Administrator

Administrator

እስከማስታውሰው ድረስ ለእያንዳንዱ ችግር መፍትሄዎች አሉ፤ በመሆኑም ያደግሁት ችግርን አሜን ብለን መቀበል የለብንም የሚል እምነት ይዤ ነው። ከአሥራ ሁለት ዓመታት በፊት ነበር በምኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ የተሻለ ትምህርት መፍጠር አስፈላጊ እንደሆነ የተገነዘብኩት፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ የሚያስችል አንድ ሀሳብ አፈለቅሁ:: ያ ሀሳብ የሕይወቴን አቅጣጫ ወደ መምህርነት፤ የማህበራዊ ስራ ፈጣሪነትና በኢትዮጵያ ትምህርት እንዲስፋፋ ወደ መቀስቀስ አመጣው፡፡ ሁሉም ነገር የተጀመረው በሀሳብ ችግርን ለመጋፈጥ በመዘጋጀትና ለሀሳቡ ተፈጻሚነት በመንቀሳቀስ ነው፡፡
የተወለድኩት በአዲስ አበባ ሲሆን ያደግሁትም በሰፊ ቤተሰብ ውስጥ ከስምንት እህቶችና ከሦስት ወንድሞቼ ጋር ነበር፡፡ ልጅ ሳለሁ ቤተሰቦቼ ወደ አማራ ክልል ስለተዛወሩ፣ እኔም ከቤተሰቡ ጋር ወደዚያው በማምራት፣ የልጅነት ህይወቴን ባህር ዳር አካባቢ አሳለፍኩ፡፡
አባቴ ስራ ፈጣሪ ነበር፤ እናቴ ደግሞ እኔንና ሌሎች ልጆችን የማሳደግ ኃላፊነት የተጣለባት የቤት እመቤት ነበረች፡፡ በቤተሰባችን ውስጥ የሴቶች ቁጥር የሚበልጥ ቢሆንም፣ የጾታ ሚናና የወንዶችን አስፈላጊነት በተመለከተ ግንዛቤ መያዝ የጀመርኩት ገና በልጅነቴ ነበር፡፡ አባቴ ወንድ ልጆች ሲወለዱ አብዝቶ ይደሰት ስለነበር፣ ሴት መሆን ጥሩ እንዳልሆነ እየተሰማኝ አደግሁ፡፡ ልጅ ሳለሁ አይናፋርና ቁጥብ ነበርኩ። ‹‹በሰዎች ፊት መናገር ነውር ነው›› ተብሎ ይነገረን እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንዳጠናቀቅሁ ነበር፣ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ግዛት ኦክላንድ ውስጥ በሚገኘው ሜሪት ኮሌጅ የመግባት እድል አገኘሁ፡፡ እንደ አባቴ ሥራ ፈጣሪ የመሆን ፍላጎት ስለነበረኝ፣ የአነስተኛ ንግድ አስተዳደር ለማጥናት ወሰንኩ፡፡
በትምህርት አቀባበል ፈጣን ስለነበርኩና እንግሊዝኛ በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቻሌ፣ አሜሪካ ካለው ሁኔታ ጋር ራሴን ለማላመድ ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡ በእርግጥ ያረፍኩባቸው ቤተሰቦቼም ብዙ ድጋፍ አድርገውልኛል። በዚህ ወቅት ነው ስለ ራሴ ብዙ ነገሮችን ማሰላሰልና ማወቅ የጀመርኩት፡፡ በልጅነቴ ወደ ውስጤ ሰርጾ ስለገባው የተዛባ የጾታ አመለካከት ጥያቄዎችን ማንሳት ያዝኩ። በሞግዚትነት የተቀበለችኝ አሜሪካዊት ጋዜጠኛ፣ በድፍረት እንድናገርና ሀሳቤን በነጻነት እንድገልጽ ታበረታታኝ ነበር፡፡ በመሆኑም ብዙም ሳልቆይ በሰዎች ፊት ለመናገር ያግደኝ የነበረው አይነጥላ ተገፈፈልኝ፡፡ እሳት የላስኩ ተናጋሪ ወጣኝ። በወቅቱ ይህ ለውጥ ለሌሎች ኢትዮጵያውያን ልጃገረዶችና ሴቶች በማስተማሪያነት የማጋራው መልካም ተሞክሮ ይሆናል ብዬ አላሰብኩም ነበር፡፡
በኮሌጁ የጀመርኩትን ትምህርት ለሦስት ዓመታት እንደተከታተልኩ ለማቋረጥና ወደ አገሬ ለመመለስ የሚያስገድድ ሁኔታ ገጠመኝ። በወቅቱ ወላጆቼ በፍቺ ትዳራቸውን አፍርሰው ተለያይተው ስለነበር፣ ወደ አገር ቤት ተመልሼ፣ ታናናሽ እህትና ወንድሞቼን የመንከባከብ ኃላፊነት ወደቀብኝ፡፡ ይህ በሕይወቴ ካጋጠሙኝ ፈታኝ ሁኔታዎች አንዱ ነበር፡፡ በቀጣይ ወዴት አቅጣጫ መሄድ እንዳለብኝ ለማሰብ አቅም አልነበረኝም፡፡ በዚህ ወቅት ነው ከባለቤቴ ጋር ተገናኝተን፣ ወደ አሜሪካ ተመልሼ ትምህርቴን የመከታተል ዕቅዴን በመሰረዝ፣ ባህርዳር ለመቆየት የወሰንኩት፡፡
በሪልእስቴት ኢንቨስትመንት መስክ የመሰማራት ሀሳብ ነበረኝ፡፡ ይሄን ሀሳቤን የቀየርኩት ግን በአጋጣሚ ነው፡፡ የሦስት አመት እድሜ ለነበረው ልጄ አጸደ ሕጻናት ሳፈላልግ በፍጹም ላገኝ አልቻልኩም፡፡ በከተማዋ የነበሩት ትምህርት ቤቶች ሁሉ ከአንደኛ ክፍል ጀምረው ነበር የሚያስተምሩት:: የተለያዩ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ተዟዙሬ ስጎበኝ፣ ያየሁትን ነገር ለማመን ተቸግሬ ነበር፡፡ በትምህርት ቤቶቹ  ያስተዋልኩት የጥራት መጓደል በጣም አስደነገጠኝ፡፡ አንድ ነገር መሥራት እንዳለብኝ ተሰማኝ። ‹‹ለምን ትምህርት ቤት አላቋቁምም?›› የሚል ሀሳብ በውስጤ ተፈጠረ፡፡ ሃሳቤን እውን ማድረግ የምችልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ጀመርኩ:: በዚህ ወቅት ነው መንግስት፣ ትምህርት ቤት መገንባት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች፣ መሬት በነጻ እንደሚሰጥ መግለጫ ያወጣው። ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ህልሜን እውን ለማድረግ ቆርጬ ተነሳሁ፡፡
