Administrator

Administrator

 * “መጸዳጃ ቤት ተቆልፎብናል፤ ውሃና መብራትም ተቋርጦብናል”   - ተቃዋሚዎች
                         * ፓርላማው 97 ሺህ ዶላር የመብራት ኪራይ አልከፈለም
    የሚመለከተው የመንግስት አካል መክፈል የሚገባውን 97 ሺህ ዶላር የመብራት ኪራይ ባለመክፈሉ ሳቢያ በኬንያ ፓርላማ ለ3 ቀን መብራት መቋረጡንና ይህም የተቃዋሚ ፓርቲ ፓርላማ አባላትን ክፉኛ ማስቆጣቱን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ተቃዋሚዎቹ ለክስተቱ መንግስትን ተጠያቂ ማድረጋቸውንና የውሎ አበል እንደማይከፈላቸው በምሬት መናገራቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ የገዢው ፓርቲ አባላት በበኩላቸው፣ ለመንግስት ወግነው መከራከራቸውን ገልጧል፡፡
ካለፈው ሳምንት አርብ ጀምሮ እስከ ሰኞ ድረስ የፓርላማው መብራት መቋረጡ በአባላቱ መካከል ውዝግብ መፍጠሩን የገለጸው ዘገባው፣ በወቅቱም የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ የሆኑት አዳን ኬናን የተባሉ የፓርላማው አባል አንድ የኤሌክትሪክ ሃይል መስመር ጥገና ባለሙያ ድንገት ከተፍ ብሎ የፓርላማውን የመብራት መስመር እንደቆረጠው ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡ሌላው የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካይ ችሪስ ዋማላዋ በበኩላቸው፣ በነጋታውም መጸዳጃ ቤት ለመጠቀም ፈልገው ወደዚያው ሲያመሩ ተቆልፎ እንዳገኙትና በፓርላማው ግቢ ውስጥ የውሃም ሆነ የመብራት አቅርቦት እንዳልነበር ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡
የኬንያ መንግስት እየተባባሰ የመጣ የገንዘብ እጥረት ቀውስ ውስጥ እንደገባ የገለጸው የቢቢሲ ዘጋቢ፣የፓርላማው የፋይናንስ ኮሚቴ አባላትም በጉዳዩ ዙሪያ ለመምከር መሰብሰባቸውን ገልጾ፣ ይሄም ሆኖ ግን ለፋይናንስ ቀውሱ ተጠያቂው ማነው በሚለው ጉዳይ ዙሪያ ተቃዋሚዎችና የገዢው ፓርቲ አባላት ሊግባቡ አለመቻላቸውን ጠቁሟል፡፡

