Administrator

Administrator

    የገጣሚ ኤፍሬም ስዩም “ኑ ግድግዳ እናፍርስ” የተሰኘ አዲስ የግጥም መድብል የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ በዋቢሸበሌ ሆቴል ይመረቃል፡፡ በእለቱ ገጣሚውን ጨምሮ ሌሎች እውቅ ገጣሚያን ግጥሞቻቸውን በሙዚቃ ታጅበው የሚያቀርቡ ሲሆን ግጥሞቹን ሰዓሊያን በቀጥታ ወደ ስዕል እየቀየሩ ታዳሚውን እንደሚያዝናኑ ተገልጿል፡፡
መፅሐፉ፤ በማህበራዊ፣ በውበት፣ በፍቅር በፍልስፍና ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 61 ግጥሞችን ያካተተ ሲሆን ግጥሞቹ በእውቁ ሀያሲ አብደላ ዕዝራ ትንታኔ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ በ150 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ በ45 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡ ገጣሚው ከዚህ ቀደም “ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር”፣ “የብርሀን ክንፎች” “ሶሊያና” (በሲዲ)፣ “ተዋነይ”፣ “የይሁዳ ድልድይ” እና ከሌሎች ገጣሚያን ጋር “ግጥም በመሰንቆ” የተሰኙ የግጥም ስራዎችን ለአንባቢ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

ትውልደ ኢትዮጵያዊው የፖፕ ሙዚቃ አቀንቃኝ አቤል ተስፋዬ /ዘ ዊኪንድ/፤ “ኧርንድ ኢት” በተባለው የፊልም ማጀቢያ ሙዚቃው፣ለዘንድሮው የኦስካር ሽልማት መታጨቱ ተዘገበ፡፡

“ፊፍቲ ሼድስ ኦፍ ግሬይ” ለተባለው ፊልም በማጀቢያ ሙዚቃነት የተሰራው “ኧርንድ ኢት”፣ በኦስካር ሽልማት የምርጥ ወጥ ሙዚቃ ዘርፍ መታጨቱን ዘ ካናዲያን ፕሬስ ዘግቧል፡፡

በዘርፉ ለሽልማት ከታጩት አምስት ሙዚቃዎች መካከል በታዋቂዋ ድምጻዊት ሌዲ ጋጋ የተቀነቀነውና “ዘ ሃንቲንግ ግራውንድ” ለተባለው ፊልም በማጀቢያነት የተሰራው “ቲል ኢት ሃፕንስ ቱ ዩ” ይገኝበታል፡፡  
የዘንድሮው የኦስካር ሽልማት ስነስርዓት በመጪው የካቲት መጨረሻ እንደሚካሄድና የመድረክ መሪውም ታዋቂው የሆሊውድ ተዋናይ ክሪስ ሮክ እንደሚሆን የተነገረ ሲሆን በኤቢሲ ቴሌቪዥን በቀጥታ ይተላለፋል ተብሏል፡፡

Saturday, 23 January 2016 13:43

የህፃናት ጥግ

(ስለ ፍቅር ተጠይቀው የተናገሩት)
-    “እሱን ማሰብ ራሴን ያሳምመኛል፡፡ እኔ ገና ህፃን ነኝ፡፡ የዚህን ዓይነት ችግር አልፈልግም፡፡”
ኮኒ (የ7 ዓመት ህፃን)
-    “የመዋዕለ ህፃናት ትምህርቴን ስጨርስ ለራሴ ሚስት እፈልጋለሁ፡፡”
ቶም (የ5 ዓመት ህፃን)
-    “በቀስት ወይም በሆነ ነገር መወጋት ያለብህ ይመስለኛል፤ የቀረው እንኳን ያን ያህል ስቃይ ያለው አይመስልም፡፡”
ማኑኤል (የ8 ዓመት ህፃን)
-    “በፍቅር መያዝ ስፔሊንግ እንደመማር ከሆነ ልገባበት አልፈልግም፡፡ በጣም ረዥመ ጊዜ ይወስዳል፡፡”
ግሌን (የ7 ዓመት ህፃን)
-    “ወደ ፍቅር ለመግባት አልጣደፍም፡፡ 4ኛ ክፍል በጣም ከብዶኛል፡፡”
ሬጂና (የ10 ዓመት ህፃን)
-    “አንድ ወንድና አንድ ሴት በሽታና ህመምን በአንድ ላይ ለማሳለፍ ቃል የሚገቡበት ነው፡፡”
ማርሎን (የ10 ዓመት ህፃን)
-    “ፍቅር ጅል ነው … ቢሆንም ግን አልፎ አልፎ እሞክረው ይሆናል፡፡”
ፍሎይድ (የ9 ዓመት ህፃን)
-    “አለመግባባት ይመረጣል … ምክንያቱም እኔ የሽንት ጨርቅ (ዲያፐር) መቀየር አልፈልግም፡፡ በእርግጥ ካገባሁ እንድ መላ እዘይዳለሁ፡፡ እናቴ ጋ እደውልና መጥተሸ ቡና ጠጪ ብዬ የሽንት ጨርቅ አስለውጣታለሁ፡፡”
ክሪስቲን (የ101 ዓመት ህፃን)
-    “አብዛኞቹ ወንዶች አዕምሮ-ቢስ ናቸው፤ ስለዚህ አዕምሮ ያላቸውን ለማግኘት ከአንድ ጊዜ በላይ መሞከር ይኖርባችሁ ይሆናል፡፡”
ኤንኪ (የ10 ዓመት ህፃን)
-    “አንድ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሳም ይወድቃል፤ ቢያንስ ለአንድ ሰዓትም ከወደቀበት አይነሳም፡፡”
ዌንዲ (የ8 ዓመት ህፃን)
-    “እናትህ ከሆነች በማንኛውም ጊዜ ልትስማት ትችላለህ፡፡ አዲስ ሰው ከሆነ ግን ፈቃድ መጠየቅ ይኖርብሃል፡፡
ሮጀር (የ6 ዓመት ህፃን)
-    “መስቲካዋን ለመስረቅ እየሞከረ ነው፡፡”
(የ6 ዓመት ህፃን (ጥንዶች ሲሳሳሙ አይቶ የተናገረው)

