
Administrator
ኢህአፓ የገዢው ፓርቲ የ5 ዓመት ጉዞ ኪሳራ ነው አለ
ባለፉት አምስት ዓመታት ገዢው ፓርቲ ተገምግሞ ከስሯል ሲሉ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ተናገሩ።
መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የብልጽግና ፓርቲ የአምስት ዓመታት ጉዞ ሲገመገም፣ የህግ የበላይነትን በማስከበርና ኢኮኖሚውን በማሳደግ በኩል ድክመት ማሳየቱን ገልፀዋል። “ከኮሪደር ልማትና ከሚያብለጨልጩ ነገሮች ውጪ ለሕዝባችን ጠብ የሚል አዲስ የኢኮኖሚ ለውጥ አልታየም” ሲሉም ተችተዋል።
በከፍተኛ የዋጋ ንረት ሳቢያ፣ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን ማግኘት አለመቻላቸውን የሚገልፁት የኢህአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር፤ በጥቅሉ አሁን ላይ ያለው ወጣት ተስፋ መቁረጡን ይናገራሉ።
የጸጥታና ሰላም ጉዳይን በተመለከተ የሕግ የበላይነት አለመከበሩን የጠቆሙት መጋቢ ብሉይ፤ “ሕገ መንግስታዊ መብቶች ጭምር እየተናዱ ነው።” ብለዋል። በመንግስትነት የሚያስተዳድረው ብልጽግና ፓርቲ፤ ሕገ መንግስቱን አክብሮ ማስከበር ሲገባው፣ እሱም አላከበረውም፤ ማስከበርም አልቻለም” ሲሉም ነቅፈዋል።” በተጨማሪም፣ ፓርቲው አገራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚጠቀመው ብቸኛ አማራጭ ጦርነት ብቻ ነው። ሲሉም ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
“ብልጽግና ፓርቲ በጉልበት እንጂ በፖለቲካዊ ውይይትና ንግግሮች መፍትሔ ለማምጣት ሲንቀሳቀስ አልታየም። ከብዙ ዕልቂት በኋላ፣ የተወሰነ ነገር ይጀምርና በሁሉም ቦታ ላይ ተግባራዊ ስለማይሆን በአንድ ቦታ ግጭት ጋብ ሲል፣ በሌላ ቦታ እንደገና ያገረሻል።” ይላሉ፣ መጋቢ ብሉይ አብርሃም።
ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ገዢው ፓርቲ ተገምግሞ ከስሯል ያሉት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበር፤ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ቅዳሜ፣ በዓድዋ መታሰቢያ ሙዚየም በተካሄደው የብልጽግና ፓርቲ አምስተኛ ዓመት የምስረታ በዓል የማጠቃለያ ፕሮግራም ላይ ለተፋላሚዎቻቸው “ሺህ ዓመት ቢታገሉንም አያሸንፉንም” ሲሉ መናገራቸው ጦርነት እንደሚፈልጉና በተቃራኒ ጎራ የሚገኙ ለሺህ ዓመት ትግል እንዲያካሂዱ ምክረ ሃሳብ እንደሰጡ የሚያስቆጥርባቸው ነው ብለዋል።
“ከአንድ አገር የሚመራ ፓርቲ ይህ ንግግር አይጠበቅም። ጉልበትና አቅሙ ቢኖረውም እንኳ፣ ችግሮችን በሰላም እንዲፈቱ ነው ማድረግ ያለበት፤ ምክንያቱም የአገር ውስጥ ችግሮች ተባብሰው ውስጣዊ አንድነት ከሌለ፣ ለጠላት በሮች ክፍት ይሆናሉ። አገርም ለከፍተኛ አደጋ ትጋለጣለች።” ብለዋል፣ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበሩ። “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፖለቲካዊ ጥያቄዎች በውይይትና ድርድር መፈታት እንደሚችሉ ነው መናገር የነበረባቸው” ብለዋል።
በሚቀጥለው ዓመት ብሔራዊ ምርጫ የሚደረግ ቢሆንም፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች ግጭቶች በመከሰታቸው ሳቢያ የፓርቲያቸው እንቅስቃሴ መገደቡን የተናገሩት መጋቢ ብሉይ አብርሃም፤ በተለይ፣ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ማደራጀትና እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳልተቻለ ገልፀዋል።
በአዲስ አበባ ከተማም ፓርቲያቸው በመንግስት በሚደርስበት ጫና ሳቢያ ጠቅላላ ጉባዔውን ለማድረግ አለመቻሉን የጠቆሙት መጋቢ ብሉይ አብርሃም፤ የፖለቲካው ምህዳር መጥበቡን የሚያሳዩ ከበቂ በላይ አብነቶች መጥቀስ ይቻላል ብለዋል።
ገዢው ፓርቲ ያለፉትን አምስት ዓመታት በጥልቀት ገምግሞ ከስሕተቶቹ በመማር ከቻለ አሁን የሚታየውን ችግር እንዲቀርፍ ያሳሰቡት ፖለቲከኛው፤ ሁሉንም ችግር በጉልበት ለመፍታት ከማሰብ ይልቅ በፖለቲካዊ መፍትሔዎች ላይ ማተኮር እንደሚያስፈልግ መክረዋል። “ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ምቹ ምህዳር መፍጠርና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማስፋት ብልጽግና ፓርቲ የሚሰጠን ልዩ ስጦታ አይደለም፤ መብታችን ነው” የሚሉት ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ መንበሩ፣ “ኢትዮጵያ አሁን እየሄደችበት ባለው መንገድ ከቀጠለች፣ የመፍረስ አደጋ ይጋረጥባታል” ብለዋል።
