Administrator

Administrator

 በቱርክ በመሬት መንቀጥቀጥ 30 ሺህ ዜጎች ሊሞቱ እንደሚችሉ ተነግሯል

    በህንድ ለቀናት የዘነበው ሃይለኛ ዝናብ ያስከተለውና ባለፉት የአገሪቱ 100 አመታት ታሪክ እጅግ የከፋው እንደሆነ የተነገረለት የጎርፍ አደጋ፤ 44 ሰዎችን ለሞት  መዳረጉ ተነግሯል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በደቡባዊ ህንድ በምትገኘው ኬራላ ግዛት የተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎችን ከመኖሪያ ቤታቸው ማፈናቀሉን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ ከ50 ሺህ በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች በመጠለያ ካምፖች ውስጥ እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኙም አመልክቷል፡፡
የጎርፍ አደጋው በተለይ ህጻናትንና ሴቶችን ክፉኛ ማጥቃቱን የጠቆመው ዘገባው፤ የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ማቋረጡንና በርካታ ቤቶችን፣ የመሰረተ ልማት አውታሮችንና ሰብሎችን ማውደሙን ጠቅሶ፣ በአደጋው ተጎጂ ለሆኑ ዜጎች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታና ህክምና ለመስጠት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም አክሎ ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የቱርክ የአደጋ ቁጥጥር ኤጀንሲ፣ በኢስታንቡል አካባቢ ይከሰታል ተብሎ የሚጠበቀው ከፍተኛ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ በከተማዋ የሚኖሩ 30 ሺህ ዜጎችን ለሞት ሊዳርግ እንደሚችል ባወጣው መግለጫ ማስጠንቀቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ ኤጀንሲው ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በኢስታንቡል በሬክተር ስኬል 7.5 የሚገመት የመሬት መንቀጥቀጥ ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቀቀ ሲሆን፣ ነዋሪዎች ተገቢውን ዝግጅት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የመሬት መንቀጥቀጡ 50 ሺህ በሚሆኑ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቀቀው ኤጀንሲው፤ 49 ሺህ ያህል ህንጻዎችንም ሊያፈራርስና 2.4 ሚሊዮን ዜጎችን ቤት አልባ ሊያደርግ እንደሚችልም አስታውቋል፡፡

 የአለማችን የሶል ሙዚቃ ንግስት እንደሆነች የሚነገርላት አሜሪካዊቷ ድምጻዊት አሪታ ፍራንክሊን፣ በካንሰር ህመም በ76 አመቷ ከትናንት በስቲያ ከዚህ አለም በሞት መለየቷ ተዘግቧል፡፡
ከስድሳ አመታት በላይ በሚዘልቀው የሙዚቃ ህይወቷ፣ በአለማቀፍ የሙዚቃ መድረክ፣ በሶል ሙዚቃ ዘርፍ አብሪ ኮከብ ሆና የዘለቀቺው አሪታ ፍራንክሊን፤ ላለፉት ስምንት አመታት በካንሰር ህመም ስትሰቃይ እንደነበር ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በታላቁ የግራሚ ሽልማት ለ18 ጊዜያት ያህል ተሸላሚ የሆነቺው አሪታ ፍራንክሊን፣ በሙዚቃ ስራዎቿ በርካታ አገር አቀፍና አለማቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቷን የጠቆመው ዘገባው፤ የፕሬዚዳንቱን የነጻነት ሜዳይ ጨምሮ በርካታ የክብር ሽልማቶችን ማግኘቷንም አመልክቷል፡፡
አሪታ ለመጨረሻ ጊዜ በመድረክ ላይ ስራዎቿን ያቀረበቺው ባለፈው ህዳር ወር፣ በኒውዮርክ በተዘጋጀ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ህልፈተ ህይወቷ መሰማቱን ተከትሎ በርካታ ዝነኞችና አድናቂዎቿ በማህበራዊ ድረገጾች ሃዘናቸውን በመግለጽ ላይ እንደሚገኙም ጠቁሟል፡፡

  ታጣቂዎች 2 ሺህ ስደተኞችን ከመጠለያ አባርረዋል

    የሊቢያ ፍርድ ቤት የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ደጋፊ የነበሩና ከሰባት አመታት በፊት በመዲናዋ ትሪፖሊ ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡ ዜጎችን በመግደል በተከሰሱ 45 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ ማስተላለፉ ተዘግቧል፡፡
ለተቃውሞ የወጡ ዜጎችን ገድለዋል በሚል ክስ ከተመሰረተባቸው 128 ሊቢያውያን መካከል ዘጠና ዘጠኙ ጥፋተኛ ሆነው መገኘታቸውን የዘገበው ዥንዋ፤ ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የትሪፖሊ ፍርድ ቤት ባለፈው ረቡዕ በዋለው ችሎት በ45ቱ ላይ የሞት ፍርድ ውሳኔውን ማስተላለፉን አመልክቷል፡፡
እ.ኤ.አ በ2011 ነሃሴ ወር ላይ የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊን ስርዓት ለመቃወም በመዲናዋ ትሪፖሊ አደባባይ የወጡ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በጋዳፊ ደጋፊዎች በአደባባይ አንገታቸውን እየተቀሉ መገደላቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
በተያያዘ ዜናም፣ የአገሪቱ ታጣቂ ቡድኖች የጋዳፊ ደጋፊ ናቸው ያሏቸውን 2 ሺህ ያህል የአገር ውስጥ ተፈናቃይ ስደተኞችን ትሪፖሊ ከሚገኝ የመጠለያ ካምፕ ማባረራቸውን የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
ተቋሙ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በሊቢያ 192 ሺህ ያህል የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ለአመታት የከፋ ኑሮን በመግፋት ላይ የሚገኙ ሲሆን በተለይም ከአናሳ ጎሳ የተወለዱ ሊቢያውያን በታጣቂዎች ከፍተኛ በደል እንደሚፈጸምባቸው አመልክቷል፡፡

