Administrator
ጠበኛ እውነቶች
" ሁሉም ሰው በልቡ ለማንም ማሳየት የማይፈልገው ቆሻሻ ይኖረዋል፡፡ ጥላቻ፣ ክፋት፣ ግልፍተኝነት፣ ራስን መውደድ ….. ብቻ አንዱ ይኖርበታል፡፡ ልዩነቱ ብዙዎቻችን ያ ባህሪያችን በአስገዳጅ ሁኔታ ፈንቅሎን ካልተገለጠ በስተቀር ንፁህ፣ ቅን እና ፍፁም እንደሆንን እናስመስላለን፡፡ "
ጠበኛ እውነቶች
በሜሪ ፈለቀ
አምስተኛ ዕትም
የሚዳኘን ህዝብ ነው!…ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ
የአዲስ አበባ የቤት ሥራ - ለአገራችን ክብር የምትመጥን መዲና እንድትሆን!
ከወር በፊት ብትጠይቁኝ፣ “ይቅርብኝ፤ ከኖርኩበት ሰፈር መነሣት አልፈልግም” ብዬ እከራከር ነበር። ዛሬ ግን “ዕድለኛ ነኝ” እላለሁ። እዚህ ሰፈር ምርጥ የኮንዶሚኒዬም ቤት ውስጥ… አዲስ ኑሮ ተመችቶኛል። ቢሆንም ያደግኩበት ሰፈር ጥዋት ማታ ውል ይለኛል፤ ሆዴ ይባባል - የልማት ተነሺዋ ኑሮና ትዝታ።
ያደግንበት አካባቢ፣ እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ በእውን ተውቦ ሲደምቅ ብናይ ማን ይጠላል? የኮሪደር ልማቱ አጀማመር ታዝባችሁ ከሆነ ደግሞ፣ ያማረ ነገር ለማየት ረዥም ጊዜ የምንጠብቅ አይመስልም። ለኮሪደር ልማት የተመረጡት አካባቢዎች ላይ፣ ገና ካሁኑ በሳምንት ውስጥ ለግንባታ እየተዘጋጁ ነው።
አዲስ አበባ ለአገራችን ታሪክ የምትመጥን መዲና፣ ለነዋሪዎቿ የምትመች ከተማ መሆን ይገባታል። የአፍሪካ መሰባሰቢያነቷን፣ የዓለማቀፍ ዲፕሎማሲ መነሃሪያነቷን የምታስከብር ዘመናዊ ከተማ መሆን አለባት።
ይሄ ሁሉ እንዴት ይቻላል?
ሌላው ይቅርና፣ ለበርካታ ዓሥርት ዓመታት የተዘነጉና የተጎሳቆሉ በርካታ የአዲስ አበባ አካባቢዎች በተሻለና ባማረ ገጽታ ነፍስ እንዲዘሩ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። አንዳንዴም ተስፋ ያስቆርጣል። “ያ ሁሉ የተከማቸ የቤት ሥራ እንዴት እንዴት ማስተካከል ይቻላል?” የሚል ጥርጣሬ ይፈጠርብናል።
ያረጁ ቤቶች ሲፈርሱ በዕጥፍ አዲስ ቤት እየገነቡ ነው
አዎ ብዙ የቤት ሥራ ተከማችቶብናል። ነገር ግን በመተከዝ ወይም በመወቃቀስ ምንም የተሻለ ለውጥ አይመጣም።
ለውጥ ሲባል፣ አንዳንዴ የማሳመርና የማስዋብ ሥራ ብቻ ሆኖ ይታየናል።
አዎ፣ አሳምሮ መስራትና ማስዋብ ያስፈልጋል። ነገር ግን የከተማችንን የሥራ እንቅስቃሴና የኢኮኖሚ እድገትን የሚያፋጥኑ መሠረተ ልማቶችን በጥራት የመዘርጋትና የመገንባት ጉዳይ ነው። ከዚህ ጋርም ነው፣ ማሳመርና ማስዋብ የሚኖረው።
ለውጥ ሲባል፣ አንዳንዴ የማፍረስ ጉዳይ ይመስለናል። አዎ፣ የሚፈርስ ይኖራል። በአብዛኛውም አርጅቶ ሊፈርስ የተቃረበ ነው።
ነገር ግን፣ የተጎሳቆለውን ቤት የማፍረስ ጉዳይ ሳይሆን፣ ለተሻለ አኗኗር በሚመች አዲስ ቤት የመተካት ጉዳይ ነው።
ለኑሮና ለጤና የማይመቹ፣ የተጎሳቆሉና የተፋፈጉ አካባቢዎችን እንደ አዲስ ማልማት፣ ተነሺዎችና ነዋሪዎችም ወደ ተሻለ መኖሪያ እንዲሸጋገሩ ማድረግ የኮሪደር ልማት አንድ ዓላማ ነው።
ታዲያ ለብቻው የተነጠለ ሥራ አይደለም። ከሌሎች የልማት ፕሮጀክቶች ጋር የተናበበ ነው። ያረጁ መኖሪያ ቤቶች ለልማት ሲፈርሱ፣ በዕጥፍ አዳዲስ ቤቶችን እየተገነቡ መሆን እንዳለበት ምን ጥያቄ አለው?