ከአጸደ ሕጻናት እስከ አስራ ሁለተኛ ክፍል የሚያስተምር ትምህርት ቤት ለመክፈት የሚያስችል የፕሮጀክት ንድፍ ማዘጋጀት ጀመርኩ፡፡ ከባለቤቴ ጋር በመሆን በማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን የመክፈል አቅም አጠናን፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች በብቁ መምህራን በኮምፒውተር ቤተ ሙከራ፣ በመጫዎች ቦታ፣ በበቂ መጻሕፍትና በሌሎች የመማር ማስተማር ቁሳቁስ ለተደራጀ ትምህርት ቤት፣ ምን ያህል ገንዘብ መክፈል እንደሚችሉ ለማወቅ ነበር ጥናቱን የሰራነው። ማህበረሰቡ የመክፈል አቅም ካለው ትምህርት ቤቱ መቋቋምና በዘላቂነት መቀጠል እንደሚችል፣ እኔም ሆንኩ ባለቤቴ እምነት ነበረን። ለጥናታችን በተጠቀምንበት መጠይቅ ውስጥ ሦስት አይነት የክፍያ አማራጮችን ነበር ያቀረብነው፡፡ በጣም የሚገርመው መጠይቁን ከሞሉ ሰዎች አብላጫ ቁጥር ያላቸው፣ ከፍተኛ የተባለውን የክፍያ አማራጭ ነበር የመረጡት። ከዚያም በመነሳት እቅዳችን ተግባራዊና የሚያዋጣ ሊሆን እንደሚችል ተረዳን። እናም የባህር ዳር አካዳሚ ግንባታ ተጀመረ፡፡  
ግንባታውን የጀመርነው በተለያዩ ምዕራፎች በመከፋፈል በአነስተኛ ጅምር ነበር፤ እናም የአጸደ ሕጻናት፣ የአንደኛ ደረጃ፣ የመካከለኛና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቶች የሚሰጡባቸውን አራት የተለያዩ ትምህርት ቤቶች ገንብተን ጨረስን። ሃምሳ ተማሪዎችን ብቻ ይዞ በ2001 ዓ.ም ሥራ የጀመረው የባህር ዳር አካዳሚ፣ በአሁኑ ጊዜ 2700 ተማሪዎች አሉት፡፡ ሌሎች በርካቶችም ተቀባይነት አግኝተው ወደ አካዳሚው ለመግባት በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ የባህር ዳር አካዳሚ ተማሪዎች የብቃት ደረጃ እጅግ ጥሩ የሚባል ሲሆን አብዛኛዎን ጊዜ በክልሉ ከሚገኙ ተማሪዎች ከፍተኛውን ውጤት የሚያስመዘግቡትም የዚሁ አካዳሚ ተማሪዎች ናቸው፡። በተማሪዎቻችንና በአካዳሚያችን መምህራን ብቃት ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል፡፡ ትምህርት ቤታችን ከመደበኛ ትምህርት በተጨማሪ ለተማሪዎች አጠቃላይ የትምህርት እድገት ድጋፍ የምናደርግበት የክትትል ፕሮግራም ነው። ለወላጆች የምናዘጋጃቸው አውደ ጥናቶችና ሥልጠናዎችም በአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ከጾታ ጋር የተያያዙ የተዛቡ አመለካከቶችን ለማስቀረት ተግተን እንሰራለን። ለወንድ ተማሪዎች የምግብ ዝግጅት፣ ለልጃገረዶች ደግሞ በራስ የመተማመን ስሜትን የሚፈጥሩ ሥልጠናዎችን እንሰጣለን፡፡
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሥራ መደቦች ተቀጥረው በመሥራት ላይ ከሚገኙ 216 የአካዳሚው የሙሉ ጊዜ ሰራተኞች መካከል 65 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤታችን የሚጠቀስበት ሌላው ትልቅ ነገር ደግሞ የትምህርት ቤቱ ሰራተኞች፣ ልጆቻቸውን የሚያቆዩበት ራሱን የቻለ የሕጻናት እንክብካቤ ክፍል በግቢው ውስጥ መኖሩ ነው:: በሥራ ቦታዎች ላይ መሰል የሕጻናት እንክብካቤ አሰራሮች መስፋፋት እንዳለባቸው በአጽንኦት እናገራለሁ፡፡ ትምህርት ቤታችንም በዚህ መልካም ተመክሮው በአገር አቀፍ ደረጃ እውቅና ሊሰጠው ይገባል እላለሁ፡፡
ትምህርት ቤቱን በማቋቋሙ ሂደት ከገጠሙን ዋነኛ ችግሮች መካከል ብቃት ያላቸው መምህራንን ለማግኘት አለመቻል አንዱ ነው፡፡ ለትምህርት ቤቱ ያስቀመጥኳቸው ደረጃዎች ከፍተኛ እንደመሆናቸው፣ የምንቀጥራቸውን መምህራን እንደገና በራሳችን በማሰልጠንና በማብቃት፣ ምርጥ መምህራን የሚሆኑበት ደረጃ ላይ ማድረስ እንዳለብን ተስማምተናል፡፡ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ለመጋፈጥ ወደ ኋላ ብዬ አላውቅም። ልናከናውነው አንችልም የምንለው ምንም አይነት ነገር መኖር የለበትም ብለን ስለተነሳን፣ ይሄን አቋማችንን አስጠብቆ ማስቀጠልም ሌለው የገጠመኝ ፈተና ነበር፡፡
ለሚገጥሟችሁ ማናቸውም ችግሮች መፍትሄዎችን ለመፈለግ በራስ መተማመንና ቁርጠኝነት ሊኖራችሁ ይገባል፡፡ ወጣት ሴቶችና ልጃገረዶች፣ በእለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሚያጋጥሟቸው ችግሮች፣ መልካም አጋጣሚዎችን መፍጠር እንዲሁም ችግሮችን ለመፍታት ምን ማድረግ እንዳለባቸው በአጽንኦት ማሰብ እንደሚገባቸው እንዲገነዘቡ እፈልጋለሁ:: የሚያጋጥሟችሁን ችግሮች ወደ ገንዘብ አመንጪ ዕድሎች በመቀየር እንደ ማህበራዊ ሥራ ፈጣሪ፣ ለውጦችን አስመዝግቡ፡፡ የተሻለች ኢትዮጵያንም ሆነ የተሻለች አለምን መፍጠር የምንችለው በዚህ መልኩ ነው፡፡
