Administrator

Administrator

የፈረንሳዩ  ሎቨር ግሩፕ፤  ከ480 ሚ.ብር በላይ በሆነ ወጪ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ ያለውን  “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ባለ 5 ኮከብ ሆቴል ለማስተዳደር፣ ”በገዝ ቢዝነስ ግሩፕ” ከተሰኘ የኢትዮጵያ ኩባንያ ጋር ተስማማ፡፡ ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው ሆቴሉ፤ 88 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ታውቋል። ሆቴሉ የሬስቶራንት፣ የስፓ፣ የስብሰባ አዳራሽ (ለቢዝነስና ተጓዦች) አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ደረጃቸውን የጠበቁ፣ የላቁ መስተንግዶዎችንም ያቀርባል ተብሏል፡፡
ሎቨር ሆቴልስ ግሩፕ፤ ሁለተኛውን ባለ 5 ኮከብ “ሮያል ቱሊፕ ፕላዛ” ሆቴል በኢትዮጵያ መክፈቱ፤ ሎቨር በአፍሪካ ያቀደውን ሆቴሎቹን የማስፋፋት ስትራቴጂ ያጠናክርለታል ተብሏል፡፡ በኬንያ፣ ሩዋንዳ እንዲሁም በታንዛንያ የሆቴሎቹን ቁጥር እያሳደገና አገልግሎቱን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ በ2017 እ.ኤ.አ ሎቨርስ ሆቴልስ፤ ወደ 15 ተጨማሪ ሆቴሎችን በክልሉ ለመክፈት አቅዷል፡፡  
ሉቨር ሆቴል ግሩፕ ከሚያስተዳድራቸው ሶስት የሆቴል ብራንዶች አንዱ የሆነውን “ጎልደን ቱሊፕ” ከጥቂት ዓመታት በፊት በቦሌ ከፍቶ እያስተዳደረ ሲሆን “ሮያል ቱሊፕ” የተሰኘው ብራንድ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ድርድር መካሄዱ በስምምነት ፊርማው ላይ ተገልጿል፡፡ ሆቴሉ በአዲስ አበባ እንዲከፈት ድርድሩን ያካሄደው በቱሪዝምና ሆስፒታሊቲ ቢዝነስ ላይ የተሰማራው “አዚ ቢዝነስና ሆስፒታሊቲ ማኔጅመንት ግሩፕ” መሆኑን የ”ኦዚ ቢዝነስ ሆስፒታሊቲ ግሩፕ ማኔጅምነት” ዋና ዳይሬክተር አቶ ቁምነገር ተከተል ገልጸዋል፡፡
የሆቴሉ በአዲስ አበባ መከፈት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን የአገሪቱን የጎብኚ ፍሰት ለማስተናገድና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መስተንግዶ ለመስጠት ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡ ሆቴሉ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ከፍተኛ የስራ እድል እንደሚፈጥርም ተጠቁሟል፡፡

  የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዛሬ የሚከበረውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቅጥር ግቢ ውስጥ ለሚገነባው የልብ ህሙማን ማዕከል የ2.6 ሚ. ብር ድጋፍ ማድረጉን ገለፀ፡፡ ባንኩ በገና ዕለት የሚተላለፍ የበዓል የቴሌቪዥንና የሬዲዮ ፕሮግራም ያዘጋጀ ሲሆን የበዓሉ ቅድመ ቀረፃም ባለፈው ማክሰኞ ረፋድ ላይ በልብ ህሙማን ማዕከል አዳራሽ መከናወኑን የቀረፃውም ምክንያት የገንዘቡ ልገሳ እንደሆነ ባንኩ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ባንኩ በልብ ህመም የሚሰቃዩ ጨቅላ ህፃናትን ለመታደግ ከማዕከሉ ጋር አብሮ እየሰራ መሆኑን ከዚህ ቀደም ድጋፍ ማድረጉን ያስታወሱት የባንኩ ተቀዳሚ ስራ አስኪያጅና ኮሚዩኒኬሽን ሃላፊ አቶ በልሁ ታከለ ይህኛው ድጋፍ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የተደረገ የልገሳ ልዩ ስነ ስርዓት እንደሆነም ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ባንኩ በቀጣይም ለማዕከሉ ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

 በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ የጉራጌ ተወላጆችን የሚያሳስብና የሚያወያይ የጉራጌ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች መድረክ ባለፈው ሳምንት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተመሰረተ፡፡ በምስረታ ስነ-ስርዓቱ ላይ ድምፃዊያን፣ ተወዛዋዦች፣ የፊልም ባለሙያዎች፣ አንጋፋ ደራሲያን፣ ሰዓሊያን፣ ተዋንያንና ሌሎችም ከመቶ በላይ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ተገኝተዋል፡፡
የጉራጌ ተወላጅ የኪነ- ጥበብ ባለሙያዎች፤ አካባቢያቸውን ባህላቸውንና ታሪካቸውን ለቀሪው ኢትዮጵያዊና ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅ፣ በሙያቸው ዙሪያ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታትና እርስ በእርስ ለመደጋገፍ የሚያስችል መድረክ እንዳልነበራቸው በምስረታው የተገለፀ ሲሆን የመድረኩ መመስረት ዋና አላማ፤ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላትና የጉራጌን እምቅ ባህልና አብሮነት በጋራ ለዓለም ማስተዋወቅ እንደሆነ፣ የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ዋና ዳይሬክተርና ደራሲ ተስፋዬ ጉይቴ ተናግረዋል፡፡
የተመሰረተው መድረክ እስኪጠናከርና በራሱ እስከሚቆም የጽ/ቤት፣ የፋይናንስና መሰል ድጋፎችን የጉራጌ ልማትና የባህል ማህበር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው የማህበሩ የባህል ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ኃ/ማሪያም ገልፀዋል፡፡
በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ መድረኩን የሚመሩ ሀላፊዎች ምርጫ፣ ስለ መድረኩ የወደፊት ጉዞ ውይይትና የመዝናኛ ፕሮግራሞች የተካሄዱ ሲሆን ድምፃዊያንና ተወዛዋዦች የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ለታዳሚው አቅርበዋል፡፡

‹‹አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም›› በሚል መሪ ቃል የፋሽን ትርኢት ተካሄደ፡፡ በአካል ጉዳተኛዋ ሳባ ከድር (ሳቤላ) የተዘጋጀውና አካል ጉዳተኞች ሁሉን ማድረግ እንደሚችሉ ግንዛቤን ያስጨብጣል የተባለው የአካል ጉዳተኞች የፋሽን ትርኢት፤ ባለፈው ሳምንት በዮድ አቢሲኒያ የባህል ምግብ አዳራሽ ተካሂዷል። የፋሽን ትርኢቱ ማየት በተሳናቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህግ ተማሪዎች፤ በአካል ጉዳተኛ ሰዓሊዎች፣ በድምፃዊያንና በሌላ ሙያ ላይ ባሉ አካል ጉዳተኞች የቀረበ ሲሆን የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ት/ቤት ዲዛይነሮችም ስራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡
በትርኢቱ ላይ በአካል ጉዳተኝነት ላይ አተኩረው የሚሰሩ እውቅ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች ማርታ ደጀኔና ተስፋዬ ገ/ማሪያም በክብር እንግድነት የተገኙ ሲሆን፡፡ አካል ጉዳተኛዋ ወ/ሪት ሳባ ከድር ለታዳሚው ተሞክሮዋን ከማቅረቧም በተጨማሪ ራሷ ፅፋ ያዘጋጀችውን ‹‹ማስተዋል›› የተሰኘ የ8 ደቂቃ ፊልም ለእይታ አቅርባለች፡፡ በቀጣይም በአካል ጉዳተኝነት ላይ ያለውን አመለካከት ለመለወጥ ፕሮጀክቶችን ነድፋ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ገልፃ ለዚህ ህልሟ እውን መሆን ድጋፍ እንዲደረግላት ጠይቃለች፡፡