60 ሺ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት በአዲስ አበባ አስተዳደር የተጀመረውን ፕሮጀክት መጥቀስ ይቻላል። የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ብቻ አይደለም። የሥራና የግብይት ማዕከላት፣ የትምህርትና የጤና ተቋማት፣ የመዝናኛና የስፖርት ሥፍራዎችም በፕሮጀክቱ ግንባታ ውስጥ ይካተታሉ።
ፕሮጀክቱ የመኖሪያ ቤት እጥረትን ለማቃለል ብቻ ሳይሆን፣ ክብር ባለው ሁኔታ አኗኗርን ለማሻሻል፣ የሥራ ዕድሎችን በብዛት ለመፍጠርም ይጠቅማል።
በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በመሠረተ ልማት ማሻሻያና በሌሎች መስኮች፣ አዲስ አበባ የቤት ሥራዎች ብዙ ናቸው። እንደ ቤት ሥራዎቿ ብዛት ያህልም፣ ለአገራችን ትልቅነትና ለታሪክ ባለቤትነቷ የምትመጥን መዲና ለመሆን መትጋት ጀምራለች። የሥራ ባህልን፣ የሌት ተቀን ትጋትን ከአገራችን ጋር ማለማመድ ይዛለች።
የአዲስ አበባ አርአያነት ወደ 31 ከተሞች
የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት፣ የከተማዋን ኑሮ ለማሻሻል፣ የነዋሪዎችን የሥራና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችን ለማሳደግ መጥቀሙ ብቻ አይደለም ቁምነገሩ።
አዲስ አበባ የአገራችን መዲና እንደመሆኗ፣ ለሌሎች የአገራችን ከተሞች መልካም አርአያ የመሆን ኀላፊነትም ይጠበቅባታል።
እና የአርአያነት ኀላፊነቷን እያሟላች ነው? የአዲስ አበባን ስኬት በማየትና የአሠራር ልምድ በማግኘት 31 የአገራችን ከተሞች ዘንድሮ የኮሪደር ልማት ጀምረዋል።
ከካዛንችስ ወደ ገላን - የልማት ተነሺ ትዝታና አዲስ ኑሮ
ካዛንችስ አካባቢ ነበር ሰፈሯ። አሁን ገላን አካባቢ የኮንዶሚኒዬም ኑሮ ጀምራለች። ትዝታዋን ታካፍለናለች። ሐሳቧን እንዲህ ትነግረናለች።
ኑሯችን እንዲህ ክብራችንን የጠበቀ ሊሆን እንደሚችል አስቤው አላውቅም። ከወር በፊት ብትጠይቁኝ፣ “ይቅርብኝ፤ ከኖርኩበት ሰፈር መነሣት አልፈልግም” ብዬ እከራከር ነበር። ዛሬ ግን “ዕድለኛ ነኝ” እላለሁ። እዚህ ሰፈር ምርጥ የኮንዶሚኒዬም ቤት ውስጥ… አዲስ ኑሮ ተመችቶኛል ትላለች።
ቢሆንም ግን ካዛንችስንም ትወደዋለች።
በካዛንችስ ሰፈራችንና ቤታችን ለኑሮ አመቺ ባይሆንም፣ ያደግኩበት ነው። ጥዋት ማታ ውል ይለኛል። ሳይታወቀኝ ቅር ቅር የሚል ስሜት ይፈጠርብኛል፤ ሆዴ ይባባል። እውነት ለመናገር፣ ከእንቅልፌ ስነሳ ቤታችንም አካባቢያችንም ጸዳ ጸዳ ብሎ ሳየው፣ “አሪፍ” ቢሆንም ግር ይለኛል። ገና አልለመድኩትም።
ጥሩነቱ፣ የከተማው አስተዳደር የተሰጠን ድጋፍ ከጠበቅነው በላይ ነው። የውስጣችንን ስሜት ለማካካስ እያገዘን ነው። ባለፈው ሳምንት፣ 25ሺ ብር በባንክ ሂሳባችን መጥቶልናል። ቀሪው 50 ሺ ብር በቅርቡ እንደሚጨመርልንም ተነግሮናል…
አዲሱ መኖሪያ ቤታችንም ያስደስታል። የተሻለ አኗኗርን የምንጀምርበትና አዲስ የሕይወት ትዝታ የምንፈጥርበት አጋጣሚ ይሆንልናል ትላለች በተስፋ።
የልማት ተነሺዎች የቀድሞ አካባቢያቸው በጥቂት ወራት ውስጥ ገጽታው ተቀይሮ ሲስተካከል፣ የቀድሞው የተጎሳቆለ ሰፈር በጥበብ ተገንብቶ ሲያምርበት መመልከታቸው አይቀርም። የቀድሞ ትዝታ ባይጠፋም፣ ያ ያደግንበትና የምንወደው አካባቢ፣ እንደ አዲስ ነፍስ ዘርቶ በእውን ተውቦ ሲደምቅ ብናይ ማን ይጠላል?
ደግሞም፣ የኮሪደር ልማቱ አጀማመር ታዝባችሁ ከሆነ፣ ያማረ ነገር ለማየት ረዥም ጊዜ የምንጠብቅ አይመስልም።
ዘንድሮ ለኮሪደር ልማት የተመረጡት አካባቢዎች ላይ፣ ገና ካሁኑ በሳምንት ውስጥ ለግንባታ እየተዘጋጁ ነው።
የመሠረተ ልማት መሥመሮች እንደቀድሞው በተተበተበና በተዘበራረቀ መንገድ ሳይሆን፣ ሥርዓት ይዞ ከመሬት ሥር ለመዘርጋትም ቁፋሮ ተጀምሯል።
ብዙ የቤት ሥራ አለብን - በዓለም መድረክ የአገራችን ክብር እንዲታደስ!