ከሌሎች አጋሮቼ ጋር በመሆን የአማራ ሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች ማህበርን በ2004 ዓ.ም ባህር ዳር ውስጥ ለማቋቋም የገፋፋኝ፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ የንግዱን ማህበረሰብ እንዲቀላቀሉ ለማበረታታት ያለኝ ጥልቅ ፍላጎት ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማህበሩ ሦስት ሺህ አባላት ያሉት ሲሆን በአገሪቱ ከሚገኙት የሴቶች ሥራ ፈጣሪዎች ማህበራት በትልቅነቱ የሁለተኛነት ደረጃ ለመያዝ በቅቷል፡፡ የማህበሩ የመጀመሪያዋ ፕሬዚዳንት ሆኜ ባገለገልኩባቸው አራት አመታት፣ በንግዱ ዘርፍ ያሉ ሴቶች እንዲነቃቁና ድጋፍ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ሥራዎችን አከናውኛለሁ፡፡
በተጨማሪም ሴቶች በክልሉ ልማት ላይ ተሳትፎ እንዲያደርጉና ሀሳቦቻቸውን ወደ ተግባር እንዲለውጡ ለማበረታታት በትጋት ሰርቻለሁ፡፡ ያ ወቅት በሕይወቴ ግሩም ከምላቸው ጊዜያት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ የሴቶችና የማህበራዊ ሥራ ፈጣሪዎች አፈ ጉባኤ በመሆኔ ኩራት ይሰማኛል፡፡ በቅርቡ የአፍሪካ ሴት ሥራ ፈጠራ ፕሮግራም የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆኛለሁ፡፡ በቦርዱ የሚጠበቅብኝን ሥራም በደስተኝነት መተግበሬን ቀጥያለሁ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአገራችን ከተቋቋሙት የግል ባንኮች በአንደኛው፣ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል በመሆን እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡
እንደነ ማህታማ ጋንዲና እማሆይ ቴሬዛ ያሉ ታላላቅ ግለሰቦች፣ የሰሯቸውን ሥራዎች፣ በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ሳደንቅ ነው የኖርኩት፡፡ ለማህበረሰባቸው ያበረከቷቸው አስተዋጽኦዎች፣ በእያንዳንዷ ቀን መነቃቃትን ይፈጥሩልኛል፡፡ የትምህርት መስፋፋት ተቆርቋሪ እንደመሆኔ፣ ከትምህርት ገበታ ራሴን አርቄ አላውቅም። በልማት ጥናቶች ላይ በማተኮር በሰብዓዊና ማህበራዊ ሳይንስ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ተቀብያለሁ፡፡ አሁንም በደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ፣ በልማት የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቴን በመከታተል ላይ እገኛለሁ፡፡
ሕጻናት ወደ ትምህርት ገበታ ከመቅረባቸው በፊት ተገቢ ምግብ መመገብ እንዳለባቸው አምናለሁ፡፡ በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሰጥቼ በመሥራት ላይ የምገኘውም በመላ አገሪቱ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች፣ የትምህርት ቤት ምሳ ፕሮግራሞች እንዲካተቱ በማድረግ ላይ ነው:: በጉዳዩ ዙሪያ ትኩረት ሰጥቼ ማሰብ የጀመርኩት ከአንድ የአካዳሚያችን ሰራተኛ በደረሰኝ መረጃ ላይ ተመስርቼ ነበር፡፡ በዕለቱ ካገኘሁት መረጃ ለመረዳት እንደቻልኩት፣ በአካዳሚያችን ተማሪ የሆነ አንድ ህጻን፣ ሁሌም ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ ነበር ወደ ትምህርት ቤት የሚመጣው፡፡ ተማሪው ባዶ የምሳ ዕቃ ይዞ በመምጣት፣ የተመገበ አስመስሎ፣ ጾሙን ውሎ ወደ ቤቱ ይመለስ ነበር፡፡ የመረጃውንም እውነትነት ካረጋገጥኩ በኋላ በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቼ ለመሥራት ወሰንኩ፡፡ በሌሎች አገራት የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራሞች እንዴት እንደተጀመሩ ጥናት ማድረግ ጀመርኩ፡፡ የመንግስትና የሕዝብ አጋርነት ለመፍጠር በአልሚ ንጥረ ነገሮች የበለጸጉ ምግቦችን እያዘጋጁ ለትምህርት ቤቶች የሚያቀርቡ አነስተኛ የንግድ ተቋማትን ለማቋቋም ነው የፈለግሁት:: በአሁኑ ሰዓት ከመላ አገሪቱ ሴቶችን እየተቀበለ በምግብ ይዘት፣ በምግብ ደህንነትና ንጽህና አጠባበቅ በማሰልጠን፣ የራሳቸውን ንግድ ፈጥረው ለትምህርት ቤቶች ምግብ ማቅረብ እንዲችሉ እድል የሚፈጥር፣ የትምህርት ቤት ምግብ ማሰልጠኛ በአዲስ አበባ በማቋቋም ላይ እገኛለሁ፡፡ መንግስት በሁሉም የአገሪቱ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራሞችን ተግባራዊ የሚያደርግ ብሄራዊ ቦርድ በማቋቋም፣ እኔ የጀመርኩትን እንቅስቃሴ፣ ከ2012 ጀምሮ በመረከብ፣ አገር አቀፍ የትምህርት ቤት የምሳ ፕሮግራም እንደሚጀምር ትልቅ ተስፋ አለኝ፡፡
ትምህርት ቤቶች ወደፊትም የምተጋላቸው ዋነኛ ትኩረቴ ሆነው እንደሚቀጥሉ አውቃለሁ፡፡ አንድ አገር የሚለወጠው በትምህርት ቤቶች ውስጥ ነው:: የለውጡ ዋነኛ ቁልፍም ትምህርት ነው፡፡ ጠንካራ ትምህርት ቤቶች የጠንካራ መጪ ዘመን መሰረቶች ናቸውና፡፡ የነገዋን ኢትዮጵያ ወደ ተሻለ አቅጣጫ የሚያመራት ጠንካራ ትምህርት ነው፡፡
(“ተምሳሌት፤ ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች”፤ 2007 ዓ.ም)


