Administrator
የብራዚል ባህል ፌስቲቫል ነገ ይጠናቀቃል
አዲስ አበባ የሚገኘው የብራዚል ኤምባሲ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀውና ከየካቲት 22 ጀምሮ ሲካሄድ የሰነበተው የብራዚል የባህል ፌስቲቫል ነገ በኤምባሲው በሚቀርብ የሙዚቃ ዝግጅት ይጠናቀቃል፡፡ የካቲት 22 ቀን 2005 ዓ.ም ሸራተን አዲስ በሼፍ ክርስቲያኖ ላና፤ በሸራተን አዲስ በቀረበና ለስምንት ቀናት በዘለቀ የምግብ ፌስቲቫል የተጀመረው ዝግጅት፤ ከመጋቢት 2 እስከ መጋቢት 7 በቆየ የፊልም ፌስቲቫለ የቀጠለ ሲሆን “The Passion of Brazilian Football” በሚል ርእስ መጋቢት 11 የጀመረው የፎቶግራፍ አውደርእይም ዛሬ ይዘጋል፡፡ የኤምባሲው አንደኛ ፀሐፊ እና የባህል አታሼ ሚስተር ማርሴሎ ቦርሄስ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ ዛሬ ማታ በኤምባሲው የሚደረገውን መዝጊያ ፊደል የሙዚቃ ባንድ ያቀርባል፡፡
የቅዱስ ያሬድን ህይወት አስመልክቶ መፅሐፍ ታተመ
ታላቁን የኢትዮጵያ የዜማ አባት ቅዱስ ያሬድ 1500ኛ ልደት ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የህይወት ታሪኩን እና ሥራዎቹን የተመለከተ መፅሐፍ ታተመ። በአቶ ታደሰ አለማየሁ የተዘጋጀው ባለ 202 ገፆች መፅሐፍ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማህበረ ቅዱሳን አሳትሞ እያከፋፈለው ነው፡፡ ይኸው መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት በብሔራዊ ቤተመዘክር ትልቁ አዳራሽ እንደሚመረቅ ከማህበሩ የተገኘው መግለጫ ያስረዳል። በመፅሐፉ ውስጥ ከተካተቱ ርእሰ ጉዳዮች መካከል የዘፈን እና የመዝሙር ልዩነትን ይመለከታል፡፡ የመፅሐፉ ዋጋ 50 ብር ነው፡፡
ኃይሌ በ40 ዓመቱ ይሮጣል
በሃዋሳ በስሙ የሚያዘጋጀው ማራቶን ትኩረት እያገኘ ነው በቅርቡ 40ኛ ዓመቱን የሚይዘው ኃይሌ ገብረስላሴ በ “ግሬት ማንችስተር ራን” እንደሚሳተፍ የውድድሩ አዘጋጆች አስታወቁ፡፡ ስለተሳትፎው የተጠየቀው ኃይሌ ‹‹ሩጫ ስለሚያስደስትኝ መሮጤን እቀጥላለሁ፤ መቼ እንደሚያበቃልኝ አላውቀውም፤ ወደ ማንችስተር ተመልሼ ለመወዳደር የምችልበትን እድል መተው አልችልም›› ብሏል፡፡ ኃይሌ በ “ግሬት ማንችስተር ራን” የ10 ኪሎሜትር ሩጫ ለ6 ጊዜያት ሲያንፍ፤ ላለፉት አምስት ተከታታይ ዓመታት የውድድሩ አሸናፊ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘንድሮ “ኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን” በሃዋሳ ከተማ መካሄዱ ትኩረት እየሳበ ነው፡፡ የውድድሩ አምባሳደር አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ለተሳታፊዎች ባቀረበው በጥሪ ለ20 ዓመታት ካሳለፈው የሩጫ ዘመን በኋላ ዓለምን ወደ አገሩ ኢትዮጵያ ሲጋብዝ በታላቅ ጉጉት እንደሆነ ገልጿል፡፡
የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን በኢትዮጵያ በአውሮፓ እና በአሜሪካ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው የውድድር አዘጋጆች በተሰባሰቡበት ቡድን የሚመራ ሲሆን ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ቀለሙ ኢትዮጵያዊ ማራቶን ነው ተብሏል፡፡ ከ1200 በላይ ተሳታፊዎች እንደሚኖሩት ከሚጠበቀው ኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ጋር በመያያዝ የግማሽ ማራቶን፤ የ5 ኪሎሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ እና የህፃናት ውድድሮችም ይደረጋሉ፡፡በውድድሩ ኦፊሴላዊ ድረገፅ በቀረበው መረጃ መሰረት በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ተሳታፊ ለሚሆኑ ራጮች የጉብኝት ፕሮግራም የተዘጋጀ ሲሆን የኢትዮጵያን ባህልና ታሪክ ለማስተዋወቅ ታስቧል፡፡ የኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን ጋር ተያይዞ በሚደረገው የገቢ ማሰባሰብ 200ሺ ዶላር ለእንጦጦ ፋውንዴሽን እንደሚበረከትም ታውቋል፡፡ በኃይሌ ገብረስላሴ ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ለሚያሸንፉ አትሌቶች ለእያንዳንዳቸው 12 ወቄት ወርቅ ይሸለማል፡፡
ለውድድሩ መሮጫ የተመረጠችው የሃዋሳ ከተማ ከዓለም አቀፉ የአማተር አትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ጋር በሚደረግ ትብብር በቀጣይ ወራት የእውቅና ሰርተፍኬት ለውድድሩ አዘጋጅነት ይሰጣታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት በፖላንዷ ከተማ ባይድጎስዝ በተደረገው 40ኛው የዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ኬንያ 5 ወርቅ በማግኘት ስኬታማ ስትሆን ኢትዮጵያ በግልና በቡድን 10 ሜዳልያዎች በመሰብሰብ ከፍተኛ ውጤት አስመዘገበች፡፡ በሻምፒዮናው አጠቃላይ የውጤት ሰንጠረዥ ኬንያ 5 ወርቅ፤ 3 ብርና 1 ነሐስ በመውሰድ አንደኛ ሆና ጨርሳለች፡፡ ኢትዮጵያ በ3 የወርቅ፤ 4 የብርና 3 የነሐስ ሜዳልያዎች በማግኘት ሁለተኛ ሆና በሻምፒዮናው በአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር፤ በአዋቂ ሴቶች ስምንት ኪሎ ሜትር እንዲሀም በወጣት ሴቶች የ4 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ኬንያውያን የወርቅ ሜዳልያዎችን በመሰብሰብ ውጤታማ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያው አትሌት ሃጎስ ገብረ ህይወት በወጣት ወንዶች 6 ኪሎ ሜትር ብቸኛውን የወርቅ ሜዳልያ ድል አስመዝግቧል፡፡ ከ32 አገራት የተወከሉ 102 አትሌቶች በተሳተፉበት የአዋቂ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ውድድር በቡድን ውጤት ኢትዮጵያ 1ኛ ደረጃ ስትወስድ አሜሪካና ኢትዮጵያ ተከታታዩን ደረጃ ወስደዋል፡፡ ከ29 አገራት የተወከሉ 97 አትሌቶች በተሳተፉበት የአዋቂ ሴቶች 8 ኪሎ ሜትር ውድድር ደግሞ በቡድን ውጤት ኬንያ 1ኛ ደረጃ ስትወስድ ኢትዮጵያና ባህሬን ተከታታዩን ደረጃ ወስደዋል፡፡
ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ጉዟቸውን እያመቻቹ ነው
ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ስታዲየም በዓለም ዋንጫ የሶስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የቦትስዋና አቻውን 1ለ0 በማሸነፍ የምድቡን መሪነት አጠናከረ፡፡ ዋልያዎቹ በዚሁ ጨዋታ ከቦትስዋና ያልጠበቁት ከባድ ፉክክር የገጠማቸው ሲሆን ብቸኛዋን የማሸነፊያ ጎል ባለቀ ሰዓት የደደቢቱ ጌታነህ ከበደ አስቆጥሮ ሙሉ ሶስት ነጥብ ሊመዘገብ ችሏል፡፡ በሌላ የምድብ 1 ጨዋታ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን በኬፕታውን ያስተናገደችው ደቡብ አፍሪካ 2ለ0 አሸንፋለች፡፡
ከዓለም ዋንጫ የሶስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በ7 ነጥብ እና በ3 የግብ ክፍያ መሪነቱን ማስጠበቅ የቻለ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ በ5 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች፡፡ ከሶስተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ በፊት ሁለተኛ ደረጃ ላይ የነበረችው መካከለኛው አፍሪካ በደቡብ አፍሪካ ከተሸነፈች በኋላ በሶስት ነጥብ ወደ ሶስተኛ ደረጃ ስትወርድ በኢትዮጵያ የተሸነፈችው ቦትስዋና በአንድ ነጥብ በነበረችበት የመጨረሻ ደረጃ ላይ ረግታለች፡፡
ኢትዮጵያ በምድብ 1 በሁለት ነጥብ ልዩነት መሪነቷን መቀጠሏ ወደ ዓለም ዋንጫው የማለፍ ተስፋ ካላቸው ቡድኖች ተርታ እንዳሰለፋት በተለያዩ ዘገባዎች ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ ዲ.ሪፖብሊክ ኮንጎ፤ አይቬሪኮስት፤ ካሜሮን፤ ሴኔጋልና ቱኒዝያ በየምድባቸው መሪነት ጉዟቸውን በስኬት ቀጥለዋል፡፡ በ2014 ብራዚል ለምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የሚደረገው የምድብ ማጣርያ በአራተኛ ዙር ከ4 ወራት በኋላ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያ ሰኔ ወር ላይ ከሜዳዋ ውጭ ከቦትስዋና እና በሜዳዋ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ትገናኛለች፡፡ በእነዚህ የ4ኛ እና የ5ኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታዎች ካሸነፈች በ6ኛ ዙር ከሜዳዋ ውጭ ከመካከለኛው አፍሪካ የምታደርገውን የመጨረሻ ጨዋታ ሳትጠብቅ ምድብ አንድን በመሪነት በማጠናቀቅ ለመጨረሻው የጥሎ ማለፍ ማጣርያ ታልፋለች፡፡
