Administrator

Administrator

     ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በስልጣን ዘመናቸው የመጨረሻቸው የሆነውን ታላቁን የፕሬዚዳንቱ የነጻነት ሜዳይ ሽልማት ባለፈው ማክሰኞ ምሽት በዋይት ሃውስ በተካሄደ ስነስርዓት ለ21 ታዋቂ አሜሪካውያን አበርክተዋል፡፡
ኦባማ የእኔ ጀግና ያሏቸውና ታላቁን የነጻነት ሜዳይ ያጠለቁላቸው 21 አሜሪካውያን በተለያዩ መስኮች ለአገራቸውና ለህዝባቸው የጎላ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሲሆኑ  የፊልምና የመዝናኛ ዘርፍ ዝነኞች፣ ሳይንቲስቶች፣ ስፖርተኞች፣ በጎ አድራጊዎችና በሌሎች መስኮች የተሰማሩ መሸለማቸው ታውቋል፡፡  
“ሁሉም የዕለቱ ተሸላሚዎች በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ በግሌ ተጽዕኖ የፈጠሩብኝ ናቸው” ሲሉ ተሸላሚዎችን አድንቀዋል፤ ኦባማ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፡፡
ኦባማ የአሜሪካን ትልቁ የሲቪል ሽልማት  በክብር ካበረከቱላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪ ታዋቂ አሜሪካውያን መካከል፣ ከመዝናኛው ኢንዱስትሪ የፊልም ከዋክብቱ ቶም ሃንክስና ሮበርት ዲ ኔሮ፣ ከበጎ ምግባር ስራዎች ቢል እና ሚሊንዳ ጌትስ፣ ከስፖርት ካሬም አብዱል ጀባርና ማይክል ጆርዳን ይገኙበታል፡፡ ከዘንድሮ ተሸላሚዎች በእድሜ ትንሹ የ53 አመቱ የቀድሞው የቅርጫት ኳስ ተጫዋች ማይክል ጆርዳን ሲሆን፣ በዕድሜ ትልቁ  ተሸላሚ ደግሞ የ91 አመት የእድሜ ባለጸጋዋ ተዋናይት ሲስሊ ታይሰን ናቸው፡፡

ናሁሰናይ በላይ
(በአ.አ.ዩ የፖለቲካ ሳይንስ እና የፌደራሊዝም መምህር

ሹም ሽር መደረጉ፣ መንግስት የለውጥ ፍላጎት እንዳለው፣ ምልክት እንደማሳየት ነው፡፡ “የለውጥ ፍላጎት አለኝ፤ ፍላጎቴንም በዚህ በሹም ሽር እዩት” የሚል ምልክት ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን፣ ከገጠመን ችግር አንፃር ሲታይ የሚያስፈነጥዝ አይደለም፡፡
እርግጥ ነው፣ ያመጣው ነገር አለ፡፡ እውቀት እና ስራ መገናኘት አለባቸው የተባለ ይመስላል፡፡ እውቀትና ስልጣን ሲገናኙ፣ የተሻለ ነገር መስራት ይቻላል የሚል አቅጣጫ ለማሳየት ተሞክሯል፡፡ ይሄ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን መጠንቀቅ አለብን፡፡
ኢትዮጵያ ላይ የተከሰተው ችግር፣ የብዙ ነገሮች ድምር ውጤት ነው፡፡ የመንግስት ቅቡልነት ቀውስ ውስጥ የገባበት ነው፡፡ በጣም ጉልህ የስራ አጥነት ችግር አለ፡፡ እንግዲህ ከገጠመን ችግር አንፃር፣ የመንግስት ጥረት በሹም ሽር የሚያበቃ ከሆነ፣ ሌላ ራሱን የቻለ ችግር ነው የሚሆነው፡፡ ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም፣ ከአገሪቱ ችግር አንፃር ትንሽ ነው፡፡
የኢህአዴግ ድርጅቶችን ግምገማ በተመለከተ፣ እኔ ከግምገማዎቹ ብዙ አልጠብቅም፡፡ ኢህአዴግ ችግሩን በቅጡ ያወቀው አልመሰለኝም፡፡ አሁን የችግሩን ምልክቶች ነው እያሯሯጠ ያለው፡፡ በሽታውን ሳይሆን የበሽታውን ምልክቶች ነው እያከመ ያለው፡፡
በዚህ ሁኔታ አሚካሄድ ግምገማና ብወዛ፣ ትልቅ ለውጥ እንዲያመጣ አልጠብቅም፡፡ በእርግጥ፣ ለምሳሌ ኦሮሚያ ክልል ጥሩ የመሻሻል ምልክት ታይቷል፡፡ የተማረና አቅም ያለው፣ ወጣት አመራር ለመፍጠር ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል፡፡ በተቃራኒው በህውሓትና በብአዴን በኩል ሲታይ ደግሞ፣ ፍላጎቱ ያላቸው አይመስልም፡፡ ወንበሩን እንደርስት የያዙ ሰዎች፣ በዚያው እንዲቀጥሉ የሚያስቡ ይመስላል፡፡
ስለዚህ ኢህአዴግም መንግስትም፣ የችግሩን መሰረታዊ ባህሪ በቅጡ ሳይረዱ፣ ችግሩን ያክማል ብለው የሚያመጡት መድኃኒት፣ ችግሩን ከማከም ይልቅ የጎንዮሽ ጉዳት ያስከትላል የሚል ስጋት አለኝ። ዋናው የኢህአዴግ ችግር የሚመስለኝ፣ ችግሩን አለማወቁ ነው፡፡ ወይ ለማወቅ አለመፈለግ፣ አሊያም ለማወቅ አለመቻል፡፡
የፌደራል ስርአቱም ሆነ ህገ መንግስቱ፣ ችግር አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡ ፖለቲካው ህገ መንግስቱን መምሰል ስላልቻለ ይመስለኛል እዚህ ሁሉ ጣጣ ውስጥ የገባነው፡፡ በተለያዩ የመንግስት መዋቅሮች ውስጥ ሊኖር የሚገባው ህግንና ህግን ብቻ መሰረት ያደረገ አሰራር፣ ገና አልተፈጠረም። ይሄ የእገሌ ወይም የእገሊት ድክመት አይደለም፡፡ ግን አሁን የተፈጠረውን ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋር ያገናኙታል፡፡ ይሄ ተስፋን የሚያጨልም ነው፡፡
