Administrator

Administrator

ከአንገቱ በላይ… “በጥቀርሻ ጉም የተሸፈነው የቱርኪሚርክ ተራራ”… ያደፈጠ አውሬ ይመስላል። በድብቅ ሳይሆን በግላጭ ያደፈጠ። ጉሙ ቢገለጥና ጭንቅላቱ ቢታይ ደግሞ አስፈሪነቱ ይብስበታል ብለው ያስባሉ - የራቶስ ከተማ ነዋሪዎች። የተከፈተ አፍ ሊኖረው ይችላል። በጣም የሚያስጨንቃቸው ግን፣ ጭንቅላት ባይኖረውስ የሚለው ስጋት ነው።
ከተማዋ መፈናፈኛ እንዳታገኝ ዙርያዋን የከበበ የእስር ቤት ግንብ ነው - ተራራው። ከእግሩ ሥር ቁልቁል በአይነ ቁራኛ የሚጠባበቅ አውሬም ይመስላል። የከተማዋ ነዋሪዎች አሁንም አሁንም ቀና ብለው ሽቅብ ያዩታል። ሁሌም ስለተራራው ያስባሉ። በሕልማቸውም በውናቸው ከአእምሯቸው አይጠፋም። ግን ሐሳባቸውንና ቅዠታቸውን በግልጽ አያወሩም።
በጥቀርሻ ጉም ከተሸፈነው አናት በታች የዝገት ክምር የመሰለ መልክ አለው። ሲነሳበት ግን መልኩና ቀለሙ ይለዋወጣል። በቁጣ ይንቀጠቀጣል። ሬንጅ የመሰለ ጅራት ያወጣል፡ መርዛማ ጭስ እየለቀቀ በከተማዋ ላይ ብናኝ ያርከፈክፋል።
ዶይቃዊው ንጉሥ ከሥልጣኑ በተባረረበትና አገር ጥሎ በጠፋበት ጊዜ ነው የተራራው ባህርይ የተቀየረው ይላሉ - ገሚሶቹ። ተለዋዋጭ መልክና አመል ያመጣው በዚያችው ዕለት እንደሆነ ይተርካሉ። ታሪክ ተበላሸ ብለው የድሮውን ይናፍቃሉ። ያልሠራነው ገድል፣ ያልሮጥንበት ዳገት የለም ብለው ይናገራሉ። ታሪክ ሁሉ ተፈጽሞ የተጠናቀቀ፣ ከእንግዲህም ማሰብና መስራት የማያስፈልግ ይመስል።
ገሚሶቹ ግን ተራራው ከነ ባህርይው ድሮም የነበረ ነው ብለው ይተማመኑበታል። ተለዋዋጭነቱ ባይጨበጥላቸውም፣ በጥቀርሻ ጉም ቢያጨልምባቸውም፣ ይሻለናል ይሉለታል።
ሌሎች እንደሚተርኩት ከሆነ ግን፣ ከሌሎች ተራሮች የተለየ ባህርይ አልነበረውም። እንዲያውም አፈጣጠሩና ተለዋዋጭ አመሉ ድንገተኛ ክስተት ነው። ከዕለታት አንድ ቀን፣ በድንገት ንጉሡ ጠፋ፤ በድንገት ተራራው ተከሰተ - ከተለዋዋጭ አመል ጋር።
(የሌሊሳ ግርማ አዲስ የረዥም ልብወለድ ድርሰት በእንዲህ ዓይነት ትረካ ነው መጽሐፉን የሚጀምረው፡፡ ማራኪ የፋንታሲ ዘይቤ ነው፡፡ ግን ምናባዊ ዓለም ብቻ አይደለም፡፡ የዛሬ የዘመናችን የዚህችው የዓለማችን ገፅታና መንፈስ ለማሳየት የተወጠነ ድርሰት ነው፡፡)
በራቶስ ነዋሪዎች ዘንድ የተለያዩ ወሬዎችና የተምታቱ ሐሳቦች ቢበዙ ላይገርም ይችላል። የለውጥ ዘመን ላይ የሐሳቦች ግርግር ይፈጠራል። ሲያስለቅሱ የነበሩ አስጨፋሪ፣ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ። የታችኞችም የበላይ። ተራራው ተንዶ ሜዳ ይሆናል፤ ሸለቆው አብጦ ተራራ ያክላል። የሐሳቦች መልክዓ ምድር ይለዋወጣል። ነገሮች በፍጥነት ይሾራሉ።
እንደ ጥንቱ ቢሆን፣ በለውጥ ምክንያት የሚከሰት ጊዜያዊ የሐሳቦች ግርግር፣ ውሎ አድሮ ይረጋጋል። መልክ ይይዛል። የዛሬው ዓለም ግን ከጥንቱ ይለያል። በመላው ዓለም የሚታየው የዘመናችን የሐሳቦች ግርግር፣ ጊዜያዊ የሽግሽግ ሆይሆይታ ወይም የሽግግር ሁካታ አይደለም።
አንድ የሐሳቦች ማዕቀፍ በብጥብጥ ደፍርሶ፣ ሌላ የተጣራና የተንጣለለ የሐሳቦች ማዕቀፍ አይፈጠርም። ነባሩ ተደፍቶ በቦታው ሌላ አዲስ ተተክቶ አያድርም። የፈራረሱት ጠጠሮች፣ የተበታተኑት ነጠብጣቦች እንደገና በአዲስ መንገድ እንዲሰባሰቡ፣ ሥርዓት እንዲይዙና ምስል እንዲፈጥሩ ማድረግ የሚችል ወይም የሚፈልግ የለም።
የጠጠሮች ክምችትና የነጠብጣቦች ትርምስ ነው የዘመናችን ግብ። ጠጠሮችን አዋቅሮ ወደ ቅርጽ ማድረስ፣ ነጠብጣቦችን አገናኝቶ ወደ መስመርና ወደ ምስል ማሸጋገር ድሮ ቀረ ተብሏል። ወይም እንደ ኋላቀርነት ተቆጥሯል።
ይህን የዘመናችንና የዓለማችንን መንፈስ ለመግለጽና ለማሳየት የሚሞክር ድርሰት ይመስላል - የሌሊሳ ግርማ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ።
“በታችም በምድር” በሚል ርዕስ ከሰሞኑ ለሕትመት የበቃው ድርሰት፣ የዘመናችንን የሐሳብ ግርግር በማሳየት ብቻ አይመለስም።
በሐሳቦች ግርግር በታመሰው ዓለም፣ የዓለማ አቅጣጫ በተምታታበት ቅብዝብዝ፣ በማንነት ቀውስ እየታመሰ ትርጉም ባጣ ሕይወት ውስጥ፣ ነጠብጣቦችን ሁሉ የሚጠቀልል ትልቅ ነጥብ የማግኘት ውጣ ውረድን ይተርካል - ድርሰቱ።
በኤሎምና በወላጆቹ ታሪክ።
ተወርዋሪ ኮከብ በመሰለው በኤሎምና በሃቴሉ የፍቅር ብልጭታ።
በተለይ ደግሞ በጠመዝማዛው የኤሎምና በአብነር ታሪክ።
እንደ ደቀ መዝሙርና እንደ መምህር ሆኖ የተጀመረው የኤሎምና የአብነር ታሪክ ወደ ሰማይ ለመምጠቅ ይምዘገዘጋል። የመምጠቂያ ጉልበቱ “እምነት” የተሰኘ ኃይል ነው። እየበረከተ እየበረታ የሚሄድ ኃይል ነው? ወይስ አላቂ ነዳጅ? ከምድር ከራቀ፣ ከዓለም ስበት ከተላቀቀስ ምን መተማመኛ ይኖረዋል?
እምነትን እያቀጣጠለ የሚምዘገዘገው የደቀ መዝሙርና የመምህር ግንኙነት፣ ሲብሰለሰል በቆየ ምክንያት ሳቢያ፣ ቁልቁል ገደል መግባት ይቀርለታል? ወደ ልዩነትና ወደ ተቀናቃኝነት ከመቀየር ይድናል?
ኤሎች የዘመናችንን የሐሳብ ግርግር አደብ ማስገዛት፣ ፍሬና ገለባውን ማጣራት፣ ትክክለኛ ሐሳቦችን በአንድ ማዕቀፍ መልክ ማስያዝ የሚቻለው፣ በሃይማኖት ወይም በእምነት አማካኝነት ነው ማለት ጀምሯል።
