Administrator

Administrator


    “አዲስ አበባ በልጆቿ መመራት አለባት” በሚል በአሁኑ የከተማዋ አመራር ላይ አሲረዋል ተብለው የታሰሩት የህግ ጠበቃና የሰብአዊ መብት ተከራካሪው አቶ ሄኖክ አክሊሉ፤ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር እንዲለቀቁ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አሳሰበ፡፡
ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ እና ሌላው ታሳሪ አቶ ሚካኤል መላኩ መታሰር፤ አሁንም በሀገሪቱ መሰረታዊ የሰብአዊ መብቶች ተሟልተው እየተከበሩ እንዳልሆነ ጉልህ ማሳያ ነው ብሏል የሰብአዊ መብት ተቋሙ፡፡
“እስሩ መንግስት የጀመረውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት እንቅስቃሴን በእጅጉ የሚጎዳ ነው” ያለው አምነስቲ፤ “ፖሊስ የመብት ተሟጋቾችን ከማሰር ይልቅ መብታቸውን ሙሉ ለሙሉ የሚጠቀሙበትን አስቻይ ሁኔታ መፍጠር ይገባዋል” ብሏል፡፡
በሀገሪቱ ሃሳብን የመግለፅና የመደራጀት መብት ተሟልቶ እንዲከበር መንግስት ያለውን ቀናኢነት ሁለቱን ግለሰቦች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር በመፍታት ማሳየት አለበት ብሏል - አምነስቲ ኢንተርናሽናል፡፡
ለበርካታ የሽብር ተከሳሾች በነፃ ጭምር ጥብቅና በመቆም የሚታወቁት የህግ ባለሙያና ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ፤ “አዲስ አበባ በልጆቿ ብቻ ነው መመራት ያለባት” ሲሉ አሲረዋል በሚል ተጠርጥረው መታሰራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤት አስታውቋል፡፡
ረቡዕ እለት በፖሊስ ተይዘው የታሰሩት ተጠርጣሪው፤ ሐሙስ ፍ/ቤት የቀረቡ ሲሆን “የክፍለ ሃገር ልጅ አዲስ አበባን ሊመራ አይገባም” በሚል ወጣቶችን በመቀስቀስና በማደራጀት፣ እንዲሁም ከፍልስጤም ኤምባሲ ጋር ግንኙነት በመፍጠርና ስልጠና ወስደዋል በሚል መታሰራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አመልክቷል፡፡
ከህግ ባለሙያውና ጠበቃው አቶ ሄኖክ አክሊሉ ጋር የታሰሩት አቶ ሚካኤል መላኩም፤ በተመሳሳይ ድርጊት መጠርጠራቸውን ፖሊስ ለፍ/ቤቱ አስረድቷል። በተጠርጣሪዎች ላይ ተጨማሪ ማስረጃ ለማሰባሰብ ፖሊስ ተጨማሪ የ7 ቀን የምርመራ ጊዜ ተፈቅዶለታል፡፡

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አብዲ ሞሃመድ ኡመር (አብዲ ኢሌ)፤ የታሰሩበትን ክፍል መስኮት በመስበርና ከጥበቃ ጋር በመተናነቅ የማምለጥ ሙከራ አድርገው ነበር ሲል ፖሊስ ትናንት ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተናገረ ሲሆን ግለሰቡ ግን ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን ለችሎቱ መግለጻቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል፡፡
አብዲ ሞሃመድ ኡመር፤ በምርመራ ወቅት ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እንደነበረባቸውና የአእምሮ ጤና ችግር ካለበት አንድ ታሳሪ ጋር በአንዲት ጠባብ ክፍል ውስጥ ታስረው እንደነበር ለችሎቱ አቤቱታቸውን ማሰማታቸውን ተከትሎ ፖሊስ በሰጠው ምላሽ፣ ግለሰቡ የጤና ችግር እንዳለባቸው በመግለጻቸው ለቢሮ በሚያገለግል ክፍል ውስጥ ታስረው እንደነበርና የማምለጥ ሙከራ ካደረጉ በኋላ ግን፣ ወደ መደበኛ የእስረኞች ክፍል ተዛውረው ለብቻቸው እንዲታሰሩ ተደርጓል ማለቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡

ሰውዬው ከሰፈሩ ሁሉ በምስኪንነቱ የታወቀ ነው፡፡ ዓመት በዓል በደረሰ ጊዜ ሁሉ፣ አንዱ ይመጣና፤
“ጋሽ ሰመረ፤ በዚህ በዓል ምን ልታርድ ነው ያሰብከው?”
ጋሽ ሰመረም፤
“ካገኘሁ በሬ፣ ካላገኘሁ አንዲት ጫጩት አላጣም!”
ሁለተኛው መንደርተኛ በቀጣዩ በዓል ይጠይቀዋል፤
“ጋሽ ሰመረ፤ በቀጣዩ በዓልስ ምን ልታርድ አስሃበል?”
ጋሽ ሰመረ፤
“በሬ፣ ፍየል፣ በግ … ከጠፋ አንዲት ጫጩት!”