የፖለቲካ ስርአት ሊበላሽ የሚችለው፣ ከግለሰብ በመነጨ ችግር ብቻ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ስልጣን ሲያገኙ አይበላሹም ማለቴ አይደለም፡፡ የሚበላሹ ግለሰቦች ሁሌም የትም አገር ይኖራሉ፡፡ ዋናው ነገር፣ የፖለቲካ ስርዓቱ፣ ባለስልጣናት እንዳይበላሹ የሚቆጣጠር መሆኑና አለመሆኑ ላይ ነው፡፡ ችግሩን በዚህ መንገድ አይቶ ሳይንሳዊ ጥናትና ትንታኔ መስራት ካልተቻለ፣ “እንታደሳለን፤ ቃል እንገባለን” ማለት ብዙም አያስኬድም፡፡

አንድ የቻይና ተረት የሚከተለውን ይላል፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ንጉሥ ልጆቻቸውን ሰብስበው፣
“ልጆቼ፤ እስከዛሬ መቼም በክፉም በደግም መንበሬ ላይ ሆኜ ሳስተዳድር ታውቁኛላችሁ፡፡ አሁን እርጅናም እየመጣ ነው፤ ሆኖም ለአንዳችሁ መንግሥቴን እንዳወርሳችሁ፤ በማስተዳድር ጊዜ የሰራሁት ጥፋት ካለ ንገሩኝ፡፡ ከእናንተ መካከል ለማን ማውረስ እንዳለብኝ እንዳመዛዝን ይጠቅመኛል” አሉ፡፡
ልጆቹ እርስ በርሳቸው መተያየት ጀመሩ፡፡ ሀሳባቸው ተከፋፈለ፡፡ ከፊሎቹ ንጉሱን በማወደስ ወንበሩን ለማግኘት ቋመጡ፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ዕውነቱን ተናግረን ያሉትን ይበሉ አሉና ሀሳባቸውን ሰነዘሩ፡፡
1ኛው/ “ንጉሥ” ሆይ! እንደርሶ ያለ መሪ በዓለም ታይቶ አይታወቅም፡፡ ሁሉን እኩል ያያሉ። ለሁሉም ፍትሐዊ ነዎት፡፡ ሰብዓዊ መብት እንዳይረገጥ ሌት ከቀን ሲለፉ ኖረዋል፡፡ ከላይ እግዚአብሔርን ከታችም እርስዎን የሚፈራ ህዝብ ፈጥረዋል፡፡ እኛ ልጆችዎ በእርስዎ እንድንወጣ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደኖሩ ማንም አይጠራጠርም፡፡ አምላክ ዕድሜዎን ያርዝምልን እንጂ ውርሱ አይጠቅመንም” አለ፡፡
2ኛ/ “እርሶን የመሰለ ንጉሥ ፈፅሞ እግር እስኪነቃ ቢኬድ አይገኝም፡፡ በተለይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ባለዎት የዲፕሎማሲ ግንኙነት አንፃር ወደር የለዎትም” አለ፡፡
3ኛ/ “በጤና፣ በትምህርት፣ በመንገድ ሥራ፣ ያመጡልን የዕድገት ውጤት ከአህጉራችን አንደኛ እንድንሆን አድርጎናል፡፡ ፀሎታችን እድሜዎትን እንዲያረዝምልን ነው” አለ፡፡
በዚህ ዓይነት ስድስቱ ልጆቻቸው የንጉሡን ደግነትና ርህራሄ፣ በህዝብ ያላቸውን ተወዳጅነት እያሞገሱ ብዙ ተናገሩ፡፡ በመጨረሻ ግን ሰባተኛው ልጃቸው ተነስቶ መናገር ጀመረ፡-
“በበኩሌ ስልጣን አልፈልግም፡፡ ስለዚህ እውነትን መናገር እመርጣለሁ፡፡ ንጉሥ ሆይ! በመጀመሪያው የግዛት ዘመንዎ ደህና አስተዳደር ነበረዎ፡፡ ትዕግሥት ነበረዎ፡፡ ወገናዊነት አልተፈታተነዎትም ባይባልም፤ ከሞላ ጎደል ዲሞክራሲያዊና ለሰው አሳቢ ነበሩ፡፡ ፍርድ ቤቶቹም ቀናና ለተበደለ ፍትህን የሚሰጡ ነበሩ፡፡ መብቶች እንደሚከበሩና ሀብት በአግባቡ እንደሚዳረስም ቃል ገብተው ነበር፡፡ በመካከለኛው ዘመንዎ ሁሉም ነገር ፈሩን እየሳተ መጣ፡፡ በመጨረሻውና አሁን በደረስንበት የግዛት ወይም የግዝት ዘመንዎ ግን ነገሩ ሁሉ ተገለባበጠ፡፡ ሙስናና ጉቦ የዕለት ሁኔታ ሆነ፡፡ ቁጥጥር ጠፋ፡፡ እንዲያውም አመራሮችም ሳይቀሩ ተዘፈቁበት፡፡ “የአሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” የሚለው ምሳሌ በዐይን ታየ፡፡ እርሶም እጅዎን ሰብስበው ተቀመጡ፡፡ የአስተዳደር ብልግና የማያስጠይቅ መሰለ፡፡ ሹም ሽር ቢያካሂዱም ቦታ መለዋወጥ እንጂ ሥርዓትዎ ስላልተለወጠ ከድጡ ወደ ማጡ መኬድ ቀጠለ፡፡ እንደ እርሶ ዕድሜ ማርጀት ሁሉ ሥርዓቱም እያረጀ ነው፡፡ “አዲስ ወይን በአሮጌ ጋን” ከመሆኑ በስተቀር ለውጥ አልተጠመቀም፡፡ አልታየም፡፡ አሁንም ሳንዋሽ ዕውነቱን አውጥተን ካልተነጋገርን መሸፋፈኑ አይጠቅመንም፤ ንጉስ ሆይ!” አለ፡፡
ንጉሡም፤
“በመጀመሪያ የተናገራችሁት ልጆቼ፤ ያሞገሳችሁኝንም፣ ዕድሜ የተመኛችሁልኝንም አመሰግናችኋለሁ፡፡ ከእናንተ ጋር በተሰበሰብን ጊዜ ሁሉ ስሰማው የኖርኩት ነው፡፡ የመጨረሻው ልጄ የተናገርከው ነገር ግን፤ ዕውነተኛው መልካችን ነው፡፡ ከፍተኛው ምሥጋናም የሚገባህ ላንተ ነው። መንግስቴንም የማወርሰው ላንተ ነው! ምክንያቱም አገር ለመለወጥ የምትችል አንተ ነህ!” ብለው አሰናበቷቸው፡፡
*      *     *
“ጅላጅል ምላስ ብቻ ናት
ማሞካሸት የማይደክማት
ቀን አዝላ ማታ እምታወርድ
ንፉግን ልመና እምትሰድ!”