Saturday, 31 August 2019 12:16

መልዕክቶቻችሁ

የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነገር!

       “በአንድ ወቅት ለአሜሪካ ድምፅ (Voice of America) ኢንተርቪው እንዳትሰጡ ተብሎ በኢህአዴግ ተወስኖ ነበር፡፡
እኔ ደግሞ በጊዜው የአሜሪካ ድምጽ ዳይሬክተር የነበረ የማውቀው ጋዜጠኛ ኢንተርቪው ለማድረግ ጠቀየኝ፡፡ ቃለ ምልልሱ በመሬት ጉዳይ ላይ የሚያጠነጥን ባለ ሁለት ክፍል ነበር፡፡
እንዳጋጣሚ ሆኖ ከፍተኛ ተደማጭነት አግኝቶ ነበር፡፡ በኋላ አቶ መለስ ስብሰባ ጠሩና፣ በጉዳዩ ላይ ውይይት ተደርጎ፤ በማስጠንቀቂያ ታለፍኩ፡፡ የዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ነገር እንዲህ ነው…”
(የቀድሞው ጠ/ሚ ታምራት ላይኔ፤
ሰሞኑን ለዋልታ ከሰጡት ቃለ ምልልስ የተወሰደ)

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ገበሬ ደጋ እየኖረ ነበር፡፡ አንድ ቀን ቆላ ገበያ ወረደ፡፡ ሲመለስ ብዙ ብር ይዞ መጣ፡፡ የሳር ቤት ጣራውን ቀይሮ ቆርቆሮ አስመታ፡፡ አጣና፡፡ የጐዳደለውን አጥሩን አጥብቆ ዙሪያውን አሳጠረ፡፡ መሬቱን በሊሾ ሲሚንቶ አስለሰነ፡፡
በጣም አሳመረው፡፡
ይህንን ያየ የጐረቤቱ ገበሬ ወደ ቤቱ ሄዶ፤
“ወዳጄ፤ ምን አግኝተህ ነው ቤትህንና ግቢህን እንዲህ ያሳመርከው?” ሲል ጠየቀው፡፡
ገበሬውም፤
“ከደጋ ብረታ ብረት የተባለ ሁሉ ሰብስቤ ሳበቃ፣ ቆላ ወርጄ፣ ለቆለኞቹ ቸበቸብኩላቸው፤
ከዚያ ገንዘቡን ይዤ ቤቴን አደስኩ፡፡ አጥሬን ጠገንኩ “አለው፡፡
ጐረቤትዬውም የወደቀ የተሰበረ ብረት ሳይቀረው አከማችቶ፣ ሁሉንም ተሸክሞ ወደ ገበያ ሲሄድ፣ ገበያው ዳገት ላይ ስለሆነ ያለው እንዴት ይድረስ? ወገቡ ቅንጥስ አለበትና ወደቀ፡፡
አንድ መንገደኛ በዚህ በወደቀው ነጋዴ አጠገብ ሲያልፍ፤
“ወዳጄ”
“አቤት”
“ምን ሆነህ ነው”
“አዬ ወገኔ አያድርስብህ”
“ምኑን?”
“ያ የጐረቤቴ ገበሬ ቤቴን ያደስኩትና አጥሬን ያስጠገንኩት ባካባቢዬ ያለ የሌለውን ብረታ ብረት ሸጬ ነው ቢለኝ፤ እኔም እንደሱ ሀብታም እሆናለሁ ብዬ፣ ይሄው የብረታ ብረቱ ሸክም ጉድ አደረገኝ! እንደኔ ጐረቤት ትርፉን ነግሮ መከራውን የማይነግር፣ አይግጠምህ!”
***
ያለ መከራ ተድላ ደስታ አይገኝም፡፡ ያለ መስዋዕትነት ድል የለም፡፡
ከጦርነት በፊት የዝግጅት ፋታ
ከማዕበል በፊት የባህር እርጋታ
ዛሬም ያው ህዝባችን የአንድ አፍታ ዝምታ
ነገር ግን ይዋጋል መታገሉ አይቀርም
ታግሎም ያቸንፋል አንጠራጠርም!
አልጋ በአልጋ መንገድ ኖሮን አያውቅም፡፡ ከእርግብ ላባ የተሠራ ፍራሽ የለንም፡፡ የአገር ጉዳይ ሳይቆረቁረን ውሎ አድሮ አያውቅም፡፡
አንዳንድ ቀን አለ
አንዳንድ ቀን አለ
ኮረኮንች የበዛው ሊሾ እየመሰለ
የምንለውም ለዚያ ነው፡፡
ዛሬም የመደራጀት ጥያቄ አልተመለሰም ዛሬም ግልጽነት አልተመለሰም የትውልድ ዕዳ አልተከፈለም ጤና እንደተዛባ ነው፡፡ ትምህርት አላደገም፡፡ ነጋ ጠባ ማህበራዊው ህይወት እየተናጋ ነው፡፡
ህይወት ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሏት፡፡ ገና ብዙ ፈተና፣ ብዙ ትግል ይጠብቀናል፡፡ ያለ ጥርጥር ግን  እንወጣዋለን፡፡ የአገርና የህዝብ ጉዳይ ኤጭ አይባልም፡፡ ድል የብዙሀን ነውና “ኩሉ አመክሩ ወዘሰናየ አጽንዑ” ያልነው ገና ጥንቱኑ ነው፡፡ ሁሉንም ሞክሩ የተሻለውን አጽኑ ማለት ነው፡፡
ስለዚህ አማራጭ እንመልከት፤ እናስላ፡፡ መላ እንምታ፡፡ እንምከር፡፡ በውይይት የማይፈታ ችግር የለም፡፡
“ሁለት ባላ ትከል
አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል”  የሚባለው ለዚሁ ነው፡፡


