Administrator

Administrator

Saturday, 14 November 2015 09:42

የፀሐፍት ጥግ

(ስለ ታሪክ)
- የምፈጥረው እያንዳንዱ ታሪክ እኔን
ይፈጥረኛል፡፡ የምፅፈው ራሴን
ለመፍጠር ነው፡፡
ኦክታቪያ ኢ.በትለር
- እውነተኛ ታሪክ የምፅፍ ከሆነ ከራሴ
ስም ነው የምጀምረው፡፡
ኬንድሪክ ላማር
- አርቲስት አይደለሁም፡፡ ካሜራዬን
እከፍትና ታሪኬን እተርካለሁ፡፡
ታይለር ፔሪ
- ህይወቴ ድንቅ ታሪክ ነው - ደስተኛና
በድርጊቶች የተሞላ፡፡
ሀንስ ክሪስቺያን አንደርሰን
- አባቴ ታሪክ መተረክ ያውቅበታል፡፡
የተለያዩ ድምፆች በማውጣት እንድስቅ
ያደርገኝ ነበር፡፡
ሊሊ ኮሊንስ
- ትልቁ ነገር ድምፅህ እንዲሰማ፣ ታሪክህ
እንዲደመጥ ማድረግ ነው፡፡
ድዋይኔ ዋዴ
- ስሜትን ሰቅዘው የሚይዙና አይረሴ
የሆኑ ገፀባህሪያትን ለመፍጠር ተግተህ
ትሰራለህ፡፡ ሆኖም የማታ ማታ ዋናው
ነገር ታሪኩ ነው፡፡
ጄምስ ዳሽነር
- በታሪክ ውስጥ ጠንካራ ሴት ገፀ ባህርይ
ስትኖር፣ ሁልጊዜ ያ ቀልቤን ይይዘዋል፡፡
ኦንግ ሊ
- አይገመቴ ሁን፡፡ እውነተኛና ቀልብ
ሳቢያ ሁን፡፡ ግሩም ታሪክ ተርክ፡፡
ጄምስ ዳሽነር
- ምንጊዜም ታሪክ ስፅፍ፣ ለወንዶችም
ለሴቶችም ማራኪ እንደሚሆን
አምናለሁ፡፡
ሱዛኔ ኮሊንስ
- ታሪክ መጀመሪያ፣ መካከልና መጨረሻ
ሊኖረው ይገባል፤ ነገር ግን የግድ በዚያ
ቅደም ተከተል መሆን የለበትም፡፡
ዣን ሉክ ጎዳርድ
- ሁሉም ገፀባህርያት ከማውቃቸው ሰዎች
የሚፈጠሩ ናቸው፡፡ ከመጀመሪያው
ንሸጣ በኋላ ግን ለታሪኩ እንዲስማሙ
አርቃቸዋለሁ፡፡
ኒኮላስ ስፓርክስ
- ይሄንን ታሪክ ከዚህ ቀደም ሰምታችሁት
ከሆነ እንዳታቆሙኝ፤ ምክንያቱም
እንደገና ልሰማው እፈልጋለሁ፡፡
ግሮቾ ማርክስ
- ሴቶች፤ ስሜት ውስጥ ጠልቆ የሚገባ
የፍቅር ታሪክ የሚወዱ ይመስለኛል፡፡
ኢ.ኤል ጄምስ

