Administrator

Administrator

በኢትዮጵያ የደም ግፊት ያላባቸው ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። ይህ ተላላፊ ያልሆነው የጤና ችግር ከወጣት አስከ አዋቂዎች ላይ እየተከሰተ ሲሆን፣ ኣሳሳቢነቱ ከፍተኛ ሆኗል።

የአኗኗር ዘይቤ፣ አመጋገብ፣ እንቅስቃሴ አለማድረግ እና ሌሎችም ለደም ግፊት ምክንያት ከሚባሉት ዋነኞቹ ሲሆኑ፣ ጤናማ አኗኗር በመከተል እራስን ከደም ግፊት ለመጠበቅ እና መቆጣጠር እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከእነዚህም መካከል የአመጋገብ ሥርዓትን በማስተካከል እና ጤናማ በማድረግ ደግም ግፊትን በሚፈለገው መጠን ውስጥ ማድረግ ይቻላል። ለዚህም ከሚመከሩት የምግብ አይነቶች መካከል አንዱ ቀይ ሥር ነው።

አንዳንዶች ቀይ ሥር እንዲሁ ለቀለሙ እንጂ የሚሰጠው የምግብነት ጠቀሜታ ይህን ያህል ነው ሲሉ ቆይተዋል። ባለሙያዎች ግን ቀይ ሥር ለሰውነት ከሚሰጠው ብርታት እና ጥንካሬ ባሻገር የደም ግፊትን በመቀነስ በኩልም ጠሜታ አለው ይላሉ።

ቀይ ሥር የደም ግፊትን ዝቅ ከማድረግ እና እድሜ እየገፋ ሲሄድ የእእምሮ ጤናን ከመጠበቅ በተጨማሪ በርካታ የጤና ጠቀሜታዎች አሉት።

የዚህን አትክልት ለየት ያለ ጠቀሜታን በተመለከተ የሥነ ምግብ እና የጤና ባለሙያዎች መረጃዎችን እያጋሩ ሲሆን፣ በዕለት ከዕለት ምግባችን ውስጥም ቀይ ሥርን እንድናካትት እየመከሩ ነው።

አምስቱ የቀይ ሥር የጤና ጥቅሞች፡

1. ጎጂ ንጥረ ነገሮችን ከሰውነት ማስወገድ
በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው ተፈጥሯዊ በጣም ደማቅ ቀለም ቤታላይን ይባላል፤ ይህም በሰውነት ውስጥ የተከማቹ ጎጂ ንጥረ ነገሮችን የማስወገድ አቅም አለው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ጣልያን ውስጥ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው ቤታላይን በአንጀት ውስጥ ሊከሰቱ የሚችሉ የካንሰር ህዋሳትን የመግደል አቅም እንዳለው ቢያንስ በቤተ ሙከራ ደረጃ በተደረገ ጥናት ለማወቅ ተችሏል።

ቤታላይን በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኝ ብቸኛው ጠቃሚ ንጥረ ነገር አይደለም። ቀይ ሥር የደም ዝውውር በበቂ ሁኔታ ወደ ተለያዩ የሰውነታችን ክፍሎች እንዲደርስ በሚያደርገው ለጤና ጠቃሚ በሆነው ናይትሬ በእጅጉ የበለፀገ አትክልት ነው።

ከአስር ዓመታት በላይ ቀይ ሥር በአትሌቲክስ ስፖርተኞች ውጤት ላይ ሊኖረው ስለሚችለው ጠቃሚ አስተዋጽኦ ሲያጠኑ የቆዩት በዩናይትድ ኪንግደም ኤክስተር ዩኒቨርስቲ የፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ኤንዲ ጆንስ አትክልቱ ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ይመሰክራሉ።

ከቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው “ናይትሪክ ኦክሳይድ የደም ሥሮችን በማስፋት የደም ዝውውርን እንዲቀላጠፍ በማድረግ ተጨማሪ ኦክስጂን ወደ ህዋሶቻችን እንዲደርስ ያደርጋሉ” በማለት ፕሮፌሰሩ ገልጸውታል።


2. ለደም ግፊት እና ለልብ ጤና
በየለቱ የተወሰነ መጠን ያለው የቀይ ሥር ጭማቂ መውሰድ የደም ግፊት ባለባቸው ሰዎች ላይ የግፊት መጠናቸውን በመቀነስ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው።

አንድ ጥናት እንዳመለከተው ለተወሰኑ ሳምንታት በየዕለቱ ሁለት ፍሬ ቀይ ሥር መመገብ የደም ግፊትን በአማካይ አምስት ሚሊሜትር ሜርኩሪ እንዲቀንስ ያደርጋል።

ስለዚህም አንድ የደም ግፊት ያለበት ሰው በዚህ መጠን ግፊቱን መቀነስ ከቻለ እና በዚሁ ደረጃ መቆጣጠር ከተቻለ ሊከሰት የሚችልን የልብ ድካምን እና ስትሮክን በ10 በመቶ መቀነስ ይቻላል።

ቀይ ሥር የደም ግፊትን በመቀነስ ረገድ ውጤቱ በአጭር ጊዜ የሚታይ ነው። በጥናት እንደታየውም የደም ግፊት ያለባቸው ሰዎች ላይ ቀይ ሥር ከተመገቡ በኋላ በተወሰነ ሰዓት ውስጥ ውጤቱን ማየት ይቻላል።

ይህም የሚከሰተው በቀይ ሥር ውስጥ ያለው የናይትሪክ ኦክሳይድ ንጥረ ነገር የደም ሥሮችን እንዲሰፉ በማድረግ ደም በሰውነት ውስጥ በቀላሉ እንዲዘዋወር ማድረግ ስለሚያስችል ነው።

3. የቀይ ሥር ጥቅም ለአንጎል
ቀይ ሥር የደም ሥሮችን ለቀቅ ብለው ደም እንደ ልብ እንዲዘዋወር በማድረግ ወሳኝ የሰውነታችን ክፍሎች የሚፈልጉትን ያህል የደም ፍሰት ስለሚያገኙ ጤናማ ተግባራቸውን በቀላሉ እንዲያከናውኑ ያደርጋል።

በዚህም ቀይ ሥር ወደ በአንጎላችን ውስጥ በቂ የደም ዝውውር እንዲኖር ስለሚያደርግ፣ የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት ሰዎች የማስታወስ ችሎታቸው እንዲዳብር ከማድረግ በተጨማሪ ፈጣን ውሳኔዎችን ለመስጠት ብቁ ያደርጋቸዋል።

ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ ቀይ ሥርን አዘውትረው የሚመገቡ ሰዎች የአንጎላቸውን ጤና ለመጠበቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚጠቁሙ ባለሙያዎች አሉ።

የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣትን ከአካላዊ እንቅስቃሴ ጋር ማጣመር ከተቻለ ደግሞ የተሳካ የደም ዝውውር ስለሚኖር በአካላዊ እና በአእምሯዊ ጤና ላይ አውንታዊ ጣምራ ውጤት ይኖረዋል።


4. ቀይ ሥር ለአፍ ጤና
ለአስር ቀናት በቀን ሁለት ጊዜ የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት በአፋችን ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ ጠቃሚ ባክቴሪያዎችን ይዘት ለማሻሻል እንደሚረዳ አንድ ጥናት አመልክቷል።

በጥናቱ ተሳታፊዎች ላይ ከባክቴሪያዎች ጋር በተያያዘ ከደም ሥር እና ከአንጎል ጤና ጋር የተያያዙ በጎ ለውጦች ከፍ ሲሉ፣ ከበሽታ እና ከእብጠቶች ጋር የሚያያዙ ጎጂ ባክቴሪያዎች እንዲቀንሱ ያደርጋል።

ዕድሜ ሲገፋ እየቀነሰ የሚሄደውን የሰውነታችንን ናይትሪክ ኦክሳይድ የማምረት አቅምን ለመከላከል የሚያስችሉ በአፍ ውስጥ የሚገኙ የጤናማ ባክቴሪያዎች መጠንን ቀይ ሥር እንዲጨምር በማድረግ የተሻለ ጤናማ እና ረጅም ዕድሜ እንዲኖረን ያደርጋል።

5. ቀይ ሥር ለስፖርታዊ እንቅስቃሴ ስኬት
የቀይ ሥር ሌላኛው ጠቀሜታ ደግሞ ከባድ ኃይል እና ጉልበት በሚፈልጉ ሥራዎች እና ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ለሚሳተፉ ሰዎች በሚሰጠው ወሳኝ ንጥረ ነገር ነው።

በተለይ በሩጫው መስክ ለተሰማሩ አትሌቶች ብቃታቸውን ከፍ በማድረግ ፈጣን እንዲሆኑ አስተዋጽ እንዳለው በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥቃት አመልክቷል።

በቀይ ሥር ምክንያት “የሰውነት ጡንቻዎች በናይትሪክ ኦክሳይድ አማካይነት የበለጠ ኦክስጂን በማግኘት በውስጣቸው በበቂ ሁኔታ እንዲሰራጭ በማድረግ ውጤታማ ያደርጋል” ይላሉ ጆንስ።

በአውሮፓውያኑ 2009 በተደረገ ጥናት የቀይ ሥር ጭማቂ መጠጣት ከባድ ልምምድ በሚደረግበት ጊዜ አካላዊ ጽናትን በ16 ከመቶ ከፍ በማድረግ ውጤታማ ያደርጋል።

ጥናቱ እንደሚያመለክተው በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኘው ናይትሪክ ኦክሳይ ስፖርተኞች በልምምድ ጊዜ የሚጠቀሙትን የኦክስጂን መጠን በመቀነስ፣ ድካም ላይ የሚደርሱበትን ሂደት ያዘገየዋል።

በዚህም ምክንያት ቀደም ሲል ብዙም ፈላጊ ያልነበረው የቀይ ሥር ጭማቂ አሁን በበርካታ አትሌቶች ዘንድ ተፈላጊው መጠጥ ሆኗል።

ይህ አትክልት ኃይልን ከማዳበር በተጨማሪም በፍጥነትም ላይ ከፍተኛ ውጤትን አሳይቷል። በ2012 (እአአ) በተደረገ ጥናት በ5 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ላይ ከተሳተፉ አትሌቶች መካከል ቀይ ሥር የተመገቡት ካልተመገቡት ይልቅ የመጨረሻውን 1.8 ኪሎ ሜትር በአምስት በመቶ ፈጣን ከመሆናቸው በተጨማሪ ያሳዩት ድካም ዝቅተኛ ሆኖ ታይቷል።

በውድድር ወቅት ውጤታማ ለመሆን ስፖርተኞች ቀይ ሥርን ከውድድሩ ጅማሬ ከሰዓታት ቀደም ብለው መመገብ ወይም ጭማቂውን መጠጣት የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል ይባላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ኤክስተር ዩኒቨርስቲ የፊዚዮሎጂ ፕሮፌሰሩ ኤንዲ ጆንስ “በቀይ ሥር ውስጥ ያለውን ጠቃሚ ንጥረ ነገር ናይትሪን ሰውነታችን ጥቅም ላይ ለማዋል ከ2 አስከ 3 ሰዓታት ስለሚፈጅ” ቀደም ብሎ መውሰድን ይጠይቃል ይላሉ።

ምን ያህል የቀይ ሥር መመገብ ይመከራል?
የሚፈለገውን ውጤት ከቀይ ሥር ለማግኘት ሁለት ወይም ሦስት መካከለኛ መጠን ያላቸውን የቀይ ሥሮችን በመፍጨት በጭማቂ መልክ መጠጣት እንደሚጠቅም ጆንስ ይመክራሉ።

“በየዕለቱ እና በየሳምነቱ ሰውነታችን የሚያስፈልገውን የናይትሬት ፍጆታ ለማሻሻል የምንፈልግ ከሆነ፣ ቀይ ሥርን በመደበኛነት መመገብ ጠቃሚ ውጤት ይኖራዋል” ይላሉ ዶክተሩ።

ከቀይ ሥር ለመጠቀም እንዴት ይዘጋጃል?
ከቀይ ሥር ከሚገኘው ንጥረ ነገር በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ ለመሆን በዝግጅት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለብን ይመከራል።

በቀይ ሥር ውስጥ የሚገኙት የናይትሬት ንጥረ ነገሮች በውሃ በቀላሉ የሚሟሙ በመሆናቸው፣ አትክልቱን በምናበስልበት ጊዜ በጣም መጠንቀቅ አለብን።

ቀይ ሥርን መቀቀል የናይትሬት ንጥረ ነገሮች ሟሙተው በውሃ ውስጥ ሊጠፉ ስለሚችሉ፣ በምንመገበው ጊዜ ጠቃሚውን ናትሬት በሚጠቅመን መጠን ላናገኘው እንችላለን።

“ቀይ ሥርን ከቀቀልን በኋላ የሚቀረውን ውሃ የምንደፋው ከሆነ፣ አብዛኛውን የናይትሬት ንጥረ ነገርን ሳንጠቀምበት እናጣዋለን” ይላሉ ዶ/ር ጆንስ።

ስለዚህም ለተለያዩ የጤና ጥቅሞቹ፣ ለጥንካሬ እና ለፍጥነት ቀይ ሥርን በመመገብ አትክልቱ የሚሰጠውን ተፈጥሯዊ ጠቀሜታን ሙሉ ለሙሉ ለማግኘት ባለበት ሁኔታ መመገብ ይመከራል።

ቀይ ሥር ተከትፎ በጥሬው፣ በተወሰነ ደረጃ ተጠብሶ ወይም ተፈጭቶ በጭማቂ መልክ ጥቅም ላይ ከዋለ ተፈጥሯዊ ይዘቱን ሳይለቅ የሚፈለገውን ንጥረ ነገር በማግኘት ሰውነታችን ተጠቃሚ ይሆን።

Monday, 11 November 2024 00:00

ተዋት ትኑርበት!