 “የአዲሲቷ ኢትዮጵያ ታዳጊዎች ፌስቲቫል” የተሰኘ በታዳጊዎች የበጎ አድራጎት የባህል፣ የኪነ ጥበብ፣ የተሰጥኦ ማሳያ፣ የግብይት፣ የቁጠባ፣ የጨዋታና የውድድር ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ታዳጊ ወጣቶች ታላቅ ራዕይ ያላቸው፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ በአገራቸው ምርት የሚኮሩ፣ በበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ የሚሳተፉ እንዲሆኑ የሚያበረታቱ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተገልጿል፡፡
የፌስቲቫሉ አዘጋጆች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት፤ ፌስቲቫሉ ታዳጊዎች ቁምነገርን በቀልድና በጨዋታ በማዋዛት የሚገነዘቡበት፣ የቁጠባ ባህላቸውን የሚያዳብሩበት የግል ተሰጥኦዋቸውን በማሳየት የሚወዳደሩበትና የሚሸለሙበትን ዝግጅቶች አካትቷል፡፡
ልደታ አካባቢ በሚገኘው የልደታ መርካቶ ገበያ አዳራሽ ውስጥ ከነሐሴ 20 እስከ ጳጉሜ 2 ቀን 2010 ዓ.ም በሚካሄደው በዚሁ ፌስቲቫል ላይ የተለያዩ የበዓል ዝግጅቶች፣ የሰርከስ ትርዒቶችና ሌሎችም በርካታ የመዝናኛ ፕሮግራሞች እንደሚቀርቡ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡ ፌስቲቫሉን ሻክርክስ ንግድና ኤቨንትስ ማኔጅመንት ከተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ጋር በትብብር ያቀርበዋል ተብሏል፡፡  

 “ሰውኛ ፕሮዳክሽን ኢንተርቴይመንት” ከጉዞ አድዋ፣ ከኢጋ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽንና ከአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ጋር በመተባበር፤ ዛሬ ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ የእቴጌ ጣይቱን፣ የአፄ ምኒሊክንና የፊታውራሪ ገበየሁን ልደት በልዩ ልዩ ዝግጅቶች እንደሚያከብር አስታወቀ፡፡
በዓሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማ በሚታደሙበት በእንጦጦው የአፄ ምኒልክ ቤተ መንግስት የሚከበር ሲሆን በልዩ ልዩ ኪነ ጥበባዊና ታሪካዊ ዝግጅቶች ተጀምሮ አዲስ አበባ የሚገኙ ዋና ዋና ታሪካዊ ሀውልቶችን በመጎብኘት እንደሚጠናቀቅ ያስታወቀው “ሰውኛ ፕሮዳክሽን ኢንተርቴይንመንት” ነው፡፡

 · ያለ ዶ/ር ዐቢይ፤ የደቡብ ሱዳን ስምምነት አይታሰብም
   · የውጊያ ቀጠናዎችን የልማት ጣቢያ እናደርጋቸዋለን
   · ሁለቱን አገራት የሚያገናኝ የባቡር ሃዲድ ይዘረጋል

     ሚስተር ጄምስ ፒተር ሞርጋን፣ በኢትዮጵያና በጅቡቲ የደቡብ ሱዳን አምባሳደር ናቸው፡፡ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ተወካይ በመሆንም እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በእርስ በርስ ጦርነት ለዓመታት ስትታመስ የቆየችው ደቡብ ሱዳን፤ በመሪዎቿ ስምምነት አለመድረስ የተነሳ ማጣት በመቶ ሺዎች የሚሰሉ ዜጎቿን ለስደትና እንግልት ዳርጋለች፡፡ ባለፈው ሳምንት ግን ታሪክ የተለወጠ ይመስላል፡፡
የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ተቃዋሚያቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ጦርነት አቁመው፣ በአገራቸው ላይ በሰላም ለመስራት በካርቱም ስምምነት ተፈራርመዋል። ስምምነቱን ተከትሎ በኢትዮጵያ የሚገኙት አምባሳደሩ ትላንት ረፋድ ላይ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጋዜጠኞች በደቡብ ሱዳን ኤምባሲ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በመግለጫው ላይ የተገኘችው የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ፤ ከዚህ ቀደም የተደረጉት ስምምነቶች ለምን እንዳልተሳኩ፣ የአዲሱ ስምምነት አስተማማኝነት ምን ያህል እንደሆነ፣ በኢትዮጵያና በደቡብ ሱዳን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዙሪያና ሌሎች ጥያቄዎች አንስታ አነጋግራቸዋለች፡፡