ይለናል ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን፡፡ አስመሳዮችና አድር ባዮችን ተማምነን፤ መልካም የሰራንና የተሻለ አቋም ላይ ያለን ከመሰለን፤ ስህተታችን ከዚያ ይጀምራል፡፡ ከቶም መልካም አስተዳደር በሙገሳ እንደማይገኝ ያለፉት አመታት በማያወላዳ ሁኔታ አረጋግጠውልናል፡፡ መሸነጋገል እንደማያዋጣም ተገንዝበናል፡፡ ዲሞክራሲ፣ ፍትህ፣ የተጠያቂነት ስርዓት፣ ግልፅነት፣ የማንነትና የባለቤትነት ጥያቄ፣ የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የሲቪክ ማህበራት ማደራጀት፣ መመሪያዎችን በለበጣ ሳይሆን ከልብ የመተግበር አሰራር፣ ወዘተ ከአፍ አልፎ በስራ የሚገለጥበት፤ በተስፋና በዱቤ ሳይሆን “እጅ - በጅ ፍቅር እንዲደረጅ” የሚባልበት፣ እንዲሆን ከተፈለገ፤ ግምገማዎች ሀቅን የተንተራሱ፣ መሬት የነከሱ እንዲሆኑ፤ ከልብ ማመን ግድ ነው! መገናኛ ብዙኃን ተዓማኒ የሚሆኑት የመንግሥት ደጃፎች መረጃ ለመስጠት ክፍት ሲሆኑ ነው፡፡ የመንግስት ሚዲያዎች እንዳይደመጡና እንዳይነበቡ የሚሆኑት … የማጋነኛ መድረኮች ሲሆኑና ዕውነት - ጠለቅ ሳይሆኑ፣ “የጌታዬ ቃል የእኔ ቃል” በሚል መርህ ስለሚጓዙ ነው፤ ለማለት ይቻላል፡፡
“ለመቶ አምሳ ጌታ
ስታጠቅ ስፈታ
ነጠላዬ
አለቀ በላዬ”
ማለት የዱሮ ፈሊጥ ይምሰል እንጂ “የሆድ የሆዳችንን እንነጋገር” በሚለው ህዝብ፣ በምሁሩ፣ በነጋዴው፣ በተማሪው፣ በዜጋው ሁሉ የሚብሰለሰለው ሀሳብ ይሄንኑ ፈሊጥ የሚገልጥ ነው፡፡ ግምገማዎች ከመፈራራት፣ ከእከክልኝ ልከክልህ፣ ከአሞግሰኝ ላሞግስህ፣ ከሾሜሃለሁ ትሾመኛለህ/ትክሰኛለህ፣ ከ “ይሄን ተናግረህ ሰው አያረጉህም” አስተሳሰብ፣ ካልፀዱ ዋጋቸው አናሳ ነው፡፡ ወይም አክሳሪ ነው፡፡ በጥናትና በፅናት መካከል ገደል አከል ልዩነት አለ፡፡ አንዱ ዘዴ፣ አንዱ መስዋዕትነት ጠያቂ ነው፡፡ የህዝብ ብሶት አራምባ፣ የግምገማው መንፈስ ቆቦ ከሆነ ውጤቱ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ነው፡፡ ያልተዘራ አይታጨድምና እናስብበት፡፡ በየግምገማው አድርባዮች ዥዋዥዌያቸውን ከቀጠሉ፣ አመራሮች ከአንገት በላይ “ተሳስተን - ነበር” ማለቱን እንደ አዘቦት ሰላምታ ከለመዱት፣ የበታች ምንዝሩም “ይሄ ቃል ተገብቶልን አልተፈፀመልንም” ማለቱን የዕለት ፀሎት ያህል መደጋገሙን እንጂ ሰርንቆና ገትቶ ተግባራዊነቱን ካልተቆጣጠረ፣ ወጥሮም ካልታገለ፣ ከህዝብ እሮሮና በደል አንፃር ስናየው፣ “ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ” ይሆናል፡፡ እናስብበት፡፡ ግምገማዎች ወደ አደባባይ ተግባር ያምሩ እንጂ፤ የአዳራሽ ቴያትር ሆነው አይቅሩ!

