Administrator

Administrator

- በሲቢኢ ብር መተግበሪያ የመግቢያ ትኬት መሸጥ ተጀመረ
- ሲቢኢ ብር ኤክስፖ 2017  አዲስ ነገር በአዲስ ዓመት ረቡዕ በድምቀት ይከፈታል
-  የፊታችን ቅዳሜ ነሐሴ 18 ደማቅ ኮንሰርት ተዘጋጅቷል
- የ100 ብር ትኬት በ100 ብር ገዝተው የ2 ነጥብ 3 ማሊዮን አዲስ መኪና ይሸለሙ
-ትኬቱ ከሲቢኢ ብር በተጨማሪ  በኤግዚቢሽን ማዕከልም ይገኛል
--ከ35 በላይ አንጋፋና ወጣት ተወዳጅ ድምፃዊያን በየቀኑ ሸማችና ጎብኚን ለማዝናናት ከፍተኛ ዝግጅት አድርገዋል
- በኤግዚቢሽን ማዕከል በተመጣጣኝ ዋጋ  የሚፈልጉትን  እየሸመቱና እየጎበኙ እየተዝናኑና እየተሸለሙ ለ20 ቀናት ይቆያሉ
-ከመኪና በተጨማሪ ከ5 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር መጠን ያላቸው የዕቃ መግዣ ኩፖኖች፣ ኢባይክ እና የዲኤስ ቲቪ ዲኮደሮች በመግቢያ ትኬት ዕጣዎ ያገኛሉ
--ይህ ሁሉ ዕድል የሚገኘው በ100 የመግቢያ ትኬት እጣ ነውና መተግበሪያውን በማውረድ አሁኑኑ ትኬትዎን ከሲቢኢ ብር ይግዙ
     በኤግዚቢሽን ማዕከል
-ሸመታውም በሽበሽ
-መዝናኛውም በሽበሽ
-ሽልማቱም በሽበሽ
አዘጋጅ
ታሜሶል ኮሙኒኬሽን ከአሴንቲክ ሶሉሽንና ከሊያን ኩባንያ ጋር በመተባበር
የኤክስፖው የክብር  ስፖንሰር
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
የወርቅ ደረጃ ስፖንሰሮች
ራይድ
ፔፕሲ
አኳኡኑ ውሃ
የኢትዮጵያ ሎተሪ አገልግሎት
ካቻ
ዋፋ
ስንቅ ማልት
ንጉስ ማልት
ለበለጠ መረጃ
0911516739 ይደውሉ
ታሜሶል ኮሙኒኬሽንስ
መልካም አዲስ ዓመት

Saturday, 17 August 2024 00:00

በለስ ታሪክን አያርገኝ

 (ከፍል 2)
                            ነ.መ


….ተንጦ ቅቤ እንዳልወጣው
እርጎም እንደማይሆን ወተት
ወርቁን እንዳጣ ሰም ቅላጭ
ውል እንደሌለው መቀነት
ግርማ ሞገሴን አክስለው፣
ዳግም ጭረው እንዳይሞቁኝ
መጎናፀፊያዬን ገፍፈው፣
እርቃኔን እንዳይጋልቡኝ፣
መልዐክ - ታሪክ ይጋርደኝ
በለስ ታሪክን አያርገኝ፡፡
እንዴ በእፍረት አንዴም በልክ
አንዴ በእክል አንዴ በእልክ
በጋን ሾመው እንዳኖሩት፣
የ3 ሺህ ዘመን ታሪክ
አንዴ ጦርነት ስታከክ
አንዴ በገዢ ስላከክ
አንዴ በጣፊ ስታወክ
አንዴ በትውፊት ስተረክ፤
አንዴ በመቶ ስወሰን
አንዴ በሺዎች ስታመን
አንዴ በ’ድሜ ልክ ስከበር
አንዴ እንደሌለሁ ስቀበር
አንዴም እንዳለሁ ስፎከር
ዘና ሲሉ እንደራሙቻ፣
እንደጉድፍ አብጠልጥለው
ሲጨነቁ እንደዳዊት፣
እንደፀሎት አነብንበው
ቀን ሲያመርር እንዳያስሩት
ጥኑ እምነቴን ማተብ አርገው
የደጉን ጊዜ መቆያ፣ ሰላምን ለጦርነት እጅ
ጦርነትንም የሰላም፣ የክፉ ቀን ነገረ-ፈጅ
አርገው አጉል እንዳይጥፉኝ
በየቀኑ እንዳልጠና፣
ዳግም ማጣሪያ እንዳያሻኝ
የዘመን ዕድሜ ቆጥሬም፣
የልደት ውሌ እንዳይጠፋኝ
መልዐከ-ታሪክ ይጋርደኝ
በለስ ታሪክን አያርገኝ፡፡
(ለቸገረን ሁሉ-የካቲት 11/1991)


 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮ ለመክፈት የሚፈልጉ የስራ ፈቃድ ማመልከቻ እንዲያቀርቡጥሪ ያደረገው ነሐሴ 3 ቀን 2016 ዓ.ም.ነበር። በዚህም ጥሪው በአገር ውስጥም ሆነ ውጭ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደኢትዮጵያውያን ማመልከቻውን ማቅረብ እንደሚችሉ መግለጹ አይዘነጋም። የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መከፈታቸው ፋይዳው ምንድን ነው? ምንስ ተግዳሮት
ይኖራቸዋል? በዚህ ረገድ የአፍሪካ አገራት ተሞክሮ ምን ይመስላል? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ከምጣኔ ሃብት ባለሞያው የፖሊሲ አማካሪው ቆስጠንጢኖስ በርሀ ተስፋ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጓል።


          የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች መከፈት ለአገራችን ምን ጥቅም ያስገኛል?
ይሄ ሁሉም አገር ውስጥ ያለ ነው። በተለይ በየአየር ማረፊያው የውጭ ምንዛሪየሚመነዝሩት እነሱ ናቸው። በአብዛኛው እነዚህ “የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች” የሚባሉት  በየኤርፖርቱ፣ ቱሪስቶች በሚበዙበት አካባቢ...ከተማ ውስጥ ደግሞ፣ በትልልቅ የገበያ አዳራሾች ይገኛሉ። በርግጥ አሁን እየጠፉ ነው ያሉት። ምክንያቱም በኤሌክትሮኒክ መገበያየት ተችሏል። ኬንያ ኤርፖርት የነበሩት በሙሉ የሉም። ምክንያቱም ሰዎች አሁን በስልካቸው የሳፋሪኮም ሲም ካርድ ይገዙና ኤምፔሳ ውስጥ ይገባሉ። ከክሬዲት ወይም ዴቢት ካርዳቸው ወደ ስልካቸው ገንዘብ ያስተላልፋሉ። ከዚያ በኋላ በሽልንግ ይመጣላቸዋል።
አገራችን ውስጥ በርከት ያለ የውጭ ምንዛሪ ሠዎች እጅ ይኖራል የሚል ግምት አለ፤ ሰዎች እንዲሁ “መጠባበቂያ” ብለው የሚይዙት። እኒህ ሰዎች ባንክ ሄደው፣ ተሰልፈው  ለመመንዘር ጊዜ የላቸውም። በቀላሉ የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ሄደው ግን መመንዘር ይችላሉ።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ኤርፖርት ውስጥ ባንኮችን ተክተው ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። በርግጥ የግል ባንኮች ከሚሰጡት ምንዛሪ በታች ነው የሚመነዝሩት። አንደኛ ኮሚሽን አላቸው። ሁለተኛ ከነእርሱ በታች በመስጠት ብዙ ትርፍ ያገኛሉ። እንግዲህ የግሎቹ አንዱ ተግዳሮት ሊሆን የሚችለው ይህ ነው። ምክንያቱም አንድ ሰው ሊመነዝር ሲሄድ፣ ዛሬ “የምንለውጥበት ገንዘብ ይህ ነው” ብለው  ይለጥፋሉ። ብዙ ትርፍ የሚገኝበት ስራ ነው። ነገር  ግን አገራችን ውስጥ ብሔራዊ ባንክ በቅርብ ስለሚቆጣጠራቸው፣ እንደዚህ ዓይነት ነገር ውስጥ የመግባት ዕቅድ አይኖራቸወም። በቀላሉ የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ሄደው ግን መመንዘር ይችላሉ።  የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለቱሪዝም ትልቅ አስተዋጽዖ “ይኖረዋል” ብዬ ነው የማስበው።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችና ባንኮች ምንና ምን ናቸው?
የግሎቹ የሚመነዝሩትን ብር ከባንክ ነው የሚወስዱት። የውጭ ምንዛሪውንም ባንክ ወስደው ነው የሚያስቀምጡት። ስለዚህ ከባንክ ጋር ነው የሚሰሩት። ብዙ አገራት የባንክ ቅርንጫፎቻቸው እየዘጉ ነው ያሉት። አሁን ስዊድን፣ ደቡብ ኮሪያ በሶስት ዓመት ውስጥ የባንክ ቅርንጫፍ የሚባል አገራቸው ውስጥ አይኖራቸውም። ምክንያቱም ሰዎች  በስልካቸው  መገበያየት ጀምረዋል። በአገራችን የኢንተርኔት ነገር የማያወላዳ ስለሆነ ነው እንጂ አሁን ኤምፔሳ የዛሬ አምስት ዓመት በስልክ የተገበያዩ ኬንያውያን፣ ወደ 45 ትሪልዮን ሽልንግ ነው ያስተላለፉት። ስለዚህ ወደፊት ባንክ ቅርንጫፎች መኖራቸው ምንም ጥቅም አይኖራቸውም። ቅርንጫፍ ሲኖር ቤት ይከራያሉ። ሰራተኛ ይቀጥራሉ። ዕቃ መግዛት አለባቸው። ይህ  ባንኮችን ከውጪ የሚያድናቸውና አትራፊ የሚያደርጋቸው  እየሆነ መጥቷል። አገራችንም ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ዝውውር ስትገባ፣ ኢንተርኔት ደህና ሲሆን፣ ከእርሱ ጋር የተያያዙ ብዙ ስራዎች ይመጣሉ። በፋይናንሻል ቴክኖሎጂ (ፊንቴክ) ብዙ ወጣቶች በናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ኬንያ፣ ግብጽ፣ ድቡብ አፍሪካ እስከ አንድ ቢሊዮን ዶላርና፣ ከዚያም በላይ ኢንቨስትመንት የአገራቸው ያመጡ አሉ። እነዚህ ልጆች በሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ ያሉ ናቸው። ቴሌ እንግዲህ አሁን በካፒታል ገበያ ውስጥ ሲገባ፣ ለወጣቶችም ትንሽ ክፍተት ይኖራል የሚል ግምት አለኝ። እነዚህ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ከባንክ ጋር ነው የሚሰሩት። እነርሱ በሚመርጡት ባንክ ሄደው ነው የውጭ ምንዛሪ የሚያስቀምጡት። አንዳንዴ የውጭ ምንዛሪም ሊፈልጉ ይችላሉ። አብዛኛው እነርሱም የሚፈልጉት የአገር ውስጥ ብር ነው። እናም፣ ከባንክ ጋር የሚወዳደሩበት ነገር የለም። የባንክን ስራ የሚያቀልሉ ናቸው።
 እንግዲህ የግል ምንዛሪ  ቢሮዎች የሚከፈቱት አንድም ስራ ለማሳለጥ ነው። ቅድም እንዳልኩት ሌሎች አገሮች የዲጂታል ግብይት ከተጀመረ በኋላ፣ እነርሱም አላስፈላጊ እየሆኑ መጥተዋል። ግን አገራችን ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ፣ ቱሪስቶች በሚመጡበት ጊዜ፣ በየቦታው  የባንክ ቅርንጫፍ ላያገኙ ይችላሉ። በአብዛኛው የባንክ ተደራሽነት (ፋይናንሻል ኢንተርሚዴሽን የሚባለው) አገራችን ውስጥ በጣም ትንሽ ነው። በተለይም የቱሪስት መዳረሻዎች  የምንላቸው አካባቢዎች፣  የባንክ ተደራሽነት ላይኖራቸው ይችላል። ስለዚህ እነርሱ ይመነዝሩላቸዋል። ሁለተኛ ባንኮች አንዳንዴ ገንዘብ ለማውጣት ሲኬድ።  “ሲስተም” የለም ይባላል። እነዚህ ግን  ሥራቸው ብር መመንዘር ስለሆነ፣ በቀላሉ ፈጣን አገልግሎት ይሰጣሉ። በተለይ ለቱሪዝም ዘርፉ አስፈላጊ ናቸው።   የዲጂታል ግብይታችን በጣም ሰፍቶ እስኪሻሻል ድረስ፣ ጥሩ ስራ ሊሰሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።
በአፍሪካ የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ተሞክሮዎች ምን ይመስላል?
- ሁሉም አገር አለው። አሁን ለምሳሌ:- ኬንያ አለ። ታንዛኒያ አለ። ዩጋንዳ አለ። ናይጄሪያ አለ። የሌለበት አገር የለም። እኛ እኮ የፋይናንስ ሴክተሩን ዘግተን ስለቆየን ነው ይህ ሁሉ ጭቅጭቅ የመጣው። በአጼ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስት የውጭ ባንኮችም ነበሩን- እነ ባንኮ ዲ ሮማ። ካፒታል ገበያም ነበረን። አብዛኞቹ ደርግ የወረሳቸው ኩባንያዎች በካፒታል ገበያ የተቋቋሙ ነበሩ። የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ድረስ አክሲዮን ኩባንያ ነው። ...በዚያን ጊዜ ትልቁ አክሲዮን ገዢ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር። ያው የግል ሴክተሩ በጣም ጠንካራ ስላልሆነ፣ ትንንሽ ኩባንያዎች ኢምፖርት ኤክስፖርት፣ እርሻ ላይ የተሰማሩ… ካፒታል ገበያ እየገቡ ነበር ገንዘብ ፈሰስ የሚያደርጉት። እርግጥ እንደ አሁኑ በጣም ውስብስብ የሆነ ካፒታል ገበያ አይደለም። አሁን በኢንተርኔት ዘመን ካፒታል ገበያዎች በጣም ውስብስብ ሆነዋል። ካፒታል ገበያዎች በጣም ተስፋፍተው ብዙ ስራ እየሰሩ ነው። አሁን ኩባንያዎች አክስዮን መሸጥ ብቻ ሳይሆን የፋይናንስ ገበያዎችም ያካሂዳሉ- ገንዘብ ይገበያያሉ። ሰዎች አንዱን ገንዘብ ይገዙና ያስቀምጣሉ። ያ ገንዘብ ይጨምራል ወይም ይከስራል ሲባል ደግሞ እንደገና እርሱን እየሸጡ ይቀይራሉ። እነ ማሌዢያ፣ ኢንዶኔዢያ እንደዚህ ዓይነት ብዙ ጨዋታዎች ተጫውተዋል። በተለይ በቅኝ ግዛት ሥር የነበሩ አገሮች የቅኝ ግዛቱን የፋይናንስ ስርዓት እንዳለ ነው የቀጠሉት። ስለዚህ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች አፍሪካ ውስጥ በደንብ ይሰራሉ። በደንብ ገንዘብ ይመነዝራሉ።
የግል የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ለነዚህ አገራት የኢኮኖሚ ዕንቅስቃሴ ምን ፋይዳ አላቸው?
ብዙ ጊዜ  ከእነርሱ ጋር የተያያዘ ችግር በሚመጣበት ጊዜ ቶሎ በይታወቃል-መንግስት አብሮ ካልተጨመረበት በስተቀር። አሁን በናይጄሪያ ለምሳሌ፣ በአንድ ወቅት 20 ቢሊዮን ዶላር ጠፋ፤ ከነዳጅ ያገኙት ክፍያ። ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ይህን የጠፋ ገንዘብ አስገኛለሁ። ብለው ነው ሁለቴ የተመረጡት። ነገር ግን እርሱንም ሳያገኙ፣ ኢኮኖሚውን አውድመውት ነው ለአዲስ ፕሬዝዳንት ያስረከቡት። እነዚህ ቢሮዎች ብዙ ወንጀል ሊሰሩ የሚችሉበት ሁኔታ አለ። ዋናው ነገር ምንድን ነው፤ በተለይ  አዳዲስ ባንኮች በሚገቡበት ጊዜ፣ ጠንካራ የገንዘብ አስተዳደር (ሞኒተሪ ፖሊሲ አድሚኒስትሬሽን) ስርዓት ያስፈልገናል። እነርሱን የሚቆጣጠር የአስተዳደር ድርጅት (ሬጉላቶሪ ኢንስቲትዩሽን) የግድ ነው። ስለዚህ ብሔራዊ ባንክና ሌሎች በቁጥጥርና አስተዳደር ስራ የሚሰማሩ የመንግስት ተቋማት፣ ከፍተኛ ክሕሎት ያላቸውና ይህን መቆጣጠር የሚችሉ መሆን አለባቸው። አሁን አንዳንድ ባንኮቻችን የብር መንሳፈፍ የሚባለው ታሪክ የገባቸው አይመስለኝም። አልለመዱትም።  ስንቶቹ የፋይናንስ ክሕሎት እንዳላቸው አላውቅም። ምክንያቱም አብዛኛዎቹ አካውንቲንግ፣ ኢኮኖሚክስ የተማሩ ናቸው። ግን ከዚያ ሌላ በእንደዚህ ዓይነት ባንክ ውስጥ መስራት ያስፈልጋል፤ ይህንን ልምድ ለማግኘት። ምናልባት በውጭ ባንኮች የሰሩ ሰዎች እኝደዚህ ዓይነት ነገር ቶሎ ሊገባቸው ይችላል። አብዛኛዎቹ የብር ዋጋ እንዲህ ወደ ሰማይ የሚቆልሉት… በዌስተርን ዩኒየን የዲያስፖራ ገንዘብ ሲመጣ፣ ኮድ ነው የሚላከው። ስለዚህ አንዱ ባንክ 57 ብር ነው የምሰጠው፤ ሌላው ባንክ 105 እሰጣለሁ ካለ፣ 107 የሚሰጠው ጋ ነው የሚሄዱት። ለዚህ ነው የሚቆልሉት። እስከ አሁን ድረስ ዶላር ያገኙ አይመስለኝም፤ ዶላርም የሸጡ አይመስለኝም። እነዚህ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በየቀኑ የሚሰሩትን ነገር ለማወቅ፣ ገንዘብ ወደ ማጠብ እንዳይገቡና፣ በጥቁር ገበያ ውስጥ እንዳይሰማሩ… ጥብቅ የሆነ አሰራር ያስፈልጋል።
እነዚህን የግል ምንዛሪ ቢሮዎች ለማስተዳደር የሚያስችል የሕግና የአስተዳደር አቅም አለን ብለው ያስባሉ?
ብሔራዊ ባንክ እንደዚህ ዓይነት መመሪያ ያወጣው ይህ አቅም ‘አለን‘ ብሎ ነው። አሁን ይህን ፈቃድ ሲሰጥ የራሱን አቅም ግንባታ ማካሄድ ይኖርበታል። ደግሞ ያንን “አድርጓል” ብዬ ነው የማስበው። ከዚህ የባሰ አሁን የውጭ ባንኮች ይመጣሉ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ። እነርሱን ማስተዳደር መቻል ይኖርብናል። በዚያ ላይ ሰፋ ያለ ክህሎት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ይህንን በማስተዳደር። ብሔራዊ ባንክ አካባቢ ከፍተኛ የአቅም ግንባታ ‘ያስፈልጋል’ ብዬ አምናለሁ።
እኔ 26 የአፍሪካ አገሮች ሰርቼአለሁ። “የጥቁር ገበያ” የሚባል ሰምቼ አላውቅም። የላቸውም። እኛ አገር ብቻ ነው ያለው። እሱንም መንግስት ነው ያመጣብን ዓለም የደረሰበት አልደርስም ብሎ  የሙጥኝ በማለቱ ነው  ለዚህ የዳረገን።  የመንግስት ሃላፊዎች ቁጥጥራቸውን አጥብቀው የሚሰሩ ከሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ምንም ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ካልሆነ ግን እነርሱም ወደ ጥቁር ገበያ ሊቀየሩ ይችላሉ የሚል ግምት አለኝ።

