Administrator

Administrator

  የአሸባሪው ቡድን አይሲስ ታጣቂዎች በሰሜን ምስራቅ ሶማሊያ በምትገኘው የፑንትላንድ ግዛት አካባቢዎች በሚንቀሳቀሱ ነጋዴዎችና ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣላቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የአይሲስ ታጣቂዎች በአካባቢው በንግድ ስራ ላይ ለተሰማሩ ግለሰቦችና ኩባንያዎች በላኩት አጭር የሞባይል የጽሁፍ መልዕክት፣ “ለቡድኑ በቋሚነት ቀረጥ የማትከፍሉ ከሆነ፣ ለመሞት ዝግጁ ሁኑ” የሚል ማስፈራሪያ መስጠታቸውን ዘገባው አመልክቷል፡፡ አይሲስ ቀረጡን የጣለው በሶማሊያ አንዳንድ አካባቢዎች ተመሳሳይ ቀረጥ በመጣል ገቢ ከሚያገኘው ተቀናቃኙ የአሸባሪ ቡድን አልሻባብ የወሰደውን ልምድ ተመርኩዞ ሳይሆን አይቀርም ያለው ዘገባው፤ አይሲስ በደቡባዊ ሶማሊያ መንግስት ጦር ላይ የሚፈጽመውን ጥቃት እያጠናከረ መምጣቱንና ከአልሻባብ ጋር የነበረው ግጭት እየተባባሰ እንደሚገኝም አመልክቷል፡፡

 ጆርጅ ክሉኒ በ239 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ቀዳሚነቱን ይዟል

    ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት በአመቱ ከፍተኛ ገቢ ያገኙ የአለማችን ወንድ የፊልም ተዋንያንን ዝርዝር ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የ57 አመቱ የሆሊውድ ኮከብ ጆርጅ ክሉኒ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 239 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በማግኘት ቀዳሚነቱን ይዟል፡፡
ዋይኔ ጆንሰን በ124 ሚሊዮን ዶላር አመታዊ ገቢ ሁለተኛ ደረጃን ሲይዝ፣ የአቬንጀርሱ ተዋናይ ሮበርት ዳውኒ ጁኒየር በ81 ሚሊዮን ዶላር ሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ፎርብስ አስታውቋል፡፡
ክሪስ ሄምስዎርዝ በ64.5 ሚሊዮን ዶላር፣ የቻይናው ኮከብ ተዋናይ ጃኪ ቻን በ45.5 ሚሊዮን ዶላር፣ አሜሪካዊው ዊል ስሚዝ በ42 ሚሊዮን ዶላር እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአመቱ ከፍተኛ ገቢ በማግኘት ከአንደኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት የፊልም ተዋንያን በድምሩ ከግብር በፊት 748.5 ሚሊዮን ዶላር ማግኘታቸው ተነግሯል፡፡

 አውሮፕላን ማረፊያው በሙጋቤ ስም መጠራቱ እንዲቀር ተጠይቋል


    በቅርቡ የተካሄደውና ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንጋዋ ያሸነፉበት የዚምባቡዌ ምርጫ የተጭበረበረ ነው፣ ሊሰረዝ ይገባል በሚል በአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተመሰረተውን ክስ ሲመረምር የቆየው ህገ መንግስታዊ ፍርድ ቤት ክሱን ውድቅ በማድረግ የምርጫ ውጤቱን አጽድቋል፡፡
በፕሬዚዳንታዊ ምርጫው 44.3 በመቶ ድምጽ በማግኘት ሳይመረጡ የቀሩት ሙቭመንት ፎር ዲሞክራቲክ ቼንጅ የተባለው የአገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ኔልሰን ቻሚሳ፣ የአገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የድምጽ አሰጣጡን ያለአግባብ በማከናወን ምናንግዋ እንዲያሸንፉ አስችሏል ሲሉ ክስ መስርተው ነበር፡፡