Friday, 06 January 2017 12:11

የህይወት ጥግ

· ህይወት በጣም ቀላል ነው፤ እኛ ግን ልናወሳስበው እንታገላለን፡፡
      ኮንፉሺየስ
· ሞትን መፍራት ህይወትን ከመፍራት ይመነጫል፡፡ ህይወትን በቅጡ የኖረ ሰው በማንኛውም ጊዜ ለመሞት ዝግጁ  ነው፡፡
     ማርክ ትዌይን
· በራስህ የማትተማመን ከሆነ በህይወት ሩጫ ሁለቴ ትሸነፋለህ፡፡
     ማርከስ ጋርቬይ
· የህይወታችን ግብ ደስተኛ መሆን ነው፡፡
     ዳላይ ላማ
· ማንም ሰው ህይወትን የኋሊት አ ይኖርም። ወደፊት ተመልከት፣ መጪው ህይወትህ ያለው እዚያ ነው፡፡
     አን ላንደርስ
· ህይወት ቢስክሊሌት እንደ መጋለብ ነው፡፡ ሚዛንህን ለመጠበቅ እንቅስቃሴህን መቀጠል አለብህ፡፡
     አልበርት አንስታይን
· ህይወት ከባድ ነው፤ ደደብ ከሆንክ ግን የበለጠ ይከብዳል፡፡
     ጆን ዋይኔ
· ዓይንህን ግለጥ፤ ወደ ውስጥህ ተመልከት፡፡ በምትመራው ህይወት ደስተኛ ነህ?
     ቦብ ማርሌይ
· በህይወት ብቸኛው አቅመ-ቢስነት አሉታዊ አመለካከት ነው፡፡
    ስኮት ሃሚልተን
· ህይወት ጉዞ ነው፡፡ ስንቆም ነገሮች ትክክል አይመጡም፡፡
    ፖፕ ፍራንሲስ
· ህይወት የተሰራው ከእምነበረድ እና ከጭቃ ነው፡፡
    ናታኔል ሃውቶርን
· እድገት የህይወት ብቸኛ ማስረጃ ነው፡፡
    ጆን ሄንሪ ኒውማን

Saturday, 07 January 2017 00:00

የዘላለም ጥግ

(ዝነኞች በመሞቻቸው ሰዓት የተናገሩት)

- “እርስ በርስ ተዋደዱ”
    ጆርጅ ሃሪሰን (እንግሊዛዊ ሙዚቀኛ)
- “መሄድ እፈልጋለሁ፤ እግዚአብሔር ይወስደኛል”
    ድዋይት ዲ. አይዘንሃወር (የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
- “እንቅልፌን ልተኛ ነው፤ ከአሁን በኋላ አልጠራችሁም፡፡ እናንተም ወደ መኝታችሁ መሄድ ትችላላችሁ”
     (ለጠባቂ ወታደሮቹ የተናገረው) ጆሴፍ ስታሊን (የሶቭየት ህብረት መሪ)
- “እንዳላሰለቸኋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ”
    ኤልቪስ ፕሪስሊ (አሜሪካዊ ዘፋኝና ተዋናይ)
- “እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን፡፡ በክፍል ውስጥ አስቂኙ ሰው መሆን ሰልችቶኛል”
    ዴል ክሎዝ (ኮሜዲያን)
- “ለእኔ አታልቅሺ፤ ምክንያቱም የምሄደው ሙዚቃ የተወለደበት ሥፍራ ነው”
     (ለሚስቱ የተናገረው) ጆሃን ሴባስትያን ባች (ጀርመናዊ ሙዚቃ ቀማሪ)
- “ያሳዝናል፤ ያሳዝናል፤ በጣም ዘገየ!”
       (ያዘዘው የወይን ጠጅ በሰዓቱ ባለመድረሱ የተናገረው) ሉድዊግ ቫን ቤትሆቨን (ጀርመናዊ ሙዚቃ ቀማሪ)
- “እኔ ፒያኖ ተጫዋች ነኝ”
      (“ፕሮቴስታንት ነህ ካቶሊክ?” ተብሎ ሲጠየቅ የመለሰው) ጆን ፊልድ (አየርላንዳዊ ሙዚቃ ቀማሪ)
- “ዛሬ ለመሞት ጥሩ ቀን ነው፡፡ ሁላችሁንም ይቅር ብያችኋለሁ፡፡ እግዚአብሔርም ይቅር እንደሚላችሁ ተስፋአደርጋለሁ”
     ቤንጃሚን መርፊ (ቅጥር ነፍሰ ገዳይ)
- “ለመሞት አልፈልግም፡፡ እባካችሁ ከሞት ታደጉኝ”
     ቻቬዝ ሁጎ (የቬኔዝዋላ ፕሬዚዳንት)
- “የለም፤ እርቃኔን አይደለም፡፡ ዩኒፎርሜን እለብሳለሁ”
     ቀዳማዊ ፍሬድሪክ ዊሊያም (የፕረሽያ ንጉስ)