 ዳሸን ባንክ ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂ ጋር በመተባበር ከወለድ-ነጻ የዱቤ አገልግሎት ማግኘት የሚያስችል “ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ” አገልግሎትን ትላንት አስተዋወቀ፡፡ ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ “IFB DubeAle” የሸሪዐህ መርሆዎችን ተከትሎ የሚሰራ አገልግሎት ሲሆን፤ እንደ ሽያጭ ውል የሚሰራና በደንበኛው ጥያቄ መሰረት የዱቤ አገልግሎት ማግኘት የሚቻልበት አሰራር ነው፡፡
ስለ አገልግሎቱ ማብራሪያ የሰጡት የዳሸን ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አስፋው ዓለሙ፤ በባንኩ ከወለድ-ነጻ ሂሳብ ያለው ደንበኛ አገልግሎቱን መጠቀም እንደሚችል አስረድተዋል፡፡ ደንበኞች የዱቤ አለ መተግበሪያን ከጎግል ፕሌይ ወይም ከአፕ ስቶር ላይ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልካቸው አውርደው መመዝገብ የሚችሉ ሲሆን፤ በአቅራቢያቸው በሚገኝ የዳሸን ባንክ ቅርንጫፍ ለዱቤ አለ ማመልከት እንደሚችሉም ገልጸዋል፡፡
ደንበኞች በባለሙያ ታግዘው የደንበኝነት መረጃዎችን ማሟላትና ከገቢ አቅማቸው ጋር የተገናዘበ የዱቤ ገደብ ማስወሰን የሚያስችላቸው አሰራር መዘርጋቱንም አክለዋል፡፡ ባንኩ አዳዲስ አገልግሎቶችን የማስተዋወቅ ጥረቱን በመቀጠል አሁንም ከኤግል ላየን ቴክኖሎጂስ ጋር በመተባበር የቆየውን የማህበረሰባችንን የዱቤ ግብይት በዘመናዊ ቴክኖሎጂና አስተማማኝ የባንክ አሰራር በማገዝ “ከወለድ-ነጻ ዱቤ አለ” የተሰኘና ሸማቾች በዱቤ በፈለጉት ጊዜ ያሻቸውን ገዝተው ቆይተው ከወለድ-ነጻ በሆነ መንገድ መክፈል የሚችሉበትን አሰራር እንዳስተዋወቀም ተመላክቷል፡፡
ይህን አገልግሎት ለማግኘት ደንበኛው በግልና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ተቀጥሮ የሚሰራ ከሆነ ከሚሰራበት መስሪያ ቤት የገቢ መጠንና የቅጥሩን ማረጋገጫ የሚገልጽ ደብዳቤ ማቅረብ ይኖርበታል። አመልካቹ በግል ስራ የሚተዳደር ከሆነ የሚሰራውን የስራ አይነትና ድርጅት የሚገልጹ ማስረጃዎችን ማሟላት ይጠበቅበታል። በተጨማሪም ደንበኛው ቋሚ ንብረት ካለው እንደ ዋስትና ማስያዥያ አልያም የሶስተኛ ወገን ዋስትና ማቅረብ ይችላል። ደንበኛው በባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ ካለው ጥሬ ገንዘብ (በዉጭ ምንዛሬ ወይም በብር) ዋስትና ማስያዝ እንደሚችልም ተብራርቷል።
ዳሸን ባንክ አሁን ላይ ባስተዋወቀው “ከወለድ ነጻ-ዱቤ አለ አገልግሎት” ደንበኞች እስከ ሰባት መቶ ሺህ ብር ድረስ ያሻቸውን መሸመት ያስችላቸዋል፡፡ ከወለድ ነጻ ዱቤ አለ ተጠቃሚዎች ዛሬ ለገዙት በሸሪዓህ ህግ የተፈቀዱ ምርትና አገልግሎቶች ክፍያውን ወደፊት የሚከፍሉ ሲሆን፤ አከፋፈሉም እንደ ደንበኛው ምርጫ በ3 ወር፣በ6 ወር እና በ12 ወር ይሆናል፡፡ ዳሸን ባንክ ከዚህ ቀደም በመደበኛው የባንክ አገልግሎት ዘርፍ “ዱቤ አለ” አገልግሎትን ማስተዋወቁ ይታወሳል ፡፡


የአረንጓዴ አሻራ ቁጥሮች አስደናቂ ናቸው- በአገርም በአዲስ አበባም። ከዓመት ዓመት እየጨመረ የመጣው የችግኝ ብዛት ዘንድሮ ወደ 40 ቢሊዮን ይደርሳል። ምን ማለት እንደሆነ አስቡት።

የአገር አሻራ እየሰፋ
የችግኝ ቁጥር እየበዛ
2011 4.7 ቢሊዮን
2012 10.6 ቢሊዮን
2013 17.7 ቢሊዮን
2014 25 ቢሊዮን
2015 32.5 ቢሊዮን
2016 40 ቢሊዮን


ኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር እስከ ዳር ቢተከል፣ ከአምስት ወይም ከስድስት ሜትር ባልበለጠ ርቀት ውስጥ የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የማግኘት ያህል ነው ብዛቱ። ታዲያ ይሄ ቀላል አሻራ ነው? የዚህ ታሪክ ተቋዳሽና ተከፋይ ኢትዮጵያውያንም ሚልዮኖች ናቸው። ደግነቱ፣ የታሪክ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆን ባለቤት ለመሆን፣ የመግቢያ ፈቃድና ክፍያ አይጠየቅበትም። ሁሉም የዐቅሙን ያህል ችግኝ እየተከለ የታሪክ አሻራውን ለትውልዶች ይተክላል።
የአዲስ አበባን ደግሞ ተመልከቱ።
ዓምና የተተከሉ 17.5 ሚሊዮን ችግኞችን ጨምሮ ባለፉት አራት ዓመታት ከ58 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል።
ዘንድሮ 20 ሚሊዮን ችግኝ የመትከል ዘመቻ ሲታከልበት፣ ከ78 ሚሊዮን ያልፋል።

የችግኝ ብዛት በአዲስ አበባ
2011-14 41 ሚልዮን
2015 58.5 ሚልዮን
2016 78.5 ሚልዮን

አዲስ አበባን ከጥግ እስከ ጥግ በሦስት ሜትር ርቀት ችግኞችን የመትከል ያህል ነው ብዛቱ። ግን ገና ይቀረዋል።
ብዙ ስለሚቀረውም የከተማዋ ነዋሪዎች በየሳምንቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን ይተከላሉ።
እናንተም ወይ ተክላችኋል። ወይ ሲዘገብ ሰምታችኋል። ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ደግሞ በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችና የኪነጥበብ ሰዎች የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ባዘጋጀው ፕሮግራም፣ የድርሻቸውን ችግኝ ተክለዋል።
ዜና በመናገርና ሰዎችን በማበረታታት ብቻ ሳይሆን በተግባር አሻራቸውን በሥራ አሳይተዋል። መልካም ተግባርን ከሩቁ ማየትና መስማት… ጥሩ ነው። በጎ ነው። በተግባር ሲሠሩት ግን ልዩ ስሜት ይሰጣል ብሏል የሚዲያ ባለሙያው ሽመልስ ለማ።
ስሜቱንና ሐሳቡን ስንጠይቀው ሽመልስ እንዲህ ብሎናል።
በአካል መጥተህ ራስህ ስትሠራው የምታገኘው ስሜት ልዩ ነው። ራስህ እየተከልክ ነው ልዩነቱ የሚገባህ። እንደ ልጅህ ነው፣ ችግኝ ስትተክል የምትሳሳለት። የተከልኳቸው ችግኞች ላይ ጂፒኤስ ባስርላቸው ደስ ይለኛል። ካደጉ በኋላ “እነዚህ የእኔ ነበሩ” ስል ይታየኛል።
አስገራሚ የመንፈስ እርካታ እንደሚገኝበት ሽመልስ ሲገልፅ፣ “እንደ እኛ እናንተም መጥታችሁ አሻራችሁን አኑሩ። ትልቅ ታሪክ ነው” ብሏል ሽመልስ።
ታዋቂው የኪነጥበብ ሰውና “የቤቶች ድራማ” ፈጣሪ ጥላሁን ጉግሳ በበኩሉ፣ ችግኝ መትከል የሁላችንም ጉዳይ ነው፤ ለሌላ ብለን ሳይሆን ለልጆቻችን ነው የምንተክለው ብሎናል።
“ነገን ዛሬ መትከል” የሚለው መሪ ቃል ትልቅ ትርጉም የያዘ እንደሆነ ሲገልጽ፣ ለነገ የሚሆነውን ነገር ዛሬ ከወዲሁ መሥራት መቻል ማለት ነው ይላል። ታዲያ ይሄ እንዴት ያምልጠን?
የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ባዘጋጀው በዚሁ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ላይ የዛሬ ዓመት መጥተን ችግኞችን ተክለናል። ነገ ስንለው የነበረው ጊዜ… ይሄውና ዓመት ቆጥሮ መጣ።
ዘንድሮ ይሄውና ደረሰ። አሁንም እንደገና ለመጪው ጊዜ ለነገ እንተክላለን።
ጥቅሙ ለአገር ነው። ጥቅሙ ነገ ለሚመጡት ታዳጊዎች ነው። ጥቅሙ ለሕዝብ ነው። ለሌላ አይደለም።
የሁላችንም የጋራ ዓላማችን መሆን አለበት።
ለማንም ብዬ አይደለም የምተክለው። እኔ የምተክለው ለነገ ለልጆቼ ነው። ነገ ኢትዮጵያን ለሚረከቧት ትውልዶች ነው።
’ቤቶች’ ድራማ 12ኛ ዓመት የገባ ድራማ ነው ፤ አምስቱንም ዓመት በችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈናል፤ ወደፊትም ይህንኑ እንቀጥላለን ብሏል- ጥላሁን ጉግሳ።
እውነት መቀጠል ማስቀጠል ነው የሚሻለው። በአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የዘንድሮውን አረንጓዴ አሻራ ሲያስጀምሩም ይህን ነበር የተናገሩት። ከተማችንን እናበለጽጋለን፤ እያስዋብን እንቀጥላለን፤ የከተማችንን አረንጓዴ ሽፋን 30 በመቶ እናደርሳለን ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከ3 በመቶ በታች ወርዶ የነበረው አረንጓዴ ሽፋን ወደ 17 በመቶ ማደጉን የገለጹት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ልምላሜን ከማስፋፋትና ከተማን ከማስዋል ጎን ለጎን የአትክልትና የፍረፍሬ ችግኞችም እንደሚተከሉ ተናግረዋል። የኢኮኖሚና የኑሮ ጉዳይ፣ መንፈስን ከሚያድስ ውበትና የአካባቢ ልምላሜ ጋር የሚስማማ እንጂ የሚቃረን አይደለም።
ሰሞኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው እንደተናገሩት ከሆነም ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴዓሻራ የተተከሉ የፍራፍሬ ችግኞች ከፍተኛ ለውጥ እያመጡ ናቸው።
የአረንጓዴ አሻራ ትርጉሞች
አረንጓዴ አሻራ፣ አገርን አረንጓዴ ማልበስ ነው። ግን ከዚያም በላይ ነው።
በእርሻ ምርት ራሳችንን ችለን ለሌሎች ለመትረፍም ነው ችግኝ የምንተክለው ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የፍራፍሬ ጭማቂ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች መስፋፋት አለባቸው። የሚሳካልን ግን ችግኞችን ከተከልን ነው።
በአፍሪካ በግዙፍነታቸው አንደኛና ሁለተኛ የሆኑ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድቦችን እየገነባን ነው። ግድቦቹ በቂ ውኃ የሚኖራቸውና ውጤታማ የሚሆኑት ግን ችግኞች ከተከልን ነው።
በእርሻም፣ በኢንዱስትሪም፣ በመሠረተ ልማትም… ሁሉም እንዲሳካ ነው ችግኝ የምንተክለው። ለነገ ለልጆቻችን የምንፈጥረው ሀብት ነው ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ። ይህንም ሐሳብ ያፍታቱታል።
ኢትዮጵያ ካለ ምንም ጥርጥር ራሷን ትመግባለች። ለራሷ የሚበቃ ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የሚተርፍ እህልና ፍራፍሬ ታመርታለች።
ካለ ምንም ጥርጥር ከተሞቿን ትለውጣለች።
ካለ ምንም ጥርጥር ከዕዳ ቀንበር ትገላገላለች።
ካለ ምንም ጥርጥር አርአያ የሆነ ሥራ በአፍሪካ ትሠራለች።
ብልጽግናዋን ታረጋግጣለች።
ይሄ ሁሉ እውነት እንደሆነ ከገለፁ በኋላ፣ ግን ምኞት ብቻ መሆን የለበትም ብለዋል።
ንግግር ብቻ መሆን የለበትም። በተግባር መሥራት አፈር መንካትና ችግኝ መትከል ይፈልጋል። ከተማ ማጽዳት ይፈልጋል።
አበርትተን ከሠራን በእርሻ ላይ ያመጣነው ውጤት በሌላም እናሳድገዋለን። በስንዴ ላይ ዓለም የሚመሰክርለት ውጤት አምጥተናል። ሩዝ በዕጥፍ ጨምሯል።
ያማረች፣ ንጹሕ የሆነች፣ ለኑሮ የተመቸችና የምትስማማ፣ ቱሪስቶችንም የምትስብ ኢትዮጵያን ለማየት እናም ለመገንባት የሚፈልግ ማንም ትውልድ ቢኖር፣ ቀላሉ ሥራ ችግኝ በመትከል መጀመር ነው።
አስፋልት፣ ግድብ፣ ሕንጻ የውጭ ምንዛሪ ይፈልጋል።
ችግኝ መትከል ግን በራሳችን ዐቅም ልንሠራው እንችላለን። 130 ሺ የችግኝ ጣቢያዎች አሉ።
ለልጆቻችን ውብ አገር ማዘጋጀት እንችላለን።
አገሩን የሚወድ ማንም ሰው፣ ማንም ዜጋ፣… ሁሉም ሰው፣ ችግኝ እየተከለ አብረን ለአገር ለትውልድ እንስራ። የመንግሥት፣ የአንድ ፓርቲ፣ የአንድ ዘመን ሥራ አይደለም ብለዋል።
የመትከል፣ የማስቀጠል፣ የማጽናት፣ የመጠበቅ ሥራ ነው።፣
አብረን ተባብረን ብንቆም አገራችን ያማረች ትሆናለች።
እየመጣ ያለውን ፍሬ፣ እየመጣ ያለውን ውጤት፣ ለሥራ በመትጋት ብቻ የሚጨበጥ ስለሆነ፣ ሁላችንም እንድንተጋ አደራ እላለሁ።
ለመነሣት ማኮብኮብ የጀመረ ሀገር ከየአቅጣጫው ዱላ ይሰነዘርበታል። ጨክነን ከሠራን ግን እናሳካዋለን። ወደ ከፍታ እንነሣለን። ደቡብ ኮሪያ አሳክታለች። ቻይና አሳክታለች። ሲንጋፖር አሳክታለች። አሜሪካ አሳክታለች። ጀርመን አሳክታለች። ኢትዮጵያ ከማንም አታንስም። እናሳካዋለን። የምናሳካው ግን፣ ጨክነን በመስራት ብቻ ነው።
ተባብረን ከሠራን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ማስረከብ እንደምንችል ምንም ጥርጥር የለውም። በዛው እምነት ነው የምንሠራው። በዛው መንፈስ ነው የምንተጋው። ውጤቱም ያማረ ነው።
ከሕዝባችን ጋር ሆነን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለልጆቻችን እናሸጋግራለን ብለዋል- ጠ/ሚ ዐቢይ።
የኢትዮጵያ መንገድ ይለያል፤ ያዋጣለል።
አንዳንድ ተላላ አገራት፣… የእርሻ መሬትን መቀነስ፣ መስኖን ማስቀረት፣ የኤሌክትሪክ ማመንጫዎችን ዐቅም ማዳከም፣ መብራት የማጥፋት ክብረ በዓል” በሚል ፈሊጥ ኢኮኖሚያቸውን ያዳክማሉ። ራሳቸውን ይቀጣሉ።
ኢትዮጵያ ግን፣ በአረንጓዴ አሻራ በቢሊዮን በቢሊዮን ችግኞችን እየተከለች በእርሻና በመስኖ ላይ ትተጋለች። ከልመና ለመገላገል ብቻ ሳይሆን ለመበልጸግ በበጋ እርሻ ስንዴ ታመርታለች።
የተራቆቱ አካባቢዎችን በአረንጓዴ አሻራ አለምልማ እያሳመረች፣ በኮሪደር ልማት መዲናዋን እንደ ስሟ እንድታብብ 24 ሰዓት ትሰራለች።
አዲስ አበባ በብርሃናት ፈክታ ለሌሎችም አርአያ ትሆናለች። ሁሉንም ከተሞች ከጨለማ አውጥታ ለማድመቅ ትሠራለች።
ያማረ ነገር ማን ይጠላል? በአዲስ አበባ በጥቂት ወራት የኮሪደር ልማት አማካኝነት የመጣውን ለውጥ መታዘብ ትችላላችሁ።
የቤተሰብ የአመሻሽ ሽርሽር ዘንድሮ እንዴት እየተለመደ እንደመጣ አይታችኋል?
አረንጓዴ አሻራ ከዚህ ሁሉ ጋር የተዋደደ ታሪክ ነው።
በቲክቶክ የሚታወቀው ምንቴ ቢሊየነር ደግሞ፣ አረንጓዴ አሻራን ከአስተሳሰብ ለውጥ ጋር ያዛምደዋል።
አስተሳሰባችንን እየተከልን ነው። ችግኝን ስንተክል፣ መልካም አስተሳሰብንም በውስጣችን እንዲተከል እፈልጋለሁ።
በአንድ ፍሬ ዛፍ ውስጥ ብዙ ጫካ እንደሚኖር ማመን አለብን። በአንድ ሰው ውስጥም እንደዛው ብዙ ሕዝብ አለ። ስለዚህ ይህንን አምነን በምንገኝበት ሁሉ አሻራችንን መጣል አለብን ይላል- ምንቴ።
ምድርን የሚያለማው የሰው ልጅ ነው።
በሰውም ላይ ጥሩ አንደበት መናገር አለብን።
አብረን ተባብረን እናልማ፤ ባላችሁበት ችግኝ ትከሉ! የሚል መልዕክት እንደሚያስተላልፍ ከገለፀ በኋላ እንዲህ ይላል።
እዚህ አገር ላይ ማንኛውም ሰው ሃብታም መሆን “አለበት” ብዬ ነው የማምነው።
ሰርተን፣ ተግተን ...ተባብረን እንደዚህ ከሰራን፣ ድህነት እኛ ጋር የሚቀመጥበት ምክንያት የለውም። አሽቀንጥረን እንጥላለን።
ስለዚህ ችግኝን ትከሉ፤ ጥሩ ሃሳቦችን እርስ በርስ እንተካከል! አገራችንን እንቀይር! እናልማ! ይላል ምንቴ።