 ጃኪ ቻን ከ56 አመታት በኋላ ኦስካር ተሸለመ፤
              ከ200 በላይ ፊልሞችን ለእይታ አብቅቷል
    የ2016 የኖቤል የስነጽሁፍ ተሸላሚው አሜሪካዊው ድምጻዊና የሙዚቃ ግጥም ጸሃፊ ቦብ ዳይላን፣ በመጪው ታህሳስ ወር መግቢያ በስቶክሆልም በሚከናወነው የኖቤል ሽልማት ስነስርዓት ላይ እንደማይገኝ ባለፈው ረቡዕ አስታውቋል፡፡
የ75 አመቱ ቦብ ዳይላን፣” በስነስርዓቱ ላይ ተገኝቼ ሽልማቱን ብቀበል ደስ ይለኝ ነበር፤ ሆኖ ግን ሌሎች ፋታ የማይሰጡ ጉዳዮች ስላሉብኝና ስራ ስለበዛብኝ ልገኝ አልችልም” ሲል ለኖቤል አካዳሚ በላከው ደብዳቤ ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡ የሽልማት አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ውሳኔ እንደሚያከብር ገልጾ፣ እንዲህ ያለው ውሳኔ ያልተለመደ ቢሆንም ሽልማቱን በአካል ተገኝቶ ባለመቀበል፣ ቦብ ዳይላን የመጀመሪያው ሰው አለመሆኑን ጠቁሞ፣ ድምጻዊውን በመወከል ሽልማቱን የሚቀበለው ሰው ማንነት ገና አለመታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
አካዳሚው የቦብ ዳይላንን ተሸላሚነት ይፋ ያደረገው ከአንድ ወር በፊት ቢሆንም፣ ተሸላሚውን ለማግኘት እጅግ ተቸግሮ መቆየቱና ዳይላንም ባልተለመደ መልኩ ሽልማቱን በተመለከተ ለሳምንታት ምንም አይነት አስተያየት አለመስጠቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ጉዳይ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡ በተያያዘ ዜና ላለፉት 56 አመታት በፊልሙ ኢንዱስትሪ ውስጥ የቆየውና አለማቀፍ ተወዳጅነትን ያተረፈው የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ሳምንት መቀበሉ ተዘግቧል፡፡ ጃኪ ቻን በየአመቱ በፊልሙ ኢንዱስትሪ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሙያተኞች የሚሰጠውን ገቨርነርስ አዋርድ የተባለውን የኦስካር የክብር ሽልማት ባለፈው ቅዳሜ በሎሳንጀለስ በተካሄደ ስነስርዓት መቀበሉን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
በረጅም አመታት የሙያ ቆይታው ከ200 በላይ ፊልሞችን በተዋናይነትና በዳይሬክተርነት ለእይታ ያበቃው የ62 አመቱ የፊልም ተዋናይ ጃኪ ቻን፣ አካዳሚ ኦፍ ሞሽን ፒክቸርስ አርትስ ኤንድ ሳይንስስ ባዘጋጀው ስነስርዓት ላይ ተገኝቶ ሽልማቱን ተቀብሏል፡፡ ጃኪ ቻን በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረገው ንግግር፤ በሽልማቱ መደሰቱን ገልጾ፣ ከ56 አመታት በላይ በዘለቀው የፊልም ስራ ቆይታው፣በርካታ ፈተናዎችን እንዳለፈ በማስታወስ፣ ለወደፊትም ሌሎች አዳዲስ ፊልሞችን መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡

  ከታክስ በፊት ከ428 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ
       ሕብረት ባንክ ያለፈው ዓመት 2008 (ጁን 30 2016) የተጠናቀቀው በጀት ዓመት በአገሪቱ ላሉ ባንኮች ፈታኝ ሆኖ ቢያልፍም፣ ባንኩ ባደረገው ያላሰለሰ ጥረት አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ 13.63 ቢሊዮን ብር በማድረስ ከግል ባንኮች 4ኛ ደረጃ ሊይዝ መቻሉን አስታውቋል፡፡
ባንኩ የባለ አክሲዮኖች 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ከትናንት በስቲያ በሂልተን ሆቴል ያደረገ ሲሆን የባንኩ የዲሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዛፉ እየሱስወርቅ ዛፉ ባቀረቡት ዓመታዊ ሪፖርት፣ የባንኩ ጠቅላላ ገቢ ከቀደመው ዓመት  ጋር ሲነፃፀር 25 በመቶ ዕድገት ማሳየቱና፣ ከግብር በፊት የተኘው ትርፍም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 358.2 ሚሊዮን ብር ጋር ሲተያይ ወደ 428.5 ሚሊዮን ብር ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ከቀደመው ዓመት (2007) ከነበረው 11.7 ቢሊዮን ብር 16.2 በመቶ ጭማሪ በማሳየት 13.63 ቢሊዮን ብር መድረሱን የጠቀሱት ሊቀመንበሩ፣ በብድር የተሰጠው ገንዘብ ከቀደመው  ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.7 ቢሊዮን ብር ወይም የ24.4 በመቶ ዕድገት በማሳየት 8.53 ቢሊዮን ብር በመድረሱ የተገኘው ውጤት አመርቂ ነው ብለዋል፡፡
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የአገሪቷ ወጪ ንግድ በመቀነሱ ከዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎት ዘርፍ የተገኘው ገቢ ከካቻምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ ቀንሷል፡፡ አምና ከዓለም አቀፍ ባንክ ዘርፍ የተገኘው ገቢ 2.98 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን የበጀት ዓመቱ 4.71 በመቶ ቀንሶ 2.84 ቢሊዮን ዶላር ወይም 400.9 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ይህም የባንኩን አጠቃላይ ገቢ 23 በመቶ እንደሚሸፍን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አያደር ሲብስበት እንጂ ሲሻሻል የማይታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለሥራቸው እንቅስቃሴ ስጋት መፍጠሩን የጠቀሱት አቶ ዛፉ፤ ስጋቱን ግምት ውስጥ በማስገባት ከዚህ በፊት ከነበረው በተጨማሪ ከሁለት ዓለም አቀፍ የካርድ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ማለትም ከቪዛ ኢንተርናሽናልና ከቻይና ዩኒየን ፔይ ጋር መሥራት ጀምረናል፡፡ የእነዚህ ድርጅቶች የባንኩ አጋር መሆን ለንግድ ተጓዦችና ቱሪስቶች የምናቀርበውን አገልግሎት ምቹና ቀልጣፋ ከማድረጉም በላይ የውጭ ምንዛሬ ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
