Administrator

Administrator

በኢትዮጵያ የብራዚል ኤምባሲ ያዘጋጀው የፊልም ፌስቲቫል የፊታችን ሰኞ እንደሚጀምር ኤምባሲው አስታወቀ፡፡ ቦሌ በሚገኘው የብራዚል ኤምባሲ ለሕዝብ ከሚቀርቡት የብራዚል ፊልሞች መካከል ሶስቱ አስቂኝ ሦስቱ ድራማ ናቸው፡፡ ፊልሞቹ በየእለቱ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚታዩ ሲሆን ለአንድ ሳምንት እንደሚቆዩ ታውቋል፡፡ የመግቢያ ዋጋ በነፃ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካውን አንጋፋ መሪ ኔልሰን ማንዴላ ሽጉጥ አስመልክቶ እየተሰራ ያለው ፊቸር ዶክመንተሪ ፊልም በኢትዮጵያም ሊቀረጽ ነው፡፡ የእንግሊዝ “ቢር ኸርት ሊሚትድ” እና የደቡብ አፍሪካ DV8 ኩባንያዎች በአሜሪካ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በእንግሊዝ ቀረፃውን ያከናወኑ ሲሆን በኢትዮጵያ “ታይኩን ሪል ስቴት” በተባለ ኩባንያ አማካይነት የአሰሳ ጥናት ተጀምሮ ፊልሙ ሊቀረጽ እንደሆነ በኢትዮጵያ ለፊልሙ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎችን የሚያስተባብረው ርእዮት ኪነጥበባት ፕሮሞሽን በተለይ ለአዲስ አድማስ አስታውቋል፡፡ ኔልሰን ማንዴላ በትጥቅ ትግል ወቅት ኮለኔል ከነበሩት ኢትዮጵያዊ ጀነራል ታደሰ ብሩ ሽጉጥ ተበርክቶላቸው እንደጠፋና ቤት ቢፈርስም ሽጉጡ አለመገኘቱ ይታወቃል፡፡

\ኢንቨስተርና ነጋዴ ሁላ! ተቃዋሚ ፓርቲ መስርት ተብለሃል። በማን? በኢህአዴግ ነፃ ገበያና “ዲሞክራሲ”፡ የህልውና ጥያቄ ሲሆኑበት ኢህአዴግ እስከ ዛሬ፤ ነፃ ገበያን እና የአሜሪካ ዲሞክራሲን ላለማጣጣል ይጠነቀቅ ነበር። በተለይ ከ1993 ዓ.ም ተሃድሶ ወዲህ፣ አውሮፓንና አሜሪካን በአርአያነት ይጠቅስ ነበር። ገናናነትና “ሶሻሊዝም”፡ የማይጥላቸው አባዜ ሲሆኑበት የኢህአዴግ መፅሄት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚን በግላጭ እያንቋሸሸ ፅፏል። የነአሜሪካን ዲሞክራሲ በማብጠልጠል፤ ኢህአዴግ በአለም ወደር እንደሌለው ገልጿል።

በአንድ በኩል፤ “ንብረት እየዘረፈ የሚያከፋፍል ቀማኛ”…. በሌላ በኩል ደግሞ “የንብረት መብትን የሚያስከብር ፖሊስ” መሆን ይቻላል? ሁለቱ ምርጫዎች ተቃራኒዎች ናቸው - የድህነትና የብልፅግና፣ የንጥቂያና የመብት፣ ወይም የሶሻሊዝምና የካፒታሊዝም ጎዳናዎች። በአንድ በኩል፣ “ያለ ፉክክር በአፈና ስልጣን የሚቆጣጠር ገናና ፓርቲ”… በሌላ በኩል ደግሞ “የአሜሪካና የአውሮፓ የዲሞክራሲ ስርዓቶችን የሚያደንቅ ባለራዕይ ፓርቲ” መሆንስ ይቻላል? እነዚህም ተቃራኒ ጎዳናዎች ናቸው - አንደኛው የውርደት፣ የመጠፋፋትና የውድቀት፣ ሌላኛው ደግሞ የመከባበር፣ የሰላምና የስኬት ጎዳና። ኢህአዴግ፤ ላለፉት አመታት መከራውን ሲያይ የቆየው እነዚህን ተቃራኒ ምርጫዎች ወይም ጎዳናዎች አቀላቅሎና አዳቅሎ ለመጓዝ ነው።

አብዮታዊ ዲሞክራሲ በተፈጥሮው፤ “ነፃነትንና መብትን ከአፈናና ከዝርፊያ” ጋር ያደባለቀ ቅይጥ ፖለቲካ አይደል? ግን ምን ዋጋ አለው? “ሁለት ወዶ” አይሆን! እንደ ህዝቡ ስሜትና እንደ አለማቀፉ አዝማሚያ፣ አንዳንዴ ወደ ግራ እየሸመጠጠ፣ አንዳንዴ እየተመለሰ፤ አንዴ የነፃ ገበያና የዲሞክራሲ “ጭንብል” እያጠለቀ፣ ሲያገረሽበት ደግሞ የሶሻሊዝምና የገናናነት ጭምብል እየለበሰ ለመጓዝ ሲሞክር… በተቃራኒ አቅጣጫዎች ተወጥሮ በጭንቀት ይሰቃያል። የኢህአዴግ መፅሄት “አዲስ ራዕይ” የቅርብ ጊዜ እትም ሲነበብ ግን፣ ፓርቲው በነፃ ገበያና በዲሞክራሲ ጭንብል ተሰላችቶ፣ ወደ ድሮው የሶሻሊዝም ፍቅር ጭልጥ ብሎ መግባት ያማረው ይመስላል። ይሄ አዲስ እና አደገኛ ነገር ነው።

ሳይረፍድበት ሰከን ብሎ፣ “ነፃ ገበያና ዲሞክራሲ” የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን እንደገና ካልተገነዘበ፤ እያንቋሸሻቸው የሚቀጥል ከሆነ፣ ጦሱ ያስፈራል። ፓርቲውና አገሪቱ በቀላሉ ከማይወጡበት የትርምስ አዘቅት ውስጥ ይዘፈቃሉ። እርግጥ ነው፤ ኢህአዴግ እንደብዙዎቹ የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎች፣ መቼም ቢሆን ለነፃ ገበያ ፍቅር ኖሮት አያውቅም። በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና ፓርቲዎች በምርጫ የሚፎካከሩበት “የሊበራል ዲሞክራሲ” ስርዓት ለኢህአዴግ አይጥመውም። ኢህአዴግኮ፣ እስከ 1982 ዓ.ም ድረስ፤ “እኔን የሚስተካከል ኮሙኒስት (ሶሻሊስት) ይምጣ!” ሲል የነበረ ድርጅት ነው። ለነገሩ ሌሎቹ አንጋፋ ፓርቲዎችም ከዚህ የተለየ ባህርይ አልነበራቸውም። በደርግ (በኢሰፓ)፣ በኢህአፓ፣ በመኢሶን፣ በኢህአዴግና በሌሎች የአገሪቱ አንጋፋ ፓርቲዎች መካከል የነበረው ፀብ፤ “ሃቀኛ ኮሙኒስት እኔ ነኝ፤ እውነተኛው ሶሻሊስት እኔ ነኝ” የሚል ነበር። ደግነቱ፤ ፓርቲዎቹ ያኔ በጀመሩት የጥፋት አቅጣጫ እስከመጨረሻው ሊዘልቁበት አልቻሉም። ደርግ በአገሪቱ ውስጥ ያሰፈነውን የሶሻሊዝም ስርዓት ይዞ መቀጠል አቅቶት በ82 ዓ.ም ቅይጥ ኢኮኖሚን ሲያውጅ፤ ኢሰፓንም ለማፍረስ አቅዶ አልነበር? ልክ እንደዚያው፤ ኢህአዴግም የድሮ ሃሳቡን የሙጢኝ ብሎ “ሶሻሊዝም” እያለ ሊቀጥል አልቻለም።