           እንደሚገማሸር የባህር ማዕበል ግለ-ታሪኳን ታዘንበው ቀጠለች፡፡ ድምጽ መቅጃዬን አስተካክዬ ጠረጴዛው ላይ ቁጭ አደረግሁ፡፡ እየተቀዳች መሆኗንም ነገርኳት፡፡ አንዳንድ ሰዎች ድምጻቸው ሲቀዳ ቃላት በመምረጥ ይጨናነቃሉ፡፡ እሷ ምንም አልመሰላት፡፡ አልፎ አልፎ የተናገረችውን መልሳ ከመድገም በቀር የማስታወስ ችሎታዋ የተመሰገነ ነበር፡፡ ጥቃቅን ነገሮችን እንኳ አልረሳችም፡፡ ስለ ማንነቴ ለማወቅ መፈለጓ አልቀረም፡፡ ዳሩ ከእርጅና ዘመን ብቸኝነት ስለገላገልኳት ጥያቄ ማብዛቴን አልጠላችውም፡፡ ከልቧ ተቀብላኝ ነበር፡፡ መደባበቅ የማታውቅ ነፃ ሰው ነበረች፡፡ ከመነሻው በአንቱታ እንድጠራት ባለመፍቀዷ ቀለለኝ፡፡
‹‹ቤት መኻእ የሚባለውን ዓዲ ታውቀዋለህ?››
‹‹አውቀዋለሁ፡፡››
‹‹እዚያ ተወለድኩ።››
‹‹መቼ ማለት ነው?››
‹‹ቁጥሩን አላውቀውም፡፡ አባቴ አብርሃ ገብረመድህን ንጉሰ ይባላል፡፡ ባረንቱ ሲገደል እኔ የአምስት አመት ልጅ ነበርኩ፡፡››
‹‹አባትሽ መቼ ተገደለ?››
‹‹የጣልያን ወታደር ሆኖ ከእንግሊዝ ጋር ሲዋጋ በዚያው ጦርነቱ ላይ ሞተ፡፡ ጣልያን መውደቁ ላይቀር አባቴ ህይወቱን አጣ፡፡ አሁን ገብቶሃል? በል እንግዲህ እድሜዬን ንገረኝ?››
አሰላሁና ነገርኳት፣
‹‹የተወለድሽው 1936 አካባቢ ነው፡፡ በዚህም የ82 አመት የእድሜ ባለጸጋ ሆነሻል፡፡ እድለኛ ነሽ በ’ውነቱ፡፡››
‹‹እውነት ብለሃል፡፡ Sono molto (በጣም እድለኛ ነኝ፡፡) በሽታ አያውቀኝም፡፡ እርጅና ብቻ ነው ህመሜ፡፡ ያም ሆኖ ቡናዬን ራሴ አፈላለሁ፡፡ ምግብ አዘጋጁልኝ ብዬ አላስቸግርም፡፡››
‹‹ከአባትሽ መገደል በሁዋላ ምን ሆነ?››
‹‹ምንም የሆነ ነገር የለም፡፡ እኔ እዚህ ዕዳጋ አርቢ አክስቴ ዘንድ መኖር ጀመርኩ፡፡ እናቴ ተኽለ ተኽለማርያም ትባላለች፡፡ ደከመኝ የማታውቅ ብርቱ ሴት ነበረች፡፡ ቤት መኻእ ትኖር ነበር፡፡ እዚያም እሄዳለሁ፡፡ እዚህም እኖራለሁ፡፡ በቃ እንደሱ ነበር…››
‹‹ትምህርት ቤት አልሄድሽም?››
‹‹እምቢ አልኩ፡፡ ተለምኜ ነበር፡፡ እናቴ ሁለት ስራ ትሰራ ነበር፡፡ ከጣልያናውያን ቤቶች ትሰራ ነበር፡፡ በፋብሪካም እንዲሁ ትሰራለች፡፡ በጥሩ ሁኔታ ልታስተምረን ትጥር ነበር። ታናሽ ወንድሜ አስመላሽ አብርሃ Scuola Italiana (ጣልያን ትምህርት ቤት) ገብቶ ሲማር እኔ እምቢ አልኩ፡፡ አስመዝግበውኝ ነበር፡፡ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ እያልኩ ከተማ ውስጥ እዞራለሁ፡፡ ጨዋታ ብቻ ሆንኩ፡፡››
‹‹የልጅነት ትዝታሽ ምንድነው?››
‹‹No ho una memoria speciale (ምንም የተለየ ትዝታ የለኝም፡፡) የአክስቴ ባል ስለ ሼኽ ዓምር ሴት ልጅ ማውራት ይወድ ነበር፡፡ ታሪኩን ከየት እንዳመጣው አይታወቅም፡፡ አውርቶ ሲጨርስ ‹እንዳንቺ ቆንጆ ነበረች› ይለኝ ነበር፡፡ ይሄ አይረሳኝም፡፡ ያኔ ገና ልጅ ነበርኩ፡። ቁንጅናዬ ግን ታውቋል፡፡ ቁመቴ ተመዟል፡፡ ሃይለኛ ነበርኩ፡፡ ልጅ ብሆንም ከተቆጣሁ ድመት ነበርኩ፡፡ እቧጨራለሁ:: ለማንም አልመለስም፡፡ ‹እንደ አባቷ ናት› ይሉኛል:: አባቴ እንዴት እንደነበር አላውቅም፡፡ ባረንቱ ላይ ሲሞት ልጅ ነበርኩ…››
ቡና ልታፈላ ምድጃው ተቀጣጥሎ ነበር፡፡
መንከሽከሽ ፈልጋ ጓዳ ገብታ ተመልሳ መጣች፡፡
‹‹…ባረንቱ ላይ በከንቱ ሞተ አባቴ፡፡›› ስትል ወጓን ቀጠለች ‹‹…ክተቱ ብለው ከሰንዓፈ ነበር የወሰዱት፡፡››
‹‹ሰንዓፈ ምን ይሰራ ነበር?››
‹‹ሰንዓፈ ነው አገራችን፡፡ እንግሊዝ እየበረታ ሲመጣ ከተቱ ተባሉ፡፡ ከዚያም ስንቱ የሰንዓፈ ጎበዝ ትዳሩን እየተወ ለጥልያን ወታደር ሆኖ ባረንቱ እየሄደ አለቀ። Ecco, cosa ti dico di an-cora? (በቃ፡፡ ይኸው ነው፡፡ ሌላ ምን ልንገርህ?)
‹‹መማር ነበረብሽ፡፡››
‹‹ልክ ነው፡፡ ‹ተማሪ› ተብዬ እምቢ አልኩ:: ልጅነት አታለለኝ፡፡ አባቴ ባለመኖሩ በቅርብ የሚከታተለኝ ሰው አልነበረም፡፡ ያኔ ተምሬ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ሌላ ሰው በሆንኩ ነበር፡፡››
ትክዝ ብላ አቀርቅራ ቆየችና ቀና አለች፣
‹‹ለምንድነው ታሪኬን የምትጠየቀኝ?››
‹‹ልጽፈው ነው፡፡››
‹‹የሚጻፍ ታሪክ የለኝም፡፡ ተራ ሰው ነኝ፡፡››
‹‹የታሪክ ተራ የለውም፡፡ ይልቁን ቀጥይልኝ?››
‹‹ምን ልንገርህ?››

