Administrator

Administrator

 የአገሪቱን ጥምር መንግስት የሚመሰርቱት 5 ፓርቲዎች በሴቶች የሚመሩ ናቸው

               የ34 አመቷ ፊንላንዳዊት ሳና ማሪን፣ ባለፈው ረቡዕ፣ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆና መመረጧን የዘገበው ዘ ኢንዲፔንደንት፤ በአለማችን ታሪክ በአነስተኛ ዕድሜዋ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታን የያዘች ቀዳሚዋ ሴት መሆኗን ገልጧል፡፡
ተሰናባቹን የፊንላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቲ ሬኒን ተክታ አገሪቱን እንድትመራ በሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ የተመረጠችውና የትራንስፖርት ሚኒስትር ሆና ስታገለግል የቆየቺው ሳና ማሪን፣ ከሰሞኑ አምስት ፓርቲዎችን ያካተተ ጥምር መንግስት እንደምትመሰርት የጠቆመው ዘገባው፤ የአምስቱም ፓርቲዎች መሪዎች ሴቶች መሆናቸውንና ከአንዷ በስተቀር ሁሉም ከ35 አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ መሆናቸው የአለምን ትኩረት መሳቡን አመልክቷል፡፡
የ34 አመቷ ሳና ማሪን ላለፉት አራት አመታት የፊንላንድ ፓርላማ አባል ሆና መዝለቋን ያስታወሰው ዘገባው፤ በፓርቲዎች አመኔታን በማጣታቸው ሳቢያ ባለፈው ሳምንት ስልጣናቸውን የለቀቁትን ጠቅላይ ሚኒስትር አንቲ ሬኒን ተክታ አገሪቱን እንደምትመራና በአገሪቱ ታሪክ ሶስተኛዋ ሴት ጠቅላይ ሚኒስትር ትሆናለች ተብሎ እንደሚጠበቅም ጠቁሟል፡፡
ሳራ ማሪን ወደ ፖለቲካው አለም የገባቺው የ27 አመት ወጣት እያለች እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ በወቅቱ የትውልድ ከተማዋ ታምፔሪ ምክር ቤት ሰብሳቢ እንደነበረችና በቀጣይ አመታትም በፖለቲካው ዘርፍ ንቁ ተሳትፎ ማድረጓን እንደቀጠለችና በፓርቲው ውስጥ ቁልፍ የአመራር ቦታን መያዟንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአሁኑ ጊዜ አገራትን በመምራት ላይ ከሚገኙ የአለማችን ጠቅላይ ሚኒስትሮች መካከል ዝቅተኛ ዕድሜ አላቸው ተብለው በዘገባው የተጠቀሱት ደግሞ የ39 አመቷ የኒውዝላንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ጃሲንዳ አርደን እና የ35 አመቱ የዩክሬን ጠቅላይ ሚኒስትር ኦሌኪሲ ሆንቻሩክ እንደሚገኙበትም አስታውሷል፡፡

  በአርጀንቲና የሜክሲኮ አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩትና በቅርቡ ከአንድ መደብር 10 ዶላር የሚያወጣ መጽሐፍ ሲሰርቁ ተይዘዋል የተባሉት ኦስካር ሪካርዶ ቫሌሮ፤ በመንግስት ውሳኔ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
የሜክሲኮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ አምባሳደሩ ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ በአርጀንቲና ከሚገኝ አንድ ታዋቂ የመጽሐፍት መደብር፣ የህይወት ታሪክ መጽሐፍ ሲሰርቁ መያዛቸውን የበርካታ መገናኛ ብዙኃን መነጋገሪያ አጀንዳ መሆኑን ተከትሎ፣ ባለፈው ዕሁድ በአፋጣኝ ወደ አገራቸው እንደሚለሱ ተደርጓል፡፡
ቦነሳይረስ ውስጥ ከሚገኘው መደብር መፅሐፉን ሲሰርቁ በጠባቂዎች በቁጥጥር ስር የዋሉትና ለፖሊስ ተላልፈው የተሰጡት የ76 አመቱ አምባሳደር ኦስካር ሪካርዶ ቫሌሮ፤ መጽሐፉን ሲሰርቁ የሚያሳየውና በተለያዩ ማህበራዊ ድረገጾችና መገናኛ ብዙኃን በስፋት እየተሰራጨ የሚገኘው ቪዲዮ እርግጥም ትክክለኛ ሆኖ ከተገኘ፣ የሜክሲኮ የስነምግባር ኮሚቴ፣ በግለሰቡ ላይ የቅጣት እርምጃ ይወስዳል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጠቁሟል፡፡  ግለሰቡ ገንዘብ ሳይከፍሉ የሰረቁት መጽሐፍ በታዋቂው የ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጣሊያናዊ ደራሲ ጂያኮሞ ካሳኖቫ የህይወት ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡


     የአመቱ የጎልደን ግሎብ ሽልማት ዕጩዎች ይፋ ተደረጉ

             ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በ2019 የፈረንጆች አመት በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ ዝነኞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን ታዋቂዋ የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ቴለር ስዊፍት፣ በ185 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ሌላው ዝነኛ ራፐር ካኔ ዌስት በ150 ሚሊዮን ዶላር የሁለተኛነት ደረጃን ሲይዝ፣ ኤዲ ሼራን በ110 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ የሶስተኛነት ደረጃ ላይ መቀመጡን ፎርብስ ባወጣው ዘገባው አስታውቋል፡፡
ዘ ኢግልሰ በ100 ሚሊዮን ዶላር፣ ኤልተን ጆን በ84 ሚሊዮን ዶላር፣ ጥንዶቹ ጄይ ዚ እና ቢዮንሴ ኖውልስ እያንዳንዳቸው በ81 ሚሊዮን ዶላር፣ ካናዳዊው ራፐር ድሬክ በ75 ሚሊዮን ዶላር፣ ፒዲዲ በ70 ሚሊዮን ዶላር፣ ሜታሊካ በ68.5 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውም ተነግሯል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ደረጃን የያዙት ዝነኞች በድምሩ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የጠቆመው ፎርብስ፤ ይህ ገቢ ባለፈው አመት 866 ሚሊዮን ዶላር እንደነበርም አስታውሷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ የ77ኛው የጎልደን ግሎብ የፊልም ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር በሳምንቱ መጀመሪያ ይፋ የተደረገ ሲሆን፣ “ሜሬጅ ስቶሪ” በስድስት ዘርፎች በመታጨት ቀዳሚነቱን መያዙ ተዘግቧል፡፡
ሆሊውድ ፎሪን ፕሬስ አሶሴሽን ባለፈው ሰኞ በካሊፎርኒያ ይፋ ባደረገው የ2020 የጎልደን ግሎብ ሽልማት ዕጩዎች ዝርዝር ውስጥ በ34 ዘርፎች የታጨችው ሜሪል ስትሪፕ፤ በራሷ ተይዞ የነበረውን ክብረወሰን አሻሽላለች፡፡ የዘንድሮው ጎልደን ግሎብ ሽልማት ስነስርዓት በመጪው ጥር መጀመሪያ ይከናወናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