ለምን ብለን ብንጠይቅ ሁለት ምክንያቶችን እናገኛለኝ። ደርግ የተዳከመበትና ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ የተቃረበበት ወቅት ላይ ሆናችሁ አስቡት። አንደኛው ምክንያት፤ ደርግ የተዳከመበትና ኢህአዴግ ስልጣን ለመያዝ የተቃረበበት ወቅት፤ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በሶሻሊዝም ተንኮታኩቶ፣ የዜጎች ድህነት የመጨረሻ ደረጃ ላይ የደረሰበት ጊዜ መሆኑ ነው። መንግስት ኢኮኖሚውን በሙሉ እየተቆጣጠረና እየዘረፈ፤ ሰዎች ህይወታቸውን ለማሻሻልና ሃብት ለማፍራት የሚያደርጉት ጥረት እንደጥፋት እየተቆጠረ… እንዴት ኢኮኖሚው አይንኮታኮት? “እንኳን ዘንቦብሽ…” ሆነና፤ ኢትዮጵያ ማለት፣ በረሃብ መቶ ሺ ሰዎች የሚረግፉባት አገር ሆና አረፈችው።

ደህይቶ እርቃኑን በቀረ አገር ውስጥ፣ የዝርፊያ ስርዓት ይዞ ለመቀጠል መፎከርና መፍጨርጨር ከእብደት የማይተናነስ እንደሆነ በግልፅ መታየት ጀመረ። የሃብት ሽታ በጠፋበት ዘመን፣ “የሃብት ክፍፍል” እያሉ ሶሻሊዝምን ማነብነብ፤ ክፋት ብቻ ሳይሆን ሞኝነትም ጭምር ይሆናል። ዝርፊያን እንደ ቅዱስ ተግባር ብንቀበለው እንኳ፣ ከአንድ ሰው ሃብት ዘርፎ ለሌላው መስጠት የሚቻለውኮ፤ በቅድሚያ ሃብት የሚፈጥሩ ሰዎች ሲኖሩ ነው። በያኔው ዘመን ግን፣ ሃብት ፈጣሪዎች ድራሻቸው ጠፍቷል። በአንድ ክረምት ድርቅ ሚሊዮን ሰዎች የሞቱባት ኢትዮጵያ፣ ከአመት አመት በሚባባስ ድህነት እየተዋጠች የነበረችበት ወቅት ነው። ሁለተኛው ምክንያት፣ በ60ዎቹ ዓ.ም የአገራችንን ተማሪዎች በስሜት እንዲጦዙ ያነሳሳቸው የኮሙኒዝም (የሶሻሊዝም) አስተሳሰብ፣ በ80ዎቹ ዓ.ም መባቻ ላይ በአለማቀፍ ደረጃ አከርካሪው መሰበሩ ነው። ዋነኛ አቀንቃኝ የነበሩ የሶቭየት ህብረትና የምስራቅ አውሮፓ ኮሙኒስት መንግስታት ፈራረሱ።

በእርግጥ “ለጭቁኖችና ለወዛደሩ ጥቅም!” በሚሉ ሰበቦች፣ ሰው እንደ መስዋእት በግ ለእርድ እንዲሰለፍ የሚያደርግ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ ተንኮታኮተ ማለት፣ ክፋት አበቃለት ማለት አይደለም። እያንዳንዱ ሰው ለራሱ እንዳያስብ፣ የራሱን ጥቅም መስዋእት እንዲያደርግና የሌሎችን ጥቅም እንዲያስቀድም የሚሰብኩ… ሰውን እንደ መስዋእት በግ የሚነዱ ሌሎች ኋላቀር አስተሳሰቦች ሞልተዋል። የጥፋት ሰባኪዎቹ፤ በዝርፊያም ሆነ በአፈና እያንዳንዱን ሰው በአጭር ለማስቀረት ያለሙ መሆናቸው ቢያመሳስላቸውም፣ የግለሰብን ነፃነትና መብት ለመርገጥ የሚያቀርቡት ማመካኛ ሰበባቸው ግን ይለያያል። አንዱ “ህዝብ ይቅደም!” ብሎ ሲጮህ፣ ሌላኛው “ኢትዮጵያ ትቅደም!” እያለ ፀብ ውስጥ ገብተው የዜጎችን ኑሮ ያምሳሉ - የሁሉም አውራ ለመሆን።