    ኢትዮጵያ ሲመጡ የመጀመሪያዎ ነው ወይስ ከዚሀ በፊት ያውቋታል?
ኢትዮጵያ ስመጣ የመጀመሪያዬ ነው፤ ኢትዮጵያን ሳውቃት ግን የመጀመሪያዬ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያን የማውቃት ባልሳሳት በ1974 ዓ.ም ነበር፡፡ ያን ጊዜ እድሜዬ ምናልባት ከ8-10 ዓመት ባለው ውስጥ ይሆና።፡ ገና የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ተማሪ ነበርኩኝ፡፡ ንጉስ ኃይለሥላሴ ጁባን ለመጎብኘት ሲመጡና ሳያቸው የመባረክ ስሜት ነበር የተሰማኝ። ከኤርፖርት እስከ ጁባ ስታዲየም ድረስ ነበር አቀባበል ያደረግንላቸው፡፡ እስካሁን ድረስ ከውስጤ ያልጠፋውና የመሰጠኝ የንጉሠ ነገሥት ኃይለሥላሴ አለባበስ ነው፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ኢትዮጵያን ማወቅ የጀመርኩት፡፡ ይሄ ደግሞ በጣም ረጅም ጊዜ ነው፡፡ ሆኖም ከጃንሆይ እስከ ቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ድረስ የነበሩት የኢትዮጵያ መሪዎች ሲደግፉንና ሲረዱን ነው የቆዩት፡፡ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያን በደንብ እናውቃታለን። እዚህ በመምጣቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ቤቴ እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡ የኢትዮጵያ የተለያዩ ብሔረሰቦች ዳንሶች ደስ ይሉኛል፡፡
የዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ዓላማው ምንድነው?
ዋና አላማው ደቡብ ሱዳን በመሪዎቹና በተቃዋሚዎቹ ምክንያት የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ገብተን፣ ሰላም አጥተን ከርመናል፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታትና አገራችን ወደ ሰላም እንድትመጣ ደግሞ ኢትዮጵያ ብዙ ደክማና ብዙ ጥረት አድርጋ፣ በመጨረሻም ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ተቃዋሚው ምክትላቸው ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነት ላይ ደርሰው፣ ባለፈው ሳምንት ጦርነት ለማቆምና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት ካርቱም ላይ ስምምነት ተፈራርዋል፡፡ ይህንን ትልቅ ስኬት ለኢትዮጵያና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲዎች ለማብሰርና ኢትዮጵያን ለማመስገን ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተዘጋጀው፡፡ ለዚህ የእርስ በርስ ጦርነት ማብቃት የወቅቱ የኢጋድ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ስራ ሰርተዋል፤ እናመሰግናል። በቀጣይ ይህንን ስምምነት በጁባም በአዲስ አበባም በደማቅ ሥነ ስርዓት እናከብረዋለን፡፡
መቼ ነው የሚከበረው?
በቅርቡ ይሆናል፡፡ አሁን ስምምነቱን ያፈራረመው ቡድን አንዳንድ ሞዳሊቲዎችን በመጨረስና የጊዜ ፍሬሙን በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ ያንን ሰርተው ሲጨርሱ በዚህ ወር አጋማሽ ወይም በወሩ መጨረሻ በደማቅ ሁኔታ በማክበር፣ ደስታችንን ለመላው አፍሪካና ለመላው ዓለም ማሳየት እንፈልጋለን፡፡
በአገራችሁ ላይ ሰላም ለማስፈን በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ስምምነቶች ተፈራርማችሁ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ለምን ነበር ያልተሳካው? የአሁኑስ ስምምነት ምን ያህል አስተማማኝ ነው ይላሉ?
እውነት ነው! እንዳልሽው የተለያዩ ስምምቶች ተደርገው አልተሳኩም፡፡ ለምሳሌ በ2015 የተደረገውን ስምምነት እንውሰድ፡፡ ይህ ስምምነት ያልተሳካበትን ምክንያት ልንገርሽ፡- አፍሪካ በአምስት ሪጅን ተከፋፍላለች፡፡ የምስራቅ አፍሪካ የቀንዱ አካባቢ አባል አገራት ድርጅት “ኢጋድ” ነው፡፡ የኢጋድ የወቅቱ መሪ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የደቡባዊው የአፍሪካ ክፍል “ሳዲክ” ይሰኛል፡፡ “ኢኮዋስ” ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ አገራትን የሚመለከት ጉዳይን የሚመራና የሚከታተል ነው፡፡ የሆነ ሆኖ የምስራቅና የቀንዱ አካባቢ አገራትን ችግር ለመፍታት፣ የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ድርጅት (ኢጋድ) በቂና ጠንካራ ነው፡፡ ነገር ግን እንደነ ሳዲክና ኢኮዋስ ያሉት ድርጅቶች እንዲሁም እንደነ አውሮፓ ህብረት፣ አሜሪካን፣ ኖርዌይንና ብሪታንያን የመሳሰሉ አገራት ጣልቃ ገብነት ነገሩን ሁሉ አበለሻሸው፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ያልሆኑ አካላት ባሳደሩት ጫናና ጣልቃ ገብነት ደቡብ ሱዳንናውያን እርስ በእርሳችን መስማማት አልቻልንም፡፡ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ሆነ፡፡ ተስፋ ቆርጠን በነበርንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን መጥቶ፣ የእኛን ጉዳይ ለምን እንዳልተሳካ ሲመረምር፣ የጣልቃ ገብነቱ ጉዳይ እንቅፋት እንደሆነ ተረዳ፡፡ ይሄ ጣልቃ ገብነት እስካለ ደረስ ደቡብ ሱዳንና ዜጎቿ በፍፁም ወደ ሰላም አይመጡም በማለት፣ በኢጋድ አደራዳሪነት ብቻ ስምምነቱ ተካሄደ፡፡ ራሳቸውን ትሮይካ (Troika) ብለው የሚጠሩት አውሮፓዊያን፣ አሜሪካውያንና ሌሎች ቡድኖች፣ ደቡብ ሱዳን ሰላም እንድትሆን ሳይሆን ጦርነቱ እንዲቀጥል ነው የሚፈልጉት፡፡
በደቡብ ሱዳን ከሚካሄደው ጦርነት ምን የሚያተርፉት አለ?
የሚያተርፉትን የሚያውቁት እነሱ ናቸው፤ ነገር ግን ጦርነቱ እንዲቀጥል ይፈልጋሉ፡፡ መጀመሪያ ችግሩን ካልተረዳችሁት መፍታት አትችሉም ብለን ብዙ ጊዜ ገልፀንላቸዋል፤ ነገር ግን እኛን ሊያዳምጡን አይፈልጉም፡፡ ዶ/ር ሪክ ማቻር አዲስ አይደለም፤ እሱ በ1991 ዓ.ም ለዶ/ር ጆን የችግር መንስኤ እንደ ነበር ይታወቃል፡፡ በ2013ም ሆነ በ2016ም የችግር መንስኤ ነበር፡፡ ይሄንን ነገር ለእኛው ተዉልንና እኛው እንፍታው ብንልም፣ ሊሰሙን ሊያደምጡን አይፈልጉም፡፡ ደቡብ ሱዳንም በነዚህ አገራት ጣልቃ ገብነት እርስ በርስ ስትባላ፣ ሀብቷን ስታወድም፣ ህዝቧን ለሞትና ለስደት ስትዳርግና በኪሳራ ስትጓዝ ቆይታለች። ትሮይካዎች የአገሪቱ ህዝብ 98 በመቶ የመረጠውን መሪ በማስወገድ፣ የአገዛዝ ለውጥ ለማድረግ ሲጥሩ ነበር፡፡ ያን ጊዜ ህዝቡ በአደባባይ ሰልፍ ተቃውሞ አሰምቷል። የደቡብ ሱዳን ህዝብ ትሮይካዎች የሚሰሩትንም ተንኮል ያውቃሉ፡፡ ፕሬዚዳንታቸውንም ያውቃሉ። በዚህ ምስቅልቅል የደቡብ ሱዳን ህዝብ ለከፍተኛ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ ተዳርጓል፡፡ ኑሮው ተቃውሷል፡፡ በብዛት ተሰድዷል፡፡
በሶማሊያም በእኛም ዘንድ ችግር በነበረ ጊዜ የኢጋድ አባል አገራት ችግሩን ለመቆጣጠር የኢኮኖሚ ችግር ስለነበረባቸው አልቻሉም፡፡ ይህንን ክፍተት በመጠቀም ትሮይካዎች ሁሉን ነገር ስፖንሰር እያደረጉ፣ ችግር ሲያባብሱ ነው የኖሩት፡፡ ጉዳዩን ወደ ኢሲኤ የስብሰባ አዳራሽ ይወስዳሉ፤ ቁርስ፣ ምሳና ቡና በማዘጋጀት፣ ለነዚህ ቡድኖች የአየር ትኬት በመግዛት ያስመጧቸውና ሃይ ሃይ ብለው ይሸኟቸዋል። በዚህ ዓይነት አገራቱ ዘላቂ የሰላም መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ አላማውን ጠለፉት (ሀይጃክ አደረጉት)፡፡ ሥለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት ያወራሉ፡፡ በአገራት መካከል የተነሳን ጦርነትና እልቂት ግን አያስቆሙም፡፡ አንድ አገሩ ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት ያለበት መሪ (አገር)፤ ስለ ሰብአዊ መብትና ስለ ህግ የበላይነት ብትነግሪው እንዴት ያዳምጥሻል፡፡ አገሩ ላይ ለተነሳው እሳት አስቸኳይ ማጥፊያ መንገድ ብትነግሪው ግን ሄዶ እሳቱን ያጠፋና፣ ከዚያ ስለ ሰብአዊ መብትና ስለ ህግ የበላይነት ይሰራል። ትሮይካዎች ግን ሲቀልዱና ሰው ሲያባሉ ነው የኖሩት፡፡ የደቡብ ሱዳንም ህዝብ በሰላም መኖር እየቻለ፣ በእነሱ ሲሰቃይ ነው የኖረው። ይሄው ዶ/ር ዐቢይ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢጋድ ፕሬዚዳንት ሆነ፡፡ ችግሩን ተረዳ፡፡ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የችግሩን ባለቤቶች አደራደረ፡፡ አወያየ፡፡ ጦርነታችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆመ፡፡ ተመልሶ ይመጣል የሚል እምነት የለኝም። ዶ/ር ዐቢይ በጣም ስማርት በሆነ መንገድ ነው፣ እነ ትሮይካ ደቡብ ሱዳንን ሊረዱ እንደማይችሉ ገልፆ፤ ጉዳዩን በካርቱም ጨረሰው፡፡ የትሮይካ አባል አገራት ሰዎች ወደ ካርቱም ዝር እንዳይሉ ተደርጎ፣ የደቡብ ሱዳን ተቀናቃኞች በቂ የሆነ ጊዜ ወስደው፣ እርስ በእርሳቸው በደንብ ተነጋግረው፣ እንዲስማሙ ነው ዶ/ር ዐቢይ ያደረገው፡፡ እጅግ በጣም ብልህና በግጭት አፈታት ለደቡብ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካን እንዲሁም ለአለም ምሳሌ የሚሆነን ነው። ፕሬዚዳንት ሳልቫኪርና ዶ/ር ሪክ ማቻር ስምምነት ላይ ሲደርሱ፣ እኔም ካርቱም ነበርኩኝ፡፡ ህዝቡ በደስታ ሲደንስና ሲስቅ ነበር፡፡ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ከካርቱም ጁባ ሲገቡ፣ ህዝቡ በደስታና በዳንስ አጅቦ በድምቀት ነው አቀባበል ያደረገላቸው፡፡ በርካታ ህዝብ ነበር ለአቀባበል የወጣው፡፡ በአጠቃላይ ዶ/ር ዐቢይ ወደ ስልጣን ባይመጣ፣ ደቡብ ሱዳን ወደ ስምምነት ልትመጣ ቀርቶ ጭራሽ ሙሉ ለሙሉ ትወድም ነበር፡፡ ስለዚህ በዶ/ር ዐቢይ ደስተኛ ነን፤ እናመሰግናለን፡፡