የፓርቲው ደጋፊዎች የምርጫ ውጤቱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ አደባባይ ወጥተው ተቃውሞ ማሰማታቸውንና ከፖሊስ ጋር ግጭት ተፈጥሮ ስድስት ሰዎች ለህልፈተ ህይወት መዳረጋቸውንም ዘገባው አስታውሷል፡፡ ባለፈው ሃምሌ ወር መጨረሻ ላይ የተካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ፣ ዚምባዌ ከ37 አመታት በላይ የገዟት ሮበርት ሙጋቤ ባልተወዳደሩበት ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዚዳንቷን ያስመረጠችበት ምርጫ ነው፡፡
በተያያዘ ዜናም የዚምባቡዌ የቀድሞ የጦር ሃይል አባላት የአገሪቱ አለማቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ስም መጠራቱን እንዲያቆም መጠየቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡ የጦር ሃይል አባላቱ የሮበርት ሙጋቤ ስም ከአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ እንዲነሳና የሌሎች ታላላቅ የአገሪቱ ባለውለታዎችና ጀግኖች ስም እንዲተካ የሚጠይቅ የድጋፍ ድምጽ አሰባስበው ለአዲሱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ምናንግዋ ለማስገባት እየተዘጋጁ ነው ተብሏል፡፡
ለረጅም አመታት ሃራሬ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ በሚል ስያሜ ሲጠራ የኖረው አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያው፣ ባለፈው አመት ሙጋቤ ስልጣን ሊለቁ ጥቂት ሳምንታት ሲቀራቸው ስያሜው ወደ ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ እንዲቀየር መደረጉን ያስታወሰው ዘገባው፤”ስማቸውን ዘላለማዊ የማድረግ ጥማት ባለባቸው ሙጋቤ የተወሰደው የስም ለውጥ እርምጃ ተገቢ አይደለምና ስያሜው ይቀየርልን” ሲሉ የጦር ሃይሉ አባላት መቃወማቸውን አመልክቷል፡፡


 በደቡብ ሱዳን ላለፉት አምስት አመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ግጭት በድርድር ለመፍታት ደጋግመው ሲሰበሰቡና ባለመስማማት ሲለያዩ የኖሩት የአገሪቱ ተቀናቃኝ ሃይሎች፣ ከነገ በስቲያ ሰኞ የመጨረሻውን የሰላም ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ተቀናቃኝ ሃይሎቹ በሰኔ ወር በሱዳን መዲና ካርቱም የሰላም ስምምነት መፈራረማቸውንና ከሁለት ሳምንታት በፊትም ስልጣን ለመጋራት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ያስታወሰው ዘገባው፤ ሶስተኛውንና የመጨረሻውን ስምምነት በመጪው ሰኞ ለመፈራረም ቀጠሮ መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
ቀጣዩ ስምምነት ባለፉት ሁለት ስምምነቶች እልባት ባልተሰጣቸውና በእንጥልጥል ላይ በሚገኙ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ መግባባት ላይ የሚደረስበትና በአገሪቱ ሰላምን ለማስፈን ተስፋ የተጣለበት እንደሆነም ተነግሯል፡፡
ባለፉት ስምምነቶች መግባባት ላይ ባልተዳረሰባቸው የስልጣን መጋራትና የግዛቶች ድንበር አከላለልን የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮችን በውይይት ለመፍታት በተቀናቃኝ ሃይሎቹ መካከል የተደረጉ ጥረቶች ተስፋ ሰጪ እንደሆኑ መነገሩን የጠቆመው ዘገባው፤ የምክትል ፕሬዚዳንቱን ስልጣን በመሳሰሉ አከራካሪ ጉዳዮች ላይም መግባባት ላይ መደረሱን አመልክቷል፡፡