Saturday, 07 January 2017 00:00

የፖለቲካ ጥግ

- ጥሩ ኳስ ተጫዋቾች፤ ጥሩ ዜጎች ይወጣቸዋል፡፡
    ቼስተር አርተር
- የፕሬዚዳንት ከባዱ ሥራ ትክክለኛውን ነገር ማከናወን አይደለም፤ ትክክለኛውን ነገር ማወቅ ነው፡፡
    ሊንዶን ጆንሰን
- መፍራት ያለብን ነገር ቢኖር ራሱን ፍርሃትን ነው፡፡
    ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት
- ሃቁን ተናገር፣ ጠንክረህ ሥራ፣ እናም ለእራት በሰዓቱ ድረስ፡፡
    ጌራልድ አር.ፎርድ
- ፖለቲከኞች ሥልጣን ይወዳሉ፡፡ እኔ ነፃነት እወዳለሁ፡፡ ለዚያ ነው ፖለቲከኛ ያልሆንኩት፡፡
    ቪክቶር ፒንቹክ
- ፖለቲከኞች መምራት አይችሉም፡፡ እነሱ የሚችሉት ማውራት ብቻ ነው፡፡
    ዶናልድ ትራምፕ
- ፖለቲከኞቻችን ከማንዴላ ብዙ ይማራሉ ብዬ አስባለሁ፡፡
    ክሊንት ኢስትውድ
- ሲጋራ ማጨስ ያረጋጋኛል፡፡ ለህይወቴ ደስታ የሚሰጠኝን ነገር ፖለቲከኞች እንዲወስኑልኝ አልፈልግም፡፡
    ዴቪድ ሆክኔይ
- ፖለቲካ ውስጥ እውነትን ከጨመርክ፣ ፖለቲካ አዲዮስ!
    ዊል ሮጀርስ
- ፖለቲከኞቻችንን በጣም ከመጥላታችን የተነሳ መዋሸታቸውን ቢነግሩን እንኳን አናምናቸውም፡፡
    ፒተር ኒውማን
- አገርህን ውደድ፤ መንግስትን ግን ፍራ፡፡
    ኤን.ኢ.ፎክ ዊዝደም
- እኒያ መርሆቼ ናቸው፡፡ ካልወደድካቸው ሌሎች አሉኝ፡፡
    ግሮቾ ማርክስ
- ነፃነት የዕድገት እስትንፋስ ነው፡፡
    ሮበርት ኢንገርሶል
- ሙቀቱን የማትችለው ከሆነ ከወጥ ቤት ውጣ፡፡
    ሃሪ ትሩማን (የአሜሪካ ፕሬዚዳንት)
- አፍንጫ ስር ያለውን ለማየት የማያቋርጥ ትግል ይጠይቃል፡፡
   ጆርጅ ኦርዌል
- መንግስት ሲሳሳት፣ ትክክል መሆን አደገኛ ነው፡፡
   ቮልቴር