በተያያዘ በ2013 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ እና ኮንፌደሬሽን ካፕ አንደኛ ዙር ማጣርያ ተጋጣሚዎቻቸውን የረቱት ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ደደቢት የመልስ ጨዋታቸውን ከሳምንት በኋላ ያደርጋሉ፡፡ በአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ የአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ግጥሚያውን በሜዳው ያደረገው ቅዱስ ጊዮርጊስ የማሊውን ዲጆሊባ 2-0 ማሸነፉ ሲታወስ፤ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ደግሞ የአንደኛ ዙር የማጣርያ ጨዋታውን ከሜዳው ውጭ ወደ ሱዳን ተጉዞ አልሼንዲን የገጠመው ደደቢት 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት እንዳሸነፈ አይዘነጋም፡፡ የአንደኛ ዙር ማጣርያ የመልስ ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ሁለቱ የኢትዮጵያ ክለቦች ወደ ሁለተኛ ዙር የማጣርያ ምእራፍ ለመሸጋገር የሚያስችል ዕድል ይዘዋል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ በሻምፒዮንስ ሊጉ ከሜዳው ውጭ በባማኮ የማሊውን ዲጆሊባ ሲፋለም ማሸነፍ እና አቻ መውጣት የሚበቃው ሲሆን ዲጆሊባ ጊዮርጊስን ጥሎ ለማለፍ በሜዳው የሚያደርገውን ግጥሚያ 3-0 ማሸነፍ ይኖርበታል፡፡ በሌላ በኩል በኮንፌደሬሽን ካፕ አዲስ አበባ ላይ የሱዳኑን አልሼንዲን የሚያስተናግደው ደደቢት በሜዳውና በደጋፊው ፊት በሚያደርገው የመልስ ጨዋታ በማሸነፍ የማለፍ እድሉን ይወስናል፡፡
በአውሮፓ ሊጎች የዋንጫ ፉክክር ቀዝቅዟል
በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች የ2012 -13 የውድድር ዘመንን ሲጠናቀቅ ከሁለት ወር ያነሰ ጊዜ ሲቀረው በየሊጐቹ የሻምፒዮናነት ፉክክሩ ብዙም አጓጊ አይደለም፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ማን ዩናይትድ፤ በስፔን ላሊጋ ባርሴሎና እንዲሁም በጀርመን ቦንደስ ሊጋ ባየር ሙኒክ የየሊጋቸውን የደረጃ ሰንጠረዥ በሰፊ የነጥብ ልዩነት በመምራት ወደ ሻምፒዮናነቱ ያለ ተፎካካሪ እየገሰገሱ ናቸው፡፡ በጣሊያን ሴሪኤ እና በፈረንሳይ ሊግ 1 ግን የዋንጫ ፉክክሩ ብዙም አልደበዘዘም፡፡ በአውሮፓ 5 ታላላቅ ሊጎች ላይ ለዋንጫዎች የሚደረግ ፉክክር በጥቂት ክለቦች መካከል ተወስኖ የየሊጎቹን ማራኪነት እየቀዘቀዘው መጥቷል፡፡ ለዚህም ባለፉት 10 ዓመታት በአምስቱ የአውሮፓ ሊጎች በሚወዳደሩ ክለቦች መካከል በፋይናንስ አቅም የተፈጠረው ልዩነት ዋና ምክንያት መሆኑ ይገለፃል፡፡ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ እና የፈረንሳዩ ሊግ 1 በሚታይባቸው የፉክክር ደረጃ እና የክለቦች የተመጣጠነ አቋም አጓጊ እና ውጤታቸውን ለመተንበይ የሚያስቸግሩ ሊጎች ናቸው፡፡ የስፔኑ ላሊጋ ደግሞ በሁለት ክለቦች ብቻ በተወሰነ ፉክክር ሚዛኑ ያጣ እና የማይስብ ሊግ ሲባል የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ትርፋማ የጣሊያን ሴሪኤ ደግሞ ደካማ ሊጐች ተብለዋል፡፡
በ21ኛው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ እስከ 29ኛው ሳምንት በተደረጉ 296 ጨዋታዎች 837 ጎሎች ተመዝግበው ሊጉ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.83 ጎሎች የሚቆጠሩበት ሆኗል፡፡ ማንችስተር ዩናይትድ ፕሪሚዬር ሊጉን ከ29 ጨዋታዎች በሰበሰባቸው 74 ነጥቦች እና 38 የግብ ክፍያዎች እየመራ ነው፡፡ ያለፈው ዓመት የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ማንችስተር ሲቲ በ59 ነጥብ እንዲሁም ቼልሲ በ55 ነጥብ ይከተላሉ፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን በመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች እንደታወቀ ሲታወስ ዘንድሮ ግን ሊጉ ከመጠናቀቁ ወር ቀደም ብሎ አሸናፊው ይለያል፡፡ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ክለባቸው በፍፁም የበላይነት የዋንጫ ፉክክሩን መጨረሱ የሚዲያዎችን ትኩረት ቢቀንስም እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል፡፡ የፕሪሚዬር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ቢቀዛቀዝም በቀጣይ የውድድር ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፎ ለማግኘት በ7 ነጥብ ልዩነት አራት ክለቦች አስጨናቂ ፉክክር ውስጥ ናቸው፡፡ አራቱ ክለቦች ቼልሲ፤ ቶትንሃም፤ አርሰናልና ኤቨርተን ሲሆኑ በቂ ጨዋታዎቻቸው እስከ አራተኛ ደረጃ ለመጨረስ ወሳኝ ፍልሚያዎችን ያደርጋሉ፡፡
ቼልሲ እና ቶትንሃም በቀሪ ግጥሚያዎቻቸው ከባድ ተጋጣሚዎእች ያሉባቸው ሲሆን አርሰናልና ኤቨርተን ቀለል ባሉ ጨዋታዎች የሻምፒዮንስ ሊግ ተሳትፏቸውን ለማሳካት ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ኪውፒአር ሬዲንግ እና ዊጋን በወራጅ ቀጠና ውስጥ እየዳከሩ ሲሆን አስቶንቪላ፤ ሳውዝ ሃምፕተንና ሰንደርላንድ በዚሁ አደጋ አፋፍ ላይ ሆነው በቀጣዮቹ አምስት ሳምንታት ከመውረድ ለመዳን ይታገላሉ፡፡ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የዓመቱ ኮከብ ተጨዋች ፉክክር የማን ዩናይትዱ ቫን ፒርሲ፤ የቶትንሃሙ ጋሬዝ ባሌ እና የሊቨርፑሉ ሊውስ ስዋሬዝ ዋና እጩዎእች ናቸው፡፡ የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር ደግሞ የሊቨርፑሉ ሊውስ ሱዋሬዝ በ22 ጎሎች ሲመራ የማን ዩናይትዱ ቫንፒርሲ በ19 ጎሎች ዱካውን ይዞታል፡፡ በታሪኩ ለ82ኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው የስፔኑ ላሊጋ እስከ 28ኛው ሳምንት 283 ጨዋታዎች ተደርገው 791 ጎሎች ከመረብ አርፈዋል፡፡
ይህም የላሊጋውን አንድ ጨዋታ በአማካይ 2.83 ጎሎች የሚመዘገቡበት አድርጎታል፡፡ በላሊጋው ባርሴሎና ባደረጋቸው 28 ግጥሚያዎች 74 ነጥብ እና 54 የግብ ክፍያ መሪነቱን እንደያዘ ሲሆን ያለፈው ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድ በ13 ነጥብ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በኮከብ ግብ አግቢ ፉክክር ደግሞ የባርሴሎናው ሊዮኔል ሜሲ በ42 ጎሎቹ የሚመራ ሲሆን የሪያል ማድሪዱ ክርስትያኖ ሮናልዶ በ27 ጎሎች በርቀት ይከተለዋል፡፡ በ50ኛው የጀርመን ቦንደስ ሊጋ እስከ 26ኛው ሳምንት በተደረጉ 234 ጨዋታዎች 665 ጎሎች ተመዝግበው ሊጉ በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.84 ጎሎች የሚያሳይ ሆኗል፡፡ ባየር ሙኒክ ባደረጋቸው 26 ጨዋታዎች 69 ነጥብ እና 58 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ቦንደስ ሊጋውን በሁለተኛ ደረጃ ከሚገኘው ቦርስያ ዶርትመንድ በ20 ነጥብ ልዩነት መሪነቱን ይዞ ወደ ሻምፒዮናነት እየገሰገሰ ነው፡፡ በኮከብ አግቢ ፉክክር የቦርስያ ዶርትመንዱ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ በ19 ጎሎች እየመራ ሲሆን የባየር ሌቨርኩዘኑ ስቴፈን ኪዬብሊንግ በ16 ጎሎች እንዲሁም የባየር ሙኒኩ ማርዮ ማንዱዚክ በ15 ጎሎች ይከተሉታል፡፡
በ81ኛው የጣሊያን ሴሪ ኤ እስከ 29ኛው ሳምንት በተደረጉ 289 ጨዋታዎች 772 ጎሎች የገቡ ሲሆን ይህም በሴሪኤው በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.67 ጎሎች ሲቆጠሩ ቆይተዋል፡፡ ያለፈው አመት የሴሪኤ ሻምፒዮን ጁቬንትስ ዘንድሮም የስኩዴቶውን ክብር የመውሰድ እድሉን እያሰፋ ሲሆን ባደረጋቸው 29 ጨዋታዎች 65 ነጥብና 39 የግብ ክፍያ በመያዝ ይመራል፡፡ ናፖሊ በ56 ነጥብ እንዲሁም ኤሲ ሚላን በ54 ነጥብ እየተከተሉ ናቸው፡፡ በሴሪኤው የኮከብ ግብ አግቢነቱን ፉክክር የሚመራው የናፖሊው ኤዲሰን ካቫኒ በ20 ጎሎች ነው፡፡ በ75ኛው የፈረንሳይ ሊግ 1 እስከ 29ኛው ሳምንት በተደረጉ 290 ጨዋታዎች 735 ጎሎች ሲቆጠሩ ይህም ሊጉን በአንድ ጨዋታ በአማካይ 2.53 ጎሎች የሚገቡበት አድርጎታል፡፡ በሊግ 1 ባደረጋቸው 29 ጨዋታዎች 58 ነጥብ እና 33 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ፓሪስ ሴንትዠርመን እየመራ ቢሆንም ሊዮን በ53 እንዲሁም ማርሴይ በ51 ነጥብ በሁለተኛ እና ሶስትኛ ደረጃ እየተፎካከሩ ናቸው፡፡ በኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክሩ የፓሪስ ሴንትዠርመኑ ዝላታን ኢብራሞቪች በ25 ጎሎች ይመራል፡፡
የዝነኛው እጣፈንታ!
