Administrator

Administrator

   87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አለው
    87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያካበተው የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ፣ በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2016 የዓለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አንደኛ ደረጃን መያዙን ታይም መጽሄት ዘገበ፡፡
ዌልዝ ኤክስ የተባለውና የአለማችንን ባለጸጎች የሃብት ደረጃ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ተቋም ከሰሞኑ በድረገጹ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአመቱ ከቢል ጌትስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ስፔናዊው ቢሊየነር አማኒኮ ኦርቴጋ ሲሆኑ ባለጸጋው 66.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው፡፡
አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት በ60.7 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዛቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ 42.8 ዶላር የተጣራ ሃብት አለው የተባለው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግም ስምንተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዘገባው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ማይክል ብሉምበርግ በ42 ቢሊዮን ዶላር ዘጠነኛ ደረጃ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 33.2 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በማካበት ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው የዎልማርት ኩባንያዋ አሊስ ዋልተን በአለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡

           በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ አግኝቷል
     ታዋቂው የቴክኖሎጂ ምርቶች አምራች ኩባንያ አፕል፣ ዝነኛውን የስማርት ፎን ምርቱን አይፎንን ለገበያ ማቅረብ ከጀመረበት እ.ኤ.አ ከ2007 ወዲህ ሽያጩ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀነሱን ማስታወቁንና ይሄን ተከትሎም የኩባንያው የአክሲዮን ድርሻ ዋጋ እንደቀነሰ ስካይ ኒውስ ዘገበ፡፡ ኩባንያው በተጠናቀቀው የፈረንጆች አመት የመጨረሻዎቹ ሶስት ወራት 74.8 ሚሊዮን አይፎኖችን በመሸጥ በታሪኩ አነስተኛውን የአይፎን ምርቶች የሽያጭ እድገት ማስመዝገቡንና በቀጣይም ሽያጩ እየቀነሰ እንደሚሄድ ማስታወቁን ዘገባው ገልጧል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ አፕል ኩባንያ ምንም እንኳን የአይፎን ምርቶች ሽያጩ ቢቀንስም፣ ባለፈው ሩብ አመት ባገኘው የ18.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ትርፉ በአሜሪካ ኩባንያዎች ታሪክ ከፍተኛውን የሩብ አመት ትርፍ ሊያስመዘግብ መቻሉን ዘገባው ጠቁሟል፡፡
አፕል ኩባንያ የአይፎን ምርቶቹ ሽያጭ መቀነሱን በይፋ ማስታወቁን ተከትሎም፣ ባለፈው ረቡዕ በኩባንያው የአክስዮን ድርሻ ዋጋ ላይ የ4 በመቶ ቅናሽ መመዝገቡንም ዘገባው አብራርቷል፡፡
አይፎን ባለፉት አመታት በስማርት ፎን ገበያ መሪነቱን ይዞ የዘለቀ የአለማችን ታዋቂ ስማርት ፎን መሆኑን ያስታወሰው ዘገባው፣ አፕል ኩባንያ ከአጠቃላይ ገቢው ሁለት ሶስተኛ የሚሆነውን የሚያገኘው ከአይፎን ሽያጩ እንደሆነም ጠቁሟል፡፡