Saturday, 23 January 2016 13:42

የፀሐፍት ጥግ

ልጄ ሂሳብና ፍልስፍና የመማር ነፃነት እንዲኖረው እኔ ፖለቲካና ጦርነትን ማጥናት አለብኝ፡፡
ጆን አዳምስ
-    የህብረተሰብ ደስተኛነት የመንግስት ማክተሚያ ነው፡፡
ጆን አዳምስ
-    ፍርሃት የአብዛኞቹ መንግስታት መሰረት ነው፡፡
ጆን አዳምስ
-    አንድን ነገር ካልወደድከው ለውጠው፡፡ ልትለውጠው ካልቻልክ አመለካከትህን ለውጥ፡፡
ማያ አንጄሎ

Saturday, 23 January 2016 13:41

የዘላለም ጥግ

(ስለ ትምህረት)
-    ትምህርት ሥልጣኔን የማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡
ዊል ዱራንት
-      ልቡናን ሳያስተምሩ አዕምሮን ማስተማር ፈፅሞ ትምህርት አይባልም፡፡
አሪስቶትል
-    ትምህርት ዓለምን ለመወለጥ ልትጠቀሙበት የምትችሉት እጅግ ሃያል መሳሪያ ነው፡፤
ኔልሰን ማንዴላ
-    አስተማሪዎች በሩን ይከፍታሉ፤
የቻይናውያን አባባል
-     የመማር ፍቅር አዳብሩ፡፡ ያኔ ፈፅሞ ማደግ አታቆሙም፡፡
አንቶኒ ጄ.ዲ'አንጄሎ
-    አስተማሪዎች ፈተና መስጠት እስከቀጠሉ ድረስ ሁልጊዜም በትምሀርት ቤቶች ውስጥ ፀሎት መኖሩ አይቀርም፡፡
ምንጩ ያልታወቀ
-    በመማር ታስተምራለችሁ፤ በማስተማር ትረዳላችሁ፡፡
የላቲኖች አባባል
-    የራሳችን መንተድ ሳናበራ የሌሎችን መንገድ ለማብራት ችቦ ልንይዝ አንችልም፡፡
ቤን ስዊትላንድ
-    ምንም ነገር ለማስተማር ብትፈልግ ቅልብጭ አድርገው፡፡
ሆራስ
-    የትምህርት ዘጠኝ አስረኛው ማበረታታት ነው፡፡
አናቶሌ ፍራንስ
-    የዘመናዊ የትምህርት ባለሙያ ተግባር ደኖችን ማጥፋት ሳይሆን በረሃን በመስኖ ማልማት ነው፡፡
ሲ.ኤስ.ሌዊስ
-    እንዴት እንደሚታሰብ የሚያውቁ አስተማሪዎችን አይፈልጉም፡፡
ማሃትማ ጋንዲ
-    የሚያደምጠው ካገኘ ሁሉም ሰው አስተማሪ ነው፡፡
ዶሪስ ሮበርትስ
-    ምርጥ አስተማሪየችሁ ለመጨረሻ ጊዜ የሰራችሁ ስህተት ነው፡፡
ራልፍ ናዴር



Saturday, 23 January 2016 13:39

የኪነት ጥግ

(ስለ ዳንስ)
-    በዳንስ ወለል ላይ አሸርን የምረታው ይመስለኛል፡፡
ክሪስ ብራውን
-    ከስድስት ወንድሞቼ ጋርነው ያደግሁት፡፡ ዳንስን የተማርኩት እንደዚያ ነው - የመታጠቢያ ቤት ወረፋ እየጠበቅሁ፡፡
ቦብ ሆፕ
-    ከፍሰቱ ጋር እፈሳለሁ፡፡ ለእኔ ምንም ዓይነት ሙዚቃ ብታጫውቱልኝ እደንሳለሁ፡፡
ጋኤል ጋርሽያ ቤርናል
-    ዕልድ የዳንስ ወለሉ ላይ ከወጡት ጋር ትደንሳለች፡፡
ኤች. ጃክሰን በራውን ጄአር
-    ዛሬ ህፃናቱ በፊታቸው መደነስ የሚች የመስላቸዋል፡፡
ጓንገር ሮጀርስ
-    ጀስቲን ቢበር የፀጉር ቁርጤን ሰረቀኝ፡፡ አክል ሮዝ ደግሞ ዳንሴን!
ዴቪ ጆንስ
-    ዴኒስ ሎው በእንቁላል ቅርፎቶች ላይ መደነስ ይችላል፡፡
ቢል ሸንክሊ
-    የምትኖረው መደነስ እስከቻልክ ድረስ ነው፡፡
ሩዶልፍ ኑሩዬቭ
-    በደብን መደነስ ባትችል ማንም ደንታ የሚሰጠው የለም፡፡ ዝም ብለህ ተነስተህ ደንስ፡፡
ዴቭ ባሪ
-    ሚስቶች፤ በበቂ ሁኔታ ደንሰናል ብለው የማያስቡ ሰዎ ናቸው፡፡
ግሮሾ ማርክስ
-    መዝፈን፣ መደነስ ወይም መተወን አልችልም፤ የቶክ ሾው አዘጋ ከመሆን ውጭ ሌላ ምን ልሆን እችል ነበር፡፡
ዴቪድ ሌተርማን
-    ሰዎች ውበትን ለማየት ይመጣሉ፤ እኔም የሚሹትን ለመስጠት እደንሳለሁ፡፡
ጁዲት ጃሚሶን
-    ዳንስ ስህተት አልባ እቅጩነት ሊኖረው ይገባል፡፡
አሪሌ ዶምባስሌ