 በተባበሩት መንግስታት የሚደገፈው የሊቢያ መንግስት በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ከ700 ሺህ በላይ የተለያዩ አገራት ስደተኞችን በቀጣይነት በግዛቱ ውስጥ የማስፈር ግዴታ እንደሌለበት በመግለጽ፣ ስደተኞቹ ወደየ አገራቸው መመለስ አለባቸው ሲል አቋሙን ማስታወቁን ዥንዋ ዘግቧል፡፡
ሊቢያ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የተለያዩ አገራት ስደተኞች በግዛቷ እንድታሰፍር በተመድ የቀረበው ሃሳብ ኢ-ፍትሃዊ ነው፤ ስደተኞቹ ወደየመጡበት መመለስ አለባቸው ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሞሃመድ ሳያላ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
የስደተኞች መተላለፊያ በመሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት ስትከፍል የኖረቺው ሊቢያ፣ ስደተኞችን በግዛቷ የምታሰፍርበት ሁኔታ ላይ አይደለችም ያሉት ሚኒስትሩ፤አለማቀፉ ማህበረሰብ የአገራት መንግስታት በሊቢያ የሚገኙ ስደተኛ ዜጎቻቸውን መልሰው እንዲወስዱ ጫና ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ በሊቢያ የሚገኙ የስደተኞች ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ድንበር አቋርጠው በሜዲትራኒያን ባህር በኩል በጀልባ ወደ አውሮፓ አገራት ለመግባት ሲሞክሩ በፖሊስ ቁጥጥር ስር በዋሉና ከአሰቃቂ የባህር ላይ አደጋዎች በተረፉ በሺዎች የሚቆጠሩ የተለያዩ አገራት ህገወጥ ስደተኞች ተጨናንቀው እንደሚገኙ የጠቆመው ዘገባው፤ ስደተኞቹ በአፋጣኝ ወደ አገሮቻቸው ካልተመለሱ ከፍተኛ ቀውስ ሊፈጠር እንደሚችል መሰጋቱንም አክሎ ገልጧል፡፡


 ሚዩዚክ ሜይዴይ ከኢትዮጵስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በክፍሉ ታደሰ “ኢትዮጵያ ሆይ ቅፅ 2” መፅሐፍ ላይ ነገ ከቀኑ 8፡00 ጀምሮ በብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ ውይይት ያካሂዳል፡፡ ለውይይቱ የመነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት የአሀዱ ሬዲዮ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አርታኢና ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠና አቶ ኩራባቸው ሸዋረጋ ሲሆኑ መድረኩ በመምህር ሰለሞን ተሰማ ጂ እንደሚመራም ታውቋል፡፡ ፍላጎት ያለው በውይይቱ ላይ እንዲሳተፍ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጋብዟል፡፡

 የዛሬ ሳምንት ቦሌ በሚገኘው የአክሰስ ሪል እስቴት ጽ/ቤት፣ ቤት ገዢዎች ያሰሙት የነበረው ጩኸት፣ በደል ደርሶባቸው ሳይሆን የቅርብ ዘመድ የሞተባቸው ያህል አዝነው ነበር፡፡
ጩኸታቸውን ማሰማት የፈለጉት በሰላማዊ ሰልፍ እንጂ በጋዜጣዊ መግለጫ አልነበረም፡፡ የሰላማዊ ሰልፍ ፈቃድ ሰጪው ክፍል “እስከ ዛሬ ታግላችኋል፤ አሁንም በትዕግስት መልዕክታችሁን ለሚመለከታቸው የመንግሥት መዋቅሮች አሰሙ፡፡…” በማለት በለገሳቸው ምክር ተስማምተው፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማካሄድ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን ትተው፣ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት መገደዳቸውን፣ የአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ፣ አቶ አክሎግ ስዩም ተናግረዋል፡፡  