“ምንድነው ዝነኝነት ሰለቸኝ ብሎ ነገር? ከሙያህ ለመውጣት ሌላ አሳማኝ ምክንያት ካለህ ንገረኝና ልቀበልህ፡፡ ተራ ሰው ሆኖ መኖር አማረኝ ማለት ግን …” አለ መርዕድ የሰለሞን ነገር አልዋጥልህ ብሎት፡፡ ለሀያ አመት በዘለቀው የፕሮሞተርነት ስራው እንደዚህ አይነት እንግዳ ነገር ሰምቶ አያውቅም፡፡ አንድ ድምፃዊ ዝነኝነት ሰለቸኝ ብሎ ድምፃዊነቱን እርግፍ አድርጎ ለመተው ሲወስን የአሁኑ የመጀመርያው ነው፡፡ ለዛውም እንደ ሰለሞን ያለ ባወጣቸው ስድስት የዘፈን አልበሞቹ በሙሉ የተሳካለት፤ በየትኛውም ስፍራ ያሉ አድናቂዎቹ ሥራውን ካላቀረበልን እያሉ በየሚዲያው የሚወተወቱት አርቲስት እንዴት ዝነኝነት ሰለቸኝ ይላል? “ሌላ ምክንያት የለኝም! … ዝነኛ ሆኖ መኖር ሰልችቶኛል፡፡ ዝነኝነትን መጥላቴ ሙያዬን እንድተው እንዳስገደደኝ ስነግርህ ማመን ካቃተህ ምን አደርጋለሁ? በቃ ተራ ሰው የሚኖረው ኑሮ አማረኝ፡፡” ዝነኛው ድምፃዊ ሰለሞን እረጋ ብሎ ነው የሚያወራው፡፡ ፕሮሞተሩ መርዕድ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የዝነኝነት ከፍታ ላይ ካወጣው ሙያው ለመለያየት ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡
“እኮ አስረዳኝ! … ስንቶች ዝነኛ ለመሆን እንቅልፍ አጥተው ሲፍጨረጨሩ … አንተ ግን ዝነኝነት ሰለቸኝ ብለህ… ፈፅሞ ልትገባኝ አልቻልክም፡፡ ቆይ ዝነኝነት እንዴት ይሰለቻል? ዝነኛ ስትሆን እኮ ሰው ያከብርሀል፣ ሰላም ይልሀል፣ ቅድሚያ ይሰጥሀል” …ላንተ ምን እነግርሃለሁ መርዕድ በሃፍረት ስሜት ሰለሞን ላይ አፈጠጠ፡፡ ሰለሞን ከሙዚቃው ዓለም ሲወጣ በፕሮሞተርነቱ ብዙ ነገር እንደሚያጎልበት ይውቃል፡፡ ከግሉ ጉዳት በላይ ደግም በሀገሪቷ ሙዚቃ እድገት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ያውቃል፡፡ ሰለሞን ተራ ድምፃዊ አይደለም፤ ኃላፊነት የሚሰማው ለብዙዎች አርአያ መሆን የሚችል በሳል አርቲስትም ጭምር ነው፡፡
“ዝነኝነት ይሰለቻል! እ…ዝነኝነት ማለት በተራራ ላይ መስታወት ቤት ውስጥ እንደመኖር ነው፡፡ ሁሉም ያይሃል፣ ሁሉም ይከታተልሃል … ለብቻህ በነፃነት የምታደርገው ነገር የሌለህ ፍጡር ነህ! ነፃነት አልባ ፍጡር!” ሰለሞን ዝነኝነትን በመንገሽገሽ ንግግሩን ቀጠለ፡፡ “የመጀመሪያ ካሴቴን ከማውጣቴ በፊት የነበረኝን ነፃነት ሳስበው እገረማለሁ፡፡ ስፈልግ በመንገድ ላይ እጆቼን ኪሶቼ ውስጥ ከትቼ፣ አሊያም ግስላ ሲጃራዬን እያጨስኩ፣ ከሰዎች ጋር እየተጋፋሁ፣ ህብረተሰቡ የሚያወራውንና የሚያማውን እየሰማሁ … መሔድ፤ መኖር ብዙ ትርጉም እንዳለው የገባኝ ዝነኛ ከሆንኩ በኋላ ነው - አሁን!…” ሰለሞን ለአፍታ ትንፋሽ ወሰደና በስሜት መናገሩን ገፋበት፤ “አሁን ዝነኛ ከሆንኩ በኋላስ? ሽንቴን መንገድ ላይ ቢወጥረኝ እንኳ ፊኛዬ ይፈነዳታል እንጂ መንገድ ላይ እንኳ ቆሜ መሽናት አልችልም! … መንገዱ ቀርቶ የህዝብ ሽንት ቤት መግባት እንኳ አልችልም፡፡
የፈለግኋትን ቆንጆ መንገድ ላይ ተከትዬ የመጥበስ እንኳን ነፃነት የለኝም እኮ! ይኼ ሁሉ በዝነኝነቴ የመጣ ባርነት ነው!” “እነዚህ ሁሉ ትርጉም የሌላቸው! ተራ ነገሮች እኮ ናቸው!” አለ መርዕድ በማቃለል “ትርጉምማ አላቸው! ነገሩን አልኩህ እንጂ እነዚህን ነገሮች ማድረግ ትክክል ነው ማለቴ አይደለም፡፡ መንገድ ላይ የማልሸናው ዝነኛ ስለሆንኩ ነው እንጂ መንገድ ላይ መሽናት ትክክል እንዳልሆነ ስላመንኩ አይደለም!” ከመርዕድ ምላሽ የፈለገ አይመስልም፡፡ “እነዚህ ሁሉ ተራ ነገሮች የነፃነት ምልክቶች ናቸው፡፡ ሰው ነፃነት ለማግኘት ጠመንጃ ያነሳል እኮ መርዕድ! የነፃነት ግንባር ብሎ ሰይሞ ድርጅት እስከማቋቋም ይደርሳል እኮ … አስበው ሰዎች ህይወታቸውን የሚገብሩለትን ነፃነት በዝነኝነት ሰበብ ስታጣው፡፡ መንገድ ላይ ቆሞ መሽናት እንኳን ብርቅ ይሆንብሀል እኮ፣ መንገድ ላይ የተጠበሰ በቆሎ እየበላህ መሔድ እንኳን አትችልም፡፡ ለምን? ዝነኛ ነሃ!” ሰለሞን ሀሳቡን በቅጡ የሚገልጡለት ቃላት ያገኘ አልመሰለውም፡፡ “ያልከው ባይገባኝም እስቲ ሙያህን አቆምክ ብለን እንውሰድ፡፡ ከዛስ ዝነኝነትህን እንደ አረጀ ኮት አጣጥፈህ ማስቀመጥ የምትችል ይመስልሀል? ሸሽተኸው ማምለጥ እንዳትችል በስድስት አልበሞች የሰራሃቸው ስራዎች ይከተሉሀል፡፡ በስድስት አልበሞች የተገነባ ዝነኝነትን እንደቀልድ ከላይህ ላይ አራግፈህ ልትጥለው… አይሆንማ! … መርዕድ ከተቀመጠበት ወንበር ላይ በስሜት እየተውረገረገ ተነሳ፡፡ “አይምሰልህ ዝነኝነት እንደ አበባ ነው… ሰርክ እየኮተኮትክ፣ ውሀ እያጠጣህ የምትንከባከበው፡፡ አበባን ካልተንከባከብከው እየቆየ እንደሚከስመው ዝነኝነትም በጊዜ ሒደት ቀለሙ እየጠፋ ይኼዳል፡፡
እከሌ እኮ ድሮ የታወቀ አርቲስት ነበር ብትል ታሪክ ነው የሚሆነው፡፡ ልክ ታዋቂ አትሌት ነበር እንደምትለው … ቢበዛ ከንፈር የሚመጥልህ ሰው ብታገኝ ነው እንጂ መውጫ መግቢያ የሚያሳጣህ ሰው አይኖርም” አለ ሰለሞን፡፡ “እና ታሪክ ለመሆን አቅጃለሁ ነው የምትለኝ?” መርዕድ በጥርጣሬ መንፈስ ተሞልቶ ጠየቀው፡፡ ሰለሞን በአዎንታ እራሱን ነቀነቀ፡፡ “አዎ! እኔ የማንም አርአያ የመሆን ፍላጎት የለኝም፡፡ ዝነኝነቴን ወስዳችሁ ነፃነቴን መልሱልኝ እያልኩ ነው!” አለ ሰለሞን ከተቀመጠበት እየተነሳ፡፡ መርዕድ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ተረድቶታል፡፡ ተስፋ በቆረጠ ስሜት ለስንብት እጁን ዘረጋለትና ተጨባበጡ፡፡ “ዝነኝነት ሱስ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ልክፍት! እርግጠኛ ነኝ በድጋሚ ዝነኝነት ይናፍቅሃል! ተራ ሰው ሆነህ ሀምሳ አመት ከመኖር ዝነኛ ሆነህ ሀምሳ ቀን መኖር እንደምትመርጥ አልጠራጠርም! … ያን ጊዜ በሬ ክፍት ነው፡፡ እስከዛው ግን ቢያንስ የት እንደምትሔድ ንገረኝ እና እየመጣሁ ልጠይቅህ፡፡” አለ መርዕድ ሰለሞን በአሉታ እራሱን ግራና ቀኝ ወዘወዘ “ይቅርታ መርዕድ፤ ዝነኝነት ለኔ ቀንበር ነው እንጂ ሀብል አይደለም፡፡ ወደ ዝነኝነቴ የሚመልሱኝን ድልድዮች ሰብሬ መሔድ ነው የምፈልገው፡፡ አንዳንዶች ዝነኛ ሆነው ለመኖር ብርቱ ጫንቃ አላቸው፤ እኔ ግን ፈፅሞ የለኝም! ዝነኝነትን መቋቋም የሚችል ትከሻ አልተሰጠኝም!” አለና ተንደርድሮ ከመርዕድ ቢሮ ወጣ፡፡ የውጪው ነፋሻ አየር ተቀበለው፡፡ ጀንበር ወደመጥለቂያዋ እያቆለቆለች ስለነበር ወርቅማ የስንብት ቀለሟን እሱን ወክላ የምትረጭ መሰለው፡፡ ጀንበሯን ተከትሎ “ዝነኝነት ያላጎበጠው ነፃ ሰው! ዝነኝነት ያልከበበው ነፃ ማንነት!” እያለ መጮህ ናፈቀው፡፡
ጀንበሯን ቆሞ በሰመመን ሲቃኝ ከጀርባው አንድ ድምፅ ሰማ፤ “እንዴ ሰለሞን! ታዋቂው ድምፃዊ ሰለሞን! ሰሌ! ሰሌ!!!” የሚል ጩኸት ሙሉ በሙሉ ከሰመመኑ አነቃው፡፡ ህፃናት፣ ኮረዶች፣ ጎልማሶች … የአካባቢው ሰዎች ሁሉ ከየቤታቸው ወጥተው እንደ ጉንዳን እየከበቡት መሆኑን ሲረዳ መኪናውን ያቆመበትን ቦታ ተመለከተ - ለማምለጥ! “ሰሌ! ፍቅር እና ትዝታ የሚለው ዘፈንህ ተመችቶኛል!...”፣ ሰሌ! “እዚች ጋር ትፈርምልኛለህ?” “ሰሌ! እንወድሃለን!” የሚሉና ሌሎች ድምፆች ከበቡት፡፡ ጨነቀው፡፡ ለከበበው ህዝብ “እኔ ዘፋኙ ሰለሞን አይደለሁም!” ብሎ ለመጮህ፤ ለማወጅ አስቦ ነበር፡፡ ግን አይገባቸውም በሚል ተወው፡፡ ከላይ እየበረረች የምትመጣ ላዳ ታክሲ ሲያይ አስቁሞ ዘሎ ገባ፡፡ የታክሲው ሾፌር በኋላ ማሳያ መስታወቱ አየውና ፈገግ አለ፡፡ “ምነው ቢኤም ደብሊዋ ደበረችህ እንዴ?” ጠየቀው ሾፌሩ፡፡ “መኪናዬ ቢኤም ደብሊው መሆኗን እንኳ ይኼ ሾፌር ያውቃል! የኔ ብቻ የምለው ምስጢር የሌለኝ ምስኪን ሰው!” እያለ በውስጡ በምሬት ይብሰለሰል ገባ፡፡
አፉ ላይ የመጣለትን መናኛ መልስ ለሾፌሩ ሰጠውና ወደ ራሱ ሀሳብ ተመለሰ፡፡ “ዝነኝነት ታዲያ ምኑ ነው የሚያስደስተው? ሰዎች በታክሲ መሳፈር እንዳለብህ እና እንደሌለብህ ይወስኑልሀል! የምትመገብበትን ምግብ ቤት የሚወስኑልህ ሌሎች ናቸው! ነፃነት የሌለው ህይወት ሲኦል አይደለም እንዴ?!” ከራሱ ጋር እያወራና ብቻውን እየተብከነከነ ሳለ ባለታክሲው አሁንም ሳቅ ብሎ ተመለከተውና “አልጋ የያዝክበት ሆቴል ደርሰናል!” አለው፡፡ “እዚህ አልጋ እንደያዝኩ በምን አወቀ?” ንዴት በሰራ አካላቱ ተቀጣጠለ፡፡ ባለታክሲውን በንዴት ገረመመውና እጁ ላይ የገባለትን ብር ከቦርሳው መዥረጥ አድርጎ ወርውሮለት ከታክሲው ውስጥ ዘሎ ወጣ፡፡ የነፃነት እጦት ትንፋሽ ያሳጣው መሰለው፡፡ እየሮጠ ወደ ያዘው የመኝታ ክፍል ሮጠ፡፡ ፍቅረኛው ካትሪን አልጋ ላይ ጋደም ብላ መፅሀፍ ታነባለች፡፡ ካትሪን የስዊዲን ተወላጅ ናት፡፡ ከሰለሞን ጋር ድንገት ነበር በግብዣ ላይ የተዋወቁት፡፡