ኢትዮጵያ ትልቅ ባለ ታሪክ አገር ናት። ነገር ግን ለአገራችን ክብር የማይመጥኑና የተከማቹ በጣም ብዙ ችግሮች አሉብን። የቤት ሥራዎቻችንም የዚያኑ ያህል ብዙ ናቸው።
የባሕር በር፡
በባሕር ንግድ በዓለም ዙሪያ የምትታወቅ አገር ነበረች - ኢትዮጵያ። ዛሬ ግን የባሕር በርና የንግድ መተላለፊያ የላትም። ለአገራችን ክብር የማይመጥን ትልቅ ስብራት ነው። ይሄን የመጠገን የቤት ሥራ አለብን። ሥራው ተጀምሯል። ነገር ግን ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። ገና ብዙ ይቀራል። ወደ ፍሬ እንዲደርስ በብርቱ ጸንተን፣ በአገራዊ መንፈስ ተባብረን መሥራት የኛ ድርሻ ነው።
ለአገራችን ክብር የሚመጥ ታሪክ መሥራት የኛ ድርሻ ካልሆነ፣ ማን መጥቶ ይሠራልናል? አዎ፣ የመንግሥት ኀላፊነት ነው። ነገር ግን፣ የእያንዳንዳችንም ሥራ ነው።
አባይና ሕዳሴ
ወደ ካርቱምና ወደ ካይሮ ከሚደርሰው የአባይውኃ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉ የሚፈልቀው ከኢትዮጵያ ማህፀን ነው። እና በአባይ ውኃ ለመጠቀም ስንሞክር እንደ ጥፋት የሚቆጥሩብን በምን ሒሳብ ነው? አንዲት ጠብታ እንድትነኩ አንፈቅድላችሁም የሚል ዛቻ ሊደርስብንስ ይገባል? ለአገራችን ክብር የማይመጥን ውርደት ነው።
እዚህ ላይም ብዙ የቤት ሥራ አለብን። ሥራችንን ጀምረነዋል። ዓለማቀፍ ተጽዕኖዎችን ተቋቁመን፣ በዓለም የዲፕሎማሲ መድረክ ተከራክረን እንቅፋቶችን እያሸነፍን፣ ሕዝባችን በአንድ ልብ ቆሞ፣ እንደየ ዐቅሙ ገንዘብ እያሰባሰበ የሕዳሴ ግድብ ወደ ፍጻሜ ደርሷል።
አንዳች መዓት እንደሚፈጠር እያስመሰሉ እንዳወሩበት ሳይሆን፣ ግድቡ እስከ አፉ ውኃ ሊሞላ ምንም አልቀረውም። ይህም ብቻ አይደለም።
ኢትዮጵያና ሌሎች የአባይ ቤተሰብ አገራት ያልተሳተፉበት፣ የቀድሞ የቅኝ ግዛት ውሎችን አሜን ብለን እንድንቀበልና የአባይን ውኃ ላለመንካን እንድንገዘት ሲካሄድብን የነበረ የዲፕሎማሲ ዘመቻ እስከወዲያኛው የሚመክንበት ጊዜም እየተቃረበ ነው። በፍርደ ገምድ የቅኝ ገዢዎች ውል ምትክ አዲስ ፍትሐዊ ዓለማቀፍ የአባይ ወንዝ ውል በይፋ ጸድቋል። ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ የአባይ ቤተሰብ አገራት ተስማምተው ተፈራርመውበታል።
ከሕዳሴ ግድብ ስኬት ጎን ለጎን፣ አዲሱ አለማቀፍ ውል፣ ለአገራችን ተጨማሪ የስኬት እመርታ ነው። በኢትዮጵያ መሪነትና አስተባባሪነት የተገኘ ስኬት መሆኑ ደግሞ፣ የመንፈስ ብርታት ሊሆንል ይችላል። የአገራችንን ታሪካዊ ክብር ማደስና ወደ ከፍታ ማድረስ እንደምንችል የሚመሰክር ስኬት ነውና።
እንዲህም ሆኖ ገና ብዙ የቤት ሥራ ይቀረናል። የሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያው እንጂ የመጨረሻው አይደለም።
እርዳታና የመስኖ እርሻ
ኢትዮጵያ ከቀደምት የሥልጣኔና የብልጽግና ማዕከላት መካከል አንዷ ናት ተብላ በታሪክ የምትጠቀስ አገር ነበረች። ለበርካታ ዓመታት ግን ስሟ በእርዳታ ጠባቂነት የሚነሣ አገር ሆናለች።
ብዙ ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ ስደት ከቤት ወጥተው፣ የበረሀ አሸዋ ሰለባ፣ የባሕር ውኃ ሲሳይ ሆነዋል እየተባለ በዓለም ዜና ይነገራል። ይሄን ስብራት የመጠገን የቤት ሥራም አለብን።
ከባድ ነው ብለን ልንተወው አንችልም። በክረምት የዝናብ እርሻን ማሻሻል ብቻ ሳይሆን፣ በበጋ የመስኖ እርሻንም ማስፋፋት እንደሚቻል በተግባር እያየን ነው። በእንስሳት እርባታም እንዲሁ ብዙ ሥራ አለብን።
የምንዛሬ ማስተካከያና የኤክስፖርት ዕድገት
የተዛባውን የገንዘብና የምንዛሬ ሥርዓት ማስተካከል ለጊዜው ሕመም ቢኖረውም፣ መንገዳችንን የሚያቃና ሌላ ዘዴ እንደሌለ ከውጤቱ ማየት ጀምረናል።
በሦስት ወራት ውስጥ የአገሪቱ ኤክስፖርት ከዓምናው ጋር ሲነጻጸር ዕጥፍ ሊሆን ምንም አልቀረውም። ከ800 ሚሊዮን ዶላር ወደ 1.5 ቢሊዮን ዶላር አድጓል። ነገር ግን አሁንም ብዙ ይቀረናል። ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ናትና።
የአፍሪካ እግር ኳስና የስታድየም ኪራይ
የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራች የሆነች አገር፣ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ከአፍረካ ዋንጫ አዘጋጅ መሆን አልቻለችም። የኢትዮጵያ ቡድን ለአህጉራዊ ውድድሮች፣ በሌሎች አገራት ስታዲየም ተከራይቶ መጫወት ግድ ሆኖበታል። ይሄም የስብራት ምልክት ነው። ይህን መጠገንና የአገራችንን ክብር ማደስ አለብን። ደግሞም ተጀምሯል። በዚህ ሳምንት እንደ ሰማነው፣ ኢትዮጵያ የ2029 የአፍሪካ ዋንጫ በብቃት ማዘጋጀት ትፈልጋለች ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለአህጉሪቱ የእግር ኳስ ፌደረሽን ተናግረዋል።
ዓለማቀፍ ደረጃቸውን ያሟሉ ስታዲዮሞች እንደሚጠናቀቁና የአፍሪካ ዋንጫ ውድድሮችን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሚሆኑ ጠ/ሚ አብይ ገልጸዋል። የአገሪቱ ከተሞችና የመሠረተ ልማት አውታሮችም በሥርዓት እየተሻሻሉ የአፍሪካ ዋንጫ ለማስተናገድ በብቃት ይሰናዳሉ ብለዋል - ጠ/ሚ አብይ። ድንቅ የታሪክና የተፈጥሮ መስህቦችም ለጎብኚዎች ተመቻችተው ይዘጋጃሉ፤ ኢትዮጵያ የቱሪዝም ማዕከል መሆኗን ለማስመስከር ይረዳሉ ተብሏል።
ብሪክስ እና ፋይዳ ያለው ክብር
ኢትዮጵያ ትልቅ አገር እንደመሆኗ፣ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም መድረክም ትልቅነቷን የሚመጥን ቦታ ማግኘት አለባት። በቀላሉ የሚሳካ አይደለም። ብዙ ጥረት ይፈልጋል። እንደሚቻል ግን ሰሞኑን በራሺያ ከተካሄደው የብሪክስ አገራት መሪዎች ስብሰባ መረዳት ይቻላል።