“በአሁኑ ወቅት በስቃይና በመከራ ላይ የሚገኘው ሕዝብ ብሶቱን ሲያቀርብ አለመናቅና ዝቅ ብሎ ማዳመጥ እንጂ በተለያየ መንገድ ለመሸወድ መሞከር ጥሩ ውጤት አያመጣም። “ያሉት የኢህአፓ አመራሩ፤” ችግሩ በፍጥነት መፍትሄ ካልተበጀለት እየሰፋ ሄዶ ብልጽግና ፓርቲንም ጭምር ሰለባ የሚያደርግ ቀውስ ሊፈጠር ይችላል”ሲሉ አሳስበዋል።
የመምህራን ማሕበሩ በማህበራዊ ሚዲያ የሥራ ማቆም አድማ መጠራቱን አላወቅም አለ
“በሥራ ማቆም አድማው የሚጎዳው አገርና ትውልድ ነው”
በተለያዩ የማህበራዊ ትስስር ገጾች በመላ አገሪቱ የሚገኙ መምህራን ከታሕሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ የስራ ማቆም አድማ እንዲያደርጉ የተሰራጨውን ጥሪ እንደማያውቅ የኢትዮጵያ መምሕራን ማሕበር አስታወቀ። “ወቅቱን ያገናዘበ የደመወዝ ጭማሪ ይከፈለን” በሚል የሥራ ማቆም አድማው በማህበራዊ ሚዲያ መጠራቱን ለማወቅ ተችሏል።
የኢትዮጵያ መምህራን ማሕበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሽመልስ አበበ ከአዲስ አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፤ ከሰሞኑ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው የሥራ ማቆም አድማ እንዲደረግ የተለያዩ ጥሪዎች እንደሚቀርቡ ጠቁመው፣ አሁን የተጠራውን የስራ ማቆም አድማ ግን ማህበራቸው እንደማያውቀው ገልፀዋል።
የደመወዝ አለመከፈል፣ የደሞዝ መቆረጥ፣ የመምህራን እስርና የመሳሰሉት ችግሮችን ዕልባት ለመስጠት ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን የገለጹት የማህበሩ መሪ፤ ባለፈው ጥቅምት ወር በአዳማ ከተማ የማህበሩ ምክር ቤት ባካሄደው ስብሰባ ላይ የመንግሥት አካላት ተገኝተው፣ በመምህራን የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እንዲያውቁ መደረጉን ተናግረዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ፣በዚሁ ስብሰባ ላይ በጉልህ የተነሱ ሃሳቦችን በውሳኔ ሃሳብና በአቋም መግለጫ መልክ በማጠናቀር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትን ጨምሮ ወደ 11 ገደማ ለሚሆኑ የፌደራል መስሪያ ቤቶች እንዲሁም መላኩንም ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም ፤የደረጃ ዕድገትና የትምሕርት ማሻሻያ፣ ውዝፍ ክፍያዎችን፣ እንዲሁም የሁለትና ሦስት ወር ደመወዝ ያልከፈሉ አካባቢዎች የትኞቹ እንደሆኑ ለማጣራት የመረጃ ማሰባሰብ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል። በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የደመወዝ አከፋፈል ላይ ችግሮች እንደሚስተዋሉ የጠቆሙት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤በተለያዩ ምክንያቶች የመምህራን ደመወዝ እንደሚቆረጥም ገልፀዋል።
“ለመምህራኑ ደመወዝ መቆረጥ እንደ ምክንያት የሚቀርበው ደግሞ ‘ለልማት’ የሚል ነው” ያሉት አቶ ሽመልስ፤ በዚያ ላይ መምህራን ደመወዛቸው እንዲቆረጥ ፈቃደኛ መሆናቸው አይጠየቅም” ብለዋል። “የደመወዛቸውን መቆረጥ ተከትሎ የመማር ማስተማር ሂደቱ ይስተጓጎላል። ምክንያቱም መምህራኑ መብታቸውን ለማስከበር የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ያደርጋሉ” ሲሉ አስረድተዋል። እነዚህን እንቅስቃሴዎች በማረጋጋት፣ መምህራን ስራቸውን እንዲሰሩ ከማስቻል ባሻገር፣ ማሕበሩ የመንግስት አካላት፣ ያለመምህራን ፈቃደኝነት ደመወዝ ከመቁረጥ እንዲታቀቡ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለአብነት ያህል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን፣ ሳርማሎ ወረዳ ከመምህራን ደመወዝ 25 በመቶ መቆረጡን ተከትሎ የወረዳው ባለስልጣናት ጥያቄ ያነሱ 66 መምህራንን በጸጥታ ሃይሎች አማካይነት ሕዳር 11 እና 