Administrator

Administrator

በዚህ አመት ማምረት እንደሚጀመር ይጠበቃል
     ፖሊ ጂሲኤል ፔትሮሊየም ግሩፕ የተባለው የቻይና የነዳጅ አምራች ኩባንያ በኦጋዴን አካባቢ የሚገኙ ሁለት የነዳጅ ጉድጓዶችን የቁፋሮ ስራ ማጠናቀቁንና በቅርቡም የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን ይፋ ያደርጋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ትናንት ዘገበ፡፡
ኩባንያው የጉድጓዶቹን የተፈጥሮ ጋዝ ይዞታ መጠን የማጥናት ስራ መጀመሩንና ውጤቱንም በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ የገለጹት የማዕድን፣ የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ዋጋሪ ፉሪ፣ በዚህ አመት የተፈጥሮ ጋዝ ምርት ልንጀምር እንችላለን ብለዋል ለሮይተርስ፡፡
እ.ኤ.አ በ1970ዎቹ የተፈጥሮ ጋዝ እንዳላቸው በጥናት ከተረጋገጠውና በካሉብ እና ሂላላ አካባቢዎች ከሚገኙት ሁለቱ ጉድጓዶች፣ 4.7 ትሪሊዮን ኪዩቢክ ጫማ ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝና 13.6 ሚሊዮን በርሜል ጋዝነት ያላቸው ተያያዥ ፈሳሾች ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
ኩባንያው በ4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ በደቡብ ምስራቅ ኢትዮጵያ አምስት ጉድጓዶችን የመቆፈር እቅድ እንዳለው የጠቆመው ዘገባው፣ ፕሮጀክቱ አካባቢውን ከማልማት በተጨማሪ፣ በጅቡቲ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማምረቻ መገንባትንና ከኦጋዴን እስከ ጅቡቲ የሚዘልቅ የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋትን ያካትታል ብሏል፡፡
ኩባንያው የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ የማምረት ስራውን እስከ 2018 መጨረሻ የመጀመር እቅድ እንዳለውና በአመት 3 ሚሊዮን ቶን በማምረት ጀምሮ፣ በሂደት አመታዊ የምርት መጠኑን ወደ 10 ሚሊዮን ዶላር የማሳደግ ዕቅድ መያዙን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

ከ3 ሺህ በላይ ስደተኞች ባህር ሲያቋርጡ ሞተዋል


    ሊጠናቀቅ የቀናት ዕድሜ በቀሩት የፈረንጆች 2015 ዓ.ም ብቻ ከ1 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞች ወደ አውሮፓ መግባታቸውንና 3 ሺህ 700 የሚሆኑትም ሜዲትራኒያን ባህርን ለማቋረጥ ሲሞክሩ ለሞት መዳረጋቸውን አለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት ማስታወቁን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
እስካለፈው ሰኞ ድረስ በአመቱ ወደ አውሮፓ የገቡ ስደተኞች ቁጥር 1 ሚሊዮን 5ሺህ 54 መድረሱን የጠቆመው ዘገባው፣ ይህም ቁጥር ባለፈው አመት ከተመዘገበው ከአራት ዕጥፍ በላይ ማደጉን ያመለክታል ብሏል፡፡
በአመቱ ከ455 ሺህ በላይ ሶርያውያንና ከ186 ሺህ የሚልቁ አፍጋኒስታናውያንን ጨምሮ ከ800 ሺህ በላይ ስደተኞች ከቱርክ ወደ ግሪክ መግባታቸውን ያስታወቀው የአለማቀፉ የስደተኞች ድርጅት፣ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ስደተኞችም ወደ አውሮፓ ለመግባት እየተቃረቡ ነው ብሏል፡፡
በጦርነት ሳቢያ አገራቸውን ጥለው የሚሰደዱና ከመኖሪያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም በዘንድሮው አመት ከ60 ሚሊዮን በላይ መድረሱን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ በመጀመሪያዎቹ የአመቱ ወራት ብቻ 839 ሺህ ሰዎች አለማቀፍ ድንበሮችን አቋርጠው ወደ ሌሎች አገራት መሰደዳቸውንና አንድ ሶስተኛ ያህሉም ሶርያውያን መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡
በዘንድሮው አመት በአለማችን ከ122 ሰዎች አንዱ በጦርነት ሳቢያ ከመኖሪያ አካባቢው እንደሚፈናቀል ወይም ወደ ሌሎች አገራት እንደሚሰደድ ድርጅቱ አክሎ ገልጧል፡፡

የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ አሁንም በስራ ላይ ነው


የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ከተጀመረ ተግባራዊ ከሆነና “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው የአለማችን የመጀመሪያው ድረ-ገጽ ተከፍቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ በዚህ ሳምንት 25 አመት እንደሞላው ዘ ቴሌግራፍ ከትናንት በስቲያ ዘገበ፡፡
ቲም በርነርስ ሊ የተባሉት እንግሊዛዊ የኮምፒዩተር ሳይንቲስት እ.ኤ.አ ታህሳስ 20 ቀን 1990 የአለማችንን የመጀመሪያ ድረ-ገጽ እንደፈጠሩ ያስታወሰው ዘገባው፣ በዚያው አመት ነሃሴ ወር ላይ ስራ የጀመረው ድረ-ገጹ አሁንም ድረስ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጧል፡፡
በወቅቱ የአውሮፓ የኒውክሌር ምርምር ተቋም (CERN) ተመራማሪ የነበሩት ሳይንቲስቱ፤ የፈጠሩት “ቲም በርነርስ ሊስ ወርልድ ዋይድ ዌብ” የተባለው ድረ-ገጽ info.cern.ch የሚል አድራሻ ያለው ሲሆን፣ ለተጠቃሚዎች ከድረ-ገጽ ጋር በተያያዘ መሰረታዊ መረጃዎችን የሚሰጥ እንደሆነ ተነግሯል፡፡
የድረ-ገጽ ቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለፉት 25 አመታት እጅግ እየተሻሻለና አሰራሩንም ሆነ አቅሙን እያሳደገ መቀጠሉን ዘገባው አስታውሶ፣ ሳይንቲስቱ አሁንም በዘርፉ እየሰሩ እንደሚገኙና የወርልድ ዋይድ ዌብ ማህበርን እየመሩ እንደሆነ ገልጿል፡፡

በበርሜል ከ37 ዶላር በታች ደርሷል

የአለም የነዳጅ መሸጫ ዋጋ ካለፉት 11 አመታት ወዲህ እጅግ ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበውን የዋጋ ቅናሽ በማሳየት በበርሜል ከ37 ዶላር በታች መድረሱን የነዳጅ አምራችና ላኪ አገራት ድርጅት ኦፔክ አስታወቀ፡፡
ባለፈው አመት በበርሜል ከ110 ዶላር በላይ ይሸጥ የነበረው ነዳጅ፣ ከፍተኛ የዋጋ ቅናሽ ሊያስመዘግብ የቻለው ከፍተኛ አቅርቦት በመኖሩና የአገራት የኢኮኖሚ እድገት እየተዳከመ ከመምጣቱ ጋር በተያያዘ የነዳጅ ፍላጎት እየቀነሰ በመምጣቱ ነው ሲል ኦፔክ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በነዳጅ ላይ የዋጋ ቅናሽ መፈጠሩ እንግሊዝን በመሳሰሉ አገራት ለተጠቃሚዎች በርካሽ ዋጋ ነዳጅ የማግኘት እድል መፍጠሩን የጠቆመው ዘገባው፣ ይሄም ሆኖ ግን ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየው የነዳጅ ዋጋው በአዲሱ አመት ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ኦፔክ መግለጹን አስረድቷል፡፡
የአለም የህዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ እድገት የሃይል ፍላጎትን እስከ 2040 በግማሽ ያህል ያሳድገዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ኦፔክ፣ ከዚህ ጋር ተያይዞም የነዳጅ ፍላጎት ጭማሪ እንደሚያሳይ ግምቱን አስቀምጧል፡፡