ኢትዮጵያ የ”ብሪክስ” አገራት ውስጥ መካተቷ አንድ ቁም ነገር ነው። ነገር ግን፣ የብሪክስ አባልነት ወደ ተጨባጭ የኢኮኖሚና የፋይናንስ ፋይዳዎች የሚመነዘር መሆን እንዳለበት ጠ/ሚ አቢይ በስብሰባው ላይ ተናግረዋል።
እንግዲህ…
የባሕር በርና የንግድ መተላለፊያ መሥመር…
የአባይ ውኃና የሕዳሴ ግድብ…
የምንዛሬ ማስተካከያና የኤክስፖርት ዕድገት…
የእርዳታ ጠባቂነት ስብራትና የመስኖ እርሻ…
የአፍሪካ እግር ኳስ መሥራችነትና የአፍሪካ ዋንጫ ዝግጅት…
የብሪክስ መድረክና ፋይዳ ያለው ዓለማቀፍ ክብር…
እነዚህን እንደ ምሳሌ ጠቀስናቸው እንጂ፣ የቤት ሥራዎቻችን ብዙ ናቸው። ተጀምረው የሚቀሩ አይደሉም። ውጤታቸውም እንዲሁ በጅምር የሚቀር ሳይሆን እየበረከተ የሚሄድ ነው።
እዚህ ላይ፣ “ምን አዲስ ነገር ተፈጠረ?” ብለን እናስብ ይሆናል።
በእርግጥም፣ ለብዙ ዘመን የተከማቹ ችግሮችን መዘርዘር ለአገራችን አዲስ ነገር አይደለም። ነገር ግን እንደተለመደው ስህተቶችንና ጥፋቶችን እየዘረዘርን ወቀሳ ለመወራወር፣ የቅሬታ ብዛት እየደረደርን ለመወዳደር፣ እያማረርን አንጀታችንን ለማሳረር አይደለም።
ከቀድሞው ስህተቶች እየተማርንና መፍትሔ እያበጀን፣ መልካም ታሪኮችን ደግሞ እያከበርንና አርአያነታቸውን እንደ መንደርደሪያ እየተጠቀምን፣ ተጨማሪ መልካም ታሪክ መሥራትና ወደ ላቀ ከፍታ መጓዝ ነው - የቤት ሥራችን።
ነጋዴዎች በመርካቶው የእሳት አደጋ ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሞብናል አሉ
ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ጀምሮ በመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ከፍተኛ ዝርፊያ እንደተፈፀመባቸው ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
የእሳት አደጋውን እንደ አመቺ አጋጣሚ ተጠቅመው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ግለሰቦች ሱቆችን እየሰበሩ በመግባት ዘረፋ መፈፀማቸውን ነጋዴዎች ይገልፃሉ፡፡
“እሳት ከሚበላው እኛ ብንበላው ይሻላል” እያሉ በርካቶች ሱቆችን ሰብረው በመግባት ሲዘርፉ እንደ ነበር ተነግሯል፡፡ በመርካቶ ሸማ ተራ የጫማ ሱቅ እንደነበራቸው የገለፁ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነጋዴ፣ የእሳት አደጋው በተከሰተበት ምሽት ስለተፈፀመው ዘረፋ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል “ቀሪ ንብረቴን ለማዳን ወደ ሱቄ ስገባ፣ ማንነታቸውን የማላውቃቸው ግለሰቦ ሰብረው ገብተው “የአክስታችን ሱቅ ነው፤ አሁኑኑ ውጣልን ብለውኛል” ይላሉ- እኒሁ ነጋዴ፡፡ በዚያው ሰፈር አጠቃላይ ፍተሻ ቢደረግ ብዙ የተሰረቁ ንብረቶ እንደሚገኙ ግምታቸውን የገለፁት እኒሁ ነጋዴ፤ ከዝርፊያ የተረፈ ንብረታቸው በእሳት አደጋው መበላቱን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ የእሳት አደጋ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸውም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
እዚያው መርካቶ በአስመጪነት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ ነጋዴ በቤተሰቦቻቸው የጫማ መደብርና በሌሎች ነጋዴዎች ንብረት ላይ በመኪና ጭምር የታገዘ ዘረፋ መፈፀሙን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የእርሳቸው የዕቃ መጋዘን በእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ነው የገለፁት ነጋዴው፤ በአጠቃላይ የ30 ሚሊዮን ብር ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል።
“ብዙ ሰው ንብረቱን ለማትረፍ ከሱቅ ወደ ውጭ ሲወረውር ነበር። በዚህም አጋጣሚ እንኳ የተወረወረውን ንብረት አንስተው የሚወስዱ ሰዎች ነበሩ” ሲሉም፣ በአደጋው ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።
ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በመርካቶ፣ ሸማ ተራ ከተደራጁ የነጋዴ ማሕበራት አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነጋዴዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በማሕበራቱ ውስጥ አባል የሆኑ ነጋዴዎች በእሳት አደጋው ሳቢያ የደረሰባቸው የንብረት ውድመት ምን ያህል እንደሆነ ለመለየት ጥረት ማድረጋቸው ተጠቁሟል፣ “አብረናችሁ እንሰራለን፣ እናንተን ለማገዝ ከጎናችሁ ነን። እናንተ መስራት በምትችሉበት መልኩ ይገነባል!” ሲሉ ቃል እንደገቡላቸውም ነው የተናገሩት።
መርካቶ ሸማ ተራ በርካታ የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድሩ ዜጎች የሚሰሩበት አካባቢ እንደነበር የመጠቆሙት ነጋዴዎቹ፣ መንግስት በአፋጣኝ መፍትሔ ሰጥቶ ወደ ስራ እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል። ነጋዴዎቹ በነበሩበት አካባቢ እንደገና ተመልሰው መስራት እንደሚፈልጉም ገልፀዋል።