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ማድረጋቸውን አቶ ሽመልስ ያወሳሉ። ማህበሩ የእነዚህ መምህራን ጉዳይ መረጃው እንደደረሰው፣ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በመነጋገር፣ እንዲሁም የማሕበሩ ተወካዮችና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ቦታው ድረስ በመገኘት የታሰሩት መምህራን ከእስር እንዲፈቱ ለማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል፣ የዩኒቨርስቲ መምህራን “የፌደራል ተቋም ሰራተኞች ናችሁ” ተብለው የቤት መስሪያ ቦታ በሚሰጥበት የመኖሪያ ቤት ፓኬጅ ተጠቃሚ አለመሆናቸውን ያነሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ ማሕበራቸው አገልግሎቱ ለዩኒቨርስቲ መምህራኑ መሰጠት እንዳለበት በማሳሰብ፣ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ደብዳቤ እንደጻፈ ገልጸዋል። ከትርፍ ሰዓት ሥራ ጋር በተገናኘም ጥያቄዎች እንደሚነሱ አቶ ሽመልስ ጠቅሰዋል፡፡
“የዩኒቨርስቲ መምህራን ‘ደብል ታክሴሽን (Double Taxation) እየተተገበረብን ነው’ ይላሉ። በመጀመሪያ መደበኛ ደመወዛቸው ታክስ ይደረጋል። የትርፍ ሰዓት ስራ ሲሰሩ ደግሞ፣ በዚያው ስራ ያገኙት ክፍያ ታስቦ በተጨማሪነት ታክስ ይደረግባቸዋል። በዚህም ምክንያት ደመወዛቸው ተቆራርጦ ለመምህራኑ የሚደርሳቸው ገቢ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። አብዛኛው ለታክስ የሚውል ነው።” በማለት ያስረዳሉ፤ አቶ ሽመልስ። ማሕበራቸው ይህ የታክስ አሰራር ትክክል አለመሆኑን ተገንዝቦ አቋም እንደወሰደበትም ጠቁመዋል።
“ከመምህራን እኩል እየወጣን እየወረድን ችግሮችን ለመፍታት በመንቀሳቀስ ላይ ነን” ያሉት የማሕበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት፤ “በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ እየተላለፈ ባለው የስራ ማቆም አድማ ጥሪ የሚጎዳው አገርና ትውልድ ነው።” ብለዋል። “መምህራን ሥራ አቁመው ወደዚህ ያልተገባ ተግባር ይገባሉ ብዬ አላስብም” ሲሉም ግምታቸውን ገልፀዋል።
ከሰሞኑ በማሕበራዊ ትስስር ገጾች ላይ የተጠራውን የመምህራን የሥራ ማቆም አድማ ማሕበራቸው እንደማያውቀውም አቶ ሽመልስ አክለው ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
በትግራይ የግሪሳ ወፍ መንጋ በብዛት መከሰቱ ተገለጸ
ብዛታቸው ከ4-5 ሚሊዮን ይደርሳሉ ተብሏል
በትግራይ ክልል የግሪሳ ወፍ መንጋ በብዛት መከሰቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ የገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ብዛታቸው ከ4-5 ሚሊዮን እንደሚደርሱ አመልክቷል፡፡ የቢሮው የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሚኪኤለ ምሩጽ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ግሪሳ ወፍ በአጎራባች ክልሎች እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፣ የግብርና ሚኒስቴር የመከላከል ስራዎችን እንደሚሰራ ስለሚገመት በትግራይ ከፍተኛ ችግር ይፈጥራል የሚል ግምት አልነበረም ብለዋል። ይሁንና ባለፈው ሳምንት የግሪሳ ወፍ መንጋ በድንገት ወደ ትግራይ ክልል መግባቱን ሃላፊው ገልፀዋል።
“የግሪሳ ወፍ መንጋው መጀመሪያ የገባው በራያ ጨርጨር ወረዳ በኩል ነው” ያሉት አቶ ሚኪኤለ፤ በወረዳው ባጌ ደልቦ በሚባል አካባቢ በሚገኙ የሳቫና እና የአል አሙዲ የግል እርሻዎች ላይ የመጀመሪያ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡ እንደ ክልል የተወሰኑ የመከላከል ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የገለጹት ሃላፊው፣ አርሶአደሩን የማንቃት ስራ መሰራቱንና በየወረዳው የመከላከል ግብረ ሃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።
“የግሪሳ ወፍ መንጋ ወደ ትግራይ ክልል ገና ሲገባ፣ የቢሮው ባለሞያዎች ወደ ስፍራው ተልከው የዳሰሳና ሕዝቡን የማንቀሳቀስ ስራ ሲሰራ ቆይቷል።