ባንኩ ጁን 30 2016 በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ በተከፈለ አክሲዮን ላይ 25 በመቶ የትርፍ ክፍያ አንዲደረግ የዲሬክተሮች ቦርድ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 17.3 ቢሊዮን፤ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል 1.25 ቢሊዮን ብር ሲሆን ባንኩ 2,998 ባለአክሲዮኖች እንዳሉት ታውቋል፡፡
ተደራሽነትን ከማስፋፋት አኳያ ባንኩ 161 ቅርንጫፎች ሲኖሩት፣ የሰው ኃይሉም 3,123 ደርሷል፡፡ በበጀት ዓመቱ 438 ሠራተኞ የተቀጠሩ ሲሆን ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲተያይ በ289 ሰራተኞች ብልጫ አለው፡፡ 149 ሠራተኞች ደግሞ ባንኩን ለቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚካሄድ የአለም ፖስታ ህብረት ልዩ ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠች ሲሆን ከ1 ሣምንት በላይ በሚዘልቀው ጉባኤ ከ3 ሺህ በላይ እንግዶች ከዓለም ዙሪያ እንደሚሳተፉ  ታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ግደይ ገ/ዮሐንስ ከትላንት በስቲያ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ በቅርቡ በቱርክ በተካሄደው 26ኛው የአለም የፖስታ ህብረት ኮንግረስ ላይ ኢትዮጵያ ከ2 አመት በኋላ የሚደረገውን የህብረቱን ልዩ ጉባኤ እንድታዘጋጅ በከፍተኛ ድምፅ መመረጧን አስታውቀዋል፡፡
ጉባኤው በኢትዮጵያ መካሄዱ የሃገሪቱን ገፅታ ለመገንባት፣ ሃገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እንድታገኝ፣ በአለማቀፍ ቱሪዝም አገሪቱን ለማስተዋወቅ ሃገሪቱ በፖስታ አገልግሎት ያላትን አቅም ለዓለም ለማሳየት ይጠቅማል ተብሏል፡፡
በጉባኤው ላይ ከ192 አባል ሃገራት የተውጣጡ የፖስታ አገልግሎት ሚኒስትሮች፣ ዋና ዳይሬክተሮች፣ የፖስታ ኤክስፐርቶች፣ ታዛቢዎች፣  አለማቀፍ ተቋማትና ህብረቶች ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በፖስታ አገልግሎት ኢትዮጵያ 4 አለማቀፍ እውቅናዎች ማግኘቷን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ በአገልግሎት ጥራት የ ‹‹ቢ›› ደረጃ ማግኘቱን አስታውቀዋል፡፡
በአሁን ወቅት የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት 16 ሺህ ያህል የአገልግሎት መስጫ ማዕከላትን ለመክፈት እየተንቀሣቀሰ መሆኑን የጠቀሡት አቶ ግደይ፤ በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥም ለግለሰብ ደንበኞች የቤት ለቤት አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል እቅድ ተይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡
ድርጅቱ አምና ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱንና በዘንድሮ ዓመትም ወደ 1.2 ቢሊዮን ብር ገደማ ብር ለማግኘት ማቀዱን ስራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ የፖስታ ድርጅት ዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂዎችን ለመወዳደር የተለያዩ ስልቶችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመው፤ በየአመቱም ገቢውን በከፍተኛ መጠን እያሣደገ ለመጓዝ እንዳቀደ ተናግረዋል፤ አቶ ግደይ፡፡

“ስፒል ጫማ ካደረገች ዝንጀሮ” እስከ “ትራምፕ ፊርማ”

         በአፍ ይጠፉ፣ በለፈለፉ
በዌስት ቨርጂኒያ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የክሌይ ከተማ ከንቲባ የሆኑት ቤቨርሊ ዋሊንግ እና ክሌይ ካውንቲ ኮርፖሬሽን የተባለ ድርጅት ዳይሬክተር የሆኑት ፓሜላ ቴለር፣ ከሰሞኑ የሚያጠፋቸውን አጉል ነገር በፌስቡክ ገጻቸው በኩል ለፈለፉ፡፡
መጀመሪያ...
“ስፒል ጫማ ያደረገች ዝንጀሮ!...” ሲሉ በገደምዳሜ ወረፏት ቴለር - የክቡር ፕሬዚዳንቱን ሚስት ሚሼል ኦባማን፡፡ ይሄን የፌስቡክ ዘለፋ ያነበቡት የከተማዋ ከንቲባ ዋሊንግም፣ ዘለፋውን የሚደግፍ አስተያየት ዝቅ ብለው አሰፈሩ፡፡
ዳይሬክተሯና ከንቲባዋ በቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ላይ እንደዋዛ የሰነዘሩት ዘለፋ፣ በፍጥነት ከፌስቡክ ወደ መሬት ወርዶ አሜሪካውያንን ክፉኛ ያስቆጣ የዘረኝነት ንግግር ሆነ፡፡ ብዙዎች በዳይሬክተሯ ዘለፋና በከንቲባዋ ምላሽ በንዴት ጦፉ፡፡ የሁለቱ ሰዎች የዘረኝነት ፖስት ያስቆጣቸው አሜሪካውያን፣ በድረገጽ አማካይነት በጀመሩትና ሁለቱም ሴቶች ከስራቸው እንዲባረሩ በሚጠይቀው የፊርማ ማሰባሰብ ዘመቻ፣ ከ170 ሺህ በላይ ሰዎች ፊርማቸውን አሰፈሩ፡፡
ዳይሬክተሯ እና ከንቲባዋ በሁኔታው እጅግ ደነገጡ። ሁለቱም ያንን ጦሰኛ ጽሁፍ ከፌስቡክ ገጻቸው ላይ ቢሰርዙትም፣ ቀድሞ በሺህዎች ተባዝቶ ምድረ ፌስቡክን አዳርሶት ነበርና፣ እንዳሰቡት አላመለጡም፡፡ በርካታ አሜሪካውያን ክፉኛ ያብጠለጥሏቸው ያዙ፡፡
ዳይሬክተሯ ሊያስተባብሉ ሞከሩ፡፡
“ለማለት የፈለግሁት አልገባችሁም!... እኔ እኮ ስፒል ጫማ ያደረገች ዝንጀሮ ያልኩት ሚሼልን ሳይሆን...” በሚል የጀመሩትን ማስተባበያ የሚቀበላቸው አላገኙም፡፡
ከንቲባዋም ዘረኝነትን የማራመድ ሃሳብ እንደሌላቸው በመግለጽ፣ ለሆነው ነገር ሁሉ ይቅርታ ቢጠይቁም፣ ጆሮ እሚሰጣቸው አልተገኘም፡፡
በስተመጨረሻም...