የእሳት አደጋው በደረሰበት ወቅት አብዛኛው ነጋዴ የራሱን ንብረት ለማሸሽ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ የእሳት አደጋው ከፍተኛ ስለነበር ብዙ ንብረት መውደሙን ነው ነጋዴዎች የደተናገሩት፡፡ እሳቱ በርካታ ንብረት ካወደመ በኋላ “ተለቀቀ” የተባለው የእሳት ማጥፊያ ውሃ መጀመሪያ ላይ ተለቅቆ ቢሆን ኖሮ፣ “የአደጋውን መጠን ሊቀንስ ይችል እንደነበር ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ አደጋውን እንደ አመቺ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ 33 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። በአደጋው ጋር በተያያዘ በሰባት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው፣ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተገልጿል፡፡
አደጋውን ለመከላከል የጸጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ሕብረተሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ሲገለጽ፣ የአደጋውን መንስዔ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈጸም ብሎም የአደጋ መከላከል ሰራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም የመከላከያ ሰራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡
አዲሱ ፓርቲ ህዝቡ አብሮት እንዲታገል ጥሪ አቀረበ
“የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ” የተሰኘው አዲስ ፓርቲ በዋቢሸበሌ ሆቴል ሊሰጠው የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ በፀጥታ ሃይሎች መከልከሉን ተከትሎ የፓርቲው አደራጆች በሰጡት አስተያየት “ይሄ ከመንግስት የምንጠብቀው ተግባር ነው” ብለዋል። የፓርቲው አደራጅ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሃብታሙ ኪታባ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ከጠዋቱ 4:30 ላይ ፓርቲያቸው በዋቢሸበሌ ሆቴል ሊሰጥ የነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በጸጥታ ሃይሎች መከልከሉን አረጋግጠዋል። “ይህም ተግባር የምንጠብቀው ስለነበር ብዙም አልገረመንም።” ብለዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫን የመከልከልና ሌሎች የመብት ጥሰቶች “ወደፊትም ሊኖር እንደሚችል ፖለቲከኛው ተናግረዋል።
“በአሁኑ ወቅት ያለው መንግስት የሃይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉንም ነገር መቆጣጠር የሚፈልግ መንግስት ነው ያለው” የሚሉት አቶ ሀብታሙ “በተለመደው መንገዳቸው ቢቀጥሉ አይገርምም” ሲሉ ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
በየጊዜው በመንግስት ላይ ለምናቀርበው ትችትና ወቀሳ እውነትነት ተጨባጭ ማሳያ ነው ያሉት አቶ ሀብታሙ በዚህም ባለፈው ረቡዕ ያለምክንያት የተከለከለው የፓርቲያችን ጋዜጣዊ መግለጫ “መንግስት ስራችንን እያቀለለልን ነው” ብለዋል። “በዚህ ዘመን መግለጫ ለመስጠት የግድ ሆቴል መከራየት አያስፈልግም፤ ቴክኖሎጂው ብዙ አማራጭ ስለሚሰጥ ያን ያህል ለእኛ አይቸግረንም።” ሲሉ በሰላማዊ ትግላቸው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የፓርቲው የቅድመ ምስረታ መግለጫ እንደተመለከተው፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለግል ሃብታቸው ዋስትና ያጡባት፣ ኢንቨስተሮች የሚሸሹባት፣ መንግስታዊ ሽብር በመስፋፋቱ ሰላም የሌለባት፣ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊ ተስፋ ቆርጦ ጥቂቶች ለጊዜው የሚፈነጩባትና ዘመነ መሳፍንትን ለመመለስ በቋፍ ላይ እንደምትገኝ ተጠቅሷል። አዲሱ ፓርቲ ባስተላለፈው ጥሪ፤ “ብልፅግና ፓርቲ የችግር ምንጭ እንጂ መፍትሔ ሊሆን የሚችል ስብስብ ባለመሆኑ፣ በኢትዮጵያ አንድነት የሚያምን ሁሉ ጥቃቅን ልዩነቶች በማራቅ በጋራ በመቆም ሊታገለው ይገባል” ብሏል።
ፓርቲው አክሎም፤ “ዕውነተኛ” የሲቪል ማሕበራት፣ የማሕበረሰብ አንቂዎች፣ የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ፓርቲዎች “በመተባበርና በመከባበር” ለጋራ ሕልውናና ለትውልዱ ቀጣይነት በጋራ እንዲቆሙ ፓርቲው ጥሪ አስተላልፏል፡፡ አገሪቱ ከተጋረጠባት ብሔራዊ አደጋ እንድትወጣ ዜጎች በአጠቃላይ ከንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ ጎን እንዲቆሙና በጋራ እንዲሰሩ የትግል ጥሪ ማቅረቡን በመግለጫው ተገልጿል፡፡
ለዕድገትና ሰላም የሚተጉ 20 ሚሊዮን ብር ሊሸለሙ ነው ሽልማቱን ያዘጋጀው አንቴክስ ኢትዮጵያ ነው
ላለፉት 7 ዓመታት በአዳማ ኢንዱስትሪያል ፓርክ፣ በጨርቃጨርቅ ምርት ላይ ተሰማርቶ አመርቂ ውጤት ያስመዘገበው የቻይናው አንቴክስ ኢትዮጵያ፤ ለኢኮኖሚ ዕድገትና ሰላም የሚተጉ 2 ኢትዮጵያዊያንን 20 ሚሊዮን ብር ሊሸልም ነው፡፡
ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም አንቴክስ ኢትዮጵያ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ድርጅቱ በኢኮኖሚ ልማትና በሰላም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶችን አወዳድሮ ለ2 አሸናፊዎች በነፍስ ወከፍ 10 ሚሊዮን ብር ይሸልማል፡፡