Monday, 26 August 2019 00:00

የወቅቱ መልዕክት


        “--ችግርን እንደ ንሥር ከላዩ ሆነን ስናየው ግን ቀልሎና ኢምንት ሆኖ ይታየናል። ልንንደው፣ ልናስወግደው እንደምንችል እናምናለን። ከከፍታ
ወርደን ታች ለመድረስ ቁልቁለቱ ይቀለናል፣ ያንን የወረድነውን መልሰን መውጣት ግን ዳገት ይሆንብናል። ሆኖም የት እንደነበርን ማስታወስ
ከዳገቱ የበለጠ አቅም እንዳለን እንድንረዳ ያደርጋል። የወረድነውን ዳገት መልሰን መውጣት ብቻም ሳይሆን ከዚያም በላይ ከፍ ማለት እንደምንችል እንድንረዳ ያደርገናል። ለዚህ ነው ችግርን ለማስተካከል ከመነሣታችን በፊት አስቀድመን ችግሩን የምናይበትን ቦታ ማስተካከል የሚያስፈልገን።
ማረግ የሚያስፈልገንም ለዚህ ነው።-ችግሮቻችንን ከበላያቸው ሆነን ለማየት እንድንችል። ኢትዮጵያን ተብትበው የያዟት አያሌ ችግሮች ሊፈቱና እስከ መጨረሻው ሊወገዱ እንደሚችሉ የሚያምኑም የማያምኑም አሉ። የሁለቱ ልዩነት ካገኙት መረጃና ካካበቱት ዕውቀት የሚመጣ አይደለም። ከቆሙበት ቦታ የሚመነጭ ነው። እንደ አሸንዳ /ሻደይ/አሸንድዬ/ ሶለል፤ ወጣት ሴቶች ለማረግ የወሰኑ፣ ችግሮቹን ከላያቸው ሆነው ያዩዋቸዋል። ራሳቸውንም ከችግሮቹ በላይ ያገኙታል። እንደ እነዚህ ወጣት ሴቶች ለዕርገት ያልተዘጋጁት ግን ራሳቸውን ከችግሮቹ ሥር ወድቀው ያገኙታል። ያኔ ተስፋ ይቆርጣሉ።--”
(ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ፤
ለአሸንዳ /ሻደይ/ አሸንድዬ/
ሶለል በዓል ካስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ
መልዕክት የተቀነጨበ፤ ነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም)