ያኔ ካትሪን ስለሰለሞን ዝነኝነት ምንም የምታውቀው ነገር አልነበራትም፡፡ ለዚህ ነው ከመቅፅበት በፍቅር የወደቀላት፡፡ ሰው በመሆኑ ብቻ የምትቀርበው እንስት ሲፈልግ ነው ያገኛት፡፡ ከሀገሩ እንስቶች ሊያገኝ ያልቻለው ይህንን አይነቱን ፍቅር ነበር፡፡ ሁሉም ሴቶች እሱን ከማወቃቸው በፊት ከዝነኝነቱ ጋር በፍቅር እየወደቁ በተቸገረበት ወቅት ካትሪን ባህር ተሻግራ ደረሰችለት፡፡ የሀገሩ ሴቶች “ወይኔ ሰሌ! የመጨረሻው ካሴትህ ላይ ያለውን ‘ፍቅር ይዞኝ ነበር’ የሚል ዜማ እንዴት እንደወደድኩት!” ሲሉት የፍቅር ተስፋው እንደጉም ይበናል፡፡ የካተሪን ግን የተለየ ነበር፡፡ መጀመሪያ ሰለሞንነቱን ነው የወደደችው… ወደ ክፍሉ እየሮጠ ሲገባ ካትሪን ደንግጣ ከአልጋዋ ተነሳች፡፡
“ከማበዴ በፊት አሁኑኑ ይኼን ከተማ ለቅቄ መሄድ አለብኝ!” አላት ሰለሞን፡፡ ሁኔታው ግራ ስላጋባት ምንም ነገር ልትጠይቀው አልደፈረችም፡፡ ልብሷን ቀያይራ ተከተለችው፡፡ እስከ ሀዋሳ ድረስም ሸኘችው፡፡ የሰለሞን ጉዞ ግን እዛ የሚያቆም አልነበረም፡፡ ከተማን ነበር ሽሽቱ… ቴሌቭዥን ብሎ ነገር የሌለበት፣ ኢንተርኔት ይሉት ጉድ ያልገባበት፣ ተፈጥሮ እና ተፈጥሮ ብቻ ወዳሉበት ምድር መሄድ… ለዚህ ደግሞ ከደቡብ ኢትዮጵያ የተሻለ… ከፀማይ መንደር የበለጠ አማራጭ አልነበረውም፡፡ ፀማይ ዝነኝነቱን እንድታከሰምለት የመረጣት ምድር ሆነች፡፡ በተፈጥሮዋ ጭምቅ አድርጋ ዝነኝነት የሚባለውን አውሬ ሲጥ እንደምታደርግለት ተማምኖባታል፡፡
*** ከሁለት ወር በኋላ… ሰው መሆን ብቻ በቂ የሆነባት ምድር-ፀማይ! ማነህ? ምንድነህ? የሚል ጥያቄ የሌለባት፣ የሰው ልጅ ከቁስ አካላዊ ግብዝነቱ ተላቆ ሲኖር ምን ያህል ውብ እንደሆነ የሚታይባት ምድር! ሰርክ ጠዋት ከእንቅልፉ ሲነቃ በህልም አለም እንደሚኖር ነው የሚሰማው፡፡ የስልክ ጥሪ ሳይሆን የከብቶች እንቧታ ከእንቅልፉ ሲቀሰቅሰው ደስታው ወሰን ያጣል፡፡ ፀማይ ውስጥ የፈርምልኝ ጫጫታ አያጋጥመውም! “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ሶደሬ አካባቢ በተደጋጋሚ ይታያል”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ከአዲሷ ፍቅረኛው ጋር በተደጋጋሚ ፀብ ውስጥ እየገባ ነው”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ ጫማውን ለጠረገለት ሊስትሮ ሁለት መቶ ብር ሰጠ”፣ “አርቲስት ሰለሞን በኩረ፤ በተደጋጋሚ ሽሮ መብላቱ ለድምፁ አስተዋፅኦ ይኖረው ይሆን?”... ቅብርጥሶ ምንትሶ ከሚሉ የጋዜጣ እና መፅሄት አናዳጅ ዘገባዎች ተገላግሏል፡፡ አናዳጅ የጋዜጠኛ ጥያቄዎችም ፀማይ ውስጥ የሉም! “አርቲስት ሰለሞን፤ በልጅነትህ መጫወት የምትወደው ጨዋታ ምን ነበር?” (እርግጫ ቢላቸው ይወዳል ግን ዋና እወዳለሁ ይላል) የህይወት ፍልስፍናህ ምን ነበር?” (እኔ እኮ ዘፋኝ እንጂ ፈላስፋ አይደለሁም ቢላቸው ይወዳል፤ ግን ከሰው ጋር አብሮ መኖር ምናምን የሚል ፍልስፍና አለኝ ይላቸዋል) “አርቲስት ሰለሞን፤ ወደፊት ምን ለመሆን ትፈልጋለህ?” (ጋዜጠኛውን እያየ የአንተን አይነሰብ በቡጢ መነረት ማለት ይፈልጋል፤ ግን በሙያዬ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ይላቸዋል)፡፡ አሁን እነዚህ ጥያቄዎች ምን ይሰራሉ? ስለዘፈኑ ሙያዊ ጥያቄ የጠየቀው አንድም ጋዜጠኛ አያስታውስም፡፡ በቀን ለስንት ሰአት ትተኛለህ? ምግብ ማብሰል ደስ ይልሃል? የመጀመሪያ ፍቅረኛህን የት ተዋወቅሃት?... ሁሉም ስለሱ ነው ማወቅ የሚፈልጉት! የራሴ የሚለው ነገር እንዲኖረው አይፈልጉም፡፡
የማስመሰል ህይወት ፀማይ ውስጥ የለም! በጫት እና በሺሻ ታጥረው እየዋሉ “እኛ አርቲስቶች ከሱስ የፀዳ ህብረተሰብ ለመፍጠር አርአያ መሆን አለብን!” የሚል ዲስኩር ማሰማት በፀማይ ውስጥ የለም፡፡ ጠዋት ስለጫት አስከፊነት አውርቶ ከሰአት “ልጄ የጥበብ ሥራ በርጫ ይዘው በፅሞና ነው! ሼክስፒር ሳይቅም እንዲህ የፃፈ ቢቅም ኖሮ የትናየት በደረሰ ነበር!…” ማለት የለም፡፡ ህዝቡን መድረክ ላይ አስር ጊዜ “በጣም ነው የምወዳችሁ!” እያሉ በመወሻከት የቁርጥ ቀን ሲመጣ “ልጄ ሁሉም ለራሱ ነው!” ብሎ ነገር የለም፡፡ ፀማይ የእውነት ምድር ነው፡፡ መውደድ እንዳይረክስ በቃል አይጠራም፤ በተግባር ነው የሚገለፀው፡፡ እነዚህን ሁሉ በረከቶች አግኝቷል፡፡ ፀማይ ሰላም ነው! በፀማይ ኮረብቶች፣ በፀማይ ሜዳዎች ላይ ቀን ከምሽት ሳይመርጥ ሲንጐራደድ፣ አፉ ውስጥ የቀረች አንዲት ግጥምን እንደ ብሔራዊ መዝሙር ይደጋግማታል፡፡
“ፍላጐት ምኞትህ ወደብ ድንበር አለው? ብለህ አትጠይቀኝ ህልሜ አንተን መሆን ነው! ያለ ስም ቅጥያ ግቤ ሰው መሆን ነው፡፡ ሰው መሆን! ሰው መሆን! በቃ ነፃ መሆን!” ግጥሟ የአንድ ፋርሳዊ ፀሃፊ ነው ብሎ ጓደኛው ነበር በቃሉ ያስጠናው፡፡ ነፃ ሰው የመሆን ስሜቱን በፀማይ አፈር፣ በፀማይ አየር፣ በፀማይ ሰዎች መካከል አግኝቶታል፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ከኦሞ ወንዝ ጋር የማይደበዝዝ ፍቅር አዳብሮ ነበር፡፡ ኦሞን እንደሰው እያዋራ፣ በኦሞ የቅዝቃዜ በረከት ሲረሰርስ፣ በኦሞ ፈሳሽ ውሃ ሲዳሰስ ዘላለማዊ መኖሪያው በኦሞ ዳርቻ እንደሚሆን ወስኖ ነበር፡፡ በሰለሞን ውሳኔ ግን ኦሞ የተስማማ አይመስልም፡፡ እጣውን ኦሞ እራሱ ፅፎ ሰጠው፡፡ እጣ ደግሞ የሚመርጡት ሳይሆን የሚወጣ ነው፡፡ በአንድ ወበቃማ ቀን ሰለሞን ወደ ኦሞ ሲወርድ ለሁለት ወራት ያህል ከውሀው ሲገባ ለወትሮ የሚያገኘውን ደስታ በልቡ እያሰበ ነበር፡፡ ወደ ወንዙ የሚያመራውን ጉብታ ቁልቁል እያቋረጠ ሳለ ግን የድረሱልኝ የሚመስል ድምፅ የሰማ መሰለው፡፡ እየሮጠ ወደ ወንዙ ደረሰ፡፡
ብቅ ጥልቅ የሚል ሰው ታየው፡፡ በውሀው ላለመወሰድ የሚታገል፡፡ ዘሎ ከውሀው ገባ፡፡ የውሃውን ሃይል እየታገለ ሰው ወዳየበት አቅጣጫ ተምዘገዘገ፡፡ ያየውን ሰው እጅ እንዳገኘ ሽቅብ ገፋው እና ከውሀው በላይ አደረገው፡፡ በአንድ እጁ እየዋኘ ወደ ወንዙ ዳር ተጠጋ፡፡ ኦሞ እንደለማዳ ፈረስ እሺ ብሎ የሚጋልብለት ይመስል በቀላሉ አቋረጠው፡፡ የተሸከመውን ሰው አውጥቶ ከወንዙ ዳር አስተኛው፡፡ በውሀ ሊወሰድ የነበረው ሰው ግዙፍ ወንድ ነበር - ፈረንጅ! ከአለባበሱ ቱሪስት እንደሆነ ገምቷል፡፡ ከነልብሱ ምን ሊያደርግ ኦሞ ውስጥ እንደገባ ለሰለሞን ሊገባው አልቻለም፡፡ “እንደኔ የከተማ ቱማታ ናላውን ያዞረው ይሆናል!” ብሎ እያሰበ ሳለ፣ የፈረንጁን ጩኸት የሰሙ ፀማዮች እየተጠራሩ ከቦታው ደረሱ፡፡ የሰውዬውን ደረት እየተጫኑ ከሆዱ የገባውን ውሀ ሲያስወጡለት ቀስ በቀስ ነፍስ ዘራ፡፡ ሰለሞን የሰው ነፍስ ማትረፍ መቻሉ ከፍተኛ ደስታ አጐናፅፎት ነበር፡፡ የፀማዮች ተደጋጋሚ የምስጋና ቃል ሲቸረው በሙሉ ልብ ሲቀበል ቆየ፡፡ ያረፈባት ቤት ፈረንጁን ከውሀ ውስጥ መንጥቆ ያወጣውን ጀግና ለማየት ከአቅራቢያ መንደሮች ጭምር በሚመጡ እንግዶች እስከምሽት ድረስ ተጨናነቀች፡፡ የሰለሞን ዝና በአንድ ምሽት ፀማይን አልፎ ጅንካ ደረሰ፡፡ ከጅንካ ምድር አልፎ አዋሳ ለመድረስ አንድ ቀን አልፈጀበትም፡፡ ከአዋሳ አዲስ አበባ በዚያው ቀን ምሽት ዜናው ተሰራጨ፡፡ የጋዜጠኞች ቡድን ካሜራ እና ማይኩን ደቅኖ ጀርመናዊውን ቱሪስት ያዳነውን ጀግና ለማየት ወደ ፀማይ አመራ፡፡
ሰለሞን ከከተማ የመጡ ሰዎች ሊያናግሩት እንደሚፈልጉ በብሔረሰቡ አባት ሲነገረው፤ ብዙም ደስ ባይለውም እሳቸውን ላለማስቀየም ወጥቶ የመጡትን ሰዎች ማነጋገር ነበረበት፡፡ “ለመንደራችን ልዩ ሲሳይ ነው ይዘህ የመጣኸው!... አሁንም ከከተማ ትላልቅ ሰዎች አንተን ለማነጋገር መጥተዋል፡፡ እንደምታየው መንደራችን ብዙም አላደገችም፡፡ አንተ የሰራኸው ስራ መንደራችንን ለማስተዋወቅ ጠቃሚ ነው!” የሚለው ንግግራቸው ይበልጥ አሳማኝ ሆነለት፡፡ ጋዜጠኞቹ ሰለሞንን ሲያዩ አይናቸውን ተጠራጥረው ነበር፡፡ ከመካከላቸው አንዱ፤ “ዝነኛው አርቲስት ሰለሞን?” አለ ባለማመን ስሜት ተውጦ ሰለሞን በአዎንታ እራሱን ነቀነቀ፡፡ የፎቶ ካሜራዎች ብልጭታ ከየቦታው ሲተኮስበት፣ የካሜራዎች እይታ እሱ ላይ ሲያነጣጥርበት አንድ ነገር ገባው፡፡ ዝነኝነት ምርጫው ባይሆንም እጣው ነበረ፡፡ ቢሸሽ የማያመልጠው! እንደ ጥላ!