(ስለ እጅጋየሁ ሽባባው ክብር የተጻፈ)

አብርሀም ገነት


ያን ሰሞን በልቦናዬ የሚመላለሱት የእጅጋየሁ ሽባባው ዘፈኖች ነበሩ፡፡ ሳልሰለች ዘፈናቸውን በተደጋጋሚ ከምሰማቸው አርቲስቶች አንዷ እጅጋየሁ ናት፡፡ ዛሬም፡፡ አርቲስት ብዬ በሙሉ ልብ ከምጠራቸው በዘመኔ ከማውቃቸው ኢትዮጵያውያን አንዷ ጂጂ ናት፡፡ ለእኔ አርቲስት የሚያስተጋባ ሳይሆን የሚፈጥር ነው፡፡
ቀኔን እንዳዋዋሌ ውዬ፣ ራቴን በልቼ ወደ መኝታዬ እሄዳለሁ፡፡ ከመተኛቴ በፊት ግን አንድ ሁነኛ ነገር ይቀረኛል፡፡ እሱም ልብሴን አወላልቄ አልጋዬ ውስጥ ገብቼ አንድ ሁለት የጂጂን ዘፈኖች አይኖቼን ከድኜ መስማት ነው፡፡ ያን ሰሞን፡፡ የጂጂን ለስላሳና አባባይ ዘፈኖች አይኖቼን ጨፍኜ ስስማ ነፍሴ ወደሆነ አለም ትንሳፈፋለች፡፡ ያለሁበትን እረሳለሁ፡፡ ለደቂቃዎች ከገላዬ ተነጥዬ ነፍስና ምናብ እሆናለሁ፡፡ ጠዋት ተነስቼ አልጋዬን እያነጣጠፍሁ ቀኔን ስጀምር የማፏጨው ከጂጂ ዘፈኖች አንዱን ነው፡፡ የጂጂ ግጥሞች ውብ ናቸው፣ ዜማዎቿ ረቂቅ፡፡ ድምጿ ነፍስን ይዳብሳል፡፡ ጂጂ ጥልቅ ናት፡፡ ብርድልብስና ጨለማ ተከናንቤ አይኖቼን ከድኜ ዘፈኖቿን ስሰማ ፍፁም ፍስሃ ውስጥ እገባለሁ፤ አንዳንዴ የዘፈኑን ምት ተከትዬ በተኛሁበት ገላዬን እየሰበቅሁ በለሆሳስ እደንሳለሁ፤ አንዳንዴ እንባ ከአይኔ ኮለል እያለ በፀጥታ ላለቅስም እችላለሁ፡፡ ነፍሴ በሁሉም ትረካለች፡፡ በዚህኛው እንደዚህ በዚያኛው እንደዚያ እሆናለሁ ብዬ ዘፈኖቹን የማልጠቅስላችሁ የቱን አንስቼ የቱን እተዋለሁ ብዬ ነው፡፡ የምናውቅ እናውቃለን፣ ዝም ብሎ ማጣጣም ነው፡፡ የጂጂ ዘፈኖች ለጆሮና ለነፍስ የተሰሩ ናቸው፡፡ የሙዚቃ ባለሙያው ሰርፀ ፍሬስብሀት አንድ ጊዜ፤ “ሙዚቃ በመሰረቱ የጆሮ ነው” ሲል ሰምቼዋለሁ፡፡ በደንብ እስማማለሁ፡፡
የሆነ ጊዜ ስለ ጂጂ ከሙዚቃው አለም መጥፋት ሰዎች በዩቲዩብና በማህበራዊ መገናኛዎች እየተቀባበሉ ሲያወሩ ሰማሁና ስለ እሷ የበለጠ ለማወቅ ፈለግሁ፡፡ በሬዲዮና በምስል ያደረገቻቸውን ጥቂት ቃለ መጠይቆች ሰማሁ፡፡ በደንብ የሰማሁት ሸገር ሬዲዮ ላይ ከመአዛ ብሩ ጋር ያደረገቺውን ቃለ መጠይቅ ነው፡፡ የጂጂን ማንነት መዘንሁ፡፡ ጂጂ ጎበዝ አርቲስት ብቻ ሳትሆን ማራኪ ሰብዕና ያላት ሴት ሆና አገኘኋት፡፡ ጂጂ ትሁት ናት፣ ምርጥ ምርጥ ስራዎችን ብትከይንም ራሷን ከፍ ከፍ አድርጋ አትኩራራም፡፡ ራሷን ከሌሎች ብቁ አርቲስቶች አንፃር ዝቅ አድርጋ ነው የምታቀርበው፡፡ አስቴር አወቀን ታደንቃለች፡፡ ከማሪቱ ለገሰ ጋር ብትዘፍኝስ ስትባል፤ “ውይ ድምጥማጤን ነው የምታጠፋው!” አለች፡፡ ይሄን ይሄን ስሰማ ጂጂን በዘፈኗ ብቻ ሳይሆን በሰብዕናዋም ወደድኳት፡፡
ጂጂ አሁን መዝፈን ከተወች ረጅም ጊዜ ሆኗታል፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳልሆነች ሰዎች ሲናገሩ እንሰማለን፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አሜሪካ ቤቷ ድረስ እየሄዱ እያገኟት ቆይታቸውን በምስል ቀርፀው ዩቲዩብ ላይ ሲለቁ አያለሁ፡፡ የእውነት ለጂጂ አስበውላት ይሆን ወይስ አጋጣሚውን ተጠቅመው ራሳቸውን ለማሳወቅ? ወይም ለመሸቀል? እሷስ በዚህ ደስተኛ ናት? እድሜ የማይድጠው፣ ጊዜና ሁኔታ የማያነሳውና የማይጥለው ሰው የለም፡፡ የጂጂም ነገር ከዚህ የተለየ ትንግርት የለውም፡፡ ጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለቺም ምናምን እያሉ፣ ጂጂን እየፈለጉ እየቀረፁ አደባባይ ላይ ማስጣት የግል ህይወቷን መጋፋት ነው፡፡ መረዳት ካስፈለጋትና ቅን ልብ ያለው ካለ፣ ያለምንም የፎቶና የምስል ጋጋታ እገዛውን በፀጥታ ማድረግ ይችላል፡፡ ምናልባት እሷ ምንም አትፈልግም፡፡ ምናልባት ጂጂ ስለ እሷ ደህና አለመሆን ከምናወራው ከብዙዎቻችን በተሻለ መረጋጋትና የአእምሮ ሰላም ውስጥ ይሆናል ያለቺው፡፡
በቅርብ ጊዜ አንድ ሰው ቤቷ ሄዶ አግኝቷት ቀርፆ የለቀቀውን ምስል አይቻለሁ፣ ጤነኛ ናት፣ ከለዛዋና ከትህትናዋ ጋር ናት፡፡ ከዚህ ጀርባ ያለውን ገመናዋን ደግሞ ለራሷና ለቅርብ ቤተሰቦቿ መተው ነው ያለብን፡፡  ቀሪ ዘመኗን በሰላም ልትኖር ይገባታል፣ የግል ህይወቷን ለራሷ ልንተውላት ይገባል፡፡ ደግሞስ ጂጂ በሙዚቃ ስራዋ የግድ መመለስ አለባት? በህይወት እስካለች ድረስ ሁልጊዜም የግድ መዝፈን አለባት? የህይወት ግቧን በጊዜ አጠናቃ ከሆነስ? ከበቃትስ? ሁላችንም በየተሰማራንበት ስራ በየአመቱ ብንመነደግ እንወዳለን፡፡ ነጋዴ ሁልጊዜ ትርፍ ቢያፍስ ደስ ይለዋል፡፡ ደራሲ በየአመቱ ቢያሳትም፣ ሙዚቀኛ በየአመት በአሉ ዘፈን ቢለቅ አይጠላም፡፡ ግን ሁልጊዜ እንደምኞታችን አይሆንም፡፡ ሁኔታዎች መሻታችንንና ጥረታችንን አግዘው አብረውን የሚፈሱበት ጊዜ አለ፡፡ በዙሪያችን ያለው ሁሉ ለእኛ ስኬት የሚያደላበት ወቅት አለ፡፡ የተገላቢጦሽ የሚሆንበት ወቅትም አለ፡፡ የሚሰራበት ጊዜ አለ፣ ዝም ተብሎ የሚኖርበት ጊዜ አለ፡፡ ጂጂ ምርጥ ምርጥ ዘመን ተሻጋሪ ዘፈኖችን አበርክታልናለች፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ላይ የራሷን መልካም አሻራ አሳርፋለች፡፡ አሁን ዝም ብላ በሰላምና በዕረፍት ኑሮዋን የምትኖርበት ጊዜ ይመስለኛል፡፡ ይሄም ለእሷ ይገባታል፡፡ ሰላም ለጂጂ ባለችበት እመኝላታለሁ፡፡
(ሚያዚያ 2013 ዓ.ም. ባህር ዳር)