ለእነዚህ ሁለት የሽልማት ዘርፎች የሚመረጡ እጩዎች ከመላው ኢትዮጵያ በህዝብ ጥቆማ ታሪካቸው ወይም ሥራቸው እንደሚሰበሰብ የተጠቆመ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ለዚህ ውድድር በተመረጡ ዳኞችና በህዝብ ድምጽ ተለይተው፣ የሽልማት ሥነስርዓቱ ታህሳስ 17 ቀን 2017 ዓ.ም በአፍሪካ ህብረት የስብሰባ ማዕከል እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡
አንቴክስ ኢትዮጵያ ላለፉት 7 ዓመታት በአገሪቱ ውስጥ በነበረው ቆይታ፣ ያሉትን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውጣ ውረዶች በመገንዘብ፣ መፍትሄ የማፈላለግ ሂደት ውስጥ የራሱን ሚና ለመወጣት ባቋቋመው ፉድ ኤንድ ፕላስ የተሰኘ ግብረሰናይ ድርጅት በርካታ እርዳታዎች ሲያደርግ መቆየቱ ተጠቁሟል፡፡
በአሁኑ ወቅት ደግሞ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትና ሰላም ዘርፍ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦችና ድርጅቶች ዕውቅና የሚሰጥ፣ ምርጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሥራዎች (Best Influencer Work Prize)ሽልማት ለማበርከት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል፡፡ ካለፈው ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም አንስቶም የእጩ ተወዳዳሪዎችን ታሪኮችና ሥራዎች መቀበል ጀምሯል፡፡ የBIW Prize ዓላማ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማምጣት በተለየ መንገድ ጥረት ለሚያደርጉና በህዝቡ መካከል ሰላማዊ አብሮነትን ለማጎልበት ለሚተጉ፣ በሥራቸውም ለሌሎች አርአያ መሆን የቻሉ ግለሰቦችና ድርጅቶችን ማበረታታትና ሥራቸውንም ማገዝ ነው፤ተብሏል፡፡
አንቴክስ ኢትዮጵያ በአዳማ ኢንዱስትርያል ፓርክ ከ10 በላይ ሼዶች ያሉት ሲሆን፤ ለ4500 ሰራተኞች የሥራ ዕድል የፈጠረ ድርጅት መሆኑ ተነግሯል፡፡ አንቴክስ ግሩፕ፤ እ.ኤ.አ በ2003 ዓ.ም በቻይና የተመሰረተ ሲሆን፣ ከቻይና በተጨማሪ በእስያና በአፍሪካ በጨርቃጨርቅና ሌሎች ዘርፎች እየሰራ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች፣ ራሳቸው ወይም ጠቋሚዎች፣ በቴሌግራም ቻናል:-@ BIWPrize ወይም በኢሜይል፡
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
በመጠቀም ለሰላምና ኢኮኖሚ ያበረከቷቸውን ሥራዎች መላክ እንደሚችሉ ተጠቁሟል፡፡
ለዚህ ሽልማት እጩ ለመሆን ተወዳዳሪዎች ማሟላት የሚገባቸውን ነጥቦች በአዲስ አድማስ ማህበራዊ ድረገጽ ላይ መመልከት ይቻላል፡፡
ኤስ ኦ ኤስ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ፈተና እንደሆኑበት አስታወቀ
ኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ፤ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ስራዎቹን በአግባቡ እንዳያከናውን አስታውቋል።
የተቋም ምክትል ብሔራዊ ዳይሬክተር አቶ ኤቢሳ ጃለታ በተለይ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፣ በአስቸጋሪና ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ላይ ድጋፍ ማድረግ የኤስ ኦ ኤስ መለያ መሆኑን ጠቁመው በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ ግጭቶች ለስራቸው ተግዳሮት እንደሆኑባቸው አመልክተዋ። አያይዘውም፣ ተቋማቸው ከሌሎች ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በአጋርነት የተለያዩ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፣ “በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ አደጋ የመጀመሪያ ተጋላጭ የሚሆኑት ሕጻናት ናቸው” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ግጭት በሚስተዋልበት የአማራ ክልል የሕይወት አድንና የማገገሚያ ስራዎች እየተሰራ መሆኑን ያብራሩት አቶ ኤቢሳ፣ ለአብነት ያህል በሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች እንዲሁም በሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች እነዚሁ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል። ይሁንና እነዚህ ስራዎች በሚሰሩበት ጊዜ በርካታ ተግዳሮቶች እንደሚገጥማቸው ተናግረዋል።
ከተግዳሮቶቹ መካከል በዋናነት የአደጋ ጊዜ ስራዎች ሲሰሩ፣ የመንገድ መዘጋትና የዕንቅስቃሴ መገደብ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ ይህም በተለይ በአማራ ክልል ካለው ግጭት ጋር እንደሚያያዝ አቶ ኤቢሳ ተናግረዋል። “ሆኖም ይህንን ገደብ በጥንቃቄ በማለፍ ስራዎቻችንን ለመስራት እየሞከርን ነው” ሲሉ ጠቅሰዋል።
የሕዝቡ ፍላጎት መብዛትና ከዚህም ጋር የኤስ ኦ ኤስ የሃብት ውስንነት ሌላኛው ተግዳሮት መሆኑን አቶ ኤቢሳ አልሸሸጉም። ከጦርነት ጋር በተያያዘ የደህንነት ስጋት መኖሩን አንስተው፣ “ስራችንን ስንሰራ ከፍተኛ ጥንቃቄ እናደርጋለን።” ብለዋል።