       የምንመገባቸው ምግቦችና መጠጦች ለከፍተኛ ራስ ምታት (ማይግሪን) መንስኤ ሊሆኑ ይችላሉ። በራስ ምታት የመያዝ አጋጣሚዎች በተለያዩ ምክንያቶች (በአየር ፀባይ መለዋወጥ፣ በጠንካራ ሽታዎች፣ በከፍተኛ ብርሃን፣ በሌሎች በሽታዎች ሳቢያ፣ በካፌይን ሱሰኝነት ወዘተ) የሚያጋጥመን ቢሆንም የምንመገባቸው ምግቦችና ወደ አንጀታችን የምንልካቸው የተለያዩ መጠጦችም ለከፍተኛው ራስ ምታት (ማይግሪን) ሊያጋልጡን እንደሚችሉ የአሜሪካ ተመራማሪዎች አስታውቀዋል፡፡ ኔቸር በተሰኘው የምርምር ጆርናል ላይ ተመራማሪዎቹ ይፋ እንዳደረጉት፤የምንመገባቸው ምግቦች ከጭንቅላት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው ታይራሚንስና ናይትሪ የተባሉ ኬሚካሎችን በስፋት ይይዛሉ፡፡ እነዚህ ኬሚካሎች ደግሞ የደም ዝውውር ሂደትን በማወክ፣ የራስ ምታትንና የዓይን አካባቢ ህመምን ያስከትላሉ፡፡
ሣይንቲስቶቹ በምርምር አረጋግጠናል ካሏቸውና ከፍተኛ የራስ ምታትን ያስከትላሉ በማለት ከዘርዘሯቸው የምግብና የመጠጥ ዓይነቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡
ቀይ የወይን ጠጅ
ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም የሚያጋልጡ ኮንጀነርስና ታይራሚን የተባሉ ንጥረነገሮችን በብዛት ይይዛል፡፡ ስለዚህም ከሌሎች አልኮል መጠጦች ሁሉ የራስ ምታት ህመምን በማነሳሳት በእጅጉ ይታወቃል። የችግሩ ከፍተኛነት በወሰድነው የቀይ ወይን መጠንና በሽታን በመከላከል አቅማችን የሚወሰን ቢሆንም ቀይ ወይን መጠጣት ለከባድ የራስ ምታት ህመም የሚያጋልጥ መሆኑን አረጋግጠናል ሲሉ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ቀይ ወይን ለራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ የሚያደርገን በአልኮልነቱ ሳይሆን በነጭ ወይን ውስጥ የሌለና በቀይ ወይን ውስጥ ብቻ በሚገኘው ተፈጥሮአዊ ውህድ መነሻነት እንደሆነም እነዚሁ ተመራማሪዎች ጠቁመዋል፡፡  
ቸኮሌት
ቸኮሌትን አብዝቶ መመገብ ለከፍተኛ ራስ ምታት ያጋልጣል፡፡ በተለይም ጠቆር ያለውና ቡናማ ቀለም ያለው የቸኮሌት አይነት ህመሙን በማባባስ ለከፍተኛ ስቃይ የሚዳርግ መሆኑን የጠቆሙት ተመራማሪዎቹ፤ ከካካዋ ቅቤ የሚሰራው ነጭ ቸኮሌት ከራስ ምታት ህመም ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር አለመኖሩን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ገልፀዋል፡፡
አይስክሬምና ሌሎች ቀዝቃዛ ምግቦች
እንደ አይስክሬም ያሉ በጣም የቀዘቀዙ ምግቦችን በምንመገብበት ወቅት በአፋችን ውስጥ የሚፈጠረው ከፍተኛ ቅዝቃዜ ለከባድ ራስ ምታት ያጋልጠናል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በአፋችን ውስጥ የተፈጠረው ቅዝቃዜ እስከ ጭንቅላታችን ድረስ ስለሚሰማን እንደሆነም አሜሪካዊያን ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል፡፡
ካፌን
ቡና እና ኮካ መሰል መጠጦች ውስጥ የሚገኘው ካፌን ሱስ የማስያዝ ባህርይ አለው። ይህንን መጠጣት በምናቆምበት ወይንም ሳንጠጣ በምንቆይበት ጊዜ ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል፡፡ ካፌይን መውሰድ ያቆሙ ሱሰኞች ለድብርት ስሜት፣ ለመጫጫንና ለከባድ ራስ ምታት ህመም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ካፌይኑ የአንጐላችንን ኤሌክትሪካል ሲስተም በማዛባት ሰውነታችን ተጨማሪ የቤታ ንዝረቶችንና አነስተኛ የቴታ ንዝረቶችን እንዲለቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ደግሞ በአንጐላችን ውስጥ የሚካሄደውን ኤሌክትሪካል እንቅስቃሴ በማዛባት ለከፍተኛ የራስ ምታት ህመም እንድንጋለጥ ያደርገናል፡፡
ካፌይን ነክ የሆነ መጠጦችን በጠዋት የመጠጣት ልምድ ያላቸው ሰዎች ካፌይኑ በሕብለ ሰረሰራቸው ውስጥ የሚገኙትን የደምቅዳ ቧንቧዎች በማጥበብ ደም በበቂ መጠን ወደ አንጐል እንዳይገባ ያደርጋል። በዚህ ሣቢያም ከባድ የራስ ምታት ህመም ያጋጥመናል ሲል ተመራማሪዎቹን ዋቢ አድርጐ ኔቸር ዘግቧል፡፡ 

