዮ ጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ኮሌጅ መመስረት ያስፈልጋል የሚል እምነት አደረብን፡፡ ስለዚ ህም ሶስት ልምድ ያላቸው ሐኪሞች ተመድበው ስራውን እንዲከታተሉ ሲደረግ እኔም ነበርኩ በት፡፡ ይህንን ጉዳይ በስራ ከምናገኛቸው የተለያዩ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ባለሙያዎች  ጋር በመመካከር ስራው ከአሜሪካ የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ ጋር የምንሰራበት መንገድ ስለተመቻቸ June/ 2016/  የመግባቢያ ሰነዱ ተፈርሞአል፡፡
ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ አስከትለው እንደተናገሩትም በኢሶግ ስትራቴጂክ ዶክመንት ላይ የተገለጸው በውጭው አቆጣጠር በ2020/ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ እንደሚመሰረት ነው፡፡ የተጀ መሩት ስራዎች በአምስት አመት ጊዜ ውስጥ ሲያልቁ እራሱን የቻለ ኮሌጅ ተመዝግቦ ስራ ይጀምራል የሚል እቅድ ተነድፎ ነበር፡፡ ነገር ግን ከድጋፍ አድራጊዎች ወገን ባልታሰበ ሁኔታ የሚገኘው እገዛ በውጭው አቆጣጠር ከሴፕቴምር 30/2018/በሁዋላ እንደማይቀጥል ስለተነገረን ይህ ዱብእዳ እንደሚባለው አስደንጋጭ ዜና ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአለምአቀፍ ደረጃ ካለው ድጋፍ የማድረግ እንዲሁም የገንዘብ አሰጣጥ ፍሰትና በተወሰነ መልኩም የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርም ከአሁን በሁዋላ ስራውን እየመራ መቀጠል ይችላል ከሚል እምነት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለ ዚህም የአሜሪካው የማህጸንና ጽንስ ኮሌጅ የሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ስለሚቋረጥ በቀጣይነት ከኢሶግ ጋር ለመስራት ምቹ ሁኔታ አለመኖሩን ተነግሮን ፕሮጀክቱ እንዲቋረጥ ተገድዶአል፡፡›› ብለዋል፡፡
የተጀመሩት ስራዎችን ቀጣይነት በሚመለከት ዶ/ር ደረጀ እንዳሉት‹‹…ኢሶግ ላለፉት 27/ አመ ታት በኢትዮጵያ የስነተዋልዶ ጤና ላይ ብዙ ሰርቶአል፡፡ በዚህም የተነሳ በተለያዩ የስነተ ዋልዶ ጤና ዙሪያ ከተለያዩ ድጋፍ አድራጊዎች ጋር የሰራ በመሆኑ ጥሩ አጋር መሆኑን ማሳ የት የቻለ ማህበር ነው፡፡ ስለዚህም አሁን የተጀመሩትን በጎ ስራዎች ከሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር በመሆን መቀጠል ይቻላል፡፡ አሁን ፕሮጀክቱ ተቋርጦአል ቢባልም ለተወሰኑ ወራት ድጋፉ እንደሚቀጥል ቃል የገቡ በመሆኑ ለወደፊትም ከእነሱው ጋር ይቀጥል ወይንም ስራውን እየሰራን ሌሎች ድጋፍ አድራጊዎችን ማፈላለግ ያስፈልጋል የሚለውን የምናየው ይሆናል፡፡ ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ በስተመጨረሻው እንደገለጹት በኢትዮጵያ የህክምና ታሪክ በተለይም ሙያውን በልዩ ደረጃ በማሰልጠን ረገድ የኢትዮጵያ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ማህበር ባለፉት ሁለት አመታት በተደረገለት የገንዘብም ሆነ የሙያ ድጋፍ የሰራው ስራ የመጀመሪያ ነው፡፡  
ኢትዮጵያ ውስጥ የማህጸንና ጽንስ ሕክምና ትምህርትን የሚሰጡ ተቋማት በሙሉ አንድ አይነት የሆነ የትምህርት መርሐ ግብር እንዲኖራቸው ለማስቻል ከጤና ጥበቃ እና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆን ስራ ተሰርቶአል፡፡ ደረጃውን የጠበቀ ፈተናን መስጠትን በተመለከተም ተሳክቶ ተካሂዶአል፡፡ ጥራቱን የጠበቀ ተከታታይ የህክምና ትምህርት መስጠትን በተመለከተም ባለሙያዎችን ለልዩ ሙያ በማሰልጠን ረገድ ካሉ ሌሎች ተቋማት በተሻለ መስራት ተችሎአል፡፡ የህክምና ስነምግባርን በተመለከተም ዶክመንት እየተዘጋጀ ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎች ጠቃሚ ስራዎች በማህበሩ እየተሰሩ በመሆናቸው እና የተሰሩም በመኖራቸው ማህበረሰቡን በበቂ ሁኔታ ለማገልገል ዝግጁ ነን ማለት ይቻላል፡፡ ወደፊትም የማህበሩ አባላት በተሰለፍንባቸው የተለያዩ መስኮች የተሻለ ስራ በመስራት ህብረተሰቡን በተሻለ ሁኔታ ማገልገል ይጠበቅብናል ብዬ አምናለሁ ብለዋል ዶ/ር ደረጀ ንጉሴ፡፡››