  - 273 ግለሰቦችና ተቋማት በዕጩነት ቀርበዋል

       የዘንድሮው የዓለም የኖቤል ሽልማት ተሸላሚዎች ዝርዝርም በያዝነው ሳምንት ይፋ መደረግ የጀመረ ሲሆን፣ ተሸላሚዎችም ከአንድ ወር በኋላ በስቶክሆልምና በኦስሎ በሚከናወኑ ስነስርዓቶች የገንዘብ ሽልማታቸውን ይቀበላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የኖቤል የሽልማት ድርጅት ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ በዘንድሮው የኖቤል ሽልማት የተለያዩ ዘርፎች 205 ግለሰቦችና 68 ተቋማት በዕጩነት የቀረቡ ሲሆን የየዘርፉ ተሸላሚዎችም ይፋ መደረግ ጀምረዋል፡፡
በሳምንቱ ይፋ ከተደረጉት የ2015 የኖቤል ሽልማት ዘርፎች አሸናፊዎች መካከል፣ የፊዚክስ ዘርፍ ተሸላሚዎቹ ጃፓናዊቷ ታካኪ ካጂታ እና ካናዳዊው አርተር ቢ ማክዶናልድ ይጠቀሳሉ፡፡ ሁለቱ ተመራማሪዎች ለዚህ ሽልማት የበቁት፣ በኒዪትሮኖች ባህሪ ዙሪያ ባደረጉት ምርምር ባበረከቱት ቁልፍ አስተዋጽኦ ነው ተብሏል፡፡
ረቡዕ ዕለት ይፋ የተደረገው የኬሚስትሪ ዘርፍ የኖቤል ተሸላሚዎች ውጤት ደግሞ፣ ስዊድናዊው ቶማስ ሊንዳል፣ አሜሪካዊው ፖል ሞድሪች እና ቱርክ-አሜሪካዊው አዚዝ ሳንካር አሸናፊ መሆናቸውን ያሳወቀ ሲሆን፣ በዲኤንኤ ዙሪያ በጋራ ያደረጉት ምርምር ተሸላሚ እንዳደረጋቸው የሽልማት ኮሚቴው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባለፈው ሰኞ በስዊድኑ ካሮሊንስካ ኢንስቲቲዩት ይፋ የተደረገው የ2015 የኖቤል የህክምና ዘርፍ ሽልማት ውጤት ደግሞ፣ የዘንድሮውን የዘርፉ ሽልማት ዊሊያም ሲ ካምቤል፣ ሳቶሺ ኦሙራ እና ቱ ዮዩ የተባሉ ሶስት ሳይንቲስቶች እንደተጋሩት ገልጧል፡፡
የሽልማቱን ግማሽ ገንዘብ የሚወስዱት በዘርፉ ተሸላሚ በመሆን የመጀመሪያዋ ቻይናዊት ሳይንቲስት ቱ ዮዩ ሲሆኑ፣ የወባ በሽታን በማዳን ረገድ ወደር እንደማይገኝለት የተነገረለትን መድሃኒት በመፍጠራቸው ለሽልማት የበቁ ተመራማሪ ናቸው፡፡ ቀሪውን ግማሽ ገንዘብ ለሁለት የሚካፈሉት ደግሞ፣ በጋራ ምርምራቸው በፈጠሩት አርቴምሲኒን የተሰኘና በጥገኛ ተዋህስያን ሳቢያ የሚከሰቱ በሽታዎችን የሚያድን መድሃኒት ተሸላሚ የሆኑት ጃፓናዊው ማይክሮ ባዮሎጂስት ሳቶሺ ኦሙራ እና አሜሪካዊው ሳይንቲስት ዊሊያም ካምቤል ናቸው፡፡
በ2015 የዓለም የኖቤል ሽልማት የስነጽሁፍ ዘርፍ ደግሞ፣ ቤላሩሳዊቷ ደራሲ ቬትላና አሌክሴቪች ተሸላሚ መሆኗን የሽልማት ድርጅቱ ከትናንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ ይፋ አድርጓል፡፡
ትናንት ይፋ በተደረገው የ2015 የኖቤል የሰላም ሽልማት ውጤት መሰረትም፣ በዘርፉ ናሽናል ዲያሎግ ኳርቴት የተባለው የቱኒዝያ ተቋም በአገሪቱ ብዝሃነት ያለው ዴሞክራሲ ለመፍጠር ባደረገው አስተዋጽኦ ተሸላሚ የሆነ ሲሆን፣ የኢኮኖሚከስ ዘርፍ ተሸላሚዎች ደግሞ ከነገ በስቲያ ይፋ እንደሚደረጉ ይጠበቃል፡፡
እ.ኤ.አ ከ1901 እስከ 2014 ድረስ ለ567 ጊዚያት በተከናወኑት የዓለም የኖቤል እና የኢኮኖሚክ ሳይንስስ ሽልማቶች፣ በድምሩ 889 ግለሰቦችና ተቋማት ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ለፓርላማ እንቅልፍ መድሃኒቱ፣ ብርቱ “ተቃዋሚ ፓርቲ; ነው!
            ሙሴቬኒም ፓርላማ ውስጥ እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ ተይዘዋል!
            አዲስ መንግስት ተቋቋመ ወይስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ተፐወዙ?
   ሰሞኑን ከፓርላማው መከፈትና አዲስ መንግስት መቋቋም ጋር ተያይዞ ሲናፈስ የሰነበተው ወሬ  የአንድ ም/ቤት አባል ማንቀላፋት (ሸለብታ!) ነው፡፡ እኔ የምለው… በፓርላማ ወይም በስብሰባ ላይ መተኛት ያን ያህል ብርቃችን ነው እንዴ? (ደርሰን ንቁ ስንመስል ገርሞኝ እኮ ነው?!) የአገራቸው የፓርላማ አባላት በጅምላ እያንቀላፉ ያስቸገሯቸው የምዕራብ አፍሪካ ጋዜጠኞች ምን አሉ መሰላችሁ? “በቲቪ የቀጥታ ስርጭት ለህዝብ በሚደርስ የፓርላማ ጉባኤ ላይ ያንቀላፉ ፖለቲከኞች፤በየግል ቢሮአቸው ሲሆኑ ምን ሊያደርጉ ነው?!” (እዚያማ አልጋ ከእነፍራሹ ይኖራቸዋል!!)
ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ--- ከጥቂት ዓመታት በፊት የሰማኋት አንዲት የፓርላማ ቀልድ ትዝ አለችኝ፡- አንድ የፓርላማ አባል በጉባኤ ላይ፣ ትኩስ ቡና ሲቀርብላቸው ምን አሉ መሰላችሁ? “አይ እኔ አልጠጣም፤እንቅልፍ ይረብሸኛል!” (የፓርላማ እንቅልፍ ለምደዋል ማለት ነው!) ዝም ብዬ ሳስበው---የሰሞኑ የፓርላማ “ማንቀላፋት” ከሌላው ጊዜ ለየት ሳይል  እንደማይቀር ገመትኩ፡፡ እርግጠኛ መሆን ቢያስቸግርም እስቲ የሚለይበትን ጥቂት መላ ምቶች ለማስቀመጥ እንሞክር፡፡  (ከማማት መላ መምታት ይሻላል!)
ምናልባት… የፓርላማው አባል ማሸለብ ትኩረት የተሰጣቸው አዲስ መንግስት በሚመሰረትበት ታሪካዊ ወቅት ላይ በመሆኑ ይሆን? ወይስ 2ኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን  ዕቅድ ይፋ በተደረገበት ማግስት ስለሆነ ይሆን? ወይስ ደግሞ የአዲስ አበባ ቀላል የኤሌክትሪክ ባቡር አገልግሎት መስጠት በጀመረበት ሰሞን በመሆኑ ይሆን? ያለዚያ እኮ የአንድ የምክር ቤት አባል ድንገት በእንቅልፍ መወሰድ እንደ ጉድ አይወራም ነበር፡፡ በተለይ እኮ ማህበራዊ ሚዲያው ቀላል ቀወጠው መሰላችሁ!! ይታያችሁ----ከ500 በላይ ከሚሆኑ የምክር ቤቱ አባላት ውስጥ አሸለቡ ወይም አንቀላፉ ተብለው ምስላቸው የተለቀቀው እኮ የአንድ ም/ቤት አባል ብቻ ነው (ከደከማቸው ደሞስ ቢተኙ!?)
አንዳንድ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ጠበኞች ምን ቢሉ ጥሩ ነው? “ተቀምጠው ምንም ከማይፈይዱ አባላት የተኙት ይሻላሉ!” (አሽሙር ሳይሆን አይቀርም!) ወደ ቁም ነገሩ ስንመጣ ግን ወደፊትም ተመሳሳይ የማንቀላፋት ወይም የማፋሸግ ወይም የድብርት ስሜት በፓርላማ አባላት ዘንድ እንዳይፈጠር መከላከያ እርምጃዎች መውሰድ የግድ ይላል፡፡ (ልብ አድርጉልኝ!! እንቅልፍ በግለ-ሂስ አይሻሻልም!) እናላችሁ ---- ዛሬ አንድ ሰው ብቻ ነው የደበተው ተብሎ ችላ ከተባለ፣ ነገ በተረጋጋ ስብሰባ በሉት በተጋጋለ ክርክር ውስጥ እንቅልፋቸውን የሚለጥጡ የፓርላማ አባላት ቁጥር መጨመሩ የማይቀር ነው፡፡
መፍትሄው ታዲያ ምንድን ነው?… ቀላልና ብዙ ወጪ የማይጠይቅ ነው፡፡ ምን መሰላችሁ? አላስተኛ የሚሉ ብርቱ ተቃዋሚዎች፣ አልፎ አልፎ ቀልድና ተረብ እንዲሁም ትኩስ ቡና ናቸው፡፡ (ፓርላማ ውስጥ ቡና ቢፈላ----- ችግር አለው?) የሆኖ ሆኖ እኒህ በሌሉበት ሁሌም  ቢሆን ፓርላማ ውስጥ “ማሸለብ” የሚጠበቅ ነው፡፡ (ስጋትና ጉጉት የለማ!)
ፓርላማ ውስጥ የማንቀላፋት ችግር ያለው በእኛ አገር ብቻ እንዳይመስላችሁ፡፡ በሌሎች የዓለም አገራትም የተለመደ ነው፡፡ ዓምና በኡጋንዳ ፓርላማ ምን እንደተከሰተ ታውቃላችሁ? ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ ንግግር ሲያደርጉ፣የ74 ዓመቱ ሁለተኛ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ሞስስ አሊ፤ ፊታቸውን በጥቁር መነጽር ጋርደው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ፣ ጋዜጠኞች በካሜራ ቀርፀው ጉድ አድርገዋቸው ነበር፡፡ ከዚያ 4 ዓመት ቀደም ብሎ ደግሞ በዚያው ፓርላማ በርካታ የተኙ ሚኒስትሮችንና የምክር ቤት አባላትን በካሜራው ያስቀረ አንድ የአገሪቱ ጋዜጣ፣ በፊት ገፁ ላይ ደርድሯቸው፣  “Sleeping Nation” (“የምታንቀላፋ አገር” እንደማለት!) በሚል ርዕስ አወጣቸው፡፡ (ተራ በተራ መተኛት እኮ የአባት ነው!)
ሙሴቪኒ እ.ኤ.አ በ1986 የፕሬዚዳንትነት ሥልጣን ሲይዙ፣ከመጀመሪያዎቹ ሚኒስትሮች አንዱ በመሆን ያገለገሉት ፕሮፌሰር ኤድዋርድ ካኮንጌ በወቅቱ ስለነበረው ፓርላማ ሲያስታውሱ፤ “እኔ በሙሴቪኒ መንግስት ውስጥ ሳገለግል ነገሮች አጓጊና በስሜት የሚያጥለቀልቁ ስለነበሩ፣ ማንም በፓርላማ ውስጥ የሚተኛበት ምክንያት አልነበረውም” ብለዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ምን ተፈጠረ? “አሁን ያለው ሁኔታ በፓርላማ ውስጥ አጓጊ ነገር አለመኖሩን በግልጽ አመላካች ነው” ሲሉ ፕሮፌሰሩ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ (የእኛስ የእንቅልፍ ሰበብ?)
አንዳንዴ ደግሞ የፓርላማ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ዋናዎቹም ሊያንቀላፉ እንደሚችሉ ጠርጥሩ፡፡ በኡጋንዳ እንዲህ አጋጥሟል፡፡ ራሳቸው ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ፤ፓርላማ ውስጥ በበጀት ጉዳይ ላይ የሚደረገውን ንግግር የሚሰሙ መስለው እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ፣ በካሜራ ተቀርጸው በአንድ የቴሌቪዥን ጣቢያ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ (እዚያስ ጋ አልደረስንም!) ወዲያው ታዲያ  የኡጋንዳ መንግስት ቃል አቀባይ ምን ብሎ ቢያስተባብል ጥሩ ነው? “ጥሞና ውስጥ ገብተው ሲያሰላስሉ እንጂ አልተኙም” ብሏል ከተፎው ቃል አቀባይ፡፡ ለነገሩ የኛዎቹም የማስተባበል ዕድል ቢያገኙ እኮ ማስተባበል አያቅታቸውም ነበር፡፡