 

Saturday, 17 August 2024 19:58

ድንቅ ሰዎች በየዐይነቱ

የመቶ ሜትር ሯጮችን አይታችኋል። ሞተር የተገጠመላቸው ነው የሚመስሉት።
ዋናተኛ ዳንሰኞችንስ አይታችኋል? ዳንሳቸው ውኃ ውስጥም፣ አየር ላይም ነው። ይሽከረከራሉ፤ ይተጣጠፋሉ፤ ይከረበታሉ።
ቀጥ ብለውም “ይቆማሉ”። ግን…
ጭንቅላታቸው ውኃ ውስጥ ነው፤ እግራቸው አየር ላይ። 8 ዋናተኞች በአንድ ዐይነት ቅርጽና ፍጥነት መደነስ አለባቸው። አስገራሚ ነው።
ተኳሾች ደግሞ አሉላችሁ።
የሀንኩክ ኢላማዎች አየር ላይ ናቸው - ግን አያመልጡም።
ሁለት ኢላማዎች ወደ አየር ይስፈነጠራሉ - አንድ ከታች አንድ ከላይ። የኢላማዎቹ መጠን መዳፍ ያህል ነው። ድንገት ይስፈነጠራሉ። በቃ፣ አየር ላይ ናቸው። ከሴኮንድ በኋላ 22 ሜትር ርቀው ይሄዳሉ። ከመሄዳቸው በፊት ኢላማዎቹን መምታት ነው ፉክክሩ - በግማሽ ሴኮንድ ውስጥ አነጣጥሮ ሁለት ሁለት ኢላማዎችን እያከታተሉ መምታት።
አየር ላይ የሚበርሩ ኢላማዎችን እዚያው በዚያው መምታት!
ለማመን የሚያስቸግር ቢመስልም፣ የኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ከ50 ኢላማዎች አንድ ወይም ሁለት ብቻ ቢስቱ ነው። ኢላማዎቻቸውን አየር ላይ እየመቱ ያፈነዳሉ።
አሜሪካዊው ተኳስ ቪንሰንት ሀንኩክ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በዚህ ውድድር የወርቅ ሜዳሊያ በመውሰድ አዲስ ታሪክ አስመዝግቧል። በአራት ኦሊምፒክ አራት ወርቅ?
ሌላ ተዓምርም ሠርቷል። ዘንድሮ ከሀንኩክ ጋር ተፎካክሮ ሁለተኛ የወጣው አሜሪካዊ ተኳሽ፣ ለሀንኩክ እንግዳ አይደለም። የሀንኩክ ተማሪ ነው። ከታዳጊነቱ ጀምሮ የሀንኩክ ማሠልጠኛ ተቋም ውስጥ ነው ሲማር የነበረው። ስልጠናው ጠቅሞታል ማለት ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ውድድር ለመሳተፍ ማጣሪያውን አልፏል። ከዚያም የብር ሜዳሊያ አግኝቷል - በአሠልጣኙ በሀንኩክ ተበልጦ።
ሌላኛዋ የሀንኩክ ሠልጣኝ አሜሪካዊትም እንዲሁ በዘንድሮው ኦሊምፒክ ሁለት ሜዳሊያዎችን አግኝታለች - የብር እና የነሐስ።
አሠልጣኝና ሠልጣኝ ተኳሾች በሜዳሊያ የተንበሸበሹት ምን ዐይነት ልዩ የብቃት ሰዎች ቢሆኑ ነው?
ሀንኩክ የራሱንም ልጆች እያሠለጠነ ነው። ዝንባሌው ካላቸው ምን ይታወቃል? እነሱንም በኦሊምፒክ እናያቸው ይሆናል። ሀንኩክ እንዲህ ይላል።
በ10 ዓመት ዕድሜዬ ነው ተኩስ የጀመርኩት… ትልቋ ልጄ የ13 ዓመት ትንሽዬዋ የ12 ዓመት ልጆች ናቸው ብላል ሀንኩክ። እነሱንም ተኩስ እያለማመዳቸው ነው ብሏል ለኤቢሲ ቴሌቪዥን።