   ወ/ሮ ዘሃራ ኑረዲን በህይወት የተለያ ምእራች በአስቸጋሮ ሁኔታ ያለፉ ሴት ናቸው፡፡ ወ/ሮዋን የላዳ ሹፌር በመሆን ሁለት ልጆቻቸውን በብቸኝነት የሚያስተዳድሩ እናት ናቸው፡፡ ያለፉበትን የህይወት ውጣ ውረድና ስኬቴ ያሉትን የታክሲ ማሽከርከር ህይወት ለአዲስ አድማሷ ጋዜጠኛ ማህሉት ኪዳነወልድ በአጭሩ አውግተዋል፡፡
እስኪ ስለ አስተዳደግዎ ያጫውቱኝ?
የተወለድኩት አዲስ አበባ አባ ኮራን ሰፈር፣ ልዩ ስሙ ሐግቤስ አካባቢ ነው፡፡ ለቤተሰቦቼ አራተኛ ልጅ ነኝ፡፡ አሁን ሁለቱ በህይወት ስለሌሉ ሁለተኛ ልጅ ሆኛለሁ፡፡ በአጠቃላይ ግን 12 ነበርን፡፡ እናትና አባቴ ከዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል የሚመደቡ ነበሩ፤በእርግጥ ወደ መጨረሻ አካባቢ  በእናቴ ጥረት ነገሮች ተቀይረዋል፡፡  
የትምህርት ሁኔታስ?
ከ8ኛ ክፍል ነው ያቋረጥኩት፡፡ እንደነገርኩሽ ወላጆቼ ኑሮአቸው ጥሩ አልነበረም፤እናም እነሱን ለመርዳት በማሰብ ትምህርቴን አቋርጬ አረብ አገር ሄድኩኝ፡፡ ለ3 ዓመት ስሰራ ከቆየሁ በኋላ እዛው የነበረ ኢትዮጵያዊ አጨኝና ትዳር ተጀመረ፡፡ ሆኖም ትዳሬ ስኬታማ አልነበረም፤ እኔ የማደላው ለቤተሰቦቼ ነው፡፡ ሃሳቤ ሁሉ የእነሱን ህይወት መቀየር ነበር፡፡ እሱ ደግሞ ለቤተሰቤ ትኩረት መስጠቴን አልወደደውም፡፡ ይባስ ብሎም እንደ እህት ከምወዳት ጓደኛዬ ጋር ግንኙነት ጀመረ፡፡ አሁን እንደውም ተጋብተዋል፡፡ ያንን መቋቋም አልቻልኩም፡፡ የአንድ ዓመት ልጄን ይዤ ወደ አገሬ፣ወደ እናቴ ቤት ተመለስኩ፡፡
ከአረብ አገር ስትመጪ የቋጠርሽው ጥሪት ነበረሽ?
በጭራሽ ቤሳቤስቲ አልነበረኝም፡፡ እዚያ የኖርኩት ለቤተሰቤ ነው፡፡ በዚያ ላይ ልጅ ነበር፡፡ ንብረት ከተባለ የራሴ የጣትና የአንገት ወርቅ ብቻ ነው የነበረኝ፡፡
ታዲያ አዲስ አበባ እንዴት ተቀበለችሽ?
እሱ ነበር ከባዱ፡፡ እናቴ ጠንካራ ሴት ናት፤ጥንካሬን አውርሳኛለች፡፡ ያልሰራችው ነገር የለም፡፡ እንጀራ ጋግራ አከፋፍላለች፡፡ ሹራብ ሰርታ ሸጣለች፡፡ ከመጣሁ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ መረጋጋት አልቻልኩም፤እኔም ከነልጄ እሷ ቤት ነው የገባነው፡፡ ትንሽ ቆይቼ ግን የቤት ደላልነት ሥራ ጀመርኩ፡፡
የቤት ደላልነት ለሴት አልተለመደም፡፡ ወደዚያ ለመግባት ያነሳሳሽ የተለየ ምክንያት ነበር? ሥራውስ አልከበደሽም?
ውይ ---- በጣም ከምነግርሽ በላይ አድካሚ ነው፡፡ አንዳንዱ ሰው ሊከራይ ሳይሆን ሊገዛ ነው የሚመስልሽ፡፡ እኔን ወደ ስራው እንድገባ ያበረታቱኝ አብረውኝ የተማሩ ሁለት ልጆች ሙያው ላይ ስለነበሩ ነው፡፡ እነሱ ያግዙኝ ነበር፡፡ የሰዎች ስሜትና ፍላጎት የተለያየ ነው፡፡ ቤት እየዞርሽ አሳይተሽ የማይፈልግም ይኖራል፡፡ አንዳንዴ አከራዮቹ እራሳቸው መንገድ ላይ ያገኙሽና በዚህን ያህል ብር የሚከራይ ቤት አለ ይሉሽና፣ ተከራዩ ደግሞ ስፋቱን ስንት ነው፣ ግድግዳው በሩ --- ይልሻል፡፡
በስራው የገጠመሽ ገጠመኝ ከአከራይ ወይ ከተከራይ
ብዙ ነገር ይገጥምሻል፤ ቀብድ ሰጥቶ የሚቀር አለ፡፡ በመሃል ካልገባሁ ብሎ የሚያስጨንቅ አለ፡፡ ጥሩው ነገር ግን ሴት ስለሆንኩ ነው መሰለኝ ሰዎች እኔን በጣም ያምኑኝ ነበር፤ የምላቸውን ይሰሙኛል፡፡  
 የድለላውን ሥራ እንዴት ተውሽው?
ድካሙን አልቻልኩም፡፡ ኩላሊቴን አመመኝ፡፡ ግን አሁን አሁን ሳስበው ድካሙን ችዬ ብቆይ ኖሮ ያዋጣኝ ነበር እላለሁ (ሳ---ቅ--)
ከዚያስ ምን መስራት ጀመርሽ ?
ለትንሽ ጊዜ የምኖርበት የቀበሌ ቤት ጥግ ላይ ውሃና ለስላሳ መሸጥ ጀምሬ ነበር፡፡ እሱም አልተሳካም፡፡ በመሃል በእናቴ እርዳታ 2ኛ መንጃ ፍቃድ አወጣሁ፡፡ ሆኖም እጅ የምፈታበት መኪና አላገኘሁም፡፡ በመሃል ትዳርም ሞክሬ ነበር፤ከሁለት ዓመት በላይ አልዘለቀም፡፡ ግን ከሁለቱም ትዳሬ ሁለት የሚያማምሩ ሴት ልጆችን አፍርቼበታለሁ፡፡  
የልጆቹ አባቶች ይረዱሻል?
በጭራሽ አንድ ቀንም አይተዋቸው አያውቁም፡፡ አሁን ሁለቱም ሌላ ሚስት አግብተዋል፡፡ ነፍሷን ይማረውና ልጆቼን በማሳደግ በኩል ብኩን እናቴ ሁሉ ነገሬ ነበረች፡፡
ባወጣሽው 2ኛ መንጃ ፍቃድ ሰራሽበት ?