አሁን በድንበር አካባቢ የፀጥታና የትብብር ጉዳይ ምን ይመስላል?
ደቡብ ሱዳን ውስጥ ቀውስ በነበረ ጊዜ የተለያዩ ቡድኖች፣ በርካታ ህፃናትን ከኢትዮጵያ ጠልፈው ወስደው ነበር፡፡ ይሄ የሚያሳየው የድንበር አካባቢ የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ አለመሆኑን ነው፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግስት፣ ከተቃዋሚዎች ጋር ጦርነት ላይ ስለነበር ድንበሮችን መቆጣጠር አልቻለም። ኢትዮጵያም በዚያ ድንበር አካባቢ እንዲህ አይነት አስደንጋጭ ችግር ይፈጠራል ብላ አላሰበችም ነበር፤ ግን ተፈጠረ፡፡ ይህን ሁላችንም የምናስታውሰው ነው። አሁን ከረጅም ችግር በኋላ እኛም ወደ ሰላም የመጣን በመሆኑ፣ የድንበር አካባቢ ፀጥታ አስተማማኝ ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ተባብረው በመስራት፣ ሰላምና ጉርብትናቸውን ያጠናክራሉ፤ ምንም የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ መንገዶች ይከፈታሉ፤ የድንበር አካባቢ ንግድ ይጀመራል፡፡
ከኢትዮጵያ ጋር ያላችሁን ጉርብትና ይበልጥ ለማጠናከር መንገዶችንና የባቡር መስመሮችን የመዘርጋት እቅድ ይኖራል?
ይህንንም ለመስራት ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ለምሳሌ የባቡር መስመርን በተመለከተ፣ ከጅቡቲ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ጁባ ለመዘርጋት ስምምነት ተፈርሟል፡፡ ፕሮጀክቱም ለአንድ የቻይና ኩባንያ ተሰጥቶ ፊርማ ተካሂዷል፡፡ የመኪና መንገድን በተመለከተ ሁለት ዋና ዋና መንገዶች አሉን። አንዱ መንገድ ከአዲስ አበባ ተነስቶ “ፓሎጅ” የተሰኘውና በብዛት ነዳጅ የሚመረትበት የደቡብ ሱዳን ቦታ ድረስ በቀጥታ የሚገባ ሲሆን ሁለተኛው ከጋምቤላ “ቦማ”ባለፈው ህፃናቱ ከተጠለፉበት ተነስቶ ጁባ የሚገባ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን ህዝቦች ወደዚያ ለመምጣትና ለመሄድ የግድ አውሮፕላን መጠቀም የለባቸውም፤ መኪና እየነዱ መግባት ይችላሉ፡፡ የድንበር አካባቢ ንግድና ቢዝነስ መስራት ይችላሉ፡፡ የደቡብ ሱዳን ህዝብ ብዙ ነዳጅ አለው። ኢትዮጵያም ነዳጅ ለመግዛት ሩቅ ሳትጓዝ፣ ከእኛ ማግኘት ትችላለች፡፡ እኛም ታላቁ የህዳሴ ግድብ ሲያልቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ከኢትዮጵያ በቅርቡ መግዛትና መጠቀም እንችላለን። ብቻ ብዙ ነገሮች በትብብርና በጋራ ለመስራት እንዲሁም አገሮቻችንን ለማልማት የሚያስችሉን፣ የምንጠብቃቸው እድሎች አሉን፡፡ ይሄ በጣም የሚያስደስትና በተስፋ የሚሞላ ነገር ነው፡፡ የውጊያ ቦታ የነበሩትን ቀጠናዎች፣ የልማት ጣቢያዎች ማድረግ እንችላለን፡፡
አገራችሁ ቀውስ ውስጥ በነበረች ጊዜ በርካታ ዜጎች መሰደዳቸው ይታወቃል፡፡ ለመሆኑ ምን ያህል ይሆናሉ የተሰደዱት? ወደ አገራቸው ለመመለስ ምን ታቅዷል?
የአገሪቱን ቀውስ ተከትሎ የተፈናቀሉ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በጋምቤላ፣ በሀዋሳና እዚያው ጋምቤላ ውስጥ ፑኚዶ በተሰኙ ቦታዎች ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ሪፖርቶች የሚያመለክቱት፤ ከ35 ሺህ በላይ ስደተኞች እንዳሉ ነው። የስደተኞቹ ሁኔታ … አገሪቱ ሰላም ስትሆን ወደ አገራቸው ስለሚመለሱ ይቀንሳል፤ እንደገና ቀውስ ሲነሳ ተመልሰው ስለሚሰደዱ ከፍ ይላል፡፡ እነሱን ወደ ቤታቸው በዘላቂነት ለመመለስ አገሪቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ሰላም መሆን አለባት። አሁን ያንን ሰላም በእጃችን አስገብተናል፡፡ በአሁን ሰዓት ራሱ ጁባ ውስጥ ሰላም ሰፍኗል፡፡ የጥይት ጩኸት ከቆመና ሙሉ ለሙሉ ሰላም ከሆነ፣ በራሳቸው ጊዜም ወደ ቤታቸው ይመለሳሉ፡፡ እኛም የስደተኞች ማቋቋሚያ ፕሮጀክት አለን፤ ሁሉም ጥሩ ይሆናል፡፡
ደቡብ ሱዳን እንደ አገር እውቅና ካገኘችና የተባበሩት መንግስታት አባል አገር ከሆነች በኋላ ከሌላው ዓለም ጋር ያላት ግንኙነት ምን ይመስላል?
እኛ ከየትኛውም የአለም ህዝብ ጋር ችግር የለብንም። ቅድም ከነገርኩሽ ከሩቅ አገር እየመጡ ጣልቃ እየገቡ ከሚበጠብጡን በስተቀር፣ ሌላው ቀርቶ ከጎረቤቶቻችን ከየትኞቹም ጋር በሰላምና በፍቅር ነው የምንኖረው፡፡ ከሩቅ መጥተው ችግር እንፈታለን በሚል፣ የራሳቸውን ፍላጎት ለማስፈፀም የሚረብሹት ከቆሙልን፤ ከየትኛውም ጎረቤትም ሆነ የሌላ አለም አገራት ጋር ሰላማዊ ግንኙነት ነው ያለን፡፡ እርስ በእርሳችን የምንናቆርበት ጦርነትም ፍፃሜ አግኝቷል። በጣም ጥሩና የተረጋጋ አገርና ህዝብ ይኖረናል፤ እናድጋለን እንለማለን፡፡ አመሰግናለሁ፡፡   