 

በ16ኛው ክፍለ ዘመን ይኖር የነበረው ላ ፎንቴን የተባለው የፈረንሳይ ገጣሚና አፈ-ታሪክ ፀሀፊ ከፃፋቸው ተረቶች ውስጥ የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ቁራ፣ ከቁራ ቤተ-ዘመዶቹ ተለይቶ፣ ለአንድ ጌታ አድሮ ያገለግል ነበር፡፡ ከብዙ ዓመት በኋላ፣ ከጌታው ቤትም ወጣና ከአንዲት ጣውስ (Peacock) ጋር ወዳጅነት ጀመረ፡፡ ሆኖም ሁሌ በመንገድ ላይ ሳሉ ውበቷ የሷን ማማር የቁራውን መጥቆር በጣም እያጎላው ስለሚታይ፣ አብረው ሲሄዱ የተመለከተ ሁሉ “ይቺ ጣውስ እንዴት ውብ ናት?” “ቁራው እንዴት ጥቁር ነው?” እያለ አስተያየቱን ይሰጥ ጀመር፡፡ ይህን የተገነዘበው ቁራ እጅጉን የበታችነት ይሰማው ጀመር፡፡ በሄደበት ቦታ እያቀረቀረ በሀፍረቱም ምክንያት የገዛ መልኩ እያስጠላው መጣ፡፡ ስለዚህም አንድ ቀን ጧት ተነስቶ ለጣውሷ እንዲህ አላት፡-
“ከዛሬ ጀምሮ እኔ እንዳንቺ ማማር አለብኝ፤ ያንቺን ዓይነት በውብ ቀለማት የተጌጠ ላባና ጭራ ተክዬ መታየት አለብኝ፡፡”
ጣውሷም፤
“ቁራ ሆይ፤ ሁለታችን ተፈጥሯችን የተለያየ ነው፡፡ ያንተ መልክ በተፈጥሮው ጥቁር ነው፡፡ የእኔ ከተለያየ ቀለማት የተሰራ የዐይን ብሌን የመሰለ ጠቃጠቆ ኅብር ያለው ነው፡፡ የእኔ ክንፍ ለስላሳ፣ የጭንቅላቴም ጉትያ ልዩ የላባ ጉልላት ያለው ነው፡፡ ጭራዬም እንደምታይው መሬቱን እየጠረገ የሚሄድ ዘርፋፋ፣ ጥቅጥቅ ያለና ከግማሽ ሜትር በላይ ርዝመት ያለው ነው፡፡ እንዴት አድርገህ እኔን ለመምሰል ትችላለህ??” ስትል ጠየቀችው፡፡
ቁራውም፤
“በምንም ዓይነት አንቺ ከእኔ አትበልጪም” ሲል በግትርነት አረመረመ፡፡
ጣውሷም፤ “እኔኮ ከአንተ እበልጣለሁ አላልኩም፡፡ ግን ከአንተ እለያለሁ ነው የምለው”
ቁራው በእልህ እየበረረ፤ “እንዴት አንቺን ለመምሰል እንደማልችል አሳይሻለሁ” ብሎ የተለያየ ቀለም ያላቸው ላባዎች ወደሚያገኝበት ቦታ ሄደ፡፡ ከዚያ የራሱን ላባ አንስቶ በገላው ላይ ልዩ ልዩ ቀለም ያለው ላባና ረዥም ዘርፋፋ ጭራ አስተከለ፡፡ ከጣውሷ እኩልም የሆነ መሰለው፡፡ “ከእንግዲህ የተለየሁ ፍጡር መሆኔን ለማሳየት በየቦታው መዞር አለብኝ በሎ ከጣውሷ ተለይቶ ሄደ፡፡ ቀጥሎም ምን ዓይነት የተፈጥሮ ለውጥ እንዳመጣ ሊያሳየው ወደ ዱሮ ጌታው ተመልሶ ሄደ፡፡ መለወጡንም አስረዳው፡፡ ጌታውም፤ “በእርግጥ መለወጥህን ለማየት የገላህ ቆዳ ምን እንደሚመስል ማየት አለብኝ” ብሎ ተነስቶ ቁራውን ጨምድዶ ያዘው፡፡
ላባና ጭራውን ሁሉ ነጭቶ ነጭቶ ልሙጡ የውስጥ ቆዳው እስኪታይ ድረስ ላጭቶት ሲያበቃ “ቅንጣት ታህል እንኳ የተለወጥከው ነገር የለም - ሂድ ውጣ ከኔ ዘንድ አትቀመጥም!” ሲል አባረረው፡፡ ቁራም ተነስቶ “ወደ ጥንት ዘሮቼ ወደ ቁራዎቹ ዘንድ ሄጄ እቀላለቀላለሁ” ብሎ ወደ ቀየው ሄደ፡፡ እዚያ ሲደርስ ግን ያልጠበቀው ነገር ገጠመው፡፡ ዘመዶቼ በቁጣ “እንደዚህ ልሙጥ ገላ ያለውና አንድም ጥቁር ላባ በቆዳው ላይ የማይታይበት የቁራ ዝርያ አናውቅም፡፡ አንተ የእኛ ዘር አይደለህም፡፡ እንዲያውም እኛን መስለህ ልታጭበረብር ነው የመጣኸው” ብለው ተባብረው ደብድበው ገደሉት፡፡
* * *
ካለ ራስ ተፈጥሮ ሌላውን መምሰል እንጂ መሆን አይቻልም፡፡ መምሰል ጊዜያዊ ቀለም ነው፡፡ መምሰል ጊዜያዊ ላባ ነው፡፡ መምሰል የሚነጭ መልክ ነው፡፡ ዕውነተኛ ማንነት በዚህም ቢሉት በዚያ መታየቱ የማይቀር ነው፡፡ ጅግራን ከጅግራ፣ ቆቅን ከቆቅ በአንድነት የሚያውላቸው የተፈጥሮ ባህሪ አላቸውና ከዝርያቸው ተነቅለው ጅግራም ቆቅ ልሁን ብትል አይሆንም፡፡ ቆቅም ጅግራ ልሁን ብትል ከንቱ ጥረት ነው፡፡
በሀገራችን ከጥንት ከጠዋት ጀምሮ ከቢሮ ወንበር እስከ ፖለቲካዊው የአደባባይ መድረክ መልካቸውን በመቀያየር፣ ሌላውን መስለውና አክለው ለመታየት የሞከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ቡድኖች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች አያሌ ናቸው፡፡ ችግሩ ግን ወንበር ቢቀያይሩ፣ የፖለቲካ ዣንጥላ ቢዋዋሱ፣ ከአገር አገር ቢለውጡ፣ ከአህጉር አህጉር ቢዞሩ የሚመስሉት ሳይሆን፣ የሆኑት ብቅ ማለቱ አሌ አይባልም፡፡ በሎሚ እንደፃፉት ፊደል ቀስ እያለ እየደመቀ ዕውነተኛው ማንነት ይታያል፡፡
“ከመሰረትህ ጋር አትጣላ፣ ለሁልጊዜ ይሆንሃል፡፡ ከካብ ጋ አትጠጋ፣ እላይህ ላይ ይፈርሳል” ይሏልና ለመመሳሰል ብሎ የመሰረትን መልቀቅ ደግ አይደለም፡፡
ከኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ጊዜ ጀምሮ በፖለቲካ ትግል ተመክሮ ውስጥ የምናየው አንድ ቋሚ ክስተት የድርጅቶች መሰነጣጠቅ ነው፡፡ በኢትዮጵያም፣ ከሀገር ውጪም በተፈጠረ በየትኛውም ድርጅት ውስጥ እስከ ዛሬ ይኸው የመሰነጣጠቅ ሂደት በተመሳሳይ በተደጋጋሚ መከሰቱ፣ ግለሰብም ቡድንም ጥሎ መውጣቱ ወደ ቋሚ ባህሪነት ማለፉን ያሳየናል፡፡ አንድም ደግሞ ወደ ጋራ ዕሳቤና መቻቻል ለመቃረብ የብዙ አንጃዎች መፈጠር እንቅፋት ሲሆን መክረሙን ያፀኸይልናል፡፡
ይሄ ክስተት የአገር ውስጥ መሆን ብቻ ሳይበቃው ከአገር ውጪም እየተዛመተ ፖለቲከኛው “በለጠች እንዲሉኝ አክሱም ጽዮን ቅበሩኝ” አለች እንደተባለው እኔ ብቻ ልደመጥ በሚል ግብዝነት እርስ በርሱ በተሻኮተ፣ ውስጥ ለውስጥ በተናቆረ ቁጥር መከፋፈል እንደ ዋና መርህ እየተያዘ ለባላንጣ ሲሳይ መሆን የእለት የሰርክ የታሪክ ምፀት ይሆናል፡፡ እየሆነም ነው፡፡ ከዚያ ለባላንጣ ማደር ይከተላል፡፡ ጠላት ተብሎ የነበረው መንግስትም “በቅሎ ወደ ፈለገችበት ትበል ብቻ ልጓም አጥብቅ” እያለ እንደየጉዳዩና እንደየጎራው እየቀየደ፣ በኪነ- ጥበቡ “እኔን ያለ የዘለዓለም ህይወት አለው” እያለ ያስጠጋል፣ ወይም ያቅፋል፡፡ ቀስ በቀስ የፖለቲካ ድርጅትነት ባህሪን ይተውና የግል የጥገኝነት ህይወት ይጀምራሉ፡፡ ዋና ባለጉዳይ የመሰሉም ያከሉም ይመስላቸዋል፡፡ “በቅሎ ፈረሶች መሀል ብትሆን ፈረስ የሆነች ይመስላታል” ነው ነገሩ፡፡
ይህ ባህሪ በተለይ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትራጆ-ኮሜዲ ተውኔት ውስጥ የተለመደ የመሆኑን ያህል የአሳዛኝ ቀልዱ መሪ - ተዋንያን ሁሌም ምሁራን መሆናቸው ደግሞ ዘግናኝ ሀቅ ያደርገዋል፡፡ ብለብስም ያምርብኛል፣ ራቁቴንም ያምርብኛል ብለው የተፈጠሙ ሊቀ-ሊቃውንት ክራራቸውን አዲስ ዘፈን የቃኙት በመሰላቸው ቁጥር የሚታዘባቸው ህዝብ “ብትናገር ያምናውን፣ ብትፈትል አንድ ልቃቂት” እያለ እንደሚተርት ልብ አይሉም፡፡ ይልቁንም “ረጅም የማይዘለው አጭር የማይሾልከው አጥር እናጥራለን” እያሉ ሊኮሩና ሊገበዙ ከአንገታቸው የጠለቀውና ሀብል ወይ ሜዳልያ የመሰላቸው ሸምቀቆ ክር፣ ጠብቆ መተንፈሻ ያሳጣቸዋል፡፡ ያነጎቱትን ቲዎሪ እንኳ አላባውን ሳይበሉ ልሳናቸው ይዘጋል፡፡
በሀገራችን ይህ አሳዛኝ የታሪክ ስላቅ ያዳበርነው ከዓለም ታሪክ ክፉ ክፉውን ወስደን ሳይሆን አይቀርም፡፡ ከሮማ ነገስታት ንጉሳዊ ሴራን ተውሰን፣ከፈረንሳይ የደም ዘመን (Reign of Terror) የአንገት መቅያውን መጥረቢያ (Guillotine) ተረክበን፣ ከሩሲያ አብዮት አብዮታዊ አምባገነንነትን፣ ምሁራዊ መከዳዳትንና አንጃ ፈጠራን ወስደን ከአገር በቀሉ የአበሻ ምቀኝነትና ክፋት ጋር ቀምመን የትግል -ስልት፣ ስር ነቀል ስትራቴጂ፣ ሂሳዊ ድጋፍ፣ ቅን ተቃዋሚነት፣ ብክነት (Decadence)፣ ሪፎርሚዝም፣ ሊበራሊዝም ወዘተ ብለን፣ የማታ ማታ በየቲዎሪው ማሳ ስንማስን ውለን ወይ በሙስና ወይ በማናለብኝነት ወይ በግል ጥቅም ወይ በወገን- ማርባት፣ ወይ በሹመት -ዘውድ መጫን፣ ወይ በእልፍኝ አስከልካይነት አሊያም ውጪ በስደት ላይ-ታች በማለት…. እንገኛለን፡፡
ዋናው ጉዳይ ግን ለህዝቡስ ለአገሩስ ምን በጀነው? የተማሩ የተመራመሩ፣ በረዥሙ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ የታገሉና የሚታገሉ የሚመስሉ፣ የሰሩና የሚሰሩም የሚመስሉ ሁሉ ከቡድናዊ ድርጅታዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ባሻገርና ከትልቁ የአገር ዕድገት ስእል አንፃር ምን ጠብ አረጉለት? ምን ግብዓት፣ ምን ፋይዳ፣ ምን ንጥረ-ነገር አፈሩለት? ብሎ መጠየቅ ያባት ነው፡፡
“ተሸክመዋል እንዳይባሉ በብታቸው፣ ፈጭተዋል እንዳይባሉ ግማሽ ቁና” የሚለውን ተረትም ልብ እንዲሉ መምከር የሚያሻው አሁን ነው፡፡