በበርማ አንድ የፓርላማ አባል በስብሰባ ውስጥ ሲያንቀላፉ በካሜራ ተቀርፆ ምስላቸው በማህበራዊ ሚዲያ በመሰራጨቱ፣የአገሪቱ ጋዜጠኞች ላይ የነፃነት ገደብ ለማበጀት ሰበብ ሆኖ እንደነበር ተዘግቧል፡፡ ጋዜጠኞች እንደ ቀድሞ አዳራሽ ውስጥ ገብተው ሳይሆን ኮሪደር ላይ ሆነው የፓርላማውን ሂደት ከቴሌቪዥን ላይ እንዲከታተሉ ተወስኖባቸው ነበር፡፡ (ማንቀላፋታቸው ሳያንስ ነፃነት ማፈናቸው!?)
የህንድ ጎምቱ ፖለቲከኞችም በፓርላማ የሞቀ ክርክር በሚካሄድበት ወቅት በተደጋጋሚ ተኝተው ለካሜራ ተዳርገዋል፡፡ በቅርቡ በህንድ ፓርላማ ውስጥ በዋጋ ንረት ላይ የሞቀ ክርክር ሲደረግ የም/ቤቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ራሁል ጋንዲ፤ እንቅልፋቸውን ሲለጥጡ በካሜራ ተቀርፀው ምስላቸው በማህበራዊ ሚዲያዎች በመሰራጨቱ፣ የተቃዋሚዎች መዘባበቻ ሆነው ነበር፡፡  
በነገራችን ላይ የየአገራቱን ተሞክሮ ያመጣነውን በፓርላማ ውስጥ መተኛትና ማንቀላፋት የተለመደና በመሆኑ ተገቢ ነው ለማለት አይደለም፡፡ ይልቁንም የኢህአዴግን ፈለግ በመከተል፣ የዓለም አገራትን ተሞክሮ ለመፈተሽና ልምዱን ለመቀመር ነው፡፡  
የማታ ማታ ግን መፍትሄው በእጃችን መሆኑን እንዳትዘነጉት፡፡ አላስተኛ የሚሉ ብርቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣በየመሃሉ ቀልድና ተረብ እንዲሁም ትኩስ ቡና ለፓርላማው መነቃቃትና እንቅልፍ አልባ መሆን ወሳኝ ናቸው፡፡ እንዲህ እንዳሁኑ ገዢው ፓርቲ ፓርላማውን መቶ በመቶ ሲሞላውስ? ቀናነቱ ካለ በየጊዜው የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በእንግድነት መጋበዝ ይቻላል፡፡ (ያልተመረጡ ተቃዋሚዎች ፓርላማ ድርሽ እንዳይሉ የሚል ህግ እንደሆነ አልፀደቀም?!)
እናላችሁ----ዋናው ነገር ምን መሰላችሁ? ፓርላማው የተነቃቃና የተሟሟቀ (እንቅልፍና ድብርት አልባ!) ይሆን ዘንድ ከፀሐይ በታች የሚቻለውን ሁሉ ማድረግ ግድ ይለናል፡፡ ያለዚያ ግን በቀጥታ በሚተላለፍ የቴሌቪዥን ስርጭት የሚያንቀላፉ የም/ቤት አባላት ቁጥር እንደ ህንድ፣ በርማና ኡጋንዳ ማሻቀቡ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ (እንደ ኢኮኖሚያችን በሁለት ዲጂት እንዳይመነደግ ፍሩልኝ!)
አሁን ደግሞ እስቲ ወደ አዲሱ የመንግስት ምስረታ ጉዳይ ልውሰዳችሁ፡፡ አዲስ ስለተመሰረተው መንግስት ተቃዋሚዎች
ቢጠየቁ ምን እንደሚሉ መገመት አያቅተኝም፡፡ ኢህአዴግንና ተቃዋሚዎችን እኮ እኩል ነው የምናውቃቸው፡፡ እናም መልሳቸው፤ “ፌዝ ነው” የሚል ነው የሚሆነው፡፡ ተቃዋሚዎች፤#ፌዝ ነው” ማለታቸውን ጠቅሰን ኢህአዴግን መልሰን ብንጠይቀውስ? እሱ ደግሞ “ይሄ ለህዝብ ያላቸውን ንቀት ያሳያል; ይለን ነበር፡፡ እኛ ገዢዎቻችንን የምናውቀውን ያህል እነሱም ቢያውቁን፣ በቀላሉ እንግባባ ነበር፡፡ (አወይ አለመተዋወቅ!)
እኔ የምለው ---- እኔና እናንተስ ስለ አዲሱ መንግስት አቋማችን ምንድነው? እውነት አዲስ መንግስት ተቋቋመ ወይስ የአራዳ ልጆች እንደሚሉት፤“ለበዓሉ ድምቀት” ዓይነት ነገር ነው የሆነው? ኢህአዴግ ብዙ ሰዎች ከመቀያየር ይልቅ ብዙ መ/ቤቶች መቀያየር ሳይቀለው አልቀረም፡፡ (ሚኒስቴር መ/ቤቶች እንደጉድ ተፐውዘዋል!)
በነገራችን ላይ አንዳንድ መዋቅራዊ ማስተካከያ የተደረገባቸው የሚኒስቴር መ/ቤቶች ክፉኛ ተተችተዋል፡፡ (እቺ ተገኝታ ነው!) ሆኖም ልማቱን እስካላደናቀፈ ድረስ ማንም መተቸትም ሆነ መቃወም ህገመንግስቱ ያጐናፀፈው መብቱ ነው፡፡ ስለዚህ ይበረታታል፡፡ እንግዲህ የትችት ኢላማ ከሆኑት አዳዲስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች መካከል በዋናነት የእንስሳትና የዓሳ ሃብት ልማት ሚ/ር፣ የነዳጅ፣ የማዕድንና የተፈጥሮ ጋዝ ሚ/ር፣ (በምኞት ---የተቋቋመ መ/ቤት ብለውታል!) ይልቅስ አንድ ሃሳብ ብልጭ አለለልኝ (ለምን የምኞት ሚኒስቴር አይቋቋምም?)
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ፣በእኔ በኩል የሚኒስቴር መ/ቤቶቹን ለመተቸት ከመጣደፍ ይልቅ ሃሳቡን ለማብላላት፤ለማንሸራሸር ቅድምያ ሰጥቻለሁ፡፡ (ባይሆን “የሃሳብ ማንሸራሸሪያ ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ሃሳብ ማቅረብ ይሻላል!) እናላችሁ…በሚኒስቴር ደረጃ መቋቋም ሲገባቸው ተዘንግተው ወይም በአንዳንድ ኪራይ ሰብሳቢ ወገኖች ሴራ ሆን ተብለው እንዳይቋቋሙ የተደረጉ መ/ቤቶችን ለመጠቆም ወይም ለማጋለጥ እወዳለሁ፡፡ (የዜግነት ግዴታዬ ነዋ!)
ለምሳሌ በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በ10 እና 8 እጥፍ እያደገ የቀጠለው የቅባት እህሎችና ጫት ምርት እንዴት ይዘነጋል?! ይታያችሁ… በ2014 እ.ኤ.አ ከሁለቱ ምርቶች የተገኘው የውጭ ምንዛሪ 940 ሚ. ዶላር ነበር፡፡ (ለችግራችን ደራሽ እኮ ነው!) ታዲያ ለእነዚህ ከፍተኛ ገቢ ላስመዘገቡ የግብርና ምርቶች የሚኒስቴር መ/ቤት መቋቋም ይበዛባቸዋል? እናም ---- “የቅባት እህሎችና የጫት ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ኃሳብ ቀርእናቀርባለን፡፡ (ሃባ ዶላር አስገኝቶ የማያውቀው ዓሳ እንኳን የሚ/ር መስሪያ ቤት ተቋቁሞለታል!) ምናልባት “ጫት” የሚለው አጠራር ደስ የማይል ከሆነ “አረንጓዴው አልማዝ” ልንለው እንችላለን፡፡
ሌላው የተረሳው አካል ማን መሰላችሁ? ዳያስፖራ ነው፡፡ እናላችሁ----በተለያዩ የዓለም አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የዳያስፖራ አባላት ለዘመዶቻቸው የሚልኩት ገንዘብ ከጠቅላላው የኤክስፖርት ገቢ በእጅጉ እንደሚልቅ መንግስት ደጋግሞ አስታውቋል፡፡ እ.ኤ.አ በ2011 በቀረበው ሪፖርት፤ በዓመቱ የመጀመሪያ 7 ወራት ከዳያስፖራ የተላከው የውጭ ምንዛሪ መጠን 1.74 ቢ. ዶላር ሲሆን ይሄም ከቀደመው ዓመት የ19.6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡ ይሄን የኢኮኖሚ ዋልታችንን እንዴት በሚኒስቴር ደረጃ ማዋቀር ተዘነጋን? (በውለታ ቢስነት ያስወቅሰናል!) እናም “የዳያስፖራ ሚኒስቴር” ዛሬ ነገ ሳይባል እንዲቋቋም ልማታዊ መንግስታችንን እንጠይቃለን (ፒቲሽን እናሰባስባለን አልወጣንም!) በነገራችን ላይ የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር ምን ገንብቶ እንደፈረሰ የሚያስረዳን ቢኖር ደግ ነበር፡፡ ተጠያቂነትና ግልጽነት ከዚህ ይጀምራል! (አንዳንዶች “አቅም የሌለው የአቅም ግንባታ ሚ/ር” ይሉት ነበር!)
ይሄኛው ለብዙዎቹ ግር ሊል ይችላል፡፡ አዎ--- “የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሚኒስቴር” ማቋቋም ----ያስፈልጋል፡፡ (የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት እታትራለሁ ለሚል ገዢ ፓርቲ ወሳኝ ጉዳይ ይመስለኛል!) ሌላው የኪነጥበብ ጉዳይ ነው፡፡
አርቲስትና ገጣሚ በሞላባት አገር ሲሆን “የግጥም (ቅኔ) ሚኒስቴር” ካልሆነ ደግሞ “የኪነጥበብ ሚኒስቴር” (Ministry of Arts) ቢቋቋም ቢያንሰው እንጂ አይበዛበትም፡፡
 ሃቁን እንነጋገር ከተባለ እኮ ----- ከተፈጥሮ ጋዝ ሃብታችን ይልቅ የግጥምና የእስክስታ ሃብታችን በብዙ እጥፍ ይበልጣል፡፡ አንድም ባህላዊ እሴት ነው - ማንነታችን የተገነባበት፡፡ አንድም ለቱሪስት እየሸጥን ገቢ የምናገኝበት ምጭ የውጭ ምንዛሪ ምንጫችን ነው (“በእጅ የያዙት ወርቅ” ሆኖብን እንጂ!!) የሚኒስቴር መ/ቤት ማዋቀሩን በነካ እጃችን እንጨርሰው ካልን “የግምገማ ሚኒስቴር” (የግምገማ ባህልን ለአፍሪካ ፓርቲዎች ለማጋራት!) “የሰላምና ማረጋጋት ሚኒስቴር” (ለጐረቤት አገራት ለምናደርገው አስተዋጽኦ!) “የፕሮፓጋንዳ ሚኒስቴር” (ፀረ - ሰላምና ፀረ - ልማት ሃይሎችን የሚመክትና የሚያከሽፍ!) “የዕዳዎች ሚኒስቴር” (IMF የውጭ ዕዳ ክምችታችሁ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርትን 50 በመቶ ያህላል በማለቱ!) የሚሉት አዳዲስ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ይቋቋሙ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡
 ሃሳብ ብልጭ ሲልልን ወይም ደግሞ በህልማችን ከታየንም ሊቋቋሙ ይገባል የምንላቸውን የሚኒስቴር መ/ቤቶች መጠቆማችንን እንቀጥላለን፡፡ (ለጊዜው #የባቡር ሚኒስቴር” እንዴት ነው?)
 እናንተ ----- ስለ ሚኒስቴር መ/ቤቶች በመጻፍ ብቻ ሚኒስትር የሆንኩ መሰለኝ!!