ከንቲባዋ ባለፈው ሰኞ በገዛ ፈቃዳቸው ስራ መልቀቃቸውን የሚገልጽ ደብዳቤ ለከተማዋ ምክር ቤት አስገቡ፡፡ ዳይሬክተሯም ከስራ መባረራቸውን የሚገልጽ አስደንጋጭ ደብዳቤ ደረሳቸው - ይላል ቢቢሲ ባወጣው ዘገባ፡፡
የራሷ ሲያርባት የሰው ያማሰለቺው ቱርክ
መንበረ መንግስቴን ለመንጠቅ አሲራችኋል በሚል ከመቶ ሺህ በላይ ዜጎቿን ከስራ በማባረር፣ ... ሺህ ያህሉን በጅምላ እያፈሰች ወደ ወህኒ በመወርወር፣ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማዋከብ የአለም መነጋገሪያ የሆነቺው ቱርክ፤ የራሷን ጉዳይ መላ መምታት ትታ፣ ወደ አሜሪካ ዞር አለችና የሰሞኑ ተቃውሞ ያሰጋኛል አለች፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት ማክሰኞ እንደዘገበው፣ ለተቃውሞ የወጡ ዜጎቿን ማሰርና መግደል የማይታክታት ቱርክ፣ በትራምፕ ላይ የተጀመረው ተቃውሞ ሊባባስ ይችላልና አደራችሁን ወደዚያ ድርሽ እንዳትሉ ስትል ዜጎቿን አስጠንቅቃለች። አሜሪካ በቱርክ መዲና ኢስታምቡል የሚገኙ የቆንስላ ሰራተኞች የሆኑ ዜጎቿን፣ የሽብር ጥቃት ሰለባ እንዳትሆኑ ወደ አገራችሁ ተመለሱ ስትል በተደጋጋሚ ማስጠንቀቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ የቱርክ መንግስትም ለአሜሪካ ምላሽ ለመስጠት፣ ወግ ደርሶት ለዜጎቹ የማስጠንቀቂያ መልዕክት ማስተላለፉን ገልጧል። የቱርክ መንግስት ከሰሞኑ ባወጣው በዚህ መግለጫ፣ በአሜሪካ የሚገኙና ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ያቀዱ ዜጎቹን፣ የጸረ-ትራምፕ ተቃውሞው ሰለባ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ ማለቱንም አስረድቷል፡፡
የትራምፕ ፊርማ ሲነበብ
“የስልጣን ጥም ያንገበገባቸው ሰው ናቸው!...” አለች ትሬሲ፡፡
እንግሊዛዊቷ ትሬሲ ትሩሴል፣ ስለ ዶናልድ ትራምፕ ነው እንዲህ በእርግጠኝነት ያወራቺው፡፡
ዘ ኢንዲፔንደንት እንደዘገበው፣የብሪቲሽ ኢንስቲቲዩት ኦፍ ግራፎሎጂስትስ ባልደረባ የሆነቺው ትሬሲ ትሩሴል፣ ከሰሞኑ በአነጋጋሪው ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባህሪ ላይ ጥናት ድርጋለች። እሷና ባልደረቦቿ እንደሚያደርጉት፣ ጥናቷን የሰራቺው በትራምፕ የእጅ ጽሁፍ እና ፊርማ ላይ ነበር። የትራምፕን ፊርማ እና የእጅ ጽሁፍ አጣጣል በትኩረት ስታጤን የሰነበተቺው ትሬሲ፣ ከሰሞኑ ብቅ አለቺና እንዲህ አለች...
“ፊርማቸውን ልብ ብዬ ሳጤነው፣ ትራምፕ የስልጣን ጥም የሚያንገበግባቸው ሰው እንደሆኑ አረጋግጫለሁ!...”