ለዚህም ተቋማቸው በጥናት ላይ የተመረኮዘ የጥንቃቄ አካሄድ እንደሚከተል ነው አቶ ኤቢሳ የገለጹት። “እንደ አገር አሁን ያለንበት ሁኔታ ማንንም አይጠቅምም። ሕጻናትን በተለየ መልኩ ይጎዳል።” ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ሁሉም ወገኖች ዓለምአቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ ሕጎችን እንዲያከበሩ ጠይቀዋል።
ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ድርጅቱ በኢትዮጵያ ስራ የጀመረበትን 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል የማጠናቀቂያ መርሃ ግብር በሸራተን አዲስ ሆቴል ሲያከብር፣ የድርጅቱ አመራሮች፤ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና የመገናኛ ብዙሃን ባለሞያዎች ተገኝተዋል።
የኤስ ኦ ኤስ የሕጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በ50 ዓመታት የበጎ ተጽዕኖ ጉዞው፤ 8 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎችን መድረስ እንደቻለ “Global Exceptional Excellence Consultancy” የተባለው ድርጅት ያደረገው ጥናት ያመለክታል።
ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል
የአንድ ቅኔ ት/ቤት ተማሪዎች ቅኔ የሚዘርፉበት እለት ነው፡፡ ከየደብሩ፣ ከየቅኔ ትምህርት ቤት ሁሉ አንቱ የተባሉ ሊቆች ተጠርተው መጥተዋል፡፡ ተማሪዎቹ ምን ያህል እንደተማሩና እንደረቀቁ ለማዳመጥና ለመመዘን፣ እግረ-መንገዳቸውንም የነሱ ዘመነኛ የሆኑ የቅኔ መምህር፣ ምን ያህል እንዳስተማሩ በማየት ከራሳቸው ጋር ሊያነጻጽሩ ነው፡፡ በተማሪዎቹ መካከል ፉክክር እንዳለ ሁሉ፣ በመምህራኑም መካከል የእኔ እሻል እኔ እሻል ውድድር አለ፡፡ በጥንቱ የቅኔ ትምህርት ይትባህል፣ አለቃ እገሌ ዘንድ የተማረ፣ መምህር እገሌ ዘንድ ቅኔ እየዘረፈ መባል ብዙ ስምና ክብር አለው፡፡ በዘመናችን ሲታሰቡ ዶ/ር እከሌ የተባለ ፕሮፌሰር ጋር ነው ያጠናሁት እንደማለት ነው፡፡ ወይ ዛሬ- የዚህ school of thought ተከታይ ነኝ እንደሚባለው-የዚህ ደብር ተከታታይ ነኝ - እንደማለትም ይሆናል፡፡ ከተማሪዎች መካከል አንድ ሃይለኛ ተማሪ አለ፡፡ መምህሩ ሳይቀሩ ይፈሩታል፡፡ ታዲያ የዚያን ዕለት መምህሩ በበኩላቸው ችሎታቸውን ለማሳየት ያህል ቅኔውን ሲዘርፉት፣ አንድ ላላ ተደርጎ ሳይረገጥ መነበብ ያለበትን “ታምረሃ” (የተዓምር ድርጊት) የሚል ቃል የኔታ እርግጥ አድርገው “ታምረሃ” ብለው ያነባሉ፡፡ ይሄኔ ያ ጎበዝ ተማሪ “የኔታ ልመልስልዎት” ይላቸዋል፡፡ የኔታ አፍረውም ተናደውም ቢሆን ምሬታቸውን ዋጥ አድርገው ሲያበቁ፤ “እሺ የእኔ ልጅ፣ መልሰኝ” አሉ፡፡ “ታምረሃ” አይጠብቅም ያላሉት፡፡ ይላቸዋል፡፡ የኔታም አላልተው በድጋሚ ይሉታል፡፡
በነዚያ ሁሉ ታዋቂ መምህራን ፊት ተማሪያቸው ስህተት ስላገኘባቸው በጣም ተናደዋል፡፡ ስነ-ሥርዓቱ ሁሉ አለቀና እንግዶቹ ሁሉ ተሸኙ፡፡ የየኔታ ቤት አፋፍ ላይ ነው፡፡ የጎበዙ ተማሪ ቤት ታች ሜዳው ላይ ነው፡፡ ለተማሪው የየኔታ ቤት ቁልጭ ብሎ ካፋፍ ይታየዋል፡፡ የኔታ ጠዋ ማለዳ ተነስተው እደጃቸው ካለው የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቆርጠው አርጩሜ መልምለው፣ በጋቢያቸው ሸፍነው ቁልቁል ሲወርዱ ተሜ ያስተውላቸዋል፡፡
ት/ቤት እንደተለመደው የኔታ፣ ተማሪዎቹ ቅኔ እንዲዘርፉ ሲመሩ፣ ሳያውቁ ያሉት አስመስለው የትናንትናውን “ታምረሃ” የሚል ስህተት በመድገም ተረግጠው አነበቡት፡፡ ተሜ ግን እንደ ትላንቱ “ልመልስዎት” ሳይላቸው ጭጭ አለ፡፡ የኔታ ትንሽ እንደ መናደድ ብለው፣ አሁንም ያችን “ታምረሃ” ረገጥ አድርገው ተናገሯት፡፡ ተሜ አሁንም ጭጭ፣ የኔታ በጣም ተናደዱ፤ ጮክ ብለው፤ በጣም ረግጠው “ታምረሃ!” አሉ፡፡ ተሜ አቀርቅሮ እረጭ፡፡ የኔታ ትዕግስታቸውን ጨርሰው፤
“አንተ አትመልሰኝም እንዴ?” ሲሉ ጠየቁት በጋለ-ቃል፡፡
ተማሪው ሲመልስ፤
“አይ የኔታ፣ ይቺ እንኳ ውስጠ-ወይራ ናት” አላቸው
ውስጠ-ወይራ ታሪካዊ አመጣጧ ይሄ ነው፡፡
***
በረዥም ጊዜ ታሪካችን ውስጥ በሀገራችን የሚካሄድ ብዙ ውስጠ-ወይራ ነገር አለ፡፡ ስህተት የሚሰራ ሞልቷል፡፡ ስህተት እያየ ውስጠ-ወይራ ናት ብሎ ጭጭ የሚልም አንድ አገር ነው፡፡ የትላንቱን ቂም ለመወጣት እንደ የኔታ አውቀው ተሳስተው፣ “አትመልሰኝም” ወይ?” የሚሉም አያሌ ናቸው፡፡ በስህተት ከማፈርና ከመናደድ፣ ብሎም ለአርጩሜ ከመዘጋጀት ይልቅ፣ ስህተትን ለማረም ዝግጁ መሆን ቢችሉ አገራችን ከስንት ህመም በዳነች ነበር፡፡ ይህ ድክመት በሁሉም የህይወት መስክ ሲንፀባረቅ ይታያል፡፡ በተለይ ግን በፖለቲካው መድረክ ላይ ተሰማርተው የተንቀሳቀሱም ሆነ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች፣ ቡድኖችና ፓርቲዎች ዕድሜያቸው ለአካለ-ትግል ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ የሚታይባቸው መሰረታዊ የድክመት ጠባይ አለ፡ ፖለቲካዊ ሸፍጥ፣ ስቶ ማሳሳት (Disinformation) አድር-ባይነት፣ አስመሳይነት (Hypocracy)፣ የባዶ ሜዳ ዛቻ፣ ዕብጠት፣ ፖለቲካዊ አክራሪነት፣ መቻቻልን ከሽንፈት መቁጠር፣ እኔ የሌለሁበት ማህበር ጥንቅር ብሎ ይቅር ማለት፤ ማጋለጥ፣ ማጋፈጥ፣ ለጠላት አሳብቆ ማስመታት፣ ታክቲካል ግንኙነትና ጡት መጣባትን አለመለየት፣ ህጋዊ ትግልን ዲፕሎማሲንና ህቡዕ ትግልን (Clandesisne struggle) ወይ አጥርቶ አለማወቅ አሊያም አንዱን ከአንዱ ጋር ማምታታት፣ እርስ በርስ እየተሻኮቱ አገርንና ህዝብን እርግፍ አድርጎ መርሳት፣ መሸመቅ፣ ያታግላል በሚል ምክንያት ብቻ አዲስ መፈክር ማውጣት ወዘተ.