Saturday, 10 October 2015 16:26

የፀሐፍት ጥግ

ሴቶች፤ ፍቅር - ረዥም ልብወለድ እንዲሆን ይፈልጋሉ፤ ወንዶች ግን አጭር ልብወለድ፡፡
ዳፍኔ ዱ ማውሪየር
አጭር ልብወለድ የፍቅር ግንኙነት ነው፤ ረዥም ልብወለድ ትዳር፡፡አጭር ልብወለድ ፎቶግራፍ ነው፤ ረዥም ልብወለድ ፊልም፡፡
ሎሪ ሙሬ
አጭር ልብወለድ ስታነቡ፣ በዙሪያችሁ ላለው ዓለም ትንሽ ተጨማሪ ግንዛቤና ትንሽ ተጨማሪ ፍቅር ይዛችሁ ትወጣላችሁ፡፡
ጆርጅ ሳውንደርስ
አጭር ልብወለድ ጨርሶ የተለየ ነገር ነው - አጭር ልብወለድ በጨለማ ውስጥ በባእድ ሰው እንደመሳም ነው፡፡
ስቲፈን ኪንግ
በሁለት ሰዓት ውስጥ አንድ አጭር ልብወለድ መፃፍ ትችላላችሁ፡፡ በቀን ሁለት ሰዓት፣ በዓመት አንድ ረጅም ልብወለድ ሰራችሁ ማለት ነው፡፡
ሬይ ብራድበሪ
አጭር ልብወለድ መፃፍ ብዙ ጊዜ የእድል ጉዳይ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
ሮበርት ሼክሌይ
ለእኔ አጭር ልብወለድ መፃፍ፣ ከረዥም ልብወለድ በእጅጉ ይከብዳል፡፡
ሊን አቤይ
ከተማርኳቸው የመጨረሻ ኮርሶች አንዱና የምወደው የሩሲያ አጭር ልብወለድ ነው፡፡
ቶቢያስ ዎልፍ
አንድ ሁለት ታሪኮች ታትመውልኛል፤ አጭር ልብወለድ በማሳተም የሚገኘው ገንዘብ ግን ኑሮዬን ለመምራት እንደማያስችለኝ ተገነዘብኩ፡፡
ሁማን ማጅድ
በየሳምንቱ አንድ አጭር ልብወለድ ፃፍ፡፡ በተከታታይ 52 መጥፎ አጭር ልቦለዶችን መፃፍ አይቻልም፡፡
ሬይ ብራድበሪ
አንድ ነጠላ ታሪክ ለመንገር አንድ ሺ ድምፆች ይጠይቃል፡፡
የአሜሪካውያን አባባል
ዩኒቨርስ የተሰራው ከታሪኮች እንጂ ከአቶሞች አይደለም፡፡
ሙሪል ሩኬይሰር
እያንዳንዱ ሰው የራሱ የህይወት ታሪክ ዋና ገፀባህሪ መሆኑ የግድ ነው፡፡
ጆን ባርዝ

በቅርቡ ምርቱን ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ለመላክ አቅዷል

       በዓለም በወተት ምርቷ ታዋቂ በሆነችው ኒውዝላንድ ውስጥ የሚገኘው ፎንቴራ የተባለው ወተት አምራች ድርጅት በፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ እየተመረተ ለገበያ የሚቀርበው አንከር ወተት፤ በዓመት 2.5 ሺህ ቶን ወተት እያመረተ ለገበያ እያቀረበ እንደሆነ ተገለፀ፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ረቡዕ በፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ውስጥ የሚገኘውንና በ600 ሺህ ዶላር ወጪ ያሰራውን የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ለጋዜጠኞች ባስጐበኙበት ወቅት የአንከር ወተት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዚኮ ሰይድ እንደተናገሩት፤ ፋብሪካው በዓመት 6ሺህ ቶን ወተት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ የሚያስችል አቅም ቢኖረውም በአሁኑ ወቅት 2.5 ሺህ ቶን ምርት እንደሚያቀርብ ተናግረዋል፡፡ በዓመት 20 ቢሊዮን ሊትር ወተት የሚያመርተውና በ140 አገራት  ቅርንጫፎች ያሉት ፎንቴራ፤ ከፋፋ የህፃናት ምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ ጋር የ30% ድርሻ ይዞ አንከር ወተትን በማምረት እያሸገ በማቅረብ ላይ ሲሆን በቅርቡ ወደተለያዩ የአፍሪካ አገራት ምርቶቹን ለመላክ እቅድ እንዳለው ተገልጿል፡፡ ከሁለት ዓመታት በኋላ ከውጪ አገር የሚመጣውን የዱቄት ወተት ግብአት እዚሁ በአገር ውስጥ ለማምረት መታቀዱን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፤ ይህንኑ ለማድረግ የሚያስችሉ ቅደመ ዝግጅቶችም በመደረግ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ህብረተሰቡ ወተት የመጠጣት ባህሉ አነስተኛ በመሆኑ ይህንኑ ለማሻሻል የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ በስፋት መሰራት እንደሚገባው አቶ ዜኮ ገልፀዋል፡፡
ፎንቴራ በአለም 25 ቢሊዮን ዶላር አመታዊ የገንዘብ ዝውውር ያለው ሲሆን በአገራችን በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን የአንከር ወተት ማቀነባበር ስራ በፋፋ የምግብ ፋብሪካ ውስጥ በመስራት ለገበየ እያቀረበ የሚገኝ ግዙፍ ድርጅት ነው፡፡ አንከር ወተት ከ30 በላይ ሚኒራሎችና ኢንዛይሞች ተጨምረውበት እንደማዘጋጅም ታውቋል፡፡

  •   በአገሪቱ የሚገኙ የአይን ሐኪሞች 130 ብቻ ናቸው
  •       2.8 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች እይታቸው የደከመ ነው
  •      በደቡብ ክልል ብቻ አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ አይነስውር የሚሆኑ 170ሺ ሰዎች አሉ