እንዲህ ብላም አላበቃችም፡፡
የማይጨበጥ ምኞት የሚያጠቃቸው ትራምፕ፣ ምንም እንኳን ሃይለኝነት ቢጠናወታቸውም በተለይ ለቤተሰባቸው ጥላ ከለላ መሆን የሚያስደስታቸው ሰው እንደሆኑ ከፊርማቸው መረዳት መቻሏን ተናግራለች፡፡ እምብዛም ሌሎችን እንደማያደምጡና በድርድር ወቅት ፈርጠም ማለት የሚቀናቸው እንደሆኑም ገልጻለች፡፡
ዙክበርግ እንደ ጲላጦስ
ቀጣዩዋ የአሜሪካ መሪ እንደሚሆኑ ብዙዎች በልበ ሙሉነት ቢናገሩላቸውም ያልተሳካላቸው ሄላሪ ክሊንተን፣ ባልታሰበ መልኩ ለመሸነፋቸውና ያልተጠበቁት ዶናልድ ትራምፕ ለመመረጣቸው ብዙ ምክንያቶች መጠቀሳቸው እንደቀጠለ ነው፡፡
ሁሉም የየራሱን ሰበብ ሲሰነዝር ታዲያ፣ ለሄላሪ መሸነፍ ምክንያቱ ፌስቡክ ነው የሚሉም አልታጡም፡፡
በርካታ አሜሪካውያን ፌስቡክ ትራምፕ እንዲመረጥ የራሱን ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለው እንደሚያስቡ የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፣ በሄላሪ ዙሪያ ያልተጨበጡ አሉባልታዎችን በማናፈስ ተወዳጅነቷን ቀንሶታል በሚል ፌስቡክን ማብጠልጠል የያዙ እንደበረከቱ ገልጧል፡፡
ምርጫው ጥቂት ቀናት ሲቀሩት፣ በፌስቡክ ከ560 ሺህ ጊዜ በላይ ሼር የተደረገውንና የሄላሪን የኢሜል ቅሌት ሚስጥር ያወጣው የኤፍቢአይ መርማሪ ሞቶ እንደተገኘ ዘ ዴንቨር ጋርዲያን ዘገበ የሚለውን ጽሁፍ ለአብነት የሚጠቅሱት እነዚህ አሜሪካውያን፣ ቆየት ብሎ ግን ዘ ዴንቨር ጋርዲያን የተባለ ጋዜጣ እንደሌለ መረጋገጡንና መረጃው ሄላሪን ለማጥላላት ሆን ተብሎ የተሰራጨ እንደሆነ ይጠቁማሉ፡፡
ለትራምፕ ድል እና ለሄላሪ ሽንፈት ምክንያት ሆኗል በሚል ፌስቡክን የሚወነጅሉ መበራከታቸውን ተከትሎ ታዲያ፣ የኩባንያው መስራችና ባለቤት ማርክ ዙክበርግ፣ ከሰሞኑ አደባባይ ወጥቶ እንደ ጲላጦስ “ከደሙ ንጹህ ነኝ” ሲል በይፋ ማስተባበሉን ዘገባው ገልጧል፡፡
“ፌስቡክ ትራምፕ እንዲያሸንፍ ረድቶታል ብሎ መናገር የማይመስል ነገር ነው!... ሰዎች ለማን ድምጻቸውን እንደሚሰጡ የሚወስኑት፣ ተጨባጭ የህይወት ልምዳቸውን መሰረት አድርገው ነው!...” ብሏል ዙክበርግ፡፡
ትራምፕ እና ሂትለር ምን እና ምን ናቸው?...
ታሪካዊው ምርጫ፣ በታሪክ መምህሩ ታሪክ ላይ የራሱን አሻራ ጣለ ይላል፤ ዘ ቴሌግራፍ፡፡
የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ፣ ላለፉት 40 አመታት በካሊፎርኒያው ማውንቴን ቪው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተግተው ታሪክ ባስተማሩት መምህር ፍራንክ ናቫሮ ላይ በተለየ መልኩ ቀጥተኛ ተጽዕኖ እንደፈጠረ ዘገባው ያስረዳል፡፡ መምህሩ ሰሞኑንም እንደወትሯቸው ታሪክ ሊያስተምሩ ወደ ክፍል ገቡ፡፡
ማስተማርም ጀመሩ፡፡ በመሃል ላይ ግን፣ የሚያስተምሩትን ርዕሰ ጉዳይ በምሳሌ ማስደገፍ ነበረባቸው፡፡ ምሳሌ ፈለጉ። አገኙ። እንደዋዛ ጉዳያቸውን በምሳሌያቸው እያዋዙ ለደቀመዝሙራናቸው ማስረዳት ቀጠሉ፡፡
የዕለቱ የታሪክ ትምህርት ክፍለ ጊዜ ተጠናቀቀና፣ መምህር ናቫሮ ተማሪዎቻቸውን ተሰናብተው ከክፍል ወጡ፡፡
ከቀናት በኋላ...
እኒሁ መምህር ያልጠበቁት ነገር ገጠማቸው። የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ከተማሪዎች ወላጆች ቅሬታ እንደቀረበባቸው ነገራቸው፡፡ የቅሬታውን ሰበብ ለማወቅ ጓጉተው ሲጠይቁ ታዲያ፣ ከቀናት በፊት ሲያስተምሩ የሰጡት ምሳሌ መሆኑ ተነገራቸው፡፡ ደንግጠው ሊያስታውሱ ሞከሩ፡፡
እውነት ነው፡፡ መምህሩ በዕለቱ ታሪክ ሲያስተምሩ በሰጡት ጦሰኛ ምሳሌ፣ ተመራጩን ዶናልድ ትራምፕ እና የናዚውን ጨፍጫፊ አዶልፍ ሂትለርን እያነጻጸሩ ሲያስተምሩ ነበር። ሁለቱም በምርጫ ለማሸነፍ ባደረጓቸው ቅስቀሳዎች ለአናሳዎች ያላቸውን አመለካከትና የዘረኝነት መንፈሳቸውን ማንጸባረቃቸው እንደሚያመሳስላቸው፤ ሁለቱም ዳግም ታላቅ ስለማድረግ ቃል መግባታቸው አንድ እንደሚያደርጋቸው ለተማሪዎቻቸው አስረድተው ነበር፡፡
በመሆኑም ትራምፕን ከሂትለር ጋር ማመሳሰል አግባብ አይደለም በሚል ተወነጀሉ፤ መምህሩ፡፡
“እኔ የፈለግኩት እንኳን፣ የ20ኛውን መቶ ክፍለ ዘመን ታሪክና አሁን እየሆነ ያለውን ታሪክ ለማስተሳሰር እንጂ ታላቁን መሪያችንን ከዚያ ሰው በላ ጋር ለማመሳሰል አልነበረም!...” በማለት የልባቸውን ተናግረው ለማስተባበል ሞከሩ፡፡
የሚሰማቸው አልተገኘም - “ላልተወሰነ ጊዜ ከስራ ታግደሃል!...” ተባሉ፡፡
ይህን የሰሙ ከ30 ሺህ በላይ አሜሪካውያን ባሰባሰቡት ፊርማ፣ መምህሩ ምህረት ተደርጎላቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ የትምህርት ቤቱን አስተዳደር መጠየቃቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ ከቀናት እገዳ በኋላ ባለፈው ረቡዕ ወደ ስራቸው እንዲመለሱ እንደተፈቀደላቸው ገልጧል፡፡

እስከ 15 አመት በሚደርስ እስር ሊቀጡ ይችላሉ