ዓለማ የጠፋበት አሰልቺ የመቅበዝበዝ ኑሯችን የሚፈወሰው፣ ዘላለማዊ እውነትን የምናገኘው እንዲሁም ዘላለማዊ የሥነምግባር መርህን የምንጨብጠው በሃይማኖት ነው የሚል ሆኗል እምነቱ።
ሕይወታችን ትርጉም የሚኖረው፣ ቅዠት ከመሰለው የማንነት ቀውስ የምንድነው፣ የሕይወትን ክብር ለማጣጣም የምንችለው፣ በእምነት እንደሆነ (የክብር አናት፣ የፍጽምና ጫፍ፣ የመልካምነት ከፍታን በማምለክ) እንደሆነም ያምናል። ይህን የማገኘው በሃይማኖት በእምነት ነው ይላል።
የሰው ልጅ በሐሳብ ግርግር የሚቃዠው፣ በዓላማ ቢስነት የሚቅበዘበዘው፣ ትርጉም ባጣ ሕይወት የሚባክነው… እምነትን በማጣት ነው እንደማለት ነው።
ለተበጣጠሱ ሐሳቦች አሰባሳቢ ማዕቀፍን፣ ለተበታተኑ የኑሮ እርምጃዎች የጉዞ መስመርን፣ ለተቃወሰ ማንነት ከውረደት ወደ ከፍታ የሚያመላክት የክብር ሰገነትን ማበጀት የግድ አስፈላጊ እንደሆነ መገንዘብና ለዚህም በጽናት መነሣት ትልቅ ቁምነገር ነው።
ሁሉንም ጉዳይ፣ ሁሉንም የሕይወት ገጽታ የሚያካትትና የሚያስተሳስር፣ ለሁሉም ሰው፣ በሁሉም ቦታና ጊዜ የሚያገለግል የሐሳቦች ማዕቀፍ ከሌለን፣ መውጫ በሌለው አዙሪት ቁልቁል እንወርዳለን፡፡ ሐሳባችንም፣ ኑሮና ተግባራችንም፣ የግል ባህሪያችንና መንፈሳችንም ሁሉ በቅዠት እየተዋጠ እንደሚሄድ የሚመሰክር ነው - የዘመናችን አዝማሚያ።
ነገር ግን፣ የዚህ ሁሉ ችግር መንሥኤ የሃይማኖት ወይም የእምነት እጦት ነው ወይ? ችግር የሚደርስብንስ ከእምነት ስለተራራቅን ነው ወይ?
መፍትሔውስ ራሳችንን ለእምነት ማስገዛት ብቻ ነው?
በእርግጥ እምነት መያዝና መጽናት ቀላል ነገር እንዳልሆነ በኤሎም ሕይወት ተተርኳል። ከቤተሰብና ከወዳዶች ጋር የመጣላት ፈተና ይመጣበታል። በሐሰት የሚወነጅሉና የሚያሳድዱ ይነሡበታል። የጠረጠሩት እርግጠኛ ሆነው ይመሰክሩበታል። ያመናቸው ይክዱታል።…
እምነት ለብዙ ችግር ይዳርጋል፤ ያመነ ፈተና ይበዛበታል ያስብላል - ነገሩ።
ግን ደግሞ፣ ችግርና ፈተና የሚበረታው እምነት በሌላቸው ሰዎች ላይ እንደሆነ፣ እምነት የችግሮች መፍትሔ እንደሆነም ይናገራል።
እምነት ችግሮችን ይጠራል ወይስ ችግሮችን ያባርራል? በሁለቱም አቅጣጫ የተምታቱ ሐሳቦችን እየያዘ ይሆን እንዴ?
በኤሎም ታሪክ ሲነሡ ካየናቸው ጥያቄዎች አንዱ ይሄ ነው፡፡ ግን ገና ብዙ አስቸጋሪ ጥያቄዎችንም ሸውዶ ማለፍ አይችልም፡፡
ከ40 በላይ ሃይማኖቶችን በያዘች ከተማ ውስጥ ነው የሚኖረው። እርስ በርስ “መናፍቅ” እየተባባሉ ይወጋገዛሉ።
የትኛው ሃይማኖት ወይም የትኛው እምነት ነው ትክክል?
የሱ እምነት ከሌሎቹ እምነቶች በምን ይበልጣል?
ማስረጃ ልዘርዝር፤ ማረጋገጫ ላቅርብ ካለ… ጉዳዩ የዕውቀት ጉዳይ ይሆናል። ትልቁ ማዕቀፍ ሃይማኖት ወይም እምነት ሳይሆን፣ በማስረጃ የተረጋገጠ ዕውቀት ነው ወደ ማለት ያመራል።
ማስረጃና ማረጋገጫ አያስፈልገኝም፤ የኔ እምነት ከሌሎች እምነቶች እንደሚበልጡ “አምናለሁ”… የሚል ከሆነ ደግሞ… ከሌሎች እምነቶች ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። ሌሎች ሰዎችም ለእምነታቸው ማስረጃና ማረጋገጫ እንደማያሻቸው ይናገራሉ። “የኔ እምነት ከሌሎች እንደሚበልጥ አምናለሁ” እያሉ ነው እርስ በርስ የሚወጋገዙት፤ የሚዘምቱት። ቢያንስ ቢያንስ፣ መናፍቅ ወይም ከሃዲ እያሉ ይሰዳደባሉ።
የኤሎም መንገድ ከነዚሁ ማህበር የተለየና የተሻለ መሆኑን እንዴት ማሳየት ይችላል?
እምነቱ በሚያመጣው ፍሬ? የኤሎምና የተቀናቃኙን ፉክክር በማነጻጸር ይሆን የእምነቱን ትክክለኛነት ማረጋገጥ የሚቻለው?
የኤሎም ፈተና ይህ ብቻ አይደለም። በየአቅጣጫው ከእልፍ ሰዎች አእምሮ እንደ አሸን እየተፈለፈሉ የሚያድሩና አገር ምድሩን የሚያጥለቀልቁ የዓመጽ ሐሳቦችን ማበጠርና ለማዕቀፍ ማስገዛት፣ አገር ምድሩን የሚያዳርሱ የዓመጽ ሤራዎችንና ጥፋቶችን ማሸነፍ ይችላል ወይ? ካልቻለ ፍሬው ምኑ ላይ ነው?
በተለዋዋጭ ዓመል ከተማዋን ከሚያስጨንቃት ከግዙፉ ተራራ ጋር እንደመፋለም ነው - ፈተናው።
ጭንቅላት ይኑረው አይኑረው የማይታወቅ የዘመናችን ተለዋዋጭ የሐሳብ ግርግርን በሃይማኖታዊ እምነት ማሸነፍ እንደማለት ነው።
ከአንገት በላይ በጥቀርሻ ጉም የተሸፈነ፣ መርዛማ ጭስ እየተፋ ብናኙን የሚያርከፈክፍ፣ መልክና ቀለሙን የሚለዋውጥ፣ አገሬውን የከበበ አውሬ ወይም የዝገት ክምር የመሰለ ግዙፍ አመለኛ ተራራ ነው የዘመናችን የሐሳብና የመንፈስ ግርግር።
እና በቅንጣት እምነት ተራራውን “ወግድ” ብሎ መናድና ማባረር ይቻላል?
ድርሰቱን ብታነብቡና ብንነጋገርበት መልካም ይመስለኛል።
አቀራረቡና አጻጻፉ ለንባብ የተመቸ ነው። ትኩረትን በየሚስቡና በሚያስደንቁ ገጸ ባሕርያት የበለጸገ ነው።
ከሁሉም በላይ ግን የዘመናችንን የሐሳብና የመንፈስ ግርግርን ለማሳየት፣ በዚሁ የትርምስ ዓለም ውስጥ የነባር ትውልድና የአዲስ ትውልድ ሕይወት ምን እንደሚመስል ለማስቃኘት የሚሞክር ድርሰት ነው።
የመዳኛው መንገድ የኤሎም እምነት ነው ከማለት ጎን ለጎን፣ የፕሮቴስታንት የመሰለ ሃይማኖት ነው መፍትሔው የሚልም ይመስላል።
እንዲህ ከማለት ግን፣ የእምነት አዳኝነት ወይም የሃይማኖት መፍትሔነት ላይ ያተኮረ ድርሰት ቢባል ይሻላል። ግን በትረካው ላይ የምናየው እምነት፣ የእውነት አዳኝ ነው ወይ? የምር መፍትሔስ ነው ወይ?


“ይህ በየቦታው ሊነገር የሚገባ ድንቅ ታሪክ ነው”


በልደታ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 የሚገኘውና በተለምዶ ዋንዛ ሰፈር እየተባለ ይጠራ የነበረው መንደር አሁን አዲስ ስያሜ አግኝቷል - ”የበጎነት“ መኖሪያ መንደር የሚል፡፡ ስያሜውን ያገኘው ደግሞ በከተማዋ በስፋት እየተለመደ በመጣው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ቀና ልብ ባላቸው ባለሃብቶች በተገነቡ በርካታ መኖሪያ ቤቶች በመሞላቱና መኖሪያና መጠጊያ ያጡ አቅመ ደካሞች መጠለያ ያገኙበትና የዘመነ አኗኗር የጀመሩበት በመሆኑ ነው፡፡
በ2015 ዓ.ም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሲጀመር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ ወደ ዋንዛ ሰፈር ጎራ ብለው ነበር፡፡ የነዋሪዎችን የኑሮ ሁኔታ ከጎበኙ በኋላም በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ተሻለ የመኖሪያ ሥፍራ  እንደሚሸጋገሩ ቃል ገቡላቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ባህል እየሆነ በመጣው የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የበርካታ ነዋሪዎች የኑሮ ጫና ተቃሏል፡፡ ነዋሪዎች ክብር ያለው ኑሮ ይገባቸዋል የሚል ጽኑ እምነት ያለው  የከተማ አስተዳደሩ፤ ዜጎች ከደቀቁና ለኑሮ ምቹ ካልሆኑ ቤቶች ወጥተው የተሟላ የመሰረተ ልማት ወዳላቸው ዘመናዊ ቤቶች እንዲሸጋገሩ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ  ጋር በመተባበር በበጎነት መንደር የገነባቸው ሁለት ባለ 9 ወለል የመኖሪያ  ህንጻዎች ተጠናቀው በከንቲባ አዳነች አቤቤ የተመረቁ ሲሆን፤ መኖሪያ ቤቶቹም  ለነዋሪዎች ተላልፈዋል፡፡
በዚህ የመኖሪያ መንደር የእንጀራ ማእከል ህንፃ ተገንብቷል፣ የወንዶችና የሴቶች የውበት መጠበቂያ፤ ፀጉር ቤት፣ የልብስ ስፌት ማሽን ተሟልቶ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም ለእናቶችና ለህፃናት አገልግሎት እንዲሆን ተቀናጅቶ የተሰራ የልማት ስራ ተካቶበታል፡፡ በእንጀራ ማእከሉ ያሉ እናቶች ከክፍለ ከተማው የተደራጁና ሰልጥነው ወደ ስራ የገቡ ናቸው፡፡
በፀጉር ቤቱ፣ በውበት መጠበቂያዎቹ፣ በህፃናት እንክብካቤዎችና በልብስ ስፌት ላይ የሚሰማሩት  የነገዋ ሴቶች ሰልጣኝ እህቶቻችን ናቸዉ፡፡
የመኖሪያ ቤቶቹ ተጠቃሚ የሆኑ ነዋሪዎች ቤታቸውን ከተረከቡና ገብተው ከጎበኙ በኋላ በሰጡት አስተያየት፤ በከተማ አስተዳደሩ የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ከግምታቸውና ከጠበቁት በላይ እንደሆነባቸው በመግለጽ፤ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
አቶ ገብረመድህን አያሌው አካል ጉዳተኛ የአካባቢው ነዋሪ ሲሆኑ፤ የቀድሞ ቤታቸው ሊወድቅ የደረሰና ዝናብ የሚያስገባ እንደነበረ ይናገራሉ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ የመጸዳጃው ሩቅ መሆን ለእርሳቸው ዓይነት በዊልቼር ለሚጠቀም አካል ጉዳተኛ አስቸጋሪ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ አሁን የተሰጣቸው መኖሪያ ቤት ግን በቃላት ከሚገልጹት በላይ ምቹና ያልጠበቁት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡  
“የበፊቱ መኖሪያ ቤት የግድ ሆኖ ነው እንጂ ለእንደ እኔ ያለው አካል ጉዳተኛ አመቺ አልነበረም፡፡  አሁን ዊልቼሩ ቤት ድረስ ገብቶ ሶፋ ላይ ቁጭ ያደርገኛል፡፡ ሁሉም ነገር ምቹ ሆኖልኛል” ብለዋል፤ አቶ ገብረመድህን፡፡ በቃላቸው መሰረት አዲስ መኖሪያ ቤት ገንብተው ለሰጧቸው ከንቲባ አዳነች አቤቤም፤ “የሥራ ጊዜያቸውን የተባረከ ያድርግላቸው” ሲሉ አመስግነዋል፡፡  