    የአለም የጤና ድርጅት መመዘኛ መሰረት፤ አንድ ሰው በሁለቱም አይኑ ከሶስት ሜትር ርቀት ላይ ጣት መቁጠር ካልቻለ አይነስውር ይባላል፡፡ አይነስውርነትን የሚያስከትሉ በርካታ አይነት በሽታዎችና ድንገተኛ አደጋዎች እጅግ በርካታ ሰዎችን ለአይነስውርነት እየዳረጉ ነው፡፡ እነዚህ የአይን እይታ አቅምን ችግር ላይ የሚጥሉ በሽታዎች የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የመከሰቻ ምክንያታቸውም የተለያየ ነው፡፡
አይነስውርነትን ከሚያስከትሉና የአይን የጤና ችግር በመሆን በስፋት ከማታወቁ በሽታዎች መካከል Cataract (የዓይን ሞራ ግርዶሽ) Trachomatous Corneal Opacity (ትራኮማ)፣ Retractive errors (የቅርብ ወይም የእርቀት የማየት ችግር) እና Glacoma (ግላኮማ) ተጠቃሽ ናቸው፡፡
የዓለም የእይታ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ ለአስረኛ ጊዜ፣ በአገራችን ደግሞ ለዘጠነኛ ጊዜ ከትናንት በስቲያ በአገር አቀፍ ደረጃ በአርባምንጭ ከተማ ተከብሯል፡፡ ይህንኑ የዓለም የእይታ ቀን አስመልክቶ ኦርቢስ ኢንተርናሽናል ሰሞኑን ለጋዜጠኞች የአንድ ቀን የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ፕሮግራም ላይ አገሪቱ በተለያዩ የዓይን በሽታዎች ሳቢያ በሚከሰቱ የዓይነ ስውርነት ችግሮች ምን የህል ጉዳት እንደደረሰባት የሚያሳይ በ2006 ዓ.ም የተደረገ ጥናት ቀርቦ ነበር፡፡
በኦርቢስ ኢንተርናሽናል ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር የኔነህ ሙሉጌታ የቀረበውና አገሪቱ በአይን ጤና ችግሮች፣ በመንስኤዎቻቸውና ችግሮቹ ያስከተሉአቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ የተደረገው ጥናት እንዳመለከተው፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 1,200,456 አይነስውራን ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ ሙሉ በሙሉ የማየት ችሎታቸውን ካጡት ሰዎች በተጨማሪ 2,776,054 የሚሆኑት እይታቸው የቀነሰ መሆኑ በጥናቱ ተረጋግጧል፡፡ ሙሉ በሙሉ የማየት ችሎታቸውን በማጣት አይነስውር ከሆኑት ሰዎች መካከል 1,049,198 የሚሆኑት በቀላሉ ሊወገድ በሚችል ችግር ሳቢያ ለአይነስውርነት የተዳረጉ ናቸው፡፡ በአገሪቱ ከሚገኙት አይነስውራን መካከል ግማሽ ያህሉ በአይን ሞራ ግርዶሽ (Cataract) ሳቢያ አይነስውር የሆኑ ሲሆን 9,034,93 የሚሆኑት ደግሞ የትራኮማ ተጠቂዎች መሆናቸውን ጥናቱ አመልክቷል፡፡ በገጠራማው የአገሪቱ አካባቢ በስፋት የሚታየው የአይን ሞራ ግርዶሽ በሽታ፣ በአብዛኛው በአዋቂዎች ላይ የሚከሰት ሲሆን አልፎ አልፎ በህፃናት ላይም እንደሚከሰትና ከቀዶ ጥገና ውጭ በሽታውን ለማዳን የሚያስችል ህክምናም የሌለው እንደሆነ ዶክተር የኔነህ ተናግረዋል፡፡
የአይን ሞራ ግርዶሽ በወቅቱ ህክምና ካላገኘ እይታን ከመቀነስ ጨርሶውኑ እስከማጥፋት የሚደርስ አደጋ የሚያስከትል በሽታ ነው ያሉት ዶክተር የኔነህ፤ ህክምናው በአገራችንም በስፋት እየተሰጠ መሆኑንና እጅግ በርካታ ሰዎችም ይህንኑ ህክምና ለማግኘት እንደሚጠባበቁ ተናግረዋል፡፡ በ2012 እ.ኤ.አ ህክምናውን ከሚጠባበቁ 2 ሚሊዮን ሰዎች ኦፕሬሽን የተደረጉት 50ሺ የሚሆኑት ብቻ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡ የቀዶ ጥገና ህክምናው ሙሉ በሙሉ ከበሽታው ሊያድን የሚችል ህክምና እንደሆነም ዶክተሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡ በካታራክት (በአይን ሞራ ግርዶሽ) ሳቢያ 39 ሚሊዮን የሚሆኑ የአለማችን ሰዎች ለአይነ ስውርነት የተዳረጉ መሆናቸውን ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡
በአገራችን ለሚከሰተው የአይነስውርነት ችግር በሁለተኛ ደረጃ መንስኤነት የሚቆጠረው የትራኮማ በሽታም በአገሪቱ በስፋት የሚታይ ችግር መሆኑን ያመለከተው የ2006 ጥናቱ፤ በአገሪቱ ከ9 ሚሊዮን በላይ የትራኮማ ህሙማን የሚገኙ ሲሆን ከ800ሺ በላይ የሚሆኑት በትራኮማ ተይዘው አስቸኳይ ህክምና የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ብቻ በትራኮማ የተያዙና አስቸኳይ ህክምና ካላገኙ አይነስውር የሚሆኑ 170ሺ ሰዎች እንደሚገኙ አመላክቷል፡፡ በአለም ከሚገኙት የትራኮማ ህሙማን መካከል 1/8ኛው የሚሆኑት በአገራችን እንደሚገኙና በሽታው ከድህነት ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልና በንፅህና ጉድለት ሳቢያ የሚመጣ በሽታ እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
ከትራኮማ በመቀጠል በአገሪቱ ለሚከሰተው የአይነስውርነት ችግር በሶስተኛ መንስኤነት የሚጠቀሰው ደግሞ የቅርብ ወይም የእርቀት እይታ ችግር ሲሆን ይህም በቀላሉ ሊታከሙት የሚችልና ሙሉ በሙሉ የዓይን የጤና ችግር ቢሆንም እጅግ በርካታ ሰዎች ለአይነስውርነት በመዳረግ ላይ የሚገኝ የጤና ችግር መሆኑን ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡
ጥናቱ በዝርዝር እንዳስቀመጠው፤ በአገሪቱ ከሚገኙት አይነስውራን መካከል 50% የሚሆኑት በአይን ሞራ ግርዶሽ ሳቢያ ለአይነስውርነት የተዳረጉ ሲሆን 11.5% የሚሆኑት ደግሞ ከትራኮማ ጋር ተያይዞ በሚመጣ የአይን ጠባሳ ምክንያት የአይን ብርሃናቸውን ያጡ ናቸው፡፡ 7.8% የሚደርሱት የቅርበት ወይም የእርቀት መነፅር የሚያስፈልጋቸው ሆነው ይህንን በተለያዩ ምክንያቶች ሳያደርጉ በመቅረታቸው ሳቢያ አይናቸው የሰነፈባቸውና ለአይነስውርነት የተዳረጉ ናቸው፡፡ ግላኮማ በተባለው የአይን በሽታ ሳቢያ አይነስውር የሆኑ 5.2% ሲሆኑ በሌላ የተለያዩ ምክንያቶች የአይን ብርሃናቸውን ያጡ 13% የሚደርሱ እንደሆኑም ጥናቱ ይፋ አድርጓል፡፡የችግሩን ስፋት በዝርዝር ያሳየው ይኸው ጥናት በአገሪቱ ያለው የባለሙያዎች እጥረት ለበሽታው መስፋፋት አስተዋፅኦ እንዳለው ጠቁሞ በአሁኑ ወቅት በአሪቱ ያሉት የአይን ሃኪሞች ቁጥር 130 ብቻ እንደሆነና ይህም 2400 የዓይን ሐኪሞች ካሏት ግብፅ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ገልጿል፡፡  

Saturday, 10 October 2015 16:07

የዘላለም ጥግ

 (ስለ ትምህርት)