አፍሪካን ቫኬሽንና “የጊዜ መጋራት
የከተማ ኑሮ በጣም አድካሚና አሰልቺ ከመሆኑም በላይ በውጥረት የተሞላ ነው፡፡ በእኛ አገር ያልተለመደና በሙጪው ዓለም የሚዘወተር የመዝናኛ ፕሮግራም አለ - ቫኬሽን መውጣት፡፡ የማያውቁትን፣ የሚያደንቁትንና የሚጓጉለትን … ነገር፣ በማየትና በመጐብኘት መደሰት አዕምሮን ከማዝናናቱም በላይ ሰውነትን ዘና ያደርጋል፡፡ አንድ ሰው በሥራ የደከመ አዕምሮውን ከቤተሰቡ ጋር ቫኬሽን በመውጣት ቢያዝናና ረጅም ዕድሜና ጤናማ ሕይወት መምራት ያስችለዋል፡፡ ይህን ባህል በእኛም አገር ለማስለመድ እየተሞከረ ነው፡፡ በዚህ ረገድ አፍሪካን ቫኬሽን ክለብ ተጠቃሽ ነው፡፡ “ታይም ሼሪንግ” የተባለ ፕሮግራም ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ክለቡ ይህን አዲስ ባህል ለማስለመድ ምን እያደረገ ነው? የፕሮግራሙ ይዘትስ ምንድነው? ምን ችግሮችስ አሉበት? ችግሮቹንስ እንዴት እየተወጣ ነው? … በሚሉ ነጥቦች ዙሪያ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ከአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ መስራችና ባለቤት ወ/ሮ ሶኒያ ፓስኩዋ ጋር ያደረገችውን ቃለ ምልልስ በዚህ መልኩ አቅርበነዋል፡፡ እስኪ ሥለ ራስዎ ትንሽ ያጫውቱኝ? ሶኒያ ፓስኩዋ እባላለሁ፡፡
ግማሽ ጣሊያን ግማሽ ኢትዮጵያዊ ብሆንም ተወልጄ ያደግሁት እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን በሊሴ ገ/ማሪያም ጨርሼ፣ ከዚያ ወደ ጣሊያን ሄድኩኝ፡፡ እዛም 13 ዓመታት በማርኬቲንግ ስሠራ ቆየሁ፡፡ ለምን እና እንዴት ነበር ወደ ጣሊያን አካሄድዎ? ወደ ጣሊያን የሄድኩት የዛሬ 35 ዓመት ገደማ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ሥርዓት ትንሽ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት እዚህ አስጊ ነገሮች ስለነበሩ ጣሊያን ሄድኩና ማርኬቲንግ ተማርኩኝ፡፡ ይህ ትምህርት በዚያን ወቅት አዲስ ነበር፡፡ ብዙ የማርኬቲንግ ፍላጐት የታየበት ስለነበር፣ እኔም ከታወቀ ዩኒቨርስቲ በማርኬቲንግ ኤክሠለንስ በሠርቲፍኬት ተመረቅኩኝ፡፡ በወቅቱ ዘርፉ አዲስ በመሆኑ በዲግሪ ደረጃ አይሠጥም ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በማርኬቲንግ ነው ስሠራ የቆየሁት፡፡
ጊዜን መጋራት (time Sharing) የተሠኘ ቢዝነስ ነው እዚህ አገር ያመጣችሁት፡፡ በዚህ አገር ይሄ ቢዝነስ አልተለመደም፡፡ እንዴት በዚህ ዘርፍ ተሠማሩ? ጣሊያን በነበርኩበት ወቅት ጊዜን መጋራት በጣም ፋሽን የሆነ ቢዝነስ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ማርኬቲንግ ላይ ባተኩርም ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስኩ ቱሪዝም ላይ ትልቅ ነገር እሠራለሁ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም “ታይም ሼሪንግ” ከቱሪዝምም ከማርኬቲንግም ጋር ስለሚገናኝ መስራት ጀመርኩኝ፡፡ “ታይም ሼሪንግ” ምንድነው? አሠራሩስ? ጊዜን መጋራት ማለት በአመት ውስጥ 52 ሳምንታት አሉ፡፡ አንዱን ቤት ሀምሳ ሁለት ሰዎች ይገዙታል፡፡ ስለዚህ ለአንድ ሰው አንድ ሳምንት ነው የሚደርሠው፡፡ አንድ አባል በዓመት ውስጥ ከ51 ሌሎች የድርጅቱ አባሎች ጋር ጊዜን ይጋራል ማለት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በውጭ ዜጐች እንድትጐበኝ፣ መልካም መሆኗ እንዲነገር እፈልግ ነበር፡፡ ለዚህም ቆንጆ ሪዞርት፣ ቆንጆ የጉብኝትና የመዝናኛ ቦታዎችን ለመገንባት እቅድ ነበረኝ፡፡
ይገርምሻል ለቱሪዝም ፍቅር ያደረብኝ በልጅነቴ አባቴ ከከተማ የመውጣትና ከከተማ ውጭ ያለውን ነገር እንዳደንቅ ያደርገኝ ሥለነበር ነው፡፡ በእርግጥ ከጣሊያን እንደመጣሁ ባሠብኩት ፍጥነት አይደለም ይሄንን ቢዝነስ የጀመርኩት፡፡ ለምን? እንደመጣሁ አባቴም እንዳግዘው ይፈልግ ነበር፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ “ፓስኩዋጁሴፔ” የተሠኘ የብረታ-ብረት እና አሉሚኒየም ማምረቻ ድርጅት ሥለነበረው እዛ ውስጥ እየሠራሁ ቢዚ ሆኜ ቆየሁ፡፡ ይህ የአባቴ ድርጅት አሁንም አለ፡፡ በቅርቡ 50ኛ ዓመቱን ልናከብር እየተዘጋጀን ነው፡፡ በዚህ ድርጅት ስሠራ ብዙ ነገሮችን እያጠናሁና እየተዘጋጀሁ ቆይቼ፣ ቱሪዝሙን የዛሬ ስምንት ዓመት እውን ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀመርኩ፡፡ አፍሪካ ቫኬሽን ክለብ እንዴት ተመሠረተ? ጊዜን መጋራት (time sharing) ጣሊያን እያለሁ በስፋት የማውቀው ሥራ ነው፡፡ አውሮፓም አሜሪካም በጣም የሚሠራበት ቢዝነስ ነው፡፡ ለቤተሠብ መዝናናት በጣም አመቺ የሆነ ዘርፍ ነው፡፡
በውጭ አገር በጣም ከመለመዱ የተነሳ ጥንዶች ተጋብተው የቤት ዕቃ ሁሉን ነገር ሲያሟሉ ጊዜን መጋራትንም ለመግዛት እንደ አንድ ፕሮግራም እቅዳቸው ውስጥ ያካትቱታል፡፡ አንዱ የጋብቻው አካል ያደርጉታል ማለት ነው፡፡ ለምን መሠለሽ በውጭው አለም በዓመት አንዴ ቫኬሽን መውጣት በጣም የተለመደ ነው፡፡ ለ15 ቀናት ያህል የማይዘጋ ድርጅት የለም፡፡ ሁሉም ቫኬሽን ይሄዳል፡፡ የአፍሪካ ቫኬሸን ክለብ ሠራተኞችም እረፍት ይወጣሉ? በትክክል! እናደርጋለን፡፡ ይኼ አጠቃላይ ፅንሠ ሐሣቡ ሁሉም ከቫኬሽንና ከእረፍት ሲመለሱ በአዲስ ኃይልና መንፈስ ጥሩ ሥራ ይሠራሉ ነው የሚባለው፡፡ ለድርጅቱም ውጤት ያስገኛል፡፡ ያኔ ታዲያ በቫኬሽን ጊዜ ሁሉም መጐብኘት ስለሚፈልግ ሪዞርት፣ ጥሩ ጥሩ የመዝናኛ ቦታዎች ማግኘት ይፈልጋል፡፡ ይሄ ደግሞ ትንሽ ውድ ስለሚሆን በተለይ ለደሞዝተኛ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለዚህ ለማረፊያና ለመዝናኛ ለ20 ዓመት የሚያገለግል አንድ ጊዜ ኢንቨስት ማድረግ በጣም ጠቃሚ ነገር ነው፡፡ አባል የሚኮነው እንዴት ነው? የአባልነት ስምምነት ይፈርምና ግዢ ይፈጽማል፤ እኛም ሰርቲፊኬት እንሰጠዋለን! ለ20፣ ለ15 አሊያም ለ12 ዓመት አባልነት ሊገዛ ይችላል፡፡ እናንተ ስትጀምሩ ለ45 ዓመት ሁሉ ትሸጡ ነበር ይባላል፡፡
እውነት ነው? ትክክል ነው ስንጀምር ለ45 ዓመት ነበር፤ አሁን ለ20 ዓመት አድርገነዋል፡፡ ከ45 ዓመት ወደ 20 ዓመት ያሻሻላችሁበት ምክንያት ምንድን ነው? በጀመርንበት ጊዜ 45 ዓመት ስንለው ሰው ይደነግጣል፡፡ ምክንያቱም 45 ዓመት ረጅም ጊዜ ነው፡፡ እኛም እናስተዋውቀው ብለን እንጂ ለአሠራር አመቺ አልነበረም፡፡ 45 ዓመት ሙሉ ተከታትሎ ሰው አንድ ቦታ ላይቀመጥ ይችላል፡፡ ወደ 20 ዓመት ሲሻሻል ግን ዓመቱ አጠር ያለ ስለሆነ እስከዛ ድረስ ያለውን ጠቀሜታ አይቶ ለመቀጠልም ላለመቀጠልም ሊወስን ይችላል፡፡ ወደ 20 ዓመት ስናሳጥረው ያየነው ለውጥ ብዙ ነው፡፡ ሰው 20 ዓመቱን ከእኛ ጋር ቆይቶ ሌላ መቀየር ሊፈልግ ይችላል፡፡ በእነዚህ ምክንያቶች ነው ያሳጠርነው፡፡ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ የአባልነት ግዢዎች አሏችሁ፡፡
ልዩነቱ ምንድን ነው? በዋናነት የሚለየው የምትጠቀሚበት ጊዜ ነው። ለምሣሌ የወርቅ አባልነትን እንውሰድ፡፡ በዚህ ጊዜ ሁሉም ቫኬሽን መውጣት የሚፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ለምሳሌ ቤተሰቦች የልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚዘጋበት፣ በአንድ ላይ ለመዝናናትና ለማረፍ ምቹና ውድ ጊዜ በመሆኑ በዋጋውም ትንሽ ወደድ ይላል፡፡ በተለይ የበዓላት ጊዜ የሚወጣው ቫኬሽን ሁሉም የሚፈልገው ጊዜ ስለሆነ የወርቅ ነው፡፡ የብር ደግሞ ትንሽ መካከለኛ ነው፡፡ ይኼ ማለት ቫኬሽን የሚኬድበትም የማይኬድበትም ጊዜ ነው፡፡ የነሐስ ደግሞ የሚመቸው ውስን የቫኬሽን መውጫ ጊዜ ለሌላቸው ነው፡፡ ለምሣሌ ጡረተኞች የሚጠቀሙበት ወቅት ነው፡፡ በውጭው ዓለም የነሐስ አባልነትን የሚጠቀሙት ጡረተኞች ናቸው፡፡ አባልነቱን የሚገዙትም ከወርቅና ከብሩ በጣም በወረደና በረከሠ ዋጋ ነው፡፡ በአብዛኛው ልጅ የሌላቸውና ጡረተኞች በጣም ይጠቀሙበታል፡፡ የወርቅ፣ የብርና የነሐስ የአባልነት ግዢ ምን ያህል እንደሆነ ሊነግሩን ይችላሉ? የማረፊያው ቤቱስ ምን ምን ነገሮችን ያሟላ ነው? ቤቱ የመኖሪያ ቤት መልክ ያለውና በሁሉም ነገር የተሟላ ነው፡፡ መኝታ፣ መታጠቢያ፣ ሳሎን፣ ኪችን … ሁሉም አለው፡፡