Saturday, 14 November 2015 09:38

አንዲት ክፉ ቀን በካዛንቺስ

    ነገሩ ወዲህ ነው፡፡ ከአንድ ጓደኛዬ ጋር ካዛንቺስ አካባቢ ተቀጣጥረን ስለ ስራ ጉዳይ ለመናጋገር ቦታ ስንመርጥ፣“ፈተና ስለደረሰብኝ የጋራ ጓደኛችን ቤት እያነበብኩ ልጠብቅህ” አለኝና ስልኩ ተዘጋ፡፡ ይህ የጓደኛችን ቤት ታዲያ ካዛንቺስ በአሁኑ ጊዜ በልማት ምክንያት ከፈረሱት ከአድዋና ኦሜድላ ሆቴል በስተጀርባ የሚገኝ ነው፡፡  በዚህ ሰፊ ግቢ ውስጥ ብዙ የቀበሌም ሆነ የግል ቤቶች የሚገኙ ሲሆን አብዛኛዎቹ ለጫት መቃሚያና ሺሻ  ማጨሻ ቤትነት ያገለግላሉ፡፡
 እኔም በዚያች ክፉ ቀን ከጓደኛዬ ጋር ወደ ተቀጣጠርንበት ቤት ስደርስ፣አንድ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ባሉበት ፍራሽ አንጥፈው ግማሹ እየቃመ ሲያነብ ፣ግማሹ ካርታ ይዞ ነበር፡፡ በመሰረቱ ቤቱ የጓደኛችን በመሆኑ ከምናውቀው ሰው ውጪ ገንዘብ አስከፍሎ ጫት የሚያስቅም አይደለም፡፡ ሌሎቹ ቤቶች ግን ገንዘብ አስከፍለው የሚሰሩ ናቸው፡፡ለወትሮው ታዲያ ጫት መሸጥ እንጂ ማስቃም ክልክል ነው የሚል የንግድ ጽ/ቤት መመሪያና ደንብ አንግበው፣ ወደ ግቢው ጎራ የሚሉ የደንብ ማስከበር ሰራተኞች አልፎ አልፎም የፖሊስ ሀይሎች አይጠፉም፡፡ ታዲያ ባለ ጫት ቤቶቹ እቃቸው እየተወሰደባቸው ስለተቸገሩ፣በድንገት ከተፍ የሚሉ ወራሪ ደንብ ማስከበሮችን ለመከላከል ወሬ አቀባይ ዘብ፣ በር ፊት ለፊት እንዲቀመጥ ያደርጋሉ፡፡ ወሬ አቀባዩ ልጅ፤ “መጡ... በሩን ዝጋው” ካለ  ያለ ቅድመ ሁኔታ በሩን.... ድርግም፣ መብራቱን.... ድርግም፣ ሞባይልን ድርግም ..... ሁሉን  ድርግም አድርጎ ---- የውጭውን ሁኔታ በጆሮ ማዳመጥ ብቻ፡፡
የደንብ ማስከበር ሰራተኞቹ እያሰለሱ ወደ ግቢው ብቅ ቢሉም ተጠቃሚንና  ባለቤቶችን ከማደናበር በቀር ምንም አይነት ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን “መጡ! በር ዝጉ” ጨዋታ እያሰለቻቸው ሲመጣ፣ በዚያች ክፉ ቀን አንድ መላ ዘይደው መጡ፡፡ አንዱ የሲቪል ልብስ በመልበስ ተጠቃሚ መስሎ ቤት ውስጥ ዘው አለና፣ የማጨሻ እቃዎቹን ወስዶ፣ የፖሊስ ድጋፍ ለመፈለግ ወደ ውጭ ወጥቶ እስኪመለስ፣ በሮች በሙሉ ተዘጋግተዋል፡፡ ፖሊሶቹ ከደንብ ማስከበሮቹ ጋር ሆነው በር ቢያንኳኩም ምላሽ ስላጡ፣ “በር ክፈቱ ካልሆነ ቤቱን እናሽጋለን” የሚል ትእዛዝ አስተላለፉ፡፡ ነጋዴዎቹ ደግሞ በሲቪል ደንብ ማስከበር እቃ በመወሰዱ ቢደናገጡም፣ በር መክፈቱን ግን ተጨማሪ እቃ የሚያስወስድባቸው በመሆኑ “አያዋጣም” በማለት “ውስጥ የነበረው ሰው ወጥቶ በሩን ዘግቶ ሄዷል” ብለው መለሱ፡፡ በዚህ መሀል በተፈጠረው ክርክርና አተካራ ነገሮች እየተካረሩ መጡና ፖሊሶች “በሩን ካልከፈታችሁ በሃይል ሰብረን እንገባለን“ ማለት ጀመሩ፡፡ በሶስቱም ቤቶች ውስጥ ተቆልፎባቸው የተቀመጡ ሰዎች አሉ፡፡ “ውስጥ ያላችሁ ሰዎች፤በሩን አስከፍቱ፤አሽገነው ከሄድን መውጫ አይኖራችሁም” ማለት ጀመሩ፡፡ ውስጥ ያሉት ሰዎች ደግሞ በፍርሀት ተውጠዋል፡፡ ፖሊስ ቢያስረንስ፣ በአደባባይ እቃ አስይዘው ቢያሰልፉንስ፣ በቪድዮ ቀርጸው በሚዲያ ቢያሳዩንስ ---- በማለት በስጋት ቢርበደበዱም ከዝምታ በስተቀር ምንም ምላሽ የሰጠ አልነበረም፡፡
ታዲያ ፖሊሶች ሀይል ጨምረው የአንደኛው ቤትን በር ገንጥለው ገቡና ውስጥ በድንጋጤ ተውጠው የነበሩ ተጠቃሚዎች ላይ የዱላ መአት ያዘንቡባቸው ጀመር፡፡ ትንሽ ትልቅ የለ መቀጥቀጥ ሆነ፡፡ አንዱ ፖሊስ፣ ሴቷን አስተናጋጅ   በጫማ ሆዷ ላይ ሲረግጣት፣”ኽረ በእናትህ ነፍሰ ጡር ነኝ” ብላ ነው የተረፈችው፡፡
በተለይ አንድ አስር አለቃ ፖሊስ፤ፍጹም ስሜታዊ ሆኖ ጫማ ለማድረግ፣ ሽንት ለመሽናት ፍቃድ ሲጠየቅ ሁሉ ምላሹ፣በዱላ አናት እየበሳ ቁጭ እንዲሉ ማድረግ ሆነ፡፡ “ፍቃድ መጠየቅ አይቻልም ወይ?” ብለህ ጥያቄ ካቀረብክማ አለቀልህ፡፡  በቆመጥ፣ በእርግጫ ያጣድፍሃል፡፡ ዋይ! ዋይ! ቢባል ሰሚ የሚልም፡፡ ወደ ሁለተኛው ቤት ጎራ አሉና አሁንም በሩን በሀይል ገንጥለው በተመሳሳይ ሁኔታ ቅጥቀጣውን ገፉበት፡፡
ከሁለቱ ቤቶች የተገኙትን ተጠቃሚዎች መታወቂያ ሰበሰቡና እያዋከቡና እያዳፉ በመኪና ጭነው ወሰዷቸው፡፡ ወደ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ አዝናኝም አሳዛኝም ሁኔታ ነበረው፡፡ አዝናኙ ሁኔታ አግዳሚ ወንበር ላይ ያስቀምጡህና የወጣ የገባ ሰው እያየህ እንዲዝናናብህ ያደርጉሃል፡፡ ለሌላ ጉዳዩ ባጠገብህ የሚያልፍ ፖሊስ ከየት እንደመጣህ ይጠይቅህና፤ “ከጫት ቤት” ስትላቸው፣ እንደ አሽሙረኛ ክፉ ጎረቤት እያሽሟጠጠ እየተሳለቀብህ ይሄዳል፡፡
አሳዛኙ ሁኔታ ደግሞ ይሄን ይመስላል፡፡ ከቤት ውስጥ ከተገኙት ተጠቃሚዎች ውስጥ አንዱ ዱላና ቅጥቀጣ ሲበረክትበት፣ “በህግ አምላክ አትምታኝ” ማለት ጀመረ፡፡ ያው ሞገደኛ አስር አለቃ፣ “ብትመታ ምን ታመጣለህ?”  “እናትክን...“. ብሎ መሳደቡን ቀጠለ፡፡” ተቀጥቃጩም “እናቴን አትስደብ፤እኔን ስደበኝ በህግ አምላክ” ይላል፡፡ አሁንም “እናትክን ብሎ” መራገጡን ገፋበት፡፡ በዚህ መሃል ታዲያ “እንደው የሚደበደብ ሰው ያለህ!” እያለ አምላኩን ሲለማመን የነበረ የሚመስል ፖሊስ፤ ተንደርድሮ መጥቶ ተደርቦ ይረግጠው ገባ፡፡ ይሄ “የመምታት ሱስ  ካልሆነ በቀር ምን ሊባል ይችላል?” ለእኔ ግልጽ አልነበረም፡፡ ለነገሩ ነብስ ያጠፋ ሰው ፖሊስ ጣቢያ ገብቶ እጅ የሚሰጥበት ምክንያት እኮ የሟች ወገኖች እንዳይገሉት መንግስት ከለላ እንዲሰጠው ነው፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ የህግ ከለላ ይሰጣል እንጂ ህግ ተላልፏል ተብሎ የተጠረጠረ ሁሉ ይቀጠቀጣል እንዴ? ህገ መንግስታዊ የሰብአዊ መብትስ? ዜጎች ፖሊስ ሲያዩ ሰላምና መረጋጋት ሊሰማቸው ይገባል እንጂ ፖሊስ ሲያዩ ሽብር፣ ፖሊስ ሲያዩ እንደሰረቀ ሰው መደናበር ውስጥ መግባት የለባቸውም፡፡