     የሩስያ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሌክሲ ኡሊካየቭ፣ በ2 ሚሊዮን ዶላር ሙስና መከሰሳቸውንና በፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትዕዛዝ ባለፈው ማክሰኞ ከስልጣናቸው መነሳታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ የሙስና ተግባራትን እንደሚፈጽሙ የሚያመላክቱ መረጃዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ጉዳዩን የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ በግለሰቡ ላይ ለወራት የስውር ክትትልና ስለላ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው ሰኞ ሮዝኒፍት ከተባለው የአገሪቱ ቁጥር አንድ የነዳጅ ኩባንያ ባለስልጣናት፣ 2 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውንም ገልጧል፡፡
ማክሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረቡት የ60 አመቱ ኡሊካየቭ፣ በሮዝኒፍትና በባሽኔፍት የነዳጅ ኩባንያዎች መካከል በተፈጸመ ግዢ ስልጣናቸውን ተጠቅመው ያለ አግባብ ላሳለፉት ውሳኔ 2 ሚሊዮን ዶላር ጉቦ ተቀብለዋል ተብለው የተወነጀሉበትን የሙስና ድርጊት አልፈጸምኩም ብለው መከራከራቸውን የዘገበው ሮይተርስ በበኩሉ፤ ጉዳዩን በመመርመር ላይ የሚገኘው የሞስኮ ፍርድ ቤት፣ ተከሳሹ ሚኒስትር እስከ መጪው ጥር ወር አጋማሽ በቤት ውስጥ የቁም እስር እንዲቆዩ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስነብቧል፡፡
ሚኒስትሩ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ እስከ 15 አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊጣልባቸው እንደሚችል የጠቆመው ዘገባው፣ ግለሰቡ እ.ኤ.አ ከ1991 ወዲህ በስልጣን ላይ እያሉ ክስ የተመሰረተባቸው የመጀመሪያው የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደሆኑም አስታውሷል፡፡
ላለፉት 3 አመታት በኢኮኖሚ ሚኒስትርነት ያገለገሉት ኡሉካየቭ፣ በፕሬዚዳንት ፑቲን ትዕዛዝ ከስልጣን መነሳታቸውን ተከትሎ፣ በምክትል ሚኒስትርነት ሲሰሩ የቆዩት የቭጌኒ የሊን በጊዚያዊነት በቦታው ላይ  መሾማቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

በብሩንዲ 600 ሺህ ዜጎች የምግብ እጥረት ገጥሟቸዋል
     በሰሜን ምስራቃዊው የናይጀሪያ አካባቢ የሚኖሩ 75 ሺህ ያህል የአገሪቱ ህጻናት አስፈላጊው ፈጣን እርምጃ ካልተወሰደ በመጪዎቹ ጥቂት ወራት ውስጥ በርሃብ ሊያልቁ የሚችሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታወቀ፡፡
በተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ፒተር ሉንበርግን ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው፣ በመጪው የፈረንጆች አመት 2017 በአካባቢው የሚኖሩ 14 ሚሊዮን ሰዎች የሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን  ከእነዚህም መካከል 400 ሺህ ያህሉ ህጻናት ናቸው፡፡ፒተር ሉንበርግ አክለውም ድርጅቱ የሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግ አደጋውን ለመቀልበስ የሚያስችል በቂ ገንዘብ እንደሌለው ማስታወቃቸውንና አለማቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ አሳሳቢ ችግር አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸውንም ዘገባው ገልጧል፡፡
በተያያዘ ዜና በብሩንዲ ባለፈው  አመት በተከሰተው ድርቅና የጎርፍ አደጋ ሳቢያ 600 ሺህ ያህል የአገሪቱ ዜጎች የምግብ እጥረት እንዳጋጠማቸው የአለም የምግብ ፕሮግራም ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ የምግብ እጥረት ያጋጠማቸው ዜጎች ቁጥር በመጪው አመት ወደ 700 ሺህ ከፍ ሊል ይችላል ያለው የአለም የምግብ ፕሮግራም፤ ችግሩ በተከሰተባቸው 5 የአገሪቱ አውራጃዎች ውስጥ የሚገኙ 65 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸውንም ጠቁሟል፡፡

 3 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን ርቀት በ4 ወራት ለማጠናቀቅ አቅዷል
      ቤን ሆፐር የተባለው እንግሊዛዊ ከሴኔጋል በመነሳት አትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ ብራዚል የሚደርሰውንና 3 ሺህ 200 ኪሎሜትር የሚሸፍነውን የውሃ ዋና ባለፈው እሁድ መጀመሩን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የ38 አመቱ እንግሊዛዊ ረጅም ርቀት የሚሸፍነውን የውሃ ዋና ለማድረግ ከ3 አመታት በላይ መዘጋጀቱን የጠቆመው ዘገባው፣ ዋናውን ለማጠናቀቅ አራት ወራት ያህል ጊዜ ይፈጅበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልጧል፡፡ ሆፐር ዋናውን በሰላም ካጠናቀቀ አንድን ውቅያኖስ አቋርጦ ከአንድ አህጉር ወደሌላ አህጉር ረጅም ዋና በማድረግ በአለም የክብረ ወሰን መዝገብ እንደሚሰፍር የጠቆመው ዘገባው፣ ዋናተኛውን ሁለት ጀልባዎች እንደሚከተሉት አመልክቷል፡፡
የቀድሞ የእንግሊዝ የፖሊስ መኮንን የነበረው ሆፐር፤ በቀን ለ12 ሰዓት ያህል በመዋኘት ረጅሙን ርቀት ለማጠናቀቅ ማቀዱ የተነገረ ሲሆን፣ በዋናው የገቢ ማሰባሰቢያ በማድረግ 1 ሚሊዮን ዶላር ለግብረ ሰናይ ድርጅቶች ለመለገስ ማሰቡም ተዘግቧል፡፡