እናቴ አንድ ቀን የሆነ ዱቄት ፋብሪካ ወሰደችኝና መንጃ ፍቃዴን ኮፒ አድርጌ ለባለቤቱ ሰጠሁት፡፡ መጀመሪያ ሴት በመሆኔ ደስ ብሎት፣ አንቺ የልጆቼ ሹፌር ትሆኛሽ፤ ጎበዝ ልጅ ነሽ፤በርቺ አለኝ፡፡ በኋላ ቢሮ ቀጥሮኝ ፈተና ሲፈትነኝ ግን እጄን ስላልፈታሁ ትንሽ አቃተኝ፡፡ እሱም ለልጆቹ ስላጨኝ ፈራ፡፡ በቃ ትንሽ ጊዜ እጅ እስክትፈቺ ብሎ የዱቄት ፋብሪካው የስምሪት ክፍል ኃላፊ አደረገኝ፡፡ እኔ ግን ህልሜ መንዳት ነበር፡፡ የሚገርምሽ በልጅነቴ እቤት ውስጥ ወደፊት የአንበሳ አውቶቡስ ሹፌር ነው የምሆነው ስል እናቴ ትናደድ ነበር፡፡ አንቺ ከልጆቼ ፈጣን ነሽ፡፡ ትልቅ ተስፋ ያለኝ ባንቺ ነው፤እንደዚህ አትበይ ትለኝ ነበር፡፡ በስምሪት ሰራተኝነቱ ብዙም አልገፋሁም፤ ደሞዜም ከ500 ብር የማይበልጥ ነበር፡፡
በዚህ መሃል 3ኛ መንጃ ፍቃድ አወጣሁ፡፡ ግን ስራ ማግኘት ቀላል አልነበረም፡፡ ያልሞከርኩበትና ማመልከቻ ያላስገባሁበት መስሪያ ቤት የለም፡፡ ግማሹ ሴት መሆኔን ሲያይ ቦታ የለም ይለኛል፡፡ እንደ በፊቱ እንዳልቸገርም የሰፈራችንን የታክሲ ሹፌሮች እየለመንኩ እጄን በደንብ ፈታሁ፡፡ በዚህ መሀል እናትና አባቴ ተከታትለው ሞቱ፡፡ ልጆቼን ይዤ የምገባበት አጣሁ፡፡ የቀበሌውም ቤት ብዙ ታሪክ አለው፤ ብቻ ተወሰደ፡፡ ግን ሁልጊዜ የምፅናናበት እናቴ ከእኔ ስምንት እጥፍ ችግሮችን ተቋቁማ ያሰበችበት መድረሷ ነበር፡፡ በኋላ ላይ እኔም የላዳ ታክሲ ሹፌር ሆንኩ፡፡
 የላዳ ሹፌርነት አልፈተነሽም ? ሴት በመሆንሽ የሰው አቀባበል እንዴት ነበር?
 አዲስ አበባ ውስጥ ያለነው ሴት ላዳ ሹፌሮች ሁለት ወይ ሦስት ብንሆን ነው፡፡ ያው ሰው በተለያ አይነት መንገድ ነው የሚቀበልሽ እንዳመጣጡ መቀበል ነው፡፡ አንዳንዴ በተለይ ከመሸ አፏጭተው አስቁመው ሴት መሆኔን ሲያዩ ደንግጠው ጥለውኝ የሚሄዱም አሉ፡፡
በታክሲ ሹፌርነት ህይወትሽ በበጎነት የምትጠቅሻቸው ገጠመኞች ይኖሩሻል ብዬ እገምታለሁ----
ሰው በጣም ያዝናል፡፡ እንደምታይው ትንሽ ወፍራም ነኝ፡፡ ቀን ቀን ከሙቀቱ ጋር ላቤ በጣም ይወርዳል፡፡ እንደውም አንዱ ተሳፋሪ፣ አባይ መገደብ የነበረበት ከአንቺ ነው ብሎ ቀልዶብኛል፡፡ እናም ከተነጋገረው ክፍያ በላይ ጨምሮ የሚሰጥሽ ብዙ መልካም ሰው አለ፡፡ ያው እንዴት ስራውን ጀመርሽ ምናምን እያለ የሚያደርቅሽም አይጠፋም፡፡  
መጥፎ የምትያቸው ገጠመኞችሽ?
ውይ እነሱ ብዙ ናቸው፡፡ ብዙ ችግሮች አይቻለሁ፤አሁን አሁን ሥራ ካልጠፋ አላመሽም፡፡ በፊት ግን ለሊትም እሰራ ነበር፡፡ ያው ገቢ ማስገባት አለብሽ፤የቤት ኪራይም አለ፡፡ የልጆች ቀለብ ምናምን --- ወጪዎች ስላሉ አመሽ ነበር፡፡ ታዲያ ሰክሮ የሚሳደብ ብዙ ነው፡፡ አንዱ ጉራንጉር ሰፈር ውስጥ ካላስገባሽኝ ሂሳብ አልከፍል ብሎ፣በፖሊስ ኃይል ያመለጥኩበት ግዜም አለ፡፡ ከኋላ ጭነሽው ድንገት ተነስቶ የሚደበድብም አለ፡፡ ሰክሮ ብር ሳይዝ ገብቶ ቦታው ሲደርስ አልከፍልም የሚልም ያጋጥማል፡፡ ብዙ አላስፈላጊና ጭንቅላት የሚነኩ ቃላቶችን የሚናገርሽም አለ፡፡ በተለይ እኔ ሙስሊም እንደመሆኔ፣ሙስሊም ደንበኞቼ ስራሽ ከእምነት ጋር አይሄድም፣በሚል ይቃወሙኛል፡፡ ከብዙ ወንዶች ጋር ስለሚያገናኝሽ አቁሚ የሚሉኝም አሉ፡፡ እንደውም አንድ ደንበኛዬ፤ባለፈው “ይሄን ስራ ከአሁን ጀምሮ አቁሚ” ሲለኝ፤ “ነገ ተቸግሬ አስር ብር ስጠኝ ብልህ፣እግር አለሽ ሰርተሽ ብይ ነው የምትለኝ፤በዚህ አልጠራጠርም፡፡ በዲናችንም የሚያስጠላው የሰው እጅ ማየት ነው” በማለት መልሼለታለሁ፡፡ ለእኔ ስራዬ ኑሮዬን አሸንፎልኛል፤እዚህ ጋ ለመድረስ ያልፈነቀልኩት ድንጋይ የለም፡፡ የታክሲ ስራ ለእኔ ትልቁ ስኬቴ ነው፡፡ ህልሜን ነው የሞላሁት፡፡ በእኔ አእምሮ ጥሩ ስራ ነው፡፡ የሰው ፊት ከማየት ገላግሎኛል፡፡ የአበራና የተሰማ ሀሳብ ለኔ ዳቦ አይሆንም፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ብዙ መልካም ሰው አለ፤ወርጄ ጎማ ስቀይር የሚያየኝ ሹፌር ሁሉ ካላገዝኩሽ ይላል፡፡ አንዳንድ ደንበኞችም፤“ትንሽ ትንሽ ብር የሚያዋጣልሽ ፈልጊና ደህና መኪና ግዢ፤እኛም እናግዝሻለን” ይሉኛል፡፡
ላዳዋ ያንቺ ናት ወይስ ተቀጥረሽ ነው የምትሰሪው?
አሁን አይደለችም፤ግን ትሆናለች፡፡ አሁን የያዝኳት ላዳ አሮጌ ብትሆንም፣ ጥረቴን ያየ አንድ መልካም ሰው ሰርቼ እንድከፍለው የሰጠኝ ነው፡፡ አሁን ግማሽ ያህሉን ከፍያለሁ፤ስጨርስ ስሙን ያዞርልኛል፡፡
ወደፊት ስንገናኝ ከአንቺ ምን ልጠብቅ?
በየቦታው የማያቆመኝን የራሴን ላዳ ታክሲ ይዤ! (…ሳ…ቅ….) ያኔ አንቺንም እሸኝሻለሁ  (ሳ…ቅ…)

     ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆነን ቅዳሜ ታህሳስ 23 ቀን 2008 ዓ.ም በአዲስ አድማስ የነፃ አስተያየት አምድ ላይ በእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ከ10.6 ሚሊዮን በላይ የሥራ እድል ተፈጥሯል የሚለውን የመንግስትን ሪፖርት፣ ከእውነት የራቀ ነው በሚል ለንባብ የበቃው የአቶ ዮሐንስ ሰ. ፅሁፍ ነው፡፡
ፀሐፊው በገለፁት መልኩ ጉዳዩ “ለመሳቂያና ለመቀለጃ ተዘጋጅቶ የተቀመጠ” ሳይሆን የጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፎችን ባህሪያትና የሚያስገኙትን ጠቀሜታ አስመልክቶ የዳበረ ግንዛቤ ካልነበረበት፣ በዘርፉ ስራዎች ላይ ከተሰማራው አስፈጻሚ አንስቶ በህብረተሰቡ መካከል ሰፊ የአመለካከት ክፍተት በነገሰበት፣ ሥራውን በታሰበው ልክ ሊፈፅም የሚችል አደረጃጀትና ብቁ የሰው ሃይል ባልተሟላበት ሁኔታ እጅግ ፈታኝ ተግዳሮቶችን በማለፍ የተገኘ ውጤት ነው፡፡
አሁን ያለንበት ወቅት የምንቀልድበት ሳይሆን እያንዳንዷ የእለት ተእለት እርምጃችን በህዝባችን የኑሮ ደረጃ ለውጥና በሀገሪቱ ቀጣይ እጣ ፈንታ ላይ የከበረ ዋጋ እንዳላት በእጅጉ ተገንዝበን፣ ከድህነት ጋር የሞት ሽረት ትግል የምናካሂድበት ነው፡፡
አቶ ዮሐንስ ሰ. ይህን ፅሁፍ ለመፃፍ ሲያስቡ፣ ከማዕከላዊ ስታቲስቲክስ ባለስልጣን አገኘሁት ባሉት ቁንፅል መረጃ ላይ ብቻ ከመንጠልጠል ይልቅ የዘርፉን መረጃዎችንም ለማየት ቢሞክሩ፤ ከተቻለም ተፈጠረ የተባለው የሥራ እድል እንዴትና ለማን ተፈጠረ ብለው ሥራውን ወደሚመራው ተቋም ብቅ ቢሉ ኖሮ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራችን  ያስገኘው ውጤት የብዙዎችን ህይወት የለወጠ፣ የብዙዎች የድካም ፍሬ እንጂ ፌዝ እንዳልሆነ በተጨባጭ ይረዱ ነበር፡፡
ይህም ካልሆነ ሩቅ ሳይሄዱ በአካባቢያቸው በሚገኘው የዘርፉ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ጐራ ብለው ሥራ ፈላጊዎችን ለመለየት፣ ለማደራጀት፣ ሥራ ለማስጀመር፣ የገበያ ትስስር ለመፍጠርና መንግስታዊ ድጋፎችን ለማመቻቸት የተሰሩ ሥራዎችንና ያስገኙትን ውጤት በተጨባጭ አስተውለው ቢሆን ኖሮ ይህን የተዛባ ጽሑፍ ለመጻፍ ባልበቁ ነበር፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ በተለይም በስራ እድል ፈጠራው ባለፉት አመታት የተከናወነው ሥራ፣ በእርግጥም የተሳካ እንደነበር የፍሬወ ተቋዳሽ የሆኑ ዜጐች በተጨባጭ የሚመሰክሩትና እኛም በሙሉ መተማመን የምንናገረው፣ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ አስፈጻሚ አካላት የአመታት ልፋትና ድካም ውጤት ነው፡፡ ከዘርፉ የአንደኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈፃፀም ለማየት እንደሚቻለው፣ ለ3.2 ሚሊዮን ዜጐች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ግብ ተጥሎ፣ በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ለ7,017,869 ዜጐች፣ በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለ3,637,786 ዜጐች፣ በጠቅላላው ለ10,655,655 ዜጐች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
በተጠቀሰው የአምስት አመታት ጊዜ ውስጥ የተፈጠረውን የስራ እድል ዘርዘር አድርገን ስናየው፤ በቋሚነት 6‚029‚875 (56.6 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 4‚625‚780 (43.4 ከመቶ) ሲሆን፣ በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም ከተፈጠረው የስራ እድል በቋሚነት 4‚543‚240 (64.8 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 2‚474‚629 (35.2 ከመቶ) እንዲሁም፣ በመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በቋሚነት 1‚486‚635 (40.8 ከመቶ)፣ በጊዜያዊነት 2,151‚151 (59.2 ከመቶ) ነው፡፡
በአጠቃላይ ከተፈጠረው የስራ እድል ውስጥ ተጠቃሚ የሆኑ ሴቶች 4‚387‚701 (41.2 ከመቶ) ሲሆኑ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ በዘርፉ ልማት 766‚990 ኢንተርፕራይዞችን ለማፍራትም ተችሏል፡፡ በእነዚህ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን ተጠቃሚ ያደረገ ቋሚና እንደ ስራው ባህሪ የቅጥር ጊዜው ተለዋዋጭ የሆነ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡
የማእከላዊ ስታቲስቲክስ ኤጀንሲ፤የከተማ ነዋሪዎችን ቁጥር አስመልክቶ ያወጣውን መረጃ ከላይ ከቀረቡት የዘርፉ መረጃዎች ጋር በማነጻጸር የቀረበው የአቶ ዮሐንስ ጽሑፍ፣ ስህተት አንድ ብሎ የጀመረው በዚህ መልኩ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውን ዜጐች ማንነት በጥልቀት መቃኘት ካለመቻል የተነሳ ነው፡፡ ከላይ እንደተገለፀው በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት፣ የሥራ ዕድል የተፈጠረው በሁለት መልኩ ነው፡፡ አንደኛው በዘርፉ መደበኛ የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም በምንለው ሥር ባሉ የስራ ዘርፎች ማለትም በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በንግድ፣ በአገልግሎትና በከተማ ግብርና ንዑስ ዘርፎች ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ መንግስት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሚያከናውናቸው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች ነው፡፡ ጸሐፊው ከመሰረቱ የሳቱት ጉዳይ በእነዚህ ዘርፎች የሚሰማሩ ሥራ ፈላጊ ዜጐች፣ የግድ በከተማ ነዋሪነት ብቻ የተመዘገቡ ናቸው ብለው መነሳታቸው ላይ ነው፡፡