 የገጣሚ፣ ተወዛዋዥና ኬሮግራፈር ኤፍሬም መኮንን (ኤፊማክ) ሁለተኛ ሥራ የሆነው “የወፍ ጐጆ ምህላ” የግጥም መፅሐፍ፣ ነገ ከቀኑ 9፡00 ጀምሮ ናዝሬት አዳማ በሚገኘው ተስፋዬ ኦሎምፒክ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በስነ ስረዓቱ ላይ ገጣሚያን አዳም ሁሴን፣ ሰለሞን ሳህለና በላይ በቀለ ወያን ጨምሮ በርካታ ገጣሚያን ስራዎቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ከመፅሐፉ የተመረጡ ግጥሞችም ይነበባሉ ተብሏል፡፡ “ፍራሽ አዳሽ” የተሰኘ የአንድ ሰው ተውኔት በተስፋሁን ከበደ ለታዳሚ እንደሚቀርብም ገጣሚ ኤፍሬም መኮንን ገልጿል፡፡
“ግጥም በውዝዋዜን” ለመጀመሪያ ጊዜ በመድረክ ያስተዋወቀው ኤፍሬም፤ ነገም ግጥምን በውዝዋዜ ለታዳሚ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡ የግጥም መፅሐፉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ 61 ግጥሞች ያሉት ሲሆን፤ በ94 ገጾች ተቀንብቦ በ-------------- ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ ገጣሚው ከዚህ ቀደም “ለባለ ቅኔው ቅኔ አጣሁለት” የተሰኘ የግጥም መፅሐፍ በግሉ ያሳተመ ሲሆን፤ “ሰሚ ያጡ ብዕሮች” እና “የግጥም ከተራ” የተሰኙ የግጥም መፅሐፎችን ከሌሎች ገጣሚዎች ጋር በጋራ አሳትሞ ለንባብ ማብቃቱ አይዘነጋም፡፡    ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ከኢትዮጵያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር ነገ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ-መፃህፍትና ቤተ-መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ በአርክቴክት ሚካኤል ሽፈራው “የሞሮኮ አገር እውነት” መፅሐፍ ላይ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት ገጣሚና ጋዜጠኛ ዮሐንስ ገ/መድህን ሲሆኑ መድረኩም በሰለሞን ተሰማ ጂ እንደሚመራ ታውቋል፡፡
ደራሲው አርክቴክት ሽፈራውም በፕሮግራሙ ላይ የሚታደም ሲሆን፤ በውይይቱ ላይ ፍላጐት ያለው እንዲሳተፍ አዘጋጁ ጋብዟል፡፡    በመላ ሃገሪቱ ከአርማና ባንዲራ ጋር በተያይዞ እየተፈጠሩ ያሉ ውዝግቦች ዘላቂ ሕጋዊ መፍትሄ እንደሚያሻቸው የገለፁት ሰማያዊ ፓርቲና ኦፌኮ፤ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው ወደ ሁከትና ብጥብጥ ከማምራታቸው በፊት መንግስት አፋጣኝ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል።
ከአርማና ሠንደቅ አላማ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ሁከቶችን ለማስቆም የሃይማኖት አባቶችና፣ አባገዳዎች፣በየአካባቢው ወጣቶችን  የማረጋጋት ስራ እንዲሰሩም ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጠይቀዋል፡፡
“የለውጡን ሂደት መደገፍና አገሪቱን እንደ አገር የማስቀጠል ጉዳይ ቅድሚያ ሊሰጠው ሲገባ፤ በየአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችና ሥርአት አልበኝነት አሳሳቢ ደረጃ ደርሷል” ያሉት ፓርቲዎቹ፤ “በተለይ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከባንዲራ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ውዝግብ ከምንም በላይ አሳሳቢ ነው፤ አስቸኳይ እልባት ያስፈልገዋል” ብለዋል፡፡
ሁሉም አካል የሌላውን ባከበረ መልኩ የየራሱን አርማ መያዝ እንደሚችል የተረጋገጠ ሁኔታ መፈጠሩን የጠቀሱት ፓርቲዎቹ፤ በዚህ ሰበብ የሚፈጠሩ ግጭቶችን በፅኑ እናወግዛለን ብለዋል፡፡
በሃገሪቱ በአሁን ወቅት እየታየ ያለው ፖለቲካዊ ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑን የጠቆሙት «ሰማያዊ» እና «ኦፌኮ»፤ ሁሉም የፖለቲካ ቡድን ይህን ተስፋ ወደተሻለ ለውጥ የማሸጋገር ኃላፊነት አለበት ብለዋል፡፡
ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡ የትኞቹም ድርጅቶች ያለ አድልኦና መገለል በመላው ህዝብ በፍቅር አቀባበል ሊደረግላቸው እንደሚገባም ፓርቲዎቹ ገልፀዋል፡፡
የባንዲራ ጉዳይ ሃገሪቱ ካለባት ውስብስብ ፖለቲካዊ ችግሮች አንፃር በቀጣይ በህዝብ ውሳኔ እልባት ሊያገኝ የሚችል መሆኑንም በመጠቆምም ሁሉም ወገን ለውጡ እንዳይቀለበስ የበኪሉን መወጣት ይገባዋል፤ ብለዋል፡፡    አንድ የፋርስ ገጣሚና ነገን ተንባይ (Philosophizing the Future) ከአንድ ሌላ የጊዜው ባለሙያ ጋር፤
አንደኛ - “የመጣነውን መንገድ ጨርሰነዋል ወይ?”
ሁለተኛ - ጥያቄዎቹን አንጥረን ስናወጣ (Crystallized Questions)፤ መፍትሄ የሚያገኙ ንጡር ጥያቄዎች ናቸው ወይ?
ሦስተኛ - “ድንገት ወደ መልስ ካመሩ ወዴት ያምሩ?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ባለሙያውም፤
1ኛ/ “ትናንትን ለመጨረስ ዛሬን መጀመር ብቻ በቂ ማረጋገጫ አይሆንም፡፡ ቢያንስ ነገን ማሰብን ይጠይቃል! ስለዚህ ካሁኑ ስለ ነገ መመራመር ጀምር!”
2ኛ/ የነጠረ ጥያቄ ለማውጣት አስቀድመን ፍላጐታችን ምንድነው? ብለን እንጀምር፡፡ ከዚያ ጥያቄዎቻችንን እናሰባስብ፡፡ ቀጥለን አንኳር አንኳሮቹ የትኞቹ ናቸው? እንበል፡፡
3ኛ/ “አንኳር አንኳሮቹን ጥያቄዎች ለማን እናቅርባቸው? ስትል ወዴት ማምራት እንዳለባቸው ራሳቸው ይመሩሃል፡፡ ሁሉንም ስታደርግ ግን በሁለት ቢላዋ ከሚበሉ ሰዎች ተጠንቀቅ!” ብሎት ባለሙያው መምህር ሄደ፡፡ ፋርሳዊው ገጣሚም “ነገን ለመጀመር ትናንትናን ጨርስ” የሚለውን ሀሳብ ዕድሜ ልኩን ይዞት ኖረ!
*   *   *
የነገ ጉዟችን ትላንትና እንደተጀመረ አንርሳ፡፡ ለዚያ ጅምር አስተዋፅኦ ያደረጉትን ሁሉ አንዘንጋ፡፡ የነገ ጉዟችን አጭር ርቀት እንዳልሆነ እናስተውል፡፡ ይህ ጉዞ ከባድ የዕውቀት መሰናዶን ይጠይቃል፡፡ መማር፣ መማር፣ አሁንም መማር ሲባል የነበረው ለትምህርት ጥማት ብቻ ሲባል አልነበረም፡፡ አንድም ትላንትናን ለመማርና ልምድን ለማካበት፣ አንድም በዛሬ ላይ ለመንቃት፣ አንድም ድግም ነገን ለመተንበይ ነው። መማርን ወደ ዕውቀት፣ ዕውቀትን ወደ ጥበብ ስናሳድግ የተግባር ብልሃት ይገባናል። ያኔ አገርን ማሳደግ ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡ ከአሮጌው አስተሳሰብ መፅዳት እንዴት እንደሚቻል ግንዛቤው ከእነ ዘዴው ይመጣልናል! የትምህርትን ነገር ዘንግቶ ስለ ዕውቀት ማውራት ዘበት ነው፡፡ ትምህርታችንን በየዕለቱ መቀጠል እንዳለብን አስተውለን፣ ምን እናድርግ? እንበል፡፡ “ከመጠምጠም መማር ይቅደምከ የሚሉት አበው፣ ጧቱኑ ነገሩ ገብቷቸው ነው፡፡ አውቀናል ብለን ከተኮፈስን፣ አዲስ ዕውቀት ያመልጠናል፡፡ አስበን መኖር ይጠፋናል፡፡ ነገን መጨበጥ ዛሬውኑ ከእጃችን ይወጣል፡፡ ሥጋቶቻችንን እንምከርባቸው እንጂ አንሽሻቸው፡፡
ከአገረ-ዳንኪራ በጊዜ እንገላገል፡፡ የጥንቱ ሥነ-ተረት ስድስት ቅዳሜና አንድ እሁድ ስለነበራቸው ድንክዬዎች የሚያወጋ ነው፡፡ ወደ ሥራ፣ ወደ ማሰብ፣ ወደ ተግባር ለመሄድ ሰባት የሥራ ቀንም አይበቃንም፡፡ በአሉባልታና በጫጫታ የፈረሰችውን እያሪኮ ሳይሆን የጠንካራዋን ኢትዮጵያን አዲስ መሠረት ለመጣል እንነሳ፡፡ አዕምሮ ለአዕምሮ በመናበብ አዕምሮ ላይ እንሥራ፡፡ ሌትና ቀን እንጣር፡፡ የማይታየንን ለማየት እንሞክር፡፡ እንዳናይ ማን ጋረደን እንበል፡፡ በግርግር ጊዜ አናጥፋ፡፡ ከአገረ-ዳንኪራ ወደ አገረ-ኮሰታራ እንቀየር፡፡ አዲስ የተባለን ሁሉ በመነካካት የተለወጥን አይምሰለን፡፡ ለውጥ ጊዜ-ወሳጅና አዳጊ ሂደት እንጂ ሙቅ ማሞቅ አይደለም! ሼከስፒር “Uneasy Lies the head that wears the crown” ይለናል፡፡ ዘውድ የጫነ ጭንቅላት ጭንቀት ይጫነዋል፤ እንደማለት ነው፡፡ ለመጪዎቹ የምናደርገው መስተንግዶ ሁሉ ዘውድ ለመጫን ከሆነ፣ ጭንቀቱንም መጋራት አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ልብ እንበል! እግረ-መንገዳችንን ገጣሚው፡-
የሄድንበትን ቦይ፣ እንጠይቅ እንመርምር
ጅምሩን ሳንጨርስ፣ አዲስ አይጀመር
ያለውን በአዕምሯችን እንያዝ!!