ሌላዋ በአዲሱ መኖሪያ ቤታቸው የተደሰቱት ወ/ሮ እልፍነሽ ሰንበቴ፤ “ከንቲባዋ በ3 ወር ውስጥ ቤት ሰርቼ እሰጣችኋለሁ ስትለኝ እንደዚህ ዓይነት ቤት ሰርታ የምትሰጠኝ አልመሰለኝም ነበር” ብለዋል፡፡ የቀድሞው ቤታቸው ምን ይመስል እንደነበር ሲናገሩም፤ “አስር ሆነን ነበር አንድ ቤት ውስጥ የምንኖረው፤ እኔ እግሬ ስለማይታጠፍልኝ መጸዳጃ ቤት ወንበር ተቀምጦልኝ ነበር የምጠቀመው” ያሉት ወ/ሮ እልፍነሽ፤ “ወደ አዲሱ ቤት ስገባ በደስታም በድንጋጤም እግሬ መሬት መርገጥ አቅቶት ነበር፡፡” ሲሉ የተፈጠረባቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
የቀድሞ ቤታቸው በክረምት ሃይለኛ ጎርፍ የሚሄድበትና የሚቸገሩበት እንደነበር የሚናገሩት ሌላዋ የቤት ተጠቃሚ ወ/ሮ አረጋሽ ቱሉ፤ እንደዚህ ጽድት ያለ ራሱን የቻለ መኖሪያ ቤት ይሰጠናል ብለን አልጠበቅንም ነበር ብለዋል፡፡ ከበፊቱ የተሻለ ይሆናል ብለን ነው የጠበቅነው እንጂ በዚህ ደረጃ አልጠበቅንም ያሉት ወ/ሮ አረጋሽ፤”እግዚአብሄር ይመስገን የእጥፍ እጥፍ አድርገው ነው የሰጡን“ ሲሉ ጥልቅ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በበጎነት  መንደር የመኖሪያ ህንጻዎች የምርቃት ሥነስርዓት ላይ  ከንቲባ  አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር፤ “ይሄንን ለመሥራት ብዙ ርቀት መሄድ አላስፈለገንም፤ መንግሥት ቦታውንና አንዳንድ ተጨማሪ የሚላቸውን ግብአቶች በማቅረብ፣ ባለሃብቱ ደግሞ ገንዘቡን ይዞ በጋራ በመተባበር ለወገኖቻችን የሰራናቸው ቤቶች ናቸው” ብለዋል፡፡
 ልማታችን ሁሉንም በየደረጃው የሚያካትት እንዲሆንና ማህበራዊ ፍትህ እንዲነግስ እየተጋን ነው ያሉት   ከንቲባዋ፤ ይሄንን ደግሞ ብቻችንን በመንግሥት በጀት ብቻ ልንወጣው ስለማንችል እንደ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያሉትን የግል ተቋማት አስተባብረን እየሰራን እንገኛለን ብለዋል፡፡
“መንግሥት ካስተባበረ የሚተባበር ህዝብ አለ፤ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ለዚህ ጥሩ  ማሳያ ነው” ሲሉም አክለዋል፤ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡ ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለሃምሳ ሰው ጌጡ የሚለውን ብሂል የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ከተባበርን ሃብት አናጣም፤ ብዙ መሥራት እንችላለን፤ ብዙ ስንሰራ ደግሞ የብዙዎችን ህይወት እንለውጣለን፤ ብለዋል፡፡  
የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ በበኩላቸው፤ የከተማ አስተዳደሩ የሰው ተኮር መርሃ ግብር፣ ባለሃብቱ ማህበራዊ ሃላፊነቱን በተገቢው መንገድ እንዲወጣ እያገዘው መሆኑን ገልጸዋል፡፡   
ለወገን ተብሎ የሚከናወን ተግባር በረከት እንጂ የሚያጎድል ነገር የለውም ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ጀማል አህመድ፤ በዚህ እምነታችን የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ 72ሺውም ሠራተኛ መግባባት ላይ ደርሶ፣ 10 ከመቶ ትርፋችንን በየክልሉ ለበጎ ተግባር እያዋልን እንገኛለን ብለዋል፡፡
በበጎነት መኖሪያ መንደር ምርቃት ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የኢትዮጵያ ተጠሪ ዶ/ር ሳም ዱ፤ በዚህ እየተመለከትነው ባለው ተግባር እኔ በግሌ ከልብ ተነክቻለሁ ሲሉ የተሰማቸውን ስሜት ገልጸዋል፡፡
“ልማት ማለት የከበረ ጉዳይ ነው፤ ልማት ማለት የትብብር ጉዳይ ነው፤ ልማት ማለት ሰዎች ትርጉም ያለው ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ ነው” ያሉት ዶ/ር ሳም፤ አሁን ላይ በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ ማየት ጀምረናል ብለዋል፡፡
“ዩኤንዲፒ በኢትዮጵያ ለ10 ዓመታት ቆይቷል፤ አሁን ላይ ግን አዲስ ታሪክ ማየት ጀምረናል፡፡ የከተማ አስተዳደሩና የግሉ ዘርፍ ዝቅተኛ ኑሮ ያላቸውን ዜጎች ኑሮ ለማሻሻል በጋራ የሰሩትን ታሪክ እየተመለከትን ነው” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
አክለውም ሲናገሩ፤“የግል ተቋማትና መንግሥት ለማህበራዊ ችግር የተጋለጡ ዜጎችን ህይወት ሲቀይሩ እየተመለከትን ነው፤ ይህ ለእኔ በየቦታው ሊነገር የሚገባ ድንቅ ታሪክ ነው፡፡” ብለዋል፤ ዶ/ር ሳም ዱ፡፡