በዓሉ ይመጣል፡፡ አንድ ጫጩት ያርዳል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ ብዙ ጫጩት እያረደ ከበላ በኋላ ከእለታት አንድ ቀን ሞላለትና አንዲት ኮስማና በግ ገዛ፡፡
በመንደሩ እየተዘዋወረ፤ የየቤቱን በር እያንኳኳም፤
“በግ ያየህ ና ወዲህ በለኝ!
በግ ያየህ ና ወዲህ በለኝ!...” ይል ጀመር፡፡
“አላየንም!” ይሉታል፡፡
ለካስ ጋሽ ሰመረ፤ በጓ ጠፍታበት ሳይሆን አንደኛው ግቢ ውስጥ በአጥር ወርውሯት ኖሯል፡፡
መዘዋወሩን የቀጠለው ግን በሌሎቹ ግቢዎች አቅጣጫ ነው፡፡ ጋሽ ሰመረ በግ እንደገዛ ሰፈሩ ሁሉ ማወቅ አለበታ!
በመጨረሻ በጓን የወረወረበት ግቢ ዘንድ ሲደርስ ሰውነቱ ዛል ብሏል፡፡
በር አንኳኳና ተከፈተለት፡፡
“ማነው?” አሉ፤ አንድ አሮጊት ሴትዮ፡፡
“እኔ ነኝ፡፡ እዚህ ግቢ በግ ገብታብኝ ነበር፡፡ ባለበጉ ነኝ!”
“ውይ ይቺ አቃስታ አቃስታ ክልትው ብላ የሞተችው በግ ያንተ ኖራለች እንዴ?”
ጋሽ ሰመረም፤
“ገደላችኋት? በምን መታችኋት ነው?”
"ደሞ በምን ትመታለች? ለራሷ ኮሳሳ? … እንደመሰለኝ በአጥር የወረወርካት ጊዜ አጥሩ ወግቷት ነው ደሟ አልቆ የሞተችው! … በል ጓሮ ዙርና ሬሳህን ተሸክመህ ሂድ!”
ጋሽ ሰመረም፤
“አይ እማማ! እጄን በጄ ነው በሉኛ!”
አሮጊቷም፤
“አይ ልጄ፤ አሁን ንዴቱም፣ ፀፀቱም አይጠቅምህም! ሚስጥሩ በእኔና ባንተ ማህል ይቆይና፤ አልሞተችም በጌ ብለህ አስበህ በሥነ ስርዓት ይዘሃት ሩጥ!” አሉት፡፡
***
የሞተውን አለ፣ ያለውን ሞቷል ከማለት ያውጣን!
ማስተዋል ያነሰው አድናቆትም፣ ማስተዋል ያነሰው ተቃውሞም ሁለቱም መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ታላቁ ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን፤
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ”
ይለናል፡፡ በትኩስ ስሜት ውስጥ የሚሰራ ስራ ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ጊዜያዊ መፍትሄ ፋታ ሊሰጠን ይችል ይሆናል እንጂ ዘላቂ ድል አያስገኝም፡፡ መሰረታዊ ድህነትን አስወግዶ መሰረታዊ የህይወት ለውጥን አያመጣም! እንደ ኢትዮጵያ በርካታ ችግሮችን ተሸክማ የኖረች አገር፤ አብዛኛው ሰቆቃዋ የሚመነጨው ከኢኮኖሚያዊ ለውጥ ማጣት ነው፡፡
“ድህነት በአፍ አይገባም” የሚለን ሎሬት ፀጋዬ “ማጣት፤ በነብስህ ጫፍ ተንጠራርተህ ሩቅ አልመህ ሁሉን መሳት” ይለናል፡፡ ነጋ ጠባና ለዘመናት ስለ ኢኮኖሚ ውድነት ማውራት የህዝብ መዝሙር እስኪመስል ድረስ ለምደነዋል፡፡ መፍትሄ ሳያገኝ የቆየ ችግር ደግሞ፣ ምንም ያህል ቢድበሰበስ፣ ቀን ቆጥሮ አመርቅዞ እጥፍ ድርብ ሆኖ ብቅ ይልብናል፡፡ ለአንድ ሰሞን የሥጋ ዋጋ ቀንሰናል ብለን ስናበቃ፣ ዛሬ የት እንደደረሰ ማስተዋል ነው፡፡ በቀን ሶስቴ እንመገባለን ብለን፣ ዛሬ ስንቴ እንደምንመገብ ልብ ማለት ነው፡፡ “ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ” የምንልባት አገር መሆን የለባትም፡፡ “ከባልሽ ባሌ ይበልጣል፤ ሽሮ አበድሪኝ" ማለትም የአፍ አመል ሆኖ ቀሪ ነው!
የኢኮኖሚ ሙያ ምሁራኖቻችን ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው፤ “ከእንግዲህ አንራብም!” ብለው ሀሞታቸውን መረር አድርገው፣ እንደ ጥንቶቹ አውሮፓውያን ቆርጠው አገር የሚገነቡ ህዝቦች ማየት አለብን ብለው፤ ምርምር ላይ ማትኮር አለባቸው፡፡ “አፍአዊ ሳይሆን ልባዊ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ተግተው፣ ለህዝብ መጠቆም፣ ፈር መቅደድ አለባቸው፡፡
ራስን መደለልም ሆነ ሌላውን ማታለል ወንዝ አያሻግርም፡፡ የፖለቲካ ስብከት መሬት አያስረግጥም፡፡ ዲሞክራሲም፣ ፍትህና እኩልነትም የአንድ ሰሞን ሰበካ እንጂ ባዶ ሆድ የሚሞሉ እህል ውሃዎች አይሆኑም፡፡ በየዓመት በዓሉ ባልነበረ በግ፤ “በግ ያያችሁ ና ወዲህ በለኝ” ከሚለው ግብዝ ባለበግ መማር አለብን፡፡ ለሰው ይምሰል ብለን የምናደርገው ነገር፣ የማታ ማታ ዋጋ ያስከፍለናልና እናስብበት!