  ትምህርት ቤት የሚከፍት ሰው የወህኒ ቤትን በር ይዘጋል፡፡
ቪክቶር ሁጐ
ዕውቀት፤ ልዩነት የመፍጠር ዕድል ያመጣላችኋል፡፡
ክሌር ፉጂን
ጥበብ (ዕውቀት) በዕድሜ አይመጣም፤ በትምህርትና በመማር እንጂ፡፡
አንቶን ቼኾቭ
የተማርኩትን ሁሉ የተማርኩት ከመፃሕፍት ነው፡፡
አብርሃም ሊንከን
ትምህርት ውድ ከመሰላችሁ ድንቁርናን ሞክሩት፡፡
ዴሬክ ቦክ
ትምህርት በራስ መተማመንን ይፈጥራል፡፡ በራስ መተማመን ተስፋን ይፈጥራል፡፡ ተስፋ ሰላምን ይፈጥራል፡፡
ኮንፉሺየስ
ራሳችሁ የምትናገሩትን በማድመጥ ጨርሶ አትማሩም፡፡
ጆርጅ ክሉኒ
የትምህርት ዓላማ፤ ባዶ አዕምሮን በክፍት አዕምሮ መተካት ነው፡፡
ማልኮልም ፎርብስ
የማይነበበውን ነገር ማወቅ፣ የትክክለኛ የተማረ ሰው መለያ ነው፡፡
እዝራ ታፍት ቤንሰን
መውጣታችሁን እስከቀጠላችሁ ድረስ የማይደረስበት የተራራ ጫፍ የለም፡፡
ባሪ ፊንሌይ
ትምህርት ለህይወት የሚደረግ ዝግጅት አይደለም፤ ትምህርት ራሱ ህይወት ነው፡፡
ጆን ዴዌይ
ተማረ የሚባለው እንዴት ተምሮ መለወጥ እንደሚቻል የተማረ ብቻ ነው፡፡
ካርል ሮጀርስ
ትምህርት የነፃነትን ወርቃማ በር መክፈቻ ቁልፍ ነው፡፡
ጆርጅ ዋሺንግተን ካርቨር
ትምህርት ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚደረግ እንቅስቃሴ ነው፡፡
አላን ብሉም
የአንዱ ትውልድ የትምህርት ክፍል ፍልስፍና የሚቀጥለው ትውልድ የመንግሥት ፍልስፍና ይሆናል፡፡
አብርሃም ሊንከን
የትምህርት ዓላማ እውቀትን ማሳደግና እውነትን ማሰራጨት ነው፡፡
ጆን ኤፍ. ኬኔዲ