አንዱ “ሃይማኖት ትቅደም!” ሲል፣ ሌላኛው “ወግና ልማድ ይቅደም!” እያለ ሰውን ያሸብራሉ - በበላይነት ስልጣን ለመያዝ። አንዱ “አንድነት ይቅደም” ሲል፣ ሌላኛው “ብሄር ብሄረሰብ ይቅደም” እያለ አገሬውን በጦርነት ያተራምሳሉ - ገናና ሆኖ ለመውጣት። ከእነዚህ በርካታ ኋላቀር አስተሳሰቦችና ባህሎች መካከል አንዱ፤ ሌሎቹን ሁሉ ጠቅልሎ ወይም አሸንፎ በበላይነት ገናና ለመሆን ሲችል፤ ግርግሩና ውጥንቅጡ ቆሞ፣ አገሬው ሁሉ ፀጥ ረጭ ይላል። “ስርዓት ያለው አፈናና ዝርፊያ” ይሰፍናል። ገናና የሚሆን አስተሳሰብ ከሌለ ግን፣ “ስርዓት ያለው አምባገነንነት” ሊፈጠር አይችልም። ትርምስና ቀውስ ይነግሳል። እንግዲህ አስቡት! በርካታ የዝርፊያና የአፈና ኋላቀር ባህሎችን በአንድ ጥላ ስር ለማሰባሰብና በበላይነት እየመራ በቀላሉ አምባገነንነትን ለማስፈን በቂ ጉልበት የነበረው የኮሙኒዝም አስተሳሰብ ተንኮታኩቶ ሲወድቅ ወደቀ። እናም በቀላሉ አምባገነንነትን ማስፈን የሚቻልበት ጊዜ አበቃለት። ለምን ቢባል፤ ኋላቀር ባህሎችን አጠቃልሎ በበላይነት የሚመራ ርዕዮተ ዓለም (አስተሳሰብ) የሌለውና በጠመንጃ ላይ ብቻ የሚተማመን አምባገነን ስርዓት ብዙ እድሜ አይኖረውም። የተለያዩ ኋላቀር ባህሎችን በየፊናቸው የሚያቀነቅኑ የተለያዩ ቡድኖች፣ በመላ አገሪቱ ብቸኛ ዘራፊና ቀማኛ ሆነው ለመግነን ሲፋጩ እርስ በርስ እየተጋጩ ይጨፋጨፋሉ። በአገር አንድነት ስም “አገርህን አስቀድም” እያለ፣ አልያም በሃብት ልዩነት “ድሆችን አስቀድም” እያለ፤ በሃይማኖት ተከታይነት “አምልኮን አስቀድም” እያለ፣ አልያም በአካባቢ ተወላጅነት “ብሄር/ብሄረሰብን አስቀድም” እያለ፣ … በጭፍን ስሜት ሰዎችን እያቧደነ ስልጣን ለመቀራመት የሚፈልግ የአፈና ጥመኛና የዝርፊያ ሱሰኛ ሁሉ፤ የጥላቻ መርዝና የሞት ጥይት ያርከፈክፋል። የዩጎዝላቪያ፣ የሶማሊያ፣ የሴራሊዮን፣ የሩዋንዳ አይነት ውጥንቅጥና እልቂት ይፈጠራል። ኢህአዴግ፤ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ በተንኮታኮተበት ዘመን፣ “ከድሮው የኮሙኒዝም አስተሳሰቤ ፍንክች አልልም፤ የመጣው ይምጣ” ቢል ኖሮ፤ ውጤቱ ከእንዲህ አይነት ውጥንቅጥ የተለየ አይሆንም ነበር። ከደርግ አምባገነንነት ወደ ትርምስ ነበር የምንሸጋገረው። በቅርቡ የታተመው የኢህአዴግ መፅሄት (አዲስ ራዕይ) እንደሚለውም፤ ኢህአዴግ የድሮ ሃሳቦቹንና አሰራሮቹን ለመለወጥ የተገደደው፤ ያኔ የኢትዮጵያ ድህነት በተባባሰበትና በአለማቀፍ ደረጃ የኮሙኒዝም አስተሳሰብ በተፈረካከሰበት ጊዜ ነው። በአጭሩ፤ ኢህአዴግ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአገራችን አንጋፋ ፓርቲዎች በሙሉ አስተሳሰባቸውን ለመቀየር የተገፋፉት ከላይ በተጠቀሱት ከህልውና ጋር በተሳሰሩ ሁለት ምክንያቶች ነው። አንደኛ ነገር፣ በሶሻሊዝም ምክንያት ድህነትና ረሃብ ተባብሶ ሚሊዮን ሰዎች አልቀው በርካታ ሚሊዮኖች የሞት አፋፍ ላይ ስለደረሱ፤ በአብዛኛው ሰው ላይ የህልውና ጥያቄ ጥርሱን አግጥጦ መጣ። የሚዘረፍ ሃብት ተሟጦ ገዢዎችም ከህልውና ጥያቄ ጋር የተፋጠጡበት ጊዜ ነው።

ሁለተኛ ነገር፣ በየፊናቸው ብዙ መልክ ይዘው የተቀመጡ የአፈናና የዝርፊያ ኋላቀር ባህሎችን በአንድነት ጠቅልሎ በበላይነት ለመምራት ያገለግል የነበረው የኮሙኒዝም አስተሳሰብ፤ በአለማቀፍ ደረጃ ተቀባይነቱ ተሸርሽሮ ተንኮታኮተ። እናም፤ እንደ ቀድሞው ዘመን አምባገነንነትን ለማስፈን መሞከር ወደ ትርምስ የሚያመራ በመሆኑ፤ በሁሉም ሰው ላይ የህልውና ጥያቄ ተጋረጠበት - ገዢ ለመሆን በሚመኙ ቡድኖች ላይም ጭምር። የለየለት የረሃብ እልቂትና የመጠፋፋት ትርምስ ወዲያውኑ ባይፈጠር እንኳ፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር መከሰቱ አይቀርም። ለምን እንደሆነ ወደ በኋላ እናየዋለን። አሁንም ከአደጋው ብዙም አልራቅንምና። ደግነቱ የረሃብ እልቂትንና የመጠፋፋት ውጥንቅጥን በማስቀረት ህልውናን ለመጠበቅ የሚያስችል ብቻ ሳይሆን ለስልጣኔና ለብልፅግና የሚያበቃ ትክክለኛ አስተሳሰብ አልጠፋም - በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና ነፃ የገበያ ስርዓትን የሚያሰፍን የካፒታሊዝም አስተሳሰብ። ካፒታሊዝም፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ነፃነት የሰፈነበት ስርዓት ነው ማለት ይቻላል። በአንድ በኩል ኋላቀር የአፈና ባህሎችንና ጅምላ ጥላቻን (ለምሳሌ በሃይማኖትና በብሄረሰብ ተቧድኖ የመጠፋፋት ጭፍንነትን) ለመከላከል የሚያስችል የፖለቲካ ነፃነት አለ። እያንዳንዱ ሰው በራሱ አእምሮ የመጠቀምና ሃሳብ የመያዝ ነፃነቱ ተከብሮ፣ በፈቃደኝነት ብቻ ሃሳብ የሚለዋወጥበት ስርዓት ነው - በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተና የአፈና ትርምስን የሚያስቀር የፖለቲካ ስርዓት። በሌላ በኩል ኋላቀር የዝርፊያ ባህሎችንና የሽሚያ ግርግርን ለመከላከል የሚያስችል የኢኮኖሚ ነፃነት አለ። እያንዳንዱ ሰው በራሱ ምርትና ንብረት የማዘዝ ነፃነቱ ተከብሮ በፈቃደኝነት ብቻ የሚገበያይበት ስርዓት ነው - የዝርፊያ ግርግርን የሚያስቀር የነፃ ገበያ ስርዓት።

በጥቅሉ፤ የሃሳብ ነፃነትንና የንብረት መብትን የሚያስከብሩ፣ አፈናንና ዝርፊያን የሚከለክሉ ህጎች ተግባራዊ የሚሆኑበት (ማለትም የህግ የበላይነት የሰፈነበት)፣ ህግ የሚያስከብር መንግስት በዜጎች ፈቃድ ስልጣን የሚይዝበት (ማለትም ፓርቲዎች በምርጫ የሚፎካከሩበት) ስርዓት ነው - ካፒታሊዝም። የሊበራል ዲሞክራሲ ስርዓት ወይም የሊበራሊዝም አስተሳሰብ በሚሉ ስያሜዎችም ይታወቃል። ህዝቡ ከእልቂት፣ አገሬው ከውጥንቅጥ መዳን የሚችለው፤ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ነፃነትን ባካተተው የካፒታሊዝም ስርዓት ብቻ ነው። ኢህአዴግ ይህንን ስለተገነዘበ ይመስለኛል፤ “የዲሞክራሲና የነፃ ገበያ ስርዓት መገንባት፤ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ብሎ በተደጋጋሚ የሚናገረው - በተለይ ከ1993 ዓ.ም “ተሃድሶ” በኋላ። የኢህአዴግ አጣብቂኝ ኢህአዴግ የገባበት አጣብቂኝ ቀላል አይደለም። በአንድ በኩል፤ ለአመታት የያዘውንና ያስተጋባውን የሶሻሊዝም አስተሳሰብ አሽቀንጥሮ ለመጣል አልፈቀደም። ከድርጅቱ ባህልና ከመሪዎቹ ስሜት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ አስተሳሰብ ነውና። እናም፤ አንድ ፓርቲ የአገሪቱን ሃብት ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ እንዳሻው “እያከፋፈለ”፣ በብቸኝነትም ስልጣን ይዞ እንዳሰኘው አገሪቱን የሚገዛበት ስርዓት ቢፈጥር በወደደ! በእርግጥ ይሄኛው ጎዳና፣ የአገሪቱንና የራሱን ህልውና ለጥፋት የሚዳርግ አቅጣጫ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ሃብት የሚፈጠረው፣ ስልጣን የሚሰነብተውና አገር ሳይታመስ ሊቀጥል የሚችለው፤ በነፃ ገበያና በ“ዲሞክራሲ” ስርዓት ብቻ ነው። ኢህአዴግ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን ፓርቲዎች፣ “ሶሻሊዝምን” ያመልካል።