የዘርፉን ስትራቴጂ ተግባራዊ ለማድረግ ከተዘጋጁ መመሪያዎች መካከል አንዱ በሆነው የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥ መመሪያ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፣ በከተማ በሚፈጠሩ የስራ ዕድሎች ውስጥ ተሳታፊ ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ዜጋ፣ ከሚኖርበት የገጠር ቀበሌ ሥራ ፈላጊነቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማቅረብ፣ በሚኖርበት ወረዳ ውስጥ በሚገኝ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ በስራ ፈላጊነት ሊመዘገብ ብሎም ከሚፈጠሩት የሥራ እድሎች ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በአጭሩ፣ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው የሥራ ዕድል ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች በከተማዋ ነዋሪነት የተመዘገቡ ብቻ ናቸው ማለት አይደለም፡፡
በመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም የሥራ ዘርፎች ከተፈጠረው የሥራ ዕድል በተጨማሪ የመንግሥት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በምንላቸው የስኳር ፋብሪካ፣ የህዳሴ ግድብ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የባቡርና የገጠር መንገድ ግንባታ፣ የኤሌክትሪክና የቴሌኮሙኒኬሽን ስራዎች፣ የቤቶች ልማትና የከተማ ማስዋብ፣ የኮብል ስቶን፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታን ጨምሮ በተለያዩ ፕሮጀክቶች ላይ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ዜጎች በርካታ መሆናቸውን በተጨባጭ ማስተዋል ይቻላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባን ባለፉት ዓመታት የተፈጠረው የሥራ ዕድል ከመደበኛው የኢንተርፕራይዞች ልማት ፕሮግራም በተጨማሪ በእነዚህ ፕሮጀክቶች ውስጥ በሚሰሩ ኢንተርፕራይዞች አማካኝነትና በግለሰብ ደረጃ በቋሚነትና  በጊዜያዊነት፣ በየጊዜው ለአጭር ጊዜ ሊሆን ይችላል /ከ1 ዓመት ያልበለጠ/ ወደ ሥራ የገቡ ዜጎችንም ጭምር የሚያካትት ነው፡፡
ይህን ሁኔታ ከግምት በማስገባት፣ የመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክቶች በሚገኙባቸው አካባቢዎች፣ ሥራ ፈላጊ ዜጎች የሚመዘገቡበትና ወደ ሥራ እንዲገቡ ሁኔታዎች የሚመቻችበት የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያዎችን ማቋቋም እንደሚያስፈልግ ከግንዛቤ በመግባቱ፣ በተለያዩ የመንግስት ፕሮጀክቶች ላይ ጣቢያው ተቋቁሟል፡፡ ጸሐፊው ሩቅ ሳይሄዱ በአዲስ አበባ በቤት ልማት ፕሮጀክቶችና የኮብልስቶን መንገድ ሥራዎች ላይ በቋሚና በጊዜያዊነት የተሰማሩ ነገር ግን የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ያልያዙ ዜጎችን እጅግ ከፍተኛ በሚባል መጠን ማግኘት የሚችሉ ሲሆን በየክልሉ በሚካሄዱ ፕሮጀክቶች የሚሰሩ ዜጎች የየአካባቢው የገጠር ቀበሌ ነዋሪ ወጣቶችንም ጨምሮ እንጂ የከተማ ነዋሪዎች ብቻ አለመሆናቸውን በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችሉት ነው፡፡
ምንም እንኳን የዘርፉ የሥራ እድሎች የሚፈጠሩት በከተማ ውስጥ እንደሆነ በስትራቴጂው ላይ ቢገለፅም ባለፉት ዓመታት የአርሶ አደሩ የአኗኗር ሥርዓት ላይ የመጣውን ለውጥ ተከትሎ በገጠር ቀበሌዎች እንደ ንግድ፣ አገልግሎትና የከተማ ግብርና የመሳሰሉ የሥራ እድሎችን ለመፍጠር የሚያስችል ምቹ ሁኔታ እንዳለ ተስተውሏል፡፡ በዚህም መሰረት በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ፣ “የገጠር የሥራ ዕድል ፈጠራ” በሚል ራሱን ችሎ በተከናወነ ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ እነዚህ ዜጎች በከተማ ነዋሪነት የተመዘገቡ ባይሆኑም ከሀገሪቱ ሀብት በፍትሃዊነት የመካፈል መብት ያላቸው ኢትዮጵያውያን እንጂ ጸሀፊው እንደሚሉን ከቅርብ የጎረቤት ሀገራት አልያም ከባህር ማዶ የመጡ ባዕዳን አይደሉም፡፡
በዘርፉ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነገር ግን የግድ የከተማ ነዋሪ መሆን ከማይጠበቅባቸው ዜጎች መካከል ከተለያዩ የቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚወጡ ዜጎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ መንግስት ለምሩቃን የሥራ ዕድል ፈጠራ በሰጠው ትኩረት፣ እስከ ሰኔ 2007 ዓ.ም ድረስ ለ407, 682 ምሩቃን የሥራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ ምሩቃንን ወደ ሥራ ለማስገባት በተዘጋጀው መምሪያ ላይም ማንኛውም ምሩቅ በሚፈልገው የሥራ ዘርፍ፣ በመረጠው የሀገሪቱ ክፍል ከትውልድ ሥፍራው ከዚህ በፊት በዘርፉ ተደራጅቶ እየሰራ አለመሆኑን የሚያሳይ ማስረጃ በማቅረብ፣ የዘርፉ የሥራ ዕድል ፈጠራ ተጠቃሚ መሆን ይችላል፡፡
የሥራ ፈጠራችን ዋነኛ ግብም ለኢንዱስትሪ ሽግግሩ መሰረት የሚሆኑ ኢንተርፕራይዞችን በስፋት ከማፍራት በተጨማሪ አቅም በፈቀደ መጠን በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ የመንግስት የልማት ፕሮጀክቶች፣ በቋሚነት ይሁን በጊዜያዊነት፣ የከተማ ነዋሪዎችም ሆኑ በሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎች ተጠቃሚ ለመሆን የሚሹ ማናቸውም ዜጎች፣ ሰርተው ራሳቸውንና ሀገራቸውን ሊለውጡ የሚችሉበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነው፡፡ ይህንን መሰረት በማድረግም ባለፉት አመታት በዘርፉ ልማት ያከናወናቸው ሥራዎች ወደ ሥራ መግባት ከሚገባቸው ዜጎቻችን አንጻር ስንመዝነው በቂ ነው ማለት ባይቻለንም፣ ጸሐፊው እንዳጣጣሉት ከእውነት የራቀና የማይጨበጥ ሳይሆን የበርካቶችን ህይወት የለወጠና በየአካባቢያችን የምናየው ሀቅ ነው፡፡
በመሆኑም አቶ ዮሐንስ፤ እንደ ዜጋ በሀገራቸው የልማት ሥራዎች ላይ ግልጽ ያልሆኑላቸውን ነገሮ የመጠየቅ መብታቸውን የምናከብር በመሆኑና በጽሁፋቸው ያሰፈሩት ጉዳይም ምን አልባትም በቂ መረጃ ካለመያዝ የመነጨ ይሆናል ብለን ስለምንገምት፣ወደፊት ተጨማሪ ማብራሪያ የሚሹ ከሆነ በራችን ሁሌም ክፍት መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን፡፡
የፌደራል የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ኤጀንሲ
የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት

     ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እጅግ ጉረኛ ሰው በአንድ መንደር ከሚስቱ ጋር ይኖር ነበረ፡፡ በድፍረት የማይከራከርበት ጉዳይ የለም፡፡ የሱን አሸናፊነት አጉልቶ ሌሎች ወንዶችን አኮስሶ ከማውራት ቦዝኖ አያውቅም፡፡
“ዛሬ አንዱን አንድ ቡና ቤት አግኝቼ ሳይቸግረው ለከፈኝ” ይላታል ለሚስቱ፡፡
ሚስትም፤
“በምን ጉዳይ ለከፈህ?” ትለዋለች፡፡
ባል፤
“እንደው ቢፈርድበት ነው እንጂ ነገሩ የሚያጣላ ሆኖ መሰለሽ? “አጐቴ በጣም አጭር ድንክዬ ሰው ነው፡፡ እኔ ደግሞ ከጥንቱም ድንክ ሰው እጣ - ክፍሌ አይደለም” አይልልሽም?”
ሚስት፤
“በጄ፡፡ ከዛስ ምን ሆነ?”
ባል፤
“ሾርኔ ንግግሩ ገብቶናል፡፡ ወንድ ልጅ ግን በአግቦ ሳይሆን በቀጥታ ነው መናገር ያለበት” አልኩኝ፡፡
ሚስት፤
“ለምን እንደዛ አልከው፤ እሱ የሚያወራው’ኮ ስለአጐቱ ነው?”
ባል፤
“አንቺ የዋህ ነሽ፡፡ እኔ አጭር መሆኔን ስላየ’ኮ ነው በጐን ወጋ ሊያደርገኝ የሞከረው፡፡”
ሚስት፤
“ከዛስ ምን ሆነ?”
ባል፤
“ጊዜ የሰጠሁት መሰለሽ፤ እንደ ነብር ተወርውሬ በቡጢ ማንጋጭልያውን አወለቅሁለታ!”
ሚስት፤
“አንተ ሰውዬ ይሄ ግሥላነት አያዋጣህም፡፡ ባለፈው ሣምንት እንኳን ከሶስት ሰው ጋር ተጣላሁ ብለኸኝ ነበር፡፡ ትዕግሥት ቢኖርህ ይሻላል” አለችው፡፡
ባል፤
“እኔኮ ካልነኩኝ አልነካም” ይላታል፡፡
አንድ ቀን ማታ ባል በጣም አምሽቶ ደም በደም ሆኖ ይመጣል፡፡ ሚስት ደንግጣ ከበር ትቀበለዋለች፡፡
“ምነው ምን ሆንክ አካሌ?”
ባል፤
“ካንድ መናጢ ጋር ተደባድቤ ድንገት ቀደመኝ”
ሚስት፤
“እንዴ፤ አላስተረፈህም’ኮ! ጭንቅላትህ ደግሞ ተፈነካክቷል፡፡ ሰውዬው ዱላ ይዞ ነበር እንዴ?”
ባል፤
“ኧረዲያ፤ ደሞ ዱላ የመያዝን ያህል ወንድነት ከየት አባቱ አምጥቶ ነው! የኔኑ ነጥቆ ነው እንጂ!”
*    *    *
ያልሆነውን ነን፣ ያላደረግነውን አድርገናል ብሎ ጉራ መንዛት መጨረሻው አሰቃቂ ነው፡፡ ከቶውንም ጥቃቅን የሚመስሉ ግን በአጉሊ መነፅር ስናያቸው አገራዊ ፋይዳ ያላቸው አያሌ ነገሮች አሉ፡፡ የምንዋሸውም ሆነ ጉራ የምንነዛው ቅርባችን ላለ ሰው መሆኑ አስገራሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙም ውሎ ሳያድር መጋለጡ በጣም ግልጽና አይቀሬ በመሆኑ ነው፡፡ ዋሽተን የተናገርነውን ማጠፍ ሲያቅተን፣ በጉልበት ለማሳመን መሞከር ይመጣል፡፡ ያኔ መሠረታዊ ሰብዓዊ መብትንም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብትን መጣስ ይመጣል፡፡ ፍትሕን እኔን በሚያግዝ መልኩ ካላስቀመጣችሁ ማለት ይመጣል፡፡ እኔ ላልኩት ካላጨበጨባችሁ ሁላችሁም ልክ ያልሆናችሁት ነገር አለ፤ ማለት ይከተላል፡፡ ግልጽነትንና ተጠያቂነትን የበላ ጅብ አልጮህ ይላል፡፡ የህዝብን ዕውነተኛ ችግር እንዳይገለጽ መጫን ይበራከታል፡፡ አመለካከትን በነፃነት መግለጫ መድረክ ይጨልምና ሆድ ለሆድ መነጋገር ዓይነተኛ ዘዴ እየመሰለ ይመጣል፡፡ መገናኛ ብዙሃን የህዝብ ድምጽ ማሰሚያ መሆናቸው ይቀራል፡፡ ከዚህ ዲበ - ኩሉ ይሰውረን!
ለአንድ አገር ህዝባዊ ውይይት መኖር አስፈላጊ ነው፡፡ ችግሮች ከአዕምሮ አዕምሮ ይዘዋወራሉ፡፡ ብሶቶች ይብላላሉ፡፡ የታፈኑ ሃሳቦች ይፍታታሉ፡፡ “አካፋን አካፋ” የማለት ባህል ይዳብራል፡፡ ሌባውን ከጨዋው የመለየት ዕድል ይሰፋል፡፡ ህዝብ ዕውነቱን የመናገር አጋጣሚ ሲያገኝ ሹማምንትን የማረም፣ የመተቸት፣ የመገሰፅ፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከመንበራቸው የማውረድ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ “ዳቦ ራበን” ብሎ ለሚጮህ ህዝብ፤ “ለምን ኬክ አይበሉም?” ብላ እንደመለሰችው እንደ ንግሥት ሜሪ አንቷኔት ያለ ቅንጡ አመራር አይኖርም፡፡ “ህዝባዊ ሸንጐ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ነው” ይላሉ ፈላስፋ ፀሐፍት፡፡ ህዝባዊ ውይይትን አቅጣጫ በማስያዝ ሰበብ ጮሌ ሊጠቀምበት እንደሚችል ግን ልብ ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ማንም ይሁን ማን የህዝብን ትኩረት በመሳብ ወደግል ጥቅሙ ልጐትት ሲል ገመዱን ለመበጠስ ዝግጁ መሆን ብልህነትም፣ ኃላፊነትም ነው፡፡ የመልካም አስተዳደር የንቅናቄ መድረክ፣ በተለይ ምዝበራን ከማጋለጥ አንፃር በየቦታው እየተሞከረ ያለው ሂደት፣ የሀገርን ሀብትና በሺዎች የሚቆጠሩ ሄክታሮችን ያድናል፡፡
የዳነውን ሌሎች እንዳይመዘብሩት የሚቆጣጠሩ ጠንቃቃ አካላት ያስፈልጋሉ፡፡ ነገሮች እንዳይድበሰበሱ፣ ጥያቄዎች በተጠየቁበት ገጽ እንዲመለሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የተጠየቁትን ትተው ያልተጠየቁትን የሚመልሱ ተጋላጫ አመራሮችን ለነገሮች ልጓም አበጅቶ ፈራቸውን እንዳይለቁና በትክክል ወንጀላቸው እንዲለይ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አለበለዛ በለመደ ምላሳቸው ወንጀሉን ለቀና ተግባር እንዳደረጉት ሊያስመስሉት ይችላሉ፡፡ ስለሆነም “ከዝሆንና ከአንበሳ ማን ይበልጣል” ቢለው፤ “ከሁሉም ከሁሉም አሣ ሙልጭልጭ ነው” አለው፤ እንደተባለው እንዳይሆን መጣር የአባት ነው!