  በአውዳመት ምድር የደቡብ ሱዳንን ቅጡ የጠፋው የሰላም ስምምነት ወይም የቻይናና አሜሪካን የንግድ ጦርነት መካረር ወይም ሌላ አለማቀፍ ዜና ከማቅረብ ይልቅ፣ ከአዲስ አመት አከባበር ጋር በተያያዘ የተለያዩ የአለማችን አገራትን አስገራሚ ልማዶችና ባህሎች በማሰባሰብ ልናስቃኛችሁ ወደድን፡፡
እነሆ!...
“የጎመን ምንቸት ውጣ፤ የገንፎ ምንቸት ግባ” እንዲል ሐበሻ መስከረም ሲጠባ፣ የዌልስ አባወራዎችም በተመሳሳይ መልኩ በአዲስ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ የቤታቸውን የጓሮ በር ከፍተው መልሰው በፍጥነት ይዘጋሉ፡፡ ያለፈው አመት ወደ ቤታቸው ይዞት የገባው መጥፎ ዕድል ሹልክ ብሎ ይወጣ ዘንድ ነው በውድቅት ሌሊት በራቸውን መክፈታቸው፡፡ በዚህም አያበቁም፤ ልክ ሲነጋ ደግሞ ያንኑ በር መልሰው ይከፍቱታል፡፡ አባወራዎቹ ሲነጋ በሩን የሚከፍቱት አዲሱ አመት መልካም ዕድልን፣ ብልጽግናንና ሰላምን ይዞ ወደ ቤታቸው እንዲገባ ነው፡፡
ጃፓናውያን በበኩላቸው፤ ኦሾጋትሱ ብለው የሚጠሩትን የአዲስ አመት በዓል የሚያከብሩት ቤታቸውን ከወትሮው በተለየ በማጽዳትና በማሸብረቅ ነው፡፡ የጃፓናውያኑን የአውዳመት ጽዳት ለየት የሚያደርገው ግን፣ ቤታቸውን ከቆሻሻ ብቻ ሳይሆን ራሳቸውንም ከዕዳ ማጽዳታቸው ነው፡፡ ሁሉም የቤተሰብ አባል ያለበትን የገንዘብ ዕዳ በሙሉ ከፍሎ፣ ከተቀያየመውና ከተጣላው ሰው ጋር እርቅ አውርዶ፣ ከቂምና ከዕዳ ከነጻ በኋላ ነው አዲስ አመትን በደስታ ማክበር የሚጀምረው።
ስፔናውያን ደግሞ በአዲስ አመት የመጀመሪያዋ ቀን ሰዓታቸውን እያዩ ልክ አንድ ሙሉ ሰዓት ሲሆን አንድ ወይን የሚበሉ ሲሆን፣ ቀኑን ሙሉ የሚበሏቸው 12 የወይን ፍሬዎች፣ በአዲሱ አመት 12 ወራት፣ መልካም ዕድልንና ደስታን ያመጡልናል ብለው ያምናሉ፡፡
አየርላንዳውያን የአዲስ አመትን አከባበር የሚጀምሩት፣ በዋዜማው ምሽት፣ በየቤታቸው ግድግዳና በር ላይ ዳቦ በማንጠልጠል ነው። ዳቦው የተትረፈረፈ ጸጋን እንደሚስብና መጥፎ መንፈስንና ክፉ እድልን ከቤታቸው እንደሚያስወጣ ያምናሉ፡፡ በዚህም አያበቁም። ከቤታቸው በዳቦ ያባረሩት መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል ከደጃፍ እንዳይጠብቃቸው በመስጋት በእኩለ ሌሊት ከቤታቸው በመውጣት፣ ጆሮ የሚበጥስ ሃይለኛ ጩኸት ያሰማሉ፡፡
ሁሉም በየደጃፉ ቆሞ አቅሙ በፈቀደው መጠን እሪታውን ያቀልጠዋል፡፡ ህጻን አዋቂው ጉሮሮው እስኪደርቅ በመጮህ፣ ከደጃፉ ያደፈጠውን መጥፎ መንፈስና ክፉ እድል፣ ከአገር ምድሩ ጠራርጎ ያስወጣና፣ አዲስ አመትን “በል እንግዲህ ሰተት ብለህ ግባ!!” ብሎ ይቀበላል፡፡
አንዲት ብራዚላዊት በአውዳመት ምድር፣ የወርቅና የአልማዝ ጌጣጌጦቿን አወላልቃ፣ ወደ ባህር ስትወረውር ቢያዩ፣ ጤንነቷን ሊጠራጠሩ ይችላሉ፡፡ አይጠራጠሩ! ጤነኛ ናት፡፡ ጌጣጌጦቿን ወደ ባህር የምትወረውረውም፣ ያለፈውን አመት በሰላም በጤና እንዳሳለፈችው ሁሉ፣ አዲሱ አመትም የሰላምና የጤና እንዲሆንላት አምላኳን ለመለመን ነው፡፡
ኮፓካባና ተብሎ የሚጠራው የብራዚል ባህር ዳርቻ፣ አመቱን ሙሉ በቱሪስቶች የሚጥለቀለቅ ታዋቂ የመዝናኛ ስፍራ ነው፡፡ ኮፓካባና ከአመት አመት የመዝናኛ፣ ከአመት አንድ ቀን ደግሞ የአውዳመት ማክበሪያና የመማጸኛ ባህር ነው፡፡
ብራዚላውያን በዘመን መለወጫ ዋዜማ በሚያከናውኑት ‘ፌስታ ዲ ኢማንጃ’ የተባለ ባህላዊ ክብረበዓል፣ ወደ ባህሩ አቅንተው ‘ኢማንጃ’ የተባለችዋን የባህር አምላክ ይለማመናሉ። አዲሱን አመት መልካም እንድታደርጋቸው ይጸልያሉ። በስተመጨረሻም ወደ ባህሩ እጅ መንሻ ይወረውራሉ፡፡ በአዲስ አመት ዋዜማ ወደ ባህሩ የሚወረውሩት ጌጣጌጦች ብቻም አይደሉም፡፡ ውድ ዋጋ የሚያወጡ ሽቶዎች፣ አበቦችና ፍራፍሬዎች ጭምር እንጂ፡፡
ድሮ ድሮ ወደ አገራችን መጥቶ በጥምቀት በዓል የታደመ እንግዳ ደራሽ ዴንማርካዊ፣ ኮበሌው ወደ ልጃገረዷ ደረት ሎሚ ሲወረውርና ጡቷን ሲመታ ቢያይ ግራ ሊጋባ ይችላል፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡ ወደ ዴንማርክ አቅንቶ የዘመን መለወጫ በዓላቸውን የታደመ የኛ አገር ሰው በተራው፣ ስኒ እንደ ድንጋይ ወደየቤቱ ደጃፍ ሲወረወር ቢያይ፣ በተመሳሳይ ግራ መጋባቱ አይቀርም፡፡ ውርወራው ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አያውቅምና፡፡
ዴንማርካውያን በአዲስ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ የማጀት እቃዎቻቸውን ለቃቅመው ወደ ጎዳና ይወጣሉ፡፡ በጨለማ ውስጥ ተደብቀው ማንም ሳያያቸው፣ ወደመረጡት ጎረቤት ወይም ወዳጅ ዘመድ ቤት ያመራሉ፡፡ ከዚያስ?... በደረቅ ሌሊት በወዳጅ ዘመዳቸው ቤት ጣራ ላይ የማጀት እቃዎቻቸውን እንደ ድንጋይ ይወረውራሉ፡፡
በዚህች የዴንማርክ ምሽት ብርጭቆ፣ ትሪ፣ ሰሃን፣ ጭልፋ፣ ማንኪያ፣ ድስትና ሌላ ሌላው የቤት እቃ በሙሉ ከየመደርደሪያው ወርዶ ወደየቤቱ ደጃፍ ይወረወራል፡፡ ከግድግዳ እየተጋጨ፣ ከመስኮት እየተፋጨ፣ በየበሩ ሲሰባበር፣ በየደጃፉ ሲነካክት ያመሻል፡፡
ንጋት ላይ… ሁሉም ከቤቱ በመውጣት በየራሱ ደጃፍ የተጠራቀመውን ስብርባሪ የማጀት እቃ በማየት ደስታን ይጎናጸፋል፡፡ የተሰባበረው እቃ የመልካም ነገሮች ምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል። ምሽቱን ወደ ቤቱ ብዙ እቃ ሲወረወርበት ያደረ፣ ሲነጋ ከደጃፉ ብዙ ስብርባሪ ተጠራቅሞ ያገኘ ቤተሰብ፣ በሌሎች ዘንድ የበለጠ ተወዳጅ እንደሆነና መጪው አመትም በተለየ ሁኔታ የደስታ፣ የብልጽግናና የጤና እንደሚሆንለት ይታሰባል፡፡