   በድሮ ጊዜ አንድ አንቱ የተባሉ አገረ ገዢ፣ በየክፍለ ሀገሩ እየተዘዋወሩ፣ ህዝቡን እየሰበሰቡ፣ ያነጋግሩ ነበር ይባላል፡፡ አብረዋቸው አዋጅ ገላጮች ነበሩ፡፡ አዋጅ ገላጮቹ በታወጁ አዋጆች ላይ ጥያቄ ቢነሳ የሚያብራሩ የሚገልጡ ናቸው፡፡
 ህዝብ ከተሰባሰበ በኋላ፣ ባለሟሉ ይነሳና፤
“የአገራችን ህዝብ ሆይ! አገረ ገዢው እዚህ ድረስ የመጡት የእናንተን ማናቸውም ብሶት ሊያዳምጡ ነውና ጥያቄያችሁን አቅርቡ” ይላል፡፡
አንዱ ባላገር ይነሳል፡-
“ጌታዬ የግጦሽ መሬት አንሶናል” ይላል
አገረ ገዢው ወደ ፀሐፊው ዞረው፤
“ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል፤
“ማዳበሪያ ይሰጣችኋል ተብለን እስከ ዛሬ አልመጣልንም!”
አገረ ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር ይነሳል - “የዘር  እህል ይታደላል ተብለን ዛሬም አልተሰጠንም”
አገረ - ገዢው - “ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን”
ሌላ ባላገር በንዴት፤
“ጌታዬ! ባለፈውም እንዲሁ እናስብበታለን ሲሉ ነበር፡፡ መቼ ነው በተግባር የሚፈፀምልን? ሁሌ እናስብበታለን ነው እንዴ?”
አገረ - ገዢው - “ይሄም ይመዝገብ፡፡ እናስብበታለን!”
ይሄ በጣም ያናደደው አንድ የጎበዝ - አለቃ፣ አገሬውን በመወከል ይናገራል፡፡
 “ጌታዬ ሆይ! በእኛ ላይ የደረሰውን በደል የሚያህል የትም አገር አይገኝም! ፍትህ ሲጠፋ አቤት የምንልበት ቦታ የለም! ጤና ሲጠፋ የምንታከምበት ቦታ የለም! ትምርት ሲጠፋ የምንማርበት ቦታ የለም፡፡ መንገዱ ሲጠፋ አሳብረን የምንሄድበት አቋራጭ እንኳን የለም፡፡ እህል ሲጠፋ አንጀታችንን የምንጠግንበት፣ ውሃ ጥም ስንቃጠል ጥማችንን የምንቆርጥበት ምንም መፍትሄ የለንም! አሁን እናንተ፤ እያስተዳደርን አገር እየመራን ነው ትላላችሁ? እኛ ህዝቡን ማስነሳትኮ አላጣንበትም! እናንተም ደግ ደጉን አርጋችሁልን፣ እኛም ደግ ደጉን አስበንላችሁ ብንኖር አይሻልም?” አለ፡፡
አገሬው አጨበጨበ!
አገረ ገዥውም፤
 “የአገሬ ህዝብ ሆይ!
ይሄ የጎበዝ አለቃ ጥሩ ይናገራል፤ ግን ዕድሜ የለውም!” አሉ
አገሬው አሁንም አጨበጨበ!
ያ ጎበዝ - አለቃም ከዚያን ቀን በኋላ አልታየም፡፡
*   *   *
ሁልጊዜ “እናስብበታለን” አያዋጣም፡፡ አፈፃፀም ያስፈልጋል፡፡ በዘመንኛው ቋንቋ ቢሮክራሲያዊ ማነቆ (Bureaucratic red - tape) መበጠስ አለበት እንደ ማለት ነው፡፡ ጥንት ንጉሡ የወሰኑትን አስፈፃሚዎቹ ባለሟሎች፤ “እሺ” “እሺ” እያሉ በተግባር ግን አንዷንም ነገር አያውሉም ነበር ይባላል፡፡ ይሄ ክፉኛ ያቆሰለው በደለኛ ንጉሡ ዘንድ ይቀርብና፤
“ጃንሆይ! ሁሉም ነገር ይቅርብኝና አንድ ሃያ አጋሠሥ ይሰጠኝ” ሲል አቤት ይላል፡፡
 ጃንሆይም “ለምንህ ነው?” ቢሉት፣
“የሸዋን መኳንንት ‹እሺታ› የምጭንበት”፣ አለ ይባላል፡፡ ውሳኔዎች፣ መመሪያዎች፣ አዋጆች፣ ወዘተ በሥራ ላይ ካልዋሉ፣ ካለንበት ንቅንቅ አንልም፡፡ ጌቶች ቢያስነጥሱ መሀረብ የሚያቀብሉ ዓይነት ሰዎች መቼም፣ የትም ድረስ አያራምዱንም! ጉዳያችሁን ተናገሩ:: ብሶታችሁን አውጡ፡፡ ጥያቄያችሁን አቅርቡ፤ ብሎ ‹እድሜህ አጭር ነው› ከሚል ይሰውረን፡፡ ለአጥቂውም ለተጠቂውም ከሚያጨበጭብ ተሰብሳቢም ይሰውረን፡፡
ያልተመለሰ ጥያቄ ያልተከፈለ ዕዳ ነው፡፡ ነገ ዋጋ ያስከፍለናል፡፡ ዛሬ አድበስብሰን የምናልፈው ጥያቄ፤ የነግ የቂም ቋጠሮ ይሆንብናል፡፡ ያ ደግሞ ዕድገትን ተብትቦ ያሰናክለዋል፡፡ የበላይ ወደ ታች የሚመራውን፣ የበታች እንደ “ኮምፒዩተር ጌም” ሲጫወትበት የሚውል ከሆነ፤ እንኳን ትራንስፎርሜሽን መደበኛውም ዕድገት አይገኝም፡፡ “ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ” መሆን የሚመጣው፣ ለትልቁ ስዕል አስተዋፅኦ የሚያደርጉት ትናንሽ ስዕሎች በቅጡ ካልተሳሉና ሥጋና ደም ሳይለብሱ የቀሩ እንደሆነ ነው፡፡ የበታች አካላት ማያያዣ ክር ናቸው፡፡ እነሱ ከተበጣጠሱ የበላይ አካላት የሉም፡፡ ይሄ በቢሮክራሲያዊው ዓለም ብቻ ሳይሆን በፖለቲካ ፓርቲዎችም ዘንድ ያው ነው፡፡ ትናንሽ ስህተቶች ለግዙፍ ስህተት አሳልፈው ይሰጡናል፡፡ ያኔ ውድቀት ቅርብ ይሆናል፡፡
 ሱን ሱ የተባለ የቻይና ጦር መሪ “በጦርነት ድል ማድረግ የሚደጋገም ነገር አይደለም፡፡ ሁሉ ቅርፁን ይለውጣል፣ ውሃ ሁሌም አንድ አይነት ቅርፅ የለውም - እንደ መያዣው ዕቃ ይለዋወጣል:: እንደ ባላንጣህ አካሄድ ቅርፅህን እየለዋወጥክ ድል መቀዳጀት ረቂቅ - ሊቅ (genius) ይባላል” ይለናል፡፡ ስለ ህይወት፣ ስለ ማናቸውም ትግል፣ ስለ ምርጫ፣ ስለ ለውጥ ስናስብ ሁሌም እንደ ሁኔታው  አካሄድን ቀይሮ በብስለት መጓዝን አንርሳ፡፡  ረቂቅ - ሊቅ የመሆን ጥበብ ይሄ ነው:: በሌሎች ድክመት ላይ ከመንተራስ በራስ መተማመን ብልህነት ነው! አንዴ የሆነው ነገር ላይ ከማላዘን ይልቅ ሁኔታዎችን በሌላ አቅጣጫ ለመለወጥ (Reversal) መሞከር አዲስ ቅያስ ለማየት ይጠቅመናል፡፡ ሳይታለም የተፈታን ጉዳይ (de facto) ደግመን ደጋግመን መወትወት ያው ውሃ ወቀጣ ነው፡፡ የተሰረቀው ተሰርቋል፡፡ የተሄደው ድረስ ተሄዷል፡፡ የባላንጣችን አቅም ታውቋል፡፡ ዘዴና መላው በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ስለዚህ የታወቀን መንገድ ትቶ፣ ያልተሄደበትን መንገድ ወይም ብዙ ያልተሄደበትን መንገድ (The Road Less Travelled) ማሰብና ማስላት ይሻላል፡፡ የሆነውማ ሆኗል - “ለሰጠውም አላሳነሰው፣ ላልሰጠውም አላቀመሰው!”  