Saturday, 30 January 2016 12:51

ካፌይንና እርግዝና

 ካፌይን ነክ የሆኑ ምግቦችና መጠጦች በእርግዝና ወቅት መውሰድ በፅንሱም ሆነ በእናቲቱ ጤና ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል በጥናት መረጋገጡን Neurology የተሰኘ የህክምና ጆርናል ሰሞኑን ዘግቧል፡፡
ነፍሰጡር ሴቶች፤ የማነቃቃትና እንቅልፍን የማባረር ባህርይ እንዳለው የሚታወቀውን ካፌይን በሚወስዱበት ወቅት የልብ ምታቸውና የደም ግፊታቸው በከፍተኛ መጠን እንደሚጨምር   የጠቆመው ዘገባው፤በእናቲቱ ማህፀን ውስጥ የሚገኘው ፅንስም በፕላሴንታ አማካኝነት በሚደርሰው ካፌይን ሳቢያ የልብ ምቱ ሊዛባና ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል አመልክቷል።  በተጨማሪም ካፌይኑን አብዝቶ መውሰዱ በተደጋጋሚ ስለሚያሸና ነፍሰጡሯ ሴት ድርቀት እንዲያጋጥማትና ፅንሱ በቂ ፈሳሽ ለማግኘት እንዳይችል እንደሚያደርገው ዘገባው ጠቁሟል፡፡
አብዛኛዎቻችን ካፌይን የሚገኘው በቡናና በለስላሣ መጠጦች ብቻ ውስጥ ነው ብለን እናምናለን ያለው ዘገባው፤ ካፌይን በበርካታ የታሸጉ ምግቦች ውስጥም እንደሚገኝና እነዚህን ምግቦች አዘውትሮ መመገብ ለጤና እክል እንደሚያጋልጥ አመልክቷል፡፡ 

   በሸካ አካባቢ የሚኖሩ ብሔር ብሄረሰቦችን ባህላዊ ትውፊትና የአካባቢውን ተፈጥሮአዊ ውበት የሚያሳየውና የ22 ደቂቃ ርዝመት ያለው “ድብቁ የሸካ ደን ውበት” ዘጋቢ ፊልም ትላንት ምሽት በልዑል ሲኒማ ተመረቀ፡፡ የሸካ ዞን አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ፣ መልካ ኢትዮጵያና የአውሮፓ ህብረት ሲቪል ሶሳይቲ ፈንድ በመተባበር የሰሩትን ይህን ፊልም፤ አርቲስት ዮሃንስ ፈለቀ ያዘጋጀው ሲሆን በብሉ ሚዲያ ፊልም ፕሮዳክሽን ተሰርቶ ቀርቧል፡፡ በምርቃቱ ላይ የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች፣ የሸካ ዞን ኃላፊዎች፣ የመልካ ኢትዮጵያ አመራሮች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶችና ጋዜጠኞች ተገኝተዋል፡፡