“በሪል እስቴት የዜጎች መዘረፍ በእኛ ይብቃ! ሀገር ከሌቦች ፀድታ ትልማ! መንግሥትና ሕግ ባለበት አገር፣ ቤት ገዢዎች ተዘርፈናል፤ ሌቦች በዘረፉት ገንዘብ ፍትህ አዛብተዋል፣…” በሚሉ መፈክሮች ታጅቦ በተጀመረው ስብሰባ፣ ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ለሚመሩት መንግሥት ባቀረቡት ጥያቄ፤ “በ50ሺ ብር ካፒታል መኖርያ ቤት ሰርቼ አቀርባለሁ” በማለት በአገር ውስጥና በውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቦ፣ በ6 ዓመት ውስጥ አንድም ቤት ሰርቶ አለማስረከብ፣ ግልጽ ሌብነት ነው ብለዋል፡፡
አክሰስ ሪል እስቴት በተመሰረተ በአምስተኛው ዓመት፣ የድርጅቱ መስራች፣ የቦርድ ሊቀመንበርና ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ኤርሚያስ ታጠቅ አመልጋ፤ በድርጅቱ ሳጥን ውስጥ 129 ብር ብቻ ሲቀር አገር ጥለው በመኮብለላቸው፣ ቤት ገዢዎች፣ የደረሰባቸውን ግፍና በደል ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትና ለቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር ኃይለማርያም ደሳለኝ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡   አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጽ/ቤት አቅርበው፣ ጽ/ቤቱም የተፈጠረውን ችግር እንዲፈታና ችግሩን ከስር መሰረቱ አጥንቶ፣ የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርብ፣ በቀድሞው የከተማ ልማትና ቤቶች ልማት ሚ/ር አቶ ሙኩሪያ ኃይሌ የሚመራ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ያሉበት ዓቢይ ኮሚቴና ከየሚኒስትሩ መ/ቤቶች ኤክስፐርቶች ያሉበት የቴክኒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ፣ ባለ 7 ነጥብ የጥናት ውጤት ለጠቅላይ ሚ/ሩ ቢያቀርብም፣ እስካሁን ድረስ አንዳችም መፍትሔ አልተሰጠንም ብሏል፤ የቤት ገዢዎች ኮሚቴ፡፡
ከቀረቡት 7 ነጥቦች መካከል፣ የአክሲዮን ማኅበሩን ህልውና በተመለከተ፣ ማኅበሩ በሕግ አግባብ የሚፈርስበት አግባብ እንዲፈለግና መብቶቹ ለቤት ገዢዎች እንዲተላለፍ፣ የኩባንያውን የመሬት ይዞታ በተመለከተ፣ ግንባታ ያልተካሄደባቸው ይዞታዎች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል በፍጥነት በአደራ ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡ፣ ግንባታ የተጀመረባቸው ይዞታዎች፣ ለግንባታ የወጣው ወጪ በመሃንዲሶች ተገምቶና የኮንትራክተሮች ወጪ ተቀንሶ ወደፊት ለቤት ገዢዎች እንዲዛወር፣ የኦዲት ሥራ ለቀጣይ እርምጃዎች ወሳኝ በመሆኑ በተቻለ መጠን በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የሚል ይገኝበታል ያለው ኮሚቴው፤ ኩባንያው፣ ከቤት ገዢዎች በሰበሰበው ገንዘብ የተገዙ ከ30 በላይ የመሬት ይዞታዎች በአደራ ወደ መሬት ባንክ መግባታቸውን፣ ነገር ግን ባዶ መሬቶቹ ከሊዝ አዋጅና ሕግ ውጪ፣ በሕገ ወጥ መንገድ በግለሰቦች ኢ-ፍትሐዊ አካሄድ፣ ከ160 በላይ ቤቶች ገዢዎች ይሰሩበታል የተባለ ቦታ፣ በማያውቁት መንገድ ተሸጦ ማስመለሱንና እንደገናም መሸጡን አመልክተዋል፡፡