Saturday, 07 December 2019 13:06

የዘላለም ጥግ

   (ስለ ጦርነት)›
- በሰላም ጊዜ ወንድ ልጆች አባታቸውን ይቀብራሉ፡፡ በጦርነት ጊዜ አባቶች ልጆቻቸውን ይቀብራሉ፡፡
   ክርሱስ
- በጦርነት ላይ ሁለተኛ የወጣ ሽልማት አያገኝም፡፡
   ጀነራል ኦማራ ብራድሌይ
- እኛ ጦርነትን የማናቆም ከሆነ፣ ጦርነት እኛን ያቆመናል፡፡
   ኤች ጂ ዌልስ
- ከጦርነት የሚያተርፈው ማን እንደሆነ አሳየኝና፣ ጦርነቱ እንዴት እንደሚቆም አሳይሃለሁ፡፡
   ሄነሪ ፎርድ
- ጦርነት ሠላም ነው፡፡ ነፃነት ባርነት ነው፡፡ ድንቁርና ጥንካሬ ነው፡፡
   ጆርጅ ኦርዌል
- ሠላም የግጭት አለመኖር አይደለም፡፡ ግጭትን በሠላማዊ መንገዶች የመፍታት ችሎታ ነው፡፡
   ሮናልድ ሬገን
- ጦርነት የዲፕሎማሲ ውድቀት ነው፡፡
   ጆን ዴንጌል
- የሁሉም ጦርነቶች ዓላማ ሰላም ነው፡፡
   ሴይንት ኦውጉስቲን
- ጦርነት ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፡፡ ፍቅር ግን ጦርነትን ሊያጠፋ ይችላል፡፡
   ሄለን ላገርበርግ
- ጦርነት ለማንኛውም ችግር ዘላቂ መፍትሔ አይደለም፡፡
   አብዱል ካላም
- ጦርነት ዘላቂ ሞት እንጂ ዘላቂ ሰላም አያመጣም፡፡
   ጃኔት ሞሪስ
- እውነተኛ ወታደር የሚዋጋው ፊት ለፊቱ ያለውን ስለሚጠላ ሳይሆን ከጀርባው ያለውን ስለሚወድ ነው፡፡
   ጂ.ኬ.ቼስቶርቶን

Saturday, 07 December 2019 13:05

ማን ምን አለ?

