Administrator

Administrator


በየመን ለአመታት የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት በዚህ መልኩ የሚቀጥል ከሆነ፣ አገሪቱ በአለማችን የ100 አመታት ታሪክ ውስጥ እጅግ የከፋ ይሆናል ለተባለ የረሃብ አደጋ ልትጋለጥ እንደምትችል ተመድ አስጠንቅቋል፡፡
ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፤በየመን ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ ያለው ጦርነት መፍትሄ ካልተገኘለትና በሳኡዲ የሚመራው ጥምር ሃይል የአየር ጥቃት መፈጸሙን ከቀጠለ በመጪዎቹ ሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ 13 ሚሊዮን ያህል የአገሪቱ ዜጎች የከፋ ረሃብ ሰለባ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስጠንቅቋል፡፡
በአገሪቱ ለአመታት የዘለቀው ጦርነትና የእርስ በእርስ ግጭት የሰብዓዊ እርዳታ የሚያቀርቡ አለማቀፍ ተቋማትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እያስተጓጎለው እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በቀጣይም አለማቀፉ ማህበረሰብ ለችግሩ ትኩረት በመስጠት ርብርብ ካላደረገ በርካታ ዜጎች በተለይ ደግሞ ህጻናት በከፋ ረሃብ ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል፡፡
የሁቲ አማጽያን ከሶስት አመታት በፊት መዲናዋን ሰንዓን ጨምሮ የአገሪቱን አብዛኛውን ክፍል መቆጣጠራቸውን ተከትሎ የመን በከፋ የእርስ በእርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባቷን ያስታወሰው ዘገባው፣ በሳኡዲ የሚመራው ጥምር ሃይልም አለማቀፍ እውቅና የተሰጠውን መንግስት በመደገፍ ከአማጽያኑ ጋር ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡የላይቤሪያው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ዊሃ በሁሉም የአገሪቱ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች በክፍያ ሲሰጥ የቆየው ትምህርት በነጻ እንዲሆን መወሰናቸውን ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርገዋል፡፡
በአገሪቱ ትልቁ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የሆነውን ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላይቤሪያን ጨምሮ በአራቱም የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሽራፊ ሳንቲም ሳይከፍሉ በነጻ ትምህርታቸውን መከታተል እንደሚችሉ ፕሬዚዳንቱ ባስተላለፉት መልእክት አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የክፍያ መቅረት ብስራቱን ያሰሙት በመዲናዋ ሞንሮቪያ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ላይቤሪያ በመቶዎች ከሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ጋር በተገናኙበት አጋጣሚ መሆኑን የዘገበው ቢቢሲ፣ በወቅቱ ተማሪዎቹ በደስታ ምላሽ መስጠታቸውንና በመላ አገሪቱ የሚገኙ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም የፕሬዚዳንቱን ብስራት በደስታ እንደተቀበሉት ጠቁሟል፡፡
ፕሬዚዳንት ዊሃም፤ ትምህርት በነጻ እንዲሰጥ ያሳለፉትን ውሳኔ ሌሎች የአፍሪካ አገራትም በአርአያነት ሊከተሉት እንደሚገባ መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በአገሪቱ የዩኒቨርሲቲዎች ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉ ተማሪዎችንና ወላጆችን ክፉኛ ሲያስቆጣና አመጽ ሲቀሰቅስ እንደነበር ያስታወሰው የቢቢሲ ዘገባ፣ በቅርቡም የአንድ ክሬዲት አወር ክፍያ በግማሽ ያህል መጨመሩ ተቃውሞ ቀስቅሶ እንደነበር አስታውሷል፡፡ የኢትዮጵያ አዋላጅ ነርሶች ማህበር 27/ኛውን አመታዊ ጉባኤ Oct/12-13/2018/ በአዲስ አበባ አካሄዶአል፡፡ በጉባኤው ላይም በተለያዩ መስተዳድሮች ባሉ የህክምና ተቋማት የሚያገ ለግሉ አዋላጅ ነርሶች እንዲሁም ከተለያዩ የሚመለከታቸው መስሪያ ቤቶች የተወከሉ ባለሙያዎች ተሳት ፈዋል፡፡ ጉባኤው በሁለት ቀን ቆይታው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደረገ ሲሆን በተጨማሪም የምርምር ጽሁፎችም ቀርበው ነበር፡፡ ከቀረቡት የምርምር ጽሁፎች ውስጥ አንዱ በቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ ለተጠቃሚዎች የሚሰጠውን የምክር አገልግሎት ጥራትና ብቃት እን ዲሁም መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች የጠቆመው አንዱ ነበር፡፡ ይህን የምርምር ጽሁፍ ያቀረ ቡት ዶ/ር እውነት ገብረሀና ናቸው፡፡ ጥናቱ የያዛቸውን ቁም ነገሮች እንደሚከ ተለው ለንባብ ብለናል፡፡
የቤተሰብ እቅድ ዘዴን የምክር አገልግሎት በሚመለከት በኢትዮጵያ፤ በሜክ ሲኮና በህንድ ጥራቱን የጠበቀ እና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መረጃን በሚፈ ለገው ደረጃ ለመስጠት እንዲቻል ለማድረግ የተሰራ ጥናት ነው፡፡ ይህንን ጥራቱን የጠበቀ የምክር አገ ልግ ሎት በሚመለከት አገልግሎት በሚሰጥባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ዳሰሳ መደረጉን መረ ጃው ይጠቁማል፡፡
በኢትዮጵያ የጤናው አገልግሎትን በጥራትና በእኩል የማዳረስ ተግባር በጤናው የልማት እቅድ ውስጥ ከተነደፉት እቅዶች ዋነኛው ግብ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡ የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስ ቴር በነደፈው ብሔራዊ አጀንዳ ውስጥ የጥራት ተግባር አንዱ ሲሆን  ጥራትንም ማሻሻል ሌላው በትኩረት እየተሰራበት ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ ጥናት ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጥ ራት ማሻሻል ፕሮግራም አስተዋጽኦ ያደርጋል በሚል እንደሚታመን ዶ/ር እውነት ገ/ሐና ገልጸዋል፡፡