በፋይናንስ ኦዲት ሪፖት መሰረት፣ ከተሰበሰበው 1.4 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለመሬት ንብረት ግዢ ከ271 ሚ. ብር በላይ፣ ለሥራ ተቋራጮ ከ178 ሚ. ብር በላይ፣ የተለያየ የጥቅም ግንኙነት ላላቸው የተከፈለ ከ245 ሚ. ብር በላይ፣ አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ከኩባንያው የወሰዱት ከ59 ሚ. ብር በላይ፣ በተለያዩ ጊዜያት ለግለሰቦች የተከፈለ ከ66 ሚ. ብር በላይ፣ ለግንባታ ሥራ የዋለ ከ211 ሚ. ብር በላይ፣ ለኮሚሽን የተከፈለ ከ39 ሚ. ብር በላይ፣ ለልዩ ልዩ ወጪዎች ከ125 ሚ. ብር በላይ… ወጪ መደረጉን፣ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ደግሞ ምንም አርዕስት የሌለው ሲሆን የተጠቀሱት ወጪዎች ከተሰበሰበው ገንዘብ በላይ ሲቀነሱ፣ በአጠቃላይ ከ900 ሚ. በላይ መባከኑ ተጠቁሟል። ኩባንያው ለሁለት ዓመት ከ2002-2004 የቦርድ አባላት እንዳልነበሩት፣ አቶ ኤርሚያስ ብቻቸውን እንደሚወስኑ፣ ብቻቸውን ትዕዛዝ እንደሚሰጡ፣ ፋይናንሱንም ብቻቸውን እንደሚያንቀሳቅሱ፣ በውሸት በፈጠሯቸውና አሁን በሌሉ ድርጅቶች ስም ከ59 ሚ. በላይ ወደ ኪሳቸው ከትተው የሚጠይቃቸው አካል ስለሌለ፣ በነፃነት በከተማዋ ይንቀሳቀሳሉ ብሏል፤ ኮሚቴው፡፡
ኮሚቴው ለጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ባቀረበው ጥያቄ፤ ዜጎች በሀገራቸው የፍትህ ስርአት የሚተማመኑ፣ በነፃነት ሀብት የሚያፈሩባት የጋራ አገር እንድትሆን፣ በአክሰስ ሪል እስቴት ቤት ገዢዎች ላይ የደረሰው በደል፤ በሌሎች ሪል እስቴቶች እንዳይደርስ፣ እንዲያደርጉ፣ ይህ ዓይን ያወጣ ዝርፊያ በእኛ እንዲበቃ፣ አገርም ከሌቦች ፀድታ እንድትለማ ፅኑ እምነት አለንና፣ መንግሥት በገባልን ቃል መሰረት፣ የመጨረሻ ውሳኔ እንዲሰጠን፣ በጀመሩት የለውጥ እንቅስቃሴም ለጉዳያችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ቁርጠኛ ውሳኔና አመራር እንዲሰጡልን እንጠይቃለን በማለት ተማፅኗል፡፡   

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ በኑሮው የደላው፤ ሀብቱ የተመቸው፣ እጅግ ቀብራራ ሰው፣ ነበረ፡፡ የሰፈር ሰው ሁሉ ደግና ለተቸገረ ደራሽ ነው ይለዋል፡፡ ወደ ቤተ - ዕምነት ሄዶ ሰባኪው የሚሉትን ይሰማል፡፡
ሰባኪው - በሀልዮ በነቢር በገቢር የተሰራ ሐጢያትን እግዚሐር ይፍታን
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪው - ለተቸገረ እርዱ!
      - በሽተኛ ጠይቁ!
      - ለደሀ መጽውቱ!
      - ሁለት ያለው አንዱን አንድ ለሌለው ይስጥ!
      - የላይኛው ቤታችሁን እምድር ሳላችሁ አብጁ!
      - ፁሙ! ፀልዩ!
      - ትምህርታችሁን ይግለጥላችሁ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - ከእናንተ የተሻለ የሚኖር ማን አለ?
ምዕመናን - ማንም!
ሰባኪ - ከእናንተ መካከል ሳይበላ የሚያድር ማን አለ?
ምዕመናን - ማንም!
ሰባኪ - ትሰጡት አትጡ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - በየመንገዱ የወደቁትን ለማሰብ ልቦና ይስጣችሁ!
ምዕመናን - አሜን!
ሰባኪ - የሰማነውን በየልቦናችን ያሳድርብን!
ምዕመናን - አሜን! አሜን!