(ስለ ኢትዮጵያ)
- ሞዴሊንግ የጀመርኩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ምክንያቱም ያደግሁት እዚያ ነው:: ት/ቤት በሚዘጋጅ የ ፋሽን ትርኢት ላይ በመስራት ነው የጀመርኩት፤ ሙያው ደስ ይለኝ ስለነበር በዚያው ገፋሁበት፡፡
   ሊያ ከበደ (ሞዴል)
- የኢትዮጵያ የልጅነት ትውስታ የለኝም:: ወደ ኒውዮርክ ተሻግሬ፣ ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ጋር መገናኘት እስክቀላቀል ድረስ ስለ ኢትዮጵያ ባህል ምንም አላውቅም ነበር፡፡
   ማርከስ ሳሙኤልሰን (ትውልደ - ኢትዮጵያዊ ሼፍ)
- አሜሪካን ከቬትናም ወይም ከኢትዮጵያ ለይቼ የማያት አይመስለኝም፡፡ ይሄ “የኛ ቡድን ከአንተ ቡድን ይሻላል” ይሉት ቅኝት - የተማሪ ሀሳብ ነው፡፡ ልጆቼ እንዲህ ያሉ የልዩነት መስመሮች አይገባቸውም፡፡ እኔም እንዲገባኝ አልሻም፡፡
    ብራድ ፒት (የፊልም ተዋናይ)
- አገሬ ሁልጊዜ በቁርጠኝነትና በጀግንነት እንደምታሸንፍ ዓለም እንዲያውቅ እፈልጋለሁ፡፡
    አበበ ቢቂላ (የማራቶን ጀግና)
- በኢትዮጵያ መልከ ጥፉ ሰዎች አላየሁም:: ኦፕራ ዊንፍሬይ
    (አሜሪካዊት የቶክ ሾው አዘጋጅ)
- ኢትዮጵያ የድሮው ዓይነት የሙስና ችግር አልነበራትም፡፡ የአፍሪካ መሪዎች በኛ ይቀኑ ነበር፡፡
    ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም (የቀድሞ ፕሬዚዳንት)
- ለኢትዮጵያ መሮጥ ብፈልግ እንኳን መንግስት ወይም ፌደሬሽን ይመርጡኛል ብዬ አልጠብቅም፡፡
    ፈይሳ ሌሊሳ (አትሌት)
- እንግሊዝ ራሷን እንደ ሰለጠነ አገር እንደምትቆጥር አውቃለሁ፤ ለእኔ ግን በብዙ መንገድ ኢትዮጵያ በእጅጉ ስልጡን አገር ትመስለኛለች፡፡
    ዶ/ር ካትሪን ሃምሊን (በኢትዮጵያ የፌስቱላ ሆስፒታል መስራች)

  በ2018 በመላው አለም 228 ሚሊዮን ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል

          ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በመላው አለም 228 ሚሊዮን ሰዎች በወባ በሽታ መጠቃታቸውንና ከእነዚህም መካከል 405 ሺህ የሚሆኑት ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
በአመቱ በአለማቀፍ ደረጃ በወባ ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከ93 በመቶ በላይ የሚሆኑት ወይም 213 ሚሊዮን ያህሉ አፍሪካውያን መሆናቸውንና በመላው አለም በበሽታው ከተጠቁት ሰዎች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የአምስት የአፍሪካ አገራት ማለትም፡- የናይጀሪያ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኡጋንዳ፣ ኮትዲቯር፣ ሞዛምቢክና ኒጀር ዜጎች መሆናቸውንም ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ይፋ ባደረገው አመታዊ ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
የወባ በሽታ ክስተት ባለፉት አስር አመታት በአለማቀፍ ደረጃ መቀነሱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በአመቱ በበሽታው ሳቢያ ለሞት የተዳረጉት ሰዎች ቁጥርም ከአንድ አመት በፊት ከነበረው 416 ሺህ ወደ 405 ሺህ ዝቅ ማለቱንም አስረድቷል፡፡ በአመቱ በከፍተኛ ሁኔታ በበሽታው ከተጠቁት የህብረተሰብ ክፍሎች መካከል ከአምስት አመት ዕድሜ በታች የሚገኙ ህጻናት ቀዳሚነቱን እንደሚይዙ የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ለሞት ከተዳረጉት መካከልም 67 በመቶው ወይም 272 ሺህ ያህሉ በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት መሆናቸውን ገልጧል፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በወባ በሽታ የተጠቁባት አገር ናይጀሪያ መሆኗንና በአለማችን በበሽታው ምክንያት ከሞቱ ሰዎች መካከል ሩብ ያህሉ ናይጀሪያውያን እንዲሁም 11 በመቶው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ 5 በመቶው የታንዛኒያ ዜጎች መሆናቸውንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
ባለፈው የፈረንጆች አመት 2018 ብቻ በአለማቀፍ ደረጃ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በመንግስታትና በአለማቀፍ ለጋሾች 2.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ያህል ገንዘብ ወጪ መደረጉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ባለፉት ሁለት አመታት ጊዜ ውስጥ 578 ያህል በኬሚካል የተነከሩ አጎበሮች ለተለያዩ አገራት መሰራጨታቸውንም አስታውሷል፡፡


  የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ” እየተባለ የሚጠራውና በየአራት አመቱ በተመረጡ የአለማችን ከተሞች የሚካሄደው አለማቀፉ የትያትር ፌስቲቫል በሩስያዋ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ እየተከናወነ እንደሚገኝ ኒውዮርክ ታይምስ ዘግቧል፡፡
ቻይና፣ ቤልጂየም፣ ፖላንድ፣ ጣሊያን፣ ህንድና ፈረንሳይን ጨምሮ 22 የተለያዩ የአለማችን አገራት በሚሳተፉበት የዘንድሮው የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ በድምሩ 104 ትያትሮች ለእይታ የሚበቁ ሲሆን፣ ከእነዚህ ትያትሮች መካከል 78 የሚሆኑት በሩስያ የተዘጋጁ እንደሆኑም ዘገባው አመልክቷል፡፡
ፌስቲቫሉ ምንም እንኳን የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”  የሚል ስያሜ ቢሰጠውም፣ በአገራት የሚዘጋጁ ትያትሮችን ለእይታ በማብቃት በኪነጥበብ አማካይነት ባህልን፣ ታሪክንና ማንነትን በማንጸባረቅ ትስስርን ከማጎልበትና በባለሙያዎች መካከል ልምድ ከመለዋወጥ ባለፈ በውድድር መልክ ሽልማት የሚሰጥበት አለመሆኑ ተነግሯል፡፡
ለ25ኛ ጊዜ በሩስያ በመከናወን ላይ የሚገኘውና የተለያዩ ዓለማቀፍ ታዋቂ የትያትር አዘጋጆችና ተዋንያን እየተሳተፉበት ያለው የ2019 የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ በመጪው ሳምንት መጨረሻ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ዘገባው ጠቁሟል፡፡ እ.ኤ.አ በ1994 የተጀመረው የአለም “የትያትር ኦሎምፒክ”፤ ከዚህ ቀደምም ቻይና፣ ግሪክ፣ ጃፓን፣ ቱርክና ደቡብ ኮርያን ጨምሮ በተለያዩ የአለማችን አገራት ከተሞች በስኬታማ ሁኔታ መከናወኑንም ዘገባው አስታውሷል፡፡  

     ሙጋቤ በባንክ ያላቸውን 10 ሚ. ዶላር ጨምሮ ሃብታቸውን ሳይናዘዙ መሞታቸው ተነገረ

                      የኡጋንዳው ፕሬዚደንት ዮሪ ሙሴቬኒ፤ ዕድሜ ዘመናቸውን ሲኖሩ፣ ከማንም ሰው ምንም ነገር ሰርቀው እንደማያውቁ ሰሞኑን ለአገራቸው ህዝብ በአደባባይ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ሙሴቬኒ ባለፈው እሁድ በሺህዎች የሚቆጠሩ ኡጋንዳውያን ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በመዲናዋ ካምፓላ በተከናወነ የጸረ-ሙስና የእግር ጉዞ ላይ ከተሳተፉ በኋላ ለህዝቡ ባደረጉት ንግግር፣ “በህይወት ዘመኔ ምንም ነገር ሰርቄ አላውቅም፤ ስላልሰረቅኩ ግን ድሃ አልሆንኩም!” ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
“ሙሰኞች ጥገኛ ተዋህሲያን ናቸው፤ ምክንያቱም የራሳቸው ያልሆነ ሃብት ነው የሚያፈሩት፡፡ መንግስታችን ሙሰኞችን ለመዋጋት ቆርጦ ተነስቷልና ህዝባችን ከጎኑ እንዲቆም ጥሪዬን አስተላልፋለሁ” ብለዋል ሙሴቬኒ፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ በቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ፣ የግል የባንክ ሂሳብ ውስጥ 10 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ ዚምባቡዌን ለ37 አመታት ያህል አንቀጥቅጠው የገዙትና ባለፈው መስከረም ወር በ95 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት የተለዩት ሙጋቤ፤ በባንክ ያስቀመጡትን 10 ሚሊዮን ዶላር፣ አራት መኖሪያ ቤቶችን፣ አስር መኪኖችንና አንድ ግዙፍ እርሻ ጨምሮ ሃብታቸውን ለማንም ሳይናዘዙ ማለፋቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ ህግ መሰረት አንድ ሰው ሃብቱን ማን እንደሚወርሰው ሳይናዘዝ ከሞተ ለትዳር አጋሩና ልጆቹ እንደሚከፋፈል የጠቆመው ዘገባው፤ የሙጋቤን ሃብትም ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤና አራት ልጆቻቸው ይወርሱታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክቷል፡፡              “ዴስትኒ ኢትዮጵያ” በሚለው ቡድን ባለፈው ሳምንት ከስካይ ላይት ሆቴል በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ሲተላለፍ የመመልከት ዕድል የገጠማቸው
ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው አዲስ ተስፋ ማቆጥቆጡን ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በታች ጥቂት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን ስሜታቸውን ለአዲስ አድማስ አጋርተዋል፡፡