  ደብረዘይት፣ አዴ ወረዳ እና ሻሸመኔ የብሾፍቱ ማህበራዊ ተጠያቂነት ማጠቃለያ
ባለፈው የደብረዘይት/ብሾፍቱ ጉዞዬን ጀምሬ ነበር፡፡ ላጠቃልለውና ወደ አጄ ጉዞዬ እቀጥላለሁ፡፡
ስለናንተ ጉዳይ (ስለማህበራዊ ተጠያቂነት) የጋዜጣችን አንባቢ ያውቅ ዘንድ ቀለል አድርጌ ልጽፍ ነው፡፡
አገልግሎት ሰጪዎችና አገልግሎት ተቀባዮች ናቸው መልስ የሰጡኝ፡፡ ማህበራዊ ተጠያቂነት በብሾፍቱ ምን ይመስል ነበር? ከዚያስ በኋላ ውጤቱ ምን ሆነ?
የት/ቤትን ችግሮች በተመለከተ ሙሉ በሙሉ ባይሆንም
የክፍል ጥበቶች ነበሩ፤ተሠርተው በነፃነት ይማራሉ
መፀዳጃ ቤቶች አዲስ መሠራት ብቻ ሳይሆን የወንድና የሴት ተብለው ተከፍለው እየተገለገሉባቸው ነው፡፡
ሜዳው አፈር ነበረ፤ አሸዋ ተደፍቶበታል፡
በአንድ ጠረጴዛ ላይ ለ5 ለ6 የሚማሩት አሁን ለ3 እንዲማሩ ተደርጓል
አንድ መጽሐፍ ለ3 ለ2 ያልነበረውን፣ አሁን መጽሐፍ ለአንድ ተማሪ እንዲያገኝ ጥረት ተደርጓል - ይህ የሆነው በህብረተሰቡ ድጋፍ ሲሆን፤ ይህም የእየሩሳሌም ህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት (ጄክዶ) አካባቢውን ለቅቆ ቢሄድ ህብረተሰቡ በዘላቂነት ሊረከብ እንደሚችል ይጠቁማል፡፡
ኤችአይቪ ፖዘቲቭ የሆኑ ስለመድሃኒቱ አጠቃቀም በጥንካሬያቸው የሚያሳምኑ የሳክ አባላት ይፋ ገለፃ እንዲያደርጉ ተደርጓል (ግን ይቀረዋል)
በውሃ በኩል አራት ችግርተኛ ቀበሌ ተለይቶ ተመርጦ ነው መፍትሔ ፍለጋ የተገባው! ት/ቤቶችም እንደዚያው!
ከአራቱ ቀበሌዎች ሁለት ሁለት መቶ ሰዎች እንዲሳተፉ ነው የተደረገው!
የመንግስት ስታንዳርድን መርምረዋል፡፡ እንዲጣጣሙ ለማድረግ ስኮር - ካርድ የምትባል መመዝገቢያ አለች፡፡ ውጤት ከ5 ይታረማል፡፡ የሁሉም ቀበሌ ስዕል ይገኛል፤ ለምሳሌ ካራ ሁራ 1.5 ሚሊዮን ብር ተመድቦ፣ 4 ባለ 8 መማሪያ ክፍል ሁለት ብሎኮች ተሠርቷል፡፡ ስታንዳርድ ጠረጴዛ ቀርቦልናል፡፡ (የሽንት ቤት ስታንዳርድም በቪዲዮ በተቀረፀው መሠረት መፍትሔ አገኘን - በህብረተሰቡና በሊንክ ኢትዮጵያ) እንደችግር የማህበረሰባዊ ተጠያቂነት ግንዛቤ አልነበረም፡፡ ችግሩን አምቆ ይይዝ ነበር፡፡
ለት/ቤቱ አባላት ብቻ ሳይሆን ለመንግሥትም ጠቀሜታ ያለው ነገር ተካሂዷል፡፡ የየክፍሉን ችግር ሁለቱም ወገኖች ተማምነው ለውጥ ስላዩበት! ተማሪዎች ረባሾችን ያጋልጣሉ! የመማር ማስተማር ሂደት በግልጽ የሚያምኑበት ሆኗል፡፡ ተማሪዎች የፈለጉትን ይጠይቃሉ!
ህዝብ አገልግሎት ሰጪዎችን ለሚጠይቅበት የካራ ሆራ ት/ቤት ምሳሌ ነው፡፡
Citizens report card እና የህብረተሰቡ ሃሳብ መስጫ ካርድ ተጠቅመዋል፡፡ መሞራረድ በመሟገት ጠቅሞናል፡፡
በ150 ብር የተሠራ ፕሮጄክት ነበር፤ በዐይናችን ሄደን አይተናል፡፡ ውሃ ልማት አይደለም፤ እኛ ነን ተሟጋቾች - ቴክኒካል ጉዳይ፣ የጥራት ጉዳይ፣ የኮንስትራክተሮችና የዕቃው ጥራት፣---- ሳቢያ እንዳለ ፓምፑ 400 ሜትር ሰመጠ፡፡ ሌላ ጄኔሬተር ተገዝቷል፡፡ ችግር along the line ነው አልተፈታም፡፡ ማህበራዊ ተጠያቂነት አጋዥ ነው፤ብቻችንን ወደላይ ስንጮህ አጋር አላገኘንምና! ትክክለኛ ኤክስፐርት እንደሌለ ነው የሚታየው! የክትትል ጥራት ማነስ!
የፍሳሽ መኪና ዕጥረት ነበር በከፍተኛ ወጪ ተገዝቷል!
በወር አንድ ጊዜ በህብረተሰቡ የጽዳት ዘመቻ ይካሄዳል
በእኛና በት/ቢሮ መካከል ትልቅ መቀራረብ አለ!
የህዝቡ አማካሪ ምክር ቤት ፀሐፊ እንዳሉት - 1ኛና ሁለተኛ ፌዝ አባል - “የመንግስት የ5 ዓመት ዕቅድ እንደስታንዳርድ ተቆጥሯል፤ በግሩፕ አስበን ያልተሳኩትን እንደ ችግር ወስደን ነው፡፡ ከንቲባው ቃል ገቡ - ዕቅድና በጀት ተፈቀደ - የገንዳ ማጠራቀሚያና የቆሻሻ ማንሻ መኪና ዕጥፍ ሆኑ!
ፊት የተገዛው ፓምፕ ለሙቅ አይሆንም ነበር፤ ህዝቡ አልረካንም ብሏል
በት/ቤት ግቢ ያሉ ቤቶች ማካካሻ ቦታና ቤት ተሠርቶላቸው ለቀዋል! ኮንዶምኒየም የገቡ አሉ!
ለመላው ኢትዮጵያ ምሳሌ እየሆነ ነው፤ ከሶማሊያና ከኬንያ ጭምር መጥተው ጐብኝተዋል! መተሃራ ምንጃር አካባቢ ልምድ ከካራ ሆራ ት/ቤት አግኝተናል ብለዋል ከዝቅተኛ ወደ ከፍተኛ ስለሄደ!
አንገብጋቢው ነገር ላይ ስላለሁ ሁሌ እንዳነባሁ ነው፤ ውሃ የለም፤ ወልደው መታጠቢያ፣ ለአስከሬን ማጠቢያ እንኳን! (ቀበሌ 08)
3 ቀን ብቻ የመጠጥ ውሃ አገኘን! ደሞ የፈላ ውሃ ብቻ ለቀቁብን ይላሉ፤ባልቴቷ ተወካይ! ይሁን አቀዝቅዘን እንጠጣ አልን፤ከ2 ቀን በኋላ ቀጥ አለ!
ወዴት እንሂድ፤ ከዚህ በላይ አቤት የት አለ፤ ከንቲባው በተቀመጡበት ተናገርን!
“የጠገበ ሰው የተራበን ሰው ነገር አያቅም! በ6 ወር ዝናብ ከዘነበ ድንገት አጠራቅመን ነው የምንታጠበው፤እነሱ ግን ፀድተው ይወጣሉ! አብሲት የምንጥለው የምናቦካው በዝናብ ውሃ ነው፤ ለአሁን ክረምት!
ግን አሁን በቦቲ ይመጣል፤ ለዛ ሁሉ ህዝብ እንዴት ያዳርሳል? እሱም ህዝቡ ቀይ አሸዋ አልብሶ ነው ----- መናገሩን በውሃ ጉዳይ ላይ አቁሜያለሁ - ጉድጓድ ውሃ ገባ አሉ፣ ሞተር ገብቷል ውስጡ ተባለ - ሄደን ውሃ ልማት መጠየቃችን አልቀረም - እኮ! ከአሜሪካን አገር ሰው አምጥተን አሉ፤ ትልቁ አገር አሜሪካን ነው አሉ እንግዲህ አቅቶት ሄደ (ሳቅ) ሌላ ማን ሊያወጣው ነው ታዲያ?
እኔ መሀይም ነኝ አላቅም፤ አፍርሰውት ቢያወጡት ሰብረው! አልወጣም አይል፡፡
ህዝቡ ከማልቀስ ውጪ አደለም፤ አንድ በርሜል 100 ብር ነው!
ትምህርትስ አልተሻሻለም?
ትምርቱ ግን ጥሩ ነው ፤ግን ሲማር ውሃ ያስፈልገዋላ መቼም!
ከላይ የተጠቀሰው የድፍን ብሾፍቱ ችግር አይደለም፤ መንግሥት ከአቅሙ በላይ ቢሆንበት ነው እንጂ!
ሰው ራሱ ተጠያቂ መሆኑን አውቋል፤ ችግሩንም ይፋ መናገር እንዳለበት ተገንዝቧል፤ ትልቅ ለውጥ አለ!
አየር ኃይልና አሻም አፍሪካ አግዘውናል
091307 ቀበሌ የበጀት ተወካይ እህማልድ ታላቅ አስተዋጽኦ ትልቅ ድርጅት ነው - የራሳችንን ችግር በራሳችን እንድናወጣ - እሾክን በሾክ! አንድ ዐይናችን ነው! 26 ሴክተር መ/ቤቶች ከነ ከንቲባው ከነአባላቱ ጭምር ከጄክዶ ጋር ተሰብስበው፤ ተወያይተው የማተ ኮሚቴ እንደ አገር ብልጽግና ታዳጊ ሆኖ ከሥር እየተመካከረ በቡና፣ በዕድር፣ በቀብር፣ በውይይት ላይ በቀበሌ ሰብሳቢዎች ላይ - ነገሬ ብሎ እንዲያስብ አድርጓል - በከተማ ልማት ዕቅድም ህዝቡ ከታች እንዲመክርበት በጐጥ አድርጓል - እኔ አውቅልሃለሁ እንዲቀር ጥሯል፡፡
እንደ ችግሩና እንደተጠቃሚው ብዛት እንዲሆን አድርጓል
በጀት ይለጠፋል፤ ህዝቡ ሃሳብ እንዲሰጥ
50 50 በጀት ከመንግሥት ጋር እንዲሠራ ደረጃ ላይ ደርሷል
የተራ ሆራ የልጅ ሃ/ማ ነው
   ለግል መኖሪያ ያሠሩት ነው!
ግልጋሎት ሰጪው የመንግሥት አካል የህዝቡን ጥያቄ እየተቀበለ ነው! ትልቁ ነገር ለመላው ኢትዮጵያ የሚሆን እየተፈጠረ ነው!
ባቦ ጋያ ህፃናት መዋያ ተጀምሯል፤ እኛ ራሳችን በጐ ተፅዕኖ መፍጠር አለብን፤ መጨቃጨቅ መካሰስ መቃወም ሳይሆን! ጀምረነዋል - በትዕግሥት!!
መጽሐፍ ስቶር ይገባል፤ይሠራጭ አይሠራጭ የሚከታተል የለም! አሁን ያ ተለውጧል!
የማህ/ተጠዋና ሥልጣን የማቀጣጠል ሥራ ነው!
በኤችአይቪ ዙሪያ ቤት እስከመስራትና እስከቁጠባ ተሠማርቷል - ጄክዶ!
የአካል ጉዳተኞች ላይ ትኩረት አድርጐ እርዳታ ያጠናክር! የመንግስት ባጀት ሲመደብ
ወጣት ላይ ይሠራ ፤ለመተካካት!
አገልግሎት ሰጪው ቆልፎ እንዳይይዝ ከፖለቲካ ጋር አይቆላለፍ awareness ይሰጥ! መልካም አስተዳደር ይታሰብበት!
***
ቀጥሎ የተጓዝኩት ወደ ሻሸመኔ ሲሆን ከዚያ 30 ኪ.ሜ ገደማ ወደቀኝ ተገብቶ አጄ ወረዳ ይደረሳል፡፡
የአጄ የማህበራዊ ተጠያቂነት ኮሚቴ መርምሮ አዎንታዊ ውጤት ማምጣቱን ሲናገር፣ የሳክ የትምህርት ኮሚቴ ሊመንበር አቶ መርዕድ ዋናው ጉዳይ አገልግሎት ሰጪውና አገልግሎት ተቀባይ የግንዛቤ ለውጥ ማምጣታቸው ነው፤ የችግሩን ባለቤት ማስገኘትና ለውጥ ማስከተል ሲሆን በዚህ ረገድ ተጨባጭ ውጤት ታይቷል፤ ድፍረት ታይቷል፤ ትምህርት፣ ውሃና ንፅህና ላይ ነው ውጤቱ የተመዘገበው፡፡ ሽንት ቤት ለሌለው ሽንት ቤት ተሠርቷል፡፡ ህዝብ ይገባኛል ያለውን መንግሥት ይገባል ብሎ ፈጽሟል፡፡ ይጠፋ የነበረውም ውሃ መጥፋት የለበትም ተብሎ የኦሮሚያ የውሃ መ/ቤት፣ ወደ አንድ ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ትልቅ ጄኔሬተር ተገዝቶ፣ የውሃም የመብራትም ችግር እንዳይኖር ሆኗል፡፡ ሻወር አልነበረም ኖረ፡፡ ልብስ ማጠቢያ ኖረ፡፡ ሃሳብ በዐይን ተተግብሮ ታየ፡፡ አቶ አማን ደግሞ ስለ ገጽ ለገጽ ምን ዕውነታ አለ ብያቸው፣ ዋናው ነገር አገልግሎት ሰጪና ተቀባይ አጠገብ ላጠገብ ተቀምጠው በድፍረት መናገራችን ነው! ብለዋል፡፡ የዛሬ ሁለት ዓመት በተወያየነው መሠረት፤ በግለሰብ ደረጃ ሽንት ቤት የሌለው እንዲኖረው፣ በማህበረሰብ ደረጃም የህዝብ ሽንት ቤት እንዲሠራ ተደርጓል፡፡ ሥራ ባግባቡ ባለቤት አግኝቶ፣ መሬት ላይ የሚታይ ለውጥ ተገኝቷል፡፡
እንዳገር ሽማግሌ ይሄን አይቻለሁ፡፡ እጅ መታጠቢያም ተሠርቷል፡፡ በጽዳት በኩልም ደረቅ ቆሻሻ አንድ ቦታ ተሰብስቦ እንዲቃጠል፣ እርጥቡ ጉድጓድ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ በውሃ በኩል ቦኖ ተደርጓል፡፡ ተማሪዎች፣ ወላጆች፣ መምህራን እና ህብረተሰብ ተገኝተዋል፡፡ የሴክተር ቢሮዎችም የልምድ ልውውጥም ተካሂዷል፡፡ የሴቶች ኃላፊም፣ ሴቶች እንዲሳተፉ በጽዳቱም፣ በውሃውም በትምህርቱም ተደርጓል፡፡
ያለው ችግር የውሃው ኃይል ማጣት ነው፡፡ ጫካው ተመናምኗል፡፡ ለመተካት እየተሞከረ ነው፡፡ ግንዛቤ መጨበጥ፣ ችግር ማጤን፣ ማቀድ መበጀትና ውጤት ማምጣት ነው ተግባራዊ ሂደቱ! “ራሳችሁ ላይ ያለው ለውጥ ምንድን ነው? ብዬ ለጠየኳቸውም፤“ስልጠና ማግኘታችንና ችግርን በድፍረት ማንም ፊት መናገር መቻላችንን ተረድተናል፣ በፊት እንፈራ ነበር” ብለዋል አባላቱ! የስዊድን ልማት ድርጅትና ዓለም ባንክ ከእየሩሳሌም ድርጅት ጋር የሠሩ ሲሆን፤ ከመጠየቅ መጠየቅ (ጠ ይጠብቃል) እንደሚከብድም አስምረውበታል፡፡
ከዚህ በኋላ ወደ ግብርና ቢሮ አመራሁ፤ እዚያው ያለውን ስብሰባ ለማየት ነው! 