የግሪሳ ወፍ መንጋ ብዛቱ መጀመሪያ ላይ አንድ ሚሊዮን እንደሚደረስ ተገምቶ ነበር። አሁን ላይ ግን የግሪሳ ወፍ መንጋው ብዛት ከአራት እስከ አምስት ሚሊዮን ይደርሳል” ብለዋል፣ ሃላፊው፡፡
የግሪሳ ወፍ መንጋው የመራቢያ አካባቢ አፋር ክልል፣ አዋሽ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሚኪኤለ፤ ነገር ግን የወፍ መንጋው ወደ ትግራይ የገባው ከአማራ ክልል ኮምቦልቻና ሸዋሮቢት አካባቢዎች ተነስቶ ነው ይላሉ፡፡ ግሪሳውን ለማባረር በአምቡላንስ የሳይረን ድምጾች ጭምር ታግዞ ከፍተኛ ድምጽ በማሰማት የመከላከል ስራ ሲሰራ መቆየቱን የሚገልጹት የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊው፤ ከግብርና ሚኒስቴር በሁለት ቡድኖች የተዋቀሩ ባለሞያዎች ወደ ትግራይ ክልል መምጣታቸውንና ከክልሉ ባለሞያዎች ጋር በመናበብ አብረው እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ከግብርና ሚኒስቴር የተላኩ አራት መኪናዎች ከእነ ኬሚካል መርጫ መሳሪያዎቻቸው፣ ኬሚካሎችና ባለሞያዎቻቸው ጭምር ወደ ትግራይ ክልል መምጣታቸውንም አስታውቀዋል።
የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ከፍተኛ ዝግጅት ተደርጎ ለአይሮፕላን ማረፊያ የሚሆን ቦታ በመቐለ አካባቢ ለማዘጋጀት ወደ ስራ መገባቱን የገለፁት አቶ ሚኪኤለ፣ በህዳር 21፣ 23 እና 25 ሦስት ጊዜ የኬሚካል ርጭት መካሄዱን ተናግረዋል። “የተካሄደው ርጭት ውጤታማ ነው። ነገር ግን የግሪሳ ወፎቹ ብዛት ከፍተኛ ስለሆነ፣ በቶሎ ሊረግብ አልቻለም። አሁንም ሕብረተሰቡ በመከላከል ስራ ላይ ይገኛል።“ ብለዋል።
ሃላፊው አክለውም፤ የግሪሳ ወፍ መንጋው ከራያ ጨርጨር ተሻግረው ወደ አላማጣ አካባቢ እየገቡ መሆኑንና በግብርና ቢሮ በኩል ወደ አንድ ሺሕ ሄክታር መሬት አሰሳ ተደርጎ፣ 500 ሄክታር መሬት በግሪሳ ወፍ መንጋ ጉዳት እንደደረሰበት መረጋገጡን ጠቁመዋል። ሆኖም ግን በተለያዩ ጉዳዩ በሚመለከታቸው የተለያዩ ተቋማት ጥልቅ ምርመራ ከተደረገበት በኋላ፣ ስለደረሰው ጉዳት ሙሉ መረጃ እንደሚገኝና ይፋ እንደ ሚደረግ አቶ ሚኪኤላ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል።
ዋልታ እና ፋና ተዋህደው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ተመሰረተ
“የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት የመደመር እሳቤ ውጤት ነው”
ሁለቱ በመንግሥት የሚተዳደሩት ዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ ሰሞኑን በይፋ ተዋህደው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ ተመሥርቷል፡፡ የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ-ግብር ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ህዳር 25 ቀን 2017 ዓ.ም በግራንድ ኤሊያና ሆቴል ተካሂዷል፡፡
ለተመሳሳይ ዓላማ የተቋቋሙት የሚዲያ ተቋማት ውህደት፣ አንድ ግዙፍና ተደራሽ ሚዲያ ለመመስረት ያለመ ነው ተብሏል፡፡ ውህደቱ የፋይናንስ፣ የሰው ሃይል፣ የቴክኖሎጂና የመሰረተ ልማት አቅምን በማቀናጀት የሃብት ብክነትን ማስቀረት እንደሚያስችል የተጠቆመ ሲሆን፤ ከዚህም ባሻገር የተቋማቱ ውህደት ትርፋማነትንና ውጤታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዝ ተገልጿል። የውህደቱ ሒደት አስፈላጊውን ሕግና ሥርዓት ተከትሎ መፈጸሙም ተነግሯል፡፡
የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን የማብሰሪያና ሥራ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ ንግግር ያደረጉት በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፤ መንግስት ከለውጡ ወዲህ የሚዲያን ጥቅም በመረዳት ሰፋፊ ስራዎች በመስራት ላይ እንደሚገኝ አመልክተዋል፡፡ ሁለቱ ተቋማት የመንግስት ግልጸኝነት እንዲታይ ሰፋፊ ሥራዎችን እንደሰሩ ጠቁመው፤ መንግሥትም ለሚዲያው ትኩረት በመስጠት ተቋማቱ የለውጡ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓል ብለዋል። የመረጃ ተደራሽነት ከፍ እንዲል ማድረግ፣ ብሄራዊ ትርክት ላይ መስራትና ኢትዮጵያ በዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ እንድትሆን ማድረግ ከአዲሱ ተቋም እንደሚጠበቅም አደም ፋራህ ገልጸዋል፡፡
የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በበኩላቸው፣ አዲስ የተመሰረተው ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስከብር ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም፤ ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን በገለልተኝነትና በብቁ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባር፣ ትውልድን በብሔራዊ ማዕቀፍ የሚገነባ፣ የተለየ ተግባር ያለው ትልቅ ሚዲያ ነው ብለዋል።
የጠ/ሚኒስትሩ የማኅበራዊ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር እና የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ቦርድ ሰብሳቢ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ባደረጉት ንግግር፤ ዋልታ ሚዲያና ኮሙኒኬሽን ኮርፖሬት እና ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተዋህደው የፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን መመስረት የመደመር እሳቤ ውጤት ነው ብለዋል፡፡ “በኢትዮጵያ ልክ ኢትዮጵያን መግለጥ ለመቻል በማሰብ ተነጣጥለው ሲንቀሳቀሱ የነበሩት ሁለቱ ሚዲያዎች ተዋህደው አንድ ሆነዋል” ሲሉም አክለዋል፡፡
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የቀድሞው የዋልታ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ኮርፖሬት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ መሐመድ ሀሰን፣ በተቋሙ ቆይታቸው ላበረከቱት አስተዋጽኦ የእውቅና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡
በዚህ መርሃ ግብር ላይ በምክትል ጠ/ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ፣ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ፣ የሚዲያው አመራሮች፣ የድርጅቱ ሰራተኞች፣ ተባባሪ አዘጋጆች፣ የሚዲያው አጋሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን አ.ማ፤ ሁለት የቴሌቪዥን ቻናሎችና ሦስት ሬዲዮ ጣቢያዎች እንደሚኖሩት ታውቋል፡፡
የፓስታ ፌስቲቫል ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ ይካሄዳል
በኢትዮጵያ ሲዘጋጅ ለሁለተኛ ጊዜ መሆኑ የተነገረለት የፓስታ ፌስቲቫል፤ በዛሬው ዕለት ከረፋዱ 5፡30 ጀምሮ በሚሊኒየም አዳራሽ ይከናወናል፡፡
በካልቸር ክለብ በተዘጋጀው የጣልያን ምግብ ፌስቲቫል ላይ ከ5ሺ እስከ 7ሺ እንግዶች እንደሚታደሙ ይጠበቃል፡፡ በፌስቲቫሉ ላይ ከ23 በላይ የፓስታ ምግብ ሻጮች የተለያዩ ዓይነት የፓስታ ምግቦች፣ ሱጎዎችና ጣፋጮችን እንደሚያቀርቡ ታውቋል፡፡
የመግቢያው ዋጋ 250 ብር ሲሆን፤ትኬቶችን በቴሌብር መግዛት ወይም መግቢያው በር ላይ ማግኘት ይቻላል፡፡
በዚህ ፌስቲቫል ላይ ከግሩም የፓስታ ምግቦች ባሻገር፣ ሙዚቃና ከምግብ ማብሰል ጋር የተያያዙ አዝናኝ ትርኢቶች ይኖራሉ ተብሏል፡፡
“ሚለርስ ፎር ኒውትሪሽን” በኢትዮጵያ ሥራ ጀመረ
ኩባንያው የተመጣጠነ ምግብ እጥረትን ለመቅረፍ እንደሚሰራ ተገልጿል
“ሚለርስ ፎር ኒውትሪሽን” የተሰኘው የውጪ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተመጣጠነ የምግብ እጥረትን ለመቅረፍ ስራ መጀመሩን አስታወቀ። ኩባንያው ይህን ያስታወቀው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ለመገናኛ ብዙኃን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫና አጠቃላይ ዕቅድና ግቡን ለባለድርሻ አካላት ባስተዋወቀበት የግማሽ ቀን መርሃ ግብር ላይ ነው።