     የኢትዮጵያ የግብር ስርአት ኋላ ቀር እንደመሆኑ መጠን ከቅርብ አስርተ አመታት ወዲህ የግብር ስርዐቱን ለማዘመን በተሻለ የግብር አሰባሰብና በዘመናዊ የካሽ ሬጅስተር ማሽን የታገዘ ቢሆንም፣ የውስጥ አደረጃጀቱ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት ባለመሆኑ፣ የግብር ስርዓቱ የጥቂት ግለሰቦችን ካዝና ሲሞላ እንደነበር ያደባባይ ምስጢር ነው፡፡  
ይህንኑ የምዝበራ ክፍተት ለመሙላትም መካከለኛና አነስተኛ ግብር ከፋዮች ላይ ተመጣጣኝ ያልሆነ ግብርና ታክስ በመጫን፣ “ክፈል አልችልም” በሚል እሰጥ አገባ፣ በየፋይናንስ ቢሮዎች ቅሬታ ሰሚ ጉባኤና በየፍርድ ቤቱ የሚጉላላው ግብር ከፋይ ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ስለ ግብር አሰባሰብ በቅርቡ በፓርላማ ባደረጉት ንግግር፤ በሀገራችን ያሉ ወደ ሶስት ሺ የሚጠጉ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ግብራቸውን ባግባቡ ቢከፍሉ በቂ በመሆኑ ታች ወርደን አነስተኛ ግብር ከፋዮችን ባላስጨነቅን ነበር ብለዋል፡፡ ይሁን እንጅ ሁሉም ግብር ከፋዮች በየደረጃቸው የሚፈለግባቸውን ግብር የመክፈል አገራዊ ግዴታ እንዳለባቸው እሙን ነው፡፡
ሆኖም ግብር ከፋዮች በየበጀት አመቱ በሂሳብ መዝገብ አቅርበው፣ ከከፈሉት ግብር ውጭ “ገቢ አነሰ” በማለትና ዘመናዊ የሂሳብ አያያዝ ዘዴን በሚጻረር “የዴስክ ኦዲት ግኝት” በተባለ የውስጥ አሰራር ተገቢ ላልሆነ የግብር ጫና ከመዳረጋቸውም በላይ በየበጀት ዓመቱ የሚቀርበው የሂሳብ መዝገብ፣ በወቅቱ ባለመመርመሩና ለብዙ አመት በመወዘፉ ምክንያት ወደፊት በተገኘው አጋጣሚ ሲመረመር የሚገኘው የልዩነት ግብር ከተጠራቀመ የባንክ ወለድና መቀጫ ክፍያ ጋር ተዳምሮ፣ ግብር ከፋዩን እንደሚጎዳው ይታወቃል፡፡
ስለሆነም አሁን አገራችን በሰነቀችው የይቅርታ፣ የምህረትና በፍቅር የመደመር ጉዞ መሰረት የታክስ ስርአቱም ለተወሳሰበውና ለተወዘፈው የውሳኔ አሰጣጥ ችግር የምህረት አዋጅ አድርጎ፣ በአዲስ መልክ የአሰራር ስርአቱን ሊያዘመን ይገባል እላለሁ፡፡
ዳኘ ከአዲስ አበባ ፒያሳ