  ከእለታት አንድ ቀን አንድ ሽማግሌ ሹም የተቋሙን ሠራተኛ ሁሉ የሚያጣላ፣ የሚያጋጭና የሚበጠብጥ ወሬ እያወራ ሰውን እያተራመሰ አስቸገረ፡፡ ሰው ተሰበሰበና መምከር ጀመረ፡፡
አንደኛው - “ይሄ ሰው የባለቤቱ ዘመድ ነው፡፡ ለዚህ ነው እንደልቡ የፈለገውን እያወራ ዘራፍ የሚልብን!” አለ፡፡
ሁለተኛው - “ታዲያ ባለቤቱም ቢሆኑ‘ኮ ውሸት አይፈቅዱም!”
ሦስተኛው - “እሱን እንኳ እሳቸው ካልተናገሩ ማንም አያውቅም”
ይሄ ሙግት እየተካሄደ ሳለ ባለቤትየው መጡ፡፡
“ምንድን ነው የሚያጯጩሃችሁ?” አለ፡፡
ከተሰበሰቡት መካከል አንዱ፤
“ጌታዬ ይሄ የርስዎ ልጅ በጣም አስቸገረን”
“ምንድ አድርጐ?”
“እየዋሸን”
“ታዲያ ውሸት ለእናንተ አዲስ ነው እንዴ? ታገሱታ!”
“እንዴት ጌታዬ፤ እሱኮ ውሸት አያልቀበትም”
“እንዴት አያልቅበትም?”
“በጣሊያን ጊዜ የሰማውን ውሸት እስከዛሬ ስለሚያስታውስ ነዋ!!”
“ያ ከሆነማ ከዛሬ ጀምሮ ተሰናብቶላችኋል!” አሉ ባለቤቱ!
***
ውሸት ሁሌም ውሸት ነው! የጣሊያን ጊዜ ውሸትና የዛሬ ውሸት ብሎ ልዩነት መፍጠር የለም! ዕውነት ያልሆነ ሁሉ ውሸት ነው ብሎ ማመን እንጂ ለውሸት ጊዜ መለየትም ሆነ፣ ቦቃ መለየት የትም አያደርስም! ማናቸውም አሉታዊ ነገር ያለው ውሸት ነው፡፡ ውሸትን ለማራመድ ሥልጣን ተጠቀምን ማለት ሹመት ለውሸት ተግባር ዋለ ማለት ነው!
“ደንጊያና ቅል ተላግቶ
ዜጋና ሹም ተጣልቶ”
አይሆንም፤ የሚለውን አባባል፤ የማንሽር ከሆነ፣ አዲስ ሹመት አዲስ ሽረት እንደማለት ነው፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነውና!
“ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል”ን ምን ያህል ረስተናል?
ሙስናን ተገላግለነዋል ወይ? የጣሊያን ጊዜን ውሸት ተፋትተናል ወይ? መልካም አስተዳደር ዜማ ነው ተግባር ነው? ፍትሕ እዚያው ፍርድ ቤት ነው ወይስ እኛ ውስጥ አለ? ስለ አንደኛውና ስለ ሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ስንቶቻችን በዕውን እናውቃለን?
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች መከፈላቸው መቼም ሳይጠና እንዳልሆነ እንገምታለን፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በርካታ አማካሪ ሲሾም (ሲመራ) ያለጥናት እንዳልሆነ እንዳልገመትን ሁሉ “ጠርጥር ጉድ አለ በሰኔ” የሚለውም ሆነ፤ “የፊት ወዳጅሽን በምን ሸኘሽው?”
    በሻሽ፡፡
ለምን?
የኋለኛው እንዳይሸሽ!”
የሚለው፤ እንደጊዜው የሚፈረጁ ናቸው!!
“ግፋው እንጂ አታርቀው” የሚለውም ያው ነው!” እዚህ ቦታ ያልረባ እዚያ ይገባ!” ማለትም ያጠያይቃል፡፡ “ጉልቻ ቢቀያየር ወጥ አያጣፍጥም!” የሚለው፤ የኃይለሥላሴ ዘመን ሲያበቃና እንዳልካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን የተሰነዘረ መፈክር ዛሬም ቢነሳ አያስቀይምም!
ዋናው ጉዳይ፤ “ወገናዊነትን ሳይሆን ሙያችንን እንሥራበት” የሚለው ነው፡፡
አፈረስነው ያልነው ኢዲሞክራሲያዊነት፣ ኢፍትሐዊነትና ሙስና፤ መልሶ እኛኑ የሚያፈርሰን ታሪክን ከደገምን ነው፡፡ “የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ” የሚለው ተረት የማይረሳንን ያህል፤
“የተወጋ በቅቶት ቢረኛ፣ የወጋ ምን እንቅልፍ አለው፤
የጅምሩን ካልጨረሰው!” የሚለውንም የማንዘነጋ መሆን አለብን!
ሀገርን በሀቀኛ ተግባር እንሞላ ዘንድ ከሆነ የተሾምነው፤ ሹመት በመቀባት ሳይሆን፣ በመመኘትም ሳይሆን፣ ለሀገር አሳቢ በመሆን ብቻ ተገኘ ማለት ነው!
ሙስናን በተመለከተ አንዲት ገጠመኝ ጠቅሰን እንደምድም፡፡ ሰውዬው መንገድ ላይ ተኝቶ ቁስሉን ዝንብ ወሮታል፡፡ ሌላ መንገደኛ መጥቶ “እሽ!” ብሎ ዝምቦቹን አባረረለት፡፡
ያ ቁስለኛም፤
“ምነው ወዳጄ ጠግበው የተኙትን ዝንቦች አባረህ አዲሶቹን ጋበዝክብኝ!” አለው፡፡

     በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ በሃጂ ስነስርአት ወቅት በተፈጠረ መጨናነቅ ህይወታቸውን ያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 47 መድረሱን የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገልጿል፡፡
ባለፈው መስከረም 13 ቀን 2008 በሳዑዲ አረቢያ ሚና አካባቢ በደረሰ አደጋ ከ1ሺህ በላይ የተለያዩ ሀገር የሃይማኖታዊ ስነ ስርአቱ ተሳታፊዎች ህይወታቸውን ባጡበት ወቅት ኢትዮጵያውያን ላይ አደጋ ስለመድረሱ ወዲያው ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን ከቀናት በኋላ 2 ኢትዮጵያን ህይወታቸው ማለፉ ተዘግቦ እንደነበርና ኋላም የሟቾች ቁጥር ወደ 31 ማደጉ ይታወቃል፡፡ ከትናንት በስቲያ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ቁጥሩ 47 መድረሱንና ተጐድተው ሆስፒታል ገብተው ከነበሩት 26 ኢትዮጵያውያን 24 ተሽሏቸው ከሆስፒታል ሲወጡ፣ 2ቱ ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ መሆኑ ታውቋል፡፡
ለሃጅ ስነስርአት ወደ ሳዑዲ አረቢያ ሄደው የነበሩ ከ1ሺህ 100 በላይ አማኞች መመለሳቸውንም ምክር ቤቱ አስታውቋል፡፡ በዘንድሮ የሃጂ ስነስርአት ላይ 10ሺ ኢትዮጵያውያን መሣተፋቸውም ታውቋል፡፡