 


   ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በባህልና በሌሎች ማህበራዊ እሴቶች እጅግ የተሰበጣጠረ ሕዝብ ያለባት አገር እንደመሆኗ፣ ሁሉንም ሕዝብ እኩል አከባብሮና አቻችሎ ሊያኖር የሚችል መንግስታዊ አወቃቀር ያስፈልጋታል። ለዚህም ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ተመራጭና ምቹ ስለመሆኑ ምንም አያከራክርም፡፡  ጥያቄው ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓቱ በምን መሰረት ላይ ይዋቀር በሚለው ላይ  ነው። ይህን ደግሞ በደመ ነፍስ እንዲህ ይሁን እንዲያ ከማለት፣ አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊና ተጨባጭ እውነታዎች በቅጡ ያገናዘበና  በባለሙያዎች የተጠና ፌደራላዊ አወቃቀር እንዲኖር ማድረግ ይቻላል። በዚህ ዘርፍ የተደረጉ በርካታ ጥናቶችም ስላሉ፣ እነሱንም በቅጡ መፈተሽ ጊዜና አቅምንም ይቆጥባል።
እኔን እያሳሰበኝ ያለው በአገሪቱ ውስጥ እየተንሰራፋ የመጣውና ለብዙ ዜጎች ህይወት ህልፈትና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ቋንቋንና ጎሳን ያማከለው የመንግስት አወቃቀር ነው። ክልሎች በዚህ መልክ በመዋቀራቸው ብቻ ሳይሆን ላለፉት ሃያ ሰባት አመታትም በመንግስትና አክራሪ በሆኑ ብሔረተኞች ሲቀነቀንና ሲሰበክ የኖረው ዘር ተኮር ፖለቲካ፣ ዛሬ ፍሬው ጎምርቶ፣ በየክልሉ አደጋዎች እያስከተለ ነው። አንዱ ስፍራ ላይ አፈናቃይና ተሳዳጅ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል፣ ሌላው ክልል ላይ ተፈናቃይ እየሆነ አገር እየታመሰች ነው።
በተለያዩ  ክልሎች የሚታዩት ዘር ተኮር ጥቃቶች ያልነኩት የህብረተሰብ ክፍል የለም። በግንባር ቀደምነት አማራው ከኖረበት ቀዬው ከወልቃይትና ራያ አንስቶ፣ በሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል የጥቃት ሰለባ ሆኗል። ኦሮሞውም እንዲሁ ከሶማሌ ክልልና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እየተሳደደ ነው። በደቡብ ክልል አንዱ ጎሳ ሌላውን እያፈናቀለ ነው። ሌሎቹም ጎሳዎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እየገጠማቸው ነው። ማቆሚያው የቱ ጋ እንደሆነ አይታወቅም።
ይህን አደጋ ያስከተለው ደግሞ አገሪቱ ስትከተል የኖረችው የጎሳ ፌደራሊዝም እንደሆነ ማሳያው የሁሉም ጥቃቶች ምንጭ አሳዳጅ የሆነው አካል፤ «ክልሌ ነው፣ የእኔ መሬት ነው፣ እናንተ ባዳዎች ናችሁ፣ በዚህ ስፍራ የመኖር ዋስትናችሁ በእኔ ፈቃድ የተወሰነ ነው--» ከሚል ስሜት የመነጨ መሆኑ ነው። ይህ ስሜት ደግሞ ዝም ብሎ ከየትም የመነጨ ሳይሆን የሕግ ድጋፍም ጭምር ያለው  ነው። ከሕገ-መንግስቱ ጀምሮ የክልል ሕገ-መንግስቶች ለዜጎች እውቅና አይሰጡም። ዜጎች የአገራቸው ባለቤት አይደሉም። እያንዳንዱ ክልል ለብሔር፣ ብሔረሰቦች የተሰጠ ስለሆነ፣ ሁለት አይነት ዜግነት እንዲኖር አድርጓል።
በቤኒሻንጉል የሚኖር ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ እዚያው ክልል እንኳን ቢወለድ፣ ከአንድ ጉሙዝ እኩል በክልሉ ውስጥ የዜግነት መብት የለውም። በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ አንድ ጉራጌ ወይም ከንባታ ወይም ወላይታ፤ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከአንድ ኦሮሞ እኩል የዜግነት መብት የለውም።