             “እጅግ የተገረምኩበትና ለአገሬ ተስፋ የሰነቅኩበት መድረክ ነው
                     ገዛኸኝ ፀጋው (ዶ/ር)

            ዴስቲኒ ኢትዮጵያ የተባለው ቡድንና አጠቃላይ ሃሳቡ በእጅጉ የተደነቅኩበትና ለአገሬ ተስፋ የሰነቅኩበት ነው፡፡ በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩና በዙሪያቸው ያሉት ሰዎች ከጀርባ ስራቸውን በዝምታና በትጋት እየሰሩ ስለመሆናቸው ያየሁበትም ጭምር ነው፡፡ የዚህ የስልጠና ሞዴሉም ቢሆን፤ ለአገራችን ጠቃሚና በደቡብ አፍሪካ ተሞክሮ በእጅጉ ውጤታማ የሆነ ነው፡፡  
ከምንም በላይ የኦነጉ ዳውድ ኢብሳና የአብኑ ዶ/ር ደሳለኝ ጐን ለጐን ተቀምጠው ሲወያዩና ሲነጋገሩ ማየት በራሱ በእጅጉ አስደሳች ነው፡፡ ይህ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም ነበር፡፡ ሁለቱ ሰዎች ማስመሰል የሌለበትና ተፈጥሯዊውን ውይይት ነው ያሳዩን፡፡ ይሄ እንደ አንድ ለአገሩ እንደሚያስብና ለአገሩ እንደሚጨነቅ ዜጋ ተስፋን የሚያጭርና የሚያስደስት ነው፡፡

_______________

                 “የአገሪቱ ትልቁ ችግር የልሂቃን አለመወያየት ነበር”
                      ጋዜጠኛ የኋላሸት ዘሪሁን

         ትልቁ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር የልሂቃን ቁጭ ብሎ አለመነጋገር ነበር፡፡ አሁን ይሄ መጀመሩ በአገራችን ላይ የተጋረጠውን አደጋ ያስቀራል የሚል ትልቅ ተስፋ ስለሰነቅኩኝ፣ ጉዳዩን እጅግ በበጐ ጐኑ ተመልክቼዋለሁ፡፡ ምክንያቱም ጽንፍ ለጽንፍ ሆነው በጥላቻ ሲተያዩ የነበሩት ሁሉ ኢትዮጵያ በምትባል በአንዲት ትልቅ አገር ስር ተሰባስበው ችግራቸውን በውይይት ለመፍታት ውስጥ ለውስጥ ከ6 ወራት በላይ ሲመክሩ መቆየታቸው፣ በራሱ በአይነቱ የተለየና እሰየው የሚያስብል ነው፡፡
በዋነኝነት አሁን የተቀመጡት ስለ ፓርቲ ወይም ስለ ግለሰብ ጉዳይ ለመነጋገር ሳይሆን  ስለ ኢትዮጵያ ጉዳይ መፍትሔ ለመፈለግ መሆኑ ነው ይበልጥ አስደሳች የሚያደርገው፡፡
በተጨማሪም በዴሞክራሲ ግንባታና ሂደቱ ላይ አብረው መስራት እንዳለባቸው፣ በምንም መልኩ ሕዝብ እርስ በእርሱ መጫረስ እንደሌለበት፣ ችግሮች ሲከሰቱም በሰከነ መንገድ በውይይት መፈታት እንዳለበት ነው የተነጋገሩት:: በሌላ መልኩ ለአገር ጉዳይ ቅድሚያ ሰጥተው በልዩነታቸው ላይ በቀጣይነት መወያየት እንዳለባቸው መነጋገራቸው በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡
ይህንን ደግሞ የተወያዩት ለመጠፋፋትና ለመጨራረስ የሚፈላለጉ ቡድኖች መሆኑ የሚደንቅ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦነግና አብንን የሚመሩ ሰዎችን ተመልከቺ፡፡ ኦነግና አብንን ተይውና የዘውግ ፌዴራሊዝምንና የጂኦግራፊ ፌደራሊዝምን የሚከተሉ እጅግ ጫፍና ጫፍ ያሉ ወገኖች ጐን ለጐን ቁጭ ብለው መነጋገር መቻላቸው በአገሬ ላይ ተስፋ እንዳልቆርጥና ጭንቀቴ ቀለል እንዲል አድርጐኛል፡፡ በዚህ ረገድ ጉዳዩ በአይነቱም ለየት ያለ ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ አገር ባለው ልምድ እንደዚህ አይነት ነገር ይጀመርና በወሬ ያልቃል፡፡ ይሄኛውን ስናይ ግን ምንም እንኳን ሰሞኑን በይፋ በሚዲያ ይውጣ እንጂ ለረጅም ወራት (ለግማሽ ዓመት) ውስጥ ለውስጥ ሲሰራ ቆይቶ እዚህ መድረሱ ያስገርማል፡፡