    በህትመት፣ ወረቀትና እሽግ ሥራዎች ላይ ያተኮረና ከ40 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች የተሳተፉበት አለምአቀፍ ኤክስፖ ትላንት በሚሊኒየም አዳራሽ ተከፈተ፡፡
በፕራና ፕሮሞሽን ተዘጋጅቶ ከጥር 13-15 በሚቆየውና በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በዶ/ር መብራቱ መለስ በተከፈተው በዚሁ “አፍሪ ፕሪንት ኤንድ ፓኬጂንግ ኤክስፓ” ላይ፤ አታሚዎች፣ የህትመት መሣሪያ አስመጪዎች፣ የህትመት ማስታወቂያ ድርጅቶች፣  የወረቀት አምራቾችና አስመጪዎች፣ የግራፊክ ዲዛይን ድርጅቶች እንዲሁም ከወረቀት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚሰሩ የአገር ውስጥና የውጭ ድርጅቶች ተሣታፊ ሆነዋል፡፡
በኤክስፖው በዘርፉ የተሰማሩ ድርጅቶች የንግድ ትስስር እንዲፈጥሩና የቴክኖሎጂና የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ታስቦ መዘጋጀቱን የተናገሩት የፕራና ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ነቢዩ ለማ፤ ፕሮግራሙ በአገራችን በዘርፉ ለተሰማሩ ድርጅቶ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል፡፡ በዚህ ኤክስፖ ላይ ለመሳተፍ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓና ከኤዥያ የመጡ ባለሀብቶችና የድርጅቶች ተወካዮች መኖራቸውንም አቶ ነቢዩ ተናግረዋል፡፡