እርግጥ ነው ሱስ አስያዥ ነገሮች በማህበረሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና  ስነልቦናዊ ቀውስ ይፈጥራሉ፡፡ ወደፊት ሀገር ተረካቢ ተተኪ ትውልድ በሱስ የሚጠመድ ከሆነ ወንጀል፣ አስገድዶ መድፈር፣ ራስን ማጥፋት፣ እብደት ወዘተ ሊከሰት ይችላል፡፡ አደንዛዥ እፅ በመጠቀም ምክንያት ከሚፈጠረው ችግር ውስጥ ይሄ እጅግ ቁንጽል ችግር ይመስለኛል፡፡ የስነልቦና ባለሙያዎች ከሱስ ጋር ተዛማጅ የሆኑ ችግሮችን በተመለከተ ብዙ ሊሉ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የእኔ ጥያቄ በሀገሪቱ እንኳን ጫት መቃም ሊያውቁ ቀርቶ “ጫት ማለት ምን ማለት እንደሆነ?” የማያውቁ የሀገሪቱ ክልል ከተሞች፣ በጫት ቤቶችና ሺሻ ቤቶች ተጥለቅልቀዋል፡፡ ለማመን በሚከብድ ፍጥነት ጫት መቃም ስልጣኔ፣ የዘመናዊነት መገለጫ ሆኗል፡፡
ፖሊስና ደንብ አስከባሪዎች “ከመቼውም ጊዜ በላይ የተጠናከረ ክትትል አድርገን ጫትና ሺሻ ቤቶችን እያሸግን ነው”፤ “ማጨሻ እቃዎች ሰብስበን አቃጥለናል” ይላሉ፡፡ በተቃራኒው ግን በተለይ ባለፉት አስር አመታት ውስጥ በአይነትም ሆነ በይዘት የተሻሻሉ ጫት ቤቶች በርክተዋል፣ የጫት ዓይነቶች በጥራት ጨምረዋል፡፡ የጫት ዋጋ የዛሬ አስር አመት ከነበረበት እጥፍ ሆኗል፡፡ ታዲያ ዋጋ እየጨመረ የመንግስት ቁጥጥር እየተጠናከረ፣የጫት ቃሚ ቁጥር ለምን ይጨምራል? ይባስ ብሎ በወር እስከ 30 ሺ ብር ድረስ ኪራይ እየከፈሉ፣ ሰፋፊ ግቢዎችን ተከራይተው አገልግሎት እየሰጡ ነው፡፡ ችግሩ የት ነው ያለው? ችግሩን ሳናውቅ መፍትሄ በመሰለን ነገር ላይ ብቻ ተመስርተን እየዳከርን ይመስለኛል፡፡ ፓራዶክስ (አያ አዎ) ነገር ነው፡፡
እኔ አንድ መፍትሄ ይታየኛል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ችግሩ እጅግ ስር የሰደደ መሆኑን በይፋ አምኖ፣ መፍትሄውን ለማመላከት እንዲረዳ ጥናት ማካሄድና የችግሩን ስፋትና ጥልቀት መገንዘብ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው፡፡ በመቀጠልም ችግሩን ለመቅረፍ ሁሉን አቀፍ ስራዎች መሰራት ቢገባቸውም ህገወጥ ጫት ቤቶችን ለመቆጣጠር ግን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወይም የከተሞች አስተዳደር ምክር ቤቶች አዲስ አዋጅ ወይም ደንብ ማውጣት አለባቸው፡፡ ችግሩ መኖሩን መንግስትም፣ ህዝብም ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ከተገነዘቡ ችግሩ የለም ብሎ መከራከር ይቆማል ማለት ነው፡፡
 አብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ችግሩ አንገብጋቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤ ስለ ችግሩ በግልጽ አያወራም፤ይልቁንም ውስጥ ውስጡን የአስቃሚዎችን እቃዎች በመውረስና ቅጣት በማስከፈል፣ ሰልችቷቸው ስራውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ ብዙ ባይሳካለትም፡፡
መሆን ይገባዋል ብዬ የማምነው፤ “ችግሩ አለ?” አዎ! ስለዚህ ለችግሩ እውቅና በመስጠት እንደማናችውም ስራ የንግድ ዘርፍ ወጥቶለት መቃሚያ ቤት ከፍቶ ለመስራት ህጋዊ ፍቃድ መስጠት፣ በሚሰጠው ፍቃድ ውስጥ ግን ዝርዝር ጉዳዮችን በማካተት፣ ለምሳሌ ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶችን ሲያስቅሙ ቢገኙ ንግድ ፍቃዳቸው እንዲቀማ ማድረግ፣ በገንዘብም በእስራትም እንዲቀጡ ህግ ማበጀት፡፡ ባለቤቱ፤ ተጠቃሚዎች በቤቱ ውስጥ ለሀገር ደህንነት ስጋት የሆኑ ስራዎች ሲሰሩ ቢያገኝ ወይም ቢሰማ ለፖሊስ ማሳወቅ እንዳለበት ግዴታ ማስገባት፡፡ ይህን ባያደርግ ግን ለሚፈጠረው ማናቸውም ችግሮች በሃላፊነት እንደሚጠየቅ ማሳመን ወዘተ እንዲካተቱ ማድረግ፡፡
ስለዚህ መንግስትና ህዝብ የወደፊት ተተኪ  ትውልድ ጤናማ እንዲሆንና አደንዛዥ እጽ ውስጥ እንዳይዘፈቅ ለሚያደርጉት ትግል፣ ከዚህ ቀደም ችግር አባባሽ የነበሩት ጫት አስቃሚዎች፣ የመፍትሄ አካል እንዲሆኑ መንገድ አመቻቸ ማለት ነው፡፡ በምእራባውያን መንግስታት ዘንድ ያሉት ህጎች ይዘታቸው ይህን ይመስላል፡፡ ለምሳሌ አንድ ባለ ሱፐርማርኬት 18 ዓመት ላልሞላው ወጣት ሲጋራ ቢሸጥለትና ወጣቱ ሲጋራ ሲያጨስ ፖሊስ ይዞት 18 ዓመት ያልሞላው መሆኑን ካረጋገጠ፣ የሸጠለት ባለ ሱቅ ወይም የሰጠው ግለሰብ በህግ ይጠየቃል፡፡ በመሆኑም ባለ ሱቁ፣ ገዢው ወጣት 18 ዓመት ያልሞላው ሊሆን ይችላል ብሎ ከተጠራጠረ መታወቂያውን ይጠይቃል፡፡ ተጠቃሚው መታወቂያ የለኝም ካለ አለመሸጥ እንጂ ሌላ አማራጭ የለውም፡፡
በህግ እንዳይዘዋወሩ፣ እንዳይጠቀሙ፣ እንዳያስጠቅሙ ክልከላ ያልተደረገባቸውን ጫት፤ ሲጋራና ሺሻ መጠቀም ወንጀል ካልሆነና፣ አንድ ለአቅመ አዳም የደረሰ ወንድ ወይም ለአቅመ ሄዋን የደረሰች ሴት፤ የምትፈጽመውን ድርጊት ጥቅምና ጉዳቱን ተገንዝበው የሚያደርጉት በመሆኑ፣ ሌላ ምክንያት ከሌለ በስተቀር ዜጎች የመጠቀም መብታቸው ሊከለከል አይገባም፡፡ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበረሰባዊ፣ የጤናና የስነልቦና ችግሮች ያስከትላል ከተባለ፣ማስተማርና ግንዛቤ የመጨመር ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል ያስፈልጋል፡፡
በካዛንቺሱ ገጠመኜ ተከድኖ ይብሰል ብለን የተውነው ችግር ቀላል እንዳልሆነ ለእኔ ተሰምቶኛል፡፡ ለዚህም ነው ያለኝን ሃሳብ ያካፈልኩት፡፡ መንግስት የዜጎችን መብት የመጠበቅ፣ ያለመናድ፣ ያለመደፍጠጥ ግዴታ አለበት፡፡ በአንዳንድ ሥነምግባር የጎደላቸው ፖሊሶች ስሜታዊነትና ግልፍተኝነት ምክንያት የዜጎች ሰብአዊና ሲቪል መብቶች ሲጣሱ ዝም ብሎ ማየት ተገቢ አይመስለኝም፡፡ ዜጎች እንዲህ መሰሉ የመብት ጥሰት በአንዳንድ ፖሊሶች ሲደርስባቸው አቤት የሚሉበትን ቦታም ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡ በተለይ እኔ እንደታዘብኩት ዓይነት የመብት ጥሰት በፖሊስ ጣቢያ ሲፈጸም ብዙዎች ግራ ሊጋቡ ይችላሉና ይታሰብበት፡፡