ይህ ጥናት በተለይም ሴቶች በቤተሰብ እቅድ ዘዴ አገልግሎት የምክር አሰጣጥ ላይ ምን ልምድ አላቸው? የሚለውን ከተጠቃሚዎች ለማወቅ ሙከራ አድርጎአል። ለዚህም በአዲስ አበባ በጉለሌ ክፍለ ከተማ በሚገኙ /4/የጤና ጣቢያዎች እንዲሁም /8/ የሚሆኑ የቡድን ውይይቶች /52/የቤ ተሰብ እቅድ ዘዴ ተጠቃሚ ሴቶች እንዲሁም በጉዳዩ ዙሪያ ቀደም ሲል ከተደረጉ የዳሰሳ ጥና ቶች የተፈተሸ ሲሆን ውጤቱም እንደሚከተለው ነው፡፡
በጥናቱ እንደተገኘው እውነታ ብዙ ሴቶች አገልግሎቱን የሚሰጡ ባለሙያዎች የሚሰጡትን ምክር እና ጥቆማ በቀላሉ የሚቀበሉ ወይንም የሚያምኑ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የበለጠ እውቀት አላቸው ብለው የሚያምኑት በቀጥታ እነሱ ያገኙዋቸውን የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሰጪ ዎችን ሆኖ ተገኝቶአል፡፡
አገልግሎት ሰጪዎች ተገልጋዮቻቸውን እንዲያዳምጡ፤ ክብር እንዲሰጡ፤ የተገልጋዮችን የግል ምስጢርን እንዲጠብቁ እና እምነት እንዲጣልባቸው እንዲሁም ከደንበኛቸው የሚነገራቸውን በጥንቃቄ እንዲያደምጡ እና እንዲተገብሩ እንደሚፈለግ ከተገልጋዮች የተገኙ ምስክርነቶች ያረጋግጣሉ። ብዙ ሴቶች እንደተናገሩትም ‹‹…አገልግሎት ሰጪዎች የሚናገሩትን እንድንሰማ ብቻ ሳይሆን እንዲ ያውም ጥያቄ እንድንጠይቅና የምናውቀውን ወይንም የምናምንበትን ነገር እንድንናገር እንዲያበረታቱ ይጠበቅባቸዋል…›› ብለዋል።
ጥናቱ እንደደረሰበት ከሆነ አንዳንድ ሴቶች ካለምርጫቸው ያልተፈለገ እርግዝና መከላከያውን እንዲወስዱ በአገልግሎት ሰጪዎች ግፊት እንደሚደረግባቸው እና ይህም እምነት እንዲያጡ የሚያ ስችል ድርጊት በመሆኑ ምናልባትም ሴቶች ተመልሰው ወደ አገልግሎት መስጫው እንዳይሄዱ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ይገመታል፡፡
የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ላይ የሚሰጠው የምክር አገልግሎት የተገልጋይዋን የግል መብት እና በራስ የመተማመን ሁኔታዋን የማያበላሽ እና የተከበረ እንዲሆን ተገልጋዮች ይፈልጋሉ፡፡ ደንበኞች የግል መብታቸው ካልተከበረ በተቃራኒው መናገር ወይንም የመናደድ ሁኔታ ሊያሳዩ እና የአገልግሎት መሰኩን ወዳለማክበር ሊሸጋገሩ እንደሚችሉ ማወቅ ለአገልግሎት ሰጪው ይጠቅማል፡፡
አብዛኞቹ የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ተገልጋዮች አገልግሎት ሰጪዎቹ ከተገልጋይ ጋር ሲገናኙ በሚ ኖረው መግባባት ወይንም መነጋገር በሚያስፈልግበት ጊዜ የበለጠ እድል ወይንም ኃይል እንዳ ላቸው ያምናሉ፡፡እንደነዚህ አይነት ሴቶች አገልግሎቱን ለማግኘት በሚኖረው ማንኛውም ድርጊት በትእግስት መጠበቅን ይመርጣሉ፡፡ ለምሳሌም ብዙ ሰአት መጠበቅ ወይንም በአገል ግሎት አሰ ጣጡ ጎደሎ ነገር ቢመለከቱም በትእግስት ሁኔታውን ከመከታተል ውጪ ምንም እርምጃ አይወስዱም ወይንም ጥያቄ አይጠይቁም፡፡
በጥናቱ ከተመለከተው እና ለጥራት አጋዥ ከተባሉት ውስጥ መረጃን የሚመለከት ይገኝበታል፡፡ ከአንዳንድ ተገልጋዮች እንደተገኘው እማኝነት ከሆነ የተለያዩ ያልተፈለገ እርግዝናን ለመከላከል የሚያስችሉ አገልግሎቶችን ከራሳቸው ምርጫ ውጪ መውሰድ እንደሚችሉ እንደተነገራቸው ይገልጻሉ፡፡ የመከላከያ አይነቶቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
በክንድ ውስጥ የሚቀበር (NorPlant)
ሉፕ በመባል የሚታወቀው (IUD)
በመርፌ መልክ የሚወሰድ
በኪኒን መልክ የሚወሰድ ነው፡፡
የምክር አገልግሎት ሰጪዎቹ የእያንዳንዱን መከላከያ ዘዴ ጥቅም እና ጉዳት በሚመለከት መረጃ ለተገልጋዮቹ የሚሰጡ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ተገልጋዮቹ ምንም ማብራሪያ ሳይሰ ጣቸው እራሳቸው የመሰላቸውን ወይንም የፈለጉትን ለመውሰድ ወስነው መጠቀም እንደሚ ጀምሩ ተናግረዋል፡፡  
የምክር አገልግሎቱን በሚመለከት ተጠቃሚዎች እንደመሰከሩት የሚነገራቸው ትእዛዛዊ በሆነ መልኩ ይሔንኛው ቢወሰድ ይሻላል በሚል አይነት ሲሆን ለዚህም በክንድ ውስጥ የሚቀበርና ሉፕ የተሰኘውን ዘዴ እንዲመርጡ እንደሚያደርጉዋቸው ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መርፌ ውንና በኪኒን መልክ የሚወሰደውን ጤናማ እንዳልሆኑና ብዙ ተያያዥ የሆኑ ችግሮችን እንደ ሚያስከትል የሚናገሩ የምክር አገልግሎት ሰጪዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
…አንዲት ሴት ከወለደች በሁዋላ በተሰጣት የምክር አገልግሎት ሉፕ የተሰኘውን የመከላከያ ዘዴ ብትወስድ እንደሚሻላት ስለተነገራት እሱዋም እንዲያውም በየጊዜው ወደጤና ተቋሙ እንዳትመላለስ እንደሚረዳት በማመን እንደተቀበለችው ተናግራለች፡፡
በተለያዩ ስፍራዎች ያሉ አማካሪዎች ከሚሰጡት ምክር በመነሳት ሴቶች የአጭር ጊዜ ያልተ ፈለገ እርግዝና መከላከያን ማግኘት እንደማይችሉ አንዳንዴም አቅርቦት እንደማይኖር የመሳሰ ለው ምክንያት ሁሉ ስለሚነገራቸው ብዙዎች ሴቶች ካለምርጫቸው ለረጅም ጊዜ መከላከያ እንደ ተጋለጡ በጥናቱ ግንዛቤ ተወስዶአል፡፡   
አንዲት የ24/አመት እድሜ ያላት ወጣት የሚከተለውን ምስክርነት ሰጥታለች፡፡
‹‹….በመርፌ የሚወሰደውን መከላከያ መውሰድ እፈልጋለሁ ስላቸው እነርሱ ግን እኔ እንድ ወስድ የመረጡት ሉፕ የተሰኘውን ነበር፡፡ እኔ እንደምገምተው …ተገልጋዩ በየጊዜው እየሄደ እንዳያሰለቻቸው የረጅም ጊዜውን ሰጥተው ለመገላገል ያሰቡ ይመስለኛል፡፡እነርሱ የመረጡትን መከላከያ እኔ አላውቀውም፡፡ ወደፊት ምን ጉዳት እንደሚኖረው ምንም ሀሳብ የለኝም፡፡ …›› ነበር ያለችው፡፡
የጥናቱ መደምደሚያ የሚያዘነብለው የተገልጋዮችን ፍላጎት ማስቀደም ይገባል ወደሚለው ነው፡፡ በእርግጥ ብዙ ሴቶች በምክር አገልግሎቱ በተገቢው መንገድ ተገልግለናል ቢሉም በምክር አገል ግሎት አሰጣጡ ምንም አልረካንም ያሉም ቀላል ቁጥር የላቸውም፡፡
ሴቶች ለሚያነሱዋቸው ጥያቄዎች ተገቢው መልስ አይሰጥም፤
የሚወሰደውን መከላከያ በሚመለከት ስላለው ባህርይ ሙሉ መረጃ አለመስጠት፤
በአማራጭ ሊወሰድ ስለሚችለው የመከላከያ ዘዴ መረጃን አለመስጠት…ወዘተ
ጥናቱ በማጠቃለያው የጠቆመው የቤተሰብ እቅድ ዘዴ የምክር አገልግሎት ሰጪዎች ለተገል ጋዮች ከፍተኛ የሆነ ክብር የሚሰጡ እና እምነት የሚጣልባቸው ከሆኑ ጥራት ላለው የቤተሰብ እቅድ ዘዴ ምክር አገልግሎት አሰጣጥ መሰረት ይሆናል፡፡
የምክር አገልግሎት አሰጣጡ ደንበኞች ስለአገልግቱ ተገቢውን መረጃ እንዲያገኙ በማድረግ እና ባጠቃላይም ተገልጋዩን ያማከለ ቢሆን ጥራት ያለው የምክር አገልግሎት መስጠት ያስችላል… ውጤቱም ይሰምራል ሲል በዶ/ር እውነት ገ/ሐና የቀረበው ጥናት መረጃውን ያጠቃል ላል፡፡