እንግዲህ ከዚህ በአንዱ፣ በጥቂቱ ወይም በሁሉም የተነሳ እስካሁን የሚታየው የትግል ስልት ሁሉ ውስጠ-ወይራ አለበት፡፡ “ጠጅ የለመደች ገንቦ፣ ያለጠላ አታድርም” እንዲሉ መልኩ ይለዋወጥ እንጅ በውስጠ- ወይራ የማያምን ፓርቲ፣ ማህበር፣ ድርጅት፣ መሪ፣ ካድሬ፣ ታጋይ የለም ለማለት ያስደፍራል፡፡ እርግጥ መጠቅለያው ይለያያል፡፡ ዞሮ ዞሮ ግን በማህበራዊ ግንኙነታን ውስጥ ውስጠ-ወይራ እንደማይጠፋ ሁሉ በየፓርቲው ፕሮግራም፣ በየቡድኑ ታክቲክና ስትራቴጂ፣ በየስምምነት ፊርማው፣ በየጋራ ግንባር ውይይት ውስጥ ሁሉ በገዛ ወገን ላይ ሳይቀር ውስጠ-ወይራ አለች፡፡
ብዙ ህይወት የጠፋባቸው፣ ብዙ ቁርሾ የተፈራባቸው፣ ለዘመናት የማሻሩ የሚባሉ ቁስሎች የተፈጠሩባቸው ዓመታትን አይተናል፡፡ በነዚህ ውስጥ ከሰራነው ስህተት ራሳችንን ማረም የቻልን ስንቶች ነን? ብሎ ለጠየቀ ሰው የሚያገኘው መልስ ግን እጅግ መንማና ቁጥር ነው፡፡ ወዳለፉት ስህተቶቻችን መለስ ብለን እንድናይ እሚያግዘን አንድ ፍቱን መሳሪያ አለ፡፡ ታሪክን በጽሁፍ ማስቀመጥ፡፡ ትንሽም ሆነ ትልቅ ታሪክ ጽፎ ማስቀመጥ፡፡ ሁሉ በሚዋሃድበት ጊዜ የሚጣረሰው ተዋዶ፣ የተሳሳተው ታርሞ፣ አንድ ቀን ሙሉ ታሪካችን አደባባይ ይወጣል፡፡
ቶማስ ኤዲሰን፤ “ከሰራኋቸው ኤክስፐርመንቶች ሁሉ ውጤት አግኝቻለሁ፡፡ ሁሉም ስህተት ናቸው፡፡ ይህ ግን ትልቅ ድል ነው፡፡ እስካሁን ድረስ እንኳን 138 እኔ ባሰብኩት መንገድ የማይሰሩ መንገዶች መኖራቸውን ተምሬአለሁ፡፡” ይለናል፡፡
ከላይ የተጠቀሱት ድክመቶች እስካሉ ድረስ ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲከኞችን እጣ ፈንታ ከወዲሁ መናገር የሚያዳግት አይሆንም፡፡ ጊዜያዊ አሸናፊ ብቅ ይላል፡፡ ይኸው አሸናፊ አንድ ሰሞን ያለፈውን ሲረግም፣ አንድ ሰሞን መጪውን እቅዱን ሲያስተዋውቅ ይከርማል፡፡
ከዚያ “ብቻውን የሚሮጥ የሚቀድመው የለ፣ ብቻውን የሚሟገት የሚረታው የለ” እንደተባለው ተረት ይሆናል፤ ነገሩ ሁሉ፡፡ ከዚያ “ስለእኔ ተሰብሰቡ”፣ “በእኔ እመኑ” “እኔ ቀናኢ” (እኔ ቀናተኛ አምላክ ነኝ) እያለ ሰውን ሲያፈጋ ይቆያል፡፡
ሰነባብቶ የአሸናፊነት ሰንጠረዥ ላይ ያለው ጠቋሚ መስመር እንደገና ማሽቆልቆል ይጀምራል፡፡ ሌላው ባለጊዜ ደግሞ ለሌላው ጊዜ አሸናፊነት የያንኑ ማንነቱን፣ ያንኑ ውስጠ ወይራውን እንደያዘ መድረኩ ላይ ብቅ ይላል፡፡ ቀለበታዊ ሂደቱ ይቀጥላል፡፡ “ራሱን የማይገዛ፣ ሀገር አይግዛ” የሚባለው ተረት የዋዛ አይደለም፡፡ ራስን መመርመር፣ ማረም፣ ስህተትን መቀበል፣ መሳሳትን በሰው ፊት ማመን፣ በጋቢው የተሸፈነውን ወይራ ለመስበርም ሆነ ወደፊትም ከነጭራሹ ከዛ ተቆርጦ እንዳይመለመል ለማድረግ ወሳኙ እርምጃ ነው፡፡ አለበለዚያ፤“ከእትብት ጋር የወጣ አመል፣ ከከፈን ጋር ይቀበራል” ማለት ብቻ ይሆናል፡፡
ሴት አባላት ሳይኖራቸው አለን በማለት ገንዘብ የተቀበሉ ፓርቲዎች መታገዳቸው ተገለጸ
ሴት አባላት ሳይኖራቸው አለን በማለት፣ በሀሰተኛ ሪፖርት ገንዘብ የተቀበሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ማገዱን፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የሌላቸውን ሴት አባላት ቁጥር አለን በማለት የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ ገንዘብ በመቀበል ህገ ወጥ ተግባር መፈጸማቸው መረጋገጡን ቦርዱ ጠቁሟል፡፡
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በቅርቡ በተሻሻለው የፓርቲዎች አገልግሎትና ምዝገባ ክፍያ እንዲሁም እገዳ በተጣለባቸው ፓርቲዎች ዙሪያ በዛሬው ዕለት ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ውብሸት በመግለጫቸው፤ ቦርዱ በፓርቲዎች ውስጥ የሚሳተፉ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ለማበረታታት ለፓርቲዎች ገንዘብ የሚሰጥበት አሰራር መዘርጋቱን ገልጸዋል።
ሆኖም ለማበረታቻ ከቦርዱ የሚመደበውን ገንዘብ አላግባብ ለመጠቀም፣ የሌላቸውን አባላት ቁጥር አለን በማለት የሚያቀርቡ ፓርቲዎች መኖራቸውን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
ቦርዱ ባደረገው ማጣራት፤ የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አገው ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ አዲስ ትውልድ ፓርቲ፣ የወላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ የሌላቸውን ሴት አባላት ቁጥር አለን በማለት የሃሰት ሪፖርት በማቅረብ ገንዘብ በመቀበል፣ ህገ ወጥ ተግባር በመፈጸማቸው የዕግድ ውሳኔ እንደተላለፈባቸው አብራርተዋል።
ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎችም ላይ እርምጃ መውሰዱን አቶ ውብሸት ገልጸዋል።