ዴንማርካውያን ከዚህ በተጨማሪም በአዲሱ አመት ዋዜማ እኩለ ሌሊት ላይ፣ ወንበር የመዝለል ባህል አላቸው፡፡ ይህም ከአሮጌው አመት ወደ አዲሱ አመት፣ ከችግር ወደ ስኬት በሰላማዊ ሁኔታ የመሸጋገር ተምሳሌት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
“ቺሊያውያን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር ነው የሚያከብሩት” ብዬ ስነግርዎት፣ “ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል?… እኛስ ከዘመድ አዝማድ ጋር አይደል እንዴ የምናከብረው?!” እንደሚሉኝ አላጣሁትም፡፡
ነገሩ ወዲህ ነው…
የቺሊያውያንን የዘመን መለወጫን በዓል ከዘመድ አዝማድ ጋር የማክበር ባህል ከእኛ የሚለየው ዋናው ጉዳይ፣ ወደ ዘመዶቻቸው የሚሄዱት በዋዜማው ምሽት መሆኑም አይደለም - በህይወት ወደሌሉ ዘመዶቻቸው መሄዳቸው እንጂ!! ቺሊያውያኑ በሞት የተለዩዋቸው ዘመዶቻቸው ወዳረፉበት መካነ መቃብር በአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ያመራሉ፡፡ በድቅድቅ ጨለማ በተዋጠው የወዳጅ ዘመዳቸው መቃብር ውስጥ አረፍ ብለውም፣ ከወዳጅ ዘመዳቸው ጋር በዓሉን በዝምታ ጨዋታ ሞቅ ደመቅ አድርገው ያከብራሉ።
አዲሱ አመት የሰላም፣ የደስታና የብልጽግና እንዲሆንላቸው የሚመኙ ሜክሲኳውያን፤ በዋዜማው ምሽት ቀይ ወይም ቢጫ የውስጥ ሱሪ የማድረግ ልማድ አላቸው፡፡ ቀዩ ለብልጽግና፣ ቢጫው ደግሞ ለፍቅርና ለሰመረ ትዳር ይመረጣል።
በአዲስ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳርን ስለ መሻት ካነሳን አይቀር፣ የአየርላንዳውያን ሴቶችን ልማድ እንመልከት፡፡ በአዲሱ አመት ጥሩ ፍቅርና የሰመረ ትዳር ይገጥማት ዘንድ የምትመኝ አየርላንዳዊት ሴት፣ በበዓሉ ዋዜማ ሚስትሌቶ የሚባል የተክል አይነት በትራሷ ስር ሸጉጣ ታድራለች፡፡
በአገራችን ስራ ተፈትቶና ዘና ተብሎ የሚከበረው የዘመን መለወጫ በዓል፣ በኮሎምቢያና በሜክሲኮ ከዋዜማው እኩለ ሌሊት አንስቶ ከባድ ሸክም በመሸከም እንደሚከበር ሲሰሙ ምን ይሉ ይሆን?
የኢኳዶር ዜጎች በበኩላቸው፤ በአዲስ አመት ዋዜማ ምሽት ከየቤታቸው ተጠራርተው ደጃፍ ላይ ይሰባሰባሉ - ለደመራ፡፡ ታዲያ ይሄ ምን ይገርማል ሊሉ ይችላሉ፡፡ የሚገርምዎት ኢኳዶራውያኑ በደመራ መልክ የሚያነድዱት እንጨት ሳይሆን ፎቶግራፍ መሆኑ ነው፡፡
እናት፣ አባት፣ እህትና ወንድም ሁሉም ባለፈው አመት ያጋጠማቸውን ማንኛውንም መጥፎ ነገርና ገጠመኝ የሚያሳዩ ፎቶግራፎቻቸውን ከአልበሞቻቸው ውስጥ በርብረው በማውጣት፣ እንደ ችቦ ደመራ አድርገው በእሳት ያጋዩዋቸዋል፡፡ ፎቶው ሲቃጠል፤ ያ መጥፎ አጋጣሚም ከአሮጌው አመት ጋር ከውስጣቸው ወጥቶ ያልፋል - እነሱ እንደሚያምኑት፡፡
ከኢኳዶር ሳንወጣ ሌላ የአዲስ አመት አከባበራቸው አካል የሆነ ልማዳቸውን እናክል፡፡ በአዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን፣ ምንም የሌለበት ባዶ ሻንጣ ይዘው ረጅም ርቀት የሚጓዙ በርካታ ኢኳዶራውያንን ጎዳና ላይ መመልከት የተለመደ ነገር ነው፡፡ ባዶ ሻንጣ ይዘው ርቀው የሚጓዙት፣ እንደዚያ ካደረጉ በአዲሱ አመት በብዛት ጉብኝት እንደሚያደርጉ ወይም ወደ ሌሎች ቦታዎች እንደሚጓዙ ያምናሉ፡፡
ሩስያውያን በበኩላቸው፤ በዋዜማው ምሽት በአንድ ላይ ይሰባሰቡና በአዲሱ አመት ሊያሳኩት የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ በዝርዝር በየራሳቸው ወረቀት ላይ ይጽፋሉ፡፡ ጽፈው ከጨረሱ በኋላ፣ ወረቀቱን በእሳት ያቃጥሉትና አመዱን ከሻምፓኝ ጋር ቀላቅለው እኩለ ሌሊት ከማለፉ በፊት ጭልጥ አድርገው ይጠጡታል - በዚህም አዲሱ አመት ያሰቡት የሚሳካበት ይሆናል ብለው ያስባሉ፡፡
እንደ ሩስያውያን ሁሉ ደቡብ ኮርያውያንም የአዲስ አመት ህልምና ምኞትን በወረቀት ላይ የማስፈር ልማድ አላቸው፡፡ የእነሱን ለየት የሚያደርገው ግን፣ በአዲሱ አመት የመጀመሪያዋ ቀን ንጋት ላይ ከደጃፍ ቆመው፣ ጎህ ሲቀድ እያዩ፣ ህልምና ምኞታቸውን በወረቀት ላይ ጽፈው፣ በፊኛ ውስጥ አድርገው ወደ ሰማይ መላካቸው ነው፡፡
ወደ ስኮትላንድ እናምራ…
ስኮትላንዳውያን ቤተሰቦች፣ የአሮጌው አመት የመጨረሻ ዕለት ተጠናቅቃ፣ የአዲሱ አመት የመጀመሪያ ቀን ስትጠባ፣ ማልደው በር በሩን ማየት ይጀምራሉ፡፡ ቀጣዩ የበዓል አከባበር የሚደምቀውና የሚሞቀውም ሆነ የቤተሰቡ የአዲስ አመት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በዚያች ማለዳ ቀድሞ ወደ ቤታቸው በሚመጣው ሰው ነው፡፡
በዚያች ማለዳ ደጃፋቸውን ቀድሞ የረገጠው ሰው፣ ቁመተ ሎጋና መልከመልካም ወንድ ከሆነ፣ አዲሱ አመት የደስታ ይሆናል ብለው ስለሚያምኑ አብዝተው ይፈነጥዛሉ፡፡ በአንጻሩ በዚያች ማለዳ ቀይ ጸጉር ያላት ሴት አልያም ህጻን ልጅ ቀድመው ወደ ቤታቸው ከመጡ ደግሞ አመቱ ለቤተሰቡ ይዞት የሚመጣው አንዳች መከራ አለ ተብሎ ይታመናል፡፡
የሚመጣውን አዲስ አመት ወደ ቤታቸው በሚመጣው ሰው የሚተነብዩት ስኮትላንዳውያን ወንዶች፣ የዘመን መለወጫ በአልን በአጉል ጨዋታ ነው የሚያከብሩት - በልባል እሳት እንደ ኳስ እያንጠባጠቡና በሰራ አካላቸው ላይ እያሽከረከሩ በመንገድ ላይ እየተደሰቱ በመጓዝ፡፡
አዲሱ አመት እንደ ስኮትላንዳውያኑ በእሳት ሳይሆን እንደ ባህላችን ከሳቅ ጋር እየተደሰታችሁ የምትጓዙበት ይሁንላችሁ!!