እነዚህ ነገሮች ከጥላቻ ፖለቲካ ጋር ተቀላቅለው የፈጠሩት ነገር፣ ይሄው ዛሬ የምናየው እርስ በእርስ መጠፋፋትና አንዱ ሌላውን ማሳደድ ነው። ይህ አይነቱ ጎሳን ያማከለ፣ ዜጎችን ያበላለጠ፣ አንዱን ተሳዳጅ ሌላውን አሳዳጅ ያደረገ ዘር ተኮር የመንግስት ፖሊሲ ሊቀየር ይገባል።
የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ አደጋ እየታየና ህዝብ በገዛ አገሩ እየተፈናቀለም፣ ፌደራሊዝሙ የተዋቀረበት መንገድ ይፈተሽና ይስተካከል ሲባል፣ አክራሪ ጎሰኞቹ ብቻ ሳይሆኑ በዘር ፖለቲካ የቆረቡ ሰዎችም፣ «ፌደራሊዝሙን ልታጠፉብን ነው የተነሳችሁት» እያሉ ሲያላዝኑና እንቧ ከረዩ ሲሉ መስማታችን ነው። ፌደራሊዝሙን ከጎሰኝነት አጽዱት ሲባል፣ «በአንድነት ስም ልትውጡን ነው» የሚል ስጋትም ነው ደጋግሞ ሲገለጽ የሚሰማው።
በአገሪቱ ውስጥ ጎጠኝነት ተንሰራፍቶ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። ሰዎች በጎጥ ከረጢት ውስጥ ሆነው ነው አገራቸውን የሚያስቡት። ያ ደግሞ የጋራ አገራዊ ራዕይም ሆነ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በጋራ እንዳንቆም ብቻ ሳይሆን አብረን እንዳንኖርም እያደረገ ነው። ችግሩ የዘር ፖለቲካውን የሚያጦዙት ልሂቃኑ የጥቃሉ ሰለባ አይደሉም። በዘር ግጭት የሚሞተው ያው በየመንደሩ ያለው ደሃና  የዚህ መሰሪ ፖለቲካ ግራ ቀኙ ያልገባው ምስኪን ሕዝብ ነው። ፖለቲከኛው ገሚሱ አዲስ አበባ፤ ቀሪውም አውሮፓና አሜሪካ ተቀምጦ ነው እሳትና ነዳጅ ወደ ድሃው መንደር የሚወረውረው። በጎሳ ፖለቲካ መዘዝ ሟቹና ተፈናቃዩ ግን ደሃው ሕዝብ ነው። በእኛ ዝቅጠት ይህ ድሃ ህዝብ እስከ መቼ ነው ባገሩ ተሳዳጅ የሚሆነው?
ጉዳዩ  በጊዜ ተመክሮበት እልባት ያግኝ የሚል ጥሪ ከመብት ተሟጋቾች ሲቀርብ፣ ፌደራሊዝሙን ልታፈርሱ ነው እያሉ የሚያንቧርቁ ጎሰኞች ቆመው ሊያስቡ ይገባል። አሁንም በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ «አዎ! ኢትዮጵያ ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ነው የሚበጃት» እዚህ ላይ ጥያቄም ሆነ ጥርጥር የለም። ጥያቄው ዘርን ያማከለ አይሁን ነው። የዘር ፖለቲካው እያስከተለ ያለው አደጋ ባሳሰብን ቁጥር ጸረ ፌደራሊዝም አድርጎ ማቅረብ፣ አንድም ዝም ለማሰኘት አለያም «በዘር ፖለቲካው እያተረፍን ስለሆነ ለእኛ ተመችቶናልና ማንም ቢሞትና ቢፈናቀል አይመለከተንም» ነው የሚሆነው።
ለማንኛውም ለለውጥ ኃይሉ መልካሙን ሁሉ እየተመኘን፣ የአገር ግንባታውም (nation building) ሆነ የመንግስት ግንባታው (state building) ትግል ከወዲሁ አሳታፊ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ግልጽነት የተሞላውና ተጠያቂነት የሰፈነበት  መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መሰረቱ ያልጸና የአገርም ሆነ የመንግስት ግንባታ አሸዋ ላይ እንደ ተጣለ ድንኳን ነውና በነፈሰ ቁጥር መንገዳገድ ብቻ ሳይሆን ከስር መመንገልም ይኖራል። ቸር ያሰማን!