የሆቴል ክፍል ሳይሆን የመኖሪያ ቤት መንፈስ ያለው ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ አብስሎ መጠቀም ይቻላል፡፡ ቤቱን ብቻ ነው የሚጠቀሙት። “ለእረፍት መጥቼ መቀቀል አልፈልግም” ካሉ ከቤቱ ውጭ ባለው ሬስቶራንት ከፍለው መጠቀም ይችላሉ። እኛ ቤቱን ያዘጋጀነው ሰው ቫኬሽን ቢወጣም የራሱ ቤት እንደሆነ እንዲሰማው ነው፡፡ በዓመት ውስጥ ለአንድ ሳምንት መጠቀም ይችላሉ፡፡ በቃ ለ20 ዓመት ከፍለውበታል፡፡ የራሳቸው ነው፡፡ የራሣቸውን ቤት እንዲመለስላቸው ሶፋ፣ ቴሌቪዥን ሁለት መኝታ ቤት ሁሉን ያሟላ ነው፡፡ የላንጋኖው ሪዞርታችን ከቤቱ ወጣ ሲባል የተለያዩ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የተለያዩ ሬስቶራንቶችና ሁሉንም ያሟላ ነው ፡፡ እዚህ ላይ አያይዤ የምነግርሽ ለቤቱ በአባልነት አንዴ ከገዛሽ በኋላ በየዓመቱ ደግሞ ለአስተዳደር የምትከፍይው አለ፡፡
በአባልነት ክፍያው ውስጥ የማይካተት ማለት ነው? በአባልነት የምትከፍይው የቤቱን ብቻ ነው፡፡ የአስተዳደር ክፍያው ሌላ ነው፡፡ አንቺ አንዴ ለቤቱ ከፍለሽ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ነው የምትመጪው። ቤቱ በየጊዜው መጽዳት አለበት፡፡ ለዚህ የፅዳት ሠራተኛ ያስፈልገዋል፡፡ የጥበቃ ሠራተኛ አለ፣ የጓሮ እና የጊቢ ፅዳትና ውበት እንክብካቤ ያስፈልገዋል፡፡ በአጠቃላይ የሪዞርቱ ሠራተኞች ደሞዝተኞች ናቸው። ይህን መክፈል ያለበት አባልነት የገዛው ሰው ነው። እነዚህ ነገሮች በእንክብካቤ ተይዘው ካልጠበቁት በዓመቱ ሲመጣ የሚያዝናናውና የሚያስደስተው ነገር አያገኝም፡፡ በውጭው ዓለም በአሮጌው ዓመት መጨረሻ አሊያም በአዲሱ ዓመት መጀመሪያ የዓመቱን የአስተዳደር ክፍያ ይፈፅማሉ፡፡ ይህን ሲያደርጉ ለመዝናናት ሲሄዱ ወጪያቸው የሚሆነው የመዝናኛና የቀለብ ብቻ ይሆናል፡፡ ቆይታቸውም በጣም አስደሳች ይሆናል፡፡ የአባልነት ክፍያው ምን ያህል ነው? ስንጀምርና አሁን ያለው ክፍያ የተለያየ ነው፡፡ እኛ ቢዝነሱን ለማስተዋወቅና ቶሎ ወደ ስራው ለመግባት ስንል በጣም በትንሽ ዋጋ ጀምረነው ነበር፡፡ ለምሣሌ 20ሺህ ከፍሎ ለ45 ዓመት አባልነት የገዛ ሁሉ ነበር፡፡ አሁን እንደዛ አይደለም፡፡ ያኔ ለፕሮሞሽን ከ20 ሺህ ብር እስከ 120ሺህ ከብር እስከ ወርቅ ለ45 ዓመት ሸጠናል። አሁን በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ስለሆነ ዋጋው ውድ ነው አዲስ እያስገነባን ላለነውና ለማስፋፊያው አዲስ ዋጋ ነው ያወጣነው፡፡
አንድ አባል በዓመት ቫኬሽን መውጣት ባይፈልግ ማከራየት ወይም ለሌላ ቤተሠብ እንዲዝናና መፍቀድ ይችላል? አባሉ፣ ለቤተሰቡ ሊያስተላልፈው ወይም ሊያከራየው ይችላል፡፡ አሊያም ክፍት ሆኖ ሊቆይ ይችላል፡፡ የምናከራየው እኛ ሳንሆን ራሳቸው የቤቱ ባለቤቶች ናቸው ማከራየት የሚችሉት፡፡ በማከራየት ጉዳይ ከአባሎቻችን ጋር አለመግባባቶች ተፈጥረው ነበር፡፡ ማከራየት ትችላላችሁ ስንል እኛ የምናከራይላቸው መስሏቸው ነበር፡፡ እኛ ይህንን ማድረግ አንችልም በሥራ ፈቃዳችንና በታክስ አከፋፈላችን ላይ ችግር ያመጣብናል፡፡ ራሱ ቤቱን ለ20 ዓመት የገዛው ሰው ለፈለገው የመስጠት፣ የማከራየት አሊያም በቫኬሽን ጊዜ ሳይመጣ ጊዜውን ዝም ብሎ ማሳለፍም የራሱ የባለቤቱ ውሳኔና ምርጫ ነው፡፡ ቤቱን የገዛ አባል ከአገር ቢወጣ፣ በአጠቃላይ ከጊዜ መጋራቱ መልቀቅ ቢፈልግ ለሌላ ቤተሰብ አሳልፎ የመስጠት፣ የመሸጥ ወይም የማከራየት መብት አለው? በሚገባ! እንደገዛው የዓመት መጠን ከላይ የጠቀስሻቸውን ነገሮች የማድረግ መብት አለው፡፡ 45 ዓመት የገዛ ከሆነ ዓመቱ እስኪያልቅ ለሌላ የማውረስ፣ የማከራየትና የመሸጥ መብት አለው፡፡
ውላችን ይህንን ግልፅ ባለ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ በእናንተ አሠራር ላይ የሚነሱ በርካታ ቅሬታዎች አሉ፡፡ አንዱ ቅሬታ፣ ገንዘብ መሰብሰብ የጀመራችሁት ሪዞርቱን ከመገንባታችሁ በፊት ነበር፡፡ እንደውም “ተጭበረበርን፣ ውሸት ነው” እያሉ ሰዎች ሲያማርሩ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ይላሉ? ስለዚያ ጊዜ ባታነሺብኝ ጥሩ ነበር፡፡ ያ ጊዜ ብዙ ስቃይ ያየሁበት ጊዜ ነበር፡፡ ታምሜ ሁሉ ነበር፡፡ እኛ በውጭው ዓለም እንዳለውና እንደተለመደው መስሎን በአንድ ዓመት ውስጥ ሠርተን እንጨርሠዋለን ብለን ነበር፡፡ ስንጀምር በእጃችን ካለው ብር በተጨማሪ ለአባልነት ከሚከፈለው ጋር አንድ ላይ አድርገን ልንገነባ እንዳሠብን ግልፅ አድርገናል፡፡ ችግሩን የፈጠረው በአንድ ዓመት ውስጥ እንከፍታለን ብለን የፈጀብን ግን ሦስት ዓመት ተኩል መሆኑ ነው፡፡ ያኔ ሰው ሁሉ በጣም ደንግጦ ነበር፡፡
ችግራችሁ ምን ነበር? ችግራችን ብዙ ነበር፡፡ አንደኛው ሥራው የሚጀመረው ጫካ ውስጥ ነው፡፡ ጫካ ገብተሽ ስትሠሪ፣ አሠራሩና ሲስተሙ ሁሉ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ የተቀናጀ ነገር የለም፣ ሠራተኛውም “ከከተማ ውጭ ሥራ” ስትይው ደስ ብሎት አይሄድም፡፡ ጥሩ ሠራተኛም ማግኘት ሌላው ፈተናችን ነበር። ጫካ ስለሆነ ለሠራተኛ የምንከፍለው ከኖርማሉ ሦስት እጥፍ ነበር፡፡ ለስራ ከወሰድናቸው በኋላ ሠልችቷቸው ሥራ አቋርጠው የሚመለሱ ነበሩ። ሌላው ችግር የአካባቢው ሰው እዚያ ቦታ ላይ ስንጀምር ደስተኛ አልነበረም፣ የጥበቃ ችግርም ነበረብን፡፡ የአካባቢው ሰው ደስተኛ ያልሆነበት ምክንያት ብዙ ሰው ሪዞርትና መዝናኛ ለመስራት ብዙ መሬት ወስዶ አልሠራም። እኛንም “መሬታችንን ቀምተው ወይ አይሠሩ ወይ እኛ አልተቀመጥን፣ በከንቱ ነው” የሚል ጥርጣሬ ነበረባቸው፡፡
እኛንም መሬት ገዝተው ዝም እንዳሉት የመቁጠር ችግር ነበረብን፡፡ በኋላ እየተሠራና እየተስፋፋ ያካባቢው ሰው የስራ እድል እያገኘ መጠቀም ሲጀምር፣ ተቀይረው በጣም ደጋፊያችን ሆኑ፡፡ ምክንያቱም ቋሚ ስራ ያገኙ አሉ፤ ስልጠና ያገኙ አሉ፤ በአጠቃላይ ብዙ የአካባቢው ህዝብ ህይወቱ ተቀይሯል፡፡ ክስ የመሠረቱ ደንበኞች እንደነበሩም ሰምቻለሁ። ችግሩን እንዴት ፈታችሁት? እርግጥ ነው፤ ብራችንን ሰብስበው ጠፉ፣ ምንም አይሠሩም፣ የሚል በርካታ ወሬና ክስ ነበር። እኛም በተቻለን መጠን ሠውን ለማሳመን ብዙ ጥረት ሥናደርግ ነበረ፡፡ አምነውንና ታግሰውን የቆዩ አሉ፡፡ ያላመነንም ብዙ ነበር፡፡ ሌላው ቀርቶ ሠርተን ጨርሠን ስንከፍት እንኳን አምኖን የመጣ ሰው በጣም ጥቂት ነበር፡፡ በኋላ ግን በጣም ጥሩ ሪዞርት መሠራቱ ሲወራ ነው መምጣት የጀመሩት።
በተለይ በተከፈተ በመጀመሪያው ዓመት ተጠቃሚ የነበሩት አባላት ጥቂት ነበሩ፡፡ ግን እኮ ሁሉም መከፈቱን ሠምተዋል፤ እኛም አስተዋውቀናል። ግን አልመጡም አላመኑበትም ነበር፡፡ ክስን በተመለከተ በቀጥታ የከሰሰን ባይኖርም፣ በአሠራሩ ላይ ብዙ አለመግባባቶች ነበሩ፡፡ በተለይ ከዓመታዊ የአስተዳደር ክፍያ ጋር ጭቅጭቆች አሁንም አሉ፡፡ ለምሣሌ “ስሄድ ነው እንጂ ለምን ቀድሜ እከፍላለሁ፣ በዚህ ዓመት ሄጄ ስላልተጠቀምኩ አልከፍም” የሚሉ አሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ነገር ደግሞ አይሠራም፡፡ አሁን ምን ያህል አባላት አሏችሁ? ወደ 1900 ያህል አባላት አሉን፡፡ ከእነዚህ አባላት መካከል አብዛኞቹ ደስተኞች ቢሆኑም አንዳንዶቹ እስካሁን ያልረኩና አሠራሩ ያልገባቸው አሉ፡፡ በዚህም ምክንያት የአባልነታቸውን እንጂ የአስተዳደር ክፍያ እስካሁን አልከፈሉም፡፡ በዚህ የተነሳ አለመግባባቶች አሉ፡፡ “እኛ እንደሚከፈል አናውቅም” ነው የሚሉት፡፡ ይኼ ሊሆን አይችልም፤ ምክንያቱም እኛ ኮንትራት ውሉ ላይ አስቀምጠናል። አንዳንዶቹ “ኮንትራቱን አላነበብኩም” የሚል አሳማኝ ያልሆነ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡ ሌላው መክፈል እንዳለበት ያውቅና “ከሄድኩኝና ከተጠቀምኩኝ ነው የምከፍለው” የሚል አለ፡፡ በዚህም በኩል ሌላ ችግር አለብን ማለት ነው፡፡ የአስተዳደር ክፍያው ምን ያህል ነው? በየዓመቱ ሶስት ሺህ ብር ነው፡፡ ይኼ ሶስት ሺህ ብር እንግዲህ ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ ለጥበቃ፣ ለፅዳት፣ ለአትክልተኛና ለጥገና ሠራተኞች የሚከፈል ነው፡፡ በላንጋኖ 114 ቋሚ ሠራተኞች አሉን፡፡ ለእነሱ ደሞዝ እንከፍላለን፣ በተጨማሪም መብራትና ውሃ አለ፡፡