ቡድኑ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን አዘግቷል

ጽንፈኛው ቡድን ቦኮ ሃራም በናይጀሪያ፣ ካሜሩን፣ ቻድና ኒጀር በሚያደርጋቸው የሽብር ተግባራት ሳቢያ ትምህርታቸውን ያቋረጡ ተማሪዎች ቁጥር 1 ሚሊዮን ያህል መድረሱን ዩኒሴፍ አስታወቀ፡፡
የሽብር ቡድኑ ከ2 ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶችን አዘግቷል፣ በመቶዎች በሚቆጠሩ ትምህርት ቤቶች ላይም የሽብር ጥቃት፣ ዘረፋና በእሳት የማቃጠል ድርጊቶችን ፈጽሟል ያለው ተቋሙ፣ ቦርኖን በመሳሰሉ የናይጀሪያ አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወደ ስደተኞች መጠለያነት መቀየራቸውን ገልጧል፡፡
ቦኮ ሃራም የምዕራባውያንን አስተምህሮ አምርሮ ከመጥላቱ ጋር በተያያዘ፣ ትምህርት ቤቶችን ልዩ የጥቃት ኢላማው እንደሚያደርግ የጠቆመው ዘገባው፣ ባለፈው አመት ሚያዝያ ወር ላይም ከናይጀሪያዋ ቺቦክ ከተማ 200 በላይ የአዳሪ ትምህርት ቤት ልጃገረዶችን መጥለፉን አስታውሷል፡፡
ቡድኑ እንቅስቃሴውን ማድረግ ከጀመረ አንስቶ ባሉት ያለፉት ስድስት አመታት 17 ሺህ ያህል ዜጎችን መግደሉንና ከ2 ሚሊዮን በላይ ሰዎችንም ከመኖሪያ ቦታቸው አፈናቅሎ ቤት አልባ ማድረጉን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

“ውህደቱ በሞት ላይ የነበረ ባንክን ህይወት ለማትረፍ የተደረገ አይደለም”

    ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የፋይናንስ ድርጅቶችን እንደገና ማዋቀር ማስፈለጉ የተገለፀ ሲሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ሰሞኑን ተዋህደዋል፡፡
የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል መግለጫውን በሰጡበት ወቅት፣ የመንግሥት የፋይናንስ ተቋማት በምን መልኩ ቢደራጁ ነው የበለጠ ጥቅም የሚሰጡት? በማለት ጥናት እያደረገ መንግሥት ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚያደርገው የመንግሥት የፋይናንስ ድርጅቶች ኤጀንሲ መሆኑን ጠቅሰው፣  በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ፣ በኢትዮጵያ ልማት ባንክና በኢትዮጵያ መድን ድረጅት ላይ ጥናት አድርጎ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ መሰረት፤ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተዋህደው እንዲሰሩ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡
ውሳኔውን ተግባራዊ ለማድረግ በአጭርና በረዥም ጊዜ የሚሰሩ ተግባራት ይኖራሉ ያሉት ዶ/ር ስንታየሁ፤ የልማት ተቋማቱ አደረጃጀት ዓላማ የኢኮኖሚ ልማቱን ለማፋጠን ታስቦ የተሰራና ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር የሚሄድ አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለፉት ዓመታት የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ መሰረታዊ የሥራ ላይ ለውጥ (ቢፒአር) ካደረገ በኋላ ባንኩ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የተሻሻለ አሰራር እንዲኖረውና የሰራተኛው የአፈጻጸም ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳለጠ እንዲሆን በማድረጉ፣ የነበሩትን ቅርንጫፎች ጨምሮ፣ የአሴት መጠንና የሚሰበሰበውን የቁጠባ መጠን በመጨመር፣ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰራር ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ሁለቱ ባንኮች ቢጣመሩ መንግሥት ከባንኮች የሚፈለገውን ተግባር የበለጠ ለማከናወን ይረዳል ብሎ በማመን የተደረገ ውህደት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ከመንግሥት በኩል ከባንኮች የሚፈለገው ኢኮኖሚውን በማሳለጥና በኢንቨስትመንት ኅብረተሰቡ ቁጠባን ባህሉ አድርጎ ገንዘብ በመሰብሰብ ሥራ መፍጠር ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፣ የተቀላጠፈ የክፍያ ሥርዓት መዘርጋት፣ ትክክለኛውን ኢንቨስተር በመለየት ብድር መስጠትና ያሉትን ስጋቶች በትክክል በመለየት ማስተዳደር እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡
ሁለቱ ባንኮች በመዋሃዳቸው በደንበኞች ላይ ምንም ዓይነት ስጋት አይፈጠርም ያሉት ዶ/ር ስንታየሁ፤ ገንዘብ አስቀማጮች ከዚህ በፊት የሚያገኙት መብትና ጥቅም ተጠብቆ ይፈጸማል። ተበዳሪዎች ከኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የገቡት ውል የጸና በመሆኑ በውላቸው መሰረት ግዴታቸውን መፈጸም አለባቸው፡፡ በሰራተኛው በኩልም የሚቀነስ ሰው ስለሌለ ስራቸውን በትጋት እንዲወጡና ዝርዝር አሰራሮች ወደፊት እንደሚገለፅ ተናግረዋል፡፡  
የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ ነው ውህደቱ የተፈፀመው ይባላል ተብለው የተጠየቁት ዶ/ር ስንታየሁ፤ ውህደቱ የተደረገው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች እንጂ በአፈፃፀም ድክመት አለመሆኑን ገልፀዋል፡፡ ባንኩ ባለፉት ዓመታት ትርፋማ እንደነበር በመጥቀስ ቅርንጫፎቹ ከ37 ወደ 120 ማደጋቸውን፣ የባንኩ አሰራርም ከማኑዋል ተላቅቆ በኔትወርክ መገናኘቱን ጠቁመው። ስለዚህ በሞት ላይ የነበረ ባንክ ሕይወትን ለማትረፍ የተደረገው ውህደት አይደለም ብለዋል፡፡
ሁለቱ ባንኮች ከተዋሃዱ በኋላ ስማቸው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደሚሆን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

   ኑሮውን በአሜሪካ ባደረገው ደራሲ አያልሰው መኮንን የተፃፉ ከ40 በላይ ወጐችና ግጥሞችን ያካተተው “ደንበሎ በአሜሪካ” የተሰኘ መድበል ሰሞኑን ለንባብ በቅቷል፡፡ በተለያዩ ማህበራዊ፣ ባህላዊና፣ ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ግጥሞችና ወጐችን የያዘው መፅሀፍ የታተመውም እዚያው አሜሪካ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ በመጽሐፉ ውስጥ ከተካተቱት ወጐችና ግጥሞች መካከል ጥቂቶቹ ሎስአንጀለስ ውስጥ ለአበሾች በሚሰራጭ “አለኝታ ሬዲዮ” መተላለፋቸውን ደራሲው በመግቢያቸው ላይ ጠቁመዋል፡፡ 146 ገፆች ያሉት መጽሐፉ፤ ለአገር ውስጥ በ60 ብር፣ ለውጭ አገራት  በ15 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