870 ሚሊዮን ብር ተመድቦለት፣ 5.6 ቢሊዮን ብር ፈጅቷል

በአፋር ብሄራዊ ክልል ከ11 አመታት በፊት የተጀመረውና ግንባታው በ3 አመታት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ታቅዶለት የነበረው የተንዳሆ የመስኖ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ከታቀደለት ጊዜ በ8 አመታት ዘግይቶ፣ ከተያዘለት በጀት 5 እጥፍ ያህል ፈጅቶ ተጠናቅቋል፡፡
በ1997 ዓ.ም የተጀመረው የተንዳሆ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክት፣ ግንባታው ለ8 አመታት ከመጓተቱ በተጨማሪ፣ 870 ሚሊዮን ብር ይፈጃል ተብሎ ቢታቀድም፣ ወጪው በአምስት እጥፍ ያህል በማደግ 5.6 ቢሊዮን ብር መድረሱን የውሃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስትር አስታውቋል፡፡
የተቋራጮች የልምድና የአቅም ማነስ፣ በፕሮጀክቱ ላይ በቂ ጥናቶች አለመደረጋቸውና ከፋይናንስ ጋር የተያያዙ ችግሮች፣ የመስኖ ግድቡ ከተያዘለት ጊዜ ዘግይቶ ለመጠናቀቁ ምክንያት መሆናቸውንም የውሃ፣ የመስኖና የኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ከበደ ገርባ ገልጸዋል፡፡
1.8 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የማጠራቀምና 60 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ያለው የተንዳሆ የመስኖ ግድብ፣ በአሁኑ ወቅትም 25 ሺህ ሄክታር የሸንኮራ አገዳና የ6 ሺህ አባወራዎችን የእርሻ ማሳዎች በመስኖ እያለማ እንደሚገኝም ተነግሯል፡፡