(ከስዩም ተሾመ ፌስቡክ ጥቅምት 3, 2018)

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ገበያ ልማት መለዮ ላይ ያተኮረ ኢትዮጵያን በፎቶ የማስተዋወቅ ውድድር ባለፈው ሳምንት የተጀመረ ሲሆን ውድድሩ ኦክቶበር 31 2018 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ታውቋል፡፡
ተወዳዳሪ የፎቶግራፍ ባለሙያዎች፤ የሀገሪቱን የቱሪዝም ሀብቶች በፎቶ በማቅረብ ውበታቸውን አጉልቶ ማሳየት የሚጠበቅባቸው  ሲሆን አላማውም የቱሪዝም መለዮ አርማውን በያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ  እንዲሰርፅ በማድረግ፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝም መስህቦች አምባሳደር ማድረግ ነው ተብሏል።  “Land of origins” ወይም  በአማርኛው “ምድረ ቀደምት” በመባል የሚታወቀውን የቱሪዝም መለዮ የማስተዋወቅ ዘመቻ ባለፈው ሳምንት መጀመሩን የጠቆመው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት፤ የዘመቻው አንዱ አካልም ኢትዮጵያን ምድረ ቀደምት ያሰኟትን በርካታ የተፈጥሮ፣ የባህልና የታሪክ ቅርሶች በተለያዩ አጋጣሚና ጊዜያት በተነሱ ፎቶዎች መግለፅ እንደሆነ አመልክቷል፡፡  
የፎቶግራፍ ባለሙያዎች ለውድድር የሚያቀርቧቸው ምስሎች በተለያዩ ባለሙያዎች ተገምግመው በደረጃ የሚለዩ ሲሆን በውድድሩ ላሸነፉ ሶስት ተወዳዳሪዎችም ጠቀም ያሉ ሽልማቶች መዘጋጀታቸውን ድርጅቱ አስታውቋል፡፡
በውድድሩ  ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት ያላቸው የፎቶግራፍ ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ከሁሉ በበለጠ ይገልፅልናል የሚሏቸውን የፎቶ ምስሎች አዘጋጅተው photocompetition@ethiopia.travel ላይ ማቅረብ እንደሚችሉ የተገለጸ  ሲሆን የፎቶው ይዘት ምን መምሰል እንዳለበትና ለውድድር የሚቀርቡት ፎቶዎች መጠን ምን ያህል እንደሆነ በድርጅቱ ድረ ገፅ www.ethiopia.travel ላይ ማግኘት እንደሚቻል ተጠቁሟል፡፡

የሠራዊት አባላቱ ጠ/ሚኒስትሩንና ህዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋ

ባለፈው ረቡዕ መስከረም 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተሲያት ላይ፣ 240 የመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ ከእነ ሙሉ ትጥቃቸው ወደ ብሔራዊ ቤተ-መንግስት ያመሩት ለግዳጅ  አልነበረም። ይልቁንም ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ለመወያየት ፈልገው ነው፡፡ የሰራዊት አባላቱ ያልተለመደ አመጣጥ እንግዳ የሆነባቸው የቤተ መንግስት ጸጥታና ደህንነት ሃላፊዎች፤ ከሁሉ አስቀድመው አባላቱን ትጥቅ እንዳስፈቷቸው  ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ነው ቤተ መንግስት እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ተብሏል፡፡
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ የዚያኑ ዕለት ምሽት ለኢቴቪ በሰጡት መግለጫ፤ ነገሩን ቀላል አድርገው ነው የገለጹት፡፡ በወታደሮቹ ቤተ መንግስት መከሰት የደነገጡ ወይም የተበሳጩ አይመስሉም፡፡ እንደውም ከሰራዊቱ አባላት ወደ ቤተ መንግስት መግባት ጋር ተያይዞ፣ በፌስቡክ ላይ በተሰራጩ የ”መፈንቅለ መንግስት ሙከራ” እየተደረገ ነው ዓይነት አሸባሪ የፈጠራ ወሬዎች ሳይደነግጡ አልቀሩም፡፡ ለዚያም ሳይሆን አይቀርም ራሳቸው ለቲቪ መግለጫውን የሰጡት። “የውሸት ዘመቻ ተቀብለን ካስተናገድን ያው መበላላት ነው” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ”በሃይማኖት፣ በዘር፣ በሥልጣን---ክፉ ሰዎች እንዲህ እየፈጠሩ ነው የሚያሰራጩት--” በማለት ህብረተሰቡ፣ ከፌስቡክ ዘመቻ ራሱን እንዲያቅብ መክረዋል፡፡    
ጠ/ሚኒስትሩ ነገሩን ቀለል ያድርጉት እንጂ ፖለቲከኞችና ምሁራን ግን የወታደሮቹን ድርጊት እንደ አደገኛ አዝማሚያ በመቁጠር መንግስት ዳግም እንዳይከሰት ወሳኝ እርምጃ መውሰድ አለበት ይላሉ፡፡  
“የሠራዊት አባላቱ የትኛውም ዜጋ ደፍሮ የማያደርገውን አማራጭ በመውሰድ፣ ትጥቅ ይዘው በአስገዳጅ ሁኔታ ቤተ መንግስት መግባታቸው አደገኛ መልዕክት ያለው ነው” ያሉት የዩኒቨርሲተ መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ፤ ”የሠራዊቱ አባላት ይህን ድርጊት ለመፈፀም የደፈሩት ስለታጠቁ ብቻ ነው፤ ይሄ ለሌላውም የሰራዊት አባላት አርአያነቱ በጎ አይደለም” በማለት ያስጠነቅቃሉ፡፡  
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የየራሱ ጥያቄ አለው፣ ነገር ግን በእንዲህ መልኩ ማቅረብ የሚችልበት ድፍረትም የህግ አግባብም የለም ያሉት መምህር ስዩም፤ያለ ብዙ ችግር ሁኔታው መጠናቀቁ መልካም ነው፤ ድርጊቱ ዳግም እንዳይሞከር ግን የማስተካከያ እርምጃዎች መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ድርጊቱ በድንገት የተካሄደ ነው ብለው እንደማያምኑ የጠቆሙት ምሁሩ፤ “በሚገባ ተመክሮበትና ታቅዶበት የተደረገ መሆኑ፣ ድርጊቱን አደገኛ አዝማሚያ ያለው ያደርገዋል” ሲሉ ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “ጉዳዩን በየደረጃው ያሉ የጦር አዛዦች ያውቃሉ ብዬ እገምታለሁ፤ ማወቅም አለባቸው፤ ለምን የሰራዊቱ አባላት ከቡራዩ ተነስተው 4 ኪሎ እስኪደርሱ በዝምታ ተመለከቱ?” ሲሉ ይጠይቃሉ፤ አቶ ስዩም፡፡  
ምሁሩ እንዲህ ይበሉ እንጂ የሰራዊቱ አባላት በእርግጥም ከቡራዩ ወደ 4 ኪሎ ቤተ መንግስት በቀጥታ መምጣታቸውን  ማረጋገጥ  አልተቻለም።  
በዚህ ጉዳይ ላይ ጥልቅ ምርመራና ፍተሻ ተካሂዶ የማስተካከያ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት በአፅንኦት የተናገሩት አቶ ስዩም፤ ብሶታቸውን ለማሰማት በዚህ መንገድ ወደ ቤተ መንግስት ያመሩትን የሰራዊት አባላት በህግ ተጠያቂ ለማድረግ መሞከር ግን ተገቢነት የለውም የሚል አቋም ያንጸባርቃሉ;፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ፤ ብሶታቸውን ሊተነፍሱ ወደ ቤተ መንግስት ያመሩትን የሰራዊት አባላት በተመለከተ በኢቴቪ ብቅ ብለው የተናገሩትን የሰማ ሰው ሁሉ፣ የቱንም ያህል ህገ ወጥ ድርጊት ፈጽመው ቢሆን እንኳን ከፑሽ አፕ የዘለለ፣ ጨከን ያለ እርምጃ ይወሰድባቸው የሚል ሃሳብ ላይሰነዝር ይችላል፡፡ በእርግጥ ትንሽ ተሃድሶ ቢጤ ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ በድጋሚ ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር ለመወያየት ወደ ቤተ መንግስት ጎራ እንዳይሉ።   
የፖለቲካ ተንታኙ ዶ/ር መንግስቱ አሰፋ በበኩላቸው፤ ውትድርና ከሌላው ሙያ በተለየ መልኩ ጥብቅ የስራ፣ የኑሮና የተልዕኮ ዲሲፕሊን ያለው ነው ይላሉ፡፡ “ወታደር ጥያቄ ሲኖረው በየደረጃው ላሉ አመራሮች  ማቅረብ ነው የሚጠበቅበት፤ ድርጊቱ ጥሩ አዝማሚያን አያሳይም” ብለዋል፡፡
“መንግስት በወታደር ዘንድ የሚከበር እንጂ በቀላሉ የሚደፈር መሆን የለበትም” ያሉት አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ያሬድ ጥበቡ በበኩላቸው፤ የሰራዊት አባላቱ ድርጊት የሚያመላክተው በሰራዊቱ ለቀናት ወይም ለሳምንታት የተካሄደ ምክክር መኖሩን ነው ይላሉ፡፡  
ውይይቱ የተካሄደውም በወታደሮቹ አስገዳጅነት ነው ብለው እንደሚያምኑ የተናገሩት አቶ ያሬድ፤ ወታደሮች ጥያቄ ሲኖራቸው መስመራቸውን ይዘው ባሉበት ይጠይቃሉ እንጂ በምንም አይነት ሁኔታ ወኪል መርጠው፣ ቤተ መንግስት ገብተው፣ ጥያቄ ማቅረብ ሊፈቀድላቸው አይገባም ነበር ብለዋል፡፡
“ከአሁን በኋላ በፈለጋቸው ሰአት እየመጡ ተመሳሳይ ትዕይንት እንደማያደርጉ ምን መተማመኛ አለ?” ሲሉ የሚጠይቁት አቶ ያሬድ፤ “ጠ/ሚኒስትሩና አመራሮቻቸው ሁኔታዎች እንዴት እዚህ ደረጃ እንደደረሱና መፍትሄ መሻት እንዴት እንዳልቻሉ፣ ራሳቸውን መፈተሽ አለባቸው ብለዋል፡፡
የወታደሮቹ ድርጊት በፑሽ አፕ የፎቶ ምስሎች የሚደበቅ ተራ ነገር ሳይሆን ኢትዮጵያ በየቀኑ እየተላመደች የመጣችው ስርአት አልበኝነት አንድ አካል ነው የሚል እምነት እንዳላቸው የገለፁት አቶ ያሬድ፤ የዶ/ር ዐቢይ አህመድ መንግስት፣ ሁለንተናዊ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
በእርግጥም ብሶታቸውን ለመናገር ቤተ መንግስት የገቡት የሰራዊቱ አባላት፤ ከጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ጋር ውይይታቸውን ሲጨርሱ ፑሽ አፕ እንዲሰሩ ተደርገዋል፤ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር። ጠ/ሚኒስትሩ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንን ባወያዩበት ወቅትም፣ ከጥቂት ወጣት ምሁራን ጋር ፑሽ አፕ መሥራታቸው አይዘነጋም፡፡ በመጨረሻም የሠራዊቱ አባላት፣ ከዶ/ር ዐቢይ ጋር ፎቶ ተነስተው ነው የተለያዩት፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሰራዊት አባላቱ ለፈጸሙት ድርጊት፣ በትላንትናው ዕለት፣ ህዝቡንና ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን ይቅርታ መጠየቃቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