Sunday, 28 October 2018 00:00

“ወርደን እናየዋለን!”

ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጎረቤታም ገበሬዎች ስለሚዘሩት እህል ይመካከራሉ፡፡
አንደኛው -
“ዘንድሮ ምን ብንዘራ ይሻላል?”
ሁለተኛው -
“በቆሎ ብንዘራስ?”
አንደኛው -
“አዬ በቆሎ አይሆንም፡፡ በቆሎ በቀላሉ በእንስሳቱ ስለሚጫር አያስተርፉልንም፡፡”
ሁለተኛው -
“እንግዲያው ባቄላ ይሁና?”
አንደኛው -
“አዬ እሱማ አልሸሹም ዞር አሉ ነው”
ሁለተኛው -
“ካልሆነ ማሽላ ይሁና?”
አንደኛው -
“ማሽላ ደግሞ ገና ከመሬት ብቅ ሳይል የወማይ ወፍ መጫወቻ መሆኑ ነው፡፡”
ሁለተኛው -
“አሁን እኛን በጣም የሚያስፈራን እህሉ ከመሬት ብቅ ሳይል ተጭሮ መበላቱ ነው እንጂ ከበቀለማ በኋላ ጠባቂ እናስቀምጥለታለን፡፡”
አንደኛው -
“ይልቅ አንድ ዘዴ ታየኝ”
ሁለተኛው -
“ምን ታየህ?”
አንደኛው
“ወጣም ወረደ የሚያስቸግሩን ዝንጀሮና ጦጣ ከሆኑ፣ መንገዳችን ላይ አንዳቸውን ማግኘታችን አይቀርም፡፡ ያልዘራነውንና ለእነሱ የማይመቻቸውን እህል ጠቅሰን ለምን አናታልላቸውም?”
ሁለተኛው -
“በጣም ድንቅ መላ ነው”
በዚህ ተስማምተው በቆሎ ዘርተው ሲመለሱ፣ ጦጢት ዛፍ ላይ ሆና አገኙዋት፡፡
ጦጢት
“አያ ገበሬ?”
ገበሬ
“እንዴት ከርመሻል ጦጢት?”
ጦጢት
“ዘንድሮ ምን ዘርተህ መጣህ?”
ገበሬ -
“ተልባ፡፡ ተልባ ዘርቼ መጣሁ፡፡”
ገበሩው ይሄን ያለው ጦጣ ተልባ ጭራ ማውጣት እንደማትችል ስለሚያውቅ ነው፡፡
ጦጢትም፤
“ይሁን፡፡ ወርደን እናየዋለን!” አለችው፡፡
***
እኛ ስለ ሌሎች ደካማ ጎን ስናስብ፣ እነሱስ ስለኛ ደካማ ጎን ምን ያስባሉ? ብሎ ማሰብ ከብዙ ስህተት ያድነናል፡፡ አስቀድሞ ነገር በሌሎች ደካማ ጎን በመጠቀም ዕድገትን ማሰብ ተላላነት ነው፡፡ “እዛም ቤት እሳት አለ” የሚለውን ተረት ማጤን እጅግ ተገቢ የሆነበት ወቅት ላይ መሆናችንን እናስተውል፡፡ ክልልና ክልል፣ ፓርቲና ፓርቲ፣ ድርጅትና ድርጅት፣ ቡድንና ቡድን ቀና ውድድር ቢያደርጉ እንጂ በመሻኮትም ሆነ በመጠላለፍ ከቶም ትርፍ አያገኙም፡፡ ቀና ያልሆነውን መንገድ ለዘመናት እንደማያዋጣን አይተነዋል፡፡ በጠረጴዛ ውይይት ካልሆነ የማይፈቱ አያሌ ችግሮች እንዳሉብን እየታወቀ፤ መልሰን ግጭትና ሴራ ውስጥ መዘፈቅ ውሃ ወቀጣ ከመሆን አይዘልም፡፡
“እኛ ሳንስማማ
እኛ እየተባላን
መቼም ሳንቻቻል
እንኳን ሰማዩና መሬቱም ይርቃል!”
ስለ ሰላም እያወራን፣ ስለ ፍቅር እየሰበክን፣ ስለ እርቅ እያወሳን ወዘተ … መልሰን ከተጋጨን የተጫረው ብርሃን ይጨለመለማል፡፡ የለኮስነው ቀንዲል ይጠፋል፡፡ ያቀድነው ዲሞክራሲ፣ እናጠራዋለን ያልነው ፍትህ ሁሉ
“ወጣ ወጣና እንደሸምበቆ፣ ተንከባለለ እንደሙቀጫ” ይሆንብናል፡፡
ምንም እንኳ የተያያዝነው የለውጥ ሂደት ዕድሜው አጭር ቢሆን፣ ገና ዳዴ እያልን ነው ብለን ስህተት እያየን እንደ ፍጥርጥሩ ማለት አንችልም፡፡ ባወጣ ያውጣው ብለን ጥፋትን ሳንዳኝ፣ ችግርን በሰዓቱ ሳንፈታ መጓዝ “ሃማሊያን በሁለት ቆራጣ እግር” እንደሚባለው ይሆንብናል፡፡ ገና ብዙ ዳገት እየጠበቀን ሜዳው ላይ ከደከምን “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ይሆናል፡፡ ከውጪው ዓለም ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና ኢኮኖሚያዊ ስምምነት መፈራረማችን በጎ ጎናችን የሆነውን ያህል፤ የውስጥ ችግራችንን በወቅቱ አለመፍታት አገርን ስጋት ላይ መጣል ነው፡፡ ችግራችን ከላይ ከላይ እንደሚወራውና የሚለባበስ ነገር አይደለም፡፡ ግልጥ ያለና አስጊ ነው፡፡ እንደ ጦጣዋ “ወርደን እናየዋለን” ማለት ዞሮ ዞሮ ጥቅሙ ለእኛው ነውና፣ መሬት የረገጠ ነገር እንሥራ፡፡
ዛሬም፤
“… ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ ያበራውን እንዲወጣ ማድረግ” ብንል ይሻላል!
ልዩ ልዩ ሹመቶች እየተሰጡና ተቋማት እየተጠናከሩ መሆኑ ደግ ነገር ነው፡፡ ሹመኞች ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ አይወጡም የሚለው መለኪያው ጊዜ ቢሆንም ቢያንስ ሙስና ውስጥ አይዘፈቁም የሚል ዕምነት አለን፡፡ ተስፋችን ትልቅ ነው፤ ጉዞው ጠመዝማዛ ነው - ጥናቱን ይስጣችሁ ማለት የአባት ነው!