መንግስት ነጻ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለጣፊ ሃይሎች ለመተካት “እያደረገ ነው” ያለውን መንግስታዊ እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ጠይቋል።
ፓርቲው ባለፈው ረቡዕ ነሃሴ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፣ በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ የተነሳ ለሚከተለው ጥፋት መንግስት ሃላፊነቱን ይወስዳል ብሏል።
በአንድ አገር ውስጥ የሕግ የበላይነት ከሌለ፣ መንግስት ሰላምና መረጋጋትን ለማምጣት የሚሞክረው በሃይል እርምጃ መሆኑን የጠቀሰው ፓርቲው፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የዜጎች የሕይወት ዋስትና ዕጦት፣ በነፃነት መንቀሳቀስ አለመቻል፣ የዜጎች መታገት፣ የዜጎች በየቦታው መፈናቀል የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው” ብሏል።
ኢሕአፓ በሰላማዊ መንገድ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ያለ ፓርቲ መሆኑን በማስታወስ፣ ገዢው ፓርቲ ግን ሰላማዊ መታገያ መንገዶችን ከዕለት ወደ ዕለት እያጠበበ እንደሚገኝ በመግለጫው አስረድቷል፡፡
መንግስት ኢሕአፓ “ጦርነት ይቁም፣ ሰላም ይስፈን” ብሎ የጠራውን ሰላማዊ ሰልፍ ከማስቆም አልፎ በርካታ አባላቶቹንና አመራሮቹን ለእስር መዳረጉን ፓርቲው እንደማሳያ ጠቅሷል።
መንግስት አሁንም ተደጋጋሚ ጫና እና ማስፈራራት እያደረሰብኝ ነው ያለው ኢህአፓ፤ ከሰላማዊ ትግል እንዲወጣም ግፊት እየተደረገበት መሆኑን ገልጿል፡፡
“በስልጣን ላይ የሚገኙ ገዢዎች የሕዝብን ፍላጎት፣ እንዲሁም የአገርን ደህንነት የሚያስጠብቅ ፖሊሲ ከሌላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች አማራጫቸውን አቅርበው ሊሞግቷቸው ቢገባም፣ ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚፈለገው ተቃዋሚ ነኝ እያለ ለገዥዎች ውዳሴን የሚያቀርብና ከገዥዎች በሚወረወርለት ፍርፋሪ ረክቶ የሚኖር ነው” ብሏል፣ ፓርቲው።
ሰላማዊ የፖለቲካ መድረኮችን መዝጋት ለየትኛውም ወገን ጥቅም እንደሌለው በመግለጫው ያመለከተው ኢሕአፓ፣ “በተለያዩ ጊዜያት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባዎች የድርጅታችንን ስም በማንሳት ‘አንድ ቦታ የተቸነከረ...’ የሚል ጸያፍ ስድብ ሰድበውናል” ብሏል።
ኢሕአፓ በቅርቡ ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ስለአገራዊ ምክክሩ የሚገልጽ መግለጫ ማውጣቱን ተከትሎ፣ ከመንግስት የሚደረግበት ጫና እየጨመረ መምጣቱን አመልክቶ፣ “መንግስት ነጻ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለጣፊ ሃይሎች ለመተካት የሚያደርገው እንቅስቃሴ በአስቸኳይ ያቁም” ሲል አሳስቧል። አክሎም፤ የፖለቲካና የሲቪክ ድርጅቶች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ህብረተሰብ እየደረሰብኝ ያለውን ጫና “ይመልከቱልኝ” ሲል አሳውቋል፡፡
በፖለቲካ ምህዳሩ መጥበብ የተነሳ ለሚከተለው ጥፋት መንግስት ሃላፊነቱን እንደሚወስድ ነው ያሳሰበው። ከሳምንታት በፊት፣ የኢሕአፓ ዋና ጸሐፊ ደስታ ጥላሁን ከፓርቲው የለቀቁ ሲሆን፣ ለመልቀቃቸው የሰጡት ምክንያትም “ድርጅቱን ለማዘመንና ዘመኑን የሚመጥን ቁመና እንዲኖረው ለማድረግ የተለያዩ ሃሳቦችን ብሰነዝርም፣ አባላቱ ከቁምነገር ውስደው ባለመተግበራቸው ነው” የሚል እንደነበር ይታወሳል።