 አንዳንድ እውነት ተረት ይመስላል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ነጋዴ - አጐበር አከፋፋይ ነበሩ፡፡ ወቅቱ፤ ወባ በአገራችን ብዙውን አካባቢ ያጠቃበት፣ ኮሌራ ስሙን ለውጦ አተት (አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት) የሚል የብዕር ስም ያገኘበት ጊዜ ነበር፡፡ (ዘመን አይለውጠው ነገር የለምና ሁሉን ተቀብሎ ተመስጌን ማለት ደግ ነው!)
አጐበር አከፋፋዩ ነጋዴ፣ ሶስት መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (NGO/ አንዳንዶች “Nothing Goes On” ይሉታል ሲተረጉሙት) ሠራተኞች ጭነው ወደ ዋናው የሥራ ቦታቸው (እናት-ክፍላቸው) እየሄዱ ነው፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ተጠሪ ከመኪናው ጋቢና ተቀምጠዋል፡፡
“ሥራ እንዴት ነው?” ይሏቸዋል ነጋዴውን፡፡
“መልካም ነው… መቼም እንፍጨረጨራለን!” አሉ፡፡
መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት (መያድ) ተጠሪ በሆዳቸው፤ “ቅቤ ነጋዴ ድርቅ ያወራል” አሉና ተረቱ፡፡
“አጐበራችንን በጥሩ ሁኔታ የምናከፋፍል ይመስልዎታል?”
“አይጠራጠሩ! ሆኖም ይሄ ህዝብ አይታመንም”
“ለምን?”
“መግዛቱን ይገዛል - ግን ደግሞ አጐበሩን ከወሰደ በኋላ፤ ግማሹ የዝናብ ልብስ ያደርገዋል፡፡ ግማሹ የእህል መቋጠሪያ ያደርገዋል፡፡ ከፊሉ ደግሞ አንገት ልብስ ያደርገዋል፡፡ ስለዚህ እናንተ የማስተማር ኃላፊነት አለባችሁ!” ይህንንና ሌላ ሥራውን የሚመለከቱ ጉዳዮች እያወጉ ሲጓዙ፤ በድንገት አንድ ወይፈን መንገዱ ውስጥ ገባ፡፡ ነጋዴው መኪናውን አቁመው ወይፈኑን ለማዳን አልቻሉም፡፡ ገጩት፡፡ ወደቀ፡፡ እሳቸው መኪናውን ከተገጨው ወይፈን አቅጣጫ ቀየስ አድርገው መንገዳቸውን ቀጠሉ፡፡ መንግሥታዊ ያልሆነው ድርጅት ተጠሪ ተደናገጡ፡፡ ወይፈኑ አሳዘናቸው፡፡ ወይፈኑን “ነገ አሳድጌ አርስበታለሁ” ብሎ በመከራ ተስፋውን ያቆየው ገበሬ ታሰባቸው፡፡ ስለዚህ፤
“ምነው? ወዴት ነው የሚሄዱት? አንድ እንስሳ ገጭተናልኮ’፤ ዝም ብለን መሄድ አንችለም፡፡ የወይፈኑን ባለቤት አግኝተን ማነጋገርና ይቅርታ መጠየቅ፣ ካሣም እፈልጋለሁ ካለ መክፈል አለብን!” አሉ፡፡
ነጋዴውም፤
“ዝም ብለን እንቀጥል! የእዚህ አገር ሰው ካልገጩለት አርዶ አይበላም!” አሉ፡፡
*   *   *
የሀገራችን ሰው መስዋዕትነት ካልከፈሉለት አይነቃቃም፤ እንደማለት ነው!
ሌላው ካልሞተለት አይነሳም! ልብ ካልሰጡት ልብ አይገዛም! ይሄ ዕውነት ሊሆን ይችላል፡፡ (ይሄ ግን ወይፈኑን እየገጩ አይደለም) በተጀመረ መንገድ ለመሄድ ግን አንደኛ ነው! መፍሰስ ከጀመረ ወንዝ ጋር መፍሰስ ይወዳል! በዚያ መንገድ ከሄደ በኋላ ደግሞ ሹሙኝ… ሸልሙኝ ካሱኝ… “ማን አለ እንደ እኔ ላገሩ የሞተ” ለማለት ቀዳሚ ነው! ይሄም ባልከፋ፤ … ግን ችግሩ ፈጦ እሚመጣው “ካሣው የዕድሜ ልክ ይሁንልኝ” ሲል ነው፡፡ “ሁሌ ተጠቃሚ ልሁን” ሲል ነው፡፡ ዛሬም የሚከተለውን ዕውነት መድገም ተገቢ ስለሆነ ደግመን እንበለው፡- He mistakes longevity for eternity (‘ረዥም ዕድሜን ከዘለዓለማዊነት ያምታታል’ እንደማለት ነው)
ዛሬ በርካታ የውጪ አገር ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ እየመጡ ነው፡፡ እየተመሙ ነው፡፡ እንግዳ ተቀባዩ የኢትዮጵያ ህዝብም አስፋልት ሙሉ እየጐረፈ እየተቀበላቸው፤ እያስተናገዳቸውም ነው፡፡ ይሄ የፍቅር፣ የመተሳሰብ፣ የናፍቆት፣ የስስት ፍሬ ነው፡፡ ያም ሆኖ እዚህ ጋ ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮችን ወይም ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡
1ኛ) የሞቀ አቀባበል ማድረጉ (ለስንቱ አቀባበል ማድረግ እንደሚቻል፣ ባንረዳም) ለሞቀ ጥያቄው መልስ የሚሰጡ ተቆርቋሪዎች አገኘሁ የሚል ተስፋ ሰንቆ መሆኑን አለመዘንጋት ነው፡፡ ስለዚህም “እጃችሁ ከምን?” ብሎ የልቡን እንደሚጠይቅ አለመርሳት ነው!
2ኛ) ሰው ሆኖ ሲያወድሱት ደስና ሞቅ የማይለው የለምና፣ ደስታው ወደ አረፋዊ መነፋፋት (Infatuation)፣ አልፎ ተርፎም ወደ ተዓብዮ እና እኔ ብቻ ነኝ ቁልፉ (Ego-Centerism) እንዳይለወጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡
አንድ የማይታወቅ ገጣሚ የፃፈው ስለ“ዝና” የሚያወሳ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
Fame
Fame is a bee
It has a song
It has a sting
O God! It also sah a wing!
(ዝና ንብኮ ነው
ይዘፍናል ዜማ አለው
መዋጊያ እሾህ አለው
እግዜር ይሰውረን! - ይበርራል
ክንፍ አለው!!)
ልብ ያለው ልብ ይበል!!
“ነይ ነይ ክብረት - ዓለም
ነይ ነይ ክብረት - ዓለም
የጀመረሽ እንጂ የጨረሰሽ የለም!”
…የሚለውን የዘፈን ግጥምም አንርሳ!
አዲስ ዘመን ዋዜማ ላይ ነን! አገራችን፤ አዲስ ሰው፣ አዲስ ባለ ራዕይ፣ አዲስ ተጓዥ ትሻለች፡፡ ጥያቄዎቿን እንመልስላት! ከድህነቷ እንታደጋት! ብንታደል የጥንቱ የተማሪዎች እንቅስቃሴ መንፈስ ቢፈጠር፣ ከዚያም ቢረቅና ቢራቀቅ መልካም ነው! ሁላችንም አገሬ! አገሬ! የምንልበት፣ ተቀራርቦና ተሳስቦ በአንድነት የመጓዝ ትግል ሊፈጠር የግድ ይላል፡፡ አይቀሬ መሆኑን እናውቃለን፡፡ ሆኖም ጊዜውን አሳጥሮ በኅብር (in harmony) መራመድ እጅግ አስፈላጊ ነው!
ሁሉም ነገር መስዋዕትነት ይጠይቃል፡፡ ሰው ጠያቂ ይፈልጋል፡፡ ሀቀኛ ተሟጋች ይፈልጋል፡፡ “የሀገሬ ዋና ዋና ችግሮች የቶቹ ናቸው?” ብሎ የሚጠይቅ ልባም ልጅ ይፈልጋል፡፡ ያ ማለት ግን መስዋዕትነቱ ሌላ ጥፋት በመፈፀም የሚመጣ መሆን የለበትም፡፡ ህዝብን የመናቅና የትም አይደርስም ከሚል ንቀትም የሚመነጭ መሆን የለበትም፡፡ “እኔ አውቅለታለሁ” ማለት የተዓብዮ ሁለ ተዓብዮ (The Peak of arrogance) ይሆናል። ከላይ የተረክናቸው ሹፌር፤ “የእዚህ አገር ሰው ካልገጩለት አርዶ አይበላም” ማለት ይሄን ሁሉ ያካተታል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት! 