____________________


                     “ፍቅር የነገሰበት፤ ጥላቻ የደቀቀበት መድረክ ነው”
                              ጋዜጠኛ ጌጡ ተመስገን


           ትንሿን ኢትዮጵያን ነው በዚያ አዳራሽ የተመለከትኩት፡፡ ከምን አንጻር መሰለሽ? የሀሳብ ልዩነት ያላቸው፣ በባላንጣነት የሚተያዩ፣ አንድም ቀን ሳይቀራረቡ ማዶ ለማዶ ሆነው ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቧ የሚያቀነቅኑ ከጀርባቸው መዓት ተከታይ ያላቸው ሰዎች ናቸው አንድ ጣሪያ ስር ቁጭ ብለው ሲነጋገሩና ሲወያዩ የነበሩት፡፡ ይሄ እስካሁን ያልተሞከረ አካሄድ ነው፡፡ ይሄ ትልቅ ጅማሮ ነው፡፡ መድረኩ ፍቅር የነገሰበት ጥላቻ የደቀቀበት፤ በተቃርኖ ጎራ የነበሩ ሰዎች ለአገርና ለሕዝብ ክብር ያሳዩበት መድረክ ነው እላለሁ፡፡
ለምን ለስድስት ወር ይፋ አልሆነም ለሚለው ‹‹ግልጽነት ለዘላለም ይኑር›› የሚለው እሳቤ በኢትዮጵያዊያን ልብና ምድር መስፈን አለበት ብዬ አምናለሁ፡፡ ምስጢር አድርገው ማቆየታቸውን አልስማማበትም፡፡ ምክንያቱም ለአገርና ለሕዝብ የሚደበቅ አንዳችም ነገር እንደማይኖር ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም ተናግረዋል፡፡ አገርና ሕዝብ አብሮ ማወቅ፣ ሀሳቡን መደገፍና የማይጥም ነገርም ካለው መንቀፍ አለበት፡፡ ስለዚህ በድብብቆሽ ሳይሆን “ግልጽነት ለዘላለም ይኑር” በሚለው እሳቤ፣ ወደፊት መራመድ አለባቸው ይህንን የምለው ለምን መሰለሽ? ይፋ ቢሆንና በርካታ ሰው ቢነጋገርበት፣ የበለጠ የዳበረና ጠቃሚ ሀሳብ ለቡድኑ ግብአት መሆን ይችል ነበር ብዬ ስለማምን ነው፡፡  ዞሮ ዞሮ ሰዎች የሀሳብ ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ሰላም እንዲሰፍን፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበርና የአገር ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ተቀራርቦ ለመነጋገርና በአገር ዕጣ ፋንታ ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳደር ቁርጠኝነት ማሳየታቸው ራሱን የቻለ ስልጣኔ ነው፡፡
እነዚህ ሰዎች ተቀራርበው ሲነጋገሩ፣ አፍ ለአፍ ገጥመው በወንድማማችነት መንፈስ ሲወያዩ የተሰማኝ ስሜት እውነተኛ ስሜት “ፍቅር ለዘላለም አይወድቅም፤ ደግሞሞ ፈጣሪ ሁሌም ኢትዮጵያን ይጠብቃታል” የሚለው ነው፡፡ ፈጣሪ ልጆቿንና ኢትዮጵያን ይታደጋታል የሚለው የምንጊዜም እምነቴ እንዳይሸረሸርና ይበልጥ እንዲፀና አድርጐልኛል፡፡ በዚያ አዳራሽ ውስጥ የነበሩት ሁሉም የአንዲት አገር የኢትዮጵያ ልጆች ናቸው፤ የተለየው ሀሳባቸው እንጂ አገራቸው ወንድማማችነታቸው አይደለም፡፡ በዚያ አዳራሽ ፍቅር፤ ወንድማማችነትና የሰለጠነ ንግግር ጐልቶ ተንፀባርቋል፡፡ የኢትዮጵያን ቀጣይ ንጋት ለማመላከት መሞከራቸው ስልጣኔን ያሳያል፡፡ በእርግጠኝነት አመርቂ ውጤት ያመጣል የሚል እምነትም ተስፋም አሳድሮብኛል፡፡    

Page 9 of 464