• ሶስት ግለሰቦች ተጠያቂዎች ሆነዋል፡፡ የስራ አስፈፃሚው አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ከሃላፊነት
ሲታገዱ ሁለቱ ሰራተኞች የጽሕፈት ቤት ኃላፊው ዘሪሁን ቢያድግልኝና፣ የአይቲ
ባለሙያዋ ዘውድነሽ ይርዳው ደግሞ ተባርረዋል፡፡
• ከስራ አስፈፃሚው አባላት አንዱ ይቅርታ ሲጠይቁ፤ ፕሬዝዳንቱና ሌሎቹ አመንትተዋል
• ጠቅላላ ጉባዔ እንደማይጠራም ተገልጿል፡፡

    በኢትዮጵያ ሴቶች እግር ኳስ  ላይ የፌዴሬሽን አስተዳደር ባደረሰው ከባድ ጥፋት ዙርያ በትናንትና እለት በኢንተርኮንትኔንታል የተሰጠው መግለጫ በቂና ተገቢ ምላሾች  ሳይሰጡት ቀረ፡፡ የሴቶች እግር ኳስ ባለድርሻ አካላት፤ የስፖርት ቤተሰቡ፤ የሚዲያ አካላትና ሌሎች ባለሙያዎች በሉሲዎች የውድድር ተሳትፎና የወፊት አቅጣጫዎች ላደረሱ ጥፋቶች አጠቃላይ አስተዳደሩ ተጠያቂ መሆን እንደሚገባውና በይፋ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ሲያሳስቡ ቢሰነብቱም መግለጫውን የሰጡት የፌደሬሽኑ አመራሮች ለደረሱት ጥፋቶች ሶስት ግለሰቦችን ተጠያቂዎች አድርገው በርካታ ጉዳዮችን አድበስብሰው አልፈዋል፡፡
ትናንት በኢንተርኮንትኔንታል ሆቴል በተካሄደው ጋዜጣው መግለጫ 4 የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የስራ አስፈፃሚ አባላት ተገኝተዋል፡፡ እነሱም ፕሬዝዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻ፤ እንዲሁም ሌሎች የስራ አስፈፃሚው አባላት ኢንጅነር ጆን ቼቤ፤ አቶ አበበ ገላጋይ፤ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው እና አቶ አሊ ሚራህ ነበሩ፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው ስራ አስፈፃሚዎቹ ሉሲዎች ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ውድድር ውጭ የሆኑባቸውን ጥፋቶች የፈፀሙት 3 ግለሰቦች መሆናቸውን እንዳረጋገጡ ሲገልፁ አንደኛው የስራ አስፈፃሚ አባል እንደሆኑና፤ ሁለቱ የፌደሬሽኑ ሰራተኞች ናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የመጀመርያው ጥፋተኛ  ተብለው ከሃላፊነታቸው የታገዱት የስራ አስፈፃሚው ኮሚቴ  አባል የነበሩት አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ናቸው፡፡ አቶ ዮሴፍ በመግለጫ ላይ ተገኝተው ለሚዲያ ቃላቸውን እንዲሰጡ እድል ተሰጥቷቸው እንደነበር ውሳኔውን ያሳለፉት የስራ አስፈፃሚ አባላት ገልፀዋል፡፡ መረጃዎች እንዳመለከቱት ግን ይህ እድል እንደተነፈጋቸውና ከስራ ካገዳችሁኝ ሃላፊነቱን እለቃለሁ ማለታቸውን ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ለእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ከካፍ የተላኩትን የውድድር ተሳትፎ ማረጋገጫ 4 ደብዳቤዎች በአግባቡ ባለመመልከታቸው ሁለት የፌዴሬሽን ተቀጣሪዎች ተጠቃቂ ተደርገዋል፡፡ ሁለቱ ሰራተኞች ለአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  በተገቢው ጊዜ ምላሾችን ባለመስጠታቸው፤ ከሚመለከታቸው ጋር በቅርበት ባለመስራታቸውና ስለ ውድድር የተሳትፎ ማረጋገጫ ማሳወቅ ቢኖርባቸውም ግድየለሽነት በማሳየታቸው ከስራቸው እንዲባረሩ ተወስኖባቸዋል፡፡ የመጀመርያው የፅህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ዘሪሁን ቢያድግልኝ ሲሆኑ ፌደሬሽኑ እንዳሰናበታቸው ከማሳወቁ በፊት የስራ መልቀቂያ አስገብተው ነበር ተብሏል፡፡ ሌላዋ ተጠያቂ ሆና ከስራዋ እንድትሰናበት የተወሰነባት ደግሞ ለረጅም ዓመታት በእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የቀድሞ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ሆና በርካታ ስራዎች ስታከናውን የነበረችው የፌደሬሽኑ የአይቲ ዲፓርትመንት ሃላፊ ዘውድነሽ ይርዳው ናት፡፡ ዘውድነሽ በደረሰው ጥፋት ከካፍ በቀጥታ ይደርሷት የነበሩትን ደብዳቤዎች በግድየለሽነት ተመልክታለች፤ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሳይሆን የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች ተሳትፎን የሚመለከት ደብዳቤ ነው በሚል አዘናግታለች በሚል ጥፋተኛ መደረጓን በመግለጫ ላይ የነበሩት የስራ ሃላፊዎች አብራርተዋል፡፡
ከ1፡30 በላይ በፈጀው ጋዜጣዊው መግለጫ ላይ ከ30 በላይ የስፖርት ሚዲያዎች ተገኝተው ነበር፡፡ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ  መድረኩ ለሁሉም ጥያቄዎች ዕድል መስጠት የማይቻበት መሆኑን በተደጋጋሚ በመግለፅ፤ የምናካሂደው ጋዜጣዊ መግለጫ እንጂ ስብሰባ አይደለም በማለት ሲናገሩ ነበር፡፡ በአጠቃላይ ጋዜጣዊ መግለጫው በርካታ ጥያቄዎች ያልተመለሱበት፤ በርካታ አሳሳቢ አጀንዳዎች ማብራርያ ሳይሰጥባቸው የተድበሰበሱበት በስፖርት ሚዲያውና በፌዴሬሽኑ የሥራ ኃላፊዎች መካከል የተለያዩ ውዝግቦች የ የተንፀባረቁበትና አለመደማመጥ የሰፈነበት  ነበር፡፡
በመግለጫው ላይ ከተገኙ የሥራ አስፈጻሚ አባላት ኢ/ር ጆን ቼቤ ብቻ በይፋ ይቅርታ ቢጠይቁም የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ እና አብረዋቸው መግለጫ ላይ የነበሩት ሦስት የሥራ አስፈጻሚ አባላት  ይቅርታ ለመጠየቅ እንዳዳገታቸው ለመታዘብ ተችሏል፡፡ አንድ ሁለት ሰው ባጠፋው ሁሉም መወንጀል የለበትም፤ የሚል አቋማቸውንም አስታውቀዋል፡፡
በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተገኙት የስፖርት ሚዲያዎች ፌደሬሽኑ ለደረሱት ጥፋቶች በይፋ ይቅርታ እየተጠየቀ ነው አይደለም በሚልም ግራ መጋባታቸውን በተለያየ መንገድ ቢገልፁም፤ የፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ይህን አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ፤ በቂ ማጣራት እና ምርመራ አድርጎ መግለጫ ከመስጠት በላይ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ፤ ጥፋተኞችን ከስራ በማገድ እንዲሁም ቀጣይ አቅጣጫዎቹን ለመወሰን ምክክር በማድረግ የተከተልናቸው እርምጃዎችን መገንዘብ አለባችሁ ከዚህ በላይ ይቅርታ ለማለት ያዳግተናል ብለዋል፡፡
ከጋዜጣዊ መግለጫው በፊት ባለፈው ሰሞን ክለቦች አቋማቸውን ያሳወቁባቸውን ደብዳቤዎችን ማሰራጨታቸው የሚታወስ ነበር፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ በጉዳዩ ላይ አፈጣኝ ማብራርያ እንደሚያስፈልግ ሲያሳስብ የቡና ስፖርት ማህበር ደግሞ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ጠይቋል፡፡  የቅዱስ ጊዮርጊስ ህዝብ ግንኙነት እንደ ክለብ ወደ ውድድር የየምንገባበት ለብሔራዊ ቡድን አስተዋፅኦ ማድረግ ቢሆንም በእቅዳችን መሰረት ስኬታማ ካልሆንን ተጫዋቾቻችን ሀገር አለመወከላቸው ያሳዝነናል ብሎ ሲያስታውቅ የቅድስተ ማርያም ኮሌጅ፤ የዳሸን ክለቦችም በደረሰው ጥፋት ያደረባቸውን ቁጭት ከገለፁት መካከል ይገኙበታል፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫው  ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ከላይ የተዘረዘሩትን የክለቦች አቋሞች በተመለከተ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ምላሾችን ሲሰጡ  ቡድን መስርተው እና በጀት መድበው ከሚሰሩ ክለቦችና ኃላፊዎቻቸው ጋር በቀጥታ ግንኙነት እያደረግን ለመግባባት  የምንችልባቸውን ሁኔታዎች እንፈጥራለን ብለው፤ ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የማያስፈልግ ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በማያያዝ ሌላው የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አበበ ገላጋይ በበኩላቸው ጠቅላላ ጉባኤ መጥራት የሚቻለው በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት እንደሆነ ገልጸው አንድ ወይም ሁለት ክለብ ስለጠየቀ ሳይሆን ከጠቅላላ ጉባኤው አካላት ሁለት ሦስተኛው እንዲጠራ ከወሰኑ ብቻ ሊፈፀም የሚችል መሆኑን ሊያስገነዝቡ ሞክረዋል፡፡
በሌላ በኩል የስፖርት ሚዲያው በመግለጫው ካነሳቸው ጉዳዮች ዋንኛው በአጠቃላይ በስልጣን ላይ ያለው የእግር ኳስ ፌዴሬሽን በሴቶች እግር ኳስ በቂ ትኩረት አልሰጠም የሚለው ነበር፡፡ አሁን የታገዱት የቀድሞው የሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ዮሴፍ ተስፋዬ ፌደሬሽኑን በመወከል፤ በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የሴቶች ልማት ኮሚቴ አባልነት መመደባቸው፤ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ተሳትፎ ዙሪያ ከአራት ጊዜ በላይ ደብዳቤ ተልኮ በቂ ትኩረትና ምላሽ አለመሰጠቱ፤ በአጠቃላይ በፌዴሬሽኑ አመራር ውስጥ ሴቶች አለመኖራቸው ለደረሱት ጥፋቶች አስተዋፅኦ ማድረጋቸውን የዳሰሱ ሃሳቦች በሁሉም ጥያቄዎች ተንፀባርቀዋል፡፡
በእነዚህ ሁኔታዎች ላይ ፕሬዚዳንቱ አቶ ጁነዲን ባሻና ሌሎቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት በሰጧቸው ማብራሪያዎች በጥቅሉ ለሴቶች እግር ኳስ በቂ ትኩረት አልተሰጠም መባሉን አልተቀበሉትም፡፡ በአገሪቱ እግር ኳስ ታሪክ በሀ-20 ደረጃ ብሔራዊ ቡድን ተቋቁሞ እስከ ዓለም ዋንጫ ዋዜማ በማጣሪያ ውድድሮች መጓዝ መቻሉ፤ በሀ-17  በአገር ውስጥ ውድድሮች መካሄዳቸውና በአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎ እንዲኖር መደረጉን የጠቀሱት የፌደሬሽኑ ፕሬዝዳንት፤ በዋናው ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ደግሞ የዋና እና  ረዳት አሰልጣኞች  ኃላፊነት ላይ ሴቶች መሾማቸው እንዲሁም የደመወዝ መሻሻሎች መደረጋቸው እንደውጤት መታየት አለበት ሲሉ አስተባብለዋል፡፡ ይሁንና ካለፈው ሰሞን አስተዳደራዊ ጥፋት በኋላ ክለቦች በሴቶች እግር ኳስ ለመስራት ያላቸው ፍላጎት መቀነሱ፤ አንዳንድ ክለቦች ከወዲሁ ቡድኖቻቸውን እያፈረሱ መሆናቸውን፤ በጉዳዩ ላይ ጠበጠቅላላ ጉባኤ እንምከርበት የሚሉት ጥያቄዎች በቂ ምላሽ ሳይገኝባቸው  ተድበስብሰዋል፡፡
የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስተዳደራቸው የፈፀመውን ጥፋት በሦስት የተለያዩ ኃላፊዎች ላይ ብቻ በመጫን ለማለፍ መሞከራቸውና በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁ በተደጋጋሚ የቀረበላቸውን ጥያቄ አልወደዱትም፡፡ ፌዴሬሽኑ አስተዳደራዊ ስህተት መሰራቱን በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ከሰጠበት እና ጥፋት በፈፀሙት ሦስት ኃላፊዎቹ ላይ እርምጃ ከወሰደ በቂ ይሆናል ብለው ተሟግተዋል፡፡
ስልጣኑን በገዛ ፍቃዱ መልቀቅ እንደሌለበት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ባንፀባረቀው አቋም ያረጋገጠው የፌዴሬሽኑ ሥራ አመራር ከክለቦች ጋር በምን አይነት ሁኔታ እንደሚመካከር የወጣቶቹ ሉሲዎች ቡድን እስከ ዓለም ዋንጫ የመጨረሻ ማጣሪያ በመጓዝ ላሳየው ጀግንነት ምን አይነት ማበረታቻና ማፅናኛ ለማድረግ ማሰቡን ሳይገልጽ ነው ያለፈው፡፡ ፕሬዚዳንቱ በተሰጣቸው ኃላፊነት የፌዴሬሽኑ ሥራዎች በትክክል መከናወናቸውን ማረጋገጥ፤ የሥራ አስፈጻሚውን አባላት የማስተባበር የመምራት የመቆጣጠር ድርሻ ቢኖርባቸውም ይህን አለመፈፀማቸው በአንደኛ ደረጃ ተጠያቂ ሆነውበት ከሥልጣን መልቀቅ እንደነበረባቸው የስፖርት ሚዲያው ሊያመለክት ሞክሯል፡፡ ይሁንና ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጠው የፌዴሬሽኑ የሥራ አመራር በአጠቃላይ ያስተዳደር ችግር እንዳለበት ሥልጣን ልቀቁ ከማለት መዋቅሩ የሚስተካከልበትን ሁኔታ መመልከት አለብን በሚለው ማስተባበያቸው አቶ ጁነዲን ባሻ ሌሎቹ የስራ አስፈፃሚ አባላት  መግለጫውን አገባደውታል፡፡

    የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር ያለን ልዩነት “ጠባብ ነው” ማለታቸው እያነጋገረ ነው፡፡ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት ባለፈው ሳምንት በዓዲግራት ሀገረ ስብከት ተገኝተው የደብረ መድኃኒት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያንን በመረቁበት ወቅት ሲሆን በሥነ ሥርዓቱ ላይ የትግራይ ክልል ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ተስፋ ሥላሴ መገኘታቸውን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ድረ ገጽ ዘግቧል፡፡
ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ፣ “ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጋር  ያለንን ጠባብ የሃይማኖት ልዩነት ጠብቀን፣ በዜግነታችንና በክርስቶስ ልጅነታችን በዋና ዋና የልማት ሥራዎች ዙሪያ በጋራ በመሥራት፣ ለክርስቶስም ለሰው ልጅም ደስታን የሚሰጥ አገልግሎት ማበርከት  ይጠበቅብናል፤” ብለዋል - ድረ ገጹ እንደዘገበው፡፡ይሁንና የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያላቸው የእምነትና የሥርዓት አስተምህሮ ልዩነት መሠረታዊ መሆኑን የጠቀሱ አስተያየት ሰጪዎች፣ ፓትርያርኩ ሃይማኖታዊ ልዩነቱ ጠባብ እንደሆነ ተናግረዋል ተብሎ በሰፈረው ዘገባ ግር መሰኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡

   በስፔናዊው ሚጌል ሊያንሶ ተፅፎ የተዘጋጀውና ከ60 በላይ በሚሆኑ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ 10 ሽልማቶችን ያሸነፈው “Crumbs” (ስብርባሪ) የተሰኘው ሳይንሳዊ ልብወለድ ፊልም፤ ትላንት ምሽት በአቤል ሲኒማ ተመረቀ፡፡ ከዓለም ጦርነቶች ፍፃሜ በኋላ ምን ሊፈጠር እንደሚችል በሚያመለክተው በዚህ ፊልም ላይ ዳንኤል ታደሰ (ጋጋኖ) በመሪ ተዋናይነት የተጫወተ ሲሆን ባሳየው የትወና ብቃትም አድናቆት ተችሮታል ተብሏል፡፡ ለትወናው አምስት ሺህ ዩሮ (125ሺ ብር) እንደተከፈለው ጋጋኖ ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡ ፊልሙ በአውሮፓና በአሜሪካ በተለያዩ ከተሞች ለእይታ ቀርቦ አድናቆትን ያተረፈ ሲሆን ከ60 በላይ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ተሳትፎ፣ ከ10 በላይ ሽልማቶችን ማግኘቱን የፊልሙ ፕሮዲዩሰር አርቲስት ዮሐንስ ፈለቀ ገልጿል፡፡ “ክረምብስ” ፊልምን፣ ለመስራት 200ሺ ዶላር እንደፈጀ ተናግሯል፡፡   

አዞ ከሰው የተሻለ ታማኝ ዘብ ነው፤ በሙስና አታታልለውም!...”

    የኢንዶኔዥያ የጸረ - አደገኛ ዕጾች ብሄራዊ ተቋም ሃላፊ፣ ከአደገኛ ዕጾች ጋር በተያያዘ ተከስሰው ሞት የተፈረደባቸውን ወንጀለኞች ለማቆያነት የሚያገለግልና ዙሪያውን በአዞዎች ተከብቦ ጥብቅ ጥበቃ የሚደረግለት አዲስ የደሴት ላይ እስር ቤት የማቋቋም ዕቅድ እንዳላቸው ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ከሰው ልጆች ይልቅ አዞዎች በአብዛኛው የተሻሉ ጠባቂዎች ናቸው፣ ምክንያቱም ሙስና አይቀበሉም ያሉት የመስሪያ ቤቱ ሃላፊ ቡዲ ዋሴሶ፣ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተዘዋውረው፣ ለሚገነባው እስር ቤት ጠባቂ ሊሆኑ የሚችሉ እጅግ ጨካኝ የሆኑ አዞዎችን የማፈላለግ ሃሳብ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡“በቻልነው አቅም ሁሉ በእስር ቤቱ ዙሪያ በርካታ አዞዎችን እናሰማራለን!... አዞዎችን በሙስና
ልትደልላቸውና፣ የፈለግኸውን እስረኛ እንዲያመልጥ እንዲያግዙህ አግባብተህ ልታሳምናቸው አትችልም!...” ብለዋል ቡዲ ዋሴሶ፡፡እስር ቤቱን የማቋቋም ሃሳቡ ገና በእቅድ ደረጃ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፤ የት አካባቢ እንደሚገነባም ሆነ ግንባታው ተጠናቅቆ በይፋ ስራ የሚጀምርበትን ትክክለኛ ጊዜ በተመለከተ ገና ውሳኔ ላይ አለመደረሱን ጠቁሟል፡፡