   22 አይነት የአገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው በሚናገሩት አቶ ካሱ ሰቦቃ የተዘጋጀውና “ሳንታ ማሪያ” የሚል መጠሪያ የተሰጠው የመዝሙር ቪሲዲ ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አዳራሽ ይመረቃል፡፡ አቶ ካሱ በኦሮምኛ፣ በአማርኛ፣ በግዕዝ፣ በስፓኒሽ በፈረንሳይኛ፣ በጀርመንኛ፣ በግሪክ፣ በቻይንኛ፣ በአረብኛና በጣልያንኛ 11 መዝሙሮችን ያዘጋጁ ሲሆን 12ኛው መዝሙር 11ዱን በምልክት ቋንቋ የሚያሳይ እንደሆነ ታውቋል፡፡ “የቅዱስ ዳዊት በገና ከቅድስት ኢትዮጵያ በዓለም ቋንቋ ሲገለፅ” በሚል መርህ የተዘጋጀው የዚህ ቪሲዲ ዋና አላማው የቅዱስ ዳዊትን በገና ለዓለም ለማስተዋወቅና የኢትዮጵያን የቱሪዝም መስህብነት ለማሳየት እንደሆነ ዘማሪው ተናግረዋል፡፡ በቪሲዲው ምርቃት ላይ ሚኒስትሮች፣ የኤምባሲ ተወካዮች፣ የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች፣ አትሌቶችና አርቲስቶች እንደሚገኙም ተነግሯል፡፡ አቶ ካሱ አስተርጓሚ ከመሆናቸውም ባሻገር ታዋቂ ሼፍና አስጎብኚም እንደሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የታዋቂው የሬጌ አቀንቃኝ የቦብ ማርሊ 71ኛ ዓመት የልደት በአል የዛሬ ሳምንት አርብና ቅዳሜ በተለያዩ የሙዚቃ ድግሶች በሻሸመኔ ከተማ እንደሚከበር አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡
በሙዚቃ ድግሱ ላይ ሲድኒ ሰልማንና ራስ ጃኒን ጨምሮ ከዛምቢያ፣ ሴራሊዮን፣ አሜሪካና ሌሎች አገራት የተውጣጡ 14 አርቲስቶችና ዲጄዎች እንደሚሳተፉበት ታውቋል፡፡
የቦብ ማርሊን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የሚቀርበው የሙዚቃ ድግስ ዋና ዓላማው፤ በስሙ የተሰየመውን ትምህርት ቤት ጨምሮ ሌሎች ፕሮጀክቶችን ለማገዝ የሚያስችል ገቢ ለማሳሰብ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
በአሉን አለምአቀፍ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረግን ነው ያሉት አዘጋጆቹ፤ የሬጌ አድናቂው ማህበረሰብ በድግሱ ላይ እንዲታደም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡ 

Saturday, 30 January 2016 12:06

የኪነት ጥግ

(ስለ ማስታወቂያ)
የማስታወቂያ ኤጀንሲ 85% ማደናገርና 15% ኮሚሽን ነው፡፡
ፍሬድ አለን
ሸማቾችን እንዲገዙ ወይም እንዳይገዙ የሚወስነው የማስታወቂያህ ይዘት እንጂ ቅርጽ አይደለም፡፡
ዴቪድ ኦጊልቪ
ፊል ናይት እባላለሁ፡፡ በማስታወቂያ አላምንም፡፡
ፊል ናይት
መጽሔት ሰዎች ማስታወቂያ እንዲያነቡ የመገፋፊያ መሳሪያ ነው፡፡
ጄምስ ኮሊንስ
ማስታወቂያ የንግድ የደም ሥር ነው፡፡
ካልቪን ኩሊጅ
በኪነጥበብ ውስጥ ኃያሲው ብቸኛው ነፃ የመረጃ ምንጭ ነው፡፡ የቀረው ማስታወቂያ ነው፡፡
ፖሊን ካኤል
ማስታወቂያ ሃጢያት የሚሆነው መጥፎ ነገሮችን ሲያስተዋውቅ ብቻ ነው፡፡
ዴቪድ ኦጊልቪ
ማስታወቂያ ህጋዊ የሆነ  ውሸት ነው፡፡
ኤች ጂ ዌልስ
ማንም ያስተላለፍከውን ማስታወቂያ የሚቆጥር የለም፤ ሰዎች የሚያስታውሱት የፈጠርክባቸውን ስሜት ነው፡፡
ቢል በርንባች
ስለማስታወቂያ ግድ የሚሰጣቸው በማስታወቂያ ውስጥ የሚሰሩ ሰዎች ብቻ ናቸው፡፡
ጆርጅ ፓርከር
ጥራትን ስጣቸው፡፡ ያ ነው ምርጡ የማስታወቂያ ዓይነት፡፡
ሚልተን ሄርሼይ
ማስታወቂያ የቢዝነስ ልሳን ነው፡፡
ጄምስ አር .አዳምስ
ራስህን የማታስተዋውቅ ከሆነ በሚወዱህ ጠላቶችህ ትተዋወቃለህ፡፡
አልበርት ሁባርድ
በማስታወቂያ የተዋጣለት ለመሆን ማስታወቂያ እንዴት እንደሚሰራ ማወቅ አያስፈልግም፡፡
ዊንስተን ፍሌቸር