ሁሉም ወደ የቤታቸው ሄዱ፡፡ ያም ሀብታም ሰው ወደ ቤቱ ለመሄድ መንገድ ጀመረ፡፡
ወደ ቤቱ መሄጃው ላይ አንድ ድልድይ አለ፡፡ እድልድዩ ላይ በግራና በቀኝ በኩል ተቀምጠው የሚለምኑ ሁለት ዓይነ - ሥውር ለማኞች አሉ፡፡ መካከላቸው ሲደርስ ከኪሱ በርካታ ሳንቲሞች አወጣ!
ለማኞቹ - “ጌታዬ አትለፈን! ካለህ አይጉደልብህ! ትሰጠው አትጣ! ትመፀውተው አትጣ! እጅህ እርጥብ ይሁን!” ይሉታል፡፡
ሀብታሙ ሰው ከኪሱ ያወጣቸውን ሳንቲሞች በሁለት እጆቹ ይዞ አንኳኳቸው፡፡ ሿ! ሿ! ሿ! አደረጋቸው፡፡ ሁለቱ ዐይነ - ስውር ለማኞች በጣም ጎመጁ፡፡ ከአሁን አሁን መጥቶ ይሰጠናል ብለው ሲጠብቁ, ሳንቲሞቹን መልሶ ኪሱ ከቶ፤
“ተካፈሉ!” ብሎ ሄደ፡፡
በወዲህ ወገን ያለው ለማኝ; “ያኛው ተቀብሏል፤ ያካፍለኛል” አለ፡፡
በወዲያ በኩል ያለውም ለማኝ፤
“እሱ ተቀብሏል፣ ያካፍለኛል!” አለ፡፡
ሁለቱም ምንም ሲያጡ ተነስተው አንዱ; “ስጠኝ! የሰጠንን አካፍለኝ!` ሌላውም; “ላንተ ነው የሰጠህ አካፍለኝ!”
`አንተ ወስደሃል … አንተ ወስደሃል” እየተባባሉ፤ ድብድብ ጀመሩ፡፡
ሀብታሙ ሰው; ከሩቅ ሆኖ ከት ብሎ ሳቀባቸውና ወደ ቤቱ ሄደ!
***
እኛ ኢትዮጵያውያን ደግ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለተቸገረ ደራሽ፣ ተዛዛኝ … እንባላለን፣ እንጂ ጭካኔያችን ለከት የለውም! ውስጣችን አልተፈተሸም፡፡ አልተመረመረም! በሰብአዊነት ሽፋን የምንኖር ኢ-ሰብአዊዎች ነን! ፈዋሽ ሀኪም አልተገኘልንም እንጂ የውስጥ ደዌ አለብን - ጭካኔ! እንዋደዳለን እንላለን እንጂ ውስጣችን በጭካኔ አባዜ የተሞላ ነው! የመሀይምነታችንና የአረመኔነታችን (Barbarism) መጠን ገና አልታወቀም - አልተጠናንም! እርግጥ ሁላችንም ላንሆን እንችላለን እንጂ የክፋታችን ልክ ይህ ወሰንህ፣ ይህ ዲካህ የሚባል አይደለም፡፡ አያምጣው እንጂ ክፉ ጊዜ ቢመጣ፣ እርስ በርስ ሊያበላላን ይችላል! ነፃነት ይከብደናል! መከራ ከመልመዳችን የተነሳ ነፃነት ሸክም ይሆንብናል፡፡ ድህነታችን የሀብት ብቻ ሳይሆን የአዕምሮም ነው! የልቡናም ነው! ደግ ጊዜ ያምጣልን እያልን፣ ደጉን ጊዜ ገፍተን እንጥላለን! ይሄ ኃይለኛ የልቡና ቀውስ ነው! አዎንታዊ ነገር የማይጥመን ከሆነ፣ አሉታዊው ነገር በደም ጎርፍ ያስተጣጥበናል!
ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን በቴያትሩ እንዳስቀመጠው፤
“ሞትን ለሚሻ ሞትን ነው መንፈግ! ህይወትንም አለመቸር! እማህል ቤት ነው የሰው ልጅ ጥቅም የሚሰጥ! ሰው ሆኖ ካሹት፣ ጥቅም የማይሰጥ የለም!” ይለናል፡፡ ለዚህ ፀሐፊ፣ የአበሻ ውስጠ ነገር ዱሮ ነው የገባው ማለት ነው!
ያም ሆኖ “በርኩቻው ማህል ፀጥ ብለህ ለመጓዝ ሞክር” ይላል፤ የጥንቱ የጠዋቱ የዴዚዴራታ ምክር! ምክሩ ከገባን ዓለም በውካታ የተሞላች ናት - አንተ ግን ተረጋግተህ ተጓዝባት ማለት ነው፡፡ መረጋጋት፣ ማረጋጋት፣ ሁኔታዎችን በሰከነ ዐይን ማየት፤ የበሳል ሰው መርህ ነው፡፡ “በካፊያው ከተረበሽክ የዶፉ ዝናብ ጊዜ ምን ይውጥሃል?” ይላሉ አበው፡፡ ህዝባችንን ማሳወቅና ማስተማር፣ መሰረታዊ ጉዳያችን መሆን አለበት፡፡ በክፋት፣ በጭካኔና በአረመኔያዊነት (Barbarism) እና በህዝባዊ እምቢተኝነት (Civil disabidience) መካከል፤ የገደል ያህል ልዩነት አለ፡፡ የፊተኛው የኃላ ቀርነት፣ የኋለኛው የአዋቂነት አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ በመሰይጠንና በመሰልጠን መካከል ያለውን አደጋ እናስተውል፡፡ የዱሮ ፍልስፍናም ቢሆን “ህግ የማይገዛውን ነፃነት፣ ኃይል ይገዛዋል” የሚለውን አባባልም እንደገና ማውጠንጠን ግዴታ ሊሆን እንደሚችል አንዘንጋ፡፡ “ጥንቃቄ ሲጠብቅ ፍርሃት ይሆናል” የሚለውንም አንርሳ፡፡ ዞሮ ዞሮ የሚመለከተውና ኋላፊነቱ የሚሰማው ክፍል የሚያደርገውን ያውቃል ብለን እንገምታለን - “እኔ ተጎድቼ ባመጣሁበት ውሰደው” ይላል ጮሌ ነጋዴ፡፡
ሀገራችን ሾተላይ ያለባት ይመስል ፅንስ ይጨነግፍባታል፡፡ ማስወረድ ልማድ ሆኖባታል፡፡ አሮጊው እንቅፋት አዲስ እንቅፋት እየፈለፈለ ያሽመደምዳታል፡፡ “እኔ ስወለድ ነው የሳቅ ጀምበር የጠለቀችው” የሚል ኢትዮጵያዊ እንዳይበዛ፤ ልባም ልባሞቹ ሰዎች መመካከር አለባቸው፡፡ “ገዢ እንጂ መሪ አያምርብንም” እንዳለው አፍሪካዊው ፀሐፊ፤ በግድ የገዢ ያለህ እያልን እንዳንፀልይ ምህረቱን ይላክልን፡፡ ውድቀትን ማቀድ አልፎ አልፎ ያዋጣል ብንልም፣ መነሻችን ጨለምተኝነት ከሆነ፣ ከ“ሁሉም ይውደም ፍልስፍና” (nhilism) አባዜ አይተናነስም! “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” እንዳለችው እንስሳም፤ የአገር ጨለማን መባጀት ክፉ እርግማን ነው! የየዓይነቱን እርግማን በበቂ አይተናልና አዲስ እርግማን ፍለጋ መባቸር ከንቱ መላላጥ ነው፡፡ “ከመርገምት ሁሉ የከፋው መርገምት፤ ቋንቋ ለቋንቋ መጠፋፋት ነው!” ይላል ገጣሚው፡፡ መግባባት እንዳይጠፋብን አሳቢዎቻችንን (Thinkers) እናዳምጥ እንሰማማ!! እርስ በርስ እንናበብ፡፡ መናበባችንን ይባርክልን ዘንድ ቀና እንሁን፡፡ አገራችን ኢትዮጵያ ከእንግዲህ “ትወልዳለች እንጂ አታሳድግም” መባሏ መቆም አለበት፡፡ የበቀሉ ዕድሎች እንዳይጠወልጉ እንንከባከባቸው! እውቀታችንንና አቅማችንን ሁሉ አፍንጫችን ሥር ባለው ጉዳይ ላይ ሳይሆን ትልቁን ስዕል አገርን (The Bigger Picture) ማየት ላይ እናውለው፡፡ የግለሰቦችን ምንነት ከአጠቃላዩ ህዝብ ህልውና ለይተን እንይ! ዛሬም ትምህርታችንን ይግለጥልን!!  