Saturday, 24 August 2019 14:37

የፖለቲካ ጥግ

 ስለ ሕግና ሥርዓት)
• ያለ ሕግ፣ ሰዎች አውሬዎች ናቸው፡፡
ማክስዌል አንደርሰን
• መጥፎ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ፣ ጥሩ ጠበቆች አይኖሩም ነበር፡፡
ቻርልስ ዲከንስ
• ሕግ፤ የሁሉም ንጉስ ነው፡፡
ሔነሪ አልፎርድ
• ሕጎች አይፈጠሩም፡፡ ከሁኔታዎች ውስጥ ይወለዳሉ፡፡
አዛርያስ
• ያለ ሕግና ሥርዓት፣ ብልፅግና ሊኖር አይችልም፡፡
ዶናልድ ትራምፕ
• ያለ ሕግና ሥርዓት፣ ሕዝባችን መኖር አይችልም፡፡
አዶልፍ ሂትለር
• አሶች ከውሃ ሲወጡ ይሞታሉ፤ ሰዎችም ያለ ሕግና ሥርዓት ይሞታሉ፡፡
ዘ ታልሙድ
• የሰዎች ሥልጣኔ የመጨረሻ መመዘኛ፣ ለሕግ ያላቸው አክብሮት ነው፡፡
ልዊስ ኤፍ. ኮርንስ
• የዳኛ ተግባር ሕግ ማውጣት አይደለም - ሕግን መተግበር ነው፡፡
ሶንያ ሶቶማዮር
• ሥርዓት፤ የመንግስተ ሰማያት የመጀመሪያ ሕግ ነው፡፡
አሌክሳንደር ፖፕ
• በጦርነት ወቅት፣ ሕግን ዝምታ ይውጠዋል፡፡
ማርከስ ቱሊዩስ
• ሕግና ሥርዓት የሚመነጩት፣ ከእርስ በርስ መከባበር ነው፡፡
ስቲቪ ዎንደር


Saturday, 24 August 2019 14:36

የፀሃፍት ጥግ

 • አንድ ሺ መጻሕፍትን አንብ፤ ያኔ ቃላት እንደ ወንዝ ይፈሱልሃል፡፡
ሊሳ ሲ
• የመጀመሪያ ረቂቅ፤ ታሪኩን ለራስህ የምትነግርበት መንገድ ነው፡፡
ቴሪ ፕራትሼት
• ምንም ይሁን ምን፣ መጻፍ ጀምር፡፡ ቧንቧው እስኪከፈት ድረስ ውሃው አይፈስም፡፡
ሉዊስ ላሞር
• ያልተነገሩ ታሪኮችን በውስጥህ ከመሸከም የበለጠ ከባድ ስቃይ የለም፡፡
ማያ አንጄሎ
• ጽሁፍ በሽታ ይመስለኛል፡፡ ልታቆመው አትችልም፡፡
ዊሊያም ካርሎስ ዊሊያምስ
• ልብ በል፤ አንተ የራስህ ታሪክ ጀግና ነህ፡፡
ግሬዳ ቦይሌ
• ስለ ራስህ እውነቱን ካልተናገርክ፤ ስለ ሌሎች እውነቱን መናገር አትችልም፡፡
ቪርጂንያ ውልፍ
• የማታ ማታ ሁላችንም ታሪኮች እንሆናለን፡፡
ማርጋሬት አትውድ
• ሁሉም ሰው በራሱ ታሪክ ጀግና ነው፡፡
ማቪ ቢንቺ
• በውስጥህ ታሪክ ካለ፣ መውጣት አለበት፡፡
ዊሊያም ፉልክነር
• አንዳንዴ እውነታ በጣም ውስብስብ ነው፡፡ ታሪኮች ቅርፅ ይሰጡታል፡፡
ዣን ሉክ ጎዳርድ
• በዚህ ምድር ላይ ከታሪክ የሚበልጥ ትልቅ ሀይል የለም፡፡
ሊባ ብሬይ
• ትረካ ከአንባቢያን ጋር የማውራት ዕድል ይሰጣል፡፡
ላውራ ሆሎዌይ
• ዜና፤ የታሪክ የመጀመሪያ ረቂቅ ነው፡፡
ቤን ብራድሊ
• ዩኒቨርስ የተሰራው ከታሪኮች እንጂ ከአቶሞች አይደለም፡፡
ሙሬል ሩኬይሰር
• እግዚአብሄር ሰውን የፈጠረው ታሪክ ስለሚወድ ነው፡፡
ኢሊ ዊሴል