ውሃው በደንብ ተጣርቶ፣ ንፁህ ሆኖ ነው የሚቀርበው፡፡ ውሃው የጫካ ስለሆነ በደንብ መታከም አለበት፡፡ ማከሚያው ደግሞ ውድ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ እናወጣለን፡፡ ሰው ኖረ አልኖረ መብራት ይበራል፡፡ ሠራተኛው ይሠራል፤ ማኔጅመንቱም አለ፤ ለዚህ ሁሉ መከፈል አለበት፡፡ መጀመሪያውኑ የወርቅም የብርም የነሀስም የአባልነት ክፍያ ሲከፍሉ ለምን አልተደመረም? ድጋሚ የአስተዳደር ብሎ መጠየቁስ ለምን አስፈለገ? በዓለም ላይ ባለው የጊዜን መጋራት ቢዝነስ ውስጥ አሁን ያልሽው ነገር አይደረግም፡፡ ምን መሠለሽ የሚደረገው? የቤቱ ክፍያ (የአባልነቱ ክፍያ) የታወቀ ወጪ ነው፡፡ ምክንያቱም የተሠራ ቤት ነው። ይኼኛው ግን በየጊዜው እየበዛና እያደገ የሚሄድ ወጪ ነው፡፡ ለምሣሌ ዛሬ የምትከፍይው የሠራተኛ ደሞዝና የዛሬ ዓመት የምትከፍይው እኩል አይደለም። የመብራት ክፍያም ይጨምራል፣ ለጥገና የሚወጣው ወጪና የሚቀየሩ የቤቱ እቃዎች ወጪም እንዲሁ ብዙ ነው፡፡ መብራት አለ ቢባልም በአብዛኛው የምንጠቀመው ጀነሬተር ነው፡፡ የናፍጣውን ወጪ አስቢው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ይጨምራል፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ የአስተዳደሩ ወጪ ከአባልነት ክፍያው ጋር ይካተት ማለት ተገቢ አይደለም፤ አይደረግምም፡፡
በዓመት ሶስት ሺህ ብር ደግሞ በጣም ፌር የሆነ ክፍያ ነው፡፡ ለምሣሌ የሲሊንደር ጋዝን ከአስተዳደር ወጪ አውጥተን አባሎች ለአንድ ሳምንት ሲመጡ ብቻ የሚጠቀሙበትን አሳውቀን ማቅረብ ጀመርን። ለምን? ቢባል፤ በየጊዜው ዋጋው እየናረ ስለሆነ መገመት አቃተን፡፡ አንዳንድ ቤተሰቦችም ለእረፍት መጥተን ለምን ምግብ እናበስላለን? በሚል ሬስቶራንት የሚጠቀሙ አሉ፡፡ እነሱ ደግሞ ባልተጠቀሙት ጋዝ ለምን የአስተዳደር ወጪ ውስጥ እንከታቸዋለን በሚል ነው ያወጣነው፡፡ ሪዞርታችሁ ባለ ሥንት ኮከብ ነው? አጠቃላይ ይዘቱስ ምን ይመስላል? ሪዞርቱ ባለ አምስት ኮከብ ሆኖ ነው እውቅና የተሠጠው፡፡ 40 ቤቶች አሉት፡፡ 30 ቤቶች ስድስት ስድስት ሰው ነው የሚይዙት፡፡ 10 ቤቶች ደግሞ ስምንት ቤተሠብ የመያዝ አቅም አላቸው፡፡ በቅርቡ ስምንት ያህል ሲንግል ክፍሎች ሠርተናል፡፡ አሁን ደግሞ ባልና ሚስት እና ሁለት ልጆች በአጠቃላይ 4 የቤተሠብ አባላት የሚችል እንዲሁም ለባልና ሚስት ብቻ የሚሆኑ ቤቶችን እየገነባን እንገኛለን፡፡ የማስፋፊያው እቅዳችን ይሄ ነው፡፡ እስካሁንም አልተቀረፈም ከሚባሉ ችግሮች ውስጥ የሽያጭ ሠራተኞቻችሁ በየሞሉ፣ በየሱፐርማርኬቱ ወይም ባለሀብቶች ይገኙባቸዋል በተባሉ ቦታዎች እየሄዱ ሰዎችን ያናግራሉ፡፡
ብዙ ሰዎች አቀራረባቸው ምቾት አይሠጥም፣ ነፃነትን ይጋፋል የሚሉ ቅሬታዎችን ያሠማሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በደንብ ያውቁታል ብዬ አስባለሁ… እርግጥ ነው አሁንም ቅሬታዎቹ አልፎ አልፎ አሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ሠራተኞቻችንን ስናሠማራ የሚያግናሩትን ሰው እንዴት መቅረብ እንዳለባቸው፣ ትህትናቸው ምን መምሰል እንዳለበት በደንብ እናሠለጥናቸዋለን፡፡ ነገር ግን የሁሉም ሰው ምላሽ እኩል አይሆንም፤ ግማሹ “ኦ! አዲስ አሠራር ነው፤ እንዴት ጀመራችሁ” ብሎና ተገንዝቦ፣ ጊዜ ሰጥቶ ከተስማማው ይቀጥላል፤ ካልተስማማው አመስግኖ ይለያል፡፡ ምክንያቱም ያኔ ይህን ቢዝነስ የጀመርነው የመጀመሪያዎቹ እኛ ነን፡፡ አሁን እንኳን ሼር የሚሸጡ፣ ቤት ሠርተው የሚሸጡ በርካታ ድርጅቶች እየሠሩበት ነው፡፡ እና ከላይ እንዳልኩት ስራው አዲስ እንደመሆኑ አድንቀው የሚሄዱ እንዳሉ ሁሉ ተሳድበው የሚሄዱም አሉ፡፡ ስድቡ አሁንም አለ፡፡ አሁንም “ሰው መረበሽ አታቆሙም እንዴ?” የሚሉና የሚበሳጩ አሉ፡፡ ይህንን ስትራቴጂ ካልቀየርን በስተቀር ያሉት ችግሮች መቀጠላቸው አይቀርም፡፡
ምክንያቱም በዚህ መንገድ ካልሆነ ሰውን ማግኘትና አባሎቻችንን ማብዛት አንችልም፡፡ ስለዚህ በየመንገዱ እየዞርን ነው የምንሠራው፡፡ ካልሆነ ሥራችን መቆሙ ነው!! ይህ እንዲሆን አንፈልግም፡፡ በእኛ በኩል ሠራተኞቻችን በአግባቡና በትህትና ሠዎችን እንዲያናግሩና በአግባቡ ውጤት እንዲያመጡ በስልጠናና በመሠል ጉዳዮች አቅማቸውን ማሣደግ ነው የሚጠበቅብን፡፡ የምናናግራቸው ሰዎች ፈቃደኛ ሲሆኑ ፎርም ይሞላሉ፤ ስልክ ይሰጣሉ፡፡ በቢሯችን የቴሌ ማርኬቲንግ አገልግሎት አለ፡፡ ማርኬተሮቹ ደውለው ቀጠሮ ይይዙና ሰውየው ወደ ቢሯችን መጥቶ ጠቅላላ ስለ አፍሪካ ቫኬሽን፣ ስለ ቱሪዝም ስራችን፣ ስለ ምንሰጠው አገልግሎት ሠፊ ማብራሪያ ይሰጠዋል፡፡ ከዚያ በኋላ አባልነቱን መግዛትና አለመግዛት እንደሰውየው ሁኔታ ይወሠናል፡፡ ሠራተኞቻችሁ መንገድ ላይ የማያውቁትን ሰው ሲያናግሩ “ሰርፕራይዝ፤ ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ የመሄጃ ሎተሪ ወጥቶልሃል” በማለት ሰውን ያስደነግጡ ነበር፡፡ በዚህ አሠራር ግማሹ ይስቃል፤ ሌላው ተበሳጭቶ ይሄድ እንደነበር ከብዙዎች ሰምቻለሁ፡፡
ይህን ነገር እርሶ ያውቁት ነበር? ምንስ ማለት ነው? አዎ አውቀዋለሁ! ያ የእኛ የማርኬቲንግ ሲስተም ነው፡፡ ሰዎችን ለመሳብ ስንል ሎተሪ ደርሶሀል ነበር የምንለው፡፡ ሎተሪው ቫኬሽን ነበር፡፡ መጀመሪያ ላይ ኢንቨስት ያደረግነው በዛ ላይ ነው፡፡ እንደምታውቂው ስራውን ስንጀምር በዚህ መልኩ የሚሠራ ሆቴል ስለሌለ ጊዜን መጋራት የሚለውን ነገር ማስረዳት እንፈልግ ነበር፡፡ ስለዚህ ኬንያ ቅርብ ጐረቤታችን በመሆኑ ከአንድ ሆቴል ጋር ተነጋግረን ወደዚያ ሰዎችን እንልክ ነበር፡፡ ሰው እዛ ሄዶ የጊዜ መጋራት ሆቴል እንዴት እንደሚሠራ፤ በአገራችን ሲጀመር አባል እንዲሆን የሚያደርገውን ግንዛቤ እንዲያገኝ እናደርግ ነበር፡፡ በእርግጥ ሰው አያምንም ነበር፡፡ እኛ አድርገነዋል። ሆቴል አይሠሩም ብለውን ነበር፤ ሠርተን አሳይተናቸዋል፡፡ በዚህ ሎተሪ አማካኝነት ብዙ ሰው ኬንያ ሄዷል፡፡ ቅርብ በመሆኑ የአውሮፕላን ቲኬቱም ብዙ አያስከፍልም፡፡ በራሱ ምርጫ ደቡብ አፍሪካ ይሁንልኝም ካለ አማራጭ እንሰጥ ነበር፡፡ ማረፊያ በነፃ ነበር የሚያገኙት፡፡ እግረ መንገዳቸውን ስለ ጊዜ መጋራት ስራ ተገንዝበው መጥተዋል፡፡ አሁን ግን የዚህ ፍላጐት ላለው ሰው ላንጋኖ ወዳለው ሪዞርታችን እንልካለን፡፡ በአንድ ወቅት የላንጋኖውን ዓይነት ሪዞርት በባህርዳር እና በጐንደር እንገነባለን ብላችሁ ነበር፡፡ ከምን አደረሣችሁት? ገና አልጀመርነውም፡፡ ነገር ግን እቅዱ አለን፡ በጐንደርና ባህርዳር ብቻ ሳይሆን ሌላም ቦታ ይኖረናል፡፡ ነገር ግን የላንጋኖው ሪዞርታችን በ45ሺህ ሜትር ካሬ ላይ ያረፈ ነበር፡፡
አሁን ወደ 70 ሺህ ሜትር ካሬ ለማስፋፋት ይሁንታ አግኝተን ቀደም ብዬ እንደነገርኩሽ የማስፋፊያ ግንባታዎች ጀምረናል። በዚህ ምክንያት ትኩረታችንን እዚህ ላይ ስላደረግን እንጂ የተያዙት እቅዶች ጊዜ ጠብቀው እውን ይሆናሉ፡፡ ባለፈው ዓመት “ዘና ብዬ” የተባለ ፕሮጀክት ከፍታችሁ “Resort Condimenuim International” (RCI) ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር የጋራ ቢዝነስ እየሠራችሁ ነበር፡፡ እስቲ ስለሱ ይንገሩኝ… RCI የሆቴል ባለቤቶች ሳይሆኑ የኤክስቼንጅ ሥራ የሚሠሩ ማርኬተሮች ናቸው፡፡ ምን ማለት ነው? እነሱ ማርኬቲንግ ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ለምሣሌ አንቺ ላንጋኖ የአባልነት ከፍለሽ ገዝተሻል፤ ሌላው ታይላንድ ውስጥ እንደዚህ የገዛ ካለ፣ እሱ ኢትዮጵያ መጥቶ በአንቺ ቤት ሲያርፍ አንቺ ደግሞ ታይላንድ ሄደሽ ሰውየው የገዛው ቤት ውስጥ ቫኬሽን ታሳልፊያለሽ ማለት ነው፡፡ ይህን የማለዋወጥ ሥራ ኤጀንት ሆነው የሚያገናኙት RCI የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ አንቺ ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት ላንጋኖ መሄድ ሊሠለችሽ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሜሪካ ሄደሽ ተመሣሣይ ቤት ካላቸው ጋር እነሱ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ አንቺ ቤት ያርፋሉ፤ አንቺም እነሱ ቤት ታርፊያለሽ፡፡ ስለዚህ RCI ይሄንን ስራ የሚሠራው በዓለም ላይ የጊዜ መጋራት ሆቴል ካላቸው ጋር ነው፡፡ አሁን በእነርሱ በኩል የእኛም አባላት ወደተለያየ አገር በልውውጥ እየሄዱ ነው፤ ከሌላውም ዓለም ወደ ላንጋኖ ይመጣሉ፡፡