• ሁለንተናዊ ለውጥ ያመጣል የተባለ መሪ ዕቅድ እንዲተገበር ተወስኗል
• ኅብረቱ በትግበራው ለመሳተፍና እስከ ግንቦት ለውጡ እንዲታይ ጠይቋል

  ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመዋቅርና የአሠራር ችግሮች ኹነኛ መፍትሔ በመስጠት ሁለንተናዊ ለውጥ ለማምጣት እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውና በአምባሳደር ካሳ ከበደ
የሚመራው የአእላፋት ድምፅ የካህናትና ምእመናን ኅብረት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ፊት ቀርቦ የአስተዳደር ለውጥ አቋሙን አስረዳ፤ ቅዱስ ሲኖዶሱም በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ
ምላሽ እንደሚሰጥ ለኅብረቱ ተወካዮች አስታውቋል፡፡ የብዙ ሺሕ ካህናት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ መንፈሳውያን ማኅበራት፣ የአገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ምእመናን ተወካዮች የኾኑና በአምባሳደር ካሳ ከበደ የሚመሩ 9 የኅብረቱ ልኡካን፣ ትናንት፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በመሪ ዕቅድ በመመራትና የምእመናንን ከፍተኛ ተሳትፎ በማረጋገጥ ማምጣት ስላለባት አስተዳደራዊ ለውጥ ያላቸውን አቋም በመካሔድ ላይ
በሚገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ስብሰባ ላይ ማስረዳታቸውን ምክትል ሰብሳቢው አርክቴክት ዮሐንስ መኰንን ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል፡፡ “ለቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ ለውጥ የካህናትንና የምእመናንን አቤቱታ ስለማቅረብ” በሚል ርእስ በንባብ በተሰማው ጽሑፍ፣ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች በጥናት የተደገፈ አስቸኳይ እርምት አለመስጠት፣ ተግባራዊ እንዲኾኑ ውሳኔ የተላለፈባቸው ጥናቶች አስፈጻሚ ማጣትና በስፋት አለመታወቅ ሁከትና ብጥብጥን እያስፋፋና ለህልውናዋ ቀጣይነትም አደጋ እያስከተሉ እንደኾነ ተጠቅሷል፤ ቅዱስ ሲኖዶሱ በአሁኑ ስብሰባው፣ ለቤተ ክርስቲኒቱ ሁለንተናዊ ለውጥ ወሳኝ የኾነው የመሪ ዕቅድ ጥናት፣ የትግበራ ጽ/ቤት ተቋቁሞለት ወደ ሥራ እንዲገባ መወሰኑና የ2.5 ሚሊዮን ብር መነሻ መመደቡን ኅብረቱ አድንቆ፣ በትግበራው ሒደት ቅዱስ ሲኖዶሱ መመሪያ ሊሰጥባቸው ያስፈልጋል ያላቸውን አምስት ዋና ዋና ጥያቄዎቹን ማቅረቡን አርክቴክት ዮሐንስ አስረድተዋል፡፡
የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤቱ መቋቋሙን የሚከታተልና የሚያስፈጽም አካል ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት እና ከባለሞያ ምእመናን ቅዱስ ሲኖዶሱ በዚሁ ስብሰባው እንዲሠይም፤ ጽ/ቤቱ  ከሚቀጠሩለት መደበኛ ባለሞያዎች ባሻገር አስፈላጊውን የሰው ኃይል ማሟላት እንዲችልና ተግባሩን በአግባቡ እንዲወጣ ሙሉ ነፃነትና ሥልጣን እንዲሰጠው፤ አባላቱም እንደ ሞያቸው  በባለቤትነት መሳተፍ እንዲችሉ ኅብረቱ ጠይቋል፡፡ መሪ ዕቅዱ ቢያንስ፣ በግንቦት ወር እስከሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ድረስ ዋና መሥሪያ ቤት በኾነው በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ጽ/ቤትና የአህጉረ ስብከት ማዕከል  በኾነው በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ደረጃ ተተግብሮ የለውጡ ተስፋና ምልክት መታየት እንዲጀምር ኅብረቱ አመልክቷል፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ በየዓመቱ በሚካሔደው አጠቃላይ ጉባኤ  ላይ የምእመናን ውክልና በሕጉ መሠረት እንዲጠበቅና የምእመናን ተሳትፎ በከፍተኛ ደረጃ የሚረጋገጥበት ሥርዐትና አሠራር በሚዘረጋበት ኹኔታ ላይ ቅዱስ ሲኖዶሱ ትኩረት ሰጥቶ
እንዲመክር ኅብረቱ ጠይቋል፡፡
የኅብረቱን ጥያቄዎች ምልዓተ ጉባኤው እንደሰማ የገለጹት ርእሰ መንበሩ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ፣ ቅዱስ ሲኖዶሱ በጥያቄዎቹ ላይ መክሮ ውሳኔውን እንደሚያስታውቅ
መናገራቸውን የኅብረቱ ልኡካን ገልጸዋል፡፡
ከ2006 እስከ 2009 ዓ.ም፤ ሊቃነ ጳጳሳትን፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ጨምሮ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ ለውጥ የሚገዳቸው ከፍተኛ ኤክስፐርቶች በሦስት ጥራዝ
አጥንተው ያቀረቡት የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ማዘመኛ ጥናት በቅዱስ ሲኖዶስ ተቀባይነት ካገኘ በኋላ እንዳይተገበር ለውጡን በማይፈልጉ አካላት ታግዶ መቆየቱን የኅብረቱ
ም/ሰብሳቢ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን ለአዲስ አድማስ አስረድተዋል፡፡