በቅርቡ በኦሮሞ አባገዳዎች ም/ቤት የአባዱላነት ማዕረግ በተሰጣቸው ባለሀብቱ አቶ ድንቁ ደያስ የተቋቋመውና በስሩ 5 ድርጅቶችን ያቀፈው ‹‹ሶሩማ ፋን ቢዝነስ ግሩፕ››፤ በተለያዩ  ማህበራዊ ሚዲያዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ እየተካሄደበት መሆኑን ገልፆ ጉዳዩን በህግ ለመፋረድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስታውቋል።
ሶደሬ ሪዞርት ሆቴል፣ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ፣ ሪፍት ቫሊ ሆስፒታል፣ ናፍያድ ት/ቤት፣ ኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ፤ ቀርሺ ማይክሮፋይናንስ የሚሉ የንግድ ድርጅቶችን በስሩ ያካተተው ቢዝነስ ግሩፑ፤ 10 ሺህ የሚደርሱ የሚደርሱ ሰራተኞችን እንደሚያስተዳድርም ተገልጿል፡፡
የቢዝነስ ግሩፑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ረታ በቀለ በፅ/ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ድርጅቶቹ ከመንግስት ጋር መልካም ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም በተለይ ሶደሬ ሪዞርትና ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ በመንግስት እንደተዘጉ ተደርጎ የተናፈሰው ዘገባ ሀሰተኛ መሆኑን ገልፀው ድርጅቶቹ መደበኛ አገልግሎታቸው እየሰጡ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡
“ከመንግስት ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፣ ከቀረጥ ነፃ እቃዎችን በማስገባት ጭምር መንግስት ድጋፍ እያደረገልን ነው” ያሉት ስራ አስኪያጁ፤ የተናፈሰው ዘገባ ምንጩ እንደማይታወቅና ጉዳዩን የኩባንያው የህግ ባለሙያዎች እየመረመሩት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የድርጅቶቹ ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስም፣ ሃገራቸውን እንዳልከዱና በውጭ ሃገር በህክምና ላይ መሠንበታቸውን ጠቁመው፣ በአሁን ወቅትም ህክምናቸውን አጠናቀው በአሜሪካ  ከሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ በትብብር በሚሠራበት ጉዳይ ላይ እየተመካከሩ እንደሆነ ዋና ስራ አስኪያጁ አስታውቀዋል፡፡
ተዘግቷል የተባለው ሶደሬ ሪዞርት ቀደም ሲል ግማሽ ድርሻው የመንግስት እንደነበር የጠቆሙት አቶ ረታ፤ በቅርቡ ባለሃብቱ ሙሉ በሙሉ ጠቅልለው መግዛታቸውንና አፈፃፀሙም እየተከናወን መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን፣ባልና ሚስት የገና በዓል ፌሽታ ወዳለበት አንድ አደባባይ በመኪና ይሄዳሉ፡፡
“የዘንድሮን ገና በደመቀ ሁኔታ ነው የምናከብረው” አለ ባል፡፡
“እንደሱ እንዳናደርግ እኔ ትላንት የገና ወጪ ስጠኝ ብልህ፣ እንደልማድህ ‹እሱን ለእኔ ተይው› አልከኝ” አለች ሚስት፡፡
“የልጆቹን ፍላጎት አንተ አታውቅም” ብልህ፣ “እንዴት? አባታቸው አይደለሁም?!” ብለህ ትቆጣለህ፡፡ አሁንም የገበያውን ነገር ካወቅኸው ገላገልከኝ”
ጥቂት መንገድ እንደሄዱ፣ አንድ የትራፊክ መብራት ጋ ይደርሳሉ፡፡ ባል ቀይ መብራቱን ጥሶ ይሄዳል፡፡
ትራፊክ ፊሽካ ይነፋል፡፡
ሹፌር ያቆማል፡፡
ለሚስቱ፤
“የዓመት ባል ገንዘብ ፈልጎ ነው እንጂ እኔ ምንም አላጠፋሁም!” ይላታል፡፡
“ቀይ መብራት ዘለህ መጥተህ፣‹እንዴት አላጠፋሁም› ትላለህ?”
“የአንቺን አላምንም፤ትራፊኩ የሚለኝን ልስማ!”
ትራፊኩ መጣ፡፡ ሹፌር መስተዋቱን ዝቅ አደረገ፡፡
ትራፊክ - “መንጃ ፍቃድ?”
መንጃ ፍቃዱን ጠየቀ፡፡
ሹፌር አሳየውና፤ “ምን አጠፋሁ ጌታዬ”
ትራፊክ፤ “ቀይ መብራት ጥሰዋል”
ሹፌር ፤“በጭራሽ አልጣስኩም!”
በመካከል ሚስት ትገባና፤
“እኔ ተው እያልኩት ነው የጣሰው፡፡ ግን ችግሩ እዚህ አገር፣ሰዎች ዶክተር ስለሆኑ የፈለጉትን ማድረግ የሚችሉ ይመስላቸዋል፡፡