(2010 እና 2011)            “ግማሹን ዓመት በጭንቀት፣ ግማሹን ዓመት በተስፋ”
               አቶ ተሻለ ሠብሮ (የኢራፓ ሊቀ መንበር)


     ኢትዮጵያውያን ዓመቱን ያሳለፉት በመስቀለኛ መንገድ ላይ ሆነው ነው፡፡ በአንድ በኩል ስጋት ያየለበት፣ በሌላ በኩል ደግሞ የተስፋ ጭላንጭል የታየበት ዓመት ነበር፡፡ በርካቶች ግማሹን ዓመት በጭንቀት፣ ግማሹን ዓመት በተስፋ ነው ያሳለፉት። ብጥብጦች የተስፋፉበት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀበት ዓመት ነው፡፡ የተፈጠሩ አሳሳቢ ሁኔታዎች መንግስትን ያስጨነቁት ሲሆን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝም በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ተገደዋል፡፡
አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ደግሞ ማንም ባልገመተውና ባልጠበቀው መልኩ በርካታ ተስፋ ሰጪ ምላሾች መስጠታቸው ይታወቃል። የፖለቲካ እስረኞች መፈታት፣ የተሰደዱ ዜጎች ወደ ሃገር ቤት መመለስ፣ ህጐችን ለማሻሻል ጥረት መጀመሩ----ትልቅ የለውጥ ተስፋ ነው፡፡ እኛ ለብሔራዊ መግባባትና ለእርቀ ሠላም ብዙ ጮኸናል፡፡ አሁንም ይህ በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲፈፀም እንጮሃለን፡፡
በ2010 ዓ.ም ትልቅ ታሪክ ተሠርቶ አልፏል። ሁሉም በየራሱ የወረወራቸውን ጠጠሮች መደልደልና ማስተካከል ደግሞ ቀጣዩ የቤት ሥራ ነው፡፡ በ2011 ዓ.ም ቢያንስ ሦስት ጉዳዮች እንዲሆኑ እንመኛለን፡፡ አንደኛው፤ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በመጀመሪያው ሩብ ዓመት፣ ራሳችንን ፈትሸን መሰባሰብ አለብን፤ ከ60 እና 70 ፓርቲዎች ወደ 10 እና 15 ዝቅ እንድንል መስራት ይኖርብናል። ሁለተኛው፤ በዶ/ር ዐቢይ የተጀመረው ለውጥ ወደ ስር ነቀል ለውጥ እንዲሸጋገር እንጠብቃለን። የምንታገለው ለትራንስፎርሜሸን ሳይሆን ለሪፎርሜሽን ነው፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ ከአየር ላይ ወርዶ ተቋማዊ ሆኖ፣ መሬት መርገጥ አለበት። ሦስተኛ፤ ለውጡ አዲስ ሥርዓት ማምጣት አለበት፡፡ ይሄ የሚመጣው ደግሞ በምርጫ ነው። ስለዚህ በምርጫው ጉዳይ በ2011  ስር ነቀል ለውጦች እንዲመጡ መሥራት ያስፈልጋል። ሁሉም አካላት ለለውጡ ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው፡፡ በአዲሱ ዓመት ህዝባችን ከስጋትና ከመስቀለኛ መንገድ ወጥቶ ወደ አስተማማኝ ሁኔታ እንዲሸጋገር ምኞቴ ነው፡፡


------------               “አመራሮቻችን ከእስር የተለቀቁበት ዓመት ነበር”
                 አቶ ሙላቱ ገመቹ (የኦፌኮ ም/ሊቀመንበር