 በክብር እንግድነት በተገኙት በምክትል ጠ/ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መስከረም 30 ቀን 2011 በሚሊኒየም አዳራሽ በድምቀት የተከፈተው 9ኛው አዲስ ቢውልድ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን ዛሬ ይዘጋል፡፡
በየትኛውም የአገር ዕድገት ኢኮኖሚ ላይ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው ያሉት ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሀገራችንን ለማዘመን ቁልፍ ከሆኑ ዘርፎች ከፍተኛ ካፒታል የሚጠይቅ፣ ከፍተኛ የሥራ ዕድል የሚፈጠርበትና ለሌሎች የልማት ፕሮግራሞች ስኬት መሰረት የሚሆነው ይኼው ዘርፍ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡ ዘርፉ፤ በርካታ የሆኑ ገንቢዎች፣ አልሚዎች፣ የግንባታ ግብአት አቅራቢዎች፣ የሥራ ተቋራጮችና ሌሎችም የሚሳተፉበት ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ማዕከል እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ ዘርፉን ለማዘመን በአገራዊ አቅም ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረግ እጅግ በጣም ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
ይህ ኤግዚቢሽን ለመንግሥት ከፍተኛ ተስፋ የሚያጭርና ተገቢ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው፣ በኮንስትራክሽን ግብአቶች አቅራቢዎችና አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ያተኮረ መሆኑ ነው ያሉት ም/ጠ ሚኒስትሩ፣ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በማመቻቸት፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የአገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአቶች፣ አምራቾችና የአገልግሎት ሰጪዎችን የበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
የቴክኖሎጂ ሽግግር የተሟላና ሙሉ የሚሆነው፣ ፋና ወጊዎችን በማበረታታት፣ ደረጃ በደረጃ በዓለም ላይ ተወዳዳሪ ማድረግ ሲቻል ነው፡፡ የአገር ውስጥ ግብአት አምራቾችና አቅራቢዎችን በጠንካራ የገበያ ትስስር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በኢንጂነሪንግ ፋብሪኬሽን አቅምን በመገንባት፣ ከልዩ ልዩ ከፍተኛ የትምህርት፣ የቴክኒክና የሙያ፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ተቋማት ጋር በማገናኘት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
መንግሥት የዜጎችን ፍላጎት በማስቀደም፣ ለወጣቱና ለመጪው ትውልድ የምትመች ኢትዮጵያን ገንብቶ ለማስረከብ፣ የተለያዩ ስትራቴጂዎችን ቀርፆ ተግባራዊ በማድረግ ላይ ይገኛል ያሉት የኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፤ የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ኢንዱስትሪውን ተወዳዳሪና ትርፋማ በማድረግ ሂደት ውስጥ የተደራጁ የሙያ ማኅበራትን በማበረታታት፣ የሙያ ሥነ ምግባርን በማስረፅ፣ መልካም ተሞክሮዎችን በማስፋት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር ለማሳለጥ፣ የግሉን ዘርፍ ጤናማ ፉክክር ለማዳበር ጥረት እያደረገ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ከ80 በላይ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪዎች፣ የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ቴክኖሎጂዎች አቅርቦት ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱ አምራቾች አቅራቢዎችና አልሚዎች የሚገኙበት ይህ ኤግዚቢሽን፤ በአገራችን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ እንደ ማነቆ የተቀመጠውን የአገር ውስጥ የኮንስትራክሽን ግብአቶች ችግር፣ ወጪና ጊዜ ቆጣቢ የኮንስትራክሽን እጥረት ለመቅረፍና የተሻለ ኢንዱስትሪ ለመፍጠር፣ ብዙ የልምድ ልውውጥና የቴክኖሎጂ ሽግግር የገበያ ትስስር የሚደረግበት ነው ብለዋል- ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ፡፡
ከ9ኛው የኮንስትራክሽን ግብአቶችና ቴክኖሎጂ ኤግዚቢሽን በተጨማሪ፣ 6ኛው አግሮፉድና ፓኬጂንግ እንዲሁም  የመጀመሪያው አዲ ፓወር ኤግዚቢሽኖችም ዛሬ ይዘጋሉ፡፡  