ባል፤“ዝም በይ! አፍሽን ዝጊ! … እሺ ትራፊክ ይቅርታ አድርግልኝ”
ትራፊክ፤ “ጥፋትዎ ያ ብቻ አልነበረም፡፡ 30 ኪ.ሜ በሰዓት በሚነዳበት መንገድ፣50 ኪ.ሜ በሰዓት በመንዳትዎ ይጠየቃሉ፡፡”
ሚስት፤
“እኔ ቀስ ብለህ ንዳ ብዬው እምቢ ብሎኝ ነው - ነግሬዋለሁ!”
ባል፤ “አንቺ ሴትዮ፤አፍሺን ዝጊ ብያለሁ!!”
ትራፊኩም፤ “እመቤት፤ሁልጊዜ እንደዚህ ነው የምትወያዩት?”
ሚስት፤
“ኧረ ጌታዬ፤ሌላ ጊዜ ጨዋ ነው፡፡ እንዲህ ሲጠጣ ብቻ ነው እንደዚህ የሚናገረኝ!”
ትራፊክ፤
“አሃ!!”
*   *   *
 አውቃለሁ፣ በቅቻለሁ ብሎ ሁሉ እኔ እንዳልኩት መሆን አለበት የማለት ግትርነት ደግ አይደለም፡፡ የየትኛውም ሙያ ባለቤት እንሁን፡፡ ከህግ በላይ አይደለንም፡፡ በሙያ ክህሎት አገኘን ማለት ከሀገርና ከሀገሬው በላይ ሆንን ማለት አይደለም፡፡ ዝርዝር ጉዳዮች ለዐቢዩ ህግ ተገዢ መሆናቸውን በፍፁም መዘንጋት የለብንም፡፡ የትራፊክ ህግን ማክበር ከሙያችን በላይ የሆነውን ያህል፤ ለትራፊኩ የእኛን ሙያ ማክበር፣ ከሙያው በላይ መከበር እንዳለበት፣ አሊያም እኩል የሙያ አክብሮት ሊኖር እንደሚገባው መገንዘብ እንዳለበት ሊያስተውል ተገቢ ነው፡፡
በቤተሰብ ህግም የባል ሙያ መከበሩ እንዳለ ሆኖ፣ ሚስት የምትለውን አለማዳመጥ ወይም መናቅ ኪሳራ ነው!!
ይህ ነገር በበዓል ሰሞን በጣም ግዘፍ ይነሳል! መደማመጥ በበዓል ሰሞን ምንዛሪው ብዙ ነው። በአንድ ወገን ባህል አለ፡፡ በሌላ ወገን ዘመናዊ ስሜት አለ፡፡ ለምሳሌ፣ በአውሮፓውያን የልደት ዛፍ (X-mas Tree) እና በእኛ ቄጤማና ነጭ አረቄ ስሜት መካከል እንደምንገነዘበው፡፡ በልጆቻችን ላይ የሚፈጠረው ስሜት፣ በወላጆቻችን ላይ የሚደረተው ስሜት፣ ማንም ስለ ምንም ማብራሪ ሳይሰጥ፣ በዘፈቀደ መከበሩና እንደፈረደብን ሳንወያይበት፣ በተድላና በደስታ ማለፋችን፤ የአልፋ - ኦሜጋ ሕግ መሆኑ ግራ ያጋባል፡፡
ባህልን መጠበቅ ግድ ነው፡፡ ባህልን መከለስ ምርጫ ነው፡፡ የሁለቱን ልዩነት ማወቅና ማስተዋል፣ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋ ግዴታ ነው!
የገና በዓልን ስናስብ የክርስቶስን ልደት እናስብ፡፡ የእኛን “ልደት”ን ግን በፍፁም፣ መርሳት የለብንም። በየቀኑ መወለድ፣ በየዕለቱ ማደግ መቼም ያስተዋልነው ጉዳይ ነው፡፡ የየዕለት ውልደታችን ውጤት እገና ዘንድ እሚደርሰው፣ የዓመት ውሎአችንን ጠቅልሎ ነው፡፡ ስለዚህም ከተወለድን አይቀር በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ባህላዊ መንፈሱ የተሟላ ልደት ይሆንልን ዘንድ እንመኝ! “ከሰማያተ - ሰማያት ወርጄ፣ ከድንግል ማሪያም ተወልጄ አድንሃለሁ” የሚለውን አስታውሶ፣ በስፋት መጠቀም ነው፡፡ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው!” ማለትም ያባት ነው፡፡
በየወቅቱ መወለድ የአዳጊ ልጅ ባህሪ ነው፡፡ እያንዳንዷን እድገት ሳይታክቱ መመርመር ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ለመወለድ ሰብዓ ሰገሎችን ሳንጠብቅ፣ ለየራሳችን ስራ፣ ጥረት፣ ትግል፣ ዕምነት ቦታ መስጠት አገርንና ህዝብን ያሳብባል፡፡ በየዕለቱ ሁላችንም አራስ ነን፡፡ ነገ ግን ወጣት፣ ጎልማሳና አዋቂ እንሆናለን፡፡ በሁሉም ገፅታችን አገራችን ትፈልገናለች!!
የለውጥ አቅም ከለመድነው መፋታት ነው፡፡ ከለመድነው መላቀቅ፣ የአዲስ አዕምሮ ቅያስ ይፈልጋል፡፡ ቅያሱ መንገድ የት እንደሚያደርሰን ለማወቅ፣ የእንቅፋቶቹን ምንነት፣ የእኛን ምርጫና ግባችንን ማወቅ፣ የእኛን ቀጣይ - ዘዴ መቀየስ፤ የለውጥ ሙከራ ባይሳካ ደግሞ መዘጋጀት ዋና መሆኑን … ማስተዋል ብልህነት ነው፡፡ ያም ሲለመድ ደግሞ እንደ ህይወት ይኖራል፡፡ “ልማድ ሲሰለጥን ተፈጥሮ ይሆናል” የሚለው አባባል ግንዛቤ ውስጥ ይገባል የሚባለው ይሄኔ ነው!! ሁሉንም በቀናው ሂደት ይባርክልን፡፡ ራሳችንን ከአደጋ እንጠብቅ!
መልካም የገና በዓል
 ለክርስትና ዕምነት ተከታዮች!!