    የታሰሩ አመራሮቻችንና አባሎቻችን ከእስር የተለቀቁበት ዓመት ነበር - 2010 ዓ.ም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በ2009 ሃገሪቱ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ነበረች፡፡
ከ2010 አጋማሽ በኋላ ግን በሃገሪቱ ውስጥ ጥሩ ለውጥ እየተካሄደ ነው፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ለዴሞክራሲ ቀና መሆናቸውን እያሳዩን ነው፡፡ ይህም ሃገሪቱ ተረጋግታ ህዝብ የሚያማክል መንግስት ማቋቋም እንደምንችል ተስፋ ሰጪ ነው። የተሻለውን ለውጥም በተስፋ እንድንጠባበቅ ያስቻሉ የለውጦች ጅማሮን ያየንበት ዓመት ነበር።
ቀጣዩ ዓመት ደግሞ ለለውጡ ተቋማዊነትና መሬት መያዝ የሚያስፈልጉ የህግ ማዕቀፎች የሚፈተሹበት፣ የሚዘጋጁበት፣ የምርጫ ቦርድ የሚቀየርበት፣ የፍትህ ተቋማት ሕገ መንግስቱን የሚያስከብሩ ብቻ የሚሆኑበት፣ ነፃ የፍትህ ሥርዓት የሚሰፍንበት ይሆናል ብለን እናስባለን፡፡ እኛም ጽ/ቤቶቻችንን በየቦታው ከፍተን፣ ህዝብን የምናደራጅበት ሁኔታ ይፈጠራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡


-----------  


             “አዲሱ ዓመት በይቅር ባይነት ወደ ፍቅር የምንሸጋገርበት ነው”
               የሸዋስ አሰፋ (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)


     ያለፉት ሦስት ዓመታት ሁላችንም እንደምናውቀው፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ ለመሻገር እልህ አስጨራሽ ትግል ያደረገበት ነበር፡፡ 2010 ደግሞ በትግሉ የአገዛዙን ጉልበት የሰበረበት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እስከ ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ መሪውን መርጦ አያውቅም፡፡ የትግሉ መጨረሻም በመረጥኩት መሪ ልተዳደር፤ እውነተኛ የስልጣን ባለቤት ልሁን የሚል ነው፡፡ በገዥው ፓርቲ በኩል የለውጥ ሃይሎች የወጡበት ዓመት ነበር፡፡ እነዚህ የለውጥ ኃይሎች ከህዝቡ፣ ከተቃዋሚዎች፣ ከአክቲቪስቶች ጋር እጅና ጓንት ሆነው፣ ለለውጥ የሰሩበት ታሪካዊ ሁነትን ያየንበት ዓመት ነበር ብሎ መናገር ይቻላል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለማርያም ደሣለኝ፤ በፈቃዳቸው፣ በህዝብ ጫና ስልጣን የለቀቁበት፣ አዲስ የለውጥ አመራር ወደ መንበሩ የመጣበት ዓመት ነበር፡፡ ምናልባትም ከ1966 በኋላ ጠ/ሚኒስትሩም የመንግስት ባለስልጣናትም ቶሎ ቶሎ የተለዋወጡበት፣ ዘርፈ ብዙ ለውጦች የታዩበት ዓመት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ፍቅርንና ይቅርታን የሚሰብክ፣ ለዜጐች የሚጨነቅ መሪ፤ ከዚያው ከኢህአዴግ ውስጥ የፈለቀበት ዓመት ነበር፡፡ በፊት መንግስት ክብር የነሳቸውን በተለያዩ አለማት የሚኖሩ ዜጐችን ክብር በመስጠት፣ ወደ ሃገራቸው እንዲመለሱ የተደረገበት፣ በርካቶች ከእስር የተፈቱበት ዓመት ነው፡፡
ይሄ ለውጥ የሁሉም ነው፡፡ የእከሌ ብቻ ነው ብሎ መናገር አይቻልም፡፡ በቀጣዩ አዲስ ዓመት ይሄን ለውጥ ተቋማዊ ቅርፅ ለማስያዝ መሠራት አለበት። አሁን ያለነው የለውጥና የሽግግር ሂደት ላይ ነው። ይሄ አስተማማኝ የሚሆነው በቦታው ትክክለኛ ሰው ሲቀመጥ፣ መዋቅራዊ ለውጥ ሲደረግና ለውጡ ተቋማዊ ሆኖ፣ በህግ ሲታሰር ነው፡፡ አዋጆችን፣ ህጐችን ማሻሻልና ሁሉም የተስማማባቸው፣ ለዲሞክራሲው አጋዥ የሆኑ ሕጐች ሲወጡ ነው ለውጡ አስተማማኝ የሚሆነው፡፡
ከዚህ አንፃር ቀጣዩ ዓመት ይሄን ተቋማዊ የምናደርግበት፣ ትክክለኛ ምርጫ ቦርድ፣ ትክክለኛ የፍትህ ሥርዓት፣ ነፃና ገለልተኛ የሚዲያ ሥርዓት የምንገነባበት ነው፡፡ የለውጡንና የሽግግሩን ሁለተኛ እርከን የምንፈፅምበት ዓመት ይሆናል ብለን ነው ተስፋ የምናደርገው። ህዝቡ ለውጥ ተደርጓል ብሎ ፊቱን ወደ ልማት የሚያዞረው፣ በድምፁ የመረጠውን መሪ ስልጣን ላይ ሲያስቀምጥ ብቻ ነው፡፡ እስከዚያው ለውጡን አሁን እንደምናየው፣ በዓይነቁራኛ እየተመለከተ ነው የሚቀጥለው፡፡ በአዲሱ ዓመት ደግሞ በይቅር ባይነት ወደ ፍቅር የምንሸጋገርበት፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናሰፍንበት ዓመት ይሁንልን የሚለው መልካም ምኞቴ ነው፡፡


-------------


                “ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የተስፋ ዓመት ነው”
                  ዶ/ር በዛብህ ደምሌ (የመኢአድ ፕሬዚደንት)


     2010 ዓ.ም ብዙ የተስፋ ጭላንጭል የታየበት ዓመት ነበር፡፡ ድርጅታችን ላለፉት 26 ዓመታት ኢትዮጵያዊነትን፣ አንድነትን አቀንቅኗል፡፡ በዘርና በቋንቋ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ህዝብ አይበጅም በሚል ብዙ ትግል አካሂዷል፡፡ የትግላችን ፍሬ አሁን እየታየ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ስልጣን ከያዙ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን ደጋግመው እያቀነቀኑ ነው፡፡ ማንም ኢትዮጵያዊ መብቱ እየተጠበቀ፣ በፈለገው አካባቢ መኖር እንደሚችል በየጊዜው እየተናገሩ ነው፡፡ እኚህ ጠ/ሚኒስትር ስልጣን እንደያዙ ያለ አግባብ የታሠሩ ፖለቲከኞችን እንዳሉ አምነው፣ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን እንዲፈቱ አድርገዋል፡፡ ይሄ በዚህች ሃገር ፖለቲካ ውስጥ ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ጅማሮ ነው፡፡ እኛ በግለሰብና በህብረተሰብ መብት የምናምን ነን፡፡ ይሄን እምነታችንን የሚያጠናክር እንቅስቃሴ ነው። እርግጥ ነው አሁንም የሚቀሩ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ ለምሳሌ፡- የሁሉም የለውጥ ግብ ማጠንጠኛ ለሆነው የምርጫ ጉዳይ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡ በቀጣይ ኢህአዴግ ከሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመሆን የምርጫ ቦርዱ በሚቀየርበትና እንደገና በሚደራጅበት ሁኔታ ላይ መስራት አለበት፡፡ የሰብአዊ መብት አከባበር በነፃና ገለልተኛ ተቋም መፈተሽ አለበት። አሁን ተቋቁመው ያሉ መሰል ተቋማት ባለፉት 25 ዓመታት፣ለህዝቡ የሰሩት ምንም ነገር የለም። የመንግስት ውግንና የነበራቸው ናቸው፡፡ ያለፈው ዓመት ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በታሪካዊነት የሚጠቀስ ነው - ልክ እንደ 1997፡፡
በቀጣይ ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብ ለራሱ የተሻለውን ነገር ያመጣል የሚል እምነት አለኝ።  እኛም ባለን አቅም ሁሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ተግተን እንሰራለን፡፡ በሠላም ጉዳይ በከፍተኛ ደረጃ መሰራት አለበት፡፡ 2011 ዓ.ም ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የተስፋ ዓመት ነው፡፡ ወደተሻለ ለውጥ የምንሸጋገርበት ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ አዲሱ ዓመት መንግስት የበለጠ ለዲሞክራሲ የሚሰራበት እንዲሆን እመኛለሁ፡፡