    አሊባባ የተባለው የቻይና የኢንተርኔት ንግድ ኩባንያ ባለፈው ረቡዕ በተከናወነው ሲንግልስዴይ የተባለ አመታዊ ልዩ የሽያጭ ፌስቲቫል
ባስመዘገበው ሽያጭ፣ በራሱ ተይዞ የቆየውን የዓለማችን የኢንተርኔት ዕለታዊ ሽያጭ ክብረወሰን ያሻሻለ ሲሆን አጠቃላይ ሽያጩ ከ13.8
ቢሊዮን ዶላር በላይ ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመት ኤንቢሲ ኒውስ ዘገበ፡፡
ኩባንያው ረቡዕ ዕለት በተከናወነው “የሲንግልስ ዴይ” የሽያጭ ፌስቲቫል ላይ በስምንት ደቂቃ
ውስጥ ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስመዝገቡንና ባለፈው አመት ያገኘውን የ9.3 ቢሊዮን ዶላርየዕለት ሽያጭ ገቢ ለማግኘት
የወሰደበት ጊዜ አምና ከነበረው በግማሽ ያነሰ መሆኑንም ዘገባው ጠቁሟል፡ ፡ኩባንያው በዘንድሮው የ “ሲንግልስ ዴይ” አለማቀፍ
ልዩ የሽያጭ ፌስቲቫል ላይ፣ ከ6 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ምርቶችን ለሽያጭ ማቅረቡንና በዕለቱም በአንድ ደቂቃ ከ120 ሺህ በላይ የግዢ
ጥያቄዎችንና 60 ሺህ ያህል ክፍያዎችን መቀበል የቻለበት ደረጃላይ መድረሱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሽያጩ በይፋ በተከፈተ በአንድ ሰዓት ጊዜውስጥ በሞባይል አማካይነት ብቻ 27 ሚሊዮን ግብይቶችን መፈጸሙን ያስተዋወቀው
ኩባንያው፤
በዕለቱ የሸጣቸውን የኤሌክትሮኒክስና የመዋቢያ
ዕቃዎች ጨምሮ ሌሎች ሸቀጦችን በ1.7 ሚሊዮን
መልዕክተኞች፣ በ400 ሺህ መኪኖችና በ200
አውሮፕላኖች ለገዢዎች እንደሚያደርስም አክሎገልጿል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች ረዥም መንገድ ሊሄዱ ይነሳሉ፡፡ ምክክር ይጀምራሉ፡፡
አንደኛው - እንዲያው ለነገሩ እንዲህ ያለ ረዥም መንገድ ስንጀምር ብዙ ስንቅ መያዝ ነበረብን’ኮ፡፡
ሁለተኛው - ያንተን አላቅም እንጂ እኔ ከቤት የተዘጋጀልኝን ስንቅ ይዣለሁ፡፡
አንደኛው - ምን ምን ይዘሃል?
ሁለተኛው - በሶ፣ ጭኮ
አንደኛው - ሌላስ?
ሁለተኛው - አንድ አገልግል አላቂ ምግብ፣ ለአንድ ቀን የሚሆነን፡፡
አንደኛው - የሚጠጣስ?
ሁለተኛው - የሚጠጣስ ከኮዳዬ ውሃ ሌላ ምንም አልያዝኩም!
አንደኛው - መንገድ ላይ አውሬም፣ ሽፍታም ሊያጋጥመን ይችላል፡፡ ምን መሳሪያ ይዘሃል?
ሁለተኛው - ኧረ መሣሪያስ ምንም አልያዝኩ፡፡ እንዲያው አምላካችንን ተማምኜ ነው የወጣሁ፡፡፡ ለመሆኑ አንተስ ምን ይዘህ ነው የመጣህ?
አንደኛው - እኔ ምግብ፣ መጠጥ፣ መሳሪያ… አንዱንም አልያዝኩም፡፡ የሁለታችንን ልባዊ ፍቅር፣ አብሮ አደግነትና ዝምድናችንን ተማምኜ ነው የመጣሁት፡፡
ሁለተኛው - ይሄንንም ካሰነበተልን ምን እንፈልጋለን፡፡ በዚሁ ተማምነን መንገዳችንን መቀጠል ነው ያለብን፡፡
አንደኛው - በጣም ጥሩ እንግዲህ፤ ልባችንን አንድና ንፁህ አድርገን እንገስግስ፡፡
ሁለቱ ጓደኛሞች ተስማምተው መንገዳቸውን ተያያዙት፡፡ ከተማውን ዘልቀው ገጠር ደረሱ፡፡ ጫካ ጫካውን ሲያቋርጡ በድንገት አንድ ድብ ከፊታቸው ከች አለ፡፡ ይሄኔ አንደኛው በከፍተኛ ፍጥነት ተስፈንጥሮ ዛፍ ላይ ወጣ፡፡ ሁለተኛው የሚያደርገው ጨነቀው፡፡ አንድ ዘዴ ትዝ አለው፡፡ ድብ በተፈጥሮው ሬሣ አይበላም፡፡ ስለዚህ ሰውዬው ድምፁን አጥፍቶ ቢጋደም ድቡ ምንም ላያደርገው ይችላል፡፡
መሬት ላይ ተጋደመ፡፡
ድቡ ወደተኛው ሰው ቀረበና ወደፊቱ ጠጋ አለ፡፡ ከዚያም አሸተተውና ሞቷል ብሎ ጥሎ ሄደ፡፡ ድቡ መሄዱን ያየው ዛፉ ላይ ያለው ሰውዬ፣ ፈጥኖ ወረደና ወደተኛው ጓደኛው በመምጣት እንዲህ ሲል ጠየቀው፤
“ድቡ ወደ ጆሮህ ጠጋ ብሎ ሹክ ያለህ ነገር ምንድነው?”
የተጋደመው ጓደኛውም እንዲህ ሲል መለሰለት፡-
“ወዳጄ ሆይ! ከእንዲህ ከማያስተማምን ከሀዲ ጓደኛ ጋር አብረህ ረዥም መንገድ አትጀምር! ብሎ ነው የመከረኝ!”
*         *         *
ረዥም ጉዞ የሚጠብቀን መንገደኞች መተማመን ይገባናል፡፡ በአንድ ልብ የማይጓዙ መንገደኞች አገር አይገነቡም፡፡ ይልቁንም ቶሎ የመፈራረስ፣ እርስ በርስ የመጠራጠር፣ አንዱ አንዱን ለመጣል የመጣር፣ የመተነኳኮስና የመካካድ ባህሪ ያነግሳሉ፡፡ ተቋማዊ
አደረጃጀታቸውን ጥያቄ ላይ የሚጥለው ይህን ዓይነት ባህሪ ሲኖር ነው፡፡ ቡድናዊነትና ወገናዊነት ከበዛ መንገዶች እንቅፋት ይበዛባቸዋል፡፡ ይህ በፈንታው አገሬውን ይበድላል፡፡
መልካም አስተዳደርን ለማምጣት አስተዳዳሪዎቹ መልካም መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ መልካምነት በድንገት የሚከሰት ነገር አይደለም፡፡
የልብ ንፅህናን ይፈልጋል፡፡ የእጅ ንፅህናንም ይፈልጋል፡፡ ብስለትን ይፈልጋል፡፡ የሙሰኞች ፀር መሆንን ይጠይቃል፡፡ ከስህተት ተምሮ በየጊዜው ራስን ማሻሻልን ይጠይቃል፡፡ ባለጉዳይን ማክበርን ይጠይቃል፡፡ ምዝበራን መከላከልን ይጠይቃል፡፡ ፍትሐዊነትን ይጠይቃል፡፡