በሞንጎላውያን አፈ-ታሪክ ውስጥ የሚከተለው  አንድ ታዋቂ ተረት ይገኛል፡፡
“ስለ ዓለም ዕጣ-ፈንታ ሦስት የተለያዩ አስተሳሰቦች አሉ፡፡
የመጀመሪያው የሳንሳ ግልባጭ መኪና (crane) አስተሳሰብ ነው፡፡ እንግዲህ ይህ መኪና በወንዝ ውስጥ ባሉ ቋጥኝ ድንጋዮች መካከል እንዴት በቀላሉ ያለሀሳብ እንደሚሄድ አይታችኋል፡፡ ጭንቅላቱን ሽቅብ አያጎነ እንደገና እንዴት ወደ ኋላ እንደሚቆለመም አይታችሁልኛል? ይሄ ክሬን የተባለ የሳንሳ - ገልባጭ- መኪና አንድ ሁነኛ እርምጃ ቢወስድ ተራሮች ተደረማምሰው እንደሚወድቁ፣ መሬት እንዴት አርዕድ አንቀጥቅጥ እንደሚይዛትና ለዘመናት የቆሙት ዛፎች እንዴት እንደሚብረከረኩ ያስባል፡፡
ሁለተኛው አንበጣ ነው፡፡ የአንበጣ አስተሳሰብ ደግሞ የተለየ ነው፡፡ አንበጣ ሆዬ አንዲት ጠጠር ላይ ቀጥ ብሎ ያስባል፡፡ ከዕለታት አንድ ቀን የጥፋት ውሃ መጥቶ ዓለምን እንደሚያጥለቀልቃትና ሁሉም ህይወት ያላቸው ፍጥረታት በጎርፍና በማዕበል እንደሚጠፉ ያሰላስላል፡፡ በዚህ ምክንያት ይኸው እስከዛሬ ከተራሮች ጫፍ ላይ የሚጠራቀመውን ዝናብ-አዘል ዳመና በዓይነ-ቁራኛ ያስተውላል፡፡
ሦስተኛዋ የሌሊት ወፍ ናት፡፡ የሌሊት ወፍ አንድ ቀን ሰማይ ወድቆ ብትንትኑ እንደሚወጣ ታምናለች፡፡ ከዚያም ህይወት ያላቸው ነገሮች በሙሉ ድምጥማጣቸው ይጠፋል፡፡ በዚህ ምክንያት ይኸው እስከዛሬ የሌሊት ወፍ አንዴ ወደ ሰማይ ተወንጭፋ ትሄዳለች፤ አንዴ ደግሞ ወደ መሬት ትወርዳለች - ይህን የምታደርገው ሰማይና መሬት ሰላም መሆናቸውን ለማረጋገጥ ነው ይባላል፡፡
****
አለምንም ሆነ ሀገርን በገልባጭ ጉልበታቸው እንዳሻቸው የሚያደርጉ አያሌ ነገሥታትና  መሪዎች አጋጥመውናል፡፡ ከቶውንም ቋጥኝ በፈነቀሉ ግንድ በጣሉና ተራራ በናዱ ቁጥር ቀጥሎ ደግሞ መሬትን አንቀጠቅጣታለሁ የሚል የሳንሳ - ግልባጩ መኪና አስተሳሰብ ያላቸው አይተናል፡፡ ንጉስ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ ያሉ ሹሞቻቸው፣ አፈ-ንጉሶቻቸው፣ አዝማቾቻቸው፣ አፈ ቀላጤዎቻቸው፣ ሰብቀኞቻቸው፣ ካድሬዎቻቸው ወዘተ ሁሉ ዛሬ ቋጥኝ አቀበቱን መደረማመስ ከተቻለ ነገ ሰማይና መሬትን ቀውጢ ማድረግ አያቅትም የሚለውን አስተሳሰብ ይጋራሉ፡፡ “የመጥረቢያ ልጅ መዘለፊያ”፣ “የአጣቢ ልጅ አለቅላቂ” እንዲል መፅሐፍ፡፡
ነገ የጥፋት ውሃ እንደሚመጣና እከሌ ከእከሌ ሳይል አገር ምድሩን የሚጠራርግ ማዕበል እንደሚያጥለቀልቀን የሚያስቡ - የአንበጣው አስተሳሰብ ያላቸው አያሌ ናቸው፡፡ እኒህኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ጥፋቱ የሚመጣው ገልባጩ እንደሚያስበው ከውስጥ ሳይሆን ከውጪ ነው፡፡ ጥፋቱ ከውጪ ይመጣል ብለው ግን እንደ መዳኛ የሚያስቡት ስፍራ እንደ አንበጣው - ጠጠር ያለ ነው፡፡ ምሽግ አልፈጠሩም፡፡ የኖኀ-መርከብ መስራት አልጀመሩም፡፡ መሣሪያ አላዘጋጁም፡፡ መአቱን እየለፈፉ፣ ስለመጪው የፍዳ ዘመን እየተናገሩ፣ ጠጠር-አናት ላይ ቆመው ጎርፍ ይጠብቃሉ፡፡
ከፊሎቹ ደግሞ ሰማይ ወድቆ እንክትክቱ እንደሚወጣ በዚያም ሰበብ ፍጥረት ሁሉ እንደሚንኮታኮት ያስባሉ፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ አንዴ ወደ ስልጣኑ መንበር ይወጣሉ፤ አንዴ ደግሞ ታች ወደ ታደመው ህዝብ ይወርዳሉ፡፡ እንደዋዠቁ ይኖራሉ፣ እንደዋዠቁ ይሞታሉ - እንደ ሌሊት ወፏ ናቸው፡፡
በሀገራችን የጉልበተኛው ገልባጭ መኪናም፣ የአንበጣውም፣ የሌሊት ወፏም አመለካከት የሚበጅ ሆኖ አልተገኘም፡፡ በእኔው ተጀምሮ በእኔው ይለቅ የሚል አስተሳሰብ ማን-ያህሎኝነትን ብቻ ነው የሚጠቁመው፡፡ እንደ አንበጣ ቅንጣት ታህል ቦታ ብቻ ስለያዙም ከመዓቱ እንድናለን ብለው የሚያስቡም ጎደሎ-መፍትሄ በማሰብ ደህንነት የሚታያቸው ናቸው፡፡ እንደሌሊት ወፍ ከስልጣኑም ከህዝቡም እየቀሰምኩ እኖራለሁ የሚለውም አስተሳሰብ ከዚህ ቀደም ደጋግመን እንዳየነው የአድር-ባዮችን ዥዋዥዌ ከመጠቆሙ በስተቀር የሚፈይደን ነገር የለውም፡፡
ይልቁንም ከኃይል ይልቅ በዲሞክራሲና በመተማመን፣ በቅንጣት የሥልጣን ምሽግ ሳይሆን በብዙኃኑ የተረጋጋ የስልጣን ባለቤትነት፣ በመዋዠቅ ሳይሆን አግባብነት ባለው ፅናት የምትመራ አገር ናት የሁላችን ማረፊያ መሆን ያለባት!
እንዲህ አይነት አገር እንድትኖረን የምንሻ ከሆነ ስለ ባለጊዜ እያወራን ጊዜያችንን አለማባከን ይጠበቅብናል፡፡ አንዱን ስንጥፍ አንዱ እየተቀደደ እንደሚያስቸግር ቦላሌ አልጨበጥ ያለውን የሀገራችንን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግር በጊዜ የምንነጋገርበት ሁነኛ መድረክ መፍጠር ተገቢ ነው፡፡ ተወያይቶ፣ ችግር ለችግር ተግባብቶ፣ ሁሉ ቢተባበርስ ችግራችን በዋዛ የሚፈታ ነወይ ብሎ ማሰብ ዋና ነገር ነው፡፡ መርሳት የሌለብን ነገር ቢኖር፣ ለመጥፎም ዘመን ባለጊዜ እንዳለው ነው!!

የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ አካባቢዎች ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጋር ለመነጋገር ከመንግሥት አቅጣጫ እንዳልተሰጠው ገልጿል። ኮሚሽኑ በምክክር ሂደቱ ውስጥ ያልተካተቱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ለማካተት ጥረቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።
ከትላንት በስቲያ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በስካይላይት ሆቴል የሦስት ዓመታት የስራ ክንውኑንና ወቅታዊ እንቅስቃሴውን በተመለከተ  ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጠው ኮሚሽኑ፤ በ10 ክልሎችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች በርካታ ስራዎች እንደተጠናቀቁ አመልክቷል። የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት፤ አካታችና አሳታፊ የሆነ አገራዊ ምክክር ለማከናወን በተሰራው ሥራ ከ1 ሺሕ 333 ወረዳዎች ውስጥ 1 ሺሕ 231 ወረዳዎች ላይ የተሳታፊ ልየታ ተከናውኗል፡፡
ይህ ስራ በተለያዩ ተባባሪ አካላት አማካይነት መከናወኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ ከዲያስፖራው ማሕበረሰብ ጋር ደግሞ በርካታ የበይነ መረብ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸውን ጠቁመዋል፡፡ “በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተካሄዱ መድረኮች ላይ ሕዝቡ በነጻነት ሃሳቡን ገልጿል” ሲሉም  አስረድተዋል።
በምክክር ጉባዔ የውክልና መድረኮች ወደ 57 ገደማ የሚሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳታፊ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ስራዎች ከ1 ሺሕ 260 በላይ የጥቃቅንና ንዑስ ቡድኖች አጀንዳ ሰነዶችን፣ በተጨማሪም 120 የተጠቃለሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አጀንዳ ሰነዶችን እንደተረከበ ፕሮፌሰር መስፍን ጠቅሰዋል። 12 የተጠቃለሉ የክልልና የከተማ አስተዳደር አጀንዳዎች ለኮሚሽኑ መቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡
“በሚቻለው መጠን የምክክር ሂደቱን አሳታፊና አካታች ለማድረግ ተችሏል” ሲሉ ማብራሪያቸውን የቀጠሉት ዋና ኮሚሽነሩ፣ በአጠቃላይ ሂደቱ ላይ የገጠሙ ፈተናዎች በዋናነት አገሪቱ በፖለቲካዊ አለመረጋጋት እየተናጠች መገኘቷና በኮሚሽኑ ነጻነትና ገለልተኝነት ዙሪያ የተዛቡና የተሳሳቱ መረጃዎች ሲሰራጩ መቆየታቸው ተጠቃሽ እንደሆኑ አስታውቀዋል። ከዚህ በተጨማሪም የፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ የተሟላ አለመሆን በኮሚሽኑ ያለፉት ሦስት ዓመታት የስራ ክንውን ላይ ጥላውን ያሳረፈ ሌላኛው ተግዳሮት እንደሆነ  ፕሮፌሰር መስፍን አልሸሸጉም።
አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በተደጋጋሚ ዝግጁነቱን በይፋ ቢያስታውቅም፣ በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖችን ለማሳተፍ አስቻይ ሁኔታ አለመፈጠሩን  ኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ከጋዜጠኞች ስለታጣቂዎች ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነሩ፤ “አንድ የታጣቂ ቡድን መሪ በስልክ ደውሎ በግል አነጋግሮኝ ነበር። እርሱና የሚመራው ቡድን ወደ ጫካ እንዲወጡ ያስገደዳቸው ጥያቄ ትኩረት ካገኘ፣ በአገራዊ ምክክር ሂደቱ ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ነግሮኛል። ይህንን ጉዳይ ለአገራዊ ምክክር ምክር ቤት አሳውቄያለሁ። እንዲሁም ከደህንነትና ጸጥታ አካላት ጋር ለታጣቂ ቡድኑ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ አጀንዳ የመቀበል ሂደት እንዲኖርና ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጥያቄ አቅርበናል” ብለዋል። ይሁንና የታጣቂው ቡድኑና መሪውን ማንነት በይፋ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም ጥያቄ የቀረበው ከኮሚሽኑ ሳይሆን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሆኑን የተናገሩት ፕሮፌሰር መስፍን፣ “ምክክር በአንድ ዓመት የሚጠቃለል አይደለም” በማለት አጽንዖት ሰጥተዋል። በአጀንዳ ማሰባሰብ መድረኮች ላይ ከአገር ምስረታና ሌሎች ከሕገ መንግስቱ ማዕቀፍ ውጭ “ናቸው” ተብለው የሚለዩ ጥያቄዎች ከቀረቡ ወደ አጀንዳ ውስጥ የመካተት ዕድሉ “ጠባብ ነው” ሲሉ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት ገብረስላሴ በበኩላቸው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለተፈቀደው ተጨማሪ አንድ ዓመት ሲናገሩ፣ “ሁሉም ነገር በትክክል ከተካሄደ ጊዜው ይበቃናል” ብለዋል። አክለውም፣ “ምክክር በዚህ ሰዓት ውስጥ ተመካክራችሁ፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ‘ስጡ’ የሚባልበት አይደለም። ሕዝቦች ቁጭ ብለው፣ ጊዜ ወስደው ተመካክረው የሚወስኑት ነው፡፡ በቀላሉ የሚወሰኑ አጀንዳዎች ይኖራሉ፤ጊዜ የሚፈጁም ሊኖሩ ይችላሉ” ሲሉ       አብራርተዋል፡፡
ከአገራዊ ምክክር ራሳቸውን ስላገለሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ማብራሪያ የሰጡት ወይዘሮ ሂሩት፣ “ፓርቲዎችን በግልም ሆነ በተለያየ መንገድ በማነጋገር፣ በዚህ ሂደት እንዲሳተፉ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል” ብለዋል፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሂደቱ እንዲሳተፉ አሁንም ጥረቱ እንደሚቀጥል ጨምረው ገልጸዋል።
ምክትል ዋና ኮሚሽነሯ አያይዘውም፣ “ከዚህ ቀደም ለመናገር ዕድል ያላገኙ ማሕበረሰቦች ዕድል እንዲያገኙ ተደርጓል። በዚህም ስኬታማ ስራ ተሰርቷል” ብለዋል። ለአስፈጻሚ አካላት ተጠቃልለው የሚቀርቡ አጀንዳዎች በመንግሥት በኩል፣ “ይፈጸማሉ የሚል ዕምነት በእኛ በኩል አለ” ሲሉ ገልጸዋል።
ከታጣቂዎች ጋር ንግግር ለማድረግ መንግሥት ለኮሚሽኑ አቅጣጫ አለመስጠቱን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ ሂሩት፤ “ከእኛ ቁጥጥር ውጪ የሆኑ ነገሮች አሉ” ብለዋል።