የአፍሪካ መሪዎች ብሩህ ተስፋ
    ዶናልድ ትራምፕ ከዋይት ሃውስ ከለቀቁ ከአራት ዓመት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በመመረጥ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ይህን ታሪካዊ ድል ተከትሎም በርካታ የአፍሪካ መሪዎች ከትራምፕ ጋር በቅርበት ለመስራትና ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ትስስር የበለጠ ለማጠናከር ተስፋና ጉጉት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ የትራምፕ ዳግም መመረጥ አፍሪካን አሜሪካን  ወደተሻለ ቅርርብና ትብብር ሊመራ እንደሚችልም ተገምቷል፡፡
ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት በማስተላለፍ ከቀዳሚዎቹ የአፍሪካ መሪዎች የአገራችን  ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ “በምርጫ ድልዎትና ወደ ስልጣን በመመለስዎ እንኳን ደስ አለዎት ማለት እፈልጋለሁ” ሲሉ በኤክስ ገፃቸው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ፤ “በእርስዎ የሥልጣን ዘመን የሁለቱን አገራት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር በጋራ የምንሰራበትን ጊዜ እጠብቃለሁ” ብለዋል፡፡
የዚምባቡዌው ፕሬዚዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በበኩላቸው፤ አገራቸው ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር በትብብር ለመሥራት ያላትን ፈቃደኝነት ገልፀዋል፡፡ “ዚምባቡዌ የተሻለች፤ የበለጠ የበለፀገችና ሰላማዊ ዓለም ለመገንባት ከእርስዎና ከአሜሪካ ህዝብ ጋር ለመስራት ዝግጁ ናት” ብለዋል፤ ፕሬዚዳንቱ በመልእክታቸው፡፡


የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ቦላ ቲኑቡ፣ ለተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያለዎት መልእክት፤ “በአንድ ላይ የኢኮኖሚ ትብብርን ማሳደግ፤ ሰላምን ማጎልበትና ዓለማቀፍ ተግዳሮቶችን መፍታት እንችላለን፡፡” ብለዋል፡፡
የሩዋንዳው ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለተመራጩ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባስተላለፉት የእንኳን ዳግም ተመረጡ መልዕክት፤ በቀጣዮቹ ዓመታት ለአገሮቻችን የጋራ ጥቅም ከእርስዎ ጋር ለመሥራት በጉጉት እጠብቃለሁ ብለዋል፡፡
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው፤ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን “የጋራ ተጠቃሚነት አጋርነት” ለመቀጠል በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡
በቅርቡ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ግብዣ በአሜሪካ ጉብኝት ያደረጉት የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ ለዶናልድ ትራምፕ  ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት፣ “ባለ ራዕይ፣ ደፋርና ፈጠራ የታከለበት አመራር ያላቸው” ሲሉ አድንቀዋቸዋል፡፡
ከመሪዎች ባሻገር አፍሪካውያንም የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤትን አስመልክቶ በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡ አብዛኞቹች ውጤቱ ለአሜሪካ ትልቅ ድል መሆኑን ጠቁመው፤ ዶናልድ ትራምፕ በዓለም ላይ እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን እንደሚያስቆሙ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡ በአንፃሩ ሌሎች ደግሞ ትራምፕ ድሉን የተቀዳጁት የተሻለ ተቀናቃኝ ስላልገጠማቸው ነው ብለዋል፡፡ ለትራምፕ አሸናፊነት የአሜሪካውያንን ለሴት ፕሬዚዳንት ዝግጁ አለመሆንን በምክንያነት የጠቀሱም አልጠፉም፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ምን አሉ?
ለዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ያስተላለፉት ቭላድሚር ፑቲን፣ ተመራጩን ፕሬዚዳንት “ደፋር” ሲሉ አሞካሽተዋል። የሩሲያው ፕሬዚዳንት በሶቺ ከተማ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ትራምፕ በዋይት ሃውስ በነበሩበት የመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከየአቅጣጫው ጫና በዝቶባቸው እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም እሠራለሁ ማለታቸው “ቢያንስ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል” ሲሉም ፑቲን በንግግራቸው አክለዋል። ባለፈው ሐምሌ በዶናልድ ትራምፕ ላይ የተፈጸመውን የግድያ ሙከራ በተመለከተም ሲናገሩ፤ “በእኔ አስተያየት በጣም ትክክለኛ በሆነ መንገድ አንድ ደፋር ሰው ማድረግ ያለበትን አድርጓል” ሲሉ ፑቲን ለትራምፕ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡ ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ የተጠየቁት ፑቲን፤ “ዝግጁ ነን፣ ዝግጁ ነን” ሲሉ መልሰዋል።
ትራምፕ ከፑቲን ጋር ለመነጋገር መዘጋጀታቸውን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ  ለኤንቢሲ ኒውስ በሰጡት ቃል፤ “የምንነጋገር ይመስለኛል” ብለዋል። ይህ በዚህ እንዳለ፣ በዩክሬንና በአውሮፓ የሚገኙ በርካቶች፣ ትራምፕ ወደ ኪዬቭ የሚላከውን የአሜሪካ ወታደራዊ እርዳታ ሊገቱ ወይም ሊያዘገዩ ይችላሉ የሚል ጭንቀት እንደገባቸው ተዘግቧል።
 የትራምፕን ድል “በቮድካ” እንዳከበሩ የገለጹት የሃንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን በበኩላቸው፤ አሁን አሜሪካና አውሮፓ በንግድ መስመር ላይ ከባድ ንግግሮች ይገጥማቸዋል ብለዋል። የትራምፕ የቅርብ አጋር የሆኑት ኦርባን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫው፤ “ከአሜሪካ ጋር የሚኖረው የንግድ ጉዳይ ከመነሳቱም በላይ ቀላል አይሆንም” ብለዋል።

የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ምክክር
50 የሚደርሱ  የአውሮፓ መሪዎች የዶናልድ ትራምፕ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጥ በአህጉሩ ላይ የሚፈጥረውን ተጽዕኖ በተመለከተ መመክራቸው ተዘግቧል፡፡ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ በሃንጋሪ ቡዳፔስት በተደረገው ስብሰባ ላይ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮልድሚር ዘለንስኪና የኔቶ ዋና ፀሀፊ ማርክ ሩትን ጨምሮ የአውሮፓ ሀገራትና ድርጅቶች መሪዎች ተገኝተዋል፡፡
መሪዎቹ በሩስያ ጉዳይ በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የስልጣን ዘመን እንዳለው ጠንካራ የጋራ አቋም እንዲንጸባርቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት ኔቶ ዋና ጸሀፊ ማርክ ሩት በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ሩሲያ ለሰሜን ኮሪያ የተለያዩ የሚሳኤልና የሳተላይት ቴክኖሎጂዎችን በመስጠት በምላሹ ከፒዮንግያንግ ወታደራዊ ድጋፍ እያገኘች ነው፤ ይህ ለአውሮፓ የኔቶ ክፍል ብቻ ሳይሆን ለአሜሪካ ደህንነትም ከፍተኛ ስጋት ነው” ብለዋል፡፡
ትራምፕ በመጀመርያው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው  የኔቶ አባል ሀገራት ለድርጅቱ የመከላከያ ወጪ የሚጠበቅባቸውን ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት 2 በመቶ እና ከዛ በላይ እንዲያወጡ እንዲሁም ከአሜሪካ ወታደራዊ እገዛ ጥገኝነት እንዲላቀቁ በጥብቅ ይገፋፉ ነበር፡፡ ይህንኑ ሀሳብ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርልስ ሚሼል በስብሰባው ላይ ያነሱ ሲሆን፤ አህጉሩ በአሜሪካ ወታደራዊ ድጋፍና የኔቶ መዋጮ ላይ ጥገኛ ከመሆን መላቀቅ አለበት ብለዋል፡፡
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ከአውሮፓ ጋር ከሚኖረው የንግድ ጦርነት አንስቶ ከኔቶ ለመውጣትና ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት መሰረታዊ የሆነ የድጋፍ ለውጥ እንደሚያደርጉ ዝተዋል፡፡ ይህም በመላው አውሮፓ በሚገኙ ሀገራት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያስከትል እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡


በ2018 የትራምፕ አስተዳደር የውጭ ምርቶች በአሜሪካ አጋሮች ቢመረቱም ለአሜሪካ ብሄራዊ ደህንነት አስጊ ናቸው በሚል በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት በሚመረቱ የብረትና አሉሚኒየም ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ አድርጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል፤ የአውሮፓ ሀገራት ትራምፕ የዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም በሚያደርጉት ጥረት ለሩስያ ሊያደሉ እንደሚችሉ ስጋት አላቸው፡፡ የአውሮፓ አገራት  መሪዎች የተሰባሰቡበትን ጉባኤ ያዘጋጀችው ሀገር ሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን፣ ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ከትራምፕ ጋር በስልክ እንደተነጋገሩና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ትልቅ እቅድ እንዳላቸው ከስብሰባው በፊት ተናግረዋል፡፡
የአሜሪካ ምርጫ ውጤት በዩክሬንና በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት፣ በስደት እንዲሁም የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከቱ ጉዳዮች ለሚቀጥሉት አመታት በአውሮፓ አጠቃላይ ግንኙነትና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡

Saturday, 09 November 2024 12:52

የወቅቱ ጥቅስ

“እንኳንስ ነጠላ አግኝታ፣ ድሮም ዘዋሪ እግር ነው ያላት፡፡” - አገርኛ

አንድ አባ ዳካ የሚባሉ  በሠፈር ባገሩ በጨዋታና በነገር አዋቂነታቸው የታወቁ አዛውንት በየጊዜው በየዕድሩ፣ በየሰንበቴውና በየድግሱ ሁሉ እየተገኙ በሚያጋጥማቸው ነገር ላይ  ይተርባሉ፣ ወግ ያወጋሉ፣ ቀልድ ይቀልዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው አባባላቸውን እየጠቀሰ፤ “አባ ዳካ እንዲህ አሉ” እያለ ይተርታል፡፡ አለቃ ገብረ- ሃና እንዲህ አሉ፡፡  ካሳ ደበሉ እንዲህ አሉ፤ እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡
አባ ዳካ፣ አንድ ቀን ከአንድ ሹም ጋር  ተጣልተው በብዙ ጅራፍ ተገርፈው ሲመጡ ወዳጃቸው የሆነ ሰው ያገኛቸውና “ምን አርገው ነው እንዲህ የተገረፉት አባ ዳካ?” ሲል  ጠየቃቸው፡፡
አባ ዳካ፣ “ያየሁትን ተናግሬ” ይላሉ፡፡
“ምን አይተው፣ ምን ተናገሩ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡
“ትላንትና ወንዝ ወርጄ ውሃ ቀጂዎቹ እወንዙ ዳር ሆነው በብዛት ውሃ ይቀዳሉ፡፡ ይሄኔ አንድ ሹም ከሚስቱ ጋር ይመጣል፡፡ ከዚያም ሚስቱ ከሌሎቹ ውሃ-ቀጂዎች እኩል መቅዳቷ  የውርደት ይመስለውና፣ በሰላም ውሃ እየቀዱ ያሉትን ሴቶች፣ “አንቺ መጀመሪያ፣ ቀጥሎ  አንቺ፣ ቀጥሎ አንተ” ማለት ጀመረ፡፡