   (“ዘ ያንግ ክሩሴደር”)
 የመጽሐፉ ርዕስ- “ዘ ያንግ ክሩሴደር”
 ደራሲ- ሰለሞን ኃይለ ማሪያም
 የገጽ ብዛት - 220
 ሒሳዊ አስተያየት - በተሾመ ብርሃኑ ከማልበደራሲ ሰለሞን ኃይለማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› (ማህበራዊ ንቅዘትን በወኔ የተፋለመው ወጣት) በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ ተደርሶ፣ በ2003 ዓ.ም በኮድ ኢትዮጵያ ለህትመት የበቃው መጽሐፍ፤ በ2010 ዓ.ም ወደ ጀርመንኛ ለመተርጎም በቅቷል፡፡ መጽሐፉ ወደ አማርኛ ከመተርጎሙ በፊት ወደ ጀርመንኛ ተተርጉሞ ለንባብ መብቃቱ የሚገርም ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ በኢትዮጵያዊ ደራሲ የተጻፈና ያነሳው ርዕሰ ጉዳይ ትምህርታዊ ከመሆኑ አንጻር፣ ይህን የሥነ ጽሁፍ ሥራ በመገምገም እግረ መንገድም ማስተዋወቅ  ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  

የመጽሐፉ መጠንሰስ
በነሐሴ ወር 2003 ዓ.ም ላይ ኮድ ኢትዮጵያ እና ኮድ ካናዳ የተባሉ አጋር መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፤ ዕድሜያቸው ከ12-18 ለሆኑ ወጣት አንባቢያን የሚመጥን የልቦለድ ታሪክ (የስነጽሑፍ) ውድድር አዋጅ ያስነግራሉ፡፡ ተወዳዳሪዎች  የሚያቀርቡት የልቦለድ ሥራ፤ ከዘመኑ ማኅበራዊ  ሕይወት ጋር የተዛመደ፣ ወጣቶች የማህበረሰቡ አባላት በመሆናቸው፣ በአፍላ ዕድሜያቸው ፊት ለፊት የሚጋፈጡት የማህበራዊ ሕይወት ቀውስ ፈተና ምን እንደሚመስል  የሚያንጸባርቅ  ወይም በሀገሪቱ ማህበራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ታስቦ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያሳስብ ነበር- የውድድር መመሪያው፡፡
ደራሲ ሰለሞን ኃይለ ማሪያም፤ ይህንን የውድድር መመሪያ ከመረመረ በኋላ ተልእኮው የማህበረሰቡን ቁስል ማወቅና የማህበራዊ ጠንቁን ዓይነት፣ ምንነት፣ ስፋትና ጥልቀት መጠቆም ብቻ ሳይሆን መፍትሔው ምን እንደሆነ ለመጠቆምም ውድድሩ መልካም አጋጣሚ የፈጠረለት ይመስላል፡፡ በዚያ ወርቃማ አጋጣሚም፣ በደራሲው ውስጥ ሲብሰለሰል የኖረው ማህበራዊ ንቅዘት፣ አድማሱ ስዩም ብሎ በቀረጸው ዋነኛ ገጸ ባህርይው አማካኝነት መፍሰስ ጀመረ፡፡

ታሪኩ
አድማሱ የተባለው ዋነኛ ገጸ ባህርይ፣ ገና ከልጅነት ዕድሜው ጀምሮ ወደ ሥራ ዓለም እስከ ተሰማራበት ጊዜ ድረስ ሙሰኝነትን የተዋጋ ቅን ዜጋ ነው፡፡ ተማሪ ሳለ ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ፣ ሰዎች የተፈጨ በርበሬን ከደቀቀ ጡብ ጋር እየቀላቀሉ ለሽያጭ ሲያዘጋጁ ይመለከትና፣ ለፖሊስ ይጠቁማል። ይህም በጓደኞቹ ዘንድ እንዲታወቅና መልካም አርአያ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በሁለተኛ ጊዜ የትምህርት ቤቱ ርእሰ መምህር ጉቦ እየተቀበሉ፣ መጠኗ አነስተኛ በሆነች ክፍል ተጨናንቀው ምን እንደሚያደርጉ  ይገነዘብና፣ ያንን አሳፋሪ ተግባር ያጋልጣል፡፡ የርዕሰ መምህሩም ጉዳይ በአድማሱ ጥቆማና ክትትል  ወደ ወላጅ ኮሚቴ ቀርቦ ከሥራቸው  ይባረራሉ፡፡ አድማሱ የ12ኛ ክፍል ትምህርቱን ጨርሶ በአንድ ዕቃ መለዋወጫ መሸጫ መደብር ሲቀጠርም፣ አጭበርባሪዎች ይገጥሙትና፣ ፊት ለፊት ተጋፍጦ፣ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ያደርጋል፡፡
ይሁንና በሕይወት የሚገጥምን ፈተና ፊት ለፊት ተጋፍጦ ማለፍና በአሸናፊነት የመወጣት ጉዞ  አልጋ ባልጋ ሊሆን አይችልም፡፡ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲል  በጀግንነት በመታገሉ ሊያሸልመው፣ ሊያስመሰግነውና ሊያስከብረው ሲገባ በሐሰት መረጃ ይወነጀላል። በዚህም ብዙ  እንግልት ይደርስበታል፡፡ ሆኖም  የሚገጥመውን ፈተና በጽናት  ይወጣዋል፡፡
ከካበተ የሕይወት ልምዳቸውና ዕውቀታቸው የሚያካፍሉት የገነተ ልዑሉ የምርምር ተቋም ባልደረባ የሆኑት ሽማግሌው አቶ ንጋቱ፤ በአድማሱ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ ስፍራ ይዘው እናገኛቸዋለን፡፡ ያለ ማቋረጥ በመለወጥ ላይ በምትገኘው ዓለም ውስጥ እራስን ከለውጡ ጋር አስማምቶ መጓዝ፣ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ  መሆኑን ከምሁሩ አንደበት እንገነዘባለን፡፡ ስለ ቤተሰብ ምጣኔ፣ ራዕይ ስላላቸው ወጣቶችና ፊት ለፊት የሚጠብቃቸውን የሕይወት ፈተና እንደምን ተጋፍጠው ድል እንደሚያደርጉት መጽሐፉ አቅጣጫ ያመላክታል፡፡