------------------


                 “የበለጠ የመግባባት ዓመት እንዲሆንልን እመኛለሁ”
                   ዶ/ር ጫኔ ከበደ (የኢዴፓ ፕሬዚደንት)

     ያለፈው 2010 ዓ.ም ሃገሪቱ ካለመረጋጋት ወደ አንፃራዊ መረጋጋት የተሸጋገረችበት ዓመት ነው። በተለይ አዲስ ጠ/ሚኒስትር ያገኘንበት ዓመት ነበር። አዲሱ ጠ/ሚኒስትር ደግሞ በይቅርታ፣ በፍቅርና በመደመር መርህ ብዙ ገንቢ ሥራዎች አከናውነዋል።
ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊነትን አግዝፈው የተናገሩበት፣ በህዝቡ ላይ ለተሠሩ በደሎችም ይቅርታ የጠየቁበት ዓመት ነበር። ኢህአዴግ ከመነሻው የነበረበትን ስህተት አርሞ፣ በአዲስ አሰራር ለህዝቡ ጥያቄ ምላሽ እየሠጠ፣ ለለውጥ የተዘጋጀበት ዓመት ሆኖ ነው ያለፈው። ይህ ሁኔታም ለኢትዮጵያ ህዝብ እርካታ የሰጠና አብዛኛው አካባቢ የተረጋጋበት ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር በ2010 የሄድንበት ርቀት፣ ለህዝቡ ትንሽም ቢሆን እፎይታ የሰጠ ነው፡፡  
ኢዴፓ እንደ ድርጅት ባለፉት አመታት፣ ለሃገሪቱ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልጋል ሲል ነበር የኖረው። ይህ ብሔራዊ መግባባት በ2010 በከፊልም ቢሆን ተጀምሯል፡፡ ከዚህ አንፃር አኛም በዓመቱ የተወሰኑ ፕሮግራሞቻችን በተለይ የብሔራዊ መግባባት አጀንዳችን ወደ ተግባር የወረደበት ዓመት ነበር። የፖለቲካ ድርጅቶችም ተቀራርበው እንዲነጋገሩ ለውጡ እድል በመፍጠሩ፣ ዳርና ዳር ቆመን የነበርን የፖለቲካ ኃይሎች፣ ለጋራ ምክክር መቀመጥ የቻልንበት ዓመት ነበር፡፡
በቀጣይ 2011 ዓ.ም ደግሞ የሠላም፣ የአንድነት፣ የፍቅር ሂደቱ ወደ መሬት ወርዶ፣ የሃገሪቱ አጠቃላይ የአሠራር ሂደት የሚለወጥበት መሆን ይገባዋል፡፡ ለዴሞክራሲ እንቅፋት የሆኑ ሕጐች፣ አዋጆች እንዲሁም ፖሊሲዎች የሚሻሻሉበት ሁኔታም ይፈጠራል የሚል ተስፋ ነው ያለን፡፡
ከምንም በላይ የምርጫ ህጉና የምርጫ ሥርዓቱ ከተስተካከለና የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉን አሳታፊ ሆኖ ከተዋቀረ፣ በ2012 የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ ያለ ምንም እንከን የሚፈፀምበት ሂደት ይኖራል፡፡ ይሄ ስራ በሰፊው የሚሰራበት ዓመት ሊሆን ይገባል። ሌሎች የዴሞክራሲ ተቋማት፣ የፍትህ አካላት ነፃና ገለልተኛ ሆነው መደራጀት አለባቸው፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይሄ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ፣ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ሂደቱን በቅርበት መከታተል ይገባዋል፡፡ እርቅና ብሔራዊ መግባባትም መፈፀም አለበት፡፡ 2011 ዓ.ም የበለጠ የመግባባት ዓመት እንዲሆንልንም እመኛለሁ፡፡

 በቀጣዩ ጥቅምት 13 ቀን 2011 በሂልተን ሆቴል ለሚካሄደው “ለዛ” የአድማጮች ምርጫ ሽልማት ለመጨረሻ ዙር ያለፉ ምርጥ አምስቶች ታወቁ፡፡ በዚህም መሰረት በየአመቱ ምርጥ ፊልም ዘርፍ “ወደኋላ”፣ “እርቅይሁን”፣ “በእናት መንገድ”፣ “ትህትናና” “ድንግሉ” ሲያልፉ በምርጥ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም ዘርፍ ደግሞ “ምን ልታዘዝ”፣ “ዘመን”፣ “ሰንሰለት”፣ “ደርሶ መልስ” እና “ቤቶች” ተመርጠዋል፡፡ በአመቱ ምርጥ ተዋናይ ዘርፍ አለባቸው መኮንን በ“ትህትና”፣ እንግዳሰው ሀብቴ በ“ሰራችልኝ”፣ ሔኖክ ወንድሙ በ“የፈጣሪ ጊዜ”፣ አለማየሁ ታደሰ በ“ድንግሉ” እና ኤርሚያስ ታደሰ በ“ታላቅ ቅናሽ” ማለፋቸውን የሽልማቱ አዘጋጅ ለዛ ሾው አስታውቋል፡፡
በየዓመቱ ምርጥ ተዋናይት ዘርፍ አዚዛ አህመድ በ“ትህትና” ዕፀህይወት አበበ በ“አስነኪኝ”፣ ሊዲያ ተስፋዬ በ“ወደኋላ”፣ አዲስአለም ጌታነህ በ“ሀ እና ለ 2”፣ እንዲሁም ፍናን ህድሩ በ“እርቅ ይሁን” ተመርጠዋል፡፡ በምርጥ የሙዚቃ ቪዲዮ ዘርፍም “የቤት ሥራ”፣ “የመጀመሪያዬ ነው”፣ የቴዲዮ “ሎኦ ሎኦ” “ትርታዬ”፣ የአቢ ላቀው “ሆዴን ሰው ራበው”ና የሄለን በርሄ “ፊት አውራሪ” ምርጥ አምስት ውስጥ ተቀላቅለዋል፡፡
በየዓመቱ ምርጥ አልበም ዘርፍ፣ የናቲማን ቁጥር 2 አልበም፣ የእሱባለው ይታዬው “ትርታዬ” የሮፍናን “ነፀብራቅ”፣ የብስራት ሱራፌል “ቃል በቃል”፣ የሄለን በርሄ “እስኪ ልየው”ና የጃኖ ባንድ “ለራስህ ነው” ሲያልፉ በምርጥ ነጠላ ዜማ ዘርፍ የሮፍናን “ጨረቃን” የያሬድ ነጉ “ዘለላዬ”፣ የአቡሽ ዘለቀና ቤኪግዕዝ “ማሎ ኢንተሎ”፣ የብስራት ሱራፌል “የቤት ሥራ” እና የናቲ ማን “የመጀመሪያዬ ነው” ወደመጨረሻው ዙር አልፈዋል፡፡
የመጨረሻውን ተሸላሚ ለመምረጥ በwww.lezashow.com ገብተው የሚያደንቁትን አርቲስት፣ ፊልም፣ ሙዚቃ ወይም ቪዲዮ መምረጥ እንዲችሉ የለዛ የሬዲዩ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ብርሃኑ ድጋፌ ጥሪ አቅርቧል፡፡

Page 9 of 409