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ጫካ ውስጥ አንድ ነብርና አንድ አጋዘን ብቻ ይቀራሉ፡፡ ነብሩ፤
“ይሄን አጋዘን ብበላው ሌላ ምንም የዱር አውሬ አይኖርምና ብቻዬን እቀራለሁ” ብሎ ያስባል፡፡ “ስለዚህ እንደ ምንም ላግባባውና በእኩልነት ተስማምተን የምንኖርበትን ዘዴ ልፍጠር” ይላል፡፡ አጋዘኑ ግን ነብሩ ይበላኛል ብሎ በመፍራት ፈፅሞ እንዳያገኘው ለማድረግ ሁሌ ይደበቀዋል፡፡
አንድ ቀን አጋዘኑ ሸሽቶ የሚያመልጥበት አጣብቂኝ ቦታ ተገኘ!
አያ ነብሮም፤
“ወዳጄ አጋዘን ሆይ! አንተን አገኝ ዘንድ ብዙ ጊዜ ደከምኩ፡፡ ነገር ግን አውቀህም ሆነ ሳታውቅ አልገኝ አልከኝ፡፡ የፈለግሁህ ለሁላችንም ለሚበጅ ብርቱ ጉዳይ ነው፡፡”
አጋዘኑም፤
“ምን ይሆን ይሄ ብርቱ ጉዳይ?” ሲል በመጠራጠር ጠየቀ፡፡
አያ ነብሮም፤
“ውድ አጋዘን፤ እንደምታውቀው በዚህ ጫካ የተረፍነው እኔና አንተ ብቻ ነን፡፡ ጠላት እንኳ ቢመጣብን በየፊናችን ብንታገል ለጥቃት የተጋለጥን ነን፡፡ አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ ሆነናል፡፡”
አጋዘን፤
“እና ምን እናድርግ ነው የምትለው? ምን ይበጀናል?”
“የሚበጀንማ ላንነካካ ተስማምተን፣ የየግላችንን ምግብ ከሌላ ጫካ አድነን መብላት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም ማንንም ላይነካ ተዋውለን በሰላም እንኑር፡፡”
አጋዘን ጥቂት ካቅማማ በኋላ፤
“በሀሳቡ እስማማለሁ፡፡ ለማንኛውም ግን መማማል ጥሩ ነው፡፡ በመሃላ እንተሳሰር፡፡ እሺ ካልክ እንማማል፡፡ ጉዳዩን ለፈጣሪ እንስጠው፡፡”
“እኮ በምን እንማማል?” አለ ነብሮ፡፡
አያ አጋዘንም፤
“እዚህ ጫካ ውስጥ እስከኖርን ድረስ ላትነካኝ ላልነካህ በፈጣሪ ፊት እንማል፡፡ ማንም ማንንም ቢነካ፣ በልጅ ልጁ ይድረስ!”
ነብሮም ደግሞ፤
“ማንም ማንንም ቢነካ በልጅ ልጁ ይድረስ! እኔም በልጄ፣ አንተም በልጅህ ይድረስ!”
“ይድረስ!” አለ አጋዘን፡፡
“ይድረስ” አለ አያ ነብሮ፡፡
በስምምነታቸው መሰረት፤ ነብሮም ባሻገር ካለው ጫካ የሚበላ ፈልጎ ይበላል፡፡ አጋዘንም ወደ ሌላ ጫካ እየሄደ፣ የዕለት ምግቡን ያሰናዳና ይበላል፡፡ በዚህ ዓይነት ብዙ ጊዜ በመከባበር አብረው ኖሩ፡፡
በአካባቢው ያሉትን ጫካዎች ነብሮ እያሰሰ ሲያድንና ሲመገብ ቆይቶ፣ ቀስ በቀስ ደኑም፣ ጫካውም እየተራቆተ መጣና የሚያድነው እንስሳ አጣ፡፡ ተራበ!
አንድ ቀን አንድ የሸለቆ ዋሻ ውስጥ በወዲያኛው ወገን መውጪያ በሌለው ሁኔታ አጋዘን አንድ ዛፍ ቅርንጫፍ ላይ ሲንጠለጠል ከኋላ ላቱና ታፋው አለትልቶ አስጎምዢ ሆኖ ሳለ፤ አያ ነብሮ ምራቁ ተዝረከረከ። ሆዱን ሞረሞረው! አመንትቶ ሲያስብ ከረሀቡ የሚብስ ነገር አልመጣልህም አለው፡፡ “መሀላ ማፍረስ ምን ይጎዳኛል?” አለ፡፡ ወሰነና ወደ አስጎምዢው የአጋዘን ገላ ተምዘገዘገ!
ሆኖም! ነብሮ ከመጎምዠቱ የተነሳ አጋዘኑን አልፎ ሄደና በሆዱ አጋዘኑ ቀንድ ላይ አረፈ፡፡ የአጋዘኑ ቀንድ የነብሮን ሆድ ዘንጥፎ ጣለው! ነብሮ ሊሞት ማጣጣር ጀመረ!! እንደምንም እያቃሰተ፤
“አያ አጋዘን፤ እንዳንነካካ አልተማማልንም ነበር?” አለው፡፡
አጋዘንም፤
“አያ ነብሮ! ያንተ አያትና ቅድመ አያት ከእኔ አያቶች ጋር ምን እንደተማማሉ ምን አውቄ?!” አለው፡፡
*   *   *
የኢትዮጵያ ጣጣ ብዙ መዘዝ አለው! የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ቂምና ማላ ስናስተናግድ፤ የዘር ማንዘራችንን በደልና ግፍ ስንቆጥር ዘመናት አሳልፈናል! ተረኛ ነብሰ - ገዳይ የማንገስ ያህል፤ ከጦር ካምፕም (Barrack)፣ ከጫካም (field) ገዢና መሪ እየቀያየርን፣ ሎሬት ፀጋዬ እንዳለው፤
“እንተዋወቃለን - ሱማሌ ተራ ሞተር ቅርጫ ገበያ! ስርዝ ያንተ፣
ድልዝ የኔ፣
እመጫት የእሷ፤ ሆያ ሆዬ
የሰፊው ህዝብ ስንባባል፤ እንተዋወቃለን”… እያልን ከረምን፡፡ ዕውነትም የፖለቲካው ተዋንያን ሰፊው ህዝብ የማያውቃቸው ፀጉረ - ልውጥ ሲሆኑ፤ ህዝብ ፍዝ - ተመልካች ይሆናል (Passive audience እንዲሉ)፡፡
ዳር ቆሞ ማስተዋል ብቻ! ሆ ማለት ብቻ! ህዝብ እንደ ደላላ አካሄድ “ባየ-በሰማ” የሚባል አይደለም፡፡ ካላሳተፍነው ዛሬም “የምታቀኝ የማላውቅህ” ይባላል፡፡ “ውሸትክን ፈጥጠህ ሳቅሁ ባይ” የሚባለውን ዓይነት ይሆናል - ክፉኛ ይታዘበናል፡፡ ውሎ አድሮም ያስከፍለናል! እንደ “ማነው ምንትስ” (እሳት ወይ አበባ)
“ሥራችንን ወስደውብን
ስሙን ብቻ በተዉልን”
ብሎ ህዝብ አይተወንም፡፡ በገዛ ኃብቱ፣ በገዛ ስልጣኑ እየተሞናደልን፣ ‹ላንተ ስንል ፎቅ ሰራን፣ ላንተ ስንል ቪ-ኤይት መኪና ነዳን፣ ላንተ ስንል ልጆቻችንን ውጪ አገር ውድ ትምህርት ቤት አስገባን› ቢሉት፤ ትዝብቱ ከስላቅና ምፀት ጋር ይሆናልና በታሪክ እጠይቅሃለሁ ማለቱ አይቀሬ ነው! ዛሬ ቢያንስ የፊት ለፊት ሸፍጥ ቀርቷል፤ እንላለን፡፡ መረጃ መደበቅም፣ ዕውነት አስመስሎ የተንሸዋረረ መረጃ መስጠትም፤ ያስጠይቃል። ያሳጣል!! ያስፈርዳል!! በዘልማድ ገዢን እያወደሱ ማስጨብጨብም ሆነ ማጨብጨብ፤ መልሶ አሳፋሪ የሚሆነው ለእኛው ነው!! በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዐውድ ላይ ለእኔ ሰፋ ያለና የተለየ ማዕረግ ካልተሰጠኝ ብሎ መመኘት፣ ዛሬ ከስግብግብነት ያለፈ ፖለቲካዊ ሙስና ነው! ቢያንስ የፈረንሳይን አብዮት ተልዕኮ ማለትም፡- “ነፃነት፣ እኩልነትና ወንድማማችነትን” እናፅና! እንፅናና!! የኢትዮጵያ በር ተከፍቶ፣ “ኑ ልጆቼ!” አለች የተባለው ቢያንስ ለመሞሻለቅና ውሻ በቀደደው ጅብ እንዲገባ ለማድረግ እንዳልሆነ ከህሊናችን ጋር ያለን ሁሉ፤ አንስተውም!! ችግራችንን በጋራ እንፍታ ለመባባል እንጂ አሁንም ዘራፍ ለማለት፣ አሁንም ጠባብ ስሜት ለመቧቸርና “እኔ በትልቁ ስታዲየም ልጫወት፤ አንተ በትንሿ ስታዲየም ተጨዋት” ለመባባል አይደለም!! እኔ እንደ ልቤ የምሄደው የሌላውን መንገድ አጥሬ ነው ማለት የወረደ አካሄድ ነው፡፡ እኔ የማድገው ሌላውን ቀብሬ ነው የሚል አስተሳሰብ አደገኛ ነው፡፡ አለበለዚያ ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፡- አሁንም “የአበሻ መኪና አነዳድ፤ በሌላው መንገድ መገድገድ!
የአበሻ ንግድ፣ የሌላውን ትርፍ ማሽመድመድ!” ይሆንብናል፡፡ ከዚህ ይሰውረን!!

