Administrator

Administrator

 ብዙዎቻችሁ ታውቁታላችሁ፤ - ኃይለመለኮት አግዘው ይባላል። የታሪክ፣ የቋንቋ ባለ ሙያና ምሁር ነው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ በከተማ አጠባበቅና የኪነ - ሕንፃ ቅርሶች ዘርፍ (Urban Conservation and Architectural Heritage) የማስትሬት ዲግሪ አግኝቷል።
በአዲስ አበባ ሙዚየም የኤግዚቢሽን አስተባባሪ፣ የትምህርት ኦፊሰር እና ዳይሬክተር፣ በኢኳቶሪያል ቢዝነስ ግሩፕ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ፣ በኢትዮዽያ ፕሬስ ድርጅት የ “Ethiopian Herald” ጋዜጣ አዘጋጅ፣ በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ባለሙያ በመሆን አገልግሏል።
በሥራ ዘመኑ የአዲስ አበባ ከተማ ቅርሶች እንዲጠኑ፣ ተለይተው እንዲመዘገቡና ጥበቃ እንዲደረግላቸው ከጓደኞቹ ጋር ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ስለ ከተማችን ቅርሶች መጠበቅ የእርሱን ያህል የጮኸ አላወቅም። በአራዳ ክፍለ ከተማ ባህልና ቱሪዝም እሰራ በነበረበት ወቅት ለብዙ ጊዜያት ከእርሱ ጋር የመገናኘት፣ የመጨዋወትና የመወያየቱን አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። ስለ ከተማችን አዲስ አበባ ታሪክ ያለው እውቀት፣ ስለ እያንዳንዱ ሰፈር፣ ወንዛወንዞች፣ ስለተለያዩ የከተማይቱ ኗሪ ህብረተሰብ ያለው እውቀት ጠሊቅ ነበር።
በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን እየሰራ ሳለም የሀገራችንን የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች በማጥናት፣ በአጠባበቅና ዓለም አቀፍ ዕቅድ በማዘጋጀት ረገድ የተጫወተው ሚና ይህ ቀረው የማይባል ነበር። እ.ኤ.አ በ2012 እና 2013 ዓ.ም በኢትዮዽያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለ ስልጣን የሀገራችንን የማይዳሰሱ ቅርሶች በተመለከተ የተዘጋጁ ሁለት ባለ 300 ገፅ መፃህፍት በተባባሪ አዘጋጅነት ለህትመት እንዲበቁ አድርጓል። በተጨማሪም ለድሬ ሼኽ ሁሴን፣ ሶፍ ዑመር እና ለጌዴኦ ቅይጥ ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ ቅርሶች ዓለም አቀፍ የቅርስ አስተዳደር ዕቅድ አዘጋጅቷል።
በተለያዩ የህትመት፣ የኤሌክትሮኒክስና የማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ዕውቀቱን በፅሁፍም በአካልም አጋርቷል። ሚዩዚክ ሜይ ዴይ ያዘጋጃቸው በነበሩት የመፅሀፍ ዳሰሳ መድረኮች ላይ ጥናታዊና ሂሳዊ ፅሁፎችን ያቀርብም ነበር። በአሃዱ ሬድዮ ላይ ዘወትር ቅዳሜ ምሽት በሚቀርበው “መናገሻ” ዝግጅት ላይ ከነ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ጋር በመሆን በተለያዩ ርዕሰ - ጉዳዮች ላይ በሳል ሀሳቦችን በመሰንዘርም አክብሮትና ተወዳጅነትን አትርፏል።
ባጠቃላይ ኃይለ መለኮት ሙሉ ሰው ነበር። እንደ ሀገር እርሱን መሰል ሰው በሞት ማጣት ትልቅ ጉድለት ነው - የምር። ታሞ አልጋ ላይ በዋለባቸው ጊዜያት በስልክ ያለበትን ሁኔታ ለመጠየቅ ስደውልልት ህመሙ ምንም እንኳ የከፋ ቢሆንም መዳንንና ወደ ሥራ መመለስን ተስፋ ያደርግ እንደነበር አውቃለሁ። ሆኖም የፈጣሪ መሻት ሆኖ ዛሬ ማረፉን ሰማሁ። አዘንኩም። ነፍስ ይማር !!!
(ከጀሚል ይርጋ ፌስቡክ የተገኘ)