 

የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ፣ “በጥቂት የመንግስት አመራሮች ምክንያት ጉባዔተኞች በፓርቲው ጉባኤ ላይ እንዳይሳተፉ እየተደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል። አቶ አማኑኤል ይህን የተናገሩት ትናንት ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ቃል አቀባዩ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ዘንድ፣ ጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔው እንዲራዘም፣ ያልገቡ አመራሮች እንዲሁም ከተለያዩ አካባቢዎች ያልተወከሉ አባላት ውይይት ተደርጎ እንዲወከሉ ጥያቄ መቅረቡን ጠቁመው፣ በጥያቄውም ላይ ውይይት እንደተደረገ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ጉባዔው አሁኑኑ ካልተካሄደ ህወሓት ወደ ውስብስብ ችግር እንደሚገባና ጉባዔውን ካካሄደ በኋላ ያልተካተቱ አመራሮችና አባላትን ማካተት እንደሚቻል ሃሳብ ያቀረቡ አባላት መኖራቸውን አብራርተው፣ ጉባዔው መካሄዱ መቀጠል እንዳለበት በድምጽ ብልጫ መወሰኑን ተናግረዋል። በተጨማሪም፣ ሶስት ሰዎች ‘ጉባዔው መራዘም አለበት’ በሚል ድምጽ መስጠታቸውንም አብራርተዋል። ከትግራይ ደቡብ ዞን፣ ከደቡብ ምስራቅ ዞን ሁለት ወረዳዎች እና ከሰሜን ምዕራብ ጸለምቲ ሁለት ወረዳዎች ተወካዮቻቸውን ወደ ጉባዔው አልላኩም ብለዋል አቶ አማኑኤል።
የጉባኤው አባላት ተወካዮቻቸውን ያልላኩት “በአመራሩ ምክንያት ነው።” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ “ከክልል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ፣ ከፍተኛ አመራሮች ጉባዔተኞች እንዳይመረጡ፣ የተመረጡትም ወደ መቐለ መጥተው በጉባዔው ላይ እንዳይሳተፉ አድርገዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።
ቃል አቀባዩ፤ ከጉባዔው ራሳቸውን ያገለሉ አባላት፣ ወደ ጉባዔው ገብተው ሃሳባቸውንና ልዩነታቸውን እንዲያቀርቡ ጥሪ አድርገዋል።
ከቀናት በፊት የህወሓት ማዕከላዊ የቁጥጥር ኮሚሽንና አስራ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከጠቅላላ ድርጅታዊ ጉባዔው ማግለላቸውን ማስታወቃቸው ይታወሳል።

በወላይታ ዞን፣ ሆቢቻ ወረዳ፣ የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ፣ የወረዳ አስተዳዳሪው፣ በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸው ተገልጿል። የወረዳው የመንግስት ሰራተኞች ላለፉት 3 ወራት ደሞዝ አልተከፈላቸውም ተብሏል።
የወረዳው የመንግስት ሰራተኞች በተደጋጋሚ የደመወዝ ክፍያ ጥያቄ ሲጠይቁ ቢቆዩም፤ ደመወዝ ሲመጣ ለመንግስት ሰራተኛ በትክክል ባለመድረሱና በሌሎች አስተዳደራዊ ችግሮች ሳቢያ ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ መቅረቱ ተነግሯል።
“ለደመወዝ ክፍያ የሚመጣው ገንዘብ የማዳበሪያ ዕዳ ክፍያን ጨምሮ ለሌሎች ወጪዎች በወረዳው በኩል ፈሰስ ይደረጋል። የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። በደመወዝ አለመከፈል ምክንያት አብዛኛው ሴክተር መስሪያ ቤት ስራ አቁሟል። የጸጥታ አካላት ደመወዝ ባይከፈላቸውም፣ ስራቸውን እየሰሩ ነው። የማዘጋጃ ቤትና የፋይናንስ ቢሮዎች አንዳንድ ሠራተኞች እየሰሩ ነው።” ብለዋል፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ። በዚህ ሳቢያም የወረዳው ሕዝብ ተገቢውን የመንግስት አገልግሎት እያገኝ አለመሆኑን አክለው ተናግረዋል።
በተደጋጋሚ ለወረዳው አስተዳደር የደመወዝ ጥያቄ ሲቀርብ፣ “ምንም ማድረግ አንችልም፣ የዞኑ ችግር ነው። በአጠቃላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ችግር ነው።” የሚል ምላሽ ሲሰጥ መቆየቱን ምንጮች ጠቁመዋል። ከሳምንታት በፊት ቁጣቸው የገነፈለ የወረዳው የመንግስት ሰራተኞች፣ ወደ አስተዳደሪው ቢሮ በመሄድ ተቃውሞ ያደረጉ ሲሆን፣ በዚህም የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ማዕረጉ ለተወሰኑ ሰዓታት ከቢሯቸው መውጣት አለመቻላቸው ተነግሯል።
ተቃውሞው ከወረዳው አቅም በላይ ሲሆን፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ወደ ሆቢቻ ወረዳ ተጠርቶ የተቃውሞ እንቅስቃሴውን ሊያረግብ እንደቻለ እኒሁ ነዋሪው አስረድተዋል። ይህን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ አቶ ማዕረጉ አስራት በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን መልቀቃቸውን ተናግረዋል።
አቶ ማዕረጉ በመልቀቂያ ደብዳቤያቸው፤ “ሌላ የገቢ አማራጭ የሌላቸው የመንግስት ሰራተኞች የሰሩበትን ደመወዝ ለወራት አጥተው ሲቸገሩ፣ ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ላይ ጥለው በሚኖሩበት ወቅት፤ እንደ አመራር የመንግስት ሰራተኞች ደመወዝ በጊዜ እንዲከፈል ለሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በተደጋጋሚ ያቀረብነው አቤቱታ ምላሽ ባለማግኘቱ መፍትሔ በሌለበት አልቀጥልም” ማለታቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
አቶ ማዕረጉ የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ለወላይታ ዞን አስተዳደርና ለዞኑ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ማስገባታቸውን የጠቆሙት ምንጮች በምትካቸው። የሆቢቻ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና ምክትል አስተዳዳሪ አቶ እምሩ ማሞ በጊዜያዊነት መሾማቸውን ተናግረዋል።
የሆቢቻ ወረዳ የመንግስት ሰራተኞች፣ የግንቦት ወር ግማሽ ደመወዝ የተሰጣቸው ሲሆን፣ የሰኔና የሐምሌ ወር ግን ከእነ አካቴው አልተከፈላቸውም ተብሏል።
በጉዳዩ ዙሪያ ከወላይታ ዞን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
በማዕከላዊ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የመንግስት ሰራተኞች፣ ደመወዝ በወቅቱ አልተከፈለንም በሚል በተደጋጋሚ የስራ ማቆም አድማዎችና የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ መቆየታቸው ይታወቃል።