  - በ48 ሰዓታት ለ50 ሚሊዮን፣ በ87 ቀናት ለ1 ቢሊዮን ጊዜያት ታይቷል

      እንግሊዛዊቷ አቀንቃኝ አዴል ባለፈው ጥቅምት ወር መጨረሻ የለቀቀችው “ሄሎ” የተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮ በዩ ቲዩብ ድረገጽ በአጭር ጊዜ ውስጥ በበርካታ ሰዎች በመታየት ረገድ “ጋንጋም ስታይል” በሚለው የደቡብ ኮርያዊው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ ፒኤስዋይ ተወዳጅ ዜማ ተይዞ የቆየውን ክብረወሰን መስበሩ ተዘገበ፡፡
ዩ ቲዩብ ላይ በተለቀቀ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለ50 ሚሊዮን ጊዜያት ያህል የታየው የአዴል “ሄሎ”፣ በ87ኛው ቀን  ላይም አንድ ቢሊዮን ተመልካቾች እንዳዩት የዘገበው አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ፤በ2012 የተለቀቀው “ጋንጋም ስታይል” በበኩሉ ይህን ያህል ተመልካች ሊያገኝ የቻለው በ160 ቀናት ጊዜ ውስጥ እንደነበር አስታውሷል፡፡
የአስር ጊዜያት የግራሚ ተሸላሚዋ አዴል፤ነጠላ ዜማውን ያካተተችበትና ባለፈው ወር ለገበያ ያበቃችው “25” የተሰኘ የሙዚቃ አልበሟም፣ በአሜሪካና በእንግሊዝ የሙዚቃ አልበም ሽያጭ ታሪክ በፍጥነት በብዛት በመሸጥ ክብረወሰን መያዙን ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአለማችን የሙዚቃ ቪዲዮ ታሪክ በዩ ቲዩብ ድረገጽ ተለቅቀው ለአንድ ቢሊዮን ጊዜያት ያህል መታየት የቻሉት የሙዚቃ ቪዲዮዎች 18 ብቻ እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡

Saturday, 30 January 2016 11:59

የጸሃፍት ጥግ

(ስለ ክዋክብት)

- ምሽት ደስ ይለኛል፤ ጨለማ ከሌለ ክዋክብትን
ፈፅሞ ማየት አንችልም፡፡
ስቲፌኒ ሜዬር
- ድቅድቅ ያለ ጨለማ ሲሆን ክዋክብትን ማየት
ትችላላችሁ፡፡
ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን
- ክዋክብትን በተመለከተ የምናየው ሁሉ የድሮ
ፎቶግራፋቸውን ነው፡፡
አላን ሙር
- እጣፈንታችን ያለው በክዋክብቱ ውስጥ
አይደለም፤ በራሳችን ውስጥ እንጂ፡፡
ሊሳ ማንትቼቭ
- እያንዳንዱ ኮከብ በውስጥህ ያለውን እውነት
የሚያንፀባርቅ መስተዋት ነው፡፡
አበርጅሃኒ
- ክዋክብት የዩኒቨርስ ጠባሳዎች ናቸው፡፡
ሪኪ ማዬ
- ማታ ማታ እዚያ ላይ የሚታዩት ክዋክብት
ከምታስቡት የበለጠ ቅርብ ናቸው፡፡
ዶውግ ዲሎን
- ጨረቃን አትጠይቁ! ክዋክብት አሉልን!
ኦሊቭ ሂጊንስ ፕሮውቲ
- ጨረቃ ሙሉ በማትሆን ጊዜ ክዋክብት ይበልጥ
ደምቀው ያበራሉ፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
- ጉድጓድን አልሞ ከመምታት ይልቅ ጨረቃን
አልሞ መሳት ይሻላል፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
- ክዋክብት የዘላለም የጎዳና መብራቶች ናቸው፡፡
ሃሪት ቱብማን
- ለክዋክብት አልም፤ ሰማይን ልትነካ ትችላለህ፡፡
ኦኪው ማንዲኖ
- ሁላችንም ክዋክብት ልንሆን አንችልም፤
ሁላችንም ግን ብልጭ ማለት እንችላለን፡፡
ሔነሪ ዋድስዎርዝ ሎንግ ፌሎው