Saturday, 24 August 2019 14:35

የተፈጥሮ ጥግ


 • የአየር ንብረት ለውጥ በአብዛኛው ሰው ሰራሽ ነው፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ
• የአየር ንብረት ለውጥ ላይ መከራከር፣ ምድር ጠፍጣፋ ናት ብሎ እንደ መከራከር ነው፡፡
ቢል ማሄር
• የአየር ንብረት ለውጥ፤ የፖለቲካ ምርጫ ነው::
ማይክ ስሚዝ
• ተልዕኮአችን አንድ ነው፡-ፕላኔቷን መጠበቅና ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ፡፡
ፍራንሶይስ ሆላንዴ
• በዚህ ምድር፣ በአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ የማይጎዳ የለም፡፡
ራጄንድራ ኬ.ፓቻዩሪ
• ለአፍሪካ ዕድገት ትልቁ አደጋ፣ የአየር ንብረት ለውጥ ነው፡፡
ፖል ፓልማን
• የአየር ንብረት ለውጥ፣ የምጽአት ቀን ትንቢት መሆኑ አክትሟል፤ ተጨባጭ እውነታ ነው፡፡
አስትሪድ ኖክልብዬ
• በዚህ ምድር ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው፣ ዓለምን የመለወጥ አቅም አለው፡፡
ኢማ ቶምፕሰን
• የአየር ንብረት ለውጥ፤ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ አይደለም፤ ከደህንነትና ኢኮኖሚ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡
ጆንቶን ፔሪት
• ለፕላኔታችን ትልቁ አደጋ፣ ሌላው ይታደጋታል የሚለው እምነት ነው፡፡
ሮበርት ስዋን
• የአየር ንብረት ለውጥ ችግርን ካልፈታን፣ ድህነትን ፈጽሞ አናጠፋም፡፡
ጂም ዮንግ ኪም
• የአየር ንብረት ለውጥ፣ ለመጪው ትውልድ ሊተው የሚችል ችግር አይደለም፡፡
ፖፕ ፍራንሲስ

Saturday, 24 August 2019 14:32

አገራዊ አባባል

(ስለ እውነት)
• ዋሾዎች ጥሩ የማስታወስ ችሎታ ያስፈልጋቸዋል፡፡
የፈረንሳዮች አባባል
• እውነትን መናገር አደገኛ ነው፤ እውነትን መስማትም አሰልቺ ነው፡፡
የዳኒሽ አባባል
• እውነቱን ተናገር፤ ነገር ግን ከአካባቢው በፍጥነት ልቀቅ፡፡
የስሎቬንያ አባባል
• ገንዘብ ሲናገር፤ እውነት ዝም ትላለች፡፡
የሩሲያውያን አባባል
• የእውነት ወዳጅ ጠላቱ ብዙ ነው፡፡
የታሚል አባባል
• የእውነት ባሪያ፣ እሱ፣ ነፃ ሰው ነው፡፡
የአረቦች አባባል
• ሦስት ነገሮች ለረዥም ጊዜ መደበቅ አይችሉም፡- ፀሐይ፣ ጨረቃና እውነት፡፡
ቡድሃ
• ያለ ጊዜው የተነገረ እውነት አደገኛ ነው፡፡
የግሪኮች አባባል
• ስለ ራስህ እውነቱን መስማት ከፈለግህ፣ ጎረቤትህን አብሽቀው፡፡
የቼኮች አባባል
• እውነትን በድምፁ ትለየዋለህ፡፡
የሂብሩ አባባል
• እውነት የ ትም ይ ወስድሃል - ወ ህኒ ቤ ትም ጭምር፡፡
የፖላንዶች አባባል
• እውነት ቅርንጫፎች የሉትም፡፡
የህንዶች አባባል
• እውነት ብዙ ቃላት አይፈልግም፡፡
የሩሲያውያን አባባል
• ግማሽ እውነት፣ ሙሉ ውሸት ነው፡፡
የአይሁዶች አባባል
• እውነቱን የሚናገር ወዳጆች የሉትም፡፡
የአፍሪካውያን አባባል
• እውነቱን ተናግረህ፣ ሰይጣንን አሳፍረው፡፡
ጥንታዊ አባባል
• የወይን ጠጅና ሕጻናት እውነቱን ይናገራሉ፡፡
የሮማውያን አባባል

Saturday, 24 August 2019 14:27

የዘላለም ጥግ


 • ተስፋ በጨለማ ውስጥም ሆኖ ብርሃንን ማየት ነው፡፡
(Live purposefully now)
• አንድ ጊዜ፣ ተስፋ ማድረግን ከመረጥክ፣ ሁሉም ነገር ይቻላል፡፡
ክሪስቶፈር ሪቭ
• ተስፋ የነቃ ህልም ነው፡፡
አሪስቶትል
• አስቸጋሪ መንገዶች፣ ብዙውን ጊዜ፣ ወደ አስደሳች መዳረሻዎች ይመራሉ፡፡
ያልታወቀ ሰው
• ምርጫዎችህ፤ተስፋህን እንጂ ፍርሃትህን ማንፀባረቅ የለባቸውም፡፡
ኔልሰን ማንዴላ
• ህይወት ባለበት ሁሉ ተስፋ አለ፡፡
JRR Tolkien
• ከፍርሃት ይልቅ ተስፋን ለመምረጥ ድፍረት ይጠይቃል፡፡
ማርክ ዙከርበርግ
• ክዋክብትን ማየት የምትችለው በጨለማ ውስጥ ብቻ ነው፡፡
ማርቲን ሉተር ኪንግ ጄአር
• ተስፋ ማድረግንና ደስተኛ መሆንን አትዘንጋ፡፡
ጆን ማክሊዎድ
• ተስፋ በሌለበት ተስፋን መፍጠር ግዴታችን ነው፡፡
አልበርት ካሙ
• ተስፋ ማድረግ፤ የሚያስወጣው ነገር የለም፡፡
ኮሊቴ
• ተስፋ የደፋር ምርጫ ነው፡፡
ቴሪ ጉይሌሜትስ
• ተስፋ፤ ማርን ያለ አበቦች የሚሰራ ብቸኛው ንብ ነው፡፡
ሮበርት ኢንገርሶል
• በእምነት እንጂ በፍርሃት መኖር የለብንም፡፡
ኤልደር ኪውንቴን ኤል.ኩክ
• ያለ ተስፋ መኖር፣ ከህይወት መፋታት ነው፡፡
ፍዮዶር ዶስቶይቭስኪ
• የፀሐይ መውጣትን ወይም ተስፋን ማሸነፍ የሚችል ጨለማ ወይም ችግር የለም፡፡
በርናርድ ዊሊያምስ


Page 12 of 453