 ስኬቶችንና የተመዘገቡ አሳፋሪ ክስተቶችን (ውድቀቶች) ለመቃኘት ሞክረናል፡፡ የአዲስ አድማስ አንባቢያንን አስተያየትና
ምላሽ ሰ ብስበናል፡፡ ከ ዚህ በ ተጨማሪም መረጃዎችና ዘገባዎችንም ተጠቅመናል፡፡ ሁለቱን በማገናዘብም የአዲስ አድማስን ‹‹የዓመቱ ስኬቶችና አሳፋሪ ክስተቶች›› ለይተናል፡፡ እነሆ ከዚህ በታች ቀርቧል፡፡
መልካም አዲስ ዓመት!!


 1 የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ የክልል ፕሬዚዳንት:- ሙስጠፋ መሃመድ (ሶማሌ ክልል)
 2 የዓመቱ ስኬታማ የመንግስት ተቋም:- ገቢዎች ሚኒስቴር
 3 የዓመቱ አሳፋሪ የመንግስት ተቋም:- ሜቴክ
 4 የዓመቱ ተስፋ የሚጣልበት የዲሞክራሲ ተቋም: - ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ
 5 የዓመቱ አስደማሚ የመንግስት ስኬት:- የኢትዮ-ኤርትራ ሰላምና እርቅ
 6 የዓመቱ ስኬታማ አገራዊ ንቅናቄ:- የሃምሌ 22 ችግኝ ተከላ
 7 የዓመቱ አስደንጋጭ ክስተት:- ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ግድያ
 8 የዓመቱ ተፅዕኖ ፈጣሪ አክቲቪስት:- አርቲስት ታማኝ በየነ
 9 የዓመቱ ምርጥ የፖለቲካ (የመንግስት) መሪ:- ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ
10 የዓመቱ ተወዳጅ የቴሌቪዥን ጣቢያ:- ኢቢኤስ
11 የዓመቱ ተወዳጅ የሬዲዮ ጣቢያ:- ሸገር 102.1
12 የዓመቱ ምርጥ ኢ-ልብወለድ መጽሐፍ:- “ትውልድ አይደናገር እኛም እንናገር”
13 የዓመቱ ተወዳጅ የኪነ ጥበብ ምሽት፡ - “ጦቢያ ግጥም በጃዝ”
14 የዓመቱ የሰላምና የፍቅር አርአያ:- የጋሞ አባቶች
15 የዓመቱ ምርጥ የቴሌቪዥን ድራማ: - “ምን ልታዘዝ”
16 የዓመቱ ምርጥ የሙዚቃ አልበም:- የአስቴር አወቀ “ጨዋ” አልበም
17 የዓመቱ ምርጥ ጋዜጠኛ:- የዋልታ ቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ስሜነህ ባይፈርስ
18 የዓመቱ አሳፋሪ የፖለቲካ ውዝግብ:- የህወሓትና አዴፓ ውዝግብ
19 የዓመቱ ምርጥ የበጎ አድራጎት ድጋፍ:- የአ.አ መስተዳድር የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ


            አንድ እጅግ ጉረኛ ሰው  ነበር፡፡ ድንገት ይመጣና ‹‹አሥራ ስድስት ቀበሮዎች አግኝቼ አንድ ላይ፣ በአንድ ጥይት ሰፋኋቸው! በጣም አስገራሚ ገድል ነው የፈፀምኩት›› አለ፡፡
‹‹እንዴት ሊሆን ቻለ?›› አሉት፡፡
‹‹እንዴ?! የዚያን ጊዜ ተዓምር በቃላት አይፈታም››
ማሰብ ይጠይቃል፡፡ እንደው ላይ ላዩን አይተን ብቻ በመሀይም ልቦና ጉዳዩ ውስጥ እንግባበት ብንል ከንቱ ድካም ነው የሚሆነው፡፡
ምንም ማስረጃ ሳያስፈልግ ለአገር መመስከር እንችላለን፤ ሕዝቦች ነንና!!
ይኸው ጉረኛ መንገድ ላይ ሰው አገኘና፡-
‹‹ከየት ትምጣለህ?›› አለው
‹‹አሥራ ስድስት ቀበሮዎች ሰፍቼ››
‹‹የት?››
‹‹ጫካ››
‹‹ጀግና ነህ! አንበሳ ነህ!››
‹‹ጀግንነቴ አስደማሚ አይደለም?››
‹‹እኔን ያስደመመኝ ያንተ ጀግንነት አይደለም››
‹‹ሌላ ምኑ ነው ታዲያ ያስደመመህ?›› አለው፡፡
‹‹የአገርህ ቀበሮዎች አሰላለፍ!!››
 *  *   *
ለማንኛውም ከጥሩ ማስተዋል ጋር አሰላለፍን ማሳመር መታደል ነው!
ገጣሚውና ፀሐፌ - ተውኔቱ መንግሥቱ ለማ፡-
ቀማኛን መቀማት
  ከሌባ መስረቅ
ለማቅለል ከሆነ
   የድሆችን ጭንቅ
በእኔ ቤት ፅድቅ ነው
አንድ ሰው ይሙት!!
አንድ መቶ ሺህ ሰው ሲኖር በምጽዋት!››… ብለዋል፡፡
ይህ ፍንትው ያለ ዕውነት ነው!!
‹‹ውሸት ዓለምን ዞሮ ሲጨርስ፣ ዕውነት ቦት ጫማውን አስሮ አይጨርስም›› ይላሉ አበው፡፡
‹‹ጓደኛሞች መጠጥ ቤት ይገናኙና፤
‹‹የት ጠፋህ›› አለ አንዱ አንደኛውን
‹‹እንደው ባንተያይ ነው እንጂ እኔ እንኳን አለሁ››
‹‹የደበቅኸኝ ነገር አለ እንጂ እዚሁ አዲሳባ እየኖርን ልንጠፋፋ አንችልም››
‹‹ምንም የደበቅሁህ ነገር አይኖርም፤ ግን ለአንድ ለስድስት ወር አሥረውኝ ነበር››
‹‹ምን አርገህ ብለው ነው?››
‹‹አንድ ኮርቻ ሰረቅህ ብለው ነው››
‹‹ለኮርቻ ስድስት ወር?››
‹‹ምን እባክህ ከኮርቻቸው ሥር አንዲት የማትረባ በቅሎ ነበረች››
ዋናውንና ምንዛሪውን ካልለየን አለመታመን የግድ ይመጣል፡፡ የግድ ተዓማኒ ለመሆን ማንነትን ማጥራት ዋና ጉዳይ ነው፡፡
ማንነት ደግሞ፤
የቀናነት
የሀቀኝነት
የፍቅር
የተስፈኝነት
የዕውቀት
ሁሉም የመልካም አስተሳሰብ ውጤት ነው፡፡
እነዚህን ሁሉ አንድ ሰው ሆድ ውስጥ ማጠራቀም ብርቱ ጥረት ይጠይቃል፤ ከልባችን እንታገል!!
ካመረርን፣ መንገዳችን ሩቅና መራራ መሆኑን ከልብ ካመንን የማናቸንፍበት አንዳችም ምክንያት የለም!!
መልካም የፍቅር ዓመት ያድርግልን!!

Monday, 09 September 2019 13:03

መልካም አዲስ ዓመት!