በኋላ ቀር ባህሎች ላይ የተመሰረተ፣ እንዲሁም ወደ ረሃብና ወደ ትርምስ የሚያደርስ የህልውና ፀር ቢሆንም፣ ለሶሻሊዝም “ሟች” ነው - እናም ከነጉዳቱም ቢሆን በከፊል ተግባራዊ ያደርገዋል። የስልጣኔና የብልፅግና መንገድ የሆነው ካፒታሊዝም ደግሞ፣ የህልውና ጉዳይ ነውና ኢህአዴግ በከፊል ተግባራዊ ያደርገዋል። በ“ግዴታ” እንደተጫነበት ሸክም ነው የሚቆጥረው። ቢሆንም፤ ነፃ ገበያን ወይም የምርጫ ዲሞክራሲን በግላጭ ለማብጠልጠልና አሽቀንጥሮ ለመጣል ከመቃጣት ተቆጥቧል - ቢያንስ ቢያንስ እስካሁን ድረስ ሳይሞክር ቆይቷል። አሁን ግን “የህልውና ሸክም” የሰለቸው ይመስል፣ አሽቀንጥሮ ለመጣል ሳይዳዳው አልቀረም - “ነፃ ገበያን”ና የምርጫ ዲሞክራሲን በግላጭ ማንቋሸሽና ማጣጣል ጀምሯል። ጭራሽ፣ ባለሃብቶችን በተቀናቃኝነት ፈርጆ፣ ተቃዋሚ ፓርቲ ማቋቋም እንደሚጠበቅባቸው በመፅሄቱ ፅፏል። በእርግጥ፣ አሁን በግላጭ ሆነ እንጂ፤ ካሁን በፊትም በዘወርዋራ መንገድ ሲያደርገው ነበር። እንዴት? በአንድ በኩል፤ “ነፃ ገበያንና የመድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲን እገነባለሁ” እያለ ይናገራል፤ ይፅፋል። በሌላ በኩል ደግሞ፤ በዘወርዋራ መንገድ ሁለቱንም ያጣጥላቸዋል - በጥላቻ ስሜት “ኒዮሊበራሊዝም” ወይም “ሊበራል ዲሞክራሲ” እያለ። ምን ማለቱ እንደሆነ ጥርት አድርጎ አይናገርም።

“ኒዮሊበራል” ወይም “ሊበራል ዲሞክራሲ” እያለ ሲያወግዝ፣ ነፃ ገበያንና የነ አሜሪካ አይነቱን ዲሞክራሲ ማንቋሸሹ ነው። ግን በግልፅ እንዲታወቅ አይፈልግም። ወዲህና ወዲያ ሳይጠማዘዝ ፊት ለፊት፤ ነፃ ገበያንና የነአሜሪካ ዲሞክራሲን በግላጭ ላለማጣጣል ይጠነቀቅ ነበር። እንዲያውም፤ “የዳበረ የነፃ ገበያና ልማታዊ የሃብት ፈጠራ ስርዓት”፣ “የዳበረ የዲሞክራሲና የመከባበር ስርዓት” … በማለት አሜሪካን እና የአውሮፓ አገራትን በአርአያነት ያወድሳቸዋል - ከኢትዮጵያና ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች የዝርፊያ ስርዓትና ኋላቀር ባህል ጋር እያነፃፀረ። ማጣጣልንና በአርአያነት ማወደስን ምን አመጣው? አሃ! የህልውና ጉዳይ እንደሆነ ስለሚያውቅ፤ ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን ያወድሳል። ለሶሻሊዝም “ፍቅር” ሲባል፣ ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን ያጥላላል - ግን በዘወርዋራ መንገድ። በግልፅ ማጥላላትማ ብዙ ጣጣ ያመጣበታል - ህልውናን ለአደጋ የሚዳርግ ብዙ ጣጣ።

በስድስት ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን ሲያውጅ ምን እንደተከሰተ ታስታውሳላችሁ? የዋጋ ቁጥጥሩ የገበያ ውጥንቅጥንና የሸቀጦች እጥረትን ቢያስከትልም፤ ቁጥጥሩ እንዲጠናከርና በሌሎች ሸቀጦች ላይም እንዲስፋፋ ነበር ከአብዛኛው ህዝብ የጥያቄ መዓት የጎረፈው። ቀውሱ ተባብሶ ቁልቁል ወደ አዘቅት ለመግባት? መንግስት ሞኝ ካልሆነ በቀር፣ እንዲህ አይኑ እያየ ህልውናውን ለአደጋ አያጋልጥም። እለት በእለት የሚዥጎደጎዱትን የቁጥጥር ጥያቄዎች መከላከልና ራሱን ከአደጋ ማትረፍ የሚችለው ደግሞ፤ “የነፃ ገበያ መርህ”ን በመከራከሪያነት ሲያቀርብ ብቻ ነው። ለነፃ ገበያ ፍቅር ባይኖረውም፤ ከጥፋት ለመዳን ሲል፣ የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ያቀርባል።