ይሄ በተለይ ለአገራችን የቱሪዝም ኢኮኖሚ መልካም አጋጣሚ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለዚህ “ዘና ብዬ” ከአፍሪካ ቫኬሽን ክለብ ተለይቶ ከRCI ጋር የሚሠራ ሌላ ቢዝነስ ነው፡፡ RCI የታወቀ ዌብ ሳይትና ካታሎግ አለው፡፡ አዲስ የጊዜ መጋራት ሆቴሎች ሲከፈቱ እየተከታተለ ያስተዋውቃል፤ ያለዋውጣል፡፡ የእኛን ደረጃ ከሌላው ዓለም ጋር ተመጣጣኝ ነው ወይ? የሚለውን በየጊዜው ይፈትሻሉ፤ ያረጋግጣሉ፡፡ በአጠቃላይ RCI በዓለም ላይ ከፍተኛ ተቀባይነት ያለው የቱሪዝም ኤጀንት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ከእኛ እንኳን እስካሁን ወደተለያየ ዓለም 300 ያህል ሰዎች በልውውጥ ሄደዋል፤ ወደፊትም ብዙ ሥራ እንሠራለን ብለን እናምናለን፡፡
ካስተማሩ አይቀር እንዲህ ነው!
በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ በወረዳ 3 ዘንድሮ የተከፈተው ሐኒኮምብ አካዳሚ የተባለ (ከኬጂ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ የሚያስተምር) ት/ቤት ገና ከጅምሩ ያሳየው በብሩህ ተስፋና ራዕይ የተሞላ አዎንታዊ እንቅስቃሴ በእጅጉ ስለማረከኝ ነው እቺን መልዕክት ለመፃፍ የተነሳሁት፡፡ በነገራችን ላይ ልጄን ቀደም ሲል አስገብቼው ከነበረው ት/ቤት በማስወጣት ነው እዚህ አዲስ ት/ቤት ያስገባሁት፡፡ እግዜር ይስጣቸው እነሱም አላሳፈሩኝም፡፡ ልጄን በምፈልገውና በምመኘው የጥራት ደረጃ እያስተማሩልኝ ነው - ያውም በፍቅርና በሥነምግባር እየኮተኮቱ፡፡ በሌላው ት/ቤት ያላየሁት መምህራንና ወላጅ መረጃ የሚለዋወጥበት “ኮሙኒኬሽን ቡክ” በእጅጉ አስደምሞኛል - የልጄን የትምህርት አቀባበልና አጠቃላይ ሁኔታ በቀላሉ እንድከታተል አስችሎኛል፡፡ በህዳር ወር መጨረሻ ላይ ት/ቤቱ “ስፔሊንግ ቢ” የተባለ የተማሪዎች የስፔሊንግ ውድድር አካሂዶ እንደነበርም መጥቀስ እፈልጋለሁ - ት/ቤቱን ለምን እንዳደነቅሁት በቅጡ እንድትረዱልኝ፡፡
በውድድሩ የተካፈሉ ተማሪዎች አሸናፊ ለመሆን ያሳዩት እልህ አስጨራሽ የፉክክር ስሜት አስገራሚና በስሜት የሚያጥለቀልቅ ነበር፡፡ በተለይ የልጁን የትምህርት ሁኔታ በቅርበት ለሚከታተል ለእንደኔ ያለው ወላጅ! በውድድሩ 1ኛ በመውጣት ያሸነፈችው ተማሪ፤ ዋንጫ እና የአንድ አመት (ከክፍያ ነፃ) የትምህርት እድል አግኝታለች- እንደሽልማት፡፡ እንዲህ ያለው የውድድር ስሜትና ሽልማቱም ጭምር ተማሪዎቹ በትምህርታቸው ላይ እንዲተጉ ያነሳሳቸዋል የሚል እምነት ስላለኝ በእጅጉ የምደግፈውና የማበረታታው ነው፡፡ የሚገርማችሁ ደግሞ ት/ቤቱ ልጆቻችንን ብቻ አይደለም የሚያስተምርልን፡፡ እኛን ወላጆችንም ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ሁለቴ አሰልጥኖናል - ልጆችን እንዴት በፍቅር ማሳደግ እንደሚገባ፣ በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ከቤት ስለምናደርግላቸው ድጋፍ እና በሌሎች ተያያዥ ርዕሰጉዳዮች ዙሪያ እነዶ/ር አቡሽን በመሳሰሉ የሞቲቬሽን አሰልጣኞች እጅግ ጠቃሚ ትምህርት ተሰጥቶናል፡፡
በመዲናችን ሲሰሙት የሚያስደነግጥ ክፍያ የሚጠይቁና “ስማቸው የከበዳቸው” አንዳንድ ቀሽም የግል ት/ቤቶች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ምናልባት ሐኒኮምብ ያስደነቀኝም ለዚህ ሊሆን ይችላል፡፡ በመጨረሻ ልጄን እዚህ ት/ቤት በማስገባቴ የተሰማኝን ልዩ ደስታና ኩራት በመግለፅ ለልጄ ፍቅር እየለገሱ የሚያስተምሩልኝን በሥነምግባር የታነፁ መምህራንና የት/ቤቱን አስተዳደር ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ሌሎችም ት/ቤቶች ከሃኒኮምብ ብዙ ሊማሩ ይችላሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ “ካስተማሩ አይቀር እንዲህ ነው” አደራ ታዲያ ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንዳትሄዱብን! (የተማሪ ጆሴፍ አባት)
የጋዜጠኛ እስክንድርና የእነ አንዷለም አራጌ ይግባኝ እልባት አላገኘም
የጋዜጠኛ ተመስገን ጠበቃ ተጨማሪ ጊዜ ጠየቁ በከፍተኛው ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት፣ በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶችና ሽብር ለመፈፀም ከሚፈልጉ ሰዎች ጋር ሰርታችኋል በሚል ተከሰው የተፈረደባቸው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እንዲሁም የአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የነበሩት የእነ አንዷለም አራጌ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረቡት የይግባኝ አቤቱታ በረቡዕ እለቱ ቀጠሮ እልባት ሳያገኝ ተላለፈ፡፡ በእለቱ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የችሎት አዳራሽ ውስጥ የታሳሪ ቤተሰቦች፣ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ችሎቱን ለመከታተል ቦታውን ሞልተው የዳኞችንና የታሳሪዎችን መምጣት እየተጠባበቁ ነበር፡፡ ቢጠባበቁም ግን አልተሳካም፡፡
በመጨረሻ የእነ አንዷለም ጠበቆችና አቃቤ ሕጉ ወደ ጽ/ቤት ተጠርተው ሲሄዱ ነው፤ ምን እንደተፈጠረ ለማወቅ የተወሰኑ ጋዜጠኞችና የታሳሪ ቤተሰቦች ተከትለዋቸው የሄዱት፡፡ የመሀል ዳኛው አቶ ዳኜ መላኩ፣ ለታሳሪ ጠበቆችና ለአቃቤ ህግ ባቀረቡት ማብራሪያ፣ በዚሁ መዝገብ 30 ያህል ሰዎች ይግባኝ የጠየቁ መሆናቸውን፣ መዝገቡም ለ10 ቀን ዘግይቶ እንደደረሳቸው ጠቅሰዋል፡፡ “መዝገቡ ሰፊ ነው፤ ጉዳዩን ረጋ ብለንና ሰፊ ጊዜ ወስደን ልንመረምረው ይገባል” በማለት የተናገሩት የመሃል ዳኛው፤ ለመጋቢት 30 ቀን 2005 ተለዋጭ ቀጠሮ እንደሰጡ ገልፀዋል፡፡ ዳኛው ከዚህም በተጨማሪ፣ ማረሚያ ቤቱ ለምን እስረኞቹን ወደ ፍ/ቤት አላቀረበም በሚል ለማረሚያ ቤቱ ተወካይ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፣ የቀጠሮ ትዕዛዝ አልደረሰንም የሚል ምላሽ አግኝተዋል፡፡
ዳኛው ግን፣ “በእኛና በማረሚያ ቤቱ ፀሐፊዎች መካከል መካካድ ተጀምሯል ማለት ነው እኛ ቀጠሮውን በወቅቱ ለማረሚያ ቤቱ ፀሐፊዎች ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ተወካይ በእለቱም በጠቅላይ ፍ/ቤት የተገኙት ሌላ ተለዋጭ ቀጠሮ ለመውሰድ እንደሆነ ለዳኛው አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል፤ የወጣቶችን ሀሳብ በማናወጥ፣ ለአመፅ በማነሳሳትና የመንግሥትን ስም ማጥፋት በሚል ክስ የቀረበበትን ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን በመወከል ጠበቃው ለከፍተኛ ፍ/ቤት ባቀረቡት ጥያቄ፤ ምስክሮችን ለማደራጀት ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀው፣ ለሚያዚያ 15 ቀን 2005 ዓ.ም መከላከያ ምስክሮች እንዲቀርቡ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