  … እንቁጣጣሽ ነበር መስከረም ሲጠባ
አውቆ የበቀለ ወፍ ዘራሽ አበባ፡፡
ለምለም አረንጓዴ…
ያልተጠበቀ መስክ ከብት የሚግጥበት
የደመና ግላጭ የሚጫወትበት፡፡
ሌላም ብዙ ነበር
   ሌላም… ደግሞ ሌላ
አለብኝ ትዝታ!
   ዘመዶቼ ሳሙኝ
  ጓደኞቼም ጋብዙኝ
  ሊስትሮ ጨብጠኝ
ባለጋሪ ንዳ መንገዴን አሳየኝ
ያገሬ ልጅ ቆንጆ ‹‹ቤት ለእንግዳ›› በይኝ
አለብኝ ትዝታ…
                           ገ/ክርስቶስ ደስታ
                               (እንደገና)
                *  *  *
…በይ ብር በይ ቢራ ቢሮ፣ ክረምት ላንቺ
                        ብቻ አለፈ
ሌላው በጎርፍ ጎረፈ
ሞተ፣ በተኛበት ረጋ…
ፀደይ ላንቺ ብቻ ነጋ
ሽር ብለሽ መንቆጥቆጥ ነው፤ ከዚያም፤
               ከዚያም፤ ከዚያም ሰምሮ
አወቅሁብሽ፤ ነቃሁብሽ፤ አንቺ ሕይወት
                 ቢራ ቢሮ…
ቀናሁ መሰል አንች ወላዋይ?
ነይ ብር በይ እንወያይ
አንቺ የዕፅዋት አዋዋይ
ከፀደይ ጋር ፀደይ መሳይ
ከአበባም አበባ መሳይ…
ምን አለበት ላንዲት ሰሞን
ቢራ ቢሮ እኔ አንቺን ብሆን?
                ፀጋዬ ገ/መድህን
              (ሕይወት ቢራቢሮ)
                *  *  *
… ወፎች ሲዘምሩ ሰማይ ደማስ መስሎ፣
ሐሴት ገባ ልቤ በውበት ተኩሎ፡፡
                      ዮሐንስ አድማሱ
         (ወፎች በተጥለግለግ - 1955 ዓ.ም)
                *  *  *
…ነበረች አበባ፣
በሾህ ተቀንብባ፣
መዓዛዋ ዘምቶ፣
   ተወርዋሪን ኮከብ አቀረበው ጠርቶ፡፡
በውበት ብትልቅ ይህች የዋህ አበባ፣
ረብ የሰው ዘየ በሾህ ተቀንብባ፣
እሾህ አያስደርስ፣ ቆንጥሩ አያስጠጋ፣ የዘመን
               ጋሬጣ አድርጓት ሰለባ፣
በእጦት መቃጠል ነው መዓዛዋ ሲያውድ
                ከልብ እየገባ፡፡
                       ዮሐንስ አድማሱ
                         (ተወርዋሪ ኮከብ)
                *  *  *
የተስፋዬ ዛፉ
ሊከረከም ቅርንጫፉ፣
ሥሩ ሲነቃቀል
ሲበጠስ ሲፈነገል፤
ጭላንጭል ስትዳፈን
ብርሀን ዐይኑ ሲከደን፣
አንጥፌ ደርቤ ማቄን
ዘንግቻት እንቁጣጣሽን
ፀደይ አበባ ዐደዬን፣
በድቅድቅ ተቀመጥሁኝ
ላለማሰብ እያሰብሁኝ፣
የልቤን ልበ ባሻነት ገሰጽኩኝ
ተስፋ መቁረጥን ተስፋ አረኩኝ፡፡
            ደበበ ሰይፉ
             (የተስፋዬ ዛፉ)               

በተለምዶ ብሥራተ ገብርኤል እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ያለው አዲስ ዴፖ የማስፋፊያ ሥራው ተጠናቅቆ አገልግሎት ጀመረ፡፡  አዲስ ሆም ዴፖ ከትናንት በስቲያ በክብር እንግድነት ተገኝተው የመረቁት የአዲስ አበባ ንግድ ም/ቤት ፕሬዚዳንት ክብርት ወ/ሮ መሰንበት ሸንቁጤና የሚድሮክ ቺፍ ኤክስኪዩቲቭ ኦፊሰርና የዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አረጋ ይርዳው ናቸው፡፡
አዲስ ሆም ዴፖ የሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ አባል የሆኑት የዘመናዊ ሕንፃ ኢንዱስትሪና የኮምቦልቻ ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ምርቶችን በጅምላና በችርቻሮ እንዲሸጥ ታስቦ በ1995 ዓ.ም 15 ሠራተኞችን ይዞ የተቋቋመ ኩባንያ ሲሆን ሥራው ሲጀመር ዓመታዊ ሽያጩ 6.2  ሚሊዮን ብር እንደነበር ዶ/ር አረጋ ገልፀዋል፡፡
የሽያጭ የቅርንጫፎቹን ቁጥር ወደ 7 ያሳደገው አዲስ ሆም ዴፖ፤ በአሁኑ ወቅት የሠራተኞቹ ቁጥር 167፣ ዓመታዊ የሽያጭ መጠኑም ወደ 317 ሚሊዮን ብር ማደጉ ተጠቁሟል፡፡  ለገበያ የሚቀርቡ የምርት ዓይነቶች ስፋትና ጥራት የጨመረው ድርጅቱ፤ በአሁኑ ወቅት የግንባታ ዕቃዎች፣ የሕንፃ መሳሪያዎች፣ የኤሌክትሪክ፣ የቤትና የቢሮ የፊኒሽንግ ቁሳቁሶች የኤሌክትሮኒክ፣ የወጥ ቤት ዕቃዎችን በማቅረብ ላይ ሲሆን፤ የሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ሽያጭም እንደሚከናውን ታውቋል፡፡
ቀድሞ ከነበሩበት ቦታ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ሎሊ (Loli የሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አላ-ሙዲ ሴት ልጅ ስም) ሕንፃ የተዛወረው የብሥራተ ገብርኤል አዲስ ሆም ዴፖ፤ ከዋንዛ ፈርኒሽንግ፣ ከቪዥን አሉሚኒየም፣ ከብሉ ናይልና ከአዳጐ ሚድሮክ ግሩፕ ኩባንያዎች ምርቶችን ተረክቦ ያከፋፍላል ብለዋል - ዶ/ር አረጋ፡፡ ሕንፃውን ለማስፋፋትና የማዘመን ሥራውን ለማከናወን 11 ሚሊዮን ብር ኢንቨስት የተደረገ ሲሆን፤ ለተጨማሪ 18 ሠራተኞች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡  


Monday, 09 September 2019 11:54

የትምህርት ጥግ

• አንድ ሕጻን፣ አንድ አስተማሪ፣ አንድ መጽሐፍና አንድ እስክሪብቶ ዓለምን መለወጥ ይችላል፡፡
 ማላላ ዩሳፍዛይ
• እኔ አስተማሪ አይደለሁም፤ አነቃቂ እንጂ፡፡
 ሮበርት ፍሮስት
• የተዋጣለት ማስተማር፡- ¼ ዝግጅትና ¾ ቲያትር ነው፡፡
 ጋይል ጎድዊን
• ማስተማር የማይወድ ማንም ሰው ማስተማር የለበትም፡፡
 ማርጋሬት ኢ.ሳንግስተር
• በመማር ሂደት ታስተምራለህ፤ በማስተማር ሂደት ትማራለህ፡፡
 ፊል ኮሊንስ
• ትርጉም ያለው ለውጥ የሚፈጥረው አስተማሪው እንጂ የመማሪያ ክፍሉ አይደለም፡፡
  ማይክል ሞርፑርጎ
• አስተማሪ፤ ፈጣሪ አዕምሮ ያለው መሆን አለበት፡፡
 ኤ.ፒ.ጄ አብዱል ካላም
• ለዓመት የምታቅድ ከሆነ ሩዝ ዝራ፤ ለ አስር ዓመታት የምታቅድ ከሆነ ዛፍ ትከል፤ ለ ሕይወት ዘመን የምታቅድ ከሆነ ሰዎችን አስተምር፡፡
 የቻይናውያን አባባል
• ትምህርት በራስ መተማመንን ይፈጥራል፤ በራስ መተማመን ተስፋን ይፈጥራል፤ ተስፋ ሰላምን ይፈጥራል፡፡
 ኮንፉሺየስ
• የትምህርት ምስጢር ያለው ተማሪውን በማክበር ላይ ነው፡፡
 ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
• ስትማር አስተምር፡፡ ስታገኝ ስጥ፡፡
 ማያ አንጄሎ
• በደስታ የተማርነውን ፈጽሞ አንረሳውም፡፡
 አልፍሬድ ሜርሲዬር
• ልጆችህን በራስህ ትምህርት ብቻ አትቀንብባቸው፤ የተወለዱት በሌላ ዘመን ነውና፡፡
  የቻይናውያን አባባል
• ማስተማር ሁለት ጊዜ መማር ነው፡፡
 ጆሴፍ ጆበርት

Monday, 09 September 2019 11:51

አገራዊ አባባል

• ዕዳ አለኝ ብለህ አትቸገር ዕዳ የለኝም ብለህ አትክበር አይታወቅም የአምላክ ነገር
• ያለ ፍቅር ሰላም፤ ያለ ደመና ዝናብ፡፡
• የሀገሬ ሰዎች ተጠንቀቁ የሰረቁት ስጋ ያስይዛል መረቁ፡፡
• ያመሰገኗት ቅል ባፏ ታፈሳለች፡፡
• መታረቃችን ስለማይቀር፣ ስንጣላ በልክ ይሁን፡፡
• የማይቀርልህን እንግዳ አጥብቀህ ሳመው፡፡
• የጅብ ፍቅር እስኪቸግር፡፡
• በቅሎ ግዙ ግዙ፣ አንድ አሞሌ ጨው ላያግዙ፡፡
• ካለ ፈጣሪ አሟጠሽ ጋግሪ፡፡
• አሳቀኝ ገንፎ ከእራቱ ተርፎ፡፡
• ዓሳውም እንዳያልቅ ውሃውም እንዳይደርቅ፡፡
• አሳዳጊ ለበደለው ፊትህን አትስጠው፡፡
• አሽከሩን አይዳኝ በገናውን አይቃኝ፡፡
• አቅለው ብለው ቆለለው፡፡
• አቀማመጥ ያላወቀ ከባልና ሚስት መሀል ይቀመጣል፡፡
• አባቱን አያውቅ አያቱን ናፈቀ፡፡
• አባት ካነሰው ምግባር ያነሰው፡፡
• አባይ ስለቱ ደስ ማሰኘቱ፡፡
• አባይ አንተ ያየኸኝ ከደረት፣ እኔ ያየሁህ ከጉልበት፡፡

Monday, 09 September 2019 11:43

የግጥም ጥግ

  ጨለማ

       ጨለማዬ
ነውሬን ሸክፎ
እርቃኔን አቅፎ
ሸሽጎ ደብቆ
አኑሮኝ ነበረ
ግና
ብርሀን ይሉት ጠላት
በጨለማዬ ላይ ብርሀኑን አብርቶ
ይኸው ጉድ ሆኛለሁ
ገመናዬ ሁሉ አደባባይ ወጥቶ፡፡
(ዳዊት ጸጋዬ)

Monday, 09 September 2019 11:52

የሙዚቃ ጥግ

 • ሙዚቃ፤ የዝምታ ስኒን የሚሞላ የወይን ጠጅ ነው፡፡
 ሮበርት ፍሪፕ
• ሰዓሊያን ስዕላቸውን በሸራ ላይ ይስላሉ፡፡ ሙዚቀኞች ግን ስዕላቸውን በዝምታ ላይ ይስላሉ፡፡
 ሊዎፖልድ ስቶኮውስኪ
• ሙዚቃ ሕይወት ነው፡፡ ለዚያ ነው ልባችን ምት ያለው፡፡
 ያልታወቀ ሰው
• ከእያንዳንዱ ተወዳጅ ዘፈን ጀርባ ያልተነገረ ታሪክ አለ፡፡
 ኩሻንድዊዝደም
• ሙዚቃ፤ ውብ፣ ቅኔያዊ ነገሮችን ለልብ የመተረኪያ መለኮታዊ መንገድ ነው፡፡
 ፓብሎ ካሳልስ
• ደስተኛ ስትሆን ሙዚቃውን ታጣጥማለህ፡፡ ስታዝን ግጥሞቹን ትረዳለህ፡፡
 ፍራንክ ኦሽን
• የሙዚቃ እውነተኛ ውበት፣ ሰዎችን ማስተሳሰሩ ነው፡፡
 ሮይ አየርስ
• ሙዚቃ የአዕምሮ መድሃኒት ነው፡፡
 ጆን ሎጋን
• ብቸኛው እውነት ሙዚቃ ነው፡፡
 ጃክ ኬሮስ
• ሙዚቃ ሚዛኔ ነው… የሕይወቴ ማዕከል፡፡
 ማንዲ ፓቲንኪን
• ህይወት ያለ ሙዚቃ ስህተት ነው፡፡
 ፍሬድሪክ ኒቼ
• ለእኔ ህይወት ያለ ሙዚቃ ባዶ ነው፡፡
 ጄን ኦስተን
• ሙዚቃ ዓለምን ይለውጣል፤ ምክንያቱም ሰዎችን መለወጥ ይችላልና፡፡
 ቦኖ


Monday, 09 September 2019 11:46

የፍቅር ጥግ


 • ራሳችን ወላጅ እስክንሆን ድረስ የወላጅ ፍቅርን በቅጡ አናውቀውም፡፡
  ሄነሪ ዋርድ ቢቸር
• የተበላሹ አዋቂዎችን ከማቃናት ይልቅ ጠንካራ ሕጻናትን መፍጠር ይቀላል፡፡
 ፍሬድሪክ ዳግላስ
• ልጆቻቸውን የማይወዱ አባቶች አሉ፤ የልጅ ልጁን የማይወድ አያት ግን የለም፡፡
 ቪክቶር ሁጎ
• ፍቅር የልጅ ጨዋታ አይደለም፤ ትልቅ ሃላፊነት ነው፡፡
 ሼክ አፊፍ
• ልጆቼን በምወድበት መንገድ ማንንም ወድጄ አላውቅም፡፡
 ኬቲ ሳጋል
• ሕጻናትን እወዳለሁ፡፡ እኔም በአንድ ወቅት ሕጻን ነበርኩ፡፡
 ቶም ክሩዝ
• የእናት ልብ የሕጻን የት/ቤት ክፍል ነው፡፡
 ሄነሪ ዋርድ ሊቸር
• ሕጻናት ሕይወትህን ተፈላጊ ያደርጉልሃል፡፡
 ኢርማ ቦምቤክ
• ወላጅነት… መጪውን ትውልድ የመምራትና ያለፈውን ትውልድ ይቅር የማለት ጉዳይ ነው፡፡
 ፒተር ክሬቶስ
• ወላጅነት የሕይወት ዘመን ሥራ ነው፤ ልጅ አድጓል ተብሎ አይቆምም፡፡
 ጄክ ስሎን
• ምድርን ከአያቶቻችን አይደለም የወረስነው፤ ከልጆቻችን ነው የተዋስነው፡፡
 የአሜሪካውያን አባባል
• ትልቁ የተፈጥሮ ሃብታችን የልጆቻችን አዕምሮ ነው፡፡
 ዋልት ዲዝኒ
• እያንዳንዱ ሕጻን ሰዓሊ ነው፡፡
 ፓብሎ ፒካሶ

Page 10 of 452