በመደራጀት ላይ የሚገኘው የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ፣ አባላቱ በጸጥታ አካላት እንደታሰሩበት አስታውቋል። ፓርቲው የታሰሩበት አምስት አባላት በፊርማ ማሰባሰብ ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሷል።
ከፓርቲው አደራጆች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሃብታሙ ኪታባ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ አምስቱ የፓርቲው አባላት የፊርማ ማሰባሰብ ስራ እያከናወኑ የነበሩ ሲሆን፤ የካቲት 9 እና በነጋታው የካቲት 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ አባላቱ በመንግሥት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን  ገልጸዋል።
“አባሎቻችን በደህንነት መስሪያ ቤት አባላት ታግተው ተወስደዋል” ያሉት አቶ ሃብታሙ፤ “በሕጋዊ መንገድ ወደ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው መመርመር ነው ያለባቸው፤ ታግተው ወዳልታወቀ ቦታ መወሰድ የለባቸውም።” በማለት ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል። ይህ ድርጊት ድርጅቱ እንዳይመሰረትና ሕጋዊ ሆኖ እንዳይወጣ ያለመ ነው፤ ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።
በመደራጀት ላይ የሚገኘው የንጋት ኮከብ ለኢትዮጵያ ፓርቲ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ለመንቀሳቀስ ጥረት እያደረገ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሃብታሙ፤ “በአባሎቻችን ላይ የተፈጸመው እስር የሰላማዊ ትግሉን ምህዳር የሚያጠብና ትግሉ እንዳይበረታታ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
አክለውም፣ “ከዚህ ቀደም የነበረው ኢሕአዴግም ሆነ የአሁኑ ገዢ ፓርቲ ብልጽግና በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ድርጅቶችን በበጎ ተቀብለው አይተን አናውቅም” በማለት ተችተዋል፡፡  
በፊርማ ማሰባሰብ ላይ ተሰማርተው ሳለ በጸጥታ አካላት የታሰሩት የፓርቲው አደራጅና የፊርማ አሰባሰብ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ሰብስቤ ዓለሙ፣ የአደራጅ ኮሚቴው አባልና የፊርማ አሰባሰብ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አማኑኤል የማነብርሃን፣ የአደራጅ ኮሚቴው አባልና የፊርማ አሰባሰብ ኮሚቴ አባል አቶ ሃብታሙ ሾተላ፤ የፊርማ አሰባሰብ ኮሚቴ አባላት የሆኑት አቶ ሱራፌል ብሩክ እና አቶ ክፍሎም ሃብቴ መሆናቸውን ፓርቲው በይፋዊ የማሕበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ጠቅሷል፡፡ የጸጥታ አካላቱ ኮድ 4፣ ኮድ 3 እና ታርጋ የሌላቸው ተሽከርካሪዎችን በመጠቀም አባላቱን እንደወሰዱም ፓርቲው አመልክቷል፡፡
ፓርቲው ጉዳዩን ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. ማሳወቁን ገልጿል፡፡
“የቀድሞው ስርዓት የጸጥታ አካላት አፍነው ወስደው ወይ ፌደራል ፖሊስ፣ ወይም አዲስ አበባ ፖሊስ ነበር የሚያስሩት። የአሁኑ ስርዓት ግን የሚወስደው እርምጃ ማገት ነው” ያሉት አቶ ሃብታሙ፤ ቀጣይ ጊዜያት ለሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ እንደሚሆኑ ግምታቸውን ሰጥተዋል። ከወራት በፊት ከፓርቲው ምስረታ ጋር በተያያዘ በዋቢሸበሌ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ቢታቀድም፣ በጸጥታ አካላት ምክንያት ሳይሰጥ መቅረቱን አስታውሰዋል፡፡
ለፓርቲው ምስረታ የሚያስፈልገው የ10 ሺህ ሰዎች ፊርማ ባለፈው  እሁድ ተሰብስቦ መጠናቀቁንና ሌሎች ለምርጫ ቦርድ የሚገቡ ሰነዶች መሟላታቸውን የገለጹት አቶ ሃብታሙ፤ የጉባዔ አዘጋጅ ኮሚቴ መዋቀሩንም   ጠቁመዋል፡፡
“አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ስለ ምርጫ የሚታሰብበት ነው ብለን አናምንም” ያሉት አቶ ሃብታሙ፤ “የምርጫ ጉዳይ ለእኛ ሩቅ የሆነ አጀንዳ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል፣ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን፣ ሰሓርቲ ወረዳ፣ አዲስ ዓለም ቀበሌ በማህተም ምክንያት በትግራይ ሃይሎችና በአካባቢው ነዋሪዎች መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት ጉዳት አስከትሏል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የተፈጠረውን ግጭት በማውገዝ መግለጫ አውጥቷል።
ግጭቱ የተፈጠረው ረቡዕ የካቲት 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ሲሆን፣ የግጭቱ መንስዔ በአዲስ ዓለም ቀበሌ የተሾሙ ሁለት አስተዳዳሪዎች በመኖራቸው መሆኑን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። ምንጮቹ አያይዘውም፣ ሁለቱም ማህተም በየራሳቸው ይዘው፣ በተቀናቃኝነት የቀበሌው ሕጋዊ አስተዳዳሪ ስለመሆናቸው በመናገር ፉክክር ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
አንደኛው አስተዳደር በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የተሾሙ ሲሆኑ፤ በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተሾሙ ሌላ አስተዳደር መኖራቸውን ምንጮቹ ያስረዳሉ። ቁጥራቸው 9 የሚሆን የትግራይ ሃይሎች አባላት ወደ አዲስ ዓለም ቀበሌ በመሄድ፤ “ህዝቡ ምሬት በማሰማት እንድንታደገው ጠይቆናል። አዛዦቻችንም ይህንን እንድንፈፅም ወደ እናንተ ልከውናል” በማለት ሁለቱም አስተዳዳሪዎች  የያዙትን ማህተም እንዲያስረክቡ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል።
የማህተም ማስረከብ ጥያቄው በቀበሌው ነዋሪዎችና በትግራይ ሃይሎች አባላት መካከል ግጭት የቀሰቀሰ ሲሆን፤ ነዋሪው ድንጋይ ሲወረውር፣ በምላሹ የትግራይ ሃይሎች አባላት ተኩስ መክፈታቸውን ምንጮቹ አብራርተዋል። በዚህም አንድ ነዋሪ እጁን በጥይት ተመትቶ ወደ ሆስፒታል መግባቱ ሲገለጽ፣ 20 ነዋሪዎች ደግሞ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቁሟል፡፡