ሚለርስ ፎር ኒውስትሬሽን በተለይ “ሰርቭ” ከተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የሚታየውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቅረፍ ስራ የጀመረ ሲሆን፤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ለ140 ፋብሪካዎች የቴክኒክ ድጋፍ እንዲሁም ለ40 ፋብሪካዎች ደግሞ ስልጠና መስጠት መቻሉን የኩባንያው ሀላፊ ተናግረዋል። የሚለርስ ፎር ኒውትሬሽን የኢትዮጵያ ፕሮግራም ሀላፊ አቶ እያቄም አምሳሉ ጨምረው እንደገለፁት፤ የተመጣጠነ የምግብ እጥረት በሀገር አቀፍ ደረጃ አሳሳቢ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚሁ ምክንያት በኢትዮጵያ የሚገኙና እድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት 22 ከመቶዎቹ ከክብደት በታች እንደሚገኙ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት፣ የምግብና የመጠጥ ኢንዱስትሪ ምርምር ልማት ማእከል በቅርቡ ያወጣውን መረጃ በዋናነት አቅርበዋል።
ከላይ የተቀመጠው አሀዝ በኢትዮጵያ ያለውን የምግብ እጥረት በመቅረፍ፣ ጤናማና አምራች ዜጋን ለመፍጠር፣ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
ከዚህ አኳያ ሚለር ፎር ኒውትሬሽን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ ይቀርፋል የተባለ ሲሆን፤ በተለይም የስንዴ ዱቄት አምራችና የምግብ ዘይት ፋብሪካዎችን በቫይታሚን በማበልፀግ እጥረቱን ለመቀነስ እንደሚሰረራ ተናግሯል።
ሚለርስ ፎር ኒውትሪሽን በአፍሪካና በእሲያ እንደሚሰራ የተገለፀ ሲሆንበኢትዮጵያ፣ በኬንያ፣ ናጄሪያ፣ ፓኪስታን፣ ባንግላዲሽን ጨምሮ በጥቅሉ በስምንት ሀገራት እየሰራ ይገኛል።
ባለፈው ሳምንት በተከናወነው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ሃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ታድመዋል።
ወጣቱ ባለሃብት ከ2 ሚ. ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል
በተለያዩ የበጎ አድራጎትሥራዎች ላይ ገንዘቡንና ጊዜውን በመሥጠት በንቃት የሚሳተፈው ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ፤ በዛሬው ዕለት አበበ በቂላ ስቴዲየም አካባቢ ባለው ባቡልኬይር በመገኘት ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የ4ሺ ሰው የምሳ ወጪ ሸፍኗል፡፡
ከዚህም ባሻገር፣ ድርጅቱ እየሰራ ያለውን የበጎ አድራጎት ለማገዝ የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።
ስጦታውን የተረከቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀናን ማህሙድ ምህረት አብ፣"ዛሬ ሰርፕራይዝ ነው ያደረግኸን፤ ይሄን ያህል መጠን ያለው ድጋፍ ሲደረግልን የመጀመሪያው ነው።" ሲሉ ለባለሃብቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በሀገራችን በራስ ተነሳሽነት በደጋግ ኢትዮጵያውያኖች ከተመሠረቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ባቡል ኬይር የበጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ሲሆን፤ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አስታዋሽ ያጡ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል፡፡
በኢትዮጵያ የሚኖሩትን የውጭ አገር ሰዎችን ያዋረደ ፣ የማይገባም ቃል የተናገረ እንደ ሕጉ በብርቱ ቅጣት ይቀጣል !!!
"የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለሕዝብ ማስታወቂያ"
ከዚህ ቀድሞ በመስከረም 11 ቀን 1928 ዓ.ም በተነገረው አዋጅ እንደሰማችሁት የኢጣልያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ሥራ በመሥራቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከተነሣበት ጠላት እንዲከላከል ምንም ቢታዘዝ ጠላት የተባሉት ወሰን አልፈው መሣሪያ ይዘው የወገኖቻችንን የኢትዮጵያን ሰዎች ደም ለማፍሰስ የሚመጡ ኢጣልያኖች ናቸው እንጂ በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን ከከተማ ውጭም ቢሆን በኢትዮጵያ የሰላማዊነት ሥራ እየሠሩ ለመኖር የመጡት አይደሉምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱና በአክባሪነቱ ከውጭ አገር ሰዎች ጋራ ተስማምቶ በሳላም በመኖሩ በዓለም የተመሰገነ ስለሆነ ይህ መልካም ስማችን