Saturday, 11 August 2018 10:56

ውሻው

 ሻምበል ባህሩ ገርበብ ብሎ በተከፈተው ፍሬንች ዶር አሻግረው ውጪውን እየተመለከቱ ቁዘማ ላይ ናቸው፡፡ ጥሪ መደበሪያቸው የነበረው ቴሌቪዥን ባይበላሽ ኖሮ፣ ይሄኔ እዚያ ላይ ነበር የሚጣዱት፡፡ ግን ከዚያ ከተረገመ መደበሪያ ማሽን ጋር ከተፋቱ ዓመት ሊሞላቸው ነው፡፡ ፊቱ ላይ ዳንቴሉን ጣል እንዳደረገ፣ እዚያው ኮመዲኖ ላይ ቦታውን እንደያዘ ነው፡፡ ቴሌቪዥኑም የተቀመጡበት ሶፋም የተገዙት ከስድስት ዓመት በፊት ነው፡፡ አንድያ ልጃቸው ብርቅነሽ አረብ አገር በሄደች በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በላከችው ገንዘብ ነው እነዚህ ነገሮች የተገዙት፡፡ ወለላቸውን ሊሾ ያደረጉትና ፍሬንች ዶር የገጠሙትም ያኔ ነው፡፡ (በድሆች መንደር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ለውጥ ከታየ፣ ወደ አረብ አገር የሄደች ልጅ መኖሩን የሚያመለክት ነገር ነው)፡፡
ቤታቸውን ቤት፣ ቤት ያሸተተችው ይህች ብርቄ አሁን የለችም፡፡ በአሰሪዋ ተገድላ አፈር ከተጨናት አራት ዓመት ከሦስት ወር ሆኗታል፡፡ ትሩፋቶቿ ብቻ ናቸው አሁን የቀሩት፡፡
ፀሐይዋ አቅሟን አበርትታ ስትጠጋው በራቸው ስር ተኝቶ የነበረው ውሻ ተነስቶ ሱክ ሱል እያለ ሲሄድ ሻምበል ባህሩ በዓይናቸው ሲከተሉ ቆዩና፤ “እኔ እኮ የዚህ ውሻ ነገር አንዳንዴ ግራ ያጋባኛል” አሉ፡፡ የንግግሩ መዳረሻ እጠባቧ ጓዳ ውስጥ እየተንጎዳጎዱ የነበሩትን ባለቤታቸውን ታሳቢ ያደረገ ነበር፡፡ ከወ/ሮ ባዩሽ ግን ምንም የተሰማ ነገር የለም፡፡
“የዚህ የቦቢ ነገር አንዳንዴ በጣም እኮ ነው የሚገርመኝ፤ ዝም ብዬ ሳየው ብዙ ነገሩ በግ እየመሰለኝ ነው፡፡” አሉና ቀጠሉ፡፡ ከአፍታ ዝምታ በኋላ፤ “ፀጉሩ ራሱ የበግ ለምድ እኮ ነው የሚመስለው፡፡” ከውስጥ በኩል ብቻ በጭቃ ወደተመረገው በር አልባ ኩሽና እያመራ ያለው ውሻ ላይ ነው አሁንም ዓይናቸው ያለው፡፡
“ጭራው ራሱ እኮ የቆላ በግ ላት ነው የሚመስለው፡፡” ሌላ ማመሳሰያ ተከተለ፡፡
“አሁንስ ይሄን ውሻ በግ አደረጉት እኮ!” አሉ ባላቸውን በአንቱታ የሚያወሩት ወ/ሮ ባዩሽ እዚያው ጓዳቸው ውስጥ እየተንጎዳጎዱ፡፡
“ምን! አይመስልም ልትይኝ ነው?” አሉ ባል ድምፃቸውን ዘለግ አድርገው፡፡ መልስ ግን አላገኙም፡፡ ውሻው ኩሽናው ውስጥ ገባና ተዘረጋ። እነ ሻምበል ባህሩ ከአራት ጎረቤቶቻቸው ጋር የሚጋሩት ኩሽና ነው፡፡ ለቦቢ ደግሞ ከከረረው የፀሐይ ቃጠሎ የሚሸሸግበት ሁነኛ ታዛው ነች፡፡
“ካልሽ እንደውም አጯጯሁ ራሱ ከሌሎቹ ውሾች የተለየ ነው፡፡ ምን! አይደለም ልትይኝ ነው!”
“አንድ ፊቱን እኮ በግ ነው ሊሉኝ ነው ምንም አልቀረዎት፡፡” አሉ ሚስት ረከቦትና ጀበና አንጠልጥለው ይዘው እየወጡ፡፡
“ቆይ ቢያንስ” አሉ ሻምበል ባህሩ፡፡ ሌላ ትንሽ ዝምታ ሆነ፡፡ “ኧረ’ዲያ!› አሉ ወደ ባለቤታቸው አዘምሞ የነበረውን አንገታቸውን ወደ ውሻው አቅጣጫ እየመለሱ፡፡
ረከቦትና ጀበናውን አስቀምጠው ወደ ጓዳ እየተመለሱ ነው ወ/ሮ ባዩሽ፡፡ የብረት ምጣድ የቆለሉበትን ከሰል ምድጃ ይዘው ተመለሱና፣ የተከበረ ቦታው ላይ አኑረው ተመልሰው ገቡ፡፡
“ባዩ! አንቺ ባዩሽ” እያሉ መጡ፤ የሆኑ ሴትዮ፡፡ ድምፃቸውንም ተከትለው በሩ ላይ ተከሰቱ፡፡
ከፊት ለፊት የተቀበሏቸው ሻምበል ባህሩ ናቸው፡፡
 “እንዴ ሻምበል--- እንዴት ዋልክ?”
“እንዴት ዋልሽ አስካለች? ግቢ፣ አረፍ በይ” እረፍት ጋበዙ፡፡
“ምኑን ተቀመጥኩት ብለህ ነው--”
“አስኩ መጣሽ! እንውጣ አይደል፣ ወይ የኔ ነገር! አቀራርቤው ብሔድ ይሻላል ብዬ እኮ ነው” እያሉ እጣን ማጨሻና የተቋጠረች ትንሽዬ ላስቲክ ይዘው ከጓዳ ወጡ፡፡
“በይ ነይ ውጪ፤ እነ ገነት ከመጡ ቆዩ” አሉ ወ/ሮ አስኩ፡፡
ወ/ሮ ባዩሽ በእጃቸው የያዙትን አስቀመጡና እዚያው ከቡናው ቦታ ጎን የግድግዳውን ጥግ ይዞ የተቀመጠው ኮመዲኖ ላይ የነበረውን ነጠላቸውን አንስተው አዘቀዘቁ፡፡
“ምግብ እንደሆነ ስትመጪ ብለዋል እንግዲህ፡፡ በይ ነይ እንውጣ”
“በል እንግዲህ ሻምበል” አሉና ወ/ሮ አስካለች በሩን ለቀቁ፡፡
“በሉ እሺ!” ሸኟቸው ሻምበል፡፡
ራቅ ብላ የምትታየው ኩሽና ውስጥ የተኛው ቦቢና ሻምበል ባህሩ ብቻ ቀሩ፡፡
“ውሻ ሰውን እየጮኸ ስለሚጠብቀውና በታማኝነት ስለሚያገለግለው ተወደደ እንጂ ከበግ ምንድን ነው የሚለየው? ሰው ደግሞ ስላገለገለው ብቻ ታማኝ ጓደኛ ምናምን እያለ ዝም ብሎ መካብ ይወዳል፡፡ ክቦ ክቦ ሲያበቃ እንደገና ያ አልበቃ ብሎ ውጉዝ በማድረግ ይጠብቀዋል፡፡ ከእነ በግ ለይቶ የሱን ስጋ እርም ማድረግ ምን የሚሉት ነገር ነው እስኪ አሁን፡፡ ፍጡር ፍጡር ነው፡፡ ስጋም ስጋ ነው፡፡ እንደውም ስጋው በጣም መድኃኒትነት አለው ነው የሚባለው፡፡” ይሄ ሁሉ ጭንቅላታቸው ውስጥ ነበር የሚመላለሰው፡፡ ወ/ሮ ባዩሽ ሲመጡ ፊት ለፊት የተቀበላቸው ትሪ ላይ የተከመረ ስጋ ነው፡፡ ከየት የመጣ ስጋ ነው ብሎ መጠየቅ አላስፈለጋቸውም፡፡
“ወዬው ጉድ …. ጉድ!” ሊጮሁ ሁሉ ከጅለው ከአፋቸው ላይ ነው የመለሱት፡፡
“ኤዲያ! ምን እዚህ እንትን ትላለች! ባክሽ ወታደር ቤት እያለን ስንቱን በልተናል፡፡ እነዚህ ቻይናዎቹ ውሾችን እየበሉ ጨረሷቸው ብለሽ የነገርሽኝ ራስሽ አይደለሽ? በቀኖና ታስረን እንጂ እኛስ ምን ለየን? ደሞም በዚህ መርከስ እንደዚያ የሚያደርግ ከሆነ መርከሱ ያዋጣል፡፡ መድኃኒት ነው ደግሞ--”
ወ/ሮ ባዩሽ ምራቃቸውን ቱ … ቱ … እያደረጉ እግዚኦታቸውን ያነበንቡታል፡፡ ከጓዳ ሳሎን፣ ከሳሎን ጓዳ እየተንቆራጠጡ ነው ቱ … ቱ…. ዋቸውን የሚያዘንቡት፡፡
“ይልቅ እምትሰሪልኝ ከሆነ ስሪልኝ፡፡ አለበለዚያ…” ብለው ሳይጨርሱ ባለቤታቸው ተቀበሏቸው፡፡
“ማ እኔ ባዩሽ!” አሉና መፀየፋቸውን በቁጣ እያቀጣጠሉ ተንቦገቦጉ፡፡ ከዚያም ጓዳ ገብተው ጠፉ፡፡
(ሰሞኑን ለንባብ ከበቃው “ሌላ ዓለም” የተሰኘ የአጭር ልብወለድ መድበል የተወሰደ)

በገጣሚ ሰላማዊት አድማሱ የተገጠሙና በማህበራዊ፣ በአገር፣ በተፈጥሮና በስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ከ55 በላይ ግጥሞችን ያካተተው “ያረፈደ ዳዴ” የተሰኘ የግጥም ስብስብ ለንባብ በቅቷል፡፡
ግጥሞቹ ከልጅነት ሀሳቦች ጀምሮ እያደጉ የመጡና በውስጧ የሚመላለሱ ጥያቄዎቿን ለመግለፅ የሞከረችበት መሆኑን ገጣሚዋ በመድበሉ መግቢያ ላይ ጠቁማለች፡፡ 86 ገፆች ያሉት መፅሐፉ፣ በ40 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