ይሁንና የሰሓርቲ ወረዳ ሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ዋና ሃላፊ አቶ አዱኛ ገብሩ ማክሰኞ የካቲት 11 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፉትና አዲስ አድማስ በተመለከተው ደብዳቤ ላይ በቁጥር 13 የሚሆኑ ታጣቂዎች ወደ ወረዳው አስተዳደር ጽሕፈት ቤት በመምጣት፣ የጊዜያዊ አስተዳደር ማህተምና የፅህፈት ቤት ቁልፍ እንዲያስረክቡዋቸው መጠየቃቸውን ጠቅሰዋል። ይህንን ድርጊት እንዲያስቆምም ለክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ተማጽኖ አቅርበዋል።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ሐሙስ የካቲት 13 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ በክልሉ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን፣ ሰሓርቲ ወረዳ፣ አዲስ ዓለም ቀበሌ የትግራይ ሃይሎች አባላት በነዋሪዎች ላይ ያደረሱትን ጥቃት አውግዟል። በተጨማሪም፣ “ሃይልን በመጠቀም የመንግሥት መዋቅር ለማፍረስ የሚደረግ ሕገ ወጥ ዕርምጃ ተቀባይነት የለውም” ሲል  አሳስቧል።
“የተወሰኑ የትግራይ ወታደራዊ ሃይል አመራሮች የጊዜያዊ አስተዳደሩን መዋቅር ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ እየተመለከትን ነው” ያለው የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ፤”በሰሓርቲ ወረዳ የተፈጸመው አሳዛኝ ተግባር እንደ አንድ ማሳያ መውሰድ ይቻላል” ብሏል፡፡
ጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫውን ሲቀጥል፣ “ሰራዊቱ የሕዝብ ህልውና ለመጠበቅ እንጂ የአንድ ቡድን የስልጣን ጥማት ለማርካት የተሰለፈ አይደለም። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ  ወደማንወጣው ቀውስ እንደምንገባ የቅርብም የሩቁም ሊገነዘበው ይገባል” ሲል አሳስቧል፡፡  በወረዳው የተፈጠረውን ሁኔታ የሚያባብሱ ፖለቲከኞችና የሰራዊት አመራሮች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም ጊዜያዊ አስተዳደሩ በመግለጫው አስጠንቅቋል።

Friday, 21 February 2025 19:53

470, 000,000 ብር ደረሰ

" ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለመቄዶንያ 10 ሚሊዮን ብር "
ተወዳጅዋ ዳጊ ከቤተሰቧቿ ጋር በመሆን አንድ ሚሊዮን ብር ለገሰች
የአዋጭ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ሸለመ በአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ስራ ማህበር አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም በአዋጭ ፋውንዴሽን ስም አንድ ሚሊዮን በድምሩ ሁለት ሚሊዮን ብር ለመቄዶንያ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአዋጭ ፋውንዴሽን በኩል በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡
ያስጀመረን ያስፈፅመናል!!!

“ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት” የተሰኘ ልዩ የኪነ-ጥበብ መርሃ ግብር፣ በመጪው ሳምንት አርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ሙዚየም ይካሄዳል፡፡

የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንት እንደገለጸው፣ በአድዋ ድል ዋዜማ በሚካሄደው በዚህ የኪነጥበብ መርሃ ግብር፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ዝክረ አድዋ” የተሰኘ ጥናታዊ ፅሁፍና ዲስኩር በምሁራን የሚቀርብ ሲሆን፤ የግጥም ምሽትና የስታንዳፕ ኮሜዲም እንደተሰናዳ ተጠቁሟል፡፡

በተጨማሪም ፖለቲከኞች በሰላምና አንድነት ዙሪያ አነቃቂ ንግግር፣ እንዲሁም ጀግኖች አርበኞች ሽለላና ፉከራ በባህላዊ ባንድ ታጅበው ያቀርባሉ ተብሏል።

በመርሃ ግብሩ ደራሲ፣ ገጣሚና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ መምህር ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ መጋቢ ቸርነት በላይነህ (ፓስተር ቸሬ)፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ፣ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤልና ሌሎችም እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በሆነው የአድዋ ድል ዋዜማ ላይ በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመግቢያ ዋጋ መደበኛ 300 ብር፣ VIP ደግሞ 500 ብር ሲሆን፤ ትኬቱ በቴሌ ብር፣ በጃፋር ቤተ-መፅሐፍት፣ በ2 ሺህ ሐበሻ የባህል ምግብ አዳራሽ እንደሚገኝ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴንመንት ጠቁሟል፡፡

• አዲሱን ኢ-ፓስፖርት በሁለት ወር ከ10 ቀን ማግኘት ይቻላል፣

• 14 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል፣

• ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኢ-ፓስፖርት ታትሞ ተዘጋጅቷል፣

• ከፓስፖርት በተጨማሪ ከ10 በላይ የጉዞ ሰነዶችን ማዘመን ተችሏል፣

• አዲሱ ኢ-ፓስፖርት በነበረው ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይሆናል፤

• ለፓስፖርት ህትመት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ ነው፣

• ከዚህ በፊት አገልግሎት እየተሰጠ የቆየው 20 ዓመት ባለፈው ቴክኖሎጂ ነው፣

• ይህንን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መገንባት መቻሉ ትልቅ ድል ነው፣

• አዲሱ ቴክኖሎጂ ደንበኞች ባሉበት ፓስፖርታቸውን በፍጥነት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል፣

• ከዚህ በፊት የሚያጋጥሙ የደህንነት ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል፤

• ነባሩ ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው እስኪያበቃ ጥቅም ላይ መዋሉን ይቀጥላል፤

• የዕድሳት ጊዜው ሲደርስ በኢ-ፓስፖርት ይተካል፤
**
(ምንጭ፡- የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት)

የG-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባዔ ለ3ኛ ጊዜ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የሚካሄድ ሲሆን፤ የአህጉሩ ቀዳሚ የቡና አምራች የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ ገብተዋል።


''የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪን በማነቃቃት ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን መክፈት'' በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ላይ ዘርፉን ለማነቃቃትና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚደረጉ ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል፡፡

Page 5 of 759