   በአዲስ አድማስ ጋዜጣ “የተማሪና አስተማሪ ወግ” ላይ “የፍሬሿ ማስታወሻ” በሚል በሄርሜላ ሰለሞን በተከታታይ ሲቀርቡ የነበሩ ታሪኮች በመጽሐፍ ተሰባስበው የታተሙ ሲሆን ከነገ ወዲያ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ ይመረቃል ተብሏል፡፡ ታሪኩ ፀሐፊዋ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ ያሳለፈችውን ህይወት የሚያስቃኝና በግል የዕለት ማስታወሻ (ዳያሪ) መልክ ሲከተብ የነበረ እንደሆነ ታውቋል።  በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ደራሲ ሲሳይ ንጉሱ፣ አርቲስት ስዩም ተፈራ፣ አርቲስት ፈለቀ አበበ፣ አርቲስት ፍቃዱ ከበደ፣ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ሞሲሳና ሌሎች ወጣትና አንጋፋ ገጣሚያን ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡም ተገልጿል። በ191 ገፆች የተቀነበበው መጽሐፉ፤ በ47 ብር ከ50 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “ሰብስቤና ፈረሱ” “ወርቃማው ወንዝ” እና “ዝርጋዳዋ ዤ” የተሰኙ የህፃናት መጽሐፍትን ማሳተሟም ታውቋል፡፡

“የማይታየውን በሚታይ” በሚል ርዕስ በጋለሪያ ቶሞካ ለወር ያህል ለተመልካች ክፍት ሆኖ በቆየው የስዕል ትርኢት ላይ ነገ ከረፋዱ 4፡00 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እንደሚካሄድ ተገለፀ፡፡ በአውደ ርዕዩ የወጣቱ ሰዓሊ ኪሩቤል አበበ ከ35 በላይ የስዕል ስራዎች የቀረቡበት ሲሆን ውይይቱ በሰዓሊው የአሳሳል ዘይቤ፣ ፍልስፍናና በስዕሎቹ ላይ እንደሚያተኩር የተናገሩት የጋለሪው ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ ነብዩ ግርማ፤ የስዕል ትርኢቱም ለተጨማሪ አንድ ወር ለተመልካች ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ አክለው ገልፀዋል፡፡

Tuesday, 29 December 2015 07:37

የቀልድ ጥግ

አንድ ሰውዬ በኒውዮርክ ሴንትራል ፓርክ በእግሩ
እየተጓዘ ሳለ አንዲት ህፃን በትልቅ ውሻ ስትነከስ
ይመለከታል፡፡ በሩጫ ይሄድና አንዳች ከሚያህለው
ውሻ ጋር ትግል ይጀምራል። በመጨረሻም ውሻውን
በመግደል የህፃኗን ህይወት ይታደጋል፡፡ ትእይንቱን
ሲመለከት የነበረ ፖሊስ ወደ ሰውየው በመጠጋት፤
“ጀግና ነህ፤ ይሄ ተግባርህ ነገ በሁሉም ጋዜጦች ላይ
ተዘግቦ ታነበዋለህ” ይለዋል፡፡ ፖሊሱ በዚህ ብቻ
አልበቃውም፡፡ የዜናው ርእስ ምን ሊሆን እንደሚችል
ሁሉ ይተነብይለት ጀመር፡፡
“ጀግናው የኒውዮርክ ነዋሪ የህፃኗን ህይወት ታደገ”
“እኔ ግን የኒውዮርክ ነዋሪ አይደለሁም” አለ
ሰውየው፡፡
እንግዲያውስ የጠዋት ጋዜጦች እንዲህ ብለው
ያወጡታል፡-
“ጀግናው አሜሪካዊ የህፃኗን ህይወት ታደገ”
“እኔ እኮ አሜሪካዊ አይደለሁም” አለ ሰውየው
በድጋሚ፡፡
“ታዲያ ምንድን ነህ?” ጠየቀ ፖሊሱ፡፡
“የፓኪስታን ተወላጅ ነኝ”
* * *
በነገታው የወጡት ጋዜጦች፤ “ፅንፈኛው
ሰላማዊውን የአሜሪካ ውሻ ገደለ” ብለው ዘገቡ፡፡