 የዛምቢያ መንግስት በአገሪቱ የትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ በተፈጸመ የ1.6 ሚሊዮን ዶላር ዝርፊያ ላይ ተሳትፈዋል ያላቸውን ከ80 በላይ ባለስልጣናት ከስራ ማገዱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአገሪቱ የትምህርት ሚኒስትር ቪንሰንት ሙዋሌ፤ ተዘርፏል ከተባለው የህዝብ ገንዘብ ጋር በተያያዘ ባለፈው ረቡዕ ለፓርላማ ባቀረቡት ሪፖርት፣ ባልተገባ የፋይናንስ አሰራር ዝርፊያው እንዲፈጸም አድርገዋል የተባሉ ከ80 በላይ ባለስልጣናት ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ ገበታቸው እንደታገዱና ጉዳዩ ተጣርቶ ወንጀለኞች ለህግ እንደሚቀርቡ አስታውቀዋል፡፡  
ለልማት የሰጠሁት እርዳታ ለባለስልጣናት የግል ጥቅም መዋሉ አበሳጭቶኛል ያለው የእንግሊዝ መንግስት፣ ጉዳዩ ተጣርቶ ዝርፊያውን የፈጸሙት ባለስልጣናት በህግ እስኪጠየቁና ከሙስና የጸዳ አሰራር እስኪቀየስ ድረስ በአለማቀፍ የልማት ክፍሉ በኩል ለዛምቢያ መንግስት ሲሰጥ ነበረውን እርዳታ ለጊዜው ማቋረጡን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
በዛምቢያ የህዝብን ገንዘብ እየዘረፉና እያጭበረበሩ ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ባለስልጣናት ቁጥር እየተበራከተ ነው ያለው ቢቢሲ፤ ባለፈው ወር ላይም ለድሃ ዜጎች ድጋፍ የተመደበ 4.3 ሚሊዮን ዶላር ከታለመለት ጉዳይ ውጭ እንዲውል አድርገዋል የተባሉት የአገሪቱ የማህበረሰብ ልማትና ጡረታ ሚኒስትር ኢምሪን ካባናሺ፣ በፕሬዚዳንት ኤድጋር ሉንጉ ትዕዛዝ ከስራቸው መባረራቸውን አስታውሷል፡፡

ባለፈው ረቡዕ በአለማቀፍ ደረጃ የአክሲዮን ገበያ ዋጋ ቅናሽ መከሰቱን ተከትሎ፣ የአለማችን 500 እጅግ ባለጸጋ ቢሊየነሮች በዕለቱ በድምሩ 99 ቢሊዮን ዶላር ያህል ኪሳራ እንዳጋጠማቸው ተነግሯል፡፡
ከአለማችን ባለጸጎች በዕለቱ ከፍተኛውን ኪሳራ ያስተናገዱት የአማዞን ኩባንያ መስራች አሜሪካዊው ቢሊየነር ጄፍ ቤዞስ ሲሆኑ፣ ባለጸጋው ረቡዕ እለት 9.1 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
በአለማቀፉ የአክሲዮን ገበያ ላይ በተከሰተው በዚህ ቀውስ ሳቢያ ከተጣራ ሃብታቸው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ የቀነሰባቸው የአለማችን ቢሊየነሮች 17 ናቸው ያለው ዘገባው፤ የአለማችን የቴክኖሎጂው ዘርፍ 67 ባለጸጎችም በድምሩ 32.1 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸውን አመልክቷል፡፡
በአንድ ቀን (ረቡዕ) ቢሊየነሮቿ በከፍተኛ ሁኔታ የከሰሩባት አገር አሜሪካ ናት ያለው ዘገባው፣ የአገሪቱ ቢሊየነሮች በድምሩ 54.5 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸውንም ገልጧል፡፡    ወላጆቿና ወዳጅ ዘመዶቿ ትዳር እንድትይዝ ነጋ ጠባ መወትወታቸው ያሰላቻት ኡጋንዳዊት የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሉሉ ጀሚማ፤ ከውትወታው ነጻ ለመውጣት በማሰብ ከሰሞኑ ከራሷ ጋር በይፋ ጋብቻ መፈጸሟን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በፈጠራ ጽሁፍ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቷን በመከታተል ላይ የምትገኘው ሉሉ ጀሚማ፤ ከሰሞኑ የ32ኛ አመት የልደት በአሏን ባከበረችበት ስነስርዓት ላይ በቬሎ ሽክ ብላ ከራሷ ጋር መጋባቷ ተነግሯል፡፡
ጀሚማ በጋብቻ ስነስርዓቱ ላይ ለታደሙት 30 ያህል እንግዶቿ ባደረገቺው ንግግር፣ የህይወቷ ተቀዳሚ አላማ ትምህርቷን በጥሩ ውጤት ማጠናቀቅና ወደ ስራ ገብታ ውጤታማ ተግባር መፈጸም እንጂ ትዳር መመስረት አለመሆኑን በመግለጽ፣ እንድታገባ የሚወተውቷትን ወላጆቿንና ወዳጅ ዘመዶቿን ለማስደሰት ስትል ከራሷ ጋር ለመጋባት መወሰኗን አስታውቃለች፡፡
“አባቴ ገና የ16 አመት ልጃገረድ እያለሁ ነበር የሰርጌ ዕለት የማደርገውን ንግግር አርቅቆ የሰጠኝ፡፡ እሱም ሆነ እናቴ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ትዳር የምይዝበትን ቀን በመናፈቅ ፈጣሪ ጥሩ ባል እንዲሰጠኝ ሲጸልዩልኝ ነው የኖሩት፡፡ እኔ ግን አላማዬ ትዳር አይደለም” ብላለች ጀሚማ፡፡
ጀሚማ ከራሷ ጋር ለተጋባችበት ሰርግ ያወጣቺው ወጪ፣ በነጻ ወዳገኘቺው አዳራሽ ለሄደችበት ትራንስፖርት የከፈለቺው 2.62 ዶላርና የቬሎ መግዣ ብቻ ነው ያለው ዘገባው፤እምር ድምቅ ያለቺባቸውን ጌጣጌጦች ከእህቷ በውሰት ወስዳ መጠቀሟን፤ የማስዋብና የማሰማመር ሃላፊነቱን አንድ ጓደኛዋ በነጻ እንደከወነችላት፣ ወንድሟ ደግሞ የኬክ ወጪውን እንደሸፈነላት አክሎ ገልጧል፡፡

Page 11 of 413