ለዚህም ነው፤ የዋጋ ቁጥጥር ማስታወቂያዎቹ ላይ ሳይቀር፤ “በምንገነባው የነፃ ገበያ ስርዓት መሰረት፤ በጥቂት ሸቀጦች ላይ የዋጋ ተመን አውጥተናል” የሚል አስቂኝ ሃሳብ ሲያሰፍር የተመለከትነው። ለሶሻሊዝም ባለው ፍቅር የዋጋ ቁጥጥርን እያወጀ፤ ካፒታሊዝም የህልውና ጉዳይ እየሆነበት የነፃ ገበያ ስርዓትን እገነባለሁ ይላል። “ህልውና” ሲባል፤ የኢህአዴግ ወይም የስልጣን ህልውና ማለት ብቻ አይደለም፤ የአገሪቱ ህልውናም ጭምር እንጂ። የመኖር እና ያለመኖር ጥያቄ ኢህአዴግ ነፃ ገበያን ሙሉ ለሙሉ በአደባባይ ሲያጣጥል፤ ፋታ በሚያሳጣ ናዳ ተቀብሮ ለመቅረት መዘጋጀት ይኖርበታል። ትንፋሽ አሳጥረው ህልውናውን በሚቀጩ፣ ቁጥር ስፍር በሌላቸው የሽሚያ ጥያቄዎች እድሜውን ለማሳጠር አምሮታል ማለት ነው…. “ድጎማ ስጠን፤ የስራ እድል ፍጠርልን፤ በብሄር ተወላጅነትና በሃይማኖት ተከታይነት እኩል የስራ ኮታ ይሰጠን፣ ማዳበሪያ በነፃ አከፋፍለን፤ ስኳርና ዘይት ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ነገር መንግስት ያቅርብልን፤ የሸቀጦችን ዋጋ ተቆጣጠርልን፤ ተወላጅ ያልሆኑ ከክልላችን ይውጡልን፤ መጤዎች በዘበዙን፤ ቅድሚያ ለነባር፣ ድጎማ ለተወላጅ! ምግብ፣ ልብስና መጠለያ ይሟላልን፤ አስፋልቱ በኛ መንደር በኩል ማለፍ አለበት፤ የባቡር መስመሩ በኛ ወረዳ በኩል ማለፍ አለበት፤ ለነ እገሌ ባህል በጀት እየመደብክ ለኛስ? የኛ ሃይማኖትኮ የአገሪቱ ባህል አንድ አካል ነው!”… የሽሚያ ግርግሩ ማቆሚያ አይኖረውም። የሽሚያው ትርጉም ሌላ ሳይሆን፤ “ከሌሎች ነጥቀህ ለኛ ስጠን” የሚል ነው።

ስለዚህ ሁሉንም ማስተናገድ አይቻልም። የአንዱን ጥያቄ አስተናግዶ የሌሎችን በቸልታ መተውም ሆነ ውድቅ ማድረግም አያዋጣም። ቅሬታዎች ይበራከታሉ። ምንም መከራከሪያ አይኖረውም። ሁሉንም ቅሬታ በጉልበት ዝም ማሰኘት ደግሞ አይቻልም። የመንግስትም ሆነ የአገሪቱ ህልውና ለአደጋ ይጋለጣል። ነፃ ገበያን ከማብጠልጠል መቆጠብ የህልውና ጉዳይ ነው። “እኛ የህዳሴ ግንባር ቀደም መሪና የአገሪቱ ብቸኛ አለኝታ ነን፤ ስለዚህ ያሰኘንን እንሰራለን፤ አርፋችሁ ተገዙ” ብሎ ያለ ተፎካካሪ ስልጣን ይዞ በጉልበት ለመግዛት እየተመኘ፤ የነአሜሪካ አይነት የምርጫ ስርዓትን በግላጭ ሲያንቋሸሽስ? በግለሰብ ነፃነት ላይ የተመሰረተ የምርጫ ዲሞክራሲን በአደባባይ ቢያጣጥልስ? ይሄም ጣጣው ብዙ ነው። በጉልበትና በጠመንጃ ስልጣን ለመያዝ የሚሞክሩ ቡድኖችን የሚያወግዝበት ምክንያት ያጣል። ላውግዝ ቢልም፣ ሰሚ አያገኝም። እነሱምኮ እንደሱ “እኛ የእገሌ ብሄር ግንባር ቀደም መሪ ነን፤ የአንድነት ተቆርቋሪ የቁርጥ ቀን ልጅ ነን! የአምልኮ ጠበቃ የሃይማኖት ቀናኢ ተዋጊዎች ነን! ያሰኘንን እንሰራለን፤ አርፋችሁ ተገዙ” የሚሉ ናቸው። ስልጣን መያዝ የሚቻለው በጠመንጃ ሳይሆን በምርጫ ፉክክር ነው ብሎ ዜጎችን ማሳመን አይችልም - ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት የምርጫ ዲሞክራሲን ሲያጣጥል ቆይቷልና። “እኛ የምናምንባቸው የሃይማኖት ትእዛዛት የመንግስት ህግ መሆን አለባቸው፤ እያንዳንዱ አማኝ የሃይማኖቱን ትእዛዛት እንዲያከብር እናደርጋለን፤ እምቢተኞቹን ልክ እናስገባለን” የሚሉ የሃይማኖት አርበኞችን ምን ብሎ መከላከል ይቻላል? “የግለሰብ ነፃነትን አክብሩ” ብሎ ሊከራከር አይችልም - የግለሰብ ነፃነትን በማብጠልጠል፣ ያሰኘንን እንሰራለን የሚል ከሆነ።

በአጠቃላይ የራሱንና የአገሪቱን ህልውና ለአደጋ አጋለጠ ማለት ነው። ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትን የዲሞክራሲ ስርአት ከማንቋሸሽ መቆጠብ የህልውና ጉዳይ ነው። ኢህአዴግ ለህልውናው ሲል፣ ነፃ ገበያንና የምርጫ ዲሞክራሲን በአደባባይ ላለማብጠልጠል ሲጠነቀቅ ቆይቷል። ነፃ ገበያን የማንቋሸሸ ዘመቻ ካካሄደ፣ ኢትዮጵያ እንደቀድሞው አንድ አገር ሆና የመቆየት እድል እንደማይኖራት ኢህአዴግ የሚገነዘብ ይመስለኛል - ቢያንስ ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይገነዘብ ነበር። ለምሳሌ “ድጎማና ድጋፍ ለአካባቢው ተወላጅ ብቻ! ኢንቨስትመንትና ስራ የሚፈቀደው ለነባር ብቻ! መጤው በዘበዘን፣ ስራ ተሻማን ይውጣልን” የሚሉ መፈክሮች አገሪቱን ወደ ቀውስ እንደሚገፉ ትጠራጠራላችሁ? ኢህአዴግም ይህንን አይክድም። ይህንን የህልውና አደጋ ለመከላከል የሚቻለው፣ የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት በማቅረብ ነው። የዲሞክራሲ ግንባታ ጥያቄ በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ አቶ መለስ ያዘጋጁትና በ1994 ዓ.ም የታተመው መፅሃፍ ውስጥ የምናገኘው መከራከሪያም ይሄው ነው። ነፃ ገበያን የማይፈልጉ ሰዎች፣ የብሄር ብሄረሰብ ግጭት ለመፍጠር ይጥራሉ በማለት አደገኛነቱን ይገልፃል መፅሃፉ። ታዲያ ግጭትንና መበታተንን ማስወገድ የሚቻለው እንዴት ነው? በምን መከራከሪያ? በመፅሃፉ የሰፈረውን ሃሳብ ልጥቀስላችሁ።

“በገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ሸቀጥ ማምረት የማይችሉና የብሄር ታርጋቸውን ለጥፈው በህዝቡ ጫንቃ ላይ ለመክበር የሚፈልጉ ጥገኞች [በነፃ ገበያ ውስጥ በሂደት] እንደሚከስሙ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ በመሆኑም… የብሄራቸውን ስም በመጠቀም አጥር አበጅተው በጥገኝነት ለመመዝበር መራወጣቸው አልቀረም፡፡ በህዝቦች መካከል አጥር ማበጀትና ቁርሾ እንዲፈጠር መጣር ከጥገኛ አመለካከታቸው የሚመነጭ ነው፡፡ … ዋናዎቹ የጠባብነትና የትምክህተኝነት አቀንቃኞች፣ በገበያ በነፃ ተወዳድረው መክበር የማይችሉ ጥገኞች… ናቸው” ታዲያ፤ የሶሻሊዝም ፍቅር የተጠናወተው ኢህአዴግ፤ የህልውና ጉዳይ ሆኖበት ነፃ ገበያን ላለማጣጣል መጠንቀቁ ይገርማል? የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ካልያዘ፤ “ሁሉህም በየብሄርህ፣ ሁሉሽም በየትውልድ ቦታሽ” ተብሎ አገር ስትታመስ ምንም መፍትሄ አይኖረውም። የህልውና ጉዳይ ሆኖበት የነፃ ገበያ መርህን በመከራከሪያነት ካቀረበ ደግሞ፣ የምዕራብ አገራትን በአርአያነት መጥቀሱ የግድ ነው። የአቶ መለስን መፅሃፍ በድጋሚ ልጥቀስላችሁ። “አንዳንድ ሰዎች፣ በአንድ አካባቢ አስር ወይም መቶ ልማታዊ ባለሀብቶች በሚሰማሩበት ጊዜ፣ ለሌሎች ባለሃብቶች ዕድሉ የተዘጋና ቦታው የተያዘ ይመስላቸዋል፡፡ ይህ የነፃ ገበያን ባህሪ በሚገባ ባለመገንዘብ የሚመጣ ችግር ነው፡፡

በአለም ውስጥ፣ እጅግ የዳበረ ኢኮኖሚ ያላት፣ ከሚልዮን ዶላር በላይ ካፒታል ያላቸው በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ባለሃብቶች የተነባበሩባት አገር አሜሪካ ነች፡፡ ይህም ሆኖ ከመላው አለም የውጭ ባለሃብት ወደ አሜሪካ በሰፊው ይጎርፋል፡፡ …በአጋጣሚ የሆነ ጉዳይ አይደለም፡፡ የግል ባለሃብቶች ልማታዊ እንቅስቃሴ በሚበራከትበትና.. በገበያ ውድድር በሚመራበት ወቅት፣ ለሌሎች ባለሃብቶች ተጨማሪ የኢንቨስትመንት ዕድል ይከፍታል፡፡ … አሜሪካኖች በላይ በላዩ የግል ባለሃብት ተከማችቶ፣ የስራ ዕድል መጣበብ ሳይሆን ቀጣይ የልማት ዕድልን ነው ያገኙት፡፡ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አንድ ተሰርቶ ያለቀለትን ዳቦ እንደመጋራት መወሰድ የለበትም፡፡ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ በስራ ላይ በሚሰማራ ልማታዊ ባለሀብት የነበረውን ዳቦ የሚጋራ ሳይሆን አዲስ ሃብት የሚፈጥር ነው፡፡

ሊፈጠር የሚችለው ሃብት ገደብ ያለው አይደለም፡፡ …በአንድ አካባቢ ልማታዊ ባለሃብቶች በሰፊው ሲሰማሩ፣ ለአካባቢው ልማታዊ ባለሀብቶች መጠናከር ዕድል ከመፍጠር በስተቀር በባለ ሃብቶቹ ላይ የሚያስከትለው ምንም ጉዳት የለም፡፡ በየአካባቢው ልማታዊ የግል ባለሃብቶች ብሄራቸው ምንም ይሁን ምን በሰፊው እንዲሰማሩ… [የነፃ ገበያ መርህ] በጥብቅ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል” ኢህአዴግ የሶሻሊዝም ፍቅር ባይለቀውም፤ ነፃ ገበያንና የእነ አሜሪካን ዲሞክራሲ በግላጭ ከማጣጣል ተቆጥቦ የቆየው፤ ካፒታሊዝም የህልውና ጉዳይ እንደሆነ በተወሰነ ደረጃ በመገንዘቡ ነው ብዬ አምናለሁ። የአቶ መለስ ፅሁፎችም ይህንን ይመሰክራሉ።

ታዲያ፣ አሁን ለአቶ መለስ መታሰቢያ ተብሎ የተዘጋጀው የኢህአዴግ መፅሄት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ነፃ ገበያንና እነ አሜሪካን በተደጋጋሚ በግላጭ ማብጠልጠሉ ለምን ይሆን? ኢህአዴግ፤ ነፃ ገበያና “ዲሞክራሲ” የምር የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን ዘንግቶ ከሆነ፤ ተሞኝቷል። የተሟላ ትክክለኛ አስተሳሰብና ፅኑ አቋም ለመያዝ ባይበቃ እንኳ፣ በተግባር ነፃ ገበያንና ዲሞክራሲን በጥራትና በፍጥነት ለማስፋፋት ፍላጎቱ ባይኖረው እንኳ፤ ቢያንስ ቢያንስ የህልውና ጉዳይ መሆናቸውን መርሳት የለበትም። ከተንሸራተቱ በኋላ ጣጣው ብዙ ነው።

በሰው ግድያና በማታለል ወንጀል ሞት ተፈርዶበት የነበረውና በይግባኝ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቀይሮለት በማረሚያ ቤት የሚገኘው ታምራት ገለታ ወርቆች በየካራታቸው ተለይተውና ተጨፍልቀው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መሆናቸውን በፌደራል መንግስት የመንግስት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የመንግስት ንብረት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አቶ አወቀ አበራ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡ ወርቆቹ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ አላቸው ተብሏል፡፡

እንደ አቶ አወቀ ገለፃ፤ የግለቡ የንብረት ጉዳይ እስከ ሰበር ችሎት ድረስ ተኪዶ የፍርድ አፈፃፀም ውሳኔ ካገኘ በኋላ የርክክብ ሂደቶቹ በኤጀንሲው በኩል መከናወናቸውንና እስካሁንም በመንግስት ግዥና ንብረት አወጋገድ አገልግሎት በኩል ሁለት ተሽከርካሪዎቹ መወገዳቸውን ገልፀው፣ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ወርቆቹም በየካራታቸው ተለይተውና ተጨፍልቀው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ሆነዋል - ብለዋል፡፡ አቶ አወቀ አክለውም በኦሮሚያ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን ፍቼ ከተማ ውስጥ የሚገኙት የግለሰቡ “አቢዶ” የተባለ ባለ ሶስት ኮከብ ሆቴልና መጠነኛ መኖሪያ ቤቱን ኤጀንሲው የተረከባቸው ሲሆን ለማስወገድ ጨረታ እንደወጣባቸውም ገልፀዋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ሁሉም የስሜት ዓይነቶች ይኖሩበት የነበረ አንድ ደሴት ነበረ ይባላል፡፡ እነዚህም ስሜቶች ደስታ፣ ሐዘን፣ ዕውቀት እንዲሁም ፍቅርን ጨምሮ በርካታ ሌሎች ነበሩ፡፡ አንድ ቀን ያ ደሴት ሊሰምጥ ነው የሚል ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ ሁሉም በየፊናቸው ጀልባ እየሰሩ፣ ዘር ማንዘሮቻቸውን ይዘው፤ እግሬ - አውጪኝ እያሉ ከደሴቲቱ ወጡ፡፡ ከፍቅር በስተቀር፡፡ ፍቅር፤ “የመጣው ይምጣ እንጂ ስንት ዘመን የኖርኩበትን ደሴት ጥዬ አልሄድም” አለ፡፡ “የመጨረሻዋ ቅጽበት መጥታ ምርጫ ካላጣሁ በስተቀር ንቅንቅ አልልም” ሲል ወሰነ፡፡ ደሴቱ ሊሰጥም ተቃረበ፡፡ ፍቅር እርዳታ የሚያሻው ሰዓት ደረሰ፡፡