የልቦለዱ ጭብጥ
ታሪኩ የሚፈጸመው በመዲናችን አዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስፍራዎች ሲሆን ዘመኑም ያለንበት ነው፡፡ የታሪኩ ምንጭም በማህበራዊ ንቅዘት የተዘፈቀው ህብረተሰብ ነው፡፡ የመጽሐፉ ዋነኛ ጭብጥ፤ ማህበራዊ ንቅዘት ለእድገታችን ጸር ነውና እንዋጋው፣ ወደዚህም የውጊያ መስክ ነገ ኃላፊነትን የሚረከበውን ወጣት ትውልድን አስገብተን፣ በለጋ ዕድሜው በማሰልጠን፣ በደመ ነፍስ ሳይሆን በስልት እንዲዋጋው እናስችለው በሚል መሠረታዊ ሐሳብ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው፡፡ ጋናዊው ደራሲ አርማህ፤ ‹‹ዘ ቢዩቲፉልስ አር ኖት የት ቦርን›› (ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም) በሚል ርእስ እ.ኤ.አ በ1968 ለንባብ ባበቃው መጽሐፉ፣በወቅቱ የነበረውን ማህበራዊ ንቅዘት እንዳሳየውና ካሜሩናዊው ደራሲ ፈርዲናንድ ኦዮኖ፤ «ቦይ» ወይም «ዘ ሐውስ ቦይ» በተሰኘው መጽሐፉ፤ የነጮችን ደካማ አስተሳሰብ እያዋዛ እንደሚተቸው ሁሉ፣ ሰለሞንም እያዋዛ ማህበራዊ ሕጸጻችንን ሊነግረን ይሞክራል፡፡ «ዘ መኒይ ኦርደር» የተሰኘ መጽሐፍ የጻፈው ሴኔጋላዊው ደራሲ ዑስማኔ ሰንባኔ «ኒው ዮርክ ታይምስ» እና «ታይምስ» ከመሳሰሉ መጽሔቶች ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ላይ ሲናገር፤ «ያደረግሁት ነገር ቢኖር አፍሪካውያን ያልተገሰሰ ድንግል የኪነ ጥበብ ሐብት በውስጣቸው እንዳላቸው ማሳየት ነው፤ መቸም አንድ ሰው ሲፈጥር አገሩን እንጂ ዓለምን እያስተነተነ አይፈጥርም። በመሠረቱም በአፍሪካ ውስጥ ለውጥ ሊያመጡ የሚችሉት አፍሪካውያን እንጂ አሜሪካዊያን ወይም ፈረንሳውያን ወይም ሩሲያውያን ወይም ቻይናውያን ሊሆኑ አይችሉም፡፡» ብሏል፡፡ ሰለሞን ኃይለማሪያም በመጽሐፉ ያሳየን ይህንኑ ነው፡፡  
የመገምገሚያ አውድ
በመሠረቱ፣ በሀገራችን ያለው ማህበራዊ ንቅዘት ምን እንደሚመስል ለማወቅ ሩቅ መሄድ አያስፈልግም። አንድ ህጻን ልጅ ለመላክ መደለያ በመስጠት ይጀመራል። በትምህርት ቤት ‹‹ካስኮረጅከኝ ይህን አደርግልሃለሁ›› በሚል ይቀጥላል፡፡ “የሚያስፈራራኝን ከመታህልኝ ገንዘብ ከየትም አምጥቼ እሰጥሃለሁ” ወደሚል የሚታለፈውም በልጅነት ዘመን ነው። በቤት ብቻ ሳይሆን በጎረቤት፣ በቀበሌ፣ በመንደር፣ በትምህርት ቤት በመደለያ፣ በጉቦ፣ በሸፍጥ፣ አስመስሎ በመንገርና በማስመሰል የሚታዩ፣ የሚሰሙና የሚደረጉ ብዙ ማህበራዊ ህጸጾች አሉ፡፡  እድሜ ከፍ እያለ በሄደ መጠን የማህበራዊ ቀውሱ ዓይነትና መጠን እያደገ እንደሚሄድም አያጠያይቅም፡፡
የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ባቀረበው አንድ የታተመ ጥናታዊ ጽሑፍ ላይ እንደጠቆመው፤ «ጉቦ» ለሚለው ቃል አዲስ የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ «ፍርድን ለማጣመምና ሐሰትን ዕውነት ለማስመሰል ለሐሰተኛ ዳኛ የሚበረከት መማለጃ ነው፡፡ ስለሆነም ጉቦ በስጦታም ሆነ በበረከት፣ በእጅ ማራሻም ሆነ በጉርሻ፣ በምልጃም ይሁን በደጅ ጥናት፣ በማሞገስም ሆነ በማሞካሸት፣ የቅዱሳን ሁሉ ቅዱስም ሆነ የብፁአን ሁሉ ብፅእ አድርጎ በግልም ሆነ በጋራ ማቅረብ፣ የማይገባን ጥቅም ለማግኘት ከሆነ፣  ዞሮ ዞሮ ሕገ ወጥ ድርጊትን ለመሸፋፈንና ፍርድን ለመገምደል የሚያገለግል ማህበራዊ ንቅዘት ከመሆን አያልፍም» ሲል ፍቺውን ከእነ ማብራሪያው ይሰጣል፡፡  
ይህንኑ ቃል ዌብስተር የእንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት ደግሞ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርብር፣ ማታለል፣ ከፍተኛ እምነት የተጣለበትን ዳኛ ወይም ባለሥልጣን ኃላፊነቱን እንዲዘነጋ የሚሰጥ ሽልማት ስጦታ ውለታ፣ ወዘተ በማለት ያፍታታዋል፡፡ ብላክስ ሎው የተባለው የታወቀ መዝገበ ቃላት ደግሞ (አነስተኛም ይሁን ከፍተኛ) በሕጋዊ ኃላፊነት ያለን ባለሥልጣንን (በአንድ ጉዳይ ላይ ያለውን) አመለካከት፣ አስተሳሰብ በተፅዕኖ ለማሳመን ሲባል ማንኛውንም ዋጋ ያለውን ነገር በስጦታ፣ በበረከት፣ በድርጎ፣ ወይም በሌላ መልክ መስጠትና መቀበል እንደሆነ ይገልጸዋል፡፡ እንደዚሁ በሌላ መዝገበ ቃላት ትንታኔ፤ «የራስ ያልሆነን ሀብትና ንብረት በተለያየ መልኩ መውሰድ» ማለት ሲሆን በቀጥታ እኪስ ውስጥ ዘው ብሎ ባይገባ፣ ቤት ሰርስሮ ሳጥን ሰብሮ በድፍረት ባይሰርቅ፣ አሳቻ ቦታ ቆሞ ባይነጥቅ፣ የዚያን ከዚህ አምጥቶ የማይሆነውን «ይሆናል»፣ የሚሆነውን «አይሆንም» በሚል ወይም ልብን አፍዝዞና አደንግዞ ባይወስድ፣ ጉቦ የራስ ሀቅ ያልሆነን ሀብት፣ ንብረት ወይም ሌላ መንፈሳዊ ስጦታን በሥልጣን ተጠቅሞ መቀበል፣ መስረቅ፣ መዝረፍ፣ ማጭበርበርና ማታለል መሆኑን ያብራራል፡፡
በርግጥም መንግሥት የጣለበትን ከፍተኛ ኃላፊነት ዘንግቶ ሥልጣኑን ለሕዝብ ዕድገትና ብልፅግና ማዋል ሲገባው የራሱን ጥቅም የሚያሳደድ ከሆነ፣ በቢሮ ውስጥ ከመቀመጡ በስተቀር ጫካ ከገባ ወንበዴ፣ ጨለማን ተገን አድርጐ ቤት ከሚሰረስር ሌባ፣ አካባቢውን በቁጥጥር ሥር አድርጐ ከሚዘርፍ ነጣቂ፣ የሰው ኪስ ከሚገባ ሞሽላቃ ሌባ ሊለይ አይችልም፡፡ ጉቦ በጉልተኛው ሥርዓት መተያያ፣ እጅ መንሻ፣ ፊት መፍቻ፣ ጉርሻ፣ ወዘተ የወግ ስሞቹ ሲሆኑ መደለያ፣ መማለጃ፣ መሸንገያ፣ ወዘተ የሐሜት መጠሪያዎቹ ነበሩ፡፡ የማዕረግ ስሞቹ ደግሞ አመኃ፣ ገፀ በረከት፣ ሙገሳ፣ ውደሳ፣ ቅደሳ፣ በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ ማስታወሻ፣ መታሰቢያ፣ ስጦታ--- የሚሉት ደግሞ ከቁልምጫ ስሞቹ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ «የመንግሥት ገቢን የሚሰበስብ ባለሥልጣን ማር የፈሰሰበት ምላስ» የሚል የህንዶች ተረት ይጨመርበታል፤ «ተሹሞ የማይበላ ተጥዶ የማይፈላ የለም» የሚል የአገራችንን አባባልም ይጠቀሳል፡፡ «ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል» ተብሎም እንደ ትልቅ ነገር አዋቂ ተብዬዎች በምክር ስም የሚሰጡት ምሳሌያዊ አነጋገር ነው፡፡
ሥነ ጽሁፋዊ ውበት
ምንም እንኳን ድርሰቱ ያነሳው ጭብጥ  ጠንካራና መረር ያለ ቢሆንም በውብ ቋንቋና ተጀምሮ እስኪያልቅ ስሜትን ሰቅዞ በሚይዝ የአተራረክ ሥልት በመቅረቡ ተነባቢና ተወዳጅ ሊሆን በቅቷል፡፡ ለሽልማት የበቃውም ሆነ በሌላ ቋንቋ ለመተርጎም የታደለው አንድም በዚህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡ በእርግጥም የተደራሲውን  ስሜት ጨምድዶ ካልያዘ፣ የታሰበለትን ግብ ከቶ ሊመታ አይችልም፡፡
ደራሲው ማነው?
ደራሲው ሰለሞን ኃይለማሪያም በ220 ገጾችና በ29 ምዕራፎች ከፋፍሎ፣ ድርሰቱን  ውድድሩን ላዘጋጀው ለኮድ ኢትዮጵያ  ያቀርባል፡፡ ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› የሚል ርዕስ የሰጠው የልቦለድ ሥራውም አንደኛ ይወጣና የበርት ሽልማት ድርጅት በአፍሪካ የአሸናፊነት የምስክር ወረቀትና የገንዘብ ሽልማት ያገኛል፡፡ ይህ መጽሐፍ ወደ ጀርመንኛ የተተረጎመ ሲሆን በምስራቅ አፍሪካ አታሚዎች ታትሞ በኬንያ፣ በኡጋንዳ፣ በታንዛኒያና እና በሱዳን የመጻህፍት መደብሮች ለሽያጭ ቀርቧል። አማዞን የተባለው የኢንተርኔት ገበያም በዲጂታልና  በሕትመት ለአንባቢያን አቅርቦታል፡፡ በሀገራችን ብዙም ባይታወቅም  በሜጋ አሳታሚና አከፋፋይ እንዲሁም በዩኒቨርሳል መጻሕፍት መደብር ይገኛል፡፡
ሰለሞን ኃይለማሪያም የተወለደውና ያደገው አዲስ አበባ ውስጥ ሲሆን ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ የኮሙኒኬሽንና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ነው፡፡ በተጨማሪም ለቪኦኤና ቢቢሲ ኮረስፖንደንት ሆኖ ሰርቷል፡፡ በኢትዮጵያ ተቋቁሞ የነበረው ፔን ኢንተርናሽናል የተባለ የስነጽሑፍ ክበብ ፕሬዚደንት በመሆንም አገልግሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከቤተሰቡ ጋር በካናዳ ይኖራል፡፡ ደራሲው “ላቭ ኤንድ አንዛይቲ” የተሰኘ መጽሐፍም ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ የበርት አዋርድ የመጀመሪያው አፍሪካዊ ተሸላሚ ለመሆንም በቅቷል። እ.ኤ.አ በ2016 እና 2017 የጻፋቸው የአጫጭር ልቦለድ መድበሎችም የተደነቁለት ሲሆን የተወሰኑት ሥራዎቹም  ወደ ጀርመንኛ፣ ፈረንሳይኛና ስዊድንኛ ተተርጉመውለታል፡፡
እንዴት ወደ ጀርመንኛ ተተረጎመ?
ሰለሞን ኃይለ ማሪያም ‹‹ዘ ያንግ ክሩሴደር›› በሚል ርእስ የጻፈው ልብወለድ መጽሐፍ  በአንድ አውስትሪያዊ ደራሲ እጅ ይገባና የመነበብ ዕድል ያጋጥመዋል፡፡ በአጻጻፍ ውበቱና በታሪኩ የተሳበው ሔልሙት ኤ ናይደር፤ ወዲያው ወደ ጀርመንኛ ተረጎመውና ለህትመት በቃ፡፡ ወደ አማርኛ ግን እስካሁን አልተተረጎመም፡፡  
በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት፣ መጀመርያውኑ ድርሰቱ በአገር ውስጥ  ቋንቋዎች ቢጻፍ፣ ያም ባይሆን ደግሞ ወዲያው በሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ቢተረጎም መልካም ነበር፡፡ አሁንም የመጽሐፉ ትምህርታዊ ፋይዳው ከግምት ውስጥ ገብቶ፣ በሀገር ውስጥ ልዩ ልዩ ቋንቋዎች ተተርጉሞ፣ በሥርዓተ ትምህርቱ ቢካተት ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