 እነዚህ አ/ አበባ ውስጥ የሚገኘው አዲሱ የሲኤምሲ - መሪ የ40/60 ኮንዶሚኒየም ሳይት ማራኪ ህንጻዎች ናቸው፡፡ ህንጻዎቹ ከሩቅ ላያቸው ማራኪ ገጽታን ቢላበሱም፣ ዙሪያቸው ግን ለከፋ የጤና ችግር በሚያጋልጥ ቆሻሻ የታጠረ ነው፡፡ያማሩ የመኖሪያ ቤቶችን መገንባቱ በጎ ሆኖ፣ ነዋሪዎችን ነጋ ጠባ በአስቀያሚ ጠረን ለሚያማርር የቆሻሻ ክምርና የተበከለ ፍሳሽ መፍትሄ መስጠትስ የማን ሃላፊነት ይሆን? የሚያምሩ ህንጻዎችን መገንባት፣ የሚያማርሩ የቆሻሻ ተራራዎችን በማፍረስ ይታገዝ!

 የአለማችንን ከተሞች የመሰረተ ልማት አውታሮች መሟላት፣ የጸጥታና መረጋጋት፣ የጤና አገልግሎት ጥራት፣ የትምህርት አሰጣጥና ሌሎች መስፈርቶች ተጠቅሞ በመገምገም፣ በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንት ዩኒት የተባለው ተቋም፣ ከሰሞኑም የ2018 ለኑሮ ተስማሚና ምቹ የአለማችን ምርጥ ከተሞችን ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የኦስትሪያዋ ቬና በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡
ላለፉት ሰባት ተከታታይ አመታት ለኑሮ ምቹ በመሆን ከአለማችን ከተሞች በቀዳሚነት የዘለቀቺው የአውስትራሊያዋ ሜልቦርን ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ማለቷን የዘገበው ሲኤንኤን፤ የጃፓኗ ኦሳካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጧን አመልክቷል፡፡
የካናዳዋ ካልጋሪ፣ የአውስትራሊያዋ ሲድኒ፣ የካናዳዋ ቫንኮቨር፣ የጃፓኗ ቶኪዮ፣ የዴንማርኳ ኮፐንሃገንና የአውስትራሊያዋ አዴላዴ እንደ ቅደም ተከተላቸው ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡ ተቋሙ በዘንድሮው ለኑሮ ምቹ የአለማችን ከተሞች ዝርዝር ውስጥ 140 የተለያዩ የአለማችን አገራት ከተሞችን ያካተተ ሲሆን፣ አውስትራሊያና ካናዳ እያንዳንዳቸው ሶስት ከተሞችን ማስመዝገብ መቻላቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በጦርነት የፈራረሰቺዋ የሶርያ መዲና ደማስቆ በዘንድሮው የአለማችን ከተሞች ዝርዝር ውስጥ በመጨረሻው ደረጃ ላይ የተቀመጠች ለኑሮ እጅግ አዳጋችና አስቸጋሪ የአለማችን ከተማ ስትሆን፣ የባንግላዲሽዋ ዳካ እና የናይጀሪያዋ ሌጎስ 139ኛ እና 138ኛ ደረጃን መያዛቸውን ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Page 9 of 406