በአንድ ትልቅ ጀልባ ላይ ሆኖ ሀብት እየተኮፈሰ በፍቅር አጠገብ ሲያልፍ ታየ፡፡ ይሄኔ ፍቅር፤ “ሀብት ሆይ! ከአንተ ጋራ ልትወስደኝ ይቻልሃልን” አለና ጠየቀው፡፡ ሃብትም፤ “ወዳጄ ፍቅር! በጀልባዬ ላይ ስፍር ቁጥር የሌለው ብርና ወርቅ፣ ሌላም ጌጣጌጥ ስለከመርኩኝ፤ አንተን የማስቀምጥበት ቦታ የለኝም፡፡ ፍቅርም ሀብት እንደማይወስደው ሲያውቅ፤ ውብ በሆነች ጀልባ ላይ ኮርቶ ተቀምጦ እየፈሰሰ በአጠገቡ እያለፈ ወዳለው ወደ አያ ከንቱነት ሄዶ፤ “ከንቱነት ሆይ እባክህ ከዚህ ከሚሰምጠው ደሴት አውጥተህ ወደ ዳርቻው ውሰደኝ፤ እርዳኝ” አለው፡፡ “አዬ፤ አየህ አቶ ፍቅር አንተ ሁለመናህ እርጥብ ነው፡፡ ውብ ጀልባዬን ታረሰርስና ታቆሽሽብኛለህ፡፡ ስለዚህ አልጭንህም” ሲል ይመልሳል፡፡ ቀጥሎ ፍቅር በአካባቢው ወደነበረው ወደ አቶ ሐዘን ሄደና፤ “አብሬህ እሄድ ዘንድ ፍቀድልኝ” አለና ተማፀነው፡፡

“አይ አቶ ፍቅር፤ በጣም አዝናለሁ፡፡ እኔ አሁን ብቻዬን መሆን ያለብኝ ሰዓት ነው” ቀጥሎ በፍቅር አጠገብ የምናልፈው ደስታ ነበረችና ወደሱዋ ተጣራ፡፡ ደስታ ግን በጣም ፍንድቅድቅ ብላ ስለነበር የፍቅርን ድምጽም ለመስማት ሳትችል አልፋው ሄደች፡፡ በዚህ መካከል አንድ ድንገተኛ ድምጽ ተሰማ፡፡ “ፍቅር ሆይ፤ ና ወደኔ እኔ እወስድሃለሁ” አለ፤ ያ የአንጋፋዋ እመቤት ድምጽ፡፡ ፍቅር ይህን የተባረከ ዕድል በማግኘቱ እጅግ ሀሴት ተሰምቶት ወዴት እንደሚሄዱ እንኳ ለመጠየቅ ጊዜ አልወሰደም፡፡ ወደ አንድ ደረቅ ምድር በደረሱ ጊዜ አንጋፋዋ እመቤት ወደራስዋ አቅጣጫ ተጓዘች፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ፍቅር ወደ አንጋፋው ዕውቀት ሄደና፤ “አሁን እርዳታ ያደረገችልኝ አንጋፋ እመቤት ማን ናት?” ሲል ጠየቀው፡፡ ዕውቀትም፤ “ጊዜ ናት” ሲል መለሰ፡፡

“ጊዜ? ጊዜ ለምን ትረዳኛለች” አለና በአግራሞት ጠየቀ፡፡ ዕውቀትም ጥልቅ ጥበባዊ ፈገግታ ፈገግ ብሎ፤ “ፍቅር ምን ያህል ዋጋ እንዳለው የሚያውቅ ዕውቀት ብቻ ነው” ሲል መለሰ፡፡ *** በወርሃ የካቲት ፍቅር፣ ዕውቀትና ጊዜ አይንሳን፡፡ ለውጥ ምን ጊዜም አይቀሬ ነው፡፡ ከሚሰምጥ ደሴት ግን ያውጣን፡፡ ዱሮ ስናውቀው በ60ዎቹ የየካቲት ወር ብዙ ነገር አርግዞ ነበር፡፡ የዛሬ አርባ ዓመት ግድም የለውጥ ንፋስ በየአቅጣጫው ወጀቡን ይዞ መምጣቱ ይታወሰናል፡፡ የሁሉም መሽከርክሪት የሥርዓት ለውጥ ነበር፡፡ የቤንዚን ዋጋ መናር፣ ከዚያ የተያያዘው የታክሲዎች ሥራ ማቆም፣ የወሎ ረሃብ፣ የተማሪዎች እንቅስቃሴ የመምህራን ሥራ ማቆም፣ የወታደሮች የደሞዝ ጭማሪ ጥያቄ፣ የሙስሊሙ ህብረተሰብ የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄ፣ ወዘተ ብርቱ የለውጥ ጥንስስ ሆነው ከተፍ ያሉት በወርሃ የካቲት ነበር፡፡ ጠቅለል አድርገን ስናነጥራቸው የኢኮኖሚ ጥያቄና የፖለቲካዊ አስተዳደር በደል ጥያቄዎችና የሃይማኖት እኩልነት ጥያቄዎች ግዘፍ - ነስተው እናገኛቸዋለን፡፡ ያኔ የአለም አቀፉ ፖለቲካ ባጠቃላይ ሲታይ ሁለት ጐራዎች ነበሩት፡፡

ስለሆነም ማናቸውም አገር የውስጥ ችግሩን ለመፍታት የውጪ እጅ ካስፈለገው ወደነዚህ ሁለት ጐራዎች ያንጋጥጣል፡፡ ያኔ ያላደጉት አገሮች ቻይና፣ ህንድ፣ አፍሪካ እና ላቲን አሜሪካ ነበሩ፡፡ አንጋፎቹ ጐራዎችም ቋታቸውን የሚሞሉት የነዚህኑ ያላደጉ አገሮች ድንግል አንጡራ ሀብት በመቦጥቦጥ ነበር፡፡ ዘመን ተሻረ፤ ሁኔታዎች ተለዋወጡ፡፡ የምዕራቡ ኃይል ብቸኛ ጐራ ሲሆን ሌሎቹ ምዕራብ ያልሆነው ክፍል ተቃራኒ ጐራ ናቸው፡፡ እነቻይናና ህንድ ወደላይ ወጡ፤ ያደጉ አገሮች ሆኑ፡፡ ላቲኖችም ወደላይ ተጓዙ፡፡ ባለበት የሚረግጡትና ቆሞ ቀር የሆኑት ከሞላ ጐደል የአፍሪካ አገሮች ናቸው፡፡ ስለዚህ ዛሬም ለውጥ ለማምጣት ጠረጴዛ ዙሪያና ምርጫን ለመንተራስ ቢፍጨረጨሩም ገና ከጫካ አልወጡም፡፡ ጠመንጃ ከመንከስ አልተላለቁም፡፡ ከጐሣ ግጭት አልወጡም፡፡