የኢንተርኔት ቁልፍ ሰባሪዎች የ29 ሚሊዮን ያህል የፌስቡክ ተጠቃሚዎችን አካውንቶች ሰብረው በመግባት መረጃዎቻቸውን መመንተፋቸውን ዴችዌሌ ዘግቧል፡፡
መረጃ መንታፊዎቹ፣ የፌስቡክ ተጠቃሚዎቹን ስም፣ የኢሜይል አድራሻና የስልክ ቁጥሮች ጨምሮ ሌሎች ድብቅ መረጃዎች ፈልፍለው ማግኘታቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ፌስቡክ ኩባንያ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ደንበኞቹ የማስጠንቀቂ መልዕክቶችን እንደሚልክ ማስታወቁንም አመልክቷል፡፡
በቅርቡ በተደረጉ ተመሳሳይ የመረጃ ምንተፋዎች ሰለባ ከሆኑት የፌስቡክ አካውንቶች መካከል፣ የኩባንያው መስራች የማርክ ዙክበርግ አካውንት አንዱ እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

 የላይቤሪያ የገንዘብ ሚኒስቴር፤ ጸጉራቸውን ቀለም የሚቀቡና ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ጸጉር ለማስረዘም ሲሉ ሰው ሰራሽ ጸጉር ወይም ዊግ የሚቀጥሉ ሴት ሰራተኞቹን እንደሚቀጣ ማስታወቁን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በአገሪቱ የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ሴቶች ጸጉራቸውን እንዳያቀልሙና ዊግ እንዳይጠቀሙ የሚከለክል ህግ ከወጣ አራት አመታት ያህል ቢሆነውም፣ የመንግስት ተቋማት ህጉን ተግባራዊ ሳያደርጉት እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፤ የገንዘብ ሚኒስቴር ግን ከሰሞኑ ድርጊቱን በሚፈጽሙ ሰራተኞቹ ላይ ቅጣት እንደሚጥል ማሳሰቡን አመልክቷል፡፡
ሚኒስቴሩ ሰራተኞቹን ማስጠንቀቁን ተከትሎ በርካታ የአገሪቱ ዜጎች በማህበራዊ ድረገጾችና በተለያዩ አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ተቃውሟቸውን ያሰሙ ሲሆን ህጉን ከአባታዊ ባህል የመነጨ አግባብነት የሌለው ጾታዊ መድልዖ ሲሉ መተቸታቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡ ሴቶች  ቀለም መቀባታቸውም ሆነ ዊግ ማድረጋቸው በስራ ገበታቸው በሚያስመዘግቡት ውጤት ላይ ምንም አይነት አሉታዊ ተጽዕኖ የለውም፣ ምንም አይነት መሰረት የሌለው ያልተገባ ክልከላ ነው ሲሉም ተቃውሟቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የመንግስት ሰራተኛ የሆኑ ላይቤሪያውያን ሴቶችን የጸጉር ቀለምና ዊግ አጠቃቀም የሚከለክለው ህጉ የወጣው በቀድሞዋ የአገሪቱ መሪ ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍ የስልጣን ዘመን እንደነበር ያስታወሰው ዘገባው፤ ባለፈው አመትም በጸጉር ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉን አስታውሷል፡፡


የኢንተርኔት አቅርቦትን በእኩልነት መጠቀም ለደቡብ አፍሪካውያን ዜጎች እንደ አንድ መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መቆጠር እንዳለበት ሚዲያ ሞኒተሪንግ አፍሪካ የተባለ ተቋም ጠይቋል፡፡ ባለፈው ረቡዕ በአገሪቱ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ዊሊያም በርድ ለአገሪቱ መንግስት ባስተላለፉት መልዕክት፤ የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ለደቡብ አፍሪካውያን ሰብዓዊ መብት መሆን እንደሚገባው መናገራቸውን ሜይል ኤንድ ዘጋርዲያን ዘግቧል፡፡
የደቡብ አፍሪካ መንግስት በተለይ ለድሃ ዜጎቹ መረጃዎችን የሚያገኙበትና የሚለዋወጡበት ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት አቅርቦት ያለምንም ገደብና መቋረጥ ካላቀረበ፣ አገሪቱ ወደ አፓርታይድ ዘመን መመለሷ አይቀሬ ነው ሲሉም ተናግረዋል፤ ዳይሬክተሩ፡፡
በአገሪቱ የኢንተርኔት አገልግሎት ክፍያ እጅግ ውድ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ሃብታሞች ገንዘብ ከፍለው ቢጠቀሙም ከአገሪቱ የህዝብ ቁጥር አብላጫውን የሚይዙት ድሃ ዜጎች ግን አገልግሎቱን ለመጠቀም የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡

ከ4.4 ቢሊዮን በላይ ሰዎች የተለያዩ ጉዳቶች ደርሶባቸዋል


    በአለማችን የተለያዩ አገራት ባለፉት 20 አመታት የተከሰቱ የተፈጥሮ አደጋዎች ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሞኑን ባወጣው ሪፖርት ማስታወቁን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በተፈጥሮ አደጋዎች ሳቢያ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ለህልፈተ ህይወት ከተዳረጉት 1.3 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 56 በመቶው በርዕደ መሬትና በሱናሚ ሳቢያ የሞቱ መሆናቸውን ያስታወቀው ሪፖርቱ፣ የተፈጥሮ አደጋዎች ለሞት ከዳረጓቸው ሰዎች በተጨማሪ በ4.4 ቢሊዮን ሰዎች ላይ የመቁሰልና ከመኖሪያ መፈናቀልን ጨምሮ የተለያዩ ጉዳቶችን ማድረሳቸውንም አመልክቷል፡፡
የተፈጥሮ አደጋዎች በአለማችን ህዝቦች ላይ የሚያስከትሉት ሁለንተናዊ ጉዳት ባለፉት 20 አመታት በ151 በመቶ ያህል መጨመሩን የገለጸው ሪፖርቱ፤ በአለማችን የተለያዩ አገራት ርዕደ መሬት፣ እሳተ ገሞራ፣ ጎርፍና ሌሎች የተፈጥሮ አደጋዎች ያስከተሉት ውድመት 2.9 ትሪሊዮን ዶላር እንደሚገመትም አብራርቷል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተፈጥሮ አደጋዎች 944 ቢሊዮን ዶላር ያህል ያወደሙባት አሜሪካ፣ ከአየር ንብረት ጋር ተያያዥ የሆነ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የገጠማት የአለማችን ቀዳሚዋ አገር መሆኗን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ቻይና፣ ጃፓን፣ ህንድና ፖርተሪኮ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም አመልክቷል፡፡

Page 10 of 413