እነዚህ ባህርያት ሂደታዊ ናቸው፡፡ እያደር ራስን በመለወጥ የሚመጡ ናቸው፡፡ አብዛኛውን የለውጥ ጉዞ አዲስ አበባ ላይ ማየት የዋና ከተማችን እምብርትነትና ከተሜነት (ሜትሮፖሊታን መሆን) አመላካች ነው፡፡ ብዙ ጥፋቶችም ልማቶችም የሚታዩት ዋና ከተማ ላይ
መሆኑ ቁልፍ ቁልፍ ተቋማትም፣ ሹማንንትም እዚችው ከተማ ላይ መከማቸታቸውን ይነግረናል፡፡ ከየክልሉ ወደ ዋና ከተማይቱ የሚፈልሰው ህዝብ፣ የነዋሪውን ህዝብ ቁጥር መጨመሩ ብቻ ሳይሆን ባለጉዳዩን ያበረክተዋል፡፡ ባለጉዳዩ የመሬት ጉዳይ አለው፡፡
የመኖሪያ ቤት ጉዳይ አለው፡፡ የፍትህ ጉዳይ አለው፡፡ የከፋ የኢኮኖሚ ጉዳይ አለው፡፡ ይህንን ጉዳይ የሚፈታለት፣ የሚያስተናግድለት መልካም አስተዳደር ይሻል፡፡፡ በንፁህ መሰረት ላይ የተቋቋሙ መሥሪያ ቤቶች ከሌሉ፣ ባለጉዳይ አስፈፃሚ ጋር እየተሞዳሞዱ ሥራ
በሚያንቀሳቅሱበት ከተማ፣ መልካም አስተዳደርን መመኘት ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ ብርቱ ቁጥጥርና ብርቱ እርምጃን ይጠይቃል፡፡ እርምጃው እውነተኛ እርምጃ እንዲሆን የተሿሚዎች እከክልኝ ልከክልህ ሰንኮፍ መነቀል አለበት፡፡ ዘረፋና ምዝበራ መቆም አለበት፡፡
ከቢሮ ውጪ የሚደረጉ ውሎችና ድርድሮች መወገድ አለባቸው፡፡ ይህ ትግል ከባድ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል፡፡
ተግባሩ ላይ ሳይሳተፉ ወይም ተግባሩን እያደናቀፉ፣ የአደባባይ ስብሰባ ላይ አንደበት ቢያሳምሩና ቢያስጨበጭቡ “ለጌሾው ወቀጣ
ማንም ሰው አልመጣ የመጠጡ ጊዜ ከየጎሬው ወጣ!” እንደሚባለው ነው እሚሆነው፡፡ ተግባሪ ሳይኖር፣ ስለመልካም አስተዳደር ዘማሪው በዛ እንደማለት ነው፡፡ ተግባሪ አመራር ይኖር ዘንድ ውስጡ መፈተሽ ይኖርበታል!

Saturday, 07 November 2015 10:33

የኪነት ጥግ

(ሞዴሊንግና ፋሽን)
• በወንዶች ዓለም ውስጥ ሆኜም እንኳን
ሴትነቴን እወደዋለሁ፡፡ ወንዶች እኮ ቀሚስ
መልበስ አይችሉም፤ እኛ ግን ሱሪ መልበስ
እንችላለን፡፡
ዊትኒ ሂዩስተን
• ፋሽን ይደበዝዛል፤ስታይል ዘላለማዊ ነው፡፡
ይቭስ ሴይንት-ሎውሬንት
• በሁሉም ነገር ውስጥ ውበት ያለ
ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎች አስቀያሚ
ባሉት ነገር ውስጥ ውበትን ማየት
እችላለሁ፡፡
አሌክሳንደር ማክኩዊን
• ሞዴሊንግ ለእኔ ቆንጆ የመሆን ጉዳይ
አይደለም፤ ለሰዎች የሚመለከቱትና
የሚያስቡት ማራኪ ነገር መፍጠር ነው፡፡
ኪሊ ባክስ
• ሞዴሊንግ በትክክል የዝምታ ትወና ነው፡፡
አሪዞና ሙሴ
• ሞዴሊንግ መቶ ፐርሰንት፣ ቅድምያ
የምሰጠው ቁጥር አንድ ጉዳዬ ነው፡፡
ኬንዳል ጄነር
• ገንዘቤን ባንክ አስቀምጣለሁ፡፡ ከሞዴሊንግ
በኋላ ላለው ህይወቴ ማሰብ አለብኝ።
ዝነኝነቴ ካከተመ በኋላ ለሚኖረው
ህይወቴ።
ኢቫ ሄርዚጐቫ
• ሞዴሊንግ የብቸኝነት ሥራ ነው፡፡
ኪም አሌክሲስ
• አንፈልግሽም እስክባል ድረስ በሞዴሊንግ
እቀጥላለሁ፤ምክንያቱም በጣም
እወደዋለሁ፡፡
ክላውዲያ ስሺፈር
• የሎስ አንጀለስ ፋሽን፣ የሞዴሊንጉ ዓለም
ስታርባክስ ነው፡፡
ጃኒሴ ዲክሰን
• ትወናና ሞዴሊንግ አንዳቸው ከሌላኛቸው
የሚያገናኛቸው ነገር የለም፡፡
ኢሌ ማክፈርሰን

      በ2002 ዓ.ም “ጀነራሎቹ” በሚል ርዕስ ለንባብ የበቃው ታሪካዊ መፅሐፍ፤ አዳዲስ አስገራሚ፣ አሳዛኝና ቀልብ የሚስቡ መረጃዎችን በማካተት እንደገና የተዘጋጀ ሲሆን በነገው ዕለት ከቀኑ 7 ሰዓት ጀምሮ በግራንድ ዮርዳኖስ ሆቴል እንደሚመረቅ ደራሲው ሻምበል ኢዮብ እንዳለ ለአዲስ አድማስ አስታወቁ፡፡
በዚህ መፅሀፍ ውሰጥ ደም ያፋሰሰውና ያልተሳካው የግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ እንዲሁም ጀነራል ተፈሪ በንቲን ጨምሮ የ106 የደርግ አባላትን ጉርድ ፎቶግራፎችና በደርግ ውስጥ በነበረው የስልጣን ሽኩቻ በተለያየ ጊዜ የተገደሉ የጦር ጀነራሎች በርካታ ፎቶግራፎች እንደተካተተቱ ተጠቁሟል፡፡  
መፅሀፉ ቀደም ሲል በ302 ገጾች፣143 ፎቶግራፎችን አካትቶ የቀረበ ሲሆን የአሁኑ 351 ፎቶዎችን በማካተት በ496 ገጾች መዘጋጀቱንና ለ6ኛ ጊዜ መታተሙን ፀሐፊው ገልፀዋል፡፡ ከ2004 እስከ 2007 ባሉት ጊዜያት ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር መፅሀፉን አንብበው አስተያየት ከላኩ ሰዎች የተገኙ ትክክለኛ መረጃዎች የተካተቱበት ነው የተባለው “ጀነራሎቹ”፤ በ165 ብር ለገበያ መቅረቡም ታውቋል። መጽሐፉ እስካሁን አምስት ጊዜ ታትሞ፣ 22ሺህ ቅጂዎች መሸጣቸውንም ጸሐፊው የላኩት መረጃ ያስረዳል፡፡