ሳይጠፋ ተከብሮ እንዲኖር ገፍቶ የመጣውን ጠላታችንን ወደድንበራችን ሒደን ለመመለስ ከማሰብ በቀር በመካከላችን እኛን ዘመድ አድርገው በሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎች ላይ ማናቸውንም የጠላትነት አሳብ የሚገልጥ ነገር እንዳታደርጉ እናስታውቃለን። አሁን ከኢጣልያን ጋራ በተነሣው ጠብ ምክንያት በማስፈራራት በመጋፋት ወይም የማይገባ ቃል በመናገር ይህን በመሰለ አደራረግ ሁሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩትን የውጭ አገር ሰዎች ያዋረደ፥ የማይገባም ቃል የተናገረ እንደ ሕጉ በብርቱ ቅጣት ይቀጣል።
መስከረም 14 ቀን 1928 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከንቲባ
ምንጭ:- ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ
ጠ/ሚኒስትሩ የዶ/ር ደብረጽዮንን ጥያቄ ውድቅ አደረጉ
• የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ተጠይቆ ነበር
ለወራት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የሚማስኑት የህወሓት አመራሮች ትላንት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በትግራይ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው ውዝግብና አለመግባባት መፍትሄ ሳይበጅለት የቀጠለ ሲሆን፤ ሁለቱም ወገኖች ቡድን ለይተው መካሰሳቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ትላንት ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በጠ/ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በክልሉ የፀጥታና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን፤ በዚህ ስብሰባ ላይም ሁለቱ ቡድኖች መካሰሳቸው ተነግሯል፡፡
ቢቢሲ ስማቸውን መጥቀስ ያለፈለጉ ውይይቱን በቅርበት የተከታተሉ ታማኝ ምንጩን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በትግራይ ክልል የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ቢሆንም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ጥያቄ ቀርቧል ብሏል፡፡
በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በትግራይ እየተከሰተ ላለው ችግር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ደካማነት በምክንያትነት በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጌታቸው ረዳ ከሥልጣን እንዲነሱ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡
"ጌታቸው ተነስቶ ምክትሉ ጄኔራል ታደሰ ወረደ" ቦታውን እንዲይዙ ሃሳብ ማቅረባቸውን ጉዳዩን በቅርብት የተከታተሉት አንድ ተሳታፊ ለቢቢሲ ትግርኛ መናገራቸው ታውቋል፡፡
በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን በበኩሉ፤ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን" በማድረግ ዶ/ር ደብረጽዮንንና ቡድናቸውን ከሷል።
"ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራዎች እንቅፋት የሆናችሁት እናንተ ናችሁ" በማለት ምላሽ የሰጡት ጌታቸው ረዳ፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋል።
በድርጅቱ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናን ያላገኘው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አቶ ጌታቸውና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ከተባረሩ በኋላ ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪዎች ሥልጣን ላይ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።
አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንትነትን ቦታ የያዙት በህወሓት ውክልናቸው ነው በሚልም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የፌደራል መንግሥቱን ሲጠይቁ ነበር ተብሏል። አሁን ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት ጊዜም፣ ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ይህንኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ተነግሯል፡፡
ዶ/ር ደብረጽዮን፣ አቶ ጌታቸው ከጊዜያዊ አስተዳደር መሪነታቸው ተነስተው በቦታው ጄኔራል ታደሰ እንዲተኩ ያቀረቡትን ሃሳብን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ታማኝ ምንጩ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።
"ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን እንዳያከናውን 'የትግራይ ሠራዊት' ከጎናችን ነው' በማለት ሕዝቡን ግራ እያጋባችሁት ነው" በማለት የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድንን የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በስመ ምክር ቤት በሚል ሕዝቡን እየረበሻችሁት ነው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።
ጠ/ሚኒስትሩ ጨምረውም፣ መንግሥታቸው የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ አድርጌለታለሁ እንደማይል በማንሳት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሚጠበቅበትን እያከናወነ እንደሚቆይ ማሳወቃቸውን የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።
“ብሔራዊ አጀንዳዎቻችን ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን”
ኢትዮጵያውያን ግጭቶችና ልዩነቶችን ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለብን ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ፡፡
ኢትዮጵያ የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ያላትን አቋም ለአረብ ሀገራት በአረብኛ ቋንቋ በስፋት በማድረስ የሚታወቁት ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ እንደ ሕዝብ ብሔራዊ የሆኑ አጀንዳዎቻችን ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኡስታዝ ጀማል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ግብጻውያን በመሀከላቸው መከፋፈል ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው አንድነት ጠንካራ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
“ግብጻውያን በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ፤ ረጅም ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙ ዜጎቻቸው ጭምር በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸው አቋም አንድ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤት ብትሆንም በዜጎች ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት ሊሠራበት የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ተተኪ ለሆኑ ትውልዶች ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብትና የዓባይን ውሃ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ በመሥራት ረገድ ያለን ተሞክሮ ደካማ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህ ጉዳይ ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ኡስታዝ ጀማል ሀገርን ወክለው በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማሳወቅ፣ በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብና የራሳቸውንም ሚዲያ በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ በመሞገት ይታወቃሉ፡፡