የበሽታ መናኸሪያ የጉስቁልና መፈልፈያ ከመሆን ገና አልዳኑም፡፡ የዱሮዎቹ ትውልዶች ጭቆናን ለመቃወም፣ ግፍን ለመጋፋትና የውስጥ ታጋዮቹ ብዝበዛን ለመታገል ቆርጠው ይነሱ ነበር፡፡ ለውስጥ ታጋዮቹ ዓለም አቀፋዊ ኃይሎችም ያግዟቸው ነበር፡፡ ዛሬ ያ የለም፡፡ ሆኖም የማይለወጥ ነገር የለም፡፡ ሁሉም ነገር ይለወጣል፤ ከለውጥ ህግ በስተቀር (Everything changes except the law of change እንዲል ፈረንጅ) ሀገራችንም ከለውጡ ሽታ መጋራቷ አይቀሬ ነው፡፡ ቢያንስ “የመሬት ላራሹ” ጥያቄን ምላሽ ማግኘት ማስታወስ ከቻልን ወርሃ የካቲትን ልናሰምርበት እንችላለን፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ዛሬም አጽንኦት መስጠት አስፈላጊ ነው - ዲሞክራሲው ሀቀኛ መሆን አለበት፡፡ የኢኮኖሚ ብዝበዛ ተቋማዊም ሆነ ድርጅታዊ፤ አሊያም ግለሰባዊ ዛሬም በፅኑ ልንዋጋው ይገባናል፡፡

ከውጪ ኃይሎች በማናቸውም መልክ የሚመጣውን አሉታዊ ተጽእኖ ዐይናችንን ከፍተን ወገባችንን አጥብቀን መቋቋም አለብን፡፡ የሃይማኖት ችግር የራሳችን ይሁን የውጪ ኃይሎች ፍላጐት ብለን አጥርተን ማሰብ አለብን፡፡ የፍትሕና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በተግባር መመለስ አለበት፡፡ ህዝብ እየለፋ እየታተረ የሚገነባውን ኢኮኖሚ የባለጊዜ ልጅ ልጆች የሚንዱ ከሆነ “እኔ እያለቀስኩ እሸምታለሁ፣ እሷ እየዘፈነች ትፈጫለች” ይሆናል፡፡

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተቋቋመበት ሃምሳኛ ዓመት የወርቅ ኢዮቤልዩ በተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች እንደሚከበር የበዓሉ አዘጋጅ ብሔራዊ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ከመንግሥት ኮሙኒኬሽን ፅህፈት ቤትና ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተዋቀረው ብሔራዊ ኮሚቴ አባላት የዛሬ ሳምንት በአምቦ ከተማ በተዘጋጀ አውደ ጥናት ላይ እንደተገለፀው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተበት ዋነኛ እለት ግንቦት 17 የሚከበር ሲሆን ከዚያ በፊት እና በኋላ የተለያዩ ኪነጥበባዊ ዝግጅቶች ይቀርባሉ፡፡ “ፓን አፍሪካኒዝምና የአፍሪካ ሕዳሴ” በሚል መሪ ቃል በሚከበረው የወርቅ ኢዮቤልዩ፤ ታዋቂ ድምፃውያን እና እግር ኳስ ተጨዋቾች ወደ አዲስ አበባ ተጋብዘው ከአድናቂዎቻቸው ጋር ይገናኛሉ፡፡
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጥናታዊ ፊልም የሚቀርብ ሲሆን የምስረታውን ጉዞ የተመለከቱ ቴምብሮችም ይታተማሉ ተብሏል፡፡ ከስምንት ሳምንት በላይ የሚቆይ የአማርኛና እንግሊዝኛ ጥያቄና መልስ ውድድር ከታሚሶል ኮሙኒኬሽን ጋር በመተባበር እንደሚዘጋጅም ታውቋል፡፡

በተለያዩ የኪነጥበባት ዘርፎች የተሰማሩ አርቲስቶች ለ “መቄደንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል” ገቢ ማሰባሰቢያ ነገ በዘጠኝ ሰዓት የእግር ጉዞ እንደሚያደርጉ ተገለፀ፡፡ በዝግጅቱ ላይ ከአርቲስቶች በተጨማሪ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርበኞች እና ሰላሳ ሺህ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የእግር ጉዞው በሚጀመርበት የኤግዚብሽን ማዕከል ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
መቄዶንያ ኮተቤ አካባቢ በሚገኘው መጠለያው 150 አረጋውያንና የአእምሮ ህሙማንን ያለምንም የውጪ የገንዘብ ድጋፍ የሚረዳ ድርጅት ነው፡፡

ኩል ፊልም ፕሮዳክሽን “አምራን” የተሰኘ አስቂኝ የፍቅር ፊልም ነገ በአዲስ አበባ የግል ሲኒማ ቤቶች እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡ በፊልሙ ላይ ማህደር አሰፋ፣ ሳምሶን ታደሰ፣ ሠለሞን ሙሄ፣ ሰላም አሰፋ እና አሸናፊ ከበደ ተውነውበታል፡፡
የ103 ደቂቃ ርዝመት ያለውን ይሄን ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ ስምንት ወራት ፈጅቷል፡፡ በብሌን ሚዲያ ፕሮዳክሽን የተዘጋጀው “ፍቅር በአጋጣሚ” የተሰኘ የ100 ደቂቃ ፊልም ነገ እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ አዝናኛ የፍቅር ፊልሙን ለመስራት አስራአራት ወራት የፈጀ ሲሆን በፊልሙ ላይ ሩታ መንግሥተአብ፣ ዮናስ አሰፋ፣ ዳንኤል ገበየሁ፣ መቅደስ መለስ፣ ሲያምረኝ ተሾመ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

 

ሚዩዚክ ሜይዴይ በገጣሚ አያልነህ ሙላቱ “ከድጡ ወደ ማጡ” የግጥም መፅሐፍ ላይ ነገ ከቀኑ ስምንት ሰዓት ጀምሮ በብሄራዊ ቤተመዘክር ውይይት እንደሚያደርግ አስታወቀ፡፡
“የመግቢያና የይዘት ተቃርኖ” በሚል ርእስ የሚደረገውን ውይይት የሚመሩት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ ናቸው፡፡

 

“ቪዚት ቱ ኢትዮጵያ” በተባለ ድርጅት ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ የታተመው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ዳይሬክተሪ በአራት አህጉራት በሚገኙ 78 ሀገራት እንደሚሰራጭ ታወቀ፡፡ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ መርአዊ ስጦት ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ ዳይሬክተሪው ስድስት በዩኔስኮ ለመመዝገብ የታጩ የኢትዮጵያ ቅርሶችንና ታላቁ ሩጫን እንደ ቅርስ ማካተቱ ልዩ እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡ ዳይሬክተሪው በተጨማሪም በዓለም የተመዘገቡ ዘጠኝ ቅርሶችና የኢትዮጵያን ብሔራዊ ፓርኮች የያዘ መረጃ እንዳካተተ የታወቀ ሲሆን በነፃ የሚታደል 10ሺህ ቅጂ እንደተዘጋጀም ለማወቅ ተችሏል፡፡