ይሄኔ እኔ በሆዴ “ወንዙ  ላገር የሚበቃ  ነው፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ መቅዳት ይችላል፡፡ አሁን ተራ ግቡ፣ በዚህ ውጡ፣ በዚህ ውረዱ፣ ማለትን ምን አመጣው?  አልኩና ባካባቢዬ  ላሉት ሰዎች የሀገሬ ሰው “ሹመት የለመደ፣ ወንዝ ወርዶ፣ እርስዎ ይቆዩ፣ እርስዎ ይቅዱ” ይላል አልኩኝ፡፡
ሰው ሲስቅ ሹሙ ተናደው  አርባ ጅራፍ ፈረዱብኝ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ አባ  ዳካ ብዙ ያገር ሰው የተጠራበት  ሰንበቴ፣ ድግስ  ሄደው ኖሯል፡፡ እዚያ የሚመገቡትን ተመግበው  ሲያበቁ የሚጠጣው ጠላ ቀረበ፡፡ በመጀመሪያ ዙር የተሰጣቸው  ጠላ ጉሽ ነበር፡፡
እንደምንም ብለው “እንትፍ፣ እንትፍ” እያሉ ጠጡ፡፡
ሁለተኛው ዙር መጣ፡፡ አጋፋሪው ቀዳላቸው፡፡ አሁንም ጉሽ ነው፡፡
ሦስተኛውን  ደገሙ፡፡ አሁንም ጎሸባቸው፡፡ ያም ሆኖ አባ ዳካ ሞቅ እያላቸው ሄዱ፡፡
በአራተኛው፣ አጋፋሪው ሲመጣ አባ ዳካ ቀና አሉና፣
“ሰማህ ወይ አጋፋሪ?”
“አቤት አባ ዳካ፣ ምን ፈለጉ?”
አባ ዳካ ጮክ ብለው ቀጠሉ፣
“ቁና- እህል ጠላ ጨረስን፣
 እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” አሉ፡፡
ተጋባዡ  ሁሉ በሆዱ  ይህንኑ ያስብ ኖሮ ሳቅ በሳቅ ሆነ፡፡
***
ፈረንጆች “ማንኛውም ነገር ሊቀለድበት የማይችልበት  ደረጃ ሲደርስ፣ ተስፋ  እየራቀ  ሄደ ማለት ነው” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ  ውስጥ ግን ምናልባት በተቃራኒው፣ ተስፋ የማይደረስበት ርቀት ላይ ቢሆን እንኳ  ህዝቡ እንደልብ መቀለዱን፣  እንደልብ  መጫወቱን፣  እንዳሻው መተረቡን አይተውም ማለት ይቀላል፡፡ እንደነሩሲያ፣ እንደነሩማኒያ፣ መራር  ቀልድ ለመቀለድ የሚችል ሕዝብ  ነው፡፡ ቻይናውያን እንደሚሉት “እሳተ-ገሞራ ላይ ሆኖም በራሱ ላይ አነጣጥሮ የሚቀልድ እውነተኛ ኮሜዲያን” ነው፡፡ አባ- ዳካ አንዱ ምሳሌ  ናቸው፡፡ አንዳንዴ እንደ አባ ዳካ ያሉ ሰዎች ባይኖሩን ምን ይውጠን ነበር? ያሠኛል፡፡ መራር ቀልድ የሚቀልዱ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡  
የሀገራችን የፖለቲካ መንገድ ሁሌም ረዥም ነወ፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ወጣ ገባም፣ መራራም ነው፡፡ የፖለቲካ መንገደኞቹ ደግሞ በብዛት  ረዥም መንገድ ተጓዥ ሆነው አይገኙም፡፡ ወይ የንድፈ-ሀሳብ ስንቅ ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ የልምድ መዳበርና መሰናዶ ያንሳል፡፡ ወይ በቀና አመለካከት የታነፁ አባላት ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ  በትግሉ ጥልቀትና ጠመዝማዛ ርቀት ላይ ያለው አስተውሎት ደብዛዛ ይሆናል፡፡ ወይ በሰርጎ-ገብ፣ ወይ በአድርባይ፣ ወይ ባለሁሉ-አለሁ ባይ፣ ወይ በዕውቀት የበታችነት ስሜት፣ አሊያም በአመለካከት የበላይነት ጫና፣ በየጊዜው  ውጥረት ውስጥ ሲገቡ  ይታያል፡፡ አጠቃላዩ የፖለቲካ አየር ሁሌ በተለመደና ተደጋጋሚ ውጥረት ውስጥ መግባቱ አስገራሚ ነው፡፡  እርግጥ የፖለቲካው ሀይል የስበት ማእከል በጋለ ሙቀት  በተከበበ ቁጥር የተቃራኒ ሀይሎች ፍትጊያ ሰበቃ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሰበቃ ውስጥ እየተሸረፈ የሚወድቅ፣ እየተፈረካከሰ የሚበተን፣ እንደ ባቡር ፉርጎ የሚጎረድ፣ እንደ ባህር  ጨው ሟሙቶ የሚቀር መኖሩ፣  ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሀቅ ገዢ ተገዢ ሳይል በየፓርቲው  ላይ ሁሉ ሲከሰት የሚታይ ነው፡፡  ዋናው ነገር ግን የዚህ ሁሉ መጨረሻ አገር ወዴት እያመራች ነው? ህዝቡስ ምን ፋይዳ  እያገኘ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለአፍታም አለመዝለል ያሻል፡፡


በሀገራችን ከ1960ዎቹ ጀምሮ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ውጪ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ ዛሬም ብዙ የፖለቲካ ፓርዎች አሉ፡፡ የዱሮዎቹ በተለይ ተቃዋሚዎቹ፣ ጥቂትና በህቡዕ (በሚሥጥር) የተደራጁ ሲሆኑ፣ የአሁኖቹ በአደባባይ ሰው አውቋቸው፣ ፀሐይ ሞቋቸው የተቋቋሙና ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ዘመን፣ በጋራ የምናየው ብርቱ ጉዳይ፣ አንዱ በሌላው ፓርቲ ወይም ቡድን ውስጥ በታኝ ሃይል ማስረጉ ነው፡፡ ያህያ ቆዳ ለብሰህ ጅብን ውጋ፣ አሊያም የበግ ለምድ ለብሰህ ተኩላ ነኝ በል፣ ነው ነገሩ፡፡ ሌላው ክስተት፣ ለብዙኃን ዲሞክራሲ  ተገዢ አለመሆን፣ የመሰነጣጠቅ አደጋ፣ የግትር እምቢተኝነት ጠባይ፣ በፊት ለፊት እምቢ ሲል በጓሮ መሄድ፣ በማላተም እምቢ ሲል፤ በማጠቋቆም መጠቀም፣ በምክክር ሲያቅት በሸር፣ በረድፈኝነት ሲያቅት በአንጀኝነት፣ በድቁና ሲያቅት በሙስና፣ በማስፈራራት ሲያቅት በመቅጣት፣ በመሞዳሞድ ሲያቅት በማዋረድ፣… መጓዝ ነው፡፡


እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ፈሊጦችና አካሄዶች አገሪቱ ባለችበት እንድትረግጥ አሊያም የኋሊት እንድትንሻተት ማድረጋቸውን ልብ አለማት፣ ክፉ የጥፋት አባዜ ነው፡፡ ነገ ከነግወዲያ ለሀገርና ለህዝብ ምን ፈየድኩ? ሲባል በእኩይነታችን ማፈር፣ በውድቀታችን መፀፀት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅቶች መኖር፣ ለዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎች ማበብ ወደድንም ጠላንም እርሾ ነው፡፡ ያለእነዚህ ድርጅቶች የህዝቦችን ፍላጎት ማንፀባረቅና ማርካት ምኞት ብቻ ነውና፡፡ በእርግጥም አንዴ የትግል አምባ ከተወጣ ድካሙን፣ ሥቃዩን፣ ውጣ ውረዱን፣ አታካችነቱን፣ በተደጋጋሚ ሊያጋጥም የሚችለውን እልህ- አስጨራሽ ፈተና መቀበል አሌ የማይባል የጉዞው አካል ነው፡፡ ይህ ግን ገና ትግልን ሲጀምሩ መጤን ያለበት የትግሉ ሥጋና ደም ነው፡፡ ትግልን ረዥምና እሾሃማ  የሚያደርገውም ይኸው ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብትን ማስከበር፣ ፍትሐዊ ሁኔታን መፍጠርና ሰላምን መጎናፀፍ የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ዐይንን ከፍቶ  ክፉና ደጉን መለየት፣ ነገሮች ሲጎሹ ሳይደናገጡ ማጥራት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሂደት ሠናይነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ “ቁና-እህል ጠላ ጨረስን፤ እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” የሚባለው  ተረትም ይህንኑ የሚያፀኸይ ነው፡፡

      የአማራ ክልል መንግስት፣ በክልሉ በታጠቁ ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን  እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጠየቀ። ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚፈጸመው እስር መቀጠሉንና  የሚያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አስታውቋል።
ተቋሙ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫ፤ አማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል። በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዊ ዞን፣ አዲስ ቅዳም ከተማ በመንግስትና በተለምዶ ፋኖ በመባል በሚታወቁ የታጠቁ አካላት መካከል ውጊያ ከተደረገ በኋላ፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች “የፋኖ ደጋፊ ናችሁ” በሚል በየቦታው ያገኟቸዉን አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን ከሕግ አግባብ ዉጭ ግድያ እንደፈጸሙባቸው ኢሰመጉ ጠቅሷል።


ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት አካባቢ ባሕር ዳር ከተማ፣ ቀበሌ 07 በሚገኘው ሃን ጤና ጣቢያ ተቀጥራ ከ30 ዓመት በላይ ስትሰራ የነበረች ሴት የጤና ባለሙያ፣ ከመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት እንደተገደለች ያመለከተው  ኢሰመጉ፤ “ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን ከጋሳይ ወደ ጉና በጌምድር [ክምር ድንጋይ] ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና፣ ከመኪናው ራስ/ፖርቶ መጋላ ላይ ተሳፍረው ሲሄዱ የነበሩ ሰዎች በታጠቁ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሁለቱ ተሳፋሪዎች ሲገደሉ፣ አንድ ተሳፋሪ ላይ ደግሞ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ መቻሉን ገልጿል፡፡


ከዚህም በተጓዳኝ በክልሉ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረገው እስር እንደቀጠለና የሚያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት እየቀረቡ አለመሆኑን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡
ኢሰመጉ በመግለጫው ላይ ለአማራ ክልል መንግስት፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይልና በታጠቁ አካላት እየተፈጸመ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በቂ ትኩረት በመስጠት እንዲያስቆምና ዜጎቹን የመጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፣ በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ከአንድ ወር በላይ ለእስር የተዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ከመስከረም ወር ጀምሮ አደረግሁት ባለው ማጣራት፣ በክልሉ በአራት ጊዜያዊ የማቆያ ስፍራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ገልጿል።


የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ ከጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያዎቹ የወጡ ሁለት ሰዎችን፣ አምስት የታሳሪ ቤተሰቦችንና ዘጠኝ ከጅምላ እስሩ ጋር በተያያዘ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማነጋገሩን አመልክቷል። በዚህም በዳንግላ፣ ሰራባ (ጭልጋ)፣ ኮሪሳ (ኮምቦልቻ) እና ሸዋሮቢት በተዘጋጁ ጊዜያዊ ጣቢያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ነው የጠቆመው።
አምነስቲ በሪፖርቱ  በአራት ከተሞች በሚገኙ ጊዜያዊ ካምፖች የታሰሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁ በኋላ፣ “ይለቀቃሉ” መባሉን ከታሳሪ ቤተሰቦች መስማቱን ገልጿል።

     በትግራይ ክልል ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መቐለ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ያልተመለሱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ነው ብሏል፡፡
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ የሆኑት አቶ ጸሐዬ እምባዬ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከ970 ሺ በላይ በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን አመልክተው፣ በረሃብና በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው የሚቀጠፍ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። አያይዘውም፣ ተቋማቸው ባደረገው ጥናት መሰረት፤ ለተፈናቃዮቹ የሚቀርበው እርዳታ በአግባቡ እየተዳረሰ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።


ሃላፊው በሰላም ስምምነቱ “ይመለከታቸዋል” ተብለው ለተጠቀሱት አካላት ባቀረቡት ጥሪ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተማጽነዋል።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሴቶችና ሕጻናት ክፍል ሃላፊ አቶ ሃፍታይ አሰፋ በበኩላቸው፤ ከሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እጥረት ባሻገር ተፈናቃዮቹ መሰረታዊ መብቶቻቸውን በመነፈጋቸው ሳቢያ፣ ለሞትና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሽረ እንዳስላሰ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል 42 ሺ ያህሉ መሰረታዊ ዕርዳታ ያላገኙ ሲሆኑ፣ ከ78 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ፣ ንጹህ ውሃ እንደማያገኙ ሃላፊው ጠቅሰዋል።


በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም በኋላ የእርዳታ አቅርቦት በቂ  አይደለም።
አገልግሎት አሰጣጥ ድክመት አንጻር ለመንግስት ሰራተኞች የ17 ወር ደመወዝ አለመከፈልና ሌሎች ምክንያቶች እንደ መንስዔ እንደሚጠቀሱ ተቋሙ አመልክቷል። የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መቐለ ቅርንጫፍ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሚቀርቡለት ቅሬታዎች በርካታ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡  

      በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ አማካይ የዋጋ ንረት 25 በመቶ እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ገልጿል። ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ባንኮች ላይ የጣለውን አስገዳጅ የ20 በመቶ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ “ያነሳል” ሲል አመልክቷል።
አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ ያደረገውን ስምምነት የሚዳስስ የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ ሪፖርት ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ በገበያ ስርዓት ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ተግባራዊ ማድረጓ የሚበረታታ እንደሆነ የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ በሪፖርቱ አስታውቋል።


የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ ስርዓቱን ዋስትና ለማረጋገጥ እየተገበራቸው የሚገኙት የማስተካከያ ጥረቶች ከአይኤምኤፍ የፖሊሲ መስፈርቶችና የፕሮግራም መመዘኛዎች ጋር መጣጣም እንደሚገባቸው ድርጅቱ አሳስቧል፡፡ የአይኤምኤፍ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የቦርዱ ሰብሳቢ ቦ ሊ የኢትዮጵያ መንግስት በብሔራዊ ባንክ አማካይነት ሲያደርጋቸው የቆዩትን በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች የመቀነስ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል “አለበት” ብለዋል።


“ቀጣይነት ያለው እና ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ፣ እንዲሁም የመንግስት የበጀት ጉድለቶችን ለመሸፈን የሚደረጉ የገንዘብ ድጎማዎች ማስወገድን ጭምሮ ጥንቃቄ የተሞላባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መተግበራቸው በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰቱ የሚዛን መዛባቶችን ለመቀነስ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው።” ብለዋል፣ የቦርዱ ሰብሳቢ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ባንኮች ላይ የጣለውን አስገዳጅ የ20 በመቶ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ እንደሚያነሳ አይኤምኤፍ ማረጋገጡን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በ2017 ዓ.ም. ሁሉም ባንኮች ከሚፈጽሙት አስገዳጅ የቦንድ ግዥ በአጠቃላይ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን መንግስት ለአይኤምኤፍ መግለጹ ተጠቁሟል፡፡


አይኤምኤፍ ይፋ ባደረገው በዚህ ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾች ሲታይ የሚኖረው የዕድገት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያመላከተ ሲሆን፣ “ዕውነተኛ የአገራዊ ጥቅል ምርት ዕድገት” በተሰኘው መስፈርት መሰረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024/25 የሚኖራት ዕድገት 6 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚሆን ተገምቷል። በተጨማሪም፣ የአገሪቱ አማካይ የዋጋ ንረት 25 በመቶ “ይሆናል” ሲል ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
አይኤምኤፍ በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ “ጥብቅ የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲዎች እንዲቀጥሉ” የሚል የመጀመሪያ ዙር መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ጥብቅ የሆነውን የገንዘብ ፖሊሲ ኢትዮጵያ “ታስቀጥላለች” የሚል መግለጫ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም።


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ “ፕሬዚዳንት እንድሆን በተደጋጋሚ ብጠየቅም ጥያቄውን ግን አልተቀበልኩም” ሲሉ ተናገሩ። ጄኔራል ጻድቃን፤ የትግራይ ሕዝብ በተመረጠለት ሳይሆን በመረጠው መሪ መተዳደር ይገባዋል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. በመላው ዓለም ከሚገኙ የዲያስፖራ ማሕበረሰብ አባላት ጋር በበይነ መረብ ውይይት ያደረጉት ጄኔራል ጻድቃን፣ ለተለያዩ ሃሳቦች  ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ጄኔራል ጻድቃን፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኬንያ ናይሮቢ እንዲሁም በሃላላ ኬላ ተገኝተው በነበሩበት ወቅት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው አስታውሰው፤ “‘እኔ ግን የትግራይ ሕዝብ ሲመርጠኝ እንጂ እናንተ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንድትሾሙኝ አልፈቅድም። ይህ ለትግራይም፣ ለታሪኬም የሚመጥን አይሆንም’ የሚል መልስ ሰጠኋቸው።” ብለዋል።


በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ባለስልጣናቱ ለአቶ ጌታቸው ረዳ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርቡላቸው  እንደነበር ያወሱት  ጄኔራሉ፣ በአሜሪካ በኩልም ይኸው ፍላጎት ሲንጸባረቅ መቆየቱንና እርሳቸው ግን ፍላጎቱ እንዳልነበራቸው አስረድተዋል። “ዶክተር ደብረጽዮን ‘በረሃ ሳለን፣ እኔን ከስልጣን ለማንሳት ፈልጎ ነበር’ ሲሉ የተናገሩት ነገር የሚያሳዝን ነው። ሰራዊታችን ከተበታተነ በኋላ ‘እንደገና ተደራጅተን እንዴት ትግሉን እናስተባብር?’ ብለን መከርን። ዶ/ር ደብረጽዮን የውጭ፣ እኔ ደግሞ የአገር ውስጥ ትግሉን ለማስተባበር ተመረጥን። ይህንን ነው ዶ/ር ደብረጽዮን ‘ከስልጣን ለማንሳት ፈልጎ ነበር’ በማለት ሊገልጹ የፈለጉት።” ሲሉ  ያስረዱ ሲሆን፣ አክለውም፤ “እኔ ሕዝቤን ለማገዝ እንጂ የሆነ ስልጣን በአቋራጭ ለመውሰድ ዓላማ የለኝም። ስልጣን ለማግኘት የፕሪቶሪያ፣ የናይሮቢና የሃላላ ኬላ እንዲሁም ሌሎች አጋጣሚዎች ነበሩ። ይህ ግን ከዓላማዬና ከሰብዕናዬ ጋር የሚሄድ ስላልሆነ አላደረግሁትም።” ብለዋል፡፡
“ውስጣዊ ችግራችንን ከፈታን፣ የውጭ ችግሮቻችንን ለመፍታት ብዙም አንቸገርም” ያሉት ጄኔራል ጻድቃን፤ የትግራይ ሕዝብ ከላይ በተመረጠለት ሳይሆን ራሱ በመረጠው መሪ መተዳደር እንደሚገባው በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ትእምት (EFFORT) የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ ድርጅቱ ወደ ዋና ባለቤቱ፣ ወደ ትግራይ ሕዝብ ሊዘዋወር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
ከተፈረመ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በውስጡ ያሉትን ዕድሎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው፣ ከገባንበት  ችግር በፍጥነት እንወጣለን ብለዋል፣ ጄኔራል ጻድቃን።

Friday, 08 November 2024 08:35

ነገረ መጻሕፍት!

ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 30  2017 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው "FSS" አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።

የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው።